Administrator

Administrator

• ተኩስ አቁም ተደርጎ ሰላማዊ መፍትሄ እንዲፈለግ ጠይቋል

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ)፤ በመንግሥትና ፋኖ ታጣቂዎች መካከል በቀጠለው ግጭት ሳቢያ በርካታ የአማራ ክልል ነዋሪዎች መገደላቸውን አስታውቋል። ኮሚሽኑ ባለፈው ረቡዕ መስከረም 15 ቀን 2017 ዓ.ም. ባወጣው የሩብ ዓመት ሪፖርቱ፣ በአማራ ክልል ተኩስ አቁም ተደርጎ፣ ለግጭቱ ሰላማዊ መፍትሔ እንዲፈለግ ጠይቋል።
በዚሁ ሪፖርት ላይ በአማራ ክልል፣ ሰሜን ሸዋ ዞን፣ የኤፍራታና ግድም ወረዳ አስተዳዳሪ፣ ግንቦት 25 ቀን 2016 ዓ.ም. እና የቀወት ወረዳ አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ግንቦት 29 ቀን 2016 ዓ.ም. በክልሉ በሚንቀሳቀሰው የፋኖ ታጣቂ ቡድን አባላት በመኖሪያ ቤታቸው መገደላቸው የተጠቀሰ ሲሆን፤ ሰኔ 2 ቀን 2016 ዓ.ም. ሌሊት ደግሞ የፋኖ ታጣቂ አባላት ከክልሉ አዊ ብሔረሰብ ዞን፣ ቲሊሊ ከተማ፣ አሽፋ ቀበሌ መውጣታቸውን ተከትሎ፣ የመንግስት የጸጥታ አካላት ወደ ቀበሌው በመግባት፣ ሰኔ 3 ቀን 2016 ዓ.ም. ከጠዋት ጀምሮ እስከ ቀኑ ስምንት ሰዓት ድረስ ቤት ለቤት በመፈተሽ “ፋኖን ትደግፋላችሁ፣ ትቀልባላችሁ፣ ቤት ታከራያላችሁ”፣ እንዲሁም “የፋኖ አባላት ናችሁ” ብለው የጠረጠሯቸውን 10 ሲቪል ሰዎች በጥይት መግደላቸው ታውቋል።
በሰሜን ጎጃም ዞን፣ ሰሜን ሜጫ ወረዳ፣ ወተት ዓባይ ቀበሌና በአካባቢው በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች እና በፋኖ ታጣቂ አባላት መካከል ከነሐሴ 6 እስከ 7 ቀን 2016 ዓ.ም. ከተካሄደ ውጊያ ጋር በተያያዘ የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች በመንገድና ቤታቸው ውስጥ ያገኟቸውን በግጭቱ ተሳትፎ ያልነበራቸውን 7 ሰዎች እንደገደሉ ነዋሪዎች ለኮሚሽኑ መጠቆማቸው በሪፖርት ላይ ተጠቅሷል። ከሟቾች ውስጥ በአካባቢው የማሕበረ ስነ ልቦና ጉዳት እንዳለበት የሚታወቅ አንድ ግለሰብና አንድ የ17 ዓመት ልጅ እንደሚገኙበት ተመልክቷል። በተጨማሪም፣ ነሐሴ 13 ቀን 2016 ዓ.ም. ከንጋቱ 11 ሰዓት ተኩል አካባቢ ቄስ አወቀ መኮንን የተባሉ አረጋዊ፣ ሃይማኖታዊ ስርዓት ለማከናወን ወደ አቡነ ዘርዓብሩክ ቤተ ክርስቲያን በመጓዝ ላይ እያሉ፣ በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች በጥይት እንደተገደሉ ለማወቅ እንደተቻለ ሪፖርቱ ጠቁሟል፡፡
በተለያዩ የአማራ ክልል ከተሞች የቦምብ ጥቃት እንደሚፈጸሙ የሚያትተው የኢሰመኮ ሪፖርት፣ ለአብነት ያህል ነሐሴ 2 ቀን 2016 ዓ.ም. ከቀኑ 9፡50፣ ነሐሴ 7 ቀን 2016 ዓ.ም. ረፋድ ላይ፣ ነሐሴ 9 ቀን 2016 ዓ.ም፣ ነሐሴ 14 ቀን 2016 ዓ.ም. እና ነሐሴ 22 ቀን 2016 ዓ.ም ምሽት 1፡00 ገደማ በአማራ ክልል፣ ባሕር ዳር ከተማ በፋኖ ታጣቂዎች አባላት እንዲሁም ለጊዜው ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች የተፈጸሙ የቦንብ ፍንዳታዎች በነዋሪዎች ላይ የደሕንነት ስጋት ከመደቀናቸው ባሻገር ለጊዜው ብዛታቸው ባልታወቁ ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት ማድረሱን አስታውቋል።
ኢሰመኮ ባጠናቀረው ሪፖርት መሰረት፣ ከአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጅ አፈጻጸም ጋር በተያያዘ
አዋሽ አርባን ጨምሮ በተለያዩ መደበኛና መደበኛ ባልሆኑ ማቆያዎች በቁጥጥር ስር ውለው የነበሩት አብዛኛዎቹ ተጠርጣሪዎች ከእስር የተለቀቁና ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ የተደረገ መሆኑ አበረታች መሆኑን አስረድቷል።
ይሁን እንጂ በአስቸኳይ ጊዜ ወቅት የሕግ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር የማዋል ስልጣን የሌላቸው የጸጥታ አካላት ጭምር ሰዎችን በቁጥጥር ስር አውለው የነበረ መሆኑን በመግለጽ፣ በቁጥጥር ስር ውለው የነበሩ በርካታ ሰዎች ብሔርን መሰረት ያደረገ ስድብ፣ በቂ ብርሃን በማያስገባ ጨለማ ቤት መያዝ፣ ድብደባን ጨምሮ የተለያዩ የማሰቃየት ተግባራት የተፈጸሙባቸውና ለተለያዩ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች የተዳረጉ መሆኑን ተጎጂዎች ለኢሰመኮ ገልጸዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ለበርካታ ወራት በእስር ቆይተው የተለቀቁ ግለሰቦች በእስር ለቆዩበት ጊዜ አሁን ድረስ መረጃ ለማቅረብ ባለመቻላቸው ወደ ስራቸውና ማሕበራዊ ሕይወታቸው ለመመለስ ከፍተኛ ችግር ያጋጠማቸው መሆኑን አክለው ለኢሰመኮ አስረድተዋል።
በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች በግጭት ተሳታፊ የሆኑ ሁሉም አካላት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ተኩስ አቁም በማድረግ፣ ለግጭቱ ሰላማዊ መፍትሔ ለማፈላለግ በቁርጠኝነት እንዲሠሩ ጥሪ ያቀረበው ኢሰመኮ፤“በማናቸውም የግጭት ሂደት ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶችና የሰብዓዊነት ሕጎች ጥሰትን ከመፈጸም ይቆጠቡ” ሲል አሳስቧል፡፡
በግጭቱ የሚፈጸሙ ጥሰቶችን በይፋ እንዲያወግዙና ተጠያቂነትን እንዲያረጋግጡ፣ እንዲሁም በሚቆጣጠሯቸው አካባቢዎች ሰብዓዊ መብቶችን አክብረው እንዲንቀሳቀሱ፣ በሲቪል ሰዎች ሕይወት፣ አካልና ንብረት ላይ ጥቃት ከማድረስ እንዲቆጠቡ ጥሪውን አስተላልፏል፡፡

• ባለፉት 4 ወራት ከ76ሺ በላይ ተፈናቅለዋል

 ባለፉት አራት ወራት፣ በአማራ ክልል፣ በአገር ውስጥ የተፈናቀሉ ሰዎች  ቁጥር መጨመሩን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታወቀ። በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት (ኦቻ) መስከረም 10 ቀን 2017 ዓ.ም  ባወጣው ሪፖርት፣ ባለፉት አራት ወራት፣ በአማራ ክልል ስምንት ዞኖች ውስጥ መፈናቀል መከሰቱን አመልክቷል፡፡
በድርጅቱ ሪፖርት መሠረት፤ በክልሉ በዚህ ወቅት በአጠቃላይ 76ሺ 345 ሰዎች ተፈናቅለዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 34 በመቶ የሚሆኑት ከአካባቢው ማህበረሰቦች ጋር ሲቀላቀሉ፣ አብዛኞቹ በተጨናነቁ የጋራ ማዕከላት መጠለልን መርጠዋል፡፡
እየቀጠለ ያለው  መፈናቀል በማያባራ  የጸጥታ ችግር መባባሱን ያመለከተው ድርጅቱ፤ ይህም መፈናቀሉን ማባባስ ብቻ ሳይሆን፤በአካባቢው ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ማሳደሩን ጠቁሟል፡፡
“ይህ የኑሮ መተዳደሪያ መስተጓጎልና በተቀባይ ማህበረሰቦች ላይ የሚያሳድረው ጫና፣ የሰብአዊ ቀውሱን የበለጠ አባብሶታል” ሲል ሪፖርቱ ይገልጻል፡፡
በቅርቡ  የወጡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፣ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶችና ጦርነቶች፣ በአሁኑ ወቅት በአማራ ክልል ለሚኖሩና በክልሉ 88 ጣቢያዎች ውስጥ ለተጠለሉ በርካታ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ዋና መንስኤዎች ናቸው።
በጥር 2015 ዓ.ም፣ የአማራ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን፣በአማራ ክልል መጠጊያ የሚፈልጉ ተፈናቃዮች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ  መጨመሩን ያመለከተ ሲሆን፤ ቁጥራቸው ከ1 ሚሊየን እንደሚበልጥም አስታውቆ ነበር፡፡
ተፈናቃዮቹን ለመርዳት ጥረት ቢደረግም በተለይ ከቅርብ ወራት ወዲህ፣ በክልሉ በመንግስት ታጣቂዎችና በፋኖ መካከል በቀጠለው ግጭት ሳቢያ እርዳታውን ለፈላጊዎቹ ማድረስ አዳጋች ሆኗል ተብሏል፡፡    
ቪኦኤ በመስከረም 2016 ዓ.ም ባሰራጨው ዜና፣ በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን፣ ለተፈናቃዮች በወቅቱ መድረስ የነበረበት የምግብ እርዳታ፣ በጸጥታ ችግር ሳቢያ መስተጓጎሉን ዘግቧል፡፡  በሌላ በኩል፣ በመጠለያ ካምፖች ውስጥ የሚኖሩ ተፈናቃዮች እንደጠቆሙት፤ የምግብ አቅርቦት እጥረቱ፣ በህጻናት ላይ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት አስከትሏል፡፡
የብሔራዊ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ለቪኦኤ በሰጠው ምላሽ፣ የምግብ አቅርቦት መጠነኛ መዘግየቶች በፀጥታ ችግሮችና በተወሰኑ አካባቢዎች በትራንስፖርት እጥረት መከሰቱን አምኖ፣ ችግሩን ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቁሟል፡፡  
የትግራይ ሁኔታም እንዲሁ አሳሳቢ ሆኖ ቀጥሏል፡፡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሪፖርት  እንደሚያመለክተው፣ በትግራይ ክልል ያለው የተራዘመ የመፈናቀል ችግር ያለማቋረጥ የቀጠለ ሲሆን፤አሁንም በርካታ ሰዎች በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ በጋራ ማእከላት ይኖራሉ።
ድርጅቱ እንዳስታወቀው፣ ባለፉት ወራት 56 ሺህ  ሰዎች ወደ ትግራይ የትውልድ ቀዬአቸው  እንዲመለሱ የተደረገ ሲሆን፤ አብዛኞቹ ወደ አላማጣ፣ ጨርጨር፣ ኮረም ከተማ፣ ላላይ ጸለምቲ፣ ማይጸብሪ ከተማ፣ ኦፍላ፣ ራያ አላማጣ፣ ራያ ጨርጨር፣ እና ዛታ የመሳሰሉ አካባቢዎች ተመልሰዋል፡፡
እየተካሄደ ያለው ተፈናቃዮችን ወደ ቀዬአቸው የመመለስ ሂደት በአዎንታዊነት የሚታይ ቢሆንም፣ በ99ኙ የጋራ ማእከላት የቀሩት ዜጎች ላይ እየደረሰ ያለው ችግር አሁንም አሳሳቢ መሆኑን ድርጅቱ አመልክቷል።
ከአንድ ወር በፊት፣ አንድ የትግራይ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ባለስልጣን፣ በክልሉ ወደ 956 ሺ የሚጠጉ ተፈናቃዮች፣ በቂ እርዳታ ሳያገኙ መቅረታቸውን ገልጸዋል።
የዛሬ ዓመት በነሐሴ ወር አጋማሽ ላይ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ድርጅት ባወጣው ሪፖርት፣ ከአራት ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያን በአገር ውስጥ ተፈናቅለው እንደሚገኙ አመልክቶ ነበር፡፡ ድርጅቱ በሁሉም ክልሎች ውስጥ ባደረገው ግምገማ፣ከ4.38 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያን በአገር ውስጥ ተፈናቅለው እንደሚገኙ ለመረዳት ችሏል፡፡
ከአራት ሚሊዮን በላይ ከሚሆኑት ተፈናቃዮች መካከል 66 በመቶ የሚሆኑት በግጭቶች ምክንያት የተፈናቀሉ መሆናቸውን ያመለከተው ሪፖርቱ፤ ከግጭት በተጨማሪም ድርቅና በማኅበረሰቦች መካከል የሚያጋጥም ውጥረት በመንስኤነት ጠቅሷል፡፡



የመስቀል በዓል አከባበር ኢትዮጵያ በዩኔስኮ ካስመዘገበቻቸው ቅርሶች መካከል የመጀመሪያው በዩኒስኮ የተመዘገበ የማይዳሰስ ቅርስ ነው።
 
ልክ የዛሬ 11 ዓመት ህዳር 2006 ዓ.ም ኢትዮጵያ ተንከባክባ እና ጠብቃ ይዛው የነበረው በዓል የዓለምም በዓል ይሆን ዘንድ ነው የተመዘገበው።
 
የመስቀል በዓል አከባበር በዩኔስኮ የማይዳሰስ ቅርስ (Intangible) ሆኖ የተመዘገበው በአዘርባጃን ዋና ከተማ ባኩ በተደረገ ስምንተኛው የዩኔስኮ የማይዳሰሱ ቅርሶች ጉባዔ ላይ ነበረ።

 
ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ፣ ደሙን አፍስሶ፣ ለሰዉ ልጆች ሁሉ ፍቅሩን ገልጿል። ይህ ሁሉ ዋጋ የተከፈለበት መስቀል ምሳሌነት በዚህች ምድር ስንኖር እርሰበርሳችን ያለ ምንም ልዩነት በፍቅር፣ በምህረት እና በመተሳሰብ እንድንኖር ነው።
መላው የከተማችን ነዋሪዎች የከተማችን ሌላኛው ድምቀት የሆነው የመስቀል ደመራ በዓል እንደ ምሳሌነቱ የሰው ልጆችን ሁሉ በመዉድ፣ እርሰበርስ በመተባበር፣ በመከባበርና በፍቅር የዓሉን እሴቶች በመጠበቅ ባማረና በደመቀ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ የበኩላችሁን እንድትወጡ ጥሪዬን አቀርባለሁ።
በዓሉ ፍቅር፣ የደስታ እና አብሮነት የሚጎላበት የተዋበ በዓል ይሁንልን።
በድጋሚ እንኳን ለብርሃነ መስቀሉ በሰላም አደረሰን፤ አደራሰችሁ!
መልካም በዓል!
ከንቲባ አዳነች አቤቤ

የመስቀል በዓል የሕልም ጉልበት የታየበት በዓል ነው፡፡

ንግሥት ዕሌኒ መስቀሉን ለማውጣት ያለመችው ምንም አመቺ ነገር ባልነበረበት ጊዜ ነው፡፡ ዙሪያዋ ጨለማ ነበር፡፡ መንገዶች ሁሉ ዝግ ነበሩ፡፡ ነገሮች ሁሉ አስቸጋሪ ነበሩ፡፡ ማንም በማያስበው ጊዜ፤ አይቻልም አይሞከርም በሚባልበት ወቅት፤ አንድ ቀን፤ ፈጣሪዋ ሲፈቅድ፤ መስቀሉን ከተቀበረበት ሥፍራ ለማውጣት ሕልም ነበራት፡፡

ሕልሟ እንዲሳካ ሠራች፤ ታገለች፡፡ ጨለማውን እየገፈፈች፤ አስቸጋሪውን ጎዳና እየጠረገች፤ ከውስብስብ ችግሮች ጋር እየተጋፈጠች ወደ ፊት ተጓዘች፡፡ በመጨረሻም ኢየሩሳሌም ተሻግራ፣ መስቀሉን ከተቀበረበት ሥፍራ ለማውጣት በቃች፡፡ ሕልሟ እውን ሆነ፡፡ ታሪክን ቀየረች፡፡ ልዕልናን ዐወጀች፡፡ ደመራ ለሚታገል፤ ተስፋ ለማይቆርጥና እስከ መጨረሻው ለሚጸና ሰው ሕልሙ አንድ ቀን እውን እንደሚሆን የሚያሳይ ትእምርት ነው፡፡

እዮሃ፤ ማለት “ይሄዋ” ማለት ነው ይባላል፡፡

ይሄው ተገኘ፤ ይሄው ተሳካ፤ ይሄው እውን ሆነ ማለት ነው፡፡ ከበረቱ፤ ከታገሉና ከጸኑ የማይሳካ ምን ነገር አለ? ሕልሙን ለሚያውቅ፤ ሕልሙ እንዲሳካ በነገሮች ተስፋ ሳይቆርጥ ለሚለፋ፤ እንደ ንግሥት እሌኒ ሕልሙ እውን ሆኖ አንድ ቀን ማየቱ አይቀርም፡፡ የሕልሙን ደመራ መደመሩ አይቀርም፡፡ “እዮሃ”፤ “ይሄዋ!” ማለቱ አይቀርም፡፡

መስቀል ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችንን በሁለት መንገድ የሚያሳይ በዓል ነው፡፡ ደመራው ከእንጨት ወደ ችቦ፤ ከችቦ ወደ ደመራ የሚያድግበት መንገድ መደመር ምን ያህል ኃይልና ጉልበት እንዳለው ያሳያል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ መስቀል በተለያየ መንገድ፣ በተለያየ ባህልና አከባበር በብዙ ብሔረሰቦች ይከበራል፡፡ ይሄ ደግሞ በኅብረ ብሔራዊነታችን ውስጥ ያለውን ነባር ትሥሥር፣ የወል ትርክትና አንድነት የሚሳይ ነው፡፡

እንዲህ ዓይነት በዓላት ሃይማኖታውያን ብቻ አይደሉም፡፡ የኅብረ ብሔራዊ አንድነታችን መገለጫዎች ጭምር ናቸው፡፡ በመደመር ውስጥ ያለውን ጥንካሬና ጉልበት የሚሳዩ ትውልድ ለእኛ ትምህርት ያቆማቸው ምልክቶች ናቸው፡፡

ደመራውን በደመርን ጊዜ፤ ደመራውን በለኮስን ጊዜ፤ እንደየባህላችን የመስቀልን በዓል ለማክበር በቤተሰብና በማኅበረሰብ ደረጃ በተሰባሰብን ጊዜ ኢትዮጵያን እናስባት፡፡

የሁላችንም ዕሴቶች፣ ባህሎች፣ ወጎች፣ ዐቅሞች፣ ጸጋዎች፣ ሀብቶች፣ ቋንቋዎች፣ ታሪኮች፣ ወዘተ. ተደምረው ኢትዮጵያን ታላቅ፣ የበለጸገችና የተከበረች ሊያደርጓት እንደሚችሉ እናስብ፡፡ ኢትዮጵያ የእነዚህ ሁሉ ድምር መሆኗን እናስብ፡፡ ከድምሩም በላይ መሆኗንም እናስብ፡፡ ደመራውን እያሳየን ለልጆቻችን ከሃይማኖታዊና ባህላዊ ትርጉሙ በተጨማሪ “እኛ ኢትዮጵያውያን ከተደመርን እንደ ደመራው ብርቱ እንሆናለን፤ እንደደመራው ከፍ ብለን እናበራለን” በሏቸው፡፡

መልካም የመስቀል በዓል ይሁን፡፡    

ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!!
ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርክ!
መስከረም 16፣ 2017 ዓ.ም

 • ዓመታዊ የእግር ኳስና የባህል መድረክ የሚዘጋጅበት ሁኔታ ተነቃቅቷል
                     • ለክለቦች፣ ለፕሪሚየር ሊግና ፌዴሬሽን ዓለም አቀፍ ትስስር አዲስ ምዕራፍ ይከፍታል
                     • ኢትዮጵያውያን በፕሮፌሽናል ደረጃ በአሜሪካ ሊግ የሚጫወቱበት እድል ይፈጠራል






          ባለፈው 2016 ዓ.ም የመጨረሻ ወራት ላይ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ አዲስ ምዕራፍ ተከፍቷል። ሱራፌል ዳኛቸው የአሜሪካውን ሁለተኛ ዲቪዚዮን ክለብ ሎውደን ዮናይትድ መቀላቀሉ፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአሜሪካ በነበረው  ቆይታ ከቢሊየነሩ እዮብ ማሞ ካቻ መገናኘቱ፤ በኢትዮጵያና በአሜሪካ  እግር ኳስ ላይ በጋራ ለመስራት ዕድል መፈጠሩ ቅዱስ ጊዮርጊስና ኢትዮጵያ ቡና በዋሽንግተን ዲሲ የሸገር ደርቢን መጫወታቸው እንዲሁም ሎዛ አበራ ለዲሲ ዮናይትድ ሴቶች ክለብ በመፈረም መጫወት መጀመሯ ይህን የሚያረጋግጡ ናቸው።
ከአሜሪካው የሸገር ደርቢ በፊት
ከሶስት ወራት በፊት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ባደረገው ጥረት  የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ልዮ ልምድ ለማግኘት ወደ አሜሪካ ተጉዞ እንደነበር ይታወሳል።  ከጉያና አቻው ጋር  የወዳጅት ጨዋታ አድርጎ 260 ሺህ ዶላር ገቢ መገኘቱን በወቅቱ የጉዞው አዘጋጅ አስታውቆም ነበር።
በወቅቱ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በብሔራዊ ቡድኑ የአሜሪካ ቆይታ የአቋም መፈተሻ ጨዋታ ከማድረግ ባሻገር የማልያ ሽያጭ በማከናወን ልዩ ተሞክሮ ያገኘ ቢሆንም በመጨረሻ መጭውን ለመሸፈን የገጠሙት ፈተናዎች ነበሩ። አቶ እዮብ ማሞ  ለብሔራዊ ቡድኑ እንደበላይ ጠባቂ ሆነው የሚሰሩበት አጋጣሚ የተፈጠረው ብሔራዊ ቡድኑ በአሜሪካ ቆይታው ከጉያና ብሔራዊ ቡድን ጋር ከተጫወተ በኋላ ነበር።
በአቶ እዮብ ድጋፍ ዋልያዎቹ ከሎውደን ዮናይትድ ክለብ ጋር የወዳጅነት ጨዋታ አደድርገው 4ለ2 ማሸነፍ ችለዋል። በዲሲ ዩናይትድ ክለብን እና ስታዲየሙ ጉብኝት   አድርገዋል።
በአሜሪካው የሸገር ደርቢ ላይ
በአሜሪካ  ለመጀመርያ ጊዜ በተካሄደው  ሸገር ደርቢ ኢትዮጵያ ቡና 2ለ1 ቅዱስ ጊዮርጊስን በማሸነፍ የዋንጫ ተሸላሚ ሆኗል። ሁለቱ ክለቦች በተሳትፏቸው እያንዳንዳቸው 25ሺ ዶላር የተከፈላቸው ሲሆን፤ አሸናፊው ቡና ከ50ሺ  ዶላር ተሸላሚ ሆኗል።
ጨዋታው  በአውዲ ፊልድ የዲሲ ዩናይትድ ስታዲየም ሲካሄድ 5ሺህ በላይ የስታድየም መግቢያ ትኬቶች ተሽጠዋል።  የትኬት ዋጋው ከ29 ዶላር ጀምሮ ነበር። አቶ እዮብ ማሞ ካቻና ክለባቸው ዲሲ ዩናይትድ ክለብ ጨዋታውን በሜዳቸው ለማዘጋጀት  ከ700ሺህ ዶላር በላይ ወጪ አድርገዋል። ስለሆነም ሁለቱ ክለቦች በአሜሪካ በነበራቸው ቆይታ ሙሉ ወጭ ተሸፍኖላቸዋል።  በአጠቃላይ የሸገር ደርቢው በዋሽንግተን ዲሲ በተሳካ ሁኔታ መካሄዱ በአሜሪካ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ አመቺ የስፖርትና የባህል መድረክ በየዓመቱ ሊዘጋጅ የሚቻልበትን ሁኔታ አነቃቅቷል።
በጨዋታው በዲሲ፤ በሜሪላንድ ፤ኒውዮርክ፤ ቨርጂንያና ሌሎች ግዛቶች የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለመታደም ችለዋል። የከተማው ከንቲባና የዲሲ ዮናይትድ ባለድርሻ አካላትና ደጋፊዎች እንግዶች ነበሩ። በአሜሪካ ሜጀር ሶከር ሊግ የሚወዳደሩ ክለቦች ላይ የሚሰሩ የተጨዋቾች መልማዮችም ተገኝተዋል።
ዲሲ ዮናይትድን ከኢትዮጵያ እግር ኳስ  
ያገናኘው ድልድይ
ከሳምንት በፊት ሲኤንኤን ባቀረበው የስፖርት ዘገባ የኢትዮጵያ እግርኳስ ልዮ ሽፋን አግኝቶ ነበር። የሜጀር ሶከር ሊግ ክለብ በሆነው ዲሲ ዮናይትድና በኢትዮጵያ እግርኳስ መካከል የተፈጠረውን አዲስ አጋርነት ይመለከታል። የሲኤንኤን እውቅ የስፖርት ጋዜጠኞችም ለጉዳዮ ልዮ ትኩረት በመስጠት  ከትውልደ ኢትዮጵያዊው ቢሊየነር እዮብ ጆ ማሞ ጋር አጭር ውይይት አድርገዋል።
ከአቶ እዮብ ጋር ቃለምልልስ ማድረግ ብርቅ መሆኑን  የሲኤንኤን ጋዜጠኞች ከመነሻው ጠቅሰዋል። ባለሐብቱ በአሜሪካ ሚዲያዎች ስማቸው ከተነሳ በተለይ በነዳጅ ማደያና በሪልስቴት ኩባንያዎቻቸው ተያይዞ እንጅ ብዙ ከስፖርቱ የተገናኘ አልነበረም።
ሰሞኑን  በሰይፉ ፋንታሁን የኢቤስ ሾው ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የቲቪ ቃለምልልስ ለኢትዮጵያ ሚዲያ ሰጥተዋል። ወደ ሲኤንኤንም፣ ወደ ኢቢኤስም ባለሃብቱን ያቀረባቸው ጉዳይ ይኸው በኢትዮጵያ እግር ኳስ ላይ ለመስራት የያዙት ዓላማ ነው።
አባታቸው ማሞ ካቻ በኢትዮጵያ እግር ኳስ  በፈርቀዳጅነት  የሰሩና በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በከፍተኛ ደረጃ ለ25 ዓመታት የተወዳደረው ፈጣን የእግርኳስ ክለብን በባለቤትነት ያስተዳዳሩ ነበሩ። አቶ እዮብ ይህን የአባታቸውን አደራ በመረከብ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ላይ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ለማድረግ ተነስተዋል።
ሸገር ደርቢ በዋሽንግተን ዲሲ በሚገኘዉ  የሜጀር ሶከር ሊግ ክለብ ዲሲ ዮናይትድ ኦውዲ ፊልድ ስታድየም መካሄዱ በሲኤንኤን ሽፋን ያገኘው Dc united  Build Bridge with Ethiopian football በሚል ርዕስ ነበር።
 አቶ እዮብ  በዋሽንግተን ዲሲ ነዳጅ ማደያዎች  ከፍተኛ ስራ አስፈፃሚ መሆናቸውን የጠቀሰው ሲኤንኤን፤ በዲሲ ዮናይትድ ባላቸው የባለቤትነት ድርሻ ክለቡን በአሜሪካ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ማስተሳሰራቸውን ዳስሷል።
በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ አሜሪካ ላይ የተደረገው የሸገር ደርቢ  የኢትዮጵያን እግር ኳስ ክብርና ዝና  የሚያጎለብት እንደሆነ ያወሳው የሲኤንኤንን ዘገባ፤ ተጠቃሚዎቹ በልዮ ግጥሚያው የተሳተፉት ሁለቱ ክለቦች ብቻ ሳይሆኑ የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግና የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽንም ከአሜሪካ እግር ኳስ ጋር ዘላቂ ትስስር የሚፈጥሩበት እድል አግኝተዋል።
ጊዮርጊስና ቡና ለጨዋታው ሲመረጡ በኢትዮጵያ እግርኳስ አንጋፋና ብዙ ደጋፊ ያላቸው ክለቦች መሆናቸው  ከግምት ውስጥ መግባቱን የገለፁት  ቢሊየነሩ ፤ በዲሲና በተለያዮ የአሜሪካ ከተሞች  የሚገኙ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና የእግር ኳስ ደጋፊዎችን ያሰባሰብንበት ጅማሮ ነው ብለዋል።
ከያዙት እቅድ አንፃር በሚቀጥሉት 10 ዓመታት ምን  ተስፋ እንደሚያደርጉ  ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ እዮብ ማሞ በሰጡት ምላሽ አሜሪካ ውስጥ እግርኳስ እንደ “አሜሪካን ፉትቦል” ከፍተኛ እድገት እያሳየ ይቀጥላል ብለዋል። እግርኳስ በአሜሪካ የሚያሳየውን አስደናቂ እድገት ማየት እንደሚያጓጓቸው የገለፁት ባለሀብቱ በአሜሪካ  ኢትዮጵያውያን በፕሮፌሽናል ደረጃ የሚጫወቱበት እድል መፈጠሩንም ተስፋ እንደሚያደርጉ ገልፀዋል።
በአሜሪካ እግርኳስ ትውልደ  ኢትዮጵያውያን ተጨዋቾች እንዲበዙ ፍላጎቴ ነው በማለትም ዋና አላማቸውን ለሲኤንኤን ተናግረዋል።
በሸገር ደርቢ ላይ ሲኤንኤን ባቀረበው ሪፖርት ላይ በኒውካስል ክለብ የሚጫወተው አሌክሳንደር ይስሐቅ  ተነስቷል ። በተለያዮ የአለም ክፍሎች የሚገኙ ትውልደ ኢትዮጵያውያን በተመሳሳይ የእግርኳስ ህይወታቸውን በፕሮፌሽናል ደረጃ ለማሳደግ ተምሳሌትነት መፍጠር እንደሚያስፈልግም ተመልክቷል ።
አቶ እዮብ ከሳምንት በፊት ከሰይፉ ፋንታሁን ጋር  ባደረጉት ቃለ-ምልልስ በዲሲ ዩናይትድ ክለብ የጀመሩት እንቅስቃሴ 32 የአሜሪካ ክለቦችን የሚያነሳሳ ተምሳሌታዊ ተግባር መሆኑን አብራርተዋል። በቀጣይ በ2025 ኢትዮጵያ ብሔራወዊ ቡድንን በድጋሚ ወደ አሜሪካ ተጋብዞ ከዲሲ ዩናይትድ ጋር ለማጫወት እንደሚያስቡ፤ ዓመታዊ ባህል ሆኖ እንዲቀጥልና የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች በአሜሪካ የተለያዩ ከተሞች ተዟዙሮ እንዲጫወቱ እንሰራለን ብለዋል።
ወደ አሜሪካ የተዘረጋው ድልድይ ለኩብለላ መሆን የለበትም
ከአሜሪካ ሸገር ደርቢ ጋር ተያይዞ ያጋጠመው ዋና ችግር ከሁለቱም ክለቦች   ተጫዋቾችና  ሌሎች ባለሙያዎች ሳይመለሱ በስደት  መቅረታቸው ነው።
ከዋሽንግተን ዲሲ የወጡት መረጃዎች እንዳመለከቱት ከሁለቱ ክለቦች በአጠቃላይ 12 ኢትዮጵያውያ የተጓዙበትን ዓላማ በመናቅ አሜሪካ ላይ ኮብልለዋል። ከጊዮርጊስ 4 ከቡና 3 ተጨዋቾች እንዲሁም በሁለቱ ክለቦች የሚሰሩ የህክምናና የህዝብ ግንኙነት ባለሞያዎች ናቸው አሜሪካ ላይ የቀሩት።
ይህ ሁኔታ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ነቀርሳ የሆነውን  ስደት ያጋለጠ ሆኗል። ከሁለቱ ክለቦች  የጠፉ ተጨዋቾች በአሜሪካ ስደታቸው ህይወታቸውን ሊቀየሩ ቢችሉም፤ በተገቢው መንገድ ዝውውር አድርገው ያሳዳጋቸውን ክለብ የሚጠቅሙበትን እድል ግን ውሳኔው አሳጥቷቸዋል።
የማሞ ካቻ ልጅ
በአሜሪካ ከ36 ዓመታት በላይ የየኒት አቶ እዮብ ጆ ማሞ በነዳጅ ማደያዎች ፤ በሪልስቴትና በገበያ ማዕከሎች የሚሰሩ ኩባንያዎችን በባለቤትነት በመምራት ከፍተኛ ልምድ ያካበቱ ባለሃብት ናቸው። ትውልደ ኢትዮጵያዊው  የካፒታል ፔትሮሊየም ግሩፕ ዋና ባለድርሻ ሲሆኑ በዋሽንግተን ዲሲና ሌሎች የአሜሪካ ከተሞች ከ300 በላይ የነዳጅ ጣቢያዎችን በባለቤትነት የሚያስተዳድሩ ሲሆን፤  ከ750 ሚልየን ዶላር  ዓመታዊ ገቢ አለው። በሁሉም ኩባንያዎቻቸው ከ5 ሺ በላይ ለሚሆኑ ኢትዮጵያውያን የስራ እድል ፈጥረዋል፡፡
አባታቸው ማሞ ካቻ በኢትዮጵያ የትራንስፖርት ኢንዱስትሪ በፈርቀዳጅነት የሚጠቀሱ ታላቅ ኢትዮጵያዊ ነበሩ።  ኢትዮጵያ ውስጥ የመጀመርያውን አውቶብስ በመገጣጠም ለአገልግሎት አብቅተዋል። የምስራቅ አፍሪካ ትልቁን የትራንስፖርት ኩባንያ የመሠረቱ ተብለውም ተደንቀዋል።
ትውልደ ኢትዮጵያዊው ቢልየነር አቶ እዮብ ማሞ ከእውቁ ራፐር ዮ ጉቲ ጋር በመሆን የዲሲ ዩናይትድ ቡድን ሼር ገዝተው ባለቤት የሆኑት ከ5 ዓመት በፊት ነው።
አቶ እዮብ ከዲሲ ዮናይትድ ክለብ  6%  ድርሻን በገዙበት ወቅት ክለቡንም በርካታ ኢትዮጵያውያን የሚደግፉትና የሚጫወቱበት ክለብ ለማድረግ እንደሚጥሩ ተናግረዋል። ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾች በአሜሪካው ሜጀር ሊግ ሶከር በቅርብ ጊዜ እንደሚታዮም ተስፋ ያደርጋሉ። ዲሲ ዩናይትድ ከአሜሪካው ሜጀር ሶከር ሊግ ከመሠረቱ ክለቦች ግንባር ቀደም  ሆኖ ይጠቀሳል። በአገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ13 በላይ ዋንጫዎችን የሰበሰበ ስኬታማ ክለብም ነው። ክለቡ በ28 ዓመታት ታሪኩ በተለይ በዋሽንግተን ዲሲ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጋር በልዩ ሁኔታ ተሸልሟል። ከ20ሺ ተመልካቾችን የሚያስተናግደው የክልሉ ዘመናዊ ስታድዬም ከሜጀር ሶከር ሊግና ከሁለተኛ ዲቪዚዮን ጨዋታዎች በተጨማሪ በዓመት ውስጥ ከ100 በላይ የተለያዩ ዝግጅቶች የሚያስተናግድ ታዋቂ ስታድዬም ነው።


የሰው ልጅ ከቦታ ቦታ በመንቀሳቀስ አዳዲስ አካባቢን መጎብኘት ተፈጥሯዊ ባህሪው ነው፡፡ በዚህ ረገድ ደግሞ አዲስ አበባ ከመዝናኛነት ባለፈ ለጥናትና ምርምር የሚሆኑ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያላቸው በርካታ ተፈጥሯዊ፣ ታሪካዊ፣ ሰው ሰራሽና የባህላዊ ቅርሶች ባለቤት የሆነች ከተማ ናት፡፡ ከዚህም ባለፈ በዩኔስኮ  የተመዘገቡ በርካታ የሚዳሰሱ እና የማይዳሰሱ ቅርሶች ባለቤትም ናት። ከማይዳሰሱ ቅርሶች መካከል ለአብነት የመስቀል ደመራ እና የኢሬቻ በዓላት በወርሃ መስከረም ከሚከበሩ ሐይማኖታዊ እና ህዝባዊ በዓላት ውስጥ ተጠቃሾች ናቸው። ከሀገራችን የአደባባይ በዓላት መካከል በሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ ወጥቶ የሚሳተፍባቸው የፍቅርና የአብሮነት በአላት በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ የሚከበረው የመስቀል ደመራ እና በአብዛኛው የኦሮሞ ህዝብ ዘንድ ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው “የሆራ ፊንፊኔ ኢሬቻ” ባማረ ድባብ፣ በከፍተኛ ድምቀትና ውበት፣ በእንግዳ ተቀባይነት ስሜት፣ ባህላዊ እሴቱንና ስርዓቱን በጠበቀ መልኩ ከመቼውም ጊዜ በላቀ አብሮነት የምናከብረው፣ ትብብራችን ጎልቶ የሚወጣበት፣ ኢትዮጵያዊ ፍቅር እና ህብረ-ብሄራዊነት ደምቆና ፈክቶ የሚታይባቸው በዓላት ናቸው፡፡ የመስቀል ደመራ በዓል በአለም አቀፉ የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የማይዳሰስ የጋራ ቅርስ ሆኖ የተመዘገበ፤ ሃማኖታዊ ትዉፊቱ ተጠብቆ በደማቅ ሥነ-ስርዓት የሚከበር ሐይማኖታዊ በዓል ነው፡፡ ይህ በዓል ለአገራችን የገጽታ ግንባታና የቱሪዝም መስህብ በመሆን ከፍተኛ የዉጭ ምንዛሬን የሚያስገኝ የጋራ ሃብታችን ነው፡፡ በተመሳሳይ ኢትዮጵያ ካሏት ቱባ ባህሎችና እሴቶች መካከል አንዱ የገዳ አስተዳደራዊ ስርዓት አካል የሆነው የኢሬቻ በዓል፣ የራሱ የሆነ ውብ ባህላዊ መልክና ቀለም ያለው የኦሮሞ ህዝብ መገለጫ ነው፡፡ ይህ በዓል ህዝቡ እጅ ለእጅ ተያይዞ ለምለም ሳር በመያዝ በወንድማማችነት/እህትማማችነት ፈጣሪውን እንኳን ከደመና ወደ ፀደይ /ብርሃን/ አሸጋገርከን በማለት የሚያመሰግንበት እና ምህረት የሚለምንበት እንዲሁም የፈጣሪን ሀያልነት የሚያደንቅበት በተጨማሪም በፍጡራን እና በፈጣሪ መካከል ያለውን የግንኙነት ምስጢር ለትውልድ የሚገለጽበት የኦሮሞ ሕዝብ ባህላዊ እሴት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ፡ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የተለያየ እምነት ተከታዮች የየራሳቸው ሀይማኖታዊ በዓላት ቢኖራቸውም፣ አንዱ የሌላውን በዓል በእኔነት በማክበር በእጅጉ ይታወቃሉ። እነዚህ በዓላት በተለይም በመዲናችን አዲስ አበባ ሕዝብ ዘንድ በአብሮነት በደማቅ ሥነ-ሥርዓት የሚከበሩ ሲሆኑ፤ የአንዱ በዓል ለሌላውም ቤት ፌሽታ ሆኖ ሲከበር ኗሯል፡፡ በተጨማሪም በበዓላት መልካም ምኞት መግለጫ ስጦታዎችን በመለዋወጥ ቤት ያፈራውንም በማቋደስ በአንድነት ባህላዊ ጭፈራዎችን በመጨፈር እና በመመራረቅ ሰላም፣ፍቅርን እና ወንድማማችነትንና እህትማማችነትን በሚያጎለብት መልኩ ማክበር የከተማው ማህበረሰብ ልዩ መገለጫ ነው፡፡ ከተማችን አዲስ አበባ በዘንድሮው ዓመት እነዚህን ሐይማኖታዊ እና ህዝባዊ በዓላትን ከወትሮው በተለየ መልኩ በኮሪደር ልማት እጅግ አምራ እና ደምቃ ለበአሉ አከባበር ዝግጁና ምቹ ሆና እንግዶቿን በተለየ መልክ ለመቀበል ሽርጉዷን በማጠናቀቅ በጉጉት በመጠባበቅ ላይ ትገኛለች፡፡ እነኚህ በዓላት ስኬታማ እና ያማረ እንዲሆኑ በማድረግ ረገድ የአዲስ አበባ ህዝብ የተለመደውን የግንባር ቀደምትነት ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡ ከተማዋን ከማስዋብ እና አካባቢን ከማፅዳት ጀምሮ እንግዶቹን በየአካባቢው ባማረ መስተንግዶ ለመቀበል፣ በዓሉ ሰላማዊ ድባቡን ይዞ እንዲጠናቀቅ መንደሩንና አካባቢውን በንቃት ከመጠበቅ፣ ጀምሮ የተለያዩ ሁኔታዎች ሲያስተውሉ በያሉበት አጋልጦ በመስጠት ረገድ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከወትሮው ላቅ ያለ ነው፡፡ በዓሉ ከከተማችን አልፎ የአገራችንን ህዝባዊ ትስስር ከማጎልበትና ባህላዊ እሴቶቻችንን ከማሳደግ አንፃር ያለውን ጉልህ ሚና ከግምት ውስጥ በማስገባት የከተማ አስተዳደሩ ከሚያደርገው ጥረት ጎን ለጎን ህብረተሰቡም ለሰላምና ለአንድነት ይበልጥ ትኩረት በመስጠት በወንድማማችነት/እህትማማችነት መንፈስ በድምቀት ሊያከብረው ይገባል፡፡ በመሆኑም ከስንዴ ውስጥ እንክርዳድ እንደማይጠፋ ሁሉ አንዳንድ የጥፋት ሀይሎች የከተማችንን መልካም ገፅታ ለማጉደፍና የሚከበረውን የመስቀል ደመራ እና ሆራ ፊንፊኔ ኢሬቻ በዓላትን በተሳካ መልኩ እንዳይገባደድ ፍላጎቶች እንደሚኖራቸው ግልፅ ነው፡፡ በመሆኑም ሰላም ወዳዱ ህዝብ፣ እንደወትሮው ከፀጥታ ሃይሎችና ከህዝባዊ ሠራዊታችን እንዲሁም ከአመራሩ ጋር በመቀናጀት የጥፋት ህልማቸውን ማክሸፍ ይኖርበታል፡፡ በተጨማሪም የሚድያ ተቋማትና የሚድያ ባለሙያዎቻችን በንቃትና በፍጥነት ትክክለኛ መረጃዎችን ለህዝብ በማድረስ የበዓሉን መልካም ገፅታ በማሳየት የህዝቡን አብሮነት በሚገባ ለአለም ህዝብ የማንጸባረቅ ሚናቸውን እንደሚወጡ ይጠበቃል፡፡ በሌላ በኩል፤ ወደ ከተማችን የሚመጡ እንግዶቻችን እንዳመጣጣቸው ወደ አካባቢያቸው በሰላም እስኪመለሱ ድረስ በተለመደው የእንግዳ ተቀባይነት ስሜት እስከመጨረሻው ድረስ በትጋት እና በቅንጅት በመስራት በዓሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ ፣ ሁላችንም ከወትሮው ይበልጥ ተጠናክረን በትብብር ስሜት ሃላፊነታችንን ልንወጣ ይገባል፡፡

“አፍሪካ ታከብራለች” ከጥቅምት 27 እስከ ሕዳር 1 ቀን 2017 ዓ.ም.  በአዲስ አበባ ከተማ ሊካሄድ መሆኑን ተገልጿል። በዚህ መርሐ ግብር ላይ በርካታ ሁነቶች እንደሚከናወኑ አዘጋጆቹ ሐሙስ መስከረም 9 ቀን 2017 ዓ.ም. በተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን (ኢሲኤ) ለጋዜጠኞች በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አመልክተዋል።

ሌጄንደሪ ጎልድ ሊሚትድ እና ማያልዝ ኤቨንትስ ከአፍሪካ ሕብረት እና ከኢሲኤ ጋር በመቀናጀት የሚያዘጋጁት ይህ መርሐ ግብር፣ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ድጋፍ እንደተደረገለት በመግለጫው ተጠቅሷል። በአፍሪካ ሕብረት እና ኢሲኤ አዳራሾች ውስጥ የሚከናወን መርሐ ግብር ሲሆን፣ “በአፍሪካ አሕጉር ያለው ብዝሃነት ውስጥ የሚገኘውን አንድነት ለማሳየት እና የኢኮኖሚ ብልጽግናን በኪነ ጥበብ ስራዎች፣ በባሕል፣ በቅርስ፣ በቴክኖሎጂ እና በንግድ እንቅስቃሴዎች ለማጉላት ታልሞ የተዘጋጀ ነው” ተብሏል።

የዘንድሮው መርሐ ግብር መሪ ቃል “ለ21ኛው ክፍለ ዘመን የሚመጥን አፍሪካዊ አስተምህሮ” እንደሆነ በጋዜጣዊ መግለጫው ተነግሯል። የመክፈቻ ስነ ስርዓቱ ጥቅምት 27 ቀን 2017 ዓ.ም. በአፍሪካ ሕብረት ዋና ጽሕፈት ቤት የሚካሄድ መሆኑን ተገልጿል።

በተከታታይ አራት ቀናት የተለያዩ የውይይት መድረኮች፣ የሙዚቃ ኮንሰርት፣ ኤክስፖ፣ የባሕል እና የሽልማት ምሽቶች እንደሚካሄዱ በዚሁ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተብራርቷል።

Thursday, 19 September 2024 00:00

ጉርሻና ቅምሻ

በደራሲና ገጣሚ ማትያስ ከተማ የተፃፈዉ "ጉርሻና ቅምሻ" የተሰኘ አዲስ መፅሃፍ የሀገራችን ደራሲዎችና የኪነጥበብ ባለሙያዎች በተገኙበት እሁድ መስከረም 12 ቀን 2017 ዓ.ም ከጠዋቱ 3:00 ጀምሮ በኢትዮጵያ ቤተመዛግብት እና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት (ወመዝክር) አዳራሽ ውስጥ ይመረቃል።

Page 3 of 727