Saturday, 08 November 2014 10:53

በሽብር የተከሰሱ የፓርቲ አመራሮች የዋስትና ጥያቄ በፅሁፍ እንዲቀርብ ቀጠሮ ተሰጠ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

          ሰሞኑን የሽብር ክስ የቀረበባቸው የአንድነት፣ የአረና እና የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮችና የሌሎች ተከሳሾች ጠበቆች፤ የዋስትና ጥያቄያችንን በፅሁፍ እናቅርብ በማለታቸው ፍ/ቤቱ የዋስትና ጥያቄውን መርምሮ ብይን ለመስጠት በድጋሚ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
ተከሳሾቹ ባለፈው ረቡዕ የዋስትና ጥያቄ አቅርበው ፍ/ቤቱ ጥያቄያቸውን መርምሮ ብይን ይሰጣል ተብሎ የተጠበቀ ቢሆንም ጠበቆቻቸው የዋስትና ጥያቄውን በፅሁፍ ለማቅረብ እንዲፈቀድላቸው ጠይቀዋል፡፡ ቀደም ሲል ለአራቱ የፓርቲ አመራር ተከሳሾች ጥብቅናዬን ለጊዜው አቁሜያለሁ በማለት መግለጫ የሰጡት ጠበቃ ተማም አባቡልጉ፤ በድጋሚ ወደ ጥብቅናቸው የተመለሱ ሲሆን በእለቱም “ደንበኞቼን አስመልክቶ የማቀርበው የዋስትና ጥያቄ በዝርዝርና በሰፊው ስለሆነ በፅሁፍ እንዳቀርብ ይፈቀድልኝ” ሲሉ ፍ/ቤቱን ጠይቀዋል፡፡ የሌሎች ተከሳሾች ጠበቆችም ተመሳሳይ ጥያቄ በማቅረባቸው፣ ፍ/ቤቱ የሚቀርበውን የዋስትና ጥያቄ መርምሮ ብይን ለመስጠት ለህዳር 2 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
የተከሳሽ ጠበቆች በክስ መዝገቡ ላይ የማስረጃ ዝርዝር አልተያያዘም፤ የከሳሽ አቃቤ ህጐች ስምም አልተገለፀም በማለት ለፍ/ቤቱ ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን አቃቤ ሕግ የማስረጃ ዝርዝርን በተመለከተ በሰጠው ምላሽ፤ “አቃቤ ህግ መስጠት የሚችለው፤ የማስረጃ ዝርዝር ሳይሆን የማስረጃ መግለጫ ነው  የሰነድ ማስረጃዎችን የተመለከቱ መግለጫዎችንም በሬጅስትራር በኩል እንዲደርሳቸው አድርገናል” ብሏል፡፡
 የአቃቤ ሕግ ስም አልተጠቀሰም ለሚለውም፤ ክሱ የተመሰረተው በተቋም ደረጃ ስለሆነ፣ የከሳሾቹ ተቋም ስምና ማህተም ከተገለፀ በቂ ነው ሲል ምላሽ ሰጥቷል፡፡አራት የፓርቲ አባላትን ጨምሮ 10 ተጠርጣሪዎችን ባካተተው የክስ መዝገብ፣ 1ኛ ተከሳሽ ሆኖ የቀረበው በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የማስተርስ ተማሪ ዘላለም ወርቅአገኘሁ፤ ከ2000 ዓ.ም ጀምሮ የግንቦት 7 አመራር ከሆነው ተድላ ደስታ የተባለ ግለሰብ ጋር በስልክና በፌስቡክ በመገናኘት በኢትዮጵያ ውስጥ የመንግሥት ለውጥ እንዴት ይምጣ በሚለው ላይ ተነጋግሯል ተብሏል፡፡

ተከሳሹ በ2003 ዓ.ም የግንቦት 7 አባል እንደሆነ፣ ማንነቱ እንዳይታወቅ በተደጋጋሚ በሌላ ሰው ስም የጂሜይል አካውንት በመክፈት፣ ከተድላ ደስታ ጋር ሲመካከር እንደነበር የክስ መዝገቡ ያመለክታል፡፡ በ2004 ዓ.ም በአረቡ ሀገር የተነሳው አይነት አመፅ በኢትዮጵያ እንዲፈጠር ሁለቱ ግለሰቦች ሲመካከሩ ነበር ተብሏል፡፡ የግንቦት 7 አባላት የሚሆኑ ግለሰቦችንም እየመለመለ ወደ ኤርትራ እንዲልክ ተልዕኮ ተቀብሎ እንደነበር የጠቆመው የአቃቤ ሕግ የክስ ዝርዝር፤ በግንቦት 7 አመራሮች 10 ሺህ ብር ተልኮለት ብሄራዊ ትያትር ቤት አካባቢ ማንነቱ ካልተጠቀሰ ግለሰብ መቀበሉን አመልክቷል፡፡
በሀገሪቱ እንዲመጣ የሚፈለገው ለውጥ ስኬታማ የሚሆነው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በአመፅ ቢዘጋ መሆኑን እንደተመካከሩም በክስ መዝገቡ ተጠቅሷል፡፡
ህጋዊ ፓርቲን ሽፋን በማድረግ የግንቦት 7 አባል በመሆን ሲንቀሳቀስ ነበር የሚል ክስ የቀረበበት 2ኛ ተከሳሽ የአንድነት ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሀብታሙ አያሌው፤ የአማራ ህዝብ ስቃይ እንዲያበቃ አሁን ያለውን መንግሥት መቀየር ያስፈልጋል ሲል ለግንቦት 7 ድርጅት መግለጫ መስጠቱ በክሱ ላይ ተመልክቷል፡፡ዘመኑ ንጉሴ ከተባለ የግንቦት 7 አባል ጋርም በስልክ በመገናኘት አንድነት ፓርቲን ሽፋን በማድረግ፣ አብረው ለመስራት መመካከራቸው የተገለፀ ሲሆን በፓርቲው ሰላማዊ ሰልፎች ላይ በመገኘትም አመፅ እንዲነሳ መልዕክት ሲያስተላልፍ ነበር ተብሏል፡፡ 3ኛ ተከሳሽ የአንድነት ፓርቲ የድርጅት ጉዳይ ምክትል ኃላፊ ዳንኤል ሺበሺ፤ ህዝቡ መንግሥትን ለመለወጥ መዘጋጀቱን፣ የመንግሥት ስልጣን ለመረከብ ምደባ መደረጉንና ተኩስ መጀመሩን ለግንቦት 7 አመራር አባል ለፋሲል የኔአቢይ መልዕክት ማስተላለፉ በክሱ ተመልክቷል፡፡
ከግንቦት 7 ጋር በጥምረት ይንቀሳቀሰል ከተባለው ዲምፀት ድርጅት ጋር ግንኙነት እንደነበረው የተጠቀሰው ሌላው ተከሳሽ ደግሞ የአረና ፓርቲ አባል አብርሃ ደስታ ነው፡፡ ተከሳሹ ኤርትራ ውስጥ ከሚገኙ የግንቦት 7 አባላት ጋር በስልክ ይገናኝ እንደነበርና አባላት መልምሎ ወደ ኤርትራ ለመላክ እንደተስማማ እንዲሁም በሥልጣን ላይ ያለውን መንግሥት አስወግዶ ህዝባዊ መንግሥት ማቋቋም እንደሚገባ መመካከሩ በአቃቤ ህግ የክስ መዝገብ ላይ ተጠቁሟል፡፡ የሰማያዊ ፓርቲ ምክር ቤት ምክትል ሰብሳቢ አቶ የሸዋስ አሰፋም ከግንቦት 7 አባላት ጋር ግንኙነት እንደነበረው ተጠቅሷል፡፡ ቀሪዎቹ ተከሳሾች፣ የግንቦት 7 አባል በመሆንና የሚሰጣቸውን ተልእኮ በመቀበል፣ የድርጅቱን አላማ ለማስፈፀም ሲንቀሳቀሱ ነበር ይላል - የክስ መዝገቡ፡፡

Read 2201 times