Saturday, 03 August 2013 10:14

በቶፊቅ መስጊድ ትላንት ተቃውሞ ተካሄደ

Written by  ሠላም ገረመው
Rate this item
(5 votes)

ችግር ፈጥረዋል የተባሉ 10 ያህል ሰዎች ተይዘዋል
በአዲስ አበባ ፍልውሃ አካባቢ በሚገኘው ቶፊቅ መስጊድ ትናንት ተቃውሞ እንደሚካሄድ ቀድሞ በመነገሩ፣ በአካባቢው በርካታ ፖሊሶችና አድማ በታኞች ከረፋዱ አንስቶ የተሰማሩ ሲሆን፣ ቀትር ላይ የተቃውሞ ድምፆች ሲስተጋቡና የተወሰኑ ወጣቶች በፖሊስ ተይዘው ሲወሰዱ ታይቷል፡፡ 
በኢንተርኔት አማካኝነት “አንድነታችን ይቀጥል” በሚል በተላለፈው የተቃውሞ ጥሪ፣ በርካታ ሰዎች ወደ ቶፊቅ መስጊድ መምጣታቸው ታውቋል፡፡
በሌላ በኩል በመስጊዱ እንዲካሄድ የታሰበውን ተቃውሞ በማስቀረት በኢድ (በረመዳን ፆም ፍቺ) ዕለት እንዲካሄድ ጥሪ የሚያስተላልፍ ሌላ መልእክት ትናንት ማለዳ እንደተሰራጨ ተነግሯል።
ከመስጊዱ ውስጥና ዙሪያ በተጨማሪ በርካታ ህዝብ በሦስት አቅጣጫ የተሰበሰበ ሲሆን፤ ፖሊሶች የአንደኛው አቅጣጫ ወደ ሌላኛው እንዳይሄድ በየመሃሉ ተሰልፈው ሲቆጣጠሩ ታይቷል፡፡
በእለቱ ከፍተኛ የተቃውሞ ድምጽ ሲስተጋባ የነበረው መስጊዱ በር አጠገብ ነው፡፡ ከበር አጠገብ ከፍታ ቦታ ላይ ከቆሙት ወጣቶች መሃል አንዱ ወጣት፣ ሲቪል በለበሱ ሁለት የፀጥታ ሃይል አባላት ተይዞ ሲወሰድ፣ እዚያው አካባቢ የነበሩ በርካታ ሰዎች ድምፃቸውን ከፍ በማድረግ በጩኸትና ጣታቸውን ወደ ላይ በማውጣት ተቃውሟቸውን ገልፀዋል፡፡ በሦስቱ የመኪና መንገድ አቅጣጫዎች በርቀት እንዲቆሙ የተደረጉ ሌሎች በርካታ ሰዎችም ተቃውሞውን መላልሰው አስተጋብተዋል፡፡ የልጁን መያዝ በመቃወም የተከራከሩ ሰዎችም እንዲሁ በፀጥታ ሃይል አባላት ተይዘው ታይተዋል፡፡ አስር የሚሆኑ ሰዎች በፖሊስ መኪና የተወሰዱ ሲሆን፤ ይህንንም ተከትሎ ብዙ ሰዎች በተቃውሞ ድምፃቸውን አሰምተዋል፡፡
በቶፊቅ መስጊድ ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ የነበሩ ሰዎች ከስግደት በኋላ፣ ተቃውሞውን ለመቀጠል በያሉበት በመቆም ሲጠባበቁ የነበሩ ቢሆንም፣ ከአካባቢው በፍጥነት እንዲሄዱ በፖሊሶች እየተነገራቸው እንዲበተኑ ተደርጓል፡፡
ተቃውሞውን ለመቆጣጠር የከተማ እና የፌደራል ፖሊስ አባላት እንዲሁም አድማ በታኞች በብዛት ከመሰማራታቸውም በተጨማሪ በመስጊዱ ዙሪያ የሚገኙ ብዙዎቹ የንግድ ቤቶች በስጋት ተዘጋግተው ነበር፡፡ ባለፈው ሳምንት አርብ ብዙ ህዝብ በተገኘበት በበኒ መስጊድ እንዲሁም ከዚያ በፊት በነበሩ ሳምንታት በአንዋር መስጊድ ተቃውሞ መካሄዱ ይታወሳል፡፡

Read 30732 times