Administrator

Administrator

      በአፍሪካ፣ ወደ ግጭት ቀጣናዎች እየተሰማራ በስነ-ምግባርና በሙያ ብቃት ስምካተረፉት መካከል የኢትዮጵያ መካከል ሃይል አንዱ እንደሆነ የገለፀው ዘኢኮኖሚስት መጽሔት፤ ኢትዮጵያና ሩዋንዳ በሰላም አስከባሪነት ጥሩ ገቢ እያገኙ መሆናቸውን ዘገበ፡፡
ቀደም ሲል ለሰላም አስከባሪነት የአውሮፓ ወታደሮች ሲሰማሩ እንደነበር መጽሔቱ አስታውሶ፤ ከ20 አመታት ወዲህ ግን በርካታ የአፍሪካ አገራት የአህጉራቱን ግጭቶች ለማብረድ የሰላም አስከባሪነት ስራዎችን እየተረከቡ ነው ብሏል፡፡
በተለይ ኢትዮጵያ እና ሩዋንዳ፤ እምነት የሚጣልባቸው ሰላም አስከባሪ ሃይል በማሰማራት መልካም ስም እንዳተረፉ መጽሔቱ ገልጿል፡፡
በርካታ ሺ ወታደሮችንና ቁሳቁሶችን፣ ለሰላም ተልዕኮ እንዲያሰማሩ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት በኩል በተደጋጋሚ የሚመረጡት ኢትዮጵያና ሩዋንዳ፤ ለሚያሰማሩት ጦር የስልጠና እና የጦር መሳሪያ ወጪያቸው በተመድ እንደሚሸፈንላቸው ዘኢኮኖሚስት ገልፆ፤ ይህም የመከላከያ ሃይላቸውን ይበልጥ ዘመናዊ ለማድረግ ያግዛቸዋል ብሏል፡፡
በዚህም በተጨማሪ ብዙዎቹ የአፍሪካ አገራት በራሳቸው ወጪ ለጦር መሳሪያ ገዢ የሚያውሉት ገንዘብ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል፡፡
የአንጐላ መንግስት ባለፈው አመት የመከላከያ በጀቱን ከ4.5 ቢሊዮን ዶላር ወደ 6 ቢ ዶላር (ወደ 120 ቢሊዮን ብር ገደማ) እንዳሳደገ መጽሔቱ ጠቅሶ፣ የናይጀሪያ መንግስትም ለአዳዲስ የጦር አውሮፕላኖች ግዢ አንድ ቢሊዮን ዶላር መመደቡን ዘግቧል፡፡
ከፍተኛ ገንዘብ ለጦር ሃይል በመመደብ በአፍሪካ ቀዳሚነቱን የያዘችው አልጀሪያየ በአመት 10 ቢ ዶላር ታወጣለች ብሏል - ዘገባው፡፡
የዛሬ 25 አመት ገደማ ሶቪዬት ህብረት የምትመራው የሶሻሊዝም አምባገነንነት ሲፈራርስ፣ በአፍሪካም በርካታ መንግስታት ከስልጣን እንደተወገዱና አንዳንዶቹም የተቃውሞ ፓርቲዎች እንዲንቀሳቀሱ የሚፈቅድ ማሻሻያ ለማድረግ እንደተገደዱ የሚታወስ ሲሆን፣ የነፃ ገበያ እና የዲሞክራሲ ስርዓት ጅምር ማሻሻያ ላይ በማተኮር ለመከላከያ ሃይል የሚያወጡት በጀት ለ15 አመታት ሳይጨምር እንደቆየ መጽሔቱ ያመለክታል፡፡
ባለፉት አስር ዓመታት ግን፣ የሃይማኖት አክራሪነትና የሽብር አደጋ፣ በዘር የሚቧደኑ ታጣቂዎችና ቡድኖች ግጭት፣ እንዲሁም የባህር ላይ ውንብድና ከፍተኛ ስጋት የሆነባቸው የአፍሪካ መንግስታት ለመከላከያ ሃይል ከፍተኛ ገንዘብ መመደብ ጀምረዋል፡፡
በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር የነበሩት ዴቪድ ሺን ለመጽሔቱ በሰጡት ገለፃ፣ አንዳንድ የአፍሪካ መንግስታት ጉድ የሚያሰኙ የጦር መሳሪያዎች እየገዙ ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ T-72 የተሰኙ ዘመናዊ ታንኮችን ከዩክሬን ማስገባት ጀምራለች፡፡ ደቡብ ሱዳን ደግሞ መቶ ታንኮችን፡፡
ሰፊ የባህር በር ያላቸው እንደ ካሜሩን እና ሞዛንቢክ፣ ሴኔጋልና ታንዛኒያ የመሳሰሉ አገራት የባህር ሃይላቸውን በጦር መሳሪያ እያፈረጠሙ መሆናቸውን ዘኢኮኖሚክስ ጠቅሶ፣ አንጐላ ደግሞ የጦር አውሮፕላኖችን የሚሸከም ተዋጊ መርከብ ለመግዛት የጀመረችው ድርድር አስገራሚ መሆኑን ጠቁሟል፡፡
የአፍሪካ አገራት ጦር፣ በስልጠናና በመሳሪያ ይበልጥ “ፕሮፌሽናል” ለመሆን እየተሻሻሉ መጥተዋል የሚለው ዘኢኮኖሚስት፣ የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገባቸው ለመከላከያ ሃይል ደህና ገንዘብ እንዲመድቡ ከማስቻሉም በተጨማሪ እንደ ኢትዮጵያና ሩዋንዳ ደግሞ በሰላም አስከባሪ ሃይል ተልእኮ አማካኝነት የማይናቅ ገቢ እያገኙ መሆናቸውን ገልጿል፡፡
እንዲያም ሆኖ የጦር መሳሪያ ግዢ በሁሉም አገራት ውጤታማ ሆኗል ማለት አይደለም፡፡ ኮንጐ ብራዛቪል ፈረንሳይ ሰራሽ ሚራዥ የጦር አውሮፕላኖችን ብትሸምትም፣ በብሔራዊ በዓላት የበረራ ትርዕት ከማሳየትና የበዓል ማድመቂያ ከመሆን ያለፈ ጥቅም አላስገኙም፡፡ ደቡብ አፍሪካም ከስዊድን 26 ተዋጊ አውሮፕላኖች ከገዛች በኋላ፣ በበጀት እጥረት ግማሾቹ ከአገልግሎት ውጭ የጋራዥ ሰለባ ሆነዋል፡፡
SU 30 አውሮፕላኖችን ከራሺያ የገዛችው ኡጋንዳ ደግሞ፤ ተስማሚ ሚሳይሎችን ስላልገዛች ዘመናዊዎቹን አውሮፕላኖች በአግባቡ ልትጠቀምባቸው አልቻለችም ብሏል መጽሔቱ፡፡   

ለአመት ያህል በበርሜር ወደ 110 ዶላር ንሮ የቆየው የድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ፤ ካለፈው ሐምሌ ወዲህ እየወረደ በያዝነው ሳምንት ከ75 ዶላር በታች የደረሰ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ የነዳጅ ዋጋ ላይ መንግስት እስካሁን ቅናሽ አላደረገም።
በአመት በአማካይ ከሰባት በመቶ በላይ እየጨመረ የመጣው የኢትዮጵያ የነዳጅ ፍጆታ፣ ባለፈው አመት 3.4 ቢሊዮን ዶላር (ከ65 ቢሊዮን ብር በላይ) ወጪ እንዳስከተለ ታውቋል። ሸቀጦች ወደ ተለያዩ አገራት በመላክ የሚገኘው የውጭ ምንዛሬ ባለፉት አራት አመታት እድገት ባለማሳየቱ አመታዊው ገቢ ከሶስት ቢሊዮን ዶላር ገደማ ብዙም ፈቅ ባለማለቱ፣ የነዳጅ ግዢን እንኳ ለመሸፈን የማይበቃ ሆኗል።
በአለም ገበያ የነዳጅ ዋጋ ባለፈው አመት በነበረበት ቢቀጥል ኖሮ፣ በቀጣዩ አመት ኢትዮጵያ ሩብ ቢሊዮን ዶላር (5 ቢሊዮን ብር) ተጨማሪ ገንዘብ ለነዳጅ ግዢ ለማውጣት መገደዷ አይቀርም ነበር። ይሁን እንጂ፣ ያለማቋረጥ እየወረደ የመጣው የነዳጅ አለማቀፍ ዋጋ በስድስት ወራት ውስጥ ሲሶ ያህል ስለቀነሰ፣ ኢትዮጵያ ለነዳጅ ግዢ የምታውለው የውጭ ምንዛሬ ዘንድሮ እንደማያሻቅብ ተገምቷል።
 እንዲያውም የድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ በበርሜል ከ80 ዶላር በታች ሆኖ ከቀጠለ፣ የአንድ ቢሊዮን ዶላር (የ20 ቢሊዮን ብር ወጪ ቅናሽ ያስገኛል፡፡) በርካታ ነዳጅ አምራች አገራትን የሚቆጣጠሩ መንግስታት በአባልነት የተካተቱበት ኦፔክ የተሰኘው ማህበር፣ ሰሞኑን በነዳጅ ዋጋ ዙሪያ የተወያየ ቢሆንም፣ ውይይታቸው በአለም የነዳጅ ዋጋ ላይ ለውጥ እንደማያስከትል ትናንት ቢቢሲ ዘግቧል። እየወረደ የመጣው የነዳጅ ዋጋ፣ የበርካታዎቹን መንግስታት ገቢ እንደሸረሸረ የገለፀው ቢቢሲ፣ ከፍተኛ የበጀት ጉድለት ያጋጥማቸዋል ብሏል። “ዋጋ እንዲያንሰራራ የነዳጅ ምርት መቀነስ አለብን” የሚል ጥያቄ ከሁለት መንግስታት በኩል እንደቀረበ ዘገባው ጠቅሶ፣ ጥያቄው በአብዛኞቹ መንግስታት ተቀባይነት ሳያገኝ መቅረቱን አመልክቷል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የነዳጅ ዋጋ መውረድ የጀመረው፣ በከፊል ከአለም ኢኮኖሚ መቀዛቀዝ ጋር በተያያዘ ምክንያት ቢሆንም፣ ዋናው ምክንያት ግን የአሜሪካ ኩባንያዎች ከፍተኛ የነዳጅ ምርትን የሚያስገኝ አዲስ ዘዴ በመፍጠራቸውና ተጨማሪ ነዳጅ ማምረት በመጀመራቸው እንደሆነ ፎርብስ መፅሔት ዘግቧል።
ከአለም ገበያ የነዳጅ ዋጋ ውጣ ውረድ ጋር፣ የኢትዮጵያ መንግስት በንግድ ሚኒስቴር በኩል በየወሩ የነዳጅ ዋጋ ተመን የሚያወጣ ሲሆን፣ ከጥቂት ጊዜያት በስተቀር አብዛኛውን ጊዜ የዋጋ ተመኑ በነበረበት እንዲቀጥል አልያም የአለም ገበያን ተከትሎ እንዲጨምር ሲወስን መቆየቱ ይታወሳል።
ባለፉት ስድስት ወራትም እንዲሁ፣ በአለም ገበያ የነዳጅ ዋጋ በፍጥነት እየወረደ ቢመጣም፣ በኢትዮጵያ ግን የችርቻሮ ዋጋ በነበረበት ደረጃ እንዲቀጥል አልያም እንዲጨምር የተደረገ ሲሆን፣ በያዝነው ወር መጨረሻ የዋጋ ተመኑ ላይ ምን አይነት ለውጥ እንደሚደረግበት ገና አልታወቀም። በተለመደው የመንግስት አሰራር፣ የዋጋ ተመን ውሳኔው በይፋ እስከሚገለፅበት እለትና ሰዓት ድረስ በሚስጥር ተጠብቆ ነው የሚቆየው።

          14ኛው የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ነገ 40ሺ ተወዳዳሪዎችን በማሳተፍ ይካሄዳል፡፡ የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫውን ከማካሄዱ በፊት ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ሰሞኑን ውድድሩን ያጀቡ የተለያዩ ዝግጅቶች ነበሩት፡፡ የመጀመርያው ባለፈው ረቡዕ በኤግዚብሽን ማእከል የተከፈተው የስፖርት ኤክስፖ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ ለመጀመርያ ጊዜ የዓለም የስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር ስራ አስኪያጅ ኮሚቴ ስብሰባም ተስተናግዷል፡፡ የዓለም የስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር የስራ አስኪያጅ ኮሚቴ ስብሰባ ትናንት እና ከትናንት በስቲያ በቀነኒሳ ሆቴል ተካሂዷል፡፡ መስተንግዶውን ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከታዋቂው የአትሌቲክስ ስፖርት ፎቶግራፈር ዢሮ ሚሹዙኪ፤ ከቀነኒሳ በቀለ እና ከአትሌቲክስ ፌደሬሽን ጋር በመተባበር አከናውነዋል፡፡ በስብሰባው ላይ ለመገኘት ወደ ኢትዮጵያ የመጡት  ከ10 የተለያዩ አገራት የተውጣጡ 29 የስፖርት ባለሙያዎች ናቸው፡፡ ከመካከላቸው ከኦስትሪያ ፤ከዩክሬን፤ ከሮማንያ ፤ከፈረንሳይ፤ ከደቡብ ኮርያ፤ ከጃፓን፤ ከእንግሊዝ ከጣሊያን ከኬንያ እና ሌሎች የዓለም ክፍሎች የመጡ ባለሙያዎች ይገኙበታል፡፡

ባለፈው ረቡእ በቀነኒሳ በቀለ ሆቴል በተዘጋጀላቸው የእራት ግብዣ ላይ የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ መስራች እና ሊቀመንበር ኃይሌ ገብረስላሴ ባሰማው ንግግር አትሌቲክስ ስፖርት ኢትዮጵያን ለዓለም ለማስተዋወቅ ሁነኛ አማራጭ እንደሆነ ትተዘባላችሁ ሲል ተናግሯል፡፡ በዚሁ የእራት ግብዣ ላይ የኢትዮጵያ የስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር ለእንግዶቹ የአገር ልብስ ስጦታ ያቀረበ ሲሆን የአትሌቲክስ ፌደሬሽን ተወካዮች በበኩላቸው ኢትዮጵያ በስፖርቱ የ65 ዓመታት ታሪክ ማሳለፏን ጠቅሰው የታላላቅ አትሌቶች መገኛ በሆነች አገር ለምታዘጋጅቱ ትልቅ ውድድራችሁ እናመሰግናለን በማለት ለታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ድጋፍ ሰጥተዋል፡፡
14ኛው የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ዛሬ በጃንሜዳ አካባቢ እስከ 4ሺ ህፃናትን በማሳተፍ በሚካሄደው ከ500 ሜትር እስከ 2000 ሜትር ውድድር ነው፡፡ ነገ ጠዋት በጃንሜዳ አካባቢ ውድድሩን የሚያስጀምሩት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ የተከበሩ አባዱላ ገመዳ ሲሆኑ የእለቱ የክብር እንግዶች እንግሊዛዊው የትራያትሎን አትሌት አሊስተር ብራውንና ኬንያዊቷ ማራቶኒስት ኤድና ኪፕላጋት አብረዋቸው ይኖራሉ፡፡ በዋናው የአትሌቶች ውድድር 40 ክለቦችን የወከሉ ከ600 በላይ አትሌቶች የሚፎካከሩ ሲሆን ፤ ለአንደኛ 40ሺ ለሁለተኛ 25 ሺ እንዲሁም ለሶስተኛ 12ሺ 500 ብር በሁለቱምፆታዎች በሽልማት ይበረከታል፡፡  ከ15 አገራት የመጡ 300 ስፖርተኞች ከ40ሺው ስፖርተኛ መካከል ሲገኙበት የ13 አገራት አምባሳደራት በኢትዮጵያን ኤርላይንስ አዋርድ ለማሸነፍ ይሽቀዳደማሉ፡፡ትናንት በሂልተን ሆቴል በተሰጠው መግለጫ ላይ  በ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫው በጋራ እየሮጥን በጋራ እንደሰት በማለት መልዕክት ያስተላለፈው ኃይሌ ገብረስላሴ፤ የውድድሩ እድገት ገና ይቀጥላል ብሏል፡፡ የክብር እንግዶች ከሆኑት አንዷ ኬንያዊቷ ኤድና ኪፕላጋት ኃይሌን ከ16 ዓመቷ ጀምራ እንደምታውቀው ገልፃ በምታደንቀው አትሌት የተዘጋጀ ውድድርን ለማስጀመር መጋበዟ ታላቅ ክብር ነው ብላለች፡፡ ኤድና ኪፕላጋት ከ12 በላይ ማራቶኖችን ያሸነፈች አትሌት ስትሆን  በሀለት የዓለም ሻምፒዮናዎች በማራቶን አከታትላ በማሸነፍ ሁለት የወር ሜዳልያዎች የተጎናፀፈች እና ዘንድሮ የለንደን ማራቶንን ለማሸነፍ የበቃች ናት፡፡ በሌላ በኩል ሌላው የክብር እንግዳ በለንደን ኦሎምፒክ በትራይትሎን ስፖርት የወርቅ ሜዳልያ ያገኘው አሊስተር ብራውንሊ በውድድሩ ለመሳተፍ መጓጓቱን ይናገራል፡፡ ትራያተሎን 500 ሜትር በዋና፤ 40 ኪሎሜትር በብስክሌት ግልቢያ እንዲሁም 10 ኪሎሜትር የጎዳና ላይ ሩጫን በማካተት የሚካሄድ ስፖርት ነው፡፡ ለታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያን በአጋርነት ሲደግፉ ከቆዩት አንዱ የሆነው የእንግሊዙ ኖቫ ኢንተርናሽናል ዲያሬክተር ዴቪድ ሊንግተን ውድድሩ ባለው ማራኪ ድባብ ከዓለማችን ምርጡ ነው ካሉ በኋላ የውድድር ተቋማቸው በመላው እንግሊዝ ካካሄዳቸው ውድድሮች አሸናፊዎቹን ይዞ በመምጣት ዘንድሮ ተሳትፎ እንደሚያደርግ ገልጿል፡፡ ኖቫ ኢንተርናሽናል አስከ 1 ሚሊዮን ተሳታፊዎች ያገኙ ውድድሮችን በማዘጋጀት በመላው ብሪታኒያ የሚንቀሳቀስ ነው፡፡ በሌላ በኩልየኢትዮጵያ ቱሪዝም ኦርጋናይዜሽን ዲያሬክተር አቶ ሰለሞን ታደሰ የሩጫ ውድድሩ የቱሪዝም እንቅስቃሴን የሚያቀላጥፍ ብለው ሲያደንቁ፤ የውድድሩ ስፖንሰር የሆነው የኢትዮጵዩ ንግድ ባንክ ሃላፊ አቶ ኤፍሬም መኩርያ የኢትዮጵያ ትልቁ ባንክ የአፍሪካን ታላቅ ውድድር ስፖንሰር በማድረጉ ደስተኛ ነው ብለዋል፡፡

ጣሊያናዊው ጂያኔ ሜርሎ የዓለም የስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር (AIPS) የወቅቱ ፕሬዝዳንት ናቸው፡፡ በታዋቂው የጣሊያን የስፖርት ሚዲያ ላ ጋዜታ ዴሎ ስፖርት ላይ በተለይ የአትሌቲክስ ስፖርት ዘጋቢ ሆነው ሲሰሩ 10 ኦሎምፒኮችን በቀጥታ በመዘገብ ከፍተኛ ልምድ ያካበቱ ባለሙያ ናቸው፡፡ ከስፖርት አድማስ የሚከተለውን አጭር ቃለምልልስ አድርገዋል፡፡
በኢትዮጵያ መሰብሰባችሁ  ምን ጥቅም አለው?
በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ የመጀመርያው ስብሰባችን ማድረጋችን ወደፊት ብዙ እድሎችን ይፈጥራል፡፡ እያገኘን ያለው መልካም መስተንግዶ ደግሞ ወደፊትም ሌሎች ዓለም አቀፍ ስብሰባዎች እና ዝግጅቶችን ለማካሄድ የሚያነሳሳን ይሆናል፡፡ ከምናገኘው ልምድ ተነስተን ብዙ ተግባራት የምናከናውን ይመስለኛል፡፡ እኔ ወደ ኢትዮጵያ ስመጣ ለ3ኛ ጊዜ ቢሆንም ሌሎቹ የዓለም የስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር ስራ አስኪያጅ ኮሚቴ አባላት ግን የመጀመርያቸው ነው፡፡ በቆይታቸው የሚኖራቸውን ልምድ በመንተራስ ብዙ የጉብኝት እድሎችን ለኢትዮጵያ የሚፈጠሩ ይመስለኛል፡፡ ኢትዮጵያ በአትሌቲክስ ስፖርት ታላላቅ አትሌቶችን በማፍራት በመላው ዓለም ገንናለች፡፡  ይህ ስኬት  ደግሞ በዓለም ስፖርት ጋዜጠኞች ትኩረት ውስጥ አስገብቷታል፡፡ በአትሌቶቻችሁ ስኬት ነው  ወደ ኢትዮጵያ ብሎም ወደ አፍሪካ ለመጀመርያ ጊዜ በመምጣት የዓለም አቀፍ ማህበራችንን የስራ አስኪያጅ ኮሚቴ ስብሰባ ለማድረግ የበቃነው፡፡ ኃይሌና ቀነኒሳ እንዲሁም ሌሎች የኢትዮጵያ አትሌቶች ምስጋና ይገባቸዋል፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ደጋግመን እንመጣለን፡፡
ስብሰባችሁ የሚያተኩርባቸው አጀንዳዎች ምንድናቸው ?
ዓለም አቀፉ ማህበራችን ከተመሰረተ 90ኛ ዓመቱን ዘንድሮ ያስቆጥራል፡፡ በስብሰባችን ይህን እናስባለን፡፡ በዋናነት የያዝናቸው አጀንዳዎች ግን በስፖርት ሚዲያው አሰራር ላይ ያተኩራሉ፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተፈጠሩ ያሉ መሰናክሎች እና ችግሮችን በዝርዝር በመመልከት የመፍትሄ ሃሳቦችን እያቀረብን ውይይት እናደርጋለን፡፡ የስፖርት ሚዲያዎች በነፃነት መስራት የሚችሉባቸውን ሁኔታዎች እንዳስሳለን፡፡ በመረጃ ምንጮቻቸው የስፖርት ሚዲያዎች ማድረግ የሚገባቸውን ከለላ  የሚያጠናክሩባቸውን አቋሞች ለመቅረፅ እናስባለን፡፡ በሌላ በኩል አዲስ በጀመርነው እና ተተኪ የስፖርት ሚዲያ ትውልዶችን ለመፍጠር ያግዘናል ያልነው የወጣት ስፖርት ጋዜጠኞች የማስተር ስልጠና ፕሮግራም አወቃቀር ዙርያ ያሉ ጅምር ተግባራትን እንገመግማለን፡፡
የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ውድድርን ማህበራችሁ እንዴት ይመለከተዋል?
ካለኝ ልምድ በመነሳት የምናገረው ውድድሩ ዓለም አቀፍ ደረጃ እንዳለው ነው፡፡ የአትሌቲክስ ስፖርት ባህል በሁሉም ኢትዮጵያዊ የእለት እለት ህይወት እንዲቆራኝ ያደረገ ነው፡፡ የሙያ ባልደረቦቼ ከስብሰባው ጎን ለጎን የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ውድድርን ለመከታተል እቅድ አላቸው፡፡ ውድድሩን በጥልቀት ገምግመው ወደየአገሮቻቸው ሲመለሱ በርካታ የዘገባ ሽፋን ይሰጡታል፡፡ ይህ ደግሞ የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያን ዝና እያሳደገ ይቀጥላል፡፡ በውድድሩ አገሪቱ እያገኘች ያለው ትኩረት ሌላው ስኬት ይመስለኛል፡፡
ስለ አበበ ቢቂላ ሲናገሩ ሰምቻለሁ፤  ከኢትዮጵያ አትሌቶች ጋር እንዴት ተዋወቁ?
በ1960 እኤአ ላይ በሮም ኦሎምፒክ ላይ ገና 13 ዓመቴ ብቻ ነበር፡፡ አበበ ቢቂላ የማራቶን ውድድር ሲያሸንፍ ተመለከትኩ፡፡ በጣም ለህይወቴ አስፈላጊውን መነቃቃት ነበር ያገኘሁት፡፡በአትሌቲክስ ስፖርተኛነት ቆርጬ የተነሳሁበት ታሪክም ሆነ፡፡  አፍሪካዊያን ሯጮች በዓለም የስፖርት መድረክ ያን ያህል ጥንካሬ አልነበራቸውም፡፡ በአበበ ቢቂላ ብቃት ግን ብዙ ተነሳሱ፡፡ እኔ በዚህ ታላቅ ኢትዮጵያዊ አትሌት  ተማርኬ  ከስፖርቱ ጋር በፍቅር ወደቅኩ፡፡ ጀግንነቱም በተተኪ የኢትዮጵያ አትሌቶች ሲደጋገም ለማየት ስታደል ደግሞ ተደሰትኩ፡፡ ከአበበ ቢቂላ በኋላ ምሩፅ ይፍጠር እና መሃመድ ከድርንም ለማወቅ ችያለሁ፡፡ በ80ዎቹ በሚላኖ ከተማ ውስጥ ከሃምሳ ሺ በላይ ስፖርተኞችን የሚያሳትፍ ውድድር ላይ ተሳትፈው ስለነበር ነው፡፡ ከእነሱ በኋላ እኔም ወደ ስፖርት ጋዜጠኝነቱ ስገባ እነ ኃይሌን ተዋወቅኩ፡፡ ከዚያም ቀነኒሳንም ጥሩነሽንም በደንብ የማውቃቸው እና የምከታተላቸው  ሆኜ አሳልፍያለሁ፡፡
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ለምስራቅ አፍሪካ አትሌቶች በረጅም ርቀት የአትሌቲክስ ውድድሮች መወዳደርያዎች ጠፍተዋል፡፡ በውጤታማነት ከሌሎች የዓለም አገራት ልቀው መሄዳቸው ምክንያት ይመስለኛል፡፡ ይሁንና በውድድሮች መመናመን የሚቆረቆር አለመኖሩ ሁኔታውን አባብሶታል፡፡ የዓለም ስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር ይህ ሁኔታ አሳስቦት ለምን አልተከራከረም?
 የዓለም ስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር በዚሁ የረጅም ርቀት የአትከሌቲክስ ውድድሮች መመናመን ዙርያ አስተያየት ለመስጠት ቢችልም ተፅእኖ በማሳደር ምንም አይነት ነገር ማስቀየር ግን  አይችልም፡፡ ይህን ሁኔታ ማረም ማስተካከል የሚችሉት አትሌቲክሱን የሚያስተዳድሩ አለማቀፍ ተቋማት ብቻ ናቸው፡፡ ዋናው ችግር እንደሚመስለኝ የምስራቅ አፍሪካ አትሌቶች ከጥራት ይልቅ በብዛት ተሳትፏቸው የዓለምን ውድድሮች ማጨናነቅ መጀመራቸው ነው፡፡ ዛሬ ከዚሁ የአፍሪካ ክፍል እንደ ኃይሌ፤ ቀነኒሳ፤ ፖል ቴርጋት ልዩ የስፖርት ስብዓና ያላቸው ስፖርተኞች የሉም፡፡ ብዛት ብቻ ነው ያለው፡፡ ለምሳሌ በ10ሺ ሜትር ውድድር ድሮ አንድ ሁለት ኢትዮጵያዊ እና ኬንያዊ ቢኖሩ ነበር፡፡ ሌሎች አገራትም በተመጣጣኝ ኮታ  ከአውሮፓ፤ ከኤስያ፤ ከአሜሪካና ሌሎች የዓለም ክፍሎች ይወከሉ ነበር፡፡ ዛሬ ግን አስራምናምን ኬንያዊ እና ኢትዮጵያዊ በየውድድሩ መስፈርቱን አሟልቶ እየገባ የሌሎች አለም ክፍሎችን ፍላጎት እያመነመነው መጣ፡፡ ውድድር አዘጋጆችም ከእነስፖንሰሮቻቸው በዚህ ደስተኛ አይደሉም፡፡ ዓለም አቀፍ ሚዲያውም ስለ ሁለቱ የምስራቅ አፍሪካ አገራት አትሌቶች በመዘገብ ተሰላችቷል፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች ለውድድሮች መጥፋት መንስኤ ይመስለኛል፡፡
ከኢትዮጵያ አትሌቶች ብቃት እና ስብዕና  ምን ያስደንቅዎታል?
በጣም ደስ የሚሉኝ እነዚህ ስፖርተኞች ከደሃ አገር ወጥተው በዓለም አቀፍ የውድድር መድረክ የሚገኑበት ጀግንነታቸው ነው፡፡ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ውድድሮች በአትሌቶቹ መካከል በተለይ በፊት የምታዘባቸው የቡድን ስራዎች እና አንድነታቸው ይማርከኛል፡፡ በኢትዮጵያ የአትሌቲክስ ስፖርት ከህዝቦች ጋር ባህል ጋር የተሳሰረበት ሁኔታም ያስደንቀኛል፡፡
በኢትዮጵያ ላሉ የስፖርት ጋዜጠኞች ምን ምክር ይሰጣሉ?
ወደ ዓለም አቀፍ መድረክ የሚያወጣቸውን የትምህርትዐ የቋንቋ እና የልምድ ብቃት ያሳድጉ ነው የምለው፡፡ በተለይ በእንግሊዘኛ ቋንቋ ያላቸውን ችሎታ ማሳደግ አለባቸው፡፡ ለታላላቅ አትሌቶች የመረጃ ምንጭ መሆን ያለባቸው የራሳቸው አገር ሚዲያዎች እንጂ የሌላ አገር ተቋማት መሆን የለባቸውም፡፡ በአገር ውስጥ ያሉ የስፖርት እንቅስቃሴዎችን በተለይ ኢትዮጵያ የምትታወቅበትን የአትሌቲክስ ስፖርት በተለያየ ሁኔታ ለመላው ዓለም የሚያሰራጩበትን አሰራር ማሳደግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ የሚያገኙትን እድል ተጠቅመው በመስራትም ከሌሎች አገራት ባለሙያዎች ጋር ወቅቱን በጠበቀ መረጃ እና ተፅእኖ ፈጣሪነት እንዲሰሩ እመክራለሁ፡፡




* የግዳጅ ጋብቻ፣ ከሚገባው በላይ ማሰራት፣ ህገወጥ የሰዎች ዝውውር፣ ህጻናትን ጦር ሜዳ ማሰለፍ---
* በህንድ 14.3 ሚሊዮን ሰዎች የዘመናዊ ባርነት ሰለባዎች ናቸው
በአሁኑ ወቅት በአለማችን የተለያዩ አገራት 36 ሚሊዮን ያህል ሰዎች ዘመናዊ የባርነት ህይወት እየገፉ እንደሚገኙ ዎክ ፍሪ ፋውንዴሽን የተባለ ተቀማጭነቱን በአውስትራሊያ ያደረገ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ተቋም ሪፖርት ጠቅሶ ዘ ጋርዲያን ዘገበ፡፡
ተቋሙ ለሁለተኛ ጊዜ ሰሞኑን ይፋ ያደረገው አመታዊ የባርነት መጠን አመልካች ሪፖርት እንደሚለው፣ በአለማችን የዘመናዊ ባርነት ሰለቦች ቁጥር ከአምናው በ23 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡
ጥናቱ ከተደረገባቸው 167 አገራት ቀዳሚውን ስፍራ የምትይዘው ህንድ ስትሆን፣ በአገሪቱ 14.3 ሚሊዮን ዜጎች የባርነት ኑሮን በመግፋት ላይ ይገኛሉ፡፡
ቻይና በ3.24 ሚሊዮን፣ ፓኪስታን በ2 ሚሊዮን፣ ኡዝቤኪስታን በ1.2፣ ሩስያ በ1 ሚሊዮን፤ ከሁለተኛ እስከ አምስተኛ ያሉትን ደረጃዎች ይዘዋል፡፡ ከአጠቃላይ ህዝባቸው ብዙ በባርነት ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች ያሉባቸው አገራትን በተመለከተ ሪፖርቱ እንዳለው፣ ሞሪታንያ በ4 በመቶ፣ ኡዝቤኪስታን በ3.9 በመቶ፣ ሃይቲ በ2.3 በመቶ፣ ኳታር በ1.3 በመቶ እና ህንድ በ1.1 በመቶ ከአንድ እስከ አምስት ያሉትን ደረጃዎች ይዘዋል፡፡ዘመናዊ ባርነት በሁሉም አገራት ውስጥ እንዳለ የተቋሙ መስራችና ሊቀመንበር አንድሪው ፎሬስት መግለጻቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ ዘመናዊ ባርነትን ለማጥፋት ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ረገድ፣ አውስትራሊያ፣ ኦስትሪያ፣ ጆርጂያ፣ አየርላንድ፣ ኔዘርላንድ፣ ኖርዌይ፣ ስዊድን፣ ስዊዘርላንድ፣ እንግሊዝና አሜሪካ ቀዳሚነቱን እንደሚይዙ ገልጧል፡፡ እንደ ሪፖርቱ አገላለጽ፤ የሚገባቸውን ክፍያ ሳያገኙ ከሚገባቸው በላይ የስራ ጫና ያለባቸውና የተለያዩ ጥቃቶች የሚደርሱባቸው ህጻናት፣ ሴቶችና በተለያዩ የዕድሜ ክልሎች የሚገኙ ሰዎች፣ ከዘመናዊ ባርነት ሰለባዎች  ይመደባሉ፡፡ ሰዎች ነጻነታቸውን ተጠቅመው የፈለጉትን እንዳይሰሩ በመጨቆን፣ የገቢ ማስገኛ አድርጎ መጠቀም፣ የባርነት አንዱ ትርጓሜ ነው ያለው ሪፖርቱ፤ የግዳጅ ጋብቻ፣ ከሚገባው በላይ ማሰራት፣ ህገወጥ የሰዎች ዝውውር፣ ህጻናትን ወደ ጦር ሜዳ ማሰለፍና የመሳሰሉት የባርነት ተግባራት በስፋት እየተፈጸሙ እንደሚገኙ አመልክቷል፡፡


  • ዓምና  በተፈጸሙ 10 ሺህ ያህል ጥቃቶች፣ ከ18 ሺህ በላይ ሰዎች ሞተዋል
  • 6ሺህ 362 ሰዎች የሞቱባት ኢራቅ ቀዳሚነቱን ይዛለች

        በአለማችን የሚፈጸሙ የሽብር ጥቃቶች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ በመምጣት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱንና ባለፈው የፈረንጆች አመት ብቻ ከ18 ሺህ በላይ የተለያዩ አገራት ዜጎች ለህልፈት መዳረጋቸውን ስካይ ኒውስ ዘገበ፡፡
የአለማቀፉን የሽብርተኝነት አመልካች ጥናት ሪፖርት ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ እ.ኤ.አ በ2013 ብቻ በአለማችን የተለያዩ ክፍሎች 10ሺህ ያህል የሽብር ጥቃቶች የተፈጸሙ ሲሆን፣ በጥቃቶቹ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከአንድ አመት በፊት ከነበረው  በእጥፍ ያህል መጨመሩንም ጠቁሟል፡፡በአመቱ በሽብር ጥቃቶች በርካታ ዜጎች የሞቱባት ቀዳሚ የዓለማችን አገር ኢራቅ ስትሆን፣ በአገሪቱ 6ሺህ 362 ያህል ሰዎች ከሽብር ጥቃቶች ጋር በተያያዘ ለሞት ተዳርገዋል፡፡
ችግሩ በከፍተኛ ሁኔታ የተስፋፋበቸው ሌሎች የአለማችን አገራት አፍጋኒስታን፣ ፓኪስታን፣ ሶሪያና ናይጀሪያ ሲሆኑ፣ አይኤስ፣ አልቃይዳ፣ ታሊባንና ቦኮሃራም ደግሞ በአገራቱ አብዛኞቹን ጥቃቶች የፈጸሙ ቡድኖች ናቸው ተብሏል፡፡ የሽብርተኝነት እንቅስቃሴዎች በሚታዩባቸው 162 የአለማችን አገራት ላይ የሰራውን አለማቀፍ የሽብርተኝነት አመልካች ጥናት ለሁለተኛ ጊዜ ይፋ ያደረገው፣ ኢንስቲቲዩት ፎር ኢኮኖሚክስ ኤንድ ፒስ የተባለ አለማቀፍ ተቋም ነው፡፡

“ፒካሶ የሚባለው ዋና የጥፋት ዲያቆን ነው፡፡ ከስዕል ጥበብ ውስጥ ምክንያታዊነትን ሙሉ ለሙሉ አውጥቶ አብስትራክት አርት ፈጠርኩ አለ፡፡ ደግሞም ፈጥሯል፡፡ በድህረ-ዘመናዊነት ማፍረስ መፍጠር በመሆኑ ማለት ነው፡፡ ባለ ሦስት አውታሩን ስዕል ወደ ሁለት አውታር፣ ሲሻው ደግሞ አውታር አልባ አድርጐ አቀረበ፡፡”


ስለ ምን ላውራ? ስለ ምንም ነገር ባወራ ከዘመኑ መንፈስ ውጭ አይሆንም አይደል? አንድ ወዳጄ ዘመኑ “ድህረ ዘመናዊነት” (Post modernism) ነው ብሎኛል፤ እኔም አምኜዋለሁ፡፡ አምኜም ለአማኝ አውርቼ አሳምኛለሁ፡፡ እንግዲህ ይህ የሀሳብ ወዳጅ እንደነገረኝ ከሆነ፣ መጀመሪያ የአዳም እና የሄዋንን ታሪክ ከስር መሰረቱ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ የአዳም እና የሄዋን ታሪክ በጣም አጭር ነው፡፡ አንድ መስመር ነው እንዲያውም፡፡ ሄዋን አንገት ናት፤ አዳም ደግሞ እራስ ነው፡፡ ይሄ አጭር ታሪክ ጥንታዊ ነው፡፡ ጥንታዊ እና ሃይማኖታዊ፡፡
ዘመናዊው የሰው ልጅ ታሪክም እንደ ጥንታዊው በጣም አጭር ነው፡፡ ጥንታዊው አዳም እራስ፣ ሄዋን አንገት ነበረች ብያለሁ፡፡ ዘመናዊው ላይ ምንም አዲስ ነገር አልተከሰተም፡፡ ጥንታዊው አዳም ዘመናዊ ሲሆን ጭንቅላቱን መጠቀም ጀመረ፡፡ ጭንቅላቱን መጠቀም ሲጀምር ልቡን መጠቀም ያቆማል፡፡ ልቡን መጠቀም ሲጀምር ደግሞ ተገላቢጦሽ፡፡ የዘመናዊነት አስተሳሰብ በአዳም ጭንቅላት መስራት እና አለመስራት ሁልጊዜ ብቅ የሚል እና ተመልሶ እልም የሚል ነገር ነው፡፡ ልክ እንደ ሀገራችን የመብራት አቅርቦት ብዬ መመሰል አይጠበቅብኝም፡፡ በግሪኮቹ ዘመን ጭንቅላቱን መጠቀም ጀምሮ ነበር ይባላል አዳም፡፡ በኋላ የክርስትና አብዮት ሲቀጣጠል ጭንቅላቱ ተመልሶ ጠፋበት፡፡ ጠፍቶበት ቆይቶ ወደ አስራ ስድስተኛው ክፍለ ዘመን አካባቢ መልሶ መብራት መጣለት፡፡ ጭንቅላቱን እና እጁን አጣምሮ ሳይንስን አዋለደ፡፡ ማሽን ሰራ፣ በጭንቅላቱ ውስጥ ብቻ የማይቀር መብራት በጐጆው አበራ፡፡ ፋብሪካው፣ መድሃኒቱ፣ መንገዱ፣ ባቡሩ…የዚህ ፈጠራው ማስታወሻ ናቸው፡፡
ይሄ ከላይ የጻፍኩት ሁሉ ወዳጄ ያወራልኝን መሆኑ አይዘንጋ!
ድህረ - ዘመናዊነትስ? አልኩት፡፡
ድህረ - ዘመናዊነት ልብንም ሆነ ጭንቅላትን በአንድ ላይ ለማጣት የሚያደርገው ሙከራ ነው አለኝ፡፡ ምሳሌ እንዲሰጠኝ ጠየቅሁት፡፡
ምሳሌውን ከፈላስፎቹ ነው የጀመረልኝ…ሳይንስ በተወለደበት ግርግም ውስጥ ሰበአ ሰገሎቹ ስጦታ ይዘው ለሰው ልጅ መጡ፡፡ ይዘው የመጡት እጅ መንሻ ግን ከርቤ፣ ወርቅ እና እጣን አልነበረም፤ አለኝ፡፡
የሰበአ ሰገሎቹ ስም ሰረን ኪርከርጋርድ፣ ማርቲን ሀይደርጋር እና ፍሬድሪክ ኒቼ ናቸው፡፡ ይዘው የመጡት ስጦታ…ሳይንስ ወይም የልጅነት ልምሻን የሚከላከል ክትባት አልነበረም፡፡ አቀጭጮ የሚገድለውን መጽሐፍ ነው ያበረከቱለት፡፡ ሳይንስ ቀጭጮም አልሞተም፤በልጅነት ልምሻ ተጠቅቶ በዱላ እየተደገፈ በህይወት መኖረ ቀጠለ፡፡
ከሳይንስ ጋር የጓደኛዬ ትረካም ቀጥሏል፡፡
ሳይንስ የሚኖረው ምክንያታዊነት እስካለ ድረስ ነው፡፡ ምክንያታዊነት በጭንቅላት ነው የሚሰራው፡፡ ምክንያታዊነት በሃይማኖት ወይንም በልብ ወይንም በስሜት አይሰራም፡፡ ድህረ - ዘመናዊነት በማይሰራው እንዲሰራ፣ በሚሰራው እንዳይሰራ የማድረጊያ ፍልስፍና ነው፡፡ አንገትን ጭንቅላት፣ ጭንቅላትን አንገት ሲደረጉ ነው ወይ የማይሰራው እንዲሰራ የሚሆነው፡፡ አልኩት፡፡ እኔ የሴቶችን ከጓዳ ወደ መስክ መውጣት ለማለት ፈልጌ ነው፡፡
ሴት እና ወንድ ሁለቱም ጭንቅላት፣ ሁለቱም አንገት አላቸው፤ልዩነታቸው በአንገት እና በጭንቅላት ሊመሰል አይችልም፡፡ ሴቶች የወንዶችን የቀድሞ ሃላፊነት መጋራታቸው እንዲያውም ምክንያታዊ-- ሳይንሳዊ ነው፡፡ እኔ የምልህ ሌላ ነው፡፡ እኔ የምልህ በደንብ እንዲገባህ ወደ ጥበባቱ ብናተኩር ይሻላል፡፡
ቅድም የጠቀስኳቸው ሰብዓ ሰገሎች፣ ፈላስፎች ወይንም ጠንቋዮች ምክንያታዊነትን የሚያጣጥል ፍልስፍና በምክንያታዊ መሳይ አቀራረብ፣በተወለደው ልጅ ደም ውስጥ ረጭተው ዞር አሉ፡፡ የተረጨው መርዝ መስራት የጀመረው…እንደ ሁልጊዜውም መጀመሪያ በተጨባጭ የታየው ጥበበኞቹ ላይ ነው፡፡ የመጀመሪያዎቹ የድህረ-ዘመናዊነት ምረዛ ሰለባዎች፣ በሃያኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ ነው ወደ አለም መድረክ የመጡት፡፡ ስማቸውን ታውቃቸዋለህ? እነ ፒካሶ፣ እነ ገርትሩድ እስታይን፣ እነ ጄምስ ጆይስ…ምናምን ናቸው፡፡ ይዘን መጣን የሚሉት የጥበብ ዘይቤ…ኪውቢዝም፣ ዳይዝም…ስትሪም ኦፍ ኮንሸስነስ…ጂኒ ቁልቋል…ጂኒ ጃንካ… ፒካሶ የሚባለው ዋና የጥፋት ዲያቆን ነው፡፡ ከስዕል ጥበብ ውስጥ ምክንያታዊነትን ሙሉ ለሙሉ አውጥቶ አብስትራክት አርት ፈጠርኩ አለ፡፡ ደግሞም ፈጥሯል፡፡ በድህረ-ዘመናዊነት ማፍረስ መፍጠር በመሆኑ ማለት ነው፡፡ ባለ ሦስት አውታሩን ስዕል ወደ ሁለት አውታር፣ ሲሻው ደግሞ አውታር አልባ አድርጐ አቀረበ፡፡
ለስነጽሑፉ ደግሞ ጄምስ ጆይስ አለልህ፡፡ የሰውን የውስጥ የሃሳብ አፈሳሰስ አሳያለሁ ብሎ በእውን ህልም የሚያዩ ገፀ ባህሪዎች ቀረፀ፡፡ መጽሐፉን እስካሁን በቅጡ የሚረዱት ጥቂት ሰዎች ናቸው፡፡ በኋላ የመጨረሻ ስራውን አወጣ፡፡ Finnigans wake ይባላል፡፡ በዓለም ላይ የመጨረሻው ከባድ የልብ ወለድ ድርሰት መሆኑ ይነገርለታል፡፡ ከባድ የተባለው ከደራሲው በስተቀር ለማንም በግልፅ ስለማይገባ ነው፡፡ የራሱን አዲስ ቃላት እየፈጠረ፣ አንድ አረፍተ ነገር የሚያክሉ ቃላትን ያለ ክፍተት አንድ ላይ እያጠባበቀ … መግለፅ ሳይሆን መደበቅን ለአንባቢ አበረከተ፡፡ … ይኸው አበርክቶቱ የድርሰት ቁንጮ መሆኑ ይሰበካል … የድርሰትን ምክኒያታዊነት ሙሉ በሙሉ ኢ - ምክኒያታዊ ማድረግ ነው ግቡ፡፡ ግቡ ተሳክቶለታል፡፡
 ቅድም ልብን በጭንቅላት ስለ መቀየር አንስቼብሀለሁ፡፡ ድህረ ዘመናዊነት ልብም ጭንቅላትም አይደለም፡፡ ሁለቱንም አፈራርሶ፣ ከፍርስራሹ ከሁለቱም ውጭ የሆነ ነገር መፍጠር ነው፡፡ ልብን እምነት፣ ጭንቅላትን እውነታ ልንላቸው እንችላለን፡፡ ድህረ-ዘመናዊነት ጭንቅላትን እና ልብን እንደ መሳሪያ ተጠቅሞ .. መሳሪያውን መልሶ ለማፍረስ የሚደረግ የትዕቢት እንቅስቃሴ ነው … አለኝ እና ከንዴቱ መለስ አለ፡፡ እናም ቀጠለ፡፡
ወደ ሀገራችን ስትመጣም ጥበቡ በዚሁ ደዌ የተመታ ነው፡፡ ግን ደዌው ምክንያታዊነትን አይገድለውም፡፡ ምክንያቱም አበሻ ምክንያታዊነት በጭንቅላቱ ውስጥ ወይንም በልቡ ውስጥ የሚገኝ ባለመሆኑ ነው፡፡  የአበሻ ምክንያታዊነት የሚገኘው በባህሉ ውስጥ ነው፡፡ ባህል ደግሞ መቼ እንደተሰቀለ የማይታወቅ  ርቆ ያለ ማስጠንቀቂያ ነው፡፡ ማስጠንቀቂያው የፈለገ ርቆ ቢሰቀልም … ግልፅ ሆኖ ባይነበብም… መስራቱ ግን አይቀርም፡፡ ማስጠንቀቂያውን “የአበሻ ጨዋነት” ብለን ብንጠራው የራቀ ስያሜ አይመስለኝም፡፡ ማስጠንቀቂያው ከላይ “የአበሻ ጨዋነት” … ዝቅ ሲል ደግሞ በደቃቅ ፅሁፍ “የአበሻ ነብራዊ ዥንጉርጉርነት” ነው፡፡
ዥንጉርጉርነቱን በምሳሌ ላሳይህ፡-
በአንድ ቀለሙ ድህነትን የሚያከብር ህዝብ ነው… በሌላ በኩል ባለፀጋነትንም ይመኛል፡፡ በአንድ በኩል ክርስቲያን ነው-- በሌላ በኩል አዶ ከብሬ አለበት፡፡ ክታብ እና መስቀሉን አቻችሎ የሚኖር ህዝብ ነው፡፡ ሰም እና ወርቅ አለው፡፡ በጨዋነት ሰምና ወርቁን እየደበቀ እና እየገለፀ አንድ ላይ ያስተናግዳል፡፡ ቋንቋው  ራሱ የሰም እና የወርቅን ባህርይ በውስጡ ያቀፈ ነው፡፡ ስለዚህ የአበሻ ምክንያታዊነት የፈረንጆቹን አይደለም፡፡ የአበሻ ሃይማኖት የአውሮፓዊያኖቹን አይመስልም፡፡ ከውጭ መስሎ ቢገኝ እንኳን ከውስጥ ግን እነሱን አይደለም፡፡ አበሻ የራሱ አንገት እና የራሱ ጭንቅላት ባለቤት ነው፡፡ በአንገቱ አዟዙሮ ቢያይም በጭንቅላቱ አዟዙሮ ቢያስብም … ከዥንጉርጉርነቱ እና ከጨዋነቱ አያፈነግጥም፡፡
እና ምን እያልከኝ ነው? አልኩት፡፡
አበሻ ዘንድ ሞደርኒዝምም ሆነ ፖስት ሞደርኒዝም አይገባም፡፡ ሳይንስን በግርግሙ ስላላዋለደ … ሳይንስን አይነጠቅም፡፡ ድሮውኑ ያልነበረ ነገር አይጠፋም፡፡ ሳይንስን ያዋለዱት ሳይንስን ሲያከብሩ አብሮ ያከብራል፡፡ የሳይንስን ምክንያታዊነት ሲያዋርዱ ያዋርዳል፤ ግን የሚያዋርደው እነሱን ለማገዝ እንጂ ራሱን ለማርከስ አይደለም፡፡ የሚያከብረውም ሆነ የሚያደንቀው በሰም ደረጃ ያለውን ነው፡፡ ወርቁን ግን አያስነካም፡፡ አበሻ ዥንጉርጉርነት እና ጨዋነት ባህሉ ነው፡፡ ሳይንስም ሃይማኖትም ለሱ እነዚህ ናቸው፡፡
ስለዚህ … ሰለሞን ደሬሳ ቅርፃዊነት ብሎ ሲነሳ .. ወይንም አንቶኔ ኢንስታሌሽን አርት ብሎ ብቅ ሲል … ከራሱ ጥፋት ወይንም ልማት ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌላቸው … በደመነብሱም ቢሆን አውቆ ነው፡፡
የአበሻ ጨዋነት እና ዥንጉርጉርነት በድህረ-ዘመናዊነት አይነካም፡፡ አበሻ ሞደርን ከመሆኑ አስቀድሞ post modern ሊሆን ይችላል፡፡ አለም የያዘውን ፋሽን ይይዛል፡፡ ስለ ማንነት ቀውስ ሲነሳ፣ የቀውሱን መገለጫዎች ተላብሶ ወየው! ይላል፡፡ የጨዋነቱ አካል ነው ይኼም፡፡
አበሻ እንደ ፒካሶ ሙሉ ለሙሉ ሊያምፅ አይችልም፡፡ ምክንያታዊነት ላይ ለማመፅ መጀመሪያ ሳይንሳዊ ማንነት ያስፈልጋል፡፡ ሳይንሳዊ ማንነት ያላቸው፣ ሳይንሳዊ ፈጠራዎች ሲልኩለት ይቀበላል፡፡ ሳይንሳዊ ማንነትን ለማጥፋት የሚቀሰቅሱትንም ይተባበራል፡፡ ዘመናዊ ልብወለድን እና ዘመናዊ ትያትርን ይመለከታል፡፡ እነሱ በሰሩት መልክ ይሰራል፡፡ ባፈረሱት መንገድ ያፈርሳል፡፡ ወርቁን ግን አያስነካም፡፡ ዘመናዊ ልብወለዱን እያጻፈ፣ ባህላዊውን ተረቱን በዥንጉርጉር ልቡ የወርቅ ማህደር ውስጥ ይዞ ይቀጥላል፡፡ ባህላዊው ተረትና ምሳሌ በዘመናዊነት ውስጥ አልተፈጠረም፡፡ በድህረ-ዘመናዊነት ውስጥም አይለወጥም፡፡ ባህላዊው አበሻ ከፍልስፍና ውስጥ የተፈጠረም አይደለም፡፡ የፈረንጆቹ ምክንያታዊነት በጥቂት ፈላስፎች የተፈጠረ ነው፡፡ በመሆኑም በጥቂት ኢ-ምክኒያታዊ ፈላስፎች ተመልሶ ሊናድ ይችላል፡
ከአበሻ ጨዋነት ጋር የሚጋጭ ፍልስፍና ይዞ የሚመጣ ወዮለት፡፡ በአበሻ ዥንጉርጉርነት ጉራማይሌ ባህሉ ውስጥ የሚጋጨው ፍልስፍና፣ ከነብሩ ዥንጉርጉሮች መሀል አንዱ ይሆናል፡፡ የአበሻ ጨዋነት አንድ ኢላማ ስላልሆነ አንድ ተኳሽ አይመታውም፡፡ በነብር ቆዳ ላይ ያሉትን ነጠብጣቦች በአንድ ተኩስ መምታት አይቻልም፡፡ የነብሩ ህልውና ያለው በነጠብጣቦቹ ላይ ነው፡፡
ስለዚህ---አንተ ምክንያታዊነትን ነው የምትደግፈው ወይንስ ፖስት ሞደርኒዝምን? ቁርጡን ጠየቅሁት፡፡ የምደግፈው አበሻነቴን ነው፡፡ በአበሻነቴ ውስጥ ሁለቱም የሉም፡፡ ግን እንደ ፋሽን ፖስት ሞደርኒዝም ወደ እብደት ያጋደለ ሲመስለኝ ወደ ምክንያታዊነት እመለሳለሁ፡፡ ምክንያታዊነት አላፈናፍን ብሎ ችክ ሲልብኝ ደግሞ ወደ ሀይደርጋር ወይንም ወደ ኤግዚዝቴንሻሊዝም እመለሳለሁ፡፡ ኤግዚዝቴንሻሊዝም ራሱ ፖስት ሞደርኒዝም የገራው ኮሚኒዝም መሆኑን አትዘንጋ---፡፡ ብሎ ንግግሩን ቋጨልኝ፡፡ ግን የነገረኝ ሁሉ ራሴ መስማት የምፈልገውን በመሆኑ፣ ከሱ ወርጄ ንግግሩን የራሴ አደረግኋቸው፡፡  

          ሰባተኛ ክፍል እያለን እንዲህ ሆነ፡፡ አንድ አርብ የክፍል ቤስት ጓደኛዬ የሆነው ልጅ ደብተሬ ውስጥ ደብዳቤ እንዳስቀመጠና ቅዳሜንና እሁድን አስቤበት ሰኞ ምላሽ እንደሚጠብቅ ነገረኝ፡፡ ልጁ ባይጽፍልኝም እንደምንዋደድ ራሳችንም እናውቃለን፡፡ አብረን እናጠናለን፣ አብረን እንረብሻለን፣ አብረን እንጫወታለን፡፡
ክፍል ውስጥ የራሱ መቀመጫ ቢኖረውም አብዛኛውን ጊዜ የኔ ወንበር ላይ ነበር የሚገኘው፡፡ ቤቶቼ ያውቁታል፤ ይወዱታል፡፡ ከዚህ ያለፈ ምን ማድረግ እንደሚቻል አላውቅም፡፡ ብቻ ለደብዳቤው መልስ ይፈልጋል፡፡ በመርህ ደረጃ 12 ሳልጨርስ ጓደኛ ብሎ ነገር በጊዜው ለኔ ስህተት ነው፡፡ በዚህ ምክንያት መልሴ ሳይጠይቀኝ የታወቀ ቢሆንም የተጨነኩት ከዚህ በኋላ ምን አይነት ግንኙነት ሊኖረን ነው ብዬ ነበር፡፡ እንደፈራሁት መፈራራትና መተፋፈር ጀመርን፡፡ ቀስ እያልንም ተራራቅን፡፡
በዚህ መሃል ማን ቢቀበለኝ ጥሩ ነው….ይሄንን ሁኔታ ያየና የተከታተለ ሌላ የክፍል ልጅ ለአባቱ እንዲህ አላቸው “…ፌቨን ጐበዝ ተማሪ ትወዳለች፡፡
ወደፊት እሷን ማግባት ስለምፈልግ ካሁኑ በትምህርቴ መጐበዝ እፈልጋለሁ፡፡ ለዚህ ደግሞ እሷ የማጠናከሪያ ትምህርት የምትማርበት ቦታ አስመዘግበኝ፡፡”
ይሄን እንግዲህ አባቱ ለአባቴ “ልጅህ ልጄን ጐበዝ ልታደርግልኝ ነው” ብለው ነግረውት የሰማሁት ነው፡፡ እሱ ግን ለኔ ምንም አላለኝም ነበር፡፡ ልጅት ሆዬ ሁኔታውን መከታተል ጀመርኩ፡፡ በርግጥም ልጁ የክፍል ውስጥ ተሳትፎው ጨመረ፡፡ የቤት ስራዎችን ጠንቅቆ ይሰራ ጀመር፡፡ አባቱ የልጄ የወደፊት ሚስት ብለው ይሁን ወይ እንደ ባለውለታቸው ቆጥረውኝ ብቻ…ባገኙኝ ጊዜ ሁሉ ፍሽክ ፍሽክሽክ ብለው ሰላምታ ይሰጡኛል፡፡ ስመውም አይጠግቡኝም ነበር፡፡ ታዲያ እኔ በማየው ነገር እየገረመኝ፣ ዮሲንም እየወደድኩት፣ አባቱ እየተደሰቱ፣ ዮሲ ዓላማውን ለማሳካት መንገዱን እየጠበጠበ ባለበት ወቅት የኢትዮ - ኤርትራ ግጭት በመጀመሩ ተለያየን፡፡
ዮሲን አደንቀዋለሁ፡፡ ሚስት ሁኚኝ አላለኝም፤ ራሱን ለብቁ ባልነት ማዘጋጀት ግን ጀምሯል፡፡ እንዲህ አይነቱን ማን አይወድም? እኔ እወዳለሁ!
ዮሲ ከሄደ በኋላ ልቤን ያስደነገጠ ሳይገኝ አመት አለፈ፡፡
ኛ ክፍል ላይ እንደገና ተረታሁ፡፡ ልጁ እንደሚወደኝ ነገረኝ፤ እንደምወደው ነገርኩት፡፡  በጣም አስብለት ነበር፡፡ ትዝ ከሚሉኝና ተቃውሜውም የማላውቀው ነገር ደብተሬ ላይ እየተፈላሰፈ የሚጽፈው ነገር ነው፡፡ ሁለት ገጽ፣ ሶስት ገጽ ይጽፋል (ስለ ፍቅር፣ ስለ ይቅርታ፣ ስለ ጓደኝነት…) አልገነጥለውም፡፡ ግን ያንን ደብተሬን ለማንም አልሰጥም፡፡ ቲቸርም የደብተር ማርክ ሲሞሉ አስተውለውት አያውቁም፡፡ የ9ኛ ክፍል የCivic ደብተሬ፣ የሱን ጥራዝ ነጠቅ ሃሳቦች እንደያዘ ማን አወቀ? ከኔና ከራሱ በቀር፡፡
ዮሲ አሁን የት እንዳለ አላውቅም፡፡
ከዚህኛው ልጅ ጋር እንኳን ከብዙ አመት በኋላ ፌስቡክ ላይ ተገናኝተን አወራን፤ መለያየታችንን ኮነንን፡፡ የአንድ የቆንጅዬ ልጅ አባት ሆኖ አገኘሁት፡፡ እኔ፤ ሆዴዴዴዴን እስኪያመኝ ቀናሁ፡፡ ሚስቱ በጣም ፉንጋ ናት አይደል? “Say” አዎ በናታችሁ!
*   *   *
የመጀመሪያ ደብዳቤ የደረሰኝ 7ኛ ክፍል ሆኜ ነው፡፡ የፃፈልኝ ልጅ በጣም ቀጭን ሲሆን ስሙ ብርሃኑ ይባላል፤ ግን ሉሲ ብሬ የሚል ቅጽል ስም ነበረው፡፡ ዳር ዳሩን በአበባ ባጌጠ ወረቀት ላይ አስቂኝ ፅሁፍ ሰጠኝ “እንደ እንጀራ ለምትርቢኝ እንደ ውሀ ለምትጠሚኝ ውድ ፍቅሬ…” ይልና በመጠማትና በመራብ ዙሪያ ትንተና ይሰጣል፡፡ ከጓደኞቼ ጋር በመሆን ወር ሙሉ ሳቅንበት፡፡ እሱም ሰኔ 30 ጥርሴን እንደሚያስለቅመኝ ዝቶ ተለያየን (እኔ በጣም ወፍራም ስለነበርኩ ማች አናደርግም ብዬ ነው)
ሁለተኛ ደግሞ እዛው 7ኛ ክፍል ሁለተኛው አጋማሽ ላይ ነው የደረሰኝ፡፡ ልጁ ሰፈር፣ ትምህርት ቤት ያስቸገረ ነውጠኛ፤ በጉልበቱ የሚያምን አይነት ነበር፡፡ ደብዳቤው የተፃፈው እንደነገሩ ነው “እወድሻለሁ ስትወጪ ጠብቂኝ” ይላል፡፡ አላመነታሁም፤ ጠበቅሁት፡፡ ምን እንዳወራን ባላስታውስም ሰፈር ድረስ ሸኘኝ፡፡ የቤታችን በር ጋ ስደርስ “ጓደኛዬ ነሽ፤ ከዚህ በኋላ ከሌላ ሰው ጋር እንዳላይሽ” ኧረ ማስጠንቀቂያ! ቤት ደግሞ ጓደኛ መያዜ ከተሰማ እገደላለሁ “እኔ ጓደኛህ መሆን አልፈልግም” አልኩት፡፡ “አስቢበት” ብሎ ጥሎኝ ሄደ፡፡ ጓደኛዬን ሳማክራት፣ ቤተሰቦቼ ሳያውቁ ጓደኛ እንዳደርገው አስማማችኝ፡፡ በበነጋታው በር ላይ ጠብቆ “እእ..” አለኝ፤ ትንሽ አመንትቼ “እሺ” አልኩት፡፡ እናም በክብር ያቺን አመት ጨረስኩ፡፡ ሰኔ ሰላሳም ሳልመታ አለፈ ግን ማርያምን ምንም አላደረግንም፡፡
ተወዳጅ መኮንን
*   *   *
ስምንተኛ ክፍል ሆኜ ነው፡፡ የሰፈሬ ልጅ ደብዳቤ ፅፎ ላከልኝ፡፡ ደብዳቤውን ያመጣው ትንሽ ልጅ ነበር፡፡ በወቅቱ ለወንድ ልጅ ካለኝ ፍርሃት የተነሳ ደፋር ነበርኩ፡፡ ፍርሃት በጣም ደፋር ያደርጋል ያሉት ለካ ወደው አይደለም፡፡
የተላከው ልጅ ከቤት አስጠርቶኝ “ለእሷ ብቻ ስጥ” ተብሏል መሰለኝ፣ ደብቆ ሰጠኝ፡፡ ገለጥ አድርጌ ሳየው ገባኝ፡፡ የልብ ቅርፅ ተስሎበታል፡፡ በአረንጓዴና በቀይ እስክርቢቶ በሚያምር የእጅ ፅሁፍ ተጽፏል፡፡ (የልጁ እጅ ፅሁፍ ማማር እራሱ ግርም ይለኛል) የወረቀቱ አስተጣጠፍ እንኳን በጣም ልዩ ነበር፡፡
በአንዴ ከድንጋጤም ድፍረትም ከየት እንደመጣ እንጃ! (አትንኩኝ ነው ነገሩ) ወረቀቱን አጣጥፌ ብጭቅ ብጭቅ አደረግሁትና፤ (ውይ ክፋቴ)
“ሲርብህ ብላው ብላሃለች በለህ” ብዬ መልሼ ሰጠሁት፡፡
አቤት…ከዚያ ወዲያ አኔም ሳላናግረው፣ እሱም ቀና ብሎ ሳያየኝ፣ ከዚያ ሰፈር ወጣሁ፡፡ በጣም ትልልቆች ሆነን እንኳን አላናግረውም ነበር፡፡
ሁለተኛውና የመጨረሻው 9ኛ ክፍል ስማር በዕረፍት ሰአት ደብተሬ ውስጥ ያገኘሁት፣ ማንነቱንና ምንነቱን ያልገለፀ ሰው በሙንጭርጭር ጽሑፍ የፃፈልኝ ደብዳቤ ነው፡፡ “መነን ት/ቤት መታጠፊያው ላይ ጠብቂኝ” የሚል ቀጠሮ ሁሉ ነበረው፡፡ (ማን እንደሆነ ሳይታወቅ!) ወይ ጊዜ፤ እንዴት ይሮጣል!
ሮሚ
*   *   *
የደረጃ…የስፔሻል ክላስ ተማሪ…ማፍቀር መፈቀር የማይታሰቡ ነገሮች…መሸ ነጋ ደብተሬ ላይ የምቸከል…ስለ ፍቅር ሲወራ “እኔ አላማ አለኝ፤ እንዲህ አይነት ነገር አላደርግም” ምናምን የምል… አካባጅ ነበርኩ፡፡ ከመምህሮቼ ጋር ጥብቅ ግንኙነት ስላለኝ ተማሪዎችም ደፍረው አይቀርቡኝም፡፡ እና ደብዳቤ ምናምን አልተጻፈልኝም (አሁን ቆጨኝ!)
ሁሌም አመሻሽ ላይ ከእህቶቼ ጋር የሃይማኖት ትምህርት ለመከታተል ቤተክርስቲያን እንሄዳለን፡፡ ትምህርት አልቆ ማታ ወደ ቤት ስንመለስ፣ ከመድሃኒያለም እስከ ሃያ ሁለት ጫፍ ዎክ እናደርጋለን፡፡ (በዚያ መስመር ብዙ ሰው ዎክ ያደርጋል) አንዳንዴ የማንገዛውን ቡቲክ ገብተን እንጠይቃለን… ሃሃሃ…
እዚያ አካባቢ የቀበሌ መዝናኛ ፑል ቤት አለ፡፡ ሁሌ በር ላይ የሚቆሙ ፍንዳታዎች ነበሩ፡፡ አንደኛው ላይ አይኔ አረፈና ተከየፍኩበት፡፡ ታዲያ የማየው ከሩቁ ነው፡፡ ቁመናውን እንጂ ጠጋ ብዬ ፊቱን አይቼው አላውቅም፡፡ እሱም በጨለማ ነው፡፡ በመንገድ መብራት ድብዝዝ ብሎ ነበር የሚታየኝ፡፡ ቆንጅዬ፤ ጠይም እንደሆነ ያስታውቃል፡፡ ዛሬ ፊቱን ማየት አለብኝ ብዬ ከሩቅ አስቤ እሄድና ልክ መቶ ሜትር ሲቀኝ አንገቴን አቀረቅራለሁ፡፡ ድፍረቴ ኦና ይሆናል፡፡ መቼም አጠገቡ ቆሜ እንደማላወራው አውቀዋለሁ፡፡ በሩቁ ብቻዬን ነበር ያፈቀርኩት፡፡ ለእህቶቼም እንኳን አልነገርኩም፡፡ አንድ ቀን ብቻዬን ወደ ቤተክርስትያን ስሄድ ከኋላዬ ደረሰብኝ፡፡ ነፍሴ ተርበተበተች፡፡
“ሃይ… ሰላም ነው” አለኝ ስሜን ጠርቶ፡፡ ስሜን መጥራቱ ቢያስደስተኝም አንደበቴ ተለጉሞ ዝም አልኩት፡፡
“ከኋላ በጣም ታምሪያለሽ” አለ፤ ቀጠለና፡፡ አስቀያሚ ብሎ የሰደበኝ መሰለኝ፡፡ ተናደድኩበት፡፡
“እንትን ጋራጅን ታውቂዋለሽ? እዛ ነው ምሰራው” አለኝ
“እግር ኳስ ተጫዋችና ጋራጅ ሰራተኛ እወዳለሁ” አልኩት፡፡ በኋላ “ለምን አልኩት” ብዬ ፀፀተኝ፡፡
“እንትናንስ ታውቂዋለሽ?” (ባለጋራጁን ማለቱ ነው)
“እንጃ ብዙ አላውቀውም” አልኩት፡፡
“ስልክ ቁጥሯን ተቀበልልኝ ብሎ ነው”
“ይሄ ትልቁ ሰውዬ?” አልኩት ድንገት በመገረም፡፡
“ኧረ ትልቅ አይደለም፤ አንቺ ስለማታውቂው ነው፡፡ ስልክ ከሌላት እኔ እገዛላታለሁ ብሏል…” ለድለላ ስራ እንደመጣ ሲገባኝ ኩምሽሽ አልኩ፡፡ አግኝቼ ያጣሁት መሰለኝ፡፡
አጋጣሚ እየጠበቀ ያናግረኝ ጀመር፡፡ እኔም እሱን ለመሳብ ይረዱኛል ያልኳቸውን ፍልስፍናዎች አዘንብበት ጀመር፡፡ ስለ ሰውየው ትተን፣ ስለ ራሳችን ማውራት ጀመርን፡፡
“እነንትና እኮ ዱሩዬ ናቸው፤ ለምን ከነሱ ጋ ትቆማለህ?” እለዋለሁ፡፡ ቀስ እያለ ያስረዳኛል፡፡
“አስፓልቱ ሰው ይበዛበታል… ውስጥ ለውስጥ እንሂድ” እያልን ከህዝብ ተገንጥለን ለብቻችን መሄድ ጀመርን፡፡ ቀጥሎ አንገትና ወገብ ተቃቅፎ መሄድ መጣ፡፡
እያለ …እያለ…እያለ… ሃሃሃ… ይበቃችኋል፡፡
*   *   *
የመጀመሪያው የፍቅር ደብዳቤ የደረሰኝ 5ኛ ክፍል እያለሁ ነበር፡፡ ስሙን የማልጠቅሰው፤ በረባሽነቱና ተጫዋችነቱ በጣም የሚታወቅ የክፍሌ ልጅ ነበር፡፡ በጣምም ደፋርና ጆሊ ነገር ነበር፡፡ የክፍላችን ወንዶች በሙሉ ጓደኞቹ ነበሩ፡፡ ትምህርት ቤታችን ውስጥ እሱን የማያውቅ ተማሪ አልነበረም፡፡ እናቱም አስተማሪያችን ነበሩ (ለድፍረትና ረብሻው አግዞት ይሆናል)
የሆነ ሆኖ አንድ ቀን “የቤት ሥራ አልሰራሁምና ደብተርሽን አውሽኝ” ይለኝና ደብተሬን ሰጠሁት፡፡ እኔ ደግሞ አታምኑኝም ይሆናል እንጂ ያኔ በጣም አይናፋርና ዝምተኛ ነበርኩ፡፡ ደብተሬን ከትምህርት ስንለቀቅ ግቢው በር ላይ ጠብቆ መለሰልኝ፡፡ እቤት ደርሼ ደብተሬን ስገልጥ፣ ዳር ዳሩ ላይ በአበባና ቢራቢሮዎች ያጌጠ፣ ሽቶ ሽቶ የሚሸት ወረቀት አገኘሁኝ፡፡ ከልጁ የተፃፈልኝ የ“እወድሻለሁ” ደብዳቤ ነበር፡፡ የተፃፉትን እያንዳንዱን ቃላት አላስታውሳቸውም፡፡ አንብቤው ለእህቶቼዋ አስነበብኩት፤ ለጓደኛዬም፡፡
ጓደኛዬ፤ “ታዲያ ምን ብለሽ ልትመልሽለት ነው? እሽ እንዳትይው፣ ረባሽ ነው፤ ከፈለግሽው ግን ይሁን” አለችኝ፡፡ መመለስ እንደሚገባኝ እራሱ አልገባኝም ነበርና ዘጋሁት፡፡ ልጁ በሶስተኛ ወይ በአራተኛ ቀን የተቀመጥኩበት ዴስክ ጋ መጥቶ “ምነው ደብዳቤዬን ሳትመልሽልኝ?” ብሎ ሲጠይቀኝ “አልፈልግም፤ ይኸው ደብዳቤህ” ብዬ ሰጠሁት፡፡ “እምቢ አልሽ አይደል፣ ቆይ ብቻ ሰኔ 30 ላግኝሽ” ብሎ ፎከረብኝ፡፡ እንዳለውም ሰኔ 30 ከጓደኞቹ ጋር መንገድ ላይ ጠብቆ እየፎከረ ሊመታኝ ሲያስፈራራኝ፣ እህቶቼና ጓደኛዬ ደፈር ብለው፣ ተለማምጠውና አባብለው ከመደብደብ አስጥለውኝ ነበር እላችኋለሁ፡፡
ሜሪ ፈለቀ



Saturday, 22 November 2014 12:39

የፀሃፍት ጥግ

 ጥሩ ተራኪ ግሩም የማስታወስ ችሎታ ያለውና ሌሎች የላቸውም ብሎ ተስፋ የሚያደርግ ነው፡፡
አይርቪን ኤስ. ኮብ  (አሜሪካዊ ተረበኛና ጋዜጠኛ)
* በስኬት ሱስ ሙሉ በሙሉ ተይዣለሁ፡፡
ስቲንግ
(እንግሊዛዊ የሮክ አቀንቃኝና የዘፈን ግጥም ፀሐፊ)
* ከምሠራው ነገር ጀርባ ሁሉ የዓይን ጥቅሻ አለ፡፡
ማዶና (የፖፕ ሙዚቃ አቀንቃኝና የፊልም ተዋናይ)
* ግጥም የተመጠነ ንግግር እንደሆነው ሁሉ ዳንስም የተመተረ እርምጃ ነው፡፡
ፍራንሲስ ቤከን (እንግሊዛዊ ፈላስፋ፣ በሳል ፖለቲከኛና የህግ ባለሙያ)
* ሙዚቃ ማቀናበር ከመጪው ዘመን ጋር በፍቅር እንደመቅለጥ ነው፡፡
ሉካስ ፎስ  (ትውልደ ጀርመን፣ አሜሪካዊ  አቀበናባሪ፤  ኮንዳክተርና ፒያኖ ቀማሪ)
* ጎበዝ አቀናባሪ አይኮርጅም፤ ይመነትፋል እንጂ፡፡
አይጎር ስትራቪንስኩ
(ትውልደ ሩሲያ አሜሪካዊ አቀናባሪ)
* ሁሉም ሰው መማር ከመጀመሩ በፊት አርቲስት ነው፡፡ ሁሉም ሰው መማር ካቆመ በኋላ አርቲስት ይሆናል፡፡
ታባን ሎ ሎዮንግ (ሱዳናዊ ገጣሚና ደራሲ)
* እግዚአብሔር ምድርን ፈጠረ በሰባተኛው ቀን ግን እረፍት ላይ ሳለ፣ ድንገት ተነሳና እንዲህ አለ፡፡
ሁሉንም ነገር ፈጥሬ ረሳሁ ሁለት ነገሮች  የፒካሶን አይንና እጆች
ራፌል አልበርቲ  (ስፔናዊ ገጣሚ)
* ታላላቅ የሙዚቃ ቀማሪዎች ታላላቅ መንታፊዎች እንደነበሩም አንርሳ፡፡ ከማንም ከየትም ሳይሉ ዘርፈዋል፡፡
ሰፓብሎ ካሳልስ (ሙዚቃ ቀማሪ)
* እብደትን በጥቂቱ መሞከር ሰዓሊን
አይጎዳውም፡፡
አዩ ክዌይ አርማህ (ጋናዊ ፀሐፊና የትምህርት ሊቅ)
* የእኔ ስራ የማውቀውን መሳል አይደለም፤ የማየውን እንጂ፡፡
ጄ.ኤም.ደብሊው ተርነር (እንግሊዛዊ ሰዓሊ)

በቅርቡ ለገበያ የዋለው የዕውቁ ድምፃዊ አብነት አጎናፍር “አስታራቂ” የተሰኘ አልበም ከትላንት በስቲያ ዝነኛ አርቲስቶች፣ ተጋባዥ እንግዶች፣ የአርቲስቱ ወዳጆችና አድናቂዎች በተገኙበት ተመረቀ፡፡ የአብነት “አስታራቂ” ሦስተኛው አልበሙ ሲሆን 14 ዘፈኖች ተካተውበታል፡፡