Administrator

Administrator

ቢጂአይ ኢትዮጵያ አብዛኛውን ወጪ ሸፍኖለታል የተባለው የቤተሰብ ፌስቲቫል በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል እየተካሄደ ነው፡፡ “በጥቅምት አንድ አጥንት” በተሰኘው በዚህ ዓመታዊ የቤተሰብ ፌስቲቫል ላይ ጥሬ ስጋ በግማሽ ዋጋ እየተቆረጠ ሲሆን፤ ቢጂአይ ኢትዮጵያ ፌስቲቫሉ የሁሉንም አቅም ያገናዘበ ይሆን ዘንድ በተለይ የጥሬ ሥጋውን ግማሽ ዋጋ ሸፍኗል ተብሏል፡፡

“የዘንድሮውን ፌስቲቫል ግማሽ ወጪ የሸፈንነው ደንበኞቻችንን ስለምናከብር ነው” ብሏል - ኩባንያው፡፡

በሴንቸሪ ፕሮሞሽንና ኤቨንትስ የተዘጋጀው የቤተሰብ ፌስቲቫል፣ ዛሬ ጠዋት ረፋድ ላይ የተከፈተ ሲሆን፤ የከተማችን 10 ታዋቂ ሥጋ ቤቶች እየተካፈሉበት ነው፡፡ በፌስቲቫሉ ላይ የቢጂአይ ምርቶች የሚቀርቡ ሲሆን፤ አንጋፋዎቹ ድምጻውያን አብነት ግርማና ፍቅር አዲስ ነቅአጥበብን ጨምሮ ሌሎችም ኹነቱን እንደሚያደምቁት ነው የተነገረው፡፡

ሴንቸሪ ፕሮሞሽንና ኤቨንትስ ፌስቲቫሉን አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ፤ ህብረተሰቡ በአንድ ቦታ ተሰባስቦ፣ አብሮ የመብላትና የመጠጣት እንዲሁም የመዝናናትና የመመካከር ባህሉን የሚያጠናክርበት ነው ብሏል፡፡

“በጥቅምት አንድ አጥንት” በሚል የሚካሄደው የቤተሰብ ፌስቲቫል ነገም እንደሚቀጥል ለማወቅ ተችሏል፡፡

በአቶ ብሉጽ ፍትዊ የተዘጋጀውና የብዙ ዓመታት ድካምና ጥረት ውጤት እንደሆነ የተነገረለት፣ የአዲስ ኪዳን ግሪክኛ - አማርኛ መዝገበ ቃላት ስራ ተጠናቅቆ ለሕትመት መበቃቱ ተገልጿል። መዝገበ ቃላቱ የግሪክ አቡጊዳ፣ ሙዳየ ቃላትና አጠቃላይ የግሪክ ቋንቋን ታሪካዊ ዳራ እንደሚያቀርብ ተነግሯል።

አቶ ብሉጽ የጤና እክል ከማረፋቸው በፊት ለዓመታት የደከሙበት የመዝገበ ቃላት ስራ የሕትመት ብርሃን ያይ ዘንድ ለገርጂ አማኑኤል ሕብረት ቤተ ክርስቲያን በአደራ እንደሰጡት የታወቀ ሲሆን፣ በዚህም መሰረት የቤተ ክርስቲያኗ አገልጋዮች ተቀብለው ተገቢውን የአርትዖትና የእርማት ሂደት በመከተል ለሕትመት ብርሃን ሊያበቁት ችለዋል። መዝገበ ቃላቱ ከ5 ሺሕ በላይ የአዲስ ኪዳን ግሪክ ቃላትን በቀጥታ ወደ አማርኛ እንደሚተረጉም፣ እንዲሁም ለእያንዳንዱ የቃል ፍቺም ተዛማጅ የአዲስ ኪዳን ክፍሎችን እንደሚያጣቅስ ለማወቅ ተችሏል።

መዝገበ ቃላቱ በኔዘርላንድ አገር በ1 ሺሕ 100 ኮፒ ብቻ እንደታተመ ተገልጿል። በ1 ሺሕ 88 ገጽ የተቀነበበው ይህ መዝገበ ቃላት በ14 ሺሕ ዩሮ ወጪ እንደታተመ ተመላክቷል።

የግሪክ አቡጊዳ፣ ሙዳየ ቃላትና አጠቃላይ የግሪክ ቋንቋን ታሪካዊ ዳራ እንደሚያቀርብ ሲጠቀስ፣ ይህም በኢትዮጵያ የመዝገበ ቃላት ሕትመት ታሪክ ውስጥ በዓይነቱ ልዩና የመጀመሪያ እንደሚያደርገው ነው የታወቀው። ሰኞ ጥቅምት 25 ቀን 2017 ዓ.ም. ከ10:00 ጀምሮ በስካይላይት ሆቴል በሚካሄደው የምረቃ መርሃ ግብር የቤተ ዕምነት መሪዎች፣ የቤተ ክርስቲያን መጋቢዎች፣ የነገረ መለኮትና ልዩ ልዩ የከፍተኛ ትምሕርት ተቋማት አመራሮች እንዲሁም የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ተወካዮችን ጨምሮ ከ 1 ሺሕ 500 በላይ እንግዶች በተገኙበት ይከናወናል።

የምረቃ መርሃ ግብሩ በበርካታ የሚዲያ አካላት የሚዘገብ ሲሆን፣ በቀጥታ ሰርጭትም ለተመልካቾች እንደሚተላለፍ ለማወቅ ተችሏል።

ፒ ኤም ጂ ኤቨንትስ በአይነቱ ልዩና ደማቅ የሆነውን የአመቱ ትልቅ ኮንሰርት - ”አይዞን“ ያዘጋጀላችሁ ሲሆን፤ በእለቱም በሀገራችን ኢትዮጵያ አንጋፋ የሆኑት የአመቱን ምርጥ አልበም ያወጣው በብዙዎች ዘንድ የሚወደደው
አብዱኪያር የተለያዩ ተወዳጅ ስራዎቹን ሲያቀርብልን፣
እንዲሁም ተወዳጁና ተናፋቂው የሃገራችን ኮከብ
ናቲ ማን ከረጅም የናፍቆት አመታት በኋላ ስራዎቹን ያቀርባል።

የተለያዩ ምግብና መጠጦች የሚኖሩ ሲሆን፤ ይህ ደማቅ አዝናኝ ምሽት እንዳያመልጣችሁ
ቀን ፦ ጥቅምት 16/ 2017 ዓ.ም
በሮች ከ 10:00 ጀምሮ ክፍት ይሆናሉ የመግቢያ ዋጋ ፦ ለመደበኛ 600 ብር፣ በር ላይ 800 ብር፣ ለቪአይፒ ደግሞ 2000 ብር
ትኬቶችን በሚሊንየም አዳራሽ፣ ቦሌ ፍሬንድሺፕ በሚገኘው ቻካ ኮፊ፣ 22 በሚገኘው ቻካ ኮፊ፣ ፊሊ ኮፊ ሜክሲኮ፣ አትላስ ቸሩ መድሀኒአለም፣ ይማና ክትፎ እንዲሁም ቴሌ ብር ላይ ማግኘት ትችላላችሁ።
ፒ ኤም ጂ ኤቨንትስ

በኢትዮጵያ ሕገ-ወጥ የሕጻናት ዝውውር፣ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

ሚኒስቴሩ ይህን ያስታወቀው፣ ከደቡብ የአገሪቱ ክፍል ወደ መሐል አገር በሚደረገው የሕጻናት ፍልሰት ዙሪያ ያስጠናውን ጥናት መሰረት አድርጎ ነው፡፡

ወደ መሀል ከተማ የሚፈልሱ ሕጻናት ቁጥር ከፍተኛ መሆኑን፣ በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ሕገ-ወጥ የሕጻናት ዝውውር ቁጥጥር ኃላፊ አቶ በለጠ ሰውአለ ለአሐዱ ሬዲዮ ተናግረዋል፡፡

ኃላፊው ሕጻናቱ የሚፈልሱበትን ምክንያት ሲያስረዱ፤ በዋናነት በክልሉ እየተባባባሰ የመጣው ድህነትና ሥራ ማጣት ነው ብለዋል፡፡ በደቡብ የተዘረጋ ሕገ-ወጥ የደላሎች መስመር መኖሩንም ጠቁመዋል፡፡

ሆኖም መንግሥት ይህንን እንቅስቃሴ ለመግታት፣ ክልሎችን ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍል በሕጻናት ፍልሰታ ላይ ከሚሰሩ ተቋማት ጋር እየመከረበት መሆኑን ገልጸዋል።

ኃላፊው አክለውም፤ የሕጻናት ዝውውርን ለመቆጣጠር በአገር አቀፍ ደረጃ መመርያ ወጥቶለት ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴዎችን እየተደረጉ ቢሆንም፣ በአፈፃፀሙ ረገድ ክፍተቶችን መኖራቸውን አልሸሸጉም፡፡

ደቡብ ኢትዮጵያ የአገሪቱ ክፍልን ጨምሮ ከተለያዩ አቅጣጫዎች የሚነሱ ህፃናት መዳረሻቸውን አዲስ አበባ እንደሚያደርጉ፣ ከሚኒስቴር መስርያ ቤቱ ያገኘነውን መረጃ ያመለክታል፡፡

የትምህርት ሚኒስቴር በ2016 የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ማጠቃለያ ፈተና ወስደው የማለፊያ ውጤት ላመጡ ተማሪዎች፣ የዩኒቨርሲቲ ምደባዎችን ይፋ አድርጓል።

እነዚህ ተማሪዎች በሚኒስቴሩ መደበኛ መርሃ ግብር፣ በመንግስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እንዲመደቡ ተደርጓል።

ተማሪዎች ምደባቸውን በሚከተሉት የማህበራዊ መድረኮች ማረጋገጥ እንደሚችሉ ተጠቁሟል።
በድረ ገጽ፡- https://placement.ethernet.edu.et
በቴሌግራም፡-https://t.me/moestudentbot

የኤርትራ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ 3.7 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት የረጅም ጊዜ ዕዳውን እንዲከፍል ጠየቀ፡፡

የኤርትራ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን በጻፈው ደብዳቤ፣ ይህ ዕዳ ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ የቆየ መሆኑን አሰታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ወደ ኤርትራ የሚያደርገውን በረራ ያቆመው ከኢትዮ- ኤርትራ ጦርነት በፊት ነበር፡፡ በኤርትራ ሲቪል አቪዬሽን እየተጠየቀ ያለው ክፍያ እ.ኤ.አ የ1997/1998 ዓ.ም ነው ተብሏል።

ይህን ተከትሎም፣ የኤርትራ መንግስት፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ኤርትራ ውስጥ በሚገኝ ፍርድ ቤት መክሰሱን ለማወቅ ተችሏል፡፡

የኤርትራ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን፣ አየር መንገዱ በኤርትራ የሚያደርገውን በረራ እስከ ሴፕቴምበር 30/ 2024 እንዲያቆም የሰጠውን የጊዜ ገደብ ተከትሎ፣ አየር መንገዱ ባለፈው ወር፣ በረራውን ማቆሙ ይታወቃል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሃላፊዎች ባለፈው ወር በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ የገንዘቡን መጠን ሳይጠቅሱ፣ የኤርትራ መንግስት፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዕዳ እንዳለበት ገልጸው ነበር፤ የገንዘቡን መጠን ሳይገልጹ።

የኤርትራ መንግሥት፣ ለአየር መንገዱ መክፈል ያለበት የ3 ሚሊዮን ዶላር ዕዳ እንዳለበት ተነግሯል፡፡

ኤስ ኦ ኤስ የሕጻናት መንደሮች በኢትዮጵያ በጀቱን ከውጭ ለጋሾች ሳያመጣ በአገር ውስጥ በሚያሰባስበው ገንዘብ ራሱን የማስተዳደር ዕቅድ እንዳለው ገልጿል። ዛሬ ጥቅምት 12 ቀን 2017 ዓ.ም. ድርጅቱ በኢትዮጵያ ስራ የጀመረበትን 50ኛ ዓመት ክብረ በዓል የማጠናቀቂያ መርሃ ግብር በሸራተን አዲስ ሆቴል አካሂዷል።

በዚሁ መርሃ ግብር ላይ በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ የኤስ ኦ ኤስ የሕጻናት መንደሮች ምስራቃዊና ደቡባዊ አፍሪካ ክልል ምክትል ዳይሬክተር አቶ በድሉ ሸገን የዓለም አቀፉን ኤስ ኦ ኤስ የሕጻናት መንደሮች ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንትን እንዲሁም የራሳቸውን መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን፣ በንግግራቸውም ድርጅቱን “ኤስ ኦ ኤስ የሕጻናት መንደሮች በኢትዮጵያ በተደራሽ ቁጥርም ሆነ በፕሮግራም አፈፃፀም የተዋጣለት ስራ በመስራት በምስራቃዊና ደቡባዊ አፍሪካ ክልል ውስጥ ካሉት የኤስ ኦ ኤስ ፕሮግራሞች መካከል የመሪነቱን ስፍራ ይዞ የዘለቀ ጠንካራ ድርጅት” ሲሉ ገልጸውታል።

በዚሁ መግለጫ ላይ በአስር ዓመት ውሰጥ “በጀቴን ከውጭ አገር ሳላመጣ፣ አዚሁ በአገር ውስጥ ገንዘብ አሰባስቤ ራሴን በራሴ የማስተዳደር ዕቅድ አለኝ” ብሏል፣ ኤስ ኦ ኤስ።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ በተወካያቸው በኩል ባሰተላለፉት መልዕክት የድርጀቱን 50 ዓመታት ጉዞ አድንቀው፣ ይህ ጠንካራ የልማት አጋርነት በቀጣይም የበለጠ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል።

የኤስ ኦ ኤስ ስዊዘርላንድ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ሚስተር አሌክስ ደ ጊዩስ በበኩላቸው፣ ድርጅታቸው ከዚህ በፊት የገንዘብ እንዲሁም የቴክኒክ ድጋፍ እንዳበረከተ አስታውሰው፣ ይህም ትብብርና ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
የኤስ ኦ ኤስ የሕጻናት መንደሮች በኢትዮጵያ በ50 ዓመታት የበጎ ተጽዕኖ ጉዞው 8 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሰዎችን መድረስ እንደቻለ Global Exceptional Excellence Consultancy የተባለው ድርጅት ያደረገው ጥናት ያመለክታል።

ኤስ ኦ ኤስ የሕጻናት መንደሮች በኢትዮጵያ የዓለም አቀፉ ኤስ ኦ ኤስ የህጻናት መንደሮች ፌዴሬሽን ብሔራዊ አባል የሆነ በሕጻናት ደሕንነት ጥበቃና ልማት ላይ አተኩሮ የሚሰራ ዓለም አቀፍ የልማት ድርጅት ነው፡፡

ላለፉት ሦስት አስርት ዓመታት የሼህ-መሐመድ አል-አሙዲ የቅርብ ወዳጅና የቢዝነስ ሸሪክ የነበሩት አቶ አብነት ገ/መስቀል ፣ ለሼህ አል-አሙዲ 852 ሚሊዮን ብር እንዲከፍሉ ፍ/ቤት ትዕዛዝ ሰጠ፡፡

ሼህ መሐመድ አል-አሙዲ፣ አቶ አብነት ገ/መስቀል፣ ለብልጽግና ፓርቲ ያለፈቃዴ “ሰጥተውብኛል” ያሉትን 75 ሚሊዮን ብር ጨምሮ፣ ለተለያዩ መንግስታዊ ተቋማት የተለገሰውን ከ800 ሚሊዮን ብር በላይ አቶ አብነት “ይመልስልኝ” ሲሉ ክስ መስርተው ሲከራከሩ ቆይተዋል፡፡

ክሱን ሲመለከት የቆየው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት፣ ጥቅምት 5 ቀን 2017 ዓ.ም በዋለው ችሎት፣ አቶ አብነት 852 ሚሊየን ብር ከነወለዱ እንዲከፍሉ ውሳኔ መስጠቱን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ሼህ መሃመድ አሊ አል-አሙዲ፣ የናሽናል ኦይል ኢትዮጵያ ኩባንያ ላይ፣ ከ2004 እስከ 2013 ዓ.ም. ድረስ ከነበራቸው 70 በመቶ የአክስዮን ድርሻ፣ ከ850 ሚሊዮን ብር በላይ የሚሆነው፣ ተወካያቸው በነበሩት አቶ አብነት ገብረመስቀል የባንክ ሂሳብ ላይ ገቢ ሲደረግ ነበር ይላል፤ የፍርድ ቤት ሰነዱ።

የሼህ አልአሙዲ ድርሻም፣ በአቶ አብነት በኩል ብልጽግና ፓርቲን ጨምሮ ለበርካታ የመንግሥት ተቋማትና ባለሥልጣናት በስጦታ መልኩ መለገሱ በሰነዱ ላይ ተጠቁሟል፡፡ ሆኖም አል-አሙዲ አቶ አብነትን ገንዘቡን በስጦታ ለመለገስ አልወከልኩህምና፣ ገንዘቡን መልስልኝ ሲሉ በፍ/ቤት ከሰው ሲከራከሩ ነበር።
የክስ መዝገቡ እንደሚለውም፤ የናሽናል ኦይል ኢትዮጵያ ኩባንያ፣ ከ2004 እስከ 2013 ዓ.ም ድረስ ካተረፈው ትርፍ ላይ፣ ለአልአሙዲ ይደርሳቸዋል ተብሎ በኩባንያው ከተረጋገጠው አጠቃላይ የትርፍ ድርሻ ውስጥ፣ በአቶ አብነት የባንክ ሂሳብ 852 ሚሊዮን 462ሺ 650 ብር ገቢ ተደርጓል።
በሰነዱ መሰረት፤ ከዚህ ገንዘብ ውስጥ፣ ከ581 ሚሊዮን ብር በላይ የመንግሥት ተቋማትን ጨምሮ ለመንግሥት ባለሥልጣናት፣ በሼኽ አልአሙዲ ፍቃደኝነት ከአቶ አብነት የባንክ ሂሳብ ተከፍሏል። ከዚህ የብር መጠን ውስጥም፣ ለብልጽግና ፓርቲ 75 ሚሊዮን ብር መከፈሉን የሚጠቅሰው የፍርድ ቤት ሰነዱ፤ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ማህበራዊ ዋስትና ፈንድ 120 ሚሊዮን ብር፣ ለፌደራል ፖሊስ 5 ሚሊዮን ብር እና ለኢንፎርሜሽን ደኅንነት መረብ ኤጀንሲ 7 ሚሊዮን ብር መሰጠቱን ያመለክታል፡፡

እነዚህና ሌሎች በሰነዱ የተጠቀሱትን ክፍያዎች አስመልክቶም፣ ሼህ ዓሊ አል-አሙዲ፣ አቶ አብነትን የወከልኩት ስጦታ እንዲሰጥልኝ አይደለም ሲሉ፣ እነዚህን ክፍያዎች ይመልስልኝ ሲሉ ተሟግተዋል። የፍርድ ቤቱ ሰነዶች እንደጠቆሙት፤ ተከሳሹ አቶ አብነት ገ/መስቀል፣ እነዚህን ክፍያዎች ወጪ ያደረኩት በተሰጠኝ ውክልና በመሆኑ፣ ልከሰስ አይገባም ሲሉ ተከራክረዋል።

ክሱን ሲመለከት የቆየው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤትም፣ አቶ አብነት ለብልፅግና ፓርቲ የተከፈለውን 75 ሚሊዮን ብር ጨምሮ፣ በክሱ የተዘረዘሩትን ክፍያዎች ሲከፍሉ፣ ለአል-አሙዲ ጥቅም ያልተፈጸሙ በመሆናቸው፣ ተከሳሹ አቶ አብነት ገ/መስቀል የተከሰሱበትን 852ሚ462ሺ650 ብር ለአል-አሙዲ እንዲከፍሉ ትዕዛዝ በመስጠት መዝገቡን ዘግቷል፡፡

ረቡዕ ጥቅምት 20 ከቀኑ 11 ሰዓት በዋልያ መጻሕፍት ታጋብዛችኋል።

"ክንፋም ከዋክብት" ቅጽ አንድ የግጥም መጽሐፍ ነገ ቅዳሜ ጥቅምት 16 ቀን 2017 ዓ.ም ከቀኑ 10:00 ጀምሮ አራት ኪሎ በሚገኘው ዋልያ መጻሕፍት ውስጥ ይመረቃል።

Page 9 of 740