Administrator

Administrator

 የታሪክ አፃፃፉ ምን ይመስላል? ደራሲው ታሪኩ የተፈፀመበትን ዘመን የተረዳው እንዴት ነው? መረጃዎቹን ከፖለቲካ፣ ከኢኮኖሚ፣ ከባህል… አንፃር እንዴት ነው የመዘነው? የሚሉ ጥያቄዎችን በማንሳት ሚዛናዊነት መመዘን ይቻላል፡፡ ማነው መዛኙ ለሚለው ፀሐፊያንም አንባቢያንም ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ታሪከ ፀሐፊ ፖለቲከኛ ሊሆን ይችላል። አንድን ታሪክ ሲጽፍ ምክንያታዊ መሆን ከቻለ ሚዛናዊ ታሪክ ፀሐፊ ነው ሊባል ይችላ

     ላለፉት 10 ዓመታት በየሁለት ሳምንቱ የመፃህፍት ላይ ውይይት ሲያካሂድ የቆየው ሚዩዚክ ሜይዴይ ኢትዮጵያ፤ በገጠመው ውስጣዊ ችግር ምክንያት የተለመደውን መድረክ ማዘጋጀት ካቋረጠ ስድስት ወራት ሆኖታል፡፡ ይህንን ክፍተት ለመሙላት የጀርመን ባህል ማዕከል፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መፃሕፍት ኤጀንሲ እና እናት ማስታወቂያ ድርጅት በጋራ በመሆን በወር አንዴ የመፃሕፍት ላይ ውይይት እንደሚያካሂዱ የተገለፀ ሲሆን የመጀመሪያው ዝግጅትም ባለፈው እሁድ በወመዘክር አዳራሽ ተከናውኗል፡፡
ለውይይት የተመረጠው “የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ መንግሥት” በሚል ርዕስ በአምባሳደር ዘውዴ ረታ ተጽፎ ባለፉት ሁለት ዓመታት ሦስት ጊዜ ለመታተም የበቃው መጽሐፍ ሲሆን፤ ለውይይት የመነሻ ሀሳብ ያቀረቡት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት አቶ አበባው አያሌው ነበሩ፡፡ የመጽሐፉ ደራሲ አምባሳደር ዘውዴ ረታ ከአገር ውጭ በመሆናቸው በዕለቱ ሊገኙ አልቻሉም፡፡
“የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ መንግሥት ዘመን በአገሪቱ በርካታ ታሪኮች የተከናወኑበት በመሆኑ ልዩ ወቅት ነበር፡፡ ዘመናዊ ለውጥ በአፄ ቴዎድሮስ ዘመን ተጀመረ የሚሉ አሉ፤ በተግባር የታየው ግን በአፄ ኃይለሥለሴ ጊዜ ነው፡፡ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ አወዛጋቢ ንጉሥ ነበሩ፡፡ የሚያደንቋቸው አሉ፡፡ በኋላ በአገሪቱ ለታየው ምስቅልቅል ትልቅ አስተዋጽኦ አድርገዋል ብለው የሚከሷቸውም አሉ፡፡ በዚህ ዙሪያ ብዙ የተፃፈ ቢሆንም ወደፊትም ብዙ የሚፃፍበት ይመስላል፡፡ አብዮተኞቹ ታሪክ ፀሐፊዎች አፄ ኃይለሥላሴን ሲያጠለሹ፤ በንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት ውስጥ ያገለገሉ ታሪክ ፀሐፊዎች ያሞግሷቸዋል፡፡ ሦስተኛው ዓይነት ታሪክ ፀሐፊዎች የውጭ አገር ሰዎች ሲሆኑ የተደረገውን ሐቅ ከማስቀመጥ ውጭ ነገሩ ጥሩ ነው፣ መጥፎ ነው ብለው ትንታኔ ውስጥ አይገቡም፡፡ ከዚህ አንፃር እነዚህ ሚዛናዊ ሆነው ይታያሉ።”
በዚህ መልኩ ገለፃ የጀመሩት አቶ አበባው አያሌው፤ የአምባሳደር ዘውዴ ረታን መጽሐፍ የቃኙት በሰባት መመዘኛዎች እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ ደራሲው ለጉዳዩ ያላቸው ቅርበት ምን ይመስላል? የመረጃ ምንጫቸው ምን ነበር? መረጃዎቹስ በመጽሐፉ ውስጥ በምን ያህል ተንፀባርቀዋል? ሚዛናዊነቱ ምን ይመስላል? በመጽሐፉ የተገለፀው ዘመን ታሪክ ምን ያህል ሙሉ ሆኖ ቀርቧል? የታሪክ ሃተታውና የቋንቋ አጠቃቀሙ ምን ይመስላል? መጽሐፉ ምን አዲስ ነገር አሳወቀን?
እነዚህን ጥያቄዎች አንስተው ምላሽ በመስጠት ማብራራት የቀጠሉት የዩኒቨርሲቲው ምሁር፤ የአገርም ሆነ የግለሰቦች ታሪክ በአንድ ሰው ብቻ ተጽፎ እንደማያበቃ ጠቁመው በአፄ ኃይለሥላሴ ዙሪያ 56 ያህል መፃሕፍት መታተማቸውን ገልፀዋል፡፡
ደራሲው ለፃፉበት ርዕሰ ጉዳይ ቅርበት ነበራቸው፡፡ የማስታወቂያ ሚኒስቴር ሰራተኛ፣ የቤተ መንግሥት ጋዜጠኛና በኋላም የማስታወቂያ ሚኒስቴር ረዳት ሚኒስትር ሆነው ያገለገሉ  ከመሆኑም ባሻገር በአምባሳደርነትም ተሹመው መስራታቸው የቃል፣ የሰነድና የፎቶግራፍ መረጃዎችን ለማግኘት ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳደረገላቸው አቶ አበባው ገልፀዋል፡፡
አምባሳደር ዘውዴ ረታ በአገር ውስጥና በውጭም መረጃዎችን ማግኘታቸው ብቻ ሳይሆን ያገኙትን በጥንቃቄ ማስቀመጥ በመቻላቸው “የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ መንግሥት” በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ በሚገባ ተጠቅመበውበታል፡፡ በአገር ውስጥ ከጽሕፈት ሚኒስቴር ሰነዶችን በቀጥታ አግኝተዋል። በዘመኑ ታላላቅ ባለስልጣናት ከነበሩት መኮንን ሀብተወልድ፣ ወልደጊዮርጊስ ወልደዮሐንስ፣ ይልማ ደሬሳ ከመሳሰሉት ቤተሰቦችም ብዙ መረጃ ሳያኙ አልቀሩም ተብሏል፡፡
“የቃል መረጃም በብዛት ተጠቅመዋል፡፡ ይህ በጥንቃቄ መታየት ያለበት ነው፡፡ ምስክርነቱን የሰጠው ሰው ማነው? የፖለቲካ አመለካከቱ፣ ዕውቀቱ … መጠየቅና መጣራት አለበት። የቃል ምስክርነት እውነታነቱ ሌላ ማመሳከሪያ ካልተገኘለት ለዘመን ፍርድ ክፍት ተደርጎ የሚተው ነው” ያሉት አቶ አበባው፤ በተመሳሳይ በዚህ መልኩ ጥያቄ አስነስቶ እስካሁንም እያነጋገረ  ነው በማለት “ሕይወቴና የኢትዮጵያ እርምጃ” የተሰኘውን መጽሐፍ በምሳሌነት ጠቅሰዋል፡፡
የቃልና የሰነድ መረጃዎች በስፋት ጥቅም ላይ ውለውበታል የተባለው “የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ መንግሥት” መጽሐፍ፤ በማጣቀሻነት የተጠቀማቸው መፃሕፍት ቁጥር ትንሽ እንደሆኑና የመረጃ አገላለጽ ችግር እንደሚታይበት ተጠቁሟል፡፡ የመረጃ ምንጩ ሰውም ይሁን ሰነድ የት እንደሚገኝ መገለጽ አለበት። በመጽሐፉ ላይ አባሪ ማኖር ገጽ ያበዛል ተብሎ ከተፈራ መረጃዎች ከየትኛው ሰነድ እንደተወሰዱ በግርጌ ማስታወሻ ቢገለጽ ጥሩ ነበር፡፡ ምክንያቱም ደራሲው ያገኘውን ምንጭ አንባቢያንም እንዲደርሱበት ያግዛል ተብሏል፡፡ መጽሐፉ በርካታ ፎቶግራፎችን ቢይዝም “የኤርትራ ጉዳይ” ከሚለው መጽሐፋቸው ጋር ሲነፃፀር ይኸኛው መጽሐፍ የያዛቸው ፎቶግራፎች ቁጥራቸው ማነሱም ተገልጿል፡፡
“የታሪክ ጠላት ፖለቲካ ነው፡፡ ፖለቲካ ታሪክን ወደራሱ ፍላጎት ይዞት ይሄዳል፡፡ ከዚህ አንፃር አምባሳደር ዘውዴ ረታ በመጽሐፋቸው ምን ያህል ሚዛናዊ መሆን ችለዋል?” ያሉት ምሁሩ፤ ደራሲው በአንዳንድ ቦታ ኃይለሥላሴን ከብዙ ነገሮች ነፃ ሲያደርጓቸው ይታያል፡፡ የታሪክ ፀሐፊ አይበይንም። ፍርዱን ለአንባቢያን ነው መተው ያለበት፡፡ እንዲህም ሆኖ መጽሐፉ ባነሳው ርዕሰ ጉዳይ ዙሪያ በአገር ውስጥ የነበረውን ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፍ ሁኔታና ተጽዕኖንም እያመሳከረ ታሪኩን ሚዛናዊ ለማድረግ ሞክሯል ተብሏል፡፡
ከ1923-1948 ዓ.ም ያለውን ዘመን ማዕከል አድርጎ የተዘጋጀው የአምባሳደር ዘውዴ ረታ መጽሐፍ፤ የ25 ዓመታቱን ታሪክ በምን ያህል መጠን ሙሉ አድርጎ አቀረበ? ለሚለውም ጥያቄ የአምስቱ ዓመት የአርበኞች ተጋድሎ ታሪክ አለመፃፉ (ደራሲውም ይህንን በመጽሐፉ መግቢያ አንስተውታል)፤ አፄ ኃይሥላሴ በስደት በእንግሊዝ በነበሩበት ጊዜ አኗኗራቸው ምን ይመስል እንደነበር አለመገለፁ፤ ከድል በኋላ አርበኞች፣ ባንዳዎች፣ ስደተኞች፣ ምሁራን በውስጣቸው የነበረው ትግል ምን እንደነበር አለመብራራቱ፤ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት አውሮፓውያን ለስደተኛ መንግሥታት ዕውቅና ሲሰጡ ኢትዮጵያ ዕድሉ ስለመነፈጓ በስፋት አለመፃፉ … የመሳሰሉት የመጽሐፉን ሙሉእነት ጥያቄ ውስጥ ያስገባዋል ብለዋል - አቶ አበባው፡፡
መጽሐፉ በታሪክ አተራረክና በቋንቋ አጠቃቀሙ የተሳካለት መሆኑን የመሰከሩት አቶ አበባው  መጽሐፉ ምን አዲስ ነገር አሳየን? ለሚለውም “ትኩረት ያልተሰጣቸው ጥቃቅን ነገሮችን አሳይቶናል፡፡ ማን ምን ብሎ ጠይቆ፤ ማን ምን ብሎ መለሰ የሚለውን ሁሉ እናይበታለን። የ1923ቱ ሕገ መንግሥት ሊፀድቅ በሂደት ላይ እያለ በዘመኑ ምሁራንና ባለስልጣናት መሐል የተደረገውን ሰፊ ክርክር አቅርቦልናል (የሞኝ ዘመን መጽሐፍ ሆኖ ነው እንጂ በህገ መንግሥቱ ዙሪያ የቀረበው ርዕስ ብቻ አንድ መጽሐፍ ይወጣው ነበር)፡፡ በሊግ ኦፍ ኔሽን የተደረገውን ክርክር በተመለከተ በአገር ውስጥና በውጭ አገራት ሰዎች ዘንድ ያለው አመለካከት ምን ይመስል እንደነበር በስፋት ገልጿል፡፡ ስለ መኮንን ሀብተወልድ፣ ወልደጊዮርጊስ ወልደዮሐንስ፣ ይልማ ደሬሳ ካሁን ቀደም የማናውቃቸውን አዳዲስ መረጃዎች ሰጥቶናል፡፡ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዲፕሎማሲያዊ ክህሎት ምን ያህል ውጤታማ (በባሩድ ሳይታጠኑ በንግግርና ውይይት በማሳመን) መሆናቸውን አይተንበታል፡፡ መጨረሻ ላይም የንጉሠ ነገሥቱ ምኞት፣ የምሁራኑ ፍላጎትና የባለሥልጣናቱ መሻት መለያየቱንና ሁሉም ብቻውን መቆሙን አመላክቶናል፡፡” ብለዋል፡፡
አቶ አበባው መጽሐፉን አስቃኝተው ከጨረሱ በኋላ ከተሰብሳቢዎች የተለያዩ አስተያየትና ጥያቄዎች ቀርበዋል፡፡ አምባሳደር ዘውዴ ረታ አንዳንዴ በሚጽፉት ስሜታዊ ገለፃ ፀሐፊ ትዕዛዛትን ይመስላሉ፡፡ በዚህ ላይ የምትለን ነገር አለ? ደራሲው የታሪክ ሰው አይደሉም፤ አምባሳደር (ዲፕሎማት) ናቸው የሚሉ ክርክሮች አሉ፡፡ ማረፊያው የቱ ነው? ታሪክን ፖለቲካ ስለሚጎትተው ታሪክ ፀሐፊ ሚዛናዊ እንዲሆን እንዴት ይጠበቃል? ታሪክ ፀሐፊ ይመዘናል ከተባለ፤ መዛኙ ማነው? ታሪክ ፀሐፊው ላይ የቀረበው አድናቆትና ነቀፌታን ለመዳኘት ዲስፕሊኑ ከየት ነው የሚገኘው?
ለቀረበላቸው ጥያቄዎች መልስ የሰጡት አቶ አበባው አያሌው፤ “የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ መንግሥት” የተሰኘው መጽሐፍ የንጉሡ ታሪክ ላይ ትኩረት ቢያደርግም አምባሳደር ዘውዴ ረታ ጸሐፊ ትዕዛዝ አይደሉም ብለዋል፡፡ በተፈጥሮም የተገኘ ይሁን በልምድ አተራረክና አቀራረቡ ጥሩ የሆነ መጽሐፍ አቅርበውልናል፡፡ ታሪክን ማንም ይጽፈዋል። ፀሐፊዎቹም ህዝባዊና ሙያዊ ተብለው በሁለት ይከፈላሉ፡፡ ተነባቢነት ያላቸው አብዛኞቹ የታሪክ መፃሕፍት የተፃፉት በጋዜጠኞች ነው፡፡ አምባሳደር ዘውዴ ረታ በማስታወቂያ ሚኒስቴር ስለሰሩ የታሪክ መጽሐፉ ለመፃፍ ችለዋል፡፡
“በታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ሚዛናዊነት መኖሩን የምናረጋግጠው ደራሲው ምን መረጃ አገኘ? መረጃውን እንዴት አቀረበው? አተረጓጎሙስ እንዴት ነው? የሚሉትን ጥያቄዎችን በማንሳት፤ ጥያቄዎቹ የሚተነተኑበትን ሂደት ተከትሎ በመመርመር ነው። የታሪክ አፃፃፉ ምን ይመስላል? ደራሲው ታሪኩ የተፈፀመበትን ዘመን የተረዳው እንዴት ነው? መረጃዎቹን ከፖለቲካ፣ ከኢኮኖሚ፣ ከባህል… አንፃር እንዴት ነው የመዘነው? የሚሉ ጥያቄዎችን በማንሳት ሚዛናዊነት መመዘን ይቻላል፡፡ ማነው መዛኙ ለሚለው ፀሐፊያንም አንባቢያንም ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ታሪከ ፀሐፊ ፖለቲከኛ ሊሆን ይችላል። አንድን ታሪክ ሲጽፍ ምክንያታዊ መሆን ከቻለ ሚዛናዊ ታሪክ ፀሐፊ ነው ሊባል ይችላል” በማለት አቶ አበባው ማብራሪያቸውን ቋጭተዋል፡፡      

ከወር በፊት በጋለሪያ ቶሞካ በተከፈተው “ውስጣዊ ግለትና እንፋሎት” የተሰኘ የስዕል ትርዒት ላይ ነገ ከረፋዱ 4፡00 ሰዓት ጀምሮ በቶሞካ ውይይት እንደሚካሄድ ዳይሬክተሩ ጋዜጠኛ ነብዩ ግርማ ገልጿል፡፡ የወጣት አሸናፊ ማስቲካ ስራዎችን በ14ኛው ዙር የስዕል ትርዒቱ ለእይታ ያቀረበው ጋለሪው፤ ሳር ቤት ካናዳ ኤምባሲ ፊት ለፊት በሚገኘው ጋለሪያ ቶሞካ በርካታ የስዕል አፍቃሪያን፣ ሰዓሊያን፣ ጋዜጠኞችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በሚገኙበት ከ35 በላይ በሚሆኑ የወጣቱ ሰዓሊ ስራዎች፣ የአሳሳል ዘይቤና በስዕል ፍልስፍናው ዙሪያ ሰፊ ውይይት እንደሚካሄድ ለማወቅ ተችሏል፡፡

Saturday, 02 May 2015 12:35

የሰዓሊያን ጥግ

  ፎቶግራፍን አታነሳውም፤ ትፈጥረዋለህ እንጂ፡፡         ቶማስ ሜርቶን
ለማየት ስል ዓይኖቼን እጨፍናለሁ፡፡
ፖል ጋውጉይን
እንደ ስሜቶች ሁሉ ቀለማትም የህይወት ነፀብራቅ ናቸው፡፡     ጃኒሴ ግሊናዌይ
ቀለማትና እኔ አንድ ነን፡፡ ሰዓሊ ነኝ፡፡
ፖል ክሊ
ሰዓሊ ጥሩ ነገር የሚሰራው እየሰራ ያለውን የማያውቅ ከሆነ ብቻ ነው፡፡
ኤድጋር ዴጋስ
የሰዓሊ ሥራ ሁልጊዜም ምስጢሩን ጥልቅ ማድረግ ነው፡፡
ፍራንሲስ ቤከን
ለመሳል ዓይኖችህን መጨፈንና ማዜም አለብህ፡፡
ፓብሎ ፒካሶ
በስዕልና በግጥም ሰስብዕና ሁሉም ነገር ነው፡
ገተ
ማንኛውም ጅል ስዕል መስራት ይችላል፤ ለመሸጥ ግን ብልህ ሰው ይፈልጋል፡፡
ሳሙኤል በትለር
መጀመሪያ ደንስ፤ በኋላ አስብ፡፡
ሳሙኤል ቤኬት
ነገሮችን የምስለው እንደማያቸው ሳይሆን እንደማስባቸው ነው፡፡     ፓብሎ ፒካሶ
ቀለማት የተፈጥሮ ፈገግታዎች ናቸው፡፡
ሊይግ ሃንት
ሰው ሁሉ ስዕልን ለመረዳት ይፈልጋል፡፡ ለምንድን ነው የአዕዋፋትን ዝማሬ የመረዳት ሙከራ የሌለው?
ፓብሎ ፒካሶ
የራሴ ስዕሎች ባለቤት አይደለሁም፤ ምክንያቱም የፒካሶ ኦሪጂናል ስዕል ብዙ ሺ ዶላሮች ያወጣል ይሄ ከአቅሜ በላይ የሆነ ቅንጦት ነው፡፡
ፓብሎ ፒካሶ

Saturday, 02 May 2015 12:22

የየአገሩ አባባል

ጥበብ አልባ ዕውቀት በአሸዋ ላይ እንዳለ ውሃ ነው፡፡
የጊኒያውያን አባባል
ሞኝ ያወራል፤ ብልህ ያደምጣል፡፡
የኢትዮጵያውያን አባባል
ጥበብ በአንድ ጀንበር አይመጣም፡፡
የሶማሊያውን አባባል
በቀውስ ሰዓት ብልህ ድልድይ ሲገነባ፣ ሞኝ ግድብ ይገነባል፡፡
የናይጄሪያውያን አባባል
በኩራት ከተሞላህ ለጥበብ ቦታ የለህም፡፡
የአፍሪካውያን አባባል
ብልህ ሰው ሁልጊዜ መላ አያጣም፡፡
የታንዛንያውያን አባባል
ማንም ብልህ ሆኖ አልተወለደም፡፡
የአፍሪካውያን አባባል
ትልቅ ወንበር ንጉስ አያደርግም፡፡
የሱዳናውያን አባባል
የአንበጣዎች ጠብ ለቁራ ፌሽታው ነው፡፡
የሌሴቶ አባባል
ደጋግሞ በመሞከር ጦጣ ከዛፍ መዝለል ትማራለች፡፡
የቡጋንዳ አባባል
ምክር እንግዳ ነው፤ የሚቀበለው ካገኘ ሌቱን ያድራል፡፡ ያለበለዚያ የዚያኑ ዕለት ይመለሰል፡፡
የማላጋሲ አባባል
መጓዝ መማር ነው፡፡
የኬንያውያን አባባል
ባለሙያዎች ባሉበት የተማሪዎች እጥረት አይኖርም፡፡
የስዋሂሊ አባባል
ወተትና ማር ቀለማቸው ይለያያል፤ ነገር ግን አንድ ቤት ተጋርተው በሰላም  ይኖራሉ፡፡
የአፍሪካውያን አባባል
መግባባት ሳይኖር ሰላም ሊኖር አይችልም፡፡
የሴኔጋሎች አባባል
እየመራሁ ነው ብሎ የሚያስብና ተከታይ የሌለው ሰው የእግር ጉዞ እያደረገ ነው፡፡
የማላዊያኖች አባባል

 በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ሰርቪስ (ኢቢኤስ) ቴሌቪዥን “የጆርዳና ኩሽና ሾው”    አዘጋጅ ጆርዳና ከብዶም የተፃፈው “የጆርዳና የምግብ አዘገጃጀት” የተሰኘ መፅሀፍ ሰሞኑን ለገበያ ቀርቦ እየተነበበ ይገኛል፡፡ መፅሐፉ ከመቶ በላይ የውጭ ምግቦች አዘገጃጀትን የያዘ ሲሆን ኢትዮጵያዊያን ከተለመደው የአመጋገብ ስርዓታቸው ወጣ ብለው እንደ ፓስታ፣ ፒዛ ያሉ የውጭ ምግቦችን በኩሽናቸው በቀላሉ አዘጋጅተው መመገብ እንዲችሉ ያግዛል ተብሏል፡፡ በኢቢኤስ ቲቪ “ጆርዳና ኩሽና ሾው” እውቅናን ያተረፈችው ባለሙያዋ፤ቦሌ ሩዋንዳ ኤምባሲ አካባቢ “ጆርዳናስ ኪችን ሬስቶራንት” የተሰኘ ምግብ ቤት ከፍታ የውጭ አገር ምግቦችን እያሰናዳች እንደምትሸጥ ለማወቅ ተችሏል፡፡

 በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ሰርቪስ (ኢቢኤስ) ቴሌቪዥን “የጆርዳና ኩሽና ሾው”    አዘጋጅ ጆርዳና ከብዶም የተፃፈው “የጆርዳና የምግብ አዘገጃጀት” የተሰኘ መፅሀፍ ሰሞኑን ለገበያ ቀርቦ እየተነበበ ይገኛል፡፡ መፅሐፉ ከመቶ በላይ የውጭ ምግቦች አዘገጃጀትን የያዘ ሲሆን ኢትዮጵያዊያን ከተለመደው የአመጋገብ ስርዓታቸው ወጣ ብለው እንደ ፓስታ፣ ፒዛ ያሉ የውጭ ምግቦችን በኩሽናቸው በቀላሉ አዘጋጅተው መመገብ እንዲችሉ ያግዛል ተብሏል፡፡ በኢቢኤስ ቲቪ “ጆርዳና ኩሽና ሾው” እውቅናን ያተረፈችው ባለሙያዋ፤ቦሌ ሩዋንዳ ኤምባሲ አካባቢ “ጆርዳናስ ኪችን ሬስቶራንት” የተሰኘ ምግብ ቤት ከፍታ የውጭ አገር ምግቦችን እያሰናዳች እንደምትሸጥ ለማወቅ ተችሏል፡፡

ማልድ የትምህርት ድጋፍ ኃ.የተ.የግ.ማ ባቀራረቡ የተለየ የልጆችን የንባብን ባህል የሚያዳብር፣ ከመጽሐፍ ጋር የተያያዘ የወላጆች ቀን “Book and fun Kids day” /የህፃናት የንባብና የትምህርታዊ ጨዋታ ቀን/ የፊታችን ማክሰኞ በትሮፒካል ጋርደን መናፈሻ ከ4-11 ሰዓት ድረስ ማዘጋጀቱን ገለፁ፡፡
ከ4-14 ዓመት ላሉ ልጆች በተዘጋጀው በዚህ የልጆች ቀን፤ ወላጆች አስተማሪዎች እንዲሁም ትላልቆች ለልጆች መጽሐፍት ያነባሉ፡፡ ጸሐፊያን በዚሁ ቀን መጽሐፍ የማሳተምን ሂደት ለልጆች ያስረዳሉ፣ የተለያዩ ጨዋታዎችም ይኖራሉ፡፡ ማልድ በ21ኛው ክ/ዘመን ልጆች ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ በሚደረገው ጥረት ውስጥ ወላጆች ልጆቻቸውን እንዴት ማሳደግ እንደሚገባቸው ይመክራል ተብሏል፡፡
ማልድ የትምህርት ድጋፍ ሰጪ አስተማሪዎችን በማሰልጠን፣ እንዲሁም ልጆችን ለክፍለዘመኑ ብቁ እንዲሆኑ የሚያግዙ በጥበብና በፈጠራ የተሞሉ ስልጠናዎችን በመስጠት ይታወቃል፡፡

 የዋይት ሃውስ ባለስልጣናት ለሳምንታት በየዕለቱ መክረዋል

   ለጊዜው ማንነታቸው በውል ያልታወቀ የኢንተርኔት አጭበርባሪዎች የፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማን ኢሜይል በህገ-ወጥ መንገድ ሰብረው በመግባት፣ መረጃዎችን ማግኘት እንደቻሉ መረጋገጡን ስካይ ኒውስ ባለፈው ሰኞ ዘገበ፡፡
የዋይትሃውስ የደህንነት ሃላፊዎች ቻይናውያን አልያም ሩስያውያን ሳይሆኑ ሲሉ የጠረጠሯቸው እነዚህ የኢንተርኔት አጭበርባሪዎች፣ የይለፍ ቁልፉን ሰብረው በመግባት ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ለሌሎች ሰዎችና ድርጅቶች የላኳቸውንና ከሌሎች የተላኩላቸውን የኢሜል መልእክቶች ማግኜት መቻላቸው ተረጋግጧል፡፡ድርጊቱ የተፈጸመው ከሳምንታት በፊት ቢሆንም፣ የዋይት ሃውስ ባለስልጣናት ጉዳዩን ሸፋፍነውት እንደቆዩ የጠቆመው ዘገባው፣የአጭበርባሪዎቹ ጉዳይ አሳሳቢ መሆኑን የሚያመለክተው ባለስልጣናቱ ላለፉት ሳምንታት በየዕለቱ እየተሰበሰቡ በጉዳዩ ዙሪያ ሲመክሩ መቆየታቸው ነው ብሏል ዘገባው፡
ሩስያውያን የኢንተርኔት አጭበርባሪዎች የኦባማን የኢሜል መልዕክቶች ለማግኘት የቻሉት፣ ባለፈው አመት በዋይት ሃውስ የሴኪውሪቲ ሲስተም ላይ በደረሰው ቀውስ ያገኙትን ክፍተት በመጠቀም ነው ተብሎ እንደሚገመት የገለጸው ዘገባው፣ ይሄም ሆኖ ግን አጭበርባሪዎቹ ከፍተኛ ጥበቃ የሚደረግለትን የኦባማ  የብላክቤሪ ስልክ መልዕክቶች ማግኘት እንዳልቻሉ አክሎ ገልጧል፡፡

- ዋና ዋናዎቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በምርጫው አልተሳተፉም
- ምዕራባውያን አገራት ምርጫው ነጻና ፍትሃዊ አይደለም ብለዋል

 ዋና ዋናዎቹ የሱዳን ተቃዋሚ ፓርቲዎች ነጻና ፍትሃዊ አይሆንም በሚል ራሳቸውን ባገለሉበት የአገሪቱ ምርጫ የተወዳደሩት ፕሬዚዳንት ኡመር ሃሰን አልበሽር፤ 94.5 በመቶ ድምጽ በማግኘት በቀጣይም አገሪቱን በፕሬዚዳንትነት እንዲመሩ መመረጣቸውን ቢቢሲ ዘገበ።የአገሪቱ የምርጫ ኮሚሽን ሃላፊ ሙክታር አል አሳም ባለፈው ሰኞ ከካርቱም በሰጡት መግለጫ፣ ናሽናል ኮንግረስ ፓርቲን በመወከል ለፕሬዚዳንትነት የተወዳደሩት አልበሽር፤ ከ5 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ድምጽ በማግኘት ማሸነፋቸውን ያስታወቁ ሲሆን የአፍሪካ ህብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድን በበኩሉ፤ ድምጽ ለመስጠት ከተመዘገቡት 13.3 ሚሊዮን ዜጎች ውስጥ ድምጽ የሰጡት አንድ ሶስተኛ ያህሉ ብቻ መሆናቸውን አረጋግጫለሁ ብሏል፡፡ አልበሽር በዘንድሮው የሱዳን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ይህ ነው የሚባል ፉክክር እንዳልገጠማቸው የዘገበው ዘጋርዲያን በበኩሉ፣ ከተፎካካሪዎች መካከል የተሻለ ድምጽ ያገኙት ፌደራል ትሩዝ ፓርቲን ወክለው የተወዳደሩት ፋደል አልሳይድ ሹያብ መሆናቸውንና ያገኙት ድምጽም 1.43 በመቶ ብቻ መሆኑን አስታውቋል።ከሚያዝያ 5 ቀን ጀምሮ ለአራት ተከታታይ ቀናት በመላ አገሪቱ በተቋቋሙ 11 ሺህ የድምጽ ጣቢያዎች በተከናወነው የድምጽ አሰጣጥ ስነስርአት ላይ ድምጽ ለመስጠት ከተመዘገቡት ውስጥ ሁለት ሶስተኛው ድምጽ አለመስጠታቸውንና ለፕሬዚዳንታዊ ምርጫው በተፎካካሪነት የቀረቡት 15 እምብዛም እውቅና የሌላቸው ዕጩ ተወዳዳሪዎች ብቻ እንደነበሩም አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡ አሜሪካ፣ እንግሊዝና ኖርዌይን ጨምሮ በርካታ ምዕራባውያን አገራት፣ ላለፉት 25 አመታት ሱዳንን በፕሬዚዳንትነት የመሩት አልበሽር፤ በከፍተኛ ድምጽ ያሸነፉበትንና ባለፈው ሰኞ የተከናወነውን የአገሪቱ ምርጫ ድምጽ አሰጣጥ ነጻና ፍትሃዊ አይደለም፣ እውቅና አንሰጠውም ሲሉ የተቹት ሲሆን፣ የቻይናው ፕሬዚደንት ዢ ጂፒንግ በበኩላቸው፤ ለአልበሽር የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክት ልከዋል፡፡
ስቲስ ኤንድ ኢኳሊቲ ሙቭመንት የተባለው የአገሪቱ አማጺ ቡድን ባለፈው እሁድ በደቡብ ዳርፉር አካባቢ በሱዳን መንግስት ጦር ላይ በከፈተው ወታደራዊ ጥቃት የጦር ካምፕ ማውደሙንና የጦር መሳሪያዎችን መማረኩን ያስታወቀ ሲሆን፣ የአገሪቱ የጦር ሃይል በበኩሉ አማጽያኑ በሚንቀሳቀሱበት አካባቢ ባደረገው ድብደባ ከፍተኛ ውድመት ማድረሱን አስታውቋል፡፡ በአየር ድብደባው 16 ሲቪል ዜጎች መሞታቸውንና ከ11 በላይ የሚሆኑ ደግሞ መቁሰላቸውን የዘገበው አይቢታይምስ ነው፡፡
በዳርፉር ግጭት የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈጽመዋል በሚል በአለማቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ክስ የቀረበባቸውና የእስር ማዘዣ የተቆረጠባቸው የ71 አመቱ አልበሽር፣ ድርጊቱን አልፈጸምኩም ሲሉ ተቃውሟቸውን ማሰማታቸውን ዘገባው ጨምሮ አስታውሷል፡
ፕሬዚዳንት አልበሽር እ.ኤ.አ በ1989 በመፈንቅለ መንግስት ስልጣን ከያዙበት ጊዜ አንስቶ አገሪቱን እየመሩ ሲሆን ሱዳንን ለረጅም ጊዜ በመምራት ቀዳሚው ሰው እንደሆኑ ይታወቃል፡፡

ባለፈው ቅዳሜ በኔፓል በተከሰተውና በሬክተር ስኬል 7.8 በተመዘገበው አሰቃቂ የርዕደ-መሬት አደጋ የሟቾች ቁጥር ከ5ሺህ በላይ መድረሱ መረጋገጡን ሲኤንኤን ዘገበ፡፡
በርዕደ-መሬቱ የተጎዱ ዜጎችን የማፈላለጉና እርዳታ የሚፈልጉ ዜጎችን የመድረሱ እንቅስቃሴ በአስቸጋሪ የአየር ንብረት ሳቢያ አዳጋች ሆኖ የቀጠለ ሲሆን እስካለፈው ረቡዕ ድረስ ለህልፈተ ህይወት የተዳረጉ ሰዎች ቁጥር ከ5ሺህ በላይ መድረሱን ዘገባው አመልክቷል፡፡
የአገሪቱ መንግስት ባለስልጣናትን ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፤ በአደጋው ከሞቱት በተጨማሪ ከ10ሺህ በላይ ሰዎችም የመቁሰል አደጋ የደረሰባቸው ሲሆን፣ ፍለጋው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልና የሟቾችም ሆነ የቁስለኞች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨምር ተገምቷል፡፡  
ኔፓልን መልሶ ለማቋቋም ከ5 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ ያስፈልጋል ተብሎ እንደሚገመት ያስታወቀው ዘገባው፣ የአሜሪካ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ መስሪያ ቤት በበኩሉ፤ በአደጋው የደረሰው ጥፋት እስከ 10 ቢሊዮን ዶላር እንደሚገመት መግለጹን አስታውቋል፡፡ ባለፈው ማክሰኞ ከሰዓት በኋላ ላንግታንግ በተባለችው የኔፓል አካባቢ በደረሱ ሁለት የመሬት መንሸራተት አደጋዎች፣ ከ200 በላይ ሰዎች የደረሱበት እንደጠፋም ዘገባው ጠቁሟል፡፡
የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሱሺል ኮይራላ በአደጋው ህይወታቸው ያለፈ ዜጎችን ለመዘከር ባለፈው ማክሰኞ ለሶስት ቀናት የሚቆይ ብሄራዊ ሃዘን ያወጁ ሲሆን ባለፉት አስር አመታት በርዕደ-መሬት ሳቢያ ለህልፈተ ህይወት የተዳረጉ ዜጎች ቁጥር ከ10 ሺህ በላይ እንደሚደርስም አስታውቀዋል፡፡
በአደጋው የተጎዱ ዜጎች ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የድረሱልኝ ጥያቄ እያቀረቡ እንደሚገኙ የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በሂሊኮፕተር የታገዘ እንቅስቃሴ እየተደረገ ቢገኝም፣ ከፍተኛ ዝናብና ውሽንፍር ከመኖሩና ከቦታዎቹ ተራራማነት ጋር በተያያዘ፣ በከፋ ሁኔታ በተጎዱ አካባቢዎች ፈጥኖ ለመድረስ አስቸጋሪ እየሆነ መምጣቱንም ገልጸዋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ የቅዳሜው የኔፓል ርዕደ-መሬት ስምንት ሚሊዮን ያህል ሰዎችን ተጠቂ እንዳደረገ ያስታወቀ ሲሆን፣ ለአስቸኳይ የአደጋ ጊዜ እርዳታ የሚውል 15 ሚሊዮን ዶላር ገንዘብ ድጋፍ አድርጓል፡፡
የተመድ ቃል አቀባይ ፋራህ ሃቅ እንዳሉት፤ የገንዘብ ድጋፉ ተጎጂዎችን ለመታደግ በመስራት ላይ የሚገኙ የሰብዓዊ ተቋማትን እንቅስቃሴ ለማሳደግና ለተጎጂዎቹ የመጠለያ፣ የውሃ፣ የመድሃኒትና የሌሎች አገልግሎቶች አቅርቦቶችን ለማሟላት የሚውል ነው።
ህንድ፣ አሜሪካ፣ ቻይና፣ ማሌዢያ፣ ፓኪስታን እና እስራኤል ተጎጂዎችን ለመርዳት የሚደረገውን እንቅስቃሴ ለመደገፍ አውሮፕላኖችን ወደ ኔፓል የላኩ ሲሆን አሜሪካ በበኩሏ ለፈጥኖ ደራሽ እርዳታ የሚውል 10 ሚሊዮን ዶላር ለመለገስ ቃል ከመግባቷ በተጨማሪ የእርዳታ ድርጅቶቿን በአደጋው የተጎዱትን ዜጎች እንዲረዱ ወደ ኔፓል ልካለች፡፡