
Administrator
በአንድ ጊዜ 16 የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ቻርጅ ማድረግ የሚያስችል የንግድ ቻርጅ ማድረጊያ ማዕከል ሥራ ጀመረ
• ለመዲናዋ የመጀመሪያው ማዕከል ነው ተብሏል
በአንድ ጊዜ 16 የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ቻርጅ ማድረግ የሚያስችል የመጀመሪያው የንግድ ቻርጅ ማድረጊያ ማዕከል በአዲስ አበባ ሥራ የጀመረ ሲሆን፤ በቀጣይም በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች እንደሚስፋፋ ተነግሯል፡፡
ዘመናዊነትና ጤናማ የከተማ ኑሮን ለማንበር ትልቅ ወጪ በማውጣት የተለያዩ ስራዎችን እያከናወነ የሚገኘው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፤ ብክለትን ለመቀነስ የሚረዱ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ከማበረታታት ባሻገር የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች መሰረተ ልማት እየገነባ ይገኛል፡፡ በዚሁ መሰረትም በከተማዋ የመጀመሪያውን የንግድ ቻርጅ ማድረጊያ ማዕከል ሥራ አስጀምሯል፡፡
በሁለተኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት ስራ፣ በከተማዋ 58 የሚደርሱ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ቻርጅ ማድረጊያ ማዕከላት እየተገነቡ እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል፡፡
አዲስ የኢትዮጵያ ኢ-ፓስፖርት ይፋ ሆነ
የኢሚግሬሽን እና የዜግነት አገልግሎት አዲስ የኤሌክትሮኒክስ ፓስፖርትን ይፋ አደረገ ፡፡
አዲሱ ፓስፖርት ደህንነቱ የተጠበቀ እና በሀገር ዉስጥ የሚመረት ነዉ ተብሏል፡፡
ፓስፖርቱ በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኘዉ የለሚ ኢንደስትሪያል ፓርክ የሚመረት ሲሆን ጥራቱ አለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ስለመሆኑም ተነግሯል፡፡
በፓስፖርቱ ገፆች ላይ የሀገር ገፅታ የሚያስተዋዉቁ የኢትዮጵያ መለያዎች እንደተካተቱበትም ለማወቅ ተችሏል፡
ፀሐይ -2 አውሮፕላን የመጀመሪያ የሙከራ በረራዋን በስኬት አጠናቀቀች

የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም
#በዛሬዋ_ዕለት
ከ 88 ዓመት በፊት ልክ በዛሬዋ ቀን በአብርሃም ደቦጭ እና ሞገስ አስገዶም መሪነት በኢጣልያኑ የጦር አዛዥ ጄነራል ግራዚያኒ ላይ በቦንብ ያደረጉት የግድያ ሙከራ ምክንያት የኢጣሊያን ወታደሮች በቂም በቀል በመነሳት በሺዎች የሚቆጠሩ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎችን ለ 3 ተከታታይ ቀናት ዘግናኝ እና ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ በህዝቡ ላይ ጭፍጨፋ ያደረሱበት ዕለት ነበር።
የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም በፋሺስት ኢጣሊያ በግፍ የተጨፈጨፉ ኢትዮጵያውያን ሰማዕታት ሲታወሱ......
የካቲት 12 ቀን በኢትዮጵያ ታሪክ የተለየ ቀን ነው፡፡ የኢጣሊያዋ ኔፕልስ ግዛት ልዑል ልጅ መውለዱን ለመዘከር ግራዚያኒ በዚህ ቀን የአዲስ አበባን ደሃዎች ሰብስቦ ለመመጽወት ባደረገው ጥሪ መሰረት ከ 3ሺ የሚበልጡ አቅመ ደካሞች በጥዋቱ በ 6 ኪሎው ቤተመንግስት ተገኝተዋል፡፡
በዚህ ቀን ኢትዮጵያውያን ጥቃት ሊያደርሱ ይችላሉ የሚለው መረጃ እስከ ሮም በመሰማቱ የቤተመንግስቱ ውስጥና ዙሪያ መትረየስ በታጠቁ ልዩ ወታደሮች እንዲጠበቅ ተደርጓል፡፡ አብርሃ ደቦጭና ሞገስ አስገዶም ይህንን ጠንካራ ጥበቃ አልፈው ውስጥ ገብተዋል፡፡
ከቀኑ ለስድስት ሩብ ጉዳይ አካባቢ ሲሆን ከፍተኛ ፍንዳታ በቤተ መንግስቱ ተሰማ፡፡ ከፍ ወዳለው የቤተመንግስቱ ደረጃ የተወረወረው ቦምብ ደግሞ ግቢውን በጩሀት አናጋው፡፡ የመጀመሪያው ቦምብ ባለመትረየስ ጠባቂውን አስወገደው፡፡ 2ኛው ቦምብ ከግራዚያኒ አጠገብ የነበረውን ምሰሶ አፈራረሰው፡፡ ግራዚያኒ ወደ ውስጥ ሲሸሽ ጀርባው፣ ትከሻውና የቀኝ እግሩን ከ 350 በሚበልጥ የቦምብ ፍንጣሪ ቆሰለ፡፡ የካሜራ ባለሙያውና ወታደሮች ግራዚያኒን ከወደቀበት አንስተው በመኪና በመጫን ወደ ሆስፒታል ይዘውት በረሩ፡፡
ሶስተኛው ቦምብ ፖጊያሊ ፊት በመውደቅ ፍንጣሪው አቡነ ቄርሎስን ሲያቆስላቸው ጃንጥላ ያዣቸውን ደግሞ ገደለው፡፡ የኢጣሊያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ጄኔራል ሊዮታ በቦምብ እግሩን አጣ፡፡ የፋሺስት ፓርቲ ዋና ጸሀፊና የቤተመንግስቱ ጠባቂዎች በድንጋጤ ለምጽዋት በ6 ኪሎ በተሰበሰበው ህዝብ ላይ እሩምታ በመተኮስ ከ1ሺ የሚበልጡትን ገደሉ፡፡ የጥቃቱ ዋና ፈጻሚዎች ሞገስ አስገዶምና አብርሃ ደቦጭ ከጊቢው በመውጣት ተሰወሩ፡፡
በቀጣይ ሰአታት ጥቁር ከነቴራ ለባሽ የኢጣሊያ ልዩ ወታደሮች የቴሌፎንና የፖስታ አገልግሎትን ዘጉ፡፡ ወዲያው መሃል ፒያሳ አራዳ ባለው የፋሽስት ዋና ጽ/ቤት የነበረው ጎዶ ኮርቴሌ የፋሽስት ወታደሮች ለሚቀጥሉት 3 ቀናት ኢትዮጵያውያንን እንዲጨፈጭፉ ትእዛዝ ሰጠ፡፡ በዚሁ ምሽት አዲስ አበባ የእርድ ቄራ ሆነች፡፡
ነዋሪዎቿ ቤት ከውጭ እየተቆለፈባቸው ከውጭ በሚለኮስ እሳት እንዲነዱ ተደረገ፡፡ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች የተገኙት ደግሞ እየታፈሱ በመኪና ተጭነው ተወስደው በግራዚያኒ ዋና መምሪያ ተረሸኑ፡፡ ከሚነዱት ቤቶች አምልጦ ለመውጣት እድል ያገኘውን ደግሞ የኢጣሊያ ወታደሮች ከደጅ ሆነው በጥይት ለቀሙት፡፡
የጥቃቱ አቀናባሪዎችንና አድራሾችን ለመያዝ ጥብቅ ምርመራና አሰሳ ተጀመረ፡፡ የኢጣሊያ ደህንነቶች ከምሽቱ በ 2 ሰአት የአብረሃ ደቦጭን ቤት ሰብረው ሲገቡም እጀታው አረንጓዴ፣ቢጫ እና ቀይ በሆነው የኢትዮጵያ ባንዲራ ቀለማት በተቀባ ሳንጃ የኢጣሊያ ባንዲራ ተቦጫጭቆ አገኙ፡፡ በመቀጠል የሞገስና የአብርሃ ጓደኞችን ማደን ተጀመረ፡፡
አብርሃና ሞገስ ከምሽቱ 1:00 ሰአት አካባቢ ወደ ጀርመን ሚሽን በመሄድ ጓደኛቸው ስብሀትን በአጥር ቢያስጠሩትም ስብሀት አብሯቸው ለመሄድ ዝግጁ ስላልነበር ብቻቸውን ከተማውን ለቀው ሸሹ፡፡ ከጥቂት ሰአታት በኋላ የኢጣሊያ ወታደሮች የጀርመንን ሚሽን በመክበብ ስብሀትን እያዳፉ ወሰዱት፡፡ አርበኛ ሸዋ ረገድ ገድሌንም በማታ ወስደው በኤሌክትሪክ ንዝረት ቢያሰቃይዋትም ሚስጥር ሳታወጣ ቀረች፡፡
ቅዳሜ ጥዋት በድንጋጤ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ሲሯሯጡ የተገኙ ነዋሪችም ታፍሰው ፒያሳ ራስ መኮንን ድልድይ አጠገብ ተረሸኑ፡፡ በአሜሪካ ኤምባሲ ተሸሽገው የነበሩ በ 100ዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን ኤምባሲው አሳልፎ እንደሰጣቸው ኤምባሲው በር ላይ እንደ ውሻ እየተቀጠቀጡ ተገደሉ፡፡
ይህ ለአሜሪካ ህዝብ ይፋ ከሆነ በኋላ የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚ/ር እና ኢትዮጵያ የሚገኘው አምባሳደር ዜናውን በማግስቱ አስተባበሉ፡፡ ምኒልክ አደባባይ አቅራቢያ ሆኖ ይህንን ግፍ ይመለከት የነበረው ወጣቱ ልጅ እምሩ ዘለቀም ከሰአታት በኋላ ቤቱን ሰብረው በገቡ የኢጣሊያ ወታደሮች ከእናቱና 2 እህቶቹ ጋር ተይዞ ታሰረ፡፡
እሁድ እለት የ 3 ቀኑን ጭፍጨፋ ለማስቆም በአዲስ አበባ የተለያዩ ቦታዎች የሚከተለው አዋጅ ተለጠፈ፣
“ ሞሶሎኒ እንደ ፈጣሪ ሃያል ነው፡፡ ፈጣሪም ሆነ ሞሶሎኒ ተመሳሳይ ባህሪ አላቸው፡፡ ሞሶሎኒ ተበሳጭቶባችሁ ነበር፡፡ አሁን ግን ቁጣው በርዷል፡፡ ወደ የቤታችሁ በመሄድ እለታዊ ተግባራችሁን ቀጥሉ፡፡”
ይሁን እንጂ ከዚህ አዋጅ በኋላም ግድያው ቀጥሎ ነበር፡፡ የበቀል ቅጣቱን ለማምለጥ ከቤታቸው ከወጡት ወደ 5ሺ የሚጠጉ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ውስጥ ብዙዎቹ የአርበኞችን ትግል ተቀላቀሉ፡፡ በሁለት ቀን ተኩል በኢጣሊያ የግፍ ጭፍጨፋ የተገደሉትን የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር አንዳንድ ወገኖች እስከ 30ሺ እንደሚደርስ ሲገልጹ ሌሎች ደግሞ ቁጥሩን ከላይ 17ሺ - 18ሺ ያደርሱታል፡፡
©️ የአርበኞች ጀብዱ፣ Jeff Pearce እንደጻፈው፣ ኤፍሬም አበበ እንደተረጎመው፣ ገጽ 205-212
ክብና ዘላለማዊ ዕረፍት ለሰማዕታት ????
#ታሪክን_ወደኋላ
የረዳን ፈጣሪ ይመስገን!
በበጎነት የመኖሪያ መንደር" ለአቅመ ደካሞች እና ለልማት ተነሺዎች ያስገነባናቸውን 192 የመኖሪያ ቤቶችን የያዙ ሁለት ባለ 9 ወለል ህንጻዎች ለነዋሪዎቻችን አስተላልፈናል።
አዲስ አበባ ባለፉት 6 ወራት ምን አከናወነች
• ከተሰበሰበው ግብር 70 በመቶው ህዝብን ለሚጠቅሙ ተግባራት ውሏል
• በግማሽ ዓመቱ 111.6 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡ ተነግሯል
• አስተዳደሩ ከዕቅዱ 90 በመቶውን ማሳካቱን አስታውቋል
የ2017 በጀት ዓመት የስድስት ወራት ዕቅድ አፈጻጸሙን ባለፈው ሳምንት ማገባደጃ ላይ የገመገመው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፤ ባለፉት ስድስት ወራት ጠንካራ የሥራ ባህል፣ የአመራር ቁርጠኝነትንና ቅንጅትን በማጠናከር፣ እንዲሁም የገቢ አሰባሰብን በማሳደግ፤ በርካታ ፕሮጀክቶችን በተያዘላቸው ጊዜና በጀት፣ በጥራት አጠናቆ፣ ለህዝብ አገልግሎት ክፍት ማድረግ መቻሉ ተነግሯል።
በግምገማው ወቅት የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት ክብርት ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ ባለፉት ስድስት ወራት በሁሉም ዘርፎች አመርቂ አፈጻጸሞች መመዝገባቸውን ጠቁመው፤ የከተማ አስተዳደሩ ከዕቅዱ 90 በመቶውን ማሳካት መቻሉን አረጋግጠዋል፡፡
በእነዚህ ስድስት ወራት የከተማዋን ገጽታ የቀየሩና የህዝቡን የልማት ጥያቄ የመለሱ ሰፋፊ ስራዎች መከናወናቸውን የገለጹት ከንቲባዋ፤ “አገልግሎት አሰጣጣችንን ቀልጣፋና ከብልሹ አሰራር የጸዳ ለማድረግና መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት አሰራራችንን ዲጂታላይዝ ለማድረግ አቅደን የሰራናቸው ሥራዎችም ለውጦችን አሳይተዋል” ብለዋል፡፡
በግማሽ ዓመቱ በመዲናዋ 111.6 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡ የተገለጸ ሲሆን፤ ይህም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ50 በመቶ ብልጫ ማሳየቱ ተነግሯል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደራዊ ወጪንና ብክነትን በመቀነስ፣ አብዛኛው ገቢ፣ ነዋሪዎችን ለሚጠቅም ተግባር በመዋሉ፣ ፈጣን ለውጦችን ማስቀጠል መቻሉንም ነው ከንቲባ አዳነች አቤቤ የጠቆሙት፡፡
“ከህዝብ ከሰበሰብነው ግብር 70 በመቶ የሚሆነውን የነዋሪዎቻችንን እንግልት ለሚቀንሱና ህዝብን ለሚጠቅሙ ተግባራት እንዲሁም ለዘላቂ ልማት በማዋላችን፣ የፈጣን ለውጦቻችንን ቀጣይነት አስጠብቀናል” ብለዋል፤ከንቲባዋ ፡፡
“ባለፉት ስድስት ወራት የዕቅድ አፈጻጸማችን፣ ከተማችንን ከነዋሪዎቿ ኑሮና አኗኗር ጋር አስተሳስረን ውብና አበባ የማድረግ እንዲሁም የቱሪስት መተላለፊያ ሳትሆን፣ መዳረሻ እንድትሆን ለማድረግ አቅደን እየሰራን ያለነውን ስራ ቀጣይነት እንዲኖረው ማድረግና ውጤታማነቱን ማስጠበቅ ችለናል” ሲሉም አክለዋል።
በተለያየ እርከን የሚገኙ የከተማ አስተዳደሩ አመራሮች በተሳተፉበት የዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ ላይ ሰፊ ማብራሪያ የሰጡት ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ በመዲናዋ የተከናወኑ ጎላ ጎላ ያሉ ተግባራትንና የተገኙ ውጤቶችንና ለውጦችን ዘርዘር አድርገው አቅርበዋል፡፡ የተስተዋሉ ጉድለቶችንና ውስንነቶችንም ጠቃቅሰዋል፡፡
በመዲናዊ ሰፊ የሥራ ዕድል እየተፈጠረ መምጣቱን ያነሱት ከንቲባዋ፤ አዲስ አበባ 24 ሰዓት የምትሰራ ከተማ ናት ብለዋል - ቀንም ሌሊትም፡፡ መሥራት ለሚችሉና ሥራን ለማይመርጡ ሁሉ በሯን ከፍታ እያስተናገደች እንደምትገኝም ጠቁመዋል፡፡
የኑሮ ጫናን ለማቃለል የተከናወኑ ተግባራት
የከተማው ህዝብ ያለበትን የኑሮ ውድነት ጫና ለማቃለል ታልመው የተከናወኑ በርካታ ተግባራት እንዳሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገልጸዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል በመዲናዋ የተለያዩ አካባቢዎች ተገንብተው አገልግሎት መስጠት የጀመሩ ትላልቅ የገበያ ማዕከላት ይጠቀሳሉ፡፡ እነዚህ የገበያ ማዕከላት በአብዛኛው የግብርና ምርቶችን እንዲሁም አትክልትና ፍራፍሬዎችን በቀጥታ ከአምራቹ ለሸማቹ (ደላላን ከመሃል በማስወጣት) የሚቀርብባቸው ናቸው፤ በተመጣጣኝ ዋጋ፡፡ ከዚህም ባሻገር፣ የኢትዮጵያ ገበሬዎች፣ ያለአንዳች ችግር አዲስ አበባ ውስጥ ገብተው፣ ምርታቸውን ሸጠው የመውጣት ዕድል እንደከፈተላቸውም ከንቲባዋ አንስተዋል፡፡
ከንቲባ አዳነች በተጨማሪም፣ በትራንስፖርት እንዲሁም በጤና መድህን በሚሊዮኖችና ቢሊዮኖች በጀት በመመደብ፣ ነዋሪው በተመጣጣኝ ዋጋ አገልግሎት ማግኘት እንዲችል እያደረግን ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡ “ይህም ለህዝባችን የገባነውን ቃል በተግባር መፈጸማችንን ማሳያ ነው” ብለዋል፡፡ በሌላ በኩል፣ በመዲናዋ በቀን 35ሺ የሚደርሱ ዜጎች በነጻ የሚመገቡባቸው የምግብ ማዕከላት ቁጥር 26 መድረሳቸውን ገልጸዋል፤ ሁለቱ ገና አገልግሎት አለመጀመራቸውን በመጠቆም፡፡ ዘንድሮ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት በርካታ የልማት ጥያቄዎችንና የኑሮ ውድነት ጫናዎችን ማቃለል በሚቻልበት ደረጃ መሰራቱንም ተናግረዋል፡፡ ባለፉት ስድስት ወራት በበጎ ፈቃድ ወደ 9.2 ቢሊዮን ብር ገደማ የሚሆን ወጪ መሸፈኑን የጠቆሙት ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ ይሄ የሚያስደንቅ ክንውን ነው ብለዋል፡፡
በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ መሻሻል ታይቷል
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በሰጡት ማብራሪያ፤ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ መሻሻል መምጣቱን ተናግረዋል፡፡ “ሰራተኞቻችንን መፈተን እና መመዘን አለባችሁ ምክንያቱም ህዝቡ በአገልግሎት እየተማረረ ነው፡፡ይሄን ዕድል የሰጠን ህዝብ ስለሆነ ህዝባችንን ለማገልገል የሚያስችል ብቃትም፣ሥነምግባርም፣ተነሳሽነትም ሊኖረን ይገባል የሚል እምነት ሰራተኞቻችን ላይ መፍጠር መቻሉ አንድ እርምጃ ነዉ፡፡” ሲሉ አስረድተዋል፡፡
ሁለተኛው ደግሞ ይላሉ ከንቲባዋ፤ “ሁለተኛው እርምጃ ደግሞ ፈተና ሰጥተን ሥራና ሰራተኛን (ባለሙያን) ለማገናኘት የሄድንበት ሂደት ነው፤ በእርግጥ በደንብ እየተመዘነ መታየት አለበት፡፡ ነገር ግን ሂደቱም ለውጥ ነው” ብለዋል፡፡ ምክንያቱንም ሲያስረዱ፤ “አንዴ ሰራተኛ ሆኜ ከተቀጠርኩ አልነካም የሚለው አስተሳሰብ መሰበሩ በራሱ ለውጥ ነው” ይላሉ፡፡
በርካታ አሳሪ አሰራሮች ተፈተዋል
ከዚህ ቀደም የነበሩ በርካታ አሳሪ አሰራሮችን ፈተናል ያሉት ከንቲባ አዳነች፤ ”ቀልጣፋ አሰራርና ግልጽነት እንዲኖር ህዝቡን የሚያሳትፍና አቅሙን የሚገነባው እንዲሁም እኛን ግልጽ ለመሆን የሚያስገድዱን አሰራሮችን አውጥተን ተግብረናል” ሲሉም አብራርተዋል፡፡
ሦስተኛው እርምጃ ቴክኖሎጂ ነው ይላሉ፡፡ 87 ያህል የአገልግሎት ዓይነቶችን በቴክኖሎጂ አገልግሎት መስጠት ጀምረናል ያሉት ከንቲባዋ፤የስራ ቦታ ምቹ እንዲሆኑ፣አገልግሎት የሚፈልጉ ተገልጋዮች ፊት ለፊት ከሰራተኞች ጋር እየተያዩ አገልግሎት የሚያገኙበት እንዲሁም ኃላፊዎች ያለውን የስራ እንቅስቃሴ መከታተልና መቆጣጠር የሚችሉበት ሁኔታ እንዲቀል እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
አምና በዚህ ወቅት ስንገመግም እዚህ ከነበረው አመራር ውስጥ ረቡዕና አርብ ቁጭ ብሎ አገልግሎት የሚሰጠው 64 በመቶ ያህሉ ብቻ እንደነበር ያስታወሱት ከንቲባ አዳነች፤ ዘንድሮ አገልግሎት የሚሰጠው አመራር 89 በመቶ መድረሱን ተናግረዋል፤ይሄም ለውጥ መሆኑን በመጠቆም፡፡
በብልሹ አሰራር ላይ ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት በተደረገው ጥረትም፣ ባለፉት ስድስት ወራት ለመጀመሪያ ጊዜ በብልሹ አሰራር የተጠረጠሩ 78 ዳይሬክተሮችና 2ሺ46 የሚሆኑ ሰራተኞች ተጠያቂ እንዲሆኑ መደረጋቸውን ከንቲባዋ ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ባለፈም በከተማችን ውስጥ የተጠረጠሩ 928 የሚሆኑ ግለሰቦች ለህግ እንዲቀርቡ መደረጋቸውንም አክለዋል፡፡
የጥንካሬያችን ምንጭ ምንድን ነው?
የእነዚህ ጥንካሬዎች መነሻ ምንድን ነው ሲሉ የሚጠይቁት ከንቲባዋ፤ የመጀመሪያው አመራር ነው ይላሉ፡፡ “አመራሩ በየደረጃው ሃላፊነቱን ለመወጣት የሚያደርገው ጥረት ተነሳሽነት እንዲሁም መሰጠት እነዚህን ለውጦች ማስመዝገብ ችለዋል” ብለዋል፡፡ ሁሉም የራሱን ሃላፊነት ለመወጣት፣ የተሻሻለ የሥራ ባህል ለመፍጠር እንዲሁም የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት የሚደረጉ ጥረቶች የዚህ ማሳያዎች ናቸው፤ ሲሉም ያብራራሉ፡፡
ሁለተኛው የገቢ አሰባሰባችን መሻሻል ነው ይላሉ፤ በዚህ ስድስት ወር ከአምናው ተመሳሳይ ጊዜ 50 ፐርሰንት ጭማሪ ያለው ገቢ መሰብሰብ መቻሉን በመግለጽ፡፡ የተሰበሰበው ገቢም ወደ 37 በመቶ ዕድገት አሳይቷል ተብሏል፡፡
በርካታ የመልካም አስተዳደር፣ የልማትና ማህበራዊ ውዝፍ ጥያቄዎች ያሉበት ትልቅ ከተማን ችግር ለመፍታት፣ በመንግሥት በጀት ብቻ እንደማይወጡት መገንዘብ መቻላቸውን የሚናገሩት ከንቲባዋ፤ ለዚህም “ዝቅ ብለን የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን ግንዛቤ ፈጥረንና አሳምነን፣ በበጎ ፈቃድ የተለያዩ የልማት ጥያቄዎች እንዲሟሉ አድርገናል” ይላሉ፡፡ ባለፉት ስድስት ወራት 9 ቢሊዮን ብር ገደማ የሚሸፍኑ ሥራዎች መከናወን መቻላቸውን - በመግለጽ፡፡
ይሄ ብቻ ግን አይደለም፡፡ የመንግሥትና የግል አጋርነትም አዲስ አበባ ላይ በደንብ እየተተገበረ መሆኑን በመጠቆም፤ በመዲናዋ የ120ሺ ቤቶች ግንባታ መጀመሩን ለአብነት ይጠቅሳሉ፡፡
በሌላ በኩል፤ ትልቁ የጥንካሬያችን ምንጭ የበጀት አጠቃቀማችን ነው፤ ይላሉ ከንቲባዋ፡፡ “ሩቅ ሳትሄዱ የዛሬ አራትና አምስት ዓመት የነበረው ዳታ በእጃችን አለ፡፡ ካፒታል በጀት ከ50 እጅ በታች ነው የነበረው፡፡ በዚህ ሩብ ዓመት 70 እጁ ነው ለካፒታል በጀት የዋለው፡፡” ብለዋል፤ በንጽጽር በማሳየት፡፡
ሌላው የጥንካሬ ምንጭ ደግሞ ውጤታማ የክትትልና የቁጥጥር (ሱፐርቪዥን) ሥራ መሆኑን የገለጹት ከንቲባ አዳነች፤ “ቆመን ባንከታተል በዚህ ደረጃ ውጤት ሊመጣ አይችልም ነበር” ሲሉ አስረግጠው ይናገራሉ፡፡ የክትትልና የድጋፍ ሥርዓቱ ውጤትን የሚያመጣ ይሆን ዘንድ የሚሰራን የሚያበረታታ፣ ጉድለት ያለበትን ጉድለቱን ማሟላት የሚችልበትን አቅም እንዲፈጥር የሚደግፍ ሆኖ መቀረጽ እንዳለበትም ያስረዳሉ፡፡ ክትትልና ድጋፍ እንዲሁም ሱፐርቪዥንና ኦዲት የሚያደርጉት ደግሞ የተለያዩ አካላት ናቸው - ከምክር ቤት እስከ ፌደራል መንግሥት እንዲሁም እስከ ፓርቲ የሚደርሱ፡፡
ወደ ኋላ መመለስ አይታሰብም
ከንቲባዋ የተመዘገቡ ውጤቶችንና የመጡ ለውጦችን ብቻ አይደለም የዘረዘሩት፤ ጉድለቶችንና ውስንነቶችንም አንስተዋል፡፡ ውጤቶችና ለውጦች የተገኙበትን መንገድ ስናይ በብዙ ክትትል፣ በብዙ ጉትጎታና በብዙ ግምገማ ነው የሚሉት ከንቲባዋ፤ በትጋት ሰርቶ ውጤት ማስመዝገብ ገና ባህልና ልምምድ አለመሆኑን ይገልጻሉ፡፡ “ክትትልና ጉትጎታው ቀዝቀዝ ቢል የጀመርናቸው ሥራዎች ይቀዛቀዛሉ፤ ስለዚህ ወደ ባህል መቀየር አለብን” ብለዋል፡፡
ከንቲባዋ አክለውም፤ “አቅዶ 24 ሰዓት መሥራትን እንዲሁም በሽፍት መሥራትን ባህል ልናደርገው ይገባል፡፡ ጽዳትና ውበት ባህል መሆን አለበት፤መቆሸሽን መጠየፍ አለብን፡፡ እኒህ የምንላቸውን አሰራሮች እንዲሁም ውጤታማነትን ባህል እያደረግን ለመሄድ ነው ማቀድ ያለብን፡፡ አዲስ አበባ ይሄን ጉዞ ጀምራለች፤ ወደ ኋላ መመለስ አይቻልም፤ መመለሻ መንገድም የለም፤ መሄድ ያልቻለ ይወጣል እንጂ፡፡” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በግምገማው ማጠናቀቂያም የአፈፃፀም ውስንነትን በማስተካከል፣ አገልግሎት አሰጣጥ በቴክኖሎጂ በማስደገፍ፤ፈጣን፤ቀልጣፋና ተደራሽ እንዲሆን አሰራሮችን ይበልጥ በማዘመን፣ ብልሹ አሰራርና ጉቦኝነትን በመታገል እንዲሁም የገቢ አሰባሰብና ቅንጅታዊ አሰራርን በማጠናከር የተጀመሩ ስራዎችን በጥራትና በፍጥነት ለማጠናቀቅ በትኩረት እንደሚሰራ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡
“አለማችን ፕላኔታዊ ውሕደት ያስፈልጋታል”
--የመጀመሪያው ሁለንታዊ መድረክ በተዘጋጀበት አዳራሽ ውስጥ ከዓለም ሀገራት ተወክለው የመጡ ሰዎች እንዲሁም ባረኖች በረድፍ በረድፋቸው ተቀምጠዋል። የመድረኩ የአዘጋጅ ክፍል አባላት (እኔን ጨምሮ) የቅድመ አዳራሽ ሥነ ስርዓቶችን አስፈፅመናል፤ የትውውቅ፣ የቁርስ፣ የሙዚቃ፣ የፎቶና ቪዲዮ ትዕይንት… ሁሉም የቅድመ አዳራሽ መርሃ ግብር በስኬት ተከናውኗል። አሁን አዳራሹ ውስጥ ሁሉም የጥያቄና መልሱን መጀመር በብሩህ ስሜት፣ በኃይልና በንቃት ተሞልቶ እየጠበቀ ነው።
የመድረኩ ተቀማጮች ሰባት ናቸው፡ ሦስት ሰዎች፣ ሦስት ባረኖችና የሰዎች እና የባረኖች አማካይ የሆነቺው ሊሊት። ሊሊት የተቀመጠቺውም ሰዎች እና ባረኖች መካከል ነው። ሊሊትን ለማየት ያልጓጓ ማን ነው? በአፈታሪክ የተሳለልንን ያን ቁመናዋንና ቁንጅናዋን በምናባችን ይዘን ሁላችንም ሊሊትን እስክናይ ቋምጠን ነበር። እንደ ባረኖች ሁሉ እሷም ብርሃን ለብሳ ስናገኛት ግን የቆመው ልባችን ሳይረካ ቀረ። ….ሦስቱ ባረኖች ከግራ ወደ ቀኝ፡ የመጀመሪያዋ ባረን09 ትባላለች፣ ሁለተኛዋ ባረን217፣ ሦስተኛዋ ባረን199። ሦስቱም ባረኖች ፌደሬሽኑን ለመመሥረትና ለማስፋፋት ከፍተኛ ሥራ የሠሩና የሰው ልጅን በደንብ ያውቃሉ የሚባልላቸው ናቸው። ሲቆሙ ላስተዋላቸው ሴቶቹ ባረኖች ከወንዶቹ የሚረዝሙ ይመስላሉ፤ ድምፃቸው ከወንዶቹ ባረኖች ይልቅ ወፍራምና ሸካራ ነው። ብርሃናቸው ስለሚከልላቸው ፀጉራቸውን (ፀጉር ካላቸው) ያሳድጉ አያሳድጉ ባላውቅም፣ ሴቶችም ባረኖች እንደ ወንዶቻቸው ሁሉ ራሰ ከባድ ናቸው። ሰዎቹ የመድረኩ ተቀማጮች ደግሞ ከግራ ወደ ቀኝ በቅደም ተከተል በሁለንታዊ ስማቸው የመጀመሪያዋ ሂዩባረን77 ትባላለች፣ ሁለተኛዋ ሂዩባረን222፣ ሦስተኛው ሂዩባረን21። ሂዩባረን77 የጥቁር ጠይም የበሰለች ወጣት ሴት ናት፣ የሚያማምሩ ዐይኖችና ወከክ የሚያደርግ ፈገግታ ታድላለች፣ መናገር በጀመረች ቁጥር ቀድማ ፈገግታዋን እንደ መብረቅ ተግ ታደርጋለች። ሂዩባረን222 ፀጉሯ በግማሽ የሸበተ ሸንቃጣ ሴት ናት፣ ብሩህ ቡናማ ፊትና ውብ ሰማያዊ ዐይኖች አሏት። 77ቷና 222ቷ ሁለቱም ዋነኛ የትምህርትና የምርምር ዘርፋቸው በይነፕላኔታዊ ንፅፅራዊ ማህበረ-ፖለቲካዊ ምህንድስና ነው። ሂዩባረን21– የጥቁር ጠይሙ፣ ጎልማሳው፣ ሽበታሙ ሸበላ የመጀመሪያው ሁለንታዊ መድረክ ላይ የነበረው የኢንተርፕላኔታሪ ኮምንኬሽን ተቋምን የሚመራው ሰውዬ ነው።
የጥያቄና መልስ መርሃ ግብሩ ከመጀመሩ በፊት ሁሉም የአዳራሹ ሰው እና ባረን ለሊሊት ክብር ለአንድ ደቂቃ ተነስቶ አጨበጨበ። ሊሊት ተነስታ ሰግዳ አመሰገነች። ያቺ ሊሊት– የመጀመሪያዋ ሴት፣ እናም የመጀመሪያዋ እብሪተኛ– ሰውነቷን (እና ሴትነቷን) በራሷ ጥረት የፈተሸቺው– የፈለገቺውን ለማግኘትና የፈለገቺውን ለመሆን ቆርጣ ከገነት የወጣቺው ሊሊት። ሊሊት ቁመቷ ከባረኖቹ ይበልጣል፣ የሰውነቷ ቅርጽ እንደ ሰው ልጅ ሴቶች ቅርጽ ነው፣ ድምጿ ትንሽ ቢሻክርም እንደ ሰው ልጅ ሴት ድምፅ ቀጭንና አባባይ ነው። እውነት ሰው ናት? እውነት ሴት ናት? እውነት እንደ ሴት ልጅ የሚታቀፍ፣ የሚለስልስ፣ የሚሞቅ፣ የሚደማ ገላ አላት? ባየኋት።
በሊሊት የጉጉት ሀሳብ ስሸመጥጥ መድረኩ ተጀምሯል። ሁለተኛው ሁለንታዊ መድረክ ለሰው ልጅ እውነተኛ ስልጣኔና ህብረት እንቅፋት በሆኑ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነበር። ጉዳዩ ለሰው ልጆች ሁሉ የሚጠቅም በመሆኑ መዝግቤ እነሆ አንብቡት እላችኋለሁ፡
ጠያቂ፡ በአፈታሪክ የምናውቃት ሊሊት እውነት ሆና ወደ ምድር በመመለሷ የተሰማኝን ስሜት የምገልፅበት ቃል የለኝም። የሁለቱ ፕላኔቶች እንዲሁም የሰው እና የባረን አማካይ እንደመሆኗ እኔ የመጀመሪያ የሆነውን ጥያቄዬን ማቅረብ የምፈልገው ለሊሊት ነው። ምድር ላይ ይሄን ፌደሬሽን የመሠረቱት ሰዎች እና ባረኖች አበክረው ሰዋዊና ፕላኔታዊ አንድነት ስለመመሥረት ይናገራሉ። የተወደድሽው እህታችን፣ ስለዚህ ጉዳይ ምን ትያለሽ?
ሊሊት፡ በመጀመሪያ አንድ አሳዛኝ እውነታ ልንገራችሁ፡ እስካሁን በሁለንታው ውስጥ ከማውቃቸው የአእምሮና የማሰብ ችሎታ ካላቸው ፍጡራን ውስጥ ዘራዊና ፕላኔታዊ አንድነት የሌለው የሰው ልጅ ብቻ ነው። ሌሎቹ የሰለጠኑ ፍጡራን ምንም ያህል ለሌሎች ለማይመስሏቸው ፍጡራን ክፉ ቢሆኑም እንኳን እርስ በርስ ግን አይጠፋፉም። የዚህ መሠረታዊ ምክንያቱ የሰው ልጅ ሰዋዊ አንድነት ከዚያም ፕላኔታዊ አንድነት አለመገንባቱ ነው። የሰው ልጅ ሰዋዊ አንድነት እንዳይኖረው ያደረገው ዋናው ምክንያት ደግሞ ራሱን በትናንሽ ማንነቶች ማጠሩ ነው። የሰው ልጅ አንድነት ጠላቶቹ ትናንሽ ማንነቶቹ ናቸው። እነዚህ ትናንሽ ማንነቶች ከሰው ልጅ መሠረታዊ ተፈጥሮ ያልመነጩ፣ የሰው ልጅ በሂደት በራሱ ላይ የጫናቸው ማንነቶች ናቸው። እነዚህ ትናንሽ ማንነቶች ለአብዛኛው የሰው ልጅ ችግር፣ መከፋፈልና ጦርነት መነሻዎች ናቸው። የሰው ልጅ የህዋ ስልጣኔን በጀመረበት በዚህ ዘመን እነዚህን ትናንሽ የማንነት ድርቶች አውልቆ መጣል አለበት። ስለ እነዚህ ትናንሽ ማንነቶች ዝርዝር በጉዳዮቹ ላይ ጥናት ያደረጉ ሰዎች እና ባረኖች እህት ወንድሞቼ የበለጠ የሚነግሩን ይሆናል።
ሊሊት ስትናገር ልክ እንደ ባረኖች ቃላቶቿ የአፏን እንቅስቃሴ ቀድመው ይወጣሉ፣ ተናግራ ስትጨርስ ወይ መሐል ላይ እልባት ስታደርግ ደግሞ ድምጿ ከአፏ እንቅስቃሴ ቀድሞ ያቆማል። እንግሊዝኛውን ታቀላጥፈዋለች። ከመቼው?
ጠያቂ፡ የሰው ልጅ ትናንሽ ማንነቶች የምትሏቸው የትኞቹን ማንነቶች ነው? ለስልጣኔና ለሰዋዊ አንድነት እንቅፋት ሊሆኑ የሚችሉትስ እንዴት ነው?
ሂዩባረን77፡ የሰው ልጅ ትናንሽ ማንነቶች ከፋፋይ ሃይማኖት፣ ጎሳ ነገድ ወይም ብሄረሰብ፣ የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም፣ የታሪክ ቅራሪ፣ የሀገር ድንበርና ብሔርተኝነት እንዲሁም የሰው ልጅን ውጫዊ አካላዊ ሁኔታን ወይም ቀለምን መሠረት ያደረጉ ማንነቶች ናቸው። እነዚህ ማንነቶች ከሰው እውነተኛ ተፈጥሮ ውጭ የሆኑ ሰው ሠራሽ ማንነቶች ናቸው። እነዚህ ማንነቶች የተቀባቡ የውሸት ሥሪቶች ናቸው፣ የሰው ልጅን በየቦታው እኛ እና እነሱ እያሉ ስለሚሸነሽኑ የሰዋዊ መስተጋብር ጋሬጣዎች ናቸው። እነዚህ ትናንሽ ማንነቶች የግብዝነት፣ የድንቁርና፣ የራስ ወዳድነት፣ የኢፍትሐዊነት፣ የመናቆርና የጦርነት መነሻዎች ናቸው። የሰው ልጅ በእነዚህ ትናንሽ ማንነቶች ውስጥ ሆኖ ዐይኑን ገልጦ እውነትን ለማየት አይችልም።
ሂዩባረን222፡ የሰው ልጅ ሲወለድ ንፁህ ነው፣ ሰው ብቻ ነው። እያደገ ሲሄድ በትናንሽ ማንነቶች ይቆሽሻል። መጀመሪያ በሃይማኖት ጣሳ ውስጥ ያስገቡታል፤ ከዚያ በጎሳ፣ በብሔረሰብና በሀገር ብሔርተኝነት ገመድ ይተበትቡታል፤ ከዚያ የታሪክ፣ የፖለቲካና የርዕዮተዓለም ሸክም ይጭኑታል። አደግሁ፣ በሰልሁ ሲል እውነቱን በእነዚህ ትናንሽ ማንነቶች ውስጥ አጥሮ ይገነባል። በዚህ አጥር ውስጥ እንደኳተነ በመጨረሻም እውነተኛ ማንነቱን ሳያውቅ ያልፋል። በከንቱ ማለፍ ብቻ አይደለም እነዚህ ትናንሽ ማንነቶቹን ለቤተሰቡና በዙሪያው ላሉት አውርሶ ነው የሚያልፈው። ሂደቱ አዙሪት ነው። እነዚህ ትናንሽ ማንነቶች እንደ ወሳኝ እውነታ ተቆጥረው በመሠረቱ አንድ አይነት ተፈጥሮና ፍላጎት ያለውን ሰው ከፋፍለው ሲያፋጁት ይኖራሉ።
ባረን199፡ እህቶቻችንና ወንድሞቻችን ስለሆኑት የሰው ልጆች የምናውቀውን ያህል በቅንነት እንናገራለን። የምንናገረው በሰው ልጅ ሕይወት ውስጥ ጣልቃ መግባት ስለምንፈልግ አይደለም፣ የምንናገረው ከሰው ልጅ ጋር ያለን ህብረት እንዲሰምር ነው። በህብረቱ እኛም የሰው ልጅም ተጠቃሚ ነን። ህብረታችን እንዲሰምር ታዲያ የሰው ልጅ ለእውነተኛ ስልጣኔው እንቅፋት የሆኑበትን ችግሮች መቅረፍ አለበት። እነዚህ ችግሮች እንዲቀረፉ ከሰዎች እህት ወንዶሞቻችን ጋር ተባብረን እንሠራለን፣ በገባን ልክ እንናገራለን። ከፋፋይ ሃይማኖት፣ ዘር ነገድ ወይም ጎሳ፣ ንዑስ ወይም ብሔረሰባዊ ብሔርተኝነትና የሀገር ብሔርተኝነት፣ ትናንሽና ትላልቅ የፖለቲካ ርዕዮተዓለሞች፣ ያለፈና የማይለወጥ ታሪክንና ትርክትን እየሳቡ እያመጡ በእሱ መነታረክና መከፋፈል… እነዚህና የመሳሰሉት ነገሮች በሰዎች መካከል የተሰነቀሩ ሰው ሰራሽ ድንበሮች ናቸው። የሰው ልጅ እውነተኛ ሞራላዊና ቁሳዊ ስልጣኔ ላይ የሚደርሰው እነዚህን የውሸት ድንበሮቹን አፍርሶ ሰዋዊና ፕላኔታዊ አንድነት ከፈጠረ ብቻ ነው።
ሂዩባረን21፡ ከሌላው የሰው ልጅ የሚለየንን ማንኛውንም ስብከት ልንቀበል አይገባም። በሰዎች መካከል የሚደረገውን ጋብቻ ከዝምድና በስተቀር የትናንሽ ማንነቶች አጥር ሊያግደው አይገባም። የጥላቻና የፖለቲካ ቀውስ አንዱ መነሻ ዘረኝነት ነው። የዘረኝነት መነሻችን አንዱ የመልካችን መለያየት ነው። የቀለማችንና የመልካችን ይሄን ያህል መለያየት አንዱ ምክንያት ደግሞ ቀደምቶቻችን ጋብቻቸውንና ዝምድናቸውን በጠባብ የማንነት ክበቦች ውስጥ አጥረው መኖራቸው ነው። የሰው ልጆች በነዚህ የውሸት ድንበሮች ሳንወስን እንገናኝ፣ እንተሳሰብ፣ እንጋባ እንዋለድ እንዛመድ። ያን ጊዜ ድንበሩና አጥሩ መፍረስ ይጀምራል፣ እውነተኛ ማንነታችን ይገለጣል፣ የሰላምና የፍትሕ መንገድ ይሰፋል። እርግጥ ነው ብዙ ሰዎች እነዚህን የውሸት አጥሮች እየዘለሉ ሲገናኙና ሲዛመዱ ኖረዋል። ሆኖም አጥሮቹ ተዘለሉ እንጂ ገና አልፈረሱም።
ጠያቂ፡ ሃይማኖት ሰው ከፈጣሪው ጋር የሚገናኝበት መንገድ ነው። ይሄን መንገድ እንዴት ይፍረስ ትላላችሁ?---
ከአዘጋጁ፡- በአብርሃም ገነት
ከተጻፈውና ሰሞኑን ለንባብ ከበቃው “ሳላዛት” የተሰኘ ረዥም ልብወለድ መጽሐፍ የተቀነጨበ ነው፡፡
የነብይ ገፅ
ከአድማስ ትውስታ ፤ 1993
ከትዝታ ፈለግ- 2 በግ ከአራጁ ጋር!!
ማእከላዊ እስር ቤት ያየሁትን ሁሉ ማስታወስ አልችልም፡፡ አንዳንድ የማልረሳቸውም አሉ፡፡-ጨለማ ቤት በገባሁ ማግስት ጥዋት ዶክተር ካሳሁን መከተን አወቅሁት፡፡
ማዕከላዊ - ታች ግቢ- 7 ቁጥር “ጨለማ ቤት” ይባላል፡፡ ነጥሎ (ለይቶ) ማስቀመጫ (Solitary confinement) ክፍል ነው፡፡ 7 ቁጥር ውስጥ አራት ትንንሽ ክፍሎች አሉት፡፡ መንግሥት “ቀንደኛ ፀረ- አብዮተኛ” የሚላቸውን የሚዘጋባቸው ክፍሎች ናቸው፡፡
እንደሰማሁት የእኔ ክፍል (Cell) ፍቅሬ ዘርጋው ከኢህአፓ ሰዎች አንዱ ነበረባት፡፡ ፍቅሬን ሕግ ትምህርት ቤት አውቀዋለሁ፡፡ እንደአጋጣሚ ካዛንችስ- ሼል ከፍተኛ 15 ቀበሌ 32 የተከራየሁት አፓርታማ የፍቅሬ ነበር፡፡ እኔ የመጣሁ እለት ለእኔ ክፍት ቦታ ለመፍጠር ይሆን ግጥምጥም ሆኖ፣ ፍቅሬ የዚያን ዕለት ማታ ተረሸነ፡፡ ሳስበው ይህ ነገር ከአጋጣሚ በላይ መሰለኝ፡፡ ሕግ ትምህርት ቤት… ካዛንችስ… ጨለማ ቤት አጉል መከታተል ነው፡፡ አካሄዱን አልወደድኩትም፡፡ ሊወድ የሚችልም ያለ አይመስለኝም፡፡ የእኔ ደወል የተደወለ መሆኑን ያሳያል፡፡
የ”ምናልባት ሕግ” (The law of probability) ከጨለማ ቤት በሁለት እግር ወጥቶ ለመሄድ ያለውን እድል አጨልሞ ያሳያል፡፡ ብርሃነ መስቀል ረዳ ጨለማ ቤት አድሮ ነው የተወሰደው፡፡ ቀኛዝማች ታዬ መሸሻም እዚሁ ነበሩ፡፡ ዓለም ሰገድና ጨርቆስ ደሞዝም እዚያው ጥቂት ሰንብተው ተሸኙ፡፡ እንዲህ ሲታይ ጉዳያችን “ጨለማ ቤት” ከደረስን በኋላ የሚወሰን አይመስለኝም፡፡ ተወስኖ አልቆ የምንገባ መሰለኝ፡፡ በዚህኛው ዓለምና በመቃብር መካከል ያለ ጊዜያዊ ማረፊያ (Half way house) መሆኑ ነው፡፡ የአንዳንዱ ሰው ጉዳይ ጨለማ ቤት ከደረሰ በኋላ የሚፈጥነው፣ የሚዘገየው በሌላ ሥራ ተጠምደው አላደርስ ብሎ ሳይሆን አይቀርም ብዬ አስባለሁ፡፡ የዚሁ ዓይነት ሥራ የሚሰራበት “ቄራ” ይኸኛው ብቻ ስለአልሆነ ሥራ ሊበዛ ይችላል፡፡
የቀኛዝማች ታዬ ከዚህ ለየት ይላል፡፡ ከ3 ዓመት በላይ ቆይተው ነው የተረሸኑት፡፡ ህግ ውስጥ “ይች ባትኖር” (But for) የሚሉት አላቸው፡፡ በምክንያቱና በውጤቱ መካከል ባለው ሁኔታ ላይ ተፅዕኖ የሚያሳድር ሐሳብ ነው፡፡ ወይ ያፈጥነዋል፣ ያዘገየዋል ወይም ግንኙነቱን ያቋርጠዋል፡፡
በቀኛዝማች መታሰር የተበሳጨ የወሎ ባላገር (ለቀው ሸሽተው ወሎ ገብተው ነበርና)፣ አንድ ወሎ የነበረን የደርግ አባል “ቀኛዝማችን አምጣ!” ብሎ ወጥሮ ሳይዘው አልቀረም፡፡ በዚህ መካከል በተፈጠረ ግርግር የደርግ አባል ወይ ሞቷል፣ ወይ ተጎድቷል፡፡ የሰማሁት ነውና እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ይህ ለቀኛዝማች “But for” የሆነ ይመስላል፡፡ ይህ ባይኖር ኖሮ ላይገደሉም ይችሉ ነበር ማለት፣ ዋጋ የሌለው የአንጎል ጅምናስቲክ ነው፡፡ እውነቱ ተገደሉ ነው፡፡ እኒህን “… አምላክ ሰው… ሰውም አምላክ ሆነ…” የምላቸውን ቀኛዝማች ታዬን በሚመለከት አንድ ቀን መመለሴ አይቀርም፡፡
እኔ ከጨለማ ቤት በእግር ከወጡት ጥቂት እድለኞች ውስጥ ነኝ፡፡ የብርሃነ መስቀል ባለቤት ወ/ሮ ታደለች ወ/ሚካኤል እና መኪያ መሀመድ ሌሎቹ ናቸው፡፡ በኋላ እንዳጣራሁት ታደለች የተረፈችው ነፍሰ ጡር ስለነበረች ነው፡፡
እኔ ጨለማ ቤት አልጨለመብኝም፡፡ የመጨረሻ ቤቴ አድርጌ ስለተቀበልኩት፣ የመጨረሻ ጉዞውን ተቀብዬ፣ ለጉዞው ሥነ-ስርዓት ዝግጅት ላይ ነበርኩ፡፡ “አሟሟቴን አሳምርልኝ” ብዬ አልፀለይኩም፡፡ በእኔው እጅ ስለነበረ እኔው ላሳምረው ወስኜ ነበር፡፡ የመጨረሻው ጠሪ መጥቶ “አሰፋ ጫቦ ጋቢህን ይዘህ ውጣ!” ሲለኝ (ጋቢህን ይዘህ ውጣ ነው የሚባለው ለመጨረሻው ሲኬድ) በክብር፣ በውስጥ ህሊና ክብር ለመሄድ ነበር፡፡ ራሴን በራሴም፣ ሌላው በሚያየኝም፣ በማያየኝ ፊት ሳላዋርድ ለመጠናቀቅ ነበር፡፡ “የመጨረሻውን ጽዋ ለመጠጣት ከወሰኑ በዚያን በመካከሉ ያለው አያስጨንቅም፡፡ እኔን አላስጨነቀኝም፡፡” ትዕቢቴ ሽመልስን ይገርመው ነበር፡፡ በኋላ ወዳጄ የሆነው ጦር ሰራዊቱ መቶ አለቃ ሽመልስ ዋለልኝ የእስረኛ አስተዳዳሪ ነበር፡፡ በኢፊሴል ማነጋገር የምችለው እሱን ብቻ ነበር፡፡ ጨለማው ቤት ከዚያ በላይ እንዳይጨልም የብርሃን ጨረር ፈንጣቂ ነበር፡፡ ጨለማ ቤት አመት ከዘጠኝ ወር ተቀምጬ ላይ ቤት (ግቢ) ተዛወርኩ፡፡
ወሬ ሲሰማ “ጨለማ ቤት” ኋላ አዲስ አይነት የብርሃን ቤት ሆኖ ነበረ፡፡ የአዲስ አይነት ምርጥ እስረኞች (በጮሌነት ወይ በገንዘብ) መኝታ ክፍል ሆኖ ነበረ፡፡ እዚያ ከተማው ውስጥ ሴክሬቶ እንደምትሉት አይነት “ሰው ከቆየ ከሚስቱ ይወልዳል” ይላል ጎንደሬ፡፡ ሌላም ብሎ ሊሆን ይችላል፡፡ እኔ የሰማሁት ጎንደር ነው፡፡
ዶክተር ካሳሁን መከተ ጎንደሬ ነው፡፡ ዕድሜው ከ40 እና 50 መካከል የሚሆን ይመስለኛል፡፡ መካከለኛ ቁመት፣ ሽንቅጥ ሰውነት አለው፡፡ ቀይና መልከ መልካም ነው፡፡ ለወንድ ይባል እንደሁ አላውቅም እንጅ ቆንጆም ሊባል የሚችል ይመስለኛል፡፡ ሽቅርቅር ነው፡፡ አለባበሱ የተመጣጠነ፣ የተመዘነና ምርጥ ነው፡፡ የልብሶቹ አመራረጥ የሰከነና የጠራ (Seasoned) ነው፡፡ እንደዚያ አሳምሮና ተጠንቅቆ የሚለብስ ያየሁት ይኖራል፡፡ የማውቀው የለኝም፡፡ እስር ቤት፣ ያውም ጨለማ ቤት እንዲህ ከሆነ ውጭ እንዴትና እንዴት ያደርገው ይሆን? እያልኩ አስባለሁ፡፡
ዶክተር ካሳሁን የዋህ፣ ጅል፣ ግብዝ፣ ልታይ ልታይ ባይ፣ ግድርድር … ነው ለማለት እችላለሁ፡፡ እነዚህን ቃላት (ቅጽሎች) በመጥፎነት (Negatively) መጠቀሜ አይደለም፡፡ ይህ በብርቱ እንዲታወቅልኝ እፈልጋለሁ፡፡ ይልቁንም በበጎ ጎኑ (Positive) ነው፡፡ እነዚህ ባህርይ ገላጭ ቅጽሎች ሌላው ሰው ላይ ያለን የተለመደውን ትርጉማቸውን ይይዛሉ፡፡ ካሳሁን ላይ ግን ያንን ደረቅ ትርጉም (Generic connotation) የሚለቁ ይመስላሉ፡፡ ለቀውም አዲስ ለየት ያለ የራሱ ለዛ ያለው ትርጉም ይይዛሉ፡፡ ለእኔ የዋህነቱን ቅንነቱን መግለጫ ብሩህ ቀለማት ሆነዋል፡፡ ተሰባስበው አዲስ ውብ ዜማ ይፈጥራሉ፡፡ አዲስ ማህሌቶች አዲስ ሽብሸቦ ይሆናሉ፡፡ ለየት ያለ ባህርይ መግለጫ ይሆናሉ፡፡ እኔ እንደ አየሁትና መግለጽ እንደሞከርኩት ማለት ነው፡፡
ዶ/ር ካሣሁን ጎንደሬ ነው ብያለሁ፡፡ ግድርድርም ነው ብያለሁ፡፡ ይህ ስለጎንደሬ ከምናውቀው ወይም እናውቃለን ከምንለው ጋር የሚሄድ አይመስለኝም፡፡ ከመሳዩ፣ ከተምሳሌቱ (Stereotype) ጋር አይሄድም፡፡ የራሱ የካሳሁን ለዛ አለው፡፡ አዲስ ለከት ይሰጠዋል፡፡ በዚህ በአውሮፓ ታሪክና ሥነ-ጽሁፍ ውስጥ (Chivalry) የሚሉት መልክ አለው፡፡ ወይም የሴርቫንተሰን (Miguel de Cervantes) ዶን ኪሆቴን (Don Quixote) የሚመስል ባህርይ አለው፡፡ ገራገርና ዘራፌነት ያለው ነው፡፡
ዶ/ር ካሣሁን የታሰረው በስለላ ተጠርጥሮ ነው፡፡ ለሲ.አይ.ኤ በመላው ዓለም፣ በኢትዮጵያም ሰላዮች እንዳሉት የታወቀ ነው፡፡ ኢትዮጵያን ለማጥፋት፣ ለመበታተንና ዛሬ የደረሰችበት ለማድረስ በብዙ ወኪሎቹ (Proxies) በኩል ብዙ ሚሊዮን ዶላር እንዳወጣ ዛሬ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ እርግጥ አደባባይ አንወጣም፤ ሚስጥሩም አይውጣብን የሚሉ አሉ፡፡ የወኔ ጉዳይ ነው፡፡ ዶ/ር ካሣሁን ሰላይ ሆኖ ሊሆን ይችላል፡፡
ዶ/ር ካሣሁን ሰላይ ቢሆን እንኳ መሆኑን የሚያውቅና የሚረዳ አይመስለኝም፡፡ ነገርን መታየት ከሚገባ ዘርፍና አንፃር ማየት አይችልም፡፡ ያመነውን ያሰበውን በዘፈቀደ እንደልቡ ይናገራል፡፡ ይህንንም እንደ-ጀግንነት ይቆጥረዋል፡፡ እንዲደነቅለትም ይፈልጋል እንጂ የነገርን አመጣጥ መነሻ፣ መድረሻ ሊያስከትለው የሚችለውን ችግር ማጣጣም የሚችል አይመስልም፡፡
ሌላም የሚደንቀኝ የዶ/ር ካሣሁን ነገር ነበር፡፡ የገባበትን ማጥ በቅጡ የተረዳው አይመስልም፡፡ “ጨለማ ቤት” መቀመጡን “ለክብሩ የተደረገ” አድርጎ ገምቶትም ሊሆን ይችላል፡፡ እንዴትና በምን መንገድና ትንታኔ ከዚያ እንደደረሰ ማወቅ ይቸግራል፡፡ ይህ ነው ከብዙዎቻችን ለየት ይላል የሚያሰኘኝ፡፡ ይህ ነው (Don Quixote) የሚመስል ባህርይ አያጣም የሚያሰኝ፡፡
ስለተከሰሰበት ጉዳይ በቀጥታ ልጠይቀው ሞክሬአለሁ፡፡ በተዘዋዋሪም ሞክሬአለሁ፡፡ ውጤቱ ያው ነው፡፡ ንቆ አናንቆ አቃሎ ይነግረኛል፡፡ ከመጤፍ አልቆጠራትም፡፡ ይልቁንም ከጥዋት እስከ ማታ ስለ አለባበሱ ስለ መሽቀርቀሩ ሲጨነቅ ይውላል፡፡ አንዳንዴ ልብስ በቀን ሦስት ጊዜ ይቀይራል፡፡ ማዕከላዊ ጥያቄው ማን ምን ለበሰ? አይደለም፡፡ ዛሬ ደግሞ የማን ተራ ይሆን? የሚል ነው፡፡ ጋቢህን ይዘህ ውጣ - የሚባል ማን ይሆን? የሚል ነው፡፡ ለበሰ፣ ራቁቱን ሄደ ተመልካች የለውም፡፡
ዶ/ር ካሣሁን አንዳንዴ ለምርመራ ጥዋት ሄዶ ለምሳ ይመለሳል፡፡ እንደሌላው በታረሰ እግር እየዳኸ ሄዶ ደም እያዘራ አይመለስም፡፡ እየሳቀ ሄዶ እየሳቀ ይመለሳል፡፡
እንዴት እንደዋለ፣ ምርመራው ከምን እንደደረሰ ስጠይቀው መልሱ ያው ነው፡፡ በጣም ስለጨቀጨቅሁት እንደመቀያየም፣ መኮራረፍም ጀምረን ነበር፡፡ ወይም “ጓድ መቆያ መርማሪው ጋር ቡና ጋብዞኝ ስንጫወት ዋልኩ” ይለኛል፡፡ “ዶሮን ሲያታልሏት” መሆኑን ተረድቻለሁ፡፡ ላስረዳው ግን አልቻልኩም፡፡
ዶ/ር ካሣሁን ትምህርቱ የቤተ ክህነት (Theology) ይመስለኛል፡፡ ለዚሁ ትምህርት ቱርክ ወይም ግሪክ ወይም ሁለቱም ጋር ሄዶ የመጣ ይመስለኛል፡፡ ብዙዎች እንደዚህ እየሄዱ ሌላ ማህበራዊ ሳይንስ (Social Science) ተምረው እንደሚመለሱ አውቃለሁ፡፡ ካሳሁን እንደዚያ ማድረግ አለማድረጉን አላውቅም፡፡ ከውጭ የሚታይ የለም፡፡
በቀን ቢያንስ አንዴ ሳያነሳ የማይውላቸው ሁለት ነገሮች አሉ፡፡ አንደኛው ስለደባርቅ-ዳባት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ኋላቀርነት ማስረጃ ያደርጋቸዋል፡፡ እስከ ዛሬ መብራት እንኳ አልገባላቸውም፡፡ ሶሻሊዝም ሶሻሊዝም ይላሉ፤ ደባርቅ መቼ መብራት ገባ ይላል፡፡ ይህችው ነች፤ አትለወጥም፡፡
ሌለው የሚያወራው አዲስ አበባ አራት ኪሎ ስለሚያውቃቸው ጉራጌ ሴት ነበር፡፡ ምግብ ቤት ያላቸው፡፡ አሁን ያሉት አቃቂ መዳረሻ ዳገቱ ላይ ነው፡፡ እናቴ ይላቸዋል፣ የሀገር እናት ይላቸዋል፡፡ ከዚህ ውጪ ስለዘመድ አያነሳም፡፡ ብዙ ያለውም አይመስለኝም፡፡ ዶ/ር ካሳሁን ያገባ የወለደም አይመስለኝም፡፡ ዋቢ ሸበሌ ሆቴል እኖራለሁ ያለኝ መሰለኝ፡፡
የወደቀበት ክብደቱን ቢያውቀው የሚለውጠው ላይኖር ይችላል፡፡ ሆኖም ቢቻል ማወቅን የመሰለ ያለ አይመስለኝም፡፡ አይኑን አፍጥጦ የመጣበትን ሳይረዳ ሰንብቶ አንድ ቀን ዶ/ር ካሣሁን ጋቢህን ይዘህ ውጣ ተባለ፡፡ በመጨረሻ የሚሄዱትን “ጋቢህን ይዘህ” ይባላል፡፡ መገነዣ ይሆን? እነብርሃነ መስቀል የተጠሩ ቀን መሰለኝ ዛሬ “ቡና ተጋብዞ” አልተመለሰም፡፡ ወደ ጨለማ ቤትም አልተመለሰም፡፡ ወዴትም አልተመለሰም፡፡ ንጹህ በግ ከአራጆቹ ጋር ሰንብቶ ተሰዋ፡፡ በራዲዮም ተነገረ፣ የብዙ ሰው መገደል ያሳዝነኛል፡፡ የዶ/ር ካሳሁን የባሰ ከሚያሳዝነኝ ውስጥ ነው፡፡
****
(አዲስ አድማስ፤ ታህሳስ 7 ቀን 1993 ዓ.ም)
የወቅቱ ጥቅስ
“ትላንት ቢያመልጠኝ ዛሬ አለልኝ የማይልና አዎንታዊ እልህ የሌለው መሪ ከስህተቱ አይማርም፡፡ ከስህተቱ ባልተማረ ቁጥር አገሩን ከድጡ ወደ ማጡ እየከተተ ህዝቡን ለባሰ ችግር ይዳርጋል፡፡”
“ለብቻዬ ስንጥር ከምሆን ከሀገር ጋር እርፍ ልሁን”
አንድ ልዑል ከቤተ-መንግስት ራቅ ብሎ ወደሚገኝ አንድ ትልቅ ጫካ ሄዶ አደን ሲያድን ውሎ ወደ ቤተ-መንግሥቱ ሲመለስ አንድ ባላገር ያገኛል፡፡ ባላገሩ ልዑሉ ማን እንደሆነ አያውቅም ነበርና አንዳችም እጅ- ሳይነሳ፣ ሰላምታም ሳይሰጥ ዝም ብሎ መንገዱን ይቀጥላል፡፡ ልዑሉም የባላገሩ ነገር ገርሞት፣
“ሰማህ ወይ ወዳጄ፣ ለመሆኑ እኔ ማን እንደሆንኩ ታውቃለህ ወይ?” ሲል ይጠይቀዋል፡፡
ባላገሩም፤ “በመንደራችን ባለው ጫካ ውስጥ በገዛ-ፈቃድህ ገብተህ አደን ስታድን እንደቆየህ አይቻለሁ፡፡ በሰላም የተቀመጡትን አዕዋፋት ስትረብሻቸው፣ እንስሳቱንም መጠጊያ ስታሳጣቸው የነበርክ ሰው መሆንህንም ተመልክቻለሁ” አለው፡፡
ልዑሉም፤ “ምን ስሰራ እንደቆየሁ ማወቅህ መልካም፡፡ ማንነቴንስ አውቀሃል ወይ?”
ባላገር፤ “አላውቅም፡፡”
ልዑሉ፤ “እንግዲያው ና ፈረሴ ላይ ውጣና አብረን ወደ ከተማ እንሂድ፡፡ ንጉሥ ማለት ምን እንደሆነ እዚያ ታውቃለህ” አለው፡፡
ልዑሉ ባላገሩን አፈናጦት ወደ ከተማ ይዞት ሄደ፡፡ በመንገድ ላይም “ንጉሥ ማለት የተከበረ፣ በሄደበት ቦታ ሁሉ ህዝብ እጅ የሚነሳው፣ መንገደኛው ሁሉ ቆሞ የሚያሳልፈው ትልቅ ሰው” ነው አለው፡፡
ከተማ ሲደርሱ፤ ህዝቡ ልዑሉን ሲያይ እየቆመ፣ እጅ እየነሳ አሳለፈው፡፡ ግማሹም አቤቱታውን አሰማ፡፡
ይሄኔ ልዑሉ ወደ ባላገሩ ዞሮ፤ “አሁንስ ንጉሡ ማን እንደሆነ አወቅህ?” ንጉሡ ማን ይመስልሃል?” ሲል ጠየቀው፡፡
ባላገሩም፤ “እንግዲህ፤ ወይ እኔ ወይ አንተ መሆናችን ነዋ” ሲል መለሰ፡፡
“ቡመራንግ” ማለት ይሄው ነው - ለሌላው የወረወሩት ቀስት ተመልሶ ወደ ራስ!
* * *
ህዝቦችና መሪዎች ሲጠፋፉ የሚፈጠረው ግራ-መጋባት አይጣል ነው! የክልል፣ የቀጠና፣ የወረዳና የቀበሌ መስተዳድር. የቢሮና የሚኒስቴር ኃላፊዎች እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲዎችና መሪዎች ከህዝብ ሲርቁ ከላይ እንደተጠቀሰው ባላገር ማንነታቸው ብቻ ሳይሆን ምንነታቸውም ለህዝብ ግራ የሚገባበት ደረጃ ይደርሳል፡፡ ህዝቡ ልቡ ክፍት ነው፡፡ ህዝብ የነገሩትን ይሰማል፡፡ የተረጎሙለትን፣ እውነት ብሎ ይቀበላል፡፡ ያወጁለትን አዋጅ፣ ይበጀኝ ብሎ ያከብራል፡፡ የደነገጉለትን ህግ፣ በወጉ ሊተዳደርበት ይነሳል፡፡ ያወጡለትን መመሪያ እመራበታለሁ ብሎ ይስማማል፡፡ እቅዶች አምረው ሲያያቸው ሰምረው አገኛቸዋለሁ ብሎ ተስፋ ያደርጋል፡፡ ችግር የሚፈጠረውና ፀብ የሚመጣው፣ አንድም በተግባር ሲተረጎሙ በመዛባታቸው፤ አንድም ባወጣቸው ክፍል በራሱ በቃል-አባይነት እንደሌሉ ሲካዱ (ሲሻሩ) ነው፡፡ “Law-maker Law-breaker” እንዲል ፈረንጅ፡፡ ያስቡልኛል ያላቸው መሪዎችና ኃላፊዎች “አንተና አንቺ” ብለው ከናቁት፣ ያወጡትን መመሪያዎች በሱው ላይ መጠቀሚያ ካደረጓቸው፣ በግልፅ-ወገናዊነት “ሁሉም ህዝቦች እኩል ናቸው ካሉት፣ አንዳንዶቹ ግን የበለጠ እኩል ናቸው” ካሉት፣ አዋጅም፣ ህግም፣ መመሪያም እንደ ብዙዎቹ ተግባር-አልባ የፕሮጄክት ጥናቶች ያማሩ ወረቀቶች ሆነው ነው የሚቀሩት፡፡
እቅድ በሥራ ላይ መዋሉን ለማየት በሚል “የግምገማ” ስብሰባ፣ ጥንት የሚታወቀው “ድርጅታዊ አሰራር” ከተንፀባረቀ፣ “በእኔ አስተያየት” በሚል የግል ካባ ቡድናዊ ስሜት የሚያስተጋባ ከሆነ አመራርና ተመሪ መራራቁ የማይቀር አባዜ ይሆናል፡፡ ህዝብን በግምገማ ማረቅ አይቻልም! መሪዎችንና መመሪያዎችን እንጂ! እነሱም በጄ ካሉ! ግምገማውም የዕውነት ከሆነ! በአንድ ወቅት ስለ ሂስና ግለ-ሂስ ሲወሳ፤ ”ሂስ እያሉ ሌላውን መዘርጠጥ፣ ግለ ሂስ እያሉ ራስን ማዋረድ አይገባም!” ያሉ እንደነበሩ ያስታውሷል፡፡ መታረም መተራረም፣ መቻል፣ መቻቻል የሚቻለው ትክክለኛ ሂስ ማቅረብ ሲቻል ነው፡፡ እዚህ ጋ ድክመት አለ ተብሎ ሲጠቆም ነው፡፡
እርግጥ ነው መማማር ያስፈልጋል፡፡ ሆኖም ትምህርቱ መታወቅ፣ አስተማሪና ተማሪውም አስቀድሞ መለየት አለበት፡፡ ገጣሚው ኦማር ካህያም እንዳለው፤ “እኔስ ማነኝሳ ቁጭ ብዬ እምማር፤ አንተ ማነህ እሱን የምታስተምር፤” ሳንባባል ለመቀጠልና ለመማማርም መቻቻል አለብን፡፡ አለበለዚያ አንድ አዋቂ የሀገራችን ፀሐፌ-ተውኔት ባንደኛው ቴያትራቸው ውስጥ እንደፃፉት ይሆናል፡፡
አንዱ ገፀ-ባህሪ፤ “ምነው ተጠፋፋን ጓድ?” ሲል ይጠይቀዋል፡፡
ጓዱም ሲመልስ፤ “የአብዮት ጊዜ አይደለም እንዴ? መጠፋፋት መች ገደደ?!” ነበር ያለው፡፡
ይህን መሰል የፖለቲካ ሰዎች ፈሊጥ ህዝብ ውስጥ እንዲገባ መደረግ የለበትም፡፡ ህዝቦች እንዲኖሩ እንጂ እንዲጠፋፉ፣ እንዲቻቻሉ እንጂ እንዲናቆሩ መሆን የለባቸውም፡፡ ቅን ልቦና፣ ፅናትና ለሀገር ማሰብ ሲኖር መቻቻል ይቻላል፡፡ መሪዎችና የፖለቲካ ድርጅቶችም ቢሆኑ መቻቻል ይችላሉ፡፡
ዋናው፤ “ለብቻዬ ስንጥር ከምሆን ከሀገር ጋር እርፍ ልሁን!” ማለት ብቻ ነው፡፡