Administrator

Administrator

   የገቢ ማስባሰቢያ መርሃ ግብርም ያካሂዳል

               አገር በቀል የበጎ አድራጎት ድርጅት የሆነው የአምላክ ልጆች ፋውንዴሽን ዛሬ ከቀኑ 8፡00 ጀምሮ በኢሰመኮ አዳራሽ ፕሮግራሞቹን ይፋ ያደርጋል። በዕለቱ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብርም ያከናውናል።
ገና በ10 ዓመቱ ራዕዩን ጽፎ ባስቀመጠውና በ23 ዓመት የወጣትነት አፍላ እድሜው ይህችን ዓለም በተሰናበተው ወጣት የአምለክ ፍቅር አለባቸው ስም የተቋቋመው “የአምላክ ልጆች ፋውንዴሽን” በዋናነት በልጆች አስተዳደግ፣ በቤተሰብ ግንባታ ኑሯቸውን በጎዳና ላይ ያደረጉ ልጆችን ህይወት በመቀየር እና ከቤተሰቦቻቸውና ከህብረተቡ ጋር በማቀላቀል ስራ ላይ የተሰማራ ሲሆን በበጎ አድራጎትና ማህበራት ኤጀንሲ በህጋዊ መንገድ የተቋቋመ ነው።
ወጣቱ የአምላክ ፍቅር አለባቸው ገና በ10 ዓመቱ (2001 ዓ.ም) ወላጅ አልባና የጎዳና ልጆችን ለመመገብ፣ ለማስተማርና ህይወታቸውን በዘላቂነት ለመቀየር እንዲሁም የሀገሩን ድህነት ለመቅረፍ የነበረውን ህልም በፅሁፍ  ጽፎ ያለፈ ሲሆን፣ የአምላክን ህልም ለማሳካት ቤተሰቦቹ በስሙ ፋውንዴሽን ያቋቋሙ ሲሆን ተቋሙ የወጣቱን ህልም ለማሳካት እንቅስቃሴ መጀመሩም ታውቋል። ዛሬ በሚካሄደው በዚህ መርሃ ግብር ወጣቱ የአምላክ ፍቅርን ከመዘከር ጀምሮ የፋውንዴሽኑ አላማና ተግባራት ለህዝብ የሚተዋወቁ ሲሆን የገቢ ማሰባሰቢያም እንደሚካሄድ ታውቋል። በእለቱ የአምላክ ወላጆች፣ ጓደኞች፣ የራዕዩ ደጋፊዎች ፣ የውጭና የአገር ውስጥ የፋውንዴሽኑ ድጋፍ ሰጪዎች በክብረ በዓሉ ላይ የሚታደሙ ሲሆን ሁሉም ይህን ፋውንዴሽን በሙያ፣ በእውቀትና በገንዘብ እንዲደግፍ ጥሪ ይተላለፋል ተብሏል።የካንጋሮ ኢንደስትሪያል ግሩፕ አካል የሆነው ዩናይትድ ቤቨሬጅስ አክሲዮን ማኅበር ዋሊን የተሰኘ አዲስ የቢራ ምርት ለገበያ ማቅረቡ ተገለፀ። በኦሮሚያ ክልል ሞጆ ከተማ ከ88 ሚሊዮን ዩሮ በላይ በሆነ መነሻ ካፒታል ዘመናዊ የቢራ ፋብሪካ በማቋቋም ከሶስት አመት በፊት ስራውን በይፋ የጀመረው ይኸው ድርጅት፤ የማምረት አቅሙን የሚያሳድግ የፋብሪካ ማስፋፊያ ማጠናቀቁን እንዲሁም የአዲሱን የዋሊን ቢራ ወደገበያ መቅረብ በማስመልከት በስካይላይት ሆቴል ደማቅ ፕሮግራም አካሂዷል። በፕሮግራሙ ላይ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት እንዲሁም ታዋቂ የንግዱ አለም ሰዎች የተገኙ ሲሆን የኦሮምኛ ቋንቋ ስያሜ ያለው አዲሱ ዋሊን ቢራ ለታዳሚዎች የማስተዋወቅና የቅምሻ ፕሮግራም ተደርጓል።
አዲሱ ዋሊን ቢራ በተለይም በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ያለውን ተጠቃሚ ማዕከል አድርጎ የተዘጋጀ መሆኑን የድርጅቱ ተጠባባቂ ስራ አስኪያጅ አቶ ተሬሳ ኡርጌሳ ተናግረዋል። ኢትዮጵያ የበርካታ ባህልና እሴቶች ባለቤት ናት ያሉት ኃላፊው ድርጅቱ አቅም በፈቀደ መጠን ልዩ ልዩ ኢትዮጵያዊ ባህልና እሴቶችን በማጉላት ህዝባችን የኔ ብሎ የሚቀበላቸውን ምርቶች ወደገበያ ማቅረባችንን እንቀጥላለን ብለዋል።
ኃላፊው አያይዘው እንደገለፁት ድርጅቱ ያለውን የምርት አይነቶች የበለጠ በማስፋት፣ ሀገር በቀል እሴትን ከሚያንፀባርቁ ምርቶች በተጨማሪ በአለም አቀፍ ደረጃ ዝነኛ የሆኑ የመጠጥ ምርቶችን አምርቶ ለሀገራችን ገበያ የማቅረብ እቅድ እንዳለውም አስታውቀዋል። አሁን ለገበያ የቀረበው ዋሊን ቢራ ፕሪሚየም ላገር ቢራ ሲሆን በተመረጡ የሀገራችን ከተሞች ለተጠቃሚዎች መቅረብ መጀመሩን ለማወቅ ተችሏል። አብሮነት የሚል አቻ ትርጉም ባለው ዋሊን የተሰየመው አዲሱ ቢራ እጅግ ዘመናዊ በሆነው የመጨረሻው የቢራ ጠመቃ ቴክኖሎጂ፣ በታዋቂው የክሮንስ ጀርመን ማሽነሪና ከ50 ዓመታት በላይ የጠመቃ ልምድ ባላቸው አንቱ የተባሉ ባለሙያዎች የሚዘጋጅ በመሆኑ ጥራትን የሚያከብረው ህዝባችን ይህንን ልዩ ምርት በደስታ እንደሚቀበለው አንጠራጠርም ሲሉ የገለፁት ደግሞ የድርጅቱ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ኤፍሬም ይርጋ ኃይሌ ናቸው።
ዩናይትድ ቤቨሬጅስ አክሲዮን ማህበር በካንጋሮ ፕላስት እና በዩናይትድ አፍሪካ ቤቨሬጅስ ጥምረት እ.ኤ.አ በ2016 የተመሰረተ ድርጅት መሆኑ ይታወቃል። ካንጋሮ ኢንደስትሪያል ግሩፕ ወይንም ይርጋ ኃይሌና ቤተሰቦቹ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በማኑፋክቸሪንግ፣ በሪል ስቴት፣ በኢምፖርትና ኤክስፖርት ንግድ፣ በግብርናና መሰል የኢንቨስትመንት መስኮች ላይ ተሰማርቶ ላለፉት 60 ዓመታት በሀገራችን ሲሰራ የቆየ ሀገር በቀል ድርጅት ነው።

ውድ ህወኃት፡-
ሰዎች ክፋትህን ለመግለፅ በሰይጣን ይመስሉህ ነበር፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ክፋቱ መጠን አጥቷል በሚል መግለጫ ቃላት አጥተው ሲቸገሩ ታዝቤአለሁ፡፡ አንተ ራስህን ይገልፀኛል ብለህ የምታስበው ቃል እንደሚኖርህ አልጠራጠርም፡፡
ካላስቸገርኩህ ብትነግረኝ ደስ ይለኛል፡፡ምስጢር እንደምጠብቅ ቃል እገባለሁ፡፡
ሳሚ፤ 7ኛ ክፍል
ውድ ህወኃት፡-
ህወኃት ከጥፋትና ውድመት በስተቀር የሚያውቀው አንዳችም በጎ ነገር የለም ሲባል እሰማለሁ፡፡
ይሄ ሃሰተኛ ውንጀላ መሆኑን በማስረጃ ልታሳምነኝ ትችላለህ፡፡ እኔ ለማመን ዝግጁ ነኝ፡፡ አደራ እሱንም ደሞ እንዳትዋሸኝ፡፡
 ገነት፤ 8ኛ ክፍል
ውድ ህወኃት፡-
ህዝብ መግደልና ማፈናቀል እንዲሁም ንብረትም ማውደም የሚበቃህ መቼ ነው?
“ሲኦል ስገባ ነው” እንዳትለኝና እንዳላዝንብህ፡፡ መልሱን በጉጉት እጠብቃለሁ፡፡
ጆሴፍ፤ 6ኛ ክፍል
ውድ ህወኃት፡-
አንዳንዶች ህወኃት ትናንሽ ህጻናትን ጦር ሜዳ ይልካል ብለው ሲያወሩ ሰምቼ አላመንኳቸውም፡፡
"የፈለገ ሰይጣን ብትሆን አታደርገውም” ብዬ አስባለሁ፡፡ ከአንተ ከራስህ ግን እውነቱን መስማት እፈልጋለሁ፡፡ እውነቱን ካልነገርከኝ ከት/ቤት ጓደኞቼ ጋር ሰልፍ ለመውጣት ተመካክረናል፡፡ እስከ መጪው እሁድ ብቻ ነው የምጠብቅህ፡፡  
ቢኒያም፤ 7ኛ ክፍል
ውድ ህወኃት፡-
“ህወኃት ት/ቤታችሁን አፍርሶታል” ተብለን እስካሁን ድረስ ትምህርት አልጀመርንም፡፡ ከክረምት ጀምሮ ቤት ውስጥ ተቀምጠን ደብሮናል፡፡
ት/ቤቱን ያፈረሳችሁት በጣም ያረጀ ነው ብላችሁ ነው አይደል?! ማንም ሳይነግረኝ ነው ያወቅሁት፡፡ ሰርታችሁ ሳትጨርሱ ማፍረሳችሁ እኔ ግን ማመን አቃተኝ፡፡
ሚኪ፤ 5ኛ ክፍልMonday, 01 November 2021 05:30

የፖለቲካ ጥግ

በፖለቲካ ሁለት ነገሮች አስፈላጊዎች ናቸው፡፡ የመጀመሪያው ገንዘብ ነው፡፡ ሁለተኛውን አላስታውሰውም፡፡
ማርክ ሃና
የንግድ መሪም ሆንክ የፖለቲካ መሪ፣ በዙሪያህ እውነት ለመናገር ዝግጁ የሆኑ ሰዎች ያስፈልጉሃል፡፡
ማይክል ሮገር
እንዲዋሹህ የማትፈቅድ ከሆነ፣ ፖለቲካን ከመከታተል ራስህን አቅብ፡፡
ስቲቨን ማጊ
ጦርነትን ብዙ ጊዜ የሚያውጁት ተዋጊዎቹ አይደሉም፡፡
ዋይኔ ጌራርድ ትሮትማን
የማይጠይቅ ሕዝብ የሚመሩ  መንግስታት እንዴት የታደሉ ናቸው፡፡
አዶልፍ ሂትለር
ህገ መንግስት አጭርና ድብቅ መሆን አለበት፡፡
ናፖሊዮን ቦናፖርት
ሰላም የጦርነት አለመኖር አይደለም፤ የፍትህ መስፈን እንጂ፡፡
ሃሪሰን ፎርድ
ዲሞክራሲ የመምረጥ መብት ብቻ አይደለም፤ በክብር የመኖር መብትም ጭምር ነው፡፡
ናኦሚ ክሌይን
ገንዘብ ሊገዛው የሚችል፣ ምርጥ መንግስት አለን፡፡
ማርክ ትዌይን
ማሳመን ካቃተህ አደናግራቸው፡፡
ሄል ኤስ. ትሩማን
መንግስቴን ሳይሆን አገሬን እወዳለሁ፡፡
ጄሲ ቬንቱራ
አሜሪካ ለእኔ ነፃነት ማለት  ናት፡፡
ዊል ኔልስን

Monday, 01 November 2021 05:36

ማራኪ አንቀፅ

 በህይወቴ የሚገርም፣ የሚወራ፣ የሚያምር፣ የሚያስፈነድቅ፣ የተኖረ የፍቅር ታሪኬ ከፍጼ ጋር የነበረኝ ጊዜ ነበር። በጣም ነበር የማፈቅረው። እናቴን እስከ መተው፣ ከእህቴ እስከ መጣላት፣ ከወንድሜ እስከ መደባደብ፣ አባቴ እስኪታዘብ፣ ጎረቤት እስኪፈርድብኝ፣ ትምህርት ቤት ሰነፍ ሆኜ ክፍል እስከ መድገም፣ ጓደኞቼ ተረድተው እስኪያዝኑልኝ… ልቤ ጥፍት እስኪል እወደው ነበር። የምር!
እሱ ግን አይረዳኝም። እሱ የአፍ ፍቅር ይወዳል። ልብ ሳይሆን አንደበት ነው የሚያዳምጠው። “ፍቅሬ፣ ማሬ፣ ባባዬ፣ ቤቢ፣ ፍጼ፣ ሕይወቴ፣ አንጀቴ…” መባል ይፈልጋል። እኔ ደግሞ አልችልም። ልብ ካለው ልቤን አያዳምጥም። እኔ ነገር አቀናብሮ ማውራት አልችልም። ያኔ የምር!
በዚያ ላይ ፍጼን በጣም አፈቅረዋለሁ። በጣም ታላቄ ይመስለኛል። ስለምፈራው ዝም እለዋለሁ። እሱ ሲሳሳትም ሆነ ትክክል ሲሆን አስተያየት ይፈልጋል። እኔ ዝም። ዝም እእእእ… እሱ ንድድ። ንድድድድድ… ለጥፋቱ ወቀሳ ለስራው አድናቆት ይጠብቃል። መጠበቅ ይጎዳል። በጠበቁት ልክ ሲጎድል ህመሙ ይከፋል። ፍጼ ይታመም ነበር። በዚያ ላይ ራሱን እንደ ስሙ ፍጹም አድርጎ ነው የሚያስበው። ትልቁ ስህተቱ። ፍጽምና። ራሱን ፍጹም አድርጎ ማሰቡ ባልከፋ (መቼስ ስሙም ፍጹም አይደል)። ችግሩ ከሌላው ሰው ፍጽምና መጠበቁ ነው።
“ለምን አታወሪም”፤ ለምን ውሎሽን ፍጼ ዛሬ እኮ እንዲህ ሆኖ እንዲህ ተፈጥሮ አትይም… ለምን ስሜን አትጠሪኝም?” ይለኛል። እንዲህ ሲለኝ ይበልጥ መናገር ይደብረኛል። መወቀስ አልፈልግም። ስለዚህ ይብስ ዝም እለዋለሁ።  ይናደዳል። ጭርጭር ላል። ሲናደድ ደስ ይለኛል በጣም የሚወደኝ ይመስኛል።
በፍጼ በጣም ደስ ያለኝ ቀን ትምህርት ቤት ወላጅ የሆነኝ ቀን ነበር። ክፍል ውስጥ “ወክማን” የምትባለውን የሲዲ ማጫወቻ ይዤ ሙዚቃ እየሰማሁ ነው። ልብ ጥፍት የሚያደርጉ የፍቅር ዘፈኖች አቀናብሮ የሰጠኝ ፍጼ ነው። ስለዚህ የቱ ጋ ምን ሊለኝ እንደፈለገ ለማወቅ፣ እያንዳንዱን የሙዚቃ ስንኝ ምዝምዝ አድርጌ እየሰማሁ ለመረዳት በጆሮ ማዳመጫ አድርጌ፣ ሙዚቃው ላይ ተመስጬ እያዳመጥኩ ነው።
በዘፈኑና በመልዕክቱ ተመስጬ ሳላየው ሒሳብ አስተማሪያችንና የክፍል ኃላፊያችን ለካ ወደ ክፍል ገብቷል። ገብቶም ሳይቆይ አልቀረም። እኔ ልብም አላልኩት። ልብስ የታለ? የለም ፍጼጋ ነው። ቀልብ የለም በዘፈኑ ተባብሎ ይዋትታል። ዓይን የለም- በፍጼ ተጋርዷል። ማስተዋል የለም፣ ፍቅር አያስተውልም። አስተማሪያችን ዘሎ መጥቶ ከጆሮዬ ላይ ማመጫውን ሲነቅለው ነው ከትዝታ ሰፈር በፍጥነት ተመልሼ ክፍል ውስጥ የነቃሁት፡፡ ማዳመጫውን ነቅሎ ሲዲ ማጫወቻውን ነጥቆኝ ከመዝጋቱ በፊት የማዳምጠውን ዘፈን ሰማና፣ ክፍል ውስጥ ላሉት ተማሪዎች ነገራቸው።
“ልጆች የምትሰማውን ዘፈን ልንገራችሁ?” እያፌዘ
የክፍል ጓደኞቼ እያሾፉና እያሽሟጠጡ በደቦ “አዎ…ኦ!” አሉ።
አስተማሪያችን አየት አድርጎኝ ሳቅ አለና፣ “የፍቅር ዘፈን…የሚካኤል በላይነህን “የነገን ማወቅ ፈለኩኝ… አንቺ ነሽ የሕይወት ምርጫዬ” ይላል። ሃሃሃ…” እያፌዘ። የክፍል ጓደኞቼ ፌዙን በሳቅ አጀቡለት። እኔ ተናደድኩ። ፊቴ ልውጥውጥ አለ።
አስተማሪያችን ጎርደድ እያለ ማውራት ጀመረ “… ማንም ነገን ማወቅ የፈለገ ሰው ዛሬን በርትቶ ይማር። ማንም የሕይወት ምርጫውን መወሰን የሚፈልግ ሰው ዛሬን ጠንክሮ ያጥና። ማንም ነገን ሊቆጣጠር የፈለገ፣ ዛሬ ራሱን ይቆጣጠር። “አንቺ ነሽ የሕይወት ምርጫዬ” ያለሽ ሰው  ነገ አይደግመውም። እርግጠኛ ነኝ ዩንቨርስቲ ካልገባሽ፣ ጥሩ ሕይወት፣ የዘመነ አእምሮ… ከሌለሽ ይሄንኑ ዘፈን ለሌላ  ሴት ይጋብዛል። ልጆች ነገን የምታውቁት ሂሳብ ስታውቁ ነው።”
ወደ እኔ ዞር አለና “… ራሄል ሒሳብ ከአርባው ስንት እንዳለሽ ታውቂያለሽ… እኔ ለሰው አልናገርም… እኔና አንቺ እናውቀዋለን” በክፍል ልጆች ፊት እንዲህ መባል እንዴት እንደሚያሳፍር። አላገጠብኝ። አላገጠብኝ።
“…ይኸውልሽ ራሄል የነገን ማወቅ ከፈለግሽ አጥኚ… የምታዳምጪው ዘፈን የነገን ማወቅ ፈለግኩ አይደል የሚለው። ጎበዝ ተማሪ ሁኚ። የአንቺ ነገ የዛሬ የማትስ፣ የሒስትሪ፣ የኢኮኖሚክስ… ውጤትሽ ላይ ነው የሚወሰነው።” ተማሪዎች ሳቁ። እኔ በጣም አፈርኩ። ተናደድኩ።
“አትሳቁ! አመድ በዱቄት ይስቃል፤ እናንተስ ያው አይደላችሁ። እሷ ዛሬ ተጋልጣ ነው። የክፍል ኃላፊያችሁ መሆኔን አትርሱ። እንግዳ አደረጋችሁኝ እኮ ስትስቁ። ውጤታችሁን አላውቀውም። አንተ ነቢል፤ አሁን አንተ ሰው ላይ የምትስቅ ነህ? አሁን እንደው ረድኤት ይህ ንግግር አንቺን ያስቃል?” ሁሉም አንገታቸውን መድፋት ጀመሩ። “…ኃጢያት የሌለበት ሰው ይውገራት…” ብሎ ኩም አደረገልኝ።
“ለማንኛውም ወላጅ አምጥተሽ ነው ወክማንሽን የምትወስጂው” ብሎ ወደ ቢሮ ወሰደብኝ። በጣም ተጨነቅኩ። ለእናቴ ብነግራት አንቃ ነው የምትገድለኝ። ሲጀመር ሲዲ ማጫወቻው የሰው ነው። የአብሮ አደጌ። የሜሪ።
“ከየት አመጣሽ… ለምን ዘፈን ትሰሚያለሽ… ብለሽ ብለሽ ትምሀርት ቤት ውስጥ… ያውም ክፍል ውስጥ… ውጤትሽ እንደዚያ ተበላሽቶ…” የሚሉትን ቁጣዎች ማስተናገድ በጣም ይከብዳል። ጉልበቱም፣ ኃይሉም፣ ትዕግስቱም… የለኝም።
ስለዚህ ብቸኛው አማራጭ ፍጼን እንደ ወንድም አድርጎ መውሰድ ነበር። ስጠይቀው እሺ አለኝ። እንዴት ደስ እንዳለኝ። ወንድም ሆኖ መምጣቱ ሳይሆን ያንን ኃላፊነት መውሰዱ። ቢታወቅበት የሚፈጥረውን ችግር ለእኔ ሲል ለመቀበል መዘጋጀቱ በጣም ነው ደስ ያለኝ። የተፈጠረውን የተባልኩትን አልነገርኩትም። የነገርኩት ሳዳምጥ እንደተቀማሁ ነበር። ፍቅሩን ተሸክሜ የወጣሁትን ቀራኒዮ ለምን ልንገረው? ሳፈቅር ከዚህ በላይ ልቸነከር ነው።
(ከቃልኪዳን ሃይሉ “ክብር” የተሰኘ መፅሐፍ የተወሰደ)

በ6ኛው ሃገራዊ ምርጫ ያልተሳተፈው የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ)፤ በሚቀጥለው ወር ይካሄዳል ተብሎ በሚጠበቀው ብሔራዊ ውይይት ላይ ለመሳተፍ አራት ቅድመ ሁኔታዎችን አስቀምጧል፡፡
እነዚህም በሠሜኑ ያለው ጦርነት እንዲቆም፣ የታጠቁ ሃይሎች የውይይቱ አካል እንዲሆኑ፣ የፖለቲካ እስረኞች በሙሉ ተፈተው በውይይቱ እንዲሳተፉ እንዲሁም አወያዩ  በአለማቀፍ ደረጃ የተመሰከረለት የታመነ አካል እንዲሆን የሚሉ ናቸው። የኦፌኮ መግለጫ  እያወዛገበ ሲሆን ብዙዎችም ትችት እየሰነዘሩበት ይገኛል።
የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ በብሔራዊ ውይይቱና አወዛጋቢ በተባለው የፓርቲው መግለጫ ዙሪያ ከኦፌኮ ዋና ፀሃፊ አቶ ጥሩነህ ገምታ ጋር ተከታዩን ቃለ ምልልስ አድርጓል። እነሆ፡-


ኦፌኮ አራት ቅድመ ሁኔታዎችን ያስቀመጠበትን መግለጫውን ያወጣው በምን መነሻ ነው?
ባለፉት ሶስት ዓመታትም ሆነ ቀደም ብለው በነበሩ ዓመታት የኦሮሞ ፌደራል ኮንግረስ፣ በኢትዮጵያ ስር የሰደደና ከምንጊዜውም እየተባባሰ የመጣውን የፖለቲካ ቀውስ ለመፍታት የሚያግዝ ሁሉን አቀፍ ውይይት እንዲካሄድ ሲጠየቅ እንደነበር ይታወሳል፡፡ እነዚህን ጥያቄዎች ደግሞ ስንጠይቀ የነበረው ዝም ብሎ በመግለጫ ብቻ ሳይሆን ይመለከታቸዋል ላልናቸው ሁሉ ጉዳዩን በትኩረት እንዲይዙት ደብዳቤዎችን ጭምር በመፃፍ ነው፡፡ በተለያዩ መድረኮች ላይም ይሄን መልዕክታችንን ሳናስተላልፍ የቀረንበት ጊዜ የለም፡፡
ለምሳሌ ለጠቅላይ ሚኒስትር ፅ/ቤት፣ ለኢፌድሪ ሠብአዊ መብት ኮሚሽን፣ ለኢፌድሪ ጠቅላይ አቃቤ ህግ፣ ለብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ፅ/ቤትና ለሌሎችም ፅፈናል አሳውቀናል፡፡ ያግዙናል ይተባበሩናል ብለን ላሰብናቸው በሙሉ ደብዳቤ ስንፅፍ፣ ለመገናኘት ብዙሃን መግለጫ ስንልክ ቆይተናል፡፡ ይሄን መግለጫም ልናወጣ የቻልነው አሁን የሃገራችን የኢትዮጵያ ሁኔታ ቀውሱ በፖለቲካውም፣ በኢኮኖሚውም በሃገር ውስጥም ሆነ በዓለማቀፍ ደረጃ  ወደ መጥፎ አቅጣጫ እያመራ መሆኑን ስለተረዳን ነው፡፡ ይሄን መጥፎ መንገድ ለማስተካከል አሁንም የተወሰኑ እድሎች ስላሉ እነዚያን እድሎች ለመጠቀም የተሻለ ሁኔታ ለመፍጠር ይቻል እንደሆነ ብለን ነው ለመንግስት፣ ለገዢው ፓርቲ፣ ለመላው ኢትዮጵያውያንና ለአለማቀፍ ህብረተሰብም ይሄንን ጥሪ ያደረግነው፡፡
በመግጫው አንዱ የጠየቃችሁት ጦርነት እንዲቆም ነው። ጦርነቱ እንዴት ነው መቆም የሚችለው? ይሄን ስትሉ ፌደራል መንግስት የተናጠል ተኩስ አቁሞ እርምጃ ወስዶ እንደነበር ምን ያህል ግምት ውስጥ አስገብታችኋል?
የመንግስትን ጥረት እናስታውሳለን። ጦርነቱን በተናጥል ለማቆም ያደረገውን ጥረት እናስታውሰለን፡፡ ነገር ግን ጦርነቱ ማቆም የነበረበት ስፍራውን ለቆ አልነበረም። የተናጥል ተኩስ አቁሙ እርምጃ ቴክኒካዊ ችግር ነበረበት፡፡ ተኩስ ማቆም ይገባ የነበረው መንግስት የያዘውን ሳይለቅ የሚነጋገሩበት ሁኔታ ከተፈጠረ በኋላ ነው። ይሄን ጦርነት ለማስቆም ገለልተኛ አካልት ሁኔታውን ማመቻቸት እንዲችሉ እድሉን መስጠት ይገባል፡፡ ጦርነቱን እንዴት ማስቆም ይቻላል በሚለው ላይ ራሱ ይሄን የሚያመቻችቹ አካላት ይኖራሉ፡፡ ይሄን ምናልባት ለአለማቀፋም ሆነ ለሀገር ውስጥ ተሰሚነት ያላቸው አካላት ማሳወቅና ጥሪ ማቅረብ ይቻላል፡፡
ህወኃትና ሸኔ በሽብርተኝነት የተፈረጁ ድርጅቶች ናቸው። እናንተ በመግለጫችሁ እንደጠቀሳችሁት፣ እነዚህን ድርጅቶች እንዴት ነው የብሔራዊ ውይይት አካል የሚሆኑት?
በሀገራችን ላይ ሽብርተኛ ናቸው የተባሉትም ሆነ አሸባሪ ያሏቻው ሁለቱም ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡ ያውም የፖለቲካ ጉዳይ የለያያቸው። አንዳንድ ጊዜ ተመዝኖ መታየት ያለበት ነገር አለ፡፡ ኦፌኮ ማንም ቡድን ተደራጅቶ ብረት ይዞ እንዲንቀሳቀስ ፍላጎት የለም፡፡ ከመንግስት ውጪ ማንም ታጥቆ እንዲንቀሳቀስ አንፈልግም፡፡ ሆኖም ግን በህዝብ የተመረጠ ህጋዊ እምነት የሚጣልበት መንግስት እስከሌለ ድረስ እነዚህ አይነት እንቅስቃሴዎች የሆነ ቦታ ላይ እየፈነዱ ይነሳሉ፡፡ እነዚህን ሃይሎች ወይም ቡድኖች እንደ ምንም ብሎ ተነስቶ “አሸባሪ” ማለት ማህበረሰቦችን ወዳልተፈለገ ሁኔታ የሚመራ ይሆናል፡፡ ስለዚህ አንድ አካል አሸባሪ ተብሎ ሲፈረጅ በጣም ጥንቃቄ ይፈልጋል፡፡ ለምሳሌ ትህነግ “እኔ ብቻ ካልመራሁ ኢትዮጵያ የምትባል ሃገር መጥፋት አለባት ብሎ ይናገራል” ነው የሚባለው፡፡ ይሄ ለኔ የስልጣን ጥያቄ ነው፤ የስልጣን ሽኩቻ ነው፤ ይሄን ስልጣን ደግሞ ያገኙት እርስ በእርስ በመገለባበጥ ነው እንጂ የህዝብ ድምጽ ታክሎበት አይደለም። ሁሉም ነገር በህዝብ ድምጽ እንዲወሰን እድል ቢሰጥ፣ ዛሬ የገባንብት ቀውስ ውስጥ ባልገባን ነበር፡፡ ስለዚህ የእነዚህ ደርጅቶች በሽብር መፈረጅ እኮ አንዳንዴ ለሃገር ሰላም ተብሎ ተገምግሞ ውሳኔው ሊታጠፍ ይችላል፡፡ ታዲያ ለምንድን ነው ተገምግሞ የማይታጠፈውና የሰላም አማራጮች የማይፈተሹት? ሁላችንም ኢትዮጵያውያን አይደለንም እንዴ? እኛ ከዚህ አንጻር ጉዳዩ ተገምግሞ ሊፈተሸ ይገባዋል የሚል እምነት ነው ያለን፡፡ ይሄን የምንለው ዝም ብለን አይደለም። የእነዚህ ድርጅቶች በሽብርተኛ መፈረጅ በሃገሪቱ ላይ የተጋረጠውን አደጋ ምን ያህል ቀነሰ? የሚለውን ገምግመን ነው፡፡ ምናልባት በዚህ ጦርነት አንዱ ሃይል አሸናፊ ሆኖ ቢመጣ ወይም መንግስት ቢያሸንፍ የወደመውን መልሶ ለመገንባት ምን ያህል ጊዜ ነው የሚወስድብን? ጦርነቱ አሁን ባለበት ቢቋጭስ ምን ያህል ነው የምናተርፈው? አሁን ባለው እልህ መጋባት ምን ያህል ርቀት መጓዝ  እንችላለን? እነዚህ ጥያቄዎች እኛ እንደ አንድ የሃገሪቱ ዜጎችም ሆነ እንደ የፖለቲካ ፓርቲ በእጅጉ ያሳስበናል። ይሄን ስንል እኛ ያቀረብነው ሃሳብ ብቻ ተቀባይነት ይኑረው ብለን አይደለም። ሌላ አሳማኝ ሃሳብ ካለም ወደ መድረኩ መጥቶ መልካምና አሳማኝ ከሆነ እንቀበላለን። እኛ በዚህ መግለጫችን ከወትሮው በተለየ ተማፅኖ ነው ያቀረብነው። ስለ ሃገራችን የሰላም መንገዶች ነው ተማፅኖአችን፣ ከተሳሳተው አቅጣጫ እንመለስ፤ ከእልህ እንውጣ፤ ሰከን እንበል፤ ስለሁላችንም የጋራ አገር ኢትዮጵያ እናስብ፤ ከጥላቻ መንፈስ መውጣት እንጀምር ነው ያልነው፡፡
በመግለጫችሁ ገለልተኛ አደራዳሪ ወይም ሶስተኛ ወገን እንዲያደራድር ጠይቃችኋል። ይሄን ስትሉ ምን ዓይነት አደራዳሪ ወገን ነው ከሃገር ውስጥ ነው ከውጭ?
እኛ ይሄን ሃሳብ ያቀረብነው ለሃገራችን ሠላም በማሰብ ነው፡፡ ገለልተኛ አካል ስንልም ዝም ብሎ አይደለም፡፡ ድርድሩ እርባና ቢስ እንዳሆን በማሰብ ነው፡፡ በጦርነቱ በለው፣ ግፋበት፣ ቀጥቅጠው ሲሉ የከረሙ የሃገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች ወይም ሌሎች ተፅዕኖ ፈጣሪ ሰዎች አሉ፡፡ ድርድሩ ወይም የውይይት መድረኩ ከእነዚህ አጋፋሪነት ነፃ መሆን አለበት፡፡ በስም እገሌ እያልን መጥራት በሚያስፈልግበት ጊዜ ልንጠራ እንችላለን፡፡
አሁን በፖለቲካ ፓርቲዎች አሰላለፍ በኩል ልዩነቶች ግልጽ ሆነው ነው የሚታዩት፤ ለድርድሩም አስቸጋሪ አይሆንም፡፡ በአንድ ወገን ከገዢው ፓርቲ ጋር በአንድ ጎራ የቆሙ አሉ በሌላ በኩል በተቃራኒው የቆሙ አሉ። ስለዚህ እነዚህ ወገኖች በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠው በሃገራቸው ችግር መፍትሔ ማምጣት አለባቸው፡፡ ይሄን የአደራዳሪነት ሚና የሚወጣ ከሃገር ውስጥ የማይገኝ ከሆነም ከውጪ ማምጣት ይቻላል፡፡ ነገር ግን በሃገር ውስጥ ማግኘት ይቻላል።
እናንተ የምትፈልጉት ድርድር ውጤቱ ምን ድረስ እንዲሆን ነው? በአንድ መግለጫችሁ ምርጫ ድጋሚ እንዲካሄድ ጠይቃችኋል፡፡ ከዚህ አንጻር የምርጫውን ጉዳይ ታሳቢ ታደርጋላችሁ?
ይሄን ነገር ደጋግመን ተነጋግረናል፡፡ እኛ የተደረገው ምርጫ ዲሞክራሲያዊና አሳታፊ ነው ብለን አናምንም፡፡ መንግስት አሁን ላይ ሊኖር ይችላል፡፡ ነገር ግን በፍጹም ዲሞክራሲያዊና ህዝብ አሳታፊ ምርጫ ተካሂዶ ነው መንግስት የተመሰረተው የሚለውን ግን እኛ አንቀበለውም፡፡ ድርድሩ ድጋሚ ምርጫ እንዲካሄድ የሚደረስበት ስምምነት ሊሆን ይችላል፡፡ አሁን ያለፈው ምርጫ ሰላምን አውርዷል እንዴ?  ሰዎች ይሄን ጥያቄ ልብ ብለው ቢጠይቁ መልካም ነው፡፡
የማያስማማ ሁኔታ እስካለ ድረስ በየትም ሃገር እንደሚደረገው ድጋሚ ምርጫ ሊደረግ ይችላል፡፡ እኛ ይሄን መግለጫ ያወጣነው ለሚያመዛዝኑት ነው፡፡ አኛም እኮ ከማንም ባላነሰ ሃገራችንን የምንወድ ዜጎች ነን። እኛ ይሄን ስንል ስልጣን ለመቀማት ወይም ለመጋራት ፍላጎት ኖሮን አይደለም። የኛ አላማ ኢትዮጵያን ማዳን ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ከወደሙ ማንን ልናስተዳድር ነው? ይሄ ሁሉ ጥፋትና ውድመት እንዲቆም ነው ፍላጎታችን። ያለፈውን መንግስት እኮ የታገለው ብዙ መከራ በመቀበል ነው፡፡ ለዚያ መከራ ግን ሂሳብ እናወራርዳለን ማለት አንችልም፡፡  በይቅርታና በወይይት መሻገር አለብን፡፡

አስረኛው የኢትዮ ፖልተሪ ኤክስፖ፣ 6ኛው የአፍሪካ እንስሳት ሀብት አውደርዕይና ጉባኤ ከትላንት በስቲያ ጥቅምት 18 ቀን 2013 ዓ.ም የተከፈተ ሲሆን ዛሬ ማምሻውን እንደሚጠናቀቅ ተገለፀ። በበይነ መረብ የሚካሄደው ደግሞ እስከ ህዳር 22 ቀን 2014 ዓ.ም ይቀጥላልተብሏል።
በኢትዮጵያ ግንባር ቀደም የንግድ ትርኢቶች አዘጋጅ የሆነው ፕራና ኢቨንትስና መቀመጫውን ሱዳን ያደረገው አጋሩ ኤክስፖ ቲም በጋራ ያዘጋጁትና ቀዳሚና ሁሉን አቀፍ የዶሮና የእንስሳት ሀብት ቴክኖሎጂ ግብአትና መፍትሄዎችን ያካተተው አውደ ርዕዩ በርካታ የአገር ውስጥና የውጪ ኩባንያዎች የተሳተፉበት ሲሆን ከአንድ ቀን የዶሮ ጫጩት አቅራቢዎች ጀምሮ በርካታ የግብርናና የእንስሳት ሀብት ውጤቶች የተጎበኙበት ነው። በእለቱ እስከ ዛሬ ያልተሞከሩና አዲስ የሆኑ የግብርናና የእንስሳት ሀብት ውጤቶች ይፋ የሆኑ ሲሆን ከነዚህ መካከል በሀሮሚያ ዩኒቨርስቲ በምርምር የተገኘው የግመል ወተትን  ወደ እርጎነት የመቀየር ስራ ሲሆን የግመል ወተት እርጎም ለእይታ ቀርቦ ነበር።
ሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ ኮፐንሀገን ዩኒቨርስቲ ጋር በጥምረት በአይነቱ ለየት ያለ በግመል ወተት እርጎ፣ አይብና ፓስቸራይዝድ የግመል ወተት መስራት መቻሉን የሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ የግብርናና ሳይንስ ኮሌጅ ተመራማሪና መምህር የሆኑት አቶ ገመቹ ጣፋ ተናግረዋል። ይህንን የምርምር ውጤትም ሀሙስ እለት ስካይ ላይት ሆቴል በተከፈተው በ6ኛው የአፍሪካ የዕንስሳት ሀብት ጉባኤ፣ በ10ኛው የዶሮ ኤክስፖና በ29ኛው የኢትዮጵያ እንስሳት አርቢዎች ማህበር ዓመታዊ ጉባኤ ላይ አስተዋውቆ አድናቆትን አትርፏል። በዚህ አውደርዕይና ጉባኤ ላይ አጠቃላይ በዘርፉ ላይ የተሰማሩና ከኢትዮጵያ፣ ከጀመርመን፣ ሃንጋሪ፣ ኔዘርላንድስ፣ ስኮትላንድ እና ሱዳን የተውጣጡ ኩባንያዎች የተሳተፉ ሲሆን በአውደርዕዩ በርካታ የንግድ ትስስሮች፣ አዳዲስ የቴክኖሎጂ ሽግግሮች፣ ውይቶችና የልምድ ልውውጦችም እየተካሄዱበት ነው ተብሏል።
የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በዓለም ላይ መከሰቱን ተከትሎ በአካል የሚካሄዱ አለም አቀፍ የንግድ ትርኢቶች ተቀዛቅዘው መቆየታቸውን የገለጹት የፕራና ኢቨንትስ ማኔጅንግ ዳይሬክተር አቶ ነብዩ ለማ  ድርጅታቸው ከ4ኛው አግሮ ፉድ ፕላስት ፕሪንት ፓክ የግብርና ኤክስፖ  ጀምሮ በተከታታይ እያዘጋጃቸው ያሉት ዓለም አቀፍ የንግድ ትርኢቶች ኢኮኖሚውንና አጠቃላይ የንግድ አንቅስቃሴውን ለማነቃቃት ወሳኝ ሚና አላቸው ብለዋል።
ዛሬ ከሚጠናቀቀው 10ኛው ኢትዮ  የዶሮ ኤክስፖ፣ 6ኛው አፍሪካ የእንስሳት ሀብት ጉባኤና ከ29ኛው የኢትዮጵያ እንስሳት አርቢዎች ማህበር ዓመታዊ ጉባኤ ጎን ለጎን በዚያው በስካይ ላይት ሆቴል በኔዘር ላንድስ ልማት ድርጅት አስተባባሪነት የወተት ሀብት ልማት ላይ ያሉ ተግዳሮቶችና ጥሩ አጋጣሚዎች ላይ ትኩረቱን ያደረገ የፓናል ውይይት የተከፈተ ሲሆን በዚህ ውይይት ላይ አለም አቀፍ የዘርፉ ምሁራን፣ የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ፣ የተለያዩ የውጪና የሀገር ውስጥ ተመራማሪዎች የተሳተፉ ሲሆን፣ በወተት ሀብት ላይ ያሉ ተግዳሮቶችንና ጥሩ አጋጣሚዎችን የተመለከቱ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበዋል። በቀረቡት ጥናቶች ላይ ውይይትና የመፍትሄ ሃሳቦችን በመስጠትና ውሳኔ በማሳለፍ ጉባኤው ዛሬ አመሻሽ ላይ እንደሚጠናቀቅም ለማወቅ ተችሏል።

ወጋገን ባንክ የተመሰረተበትን 25ኛ ዓመት የብር ኢዩቤልዩ በዓል በተለያዩ ክዋኔዎች ማክበር ጀመረ። ከትናንት በስቲያ ስታዲየም ፊት ለፊት በሚገኘው ዋና መስሪያ ቤቱ ማክበር የጀመረው የብር ኢዩቤልዩ በዓል በበጎ አድራጎት ሥራ ያለፈ ሲሆን ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ግቢ ውስጥ ለሚገኘውና የልብ ህሙማን ህፃናትን በነፃ ለሚያክመው የኢትዮጵያ የልብ ህሙማን ህፃናት መርጃ ማዕከል የ1 ሚ. ብር ድጋፍ አድርጓል።
በልገሳ ስነ-ስርዓቱ ላይ የማዕከሉ የበጎ ፈቃድ አምባሳደሯ አርቲስ መሰረት መብራቴና የማዕከሉ አመራሮች ተገኝተው ድጋፉን ተቀብለዋል።
በክብረ በዓል  ስነ-ስርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የባንኩ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ አብድሽ ሁሴን ባንኩ ባለፉት 25 ዓመታት የባንክ አገልሎት ባልደረሰባቸው የሀገሪቱ አካባቢዎች በርካቶችን የባንክ አልግሎት ተጠቃሚ ከማድረጉም በላይ፣ ለሀገሪቱ የባንክ ዘርፍ እድገት የጎላ አስተዋፅኦ ስለማበርከቱም ተናግረዋል።
ባንኩ እስካሁን ለ5 ሺህ ዜጎች የስራ እድል ከመፍጠሩም በተጨማሪ ማህበራዊ ሃላፊነቱን በመወጣት፣ የልማት ጥሪዎችን በመቀበልና ፈጣን ምላሽ በመስጠት ሀገራዊ ሃላፊነቱን ሲወጣ መቆየቱን የተናገሩት አቶ አብድሽ በጠንካራ አመራሮቹና በሚከተለው የዘመነ አሰራ እዚህ ደረጃ መድረሱንም ጨምረው ገልፀዋል።
ወጋገን ባንክ ሰኔ 4 ቀን 1989 ዓ.ም በ16 ባለሃቶች በተፈረመ 60 ሚ. ብር መነሻ ካፒታልና በተከፈለ 30 ሚሊዮን ብር ተመስርቶ በአሁኑ ወቅት ከ4 ሺህ በላይ ባለ አክስዮኖች ያሉት ሲሆን እ.ኤ.አ ሰኔ 30 ቀን 2021 ዓ.ም የተከፈለ ካፒታሉ 3.2 ቢሊዮን መድረሱና አጠቃላይ ካፒታሉም  ወደ 5.5 ቢ. ማደጉም ተገልጿል። በአሁኑ ሰዓት የባንኩ አጠቃላይ ሀብት ከ40 ቢሊዮን ብር በላይ ሲሆን በመላ ሀገሪቱ 398 ቅርንጫፎች መክፈቱንና በቅርቡም በዘርፉ ተወዳደሪና ስኬታማ ሆኖ ለመቀጠል የሚያስችለውን  የአምስት ዓመት ስትራቴጅክ እቅድ ነድፎ ስራ ላይ ያዋለ ሲሆን እቅዱን ተግባራዊ ለማድረግ አዲስ መዋቅር አዘጋጅቶ ለደንበኞቹ አርኪና ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኝም በመክፈቻ ስነ-ስርዓቱ ላይ ተገልጿል። ባንኩ የተመሰረተበትን 25ኛ ዓመት ለቀጣዮቹ  8 ወራት በተለያዩ ተግባራት ማክበሩን እንደሚቀጥል የባንኩ አመራሮች ገልጸዋል።

በቀጣዮቹ  አምስት ዓመታት 25 ሺህ መኪኖችን ስራ ላይ ያሰማራል
ከሶስት ዓመታት በፊት በ7.7 ቢ ብር በጀት የተቋቋመውና የ2021 የአውሮፓ  ስሪት የሆኑ ባለ አምስት ባለ 7 እና ባለ 26 መቀመጫ የትራንስፖርት መኪኖችን በሀገራችን በመገጣጠም ስራ ላይ የተሰማራው አቤት ታክሲ፣ የመጀመሪያዎቹን መኪኖች በቅርቡ ስራ ላይ እንደሚያሰማራ አስታወቀ፡፡ ድርጅቱ ባለፈው ረቡዕ ጥቅምት 17 ቀን 2014 ዓ.ም በቤስት ዌስተርን ፕላስ ሆቴል በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ባለፉት ሶስት ዓመታት መገጣጠሚያ ፋብሪካ  በመገንባት፣ አንዳንድ ህጋዊ ሂደቶችን የመጨረስና አስፈላጊ የህግ  ሂደቶችን በመከወን ስራ ላይ መቆየቱን የገለፁት ሀላፊዎቹ በተለይ አንዱና ዋናው የመኪኖቹ መገጣጠሚያ ኮምቦልቻ ከተማ እንደመሆኑና አሁን ያለው የሀገራችን ወቅታዊ ሁኔታ ችግር እስካልፈጠረ ድረስ የመጀመሪያዎቹ መኪኖች ተገጣጥመው ስራ እንደሚጀምሩ ተናግረዋል፡፡ እነዚህ ጀርመን ጣሊያንና ራሽያ ሰራሽ የቮልስ ዋገንና የላዳ ኩባንያ የ2021  ባለ 5፣ባለ 7 እና ባለ 26 መቀመጫ ሚዲባስና ሜትር ታክሲዎች ሲሆኑ በኤሌክትሪክና በቤንዚን የሚሰሩ እንዲሁም ከአየር ንብረት ጋርም የተዋደዱ ናቸው ተብሏል፡፡
አቤት ታክሲ በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ ያለውን የትራንስፖርት ችግር ግምት ውስጥ በማስገባት ዘመናዊ የሜትር ታክሲዎችንና መለስተኛ አውቶቡሶችን በማሰማራት ችግሩን ለማቃለል የተፈጠረ ድርጅት መሆኑን የአቤት ታክሲ ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶ/ር ሙሉ ደሜ ገልጸው ድርጅቱ በቀጣዩ አምስት ዓመታት ውስጥ 60 ሺህ ሰዎችን የመቅጠር፣ ብዙ ጋራዦችን የመስራት፣ በርካታ የጥሪ ማዕከሎችን የመክፈትና 15 ሺህ ባለ 5 እና ባለ 7 እንዲሁም መቀመጫ እንዲሁም 10 ሺህ ባለ 26 መቀመጫ ሚዲ ባሶችን ስራ ላይ የማሰማራት እቅድ ተነድፎ እየተሰራ መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል፡፡
በርካታ ድርጅቶች መኪና እናስመጣለን እያሉ ገንዘብ በመሰብሰብ ቃላቸውን ሳይጠብቁ ስለ መቅረታቸውና ድርጅታቸው ከዚህ አንጻር እምነት ይጣልበት እንደሆነ ተጠይቀው ሲመልሱ “እኛ ወደ ስራው ስንገባ ትልቅ ተግዳሮት የሆነብን ይሔው የእምነት ጉዳይ” ነው ያሉት ዶ/ር ሙሉ ለወረፋ መጠበቂ ብቻ 30 ሺህ፣50 ሺህ እና 60 ሺህ ብር ከማስከፈል ውጪ ሌላ ገንዘብ እንደማይቀበሉና የመኪናውን 25 ወይም 30 በመቶ የሚያስከፍሉት መኪናውን ሲያስረክቡ ብቻ እንደሆነ ገልጸው በእምነት በኩል ችግር እደማይገጥማቸውና እስካሁንም ከ200 በላይ ሰዎች መመዝገባቸውን ተናግረዋል፡፡
የውጪ ምንዛሬ እጥረትን በተመለከተ ከጋዜጠኞች ለተነሳው ጥያቄም ስራው የተጀመረው ከውጪ አገራት በተገኘ ብድርና ብድሩም በውጪ ምንዛሬ ተገኘ በመሆኑ በምንዛሬ እጥረት የሚስተጓጎልበት ምክንያት የለም ብለዋል፡፡
አቤት ታክሲ ሀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር በአሁኑ ወቅት ጋራዞችን በግዢና በኪራይ  ቦታዎች እያስተከለ እንደሆነ የገለጹት ሀላፊዎቹ፣ታክሲዎች ስራ ሲጀምሩ የእጅ በእጅ ክፍያና በኤሌክትሮኒክስ ክፍያም አገልግሎት የሚሰጡ ሲሆን፣ የክፍያ ታሪፍን በተመለከተ አሁን ገበያ ላይ ካለው ታሪፍ የሚቀንስ ይሆናል ተብሏል። አቤት ታክሲ በዋናነት የትራንስፖርት ችግሩን ለመቅረፍ በአዲስ አበባና በአጎራባች አካባቢዎች የሚሰራ ይሁን እንጂ በቴክኖሎጂ ሽግግርና ሰፊ የስራ እድል በመፍጠር በኩል በአገር ኢኮኖሚ ላይ የሚያመጣው በጎ ተፅዕኖ ቀላል እንዳልሆነ ሀላፊዎቹ ገልጸዋል። አቤት ታክሲ በሙሉ አቅሙ ስራ ሲጀምር በቀን 50 መኪኖችን የመገጣጠም አቅም  የሚኖረው ሲሆን፣የራሽያው ስሪት ለዳ በባህር ዳር የጀርመኑ ቮልስዋገን በኮምቦልቻ እንደሚገጣጠሙ ታውቋል፡፡

Sunday, 31 October 2021 19:34

ከፌስቡክ ገጾች በጨረፍታ

የጥፋቱ ሀይል፤ ዛሬም እንደ ትናንቱ
ተቦርን በየነ

  ይህ የሆነው ከ33 ዓመታት በፊት ነው!
“እንዴት አላማጣን የመሰለ ቦታ ይለቀቃል? እንዴት እንደ ግራካሶ የመሳሰሉ ቦታዎች ይተዋሉ? በሚል ብዙ ተከራከርኩ። እንግዲህ እምቢ ካልክ ያንተ ፋንታ ነው አሉኝ። ከዛ የሶቪየት አማካሪዎችን ሎቢ አደረጉብኝ። በዚህ አይነት ትግራይ እንዲለቀቅ ሆነ።”
(የሌ/ኮ መንግሥቱ ኃ/ማርያም ትዝታዎች፤ ገፅ 272-273)
ኢህአዴግ ከላይ ከተጠቀሰው የትግራይ መለቀቅ በኋላ በሶስት አቅጣጫ ትኩረት በማድረግ፣ ኢህአዴግ ፋና በሚል ስያሜ ወደ መሀል ሀገር የሚያደርገውን ዘመቻ ጀመረ።
አቅጣጫ 1-
ከስታይሽ ተነስቶ በዋጃና ቆቦ መሀል ላሊበላን ወደ ቀኝ ትቶ፣ የወረታ-ወልዲያን መንገድ ቆርጦ ኮን በመግባት፣ ጊጣ የሚባል በረሀ አቋርጦ ወገልጤና ይገባል። ከዚያም ወደ መቅደላ፣ አጅባር፣ተንታ፣ኩታበር ድረስ በመዝለቅ ደሴን ይከባል። የዚሁ አካል የሆነው ሌላው ሀይል ለጋምቦ፣ አቅስታ፣ ገነቴ፣ መካነሰላም፣ ሳይንት፣ ጓሜዳ፣ ጫቀታ፣ ሶማ እያለ ጎጃም ድረስ ይዘልቃል። ሌላኛውም ሀይል ወደ ወረኢሉ በመገስገስ ካቤ፣ ጀማ፣ መራኛ፣ መሀልሜዳ፣ አለም ከተማ እያለ ወደ ደብረ ብርሀን ይገባል።
አቅጣጫ 2-
ወልዲያ፣ጋሸና፣ገረገራ፣ደብረዘቢጥ፣ጋይንት፣ጉና፣ክምርድንጋይ፣ጋሳኝ፣እያለ ወደ መሀል ይዘልቃል።
አቅጣጫ 3-
ቆቦ፣ መርሳ፣ ኡርጌሳ፣ ሀይቅ፣ እያለ ደሴ ድረስ ይዘልቃል።
ይህ ወታደራዊ እቅድና ስልት ኢህአዴግ ከ33 አመታት በፊት ለስልጣንና ለድል በቃሁበት ያለው ነው። ይህንንም አስመልክቶ ሜ/ጄ ታደሰ ወረደ በአንድ ወቅት የሰጡት ምስክርነት በቪዲዮ ውስጥ ተካትቷል። በተመሳሳይ አሁን ጦርነቱ እየተካሄደባቸው ያሉ የደቡብ ወሎ የተለያዩ አካባቢዎች ያላቸውን ወታደራዊ ጠቀሜታ በተመለከተ ሌ/ጄ አበባው ታደሰ የሰጡት ቃለምልልስም አብሮ ተካትቷል።
የጥፋቱ ሀይል ዛሬም እንደ ትናንቱ ተመሳሳይ በሆነ ስልት ወረራውን እያከናወነ መሆኑን ልብ ይሏል!

==========================================


ከድህረ-ጋዳፊ ሊቢያ ምን እንማር?
ጌታሁን ሔራሞ


  ሊቢያን ለ42 ዓመታት ያህል በውዴታም ይሁን በግዴታ ሲመራት የነበረው ኮሎኔል መሐመድ ጋዳፊ እ.ኤ.አ. በ2011 ዓ.ም. በሀገሪቱ ውስጥ (ቤንጋዚ) የተቀሰቀሰውን ሕዝባዊ አመፅን ተከትሎ በተከሰተው በምዕራባውያን ጣልቃ ገብነት ከሥልጣኑ ተወግዶ እስከ ወዲያኛው ማሸለቡ ይታወሳል። ከጋዳፊ መወገድ በኋላ ላለፉት አስርት ዓመታት ሊቢያ ያለችበት ሁኔታ ምን ይመስላል?
የመሐመድ ጋዳፊን መወገድ ተከትሎ ሊቢያ እስካሁን ድረስ በከፍተኛ አለመረጋጋትና ምስቅልቅል ውስጥ ነች። በእርግጥ ለምስቅልቅሉ ብዙዎቻችን በዋናነት የምንጠቅሰው የምዕራባውያኑን ጣልቃ ገብነት ነው። ይህ እውነት ቢሆንም ጣልቃ ገብነቱ የጋዳፊን ቀደምት የአመራር ስህተቶቹን በተወሰነ ደረጃ ሸፍኖለታል ማለት ይቻላል። ኮሌኔል መሐመድ ጋዳፊ የሊቢያ መሪ ብቻ ሳይሆን ተቋሟም ነበር ብንል ማጋነን አይሆንብንም። ሀገር በጠንካራ ተቋማት ላይ ሳይሆን በግለሰብ ሰብዕና ላይ ስትቀነበብ መጨረሻዋ ምን ሊሆን እንደሚችል ለማስተዋል ሊቢያ ጥሩ ምሣሌ ነች። ከአንድ አቶም ውስጥ “nucleus” ሲወገድ ኤሌክትሮኖቹ እንደ ወትሮው ሥርዓታቸውን ጠብቀው በምህዋራቸው መዞር ስለሚያቅታቸው ውጥንቅጥ ይፈጠራል። ጋዳፊ ሲወገድ ሊቢያ የሆነችው እንደዚያ ነው። የጠንካራ ተቋማት ግንባታ ለሀገር ሕልውና ቀጣይነት ዋስትና እንደሆነ የሚነገረውም ከዚሁ የተነሳ ነው።
በድህረ-ጋዳፊ በሊቢያ ውስጥ የተከሰቱ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ተዋንያን ብዛት ለቁጥር የሚታክቱ ናቸው።
እስቲ ለየብቻ በየምድባቸው እንቃኛቸው፦
1. የሀገር ውስጥ ተዋንያን (Domestic Actors)
የሊቢያ ዓመታዊ የነዳጅ ገቢዋ ወደ 25 ቢሊየን ዶላር ይጠጋል፤ አጠቃላይ ዓመታዊ ገቢዋ ደግሞ ከ150-200 ቢሊየን ዶላር ይደርሳል። የተፈጥሮ ሀብት ባለጠጋነት በረከትም ቢሆን በአግባቡ ካልተያዘ የራሱ የሆነ መርገምትም አለው። በተለይም የሀብት ክፍፍሉ ፍትሐዊ ካልሆነ ለማያባራ ግጭትና ቀውስ መንስኤ ይሆናል። ለምሣሌ በአሁኑ ወቅት ናይጄሪያ ውስጥ በሀብት ክፍፍል ምክንያት የሚፈጠሩ ግጭቶችና አለመግባባቶች ከብሔር ግጭቶች ቢበልጡ እንጂ አያንሱም። ከጋዳፊ በኋላም ሊቢያን የገጠማት ፈተና ይኸው ነበር። ቀደም ሲል ጋዳፊ እንዳሻው ሲጠቀምበትና ሲያከፋፍለው የነበረው የነዳጅ ሀብት፣ የእሱን ሞት ተከትሎ በምን አግባብ መሰራጨት እንደነበረበት መወሰን በቀላሉ ለስምምነት የሚያበቃ አልነበረም። በዚህና በሌሎች ተጨማሪ ምክንያቶች የሀገር ውስጥ ተዋንያን ስብጥር የሚከተለውን ይመስላል፦
1.1. የፖለቲካ ቡድኖች፦ በዚህ ምድብ ሥር ወደ 5 ንዑሳን ቡድኖች አሉ። እነርሱም በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚንቀሳቀሱ የጋዳፊ ዘመን የፖለቲካ ልሂቃን፣ በክልል ደረጃ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ልሂቃን፣ በክልል ደረጃ ያሉ የጎሳ አለቆች፣ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና በትምህርታቸው ላቅ ባለ ደረጃ ያሉ ምሁራንና ከጣሊያን አቻዎቻቸው ጋር ቀረቤታ ያላቸው ምሁር ሊቢያዊያን ሴቶች ናቸው።
1.2. የፀጥታ ኃይሎች ቡድን፦ በዚህኛው ምድብ ደግሞ ወደ 6 ንዑሳን ቡድኖች ይገኛሉ። ዝርዝራቸውን እንደሚከተለው በእንግሊዝኛ ላስቀምጥ፦
Remnants of the Libyan Army under Gaddafi.
Heads of Militias
Local Salafist Islamist Extermists and Terrorists
International Terrorist Groups with Libyan components, including al-qaeda in the islamic Maghreb and later, ISIS.
Petroleum Guards with Tribal ties
Criminal Ganfs, including kidnappers and smugglers.
2. ጣልቃ ገብ የውጭ ኃይሎች፦
እነዚህን ጣልቃ ገብ የውጭ ኃይሎችን በሶስት ጎራ መክፈል ይቻላል፤እነርሱም፦
ከጋዳፊ መወገድ በፊት ፈረንሳይ ፣ እንግሊዝና አሜሪካ ከፍተኛውን ሚና ከተጫወቱ በኋላ ከጋዳፊ መወገድ በኋላ በስመ-ፀጥታና ኢኮኖሚ ዕርዳታ ጣልቃ ገብነቱን ቀጥለውት ነበር።
ግብፅ፣ ሳኡዲ አረቢያ፣ ጆርዳንና የአረብ ኢሚሬትስ በአንድ በኩል በመሆን እገዛቸውን ቶቡሪክ ከተማን ማዕከል ላደረጉ ኃይሎች አደረጉ። ቆይቶ ራሺያ ይህን ምድብ ተቀላቅላለች።
እገዛቸውን ሚስራታና ትሪፖሊ ላሉ የሊቢያ ኃይሎች ካደረጉ ሀገራት ውስጥ ደግሞ ኳታር ፣ ቱርክና ሱዳን ይገኙበታል።
እንግዲህ ሊቢያ ከፈራረሰች በኋላ በሀገር ውስጥ 11 ቡድኖች፣ ከሀገር ውጭ ያሉ ደግሞ ወደ 10 ሀገራት እያመሷት ይገኛሉ። በሊቢያ ዘመቻ ወቅት ጦርነቱን በቀጥታ የመራው 44ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ፣ ከሥልጣኑ ከወረደ በኋላ፣ በውሳኔው እንደተፀፀተ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል። እንደዚያም ሆኖ ከባራክ ኦባማ ውሳኔ በስተጀርባ የነበሩ ሶስቱ ሴቶች (ሂላሪ ክሊንተን፣ ሱዛን ራይስና ሳማንታ ፓዋር) ለሊቢያ ቀውስ ተጠያቂ ስለመሆናቸው ብዙዎች የሚስማሙበት ሃቅ ነው።
እንግዲህ እኛም ሕወሓት በየጊዜው “ኢትዮጵያ ትፈራርሳለች” የሚለውን ነጠላ ዜማውን በሚያሰማን ወቅት ሊቢያ ትዝ ትለን ዘንድ ግድ ነው። ሟቹ የቀድሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ስዩም መስፍን፣ ጦርነቱ ኢትዮጵያ ውስጥ ከተካሄደ ቀጠናዊና ብዙዎችን የሚያሳትፍ ስለመሆኑ በግልፅ ተናግሮ ነበር፡፡ እንደዚህ ዓይነት ጦርነት በአንዳንዶች “The New War” ወይም “The Postmodern War” እየተባለ ይጠራል።፤ ሌሎች ደግሞ The Hybrid War ይሉታል። ያም ሆነ ይህ ኢትዮጵያ እንደ ሊቢያ ሆና ማየት የሕወሓት የጦር አበጋዞች የሰርክ ሕልማቸውና ትልማቸው ነው...አይሳካላቸውም እንጂ!
ምንጭ ፦( Origins of the Libyan Conflict and Options for its Resolution
By Jonathn M. Winer, 2019 (Free pdf download available online)

 ==========================================

ትኩረታችን  ሁሉ በህወሓት ላይ መሆን አለበት

ሃይለሚካኤል አደራ

የሽብር ቡድኑ አንደበት የሆነው ጌታቸው ረዳ፤ በአብን አመራሮች ላይ የሰነዘረው ዘለፋ ህወሓት ማእከላዊውን መንግስት ለማዳከም ትሄድበት የነበረውን ርቀት ጠቋሚ ነው። በምእራብ ኦሮሚያ፣ በመተከል እንዲሁም  በአዲስ አበባ በተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎች፣ መንግስትን የፖለቲካ ውጣሬ ውስጥ ለመክተት ያልተሞከረ ነገር አልነበረም - እንዳሰቡት ብዙም ባይሳካም። ከነዚህ የፖለቲካ ኃይሎች ውስጥ በተለይ አብን (የአማራ ፖለቲካ አክቲቪስቶች) በማዕከላዊው መንግስት ላይ እምነት እንዲያጡና እንዲያምፁ ያልተረጨ ፕሮፓንዳ አልነበረም። ግና የተሸረበውን ሴራ ሁሉ አንድም በመንግስት የውስጥ አላማ አንድነት፤ አንድም ለሀገር ተቆርቋሪ የተፎካካሪ ፖለቲካ ኃይሎች ብስለት እየከሸፈ፣ ህወሓቶችን ጭራ ሲያስበቅላቸው እየታዘብን ነው።
አሁንም ለኢትዮጵያ ሰላምና አንድነት ተቆርቋሪ የፖለቲካ ኃይሎች ትኩረት ሁሉ ህወሓት ላይ መሆን አለበት። ለብዙ ችግሮቻችን ስርአታዊና መዋቅራዊ ምንጭ የሆነው ህወሓት ከስሩ ካልተነቀለ፣ በየቦታው የሚከሰቱ ችግሮችን በዘላቂነት መፍታት አዳጋች ነው።


=================================

እውነተኛ ባለጠግነት፣ እውነተኛ ስልጣን፣ ራስን መሆን ነው
ኦሾ/Osho

አባቱ ጫማ ሰፊ የሆነው አብረሃም ሊንከን፣ የአሜሪካን ፕሬዚዳንት በሆነ ጊዜ ሀብታም ከሆኑት ሰዎች ፣የላቀ ደረጃ ካላቸው ሰዎች፣ከተከበረና ዝነኛ ሆኖ ከኖረ ቤተሰብ በመምጣታቸው የበላይነት ስሜት ያላቸውን ሰዎች በሙሉ፣ የጫማ ሰሪ ልጅ ከአናት ሆኖ ሲያዛቸው፣የሃፍረት ስሜት ተሰምቷቸው ነበር። ሊንከን ፕሬዚዳንት በመሆኑ ሁሉም መሸማቀቅ፣ ቁጣ፣ብስጭት አጠላባቸው እንጂ ደስተኛ የነበረ ሰውም የለም።
ሊንከን የመጀመሪያውን ንግግሩን ለህግ መወሰኛ በሚያቀርብበት ጊዜ አንዱ ዘላፊ የሆነ ሰው ተነስቶ፤ “ሚ/ር ሊንከን፤ ንግግርዎን ከመጀመርዎ በፊት የጫማ ሰሪ ልጅ መሆንዎን ላስታውስዎት እወዳለሁ” አለው። ያን ጊዜ ሴኔቱ በሙሉ ሳቀ። ሊንከንን ሊያሸማቅቁት ፈልገው ነበረ። ሆኖም ሊያሸንፉት አይችሉም። ነገር ግን እንዲያፍር ሊያደርጉት ይችላሉ። ይሁን እንጂ እንደ ሊንከን ያለውን የህይውት ስንክሳር አይቶ ወደ ስልጣን የመጣን ሰው እንዳያፍር ለማድረግም እጅግ አስቸጋሪ ነው። ሊንከን ሰውየውን “አሁን በህይወት የሌለውንና ጫማ ሰሪ የነበረውን አባቴን ስላስታወስከኝ እጅግ ከፍ ያለ ደስታ ይሰማኛል። የሰጠኸኝን ምክር ምን ጊዜም አልረሳውም። ጫማ ሰሪው አባቴ ባይሆን ኖሮ እንደዚህ ታላቅ ፕሬዚዳንት መሆን እንደማልችል ጠንቅቄ አውቀዋለሁ” አለ። ፍጹም ፀጥ ረጭ ያለ ሁኔታ ተፈጠረ። ሊንከን ንግግሩን ቀጠለ......
“እስከማውቀው ድረስ ለአንተም ቤተሰቦች ቢሆን አባቴ ጫማቸውን ይሰራላቸው ነበር። ትልቅ ጫማ ሰሪ ባልሆንም ገና ከልጅነቴ ጀምሮ ከአባቴ ዘንድ ጥበብን ስለተማርኩ፣ ጫማዎችህ ሲያልቁም ሆነ ችግር ሲያጋጥምህ ላስተካክልልህ እችላለሁ። እንደዚሁም አባቴ ጫማ ይሰራ ስለነበረ የሚሰፋና የሚስተካከል ካላችሁም እዚህ ሴኔት ውስጥ ላላችሁት ለማንኛችሁም ለመስራት ዝግጁ ነኝ። ሆኖም ግን አንድ ነገር እርግጠኛ ሁኑ፤ እንደ አባቴ ግን ፍጹም አይደለሁም። የእርሱ ስራ ፍፁም ወርቅ ነው” ሲል ተናገረና፣ አባቱን እያሰበ አይኖቹ በእንባ ታጠቡ።
እናም ምን ለማለት ነው፤ አንተ ከተራ ቤተሰብ የወጣህ ፕሬዚዳንትም ሁን አንደኛ የተባልክ ጫማ ሰሪ፣ ልዩነት አያመጣም። ቁም ነገሩ ያለው የምትሰራውን ስራ በፍላጎት መስራትህና ያለህን ጉልበት ሁሉ እዛ ላይ ማዋልህ ነው። እራስህን እንጂ ማንንም ሰው ለመሆን መፈለግ የለብህም። በዚህም ጊዜ ተፈጥሮ በድራማ ውስጥ የሰጠችህን ክፍል በደንብ ለመጫወት ከተፈጥሮ ጋር ትስማማለህ፤ ያን ጊዜ ንጉስም ሆነ ፕሬዚዳንት ለመሆን ራስህን አትቀይረውም።
እናም በመጨረሻም እንዲህ እላለሁ፤ ‘’እውነተኛ ባለጠግነት፤ እውነተኛ ስልጣን፣ ራስን መሆን ነው’’።


Page 9 of 566