Saturday, 27 April 2013 10:23

‹‹የኛ›› የሬዲዮ ፕሮግራም ነገ ይጀምራል ፕሮግራሙ ከ152 ሚሊዮን ብር በላይ ይፈጃል

Written by  በጋዜጣው ሪፖርተር
Rate this item
(7 votes)

ዕድሜያቸው በ18 ዓመት ክልል ውስጥ የሚገኙ ታዳጊ ሴት ወጣቶች የሚገባቸውን ማኅበራዊ ዋጋ እንዲያገኙ፣እንዲበረታቱና ካሰቡት ስፍራ እንዲደርሱ የሚደግፍ እንዲሁም ኅብረተሰቡ የበኩሉን አስተዋፅኦ እንዲያበረክትና ማኅበረሰባዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣ የሚያስተምር ‹‹የኛ›› የተሰኘ የሬዲዮ ድራማና የውይይት መድረክ ከሙዚቃ ጋር ተቀናጅቶ ነገ በሸገርና በአማራ ኤፍ.ኤም. የሬድዮ ጣቢያዎች ከቀኑ በ7:00 ሰዓት እንደሚጀምር ተገለፀ፡፡ ፕሮግራሙ ሦስት ድርጅቶች በጋራ ባሸኘፉት ጨረታ ባገኙት ከ152 ሚሊዮን ብር በላይ የሚዘጋጅ ሲሆን የገንዘብ ድጋፉን ያደረጉት የናይኪ ፋውንዴሽንና ‹‹ገርል ሃብ ኢትዮጵያ›› እንደሆኑ ታውቋል፡፡

የሬዲዮ ድራማው በተለያየ ማኅበራዊ ሕይወት ውስጥ የሚገኙ አምስት ታዳጊ ሴቶች፣ ለሙዚቃ ባላቸው ፍቅር በጠነከረ ጓደኝነት ተሳስረው የሙዚቃ ባንድ ለማቋቋም በሚያደርጉት ጥረት ዙሪያ የሚያጠነጥን ታሪክ ያለው ነው፡፡ አንዱ ድራማ በአሥራ ሦስት ክፍሎች የተከፋፈለ ሲኾን አንዱ ክፍል እንደተጠናቀቀ አንድ አዲስ ዘፈን አብሮ ይለቀቅለታል፡፡ ለሦስት ወራት ለሚተላለፈው የመጀመሪያው አስራ ሦስት ክፍል ‹‹የኛ›› የሬዲዮ ድራማና ቶክ ሾው የተዘጋጀው ‘አቤት’ የተሰኘው ነጠላ ዜማ ከእነ ቪዲዮ ክሊፑ በማኅበራዊ ድረገጾችና በዲጂታል ሚዲያ በተለቀቀ በአጭር ጊዜ ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ ተመልካቾችን ማግኘት እንደቻለ ታውቋል፡፡

ከትናንት በስቲያ ማምሻውን በብሔራዊ ትያትር ቤት መናፈሻ በተሰናዳ ደማቅ የምረቃ ሥነስርዓት ላይ፣አምስቱ ተዋንያንና ድምጻውያን ከተጋባዥ ድምጻዊ ኃይሌ ሩትስ ጋር በመሆን ዘፈኑን በመድረክ ተጫውተውታል፡፡ የፕሮግራሙ የሙዚቃ አስተባባሪ ድምጻዊት ሙኒት መስፍን ስትኾን ‹‹አቤት›› የተሰኘውን ዘፈን አርቲስት አብርሃም ወልዴ፣ ቪዲዮ ክሊፑን ደግሞ የፊልም ባለሞያዋ ወ/ሮ አይዳ አሸናፊ ሠርተውታል፡፡ ሌሎቹን አሥራ ሦስት ዘፈኖች ደግሞ ታዋቂው የሙዚቃ ባለሞያ አበጋዝ ክብረወርቅ ሺወታ እንደሠራው ታውቋል፡፡ የኢትዮጵያ ሬዲዮ እና ቴሌቭዥን ድርጅት የቀድሞ ሥራ አስኪያጅ እና የቀድሞ የመንግሥት ቃል አቀባይ የነበሩት ወ/ሮ ሰሎሜ ታደሰ የሚመሩት “ኢመርጅ ኮንሰልቲንግ”፣ የወ/ሮ አይዳ አሸናፊ “ማንጎ ፕሮዳክሽን” እና የታዋቂው የሒሳብ ባለሞያ አቶ ኃይለልኡል የሚመሩት “ዴሎይት ኮንሰልቲንግ” በጥምረት ባቋቋሙት “የኛ ቤት” የተሰኘ ሥራ አስፈፃሚ ቡድን የሚመራውና ለአራት ዓመታት የሚዘልቀው ፕሮጀክት፤ከድራማው፣ከሙዚቃውና ቶክሾው በተጨማሪ ቀጣይ ሥራዎች እንደሚኖሩት ታውቋል፡፡ ለ‹‹የኛ›› የገንዘብ ድጋፍ የሚያደርገው የናይኪ ፋውንዴሽን እና የእንግሊዝ መንግሥት የዓለም አቀፍ የልማትና ተራዶኦ ድርጅት ስትራቴጂያዊ ትብብር የኾነው ‹‹ገርል ሃብ ኢትዮጵያ›› ናቸው፡፡

Read 4590 times