Administrator

Administrator

መተግበሪያው ሙስናንና ህገወጥ አሰራርን ይቀርፋል ተብሏል


ቲዮስ ቴክኒሎጂ ከአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮና ከአሽከርካሪና ተሽከርካሪ ፍቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን ጋር በመተባበር፣ የተሽከርካሪ ቴክኒክ ምርመራን የሚያከናውን አዲስ ቴክኖሎጂ ሥራ ሊጀምር ነው፡፡
ተቋማቱ ለ5 ዓመት በጋራ ሊሰሩ የሚችሉበትን ሥምምነት ባለፈው ማክሰኞ መጋቢት 26 ቀን 2015 ዓ.ም በሳፋየር አዲስ ሆቴል ተፈራርመዋል፡፡
በፊርማ ስነ ሥርዓቱ ላይ የአሽከርካሪና ተሽከርካሪ ፍቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን ዋና ሥራ አሥኪያጅ አቶ ፍሬው ደምሴ፣ የትዮስ ቴክኖሎጂ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ቴዎድሮስ አጥናፉ የተሽከርካሪ ምርመራ ተቋማት ፕሬዚዳንት አቶ ሀይሉ ገረሱና ሌሎችም እንግዶች ተገኝተዋል፡፡የተሽከርካሪ ቴክኒክ ምርመራን ቴክኖሎጂው በውጭና በሀገር ውስጥ ከፍተኛ ባለሙያዎች የበለፀገ ዘመናዊ መተግበሪያ ሲሆን የተሽከርካሪ ቴክኒክ ምርመራ ከሶስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት ጠብቆ ውጤቱን ለማእከላዊ የመረጃ ቋት እንደሚያቀብል የቲዮስ ቴክኖሎጂ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ቴዎድሮሰ አጥናፉ አብራርተው ይህም ሙሰኝነትንና ህገ-ወጥ አሰራርን በእጅጉ ከመቀነስ አኳያ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ብለዋል፡፡
እስከ ዛሬ የነበረውን የቴክኒክ ምርመራ ክፍተት አስመልክተው ማብራሪያ የሰጡት የተሽከርካሪና አሽከርካሪ ፈቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ፍሬው ደምሴ፤ ተሽከርካሪዎች በምርመራ ተቋማት የምርመራ ሂደት ሳያልፉ፣ ህገ ወጥ ቦሎ እየወሰዱ መሆናቸውን አብራርተው፣ ይህም ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱና የተሽከርካሪ ምርመራ ድርጅቶች ሊያገኙ የሚገባቸውን ገቢ በማሳጣት በተቋማቱም በአገር ኢኮኖሚም ላይ አሉታዊ ተፅእኖ ሲፈጥሩ ቆይተዋል ብለዋል፡፡ ኃላፊው አክለውም፤ ደህንነታቸውና ጤንነታቸው ያልተረጋገጡ ተሽከርካሪዎች በስራ ላይ እየዋሉ በህይወትና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጥፋት እየደረሰ መሆኑን ጠቁመው፤ ቲዮስ ቴክኖሎጂ ያበለፀገው አዲስ  መተግበሪያ እነዚህን ሁሉ ተግዳሮቶች ከመቅረፍ አኳያ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው አስታውቀዋል፡፡
‹‹ ቴክኖሎጂውን ያበለፀግነው ትራንስፖርቱን ከማዘመን ፣ ህገ ወጥ አሰራርና ሙስናን ከማስቀረትና በህይወትና በንብረት ላይ የሚደርሰውን ጥፋት ከማስቀረት አኳያ አስበን ነው” ያሉት ደግሞ የቲዮስ ቴክኖሎጂ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ቴዎድሮስ አጥናፉ ሲሆኑ ፤ መተግበሪያው በአዲስ አበባ ከሚገኙ 60 የተሽከርካሪ ምርመራ ተቋማት በ15ቱ ላይ የሙከራ ስራ ተሰርቶበት ውጤታማነቱ ተረጋገረጧል  ብለዋል፡፡
እንደ አዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ መረጃ የአዲስ አበባ (አ.አ)፣ የኢትዮጵያ (ኢቲ) እና የኮር ዲፕሎማቲክ (CD) ሰሌዳ ያላቸው ከ650 ሺህ በላይ ተሽከርካሪዎች በአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ተመዝግበው የሚገኙ ሲሆን፤ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ330 ሺህ በላይ ተሽከርካሪዎች ተመርምረው ቦሎ መውሰዳቸውንና እስከ በጀት ዓመቱ መጨረሻ ተመርምረው ቦሎ የሚወስዱ ተሽከርካሪዎች ቁጥር 450 ሺህ ይደርሳል ተብሎ እንደሚጠበቅ በዕለቱ ተገልፃል፡፡

በየዓመቱ ለዩኒቨርስቲ ተማሪዎች የሚዘጋጀው ባለፈው ኖቨምበር 11 ቀን 2022 በተጀመረው ዓለማቀፍ የሁዋዌ አይሲቲ (ICT) ውድድር ከ1500 በላይ ተማሪዎች መሳተፋቸውንና ስድስት ተማሪዎች  በቻይና ለሚካሄደው የመጨረሻ ዙር ውድድር ማለፋቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡
በኢትዮጵያ ለ7ኛ ጊዜ በተካሄደው የሁዋዌ አይሲቲ ውድድር ከተለያዩ የትምህርት ተቋማት ከ1500 በላይ ተማሪዎች ተመዝግበው በኦንላይን የተሰጠውን የመጀመሪያ ፈተና መውሰዳቸውን ሁዋዌ በላከው መግለጫ  አስታውሷል፡፡
ከእነዚህም መካከል 63 ተማሪዎች ፈተናውን አልፈው ከት/ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በተዘጋጀውና ዲሴምበር 28 ቀን 2022 ዓ.ም በአዲስ አበባ በተካሄደው አገር አቀፍ የአይሲቲ ውድድር ላይ የተሳተፉ ሲሆን 15 ያህሉ ለቀጣዩ ክልላዊ የአይሲቲ ፈተና ማለፋቸውን ኩባንያው አመልክቷል፡፡ እነዚህም 15 ተማሪዎች ማርች 22 ቀን 2023 ዓ.ም በአዲስ አበባ የሁዋዌ ኢትዮጵያ ዋና መ/ቤት የተሰጠውንና ለስድስት ሰዓት የዘለቀውን የአይሲቲ ኦንላይ ፈተና   ወስደዋል።በውጤቱም ከጎንደር ዩኒቨርስቲ፣ ከዋቻሞ ዩኒቨርስቲ፣ ከአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ እንዲሁም ከአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዪኒቨርስቲ 6 ተማሪዎች ፈተናውን አልፈው ወደ መጨረሻ ዙር የሁዋዌ አይሲቲ ውድድር ማለፋቸው ተገልጿል፡፡ እነዚህም ተማሪዎ ዘንድሮ በቻይና በሚካሄደው የመጨረሻው የሁዋዌ አይሲቲ ውድድር ኢትዮጵያን ወክለው ይሳተፋሉ።እ.ኤ.አ ከ2015 ዓ.ም ወዲህ የሁዋዌ አይሲቲ ውድድር ተፅእኖ እያደገ መምጣቱን ያመለከተው ኩባንያው፤ በ2022 የተካሄደው 6ኛው የሁዋዌ አይሲቲ ውድድር ከ85 አገራትና ክልሎች የተውጣጡ 150 ሺ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎችን ማሳተፉን  አስታውሷል፡፡

ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ፤ ከ1ሚ.በላይ ደንበኞች የ07 ኔትወርኩን በመቀላቀላቸውና ምርትና አገልግሎቶችን በመጠቀማቸው ተሸላሚ የሚሆኑበትን የመጀመሪያ የዕጣ ሽልማት መርሃ ግብር በዛሬው ዕለት በኩባንያው ዋና መ/ቤት በይፋ አስጀምሯል፡፡
ለ14 ሳምንታት በሚዘልቀው "ተረክ በጉርሻ" በተሰኘው የሽልማት መርሃ ግብር፤ ደንበኞች የሳፋሪኮም ሲምካርዳቸውን ሲያወጡ፣ የአየር ሰዓት ሲገዙና ጥቅሎችን ሲሞሉ እንዲሁም የዋትሳፕ ጥቅሎችን ሲጠቀሙ ፤ ለባለ ዕድለኝነት ብቁ የሚያደርጋቸውን የዕጣ ቁጥር ያገኛሉ ተብሏል፡፡
ደንበኞች በቀን ውስጥ እስከ 10 የሚደርሱ የዕጣ ቁጥሮችን እንደሚያገኙና ቁጥሮቹም የዕለት፣ የሁለት ሳምንት እንዲሁም የወር ሽልማቶችን ለማሸነፍ በሚወጡ ዕጣዎች ውስጥ የሚካተቱ እንደሚሆኑ ተነግሯል፡፡
የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አንዋር ሱሳ የሽልማት መርሃግብሩን አስመልክቶ ሲናገሩ፤" የዛሬው ሁነት ደንበኞቻችንን ለማመስገን የተዘጋጀ ነው፡፡ በተረክ በጉርሻ መርሃ ግብራችን፣ በቀጣዮቹ 14 ሳምንታት ከ1ሚ.በላይ ለሚሆኑ ደንበኞቻችን ሳፋሪኮምን ሲቀላቀሉ፣ የአየር ሰዓታቸውን ሲሞሉና ጥቅሎችን ሲሞሉ በሚደርሷቸው የዕጣ ቁጥሮች 3 መኪኖች፣7 ባጃጆች፣ 7 ሞተር ሳይክሎች፣ ስልኮች ታብሌቶችና ዕለታዊ የአየር ሰዓትን ሽልማትን ጨምሮ የተለያዩ ሽልማቶችን የምንሸልም ይሆናል፡፡ ቢዝነሳችንን እየገነባን ያለነው ደንበኞችን ታሳቢ ባደረጉ መልኩ ሲሆን፤ እያደግን በመጣን ቁጥር ደግሞ ደንበኞቻችንን ከእኛ ጋር በመዝለቃቸው ዕውቅና ልንሰጣቸው ይገባል፡፡" ብለዋል፡፡
ደንበኞች የአየር ሰዓት ለመሙላት ወይም የድምፅ፣ የፅሁፍ መልዕክት ወይም የዳታ ጥቅሎችን ለመግዛት በሚያወጡት እያንዳንዱ 10 ብር፣ 1የዕጣ ቁጥር የሚደርሳቸው ሲሆን፤ ሲምካርድ በመግዛት ኔትወርኩን የሚቀላቀሉ አዳዲስ ደንበኞች በ24 ሰዓት ውስጥ አየር ሰዓት ከሞሉ 3 የዕጣ ቁጥሮች ያገኛሉ፡፡ 1 ጂቢ የዋትሳፕ ጥቅሎችን ከተጠቀሙ ደግሞ 7 የዕጣ ቁጥሮች ያገኛሉ ተብሏል፡፡
ለሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ደንበኞችም ክፍት የሆነው የሽልማት መርሃግብር፣ እስከ ሰኔ 28 ቀን 2015 ዓ.ም የሚዘልቅ ሲሆን፤ ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ኔትዎርኩን በዘረጋባቸውና ሥራ በጀመረባቸው የኢትዮጵያ ክፍሎች የሚገኙ ከ1 ሚሊዮን በላይ ደንበኞችን ዕድለኞች የሚያደርግ እንደሚሆን ተጠቁሟል፡፡
አሸናፊዎች ከብሔራዊ ሎተሪ ጋር በመተባበር በየሁለት ሳምንቱ በዕጣ ተለይተው የሚሸለሙ ሲሆን፤ የዕጣ አሸናፊ መሆናቸውም በ0700 700 700 ተደውሎ እንደሚነገራቸውም ሳፋሪኮም አስታውቋል፡፡
የቴሌግራም ቻናልችንን በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…
 
• በአንድ ወር 500 ሚ. ብር ለማሰባሰብ ታቅዷል
በምስረታ ላይ የሚገኘው ግዕዝ ባንክ አክሲዮን ማህበር፤ ዳግም የአክሲዮን ሽያጭ መጀመሩን አስታወቀ።
በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ከመላው ኢትዮጵያና ከዳያስፖራው የ500 ሚሊዮን ብር የአክሲዮን ሽያጭ በማሰባሰብና የሚፈለገውን የካፒታል መጠን በማሟላት በፍጥነት ወደ ሥራ ለመግባት ታቅዷል ተብሏል፡፡
የባንኩ አደራጅና አስተባባሪ ኮሚቴ አባላት በዛሬው ዕለት ወጋገን ባንክ አንደኛ ፎቅ ላይ በሚገኘው ቢሮአቸው በሰጡት የጋራ መግለጫ፤ግዕዝ ባንክ ከመጋቢት 2012 ዓ.ም ጀምሮ ለምስረታ ሂደት የሚያበቃውን የአክሲዮን ሽያጭ ማከናወን መጀመሩን አስታውሰዋል፡፡
ለባንኩ ምሥረታ የሚያስፈልገውን የካፒታል መጠን ለማሟላት ጥቂት ሲቀራቸው ግን በአገሪቱ ላይ በተፈጠረው የሰላምና መረጋጋት ችግር ሳቢያ ከእንቅስቃሴያቸው ተግተው መቆየታቸውን ያስረዳሉ፡፡ ፡
በህዳር 2013 ዓ.ም የአክሲዮን ሽያጭ እንደሚያበቃም ለሚዲያዎች አስታውቀው እንደነበር ያስታወሱት የኮሚቴው አባላት፤ ሆኖም በተፈጠረው ድንገተኛ ችግር ሳቢያ ያቀዱትን ሳያሳኩ እስካሁን መዘግየታቸውን ተናግረዋል፡፡
አሁን በአገሪቱ የተፈጠረውን ሰላምና መረጋጋት ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ ዳግም የአክሲዮን ሽያጭ መጀመራቸውን ነው፣ የአደራጅ ኮሚቴው አባላት ያስታወቁት፡፡
በምስረታ ሂደቱ ላይ በመሳተፍ የባንኩ መስራች ለመሆን ፍላጎት ያላቸው ግለሰቦችና ድርጅቶችም፤ ከዛሬ ጀምሮ በመላ አገሪቱ ባሉ ባንኮች በተከፈቱ የዝግና የአገልግሎት ሂሳብ ቁጥሮች፣ የግዕዝ ባንክ አ.ማ የመመስረቻ አክሲዮን ግዢን ከብር 50ሺ ጀምሮ ማከናወን እንደሚችሉ ተገልጿል።
የመሥራች አክሲዮን ሽያጩ ቀድሞ እንደነበረው የአንድ አክሲዮን መጠን 1ሺ ብር ሲሆን፤ መሥራች አባል ለመሆንም 50 አክሲዮኖችንና ከዚያ በላይ መግዛት እንደሚያስፈልግ ታውቋል። የመሥራች አባል ከፍተኛው የአክሲዮን ሽያጭ 100 ሚሊዮን ብር ነው ተብሏል።
ዳያስፖራዎችን በተመለከተ እንደተለመደው፣ አክሲዮኖችን ባሉበት ሆነው፣ በሚኖሩበት አገር የመገበያያ ገንዘብ መግዛት እንደሚችሉ ተጠቁሟል።
የአደራጅና አስተባባሪ ኮሚቴው አባላት፤በአገሪቱ ላይ ተከስቶ በነበረው የሰላም ችግር ምክንያት የአክሲዮን ሽያጫቸውን አቋርጠው በነበረበት ወቅት፣ ደንበኞች ላሳዩት ትዕግስትና ድጋፍ ልባዊ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
የቴሌግራም ቻናልችንን በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…

የፌዴራል ፍርድ ቤቶችን አገልግሎት አሰጣጥ በቴክኖሎጂ ለማገዝና ለዜጎች ይበልጥ ተደራሽ፣ ቀልጣፋና ፈጣን ፍትህ ለመስጠት የሚያስችል፣ በዲጂታል የታገዘ የዳኝነት አገልግሎትን ተግባራዊ ያደርጋል የተባለ  ስምምነት፣ በኢትዮ ቴሌኮም እና በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት መካከል ተፈጸመ፡፡

በዛሬው ዕለት በተፈጸመው ስምምነት መሠረት፣ ኢትዮ ቴሌኮም፣ አስተማማኝና ደረጃውን የጠበቀ የኢንፎርሜሽን ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ መሰረተ-ልማት:- አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት፣ የመጠባበቂያ ኔትወርክና የኔትወርክ ደህንነት ያለው ዘመናዊ የሞጁላር መረጃ ማዕከል፣ የኔትዎርክ ኦፕሬሽን መቆጣጠሪያ ማዕከል፣ የዋይድ ኤሪያና ሎካል ኤሪያ ኔትወርክ ግንባታ እንዲሁም የሶፍትዌር ደረጃ ዋይድ ኤሪያ ኔትወርክ ማስተዳደሪያ (SD-WAN) ዓለም አቀፍ ደረጃውንና ጥራቱን ጠብቆ በመገንባት ያስረክባል፡፡

ይህም የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተግባራዊ በሚያደርገው የኢ-ኮርት ሲስተም አማካኝነት በፌደራል ፍርድ ቤቶች የሚሰጡ የዳኝነት አገልግሎቶች ለተጠቃሚዎች ቀልጣፋ፣ ውጤታማ፣ ዘመናዊና ተደራሽ እንዲሆኑ ያስችላቸዋል ተብሏል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ስምምነቱ ከዚህ ቀደም በሁለቱ ተቋማት መካከል የነበሩትን የቴሌኮም አገልግሎቶች የትብብር ሥራዎችን በተጠናከረ ሁኔታ ተፈጻሚ ለማድረግ በተለይም በሁለቱ ተቋማት መካከል የአቅም ግንባታ፣ ሥልጠና፣ የእዉቀት፣ የክህሎትና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲከናወን  ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር  እንደሚያስችል ተጠቁሟል፡፡

የመሠረተ ልማቱ ግንባታ ሲጠናቀቅ፣ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በአሁኑ ወቅት በፌዴራል ፍርድ ቤቶች የሚሰጠውን የዳኝነት አገልግሎት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ለመደገፍ፣ ባለድርሻ አካላት በቀላሉ መረጃ እንዲያገኙ ለማድረግ፣ ጊዜና ገንዘብን ለመቆጠብ፣ በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ ግልጸኝነትን  ለማስፈን እንዲሁም ዜጎች በፍትሕ ስርዓቱ ላይ እምነት እንዲኖራቸው ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል ተብሏል፡፡

Saturday, 01 April 2023 20:45

ከሶሻል ሚዲያ በጨረፍታ

 ለህሊናቸው “ምን ሥንሰራ ውለን መጣን” ብለው ይነግሩት ይሆን ?
                        ቴዎድርስ ተ/አረጋይ

       እያንዳንዳችን የብቻችን ሰዓት አለን። ማታ ቤት ገብተን በጀርባችን ተንጋለን ስለ ውሏችን፣ ድካማችን፣ ደስታችን፣ ሀዘናችን ለአፍታም ቢሆን የምናስብበት ቅጽበት አለን። በዚያች ቅጽበት መንፈሳዊነት ካለን ከአምላካችን፣ ኢ - አማኒም ከሆንን ከህሊናችን ጋር እንገናኛለን። ከራሳችን ጋር ጥያቄና መልስ እናደርጋለን። እነዚህ የስራ ጠባያቸው ቤት ማፍረስ የሆኑ ወንድሞቻችን፣ ማታ ደክሟቸው ቤታቸው ገብተው አረፍ ሲሉ ምን ያስቡ ይሆን? ለሚስታቸው ፣ለልጃቸው ወይም ለህሊናቸው “ምን ስንሰራ ውለን መጣን” ይሉ ይሆን? የንጹሀንን ቤት ስናፈርስ? ቤታቸውን የሚያፈርሱባቸውና ንብረታቸውን የሚያወድሙባቸውን ዜጎች ዓይን ሲያዩ ምን ይሰማቸው ይሆን ? የሰውን ተስፋ የመስበርን ስሜት እንዴት ይቋቋሙት ይሆን ? ለአምላክም ለሰውም ይቅር፣ ለህሊናቸው ምን ብለው ነው የሚነግሩት? “ሥራ ነው” ነው የሚሉት? የሰዎችን ሀዘን ከማየት በላይ፣ የሀዘናቸው ምንጭ መሆን ምን ያህል መራር እጣ ፈንታ ነው ?


 በጥበብ አፍቃሪያኑና በጥበበኛው ዘንድ በየዓመቱ በጉጉት የሚጠበቀው ’The Big Art Sale’ ዓውደ ርዕይ በመጪው ሳምንት ለ18ኛ ጊዜ ሊካሄድ መሆኑ ተገለፀ።
በዘንድሮው ታላቅ የሥዕል አውደ ርዕይ ላይ ከ5ሺ በላይ ጎብኚዎች እንደሚታደሙ ይጠበቃል ተብሏል።
 ’The Big Art Sale’ ተወዳጅ ከሆኑ የከተማችን የሥነጥበብ  ዝግጅቶች አንዱ መሆኑን የጠቀሰው አዘጋጁ “ዋትስ አውት አዲስ”፤ከሒልተን ሆቴል ጋር በመተባበር በዓመት አንድ ጊዜ የሚካሄድ የጥበብ ዓውደ ርዕይ መሆኑን ጠቁሟል፡፡
የዘንድሮው አውደ ርዕይ እንደተለመደው በሒልተን አዲስ በመጪው ቅዳሜ መጋቢት 30 እና እሁድ ሚያዝያ 1 ቀን 2015 ዓ.ም ከረፋዱ 4 ሰዓት ጀምሮ እስከ ምሽቱ 12 ሰዓት ድረስ እንደሚካሄድ ያስታወቀው አዘጋጁ፤በአውደ ርዕዩ ከ100 በላይ ሰዓሊያንና ቀራፂያን አዳዲስ ሥራዎቻቸውን ለጎብኚዎችና ለገዢዎች ያቀርባሉ ብሏል፡፡
ከጥበብ ስራዎች በተጨማሪ ጥበብ አፍቃሪያኑ ከቤተሰቦቻቸው ጋር የሚዝናኑባቸው የመጠጥና የምግብ ኮርነሮች ሲኖሩ፤ለልጆች ልዩ የመጫወቻ ሥፍራም ተዘጋጅቶ ይጠብቃቸዋል ተብሏል፡፡ ይህ ልዩ ዓውደ ርዕይ ጠቢብያኑ ሥራቸውን እንዲሸጡ እድል የሚሰጣቸው ሲሆን ገቢውም  ለበጎ አድራጎት ሥራዎች እንደሚውል ተጠቁሟል።  


 አንድ ጠና ያሉ አዛውንት የስጋ አምሮታቸውን ሊወጡ አንድ ስጋ ቤት ገብዋል። መቼም ስጋ መጀመሪያ በአይን ነውና የሚበላው፣ማተር ማተር አደረጉት የተሰቀለውን ስጋ።ሽንጡ ጮማ ነው። ከመቶ ሻማ አምፖል ስር ይቅለጠለጣል። ዳቢቱ ይገላምጣል። ሻኛው ያለተልታል። አዛውንቱ፤”አንድ ኪሎ ቆንጆ አድርገህ ለጥብስ!” አሉና ወደ ጓዳ ገቡ። ስጋ ቤቱን ያውቁታል። ስጋ ቤቱም ያውቃቸዋል። ባለፈው ሰሞን አሟቸው ስለነበር፣ ዛሬ ጥሬ ስጋ አልፈለጉም።
 “ኪሎ ጥብስ አዝዣለሁ” አሉ ገና ቦዩ “ምን ልታዘዝ” ሊል ሲመጣ። “ደረቅ ይበል ታዲያ!” አሉት፤ ቦዩ ፊቱን አዙሮ ሲሄድ። የሰማቸው አይመስልም።
ጥብሱ ቀረበላቸው። ሽንኩርትና ቃሪያ ሰንጠቅ ሰንጠቅ ተደርጎ ተጨምሮበታል። መልኩም ያምራል። ጭሱ ቁና ቁና ይተነፍሳል። በዘመድ የተጠበሰ ሳይሆን አይቀርም። ፈገግ አሉለት አዛውንቱ - ለጥብሱ። “ዌል ካም” እንደማለት።
“ጎሽ እንዲህ ነው እንጂ” አሉና እጅጊያቸውን ሰብሰብ አደረጉ። ሊወርዱበት ነው እንግዲህ -የ78 አመቱ አዛውንት። በተለይ ጎድን ሲበሉ ነጭ አጥንቱ ከጥግ ጥግ  እስከሚታይ፣ እንደ እርሳስ ነው በጥርሳቸው የሚቀርፁት!
ቀና ብለው ሲመለከቱ ወጣት ወጣት ልጆች፣ ያዘዙት እስኪመጣላቸው እየጠበቁ ከፊት ለፊቱ ጠረጴዛ አግዳሚ ላይ ተኮልኩለዋል።
“ጎበዝ ኑ እንብላ እንጂ ታድያ” አሉ አዛውንቱ። ወጣቶቹ ጥቂት አመነቱ።
“ምን ሆናችኋል፤ ብቻዬን ይሄን ሁሉ ምን ላደርገው ነው? ኑ እንጂ ጎበዝ ነውር’ኮ ነው!”
ወጣቶቹ መጥተው ሽማግሌውን ከበቡና፣ ጥብሱን በነዚያ በመረመንጅ የጎረምሳ እጆቻቸው ይሻሙ ገቡ፡፡ በአንድ አፍታ ትሪዋ ወለልዋ ታየ፡፡ “Made in China” የሚለው ተነበበ፡፡ አይ ጉርምስና ደጉ፤ በሚል አስተያየት ልጆቹን አስተዋሉ፡፡ ወጣቶቹ ወደ ቦታቸው ተመለሱ፡፡ ሽማግሌውም ትንሿን ጉደር ወይን ጠጅ አዝዘው መጠጣት ጀመሩ፡፡
ጥቂት ቆይቶ ወጣቶቹ ያዘዙት ስጋ በትሪ ሙሉ መጣ፡፡ ወጣቶቹ ቀናም ብለው ወደ ሽማግሌው ሳያዩ፣ ያንን ትሪ ሙሉ ስጋ ተያያዙት፡፡ አዛውንቱም የወጣቶቹ ነገረ-ሥራ ገርሟቸው በትዝብት እያስተዋሉ ወይናቸውን ይጎነጫሉ፡፡
ወጣቶቹ ስጋውን አገባደው፣ ጉደር አዘዙና ዘና ብለው ተቀመጡ፡፡
ይሄኔ ሽማግሌው፤”ልጆች፣ ጎጂ ባህል ምንድነው?” ሲሉ ጠየቁ፡፡
አንደኛው፤ “ግርዛት ነዋ!” አለ::
‹‹አይደለም›› አሉ አዛውንቱ፡፡
ሁለተኛው፤ ‹‹እንጥል ማስቆረጥ›› አለ፡፡
‹‹አይደለም›› አሉ፤ አዛውንቱ አሁንም፡፡
ሦስተኛው፤ ‹‹ጉሮሮ መባጠጥ…በወር አበባ ጊዜ  መገለል … እ …በአንዳንድ ጎሳ የሴቶችን አካል…››
‹‹ኧረ በጭራሽ!›› አሉ አዛውንቱ እየሳቁ፡፡
አንደኛው፤ ‹‹ካለ እድሜ ከማግባት የሚከሰት የማህፀን ብልሽት ፌስቱላ!››
‹‹መልሱ አጠገብም አልደረሳችሁ›› አሉ ሽማግሌው።
ሁለተኛው፤ ‹‹እንግዲህ በሬዲዮ እና በቴሌቭዥን የሰማነውን ሁሉ ነገርንዎ፡፡ አሁን የእርሶን ንገሩን››
አዛውንቱም፤ ‹‹ልጆች፤ጎጂ ባህል ምን መሰላቹ?...‹‹ኑ እንብላ›› ማለት፡፡
XXX
ሀገራችን በጋራ የሚያስቡ ልጆች ያስፈልጓታል፡፡ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊ እና የፖለቲካ ችግሮቻችን ብዛትና ስፋት በጥቂት ሰዎች፣ ድርጅቶች እና ፓርቲዎች አቅም ብቻ እንወጣው ከምንልበት ደረጃ ካለፈ ውሎ አድራል፡፡ በተለይ ዛሬ ይህ እውነታ ተፈላጊ ብቻ ሳይሆን ግዴታም ነው፡፡ የሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል እርዳ-ተራዳ የሚጠይቅም ሆኗል፡፡ አንድ የፖለቲካ ውጥረት ሲፈጠር፣ አንድ የኢኮኖሚ ጫና ሲመጣ ወይም አንድ ማህበራዊ ቀውስ ሲከሰት ብቻ እንተባበር፣ እንተጋገዝ ብለን ብንጮህ፣ ከእንግዲህ የቱንም ወንዝ የሚያሻግር መላ አናገኝም፡፡ ችግሮች ተባብሰው መጨረሻው ደረጃ ከመድረሳቸው በፊት ህዝብ እንዲነጋገርባቸው እድል መገኘት አለበት፡፡ ብሶቶች ከታመቁ የፈነዱ እለት የሚፈጥሩት ጎርፍ፣ በዋዛ የሚገደብ አለመሆኑን ብዙ ማህበራዊ ትእይንቶች አረጋግጠውልናል፡፡ ብሶቶች መተንፈሻ፣ ጥያቄዎች መልስ ይፈልጋሉ፡፡ ሁኔታዎች አንዴ ከቁጥጥር ውጪ ከሆኑ የፖለቲካ መተረማመስ፣ የኢኮኖሚ አደጋ እና የማህበራዊ ውጥንቅጥ መፍጠራቸው አይቀርምና በጊዜ መጠንቀቅ ያሻል፡፡
‹‹ዛር ልመና ሳይያዙ ገና
ከተያዙ ብዙ ነው መዘዙ›› የሚባለው ለዚህ ነው፡፡
ከአፄ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግስት ጀምሮ በየዘመኑ ህዝባዊ እንቅስቃሴዎች እና አመፆች ተከስተዋል፡፡ ወደ ጦርነትም አድገዋል፡፡ የሁሉ መንስኤ፣ ብሶት (Discontent) ነው፡፡ በመንግስት ባለሥልጣናት ላይ ያለ ብሶት፤በሥርአቱ ላይ ያለ ብሶት፣ በመንግሥት ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ያለ ብሶት፣ በሰብአዊ መብት አያያዝ ጉዳይ ያለ ብሶት፣ በዜጎች ግድያና መፈናቀል ያለ ብሶት፣ ሃሳብን በነጻነት በመግለጽ ዙሪያ ያለ ብሶት፣ ከአቅም በላይ በሆነ የኑሮ ውድነት ላይ ያለ ብሶትና ምሬት ወዘተ በተጠራቀመ ጊዜ ለማህበራዊ እንቅስቃሴ ፍንዳታ ምቹ ማኮብኮቢያ ይሆናል፡፡ ኢንቨስተሮች ይሸሻሉ፤ ሌላውንምያሸሻሉ፡፡ ሥራ አጥነት ያጥጣል፡፡ ማህበራዊ ቀውስ ግራ ቀኙን ያቃውሳል፡፡ ወሮ በላው በረንዳ ያጣብባል፡፡ ለያዥ ለገራዥ ያስቸግራል! ዛሬ አገራችን የደረሰችበት ሁሉን- ዳሰስ ችግር የባለሙያዎችን፣ የምሁራኑን፣ የፖለቲካ አዋቂዎችን፣ የዳያስፖራውን፣ የልዩ ልዩ ማህበራትን እና ድርጅቶችን ሁሉ ልባዊ ተሳትፎ የሚጠይቅ ነው፡፡ እነዚህን ሁሉ ለማሳካት ደግሞ ሆደ- ሰፊ የሆነ የፖለቲካ አመለካከትን ይጠይቃል፡፡
 ለመታረም ምክርን የሚያዳምጥ፣ ለግለ ሂስ ቀና መንፈስና ፅናት ያለው፣ ከኔ በላይ አዋቂ ለአፈር የማይል፣ ጉራ ሳይሆን ትህትና፣ ድንፋታ ሳይሆን የጥሞና ውይይትን፣ መቅጠፍን ሳይሆን በሀቅ ማሳመንን የሚያምን ሃላፊ ያስፈልጋል፡፡ ዊንስተን ቸርችል እንዳሉት፤ ‹‹ድል በተገኘ ሰአት ደግ መሆን መቻል ትልቅነት ነው፡፡ በውድቀትም ሰዓት ሽንፈትን መቀበል ብልህነት ነው››፡፡ ከጉልበት ይልቅ ብልሃትን መጠቀም ያዋቂ መሪዎች መገመቻ ነው፡፡ ትላንት የጀመርነው መንገድ የግድ መቀጠል አለበት ብሎ መታበይ አያዋጣም፡፡ ይልቁንም ሰፋ ያለ ፖለቲካዊ የተሳትፎ መድረክ ለመፍጠር መትጋት  ያስፈልጋል፡፡
    ሆደ-ሰፊ የፖለቲካ አመለካከት ያለው፤ ከትምህክተኝነትም ሆነ ከጠባብነት አደጋ የመዳን እድሉ ሰፊ ነው፡፡ ይህ አመለካከት ያለው የሥልጣንን ገበታ ብቻዬን ልያዘው አይልም፡፡ መቻቻልን ከጠረጴዛው የማይለየው አጀንዳ ያደርጋል፡፡ ልዩነትን በማጥበብ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ወደ ገበታው ይጋብዛል፡፡ ‹‹ኑ እንብላ›› ለማለት ይችላል፡፡ ለለውጥም በሩ ሁሌም ክፍት ነው፡፡ አለማወቅን እንደ ውርደት ሳይቆጥር የማያውቀውን ይማራል፡፡ በዙሪያው በአጨብጫቢነት የተኮለኮሉ ግለሰቦችን በጥንቃቄ ያፀዳል፡፡ ምላሳቸው እረጃጅም የሆኑ መጣፍ ገላጮችን እና ቲኦሪ አንጋቾችን የፕሮፓጋንዳ አፎቶችን፣ የልሳን እና የብእር አንጋቾችን፣ በክፉ ሰአት ሁሉ ይመዝናል፡፡ በትላንት በሬ አያርስምና ለአዳዲስ የፖለቲካ ፈለግና ራእይ በሳል የሀገሪቱን ሰዎች ከእንቅስቃሴ መስክ አያርቅም፡፡ ዜጋ ሁሉ በሀገሩ በሚመለከተው ጉዳይ ‹‹ለምን?››  ብሎ የመጠየቅ መብት እንዳለው አበክሮ ይረዳል፡፡ ስለ ጎረቤት አገሮች ጉዳይ ከአገሬው ጋር ይመክራል፤ ይዘክራል፡፡ ኢንፎርሜሽን ይሰጣል፡፡
ፖለቲካን እንደ ጊዜያዊ ስራ (Part time job) የሚይዙ፣ ሁሌ ቤቴ የሆኑ፣ ለህዝቡ እንደ ጊዜያዊ ወዳጅ (part time lover) የሆኑ እና ‹‹ቱሪስት እና ፒስኮር የማይለዩ›› ካድሬዎችን እንዲሁም እምቡጣዎችን አበጥሮ ያወጣል፡፡ ጭፍን አምልኮ-ሰብ (cult) ለመፍጠር የሚሹትን እንደሚያንገዋልል ሁሉ ከመሀይም ምእመናንም በጊዜ ይገላገላል፡፡ ኩርፊያ ሳይሆን ውይይትን ያደንቃል፡፡ በዚህ ሁሉ መካከል ግን በሩን ለትችት ክፍት ያደርጋል፡፡ ከተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር አብሮ ለመስራት የሚችልበትን መንገድ ይጠርጋል፡፡ የአንገት በላይ ፍቅር አንገት ሲቆረጥ ወድቆ ይቀራል ይሏልና፣ ለህዝብ ያለው ፍቅር ልባዊ መሆን ይኖርበታል፡፡
እነዚህ ሁሉ ዲስፕሊኖችና ባህሪያት ከእውነተኛ ሰብአዊ መብት፣ ከእውነተኛ ነጻነት እና ዲሞክራሲ አብራክ የሚወለዱ ናቸውና ተዓማኒ እንጂ የይስሙላ እንዳይሆኑ ብርቱ ጥረት ማድረግ አለበት፡፡
 ‹‹ዲሞክራሲ፣ ሰላም፣ ሰብአዊ መብት፣ እኩልነት፣ መቻቻል…›› ተደጋግሞ ቢጮሁ፣ የተግባርን ፀጋ ካልተጎናፀፉ አፋዊ አተታ ብቻ ናቸው፡፡ ሺ ጊዜ ቢንጡት የቁልቋል ወተት ቅቤ አይወጣውም እንደሚባለው ማለት ነው፡፡ ተግባር፣ ተግባር አሁንም ተግባር፤ ያስፈልጋል፡፡ ‹‹ኑ እንብላ›› ጎጂ ባህል የማይሆነው፣ ያኔና ያኔ ብቻ ነው፡፡

በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ለተገደሉበት ግጭት ዓለማቀፍ ተቋማት በቂ ምላሽ አልሰጡም ሲል ወቅሷል፡፡
       ባለፈው ዓመት በዓመት የጦር ወንጀል ከተፈፀመባቸው 20 አገራት አንዷ ኢትዮጵያ ናት ብሏል፡፡
               አለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ አምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ የአለም አገራትን የሰብአዊ መብት አያያዝ የሚፈተሽበትን ዓመታዊ ሪፖርቱን ይፋ ያደረገ ሲሆን፤ ድርጅቱ በዚሁ ሪፖርቱ ባለፈው የፈረንጅ ዓመት በዓለማችን ከተፈፀሙ ግጭቶች እጅግ አስከፊውና ገዳዩ የተፈፀመው በዩክሬን ሳይሆን በኢትዮጵያ ነው ብሏል። ይህ በአገሪቱ የተፈፀመው ዘግናኝ በደል የተፈፀመውም ከአለም የትኩረት  አቅጣጫ ውጪ ነው ሲልም አምነሲት ጠቁሟል። አመልክቷል።
ከትናንት በስቲያ ይፋ በተደረገው በዚሁ የድርጅቱ አመታዊ ሪፖርት ላይ እንደተመለከተው ያለፈው የፈረንጆች አመት በአለም ዙሪያ እጅግ ዘግናኝ ግድያዎች የተፈፀሙበት ዝርፊያዎች፣ ፆታዊ ጥቃቶችና፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች የተፈፀሙበት አመት ነበር። ድርጅቱ በተለይ በኢትዮጵያ ተፈፀሙ ያላቸውን የግፍ ግድያዎች ህገ-ወጥ እስሮችና መልከ ብዙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን የዘረዘረ ሲሆን እነዚህ የጦር ወንጀሎችና የግፋ ግድያዎች በአለማችን እጅግ ከባድ ተብለው ከሚጠቀሱት የሩሲያና ዩክሬን ጦርነትም የከፋ ነው ብሏል። ባለፈው የፈረንጆች አመት እጅግ ገዳዩ ግጭት የተፈፀመው ዩክሬን ሳይሆን ኢትዮጵያ ውስጥ ነው ብሏል ሪፖርቱ። በዚህ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ለተገደሉበት ግጭት አለማቀፍ ተቋማት ሰጡት ምላሽ በቂ አለመሆኑንም በሪፖርቱ አመልክቷል።
አሚኒስቲ ኢንተርናሽናል ሰሞኑን ይፋ ባደረገውና ባለፈው የአውሮፓውያን አመት በአለም ላይ በተከሰቱ ግጭቶችና ተቃውሞዎች ላይ ትኩረቱን ባደረገው በዚሁ ሪፖርቱ በኢትዮጵያ በሰሜኑ ክፍል በተካሄደው ጦርነትና በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በተቀሰቀሱ ተቃውሞዎች ምክንያት በርካታ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተፈፅመዋል ብሏል።
ድርጅቱ ጥናት ካካሄደባቸው 156 አገራት መካከል በሃያዎቹ የጦር ወንጀሎችን ጨምሮ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መፈፀማቸውን ያመለከተው የድርጅቱ ሪፖርት በ79 አገራት ደግሞ ሃሳብን በነፃነት በሚገልፁ መብት ተሟጋቾችና አንቂዎች ላይ እስር ድብደባና በደል ተፈፅሞባቸዋል ብሏል። ባለፉት ሁለት ዓመታት በሰሜኑ አገራችን ክፍል የተካሄደውን ጦርነት በአለማችን ከተካሄዱ አውዳሚ ጦርነቶች መካከል አንዱ ነው ያለው የድርጅቱ አመታዊ ሪፖርት በጦርነቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል። ሰብዓዊ መብት ጥሰት ተፈፅሟል። ጦርነቱ በተካሄደባቸው በትግራይ፣ አማራና አፋር ክልል ውስጥ የሚኖሩ ከ8.35 ሚሊዮን በላይ ዜጎች እርዳታ ጠባቂ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል ብሏል።
አለም አቀፍ እርዳታ ሰጪ ድርጅቶች ለግጭቱ የሰጡት ምላሽ በቂ አይደለም ሲልም ወቅሷል።አለም አቀፍ ሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ድርጅት ይፋ ባደረገው በዚሁ አመታዊ የአለም የሰብዓዊ መብት አያያዝ ሪፖርት በኢትዮጵያ ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት በከፍተኛ ሁኔታ መሸርሸሩንና ባለሞያዎች ታስረው እንደሚገኙ አመልክቷል።


በጥበብ አፍቃሪያኑና በጥበበኛው ዘንድ በየዓመቱ በጉጉት የሚጠበቀው ’The Big Art Sale’ ዓውደ ርዕይ በመጪው ሳምንት ለ18ኛ ጊዜ ሊካሄድ መሆኑ ተገለፀ።
በዘንድሮው ታላቅ የሥዕል አውደ ርዕይ ላይ ከ5ሺ በላይ ጎብኚዎች እንደሚታደሙ ይጠበቃል ተብሏል።
 ’The Big Art Sale’ ተወዳጅ ከሆኑ የከተማችን የሥነጥበብ  ዝግጅቶች አንዱ መሆኑን የጠቀሰው አዘጋጁ "ዋትስ አውት አዲስ"፤ከሒልተን ሆቴል ጋር በመተባበር በዓመት አንድ ጊዜ የሚካሄድ የጥበብ ዓውደ ርዕይ መሆኑን ጠቁሟል፡፡
የዘንድሮው አውደ ርዕይ እንደተለመደው በሒልተን አዲስ በመጪው ቅዳሜ መጋቢት 30 እና እሁድ ሚያዝያ 1 ቀን 2015 ዓ.ም ከረፋዱ 4 ሰዓት ጀምሮ እስከ ምሽቱ 12 ሰዓት ድረስ እንደሚካሄድ ያስታወቀው አዘጋጁ፤በአውደ ርዕዩ ከ100 በላይ ሰዓሊያንና ቀራፂያን አዳዲስ ሥራዎቻቸውን ለጎብኚዎችና ለገዢዎች ያቀርባሉ ብሏል፡፡
ከጥበብ ስራዎች በተጨማሪ ጥበብ አፍቃሪያኑ ከቤተሰቦቻቸው ጋር የሚዝናኑባቸው የመጠጥና የምግብ ኮርነሮች ሲኖሩ፤ለልጆች ልዩ የመጫወቻ ሥፍራም ተዘጋጅቶ ይጠብቃቸዋል ተብሏል፡፡
 ይህ ልዩ ዓውደ ርዕይ ጠቢብያኑ ሥራቸውን እንዲሸጡ እድል የሚሰጣቸው ሲሆን፤ ገቢውም  ለበጎ አድራጎት ሥራዎች እንደሚውል ተጠቁሟል።

Page 10 of 647