Saturday, 28 June 2014 10:19

በረመዳን ፆም ከ47 ሚ. ዶላር በላይ ገቢ ለማግኘት ታቅዷል

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(0 votes)

ኢትዮጵያ በሚቀጥለው ሳምንት በሚጀመረው የረመዳን ፆም ወቅት ለመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ከምታቀርበው ሥጋና ከብቶች ሽያጭ ከ47 ሚ. ዶላር በላይ ገቢ ለማግኘት አቅዳለች፡፡
“በረመዳን ወር የሥጋ ፍላጎት ስለሚጨምር መልካም የንግድ አጋጣሚ ነው” ሲሉ የተናገሩት የንግድ ሚ/ር የስራ ኃላፊ አቶ ከሊፋ ሀሰን፤ ከብቶችን ለሶማሊያ፣ ግብፅ፣ ጅቡቲ፣ ሳዑዲ አረቢያና ለተባበሩት ዐረብ ኢሚሬትስ (ዱባይ) እንደሚቀርቡ፣ ሥጋ ደግሞ ወደ ቱርክና ሆንግኮንግ እንደሚልኩ ተናግረዋል፡፡
እንደ አቶ ከሊፋ ገለጻ ከሆነ፣ ገቢው በዚህ ወር ብቻ ለማግኘት ከታቀደው 21 ሚሊዮን ዶላር ይልቃል፡፡ ባለፉት 11 ወራት ወደ ውጭ ከተላኩት የቁም ከብቶች 176 ሚሊዮን ዶላር፣ በተመሳሳይ 11 ወራት ጊዜ ውስጥ ወደ ውጭ ከተላከ ሥጋ 66.8 ሚሊዮን ዶላር መገኘቱን ጠቅሰው፣ “ከሥጋ ኤክስፖርት የሚገኘው ገቢ በዚህ የፆም ወር ወደ 70 ሚሊዮን ዶላር ሊያድግ እንደሚችል ተገምቷል” ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ የሥጋ አቅራቢዎችና ላኪዎች ማኅበር ዋና ፀሐፊ አቶ አበባው መኮንን በበኩላቸው፤ በረመዳን ፆም 5.4ሚ. ኪሎ ግራም ሥጋ ወደተለያዩ አገራት በመላክ 26.48 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት ማቀዳቸውን ገልጸዋል፡፡ “ወደ ውጭ ከምንልከው ሥጋ ዘጠና በመቶውን የሚወስዱት ሳዑዲ አረቢያና ዱባይ ናቸው ያሉት አቶ አበባው፤ ቀሪውን አስር በመቶ ለኩዌት፣ ኦማንና ግብፅ እንልካለን ብለዋል፡፡
ቀደም ሲል የኢትዮጵያ አየር መንገድ በየበረራው የሚያጓጉዘው 24 ሺ ኪ.ግ ሥጋ ብቻ ነበር ያሉት ዋና ፀሐፊው፤ አሁን ግን በየበረራው የሚያጓጉዘውን መጠን ወደ 60 ሺ ኪ.ግ ለማድረስ እቅድ አለ ብለዋል፡፡
ከአፍሪካ፣ ከፍተኛ የከብት ሀብት ያላቸው የኢትዮጵያ ሶማሌ ዞንና የኦሮሚያ ዞኖች መሆናቸውን የሚጠቁመው የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ መረጃ፤ በአገሪቱ 53.8 ሚሊዮን ከብቶች፣ 25.51 ሚሊዮን በጎች፣ 22.79 ሚሊዮን ፍየሎች፣ 2.17 ሚሊዮን ግመሎችና 49.3 ሚሊዮን ዶሮዎች እንዳሉ ያመለክታል፡፡

Read 1302 times