Monday, 10 February 2014 07:05

የአዲስ አበባ ከንቲባና ፖሊስ ኮሚሽነር በ“አንድነት” ተከሰሱ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(18 votes)

ከንቲባ ድሪባ ኩማና ኮሚሽነሩ መከራከሪያቸውን ለፍ/ቤት ያቀርባሉ
አንድነት፣ የመንግስት አካላትን በተከታታይ እከሳለሁ ብሏል

አንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ፓርቲ (አንድነት)፣ የአዲስ አበባ  ከንቲባና የፖሊስ ኮሚሽነራቸው ላይ በፌደራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት 8ኛ ወንጀል ችሎት ክስ የመሰረተ ሲሆን ተከሳሾች መልሳቸውን ይዘው እንዲቀርቡ ለየካቲት 24 ቀን 2006 ዓ.ም ቀጠሮ ተሰጠ፡፡
አንድነት ፓርቲ፤ “የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት” የተሰኘ አገር አቀፍ የ3 ወር ንቅናቄ ማጠቃለያን በአዲስ አበባ ባካሄደበት ወቅት በከተማ አስተዳደሩና በፖሊስ ኮሚሽን እስርና ወከባ እንደተፈፀመበት ገልፆ፤ በደላቸውን በማስረጃ በመዘርዘር ክስ መመስረቱን አስታውቋል፡፡
በፖሊስ ተፈፀመ በተባለ በደል ከንቲባውን በቀጥታ ለምን እንደከሰሰ ፓርቲው ሲያስረዳ፣ የአዲስ አበባ መተዳደሪያ ቻርተር ከንቲባው የከተማዋን ፖሊስ የእለት ተእለት እንቅስቃሴ የመቆጣጠር ኃላፊነት እንዳለበት ስለሚደነግግ ከንቲባውን በቀጥታ ተጠያቂ ያደርጋቸዋል ብሏል፡፡
ቅስቀሳ ላይ የነበሩ የፓርቲው አመራሮችና አባላት በጅምላ በፖሊስ ታስረው መዋላቸውን ፓርቲው ጠቅሶ፣ የቅስቀሳ ቁሳቁስ ተነጥቀናል፤ ፖስተሮችን እንዳንለጥፍ ተከልክለናል ብለዋል። የፖሊስን የእለት ተእለት እንቅስቃሴ የመከታተል ሃላፊነት የተጣለባቸው ከንቲባውና ኮሚሽነሩ፣ የፖሊስን ህገወጥ ተግባር በቸልታ አልፈውታል ብሏል - አንድነት ፓርቲ፡፡
“በቂ ማስረጃ ከተደራጀ በኋላ ነው ወደ ክስ የሄድነው” ያሉት የፓርቲው አመራሮች፤ ክሱን የመሰረቱት ጠበቃ ተማም አባቡልጉ እና ረዳታቸው መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ከንቲባውና ኮሚሽነሩ የካቲት 24 ቀን መልሳቸውን ካቀረቡ በኋላ መጋቢት 2 ቀን ክርክር ይካሄዳል ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥ ፍ/ቤት የለም ብለው እንደሚያምኑ የተናገሩት የፓርቲው መሪዎች፤ የመንግሥት አካላት የሚፈፅሙትን አፈና በይፋ ወደ ፍ/ቤት በመውሰድ የፍትህ ስርአቱን መፈተንና ለህዝብ ማጋለጥ አንዱ የትግል አላማችን ነው ብለዋል፡፡
ከሰኔ እስከ ነሐሴ 2005 ለ3 ወራት፣ “የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት” በሚል በመላ አገሪቱ  የተደረጉት ሰላማዊ ሰልፎችና ህዝባዊ ስብሰባዎች ህዝብን በማነቃቃት ስኬታማ ውጤት አግኝተንባቸዋል ሲሉ የፓርቲው መሪዎች ተናግረዋል፡፡ በሌላ በኩል፤ በፀጥታው ኃይል እና  በገዢው ፓርቲ ካድሬ መካከል ልዩነት አለመኖሩን አይተናል፤ በአገሪቱ በተዘረጋ የአፈና መዋቅር ከፍተኛ የህግ ጥሰት እንደሚፈፀም አረጋግጠናል ያሉት የፓርቲው መሪዎች፤ የመንግስት ጫና ሳያሸብረው ፓርቲው ተመሳሳይ ንቅናቄዎችን በተከታታይ ያዘጋጃል ብለዋል፡፡  
“የፀረ-ሽብር አዋጁን ለማሰረዝ የሰበሰባችሁትን ድምፅ የት አደረሳችሁት” የሚል ጥያቄ ከአዲስ አድማስ የቀረበላቸው አመራሮቹ፤ “የተሰበሰበውን የህዝብ ድምፅ ወደ ፍ/ቤት ለመውሰድ የህግ ባለሙያዎች እየመከሩበት ነው፣ በሁለተኛ ዙር የክስ ሂደት ውስጥ የሚካተት ይሆናል ብለዋል፡፡ በተካሄደው የ3 ወር የህዝብ ንቅናቄም መንግሥት ለጉዳዩ ይበልጥ ትኩረት እንዲሰጥ ፓርቲው ጫና ማሳረፉን የሚያመለክቱ ውጤቶች መታየት መጀመራቸውን የጠቀሱት የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሃብታሙ አያሌው፤ የፀረ-ሽብር አዋጁ ከመፅደቁ በፊት ለህዝብ ውይይት መቅረብ ሲገባው  አዋጁ ወጥቶ ብዙዎችን ሰለባ ካደረገ በኋላ መንግስት ራሱን ለመከላከል የፕሮፖጋንዳና የስልጠና ዘመቻ ጀምሯል ብለዋል፡፡ ይህም ፓርቲያቸው ይዞት የተነሳው ጥያቄ ጫና ማሳረፉንና ትክክለኛ እንደነበር የሚያረጋግጥ መሆኑን አቶ ሃብታሙ ገልፀዋል፡፡
“ማንም ሰው ወይም አካል ከህግ በላይ ሊሆን አይችልም” ያለው ፓርቲው፤ ህግ በሚጥሱ የመንግስት አካላት ላይ በተከታታይ ክስ እመሰርታለሁ፤ በቅርቡም በመንግሥት ከፍተኛ አመራሮችና በገዢው ፓርቲ ላይ ተጨማሪ ክስ ለመመስረት እየተዘጋጀሁ ነው ብሏል፡፡

Read 9991 times