Administrator

Administrator

ሳዑዲ ወደተከለከሉ አገራት የሄዱ ዜጎችን ለ3 አመታት ከጉዞ ልታግድ ነው


             የአውሮፓ ህብረት አባል አገራት የኮሮና ቫይረስ ክትባቶችን እስከ ሃምሌ ወር መጀመሪያ ድረስ ከአጠቃላይ አዋቂ ዜጎቻቸው ለ70 በመቶ ያህሉ ቢያንስ አንድ ዙር ለመስጠት የያዙትን ዕቅድ ማሳካታቸውን ፎርብስ መጽሄት ዘግቧል፡፡
ህብረቱ ባለፈው ማክሰኞ ያወጣውን መግለጫ ጠቅሶ ዘገባው እንዳስነበበው፣ በአሁኑ ሰዓት በየዕለቱ በአማካይ 3.1 ሚሊዮን ያህል ክትባቶችን በመስጠት ላይ የሚገኙት አባል አገራቱ 70 በመቶ ያህል ዜጎቻቸውን ቢያንስ ለአንድ ዙር ለመከተብ የያዙትን ዕቅድ ሲያሳኩ፣ አንከተብም የሚሉ ዜጎቿን ለማሳመን ጊዜ የፈጀባት አሜሪካ በበኩሏ፤ 69 በመቶ ያህል ዜጎቿን ብቻ ነው ለመከተብ የቻለችው፡፡
የአውሮፓ ህብረት አገራት 70 በመቶ ዜጎችን በመከተብ ከአሜሪካ ቀዳሚ ቢሆኑም፣ በሁለት ዙር ሙሉ ክትባት በመስጠት ረገድ ግን አሜሪካ የበለጠ ውጤታማ መሆኗን የጠቆመው ዘገባው፣ ከአጠቃላዩ የአሜሪካ ህዝብ ሙሉ ክትባት ያገኘው 49.1 በመቶ ያህሉ ሲሆን በአውሮፓ ግን 47.3 በመቶው ብቻ መሆኑንም አስረድቷል፡፡ በአለማቀፍ ደረጃ በርካታ ቁጥር ያላቸው ዜጎችን ለመከተብ ከቻሉ የአውሮፓ ህብረት አባል አገራት መካከል ዴንማርክ፣ ማልታ፣ ቤልጂየም፣ ኔዘርላንድስና ስፔን እንደሚገኙበትም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡
በሌላ ዜና ደግሞ፣ አዳዲስ የኮሮና ቫይረስ ዝርያዎች እንዳይስፋፉ ለመከላከል ያቀደው የሳዑዲ አረቢያ መንግስት፤ ኢትዮጵያ፣ አፍጋኒስታን፣ ብራዚል፣ ደቡብ አፍሪካና ቱርክን ጨምሮ የኮሮና ቫይረስ ከፍተኛ ስጋት አለባቸው ብሎ የጉዞ ክልከላ ወደጣለባቸው የተወሰኑ አገራት የተጓዙ ዜጎቹን ለ3 አመታት ያህል ከአገር እንዳይወጡ እንደሚከለክልና ሌሎች ከፍተኛ ቅጣቶችን እንደሚጥልባቸው ማስጠንቀቁ ተዘግቧል፡፡
የሳዑዲ አረቢያ የአገር ውስጥ ሚኒስቴርን አንድ ከፍተኛ ባለስልጣን ጠቅሶ አረብ ኒውስ ባለፈው ማክሰኞ እንደዘገበው፣ የአገሪቱ መንግስት የኮሮና ቫይረስ ከፍተኛ ስጋት አለባቸው ብሎ ወደለያቸውና ዜጎቹን እንዳይጓዙባቸው ወይም እንዳይመጡባቸው ወደከለከላቸው አገራት የተጓዙ ዜጎች ወደ አገራቸው ሲመለሱ ከፍተኛ ቅጣት እንደሚጣልባቸውና ለ3 አመታት ያህል ከአገር እንዳይወጡ እንደሚከለከሉ ለማወቅ ተችሏል፡፡ የአገሪቱ መንግስት የኮሮና ቫይረስ ከፍተኛ ስጋት አለባቸው ብሎ የዘረዘራቸውና የጉዞ ክልከላ ገደብ የጣለባቸው ሌሎች አገራት አርጀንቲና፣ ግብጽ፣ ህንድ፣ ኢንዶኔዢያ፣ ሊባኖስ፣ ፓኪስታን፣ ቬትናም እና የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ እንደሆኑም ዘገባው አመልክቷል፡፡


 አንድ አለማቀፍ የገበያ ጥናት ተቋም ከሰሞኑ ይፋ ባደረገው አመታዊ የግንባታ ገበያ አለማቀፍ ሪፖርት መሰረት፣ የጃፓን ርዕሰ መዲና ቶክዮ ከአለማችን ከተሞች መካከል በኮንስትራክሽን ዘርፍ የዋጋ ውድነት በ1ኛ ደረጃ ላይ መቀመጧን ፎርብስ መጽሄት ዘግቧል፡፡
ተርነር ኤንድ ታውንሴንድ በ45 የአለማችን አገራት በሚገኙ ከተሞች 90 ገበያዎች ላይ ያደረገውን የኮንስትራክሽን ገበያ ጥናት መሰረት በማድረግ ከሰሞኑ ይፋ ያደረገውን የ2021 የፈረንጆች አመት አለማቀፍ የኮንስትራክሽን ዋጋ ሪፖርት ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ በቶክዮ አንድ ስኩየር ሜትር ስፋት ያለው ግንባታ ለማከናወን በአማካይ 4,002 የአሜሪካ ዶላር ወጪ የሚጠይቅ ሲሆን ይህም በአለማችን ከፍተኛው ዋጋ ነው፡፡
ለአንድ ስኩየር ሜትር ግንባታ 3,894 በዶላር ወጪ የሚደረግባት ሆንግ ኮንግ በአመቱ የተቋሙ የኮንስትራክሽን ዋጋ ውድነት ዝርዝር በሁለተኛ ደረጃ ላይ ስትቀመጥ፣ የአሜሪካዋ ሳን ፍራንሲስኮ በ3,720 ዶላር ሶስተኛ ሆናለች፡፡
የአሜሪካዋ ከተማ ኒው ዮርክ ሲቲ በ3511 ዶላር፣ የስዊዘርላንዶቹ ከተሞች ጄኔቫና ዙሪክ በ3478 ዶላርና በ3375 ዶላር፣ የአሜሪካዎቹ ቦስተንና ሎስ አንጀለስ በ3203 እና በ3186 ዶላር አማካይ የአንድ ስኩየር ሜትር ግንባታ ዋጋ ከአራተኛ እስከ አስረኛ ያለውን ደረጃ የያዙ የአለማችን ከተሞች መሆናቸውንም ዘገባው አመልክቷል፡፡


 በሩብ አመቱ 40 ቢሊዮን አይፎን ስልኮችን ሸጧል

               በአለማችን እጅግ ከፍተኛ የገበያ ዋጋ ያለው ቁጥር አንድ ኩባንያ የሆነው የአሜሪካው የቴክኖሎጂ ኩባንያ አፕል እስከ ሰኔ በነበሩት ያለፉት 3 ወራት በድምሩ 81 ቢሊዮን ዶላር ያህል አጠቃላይ ገቢ ማግኘቱንና ይህም፣ በኩባንያው ታሪክ ከፍተኛ ሆኖ የተመዘገበ የሁለተኛ ሩብ አመት ገቢ መሆኑን አስታውቋል፡፡
ዋና መስሪያ ቤቱን በካሊፎርኒያ ያደረገው ግዙፉ ኩባንያ አፕል በሩብ አመቱ ያገኘው ገቢ ካለፈው አመት ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲነጻጸር በ35 በመቶ ያህል ብልጫ እንዳለው የጠቆመው ዘገባው፣ በሩብ አመቱ ያገኘው የተጣራ ገቢ በበኩሉ 21.7 ቢሊዮን ዶላር መሆኑን ኩባንያው በሳምንቱ መጀመሪያ ይፋ ያደረገውን መረጃ ጠቅሶ ዘገባው አመልክቷል፡፡
ኩባንያው በሩብ አመቱ ከፍተኛ ገቢ እንዲያገኝ ካስቻሉት ምክንያቶች መካከል የአይፎን ሞባይል ስልኮቹ ሽያጭ ማደጉ በቀዳሚነት እንደሚጠቀስ የጠቆመው ዘገባው፣ ከአጠቃላይ ገቢው 53 በመቶ ያህሉ ከዚሁ ሽያጭ መገኘቱንና ኩባንያው ባለፉት 3 ወራት ብቻ 40 ቢሊዮን ያህል አይፎኖችን መሸጡንም ገልጧል፡፡
የአፕል የአክሲዮን ዋጋ ባለፉት አምስት አመታት በ500 በመቶ ያህል ማደጉን ያስታወሰው ዘገባው፣ በአሁኑ ወቅት የኩባንያው አጠቃላይ ሃብትና የገበያ ዋጋ ወደ 2.5 ትሪሊዮን ዶላር መድረሱንም አክሎ ገልጧል፡፡


 ብራዚላዊቷ የ7 አመት ታዳጊ ኒኮል ኦሊቬራ በቅርቡ ከባልደረቦቿ ጋር በጥምረት ባደረገችው ምርምር 7 አዳዲስ አስቴሮይዶችን ማግኘቷንና በዚህም በአለማችን የአስትሮኖሚ ወይም ስነከዋክብት ምርምር ታሪክ በለጋ ዕድሜዋ በሙያው አዲስ ግኝት ያበረከተች ቀዳሚዋ አስትሮኖመር ተብላ መሸለሟን ቴክታይምስ ድረገጽ አስነብቧል፡፡
ኦሊቬራ በአሜሪካው የጠፈር ምርምር ማዕከል ናሳ እና ኢንተርናሽናል አስትሮኖሚካል ሰርች ኮላቦሬሽን በተባለው አለማቀፍ ተቋም በተከናወነው አስቴሮይድ ሃንት ሲቲዝን ሳይንስ የተሰኘ የምርምር ፕሮግራም ተሳታፊ በመሆን 7 አዳዲስ አስቴሮይዶችን ማግኘቷን የጠቆመው ዘገባው፣ በዚህ ውጤታማ ስራዋም የአለማችን ትንሽዋ አስትሮኖመር የሚል ዕውቅና ከተቋማቱ ልታገኝ መብቃቷን ገልጧል፡፤
ታዳጊዋ ለጠፈርና ለስነከዋክብት ልዩ ፍቅርና ፍላጎት ያድርባት የጀመረው ገና የሁለት አመት ህጻን ሳለች እንደነበር ያስታወሰው ዘገባው፣ ዕድሜዋ ከፍ እያለ ሲመጣ ወደሙያው የበለጠ መሳቧንና በራሷ ጥረት ከፍተኛ ዕውቀት ለማካበት መቻሏን እንዲሁም በስድስት አመት ዕድሜዋ አላጎኣስ የተባለው የብራዚል የአስትሮኖሚ ጥናት ማዕከል አባል ሆና የበለጠ ዕውቀት መገብየቷንና በከፍተኛ ውጤት ማለፏን ተከትሎም በትምህርት ቤቶች እየተጋበዘች ትምህርት መስጠት እንደጀመረች ገልጧል፡፡
የብራዚል የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ሚኒስቴር ባለፈው ወር ባካሄደው የመጀመሪያው አለማቀፍ የአስትሮኖሚና ኤሮኖቲክስ ሴሚናርም ብራዚላዊቷን በመጋበዝ ትምህርታዊ ማብራሪያ እንድትሰጥ ማድረጉን የጠቆመው ዘገባው፣ በቅርቡም አስቴሮይድ ሃንት ሲቲዝን ሳይንስ ፕሮግራም ተሳታፊ በመሆን 7 አዳዲስ አስቴሮይዶችን ማግኘቷንና በዚህም በእድሜ ለጋዋ የአለማችን አስትሮኖመር ለመባል መብቃቷን አመልክቷል፡፡
ታዳጊዋ ኦሊቬራ የኮሮና ወረርሽኝን ተከትሎ የራሷን የዩቲዩብ ቻናል በመክፈት በስነከዋክብት ዙሪያ ከሙያ አጋሮቿ ጋር ገለጻ መስጠት መጀመሯንም ዘገባው አስነብቧል፡፡


ትላንት በጃፓን ቶክዮ ኦሎምፒክ በተደረገው የ10ሺ ሜትር የሩጫ ውድድር  አትሌት ሰለሞን ባረጋ ርቀቱን በ27፡43.22 በማጠናቀቅ የኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊ ሆኗል። በ10ሺና በ5ሺ ሜትር የዓለም ሪከርዶችን የያዙት ኡጋንዳዊ  አትሌት ቼፕቴጊ እንዲሁም ሌላ ኡጋንዳዊ አትሌት ጄፕቴጊ ቼፕሊሞ ውድድሩን የ2ኛና 3ኛ ደረጃን አግኝተዋል። ሌሎቹ የኢትዮጵያ አትሌቶች አትሌት በሪሁ አረጋዊ በ4ኛ ደረጃ  እንዲሁም አትሌት ዮሚፍ ቀጀልቻ በ8ኛ ደረጃ ውድድሩን አጠናቅቋል።
ከ32ኛ ኦሎምፒክ በፊት ኢትዮጵያ በተሳተፈችባቸው ባለፉት 13 ኦሎምፒኮች  በ10ሺ ሜትር ወንዶች 5 የወርቅ፤ 2 የብርና 5 የነሀስ ሜዲሊያዎችን የሰበሰበች ሲሆን የሰለሞን ባረጋ ድል  በ10ሺ ሜትር 6ኛ የኢትዮጵያ የወርቅ ሜዳሊያ ሆኖ ተመዝግቧል።
በ2012 እ.ኤ.አ በለንደን ኦሎምፒክና በ2016 በሪዮ ዲጀነሪዮ ኦሎምፒክ፣ የወርቅ ሜዳሊያዎችን አከታትሎ ማሸነፍ የቻለው እንግሊዛዊ አትሌት ሙፋራህ ሲሆን ሰለሞን ባረጋ የኢትዮጵያ የወርቅ ሜዳሊያ ክብርን ያስመለሰው ከሁለት ኦሎምፒኮች በኋላ ነው።
በ10ሺ ሜትር ለኢትዮጵያ የመጀመሪያውን ውጤት በብር ሜዳሊያ ያስመዘገበው አትሌት ማሞ ወልዴ በ1968 እ.ኤአ በሜክሲኮ ኦሎምፒክ ነበር። ከዚም በ1972 እ.ኤአ በሙኒክ ኦሎምፒክ ምሩጽ ይፍጠር የነሃስ፤ በ1992 እ.ኤ.አ በርሴሎና ኦሎምፒክ አዲስ አበባ የነሀስ፤ በ1996 እ.ኤ.አ በአትላንታ ኦሎምፒክ ኃይሌ ገ/ስላሴ የወርቅና በ2000 እ.ኤ.አ በሲድኒ ኦሎምፒክ ኃይሌ ገ/ስላሴ የወርቅ እንዲሁም አትሌት  አሰፋ መዝገቡ የነሀስ፤ በ2004 እ.ኤ.አ በአቴንስ ኦሎምፒክ ቀነኒሳ በቀለ የወርቅና አትሌት ስለሺ ስህን የብር፤ በ2008 እ.ኤ.አ በቤጂንግ ኦሎምፒክ ቀነኒሳ በቀለ የወርቅና  ስለሺ ስህን ብር እንዲሁም በ2012 እ.ኤአ በለንደን ኦሎምፒክ ታሪኩ በቀለ የነሀስ ሜዳሊያን አግኝተዋል። አዲስ አበባ የዓለም ዓቀፍ ከተሞች መረብ አባል እንደመሆኗ የከተማዋ ኮሪደር ደኅንነት ማሻሻያና ሁለተኛ ዙር የፍጥነት አስተዳደር ፕሮጀክት መጠናቀቁን የትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ ም/ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ብርሀኑ ግርማ አስታወቁ፡፡
 የጤናማ ከተሞች ሽርክና እውቅና ያለው ዓለም ዓቀፍ የከተሞች መረብ ሲሆን እንደ ካንስር፣ ስኳር፣ የመንገድ ትራፊክ አደጋና የመሳሰሉ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን በመከላከል በዓለም ዙሪያ ከ300 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎችን ህይወት ለመታደግ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ይታወቃል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ከዚህም ዓለም አቀፍ ኢኒሽዬቲቭ ጋር የመንገድ ደህንነት ማሻሻያ ሥራዎችን  በጋራ እንደምታከናውን የትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ መግለጫ ጠቁሟል፡፡
“የማህበረሰብ ጤናን ለማሻሻል ጠንካራ አመራር ይጠይቃል” ያሉት ኢንጂነር ብርሀኑ፤ የጤናማ ከተሞች ሽርክና ዓለም ዓቀፍ መረብ የመጀመሪያ ዙር በመዲናዋ የተጀመረው በ2010 ዓ.ም እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ ም/ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም፤ “ነዋሪዎቻቸው የተሟላ ህይወትና ረጅም እድሜ እንዲኖራቸው አበክረው ከሚሰሩ ከእነዚህ ዓለም አቀፍ እውቅና ካላቸው የከተሞች ቡድን አባላት ጋር በጋራ የመስራት እድል በማግኘታችን ደስተኛ ነን” ብለዋል፡፡
የትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ ባወጣው መግለጫ እንደጠቆመው፤ ከፍጥነት ወሰን በላይ በማሽከርከር የሚከሰት የትራፊክ አደጋን ለመከላከል የጤናማ ከተሞች ሽርክና 50 ሺ ዶላር ቀጣይነት ያለው እርዳታ (renewal grant) ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፍጥነት መቆጣጠሪያ ራዳር መግዢያ አበርክቷል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ኢንጂነር ብርሀኑ እንዳስታወሱት፤ ባለፈው ዓመት በዚሁ ድርጅት ለመጀመሪያ ዙር የፍጥነት አስተዳደር ፕሮጀክት፣ በ90,819.12 ዶላር እርዳታ፣  ዲጂታል ቋሚ የፍጥነት መጠን ጠቋሚዎችን በመግዛትና በፒያሳ ዙሪያ በመትከል፣ በአካባቢው ያለውን ከፍጥነት ወሰን በላይ ማሽከርከር ለመቀነስና የህግ ማስከበሩን ስራ በቴክኖሎጂ ለመደገፍ ተችሏል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ በየዓመቱ በአማካይ ከ450 ሰዎች በላይ በትራፊክ ግጭት ምክንያት ህይወታቸውን እንደሚያጡ ያመለከተው መግለጫው፤ ለመንገድ ትራፊክ አደጋ ከሚያጋልጡ ምክንያቶች ውስጥ ደግሞ ከፍጥነት ወሰን በላይ ማሽከርከር የአደጋ መንስኤ ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚይዝ ያመለክታል። በፍጥነት ማሽከርከር ለአደጋ የማጋለጥ እድሉ ከፍተኛ ሲሆን የሚያደርሰውን ጉዳትም እንዲሁም የከፋ ያደርገዋል፡፡ በአጠቃላይ ከሚደርሰው የትራፊክ ግጭት ውስጥ 1/3ኛ የሚሆነውን ከፍጥነት ወሰን በላይ ማሽከርከር እንደሚሸፍን ጥናቶች እንደሚያመለክቱ ተጠቅሷል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ የማህበረሰቡ ከፍተኛ የጤና ችግር የሆነውን በተለይም አምራች የሆነውን ዜጋ እየቀጠፈ ያለውን የትራፊክ ግጭት ችግር ለመቅረፍ የተለያዩ የመፍትሔ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ እንደሚገኝ ተጠቁሟል። ይኸውም የትራፊክ አደጋ መረጃዎች አያያዝና አስተዳደር ስርዓትን ማዘመን፣ የመንገድ መሰረተ ልማት ግንባታና ዲዛይን ማሻሻያ፣ የግንዛቤ ማስጨበጫ እንዲሁም የትራፊክ ደንብ ማስከበር በተለይም የፍጥነት ገደብ ቁጥጥር ሥራዎች ዋና ዋናዎቹ ናቸው ተብሏል፡፡
የአዲስ አበባ ትራፊክ ማጅመንት ኤጀንሲ ከጤናማ ከተሞች ሽርክና ጋር በመተባበር በከተማዋ የተመረጡ የተለያዩ ኮሪደሮች የመንገድ ደህንነት ለማረጋገጥ ሁለተኛውን ዙር የመንገድ  አካፋይ ደህንነት ማሻሻያና የፍጥነት አስተዳደር ፕሮጀክት በስፋት አከናወኗል የሚለው መግለጫው፤ ኤጀንሲው በመጀመሪያ 4.5 ኪ.ሜ የሚሸፍኑትን አጎሮ-ጃክሮስ መብራት ኃይል- ሃያ አራት ኮሪደሮች ለይቷል ብሏል። የኮሪደሮቹ ሁለቱም አቅጣጫዎች 30 ሜትር ስፋት ያላቸው ሁለት መስመሮች (lanes) የያዙ ሲሆኑ በተጨማሪም የእግረኛ መንገድና መከለያ አጥር ዲዛይን የተደረገውና የተገነባው ዋና መንገዶችን (principal arterial street) ጥቅም ላይ ለማዋል ባወጣው መመዘኛ መስፈርት መሠረት መሆኑም  ተጠቁማል፡፡
“የተመረጡ ኮሪደሮች ከመሀል ከተማ ወደ ምስራቅ አቅጣጫ ከመኖሪያ አካባቢ ወደ ስራ ቦታ ደርሶ መልስ የሚያጓጉዝ መስመር በመሆኑ ስትራቴጂካል እንደሆነም ታምኖበታል፡፡ ከምንም በላይ ኮሪደሮቹ የተመረጡት የመንገድ ደህንነትና የትራፊክ እንቅስቃሴ ችግር ያለባቸው በመሆኑ ነው። ከ2008 እስከ 2010 ዓ.ም ያለው የትራፊክ አደጋ መረጃ እንደሚያሳየው፤ በእነዚህ የመንገድ አካፋዮች ከ31 ሰዎች በላይ በትራፊክ ግጭት  ምክንያት ህይወታቸው አጥተዋል፡፡”
 “በእነዚህ የተለዩ ኮሪደሮች የመንገድ ደህንነትና ፍሰት ላይ የሚስተዋሉ ችግሮች ለመቅረፍ ከተወሰዱ የመፍትሔ እርምጃዎች መካከል በመጋጠሚያና ማቋረጫ ቦታዎች ላይ የተደረገ ማሻሻያ፣ የፍጥነት ወሰን፣ የትራፊክ ማቀዝቀዣ እርምጃዎችና የእግረኛ መከላከያ አጥሮች ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡ እነዚህ በኢንጂነሪንጉ የተወሰዱ እርምጃዎች ከትራፊክ ደንብ ማስከበር ሥራዎች ጋር ተደምረው በኮሪደሮች አካባቢ ያለውን የተሽከርካሪዎች ፍጥነት ለመቆጣጠር ያስችላሉ”
ከጤናማ ከተሞች ሽርክና በእርዳታ  የተገኘው 50 ሺህ ዶላር ለትራፊክ ደንብ ቁጥጥር ስራ የሚያገለግል ዘመናዊ ተንቀሳቃሽ የፍጥነት መቆጣጠሪያ ራዳር ግዢ መዋሉ የተጠቆመ ሲሆን የተገዛው ራዳር  ቀንም ሌሊት የመስራት አቅም አለው፤ ምንም ዓይነት ስህተት እንዳይሰራና አውቶማቲክ (automatic calibration with zero tolerance/error) ተደርጎ የተዘጋጀ ነው ተብሏል። "በተጨማሪም በቪዲዮ የተደገፈ ዳታ ቤዝ አለው፤ በመስክ ላይ ማተም (ፕሪንት ማድረግ) ያስችላል፤ ለመቆሚያ የሚያገለግል ትራይፖይድ አለው፡፡ ለ12 ደንብ አስከባሪ ባለሙያዎችም የራዳሩን አጠቃቀም አስመልክቶ ስልጠና ተሰጥቷቸዋል፤ ሰርተፌኬትም አግኝተዋል።" ሲል መግለጫው ያብራራል፡፡
ይህ የጤናማ ከተሞች ሽርክና የብሉምበርግ ፊላንትሮፒስ፣ ከዓለም ጤና ድርጅትና ቫይታል ስትራቴጂ ጋር በመተባበር ድጋፍ የሚሰጡት ፕሮጀክት መሆኑ ታውቋል፡፡

 ዮንሴ ዓለም አቀፍ የጤና ማእከል በ1.7 ሚሊዮን ዶላር፣ ከ40 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያንን ተጠቃሚ የሚያደርግ ፕሮጀክት ለማከናወን  ከጤና ሚኒስቴር ጋር ሐምሌ 1 ቀን 2013 ዓ.ም የመግባቢያ ስምምነት መፈራረሙን በላከው መግለጫ አስታወቀ፡፡
በተደረሰው የመግባቢያ ስምምነት መሰረት ዮንሴ ዓለም አቀፍ የጤና ማዕከል፤ “ብሔራዊ ዘመቻ ለእውቀት አመለካከትና ባህሪ ለውጥ ስለ ህዝብ ብዛትና ተዋልዶ ጤና (በኢትዮጵያ ውስጥ የተመጠነ፣ደስተኛና ውጤታማ የሆነ ቤተሰብ ፕሮጀክት ሁለት)ን እ.ኤ.አ 2023 ዓ.ም መጨረሻ ድረስ ተግባራዊ ያደርጋል ተብሏል፡፡
ፕሮጀክቱ የሚያከናውነው ከኮሪያ ዓለማቀፍ የትብብር ኤጀንሲ፤(ኮይሳ) በተገኘ 1.7 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን በአዲስ አበባና ድሬዳዋ የከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም በአማራ፣ኦሮሚያ፣ሶማሊያ፣ትግራይና የደቡብ ብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልሎች ውስጥ የሚተገበር መሆኑ ተጠቁማል፡፡
ፕሮጀክቱ ዮንሴ ዓለም ዓቀፍ የጤና ማዕከል በ12 ሚሊዮን ዶላር እየተገበረ የሚገኘው ጥቅል ፕሮጀክት አንድ ክፍል ነው፡፡ የዚህ ፕሮጀክት ሌላኛው ክፍል በልማት ዕቅዱ ፑል ፈንድ አማካኝነት በኦሮሚያና ደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልሎች ስድስት ወረዳዎች እንዲሁም በጌዲዮና ጉጂ ዞኖች ውስጥ በመተግበር ላይ  ሲሆን የዚሁ ፕሮጀክት ሌላኛው ክፍል በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሕዝብ ፈንድ በተመደበለት 2 ሚሊዮን  ዶላር እየተገበረ እንደሚገኝ ማዕከሉ በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡
ዮንሴ ዓለም አቀፍ የጤና ማዕከል የካቲት 22 ቀን 2006 ዓ.ም ደቡብ ኮሪያ ውስጥ በሚገኘው ዮንሴ ዩኒቨርስቲ ዎንጁ ካምፓስ ውስጥ የተመሰረተና በዓለም አቀፍ የህብረተሰብ ጤና ላይ ልዩ ትኩረት አድርጎ የሚሰራ ኢንስቲቲዮት ሲሆን ዓለማቀፍ ድህነት እንዲቀንስና በዓለማቀፍ የሕዝብ ጤና ላይ ከ2030 የልማት ግቦች ጋር በተገናዘበ መንገድ አስተዋፅኦ ማድረግን ዓላማው ያደረገ ተቋም ነው፡፡


 (ከኢዜማ የተሰጠ መግለጫ)


             መንግሥት በትግራይ ያለው ግጭት ቆሞ ለሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረስ የተሻለ ሁኔታ ለመፍጠርና ሌሎች ምክንያቶችን ጠቅሶ የተናጥል ተኩስ አቁም ማወጁን ተከትሎ፣ ሰኔ 26 ቀን 2013 ዓ.ም የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ባወጣው የቢሆንስ ትንተና ሊሆን ይችላል ብለን ያስቀመጥነው ሁለተኛው ቢሆንስ (Scenario)፣ መንግሥት በትግራይ ክልል የተናጠል ተኩስ አቁም ካወጀ በኋላ የትግራይ አማጺዎች ግጭቱን ለማስፋት የሚያደርጉት ሙከራ ቀጥሎ ግልፅ አሸናፊ የማይኖርበት ሁኔታ ይከሰታል የሚል ነበር። ይህም ከቀጠለ በክልሉ ሕግና ሥርዓትን ማስከበር አዳጋች መሆኑ የሚፈጥረውን አጋጣሚ በመጠቀም ዘረፋዎች ሊበራከቱ እንደሚችሉ፣ የእለት እርዳታ የሚያስፈልጋቸው የክልሉ ነዋሪዎች በሚፈለገው ደረጃ እርዳታ ሳያገኙ ቀርተው ለከፍተኛ አደጋ ሊጋለጡ እንደሚችሉ፣ መሰረታዊ ለኑሮ የሚያስፈልጉ አገልግሎቶችና ግብዓቶች (የውሃ፣ የመብራት፣ ህክምና) ማግኘት የማይቻልበት ሁኔታ ሊፈጠር የሚችልበት ዕድል ከፍተኛ በመሆኑ የክልሉ ሕዝብ ለከፍተኛ ችግር የሚጋለጥበት ሁኔታ ሊበራከትና ለረጅም ጊዜ ምንም ዓይነት አስተዳደራዊ አገልግሎት ሊያገኝ የማይችልበት ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችልና የዚህ ዓይነት የማያቋርጥ ግጭት ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ብዙ ችግሮችን ስቦ በማምጣት (ኢንቬስትመንት ይቀንሳል፤ ቱሪዝም ይቀንሳል፤ በዚህም የሥራ አጥ ቁጥር ይጨምራል)፣ በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎችም አለመረጋጋትን ያስከትል ይችላል የሚል ትንተና አስቀምጠን ነበር። በትንተናችን ውስጥ ይህ ቢሆንስ (Scenario) የመሆን ዕድሉ ከሌሎቹ የበለጠ መሆኑን ጠቅሰን፣ በክልሉና ባጠቃላይ በሀገራችን ከብሔር ፖለቲካ ጋር ተያይዞ የመጣውን አደጋ በዘላቂነት የማይፈታ፣ ሀገሪቱን ቀስ እያለ ውስጧን እንደሚበላ በሽታ ከመግደሉ በፊት መፍትሄ የሚፈልግ እንደሆነ ገልፀን ነበር። በተጨማሪም በዚህ ሁኔታ ውስጥ መረጋጋትን ማስፈን ስለማይቻል የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ ወደ ከፍተኛ ግጭት ማምራቱ እንደማይቀር በትንታኔያችን ውስጥ አስቀምጠን ነበር።
የፌደራል መንግሥቱ የተናጠል ተኩስ አቁም አውጆ የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት በይዞታው ስር የነበሩ ቦታዎችን ለቆ ከወጣ በኋላ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ያስተዋልነው እንቅስቃሴ በቢሆንስ (Scenario) ትንተናችን ውስጥ ከሁሉም የተሻለ የመከሰት ዕድል አለው ብለን ያስቀመጥነው ሁለተኛው ቢሆንስ (Scenario) እውን እየሆነ እንደሆነ የሚያመላክት ነው።
በእርግጥ ከላይ በጠቀስነው ትንተናችን ውስጥ ሕወኃት የሚያደርሳቸው ትንኮሳዎች በኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት እየተመከቱና እየከሸፉ ሊሄዱ ይችላሉ የሚል ግምታችንን ብናስቀምጥም፣ በተግባር ያየነው ግን የፌደራል መንግሥት ሕወኃት ግጭቱን ለመቀጠል የወሰዳቸውን እርምጃዎች በግንባር ቀደምነት አመራር እየሰጠ ለማክሸፍ ከመሞከር ይልቅ ግጭቱን በክልሎች መካከል ያለ ግጭት እስኪመስል ድረስ የወሰደው ግልፅ ያልሆነ አቋም እጅግ አስደንጋጭ ሆኖ አግኝተነዋል።
ከዚህም በላይ ግጭቱን በተመለከተ በፌደራል መንግሥቱ በኩል የሚወሰዱ እርምጃዎች የተጣደፉና በቅጡ ያልታሰበባቸው መምሰላቸው፣ በአጭር ጊዜ ከሕወኃት የተደቀነውን አደጋ በማንኛውም መንገድ ከማክሸፍ ባለፈ እርምጃዎቹ ለሀገራችን ሰላምናና አንድነት በዘላቂነት የሚኖራቸውን አንድምታን ያልገመገሙ ስለመሆናቸው አመላካች ሆነው አግኝተናቸዋል።
መንግሥት የሚወስዳቸው እርምጃዎችን በተመለከተ ጊዜውን የጠበቀና ትክክለኛ መረጃ ለሕዝብ ባለማድረሱ በሕዝብ ዘንድ ከፍተኛ መደናገጥ ከመፍጠሩም ባለፈ በመንግሥት ላይ ያለው እምነት እንዲሸረሸር ምክንያት ሆኗል። በተጨማሪም ሕወኃት ያደረሳቸውን ወንጀሎችና የሚፈጽማቸውን ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶች ከተራ ክስ ባለፈ በተጨባጭ ማስረጃዎች አስደግፎ ለዜጎችና ለዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ እንዲደርስ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ክፍተት እየተስተዋለ ይገኛል። እነዚህ ክፍተቶች በጊዜ መፍትሄ ካልተበጀላቸው ችግሩን የበለጠ እያባባሱት እንደሚሄዱ እናምናለን።
መንግሥት በተጨባጭ ማስረጃዎች ላይ ተመስርቶ ለሕወኃት የሚደረግ ማንኛውንም ዓይነት ድጋፍ ለማስቆምና ተጠያቂነትን ለማስፈን ያለበትን ኃላፊነት ሙሉ በሙሉ የምንደግፍ ቢሆንም፣ በሌሎች የሀገራችን አካባቢዎች ሕወኃትን ትደግፋላችሁ በሚል ምክንያት የሚወሰዱ እርምጃዎች ማስረጃ ላይ የተመሰረቱ ከመሆን ይልቅ እንዲሁ በጅምላ የሚወሰዱ መሆናቸው የዜጎችን ሰብዓዊ መብት የሚጋፉና በትግራይ ያለውን ችግር የበለጠ የሚያወሳስቡ ድርጊቶች ናቸው። ለአብነት
በአዲስ አበባ ከተማ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ብቻ በተመሳሳይ ወቅት ቢያንስ 60 የንግድ ተቋማት/ሱቆች ከግጭቱ ጋር በተያያዙ ምክንያቶች ታሽገው ላለፉት ሁለት ሳምንታት ተዘግተው ቆይተዋል። ከግጭቱ ጋር በተያያዘ ሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚደርስ እንግልት፣ ከሕግ አግባብ ውጪ የሆነ እስርና ጥቃት በአፋጣኝ መቆም እንደሚገባው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን
ሐምሌ 8 ቀን 2013 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ መጠየቁ ይታወሳል። ከላይ የተጠቀሱትን መሰረት በማድረግ የሚከተሉት ምክረ ሀሳቦች ተግባራዊ እንዲደረጉ
እንጠይቃለን፥
1. በሁሉም የሀገራችን አካባቢዎች የሚገኙ የፀጥታ አስከባሪዎች ሕወኃት የደቀነው አደጋን ለማክሸፍ እያደረጉ ያሉትን መረባረብ በከፍተኛ አክብሮት እናደንቃለን። ሕወኃት የፌደራል መንግሥቱን በበላይነት ይቆጣጠር በነበረበት ጊዜ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን ላይ በሙሉ ግፍ ሲፈጽም እንደነበረ ሁሉ አሁንም የደቀነው አደጋ በሀገር አንድነትና ሰላም ላይ እንጂ በአንድ ወይንም በጥቂት ክልሎች ላይ ብቻ ያነጣጠረ እንዳልሆነ በመረዳት አደጋውን ለመከላከል የሚወሰደው እርምጃ አንድ ወጥ የዕዝ ሰንሰለት ኖሮት በፌደራል መንግሥትና በኢፌዲሪ መከላከያ ሠራዊት አመራር ሰጪነት ብቻ እንዲወሰድ፤
2. በትግራይ ክልል ያለውን ችግር አሁን ከፊታችን ሕወኃት ከደቀነው አደጋ እንፃር ብቻ በማየት ሕወኃትን ማሸነፍን ብቻ ዓላማ ያደረገ የአጭር ጊዜ ስልት ይዞ ከመንቀሳቀስ ባለፈ በዘላቂነት ክልሉ ወደተረጋጋ ሰላምና ዜጎች ወደ መደበኛ ሕይወታቸው ሊመለሱ የሚችሉበት እንዲሁም ግጭቱ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተቋጭቶ የሀገር ህልውና እና
አንድነትን በዘላቂነት ማረጋገጥ የሚቻልበት ስልት የአካባቢውን ተወላጆች በማሳተፍ እንዲነደፍና ተግባራዊ እንዲደረግ፤
3. አሁን ያለው ግጭት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲያበቃና ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ በትግራይ ክልልም ሆነ በሌሎች የሀገራችን አካባቢዎች የምትገኙ የሀገር ሽማግሌዎችና ሌሎች ልሂቃን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የምታስፈልጉበት ወቅት ላይ መሆናችሁን ተረድታችሁ የሚጠበቅባችሁን ኃላፊነት እንድትወጡ፤
4. የሰብዓዊ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ዜጎች ድጋፍ እንዲደርሳቸው የሚደረገው ጥረት አሁን ከምንዜውም በላይ ተጠናክሮ እንዲቀጥልና መንግሥት የሰብዓዊ እርዳታ በክልሉ ለሚኖሩ ዜጎች እንዲዳረስ የሚያደርገውን ጥረት በግልፅ እንዲያሳውቅ፤ እንዲሁም በዚህ ተግባር የሚሳተፉ የሰብዓዊ ድርጅቶች በግልፅነት እንዲንቀሳቀሱ ተገቢው ክትትል እንዲደረግ፤
5. የተለመዱ መንግሥትን የሚያሞግሱ የፕሮፓጋንዳ ሥራዎችን እየደጋገሙ ሕዝብን ከማሰልቸት ይልቅ መንግሥት የወሰዳቸውን እርምጃዎች በተመለከተ ትክክለኛና ወቅታዊ መረጃ ለሕዝብ እንዲደርስ እንዲደረግና ሕወኃት የሚፈፅማቸውን ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶችና ታዳጊዎችን በወታደርነት መመልመልና በጦርነት ማሳተፍን የመሳሰሉ ወንጀሎችን በተገቢው ፍጥነት በተጨባጭ ማስረጃዎች እያስደገፉ ይፋ የማድረግ ሥራ ተገቢው ትኩረት ተሰጥቶት እንዲሠራ፤
6. ዜጎች ለሕወኃት የሚደረግ ማንኛውም የሞራልም ሆነ ቁሳዊ ድጋፍ በሕዝብ ሠላም፣ በሀገር ደህንነትና ሕይወቱን ለመስዋዕትነት አዘጋጅቶ በተሰለፈው የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ላይ የሚደረግ ክህደት መሆኑን በመረዳት ከተመሳሳይ ድርጊቶች እንዲታቀቡ፤
7. ሕወኃትን ደግፋችኋል በሚል በጅምላ የሚወሰዱ እርምጃዎች ባስቸኳይ እንዲቆሙና እስካሁንም በዚህ መልኩ የተወሰዱ እርምጃዎች ላይ አፋጣኝ ማጣራት ተደርጎ እርምት እንዲወሰድ እንዲሁም አሁን ያለውን ሁኔታ እንደ አጋጣሚ በመጠቀም የግል ጥቅም ለማግኘት ዜጎች ላይ እንግልት የሚፈፅሙ የመንግሥትና የፀጥታ ሠራተኞች ላይ አስፈላጊው ማጣራት በአስቸኳይ ተደርጎ የማያዳግም ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ፤በመጨረሻም የሀገራችን ሰላምና አንድነት በዘላቂነት ተረጋግጦ፣ የሁሉም ዜጎች መብት እኩል የሚከበርበትና እኩል ዕድል የሚሰጥበት እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት ሁላችንም የምንችለውን ሁሉ የምናዋጣበት አሳሳቢ ወቅት ላይ እንዳለን እያስታወስን፣ ሁላችንም ኃላፊነታችንን ከምር ወስደን እንድንወጣ እናሳስባለን።
ሐምሌ 10 ቀን 2013 ዓ.ም


   67.6 በመቶ ህንዳውያን ኮሮናን የመከላከል አቅም አዳብረዋል ተባለ


           የጤና ባለሙያዎች በዓለማችን የኮሮና ክትባት ስርጭት ቅድሚያ ይሰጣቸዋል ተብሎ የነበረ ቢሆንም፣ እስካሁን ድረስ በ10 ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የጤና ባለሙያዎች የመጀመሪያውን ዙር ክትባት እንኳን እንዳልተከተቡ ቢቢሲ ባወጣው ዘገባ ገልጧል፡፡
27 ሚሊዮን የጤና ባለሙያዎችን በአባልነት የያዘው ኢንተርናሽናል ካውንስል ኦፍ ነርስስ የተባለ አለማቀፍ ቡድን ያወጣውን መረጃ ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ የጤና ባለሙያዎች ለቫይረሱ የመጋለጥ እድላቸው ከፍተኛ እንደመሆኑ ቅድሚያ ተሰጥቷቸው እንደሚከተቡ የአለም የጤና ድርጅትና መንግስታት በተደጋጋሚ ሲናገሩ ቢቆዩም በአስር ሚሊዮኖች የሚቆጠሩት ግን አሁንም መከተብ አልቻሉም፡፡
የአለም የጤና ድርጅት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ በመላው አለም በየቀኑ በአማካይ 200 ያህል የጤና ባለሙያዎች በኮሮና ሳቢያ እንደሚሞቱ መግለጹን ያስታወሰው ዘገባው፣ መንግስታት ለዚህ አደገኛ ክስተት ትኩረት አለመስጠታቸው የሚያሳዝንና እጅግ አደገኛ መሆኑን የኢንተርናሽናል ካውንስል ኦፍ ነርስስ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሆዋርድ ካተን መናገራቸውን አመልክቷል፡፡
በአለም የጤና ድርጅት የአፍሪካ ቢሮ በአህጉሪቱ በሚገኙ 38 አገራት ውስጥ 2.4 ሚሊዮን ያህል የጤና ባለሙያዎች የተለያዩ የኮሮና ቫይረስ ክትባቶችን መውሰዳቸውን እንዳስታወቀ የጠቆመው ዘገባው፣ ሁሉም የአፍሪካ የጤና ባለሙያዎች ሁለት ዙር እንዲከተቡ ተጨማሪ 66.2 ሚሊዮን ክትባቶች ያስፈልጋሉ መባሉንም አስረድቷል፡፡  
የአለም የጤና ድርጅት በአለማችን በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ ለሞት የተዳረጉ የጤና ባለሙያዎች ቁጥር ከ115 ሺህ በላይ ነው ማለቱን ያስታወሰው ዘገባው፣ ይህ ቁጥር ግን ከዚህም በእጅጉ ይበልጣል ተብሎ እንደሚገመትና በአሁኑ ወቅት በመላው አለም የጤና እንክብካቤ የሚሰጡ ባለሙያዎች ቁጥር 135 ሚሊዮን ያህል  እንደሚደርስም አክሎ ገልጧል፡፡
በሌላ የኮሮና ቫይረስ ዜና ደግሞ፣ በህንድ የተሰራ አንድ ጥናት ከአጠቃላዩ የአገሪቱ ህዝብ 67.6 በመቶ ያህሉ በኮሮና ቫይረስ በመጠቃታቸው ወይም ክትባት በመውሰዳቸው ሳቢያ ሰውነታቸው የኮሮና ቫይረስን የመቋቋም አቅም እንዳዳበረ ማረጋገጡን ዘ ጋርዲያን ዘግቧል፡፡
በአገሪቱ የተሰራው ይህ ብሔራዊ ጥናት በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ቫይረሱን የመቋቋም አቅም ማዳበራቸው ቫይረሱ ምን ያህል በማህበረሰብ ደረጃ እንደተስፋፋ ያመለክታል ማለቱን የጠቆመው ዘገባው፣ ጥናቱ ከተሰራባቸው ሰዎች መካከል 62.2 በመቶ ያህሉ የኮሮና ክትባት አለመውሰዳቸውንንም አክሎ ገልጧል፡፡
በጥናቱ በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች የሚገኙ 29 ሺህ ያህል ሰዎች መካተታቸውን የገለጸው  ዘገባው፣ 400 ሺህ ህንዳውያን የኮሮና ቫይረስን የመከላከል ተፈጥሯዊ አቅም እንዳላዳበሩና ለሶስተኛ ዙር የወረርሽኙ ማዕበል የመጋለጥ ዕድላቸው ከፍ ያለ እንደሆነ አመልክቷል፡፡ በአገረ ህንድ ባለፈው ጥር ወር ላይ በተሰራ ተመሳሳይ ጥናት ኮሮና ቫይረስን የመቋቋም አቅም ያዳበሩ ሰዎች 24 በመቶ ያህሉ ብቻ እንደነበሩም ዘገባው አስታውሷል፡፡


               በደቡብ አፍሪካ ባለፉት ሳምንታት በተከሰቱት የሁከት፣ ዝርፊያና ብጥብጥ ድርጊቶች በድምሩ 215 ሰዎች ለሞት መዳረጋቸውና እስካሁን ባለው መረጃ በአገሪቱ የደረሰው የንብረት ውድመት ከ1.38 ቢሊዮን ዶላር በላይ ይደርሳል ተብሎ እንደሚገመት ዘ ናሽናል ድረገጽ ዘግቧል፡፡
የቀድሞው የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ጃኮብ ዙማ መታሰራቸውን ሰበብ አድርጎ በተቀሰቀሰውና በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በተስፋፋው ሁከትና ብጥብጥ ከ40 ሺህ በላይ የንግድ ድርጅቶች በቀጥታ ተጠቂ መሆናቸውንና ድርጅቶቹ ዘረፋ ቃጠሎና ውድመት እንደደረሰባቸው የአገሪቱ መንግስት ማስታወቁን ኦል አፍሪካን ኒውስ ዘግቧል፡፡ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች 161 የገበያ አዳራሾችና መደብሮች፣ 11 መጋዘኖች፣ 8 ፋብሪካዎች፣ 161 የመጠጥ ማከፋፈያዎች ውድመት እንደደረሰባቸው የአገሪቱ መንግስት ባወጣው መረጃ ያስታወቀ ሲሆን፣ በሁከትና ብጥብጡ ተሳትፈዋል የተባሉ ከ2 ሺህ 500 በላይ ሰዎች መታሰራቸውንና በተወሰኑት ላይ ዝርፊያና ግድያን ጨምሮ የተለያዩ ክሶች መመስረታቸውንም አልጀዚራ ዘግቧል፡፡ ተደራራቢ የሙስና ክሶች ተመስርተውባቸው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ የሚገኘው የ79 አመቱ ጃኮብ ዙማ የተመሰረቱባቸውን ክሶች በተመለከተ ችሎት ቀርበው ምላሻቸውን እንዲሰጡ በፍርድ ቤት ጥሪ ቢደረግላቸውም፣ በተደጋጋሚ በእምቢተኝነት ፍርድ ቤት ሳይገኙ በመቅረታቸው የአገሪቱ ከፍተኛ የህገ መንግሥት ፍርድ ቤት የ15 ወራት እስር ቅጣት እንደጣለባቸውና ለእስር መዳረጋቸውን የተቃወሙ ደጋፊዎቻቸው ያስነሱት ተቃውሞ ወደ ከፋ ሁከትና ብጥብጥ ማምራቱን ባለፈው ሳምንት መዘገባችን ይታወሳል፡፡


Page 10 of 546