Saturday, 28 June 2014 10:20

የሸራተን ሰራተኛ ማህበርና ማኔጅመንቱ እንዲደራደሩ ተወሰነ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የሸራተን ሠራተኛ ማህበርና ማኔጅመንቱ ለድርድር እንዲቀርቡ በሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የአሰሪና ሰራተኛ ወሳኝ ቦርድ ባለፈው ማክሰኞ የወሰነ ሲሆን፤ የአዲስ አበባ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ፣ አደራዳሪ እንዲመደብ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡
የሸራተን ሆቴል ጠበቃ አቶ ተካ አስፋው፤ ክሱ እንዲሰረዝና ያለ አደራዳሪ ራሳቸው እንዲደራደሩ ያቀረቡት ጥያቄ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል፡፡
ላለፉት 6 ወራት የሸራተን ሰራተኛ ማህበር ማኔጅመንቱ በህብረት ስምምነቱ ላይ እንዲደራደር ጥያቄ ሲያቀርብ ቢቆይም ማኔጅመንቱ ለድርድር ፈቃደኛ ባለመሆኑ፣ ለኢንዱስትሪ ፌዴሬሽን የእገዛ ጥያቄ ማቅረቡን እንዲሁም ጉዳዩ ከፌዴሬሽኑ አቅም በላይ በመሆኑ ለኢሰማኮ ደብዳቤ መፃፉንና ኢሰማኮ ለማኔጅመንቱ የአምስት ቀን ጊዜ መስጠቱን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ ማኔጅመንቱ የተሰጠውን የአምስት ቀን የጊዜ ገደብ ከጨረሰ በኋላ የኢንዱስትሪ ፌዴሬሽኑ ለአሰሪና ሰራተኛ ወሳኝ ቦርድ ክስ መስርቶ፣ ባለፈው ማክሰኞ  የፌዴሬሽኑ ጠበቃ አቶ ሰኢድ ይመርና የማኔጅመንቱ ጠበቃ የቀድሞው የስፖርት ፌዴሬሽን ም/ፕሬዚዳንት አቶ ተካ አስፋው በተገኙበት ውሳኔ ተሰጥቷል፡፡
ቦርዱ፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ፤ አደራዳሪ እንዲመድብ ትዕዛዝ እንደሚያስተላልፍ ገልጿል፡፡
በጉዳዩ ላይ ፌዴሬሽኑ በአደራዳሪነት እንዲገባ የኢንዱስትሪ ፌዴሬሽኑ ጠበቃ አቶ ሰኢድ ይመር የጠየቁ ሲሆን የሸራተን ሆቴል ጠበቃ አቶ ተካ አስፋው ጥያቄውን ተቃውመውታል፡፡ “በጭራሽ መደረግ የለበትም፤ ፌዴሬሽኑ በአደራዳሪነት ገባ ማለት በእሳት ላይ ቤንዚን እንደማርከፍከፍ ይቆጠራል” ብለዋል - አቶ ተካ፡፡ የፌዴሬሽኑ ጠበቃ አቶ ሰኢድ በበኩላቸው፤ “በህግ አምላክ! ህጋዊ ሰውነት ያለውን ድርጅት በዚህ መልኩ መዝለፍ በህግ ያስቀጣዎታል” ሲሉ ምላሽ የሰጡ ሲሆን ቦርዱ አቶ ተካ ከንግግራቸውን እንዲታቀቡ አድርጓል፡፡
የሠራተኛ ማህበሩና ማኔጅመንቱ ለድርድር ቀርበው እስከ ሀምሌ 1 ቀን 2006 ዓ.ም  የደረሱበትን ሁኔታ ለቦርዱ ሪፖርት እንዲያደርጉ ትዕዛዝ ተሰጥቷል፡፡
በእለቱ ጉዳዩን ለመከታተል ከመጡት በርካታ የሸራተን ሰራተኞች መካከል አብዛኞቹ እንደገለፁልን፤ ሰራተኞች ችግራቸውን በሚዲያ ከገለፁ በኋላ፣ ሥራ አድረው ጠዋት ወደ ቤት ለሚሄዱ ሰራተኞች የሚቀርበው ሰርቪስ (የትራንስፖርት አገልግሎት) የቆመ ሲሆን በህመም፣ በጋብቻና በዘመድ ሞት ምክንያት አስፈቅዶ የቀረ ሰው ሰርቪስ ቻርጅ አይከፈለውም ተብሎ በድርጅቱ ሰሌዳ ላይ እንደተለጠፈም ጠቁመዋል፡፡
“የኪችን ሰራተኛ 350 ብር፣ የላውንደሪ ሰራተኛ፣ 400 ብር፣ የጥበቃ ሰራተኛ 450 ብር፣ እንግዳ ተቀባይ 700 ብር፣ አስተናጋጅ 450 ብር ደሞዝ እያገኘ በችግር ምክንያት የቀረን ሰው ሰርቪስ ቻርጅ አንከፍልም ማለት አሳፋሪ ነው” ብለዋል ሰራተኞቹ፡፡ የኢንዱስትሪ ፌዴሬሽኑ ጠበቃ አቶ ሰኢድ ይመር በበኩላቸው፤ በሰራተኞቹ ላይ እየተወሰደ ያለው እርምጃ አግባብ ባለመሆኑ ድርጅቱ ከዚህ ድርጊቱ እንዲታቀብ ለቦርዱ አቤቱታ አቅርበዋል፡፡
ሰራተኞቹም የተወሰደው እርምጃ በህብረት ስምምነቱ የሌለና አዲስ የመጣ በመሆኑ ድርጅቱ የወሰደውን እርምጃ በአሰሪና ሰራተኛ አዋጁ መሰረት እንዲያነሳ ጠይቀዋል፡፡
ስለቀጣዩ የማህበሩና ማኔጅመንቱ ድርድር የጠየቅናቸው የሰራተኛ ማህበሩ ፕሬዚዳንት አቶ ዳዊት ሳሙኤል፤ ጉዳዩ በፍ/ቤት የተያዘ መሆኑን ጠቅሰው፤ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡  

Read 1874 times