Administrator

Administrator

 •ከ12 እስከ 15 ሺ የሚደርስ  ሕዝብ ይሳተፋል ተብሏል
                              ከሦስት ወራት በኋላ የድርጅቱ ሆስፒታል ይመረቃል


       ከተመሰረተ 31 ዓመታትን ያስቆጠረው ሜሪጆይ ኢትዮጵያ የበጎ አድራጎትና የልማት ድርጅት፣ ከብራይት  አድቨርትና ኢቨንት ጋር በመተባበር፣ የገቢ ማሰባሰቢያ ሩጫ መርሐ ግብር ሊያካሂድ መሆኑን ገልጿል።
ባለፈው ረቡዕ መጋቢት 10 ቀን 2017 ዓ.ም፣ በዮድ አቢሲንያ የባሕል ምግብ አዳራሽ ለመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ የገቢ ማሰባሰቢያ ሩጫው መጋቢት 28 ቀን 2017 ዓ.ም. ጠዋት በዑራኤል አድርጎ ወደ ወሎ ሰፈር በሚወስደው የፒኮክ መናፈሻ አዲሱ አስፋልት መንገድ በመዝለቅ፣ የወሎ ሰፈርን አደባባይ ዞሮ በታችኛው አስፋልት ወደ መነሻው በመመለስ የሚጠናቀቅ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡  ሩጫው የሚሸፍነው አጠቃላይ ርቀት 5 ኪሎሜትር ሲሆን፣ በዚህ መርሐ ግብር ላይ ከ12 እስከ 15 ሺ የሚደርስ  ሕዝብ ይሳተፋል  ተብሎ እንደሚጠበቅ ተነግሯል፡፡
ለመርሐ ግብሩ ተሳታፊዎች የአዋቂና ሕጻናት ቲ-ሸርት መዘጋጀቱ የተገለጸ ሲሆን፤ ቲ-ሸርቶቹ ለአዋቂ 500 ብር፣ ለሕጻናት 300 ብር እንደሚሸጡ  ታውቋል፡፡  ቲ-ሸርቶቹን በሁሉም የሜሪጆይ ኢትዮጵያ ቢሮዎች  (በአስኮ ፣ በመገናኛ፣ በጊዮርጊስና ገዳም ሰፈር) እንዲሁም በዋና ዋና የዳሽን ባንክ ቅርንጫፎች (በልደታ፣ በጣና ገበያ ፣ በአድዋ አደባባይ፣ በፒያሳ፣ በጦር ሐይሎች፣ በቄራ፣ በንፋስ ስልክ፣ በቦሌ መድሃኒያለምና በሰሚት ቅርንጫፎች) ማግኘት እንደሚቻል ነው የተገለጸው።
የሜሪጆይ ኢትዮጵያ መስራችና ዋና ስራ አስፈጻሚ ሲስተር ዘቢደር ዘውዴ ባስተላለፉት መልዕክት፤ “አረጋውያንን እመግባለሁ፣ ጤንነቴን እጠብቃለሁ” በሚል መሪ ቃል በሚካሄደው የገቢ ማሰባሰቢያ ሩጫ መርሐ ግብር ላይ፣ ሁሉም ለበጎ አድራጎት ስራ ተነሳሽነት ያለው ዜጋ እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርበዋል።
 መቶ ሕጻናትን በመርዳት ሥራውን ሀ ብሎ የጀመረው ሜሪጆይ ኢትዮጵያ፤ በአሁኑ ወቅት ከአንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን በላይ ወገኖችን እየረዳ እንደሚገኝ ሲስተር ዘቢደር ገልጸዋል። በተጨማሪም፣ “ኢትዮጵያውያን ለኢትዮጵያውያን” በተሰኘው የበጎ አድራጎት እንቅስቃሴ፣ ከ6 ሺ 500 በላይ ሕጻናት እርዳታ ማግኘታቸውን ጠቁመዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ፣ አስኮ አካባቢ የተገነባው የሜሪጆይ ሆስፒታል ከ3 ወራት በኋላ እንደሚመረቅ የገለጹት ሲስተር ዘቢደር፤ ሆስፒታሉ ለ25 ሺ ታካሚዎች ነጻ የሕክምና አገልግሎት እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም፣ ከአሜሪካ የሲያትል ከተማ የነርሶች ማሕበር ለሜሪጆይ ኢትዮጵያ 18 የዳያሌሲስ ማሽኖች እንደተላኩ፣ በእነዚህም ማሽኖች አማካይነት ሐዋሳና አዲስ አበባ የኩላሊት ሕክምና ማዕከላት እንደሚከፈቱ ሲስተር ዘቢደር አክለው ጠቅሰዋል። በሌላ በኩል፣ ወጣት ባለሃብቶች የሚሳተፉበት ለሜሪጆይ ኢትዮጵያ አጋዥ የሆኑ የድጋፍ ስራዎችን የማስተባበር እንቅስቃሴ፣ ሐዋሳና አርባምንጭ ከተሞችን ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች በቅርብ ቀናት ውስጥ እንደሚከናወን ተናግረዋል።

 ታዋቂዋ ድምጻዊት ቬሮኒካ አዳነ፣ የቤት እቃዎችን  ለገበያ የሚያቀርበው  የሚዲያ ኢትዮጵያ ብራንድ አምባሳደር ተደርጋ የተሾመች ሲሆን፤ በኢትዮጵያ ብቸኛው የሚዲያ የቤት እቃዎች አስመጪና ዋና አከፋፋይ ከሆነው ከኬ.መቅድም ጄነራል አስመጪና ላኪ ድርጅት ጋር የአጋርነት ስምምነት ፈጽመዋል፡፡
ባለፈው ረቡዕ  መጋቢት 10 ቀን 2017 ዓ.ም፣ ኬ.መቅድም አስመጪና ላኪ ድርጅት ከአርቲስት ቬሮኒካ አዳነ ጋር በመሆን በአጋርነት ስምምነታቸው ዙሪያ በስካይላይት ሆቴል ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ አርቲስቷና ድርጅቱ በአጋርነት ለመሥራት የሚያስችላቸውን  የፊርማ ሥነስርዓትም አከናውነዋል፡፡
የሚዲያ ኢትዮጵያ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሲሳይ በየነ በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ በሰጡት ማብራሪያ፤ “ቬሮኒካ ድርጅታችንን የበለጠ ታስተዋውቅልናለች ብለን ብራንድ አምባሳደር አድርገን መርጠናታል፤ ማህበራዊ ሃላፊነታችንን ለመወጣትም አብረናት እንሰራለን፡፡” ብለዋል፡፡
የሚዲያ ብራንድ አምባሳደር በመሆኔ በጣም ዕድለኛ ነኝ ያለችው ድምጻዊት ቬሮኒካ፤ ስሙን ባላውቀውም የሚዲያን የቤት እቃዎች  መጠቀም የጀመርኩት ከሁለት ዓመት በፊት ነው ብላለች፡፡  “የምርቶቹን ጥራት በተመለከተ  እኔ ምስክር ነኝ፤ ተጠቅሜበት  አይቼዋለሁ” ስትልም ማረጋገጫ ሰጥታለች፡፡
ሚዲያ ኢትዮጵያ 12 ዘፈኖቿን ሙሉ ወጪውን ሸፍኖና የሚገባትን ክፍያ ፈጽሞ በጥራት እንዳሰራላት የገለጸችው ድምጻዊቷ፤ ይህም የአጋርነት ስምምነታቸው አካል መሆኑን ጠቁማለች፡፡
ባለፈው የፈረንጆች ዓመት በ”ፎርቹን 500”፣ በ227ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው የቻይናው የቤት እቃዎች አምራች ሚዲያ፣ የማንችስተር ክለብ ኦፊሴላዊ አጋር ሲሆን፣ የክለቡ ተጫዋች ERLING HALLAND ደግሞ  የኩባንያው  ዓለማቀፍ ብራንድ አምባሳደር መሆኑ ይታወቃል፡፡
ኬ.መቅድም ላለፉት 8 ዓመታት ጥራት ያላቸው የሚዲያ የቤት ዕቃዎችን በብቸኝነት በማስመጣት ሲያከፋፍል የቆየ ሲሆን፤ ከእነዚህም መካከል ፍሪጆች፣ አየር ማቀዝቀዣዎች፣ የልብስ ማጠቢያ ማሽኖች፣ የውሃ ማከፋፊያዎች፣ እቃ ማጠቢያዎችና የውሃ ማጣሪያዎች ይገኙበታል፡፡ በተጨማሪም  ኬ.መቅድም፤ ከ30 ዓመታት በላይ  ሰሊጥ፣ የቅባት እህሎች፣ ጥራጥሬ፣ ቅመማቅመም፣ ጣሂኒ እና ቡና ለውጭ ገበያ ሲያቀርብ መቆየቱን ለማወቅ ተችሏል፡፡


“ለእናቴ”  የጽሁፍ ውድድር ለ10 ቀናት ተራዝሟል



          እናት ባንክ፤ የድካማቸውን ያህል ያልተነገረላቸውን ብዙኃን ኢትዮጵያውያን እናቶችን የሚወክል “እማዬ” የተሰኘ ቅርንጫፍ ከትላንት በስቲያ ሐሙስ  በይፋ ከፍቶ ሥራ ያስጀመረ ሲሆን፤ ቅርንጫፉ ልጆች ለእናቶቻቸው ልዩ ልዩ ፕሮግራሞችን በነፃ ማከናወን የሚችሉበት ነው ተብሏል፡፡
“እማዬ” የተሰኘው ቅርንጫፍ የተከፈተው ቅዱስ አቡነ ጴጥሮስ ሃውልት ፊት ለፊት በሚገኘው የቀድሞው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን ት/ቤት ህንጻ ላይ ሲሆን፤ የእናት ባንክ አመራሮች የቅርንጫፉን መከፈት አስመልክቶ ለጋዜጠኞች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
የእናት ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት ወ/ሮ ገነት ሃጎስ በሰጡት ማብራሪያ፤ “ባንኩ “እማዬ” የሚል ስያሜ የሰጠው ይኸው ቅርንጫፍ፤ በእናትነታቸው ብዙ ዋጋ የከፈሉ፣ ነገር ግን የልፋታቸውን ያህል ያልተጻፈላቸውና ያልተነገረላቸው እናቶች ውክልና እንዲኖራቸው ታስቦ የተከፈተ ነው፡፡” ብለዋል፡፡    
 “ልጆች ለእናቶቻቸው ልዩ ልዩ ፕሮግራሞችን በነጻ ማከናወን የሚችሉበት፣ ዲዛይኑም ሆነ በውስጡ ያሉት ግብዓቶች ብዙኃኑን የአገራችንን እናቶች እንዲወክል ታስቦ የተሰናዳ ነው፡፡” ሲሉም አክለዋል፤ምክትል ፕሬዚዳንቷ፡፡
ማንኛውም ሰው በቅርንጫፉ ተገኝቶ ስለ እናቱ ስሜቱን የሚገልጽበት እንዲሁም በእናቶች ዙሪያ የተጻፉ መጻህፍትን የሚያነብበትና ራሱም የሚጽፍበት ሥፍራ ተዘጋጅቷል ተብሏል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ጥር 30 ቀን 2017 ዓ.ም ይፋ የሆነው “ለእናቴ” የተሰኘ የፅሁፍ ውድድር መጠናቀቁን የጠቀሰው ባንኩ፤ የ”እማዬ” ቅርንጫፍ መከፈትን ምክንያት በማድረግ ውድድሩን ለቀጣዮቹ አስር ቀናት ማራዘሙን አስታውቋል፡፡
ለ”እናቴ” የተሰኘው የጽሁፍ ውድድር ሁሉም ሰው ለእናቱ ያለውን ፍቅር፣ አክብሮት፣ ውለታና ምስጋና በዝርው ጽሁፍ (ግጥም ያልሆነ፣ በወግ መልክ፣ በደብዳቤ ቅርጽ) የሚያቀርብበት ሲሆን፤ “የዓመቱ ድንቅ እናት” የተሰኘው ውድድር ደግሞ ተወዳዳሪዎች በአካባቢያቸው በሕይወት ያሉና የሚያውቋቸውን ወይም የራሳቸውን እናቶች በጽሁፍ በድምጽና በምስል ቀርጸው በቀጥታ የሚሳተፉበት ነው፡፡
አዲስ አበባ የሚገኙና በውድድሩ መሳተፍ የሚፈልጉ በአዲሱ “እማዬ” ቅርንጫፍ እንዲሁም በክልሎች ያሉ ተወዳዳሪዎች በአቅራቢያቸው በሚገኙ የባንኩ ቅርንጫፍ ሥራዎቻቸውን ማስገባት ይችላሉ ተብሏል፡፡
የዘንድሮ የጽሑፍ ውድድር የመዝጊያ መርሃ-ግብር፣ የእናቶች ቀን በሆነው የግንቦት ወር መጀመሪያ፣ በደማቅ ሥነ-ስርዓት እንደሚካሄድ ባንኩ አስታውቋል፡፡    
በመላ ሃገሪቱ “እማዬ” ቅርንጫፍን ሳይጨምር 206 ቅርንጫፎች ያሉት እናት ባንክ፣ በአዲስ አበባ የሚገኙ ቅርንጫፎቹን ለሃገርና ለወገን በጎ በዋሉና  ዝናን ባተረፉ እንስቶች ስም ሲሰይም መቆየቱን አስታውሶ፣ ወደፊትም ቅርንጫፎቹን በመሰል እንስቶች ስም መሰየሙን  እንደሚቀጥልበት  ጠቁሟል፡፡

 “ደንቡን መተላለፍ ከ2ሺ ብር እስከ አንድ ሚሊዮን ብር ያስቀጣል!”


      አዲስ አበባ ለመመስረቷ ምክንያት ከሆኗት ወሳኝ ምክንያቶች መካከል ማራኪና ተስማሚ ውበቷ እንዲሁም የተፈጥሮ ሃብቷ ይጠቀሳሉ፡፡ ከእነዚህ የተፈጥሮ ጸጋዎች መካከል ደግሞ  ዓመቱን ሙሉ ይፈሱ የነበሩ ንጹህ ወንዞቿ ይገኙበታል፡፡
በጊዜ ሂደት ከህዝብ ቁጥር መጨመርና ከከተሜነት መስፋፋት ጋር ተያይዞ ወደ ወንዞች በሚለቀቁ ቆሻሻዎች እንዲሁም የተለያዩ ተረፈ ምርቶችና የኢንዱስትሪ ፍሳሾች ሳቢያ ለመዝናኛ ጭምር ያገለግሉ የነበሩት የመዲናዋ ንጹህ ወንዞች በእጅጉ ተበክለው ለዕይታም ለጤናም አደገኛ እየሆኑ መጥተዋል፡፡ የወንዞቹ መበከል የከተማ ግብርና ላይ ለተሰማሩ አርሶአደሮችም  ትልቅ ተግዳሮት መደቀኑ ይነገራል፡፡  
ባለፉት 20 ዓመታት የአዲስ አበባ ህዝብ ቁጥር እንደ ሌሎች የአፍሪካ ከተሞች ሁሉ ከእጥፍ በላይ እንዳደገ  መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ባለፉት ጊዜያት ዝናብ በዘነበ ቁጥር  የመዲነዋ ወንዞች መሀል ከተማዋን በጎርፍ የሚያጥለቀልቁ ሲሆን፤ ጎርፉ ተሸክሞት የሚመጣው ቆሻሻም  የነዋሪውን ጤና ለአደጋ ይዳርጋል፡፡ የመዲናዋን ንጽህናም ይበክላል፡፡
በመዲናዋ የሚገኙ ወንዞች ለበርካታ ዓመታት ትኩረትና ጥበቃ ተነፍጓቸው በመቆየታቸው   ለነዋሪው ጥቅምና ውበት ከመሆን ይልቅ ጉዳትና ጠንቅ ሆነዋል፡፡ እንኳንስ የመዝናኛ ሥፍራና የቱሪዝም ማዕከል ሊሆኑ ቀርቶ፣ በይፋ የቆሻሻና ፍሳሽ መልቀቂያና ማከማቻ ተደርገው መቆየታቸው ይታወቃል፡፡ ይሄ  ደግሞ በአፍሪካ መዲናነቷና በዓለማቀፍ ተቋማት መቀመጫነቷ ለምትታወቀው አዲስ አበባ ፈጽሞ የሚመጥናት አይደለም፡፡    
 በህገ መንግሥቱ አንቀፅ 44 ንኡስ አንቀፅ 1 ላይ በግልፅ እንደተቀመጠው፤ ሁሉም ሰው ንፁህና ጤናማ በሆነ አካባቢ የመኖር መብት ያለው ሲሆን፤ የተሻሻለው የአዲስ አበባ ቻርተር 361/1995 ህግም ይህንኑ ይደነግጋል፡፡ ምንም እንኳን ከ23 ዓመት በፊት የወጣ የብክለት መከላከል አዋጅ ህግ ቢኖርም፣ በትግበራው ላይ በነበረው ክፍተት ሳቢያ ውጤታማ ሳይሆን መቅረቱ ይታወቃል፡፡ በዚህም የተነሳ የመዲናዋ ወንዞች እጅጉን ቆሽሸውና ተበክለው አደገኛ የጤና ጠንቅ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል፡፡     
ከጥቂት ዓመታት በፊት ታዲያ በጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ሃሳብ ጠንሳሽነት፣  አዲስ አበባን እንደ ስሟ ለማስዋብና ለማዘመን እንዲሁም ከአፍሪካ ተመራጭ መዲና ትሆን ዘንድ   ያለመ የወንዝ ዳር ልማት ፕሮጀክት ተቀርጾ  በይፋ መተግበር ጀምሯል፡፡
የአዲስ አበባ የወንዝ ዳር አረንጓዴ ልማት ፕሮጀክት፣ ወይም “ሸገርን የማስዋብ ፕሮጀክት” እ.ኤ.አ በየካቲት ወር 2019 ዓ.ም በይፋ  የተጀመረ ሲሆን፤ ዓላማውም በዋናነት የከተማዋን ወንዞች በማጽዳት አረንጓዴና ውብ የህዝብ መዝናኛ ሥፍራ መፍጠር ነው፡፡ ፕሮጀክቱ በአጠቃላይ 56 ኪ.ሜ የሚረዝም ሲሆን፤ ከእንጦጦ ተነስቶ አቃቂ የፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያ ይደርሳል፡፡
በአሁኑ ወቅት የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክቱ የመዲናዋን ወንዞች ወደ ቀድሞ ተፈጥሯዊ ማንነታቸው ለመመለስና የመዝናኛና የቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ ታልሞ በትጋት እየተሰራ ይገኛል፡፡ ለአብነትም በከተማው አስተዳደር በ2ኛ የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት ስራዎች ከሚለሙ 8 ኮሪደሮች መካከል 21.5 ኪ.ሜ እርዝመት ያለው የእንጦጦ-ፒኮክ ወንዝ ዳርቻ ልማትና 20 ኪ.ሜ የሚረዝመው የቀበና ወንዝ ዳርቻ ልማት ተጠቃሽ ናቸው፡፡   
ፕሮጀክቱ በወንዝ ዳርቻዎች ላይ ስር የሰደደ ችግር ለሚታይባት አዲስ አበባ መሰረታዊ ለውጥ እንደሚያመጣም በከተማ አስተዳደሩ ጭምር ታምኖበት በቁርጠኛ አቋምና ትጋት ቀን ከሌት እየተሰራ ይገኛል፡፡
በከተማዋ እየተከናወነ የሚገኘው 2ኛው የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት  አንድ አካል የሆነው የወንዝ ዳርቻ ልማት፤ መዲናዋ የተፈጥሮ ፀጋዎቿን በአግባቡ ለመጠቀም በሚያስችል መልኩ ወንዞቿን ፅዱና አረንጓዴ በማድረግ፣ ለራሷም ሆነ ለተቀረው ዓለም አርአያ  ለመሆን ታይቶ በማይታወቅ የለውጥ ጉዞ ላይ ትገኛለች፡፡
ይሁን እንጂ አሁንም አንዳንድ ግለሰቦችና ድርጅቶች ደረቅ ቆሻሻዎችና የኬሚካል ፍሳሾችን ወደ ወንዞች በመልቀቅ የወንዞችን ብክለት እንዲባባስ እያደረጉ ናቸው። የብክለት መጠኑ ከላይኛው ተፋሰስ ወደ ታችኛው ተፋሰስ እየጨመረ በመምጣቱ በማህበረሰቡ ላይ ከፍተኛ የጤና መታወክን እያስከተለ ይገኛል።
በዚህም ምክንያት በህገ-መንግሥቱ የተቀመጠውን መብትና ግዴታ መፈፀም የግድ ብቻ ሳይሆን ወቅቱ የሚጠይቀው አሳሳቢ ጉዳይ በመሆኑ የማህበረሰቡን ጤና የሚያውኩና የወንዞችን ብክለት የሚያባብሱና ሌሎች መሰል ተግዳሮቶችን መፍታት አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል። ወንዞችን ማልማትና ከብክለት መከላከል ካልቻልን አዲስ አበባን የማስዋብና ማዘመን ራዕያችንን እውን ማድረግ አይታሰብም፡፡
የወንዞችን ደህንነት ለመጠበቅና ከብክለት ለመከላከል በአስተዳደሩ እየተከናወነ ከሚገኙ የወንዞች ዳር ልማት ጎን ለጎን፣ አዲሱ የወንዞች ዳርቻ ብክለት መከላከል ደንብ ቁጥር 180/2017 በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ፀድቆ፣ ከታህሳስ 4 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ ተደርጓል፡፡
ደንቡን በተገቢው ሁኔታ ተረድቶ ተግባራዊ ማድረግ ይቻል ዘንድ በተለያዩ ጊዜያት በርካታ የግንዛቤ ማስጨበጫ የውይይት መድረኮችን በመፍጠር ከማህበረሰቡ ጋር መግባባት ላይ የተደረሰ ሲሆን፤ አሁንም የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራው ይበልጥ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት በመታመኑ በወንዞች ዳርቻ አካባቢ ለሚገኙና ከጉዳዩ ጋር በቀጥታ ግንኙነት ያላቸው አምራችና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በደንቡ ዙሪያ በቂ ግንዛቤ እንዲጨብጡ እየተደረገ ነው፡፡
በከተማው የሚገኙ ወንዞች ለከተማዋ የውበት ምንጭ ሳይሆኑ የቆሻሻ መጣያ ሆነው መቆየታቸውን የሚናገሩት የአዲስ አበባ ከተማ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዲዳ ድሪባ፤ ይህ ታሪክ እንዲቀየር አስተዳደሩ በርካታ ሥራዎችን በመሥራት ላይ እንደሚገኝ ይገልጻሉ፡፡
ከተማችን ከግብር ከፋዮች በምታገኘው ገቢ የኮሪደር ልማትን ጨምሮ በርካታ ፕሮጀክቶችን በማከናወን ላይ እንደምትገኝ የጠቁሙት ዋና ሥራ አስኪያጁ፤ እነዚህን የለሙና የተገነቡ ስፍራዎች ለመጠበቅ የተለያዩ ደንቦች ጸድቀው ወደ ትግበራ መገባቱን ይናገራሉ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ወንዞች ብክለት በአካባቢና በጤና ላይ የሚያደርሰው ጉዳትና  መፍትሔዎች እንዲሁም የወንዞች ዳርቻ ልማትና ብክለትን ለመከላከል በወጣው ደንብ ቁጥር 180/2017 እና የቅጣት ሰንጠረዥ ዙሪያ ከማህበረሰቡ ጋር በስፋት ውይይት ተደርጎበት የጋራ መግባባትና  ግንዛቤ ላይ መደረሱን አቶ ዲዳ ድሪባ አብራርተዋል፡፡
በአሁኑ ወቅትም  ከግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራው ጎን ለጎን፣ ደንቡን ተላልፈው በሚገኙ አካላት ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ መወሰድ መጀመሩን ነው ዋና ሥራ አስኪያጁ የገለጹት፡፡
በአስተዳደሩ ካቢኔ በጸደቀው አዲሱ የወንዞች ዳርቻ ብክለት መከላከል ደንብ መሠረት፣ ደንቡን ተላልፈው በሚገኙ ግለሰቦችና ተቋማት ላይ የገንዘብ ቅጣት የሚጣል ሲሆን፤ ዝቅተኛው የገንዘብ ቅጣት ሁለት ሺህ ብር፣ ከፍተኛው ደግሞ እስከ አንድ ሚሊዮን ብር እንደሚደርስ  በሰነዱ ላይ  ተመላክቷል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደንብ ማስከበር ባለስልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ ሻለቃ ዘሪሁን ተፈራ ባስተላለፉት መልዕክት፣ንፁህ ወንዝና ጤናማ አካባቢ ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት፣ ማህበረሰቡም ሆነ ተቋማት ሃላፊነታቸውን በአግባቡ በመወጣት፣ ከአስተዳደሩ ጎን እንዲቆሙ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ወደፊትም ለህብረተሰቡ የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራው ተጠናክሮ የሚቀጥል ሲሆን፤ ደንቡን ተላልፈው በሚገኙ ግለሰቦችና ተቋማት ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ መውሰድ መጀመሩም አስታውቀዋል፡፡

አንዳንድ ተረቶች በአንድ ወቅት አልደመጥ ሲሉ፣ በሌላ ወቅት ተደግመው መነገራቸው ግድ ይሆናል፡፡ የሚከተለውም እንደዚያው ነው፡፡
ከእለታት አንድ ቀን ሦስት አህዮች በጠፍ ጨረቃ ሰፊ መስክ ላይ እየጋጡ ሳሉ፤ ሦስት ጅቦች የሚበላ ፍለጋ ሲዘዋወሩ ያገኙዋቸዋል፡፡
ጅቦቹ ገርሟቸዋል፡፡
አንደኛው ጅብ፤
“እነዚህ አህዮች እንዴት ቢጠግቡ ነው በእኛ ሰዓት፤ በእኛ ግዛት እንደዚህ ተዝናንተው የሚግጡት?”
ሁለተኛው ጅብ፤
“እውነትም የሚገርም ነው፡፡ የተማመኑት ነገር ቢኖር ነው እንጂ እንዲህ ያለ ድፍረት አይፈጽሙም ነበር”
ሦስተኛው ጅብ፤
“ታዲያ ለምን ችሎት ተቀምጠን አንፈርድባቸውም?” ሲል ሃሳብ አቀረበ፡፡
አህዮቹን ከበቡና ተራ በተራ ሊጠይቋቸው ተሰየሙ፡፡
የመጀመሪያዋን አህያ ጠሩና ጠየቋት፡፡ የማህል ዳኛው ነው የሚጠይቃት፡፡
“እሜቴ አህያ፤ ለመሆኑ በእኛ ሰዓት፣ በእኛ ግዛት፣ በጠፍ ጨረቃ፣ እንዲህ ዘና ብለሽ የምትግጪው ማንን ተማምነሽ ነው?”
እሜቴ አህያ፤
“አምላኬን፣ ፈጣሪዬን ተማምኜ ነው፡፡ በእኔ ላይ ግፍ የሚሰራን አምላኬ ዝም አይለውም፡፡ መአት ያወርድበታል፡፡”
የማህል ዳኛው ጅብም፤
“መልካም ሂጂ፡፡ ፍርድሽን ትሰሚያለሽ፡፡ ሌላዋን ጥሪያት”
ለሁለተኛዋ አህያም ጥያቄው ቀረበላት፤
“አንቺስ ማንን ተማምነሽ ነው በጠፍ ጨረቃ፣ በእኛ ሰዓት፣ በእኛ ግዛት
ፍንጥዝጥዝ ብለሽ የምትግጪው?”
ሁለተኛይቱ አህያም፤
“ጌታዬን፣ አሳዳሪዬን ተማምኜ ነው፡፡ በእኔ ላይ ጥቃት የሚያደርስን ማንምም ቢሆን ጌታዬ አይምረውም፡፡ ይበቀልልኛል ብዬ በማመን ነው” ስትል መለሰች፡፡
ማህል ዳኛው ጅብ፤
“መልካም፡፡ አንቺም ፍርድሽን ትሰሚያለሽ፡፡ ሌላዋን ጥሪያት” አላት፡፡
ሦስተኛይቱ ቀረበች፡፡
ማህል ዳኛ ጅብም፤
“አንቺስ ማንን ተማምነሽ ነው ይሄ ሁሉ መዝናናት?” አላት
ሦስተኛይቱ አህያም፤
“እናንተን፣ እናንተን፣ የአካባቢውን ገዢዎች ተማምኜ ነው ጌቶቼ”
ዳኛውም፤
“መልካም፡፡ ሁላችሁም ፍርዳችሁን ጠብቁ” አሉና ሸኟት፡፡
ዳኞቹ መምከር ጀመሩ፡፡
ግራ ቀኝ ዳኞች አስተያየት ከሰጡ በኋላ፣ የማህል ዳኛው ጅብ እንዲህ አሉ፡-
“የመጀመሪያዋን ብንበላት እንዳለችው አምላክ አይለቀንም፡፡ ይበቀልላታል፡፡ ሁለተኛዋን ብንበላት ምናልባት አሳዳሪ ጌታዋ ተከታትሎ ያጠፋናል፡፡ ይቺን ሦስተኛዋን እኛን የተማመነችውን ብንበላት ማናባቱ ይጠይቀናል!?”  ሲል መሪ - ሀሳብ አቀረበ፡፡
ሁለቱ ጅቦች ባንድ ድምጽ፤
“እውነት ነው፡፡ እኛን የተማመነችውን እንብላት!” አሉ፡፡
እነሱን የተማመነችው ላይ ሰፈሩባት፡፡
***
የጌቶች አስተሳሰብ ምን እንደሚመሰል ተገዢ ወዳጆች ማወቅ አለባቸው፡፡ ሎሌነቱን በቅጥ አለመያዝ የመጨረሻውን ቀን ከማፋጠን አያልፍም፡፡ “የምጣዱ እያለ የእንቅቡ ተንጣጣ” የሚለውን ተረት፣ በአፉ የሚንጣጣ ሁሉ በጊዜ ሊገነዘብ ይገባል፡፡ መጨረሻው፤ “ያመኑት ፈረስ ይጥል በደንደስ” ነውና፡፡ “እናቴን ያገባ  ሁሉም አባቴ ነው” ለሚሉ የዋሀን ሁልጊዜ ፋሲካ ሊመስላቸው ቢችልም፣ ለሁሉም ጊዜ አለውና “ምነው ምላሴን በቆረጠው” የሚያሰኝ የፍርድ ቀን እንደሚኖር አሌ አይባልም፡፡ “እንብላም ካላችሁ እንብላ፣ አንብላም ካላችሁ እንብላ” በሚል ጅባማ ፍልስፍና ውስጥ መበላላት መሪ መርሀ-ግብር መሆኑን ለአፍታም መዘንጋት የለበትም፡፡
“ለጋማማ አህያም ጋማ አላት
አያስጥልም እንጂ ጅብ ሲዘነጥላት” ሲባል የከረመው ያለ ነገር አይደለም፡፡
“እነሆ ብዙ ዘመን አለፍን፡፡ ከሁሉም የተረፈን ብዙ ምላሶችና እጅግ ጥቂት ልቦች ናቸው” ይላል ሲጆርጅ የተባለው ፀሀፊ፡፡ በሀገራችን በቅንነት ሃሳብ የሚሰጡና በሎሌነት ሀሳብ የሚሰጡ መለየት አለባቸው፡፡ “ውሸት አለምን ዞሮ ሊጨርስ ሲቃረብ እውነት ገና ቦት ጫማውን እያጠለቀ ነው” መባሉ በምክንያት እንጂ በአቦ - ሰጡኝ አይደለም፡፡ በየአገሩ፤ የንጉስ አጫዋቾች የተለያዩ ናቸው፡፡ አንድ የጋራ ባህሪ ግን አላቸው - ንጉሱ ሲያስነጥሱ ማስነጠስ፡፡ አድር ባይነት፡፡ በመካያው ራሱ አድርባዩ ማንነቱ ይጠፋበትና፤ “የዘሬን ብለቅ ያንዘርዝረኝ” ማለት እንኳ ይሳነዋል፡፡ “ነገር አንጓች እንኳን ለጌታው ለራሱም አይመችም” ነውና ፍፃሜው አጓጉል መሆኑ እሙን ነው፡፡
የትእዛዝ ሁሉ ጉልላት ለህሊና መታዘዝ ነው፡፡ ማንም ቢሆን ማን፤ ህሊናውን ሲክድ አታላይ መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡ ብልጥ ለማኝ፤ “ጌታዬ ጌታዬ፣ አምና የሰጡኝን ልብስ አምስት ዓመት ለበስኩት” እያለ ይኖራል፡፡ በእውቀት ያልተደገፈ ድፍረት፤ የህሊና ማጣት ምርኩዝ ነው፡፡ ወትሮም “መራዡ ተኳሹ” ሲል የኖረ፣ “በራዡ ከላሹ” ማለት ከጀመረ ሁለተዜ ጥፋት ነው፡፡ ሀገራችን አያሌ አድር - ባይ አይታለች፡፡ ለሀገራችን ጎታቿም አጥፊዋም “አሾክሹዋኪው” ነው፡፡ ከታሪክ መማር እርም በሆነባት አገር፣ ቀለሙን እየለዋወጠ አድር - ባይ  ሁሉ እየመጣ፤ “እንቅፋት በመታው ቁጥር ቲዎሪ ድረስ (ያውም እውነተኛ ቲዎሪ ካለው) እያለ፤ “መንገድ ባስቸገረው ቁጥር “መመሪያ ማሪኝ” እያለ ህሊናውን እየሸጠ ይኖራል፡፡ ልባም አይደለምና አፍ ያወጣል፡፡ ምላሹ እየረዘመ፣ አንጎሉ እየጨለመ ይሄዳል፡፡ አበው “ከመሃይም ምላስ ይሰውረን” የሚሉት ለዚህ ነው፡፡ ማህታማ ጋንዲ እንግሊዝን “በመጨረሻ ባዶህን ትወጣለህ!” ማለቱን አንርሳ፡፡
“ቅዳሴ ሲያልቅበት ቀረርቶ አከለበት” እንዲሉ፣ በምላሱ የሚተዳደር ሰው፣ ውሸት ማብዛቱ ግዱ ነው፡፡ እውቀተ - ቢስ መሰረቱ ለእውነት ረሃብ ያጋልጠዋል! “አፈኛ ሴት፣ የአምስት ዳኛ ሚስት ነኝ፤ ትላለች” የሚለው የወላይታ ተረት ኢላማ ይሆናል፡፡



 •እነ አቶ ጌታቸው ረዳ በጠ/ሚኒስትሩ ተመስግነዋል
                        •በፓርላማ ቄስ ሞገሴና ፊት አውራሪ መሸሻ ተነስተዋል

          ከትላንት በስቲያ ሐሙስ ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፣የግማሽ ዓመት የመንግሥታቸውን የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ያቀረቡበት የምክር ቤት ውሎ፣በርካታ አገራዊ አጀንዳዎች የተነሱበት ሲሆን፤ የበርካቶችን ትኩረት የሳቡ ጉዳዮችም ነበሩ፡፡ በ”ፍቅር እስከ መቃብር” ልብወለድ ድርሰት ውስጥ የምናውቃቸው ገጸባህርያት በፓርላማ መነሳታቸው ያስገረማቸው አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች አልጠፉም፡፡
ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት ጠ/ሚኒስትሩ፤ የባሕር በር ጥያቄን በተመለከተ ሰፊ ማብራሪያ አቅርበዋል። ከባህር በር ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ ኤርትራን የመውረር ፍላጎት እንደሌላት ያረጋገጡት ጠ/ሚኒስትሩ፤ “የኢትዮጵያ ፍላጎት ‘እንነጋገር፣ሰጥቶ በመቀበል መርህ--እንወያይ’ የሚል ነው” ብለዋል።
 “የኤርትራ ሕዝብ የሚያስፈልገው ልማት ነው። ተባብረን መልማትና መስራት እንጂ አንዱ አንዱን መውጋት የእኛ እቅድ አይደለም” ያሉት ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ፣ “ኢትዮጵያ ላይ ማንም አገር ወረራ ሊፈጽምና ከጀመርነው ህልም ሊያስቆመን ‘ይችላል’ የሚል ስጋት የለብንም” በማለት ተናግረዋል። አክለውም፤ “በቂ ዝግጅት ስላለን ማንም አያስቆመንም። ዝግጅት የምናደርገውም ጦርነትን ለማስቆም ነው” ሲሉም አክለዋል፡፡
 “የባሕር በር ጥያቄን ማንሳት ነውርነቱ ቀርቷል--የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ አጀንዳ ለመስጠት የመጣ ሳይሆን ባለፉት ዓመታት ትኩረት የተሰጠውና በ’መደመር’ መጽሐፍ ላይ የተካተተም ነው” ሲሉም አብራርተዋል፡፡
በዚሁ የምክር ቤት ውሎ የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን)ተወካይና የምክር ቤት አባል ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ ትችት አዘል የሆኑ ጥያቄያዎችን ለጠ/ሚኒስትሩ አቅርበዋል። “ችግሮችን በጠመንጃ ለመፍታት መሞከር አገሪቱን ወደ ማትወጣው ቀውስ ውስጥ ሊያስገባት ይችላል” ያሉት ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ፤ “አሁን ያሉትን ችግሮች መፍታት የሚቻለው በሃሳብ ልዕልና ብቻ ነው” ብለዋል፡፡
ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተቋማት፣ በኢትዮጵያ መንግሥት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች “ተፈጽመዋል” ሲሉ በተለያዩ ጊዜያት ያወጧቸውን ሪፖርቶች በመጥቀስ፣ “የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስለ እነዚህ የሰብዓዊ መብት ጉዳዮች አንድም ቀን አጀንዳ ይዞ ሲወያይ አልተመለከትንም” ያሉት ዶ/ር ደሳለኝ፤  “መንግሥት በተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ላይ ሃላፊነት ወስዶ በግልጽ ማብራሪያ የሚሰጠው መቼ ነው?” ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
በተለያዩ ቦታዎች ባሉት ግጭቶች ዜጎች ሕይወታቸውን ማጣታቸውንና በርካቶች ከቀያቸው መፈናቀላቸውን የጠቆሙት የምክር ቤት አባሉ፤ ባለፉት ዓመታት በትግራይ፣ አማራ፣ ኦሮሚያና ቤንሻንጉል ክልል ያሉት የጸጥታ ችግሮች የኢኮኖሚው ዘርፍ የሚፈለገውን ያህል እንዳያድግ ዕንቅፋት መሆናቸውንም አንስተዋል፡፡
በአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጁ ምክንያት ለእስር የተዳረጉ ፖለቲከኞችና ሌሎች ዕውቅ ግለሰቦች፣ እንዲሁም ምሁራን እንዲፈቱ የምክር ቤት አባሉ ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ ጠይቀዋል፡፡ “ባለፉት ሰባት ዓመታት በተለይም በኦሮሚያ፣ በአማራና በሌሎችም ክልሎች የሚፈፀሙ የጦር ወንጀሎችን ለፍርድ ማቅረብ ለምን አልተቻለም? የአገራዊ ምክክር ኮሚሽንን የመሰሉ ጉዳዮች ውጤታማ እንዲሆኑ ከተፈለገ በተለይም በኦሮሚያና አማራ ክልል የተኩስ አቁም መደረግ አለበት” ብለዋል፡፡
ከመንግሥት ጋር ቀረቤታ “አላቸው” ያሏቸውንና እርሳቸው የጠቀሷቸው ጉዳዮች ሲፈጸሙ” ችላ ብለዋል” በማለት የወቀሷቸውን ፖለቲከኞችና ምሁራን “ቄስ ሞገሴ” የሚል ስያሜ የሰጡት ዶ/ር ደሳለኝ፤ “የእርስዎ መንግሥት በቄስ ሞገሴዎች ውዳሴ ተከብቧል” ሲሉ ትችት ሰንዝረዋል፡፡
ጠ/ሚኒስትሩ የዶ/ር ደሳለኝ አስተያየት እንዳስገረማቸው በመግለጽ በሰጡት ምላሽ፤ “እኛ ሰፈር ፊት አውራሪ መሸሻ የሉም፡፡ ቄስ ሞገሴዎች ምን ያደርጋሉ?” ብለዋል፡፡ “ቄስ ሞገሴ፣ ፊት አውራሪ መሸሻ በሌሉበት ሕልውና እንደሌላቸው ይታወቃል፤ ባይሆን እኛ ጉዱ ካሳዎች ብንባል ያምር ይሆናል እንጂ በየት በኩል ነው ቄስ ሞገሴዎች እኛ ሰፈር የሚታዩት?” ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ አክለውም፤ “እኛ ትናንትናን ናፋቂዎች፣ ትናንትናን ለማጽናት የምናሸረግድ ሰዎች ሳንሆን፣ ነገን ለልጆቻችን ለመስራት መጋፈጥ የማይገባንን ጉዳይ የምንጋፈጥ ለውጥ ፈላጊዎች ነን።” ብለዋል።
ከእርሳቸው ሌላ በርካታ የምክር ቤቱ አባላትም “በኢትዮጵያ የተሟላ ሰላም ለማምጣት ምን እየተሰራ ይገኛል? በተለይም ከታጠቁ ሃይሎች ጋር ለመወያየት የመንግስት ቁርጠኝነት ምን ይመስላል? የቀድሞ ታጣቂዎችንም መልሶ ከሟቋቋም አንፃር የሚሰሩ ስራዎች ምን ይመስላሉ? እንዲሁም በሰላም ዕጦት ምክንያት በሕዝብ የሚደርሱ ዕንግልትን መፍታት ምን እየተሰራ ነው?” በማለት ጠይቀዋል።
“ኢትዮጵያ ውስጥ ሁለት ችግር አለ” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ “ዋናውና የመጀመሪያው የመጠፋፋት ባሕል ነው። ሁለተኛው ደግሞ የወታደራዊ መንግስት ዕሳቤ ነው” ሲሉ ገልጸዋል፡፡
“በድርድርና በውይይት የሚባል ልምምድ ባለመኖሩ ምክንያት አብዛኛው ፖለቲከኛ በመገዳደል የማመን አባዜ ዛሬም ችግር ሆኖብናል” ብለዋል፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፡፡ “የፍረጃ ችግር ኢትዮጵያ ውስጥ በስፋት አለ” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “ካዛንቺስን የመሰለ መንደር እንደዚህ አምሮበት ሲታይ የሚያደንቅ አንድ ፓርቲ የለም” በማለት ወቀሳቸውን ሰንዝረዋል፡፡
 “በአንድ እግራቸው በረሃ፣ በአንድ እግራቸው ፓርላማ ያሉ አካላት አራት ኪሎ የመግባት አባዜያቸው የሚለቃቸው አይደለም” ሲሉም ተናግረዋል።
በኢኮኖሚው በኩል፤ በ2017 ዓ.ም. የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት የስራ አፈጻጸም ምን እንደሚመስል ማብራሪያ የሰጡት ጠ/ሚኒስትሩ፤ ባለፈው ዓመት 8 ነጥብ 1 በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት መመዝገቡን ገልጸው፣ በተያዘው በጀት ዓመት ዕድገቱ  ከ8 ነጥብ 4 በመቶ በላይ ‘ይሆናል’ ተብሎ ይጠበቃል” ብለዋል፡፡
“ከአምስቱ ዘርፎች አንዱ የሆነው ግብርና ለኢኮኖሚው ሰፊ የሆነ ድርሻ አለው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በአነስተኛ ግብርና ባለፈው ዓመት ከነበረው 17 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር፣ ዘንድሮ 20 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በምርት መሸፈኑን አንስተዋል። እንዲሁም በኩታ ገጠም ግብርና ባለፈው ዓመት 8 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በምርት ሲሸፈን፣ ዘንድሮ ወደ 11 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሄክታር ከፍ ማለቱን አክለው ገልጸዋል፡፡
ጠ/ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ በስንዴ ምርት በከፍተኛ ደረጃ ላይ መቀመጧን ጠቅሰው፣ በመኸር ወቅት 4 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር ሲሸፈን፣ በበጋ 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በስንዴ ምርት መሸፈኑ አንስተዋል። ሆኖም በስንዴ ምርት በተገኘው ውጤት ነቀፌታቸውን ለሚሰነዝሩ ወገኖች፣ “የሚያማቸው፣ የሚቃጥላቸውና የሚያቀረሻቸው ቢኖሩም፣ እውነታው ይሄ ነው” በማለት ምላሽ ሰጥተዋል።
ከኮሪደር ልማት ጋር በተያያዘ በአዲስ አበባ ሕጋዊ ማስረጃ ኖሮት መሬት ወይም ካሳ ሳይከፈለው የተነሳ አንድም ሰው የለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከ17 ቢሊዮን ብር በላይ ካሳ መከፈሉን ገልጸዋል። “የተነሳንበትን ሕዝብ ልንጨፈልቀው አንችልም” ሲሉም አብራርተዋል፡፡
 “የኮሪደር ልማት ዋና ዓላማ ለልጆቻችን መልካም ሀገርና ከተማ ጥሎ ማለፍ ነው” ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ፤ በአዲስ አበባ፣ በጎንደር፣ በባሕር ዳር፣ በደሴ፣ በአምቦ፣ በሐረር፣ በሐዋሳ እና በሌሎች ከተሞች የኮሪደር ልማት እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል። ባለፉት አምስት ዓመታት 167 ሺህ ቤቶችን በመገንባት ጥቅም ላይ መዋላቸውን አያይዘው ጠቅሰው፣ አሁንም ከ100 ሺሕ በላይ ቤቶች በመንግስትና በግል አጋርነት እየተገነቡ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ከምክር ቤት አባላት በፕሪቶሪያው ስምምነት አፈፃጸም ላይ ለተነሳው ጥያቄ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በሰጡት ማብራሪያ፣ “ስምምነቱ ከፍተኛ ድል የተገኘበት ታሪካዊ ስምምነት ነው” ብለዋል፡፡ በተጨማሪም፣ “ስምምነቱን የተፈራረምነው ያሸነፍነውን ጦርነት አቋርጠን ነው፡፡ ይህም ለሰላም ያለንን ከፍተኛ ፍላጎት አሳይቷል” ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ከስምምነቱ ጋር በተያያዘ ከታዩ ክፍተቶች መካከል የታጣቂዎች ጉዳይ አንዱ መሆኑን የጠቀሱት ጠ/ሚኒስትሩ፤ “የተሃድሶ ስራው በተሟላ መንገድ አለመፈጸሙ በዋናነት የሚጎዳው የትግራይን ሕዝብ ነው” ብለዋል።
 “ተፈናቃዮችን በመመለስ ረገድ፣ በራያ እና በጸለምት ጥሩ ስራ ተሰርቷል፡፡ በወልቃይት አካባቢ የተጀመሩ ስራዎች ግን በሚገባው መንገድ አልሄዱም” ሲሉ ተናግረዋል፡፡ አያይዘውም፣ “የፌደራል መንግስት ዜጎችን ወደ ቀያቸው የመመለስ ፍላጎት ቢኖረውም፣ በተፈናቃዮች ላይ የሚሰራ አፍራሽ ፖለቲካ አስቸጋሪ ሆኖብናል” ሲሉም ገልጸዋል፡፡
“ባለፉት ዓመታት በፕሬዝዳንት ጌታቸው፣ በጄኔራል ታደሰ ወረደእና ጄኔራል ጻድቃን ገብረትንሳኤ የተመራው ጊዜያዊ አስተዳዳር ጦርነት እንዳይኖር አድርጓል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ምንም እንኳ ቀድሞ በነበረ ጦርነት ላይ ብንወቅሳቸውም፣ ባለፉት ሁለት ዓመት በነበረው ቆይታ ግን ማድነቅ ያስፈልጋል” ብለዋል። ማብራሪያቸውን ሲቀጥሉም፣ “ጊዜያዊ አስተዳደሩ ጊዜው በመጠናቀቁ እርሱን በተመለከተ ስራዎች እየተሰሩ ነው” በማለት ለምክር ቤቱ አስረድተዋል፡፡
በዚህም እስከ ቀጣዩ ምርጫ ያለውን የቆይታ ጊዜ ጊዜያዊ አስተዳደሩ የሚመራበትን ሕግ የማሻሻል ስራዎች እንደሚሰሩና አመራሮች የመቀያየር ስራ እንደሚከናወንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡
“የትግራይ ሕዝብ ጦርነት አይፈልግም፡፡ በውይይታችንም የተረዳነው ይህንን ነው፡፡ ጦርነት የሚፈልጉ ሃይሎች ጦርነት እንደማያዋጣ መገንዘብ አለባቸው፡፡” ሲሉ ማብራሪያቸውን የቀጠሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤”መከላከያ በሌሎች ክልሎች ‘ስራ ላይ ነው’ በሚል፣ ከሕግ አግባብ ውጪ የሚንቀሳቀሱ ከድርጊታቸው መቆጠብ አለባቸው” ሲሉ አሳስበዋል፡፡

የትግራይ ክልል ነጋዴዎች ችግር ፖለቲካዊ መፍትሔ እንደሚያሻው የተገለጸ ሲሆን፤ ነጋዴዎቹ በተለያዩ የክልሉ ከተሞች አስፈላጊ ሸቀጣሸቀጦችን የመደበቅ ተግባር ተስፋፍቶ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
የትግራይ ክልል ንግድና ዘርፍ ማሕበራት ምክር ቤት አመራሮችና ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው የስራ ሃላፊዎች ባለፈው ማክሰኞ መጋቢት 9 ቀን 2017 ዓ.ም.፣ መቐለ ከተማ በሚገኘው የምክር ቤቱ ጽሕፈት ቤት ለጋዜጠኞች ማብራሪያ ሰጥተዋል። የምክር ቤቱ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አታክልቲ ስዩም፣ የተወሰኑ ነጋዴዎች ተጨባጭነት የሌላቸውን ምክንያቶች በመፍጠር፣ አስፈላጊ ሸቀጣሸቀጦችን በመደበቅ የክልሉን ሕብረተሰብ ወደ አስከፊ ሁኔታ እንዲገባ እያደረጉት መሆኑን ገልጸዋል።
የንግዱ ማሕበረሰብ ከክልሉ ነዋሪዎች ጋር በመተባበር፣ ሸቀጣሸቀጥ የሚደብቁ ነጋዴዎችን ስርዓት ለማስያዝ እንደሚታገል የጠቁሙት አቶ አታክልቲ፤ “ጉዳዩ የሚመለከተው አካል በሕብረተሰቡ ዘንድ ግንዛቤ በመፍጠር፣ የገበያ ስርዓቱ ላይ ችግር በሚፈጥሩ ነጋዴዎች ላይ በተጠና አግባብ እርምጃ መውሰድ አለበት” ብለዋል።
የትግራይ ክልል የኢኮኖሚ መልሶ ማቋቋም ግብረሃይል አባል የሆኑት አቶ ሃየሎም መድህን በበኩላቸው፤ “ተጨባጭነት የሌለው ወሬ በመንዛት የገበያ ስርዓቱን የሚያደፈርሱ ደላሎች ከተግባራቸው ሊቆጠቡ ይገባል” ያሉ ሲሆን፤ የትግራይ ክልል የንግድ ማሕበረሰብ ከጦርነቱ በኋላ “አጋጥሞታል” ስላሉት ችግር አብራርተዋል።  የክልሉ የንግድ ማሕበረሰብ በጦርነቱ ሳቢያ ከደረሰበት ጉዳት ተከትሎ፣ እያጋጠሙት ላሉት ችግሮች የፌደራል መንግሥት ፖለቲካዊ መፍትሔ እንዲሰጠው ጠይቀዋል፤ አቶ ሃየሎም፡፡
የትግራይ ክልል ዘርፍ ማሕበራት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ጸጋይ ሓድጉ፣ “የትግራይ የንግድ ማሕበረሰብ ከባንክ ተበድሮ የተለያዩ ንብረቶችን በመግዛት ሲሰራ ቢቆይም፣ እነዚሁ ንብረቶቹ ግን በጦርነቱ ምክንያት ወድመውበታል።
ይህ በሆነበት ሁኔታ የተበደረውን ብድር ከእነወለዱ እንዲከፍል እየተገደደ ነው።” ብለዋል። “ከብሔራዊ ባንክና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት ተደርጎ የተወሰኑ መፍትሔዎች ተቀምጠዋል” ያሉት አቶ ጸጋይ፤ “የትግራይ ክልል ንግድ ማሕበረሰብ ዋና ዋና ችግሮች ፖለቲካዊ መፍትሔ የሚያስፈልጋቸው በመሆናቸው፣ ከጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር ለመወያየት ደብዳቤ ጽፈን ጠይቀናል። ምላሻቸውንም እየጠበቅን እንገኛለን።” ሲሉ ተናግረዋል።
የትግራይ ክልል ንግድና ዘርፍ ማሕበራት ምክር ቤት፣ የንግዱ ማሕበረሰብ የተጋረጡበትን ችግሮች ለመለየት በሁሉም የትግራይ ክልል ወረዳዎችና ከተሞች ሰሞኑን የውይይት መድረኮችን ለማካሄድ ማቀዱን አስታውቋል። ከዚህም በተጨማሪ፣ መጋቢት 14 ቀን 2017 ዓ.ም. በክልሉ ዋና ዋና ከተሞች ሰላማዊ ሰልፍ ለማካሄድ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም፣ በክልሉ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት ላልተወሰነ ጊዜ እንዲራዘም መደረጉ ታውቋል፡፡

 የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት፣ በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን ለሚሰሩ ጋዜጠኞች  አገር አቀፍ የጋዜጠኞች የዕውቅና ማረጋገጫ መታወቂያ እንደሚያዘጋጅ የተገለጸ ሲሆን፤ ከሚዲያ ባለሙያዎች ትችት ቀርቦበታል፡፡
የዕውቅና ማረጋገጫ መታወቂያው ጋዜጠኞች በሥራቸው ወቅት ለሚደርስባቸው ተፅዕኖ፣ እንግልትና አፈና ጥበቃና ከለላ ይሰጣል ያለው  ምክር ቤቱ፤  በጉዳዩ ዙሪያ ተጨማሪ ምክረ ሃሳቦችን ለማሰባሰብ መድረኮችን እንደሚያዘጋጅ አስታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት፣ ባለፈው ማክሰኞ መጋቢት 9 ቀን 2017 ዓ.ም.፣ በኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ምዝገባ፣ የሙያ ማረጋገጫና በብሔራዊ ሚዲያ ሽልማት ዕውቅና አሰጣጥ ዙሪያ ዓውደ ጥናት ያካሄደ ሲሆን፤ የመገናኛ ብዙኃን  ባለሞያዎችና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈውበታል፡፡ በዕለቱ ጥናት ያቀረቡት በባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን  መምህር ዶ/ር አየለ አዲስ፣ በኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኃን ነባራዊ ሁኔታ በርካታ ተግዳሮቶች ያሉበት ነው ብለዋል።
 የጋዜጠኛው መረጃ የማግኘት መብት የተገደበበትና የጋዜጠኛው ደኅንነት አደጋ ውስጥ የሚወድቅበት ሁኔታ እንዳለ  የጠቀሱት ዶ/ር አየለ፤ ‹‹የዘፈቀደ እስር፣ እንግልት፣ ስደትና ከሚሠሩበት የሚዲያ ተቋም ጋር ተያይዞ የሚከሰት መገለል በጋዜጠኞች ላይ የሚደርሱ ችግሮች ናቸው›› ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ጋዜጠኝነትና አክቲቪስትነትን መለየት እንዳልተቻለ የጠቆሙት መምህሩ፤ ለዚህም ምክንያቱ የዕውቅና ማረጋገጫ መታወቂያ ባለመሰጠቱ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ “የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት ባስጠናው ጥናት መሰረት፣ በአገር ውስጥ የሚሰሩ ሁሉም ጋዜጠኞች ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የዕውቅና ስርዓት ውስጥ በመታቀፍ ዲጂታላይዝድ የሆነ መታወቂያ ያገኛሉ።” ያሉት ዶ/ር አየለ አዲስ፤ “በየትኛውም የዓለም ክፍል በሚንቀሳቀሱበት ጊዜ የጋዜጠኝነት ሞያቸው መለያ ሆኖ ያገለግላቸዋል። በተጨማሪም በጋዜጠኝነት ስራቸው ከሚደርስባቸው ተጽዕኖ በመነሳት፣ ይህን የመብት ጥሰት በሕግ ፊት ለመሞገት የሚያስችል ስርዓት ለመዘርጋት ያስችላል።” ብለዋል፡፡
ማብራሪያቸውን ሲቀጥሉም፤ “በጋዜጠኞች ላይ የሚደርሱ የተለያዩ ዕመቃዎችና ጥቃቶችን በተመለከተ ለእነርሱ ድምጽ የሚሆን ማሕበረሰብ ለመገንባት የራሱን አስተዋጽዖ ያደርጋል። የጋዜጠኝነት ሞያን በአግባቡ፣ በተለያዩ አመላካቾች ለይቶ በመበየን ሞያተኞቹ ሕብረተሰቡን በዕኩል ዓይን እንዲያገለግሉ የሚያግዝ ነው።” ብለዋል። አክለውም፤ “የመረጃ ማዛባትና ሌሎች ስሕተቶችን ለመቅረፍ መታወቂያው የራሱን አስተዋጽዖ ያበረክታል። ምክንያቱም አንድ ዘገባ በማን እና መቼ መሰራቱን በቀላሉ ለመለየት የሚያስችል ስለሆነ፣ የተጠያቂነትን ስርዓት ይፈጥራል።” ሲሉ አስረድተዋል፡፡ በጋዜጠኞች የብቃት ማረጋገጫ ጉዳይ ላይ ለአንድ ዓመት ያህል ስድስት ሰነዶች መዘጋጀታቸውንም ምሁሩ ጠቁመዋል፡፡
የምክር ቤቱ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በቅርቡ  የተዘጋጀውን መመሪያ አጽድቆ ወደ ስራ እንደሚገባ የጠቀሱት ዶ/ር አየለ፤ ጋዜጠኞችን በዕውቅና ስርዓት ውስጥ ለማካተት የሚከናወነው የምዝገባ ስራ ተግዳሮቶች ሊገጥሙት እንደሚችሉ አንስተዋል። “ተግዳሮቶች ሊኖሩ ይችላሉ። አንደኛ የኢንተርኔት መዘጋት ነው። ነገር ግን በአካል የሚመዘገቡበት አሰራር ይፈጠራል። ሌላው የሚሰሩበት የመገናኛ ብዙኃን ሃላፊነት ወስዶ ጋዜጠኞችን ማስመዝገብ ስለሚችል፣ ይህንን አማራጭ መጠቀም ይችላል። አልያም ጋዜጠኞች የስራ ማመሳከሪያዎቻቸውን አቅርበው በበይነ መረብና በአካል መመዝገብ የሚችሉበት አማራጭ አለ።” ሲሉ ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ ይህ የዕውቅና ማረጋገጫ መታወቂያው ከመገናኛ ብዙኃን  ባለሞያዎች ትችት ቀርቦበታል። የ”ኢትዮጵያን ኢንሳይደር” የበይነ መረብ ሚዲያ መሥራችና ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ተስፋለም ወልደየስ ባቀረበው ሃሳብ፣ የዕውቅና ማረጋገጫ መታወቂያን በተመለከተ ከጥናታዊ ጽሁፍ ጋር የቀረበውን መመሪያ እያንዳንዱን አንቀጽ በመፈተሽ ውይይት ማድረግ እንደሚያስፈልግ  ገልጾ፣ ለዚህም  ሌላ የውይይት መድረክ ሊመቻች እንደሚገባ ጠቁሟል።
ጋዜጠኛ ተስፋለም ሃሳቡን ሲቀጥል፤ “የሚዲያ ምክር ቤቱ እነዚህን ሕጎች ያወጣው ለማን ነው? ለምሳሌ፡ የእኛ ተቋም የሚዲያ ምክር ቤቱ አባል አይደለም። ካነበብኳቸው መመሪያዎችና ጥናቶች እንደተረዳሁት፣ የተፈጻሚነት ወሰኑ ሁሉም ጋዜጠኛ ላይ ነው የሚሆነው። የሚዲያ ምክር ቤቱ በየትኛው ሃላፊነቱ ነው ሁላችንም የምንተዳደርበት ሕግ ሊያወጣ የሚችለው?” በማለት ትችቱን  ሰንዝሯል። አክሎም፣ ይህ ሃላፊነት በምክር ቤቱ የመተዳደሪያ ደንብ ላይ እንደሌለና የመገናኛ ብዙኃን ዓዋጅ ላይ የእርስ በርስ ቁጥጥርን በተመለከት የተጠቀሰ ነጥብ እንጂ ሌላ ዓይነት ሃላፊነት ለምክር ቤቱ እንደማይሰጥ ጠቁሟል።
በምክር ቤቱ የሚዘጋጀው መታወቂያ ለየትኛው ወገን እንደሚሰጥ  የጠየቀው ጋዜጠኛ ተስፋለም፤ በተዘጋጀው መመሪያ ውስጥ ጋዜጠኝነትን ለመበየን የተቀመጡት ማብራሪያዎች ብዙ የሚያነጋግሩ መሆናቸውን ገልጿል። በመጨረሻም፣ “[መታወቂያው] ‘ይፈታል’ ያላችሁትን ችግር በእርግጠኝነት ይፈታል? ስነ ምግባር ማስከበር የእናንተ ሚና ነው። እስማማበታለሁ። ነገር ግን ጋዜጠኝነት ምን እንደሆነ በመበየን የኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞችን ችግር መፍታት እንደሚቻል ነው የምታምኑት? በጋዜጠኞች ላይ የሚደርሰው ጥቃት አንድ መታወቂያ በመያዝ የሚቀር ነው ማለት ነው?” ሲል ለምክር ቤቱ የስራ አመራሮች ጥያቄውን አቅርቧል።
ሌላኛው ትችታቸውን ያቀረቡት የመርሳ ሚዲያ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሄኖክ ሰማግዜር ሲሆኑ፤ የጋዜጠኞች ዕውቅና ብቃት ማረጋገጫ ስርዓትን እንደማይቀበሉትና መሰረታዊ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽና የዜጎች መረጃ የማግኘት መብቶችን የሚጻረር መሆኑን ተናግረዋል። በማያያዝም፣ ይህ መመሪያና ስርዓት ተግባራዊ እንዳይደረግና ውድቅ እንዲሆን የጠየቁት አቶ ሄኖክ፤ “ለመገናኛ ብዙኃን ዘርፍ የማይጠቅምና ሌሎች የባሱ መዘዞችን የሚያመጣ ነው” ብለዋል።
አቶ ሄኖክ በአማራጭነት ባቀረቡት ሃሳብ፣ ጋዜጠኞች የመገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት ባወጣው የስነ ምግባር ደንብና ተቀጥረው እየሰሩበት ባለው ተቋም የኢዲቶሪያል ፖሊሲ መሰረት ተስማምተው ለመስራት መስማማታቸውን የሚገልጽ ፊርማ ከፈረሙ በኋላ፣ መታወቂያ እንዲሰጣቸው ቢደረግ የተሻለ እንደሚሆን አመልክተዋል። በውይይት መድረኩ ላይ የቀረበውን ጥናት “መሰረታዊ የሕግና የስነ ምግባር ጉዳዮችን በአግባቡ ያልተረዳ” ሲሉም ነቅፈውታል፡፡
የምክር ቤቱ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ታምራት ሃይሉ በበኩላቸው፤ ይህ መታወቂያ እንደ ሌሎች ዘርፎች ሁሉ፣ የጋዜጠኝነት ሞያ የተከበረ መሆኑን ለማሳየት እንደሚያግዝ ተናግረዋል። ይህም አሰራር በሌሎች አገራት የተለመደ መሆኑን ያነሱት አቶ ታምራት፤ በኢትዮጵያ ተግባራዊ ቢደረግ ለዘርፉ የራሱን ዕመርታ እንደሚያመጣ  ጠቁመዋል፡፡
በዓውደ ጥናቱ ላይ የተሳተፉ የዘርፉ ባለሞያዎች የተለያዩ ጥያቄና አስተያየቶችን አንስተዋል። ለጋዜጠኞች የፕሬስ መታወቂያ መሰጠቱን በአጽንዖት የተቃወሙና አሰራሩ በሌላ አማራጭ ሃሳብ እንዲተካ የጠየቁ ባለሞያዎች ሲኖሩ፣ ሌሎች ደግሞ መታወቂያ የመስጠቱ ሂደት የምክር ቤቱ ሃላፊነት ስለመሆኑ በአንክሮ ጠይቀው፣ ጉዳዩ እንደገና እንዲፈተሽ አሳስበዋል፡፡
ዓውደ ጥናቱ ለረቂቅ መመሪያውም ሆነ ለሌሎች የአሰራር ሂደቶች እንደ ሃሳብ ግብዓት ማሰባሰቢያ ያገለገለ መሆኑን ያስታወቁት አቶ ታምራት፤ በቀጣይም ምክር ቤቱ የውይይት መድረኮችን በማዘጋጀት የረቂቅ መመሪያውንም ሆነ ሌሎች የአሰራር ሂደቶችን የሚያዳብሩ ሃሳቦችን የማሰባሰብ ስራ እንደሚሰራ ነው ያመለከቱት።


• "ለእናቴ" የተሰኘው የጽሁፍ ውድድር ለ10 ቀናት ተራዝሟል
እናት ባንክ፤ የድካማቸውን ያህል ያልተነገረላቸውን ብዙኃን ኢትዮጵያውያን እናቶችን የሚወክል "እማዬ" የተሰኘ ቅርንጫፍ በዛሬው ዕለት በይፋ ከፍቶ ሥራ ያስጀመረ ሲሆን፤ ቅርንጫፉ ልጆች ለእናቶቻቸው ልዩ ልዩ ፕሮግራሞችን በነፃ ማከናወን የሚችሉበት ነው ተብሏል፡፡
"እማዬ" የተሰኘው ቅርንጫፍ የተከፈተው ቅዱስ አቡነ ጴጥሮስ ሃውልት ፊት ለፊት በሚገኘው የቀድሞው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን ት/ቤት ህንጻ ላይ ሲሆን፤ የእናት ባንክ አመራሮች የቅርንጫፉን መከፈት አስመልክቶ ለጋዜጠኞች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
የእናት ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት ወ/ሮ ገነት ሃጎስ በሰጡት ማብራሪያ፤ "ባንኩ "እማዬ" የሚል ስያሜ የሰጠው ይኸው ቅርንጫፍ፤ በእናትነታቸው ብዙ ዋጋ የከፈሉ፣ ነገር ግን የልፋታቸውን ያህል ያልተጻፈላቸውና ያልተነገረላቸው እናቶች ውክልና እንዲኖራቸው ታስቦ የተከፈተ ነው፡፡" ብለዋል፡፡
"ልጆች ለእናቶቻቸው ልዩ ልዩ ፕሮግራሞችን በነጻ ማከናወን የሚችሉበት፣ ዲዛይኑም ሆነ በውስጡ ያሉት ግብዓቶች ብዙኃኑን የአገራችንን እናቶች እንዲወክል ታስቦ የተሰናዳ ነው፡፡" ሲሉም አክለዋል፤ምክትል ፕሬዚዳንቷ፡፡
ማንኛውም ሰው በቅርንጫፉ ተገኝቶ ስለ እናቱ ስሜቱን የሚገልጽበት እንዲሁም በእናቶች ዙሪያ የተጻፉ መጻህፍትን የሚያነብበትና ራሱም የሚጽፍበት ሥፍራ ተዘጋጅቷል ተብሏል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ጥር 30 ቀን 2017 ዓ.ም ይፋ የሆነው "ለእናቴ" የፅሁፍ ውድድር መጠናቀቁን የጠቀሰው ባንኩ፤ የ"እማዬ" ቅርንጫፍ መከፈትን ምክንያት በማድረግ ውድድሩን ለቀጣዮቹ አስር ቀናት ማራዘሙን አስታውቋል፡፡
ለ"እናቴ" የተሰኘው የጽሁፍ ውድድር ሁሉም ሰው ለእናቱ ያለውን ፍቅር፣ አክብሮት፣ ውለታና ምስጋና በዝርው ጽሁፍ (ግጥም ያልሆነ፣ በወግ መልክ፣ በደብዳቤ ቅርጽ) የሚያቀርብበት ሲሆን፤ "የዓመቱ ድንቅ እናት" የተሰኘው ውድድር ደግሞ ተወዳዳሪዎች በአካባቢያቸው በሕይወት ያሉና የሚያውቋቸውን ወይም የራሳቸውን እናቶች በጽሁፍ በድምጽና በምስል ቀርጸው በቀጥታ የሚሳተፉበት ነው፡፡
አዲስ አበባ የሚገኙና በውድድሩ መሳተፍ የሚፈልጉ በአዲሱ "እማዬ" ቅርንጫፍ እንዲሁም በክልሎች ያሉ ተወዳዳሪዎች በአቅራቢያቸው በሚገኙ የባንኩ ቅርንጫፍ ሥራዎቻቸውን ማስገባት ይችላሉ ተብሏል፡፡
የዘንድሮ የጽሑፍ ውድድር የመዝጊያ መርሃ-ግብር፣ የእናቶች ቀን በሆነው የግንቦት ወር መጀመሪያ፣ በደማቅ ሥነ-ስርዓት እንደሚካሄድ ባንኩ አስታውቋል፡፡
በመላ ሃገሪቱ "እማዬ" ቅርንጫፍን ሳይጨምር 206 ቅርንጫፎች ያሉት እናት ባንክ፣ በአዲስ አበባ የሚገኙ ቅርንጫፎቹን ለሃገርና ለወገን በጎ በዋሉና ዝናን ባተረፉ እንስቶች ስም ሲሰይም መቆየቱን አስታውሶ፣ ወደፊትም ቅርንጫፎቹን በመሰል እንስቶች ስም መሰየሙን እንደሚቀጥልበት ጠቁሟል፡፡

“ለፋሲካ ሌሊት “ አዲስ ፊልም በGerman ሀገር በተካሄደው European wip festival ተሸላሚ የሆነው ፊልም ማክሰኞ መጋቢት 9 ቀን 2017ዓ.ም ከምሽቱ 12:00 ሰዓት ጀምሮ በዓለም ሲኒማ በቀይ ምንጣፍ ስነ ስርዓት ታዋቂ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ጥሪ የተደረገላቸው የክብር እንግዶች በተገኙበት ልዩ በሆነ ደማቅ የቀይ ምንጣፍ ስነ-ስርዓት ይመረቃል፡፡

Page 1 of 760