Administrator

Administrator

የ“ፍትሕ መጽሔት” ማኔጂንግ ዳይሬክተር ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ፣ ዛሬ ኅዳር 11 ቀን 2016 ዓ.ም. በጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ከጠበቆቹ ጋር ቀርቧል።
ፍርድ ቤቱ በዛሬው ዕለት ቀጠሮ ሰጥቶ የነበረው፣ በባለፈው ቀጠሮ ፣ የጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ጠበቆች፤ “የጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት፣ የዐቃቤ ሕግን የይግባኝ ቅሬታና የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ሲሰጠን ገጽ አጉድሎ ስለሆነ የተሟላ መልስ መስጠት ባለመቻላችን፣ መልሳችን እንድናሻሽል ይፈቀድልን” በሚል አቤቱታ አቅርበው ነበር፡፡
ዐቃቤ ሕግም በበኩሉ፤ “በዚህ አቤቱታ ላይ እኔም አስተያየት መስጠት አለብኝ” ብሎ ተከራክሯል፡፡
ጠበቆቹም፤ “እኛ ስህተት ሠራ ያልነው ፍርድ ቤትን ነው፡፡ ስህተቱን እንዲያርምም የጠየቅነው ፍርድ ቤቱን ነው፡፡ ከዐቃቤ ሕግ ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም፡፡ ስለዚህም ዐቃቤ ሕግ ስለማይመለከተው ጉዳይ አስተያየት እንዲሰጥ ሊፈቀድለት አይገባም፤” በሚል ተከራክረዋል፡፡
ፍርድ ቤቱም፤ “ዐቃቤ ሕግ አስተያየት ይስጥ ወይስ አይስጥ ብሎ ትእዛዝ ለመስጠት ዳኛ ስለሚጎድል ለህዳር 11 ቀን 2016 ዓ.ም  ቀጠሮ ስጥተናል፤” ማለቱ ይታወሳል፡፡
በአቶ ሸምሱ ሲርጋጋ የመሀል ዳኝነት (ሰብሳቢነት)፣ በሀፊዝ አባጀማል እና መሀመድ አህመድ የግራና ቀኝ ዳኝነት ጉዳዩን ያየው ፍርድ ቤትም፣ “ዐቃቤ ሕግ አስተያየት መስጠት ይገባዋል” ሲል የሰጠው ትእዛዝ ዛሬ ህዳር 11 ቀን 2016 ዓ.ም በችሎት በንባብ ተሰምቷል፡፡
ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በሰጠው አስተያየት፤ “የተሰጠው ትእዛዝ  ፍጹም ስህተት ነው፡፡ ይሄ የፍርድ ቤቱን ተአማኒነት ገና ከመነሻው ጥርጣሬ ውስጥ የሚጥል ነው፡፡ ችሎቱ፣ ዐቃቤ ሕግ የሚጠይቀውን ሕገ-ወጥ ጥያቄ በሙሉ እየተቀበለ የሚሄድ ከሆነ ታዲያ፣ እንዴት ነው ነፃና እውነተኛ ፍትሕ የሚገኘው?” ሲል ቅሬታውን ገልጿል፡፡
በጉዳዩ ዙሪያ  ያነጋገርናቸው አንዳንድ የሕግ ባለሙያዎችም፤ “ዐቃቤ ሕግ አስተያየት ይስጥ” ተብሎ መታዘዙ አግባብነትና ተቀባይነት የሌለው መሆኑን በአጽንኦት ተናግረዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ፣ የዐቃቤ ሕግን አስተያየት ህዳር 30 ቀን 2016 ዓ.ም  በቢሮ በኩል ከተቀበለ በኋላ፣ የጋዜጠኛ ተመስገን ጠበቆች ያቀረቡት የመልስ ማሻሻያን በተመለከተ ውሳኔ ለመስጠት ለታኀሣስ 11 ቀን 2016 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
 የቴሌግራም ቻናልችንን  በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…
https://t.me/AdissAdmas

የባንኩ  የሃብት መጠን  83 ቢሊዮን ብር መድረሱን አስታውቋል

 ሕብረት ባንክ የ25ኛ ዓመት የብር ኢዮቤልዩ ክብረ በዓሉን በዛሬው ዕለት በይፋ ያበሰረ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት የባንኩ የሃብት መጠን  83 ቢሊዮን ብር መድረሱን አስታውቋል።

 አጠቃላይ ካፒታሉ 9. 3 ቢሊዮን ብር፣ እንዲሁም  60 ቢሊዮን ብር ብድር እና 64 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ተቀማጭ እንዳለው የገለጸው ባንኩ፤ በየዓመቱ ከ25 እስከ 30 በመቶ እድገት እያስመዘገበ  መምጣቱንም ጠቁሟል።

ባንክ ባለፉት 25 ዓመታት የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ መዝለቁ የተገለፀ ሲሆን፤ ከ15 ዓመታት በፊት ሞባይል ባንኪንግን፣ ኤስኤምኤስ ባንኪንግ በሚል በመጀመር ቀዳሚ ባንክ እንደሆነ ተመልክቷል፡፡

በተጨማሪ ባንኩ የኮር ባንኪንግ ሲስተም በራሱ ሰራተኞች መተግበሪያ በማበልፀግ በኢትዮጵያ ብቸኛው ባንክ መሆኑም ተነግሯል፡፡  

ባንኩ የተመሠረተበት የ25ኛ ዓመት የብር ኢዮቤልዩ ክብረ በዓል፣ ዓመቱን በሙሉ በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚያከብርም ተጠቁሟል።

*ኩባንያው በቅርቡ በ3 የአፍሪካ አገራት የዳታ ማዕከሎቹን ይከፍታል

በሰባት የአፍሪካ አገራት የሚንቀሳቀሰው  ራክሲዮ የዳታ ማዕከል ኩባንያ፣ በአዲስ አበባ አይሲቲ ፓርክ የገነባው ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የዳታ ማዕከሉ  በይፋ ሥራ መጀመሩን አበሰረ፡፡

በዓይነቱ ልዩ መሆኑ የተነገረለት የራክሲዮ ኢትዮጵያ የዳታ ማዕከል፣ በይፋ ሥራ መጀመሩን የማብሰሪያ ሥነስርዓት ዛሬ ጠዋት ረፋዱ ላይ በአይሲቲ ፓርክ የተከናወነ ሲሆን፤ በሥነሥርዓቱ ላይ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ አምባሳደሮች፣ የፋይናንስ ተቋማት ሃላፊዎች፣ የቴክኖሎጂ ዘርፉ መሪዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

ራክሲዮ ኢትዮጵያ በይፋ ሥራ መጀመሩን አስመልክቶ ባወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ፤ “በኢትዮጵያ ዋና ከተማና የአገሪቱ የኢኮኖሚ ማዕከል በሆነችው አዲስ አበባ የሚገኘው አዲሱ የራክሲዮ ደረጃ III ዕውቅና የተሰጠው ዘመናዊ የዳታ ማዕከል፣ ከምንጊዜውም በላይ እያደገ ለመጣው የመንግሥትና የግል ተቋማት የዳታ ማዕከል አገልግሎት ጥያቄዎች፣ አስተማማኝና የማይቆራረጥ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መፍትሄ በማቅረብ መልስ የሚሰጥ ይሆናል፡፡” ብሏል፡፡

ማዕከሉ፤ 800 ራኮችና እስከ 3 MW የአይቲ ሃይል፣ ደህንነቱ በተጠበቀ የዳታ ማዕከል አገልግሎት ለመስጠት፣ ሙሉ በሙሉ ምትክ ያለው ያለማቋረጥ የሚሰራ የአይቲ መሰረተ ልማቶች  ዝግጁ አድርጓል - ሲል አክሏል ኩባንያው በመግለጫው፡፡

በኢትዮጵያ የራክሲዮ ዳታ ማዕከል ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ በዕውቀቱ ታፈረ ባደረጉት ንግግር፤ “ይህ አገልግሎት በአዲስ አበባ መጀመሩ ለራክሲዮና ለአገራችን በዲጂታል መሰረተ ልማት ረገድ መሰረት የሚጥል ነው፡፡ አገልግሎቱ በኢትዮጵያ የምጣኔ ሃብት ዕድገት ውስጥ ከፍተኛ ሚና የሚጫወት ሲሆን፤ በተለያዩ አካባቢዎች የሚከናወኑ የንግድ ሥራዎችንና የመንግሥት ኤጀንሲዎች የሥራ እንቅስቃሴን ከማፋጠንም ባሻገር፣ አህጉራዊና ዓለማቀፍ አገልግሎትና የይዘት አቅራቢዎችን ወደ ኢትዮጵያ ለመሳብ አጋዥ እንደሚሆን እናምናለን፡፡” ብለዋል፡፡

ዋና ሥራ አስኪያጁ በማከልም፤ “የማዕከላችን ደረጃ III ዓለማቀፍ የምስክር ወረቀት፣ እኛ  እየሰጠን ያለው የአገልግሎት ጥራት መጠን ማሳያ ሲሆን፤ ለደንበኞቻችን ደግሞ ለማናቸውም ንብረቶቻቸው ከፍተኛ ደህንነት አስተማማኝ ማረጋገጫ የሚሰጥ ነው፡፡” ሲሉ አስረግጠው ተናግረዋል፡፡

የዳታ ማዕከሉ በይፋ ሥራ መጀመሩን ያበሰሩት የራክሲዮ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሮበርት ሙሊንስ በበኩላቸው፤ “ይህንን በዓይነቱ ልዩና የመጀመሪያ የሆነ ወሳኝ መሠረተ ልማት በኢትዮጵያ ተግባራዊ በማድረጋችን እጅግ ኩራት ይሰማናል፡፡ የኢትዮጵያን ቀጣይ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽንና የዲጂታል አካችነት ጅምር ግቦችን የሚደግፍ እንደሆነ ሙሉ እምነታችን ነው፡፡ ብለዋል፡፡

ሮበርት ሙሊንስ አክለውም ሲናገሩ፤ “ይህ ጊዜ ለእኛ እንደ ኩባንያ እጅግ በጣም ደስተኛ የሆንበት ነው፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት በኡጋንዳ እንደዚሁ ተመሳሳይ ማዕከላችንን ከጀመርን በኋላ፣ ራክሲዮ ኢትዮጵያ በአህጉሪቱ ሁለተኛው ማዕከላችን  መሆኑ ነው፡፡ እ.ኤ.አ. እስከ 2024 የመጀመሪያ አጋማሽ ድረስ ተመሳሳይ ማዕከሎችን  በሞዛምቢክ፣ በአይቮሪኮስትና በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የምንከፍት ይሆናል፡፡” ብለዋል፡፡

ዛሬ ረፋድ ላይ በአይሲቲ ፓርክ የተገነባው የራክሲዮን ኢትዮጵያ የዳታ ማዕከል በይፋ ሥራ መጀመር ከተበሰረ በኋላ፣ የዕለቱ እንግዶችና ባለድርሻ አካላት እንዲሁም የሚዲያ ባለሙያዎች  የዳታ ማዕከሉን ጎብኝተዋል፡፡

“--በሙድ የመተረክ ዘዬ፣ ዶ/ር ፍራንክልን የረዳቸው ይመስለኛል። የሥነ-ልቡና እና ሥነ-አዕምሮ ይዘት ያለውን ድርሰት በጊዜው በነበረው ሙድ ላይ ተመርኩዘው የእስረኞችን ሁኔታ፣ ችግርና መፍትሄ ለመተንተን ጠቅሟቸዋል የሚል ዕምነት አለኝ። እዚህ ላይ ሙድ/ሁኔታ ለአንድ ርዕሰ-ጉዳይ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው
መዘንጋት የለብንም

መነሻ:- ድርሰትን መተርጎም የተለመደ
እና የሚበረታታ ሲሆን፤የትርጉም ሂደቱ ከዋናው መጽሐፍ ላይ ከቀጥታ ትርጉም (equivalent
translation) ይልቅ በአገባብ/ በሁኔታ በመወሰን (contextual/ context-based translation) አንቀጽ-በአንቀጽ መተርጎም ይመከራል። ብሎም፣ የአንቀጾቹ ስብስብ (ወደ essay ከፍ ያሉ አንቀጾች) በessay መልክ ሲሆኑ የሚሰጡትን ትርጉም/ እንድምታ ማጤን ተገቢ ነው። ይህ ማለትአንቀጾቹ በessay ተጠቃለው/ተዋህደው የሚሰጡትን መልዕክት ከዋናው መጽሐፍ ፍሬ-ሀሳብ ጋር ማመሳከር አግባብ ነው እንደማለት ነው።
በትርጉም ሥራ ውስጥ፣ የመጀመሪያው (የዋናው) ድርሰት ማሕበረሰብ ታሪክ፣ ባሕል፣ ዕምነት… ወዘተ. የሚተረጎምለትን ሕዝብ ታሪክ፣ ባሕል፣ ዕምነት… ሊጫን፣ ወይም ሊጣረስ ይችላል። ስለሆነም፣ ለሕዝቡ/ለአንባቢው ባመቸ መልክ (ዋናው ሃሳብ ሳይሸራረፍ) እየተኩ መተርጎም ይመከራል። እዚህ ላይ፣ ‹‹ዘርህ እንደ ምድር አሸዋ ይብዛ›› የሚል የወንጌል ቃል፣ አሸዋ በሌለባቸው፣ በረዶ በመላባቸው
አካባቢዎች ‹‹ዘርህ እንደ ምድር በረዶ ይብዛ›› ተብሎ ተተክቶ ተተርጉሞ አይተናል። (ግን ‹‹ዘርህ እንደ ምድር በረዶ ይቅለጥ›› ማለት አይቀልም ነበር?) በአገራችን የተነበቡ የትርጉም ሥራዎች ከመጀመሪያው ድርሰት ላይ ትረካዎችን፣ ወይም የትረካ ክፍሎችን የመቆራረጥ/ የመሸራረፍ አባዜ ይታይባቸዋል። ይኼ ጉዳይ የድርሰቱን ሙሉ ሃሳብ እንዳንረዳው ያደርገናል። ለምሳሌ፣ ‹‹ፍቅር እስከ››
መቃብር ላይ የተተረከውን የሰብለንና የበዛብህን ውብ ጾታዊ መቧጠጥ/ንክኪ ቆርጠን ወደ ሌላ ቋንቋ ብንተረጉም የዚያ ቋንቋ ተናጋሪ የድርሰቱን ሙሉ ጭብጥ እንዳይረዳው ያደርጋል። የ‹‹ለምንን ፍለጋ›› በረከቶች:- “Man’s Search for Meaning”: - ትርጉም ድርሰቱ በጀርመን ውስጥ የነበረ የእስር ቤት ታሪክ ሲሆን፣ ባለ ታሪኩ (ቪክቶር ፍራንክል - የአዕምሮ ሕክምና ዶክተር ናቸው) ከሌሎች ታሳሪዎች ጋር የነበራቸውን ቆይታ፣ ያሳለፉትን ፍዳ፣ ገጠመኞች…. ወዘተ. ያሠፈረበት ድርሰት ነው።
ሲግመንድ ፍሮይድ፣ ለአዕምሮ መታወክ መንስኤው ከወሲብ ጋር በተገናኘ የሚከሰት ደስታ-ቢስነት ነው ይላል። ቪክቶር ፍራንክል ደግሞ፣ የአዕምሮ መታወክን ከፈቃድ ትርጉም (the will to meaning) ጋር ያያይዛል። ደራሲው ምንም እንኳን የግል የእስር ታሪኩን ቢያትትም፣ በዙሪያው የሚስተዋለውን የአዕምሮ ዝቅጠት (ለምሳሌ፣ በእስረኞቹ ዘንድ ሕይወትን ለማቆየት ሲባል ዝቅ ያሉ/ተራ የሆኑ ጉዳዮችን በማምሰልሰል፣ በማለም፤ ስለ

ምግብና ስለ መጠጥ አብዝቶ በመጨነቅ)
የሚፈጠረውን የሥነ-ልቡና እና የሥነአዕምሮ ድቀት ፍቅረኛን በማለም፣ በጥበብ በመደሰት፣ የተፈጥሮ ጸጋን በማድነቅ፣ ጀንበርን/ብርሃንን በመናፈቅ፣ ውበትን በማድነቅ… ወዘተ. መቅረፍ እንደሚቻል ይገልጻል። ከአዕምሮ ዝቅጠት (mental regression) ለመላቀቅ (በአራዶች አባባል ‹ለመፋታት›) ፍቅር፣ ብርሃን፣ ውበት፣ ጥበብ፣ ተፈጥሮ… ወዘተ. አዎንታዊ ፋይዳ እንዳላቸው ተገልጿል።
የምሳሌያዊ አነጋገር፡- በትርጉም ሥራዎች ላይ ትኩረትን ከሚሹ ጉዳዮች አንዱ የምሳሌያዊ አነጋገር ነው። በድርሰት ውስጥ አንድን ሃሳብ፣ ወይም ትረካ በምሣሌያዊ አነጋገር፣ በዘይቤአዊ ንግግር፣ በፈሊጥ፣ በተረት… መግለጽ ነገሩን ለማግዘፍና ግልጽ ለማድረግ ይረዳል። ተርጓሚው የምሣሌያዊ አነጋገርን የተጠቀመ ሲሆን፣ ይኼም ለአንባቢው ባሕል እና ልምድ በቀረበ መልኩ ነው። ለምሳሌ፣ ‹‹የተቸገረ እርጉዝ ያገባል››፤
ገጽ 21 ላይ መጥቀስ ይቻላል።የግርጌ ማስታወሻዎች፡- ይኼ ነጥብ የትርጉም ሥራው ልዩ መገለጫው ይመስለኛል። በትርጉም መጽሐፉ
ውስጥ የተካተቱ የኅዳግ ማስታወሻዎች (በተርጓሚው የተጨመሩ)፣ አንድን ቃል ከማብራራት እስከ አንድን ርዕሰ-ጉዳይ በሰፊው እስከ መተንተን ይደርሳሉ። የዚህ ፋይዳ በትረካው ውስጥ የተነሱ፣ ምናልባት ግርታን/ የግንዛቤ ችግርን ሊፈጥሩ ለሚችሉ ቃላትና ርዕሰ-ጉዳዮች አንባቢ ሰፋ ያለ ማብራሪያ እንዲያገኝ ይረዳል። ብሎም፣ የኅዳግ ማስታወሻዎቹ ከዋናው የመጽሐፉ ጭብጥ ያፈነገጡ አይደሉም።
ለማሳያ፣ ገጽ 18፣ 22፣ 32፣ 35፣ 51፣ 78…
ላይ በኅዳግ ማስታወሻ የተካተቱ ገለጻዎችን መመልከት ይቻላል። ይኼ ሙከራ እንደ አርአያ ተቆጥሮ ሌሎች ደራሲዎች በትርጉም ሥራዎቻቸው ላይ ቢሞክሩት ጠቃሚ ነው የሚል ሃሳብ አለኝ።የሙድ ዓይነት ጸሐፊ፡- አንድን ጉዳይ/ ታሪክ በቁመናው ልክ ከመዘክዘክ፤ በወቅቱ የነበረውን ሙድ መተረክ ለድርሰት ሀሳቡ ግዝፈትን ይሰጣል። ለአብነት ያህል፡- አንኮበር ተጉዘን የአጼ ምኒልክን ቤተመንግሥት እየጎበኘን ነው እንበል፤ ‹‹የንጉሠነገሥቱን ሲናድር አይተን ተደመምን፤ ነካንም›› ከምንል ‹‹የንጉሠ-ነገሥቱን ሲናድር ለመንካት ተራኮትን›› ብለን ብንገልጽ ግዝፈት ይኖረዋል። ደራሲው፣ (ከሞላጎደል) ታሪኮቹን/ገጠመኞቹን በሙድ ለመግለጽ ክሯል፤ በጊዜው የነበሩ ሁኔታዎች የጫሩበትን ሥሜቶች በምስል መልክ ተርኳል።
ምሳሌ እንጥቀስ፡- ‹‹የጠፈር አለንጋዎች እርቃን ገላዎችን ሲገርፉ ሰማን።…. ቀጥሎ ለመላጨት ወደ ሌላ ክፍል ተነዳን።›› ገጽ 28፤ በማለት የእስረኛውን ውርክብ እና የካፖዎቹን ያፈነገጠ አሠራር ተርኳል። በሙድ የመተረክ ዘዬ፣ ዶ/ር ፍራንክልን
የረዳቸው ይመስለኛል። የሥነ-ልቡና እና ሥነ-አዕምሮ ይዘት ያለውን ድርሰት በጊዜው በነበረው ሙድ ላይ ተመርኩዘው የእስረኞችን ሁኔታ፣ ችግርና መፍትሄ ለመተንተን ጠቅሟቸዋል የሚል ዕምነት አለኝ። እዚህ ላይ ሙድ/ሁኔታ ለአንድ ርዕሰጉዳይ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው መዘንጋት የለብንም። ሙዶች/ሁኔታዎች ጉዳይን የመገንባት/ ወደ-ጉዳይነት የማደግ አቅም አላቸው። የጉዞና የሥነ-ልቡና እንዲሁም
የሥነ-አዕምሮ ድርሰቶች በሙድ መልክ ሲተረኩ ሃሳቡ ይገዝፋል ብዬ አምናለሁ። ደራሲው ከሙድ በመነሳት የተለያዩ መላምቶችን ማስቀመጥ ይችላል።እዚህ ላይ የተርጓሚው ድርሻ የሚናቅ አይደለም፤ የትርጉሙ መልክ ታሪኮቹን
በጥሬው መዶለት ሳይሆን፣ በጊዜው የነበሩ ሙዶችን/ሥሜቶችን በውብ ቋንቋ እያስደገፉ መተረክ ነው። እሰይ የሚያሰኝ ነው።
ንድፍ/methodology እና መቃን/
frame-work፡- በቀለም ትምህርት መስክ፣ ጥናታዊ ጽሑፍን ለማስኬድ ሁነኛ/ትክክለኛ ንድፍ፣ ብሎም መቃን እንደሚያስፈልግ ይታወቃል። ለአብነት፡- survey design, experimental design, correlational design, causal comparative/ex-postfacto design, case-study design…
ወዘተ. ተጠቃሽ ናቸው። እንዲሁም፣ ንድፍና መቃን ድርሰትን በአግባቡ ለማስኬድ ይረዳሉ።
ለማሳያ፡- ታሪክ፣ ፍልስፍና፣ ሥነልቦና፣ ሥነ-አዕምሮ… ወዘተ. በድርሰት ዓለም የተለመዱ ንድፍና መቃን ናቸው። ለጥቁምታ፡- ራሻዊያን ጸሐፊዎችን ብንመለከት፣ በድርሰቶቻቸው በሚስሉት ገጸ-ባሕሪይ በኩል የአንድን ፍልስፍናዊ ኅልዮት ሕልው መሆን፣ ወይም ውድቀት ለማሳየት ይሞክራሉ። ድርሰቱ በፍሬድሪክ ኒቼ ኅልዮት (theory)፣ ‹‹የሚኖርለት ለምን ያለው (ለ-ጠበቅ ተደርጋ ትነበብ) ሰው፣
ማንኛውንም እንዴት ይቋቋማል›› መሠረት ያደረገ ሲሆን፤ ባለታሪኩ በኅልዮቱ ልክ ከከበበው ጨለማ ወደ ብርሃን ይሸጋገራል። መውጫ፡- ‹‹ለምንን ፍለጋ›› ከታሪካዊ ዘገባ ይልቅ፣ የሙድ ጽሑፍ እንደሆነ ይሰማኛል። በትርጉም ሥራው ላይ በስፋት የተካተቱ የግርጌ ማስታወሻዎች ወገግታን ይፈጥራሉና ሌሎች ተርጓሚዎች ፈለጉን ይከተሉት እላለሁ። ከዚህ በዘለለ፣ ያለአግባብ የተጣመሩ ቃላት በትርጉም
ሥራው ላይ ሠፍረዋል። (ጥምር ቃላት፡-
ለምሳሌ ‹‹ሥጋ›› እና ‹‹ቤት›› የሚሉ ቃላት ሲጣመሩ - (ሥጋ-ቤት) - ትክክለኛ ፍቺ ያለው ቃል እንደሚፈጥሩ ይታወቃል፤ ነገር ግን በ‹‹ለምንን ፍለጋ›› ውስጥ በርካታ ቃላት ያለግብራቸው ተጣምረው ተገኝተዋል /ምናልባት በድንገት/።
 በንባብ ወቅት መታከትን ሊፈጥሩ እና ትርጉም ሊያዛቡ ይችላሉ። ‹ከልጅ ልጅ ቢለዩ› ነውና፣ ይኼ ሃቲት ንጡል ሳይሆን፤ ዋናውንና ትርጉሙን ሥራ በወፍ-በረር
የማየት ሙከራ ነው።

ኢትዮጵያ ወደከፋና የለየለት የእርስበርስ ጦርነት እንዳትገባ፣ በአገሪቱ ሰላም ለማስፈን የሚቻልበትን መንገድ በማፈላለግ፣ ከከፋ አደጋ ትታደጋት ዘንድ ለአሜሪካ ጥሪ ቀረበ። ጥሪውን ለአሜሪካው ፕሬዚዳንት ያቀረቡት በአሜሪካ የሚገኙ የኢትዮ-አሜሪካን ሲቪል ማህበራት
ናቸው።
ማህበራቱ በአሁኑ ወቅት ደብዳቤውን ለፕሬዚዳንት ባይደን ለመፃፍ የተነሳሱበትን ምክንያት ሲያስረዱም፤ በአገሪቱ በአሁኑ ወቅት እየተካሄደ ያለው የእርስበርስ ጦርነት በአለማቀፍ ማህበረሰብ፣ በአሜሪካ መንግስትም ሆነ በሌሎች ተፅዕኖ ማሳደር በሚችሉ አካላት ሁሉ ታውቆ በዲፕሎማቲክ መንገድ ጦርነቱን ለማስቆም እንዲችሉ ለማድረግ ታልሞ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡
በፊደራል መንግስቱና በአማራ ከልል ውስጥ በሚንቀሳቀሱ የፋኖ ታጣቂዎች መካከል ያለው ውጥረት ተባብሶ የትጥቅ ትግል ማስከተሉን ያወሳው የማህበራቱ ደብዳቤ፤ ይህ ችግር አፋጣኝ መፍትሄ ካላገኘ ወደ የእርስበርስ ጦርነት በማደግ ኢትዮጵያን ወደ ማተራመስና ለአፍሪካ ቀንድ ትልቅ ስጋት መጋረጡ አይቀሬ ኢትዮጵያ ወደከፋ የእርስበርስ ጦርነት እንዳትገባ አሜሪካ ትታደጋት ዘንድ ተጠየቀ መሆኑን አመልክቷል፡፡ አሜሪካ ይህንን ጦርነት የማስቆምና ሰብአዊ መብቶችን የመጠበቅ የሞራል ግዴታ እንዳለባትም ተጠቁሟል፡፡  

አሁን በአገሪቱ በስራ ላይ ያለው ብሄር ተኮር ፊደራሊዝም ሀገሪቱን በፍጥነት ከቁጥጥር ውጪ ወደሚሆን ሁከት እየከተታት እንደሆነም ማህበራቱ በደብዳቤያቸው መጠየቃቸውን የዘገበው ዶቼቪሌ የዜና አውታር አሜሪካ ተቀባይነት ያለው መንግስታዊ ሽግግር በማመቻቸት ለኢትዮጵያ አዲስ ህገ መንግስት የሚዘጋጅበት ሂደት እንድትደግፍ ጥሪ ማቅረባቸውን ገልጿል፡፡

በአሜሪካው ተራድኮ ድርጅትና በአለም ምግብ ፕሮግራም ይሰጥ የነበረው ተቋርጦ የነበረው የቆየው የምግብ እርዳታ ዳግም መጀመር የመኖር ተስፋን እንዳሳያቸው ተረጂዎች ገለፁ፡፡ እርዳታው በተገቢው መንገድ ለተረጂዎች የሚደረስበትን መንገድ በማመቻቸቱ ረገድ እርዳታ
አቅራቢ ድርጅቶቹ ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ ይገባልም ብለዋል፡፡
የአሜሪካው የተራድኦ ድርጅት (ዩኤስኤይድ) እና የአለም የምግብ ፕሮግራም (WFP) ባለፈው አመት ሰኔ ወር ላይ ሰብአዊ እርዳታው እየተሰረቀ ላልተፈለገ ዓላማ እንዲውል ተደርጓል በሚል ምክንያት ሰብአዊ እርዳታውን መቋረጡን ተከትሎ፣ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የነበረው
ሰብአዊ ቀውስ እንዲባባስ ረሃብና ረሃብ ወለድ ሞት እንዲበራከት ምክንያት መሆኑም ተገልጿል፡፡በጦርነቱ ሳቢያ ከመኖሪያ ቀዬአቸው ተፈናቅለው በትግራይ በአማራና በአፋር  ክልሎች የተለያዩ አካባቢዎች የሰፈሩ ተፈናቃዮች፣ የሰብአዊ እርዳታው ዳግም መጀመር በእለት ደራሽ እርዳታ እጦት ሳቢያ ለአስከፊ ረሃብና ሞት የሚዳረጉ ወገኖችን የሚታደግ በጎ እርምጃ ነው ብለዋል፡፡ የሰብአዊ እርዳታ አሰጣጥ ላይ ግን ትኩረት ተደርጎ ለእርዳታው ፈላጊዎች
ብቻ እንዲደርስ የሚደረግበት አሰራር ተግባራዊ ሊደረግ እንደሚገባው ተረጂዎቹ ተናግረዋል፡፡
የዓለም የምግብ ፕሮግራም በስርቆት ሳቢያ ኢትዮጵያ ውስጥ አቋርጦት የቆየውን የምግብ እደላ ዳግም ሲጀምር አሰራሩን በመቀየር ግልጽ፣ በማስረጃ በተደገፈና ገለልተኛ በሆነ አሰራር ላይ በማተኮር፣ እርዳታው ከ3.2 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑት ተረጂዎች መድረስ የሚያስችልበትን አሰራር ተግባራዊ እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡
አዲሱ አሰራር በስፋት የተሞከረና ጠንካራ የቁጥጥር አሰራርን ተግባራዊ ያደረገ ይሆናልም ተብሏል፡፡ ሰብአዊ እርዳታው ምግብ ወደ ሚከማችባቸው መጋዘኖችና እደላው ወደሚካሄድባቸው አካባቢዎች በሚጓጓዝበት ወቅት የተጠናከረ ጥበቃና ክትትል እንደሚደረግባበትም የአለም ምግብ
ድርጅት አስታውቋል፡፡ የምግብ እርዳታው ከታለመለት አላማ ውጪ ውሎ በሚገኝበት ወቅት አስቸኳይ ጥቆማና ሪፖርት በማቅረብ አፋጣኝ እምጃ መውሰድ የሚቻልበትን አሰራር እንደሚከተልም የዓለም ምግብ ድርጅት በመግለጫው አስታውቋል፡፡

የማህፀን ሞኝ ዕጢ የምንለው የካንሰርነት ባሕርይ የሌለው የማሕፀን ውስጥ እባጭ ሲሆን ከማሕፀን ግድግዳ ጡንቻዎች የሚነሳ ነው ።
** በቁጥር እና በመጠን ይለያያሉ ።
** በፍጥነት ወይንም በዝግታ የሚያድጉ ሊሆኑ ይችላልሉ፡፡ አንዳንድ ጊዜም  በራሱ ሊጠፋም ይችላል፡፡

** አንዲት ሴት በመውለጃ ዘመኗ እንዲሁም ከ 30 እስከ 40 አመት እድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሴቶች ላይ አብዝተው ይከሰታሉ።
** በአብዛኛው ግን የሚገኘው በድንገት በሚደረግ ምርመራ ነው ፤ ብዙ ሰዎች በሕይወት ዘመናቸው ውስጥ የማሕፀን ዉስጥ እጢ  እንዳለ እንኳ ላያውቁ ይችላሉ ምክንያቱም
ብዙ ጊዜ ምንም አይነት ምልክቶች አያሳይም ።
➡️ የማሕፀን ሞኝ ዕጢ ምልክቶች
የማኅፀን ሞኝ ዕጢ በአብዛኛው ምንም ዓይነት ምልክት የማያሳይ ቢሆንም በአንዳንድ ሰዎች ላይ የሚከሰቱ ምልክቶች እንዚህ ናቸው፡፡
▪️ ከፍተኛ የሆነ የወር አበባ  ደም መፍሰስ ወይም የሚያሰቃዩ የወር አበባዎች
▪️ ከሰባት ቀናት በላይ የሚቆይ የወር አበባ ማየት
▪️ ማሕፀን አካባቢ ግፊት መሰማት ወይንም ሕመም
▪️ ቶሎ ቶሎ የውሃ ሽንት መምጣት ወይም ለመሽናት መቸገር
▪️ የሆድ ድርቀትና በሆድ አካባቢ ወይም በታችኛው ጀርባ ላይ ህመም
▪️ በግንኙነት ወቅት ህመም.
➡️  ሐኪምዎን ማማከር የሚገባዎ መቼ ነው?
     ▪️ ብዙን ጊዜ ምንም አይነት ህመም ከሌላቸው በጊዜ ሂደት አንዲት ሴት ስታርጥ ወይም የወር አበባ ማየት ባቆመች ጊዜ መጠናቸው እየኮመሸሸ እና እያነሰ ስለሚመጣ በመድሀኒትም ሆነ በቀዶ ህክምና መታከም አያስፈልጋቸውም፤ ነገር ግን አንዲት ሴት :-
    ▪️ በእጢው ምክንያት የመጣ የወር አበባ መዛባት ፣ በብዛት ካለ እና ደም ማነስ ካመጣባት
    ▪️ ከፍተኛ የሆነ ህመም ካላት (ከእጢው ጋር የተገናኘ)
    ▪️ እጅግ መጠኑ የበዛ እጢ ከሆነ
    ▪️ እርግዝና ከከለከላት ወይም ደግሞ እርግዝና ተከስቶ ለውርጃ እንደምክንያት ከሆነ (ሌሎች እርግዝና የሚከለክሉ ወይም ውርጃን የሚያመጡ ነገሮች ሁሉ ከተጣሩ በውሀላ)
➡️  የማሕፀን ሞኝ ዕጢ እና እርግዝና
የማሕፀን ሞኝ ዕጢ በአብዛኛው እርግዝናን የማይቃረን ቢሆንም አንዳንዴ ዕጢው በሚገኝበት ቦታ ምክንያት በጥቂት ሰዎች ላይ እርግዝና እንዳይፈጠር መንስዔ ይሆናል፡፡ ይህ በሚሆንበት ጊዜ ሐኪምን በማማከር ከእርግዝና በፊት
መደረግ ያለባቸውን ቅድመ ሆኔታዎች ማድረግ ተገቢ ነው፡፡
➡️  ኢትዮ ጠቢብ ሆስፒታል

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ከዶክተር ጌታቸው ተድላ  ጋር በትብብር ያዘጋጁት ጸሀፌ ትእዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድን የሚዘክር መርሃ ግብር፣ የፊታችን  እሁድ  ከጠዋቱ  3 ሰዓት ጀምሮ  በሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ይካሄዳል፡፡

የጸሀፌ ትእዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ ቤተሰቦች  የመርሃ ግብሩ  አጋር ሲሆኑ፤ በዕለቱ ‹‹የአክሊሉ የህይወት ጉዞ በምስል››  የተሰኘ በዶክተር ጌታቸው ተድላ  የተሰናዳ መጽሐፍም ይመረቃል ተብሏል፡፡

የተወዳጅ ሚድያና ኮሚኒኬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ እዝራ እጅጉ ለአዲስ አድማስ  እንደተናገረው፤ በሚመረቀው መጽሐፍ ውስጥ እጅግ አስደናቂ የሆኑ የአክሊሉ የህይወት ጉዞን የሚያሳዩ 166 ፎቶግራፎች ተካትተዋል፡፡ ዶክተር ጌታቸው  መጽሐፉን ለማዘጋጀት ሁለት አመት እንደፈጀባቸው ታውቋል፡፡

በመጽሐፉ የምረቃ ሥነ-ስርአት ላይ ዶ/ር ያእቆብ አርሳኖ፤ ዶ/ር ፍሬህይወት ስንታየሁና ሌሎች ምሁራንም የአክሊሉ ሀብተወልድን አስተዋጽኦ የሚያስረዱ ሲሆን፤ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተጋበዙ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎችም ይታደማሉ ተብሏል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አክሊሉ ሀብተወልድ፣ ከወጣትነታቸው አንስቶ ሀገራቸውን በዲፕሎማሲ ያገለገሉ ሲሆን፤ በተለይም በኢትዮጵያ የባህር በር ህጎች እንዲወጡ፤ ኤርትራ በፌዴሬሽን ከኢትዮጵያ ጋር  እንድትቀላቀል ትልቅ ስራ የሰሩ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ነበሩ፡፡  አክሊሉ ሀብተወልድ፣ 60ዎቹ የቀዳማዊ  ኃይለስላሴ ባለሥልጣናት በግፍ ሲገደሉ ህይወታቸውን ያጡ ታላቅ ሰው ነበሩ፡፡

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን፣ የአክሊሉ ሀብተወልድን አሻራ ለትውልዱ ለማስተላለፍ ባለፉት  ዓመታት በርካታ ሥራዎችን ያከናወነ ሲሆን፤ ከእነዚህም ውስጥ ስለ አክሊሉ ሀብተወልድ በኦድዮ ሲዲ እና በዲቪዲ ታሪካቸው  በዘጋቢ ፊልም እንዲሰራጭ ማድረጉ ተጠቃሽ ነው፡፡ በተጨማሪም የዋሉት ውለታ በእንግሊዝኛም ተዘግቦ እንዲቀርብ አድርጓል፡፡  ባለፉት 8 አመታት፣ ከ59 ጊዜ በላይ የአክሊሉ ሀብተወልድ አስተዋጽኦ በመገናኛ ብዙኃን እንዲዘገብም ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን  የመሪነት ሚናውን ተወጥቷል፡፡

ይህ ፕሮጀክት አሁን ላለበት ደረጃ እንዲበቃ ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትር አክሊሉ ሀብተወልድ ልጅ  አቶ አምዴ አካለወርቅ ትልቁን የአንበሳ ድርሻ የሚወስዱ ሲሆን  በመቀጠል ደግሞ ከ10 አመት በፊት የአክሊሉን የእስር ቤት ማስታወሻ ወደ እንግሊዝኛ  የመለሱት ዶክተር ጌታቸው ተድላ  ለእኚህ ታላቅ ኢትዮጵያዊ  መታወቅና መታወስ የበኩላቸውን ተወጥተዋል፡፡

ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ለኩባንያው አዲስ ሥራ አስፈፃሚ መሾሙን አስታወቀ
ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ፣ በቅርቡ ለቅቀዋል ሲባል የነበሩትን የቀድሞ ዋና ሥራ አስፈፃሚ በመተካት፣ ለኩባንያው አዲስ  ዋና ሥራ አስፈፃሚ እንደተሾመለት አስታወቀ፡፡

ቤልጂየማዊው አዲሱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዊልያም ቫንሀለፑተን፣ የቀድሞውን ሥራ አስፈፃሚ አንዋር ሶሳን በመተካት የተሾሙ መሆናቸውን  ኩባንያው በዛሬው ዕለት ለመገናኛ ብዙኃን ይፋ አድርጓል፡፡ አዲስ የተሾሙት ሥራ አስፈፃሚ በዘርፉ ትልቅ እውቀትና የ25 ዓመታት ልምድ ያላቸው መሆኑ ተነግሯል፡፡
 
ሳፋሪኮም በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ  ከ2 ሺህ በላይ የቴሌኮም አገልግሎት መስጫ ጣቢያዎች እንዳሉት የተናገሩት አዲሱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ፤ በቀጣዮቹ ሁለት አመታት ይህንን ወደ 7 ሺህ ለማሳደግ ማቀዱን አስታውቀዋል፡፡

በተጨማሪም በአሁኑ ወቅት 35 በመቶ የኢትዮጵያን ክፍል በኔትወርክ መሸፈን መቻሉን የገለጹ  ሲሆን፤ ይህንንም በሁለት ዓመታት ውስጥ ከ80 በመቶ በላይ ለማሳደግ መታቀዱን ጠቁመዋል፡፡

ኩባንያው  በአሁኑ ሰዓት ትርፍ አግኝቷል ለማለት ከባድ ነው ያሉት ሥራ አስፈፃሚው፤ በቀጣዮቹ ሁለትና ከዛ በቀረቡ ዓመታት ውስጥ ወደ ትርፍ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

ኩባንያው በኢትዮጵያ ከ900 በላይ ሰራተኞች ያሉት መሆኑን የተናገሩት አዲሱ ሥራ አስፈፃሚ፤ በቀጣዮቹ ሁለት አመታት 500 ለሚሆኑ ሰዎች ቀጥተኛ የስራ እድል እንደሚፈጥርም አመልክተዋል፡፡
በአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ በ14 .5 ሚሊዬን ዶላር የተገነባ ዘመናዊ የፕላስቲክ ቧንቧና መገጣጠሚያ ማማረቻ ፋብሪካ የፊታችን ቅዳሜ ይመረቃል፡፡
ፋብሪካውን “ኢ ዜድ ኤም ትሬድ እና ኢንቨስትመንት” የተሰኘው ኢትዮጵያዊ የንግድ ኩባንያና የቻይናው ዓለም አቀፍ ድርጅት ሪፎ በጋራ እንደገነቡት ተገልጿል፡፡
የፋብሪካውን ምርቃት አስመልክቶ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽንና የኩባንያዎቹ ከፍተኛ አመራሮች በዛሬው ዕለት በጋራ መግለጫ የሰጡ ሲሆን፤ ፋብሪካው በዘርፉ ያለውን የአቅርቦት እጥረት ለመፍታትና ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን ለመተካት ያለመ ነው ተብሏል።
ፋብሪካው ወደ ስራ ሲገባ 2ሚሊዬን ሜትሪክ ቶን ፒፒአር ቱቦዎችና 1 ነጥብ 9 ሚሊዬን የፒፒአር መገጣጠሚያዎች ፣ 1 ሚሊዬን ሜትሪክ ቶን የፒቪሲ ፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦዎችና 9 መቶ ሺህ የፒቪሲ መገጣጠሚያዎች እንዲሁም 3 ነጥብ 5 ሚሊዬን ሜትር በላይ የፒቪሲ ኮንዲዩት የማምረት ዓመታዊ አቅም አለው ተብሏል፡፡
ፋብሪካው በአሁኑ ሰዓት የሙከራ ምርት እያመረተ ሲሆን ፥ ሙሉ በሙሉ ወደ ስራ ሲገባ ከ600 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል እንደሚፈጥር ተጠቁሟል፡፡
በ3 ሺህ ካሬ ሜትር ላይ ያረፈው ፋብሪካው፤ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዘመናዊ የፕላስቲክ ቧንቧና መገጣጠሚያ ማምረቻ ኢንዱስትሪ በመሆን እውቅና ማግኘቱም በመግለጫው ተመላክቷል፡፡
የቻይናው ሪፎ ኩባንያ በዘርፉ የ27 ዓመት ልምድ ያካበተና በመላው ዓለም እየሰራ እንደሚገኝ፣ በኢትዮጵያም ልምዱን፣ የቴክኖሎጂ ሽግግሩንና ብራንዱን ይዞ እንደመጣ የተገለጸ ሲሆን፤ ኢትዮጵያዊው ኢ ዜድ ኤም በበኩሉ፣ ላለፉት 6 ዓመታት የሪፎን ምርቶች ብቸኛ ወኪል አስመጪ ሆኖ ሲሰራ እንደቆየ የጠቆሙት ዋና ሥራ አስፈፃሚው አቶ እስመለአለም ዘውዴ፣ ምርቱን በማስመጣት ብቻ በአገር ውስጥ ያለውን ፍላጎት ማሟላት ስላልተቻለ በአገር ውስጥ ማምረቱ አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን አብራርተዋል።
ፋብሪካው በሙሉ አቅሙ ስራ ሲጀምር፣ 50 በመቶ ምርቱን ለጎረቤት አገራት ምርት እንደሚልክም ተገልጿል፡፡