Administrator

Administrator

Monday, 05 January 2015 08:10

ፖለቲካዊ ሃሜቶች

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በቅርቡ በዓለም የኢኮኖሚ ሰሚት ላይ ለመሳተፍ ወደ ቻይና መዝለቃቸው ይታወሳል፡፡ በቤጂንግ ቆይታቸው ታዲያ ሲወጡ ሲገቡ ማስቲካ እያኘኩ ያዩዋቸው ቻይናውያን “እኚህ ፕሬዚዳንት ሳይሆን ራፐር ነው የሚመስሉት” በሚል ክፉኛ ነቅፈዋቸዋል፡፡
*           *          *
በዚሁ የቤጂንግ ስብሰባ ላይ የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲንም ተገኝተው ነበር፡፡ እሳቸው ደግሞ የቻይናን ቀዳማዊት እመቤት አሽኮርምመዋል በሚል ነበር የተወነጀሉት፡፡ ውንጀላው ከበድ ቢልም አንዳንድ ወገኖች “የሰው ድንበር መጣስ ለፑቲን ብርቃቸው አይደለም” ሲሉ የባሰ ወንጅለዋቸዋል፡፡
*           *          *
በቻይና፡-
ሳንሱር - አያሳስብም
ግርፋት - አያሳስብም
የህፃናት ጉልበት ብዝበዛ - አያሳስብም
ማስቲካ ማኘክ ግን - ዓይንህን ላፈር ያስብላል!!
*           *          *
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሮናልድ ሬገን እ.ኤ.አ በ1981 ዓ.ም የግድያ ሙከራ ተፈፅሞባቸው ነበር፡፡ ሆስፒታል ተወስደው ወደ ቀዶ ህክምና ክፍል ሊገቡ ሲሉ ሃኪሞቹን ትክ ብለው እያዩ፤ “ሁላችሁም ሪፐብሊካን እንደሆናችሁ ተስፋ አደርጋለሁ” ብለው ነበር ይባላል፡፡ (ዲሞክራት ሃኪሞችን አያምኗቸውም!)
“ይሄ ቡና ከሆነ እባካችሁ ጥቂት ሻይ አምጡልኝ፡፡ ይሄ ሻይ ከሆነ አባካችሁ ጥቂት ቡና አምጡልኝ”
አብርሃም ሊንከን

ከዕለታት አንድ ቀን ሁለት ወንድማማች ዝንጀሮዎች በአንዲት ዝንጀሮ ወዳጃቸው ይጣላሉ፡፡
አንደኛው ለሁለተኛው፤
“እንግዲህ እዚች ሚስቴ ዝንጀሮዬ ጋ ድርሽ እንዳትል” ይለዋል፡፡
ሁለተኛው፤
“አይ ወዳጄ እኔ ልልህ ያሰብኩትን ነው አንተ አሁን ያልከው፡፡ የሀሳብ መመሳሰል ያስገርማል፡፡ ዞሮ ዞሮ እዚች ሚስቴ ጋ ድርሽ ካልክ በራስህ ፈረድህ”
አንደኛው
“እንዴት?”
ሁለተኛው፤
“ሚስትነትዋ ያለጥርጥር የእኔ ነው፡፡ አርፈህ ተቀመጥ”
አንደኛው፤
“አርፈህ መቀመጥ ከቻልክ አንተው አርፈህ ተቀመጥ! አለዛ እንግዲህ እንዴት በቡጢ እንደማንገጫግጭህ ስታይ ዋጋህን ታውቃለህ!”
ሁለተኛው፤
“አንተ እኔን?”
አንደኛው፤
“አዎ አንተን ምናባክ እንዳትሆን ነው?”
ተጋጋሉ፡፡ ሁለቱም ለቡጢ ተቀራረቡ! ተሰነዛዘሩ፡፡ ሌሎች ች መጡና ከበቡዋቸው፡፡ ጩኸት በረከተ! የሠፈሩ አለቃ የሆነው የሁለቱ ወንድማማች ዝንጀሮዎች አባት መጣና ገላገላቸው፡፡
ሁሉም ፀጥ እርጭ አሉ፡፡
አባት፤
“እሺ የፀቡ መንሥዔ ምንድን ነው?” ሲል ጠየቀ፡፡
አንደኛው፤
“ሚስቴን እየነካ አስቸገረኝ”
ሁለተኛው፤
“እኔንም ሚስቴን እየነካ አስቸገረኝ”
አባት፤
“ሁለታችሁም ስለአንዲት ዝንጀሮ ሴት ነው የምታወሩት?”
አዎን አሉ ሁለቱም፡፡
“እንግዲያው” አለ አባት “ይቺ ዝንጀሮ ትጠራና ትምጣ” አለ፡፡
ዝንጀሮይቱ ተጠርታ መጣች፡፡
አባት፤   
“ይሄኛውም ልጄ የአንቺ ባል ነኝ ይላል፡፡
ይሄኛውም ልጄ የአንቺ ባል ነኝ ይላል…የትኛው ነው ትክክለኛ ባልሽ?”
ዝንጀሮይቱ ራሷን ደልደል አድርጋ ተቀመጠችና፤
“ጌታዬ፤ ከእነዚህ ልጆችዎ አንዱ እንኳ ዕውነተኛ ባሌ ቢሆን ከእኔው ጋር እቤቴ ተቀምጦ ያገኙት አልነበር? አርፎ የተቀመጠ ልጅ ኖሮዎት ያቃል?” ስትል መልሷን በጥያቄ አጠቃለለች፡፡
አባት፤
“እግዜር ይስጥሽ ያቺንም ያቺንም እየነካኩ ባል ነኝ ማለት አቋም የለሽነት ነው፡፡ አሳዳጊ የበደለው ልጅ ማለት የእኔ ልጆች ናቸው!! አንቺ ሂጂ፡፡ እኔም ልጆቼን ልሰብስብ” አሉ ይባላል፡፡
*   *   *
በማናቸውም የህይወት ዘርፍ ውስጥ ምግባረ - ብልሹ መሆን የአስተዳደግን ጉድለት ያሳያል፡፡ የአስተዳደግ ጉድለት ግብረገብነትን፣ ዕምነትን፣ ትምህርትን የሚመለከት በመሆኑ በአብዛኛው ከባህል ጋር ቁርኝት ያለው ነው፡፡ ምግባረ - ሠናይ መሆንም እንደዚሁ እንደ ባህሉ፣ እንደአስተሳሰቡ፣ እንደ አኗኗሩ የሚዳኝ ነው፡፡ በየሥራ መስኩ የምናየው የሰዎች አኳኋንም እንደየአስተዳደሩ የሚመዘን ነው የምንለው ለዚህ ነው፡፡
የሥራ - ዲሲፕሊን፣ የሥራ ፍቅር፣ ለሥራውም ለህሊናም ታማኝ መሆን፣ የኃላፊነት ስሜት ወዘተ ከመልካም አስተዳደር ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡ በሀገራችን የመልካም አስተዳደር ጉድለት ከሥራ ባህሉና ከፖለቲካው ተፅዕኖ ጋር በተሠናሠለ መልኩ እግለሰቦች አስተዳደግ ጉድለት ድረስ የተለጠጠ እየሆነ መጥቷል፡፡ ከተቋማዊ አቅም ይልቅ ግለሰባዊ አቅም አይሎ ይታያል፡፡ አሳዳጊ - የበደለው ሆኗል እንደማለት ነው፡፡ በዚሁ ላይ የሙስና እጀታ ሲሠራለት በደምባራ  በቅሎ ቃጭል ተጨምሮ ሆኗል፡፡ ይህንኑ በውል ለመነጋገርም ሌላ ሙስና ውስጥ መዘፈቅ የሚያስፈልግበት ጊዜ ሆኗል፡፡
ፓቮ ፒልካነን የተባለ ሐያሲ፤
“ከሰው ልጅ በርካታ ችግሮች ውስጥ ጉልህ ቦታ የሚይዘው ስለችግሮቹ ለማውራት አለመቻሉ ነው፡፡ ለዚህ ትልቅ አስተዋፅዖ ይኖረው የነበረው ደግመ ጥበብ ነው” ይለናል፡፡ ጥበብ የኮሙኒኬሽን ቱባ መሣሪያ ነው እንደማለት ነው፡፡ የአንድ ህብረተሰብ መንፈሣዊ ዕሴት መገለጫ ጥበብ ነው፡፡ ይህ ጥበብ ዕፁብ፣ ክቡርና ንፁህ ዋጋ ያለው ሲሆን ዕውነተኛ ማንነትን ቁልጭ ንጥር አድርጐ ያሳያል፡፡ ያልታየውን ይገልጣል፡፡ ዕሙናዊውን ህይወት ያፀኸያል፡፡ የህብረተሰቡ ማህበራዊ ስነልቡና ሲነክትም ቀና ብሎ ጠቋሚው ጥበብ ነው፡፡ ለህብረተሰብ በጐ በሆነ ገፁ ያፀኸያል፡፡ ይህን ንፁህ ጥበብ ሰውንና ህይወቱን ከመግለፅ አልፎ የፖለቲካ ቅብ ለመቀባት ከተሞከረ ግን ይበረዛል፡፡ ኦርጅናሌነቱን ያጣል፡፡ እንደተቀባው ቅብ ያለ ቀለም እየያዘ የእስስት ጠጨባይ ያመጣል፡፡ ህይወት እንድትፈስ በተፈቀደላት ተፈጥሮአዊ ሂደት መሄዷ ቀርቶ በግድ በፒንሣ ተጠምዝዛ የመሄድ ያህል ጫና ይበዛባታል፡፡ የሀገራችን የጥበብና የጥበብ ባለሙያ ሁኔታ በዚህ መልክ ሊጤን ይገባል፡፡ የጥበብ ባለሙያ መናቅ ጥበብን መግደል ነው፡፡ እርግይ እንደጠባይ ዘርፉ ከጥንተ - ፍጥረቱ ፖለቲካዊ ቃና ያለውም ጥበብ አለ፡፡ ይሄ ለፖለቲካዊ ህይወት መገለጫ ብቻ ነውና በፖለቲካ ሥነ-ውበትና ቃለ-ኃይል ላይ የሚንተራስ ይሆናል፡፡ ከመግባቢያነት አልፎም መቀስቀሻ ዓላማን ማራመጃ ሊሆን ይችላል፡፡ የዚህ ጥበብ ችግር ፖለቲካው ትኩሳት ካበቃ ሽባ ሆኖ የመቅረት ዕጣ ፈንታው ነው፡፡ ስለዚህ ቀድመን የገለፅነው ዓይነቱ ንፁህና ኦርጅናሌ ጥበብ የአብዛኛው የጥበብ ማህበረሰብ መናኸሪያና ዘላቂነት ያለው ነው፡፡ የህብረተሰብን ንቁ ተሳትፎ፣ መንፈሳዊ ልሳን የሚከፍትለትም ንፁህ ጥበብ ነው፡፡ ይህን ዓይነቱን ጥበብ መንከባከብና ማሳደግ ያስፈልጋል፡፡ ጥበብን ማሳደግ የፈጠራ ኃይልን፣ አዲስ የመፍጠርን ባህል ማበልፀግ ነው፡፡ ጥበብ እንደፖለቲካ መፈክር ለጊዜያዊ ግብ ብቻ የምናውለው መሪ ቃል አይደለም፡፡ የፖለቲካ ዲኮሬሽንም፣ ቀለምም አይደለም፡፡ እንደዲፕሎማሲ ነገረ - ስራ የሆድን በሆድ ይዞ አፍአዊ ማማለያ አይደለም፡፡ የጥበብ ሰውን መውደድ፣ ማበረታታትና ማሳደግ መሰረቱ መሆን ያለበት ይሄና ይሄ ዕሳቤ ነው፡፡ ባለፈው ስርዓት “ ኪነት ለመደቧ” ስንል ከርመን አሁን ደግሞ “ ኪነት ለወገኗ” እንዳንል መጠንቀቅ ይገባናል
“የጥበብ ሰው ህሊናውን የተነጠቀ ዕለት አለቀለት” ይላሉ የጥበብ ሊቃውንት! አንድን የጥበብ ሰው ከህሊናው ውጪ እንዲጓዝ ካደረግነው ጥበቡን በንቀት ዐይን ማየታችን ነው፡፡ ፈጠራን ማቀጨጫችን ነው፡፡ በሞቀበት ዝፈን ማለታችን ነው፡፡ ጥበብን ስንንቅ የመወያያ ገመዳችንን መበጠሳችን ነው፡፡ በፖለቲካውም ሆነ በጥበቡ መስክ መናናቅ ካለ ተያይዞ እረብ ማለት አይቀሬ ነው፡፡ “በቆሎ ጤፍን አይታ አሁን እዚችም ሆድ ውስጥ እህል አለ?” ብትል፣ ጤፍ “ሁለታችንም ስንፈጭ ዱቄት ነን” አለች አሉ የሚለው ይሄንን ሁሉ ያካትታል፡፡

         በ1.8 ቢሊዮን ዶላር ወጪ በኦሞ ወንዝ ላይ እየተከናወነ የሚገኘው የግልገል ጊቤ 3 የውሃ ሃይል ማመንጫ
ግድብ ግንባታ 88 በመቶ መጠናቀቁንና በመጪው ሰኔ ወር በከፊል ሃይል ማመንጨት እንደሚጀምር ሮይተርስ ዘገበ፡፡የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ወ/ሮ አዜብ አስናቀ ከትናንት በስቲያ ለሮይተርስ እንደገለጹት፣ ግድቡ ከሚኖሩት አስር ሃይል ማመንጫ ክፍሎች ሁለቱ በመጪው ሰኔ ወር ሃይል ማመንጨት የሚጀምሩ ሲሆን፣ በቀጣይም በየወሩ አንዳንድ ማመንጫዎች ወደ ስራ እንደሚገቡ ይጠበቃል፡፡ከአንድ አመት በኋላ ግንባታው ሙሉ ለሙሉ ይጠናቀቃል ተብሎ የሚጠበቀው የግድብ ፕሮጀክቱ 1ሺህ 870 ሜጋ ዋት ሃይል የማመንጨት አቅም እንደሚኖረው የገለጹት ወ/ሮ አዜብ፣ ግንባታው ተጠናቅቆ በሙሉ ሃይሉ ማመንጨት ሲጀምር አገሪቱ በአሁኑ ወቅት በማምረት ላይ የምትገኘውን የኤሌክትሪክ ሃይል በእጥፍ ያህል ያሳድገዋል ተብሎ እንደሚጠበቅም ገልጸዋል፡፡ግንባታው እ.ኤ.አ በ2008 የተጀመረው የግልገል ጊቤ 3 የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ ግድብ ፕሮጀክት፣ የአካባቢ ጥበቃ ቡድኖች ግድቡ በአካባቢ ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል በሚል ያካሄዱትን አለማቀፍ የተቃውሞ ዘመቻ ተከትሎ፣ የአፍሪካ ልማት ባንክ እና የአውሮፓ የኢንቨስትመንት ባንክ ለፕሮጀክቱ የሚያስፈልገውን የገንዘብ ብድር በመከልከላቸው ግንባታው እንደተጓተተ ይታወቃል፡፡

   የሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በተከሰተው የኢኮኖሚ ቀውስ ምክንያት ሚኒስትሮቻቸው የአዲስ ዓመት እረፍት እንደማይወስዱ ሰሞኑን አስታወቁ፡፡ በሩሲያ ትልቁ በዓል እንደሆነ በሚነገርለት የፈረንጆች አዲስ ዓመት፤ በመላ አገሪቱ የሚገኙ የሩሲያ ኩባንያ ሰራተኞች ለበዓሉ የ12 ቀናት እረፍት ይወስዳሉ፤ ከጃንዋሪ 1 እስከ 12፡፡
ፑቲን ባለፈው ሐሙስ በቴሌቪዥን በተሰራጨ የመንግስት ኃላፊዎች ስብሰባ ላይ፣ በዚህ ዓመት የካቢኔ ሚኒስትሮቻቸው እረፍት መውሰድ እንደማይገባቸው ተናግረዋል፡፡ “ቢያንስ ለዚህ ዓመት መንግስት ይሄን ረዥም የበዓል ዕረፍት መስጠት አይችልም - መቼም የምለው ይገባችኋል” ብለዋል - ፕሬዚዳንቱ፡፡
የአገሪቱ ጠ/ሚኒስትር ዲሚትሪ ሜድቬዴቭ በበኩላቸው፤ በበዓሉ ወቅትም ጭምር (ከዓመቱ የመጀመሪያ ቀናት አንስቶ) የኢኮኖሚውን ሁኔታ እንዲከታተሉላቸው እንደሚፈልጉ ለሚኒስትሮቹ ነግረዋቸዋል፡፡
በነዳጅ ዋጋ መቀነስና በምዕራብ አገራት ማዕቀብ ክፉኛ የተጎዳው የሩሲያ ኢኮኖሚ፤ ከስድስት ዓመታት ወዲህ ለመጀመሪ ጊዜ በቀጣዩ ዓመት “ድቀት” ውስጥ የሚገባ ሲሆን፣ የአገሪቱ ገንዘብ ሩብልም በአሁኑ ሰዓት ከዋጋው ግማሽ በታች ወርዷል፡፡ ከያዝነው ወር መጀመሪያ አንስቶ አንድ ዶላር በ80 ሩብል ሲመነዘር የቆየ ሲሆን፣ ባለፈው ሐሙስ የ2 በመቶ መጠነኛ መሻሻል አሳይቶ አንድ ዶላር በ52 ሩብል መመንዘሩ ታውቋል፡፡
የሩሲያ ማዕከላዊ ባንክ የአገሪቱ መጠባበቂያ ገንዘብ ከ2009 ዓ.ም ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ከ400 ቢሊዮን ዶላር በታች መውረዱን አስታውቋል፡፡ ዋጋው እጅግ ያሽቆለቆለውን የአገሪቱን መገበያያ ሩብል ማረጋጋት፣ የሩሲያ የገንዘብ ኃላፊዎች ተቀዳሚ ስራ ይሆናል ተብሏል፡፡ ከዩክሬን ጋር በተያያዘ በአገሪቱ ላይ የተጣለው ማዕቀብ፣ በርካታ የሩሲያ ኩባንያዎችን ከምዕራብ አገራት የፋይናንስ ገበያ እንዳስወጣቸው ተዘግቧል፡፡

የትንፋሽ ማጠር ገጥሟቸው ባለፈው ማክሰኞ ሂዩስተን ሜቶዲስት ሆስፒታል የገቡት የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት  ጆርጅ  ኤች ደብሊው ቡሽ፤ ከትላንት በስቲያ የተከበረውን የፈረንጆች የገና በዓል በሆስፒታል አሳለፉ፡፡
የፕሬዚዳንቱ ቃል አቀባይ ጂም ማክግራዝ፤ ቡሽ በጥሩ ጤንነት ላይ እንደሚገኙና የገና በዓልን በሆስፒታል ያሳለፉት በሽታው ከፍቶባቸው ሳይሆን ለጥንቃቄ ሲባል እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ የዛሬ ሁለት ዓመት በተመሳሳይ ጊዜ ብሮንካይትና በሃይለኛ ሳል ይዟቸው ሆስፒታል ከገቡ በኋላ የገና በዓልን ጨምሮ ለሁለት ወራት እዚያው መቆየታቸውን ያስታወሱት ቃል አቀባዩ፤ የአሁኑ ግን ከቀድሞው በጣም ይለያል ብለዋል - የፕሬዚዳንቱን ጤናማነት ሲገልፁ፡፡
የፕሬዚዳንቱ ሆስፒታል መግባት ላሳሰባቸው በርካታ ወዳጆችና አድናቂዎቻቸው የቡሽ ዋና ኃላፊ በሰጡት መግለጫ፤ “የቡሽ ቤተሰብ፤ ለጭንቀታችሁ፣ ለፍቅራችሁና፣ ለፀሎታችሁ በእጅጉ ያመሰግናል፡፡ ይሄ የዛሬ ሁለት ዓመት እንደሆነው ዓይነት አይደለም፡፡ የትንፋሽ ማጠር ነው፡፡ በጥቂት ቀናት ውስጥ ወደ ቤታቸው ይመለሳሉ” ብለዋል፡፡ ቡሽ ሆስፒታል መግባታቸውን የሰሙት ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ እና ባለቤታቸውም ለቀድሞው ፕሬዚዳንትና ለመላው የቡሽ ቤተሰብ የመልካም ጤንነት ምኞታቸውን ልከዋል፡፡
ሪፐብሊካኑ የ90 ዓመቱ ቡሽ፤ 41ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት በመሆን አገራቸውን ያገለገሉ ሲሆን የ43ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆርጅ ደብሊው ቡሽም አባት ናቸው፡፡ የዊልቸር እስረኛ ባደረጋቸው ከፍተኛ የነርቭ ህመም ሲሰቃዩ የቆዩት ቡሽ፤ በቅርቡ ግን ነቃ ነቃ ማለት ጀምረው ነበር ተብሏል፡፡ ባለፈው ሰኔ ለ90ኛ ዓመት የልደት በዓላቸው ከሄሊኮፕተር ላይ በፓራሹት የዘለሉ ሲሆን የዛሬ ወር “41፡ A Portrait of My Father” የተሰኘ አዲስ መፅሃፋቸው የምረቃ ስነስርዓት ላይ ከልጃቸው ጋር ተገኝተው ነበር፡፡
ፕሬዚዳንት ሆነው የተመረጡበትን 25ኛ ዓመት በዓል በቅርቡ ያከበሩት ጆርጅ ቡሽ፤ በፕሬዚዳንት ሮናልድ ሬገን ዘመን ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው አገልግለዋል፡፡
በሁለተኛው የዓለም ጦርነት በባህር ኃይል አብራሪነት የተሳተፉ ሲሆን ወደ ፖለቲካው ዓለም ከመግባታቸው በፊት በቴክሳስ የነዳጅ ኢንዱስትሪ ውስጥ እንደሰሩ የህይወት ታሪካቸው ያወሳል፡፡

መኪና ሲያሽከረክሩ የተያዙ ሁለት የሳኡዲ ሴቶች ለአንድ ወር ገደማ ከታሰሩ በኋላ ባለፈው ሳምንት ጉዳያቸው ሽብርተኝነትን ለሚመለከት ልዩ ፍ/ቤት እንደተላለፈ ተገለፀ፡፡
የ25 ዓመቷ ሎዩጄይን አል ሃትሎል እና የ33 ዓመቷ ማይላ ይሳ አል - አሙዲ ጉዳይ ወደ ልዩ ፍ/ቤት የተላለፈው በማህበራዊ ሚዲያ ላይ በሰጡት አስተያየት ነው ብለዋል - የመብት ተሟጋቾች፡፡ ሳኡዲ በዓለም ላይ ሴቶች መኪና እንዳያሽከረክሩ የምትከለክል ብቸኛ አገር ናት፡፡
ሴቶች መኪና እንዳያሽከረክሩ በፅሁፍ የተቀመጠ ህግ ባይኖርም የመንጃ ፈቃድ የሚሰጠው ግን ለወንዶች ብቻ ነው፡፡ ሴቶች በአደባባይ ሲያሽከረክሩ ከተገኙም በፖሊስ ተይዘው ከመታሰርም ባሻገር ይቀጣሉ፡፡
የሳኡዲ ሴቶች መኪና እንዳያሽከረክሩ የተጣለባቸው እገዳ እንዲነሳላቸው ማህበራዊ ሚዲያን ጨምሮ የተለያዩ ተከታታይ እንቅስቃሴዎች ሲያካሂዱ ቆይተዋል፡፡
አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ የዜና ወኪል እንደዘገበው፤ ሚስ ሃትሎል የተያዘችው ከጐረቤት አገር፣ ዩናይትድ አረብ ኢምሬትስ እያሽከረከረች ወደ ሳኡዲ ለመግባት ስትሞክር ነው፡፡
ነዋሪነቷን በዩናይትድ አረብ ኢምሬትስ ያደረገችው የሳኡዲ ጋዜጠኛ ሚስ አላሙዲም የተያዘችው ሚስ ሃትሎልን ለመርዳት ድንበር ላይ ስትደርስ ነው ብሏል - የዜና ወኪሉ፡፡
ሁለቱም ሴቶች በትዊተር እጅግ በርካታ ተከታይ ያሏቸው ሲሆን ሚስት ሃትሎል ወደ አገሪቱ ለመግባት አንድ ቀን ሙሉ ያችውን ውጣ ውረድ በትዊተር ገጿ ላይ እንዳሰፈረች ተዘግቧል፡፡ ባለፈው ሐሙስ በአገሪቱ ምስራቃዊ ክፍል የሚገኘው አል - አህሳ ፍ/ቤት፤ የሁለቱ ሴቶች ጉዳይ በሪያድ የሽብርተኝነት ክሶችን ለመከታተል በተቋቋመው ልዩ ፍ/ቤት እንዲዳኙ በይኗል፡፡ የሴቶቹ ጠበቆች ግን ይግባኝ ለመጠየቅ ማሰባቸውን የመብት ተሟጋቾች ለአዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ጠቁመዋል፡፡

     በደራሲ ሐማቱማ “The case of the Socialist witchdoctor” በሚል ርዕስ ተፅፎ በህይወት ታደሰ “የሶሻሊስቱ ጠንቋይ ጉዳይ” በሚል ወደ አማርኛ የተመለሰው መፅሃፍ ለንባብ በቅቷል፡፡ የተለያዩ በርካታ ታሪኮች ስብስብ የሆነው ይሄው መፅሃፍ፤ በአንድ ሶሻሊስት ጠንቋይ ላይ ያተኮረ ታሪክ የያዘ ሲሆን ሌሎችም አስገራሚ ፖለቲካዊ ታሪኮችን አካትቷል፡፡ መፅሃፉ በ307 ገፆች የተቀነበበ ሲሆን በ50 ብር ከ65 ሳንቲም ለገበያ ቀርቧል፡፡

 “የዘንድሮ ትዳሮች” በሚል ርዕስ በመቅደስ በቀለ (ማክዳ) ተፅፎ በእርከን ቢዝነስ ዲቨሎፕመንት አሳታሚ የታተመው መፅሐፍ በገበያ ላይ ውሏል፡፡ በቅርቡም ይመረቃል ተብሏል፡፡
በመፅሀፉ የዘንድሮ ትዳሮችን ጨምሮ ሌሎች እውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሰረቱ ከ15 በላይ አጫጭር ልቦለዶች እንደተካተቱበትና በ200 ገፆች ተሰናድቶ በ60 ብር ለገበያ እንደቀረበ ለማወቅ ተችሏል፡፡
የመፅሃፉ ደራሲ መቅደስ በቀለ (ማክዳ) የበርካታ ፊልሞች ደራሲና ዳይሬክተር ስትሆን “የዘንድሮ ትዳሮችና ሌሎች” ሁለተኛ መፅሃፏ መሆኑ ታውቋል፡፡ ደራሲዋ ከዚህ ቀደም “የፍቅር መስዋዕት” የተሰኘ መፅሃፍ አሳትማለች፡፡

የገጣሚ የሺመቤት ካሳ “አመሻሽ” የግጥም መድበል ሰሞኑን በ25 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡
የግጥም መድበሉ 62 አጫጭርና ረጃጅም ግጥሞች የተካተቱበት ሲሆን ገጣሚዋ ማስታወሻነቱን ለቀደምት ደራሲያንና ለነገው ደራሲያን ማድረጓን አስታውቃለች፡፡

የደራሲ ስንዱ አካልነህ “ኤል-ማጐት” የተሰኘ የረዥም ልቦለድ መፅሃፍ እየተነበበ ነው፡፡
በጐንደር ማተሚያ ድርጅት ታታሞ ለገበያ የቀረበው መፅሃፉ መቼቱን በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ያደረገ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡ መፅሃፉ በ75 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡