Administrator

Administrator

Monday, 23 December 2013 09:58

እቴጌ ጠየቁ

አዲስ ሐሳብ አፈለቁ ሳይደብቁ
        የኔ ምኒልክ ይስሙኝ
        ይህን ውብ ቦታ አገር ስጡኝ
        ቤት ልሥራ ጌታዬ ባፋጣኝ
        ይህችን አዲስ አደይ አበባ አዩልኝ
    የፍንፍኔ ውበት አይሎ
    የጣይቱስ ያገር ጥያቄ መች ተዘሎ
ሕይወት አገር አበባ
በፍል ውኃ ዳርቻ ተገነባ
ይህች አደይ አበባ
ስመ ውልደቷ በዓለም ዙሪያ አስተጋባ
የእኛይቱ ውብ አዲስ አበባ
እንሆ የኔ ውብ ጣይቱ
ቤት ሥሪና ያንቺ ትሁን አገሪቱ
በማለት
    ምኒልክ ለጣይቱ መረቋት
    በፍቅር ቃለ አንደበት ለገሷት
ይኸው የምኒልክ በረከት
የጣይቱ ልብ ምርኮ መሠረት
ሕዝብ ከቶባት ሕዝብ ገንብቷት
    የአፍሪከ አንድነት መዲና አለኝታ
    የዓለም ሰላም መድረክ መከታ
    የአገር ኤኮኖሚ የአገር ፖለቲካ ዋልታ
    እናት አዲስ አበባ ውብ አገር ውብ ስጦታ
ገ.ክ.ኃ




በተሰማሩበት መስክ ጉልህ ስራ ሰርተዋል፣ የላቀ ውጤት አስመዝግበዋል፣ ብዙዎችን ተጠቃሚ አድርገዋል፣ ሃያልነታቸውንም አስመስክረዋል ያላቸውን የአለማችን ሴቶች በየአመቱ የሚመርጠው ታዋቂው ፎርብስ መጽሄት፣ ዘንድሮም የ2013ን የአለማችን 100 ሃያላን ሴቶች ዝርዝር ይፋ አድርጓል፡፡
ፎርብስ በመላ አለም ከሚገኙ የተለያዩ አገራት ከመረጣቸው 100 የአመቱ ሃያላን ሴቶች መካከል፣ የቀለም ልዩነት ሳይበግራቸው ጉልህ ስራ ሰርተዋል፣ የጥቁር ሴቶች የስኬታማነት ተምሳሌት ሆነዋል ብሎ በዝርዝሩ ውስጥ ያካተታቸው ጥቁር ሴቶች አስራ አንድ ብቻ ናቸው፡፡ ከአስራ አንዱ ጥቁር ሃያላን ሴቶች መካከልም፣ ከአፍሪካ አህጉር የተመረጡት ሶስት ብቻ ናቸው፡፡
ፖለቲከኞችን፣ የኩባንያ ስራ አስኪያጆችን፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ሃላፊዎችን፣ የመንግስት ባለስልጣናትንና በሌሎች መስኮች የተሰማሩ ሴቶችን የያዘው የፎርብስ የአመቱ ምርጥ ሃያላን ሴቶች ዝርዝር ከጥቁር ሴቶች መካከል በቀዳሚነት ያስቀመጠው ቀዳማዊ እመቤት ሚሼል ኦባማን ነው፡፡
ፎርብስ ሚሼል ኦባማን የመረጠው፣ በቀዳማዊ እመቤትነቷ በመጠቀም ህጻናትን ከመጠን በላይ ከሆነ ክብደት ለመታደግና ጤናማ አኗኗርና አመጋገብን ለማስፋፋት በምታደርገው ጥረት ነው፡፡ ሚሼል ከባራክ ኦባማ ጋር ሲነጻጸር በአሜሪካውያን ዘንድ የበለጠ ተወዳጅነት እንዳላቸው የገለጸው የፎርብስ መረጃ፣ ከአጠቃላዩ የአሜሪካ ህዝብ 67 በመቶ የሚሆነው ከባራክ ኦባማ ይልቅ ለሚሼል ጥሩ አመለካከት እንዳለው ያሳያል፡፡
በሃያላኑ ጥቁር ሴቶች ዝርዝር ውስጥ የተካተተችው ሌላዋ አፍሪካ አሜሪካዊት ደግሞ ኦፕራ ዊንፍሬይ ናት፡፡ ለ25 አመታት ስትመራው በነበረው ኦፕራ ሾው የተባለ ፕሮግራም አለማቀፍ ዝናን ያተረፈችው ኦፕራ፣ በሃብት መጠን ቀዳሚዋ አፍሪካ አሜሪካዊት መሆኗንም ፎርብስ ጠቅሷል፡፡ አዲስ ያቀዋቀዋመችው ዘ ኦፕራ ዊንፍሬይ ኔትዎርክ የተሰኘ የቴሌቪዥን ጣቢያ ባለፈው አመት ብቻ 83 ሚሊዮን ተመዝጋቢ ተመልካች ቤተሰቦችን ለማግኘት በቅቷል። ኦፕራ በበጎ አድራጎት ስራ ስማቸው ጎልቶ ከሚጠራ የአለማችን ለጋስ ሴቶች አንዷ ስትሆን፣ እስከ አሁን ድረስ ከ400 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ ገንዘብ ለበጎ አድራጎት ስራ አበርክታለች፡፡
የዜሮክስ ኩባንያ ዋና ስራ አስፈጻሚ የሆነችው አሜሪካዊቷ ኡርሱላ በርንስ፣ ኩባንያውን ከማተሚያ መሳሪያ አምራችነት፣ ጠቅላላ አገልግሎቶችን ወደሚሰጥ ግዙፍ ኩባንያነት አሳድጋለች በሚል ነው በሃያላኑ ዝርዝር ውስጥ የተካተተችው፡፡ እ.ኤ.አ በ1980 በተለማማጅ ሰራተኛነት ዜሮክስ ኩባንያን የተቀላቀለችው ኡርሱላ በርንስ፣ በሜካኒካል ኢንጂነሪንግ ከኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ ሁለተኛ ዲግሪዋን መመረቋን ተከትሎ በቀጣዩ አመት የኩባንያው መደበኛ ሰራተኛ ሆና ተቀጥራለች። በስራዋ ውጤታማ በመሆኗ እ.ኤ.አ በ2000 የኩባንያው ምክትል ፕሬዚዳንት ተደርጋ ተሹማለች፡፡ ይህቺው ታታሪ ሰራተኛ እ.ኤ.አ በ2009 የዜሮክስ ዋና ስራ አስፈጻሚ ከሆነች በኋላም፣ የበለጠ ውጤታማ ስራ በማከናወኗና ኩባንያውን ወደተሻለ ትርፋማነት በማሸጋገሯ ነው፣ ፎርብስ ከሃያላኑ ጎራ የቀላቀላት፡፡
ሌላዋ የፎርብስ የአመቱ ሀያል ሴት አሜሪካዊቷ ድምጻዊት ቢዮንሴ ኖውልስ ናት፡፡ ፎርብስ እንዳለው፣ ቢዮንሴ በሙዚቃ ስራዎቿ ከምታገኘው በሚሊዮን የሚቆጠር ገቢ በተጨማሪ፣ ሀውስ ኦፍ ዴሪዮን በሚል ስያሜ ባቋቋመችው የአልባሳት አምራች ኩባንያዋም ከፍተኛ ትርፍ ማካበቷን ቀጥላለች፡፡
ከፔፕሲ ጋር የፈጸመችው የማስታወቂያና የኮንሰርት ስምምነት 50 ሚሊዮን ዶላር ያሳፈሳት ቢዮንሴ፣ የምንጊዜም ምርጥ ሽያጭ ካስመዘገቡ የአለማችን ታዋቂ ድምጻውያን ተርታ የምትመደብ ሲሆን 17 የግራሚ ሽልማቶችንም ተቀብላለች፡፡ ከወራት በፊት በተዘጋጀ የሱፐር ቦውል የሙዚቃ ዝግጅት ላይ ያቀረበችው የ15 ደቂቃ ሙዚቃዋን በአለም ዙሪያ የሚገኙ ከ104 ሚሊዮን በላይ ተመልካቾች እንደተመለከቱት የሚጠቅሰው የፎርብስ መረጃ፣ ድምጻዊቷ በአለም ዙሪያ ያላትን ተቀባይነት የበለጠ እያሳደገች መምጣቷ በሃያልነት እንዳስመረጣት ይናገራል፡፡
የታዋቂው ዎልማርት ኩባንያና ከአሜሪካ ታላላቅ የንግድ ኩባንያዎች አንዱ የሆነው የሳምስ ክለብ ፕሬዚዳንትና ዋና ስራ አስፈጻሚ በመሆን የሰራችው ሮዛሊንድ ብሪዌርም ሌላዋ የፎርብስ የአመቱ ሀያል ጥቁር ሴት ናት፡፡ ባለፈው አመት ጥር ወር ላይ የሳምስ መሪ ሆና የተመረጠችው ብሪዌር፣ ለኩባንያው ትርፋማነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቷ ይነገራል። እ.ኤ.አ በ2006 ዎልማርትን በመቀላቀል ዋና ስራ አስፈጻሚ ሆና ያከናወነቻቸው ስራዎቿ ኩባንያውን ማሳደግ፣ የእሷን ጥንካሬም ማስመስከር የቻሉ በመሆናቸው በሃያላኑ ዝርዝር ውስጥ መካተቷን ፎርብስ ተናግሯል፡፡
አፍሪካን የጥቁር ሃያላን ሴቶች እናት አድርገው ካስጠቀሷት ሶስት የአመቱ የፎርብስ ሃያላን ሴቶች መካከል፣ የማላዊ ፕሬዚዳንት ጆይስ ባንዳ አንዷ ናት። የአገሪቱ የመጀመሪያዋ ሴት ፕሬዚዳንት በመሆን ወደ መሪነት የመጣችው ጆይስ ባንዳ፣ የመጀመሪያዎቹን የስልጣን አመታት ከአለማቀፉ ማህበረሰብ እርዳታ በማሰባሰብና አገሪቱን ከሚፈታተናት የዋጋ ግሽበት ጋር በመታገል ነበር ያሳለፈቻቸው፡፡
ጆይስ ባንዳ ከአጠቃላይ አመታዊ ገቢዋ 40 በመቶ ያህሉን ከውጭ እርዳታ የምታገኘውን ይህቺን ድሃ አፍሪካዊት ሀገር ከገንዘብ ዕጦት ለመታደግ፣ በአለም ዙሪያ እየተንቀሳቀሰች የገንዘብ ተቋማትን በማሳመን ስራ ተጠምዳ እንደኖረች ፎርብስ ተናግሯል፡፡ ባንዳ ያለፉት መንግስታት አያደርጉ አድርገዋት የሄዷትን ማላዊ እንድታገግምና ራሷን ችላ እንድትቆም ለማስቻል እያደረገችው የምትገኘው ተጠቃሽ ጥረት የፎርብስን ሚዛን በመድፋቱ ከሃያላኑ ጎራ ተቀላቅላለች፡፡
የአፍሪካ የመጀመሪያዋ ሴት ፕሬዚዳንትና እ.ኤ.አ የ2011 የኖቬል የሰላም ተሸላሚዋ ሊይቤሪያ ፕሬዚዳንት ኤለን ጆንሰን ሰርሊፍ፣ የአፍሪካን ሴቶች ሃያልነት ያስመሰከረች ሌላኛዋ የፎርብስ ምርጥ ናት። በሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርቷን የተከታተለችው ኤለን ጆንሰን ሰርሊፍ፣ የላይቤሪያን የእርስ በርስ ግጭት በሰላማዊ ድርድርና መግባባት ለመቋጨት ከመቻሏ በተጨማሪ፣ አለማቀፍ አበዳሪዎች የዕዳ ስረዛ እንዲያደርጉ በማግባባት ረገድ የሰራቻቸው ስራዎችም ጠንካራና ስኬታማ ሴትነቷን ያስመሰክራሉ ብሏል ፎርብስ፡፡
ፎርብስ የአመቱ ሃያል ሴት ብሎ የጠቀሳት ሌላዋ አፍሪካዊት፣ የናይጀሪያ የፋይናንስ ሚንስትርና የኢኮኖሚ አስተባባሪ ሚንስትር ንጎዚ ኦኮንጆ ኢዌላ ናት፡፡ ኢዌላ በአለም ባንክ የነበራትን የማኔጂንግ ዳይሬክተርነት ስራ ለቅቃ፣ እ.ኤ.አ ከ2011 በሚንስትርነት ከተሸመች በኋላ ተጠቃሽ ስራ መስራቷን የጠቀሰው የፎርብስ መረጃ፣ በቀጣዩ አመት የአገሪቱ ኢኮኖሚ 6.5 በመቶ እድገት እንዲያሳይ የእሷ አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ያሳያል፡፡ እ.ኤ.አ ከ2003 እስከ 2006 በአገሯ ናይጀሪያ የኢኮኖሚ አማካሪ ሆና ትሰራ የነበረው ኢዌላ፣ አበዳሪዎች የናይጀሪያን 18 ቢሊዮን ዶላር ዕዳ እንዲሰርዙ በማስቻል ረገድ ተጠቃሽ ስራ መስራቷ ይነገራል፡፡
ከፎርብስ የአመቱ ሃያላን ጥቁር ሴቶች ዝርዝር ውስጥ የተካተተችዋ ሌላኛዋ ትጉህ ደግሞ፣ እ.ኤ.አ በ2012 የአለም የምግብ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር ሆና የተመረጠችው አሜሪካዊቷ ኤርታሪን ኮሲን ናት።
ድርጅቱ በአለም ዙሪያ በሚገኙ 78 የተለያዩ አገራት ከርሃብ፣ የምግብ ዋስትናና የምግብ እጥረት ጋር  በተያያዘ የሚሰራውን ሰፊ ስራ በአግባቡ የመምራትና በስሯ የሚገኙ ከ15ሺህ በላይ ሰራተኞችን በወጉ የማስተዳደር ታላቅ ሃላፊነት የተጣለባት ኮሲን፣ ውጤታማ ስራ ማከናወኗን ፎርብስ ይመሰክራል፡፡ የመጀመሪያውን አመት በምዕራብ አፍሪካ በድርቅ፣ በሶሪያ ደግሞ በእርስበርስ ጦርነት ሳቢያ የተከሰተውን ርሃብ ለማሰወገድ ትኩረት ሰጥታ በመስራት ያሳለፈችው ኮሲን፣ በቀጣይም ከምግብ እርዳታ ወደ ራስን ማስቻል የሚደረገውን ሽግግር በመምራት ተጠቃሽ ስራ ማከናወኗን ፎርብስ ዘግቧል፡፡
በሃያላኑ ዝርዝር ውስጥ ለመቀላቀል የቻለችው ሌላዋ አሜሪካዊት፣ የኬር ዩኤስኤ ፕሬዚደንትና ዋና ስራ አስፈጻሚ ሄለን ጋይሌ ናት፡፡ እ.ኤ.አ በ2006  የኬር ዩኤስኤ ፕሬዚደንትና ዋና ስራ አስፈጻሚ ሆና የተሸመችው ሄለን፣ በ87 የአለም አገራት ድህነትን ለመዋጋት የሚከናወኑ ስራዎችን በአግባቡ መምራቷ ይነገርላታል፡፡
በቻድ፣ ኒጀር፣ ማላዊና ሌሎች የአፍሪካ አገራት ከ750 ሺህ በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ያደረጉ የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ፣ የምግብና የንጹህ የውሃ መጠጥ አቅርቦት ስራዎችን አከናውናለች፡፡
እ.ኤ.አ በ2003 ሮበርት ውድ ጆንሰን ፋውንዴሽን የተባለው የአሜሪካ ትልቁ የጤና ክብካቤ ተቋም ፕሬዚደንትና ዋና ስራ አስፈጻሚ ሆና የተመረጠችው ሪዛ ላቪዞ ሙርኒ፣ ሌላኛዋ የፎርብስ የአመቱ ሃያል ጥቁር ሴት ናት፡፡ ፋውንዴሽኑን ለአመታት በስኬታማነት መምራቷ የሚነገርላት ሙርኒ፣ ተቋሙን በመምራት የመጀመሪያዋ ሴት እንዲሁም የመጀመሪያዋ አፍሪካ አሜሪካዊ ናት፡፡

ምእመናን ለሚከፍሉትና ለሚሰጡት ገንዘብ ደረሰኝ የመጠየቅ ልማድ ሊኖራቸው ይገባል
ድብቅ ሙዳየ ምጽዋት ማስቀመጥ፣ በዣንጥላና በምንጣፍ ገንዘብ መለመን ይከለከላል

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ገዳማት፣ አድባራትና አብያተ ክርስቲያናት የካሽ ሬጅስተር ማሽንን ለገቢ መሰብሰቢያነት ለመጠቀም  ቅድመ ዝግጅት እያደረጉ እንደሆነ ተገለጸ፡፡
ዘመኑን ያልዋጀውንና ጥራት የጎደለውን፣ ለሙስናና ብክነት የተጋለጠውን የቤተ ክርስቲያኒቱን የፋይናንስ አሠራርና ቁጥጥር ችግር፤ ግልጽነት፣ ወጥነት፣ ተቀባይነትና ተጠያቂነት ባለው የፋይናንስ አያያዝ ሥርዐት ለመቅረፍና ለማድረቅ ያስችላል፤ በሚል በቀረበው የሀገረ ስብከቱ የሒሳብ አያያዝ ፖሊሲና ዝርዝር የአፈጻጸም መመሪያ ረቂቅ ላይ እንደተጠቀሰው÷ በማንኛውም መንገድ የተሰበሰበ ገንዘብ፣ ሕጋዊ የገቢ መሰብሰቢያ ደረሰኝ ወዲያውኑ ሊቆረጥለት የሚገባ ሲኾን ይህም በዋናነት በካሽ ሬጅስትር ማሽን እንደሚከናወን ተመልክቷል፡፡
የሀ/ስብከቱ አብያተ ክርስቲያናት የካሽ ሬጅስተር ማሽን ተጠቃሚ መኾናቸው፣ በገቢ ሒሳብ አሠራርና ቁጥጥር እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን ለመከላከል ያስችላል ተብሏል፡፡ በጥናቱ ላይ በመነሻነት ከተዘረዘሩት ችግሮች መካከል የዕለት ገቢዎችና ደረሰኝ አጠቃቀም ተጠቅሷል።  የቤተ ክርስቲያኒቱን የገንዘብ ገቢ ሰነዶች በሕገ ወጥ መንገድ አሳትሞ በቤተ ክርስቲያኒቱ ስም ለግል ገንዘብ ይሰበሰባል፤ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የተከለከለ ደረሰኝ ጥቅም ላይ የሚውልበት አጋጣሚ ታይቷል፤ ከደረሰኙ /ለከፋዩ ከሚሰጠው/ የተለየ መጠን በቀሪው ላይ መጻፍና የግል ጥቅምን ማካበት ይዘወተራል፤ ዘወትርና በክብረ በዓላት በርካታ ገንዘብ ገቢ ቢኾንም በዕለቱ ወደ ባንክ ያለማስገባት ኹኔታ አለ፤ ምእመናን ለሚከፍሉትና ለሚሰጡት ገንዘብ ደረሰኝ የመቀበል ልማድ የሌላቸው መኾኑን እንደክፍተት በመጠቀም፣ ለቤተ ክርስቲያን የመጣው ገንዘብ ‹‹በየመንገዱ እየተንጠባጠበ ወፎች የሚለቃቅሙት ይበዛል››፣ በሥራ ላይ ያልዋሉ የገንዘብ ገቢና ወጪ ሰነዶች (ሞዴላሞዴሎች ሴሪ ንምራ ቁጥር) መሠረታዊ ችግር ተጠንቶ መፍትሔ አልተሰጠም፡፡
በንግሥ፣ በወርኃዊ በዓላትና በዕለተ ሰንበት በሙዳየ ምጽዋት ሳይኾን በተዘረጋ ጨርቅ ላይ የሚሰበሰብ ገንዘብ መኖሩን የሚጠቅሰው ጥናቱ፤ በዚህ መልክ የተሰበሰበው ገንዘብ ሀ/ስብከቱ በታኅሣሥ፣ 2003 ዓ.ም. ባስተላለፈው የገንዘብ ቆጠራ፣ የንብረት አመዘጋገብና አጠባበቅ የሥራ መመሪያ መሠረት/ የምእመናንና ካህናት ሰበካ ጉባኤ ተወካዮች በሙሉ በተገኙበት ቆጠራ የማይካሄድበትና በተወሰነ መልኩም ሙሉ ገንዘቡ ገቢ የማይደረግበት ኹኔታ በመኖሩ አሠራሩ ለብኩንነት፣ ሐሜትና አሉባልታ መጋለጡን አመልክቷል፡፡ በንግሥ በዓላት ወቅት ጥላ ዘቅዝቀው የሚለምኑ ሰዎች ኹሉም ስለማይታወቁ የተኣማኒነት ችግር አለ፡፡ በስእለትና በሙዳየ ምጽዋት በውጭ ምንዛሬ የሚገቡ የውጭ ሀገር ገንዘቦች፣ በመመሪያው መሠረት በዕለቱ የባንክ ምንዛሬ ወደ ብር እየተቀየሩ በተገቢው መንገድ ገቢ አለመኾናቸው፣ በምትኩ ቅያሬው ወጥነት ያለውና ለብኩንነት የተጋለጠ እንደኾነም ተገልጿል፡፡
በቃለ ዐዋዲ ድንጋጌው የተመለከተውንና በዝርዝር የሥራ መመሪያ የተላለፈውን የገቢ አሰባሰብ በተሻለ አሠራር ያጠናክራል የተባለው በፖሊሲና መመሪያ ረቂቁ የሒሳብ ሰነዶች አያያዝ፣ ምዝገባና አወጋገድ መሠረት÷ ለሒሳብ ሥራ የሚያገለግሉ ደረሰኞችና ቫውቸሮች የዋና ተጠቃሚውን ተቋም ስም ይዘው፣ በሀገረ ስብከቱ ምስጢራዊ ኮድ ይታተማሉ፤ የማሳተም ሓላፊነቱም የሀገረ ስብከቱ የፋይናንስና በጀት ዋና ክፍል ሲኾን ይህም በዋና ሥራ አስኪያጁ ፈቃጅነት የሚከናወን ይኾናል፡፡
በማንኛውም መንገድ የተሰበሰበ ገቢ ሕጋዊ የገንዘብ መሰብሰቢያ ደረሰኝ ወዲያውኑ ሊቆረጥለት ይገባል፤ ይህም በዋናነት በካሽ ሬጅስተር ማሽን ተፈጻሚ ይኾናል፤ የገንዘብ መሰብሰቢያ ደረሰኝ ከገንዘብ ሰብሳቢ ውጭ መያዝና መጠቀም አይቻልም። ማንኛውም የገንዘብ ስጦታ በገንዘብ ያዡ በኩል መሰጠት ይኖርበታል፤ ስጦታው እንደተበረከተም ወዲያውኑ የገንዘብ መቀበያ ደረሰኝ ሊቆረጥለት ይገባል፡፡ በዐይነት የሚሰጥ ስጦታ በግዥ፣ ሽያጭና ንብረት አስተዳደር ፖሊሲና ዝርዝር የአፈጻጸም መመሪያ መሠረት በተተመነለት ዋጋ ይመዘገባል፡፡ ከአጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ውጭ በሙዳየ ምጽዋት ሣጥን ገንዘብ መሰብሰብ አይቻልም፤ ቋሚ ሙዳየ ምጽዋት በቅጽረ ቤተ ክርስቲያን የሚቀመጥበት ቦታ ተጠንቶ፣ በሰበካ ጉባኤው መጽድቅ አለበት፤ ለቆጠራ ካልኾነ በቀር ከተቀመጠበት ማንቀሳቀስ አይቻልም፤ በትከሻና ተይዘው የሚዞሩ ሙዳየ ምጽዋት ሣጥኖች ሙሉ መረጃ ተመዝግቦ ይያዛል፡፡ የሙዳየ ምጽዋት ቆጠራ በሚካሄድበት ወቅት ሣጥኖቹ ከመከፈታቸው በፊት ሁሉም ቆጣሪዎች የቁልፍ ካዝናውና የቁልፍ ሣጥኖች፣ የሣጥኖቹን ብዛትና እሽጋቸው አለመከፈቱን ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል፤ የተቆጠረ ገንዘብ ሙሉ በሙሉ ወዲያውኑ ካልተቻለ ከሌላ ገንዘብ ጋራ ሳይቀላቀል በበነጋው ወደ ባንክ አካውንት መግባት አለበት፤ ዣንጥላን፣ ምንጣፍንና የመሳሰሉትን በመጠቀም ገንዘብ መሰብሰብ ፈጽሞ የተከለከለ ይኾናል፡፡ዘመናዊው የፋይናንስ አሠራር በሀገረ ስብከቱ ተቋማትና አብያተ ክርስቲያናት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ሲኾንም በተጭበረበሩ ደረሰኞችና በማይታወቁ የገንዘብ አሰባሰቦች የግል ጥቅምን ማካበት በመከላከል ለክትትልና ቁጥጥር አመች ለማድረግ እንደሚያበቃ ተመልክቷል፡፡ በሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት፣ በልማትና በጎ አድራጎት ተቋማቱ እንዲሁም በአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናቱ የሚዘጋጁ የፋይናንስ ሪፖርቶች ግልጽነት፣ ወቅታዊነትና ተኣማኒነት/ተቀባይነት እንዲኖራቸው ለማድረግ፣ ሀገረ ስብከቱ በሚሰበሰበው የኻያ በመቶ ፈሰስና ከአብያተ ክርስቲያናቱ በቅጽ ተሞልቶ በሚላከው ሒሳብ መካከል በየዓመቱ የሚያጋጥመውን ልዩነት ለማስወገድ እንደሚያስችል ተገልጧል፡፡
ይህም በሒደት ከፍተኛ የሀብት ክምችት የሚገኝበት የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በፋይናንስ አሠራሩና መልካም አስተዳደሩ የሁሉም አህጉረ ስብከት ሞዴል በመኾን ቤተ ክርስቲያኒቱ በመንበረ ፓትርያርክ ደረጃ ማእከላዊ የፋይናንስና በጀት አስተዳደር ይኖራት ዘንድ መሠረት ለመጣል፣ የካህናቷን ኑሮ በማሳደግና በማሻሻል ሐዋርያ ተልእኮዋን ለማጠናከር ከፍተኛ አቅም የምትፈጥርበት መሠረት ለመጣል እንደሚያስችላት ታምኖበታል፡፡

የሸራተን አዲስ ሆቴል ሰራተኞች፤ የውጭ አገር ዜጋ በሆኑት የሆቴሉ ስራ አስኪያጅ የሚደርስብን ችግር ከአቅም በላይ በመሆኑ ሰላማዊ ሰልፍ ልንወጣ ነው አሉ፡፡ ከዚህ በፊት  የመብት ጥሰት እንደደረሰብን ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ለሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በደብዳቤ ብንገልፅም ምላሽ ባለማግኘታችን በድጋሚ ደብዳቤውን አስገብተናል ብለዋል - ሰራተኞቹ፡፡
በትምህርት ደረጃና በእውቀት ከሀበሾቹ የማይበልጡ የውጭ ዜጐች አሰሪዎቻችን ያንቋሽሹናል፤ ዛሬ ፆም ነው ይህን አንበላም ስንል “ድሮ ረሀብተኞች ስለነበራችሁ ረሀባችሁን ለማስታወስ የምታደርጉት ነው” ይሉናል፤ ጥቅማጥቅሞቻችን አይከበሩም፣ እድገት እንከላከላለን ያሉት ሠራተኞቹ፤ “ፈረንሳዊው ስራ አስኪያጅ ዲፓርትመንቶችን በመበታተን፣ ሰራተኞችን ወዳልፈለጉትና ወደማይመለከታቸው ቦታ ይመድባሉ፤ ይህን ስንቃወም እስከመደብደብ እንደርሳለን” ብለዋል፡፡
“የዜጐች ደህንነት ጥበቃ ከአገር ውስጥ ይጀምራል፤ በአገራችን ነጮች እያንቋሸሹን እና ሞራላችን እየተነካ ነው” የሚሉት ሰራተኞቹ፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ችግራችንን በዝምታ ማለፋቸው አሳዝኖናል ብለዋል፡፡
“ችግራችን ሲብስ ፒቲሽን ተፈራርመን ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያስገባነው ደብዳቤ፤ ለሆቴሉ ስራ አስኪያጅ ለሚስተር ዦን ፒይር ማኒንጐፍ ከደረሰ በኋላ፣ ስቃያችን በዝቷል ያሉት ሰራተኞቹ፤ አንድ ነገር ለማስፈቀድ፣ አቤቱታ ለማሰማትና ለእድገት ለመወዳደር ስንጠይቅ ስራ አስኪያጁ  ፒቲሽን የፈረሙትን ሰራተኞች ስም ያወጡና “በእኔ ላይ ፈርመሀል፤ እድሜ ልክህን እድገት አታገኝም፣ ይህ አይፈቀድም” እያሉ እንደሚያንገላቷቸው ተናግረዋል፡፡ ሸራተን አዲስ ሆቴል ከ800 በላይ ቋሚ ሰራተኞች እንዳሉት የገለፁት ሰራተኞቹ፤ ይህ ሁሉ ሰራተኛ ባለበት ስራ አስኪያጁን ጨምሮ አንዳንድ የውጭ አሰሪዎቻችን እያንጓጠጡንና ጫና እየፈጠሩብን ስለሆነና የሚመለከተው የመንግስት አካል ምላሽ ስላልሰጠን በቅርቡ ሰላማዊ ሰልፍ ለመውጣት አስበናል ብለዋል፡፡
የሆቴሉ ሰራተኞች ማህበር ሊቀመንበሩ አቶ ዳንኤል አለሙ ታሪኩ በበኩላቸው፤ “ሰራተኞቹ ከማህበሩ ወጥተው በራሳቸው ተደራጅተዋል፤ ነገር ግን ማኔጅመንቱና ሰራተኛው ተቀራርበው እንዲሰሩና በውይይት ችግራቸውን እንዲፈቱ ብዙ ርቀት ብንሄድም የሆቴሉ ስራ አስኪያጅ ሚስተር ዦን ፒይር ማኒንጐፍ ፈቃደኛ አልሆኑም” ብለዋል፡፡
የሆቴሉን ስራ አስኪያጅ  ሚስተር ዦን ፒይር ማኒንጐፍን ለማነጋገር ብንሞክርም እረፍት ላይ በመሆናቸው ሳይሳካልን ቀርቷል፡፡ ሌላ ሃላፊ ለማነጋገር ፀሃፊዋን ጠይቀን፤ በጉዳዩ ላይ ምላሽ የሚሰጡት ስራ አስኪያጁ ብቻ እንደሆኑ ገልፃልናለች፡፡    

ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ሌባ ወደ አንድ አሮጊት ቤት ገብቶ ሊሰርቅ አካባቢውን በትክክል ለማጥናት ፈልጐ አንዴ በግራ፣ አንዴ በቀኝ፣ ይሄዳል፡፡ አንዴ በፊት ለፊት፣ አንዴ በጓሮ ይዞራል፡፡ በመጨረሻ ማንም እንደሌለና ማንም እንዳላየው ካረጋገጠ በኋላ ወደ ቤት ዘው ይላል፡፡
ዘወር ዘወር ብሎ ሲያይ፤ ጠባብ አፍ ያለው ማሠሮ ውስጥ እህል አለ፡፡ እጁን ወደማሰሮው ሰደደ። የቻለውን ጨብጦ እጁን ለማውጣት ሲሞክር አልወጣም አለው፡፡ ትንቅንቁን ቀጠለ፡፡ የጨበጠውን እህል ሊተው አልፈለገም፡፡ እንደጨበጠ ላውጣህ ቢለው ደግሞ ጠባቡ የእንስራው አፍ አላሳልፍ አለው፡፡ እንዲሁ ሲታገል ይቆያል፡፡
በሌላ በኩል፤ አሮጊቷ ወንዝ ወርዳ ውሃዋን ቀድታ ስትመለስ፤ መንገድ ላይ ያገኘችውን ሰው ሁሉ ሰላም ትላለች፡፡
ለመጀመሪያው፤
“እንዴት ዋላችሁ?” ትላለች፡፡
“ደህና” ይላል ያገኘችው ሰው፡፡
“ሠፈር ደህና?”
“ደህና”
“አዝመራ ደህና?”
“አዬ ዘንድሮስ እንጃ ዝናቡ ደህና አልሰጠም!”
“እንበሶች፣ ላሞች ደህና?”
“አዬ ኧረ እንጃ! በሽታው ከፍቷል“
“ሰዉስ ደህና ነው?”
“አዬ ሰዉስ ድህነቱን አልቻለውም፡፡”
“የእኔ ቤትስ ደህና ነው?”
“ኧረ አላወቅንም - የወጣም ሲገባ አላየን፤ የገባም ሲወጣ አላየን” ይላል ሰውዬው፡፡
“ደህና፤ ሁሉን ለደግ ያርገው ይሄን ዓመት!” ብላ መንገዷን ቀጠለች፡፡
ቤት ስትደርስ፤ ያን ሌባ ሳታስተውል፣ የቀዳችውን የቀርበታ ውሃ አስቀምጣ እፎይ አለች፡፡
ከዚያም፤
“አዬ! ይሄ ገደ - ቢስ ዓመት!” አለች፡፡
ይሄን ጊዜ ያ ሌባ፤
“ገደ - ቢሱን ዓመት ተይውና፤ ነይ የእኔን እጅ ከማሠሮው አውጪልኝ!” አላት፡፡
*   *   *
በተረቱ፤ ስለዓመቱ ማማረር ትተሽ ነይ ይልቅ ሥራ ሥሪ፤ ነው ምፀታዊ ትርጉሙ፡፡ ስላቁ ደግሞ የሰው ቤት እየዘረፈ፣ እንደመልካም ነገር ይሄ ያንቺ እንሥራ የሚያጠፋውን ጥፋት ተመልክተሽ ነይ እጄን አላቂኝ ነው! የእኔን ሌብነት አታስቢው ነው፡፡ እያደር ሙስና ወደ ዐይን አውጣ ሙስና ሲቀየር እንዲህ ፈጣጣ ይሆናል፡፡ “እግሮችህ እንዳይሰረቁብህ መሮጥ የማስፈለጉ ነገር፤ በአሁኑ ጊዜ አስከፊ ደረጃ ላይ ደርሷል” ይላል ቤርቶልት ብሬሽት፡፡ በሀገራችን ይቆማል፣ ከቀን ቀን ይሻለዋል ሲባል የነበረ በሽታ ዛሬም ያው ሙስና ነው፡፡ ወይ የካንሠሩ ሥር አልታወቀም፣ ወይ ጋንግሪኑን ለመቁረጥ አልተቻለም፡፡
የሌብነት ቦቃ እንደሌለው የሚያስረዱን የጥንቱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ቲዮዶር ሩዝቬልት፤ “ቢሮ በመስረቅና፣ ቦርሳ በመስረቅ መካከል ልዩነት ፈጥሮ “ጉድ! ጉድ!” ማለት ላይ ባለ አገር! ህዝብ ሙሉ በሙሉ ሰልጥኗል ለማለት አይቻልም” ይሉናል፡፡ በዐቢይ ሌባና በንዑሥ ሌባ መካከል ስናማርጥና ዋናውን ሥረ- ሙስና ሳናገኝ፣ በላይ በላዩ አዳዲስ ሌባ እንደምንጨምርበት ልብ - እንበል፡፡ ነባሩ እየደበዘዘ አሊያም እየተለመደ፤ አዲሱ የወረት ሞሳኝ፤ “ቀንደኛ” ተብሎ ሆይ ሆይ መባሉ፤ ዋናው ደዌ ሥሩ ሳይነቀል እንዲቀር ያደርገዋል!
በሀገራችን፤ በሚገርም ሁኔታ አንዳንዶቹ የሙስና ቧንቧዎች፤ በተለይም ቀጫጭኖቹ ታሽገው፤ ዋናው ቱቦ - አከል ቱባ ቧንቧ ሳይነካ በመቅረቱ፤ “ፈረሱ ከተሰረቀ በኋላ የጋጣውን በር ጥርቅም አድርጐ ዘጋ!” የሚለውን የፈረንጆች ተረት እንኳ በቅጡ ልንተርት እንዳንችል አድርጐናል፡፡ ለምን? ቢባል፤ ማን ጥርቅም አድርጐ ይዝጋው? ነውና ጉዳዩ!
ሼክስፒር፤
“The strongest poison ever known
came from Caesar’s Laurel Crown” ይላል፡፡
“ከቶም ዋንኛው መርዝማ፣ እስከዛሬ እሚታወቀው፣
ቄሣር ካጠለቀው ዘውድ ውስጥ፣ ከወይራ አክሊል የመጣው ነው” እንደማለት ነው፡፡
አናቱን ሳናጣራ እግር - እግሩን ብቻ ብንመነጥር፣ ዞረን እዚያው ክብ ቀለብት፣ እዚያው ክብ ጨዋታ ውስጥ ነው የምንከርመው፡፡ ሙስና የገንዘብና የንብረት ዘረፋ ብቻ እንዳልሆነም አንዘንጋ! የኢፍትሐዊነትና የፖለቲካ ወንጀል ቅይጥ ሙስናም አለና!
አሜሪካዊው ታሪክ ፀሐፊ፤ ዊል ዱራንት፤ እንዲህ ይለናል:-
`ሥልጣኔ ዳርቻ ያለው ወንዝ ነው፡፡ ወንዙ፤ የታሪክ ፀሐፊዎች በመዘገቧቸው አንዳንዴ በነብሰገዳዮች፣ በሌቦች፣ በጯሂ - ሰዎችና በመሳሰሉ፤ ደም የተሞላ ነው፡፡ ልብ መባል ያለበት ግን፤ ከዚህ ወንዝ ዳርቻ ላይ የማይታወቁ ሰዎች አሉ፡፡ ቤት ይሠራሉ፡፡ ፍቅር ይሠራሉ፡፡ ልጆች ያሳድጋሉ። ዘፈን ይዘፍናሉ፡፡ ግጥም ይጽፋሉ፣ እንዲያውም አንዳንዴ ሐውልት ሁሉ ያቆማሉ፡፡ የሥልጣኔ ታሪክ እንግዲህ እባህሩ ዳርቻ ላይ ስለሚሆነው ነገር መሆን ሲገባው፣ ታሪክ ፀሐፊዎች ግን (ተስፋ ቆርጠው ተስፋ እሚያስቆርጡ ሰዎች በመሆናቸው)፤ የባህሩን ዳርቻ ሰዎች ከቁብ ሳይጽፉ ስለ ወንዙ ብቻ ይጽፋሉ፡፡”
አገራችን በኮንትሮባንድ ትተዳደር ይመስል የነጋዴው ትኩረት በስውርና በግልጽ የሚያካሂደው የኮንትሮባንድ ዝውውር መሆኑ ሳያንስ፤ እንደፈረንጆች አባባል፤ ‘ኮንትሮባንድስቶችን የሚያሳድዱት ባለሥልጣኖች ሁሉ ውርሱን መቦጥቦጡን ተያይዘውታል’ ይላል፤ ይባላል”፡፡ ላቲኖች፤ “ዋናው ሌባ፤ ‹ሌባ ያዙ!› እያለ የሚጮኸው ነው ይላሉ” እንደሚባለው ነው፡፡
የእንግሊዙ የፖለቲካ ቀስቃሽና- አማላይ (Lobbyist) ኢያን ግሪር፤ “እንግሊዝ ውስጥ የለንደን ታክሲ እንደምንከራይ ሁሉ የፓርላማ አባልም መከራየት ያስፈልጋል” ይለናል፡፡ (You need to rent an MP just like you rent a London taxi)
ከአናት የመጣ አናት ይመታል፤ ነው ነገሩ! የራሳችንን ዐይን ጉድፍ ሳናወጣ የሌላውን ዓይን እናውጣ ማለት፤ የራሳችንን ፓርቲ ቁስል ሳናክም የሌላውን ቁስል አካሚ መስለን መገኘት፣ የራሳችንን ዓይን ያወጣ ሙስና ሳናይ፣ የሌላው ሙስና ላይ መጮህ፤ “ጦጢት ራሷ ሳትገረዝ፣ የሌላውን ዐይን ትይዛለች” ዓይነት ይሆናልና፤ ልብና ልቦናውን ሰጥቶን ሁሉን በአግባብ የምንይዘበት ጊዜ ያምጣልን! ዕውነተኛ ልደት ለማክበር ያብቃን!!   

የሸራተን አዲስ ሆቴል ሰራተኞች፤ የውጭ አገር ዜጋ በሆኑት የሆቴሉ ስራ አስኪያጅ የሚደርስብን ችግር ከአቅም በላይ በመሆኑ ሰላማዊ ሰልፍ ልንወጣ ነው አሉ፡፡ ከዚህ በፊት  የመብት ጥሰት እንደደረሰብን ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ለሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በደብዳቤ ብንገልፅም ምላሽ ባለማግኘታችን በድጋሚ ደብዳቤውን አስገብተናል ብለዋል - ሰራተኞቹ፡፡
በትምህርት ደረጃና በእውቀት ከሀበሾቹ የማይበልጡ የውጭ ዜጐች አሰሪዎቻችን ያንቋሽሹናል፤ ዛሬ ፆም ነው ይህን አንበላም ስንል “ድሮ ረሀብተኞች ስለነበራችሁ ረሀባችሁን ለማስታወስ የምታደርጉት ነው” ይሉናል፤ ጥቅማጥቅሞቻችን አይከበሩም፣ እድገት እንከላከላለን ያሉት ሠራተኞቹ፤ “ፈረንሳዊው ስራ አስኪያጅ ዲፓርትመንቶችን በመበታተን፣ ሰራተኞችን ወዳልፈለጉትና ወደማይመለከታቸው ቦታ ይመድባሉ፤ ይህን ስንቃወም እስከመደብደብ እንደርሳለን” ብለዋል፡፡
“የዜጐች ደህንነት ጥበቃ ከአገር ውስጥ ይጀምራል፤ በአገራችን ነጮች እያንቋሸሹን እና ሞራላችን እየተነካ ነው” የሚሉት ሰራተኞቹ፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ችግራችንን በዝምታ ማለፋቸው አሳዝኖናል ብለዋል፡፡
“ችግራችን ሲብስ ፒቲሽን ተፈራርመን ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያስገባነው ደብዳቤ፤ ለሆቴሉ ስራ አስኪያጅ ለሚስተር ዦን ፒይር ማኒንጐፍ ከደረሰ በኋላ፣ ስቃያችን በዝቷል ያሉት ሰራተኞቹ፤ አንድ ነገር ለማስፈቀድ፣ አቤቱታ ለማሰማትና ለእድገት ለመወዳደር ስንጠይቅ ስራ አስኪያጁ  ፒቲሽን የፈረሙትን ሰራተኞች ስም ያወጡና “በእኔ ላይ ፈርመሀል፤ እድሜ ልክህን እድገት አታገኝም፣ ይህ አይፈቀድም” እያሉ እንደሚያንገላቷቸው ተናግረዋል፡፡ ሸራተን አዲስ ሆቴል ከ800 በላይ ቋሚ ሰራተኞች እንዳሉት የገለፁት ሰራተኞቹ፤ ይህ ሁሉ ሰራተኛ ባለበት ስራ አስኪያጁን ጨምሮ አንዳንድ የውጭ አሰሪዎቻችን እያንጓጠጡንና ጫና እየፈጠሩብን ስለሆነና የሚመለከተው የመንግስት አካል ምላሽ ስላልሰጠን በቅርቡ ሰላማዊ ሰልፍ ለመውጣት አስበናል ብለዋል፡፡
የሆቴሉ ሰራተኞች ማህበር ሊቀመንበሩ አቶ ዳንኤል አለሙ ታሪኩ በበኩላቸው፤ “ሰራተኞቹ ከማህበሩ ወጥተው በራሳቸው ተደራጅተዋል፤ ነገር ግን ማኔጅመንቱና ሰራተኛው ተቀራርበው እንዲሰሩና በውይይት ችግራቸውን እንዲፈቱ ብዙ ርቀት ብንሄድም የሆቴሉ ስራ አስኪያጅ ሚስተር ዦን ፒይር ማኒንጐፍ ፈቃደኛ አልሆኑም” ብለዋል፡፡
የሆቴሉን ስራ አስኪያጅ  ሚስተር ዦን ፒይር ማኒንጐፍን ለማነጋገር ብንሞክርም እረፍት ላይ በመሆናቸው ሳይሳካልን ቀርቷል፡፡ ሌላ ሃላፊ ለማነጋገር ፀሃፊዋን ጠይቀን፤ በጉዳዩ ላይ ምላሽ የሚሰጡት ስራ አስኪያጁ ብቻ እንደሆኑ ገልፃልናለች፡፡    

“የጐበዝ አለቃ” እሽ ያለውን በፈቃዱ፣ እምቢ ያለውን በግድ የሚገዛ ወንዝ አፍራሽ ገዥ ነው። የጐበዝ አለቃ የመሰለውን ይፈርዳል እንጂ ሕግ የሚባል ነገር አይገባውም፤ ወይም ለሕግና ሥርዓት ደንታ የለውም፡፡
የጐበዝ አለቆች ብዙውን ጊዜ የሚከሰቱት የመንግሥት አቅም ሲላላ ወይም “መንግሥት የለም” ብለው ሲያምኑ ነው፡፡ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ማይጨው ላይ ሠራዊታቸውን ለነጭ አሞራ በትነው ወደ እስራኤል ቀጥሎም ወደ እንግሊዝ የሄዱ ጊዜ የተከሰተውን ማንሳት ለርዕሰ ጉዳያችን ጥሩ ምሳሌ ሊሆን ይችላል። ንጉሡ በመሸሻቸው አገሪቱ ያለ መሪ ቀረች፤ በአንጻሩ ጣሊያኖች ፋሽስታዊ ቅጣታቸውን በወታደሩ ላይ ብቻ ሳይሆን በህፃናትና ሴቶች፣ በመነኮሳትና እንስሳት ላይ ሳይቀር እየፈፀሙ በማስቸገራቸው ህዝቡ ተቃውሞውን ለመግለጽ መደራጀት ነበረበት፡፡ ግን የሚያደራጀውም ሆነ የተደራጀ አካል በማጣቱ የሚያስተባብሩትን የጐበዝ አለቆች መፈለግ ነበረበት፡፡ ስለሆነም በጊዜው ጉልበት ያለው ሁሉ የጐበዝ አለቃ ሆነ፡፡ በላይ ዘለቀ፣ አበበ አረጋይ፣ ገርሱ ዱኪ፣ ወዘተ የጐበዝ አለቆች ነበሩ። እንዲያውም አበበ አረጋይንማ “ራስ” የሚል ማዕረግ ያስገኘላቸው የጐበዝ አለቅነታቸው ነው፡፡
በጣሊያን ጊዜ የነበሩ የጐበዝ አለቆች ዓላማቸው ኢትዮጵያን ከፋሽስት መንጋጋ ማላቀቅ ነበር። የተሳካ እንቅስቃሴ በማድረጋቸውም ከአምስት ዓመት የሞት ሽረት ትግል በኋላ ንጉሡን ለዘውድ አብቅተዋል። በ1960 ዓ.ም ጐጃም ላይ ተከስቶ የነበረውን ህዝባዊ አመጽ የመራውም “ባምላኩ አየለ” ወይም በፈረስ ስሙ “ባምላኩ አባ ግዮን” የሚባል የጐበዝ አለቃ ነበር፡፡
ባምላኩ አባ ግዮን የሚመራው የገበሬ ጦር፣ መላ ጐጃምን ለጊዜውም ቢሆን ከንጉሡ አገዛዝ ነፃ ማውጣት ችሎ ነበር፤ ለአመጽ ምክንያት የነበረውን የብር ከሃምሳ ተጨማሪ ግብርም በጉልበቱ አስነስቷል፡፡ በትግራይም “የቀደማይ ወያኔ” አመጽ የተመራው በጐበዝ አለቆች ነው። የኃይለ ሥላሴን ሥርዓት ያንኮታከቱትም ከየወታደሩ ክፍል በጉልበት የተሰባሰቡ የጐበዝ አለቆች ናቸው፡፡ ዙሩ ሲደርስ ደርግን ራሱን የጣሉትም የኢህአዴግ የጐበዝ አለቆች ናቸው፡፡
ወያላዎች የጐበዝ አለቆች ሆነዋል
የከተማዋን የታክሲ ስምሪት ሥርዓት ለማስያዝ ሲባል የትራንስፖርት ባለስልጣኑ መሥመር አመልካች ጽሑፎች (ታፔላ) በየታክሲው አናት ላይ እንዲለጠፍ ወስኖ ነበር፤ እሱን ተግባራዊ ለማድረግም ብዙ ጊዜ አምጦበታል፡፡ ግን እርምጃው የመጓጓዣ ችግሩን ከመፍታት ይልቅ ይበልጥ አወሳሰበውና ህዝቡን ቁምስቅሉን ያሳየው ጀመር፡፡
በከተማዋ ትራንስፖርት ባለሥልጣን እርምጃ የተበሳጩት ወያላዎች፤ ከህዝቡ ትከሻ ላይ ፊጥ አሉና ሲፈልጉ ለሁለት ሰው በተዘጋጀ ወንበር ላይ “ጠጋ በል” እያሉ ሶስትና አራት ተሳፋሪ እንደ ቂጣ እየደራረቡ ያሰቃዩታል፤ ሲያሻቸውም ትራንስፖርት ባለሥልጣኑ ካወጣው ታሪፍ በላይ ይወስኑበታል። የጐበዝ አለቆችን ውሳኔ የሚጥስ ካለ፣ ክብሩንም ገንዘቡንም አጥቶ ተዋርዶና ተደብድቦ መግባት ግድ ሆኖበታል፡፡
ሰሞኑን ያጋጠመኝን ልጥቀስ፤ ከታህሳስ አንድ ጀምሮ መንግሥት “መጠነኛ ማስተካከያ አድርጌያለሁ” ያለውን ዋጋ፣ ህዳር 30 ምሽት በቴሌቪዥን ቁጭ ብዬ አስተውያለሁ፡፡ በ “መጠነኛ” ማስተካከያው መሠረት 1.40 የነበረው ወደ 1.45፤ 2፡70 የነበረው ወደ 2፡80 ማደጉ ገርሞኝ፣ ጥዋት ከመገናኛ ወደ ካዛንችስ ታክሲ ከተሳፈርን በኋላ (ያውም በሰልፍ መከራ አይተን) የጐበዝ አለቃው “ዋጋው አራት ብር ነው” የሚል አዋጅ በኩራት አሰማን፡፡ “እንዴ! ማታኮ በቴሌቪዥን 2.80 ተብሏል፤ እንዴት? ከየት የመጣ አራት ብር ነው?” ብለን ሁላችንም ስንጮህ “የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ታክሲ ይግዛላችሁ” አለን የጐበዝ አለቃው፡፡
የወያላው ሳይንስ ሹፌሩም ዳር ይዞ ቆመና “ከፈለጋችሁ ክሰሱ፤ መውረድ ትችላላችሁ፤ ጥሩንባ ሁሉ” አለና ታክሲ ሙሉ ሰው ዳቦ በቀደደ አፉ መዘርጠጥ ጀመረ፡፡ ሌላ የጐበዝ አለቃ ተጨማረ ማለት ነው፡፡ በወቅቱ የነበረው ምሬትና ሃዘን እንዲህ በቀላሉ የሚገለጽ አይደለም፡፡ ከሁሉ ትዝ የሚለኝና የገረመኝ አንዲት ወይዘሮ የተናገሩት ነው፡፡ “መክሰስ አለብን ትራፊክ ፖሊስ? እንሂድ፤ የለም ትራንስፖርት ባለሥልጣን ይሻላል ወደዚያ እንሂድ” የሚሉ ሰዎች ስለነበሩ ወይዘሮዋ ምን አሉ መሰላችሁ? “ሚስት አረገዘች? ብሎ ጓደኛውን ቢጠይቀው “ማንን ወንድ ብላ?” አለው ይባላል፡፡ ለመሆኑ መንግሥት ቢኖር ቂጡን ያልጠረገ ውርጋጥ መቀለጃ እንሆን ነበር?” ሲሉ እንባቸውን በነጠላቸው ጫፍ ጠራረጉ፡፡ እውነት ለመናገር የሴትዮዋ አባባል ልክ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ምክንያቱም ትንሹን ወያላ መቆጣጠር ካልቻለ እንዴት ነው ሌሎች ከባድ ወንጀሎችን በመቋቋም ህዝቡን ከስጋትና ከዝርፊያ መታደግ የሚችለው?
አሁን እየባሰበት የመጣው ሌላው ጉዳይ ደግሞ የእነዚህ የጐበዝ አለቆች የሥምሪት መስመር ነው “ከካዛንችስ በአራት ኪሎ ፒያሳ” የሚል ጽሑፍ ለጥፎ “ፒያሳ በአቋራጭ!” ይላል፡፡ በአራት ኪሎ ሂድ ሲባልም በፍጹም በእጅ አይልም፡፡ ይህ የአቋራጭ መንገድ በአቋራጭ ለመክበር እንጂ በአቋራጭ ህዝብን ለማገልገል እንዳልሆነ ግን ግልጽ ነው፡፡ ይህንንም የትራንስፖርት ባለሥልጣኑ መቆጣጠር አልቻለም፤ የትራፊክ ፖሊሶችም እያዩ ትንፍሽ አይሉም፡፡ የህዝብን ችግር የማይፈቱ ከሆነ ትራንስፖርት ባለሥልጣንና ሰራተኞቹ ለምን ያስፈልጋሉ? የትራንስፖርት ዘርፉ የሚመራውኮ በእነሱ ሳይሆን በጐበዝ አለቆች ነው፡፡
“ተራ አስከባሪ” የሚባሉትም ሌሎች የጐበዝ አለቆች ናቸው፡፡ ከታክሲ ሹፌሮች ጋር በመሞዳሞድ ሕዝቡን ቁም ስቅል ያሳያሉ እንጂ ለህዝቡ የፈየዱት ነገር የለም፡፡ ቀድሞ ነገር የሰውን ነው የመኪናውን ተራ የሚያስጠብቁት? የቱ መኪና ገዝቶ ነው ተራ የሚያስጠብቁት? መላ የጠፋው ተቋም!
መንገድ ጠራጊዎች የጐበዝ አለቆች ናቸው
መንገዱም ሆነ ሌላው ነገር የሚፀዳው ለህዝቡ ጤንነት ሲባል ነው፡፡ ባህርዳር፣ አዋሳም ሆነ ሌሎች የአገራችንና የውጭ አገር ከተሞች መንገዶች የሚፀዱት ህዝቡ እንቅስቃሴ ሳይጀምር ንጋት ላይ ነው፡፡ አዲስ አበባ ግን “ጽዳቱ” የሚጀመረው ነዋሪው ሥራ ለመግባት ሲጣደፍ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ ህዝቡ የታክሲ ወረፋ ለመያዝ ረጅም ሰልፍ ይዞ ካዩት፣ ወይም ንፁህ የለበሰ ካዩ ቅናት ያለባቸው ይመስል አስፋልት ላይ የነበረውን አቧራ አንስተው ይከምሩበታል፡፡
“ለምን እንዲህ አረጋችሁ?” የሚላቸው አካልም የለም፤ በድርጊታቸው የተበሳጨ ሰው አቧራውን ከልብሱና ከሰውነቱ ላይ እያራገፈ “ለምን እንዲህ ታረጋላችሁ?” የሚል ጥያቄ ሲያቀርብላቸውም መልሳቸው የሰሌን መጥረጊያ ሊሆን ይችላል፡፡
ለመሆኑ መንገዱ የሚጠረገው ለማን ጤንነት ታስቦ ነው? ለነዋሪው ነው? ወይስ ለአስፋልቱ ታስቦለት መንገድ ጠራጊ የጐበዝ አለቆችና ኃላፊዎቻቸው (ምን አልባት ካላችሁ) እባካችሁ የጽዳት ዓላማ ይግባችሁ፡፡ መንገድ የምትጠርጉት ለነዋሪው ጤና እንጂ ለአስፋልቱ ታስቦ አይደለም፡፡
መብራት ኃይልና ቴሌም ሌሎች የጐበዝ አለቆች ናቸው
መብራት ኃይልና ቴሌ በህግ የተቋቋሙ የመንግሥት አካላት ቢሆኑም ከመንግሥት አፈንግጠው የራሳቸውን ደሴት ፈጥረዋል።  በህጋዊነት ኃላፊነታቸውን ከመወጣት ይልቅ የጐበዝ አለቅነትን የመረጡ መስለዋል፤ ያለምንም ማስጠንቀቂያ አገልግሎት ያቋርጣሉ፤ ለምን ተብለው ሲጠየቁም ሠራተኞቻቸው ደንበኛቸውን ይገላምጣሉ፤ አገልግሎቱንም ይበልጥ ያሽመደምዳሉ፡፡
የሁለቱም ተቋሞች አገልግሎት ይሻሻል ዘንድ መንግሥት በየጊዜው የመዋቅር ማሻሻያና የመሣሪያ ግዥ እንደሚያደርግና እያደረገም እንደሆነ በየጊዜው በኢቴቪ እናያለን፤ እንሰማለን፡፡ ግን አቅመ ደካማነታቸውን ሊያሻሽሉ አልቻሉም፡፡
ለምሳሌ መንግሥት ቴሌን ከኮርፖሬሽን ወደሚኒስቴር መ/ቤት አሳድጐታል፤ አገልግሎቱ ግን እየባሰ፣ እየዘቀጠ ሄደ እንጂ አንዳችም መሻሻል ሊያሳይ አልቻለም፡፡ ትላንት የተቋቋመችው ደቡብ ሱዳንና የተረጋጋ መንግሥት የሌላት ሶማሊያ፤ ከእኛ በአያሌው የተሻለ አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡ እኛ ግን ገና እንድሃለን፡፡ ለመሆኑ ልናገኘው የፈለግነውን ሰው ያለምንም ድምጽ መቆራረጥና ጥሪ መሰናከል መቸ ይሆን ማናገር የምንችለው? የጐበዝ አለቆች ሆይ፤ እባካችሁ ወደነበረው ባለገመድ ስልክ መልሱን፡፡
የመብራት ኃይል ኮርፖሬሽን የሥራ ኃላፊዎች በመቅበጥ (ኪራይ ሰብሳቢነት) ተጠርጥረው ከርቸሌ መግባታቸውን ፀረ ሙስና ኮሚሽን ነግሮናል፡፡ የተከሰሱበት ወንጀል እውነት ሆኖ ከተፈረደባቸው “እሰየው” ያሰኛል፡፡ መብራቱን እያጠፉ የእኛን አንጀት ነበራ ሲያቃጥሉ የኖሩት፡፡ መንግሥት ቢቸግረው የመብራት ኃይል ባለሥልጣኑን ሰሞኑን በሌላ ቀይሯል። ግንኮ ስርዓቱን (ሲስተሙን) ማስተካከል ነው እንጂ ሰው ቢቀያየር ለውጥ ሊመጣ አይችልም፡፡ በአጠቃላይ በከተማችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎችና በተለያዩ የሥራ መስኮች ላይ የጐበዝ አለቆች ተበራክተው ነዋሪውን ቁምስቅሉን እያሳዩት ነው፡፡ መንግሥት መንቃት አለበት። ክቡር ከንቲባውም በየቦታው ምን እየተሰራ እንደሆነ ተዘዋውረው ሊያዩና አፋጣኝ መፍትሔ ሊሰጡ ይገባል። አለዚያ ከተማቸውን የጐበዝ አለቆች እየተቀራመቷት ነውና የመረረው ሕዝብ…

አንድ ዝነኛ ዕዳና ነጋዴን የሚያሳይ ወግ አለ፡፡  ሲቆይ ተረት ይመስላል እንጂ ዕውነተኛ መሰረት አለው፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን በአንድ ከተማ፣ አንድ ባለፀጋ ቱሪስት፣ ወደ አንድ ሆቴል ይመጣል፡፡ በዚህ ወቅት በዚያ ከተማ ዝናብ በጣም ይዘንባል፡፡ከተማው የተወረረ ይመስላል፡፡ ሰው በመንገድ አይታይም።  ጊዜው ክፉ ጊዜ ነው፡፡ ሰው ገንዘብ ስለሌለው አንዱ ከአንዱ እየተበደረ ነው የሚኖረው፡፡ ብድር የሌለበት ሰው የለም፡፡ ዕዳ በዕዳ ሆኗል ከተማው፡፡
ባለፀጋው ቱሪስት እንግዲህ የመጣው ይሄን ሰዓት ነው፡፡ ጥሩ መኝታ ያለው ትልቅ ሆቴል ፍለጋ ላይ ነው፡፡ ብዙ ሆቴሎች አይቶ የተመቸ አይነት ክፍል አላገኘም፡፡ ይሄኛውን ሆቴል በዐይኑ ወዶታል፡፡
“ጤና ይስጥልኝ” አለ ወደ ሆቴሉ ባለቤት ቀርቦ፡፡
“እንኳን ደህና መጡ ጌታዬ”
“ጥሩ ክፍል አላችሁ - ለመኝታ?”
“አዎ ጌታዬ፤በጣም በርካታ ክፍሎች አሉን፡፡ ቢፈልጉ ምድር ቤት፣ቢፈልጉ ፎቅ ላይ፡፡ ብዙ ዓይነት ክፍሎች አሉን”
“መልካም፤ የሚያሳየኝ ልጅ መድብና ክፍሎቹን ልያቸው፤ከተስማማኝ ልጁን እልከዋለሁ - ትመዘግበኛለህ፡፡ ካልተስማማኝ ራሴ እመጣለሁ፡፡ ይኸው ይሄንን መቶ ዶላር ያዝ” ብሎ ባንኮኒው ላይ ብሩን አስቀምጦ ወደ ፎቁ ወደ ሚያወጣው ደረጃ ሄደ፡፡
የሆቴሉ ባለቤት ፈጠን ብሎ መቶ ዶላሩን ወስዶ አጠገቡ ለሚገኘው ባለልኳንዳ ዕዳውን ከፈለ፡፡
ባለልኳንዳው ደግሞ ወዲያው፤ በሬ ለሚያመጣለት በሬ - አድላቢ - ነጋዴ ዕዳውን ሊከፍል በረረ፡፡ በሬ አድላቢው - ነጋዴ በበኩሉ፤ መኖና አትክልት ወደሚያቀርብለት ነጋዴ በፍጥነት ሄደና “እንካ ዕዳዬን አወራርድ” አለው፡፡
መኖና አትክልት አቅራቢው ነጋዴ ደግሞ እየበረረ በከተማው ወደታወቀችው ሴተኛ አዳሪ ሄዶ፤ በክፉ ጊዜ በዱቤ ስላሳደረችው አመስግኖ 100 ዶላሩን ሰጥቶ ከዕዳ ነፃ ሆነ፡፡
ሴተኛ አዳሪዋ በጣም ፈጥና ወደዚያ ሆቴል ሄደች፡፡ ከዚያም፤ ደምበኞቿን እያመጣች በተከታታይ በዱቤ የተኛችበትን የክፍል ሂሳብ ለባለ ሆቴሉ ዕዳዋን ከፈለች፡፡
ባለሆቴሉ ያንን መቶ ዶላር ባንኮኒው ላይ አስቀመጠው፡፡ ቱሪስቱ እንዳይጠረጥርም፤ በትክክል ባስቀመጠበት ቦታ ነው ያኖረለት፡፡ ባለፀጋው ቱሪስት የፎቁን የመኝታ ክፍሎች ሁሉ ሲያይ ቆይቶ፣ አንዱም ሳይስማማው ስለቀረ፤ ከፎቁ ወርዶ፣ወደ ባለቤቱ መጣ፡፡ ከዚያም “የሆቴሉን መኝታ ክፍሎች፣ በሙሉ ለማለት እችላለሁ፤አየሁዋቸው፡፡አንድም ክፍል እኔ የምወደው ዓይነት አልሆነልኝም፡፡ ስለዚህ 100 ዶላሩን ስጠኝና  ሌላ ቦታ ልፈልግ” አለ፡፡
“በጣም እናመሰግናለን ጌታዬ” አለ ባለሆቴሉ፤ በትህትና ገንዘቡን እየሰጠ፡፡
ባለፀጋው ቱሪስት ገንዘቡን ተቀብሎ ሄደ፡፡
በዚህ የመቶ ዶላር ታሪክ ውስጥ፤ ማንም ምንም ገንዘብ አላገኘም፡፡ ያም ሆኖ የከተማው ነጋዴዎች አሁን ዕዳቸውን አቃለዋል፡፡ ወደፊት ያልፍልናል ብለው በተስፋ ተሞልተው ተቀምጠዋል፡፡
*     *     *
የትኛውም ባንክና ኢንሹራንስ በዚህ ህግ እንደሚሰሩ ልብ እንበል!
ዕዳ ስንፈራረም የነገ እጣችንን እናስብ፡፡ ማ እየተጠቀመብን እንደሆነ እናስብ፡፡ ስልጣኔ ብዙው እጁ ከቀናን መበዝበዝ ካልቀናን መበዝበዝ ነው፡፡ “ዕዳ ይሻግታል እንጂ አይበሰብስም (a debt may get moldy but it never decays) ይላል፤ ናይጄሪያዊው ደራሲ ቺኑዋ አቼቤ፡፡
“ሰርቼ እከፍላለሁ” ብሎ መበደር የያያዋጣበት ጊዜ አለ፡፡ ግን ሁል ጊዜ አያዋጣም፡፡ በተለይ ደሀ አገሮች የሚያስይዙት ንብረት ወይም ቅድመ - ሁኔታ (conditionality) ስለሚኖር መቼ እጃቸውን ተጠምዝዘው አንዳች ግዳጅ ውስጥ እንደሚገቡ ማስተዋል ይገባቸዋል፡፡ “አሁን እየተበደርን ባለንበት ፍጥነት በሶስት አመት ጊዜ ውስጥ ከ2ኛው ዓለም ጦርነት ጀምረን የገነባናቸው ህንፃዎች በሙሉ የኛ አይደሉም ማለት ነው” ይላል አሜሪካዊው ኢኮኖሚስት ፖል ቮልከር፡፡ ይህን አጥብቆ ልብ - ማለት ይገባል! ብድር እንዲህ ከሆነ እግዚሃር ያውጣን፡፡ ነገን ሳናጤን የምንጓዝበት መንገድ ትውልድን የማይችለው ጣጣ ውስጥ መክተት ነው፡፡ “ያባት ዕዳ ለልጅ” የሚለውን ስሜት በአግባቡ መመርመር ግዴታ ነው! “የኑሮ ደረጃችን እየተጠገነ ያለው በምርታማነት! ወይም በደሞዛችን አይደለም፡፡ በውጪ አገር ካፒታል እንጂ”  የሚለውን የጄፍሬይ ሳችስ (ታይም) አስተሳሰብ ጠለቅ ብሎ ማየት ያባት ነው! የሀገር ዕዳ ከነእንድምታው መጤን ይኖርበታል፡፡ ብድር የኢኮኖሚ ጉዳይ ብቻ ነው ብለን ካሰብን ቢያንስ የዋህነት አጥቅቶናል፡፡
“በሃገር ደረጃ ያለ ዕዳ ጥሩ ነገር ነው፡፡ አደገኛው ነገር ግን መልሰን እንዳንከፍል የፖለቲካል ኢኮኖሚ ጣጣ መኖሩ ነው” ይላል የብሪታኒያው ስላቅ ፀሃፊ ደብሊው ሴላር፡፡
ዕዳ አባዜው ብዙ ነው፡፡ የዕዳ ማስወገድን ችሎታና ጥበብ ከላይ የጠቀስነው፤ ተረት - መሰል ዕውቀት ይነግረናል! “ለኗሪዎች አክብሮትን፣ ለሟቾች ዕውቀትን የመስጠት ዕዳ አለብን”
የሚለው የፈላስፋው ቮልቴር አባባል ደግሞ፤ የራሳችንን ሰዎች እንዴት እንደምናከብር ይጠቁመናል።
የአገራችን ትላልቅ አበዳሪ ነጋዴዎች ስናይ ተበዳሪዎች ጤና መሆናቸውን ለማረጋገጥ በየሆቴል ጅምናስቲክ መስሪያ ቦታ ማለዳ እየሄዱ ያረጋግጣሉ፤ይባላል፡፡
“ዕመነኝ አበዳሪዎችህ፤ በቆራጥነት አምላክ ዕድሜህን እንዲያረዝምላቸው ይፀልያሉ፡፡ ከአንተ ሞት የበለጠ የሚያስፈራቸው ነገር የለምና!” ይለናል ፈረንሳዊው ምፅታዊ ደራሲ ፍራንሷ ራቤሌ፡፡ እናስብበት!
አገር በዱቤ መተዳደሯ፤መጨረሻው አሰቃቂ ነው!
“በመበደርና በእዳ ላይ የተመሰረተ ቤተሰብ አንድም ነፃነትን፣ አንድም ውበትን ያጣ ይሆናል” የሚሉትን ፈረንጆች፤ “በሽታ የሌለበት ክሳትና እዳ የሌለበት ድህነት አያሳስብም” በማለት ያጠናክረዋል፤ የወላይታ ተረት፡፡ አገርን በብድር ማስተዳደር አዳጋች የመሆኑን ያህል፤ ብድርን ለመክፈል፤ በጥድፊያ አገር እናለማለን ብሎ ማለምም አደጋ አለው፡፡ ሆነ ራሳችንን የምናይበት የሀብት ማፍራት መንገድ፤ በቅጡ የተፈተሸና በተግባር የተፈተነ መሆን ይኖርበታል፡፡ ምርታማነታችንና አልሚነታችን መፈክርና ዲስኩር ላይ የተንጠለጠለ ሳይሆን፤ በእርግጥ የኢኮኖሚ መስፈርቶችን ቁቤ ያለ ቢሆን አግባብነትና አስተማማኝነት ይኖረዋል፡፡ አለበለዚያ “ጦጣ፤ ጠዋት ነጭ ሽንኩርት ተክላ፣ ማታ ወደቤት ስትመለስ ነቅላ፤ “አይ የመሬት ነገር፤ ይገርማል!” ትላለች፤ የተባለው የወላይታ ተረት ይመጣል፡፡

አዲሱ የኢትዮጵያ ደራስያን ማህበር ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ነባሩን የሥራ አስፈፃሚ አባላት ባለፈው ሐሙስ በወይን ኢትዮጵያ የባህል ምግብ አዳራሽ በደማቅ ሥነ ሥርዓት ሸኘ፡፡
አንጋፋና ወጣት ደራስያን እንዲሁም የልዩ ልዩ ሙያ ማህበራት መሪዎች በተገኙበት  የተሰናባቹ ሥራ አስፈጻሚ አባላት ገጠመኞቻቸውን እያቀረቡ ታዳሚውን ከማዝናናታቸውም በላይ ለስምንት ዓመታት ማህበሩን ሲመሩ፣ የነበራቸው የእርስ በርስ መናበብ ሐላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ብርታት እንደሰጣቸው ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ማህበሩን በፕሬዚዳንትነት የሚመሩት ዶ/ር ሙሴ ያዕቆብ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር እንደገለጹት፤ የግል ሥራቸውንና ማህበራዊ ጉዳዮቻቸውን በመተው ለማህበሩ ዕድገት ሲጥሩ ለነበሩት የቀድሞ መሪዎች ክብርና ሞገስ ሊቸራቸው ይገባል፣ አዲሱ አመራርም አርአያነታቸውን ተከትሎ በትጋትና በፍቅር በመሥራት ማህበሩን ወደተሻለ የዕድገት ደረጃ ከፍ ለማድረግ ይጥራል ብለዋል፡፡
ክቡር አቶ ሙሉጌታ ሰኢድ የኢፌዴሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ በበኩላቸው፤ ለተሰናባቾቹ ሥራ አስፈጻሚ አባላት ማህበሩ ያዘጋጀላቸውን የዋንጫና የአድናቆት ምስክር ወረቀት ከሰጡ በኋላ ባደረጉት ንግግር፣ ሌሎች የሙያ ማህበራት መሪዎችም ከኢትዮጵያ ደራስያን ማህበር ሊማሩ ይገባል፤ ሚኒስቴር መ/ቤታችንም ከኪነ ጥበብ ማህበራት ጋር ለመሥራት ከመቸውም ጊዜ በላይ ዝግጁ ነው ብለዋል፡፡
ቀደም ሲል ማህበሩን በፕሬዚዳንትነት ይመሩ የነበሩት አቶ ጌታቸው በለጠ ከመስከረም 25 ቀን 2006 ዓ.ም ጀምሮ ከሃላፊነታቸው ወርደው በዶ/ር ሙሴ ያዕቆብ ፕሬዚዳንትነት የሚመራ አዲስ ሥራ አስፈፃሚ መሰየሙ ይታወሳል፡፡

Saturday, 14 December 2013 13:06

ማንዴላንአትመልስም!

“የታሪክህ አፅም
ተቆፍሮ ቢወጣ፤
ቀን የጣላት፣ ዘውድ ናት
የደፋሃት ባርኔጣ
የማንነትህ ዙፋን ነው
በርጩማህንም ነፃ አውጣ፣
ሥርወ - ቤትህን አውጅ
ጐጆህ ሀገር ትውጣ
ሳትነግሥ እንዳትሞት
አንጋለህ ሳትቀጣ
ብድርህን ሳትመልስ
ወግረህ ሳትቆጣ”
…እያለ ከሚያዝህ
ከዚያ ውዥንብር መንፈስ፣
ቀልብያህ ሳትድን
ነፍስህ ሳትፈወስ፣
ማንዴላን አታንሳ
ትርጉም ለማልፈስፈስ፡፡
ከተጠናወተህ፤ ስም አይጠሬ ህመም
የትውልድ በሽታ፣
ከሚያስደረድርህ፤ ጠመንጃና መውዜር
በበገና ፈንታ፣
አረር ከሚያስጤስህ
ከከርቤ እያፋታ፣
ጐጆ ከሚያስመልክ
ሀገር እያስረታ፤
ታሞ ካሳመመህ
ከይሄ ርኩስ መንፈስ፣
ቀልብያለህ ሳትድን
ነፍስህ ሳትፈወስ
ሕዋ ያህል ቃልን
በጐጆ አፍ ማወደስ
የጀግናውን ገድል
ትቢያ ላይ መለወስ፡፡

ሳምሶን ጌታቸው ተ.ሥ