Administrator

Administrator

   ዲቢኤል ግሩፕ የተባለው ታዋቂ የባንግላዴሽ የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት አምራች ኩባንያ በትግራይ ክልል ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ፋብሪካ ሊገነባ መሆኑን ዴይሊ ስታር ድረገጽ ትናንት ዘገበ፡፡
በቀጣዩ አመት የካቲት ወር ላይ ግንባታው ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ የማምረት ስራ ይጀምራል ተብሎ የሚጠበቀው የጨርቃ ጨርቅና የአልባሳት ፋብሪካው፤ ለ3 ሺህ 500 ሰራተኞች የስራ ዕድል እንደሚፈጥር የኩባንያው ከፍተኛ የስራ ሃላፊ መናገራቸውን ዘገባው አመልክቷል፡፡
ኩባንያው ለፋብሪካው ግንባታ ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ ካገኘው 55 ሚሊዮን ዶላር ብድር በተጨማሪ የ15 ሚሊዮን ዶላር ብድር ከስዊድን መንግስት የልማት ፈንድ ማግኘቱን የጠቆመው ዴይሊስታር፣ ምርቶቹን ወደተለያዩ የአውሮፓ፣ የአፍሪካ፣  የመካከለኛው ምስራቅ ሃገራትና ወደ አሜሪካ ኤክስፖርት ለማድረግ ማቀዱንም አስታውቋል፡፡

የ100ሺ ብር የፍትሃብሔር ክስም ቀርቦበታል

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ክርስቲያን መንበረ ፓትሪያርክ ጠቅላይ ፅ/ቤት፣ የፓትሪያርኩን ስም በማጥፋት ወንጀል የተከሰሰው የ“ሰንደቅ” ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ አቶ ፍሬው አበበ ፍ/ቤት ቀርቦ በ5ሺህ ብር ዋስ ተለቀቀ፡፡ ቤተ ክህነት ከወንጀል ክሱ በተጨማሪ ላይ የ100 ሺህ ብር ካሳ እንዲከፈላትም በጋዜጠኛው ላይ የፍትሃ ብሄር ክስ አቅርባለች፡፡
መጋቢት 25 ቀን 2008 ዓ.ም በ“ሰንደቅ” ጋዜጣ ዕትም ላይ “ፓትርያርኩ ለኢትዮጵያ የደህንነት ስጋት ለምዕመናን የድህነት ስጋት” በሚል ርዕስ የተፃፈውን ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ፅሁፍ በማተሙ ነው ቤተ ክህነት ክሱን የመሰረተችው፡፡
ቤተክህነት ያቀረበችው የቀረበው የክስ ዝርዝር እንደሚያስረዳው፤ ለክሱ ምክንያት የሆነው የዲያቆን ዳንኤል ክብረት ፅሁፍ፤ የቤተ ክርስቲያኒቱን ተቋዋማዊ አሰራር ጥላሸት የሚቀባና የፓትርያርኩን ስም የሚያጠፋ እንዲሁም በመልካም ስምና ዝናቸው ላይ ከባድ ጉዳት በማድረስ ህዝበ ክርስቲያኑ የቤተ ክርስቲያኒቱን ተቋማዊ አሰራር እንዳይቀበል የሚያደርግ ፅሁፍ በጋዜጣው ታትሞ እንዲወጣ ያደረገ በመሆኑ በፈፀመው ስም የማጥፋት ወንጀል መከሰሱን ይጠቁማል፡፡ ቤተ ክህነቷ ከዚሁ የክስ ጭብጥ ጋር በተያያዘ ጋዜጠኛው አድርሶብኛል ላላቸው የህሊና ጉዳት የ100 ሺህ ብር ካሳ የጠየቀችበትን የፍትሃ ብሄር ክስም አቅርባለች፡፡ ጋዜጠኛው ባለፈው ረቡዕ በፌደራል የመጀመሪያ ፍ/ቤት ቂርቆስ ምድብ 2ኛ ወንጀል ችሎት ቀርቦ፤ በስራ መደራረብ ምክንያት ባለሙያ ለማማከር እንዳልቻለ በማስረዳት ተለዋጭ ቀጠሮ እንዲሰጠው በጠየቀው መሰረት ፍ/ቤቱ ለግንቦት 23 ቀን 2008 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ ለቀረበበት የ100 ሺህ ብር የፍትሃ ብሄር ክስ ክርክር ለግንቦት 26 ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡

554 እስረኞች እንዲለቀቁ ወስኗል
የዛምቢያ ፕሬዚዳንት ኤድጋር ሉንጉ 40 ኢትዮጵያውያን ወጣት ጥፋተኞችን ጨምሮ በተለያዩ ወንጀሎች ተከስሰው ለተቀጡና በእስር ላይ ለሚገኙ 554 እስረኞች ባለፈው ማክሰኞ ምህረት ማድረጋቸውን ዛምቢያን ናሽናል ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ዘገበ፡፡ፕሬዚዳንቱ ባለፈው ረቡዕ የተከበረውን የአፍሪካ የነጻነት ቀን ምክንያት በማድረግ ባስተላለፉት የምህረት ውሳኔ፣ ከእስር እንዲፈቱ የተወሰነላቸው ኢትዮጵያውያን ወጣት ጥፋተኞች መቼና በምን ወንጀል ተከስሰው ለእስር እንደተዳረጉ የታወቀ ነገር የለም ያለው ዘገባው፣ ከ2015 አንስቶ ከ100 በላይ ኢትዮጵያውያን በዛምቢያ እንደታሰሩ ጠቁሟል፡፡ምህረት የተደረገላቸው ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ሁሉም በወጣትነት የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ እንደሆኑ የጠቆመው ዘገባው፣ ታስረውበት የነበረው እስር ቤት ግን የአዋቂዎች እንደሆነና፣ መንግስት ባወጣው የምህረት ውሳኔ ኢትዮጵያውያኑን ማካተቱ ትርጉም ያለው ነገር ነው መባሉን ገልጧል፡፡በርካታ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በዛምቢያ ሉዋንጉዋ ድንበር በኩል አድርገው ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመሻገር እንደሚሞክሩ የገለጸው ዘገባው፣ የአገሪቱ ፖሊሶችና የኢሚግሬሽን ሰራተኞችም በህገወጥ መንገድ ድንበር የሚያቋርጡ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን እየተከታተሉ በቁጥጥር ስር ማዋል መቀጠላቸውን አስረድቷል፡፡

         አንጋፋው ድምጻዊ ማህሙድ አህመድ፤የክብር ዶክትሬቱን ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ ትላንት ተቀበለ፡፡ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ አርቲስቱ ላበረከተው ድንቅና የረጅም ጊዜ የኪነ ጥበብ ስራ በ2007 ዓ.ም መጨረሻ ላይ ተማሪዎቹን ሲያስመርቅ፣ የክብር ዶክትሬት ከሰጣቸው አራት ሰዎች አንዱ አንደነበር የሚታወስ ሲሆን ማህሙድ በወቅቱ በአገር ውስጥ ባለመኖሩ ተወካዩ በሥነ ስርዓቱ ላይ ተገኝተው እንደነበረ የዩኒቨርሲቲው የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ደምሴ ደስታ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡ በትላንትናው እለት አርቲስቱ ራሱ በአካል ተገኝቶ ከዩኒቨርሲቲው የክብር ዶክትሬቱን ተቀብሏል፡፡ በዚህ ሥነ ስርዓት ላይ የቀድሞው የጎንደር ፋሲለደስ የኪነት ቡድን ዳግም  ምስረታም ተካሂዷል፡፡ ማህሙድ አህመድ፤ በቅርቡ 75ኛ ዓመት የልደት በዓሉን ሲያከብር በማሪዮት ሆቴል ለእይታ ከቀረቡት 75 ፎቶዎቹ መካከል 40 ያህሎ በጎንደር ሥነ ሥርዓቱን ምክንያት በኤግዚቢሽን መልክ ለእይታ የቀረቡ ሲሆን ለአንድ ሳምንት ለተመልካች ክፍት ሆነው እንደሚቆዩም አቶ ደምሴ ጨምረው ገልፀዋል፡፡ በሥነ-ሥርዓቱ ላይ በርካታ አርቲስቶች፣ ታዋቂ ሰዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡  

          የአዲስ አበባ ከተማን የትራንስፖርት ችግር እንደሚፈታ የተነገረለት ሸገር የከተማ አውቶቡስ ትናንት ስራ የጀመረ ሲሆን ለአንድ አውቶቡስ 3.61 ሚ. ብር ፣ ለ50 አውቶብሶች 180 ሚ. ብር ወጪ መደረጉ ታውቋል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ጽ/ቤት፣ ብረታ ብረት ኢንጂነሪግ ኮርፖሬሽን እንዲሰራለት ካዘዛቸው 300 አውቶቡሶች ውስጥ 50ዎቹን ተረክቦ ሥራ
ማስጀመሩን የአስተዳደሩ የትራንስፖርት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ካፓሲቲ ኦፕሬሽን መምሪያ ኃላፊ
አቶ ሙሉቀን አማረ ገልጸዋል፡፡ አውቶብሶቹ ከአንድ ኪሎ ሜትር በታች የሚቆሙ ስላልሆነ፣ የረዥም ርቀት ፍላጎት የሚያሟሉ ናቸው ያሉት አቶ ሙሉቀን፤ ታሪፋቸውም ኪስ አይጎዳውም ብለዋል፡፡ እስከ 4 ኪሎ ሜትር 1.50፣ ከ4-6 ኪ.ሜ 2 ብር፣ ከ6-9 ኪ.ሜ 3 ብር፣ እስከ 10 ኪሎ ሜትር ርቀት 3.50 እንደሚያስከፍሉ በመግለፅ፡፡ አውቶብሶቹ ለጊዜው የሚጓዙባቸውና የተመረጡ መስመሮች፡- ከሜክሲኮ ቦሌ፣ ከቦሌ ፒያሳ፣ ከፒያሳ መገናኛ፣ ከሜክሲኮ ዓለም ባንክ፣ ከሳሪስ አቦ መገናኛ እንደሆኑ የጠቀሱት ኃላፊው፤ ከ3ወር በኋላ 150 አውቶብሶች ሲረከቡ የመስመሮቹ ቁጥር 21 እንደሚደርስና የቀሩትን አውቶቡሶች አጠናቀው አጠናቀቁ ሲረከቡ እንደየአስፈላጊነቱ ሌሎች መስመሮች እንደሚከፈቱ አስረድተዋል፡፡ ሸገር አውቶቡስ የተቋቋመበት ሦስት መሰረታዊ ነገሮች አሉት ያሉት ኃላፊው፣ በአንድ ኪ.ሜ የሚቆም መደበኛ አገልግሎት፣ የተማሪዎች የትራንስፖርት አገልግሎትና ፈጣን የትራንስፖርት
አገልግሎት (ከአስኮ እስከ ጀሞ (16 ኪ.ሜ) እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ሸገር አውቶቡስና አንበሳ አውቶቡስ ሁለቱም የመንግስት የልማት ድርጅቶች ስለሆኑ ጎን ለጎን ይሰራሉ ያሉት አቶ ሙሉቀን፤ አንበሳ አውቶቡስ 814 አውቶቡሶች፣ ሲቪል ሰርቪስ ወደ 400 አውቶቡሶች፣ ሸገር ደግሞ 300 አውቶቡሶች ይኖሩታል፣ ሆኖም ጥናቶች፤ የከተማዋ የትራንስፖርት ፍላጎት በአማካይ 3500 አውቶቡሶች እንደሆነ የሚያመለክቱ ስለሆነ ሌሎች ተጨማሪ አውቶቡሶች ያስፈልጋሉ ብለዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት አውቶቡስ ለመጠበቅ ከአንድ ሰዓት በላይ መጠበቅ ያስፈልጋል ያሉት ኃላፊው፤ የሸገር አውቶቡሶችን በ10 ደቂቃ ውስጥ ማግኘት እንደሚቻል ቢገልፁም በምን መንገድ እንደሆነ አልገለፁም፡፡ የሸገር ዘመናዊ አውቶቡሶች የደህንነት ካሜራ የተገጠመላቸው ሲሆን፣ አውቶብሶቹ የት እንዳሉ መቆጣጠር የሚያስችል ጂፒኤስ፣ የአየር መቆጣጠሪያ ኤሲ እንዳላቸውና፣ አውቶማቲክ ትኬት እንደሚጠቀሙ ሃላፊው ተናግረዋል፡፡

አንድ ተኩላ አንዲት የበግ ግልገል፣ ከዕለታት አንድ ቀን አግኝቶ በጣም አስጐመዠችው፡፡ እንዲሁ
እንይበላት ምክንያት ያስፈልጋል ብሎ አሰበ፡፡ ስለዚህ አንዳንድ ጥያቄና ወቀሳ መሰንዘር ጀመረ፡፡
“አንቺ’ኮ ባለፈው ዓመት ሰድበሽኛል፤ ታስታውሻለሽ?”
ግልገሊትም፤
“ኧረ በጭራሽ ጌታ ተኩላ፤ እኔ አምና አልተወለድኩም”
ጌታ ተኩላ፤
“አንቺ ቀጣፊ! እንዲያውም በኔ መስክ ላይ እየተዘዋወርሽ ትግጪ ነበረ፡፡”
ግልገሊት፤
“ኧረ እኔ ገና ሣር ለመብላት ያልደረስኩኝ ጨቅላ ነኝ፡፡ ጥርሴም አልጠነከረም’ኮ!”
ጌታ ተኩላ፤ ድምፁ እየሻከረና ቁጣ ቁጣ እያለው መጣ፡-
“እንግዲያው ውነቱን ልንገርሽ፣ አዲስ ከፈለቀው ኩሬዬ ውሃ ስትጠጪ ታይተሻል፡፡ ጥግብ ብለሽም
በአካባቢው ፈንጭተሻል!”
ግልገሊትም፤
“ጌታ ተኩላ፤ እኔ ፈፅሞ ውሃ ጠጥቼ አላውቅም፡፡ ገና የእናቴን ጡት ጠጥቼ ያልጠገብኩ አንድ ፍሬ
ግልገል ነኝ!”
ጌታ ተኩላም፤
“ልታጭበረብሪኝ አትሞክሪ! እኔ ደጋ ወጥቼ፣ ቆላ ወርጄ ያጠራቀምኩትን ሥጋ በልተሽብኛል!”
ግልገል፤
“ጌታ ተኩላ! እንዴት መግባባት እንዳቃተን አልገባኝም፡፡ እኔ’ኮ በግ ነኝ፡፡ በግ ሥጋ አይበላም፡፡
ደሞም ከአንተ መኖሪያ ዋሻ ገብቼም አላውቅም፡፡ በቅጡ ተረዳኝ እንጂ እንግባባ”
ጌታ ተኩላም በጣም ተቆጥቶ፤
ያ “ለመግባባታችን ዋና ምክንያትማ የእኔ ረሀብ ነው”
ግልገልም፤
“እኛ ውይይት ውስጥ ያንተን ረሃብ ምን አገባው?” ስትል በጥሞና ጠየቀችው፡፡
ጌታ ተኩላ፤
“አየሽ፣ ያንቺ ችግር ይሄ ነው፡፡ አርቀሽ አታስተውይም፡፡ እኔ ተኩላ፤ ሰማይ ዝቅ መሬት ከፍ ቢል
እራቴን ሳልበላ ማደር የለብኝም!”
ግልገሊትም፤
“እሱ ልክ ነው፡፡ ግን ዕቅድህን ሳታሳውቅ (ፕሮፖዛል ሳታቀርብ)…” ብላ ሃሳቧን ተናግራ
ሳትጨርስ፣ ጌታ ተኩላ እንደ ጉድ ተስፈንጥሮ ግልገሊት ላይ ሰፈረባት፡፡
አንዲትም አጥንት ሳትቀረው ቆረጣጥሞ እራቱን በላ!
(እነሆ ግልገሊት፤ “ሳታመሃኝ ብላኝ” የተሰኘውን ምርጥ የአማርኛ ተረት ባለማወቋ፣ ጉዳዬን
አስረዳለሁ ብላ ስትዳክር ተበላችና አረፈችው!”)
    ***
ችግርን በአግባቡ በውይይት መፍታት የሠለጠነ መንገድ ነው፡፡ ሆኖም ይህ ሊሆን የሚችለው ሁለቱም ተወያይ ወገኖች ከጀርባ የተደበቀ ዓላማ (አጀንዳ) የሌላቸው እንደሆነ ነው፡፡ በአብዛኛው የአገራችን ሰው፣ ቡድን ወይም ፓርቲ የተደበቀ አጀንዳ በሆዱ ይዞ በመወያየቱ ምክንያት ውይይቶች ችግርን የመፍታት አቅም የላቸውም፡፡ ተወያዮቹ የመቀራረቢያ ምክንያት ፍለጋ ሳይሆን የመበላላት ሰበብ ፍለጋ ነው የሚሄዱት፡፡ If you are in the business of duck – hunting, you go where the ducks are. (God
is back: Exporting America’s God ከሚለው መጽሐፍ) ይላሉ ፈረንጆቹ፡፡ ወደምታድነው
እንስሳ ሂድ ነው ነገሩ፡፡ ዳክዬ አዳኝ ከሆንክ ዳክዬ ወዳለበት ሂድ እንደማለት ነው፡፡
ለጉዳይህ መፍትሔ የምታገኘው ጉዳይህ ወዳለበት በመሄድ ነው ማለትም ነው፡፡ አደን ሄደህ
ውይይት ምን ይፈይዳል? ማለትም ነው፡፡
ለየጉዳዩ ሰበብ ከጀርባ እየቋጠረች አገራችን ዛሬ እደረሰችበት ደርሳለች፡፡ በንጉሡ ዘመን፤ በደርግ
ዘመንና አሁንም መጠኑ ይለያይ እንጂ፤ ወይ በእጅ አዙር መነጋገር፣ ወይ በድብቅ አጀንዳ መተጋተግ አሊያም ተቀናቃኝን ጥርስ ውስጥ ማስገባት፤ ከልማድም አልፎ ባህል የማድረግን ሁኔታ ለዓመታት ስንታዘብ ኖረናል፡፡ ትዕግሥቱን ሰጥቶንና “ተመስገን ይሄንንም አታሳጣን!” እያልን እዚህ ደርሰናል፡፡
“ተመስገን ይለዋል፣ ሰው ባያሌው ታሞ
ካማረሩትማ ይጨምራል ደሞ!”
ይሏል ይሄው ነው፡፡ በበገናና ዘለሰኛ ሲሆን ይበልጥ በለሆሣሥ ይሰማል፡፡ ተመስገን ከማለት አልፈን፣ አዕምሮአችንን አንቅተን፣ ችግሮቻችንን አይተን፣ መፍትሔዎቻችንን ሸተን፣ አገራችንን አገር ለማድረግ አንዱ ቁልፍ ነገር በለውጥ ማመን ነው፡፡ ግትር አለመሆን ነው፡፡ እኔ ያልኩት ብቻ ነው ከሚል የአስተሳሰብ ጋግርት መላቀቅ ነው፡፡ ስለሠራነው ሥራ አለመኮፈስ ነው፡፡ ስለቀረንና፤ ድክመታችን ነው ወደምንለው፤ መሄድ ነው፡፡ እንደ አጭበርባሪ ነጋዴ “ባመጣሁበት ውሰደው” ማለትን መተው ነው፡፡ ስንጥቅ ማትረፋችን የታወቀ ነውና እንዳያስተዛዝበን ነው፡፡ ዛሬ የሃያ አምስት ዓመት ጉዟችንን ስናወሳ ለመሞጋገስ ብቻ መዘጋጀት የለብንም፡፡ ገጣሚ ፀጋዬ ገብረመድህን እንደሚለው፤
“ጅላጅል ምላስ ብቻ ናት፣
ማሞካሸት የማይደክማት
ቀን አዝላ ማታ እምታወርድ
ንፉግን ልመና እምትሰድ”
ከውዳሴው ባሻገር ራሳችንን መጠየቅ ያሻል፡፡ አንድ ፀሐፊ እንዳለው፤ “እስከዛሬ የሆነው ሁሉ ለዚህ
ቀን ዝግጅት ነበር፡፡ ይሄኛው ቀን ደግሞ ለነገው መዘጋጃ ነው” (all that has gone before was
a preparation to this day, and this, only a preparation to what is to come)
ዲሞክራሲ የት ደረሰ? የፖለቲካ አመለካከት ልዩነት ጠበበ ወይስ ሰፋ? የኢኮኖሚ ዕድገታችን ምን ውጤት አመጣ? ብዙዎች እየማቀቁ ጥቂቶች እየመጠቁ ያሉበት የሃብት ክፍፍል ነገ የት ያደርሰናል? የሕግ የበላይነት ዕውን ሆኗል? የሲቪክ ማህበረሰቦች ሚናቸውን እንዲወጡ ተገቢው ሁኔታ ተመቻችቶላቸዋልን? ከግንባር ወደ ፓርቲነትን የመቀየር ምኞታችን የት ደረሰ? ወደ ብሔራዊ መግባባት ለመድረስ ምን ያህል በቀናነት እየተጓዝን ነው? በዋናነነት ደግሞ ሙስናን የሙጥኝ ያለውን ሥርዓት እንዴት ልንገላገለው ነው? ከአመራር እስከ ምንዝር የተዘፈቀበት የሙስና አረንቋ፤ ዛሬ ሀ ብሎ እንቅፋቶቹን ማስወገድ የጀመረ ይመስላል፡፡ ዘግይቷል፡፡ ይሁን፡፡ ግን ገና ብዙ ይቀረዋል፡፡ በሥልጣን የባለጉትን አውርደን፤ ጨዋዎችን መተካት ነገ የሚጠብቀን ከባድ ተግባር ነው፡፡ የተመቻቸ የመቦጥቦጫ ክፍተት ዛሬም ሰፍቶ ተንሰራፍቶ እያለ፤ አዳዲስ ሹማምንት ብናስቀምጥ እዚያው ማጥ ውስጥ አዳዲስ ጥርስ እንደ መትከል ነው፡፡ ጓዳ ጐድጓዳው ተፈትሾ፣ ቀዳዳው ሁሉ መደፈን አለበት፡፡ አለበለዚያ ጋሞዎች እንደሚሉት፤ “ገመድ የምትበላው በቅሎዬ ብትሄድ፣ ልጓም (ብረት) የምትበላዋ መጣች” ይሆንና ለከፋ ብዝበዛ እንጋለጣለን!



 እስካሁን ከተሞከሩት የተሻለ ውጤታማ ነው ተብሏል
   ከዚህ በፊት ከተሞከሩት የኤችአይቪ/ ኤድስ መከላከያ ክትባቶች ሁሉ የተሻለ ውጤት አስገኝቷል የተባለ አዲስ ክትባት በመጪው ህዳር ወር ላይ በደቡብ አፍሪካ ሊሞከር እንደሆነ ኤንቢሲ ኒውስ ዘገበ፡፡ የኤችአይቪ/ኤድስ ኢንፌክሽንን በአንድ ሶስተኛ ያህል የመከላከል አቅም አለው የተባለው ይህ ክትባት በቀጣይ ሊደረግ በታሰበው ሙከራ የበለጠ ውጤታማ ይሆናል ተብሎ እንደሚጠበቅ የጠቆመው ዘገባው፤ክትባቱ የሚሞከረው በ5ሺህ 400 ሰዎች ላይ እንደሚሆንም ገልጧል፡፡
ቫይረሱ በአለማቀፍ ደረጃ 35 ሚሊዮን ሰዎችን እንዳጠቃ የጠቆመው የኤንቢሲ ኒውስ ዘገባ፤በየአመቱ 1.2 ሚሊዮን ሰዎችን ለሞት እየዳረገ እንደሚገኝም አስረድቷል፡፡

Tuesday, 24 May 2016 08:29

የዘላለም ጥግ

- ድል አንድ ሺ አባቶች ሲኖሩት፤
ሽንፈት ግን ወላጅ አልባ ነው፡፡
ጆን ኤፍ.ኬኔዲ
- ድል፤ የዝግጁነትና የቁርጠኝነት
ልጅ ነው፡፡
ሳን ሃምፕተን
- ረዥም ዕድሜ ከኖርክ እያንዳንዱ
ድል ወደ ሽንፈት እንደሚለወጥ ታያለህ፡፡
ሳይሞን ዲ ቢዩቮይር
- ጠላት ባይኖር ትግል አይኖርም፡፡
ትግል ባይኖር ድል አይኖርም፡፡ ድል ባይኖር
ደግሞ ዘውድ አይኖርም፡፤
ቶማስ ካርሊሌ
- ከድል ጥቂት ነገሮችን ልትማር
ትችላለህ፡፡ ከሽንፈት ግን የማትማረው ነገር
የለም፡፡
ክሪስቲ ማቴውሶን
- በጦርነት ውስጥ ድልን የሚተካ
ምንም ነገር የለም፡፡
ዳግላስ ማክአርተር
- ድል ጣፋጭ የሚሆነው ሽንፈትን
ስታውቀው ነው፡፡
ማልኮም ፎርብስ
- ወደ ድል በሚደረግ ጉዞ
የመጀመሪያው እርምጃ ጠላትን መለየት ነው፡

ኮሪ ቴን ቡም
- ያለ ዕቅድ ጥቃት የለም፡፡ ያለ ጥቃት
ድል የለም፡፡
ኩርቲስ አርምስትሮንግ
- እውነተኛው ድል የዲሞክራሲና
የብዝኃነት ድል ነው፡፡
ሆስኒ ሙባረክ
- አሸንፋለሁ ብለህ ካሰብክ
ታሸንፋለህ፡፡ እምነት ድል ለማድረግ ወሳኝ
ነው፡፡
ዊሊያም ሃዝሊት
- ዲሞክራሲ፤ ዲሞክራት ያልሆነን
ቡድን ወደ ስልጣን ካመጣ፣ ያንን
የዲሞክራሲ ድል ልንለው እንችላለን?
ሪቻርድ ኢንጄል
- ድል ጣፋጭ የሚሆነው ያንተ
ወገን በማሸነፉ ነው - ወይስ የጠላት ወገን
በመሸነፉ?
ጆን ፓድሆሬትዝ
(ስለ ድል)



ይህ ጽሁፍ ሚያዝያ 21 ቀን 2008 ዓ.ም የአቶ አሰፋ ጫቦ ”የትዝታ ፈለግ” መጽሐፍ በጣይቱ የባሕልና ትምህርት ማዕከል አዳራሽ
በተመረቀበት ወቅት መጽሐፉን ለማስተዋወቅ ካደረግሁት ንግግር አጥሮና ተስተካክሎ (Edited) የቀረበ ነው፡፡

ዓለም ፀሐይ ወዳጆ
(Silver Spring, Maryland USA)

   የተወደዳችሁ እንግዶች፤ በቅድሚያ የዛሬው እንግዳችን አቶ አሰፋ ጫቦ ‹የትዝታ ፈለግ› በሚል ርዕስ ያሳተመውን መጽሐፍ ለምርቃት በማብቃቱ በጣይቱ የባህልና የትምህርት ማዕከል ስም ‹እንኳን ደስ አለህ!› እላለሁ::
በዛሬው ምሽት የትዝታ ፈለግ  በሚል ርዕስ ለንባብ ያበቃውን መጽሐፉን ልንመርቅ ነው የተሰባሰብነው:: መጽሐፉን በማነብበት ወቅት ብዙ ወደ ማውቃቸው ጊዜያትና ግለሰቦች የወሰደኝ ሲሆን የአጻጻፍ ውበቱም እጅግ አስደንቆኛል፤ የባህሪይ አቀራረፅ ችሎታውና የአካባቢ ስዕላዊ መግለጫውም አርክቶኛል::
አቶ አሰፋ ጫቦ፤ ከተራራ አናት ላይ ከሚገኝ ሜዳማ ቦታ ላይ ጨንቻ ከተማ ነው የተወለደው:: ከጋሞ ሰንሰለት ተራራዎች አንዱ ጫፍ ላይ የሚገኝ ጠረጴዛ ነው ይላታል፤ጨንቻን ሲገልጣት፡፡  ከ 2ኛ- 6 ኛ ክፍል እዚያው ጨንቻ የተማረ ሲሆን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በአዲስ አበባ ኮከበ ጽባህ እስከ ፲ኛ ክፍል ተምሮ አቋረጠ። ሆኖም በራሱ መንገድ ህግ ተምሮ መመረቅ ብቻ ሳይሆን በአለም አቀፍ ውድድሮችም ሁለቴ ተካፍሎ፣ከንጉሱ እጅም የወርቅ ኦሜጋ ሰአት ለመሸለም በቅቷል፡፡
በመጽሐፉ ውስጥ በወህኒ ቤት ሳሉ፣ በሙሉጌታ በቀለ አካሚነት (ገጽ15-18) ሰለሞን ደርቤን በእግሩ ማቆም መቻልን አልፎም ፈጣን ሆኖ የእስረኛ ምግብና ቡና አመላላሽ ተደርጎ መመደቡን አሳይቶ አስደምሞኛል:: የአገራችንን የአብያተ ክርስቲያኑንም ጭምር ድንቅ ውበት በማስቃኘት፣ ለቱሪዝም አዳዲስ አካባቢዎችን ለማስተዋወቅ ሞክሯል፡፡
በመጽሐፉ ላይ በጠቀሳቸው (ገጽ 25-34) በረዘነና በወይናይ ባለው ችግር መነሻነት በትግራይና በኤርትራ መካከል የነበረው ቅራኔ ምን እንደሚመስል እንድናይ ያደረገበት ዘዴ አስገርሞኛል:: የሕግ አዋቂነቱን ለአቀራረቡ ማነጻጸሪያ ተጠቅሞበታል፡፡ “ረዘነ ወልዱና ወይናይ ሁለት የተለያየ ባህርይ ያላቸው ሰዎች ናቸው። ረዘነ ተጫዋች፤ተግባቢ፣ደግ፤ገራገር፤ተናጋሪና በመጠኑም ቢሆን ችኩልም ነው። ፈጣን ነው ማለት ይቻላል። ሀብታም ነው ማለትም ይቻላል። ወይናይ ምስኪን ነው። ሁለመናው ምስኪን ነው። ከ3 አመት በላይ ሲኖር ከመንሾካሸክ ያለፈ ድምጽ ሲወጣው አልሰማሁም። -----” ይለናል።
በመጽሐፉ (ገጽ19-24) ጎንደሬውን፤ቀናና የዋሁን፤እንደወጣ የቀረውን ዶ/ር ካሳሁን መከተን ያነሳዋል፡- ‹‹ በቀን ቢያንስ አንዴ ሳያነሳቸው የማይውላቸው ሁለት ነገሮች አሉ። አንደኛው ስለደባርቅ/ዳባት ነው። የኢትዮጵያን ኋላ ቀርነት ማስረጃ ያደርጋቸዋል። እስከ ዛሬ ማብራት እንኳን አልገባላቸውም! ይላል። “ሶሻሊዝም፤ሶሻሊዝም!” ይላሉ ደባርቅ መብራት መች ገባ ?” ይላል። ይህችው ነች! አይለዋውጥም!”
ብዙ ባለታሪኮና ተረቶች መጽሐፉን አጣፍጦለታል፡፡  እናቱን አክብረው “እንዬ” እያሉ ባደጉት ጓደኞቹ በእነ ዶክተር ገዛኸኝ በላይና በፍስሀ ዘለቀ ታሪክ ውሰጥ አጥልቆ የመንፈስን ከመንፈስ ጋር መዋሃድ እንዲሁም የህዝብን ሥነልቦናዊ አመለካከትን እንድናይ ያደርገናል::
“ነፍጠኛ” ማለት አማራ ብቻ ነው ማለት እምነት እንጂ እውነት እንዳልሆነና “ነፍጠኛ” (117-151) በሚል የሚበጠብጠንን ጥያቄ ለመመለስ ናችሁ የተባልነውን ሳይሆን ውስጣችን ገብተን ሆነን ያለነውን እንድናስተውል ይጎተጉተናል፡፡ ጋሽ አሰፋ፤“አቅብጦኝ ከደርግ ጋር ገጠምኩ” ብሎ አያውቅም:: አምኖ እንጂ ምናምን ፍለጋ ወይም ሰው ገፍቶት እንዳልገባ በግልጽ አስቀምጦልናል:: እንዲያውም “በመሸ በጠባ ቁጥር በጥሼ የምቀጥለው ማተብ የለኝም !” ይለናል::
በትረካዎቹ ጸሃፊው በንባብ የዳበረና የበሰለ መሆኑን ከማሳየቱም ሌላ ወደ አሜሪካ ስለ መምጣትና መኖር ያካፈለው ምክርም በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ ስለ ስደቱ ዓለም ችግርና ውጥንቅጥ ሲጽፍም፤ ስደተኛው በሃብት ድህነትና በአእምሮ  ድህነት መካከል ያለው ልዩነት የጠፋበት መምሰሉን ፍንትው አድርጎ ያሳየናል፡፡ በአጠቃላይ ጆሮ ጠገብነት ማወቅን አለመተካቱን ይገልጽልናል፡፡   
ጀግና ፍለጋ ጦር ሜዳ መሪዎች አምባ፣ የፖለቲካ ሰዎች አምባ እንሄዳለን:: ጀግና ሲገኝ አገር ያውቀዋል፤ ፀሃይ ይሞቀዋል:: ያልታወቁ በየቤቱ የታጨቁ ተራ ሰው የሆኑ ጀግኖች አሉ በማለት፣ በዕለት ተዕለት ኑሮአችን ያልተሰጣቸውን በመፈጸም የበለጠ ጀግና ስላደረጋቸው የአማቾቹ የቤት ሠራተኛ ስለሆነችው ስለ ወሎየዋ ዘውዲቱ አስማረ “የኔይቱ ጀግና!” (63-67) በሚል ርዕስ ይተርክልናል፡፡  “ጋሞ” ይላል “ጋሞ ግብር ገበረ እንጂ ሥርዓቱን አልገበረም” በማለት ጥፋቱን ስህተቱን በማመን መቀበልና ባደባባይ ይቅርታ መጠየቅ የጋሞነት መገለጫና አብሮ የተወለደ የውስጥ ባህርይ መሆኑን በመተንተን፣ ለየት ስላለው የአገርና የህዝብ አስተዳደር ሥርዓት ሲያጫውተን፤ አንዳንዶቻችን በአገራችን ውስጥ ይህ መኖሩን ባለማወቃችን እንቆጫለን:: ወደ ዛሬያችን ለማምጣት በምኞት እንጋልባለን::
 ሌላው የጋሽ አሰፋ ትልቅነቱ፣ እንደ አንዳንዶቹ ፀሃፊዎች በራሱ አራት ነጥብ ዘግቶ እመኑልኝ ሳይለን፣ “ያየሁትና የኖርኩት እንጂ ያጠናሁት አይደለም” ማለቱ ነው:: በትዝታዎቹ ውስጥ እየሾለከ የሁላችንንም ትዝታ ይቆሰቁሰዋል፡፡ በተለይ በመጽሃፉ የጠቀሳትን፣ ይህንን ማዕከል ‹‹ጣይቱ›› ብዬ እንድሰይም ምክንያት የሆነችኝን Empress Taytu and Menilik the II of Ethiopia ደራሲ ክሪስ ፕራውቲን  (Chris Prouty 111-115)  እንደኔው አግኝቶ ስላደነቃትና ስላሞካሻት ይበልጥ ተደስቻለህ::
ዛሬ በአገራችን ስለተንሰራፋው ሥርዓትም በማዘን እየገለጸ ወደተሻለ እንድንጓዝ ይማፀነናል:: በእስራት ብዛት የህዝብ ነጻነት ታፍኖ የቀረበት ዘመንም አገርም አለመኖሩን በማስረገጥ፣ለ“የጋራ ቤታችን ” የሚፈለገውን መጠነኛ ጥገና በማካሄድ ፈንታ መናድ የመረጡትን ያወግዛቸዋል፡፡ አገራቸውን ባለማወቅ ወይም ለማወቅ ባለመፈለግ፣ ነቀዝ የበላው ቤት እንድትሆን ማድረጋቸውን በመውቀስም፣የምትፈለገዋን  ከስህተቷ ልምድ የቀሰመች አዲሲቷ ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን እንድንገነባ ይጣራል:: የትዝታ ፈለግ ራስ ወዳዶች እራሳቸውን እንዲጠይቁና እንዲፀየፉም ይገፋፋል፡፡ በተለይም ገጽ 244 “አልዘቅጥም መባል ያለበት ወደ ታች ወደ ምድር ቤት ምን ያህል ሲዘቅጡ ይሆን?›› ሲል በመጠየቅ ‹‹ከዚህ በላይ አልወርድም በቃኝ አይባልም! በቃኝ አታውርደኝ ተብሎስ አይፀለይም …” በማለት እነዚህን ወገኖች ይሸነቁጣቸዋል:: ከቁጣ ይልቅም ወደ ዳኝነት፣ ወደ ማመዛዘን እንድናደላ  ይጋብዘናል::
 አብርሃም ሊንከን እንዳለውና ጋሽ አሰፋም በመጽሃፉ ላይ እንደጠቀሰው፤ ‹‹ማንንም ያለ ቂም እንድንመለከት፣ሁሉንም በልግስና እንድናቅፍ፣በሃቅ ላይ እንድንጸና፣አምላክም ይህንን ሐቅ እንድናይ እንዲረዳን እንማጸን”:: ኢትዮጵያውያንንም የማይመጣን ነገር ከመጠበቅ ረጅምና ዝነኛ ታሪካችን ይገላግለን !
ጋሽ አሰፋም፤ “እመለስበታለሁ “ እያለ ያለፋቸውን ጉዳዮች፡- ስለ እስረኛው ቡና ማፍያ፣ ስለ ሁለንተናዊ የኑሮ ዘርፍ ማሟያ፣ ስለ ቀኝ አዝማች ታዬና ስለ ኮሎኔል መንግስቱ ኃ/ማርያም፣ ስለ አሜሪካ አገር ድመትና ውሻ ዘውድ መጫን፣ ወዘተ አሰባስቦ ሁለተኛ መጽሐፉን ለአንባቢያን እንዲያደርስ ያብቃው::
  “በትዝታ ፈለግ” ምክንያት እኔም እንደ ጋሽ አሰፋ ግርጫ ቤት መስራት አማረኝ:: እኔም ጨንቻን ወደ ታች የዞዞን ተራራ ማዶ ለማዶ ማየት አማረኝ:: ጨንቻን ለመሞት ሳይሆን ለመኖር መረጥኳት!! እዚያ ሰው አይሞትምና…በዝግታ መራቅ…ባልተስተዋለ መልኩ ማለፍ…አማረኝ!
   በድጋሚ እንኳን ደስ አለህ !!!

  ይህን የማያደርጉ መገናኛ ብዙኃን እርምጃ ይወሰድባቸዋል
        በካምቦዲያ የሚገኙ መገናኛ ብዙኃን የአገሪቱን ጠቅላይ ሚኒስትር በተመለከተ በሚሰሯቸው ዘገባዎች ላይ ተገቢውን ክብር መስጠት እንደሚገባቸውና ሙሉ ማዕረጋቸውን መጥቀስ እንዳለባቸው በአገሪቱ የመረጃ ሚኒስቴር ትዕዛዝ እንደተሰጣቸው ቢቢሲ ዘገበ፡፡ሚኒስቴሩ ለአገሪቱ የህትመትና የኤሌክትሮኒክስ መገናኛ ብዙኃን በሰጠው መግለጫ እንዳሳሰበው፣ ከመጪው ነሐሴ ወር ጀምሮ በሚሰሯቸው ዘገባዎች ላይ የጠቅላይ ሚኒስትሩን፣ የባለቤታቸውንና የተወሰኑ ባለስልጣናትን ከእነ ሙሉ ማዕረጋቸው መጥራት ይገባቸዋል፡፡መገናኛ ብዙኃኑ የአገሪቱን መሪ በተመለከተ በሚሰሯቸው ዘገባዎች ላይ፣ “ጌታ ጠቅላይ ሚኒስትርና የጠቅላይ ጦር አዛዥ ሁን ሴን” በማለት ከነ ሙሉ ማዕረጋቸው እንዲጠሯቸው ማሳሰቢያ እንደተሰጣቸው የጠቆመው ዘገባው፣ ሚኒስቴሩ ይህን በማያደርጉ መገናኛ ብዙኃን ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ ቢናገርም እርምጃውን በተመለከተ የጠቀሰው ነገር እንደሌላ አመልክቷል፡፡