Administrator

Administrator

“...ትዳር ከያዝኩኝ ከአስራ ሁለት አመት በሁዋላ ነበር ያረገዝኩት፡፡ እርግዝናው ከመከሰቱ

አስቀድሞ በእኔም ይሁን በባለቤቴ ቤተሰቦች ዘንድ የተመሳሰለ ቅሬታን አስተናግጃለሁ፡፡ በጣም የሚያሳዝን ነበር፡፡ የእሱም ቤተሰቦች እኔን መሐን ሲሉ ...የእኔም ቤተሰቦች እሱን መሐን ሲሉ ...እጅግ የሚያስጨንቅ ሁኔታ ነበር ሁለታችንንም የገጠመን፡፡ እኔ እንዲያውም ቢቸግረኝ... ባለቤቴን ...በቃ ልጅ አስወልደህ አምጣ...የሚል ፈቃድ ሰጥቼዋለሁ፡፡ እሱ ግን በምንም ምክንያት አንቺን ትቼ ሌላ ጋ አልሄድም በማለቱ ኑሮአችን በቤተሰብ ውጥረት ሲሰቃይ ቆይቶአል፡፡ በሁዋላ ግን ሕክምናው ...ጸበሉ ...የተቻለው ሁሉ ተደርጎ ሳይሳካ ከቆየ በሁዋላ እርግዝናው ሳይታሰብ ተከሰተ፡፡ እኔ እንዲያውም ሕመም ይሆናል እንጂ መቼም እርግዝና አይደለም ብዬ አስቤ ነበር፡፡ ሐኪሞቹ ግን ሕመም አይደለም ...እርግዝና ነው... በማለታቸው ተደሰትን፡፡ ምን ያረጋል... ደስታው ደስታ እንደሆነ ቢዘልቅ ጥሩ ነበር፡፡ ነገር ግን አልሆነም፡፡ በማህጸኔ ውስጥ ኢንፌክሽን በመኖሩ ምክንያት ጽንሱ መቀጠል ስላልቻለ እና እኔም በጣም ስለታመምኩ እርግዝናው እንዲቋረጥ ተደረገ፡፡ ከምንጊዜውም በላይ እጅግ በጣም ነበር ያዘንኩት፡፡ ከዚያም በሁዋላ ማርገዝ አልቻልኩም፡፡         ትእግስት ሺፈራው ከኮተቤየትእግስት ደብዳቤ የደረሰን በፖስታ ነበር፡፡ እኛም ገጠመኙን ይዘን ወደሕክምና ባለሙያ ነበር ያመራነው፡፡ ዶ/ር ታደሰ ኡርጌ በጳውሎስ ሆስፒታል የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻ ሊስት በማህጸን ኢንፌክሽንና እርግዝና ዙሪያ ለዚህ እትም ማብራሪያ እንዲሰጡ  ተጋብዘዋል፡፡ ዶ/ር ታደሰ እንደሚሉት ኢንፌክሽን ሲባል መገለጫው ብዙ ነው፡፡  በሽታን ሊያመጡ የሚችሉ ተሀዋስያን መገኘት የሌለባቸው ቦታ ላይ ከተገኙ ኢንፌክሽን ወይንም መመረዝ ይከሰታል፡፡ የማህጸን ኢንፌክሽንን ለይተን ስናይ ደግሞ በተለምዶ ብዙ አይነት ሲሆን ምንጩ ባክቴሪያ፣ ፈንገስ፣ ቫይረስ ወይንም ሌሎች ፓራሳይትስ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ኢንፌክሽኑ ያጠቃውስ የትኛውን
የማህጸን ክፍል ነው የሚለውን መለየትም ያስፈልጋል፡፡ ኢንፌክሽኑ በታችኛው የማህጸን ክፍል ውስጥ የሚገኝ ከሆነ ብዙውን ጊዜ ቀላል የሆነ ኢንፌክሽን ነው፡፡ ቀላል ሲባልም ...ለአጭር ጊዜ የሚቆይ ምልክታቸውም በፍጥነት የሚታይ ነው፡፡  በታችኛው የማህጸን ክፍል የሚከሰተው ኢንፌክሽን በአብዛኛውም በግብረስጋ ግንኙነት ጊዜ የሚተላለፍ እንደ ጨብጥ (ጎኖሪያ) የመሳሰሉት ስለሆኑ ምልክታቸው በታየ ጊዜ ሕክምናው ስለሚሰጥ በቀላሉ ሊድኑ የሚችሉ ናቸው፡፡ ስለዚህም ከእርግዝና ጋር በተያያዘ ምንም ችግር አያስከትሉም፡፡/ር ታደሰ እንደሚሉት የታችኛው የማህጸን ክፍል በኢንፌክሽን ተያዘ ሲባል ብዙ ጊዜ ኢንፌክሽኑ ወደላይኛው የማህጸን ክፍልም የመዛመት እድል ይኖረዋል፡፡ በዋናው ማህጸን ክፍል ወይንም በዘር መተላለፊያው እንዲሁም በዘር ፍሬ መፈጠሪያው አካባቢ ወይንም ዙሪያውን ያሉትን የሰውነት ክፍሎች የተዛመተው ኢንፌክሽን ጉዳት ሊያስከትል የሚችልበት ሁኔታ ያጋጥማል፡፡
ከእርግዝና ጋር በተያያዘ ችግር የሚፈጠረው ኢንፌክሽኑ ወደላይኛው የማህጸን ክፍል ከገባ በሁዋላ፡-
የማህጸን የውስጥ ክፍል የመቁሰል እና ጠባሳ ምልክት ሊያሳይ ይችላል፡፡የዘር መተላለፊያ ቱቦው ሊቆስልና ሊዘጋ ይችላል፡፡የዘር ፍሬ የሚመረትበት አካባቢ መግል የመቋጠርና የመያያዝ ሁኔታ ሊኖረው ይችላል፡፡
ከላይ የተዘረዘሩት ሁኔታዎች እርግዝና እንዳይከሰት ማድረግ ወይንም እርግዝናው ቢከሰትም እንዳይቀጥል ምክንያት የመሆን አለበለዚያም ከማህጸን ውጭ እርግዝና እንዲከሰት የማድረግ አቅም አላቸው፡፡ ይህም የረጅም ጊዜ ጠንቅ ተብሎ ይገለጻል፡፡ ኢንፌክሽኑ ከእርግዝና ጋር በተያያዘ ጉዳት ያስከትላል ሲባል በሰውነት ክፍል ውስጥ ስለተገኘ ብቻ ሳይሆን ለመራቢያ የሚያገለግሉ የሰውነት ክፍሎች ላይ በሚያደርሱት ጉዳት ነው፡፡ የመራቢያ አካላቱ ጉዳት ደረሰባቸው ሲባልም የሰውነት የመከላከል አቅም እነዚህን በሽታ አምጪ ሕዋሳት ለማጥፋት ሲል የሚያደርገው ጦርነት  ውጤት ነው፡፡ ለምሳሌም የዘር ማስተላለፊያ ቲዩብ ቆስሎ ቢገኝ  ምክንያቱ ሰውነታችን እነዚያን እየተባዙ ያሉ ጀርሞች ለማጥፋት በሚያደርገው ቁጣ የተነሳ ነው፡፡ ስለዚህም በዋናነት ከኢንፌክሽኑ በላ ችግር የሚሆነው ሰውነት ተሐዋስያኑን ለማጥፋት ሲል በሚወስደው ተፈጥሮአዊ እርምጃ ሰውነት ላይ የሚደርሰው ጉዳት ነው፡፡ ኢንፌክሽን ሲከሰት ጉዳት እስኪያደርስ ድረስ የተወሰነ ጊዜ ስለሚወስድ በዚህ መሀል እርግዝና ሊከሰት ይችላል፡፡ በማህጸን የታችኛው ክፍል የሚታይ ችግር ከሆነ በቀላሉ ሊታከም የሚችል ሲሆን በላይኛው የማህጸን ክፍልም ቢሆን ምልክት ሲታይ እርግዝናውም ቢኖር ሕክምናው ይሰጣል፡፡ በእርግዝና ጊዜ ማህጸን ይዘጋል... ስለሆነም ምልክቶቹን እንዴት ማየት ይቻላል?  ለሚለው ዶ/ር ታደሰ ኡርጌ እንደሚሉት የተጎዳው ክፍል የታችኛው የማህጸን ክፍል ከሆነ የፈሳሽ መኖር የደም መፍሰስ የመሳሰሉት ምልክቶች ሊታዩ ይችላል፡፡ ኢንፌክሽኑ የደረሰው በላይኛው የማህጸን ክፍል ላይ ከሆነ ደግሞ ከፈሳሽ ይልቅ ሌሎች ምልክቶች ይታያሉ፡፡ ለምሳሌም ትኩሳት፣ በሆድ አካባቢ ከበድ ያለ ህመም (በምርመራ ወቅት በትንሽ እንኩዋን ሲነካ ከፍተኛ ሕመም የመሰማት ሁኔታ) ይከሰታል፡፡ ከዚህም ባለፈ የላቦራቶሪ ምርመራ የመሳሰሉት ተደርገው በማህጸን ውስጥ
ኢንፌክሽን ካለ ጽንሱ እያለም ቢሆን ሕክምና ይደረጋል፡፡ በእርግጥ ሕክምናው ጠንከር ያለና
ክትትል የሚያስፈልገው ስለሚሆን ሆስፒታል እስከመተኛት የሚያደርስ ሊሆን ይችላል፡፡ የጽንሱ ሁኔታ እናትየው ሕክምናውን እየወሰደች እድገቱን ሊቀጥል ይችላል... አለበለዚይም ሕመሙ ከፍተኛ ከሆነ ሊያጨናግፈውም ይችላል፡፡ ኢንፌክሽን መኖሩ ብቻ ጽንሱን የሚያቋርጠው ሳይሆን ሙሉ በሙሉ ሰውነትዋን ከመረዘው ምናልባት የሚኖር አጋጣሚ ነው፡፡ በግብረስጋ ግንኙነት ጊዜ የሚተላለፉት እንደ ጨብጥ፣ ቂጥኝ የመሳሰሉት ኢንፌክሽኖች በእርግዝና ወቅት ሊከሰቱ ወይንም ከእርግዝናም በፊት ሊከሰቱ የሚችሉ ናቸው፡፡ እንደዚህ ያሉት ኢንፌክሽኖች እርግዝናው እንዲወርድ ምክንያት ሊሆኑ ሲችሉ ከዚህም ባለፈ ወደ ጽንሱ የመተላለፍ አቅም አላቸው፡፡ ጽንስ ሆድ ውስጥ የመቀጨጭ፣ጽንስ ሆድ ውስጥ የመጥፋት ወይንም ያለቀኑ መወለድ ወይንም... እነዚህ ሁሉ ሳይከሰቱ ቀርተው ልጅ የኢንፌክሽኑ ተጎጂ ሆኖ ሊወለድ ስለሚችል እናትየውን ቶሎ በማከም ልጁንም ማዳን ይቻላል፡፡ባለሙያው እንደሚገልጹት እርጉዝ ሴቶች እንደተገኘ ወይንም በቀላሉ መድሀኒትን አይጠቀሙም ቢባልም በአንዳንድ ምክንያቶች ግን የተለየ ሕክምና ይሰጣል፡፡ ነገር ግን በጽንስ ላይ ችግር የሚያስከትሉ ...ፈጽሞ በእርግዝና ወቅት የማይወሰዱ ተብለው የተለዩ መድሀኒቶች አሉ፡፡ንስ ላይ ምናልባት ችግር ሊያስከትሉ ይችላሉ፡፡ ግን የመድሀኒቱ ጠቀሜታ ከጉዳቱ ሊያመዝን ይችላል ተብሎ የሚሰጡ አሉ፡፡ ጽንስ ላይ ችግር ያምጣ አያምጣ አይታወቅም፡፡ ግን የመድሀኒቱ ጠቀሜታ ለእናትየውም ይሁን ለጽንሱ ጠቀሜታ አለው የሚባሉ መድሀኒቶች አሉ፡፡ ፈጽሞ በጽንስ ላይ ምንም ችግር አያመጡም የሚባሉ የመድሀኒት አይነቶች አሉ፡፡
ስለዚህ እነዚህ መድሀኒቶች በውል ተለይተው የሚታወቁ ሲሆን እንደሌላው መድሀኒት ዝም ተብሎ በቀላሉ የሚወሰድ ሳይሆን በሐኪሞች ልዩ ትእዛዝ በከፍተኛ ጥንቃቄ የሚሰጡ ናቸው፡፡ በአብዛኛው ያለው ግንዛቤ ከማህጸን ፈሳሽ ከታየ እንደ ኢንፌክሽን የመቁጠር ዝንባሌ ያለው ነው፡፡ ነገር ግን በተለይም በእርግዝና ወቅት በማህጸን አካባቢ ብዙ ለውጥ ያለ ሲሆን ከነዚህም አንዱ የፈሳሽ መብዛት ነው፡፡ አንዳንድ እርጉዝ ሴቶች አልፎ አልፎ ሞዴስ እስከመጠቀም የሚደርሱበት ሁኔታም ይስተዋላል፡፡ ነገር ግን ፈሳሽ ከኢንፌክሽን የመጣ ነው የምንለው መቼ ነው የሚለውን መለየት ያስፈልጋል፡፡ በእርግጥ መብዛቱ አንዱ ምልክት ቢሆንም ብቻውን ግን ኢንፌክሽን ነው አያሰኘውም፡፡ ከዛ ባለፈ ግን የማሳከክ ወይንም የማቃጠል ስሜት ካለው ወይንም መልኩ ከሌላ ጊዜ የተቀየረ ሲሆን ...ወዘተ ኢንፌክሽን መሆኑን ሊያረጋግጥ ይችላል፡፡ ስለዚህም ሕክምናውን በጊዜው ማድረግ ተገቢ ነው ይላሉ ዶ/ር ታደሰ ኡርጌ፡፡ በስተመጨረሻም ዶ/ር ታደሰ በተለይም በእርግዝና ወቅት ከሚኖረው የአካል ገጽታ ጋር በተያያዘ የገለጹትን እናስነብባችሁ፡፡ “...አንዲት እናት ከማርገዝዋ በፊት እና በእርግዝና ላይ እያለች የሚያመሳስላት ነገር     ቢኖር ስምዋ ብቻ ነው፡፡” ለምን? የሚለውን ጥያቄ መልስ በቀጣዩ እትም እናስነብባችሁዋለን፡፡ ይቀጥላል

ከዕለታት አንድ ቀን ዕመት ጦጢት ዘር ልትዘራ ወደ እርሻ ቦታ ትሄዳለች፡፡ ከዚያም በሰፊው እርሻ

ላይ በመት በመት ስትዘራ ትታያለች፡፡
በእርሻው ዳር የሚያልፈው ሰው ሁሉ ጥያቄ ይጠይቃል፡፡
ጦጢት ምን ዘራሽ?“ ይላታል አንዱ፡፡
“ዘንጋዳ” ትላለች ጦጢት፤ ኩራቷ ፊቷ ላይ እየተነበበ፡፡
“ጦጢት ምን ዘራሽ?” ይላታል ሁለተኛው፡፡
“ስንዴ!” ትላለች ጦጢት፡፡
“ጦጢት ምን ዘራሽ?” ይላታል ሌላው፡፡
“ጤፍ!” ትላለች፡፡
“ጦጢት ምን ዘራሽ?” ደሞ ሌላው፡፡
“አተር!” ትላለች፡፡
አንዳቸውም ከእጁዋ የሚወጣውን ዘር አለማየታቸው እየገረማት ነው መልስ የምትሰጠው፡፡ የመጨረሻው ሰው መጣና፣ “እሜት ጦጢት፣ ምን ዘራሽ?” አላት
“ባቄላ!” አለችው፡፡
“እንዲያው ባቄላ እዚህ መሬት ላይ ይበቅል ይመስል … ምን ይበጅሻል?
“ማምሻውን ሁኔታውን እዩ?” ብላ መለሰች፡፡ ጦጢት ስትዘራ ስትታይ ዋለችና ወደ ማታ ወደ እርሻው ተመልሳ መጣች፡፡ ከዚያም ቀን ስትዘራ የዋለችውን ዘር እንደገና ከእርሻው እያወጣች ስልቻዋ ውስጥ ትከት ጀመር፡፡ ቀን ስትዘራ ያዩዋት ሰዎች ከገበያ ሲመለሱ የምታደርገውን አይተው በመገረም፤ “እመት ጦጢት፤ ብልጥ የነበርሺው ሴትዮ አሁንስ ተጃጃልሽ መሰል! ደሞ ምን ልሁን ብለሽ ነው

የዘራሽውን መልሰሽ የምትለቅሚው?”
ጦጢትም፤
“ወዳጆቼ! ያለንበት ዘመን አያስተማምንም! የያዙትን ይዞ ወደ ቤት ክትት ነው የሚሻለው፡፡ ንብረትን በእጅ ይዞ ማደርን የመሰለ ነገር የለም!!” ብላ መለሰች፡፡
*                  *               *
በማናቸውም የህይወታችን መንገድ ጥርጣሬን ይዘን ከተጓዝን ዕቅዳችን በቅጡ አይሳካም፡፡ የምናደርገው ነገር ሁሉ ልባዊ አይሆንምና ውሽልሽል አጥር ነው የምናጥረው፡፡ ውሽልሽል አጥር ለአደጋ የተጋለጠ ነው፤ እንደጦጢት የምንዘራውን እየደበቅን መጓዝ፣ አልፈን ተርፈንም የዘራነውን መልሰን መልቀምና ይዘን ማደር ግዴታ እስኪሆን ድረስ ኑሮአችን ያልተረጋጋ ይሆናል፡፡ ያልተረጋጋ ዲሞክራሲ፣ ያልተረጋጋ  ፖለቲካን ነው የሚወልደው፡፡ ያልተረጋጋ ፖለቲካ ያልተረጋጋ ኢኮኖሚን ነው ይዞ እሚያዘግመው፡፡ የዚህ ባለቤት የሚሆነው ያልተረጋጋ ህዝብ ነው፡፡ ህዝብ ሲጠራጠር ደግ አይደለም፡፤ ይሄን ልብ ብሎ ማስተዋል ይጠይቃል፡፡ ሼክስፒር እንደሚነግረን፣
“ግን እንደዚሁ እንደህንፃ፣ ላዩ በሰም አንፀባርቆ
አካባቢው በጌጥ ደምቆ
መሰረቱ ግን በግድፈት፣ በአገም ጠቀም ተደባብቆ
በመሀንዲስ ጥበብ ጉድለት፣ ወይ ባጉል መራቀቅ ዘፍቆ
ከስህተቱም ከጥራቱም፣ ተቻችሎ አለ ተጣብቆ፡፡
እንግዲህ  ሐምሌት ምናልባት፣ ዛሬ እወድሻለሁ ሲል
በፍቅሩ የልብ ጥራት፣ አይገኝ ይሆናል እክል
ግን የልደቱን ደረጃ፣ ስታስቢው ደሙን ቅጅ
ፍቃዱ የሱ እንዳልሆነ፣ አስተውይ የእናቴ ልጅ፡፡”
ሌላው አስጊና አትጊ ነገር እርስ በርስ መጠራጠር ነው፡፡ መሪዎች ካልተማመኑ ተመሪዎች ተግባብተው መራመድ ይቸግራቸዋል፡፡ ተግባብተው የማይራመዱ ሰዎች ወንዝ ለወንዝ ሲማማሉ ነው የሚኖሩት፡፡
“ዕምነት ሲታመምሺ ወረቀት መፈራረም” ይለዋል ጸጋዬ ገ/መድህን፡፡ ቢሮክራሲያችን፣ ፓርቲዎቻችንም፣
አመራሮቻችንም ከአበሻ የጥርጣሬ ድርና ማግ ነው ተሰሩት፡፡ ዛሬ የተባለው ነገ የሚሻረው ለዚህ ነው፡፡
እኔ ከሁሉ በላይ ነኝ የሚል አስተሳሰብ አጥፊ ነው፡፡ የበላይነትን በተሻለ ሥራ ካላሳየን ከፉከራ አያልፍም፡፡
“የተሻልን ነን እያልን
ያልተሻለ ነገር ከሰራን
መሻላችን ምኑ ላይ ነው፣ ትላንት ላይ ከተጋደምን”እንደሚለው ነው ገጣሚው፡፡
ህዝብ መንግስትን አምኖ በራሱ ተነሳሽነት ካልተንቀሳቀሰ፣ ዲሞክራሲው ጤነኛ ነወይ? ብሎ መጠየቅ ያባት ነው፡፡ የምስራቅ አውሮፓ መንግስታት ብትንትናቸው እስኪወጣ ድረስ 98 በመቶ ምርጫውን አሸንፈናል ይሉ እንደነበር አለመርሳት ብልህነት ነው፡፡ ያልመረጠው ለምን እንዳልተመረጠ ብቻ ሳይሆን የመረጠው ለምን እንደሆነ መጠየቅ ያባት ነው፡፡ ቀስቅሰን፣ አስገድደን ወይ አታለን መመረጥ ጭብጨባን እንጂ ልባዊ ድጋፍን አያስገኝም፡፡ በእርግጥ የፖለቲካ ጸሀፍት፤ “ገባው አልገባው አይደለም የፖለቲካ ሚስጥሩ፡፡ ተቀበለ አልተቀበለ  ነው እንጂ” ይላሉ፡፡ ሆኖም ጊዜያዊ ነው፡፡ እንደሚታወቀው እንኳን ፖለቲካው ታሪክም አሸናፊዎች የሚፅፉት ተረት ነው፤ ይሏል፡፡ ስለዚህም ኢ-ተዓማኒ ሪፖርት በተነገረ ቁጥር፣ ሙገሳና የአፍ ሙካሽን የተንተራሰ ሲሆን “እሰይ እሰይ! እልል በይ ጉሜ!” ማለት ቢያንስ የዋህነት ነው፡፡ በማንኛውም የለውጥ ንፋስ ውስጥ ጊዜን፣ ወዳጅንና ባላንጣን ማሰብ ዓይነተኛ ብልህነት ነው፡፡ ጊዜው እንጂ ሁኔታው አይደለም ጥፋተኛው፡፡ “ሳህን ቢጠፋ አብረን በላን” እንደሚባለው የትግሪኛ ተረት፤ “የሰሜን ብርድ ከማትወድደው ጋር ያስተቃቅፋል” የሚለው ተረት ዋና ጉዳይ ነው!

  • የመን እንደ ሶማሊያ መታመሷ፣ ለኤርትራ መንግስት አመቺ ይሆናል

የኤርትራ መንግስት አካባቢውን እየበጠበጠ ስለሆነ በጋራ እንመክተዋለን ያሉት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትርና የጅቡቲ ፕሬዚዳንት፤ በኤርትራ መንግስት ላይ የተጣለው አለማቀፍ ማዕቀብ እንዲቀጥል
የጠየቁ ሲሆን፤ የኤርትራው ፕሬዚደንት በበኩላቸው ውንጀላውን አስተባበሉ፡፡ሰሞኑን  በጅቡቲ የሶስት ቀናት ጉብኝት ያደረጉት ጠ/ሚ ኃይለማርያም ደሳለኝ እና የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ኢስማኤል ኦማር ጊሌ፤ የኤርትራ መንግስት ለአካባቢው አገራት ፀጥታ ስጋት ስለሆነ ኢትዮጵያና ጅቡቲ በጋራ እየሰሩ ነው ብለዋል፡፡ የኤርትራ መንግስት የጅቡቲን ጨምሮ የአካባቢውን አገራት ፀጥታ እያወከ ነው ያሉት ፕሬዚደንት ኦማር ጊሌ፤ ኤርትራ ላይ የየተጣለው ማዕቀብ እንዲቀጥል ከጠ/ሚ ኃይለማርያም ጋር መስማማታቸውን ገልፀዋል፡፡ ኢትዮጵያና ጅቡቲ ድንበራቸውን በጋራ ለመጠበቅ ዝግጁ መሆናቸውን የገለፁት ጠ/ሚ ኃይለማርያም በበኩላቸው፤ የኤርትራ መንግስት አካባቢውን ከመበጥበጥ ስላልተቆጠበ ስድስት አመት ያስቆጠረው አለማቀፍ ማዕቀብ እንዲቀጥልና ተመጣጣኝ እርምጃ እንዲወሰድበት ንጠይቃለን ብለዋል፡፡ በአፍሪካ ህብረት፣ ከዚያም በተባበሩት መንግስታት የፀጥታ ምክር ቤት አማካኝነት ኤርትራ ላይ ማዕቀብ የተጣለው፣ የሶማሊያ አሸባሪዎችን በመደገፍና በማስታጠቅ አካባቢውን ይበጠብጣል በሚል ምክንያት እንደሆነ ይታወሳል፡፡ የኤርትራ መንግስት የሶማሊያ አሸባሪዎችን እንዲሁም በየአገሩ አማፂ ቡድኖችን ያስታጥቃል በሚል ከፍተኛ ስጋት ያደረባቸው አገራት በተለይም ኢትዮጵያና ጅቡቲ ከየመን ጋር ትብብር በመፍጠር ጫና ለማሳደር ሲጥሩ የነበረ ሲሆን፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የየመን ቀውስ እየተባባሰ መንግስት አልባ መሆኗ ለሁለቱ አገራት ይበልጥ አሳሳቢ ሆኖባቸዋል። ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በበኩላቸው፤ ከኢትዮጵያ የሚሰነዘረውን ውንጀላ በማስተባበል፤ በኤርትራ ላይ የተጣለው ማዕቀብ እየላላ ስለመጣና ማዕቀቡ ይነሳል የሚል ስጋት ስላደረባቸው ነው ውንጀላውን የሚደጋግሙት ብለዋል፡፡ የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባሰራጨው ተመሳሳይ ምላሽ፣ ኢትዮጵያ የድንበር ዳኝነትን
ባለማክበር አካባቢውን ትበጠብጣለች በማለት የወነጀለ ሲሆን፤ ከጅቡቲ ጋር በኳታር ሸምጋይነት ድርድር ከተጀመረ በኋላ የጅቡቲ መንግስት ከኢትዮጵያ ጋር ማበሩ አሳዝኖናል ብሏል፡፡ የኤርትራ መንግስት የሶማሊያ አሸባሪዎችን በማስታጠቅ፣ የጎረቤት አገራትን ፀጥታ ያውካል  በሚል በቀረበ ክስ፣ በ2001 የፀጥታው ምክር ቤት ኤርትራ ላይ ማዕቀብ ሲጥል፤ ከቻይና እና ከራሺያ የተአቅቦ ድምፅ በስተቀር የምክር ቤቱን ይሁንታ በማግኘት ያለፈ ውሳኔ እንደሆነ ይታወሳል፡፡ በወቅቱ ኢትዮጵያ የተለያዩ ሰነዶችን በማስረጃነት ያቀረበች ሲሆን የኤርትራ መንግስት ጐረቤት አገራትን የሚበጠብጠው በመከላከያ ሚኒስትሩ ጀነራል ኤፍሬም ስብሀት አስተባባሪነት እንደሆነና፤ የአየር ሀይል እና የባህር ሀይል አዛዞችን ጨምሮ 12 ጀነራሎች የእንቅስቃሴው መሪዎች እንደሆኑ በሰነዶቹ ተዘርዝሯል፡፡ የኤርትራ የባህር ሀይል ዋና አዛዥ ሜ/ጀ ሁመድ ካሪካሬ፣  ባለፈው አመት የሞቱት  ሜ/ጀ ገብረ እግዚአብሄር አንደማርያም፣ ሜ/ጀ ሀይለ ሳሙኤል፣ የኤርትራ ብሄራዊ ደህንነት አዛዥ ብ/ጄ አብርሀ ካሳ የኢትዮጵያ እና የጅቡቲን ፀረ ሰላም ሀይሎች በማስተባበር ያሰማራሉ ተብለው በስም ተጠቅሰው ነበር፡፡

ሩስያ ለግብጽ የኒዩክሌር ሃይል ማመንጫ ልትገነባ ነው

     የግብጹ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሳሜህ ሹክሪ፤ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብና በሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ ከኢትዮጵያው አቻቸው ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ጋር ትላንትና በአዲስ አበባ የሁለትዮሽ ውይይት አደረጉ፡፡ በውይይቱ ላይ የሱዳን የመስኖ ሚኒስትር እንደተገኙም ታውቋል፡፡ ሁለቱ ሚንስትሮች በአገራቱ መካከል የተጀመሩ የሁለትዮሽ ግንኙነት ውይይቶችን እንደሚቀጥሉ የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ቃል አቀባይ ባድር አብደል አቲ ገልጸዋል፡፡በቅርቡ በአዲስ አበባ በተካሄደው የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው የነበሩት የግብጹ ፕሬዚዳንት አብደል ፋታህ አል ሲሲ፤ በሰሜናዊ ሲና አካባቢ ታጣቂዎች ጥቃት መሰንዘራቸውን ተከትሎ ከኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚንስትር ጋር ሊያደርጉት የነበረውን ውይይት ሰርዘው ወደአገራቸው መመለሳቸውን ያስታወሰው ዘገባው፤ የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ የኢትዮጵያው አቻቸው ያደረጉላቸውን ግብዣ በመቀበል ውይይቱን ለመቀጠል ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸውን ጠቁሟል፡፡በሌላ በኩል ሩስያ፤ ለግብጽ የኒዩክሌር ሃይል ማመንጫ ልትገነባ እንደሆነ የሁለቱ አገራት መሪዎች ባለፈው ማክሰኞ በካይሮ በሰጡት የጋራ መግለጫ እንዳስታወቁ አልጀዚራ ዘግቧል፡፡ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን፤ ከግብጹ አቻቸው አብደል ፋታህ አል ሲሲ ጋር የሃይል ማመንጫ
ግንባታ ስምምነቱን ከተፈራረሙ በኋላ በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት፣ ስምምነቱ የመጨረሻ ውሳኔ ላይ የሚደረስበት ከሆነ፣ ጉዳዩ የኒውክሌር ሃይል ማመንጫ ግንባታ ብቻ ሳይሆን በግብጽ አዲስ የአቶሚክ ኢንዱስትሪ ጅማሬ ይሆናል ብለዋል፡፡ግብጽ ከዚህ በፊት ባቋቋመችውና ከአሌክሳንድሪያ የወደብ ከተማ ምዕራባዊ የሜዲትራንያን ባህር ዳርቻ ላይ በምትገኘው ዳባ ከተማ ውስጥ ባለው የኒውክሌር ምርምር ጣቢያ ላይ የሚገነባው ይህ የሃይል ማመንጫ፣ እያንዳንዳቸው 1ሺህ 200 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ያላቸው አራት ማብላያዎች እንደሚኖሩት ተገልጿል፡፡ግንባታው በተለይ ከቅርብ አመታት ወዲህ የኤሌክትሪክ ሃይል እጥረት እየተስፋፋ ላለባት ግብጽ ሁነኛ መፍትሄ ይሆናል ተብሏል፡፡ የግብጹ አሽራቅ አል አውሳት ድረገጽ በበኩሉ፤ ምንም እንኳን የአገራቱ መሪዎች በይፋ ባያረጋግጡትም፣ አገራቱ ከሃይል ማመንጫ ግንባታው በተጨማሪ የረጅም ርቀት የጦር መሳሪያ ግዢ ስምምነት ፈጽመዋል ሲል ኢንትራ ፋክስ የዜና ተቋምን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡

       የኩዌት መንግስት የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ኢትዮጵያውያን ሴቶችን በህገወጥ መንገድ ወደ አገሪቱ በማስገባት በቤት ሰራተኝነት ያስቀጥራሉ የተባሉ  12 ኢትዮጵያውያን ሴቶች በህገወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር መዋላቸውን እንዳስታወቀ አረብ ታይምስ ዘገበ፡፡
የሚኒስቴሩን መግለጫ ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፤ 12 ሴቶችንና አንድ አሽከርካሪን በአባልነት ይዞ በህገወጥ የሰዎች ዝውውር ስራ ላይ እንደተሰማራ የተገለጸው ይህ ቡድን፣ በአንዲት ኢትዮጵያዊት ሴት መሪነት በህገወጥ መንገድ ወደ ኩዌት የሚያስገባቸውን ኢትዮጵያውያን ሴቶች ለአገሪቱ ዜጎችና ለሌሎች አገራት በቤት ሰራተኝነት ሲያስቀጥር ቆይቷል፡፡
የኩዌት የነዋሪዎች ጉዳይ ምርመራ ክፍል ባለስልጣናት፤ በድኑ በህገወጥ የሰዎች ዝውውር ተግባር ላይ እንደተሰማራ ከታማኝ ምንጭ ያገኙትን መረጃ መሰረት በማድረግ ባካሄዱት ክትትል፣ የቡድኑን አባላት የህገወጥ የሰዎች ዝውውር በሚያከናውንበት ጀሊብ አል ሹዮክ የተባለ የአገሪቱ ክፍል በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን ዘገባው ጠቁሟል፡፡
የቡድኑ አባላት ከአገሪቱ የሰራተኞች ቢሮ ጋር የስራ ግንኙነት ያላቸውና በህጋዊነት የሚንቀሳቀሱ በማስመሰል በበርካታ የኩዌት ነዋሪዎች ላይ የማጭበርበር ድርጊት ሲፈጽሙ ነበር ብሏል፤ ዘገባው፡፡
በቁጥጥር ስር በዋሉት ኢትዮጵያውያን ሴቶች ላይ ምርመራ እየተደረገ መሆኑንና ተገቢውን ህጋዊ እርምጃ ለመውሰድ ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ጋር እየሰሩ እንደሚገኙም ዘገባው አመልክቷል፡፡

  • “ሠማያዊ ፓርቲ የኔን መዋቅር ተጠቅሞ ነው እጩ ያስመዘገበው” አንድነት ፓርቲ  
  • -“እጩዎቻችንን ለማስመዝገብ ከቦርዱ አስፈፃሚዎች ተግዳሮት ገጥሞናል” ሰማያዊ ፓርቲ

      በቅርቡ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በአቶ ትዕግስቱ አወሉ እየተመራ ወደ ምርጫ እንዲገባ የወሰነለት እና በአቶ አበባው መሃሪ እንዲመራ የተወሰነው መኢአድ በምርጫው ለመወዳደር እጩዎቻቸውን ማስመዝገባቸውን ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተገኘው መረጃ ጠቁሟል፡፡
አንድት ፓርቲ ከ200 በላይ እጩዎች ማስመዝገቡን ያስታወቀ ሲሆን መኢአድ በበኩሉ፤ መረጃዎቹ ተጠናቅረው አልደረሱኝም ብሏል፡፡ ከብሄራዊ ምርጫ ቦርድም ፓርቲዎቹ ያስመዘገቧቸው እጩዎችን ብዛትን በተመለከተ ማረጋገጫ ማግኘት አልተቻለም፡፡  
የአንድነት ፕሬዚዳንት አቶ ትዕግስቱ አወሉ፤ ቦርዱ ፓርቲውን እንዲመሩ ከወሰነ ጊዜ አንስቶ ከቢሮ መረካከብ ጋር በተፈጠረው የጊዜ መጓተት ምክንያት በ5 ቀናት ውስጥ ብቻ በአዲስ አበባ ሃያ ሶስቱም የምርጫ ክልሎች ጨምሮ ከሱማሌ፣ ጋምቤላና ትግራይ በስተቀር በሌሎች ክልሎች 201 እጩዎችን ማስመዝገብ መቻላቸውን ገልፀዋል፡፡
ለሌሎች ፓርቲዎች የተሠጠው 49 ቀን ሲሆን ለእነሱ 7 ቀን ብቻ እንደተሰጠና ፓርቲው በ5 ቀን ብቻ እጩዎቹን ለማስመዝገብ መገደዱ የፈለገውን ያህል እጩ ማቅረብ እንዳላስቻለው የጠቀሱት አቶ ትዕግስቱ፤ በማስመዝገብ ሂደቱ ፓርቲው በውዝግብ ውስጥ ማለፉ ተግዳሮት እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል፡፡
የተፈጠረውን ውዝግብ ተከትሎም አባላት ወደ ሠማያዊ ፓርቲ መቀላቀላቸው፣ ሠማያዊ ፓርቲ የኛን መዋቅር ተጠቅሞ እጩዎቹን ለማበራከት አስችሎታል ያሉት አቶ ትዕግስቱ፤ የአንድነትን አባላት ማስመዝገቡ የተገቢነት ጥያቄ ያስነሳል ነው ብለዋል፡፡ “ሠማያዊ ፓርቲ በተለይ በደቡብ፣ በኦሮሚያ እና በአማራ የተለያዩ ቦታዎች ላይ የአንድነት አባላትን አስመዝግቧል” ያሉት የአንድነት ሊ/መንበር፤ ይህም ፓርቲው ቀደም ሲል በአካባቢዎቹ መዋቅር እንዳልነበረውና አጋጣሚውን እንደተጠቀመ ያመለክታል ብለዋል፡፡ “የኛ ሰዎች ባይኖሩ ሠማያዊ ፓርቲ ምን ያስመዘግብ ነበር?” ሲሉ አቶ ትዕግስቱ ጠይቀዋል፡፡
በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን የሠጡን የሠማያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ዮናታን ተስፋዬ በበኩላቸው፤ እንኳን ከአንድነት ወደ ሠማያዊ የተቀላቀሉትን ቀርቶ የፓርቲውን ነባር አባላት እንኳ ለማስመዝገብ ችግር ገጥማቸው እንደነበር ጠቅሰው በተለይ ጐጃም ውስጥ ለፓርላማ 10 እጩዎችን እንዳናስመዘግብ ተደርገናል ብለዋል፡፡ ደቡብ እና ኦሮሚያ ላይ በግልጽ ሠማያዊ ፓርቲን የተቀላቀሉ የአንድነት አባላት መኖራቸውን የጠቆሙት አቶ ዮናታን፤ አዲስ አበባ ላይም ከ23 ቦታዎች በ4ቱ የአንድነት አባላት የነበሩት ይወዳደራሉ ብለዋል፡፡
ሠማያዊ ፓርቲ ከመነሻው 380 መቀመጫ ለማሸነፍ አልሞ 400 እጩዎችን እንደሚያቀርብ አረጋግጦ ወደ ምርጫው እንቅስቃሴ መግባቱን የጠቆሙት አቶ ዮናታን፤ የአንድነት አባላት የነበሩት በፖለቲካ ትግሉ ያበረከቱት አስተዋጽኦ እየተመዘነ ለቦታዎቹ ታጭተው የነበሩ የሠማያዊ ፓርቲ አባላትን በመተካት እንዲገቡ ተደርጓል እንጂ ሠማያዊ የእጩ ችግር የለበትም ብለዋል፡፡ ለአንድነት የተመዘገቡ እጩዎች ሣይቀሩ ከአንድነት ለቀው ለሠማያዊ የመመዝገብ መብትም እንዳላቸው ሊታወቅ ይገባል ብለዋል አቶ ዮናታን፤ የመኢአድ የምርጫ አስተባባሪ በበኩላቸው፤ ፓርቲው በተሰጠው አጭር ጊዜ ውስጥ እጩዎቹን ለማስመዝገብ መሞከሩን ጠቅሰው ምን ያህል እጩዎች ተቀባይነት አግኝተው ተመዘገቡ የሚለውን ለማወቅ ገና ጥረት እያደረጉ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

አንድ ተጫራች 7 ሚሊዮን ዶላር አቅርቧል

የኢራን፣ የእስራኤልና የኩዌት ዜግነት ያላቸው ባለጸጎች፣ ቤተሰቦችና ተቋማት የቀድሞው የኢራቅ ፕሬዚዳንት ሳዳም ሁሴን በስቅላት የተገደሉበትን ገመድ በከፍተኛ ገንዘብ በመግዛት የራሳቸው ለማድረግ የጦፈ ፉክክር ውስጥ ገብተዋል ሲል ቢቢሲ ዘገበ፡፡
ተቀማጭነቱ በለንደን የሆነውን አል አራቢ አል ጃዲድ ድረገጽ ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ ግለሰቦቹ በቀድሞው የኢራቅ ብሄራዊ ደህንነት አማካሪ ሞዋፋቅ አል ሩባይ እጅ ውስጥ የሚገኘውን ይህን ገመድ የራሳቸው ለማድረግ እየተፎካከሩ ነው፡፡
ግለሰቡ በመኖሪያ ቤታቸው ከነሃስ በተሰራ የሳዳም ሃውልት አንገት ላይ ገመዱን አጥልቀው የሚያሳየውን ፎቶግራፍ ከሁለት አመታት በፊት ይፋ ማድረጋቸውን ተከትሎ ገመዱን በእጃቸው ለማስገባት ፍላጎት የሚያሳዩ ግለሰቦች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ማደጉን አንድ የወቅቱ የአገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣን ተናግረዋል፡፡
ገመዱን ለማግኘት በሚደረገው ፉክክር ከተሳተፉት መካከል፣ ሁለት የኩዌት ባለጸጎች፣ አንድ የኢራን የሃይማኖት ተቋም እና አንድ የእስራኤላውያን ሃብታሞች ቤተሰብ እንደሚገኝበት የጠቆመው ዘገባው፣ አንድ ተጫራች 7 ሚሊዮን ዶላር ማቅረቡን አክሎ ገልጧል፡፡
የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ገመዱን ለማግኘት የተጀመረውን ጨረታ የተቃወሙ ሲሆን፣ ጨረታው የሚቀጥል ከሆነ ግን የሚገኘው ገንዘብ የአገሪቱን ህዝቦች ተጠቃሚ ለሚያደርግ ተግባር መዋል ይገባዋል ብለዋል፡፡

ብዙ ወጣቶች በምርጫ ድምጽ እንዲሰጡት ለማድረግ ነው
የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሩን አባል የሆኑበት ወግ አጥባቂው ትሮይ ፓርቲ በቅርቡ በሚከናወነው ምርጫ ብዙ ድምጽ ለማግኘት በፌስቡክ ለሚያደርገው ቅስቀሳ በአመት ከ1 ሚሊዮን ፓውንድ በላይ ገንዘብ ወጪ እንደሚያደርግ ዘ ኢንዲፔንደንት ዘገበ፡፡
ፓርቲው ባለፈው አመት መስከረም ላይ ብቻ የፌስቡክ ተጠቃሚዎች እንዲወዱት ለማድረግ የከፈለውን 25 ሺህ ፓውንድ ጨምሮ፣ በወሩ በድምሩ 123ሺህ የእንግሊዝ ፓውንድ ለፌስቡክ ኩባንያ ገቢ ማድረጉን የጠቆመው ዘገባው፤ ባለፈው ህዳር ወር ፖለቲካዊ ይዘት ላለው ሌላ ድረገጽ 115 ሺህ ፓውንድ መክፈሉን አስታውቋል፡፡
ለፌስቡክ ይህንን ያህል ወጪ ማውጣቱን እንደ ትልቅ ኢንቨስትመንት እንደሚቆጥረው የገለጸው ትሮይ ፓርቲ፤ ገንዘቡን የሚያወጣው ቁጥራቸው የበዛ ወጣቶች በምርጫ ድምጻቸውን እንዲሰጡት በማሰብ እንደሆነ ቢገልጽም፣ የሚሳካለት አይመስልም ብሏል ዘገባው፡፡
በፌስቡክ ተጠቃሚዎች ዘንድ ተወዳጅነትን በማትረፍ ረገድ፣ ብሪቴን ፈርስት የተባለው ፓርቲ ትሮይን በእጥፍ ያህል እንደሚበልጠው የጠቀሰው ዘገባው፣  ብሪቴን ፈርስት 650 ሺህ፣ ትሮይ ደግሞ 340 ሺህ ያህል የፌስቡክ ወዳጆች እንዳሏቸው ጨምሮ ገልጧል፡፡




*ውሳኔው ጨረቃ የማን ናት
በሚለው ጥያቄ ላይ ተጽዕኖ አለው ተብሏል

የአሜሪካ መንግስት፤ አገራት፣ የግል የህዋ ምርምር ተቋማትና ኩባንያዎች በጨረቃ ላይ የሚያከናውኗቸውን የንግድ ስራዎች በተመለከተ ቁጥጥር ማድረግ ሊጀምር እንደሆነ ዘ ኢንዲፔንደንት ዘገበ፡፡
አሜሪካ ቁጥጥር ማድረግ እንደምትጀምር ማስታወቋ፣ ጨረቃ የማን ናት፣ የተለያዩ ቁሳቁሶችን ወደ ጨረቃ መላክ የሚችሉትስ እነማን ናቸው የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ የተጀመሩ ጥረቶችን አንድ እርምጃ ያራመደ ነው ተብሏል፡፡
የአገሪቱን ኩባንያዎች ጨምሮ በመስኩ የተሰማሩ የመላው አለም ኩባንያዎች መንኮራኩሮችን ወደ ጨረቃ መላክና የተለያዩ ስራዎችን ማከናወን የሚችሉት ከአሜሪካ ፈቃድ ሲያገኙ ብቻ ነው ያለው ዘገባው፤ ፍቃዱን የሚሰጠውም የአገሪቱ የፌዴራል አቪየሽን ባለስልጣን እንደሚሆን ጠቁሟል፡፡
ባለስልጣኑ ያወጣው የቁጥጥር መመሪያ ኩባንያዎችና ተቋማት ወደ ጨረቃ ለሚያደርጉት ጉዞ ፈቃድ ከመስጠት በተጨማሪ፣ በጨረቃ ላይ የሚኖራቸውን ክልል የሚወስን ነው፡፡
አሜሪካ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸደቀውንና ጨረቃ እና ሌሎች የህዋው አለም ቦታዎች በማንኛውም መንግስት ባለቤትነት ስር አይሆኑም የሚለውን ህግ እንደተቀበለች ያስታወሰው ዘገባው፣ ህጉ የግል ኩባንያዎች በጨረቃ ላይ እንዳያስቀምጡ ባይከለክልም፣ አሜሪካ ግን ይሄን አካሄድ ለመቆጣጠር መነሳቷን አስረድቷል፡፡

በ189 ዜጎች ላይም የሞት ቅጣት ጥላለች

   የቀድሞውን የግብጽ ፕሬዚዳንት ሆስኒ ሙባረክ በአመጽ ከስልጣን ለማውረድ ከአራት አመታት በፊት በተቀሰቀሰው አመጽ ተሳትፈዋል የተባሉ 230 የአገሪቱ አብዮተኞች ባለፈው ረዕቡ በካይሮ የእድሜ ልክ እስራት እንደተፈረደባቸው  ቢቢሲ ዘገበ፡፡
እ.ኤ.አ በ2011 ታህሳስ ወር ላይ በካይሮው ታህሪር አደባባይ በተካሄደው አመጽ ከአገሪቱ የጸጥታ ሃይሎች ጋር ተጋጭተዋል፣ የተለያዩ የመንግስት ህንጻዎችንና ተቋማትን በእሳት አቃጥለዋል የተባሉት እነዚሁ ተከሳሾች፣ ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው የቅጣት ውሳኔው እንደተላለፈባቸው ዘገባው ጠቁሟል፡፡ ተከሳሾቹ ከእስራቱ በተጨማሪ በድምሩ 2ነጥብ 2 ሚሊዮን ዶላር በቅጣት መልክ እንዲከፍሉ በፍርድ ቤቱ ተውስኖባቸዋል፡፡
ቅጣቱ ከተላለፈባቸው ግለሰቦች መካከል በችሎቱ ተገኝቶ የፍርድ ውሳኔውን ያደመጠው ብቸኛ ተከሳሽ፣ አመጹን በማቀጣጠልና በመምራት ጉልህ ሚና እንደተጫወተ የሚነገርለት የ26 ዓመቱ አህመድ ዱማ፤ ዳኛው ክሱን በሚያነቡበት ወቅት በማጨብጨብና ጮክ ብሎ በመናገር፣ ተቃውሞውን ለማሰማት ሞክሯል ተብሏል፡፡
የተከሳሾቹ ጠበቆች በበኩላቸው፤ ፍርድ ቤቱ ያስተላለፈውን ውሳኔ የተቃወሙ ሲሆን ዳኛው በተከሳሾቹና በጠበቆቻቸው ላይ ተጽዕኖ ሲፈጥሩ ነበር፣ የፍርድ ሂደቱ በአግባቡ አልተከናወነም፣ ውሳኔውም በአገሪቱ ታሪክ አስደንጋጭና የማይጠበቅ ነው ብለዋል፡፡
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፍርድ ቤቱን ውሳኔ የተቃወመ ሲሆን፣ የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይም በአገሪቱ የሚታየው የጅምላ እስራትና ቅጣት ከዲሞክራሲያዊ መርሆዎች ጋር የሚጋጭ ነው ብለዋል፡፡ የአውሮፓ ህብረት በበኩ፤ ግብጽ አለማቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ግዴታዎችን ስትጥስ ቆይታለች፤ የግብጽ ባለስልጣናት ይህንን ግዴታ ማክበርና ፍትሃዊ የፍርድ ውሳኔ እንዲሰጥ ማድረግ ይገባቸዋል ብሏል፡፡
ውሳኔውን ያስተላለፉት ዳኛ ባለፈው ሰኞም የእስላማዊ ቡድን አባላት ናቸው ተብለው በተጠረጠሩ 183 ግለሰቦች ላይ ባለፈው ሰኞ የሞት ፍርድ መበየናቸውን ያስታወሰው ዘገባው፣ አለማቀፍ የሰብዓዊ መብት  ተሟጋች ተቋማት ፍርዱን መቃወማቸውን እንደገለጹ አመልክቷል፡፡