Administrator

Administrator

Saturday, 16 January 2021 12:16

ሰውነት

ጭንቅላት ዓለም ነው።
ዕድል ደግሞ እንደአንገት፣
ስንዞር የሚታይ…
ባግራሞት፣ በድንገት።
ካንገት በታች ያለው…
ትውልድ የሚያስቀጥል…
ዕድሜ የሚባለው የመኖሪያ ዘመን፣
ሕይወት ነው ይባላል…
አካል አጠቃላይ አንድ ላይ ሲተመን።
(ከበቃሉ ሙሉ “እኔ እና ክርስቶስ”)


Saturday, 16 January 2021 12:08

የግጥም ጥግ

ያንቺን ድምፅ ብቻ፣ ሲያቃጭል የኖረ
የቆለፍሺው ጆሮ፣ በምን ተሰበረ?
ይኸው ብዙ ድምፆች
ከየትም እየመጡ፣ ይሰሙኝ ጀመረ።
የዘጋሽው ልቤ!
የቆለፍሽው ልቤ!
የተሰባበረው
እንዴት ሰው አማረው?
። ። ።
ልረሣሽ ነው መሠል፣ ወይ ደግሞ
ልትመጪ
ይሰማኝ ጀመረ
ያውደኝ ጀመረ
ይታየኝ ጀመረ፣ ሕይወት ካንቺ ውጪ።
(በላይ በቀለ ወያ)


__________________


          የዕድሜ ልክ ደብዳቤ

ይድረስ ለምወድሽ…
ዓለም ያክል ሐሳብ የተሸከመ ሰው፣
ዕረፍት አያገኝም ፍቅር ቢዳብሰው።
ቢሆንም እውነታው፣
ሞቴ አንች ነሽና…!


"በየሳምንቱ ሳላቋርጥ በማንበብ ላይ ነኝ"


           አቶ መስፍን ወልዴ መሃል ኮልፌ ላይ የሚገኝ “አጋዝ ካፌና ሬስቶራንት” ባለቤት ነው። መተዳደሪያው ንግድ ነው፡፡ የዛሬ እንግዳችን ያደረግነው በንግድ ሥራው አይደለም፡፡ በአንባቢነቱና በአዲስ አድማስ የረጅም ዘመን ወዳጅነቱ ነው፡፡ ከጋዜጣችን ጋር ዝምድና አለው፤ ያቆራኘው ኪዳን፣ የሳበው እውነት አለ።  ከ20 ዓመት በላይ የአዲስ አድማስ ጋዜጣ አንባቢ ነው። ፍቅሩም እስከ ዛሬ ዘልቋል፣ በጊዜ ርቀት አልተነነም፣ … ዘወትር ቅዳሜን በናፍቆትና በጉጉት እንደሚጠብቅ ይናገራል። ከራሱም አልፎ ለካፌ ደንበኞቹ ከቡና ጋር አዲስ አድማስን እንዲያነቡ ያቀርብላቸው ነበር።  ለመሆኑ ከጋዜጣው ጋር መቼ ተዋወቀ? የፍቅሩስ ምስጢር ምን ይሆን? …እንዲህ አውግቶናል፡-


                     እንደምታየው ስራዬ ንግድ ነው። አዲስ አድማስ ጋዜጣን ማንበብ የጀመርኩት ገና ሲጀመር፣ በምስረታው ነው፤ ሃያ ዓመት አልፎኛል። እስካሁን በየሳምንቱ ሳላቋርጥ በማንበብ ላይ ነኝ፡፡ አሁን ሁኔታው ከልክሎኝ እንጂ ሌሎች ሰዎችም  (ደንበኞቼ) እንዲያነብቡ ገዝቼ በየጠረጴዛው ላይ አስቀምጥ ነበር።
ጋዜጣ ወይም መጽሄት ሳታቋርጥ የምትከታተለው፣ አንዳች የወደድከው ነገር ሲኖር ነው። አዲስ አድማስን በምን ወደድካት?
አዲስ አድማስን የወደድኩበት የመጀመሪያውና ዋናው ምክንያት፣ ሚዛናዊ መጣጥፎች ይዞ መውጣቱ ነው። በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የሚጽፉትን ዐምደኞች ሀሳብ እወድደዋለሁ። በጎና ጠቃሚ ሀሳብ የሚያስተላልፉ ናቸው። በዋናነት ርዕሰ አንቀፁ በጣም የምወደውና የሚመቸኝ ነው፡፡ ለሀገራችን ኢትዮጵያ የሚበጅ፣ ሚዛናዊ የሆነ መልዕክትና ቁምነገር የሚያስተላልፍ ፅሁፍ  ነው። … በሀገራዊ ስነ-ቃልና ተረቶች ጀምሮ፣ መደምደሚያው ላይ የሚቋጭበት መንገድ፣ ከተጨባጩ ህይወት ጋር የሚዛመድና ገላጭ ነው። ያ በጣም ይገርመኛል፡፡ አንዳንድ ሰዎች ውስብስብ ነው ሲሉ እሰማለሁ፤ … አጣጥመህ ካነበብከው ግን በጣም አስተማማኝ፣ የሀገሪቱን ተጨባጭና ወቅታዊ ሁኔታ የሚያንፀባርቅ ነው። ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ ጉዳዮችን  አዋዝቶ በማራኪ ቋንቋ ያቀርባል።
ከጋዜጣው አምዶች የትኞቹን በቅድምያና በትኩረት ታነባለህ--?
በሚገርም ሁኔታ ሁሉንም አነብባለሁ፤… ፖለቲካ ይመስጠኛል፤ ምክንያቱም የሁሉም ነገር መነሻ እርሱ ነውና፡፡ ፖለቲካው ካልተስተካከለ ብትነግድም ዘለቄታው አስተማማኝ አይሆንም፤ ፖሊሲዎችና ህጎች ለችግር ሊዳርጉህ ይችላሉ። የአዲስ አድማስ ፖለቲካ ደግሞ ሚዛናዊ ነው፤ ጽንፈኛ አይደለም፤ ከሚነቅፈውና ከሚደግፈው ጎን አይቆምም፤ ሀሳብን  ብቻ ሞጋች ነው። በመቀጠል ኢኮኖሚውን አነብባለሁ። ለምሳሌ የንግዱን ማህበረሰብ ተሞክሮዎች አነብባለሁ። ቀደም ሲል ብርሃኑ ሰሙ የሚያቀርባቸውን ንግድ ተኮር ጽሁፎች ስከታተል የስራ መንገዴንም ያሳየኛል። እንደ ዘምዘም ያሉትን የመርካቶ የንግድ መሰረቶች ታሪክ ሳነብ የምማረው ነገር አለ። እርሳቸው በሴትነት በዚያ ዘመን የሰሩትን ጠንካራ ስራ ሳይ እደነቃለሁ፤ የምወስደውም ተሞክሮ ይኖራል። ሌላው የጥበብ ዓምድ ነው፡፡ በጥበብ አምድ መፃሕፍት ላይ የሚሰጡትን አስተያየቶች፣ ሂሳዊ መጣጥፎች ማንበብ ደስ ይለኛል። እነ ገዛኸኝ ጸ.  የመሳሰሉት ፀሐፍት የሚያቀርቡትን እከታተላለሁ፡፡
ከቃለ ምልልሶች በአእምሮህ ተቀርፀው የቀሩ ይኖራሉ ብዬ እገምታለሁ---
በንግዱ ዘርፍ፣ የአስፋወሰን ሆቴል ባለቤት የነበሩት ወ/ሮ ዘምዘም ጥንካሬ ይደንቀኛል፡፡ መርካቶ ውስጥ፣ በዚያ ዘመን ይህን የሚያህል ሕንፃ መገንባታቸው የሚያስደስትና ፈለጋቸውን ለመከተል የሚያስመኝ ነው። በፖለቲካው በኩል፣ በሃያ ዓመታት በርካታ የፖለቲካ ሰዎች ቃለ ምልልስ አድርገዋል። በገዢውም  ወገን ሆነ በተፎካካሪዎች ቃለ ምልልስ ያልተደረገለት ስመጥር ፖለቲከኛ የለም። ዶክተር ብርሃኑ ነጋ፣ አቶ ልደቱ አያሌውና ፕ/ር መስፍን ወልደማርያምን የመሳሰሉ ቀርበው ሃሳባቸውንና መንገዶቻቸውን ገልፀውበታል። ሁሉንም አንብቤያቸዋለሁ ማለት እችላለሁ። የሚቀርበው ቃለ ምልልስ ሚዛናዊ ነው፡፡ አጠቃላይ ግቡ ኢትዮጵያ ተኮር ነው። ጋዜጣው የሚሰራው ኢትዮጵያዊነት አሸናፊ እንዲሆን ነው።
ተከታታይ መጣጥፎችስ ታነባለህ--? ለምሳሌ "የኛ ሰው በአሜሪካ"---?  
ነቢይ መኮንን ትልቅ ገጣሚ ነው፤ አዲስ አድማስም ላይ ብዙ አንባቢ ያለውና ጋዜጣዋን ተወዳጅ ካደረጉት ፀሐፍት መካከል ተጠቃሽ ነው፡፡ ጋሽ ነቢይን አመሰግነዋለሁ። “የኛ ሰው በአሜሪካ” በጣም የሚወደድ፣ ጥሩ ፍሰት ያለው፣ ማራኪና የስደት ሀገር የሕይወት ገጽታዎችን የሚያሳይ ነበር። መነሻውን፣ መድረሻውን የሚያውቅ፣ አሜሪካንና ኢትዮጵያን የሚያነጻጽርና የሚያስተሳስር አስደሳች ጽሑፍ ነው። የአሜሪካን ሀገር ሰዎች ሕይወትና አኗኗርን ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ትረካ በመሆኑ ሳምንት እስኪደርስ የሚናፍቅ ነበር። እኔ ብቻ ሳልሆን ብዙ ሰዎች ጋዜጣውን ሲያገኙ ዘለው ጉብ የሚሉት እሱ ላይ እንደነበር አስታውሳለሁ። እውነት ለመናገር በጣም የተነበበ ጽሁፍ ነው። እዚያ ያሉት ኢትዮጵያውያን አኗኗር፣ ሀገር ቤት ያለው ምኞትና በእውን ያለው ሕይወት፣ መስተጋብር -- ሁሉ የሚገርም ነበር። እዚህ የናቁትን ስራ እዚያ እንዴት እንደሚሰሩት…  እዚህ ያሰቡት ዶላር እዚያ በቀላሉ እንደማይገኝ፣ ዝቅ ካለ ቦታ ተነስተው፣ ትልቅ ቦታ የደረሱ ጠንካሮችንም ያየንበት ነው።
ከአዲስ አድማስ የሃያ ዓመት ወዳጅነትህ ምን ተጠቀምኩ ትላለህ?  
እውነት ለመናገር ከሁሉ በላይ የንባብ ፍላጎቴን አጎልብቶልኛል፡፡ እንደምታውቀው የንግድ አገልግሎት፣ በተለይ ካፌ ጊዜ ይፈልጋል። ሠራተኞችን ማስተዳደሩም ቀላል አይደለም፤ ከደንበኞች ምቾት ጋር የሚያያዝ ስለሆነ ስራው ከባድ ነው። ሆኖም ግን አዲስ አድማስ ይዛ የምትወጣው ነገር ሳቢ ስለሆነ እኔም በፖለቲካው፣ በኢኮኖሚው፣ በጥበቡ ዘርፍ --- ብዙ ዕውቀት እንድጨብጥ አድርጎኛል። ከመጻሕፍት በላይ ጠቅሞኛል። ምክንያቱም አንድ መፅሐፍ የሚነግርህ ስለ አንድ ነገር ይሆናል። አዲስ አድማስ ላይ ግን ባንድ ቀን እትም ስለ ኢኮኖሚ፣ ፖለቲካ፣ ስለ ጥበብ መጠነኛ ግንዛቤ የምትጨብጥበትን ሀሳብ ታገኛለህ። በአጠቃላይ በጋዜጣው የማይዳሰስ ነገር የለም። በዚያ ላይ የብዙ ፀሐፍት የሃሳብና የዕውቀት ክምችት ይገኛል። የአስርና ከዚያ በላይ ሰዎችን እውቀትና ምልከታ ትካፈላለህ፤ ይህ ቀላል አይደለም። በሁሉም አቅጣጫ በዕውቀት ትታጠቃለህ። ስለዚህ ብዙ ዕውቀት አግኝቻለሁ፤ በሌላ በኩል መፃሕፍትም እንዳነብ አግዞኛል። በአጠቃላይ፡- በሕትመቱ ዘርፍ ወገንተኝነት የሌለበት፣ ዛሬ አንብበህ ነገ የማትጥላቸው፣ የሃሳብ የበላይነት የሚንፀባረቅባቸውን መጣጥፎች አግኝቻለሁ።…  ለሀሳብና ሀሳብ ብቻ ቦታ ያለው ጋዜጣ ነው። አንዳንድ ሰዎች “ለዘብተኛ ነው” በሚሉት አልስማማም። ትክክለኛ ዘገባ ስታቀርብ ከሚያስጮሁት ግን ቶሎ ከሚጠፉት ወገን አትሆንም።... ማስጮህ ያጠፋል!... ምክንያቱም ቋሚ የሃሳብ ልዕልና አይኖርህምና!
በዚህ አጋጣሚ የጋዜጣውን መስራች አቶ አሰፋ ጎሳዬን ላመሰግን እፈልጋለሁ። እሱ በጥሩ መሰረት ላይ ስላቆመው ይኸው ዛሬም ድረስ ቀጥሏል። እርሱ ባይኖርም ስራው ዛሬም ለሀገር እየጠቀመ ነው።
በኛ አገር የንባብ ባህል አልዳበረም። አንተ በተለይ ነጋዴ ሆነህ እንዴት ወደ ንባብ ገባህ ?
እኔ ንባብ የለመድኩት እዚሁ አዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ ነው። በአንድ ወቅት  "ሙሉ ሰው እንድትሆን አንብብ!” የሚል አባባል ጋዜጣው ላይ ይወጣ ነበር። ያ - ነገር በጣም ሳበኝ። በርግጥም አንድ ሰው ሙሉ ሊሆን የሚችለው ሲያነብ ብቻ ነው። እኔ እንኳ ብዙ የተረፈ ጊዜ ኖሮኝ አነብባለሁ ባልልም፣ መታገሌ በራሱ ጥሩ ነገር ነው። መፃሕፍትን አነብባለሁ። እንደምታየው ባሁን ጊዜ ንባብ የወደቀ ይመስላል። ቢሆንም ሰው ያለ ንባብ ሙሉ አይደለም፤ ምክንያቱም፤ ሰው ኢኮኖሚክስ ቢማር፣ የሚያውቀው ስለዚያ ዘርፍ ብቻ ነው። ያው በንድፈ ሀሳብ ደረጃ! ምህንድስና ቢማርም እንደዚያው ነው። በሌሎችም! ሲያነብ ግን ስለ ፖለቲካው ያውቃል፤ ስለ ኢኮኖሚው፣ ስለ ሌላው ዘርፍ ያውቃል። ስለ ምህንድስና ለማወቅ፣ የዘርፉን መፃሕፍት ማንበብ አለበት። ስለ ንግድም እንደዚሁ። አንድ ሰው ፕሮፌሰር እንኳ ቢሆን ስለተማረበት፣ ስፔሻላይዝ ስላደረገው ነገር እንጂ ሌላ ነገር አያውቅም። ከማንበብ ግን የማታውቀው ነገር የለም። በተለይ ለጋዜጠኞች፣ ለሀገር መሪዎች ሰፊ ንባብ ያስፈልጋል። ምክንያቱም ሞያቸውም ያስገድዳቸዋል። አገልግሎታቸው ሙሉ እንዲሆን ስለ ኢኮኖሚ፣ ስለ ጥበብ፣ ስለ ንግድ ወዘተ ሊያውቁ ይገባል። ጋዜጠኛም ሚዛናዊ ሊሆን የሚችለው ሲያነብብና ሲያነብብ ብቻ ነው። ካልሆነ ጥራዝ ነጠቅ ይሆናል። የተሟላ መረጃ ማቅረብም አይችልም።
ወደ እኔም ስንመጣ ማንበብ ያስደስተኛል። አዲስ አድማስ ሳምንት ቅዳሜ እስኪደርስ ይጨንቀኛል። ጠዋት ጋዜጣውን ገላልጬ ካላየሁ እንደ ቡና ሱስ ነው። ቁርስ ከመብላቴ በፊት እርሱን አያለሁ። ከሃያ ዓመት በላይ ያነበብኩት ሱስ ሆኖብኝ ነው፡፡ ማንበብ ሙሉ ሰው ያደርጋል! በሚለውም አምናለሁ። ሰው ለሌላ ነገር ገንዘብ የሚያወጣውን ያህል ጋዜጣና መፃሕፍት ገዝቶ በማንበብም ራሱን ማሻሻል አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡ እኔ ከራሴ አልፌ የተለያዩ ጋዜጦችና መፅሔቶችን እየገዛሁ ለካፌ ደንበኞቼ አስቀምጥ ነበር። ሰውም ማኪያቶና ቁርስ እስኪመጣለት ድረስ ማንበቡንም ተለማምዶ ነበር። አንድ ወቅት ላይ በተፈጠረው የፖለቲካ ግለት የማይመች ሁኔታ ገጥሞኝ ለራሴ ብቻ ማንበብ ቀጠልኩ።
አዲስ አድማስ ጋዜጣ እስከ ዛሬ ብዙ ሃሳቦች አካፍሎናል።… በአካል ባይኖርም ይህን ጋዜጣ የመሰረተውን አሰፋ ጎሳዬን፣ ነቢይ መኮንንን፣ ዮሐንስ ሰን፣ ገዛኸኝ ፀን፣ ኢዮብ ካሣንና ሌሎቻችሁንም ማመስገን ይገባኛል።… ከሃያ ዓመት በላይ በህትመት መዝለቅ ማለት ትልቅ ስኬት ነው። ጋዜጠኞችንና የጥበብ ሰዎችን ሁሉ አመሰግናለሁ፤ ዕውቀት በገንዘብ አይገዛም፤ በፍላጎት የሚገኝ ነው። ስለዚህ ጋዜጣው ባለውለታችን ነው፡፡.. የዚህን ያህል ተጉዞ ለዚህ መድረሱ የጥንካሬው ማሳያ ነው…ብዬ አምናለሁ።… የመረጥኩትም ለዚያ ነው፤ ተገድጄ አይደለም፡፡


አንድ ልዑል ከቤተ መንግስት ራቅ ብሎ ወደ ሚገኝ አንድ ትልቅ ጫካ ሄዶ፣ አደን ሲያድን ውሎ በፈረሱ ወደ ቤተ መንግስት ሲመለስ፣ አንድ ባላገር ያገኛል፡፡ ባላገሩ ልዑሉ ማን እንደሆነ አያውቅም ነበርና አንዳችም እጅ ሳይነሳ፣ ሰላምታም ሳይሰጥ ዝም ብሎ መንገዱን ይቀጥላል፡፡ ልዑልም የባላገሩ ነገር ገርሞት፤
“ሰማህ ወይ ወዳጄ፤ ለመሆኑ እኔ ማን እንደሆንኩ ታውቃለህ ወይ?” ሲል ይጠይቀዋል፡፡
ባላገሩም “በመንደራቸውን ባለው ጫካ ውስጥ በገዛ ፍቃድህ ገብተህ አደን ስታድን እንደቆየህ አይቻለሁ፡፡ በሰላም የተቀመጡትን አዕዋፋት ስታባርራቸው፣እንስሳትንም መጠጊያ ስታሳጣቸው የነበርከው ሰው መሆንህንም ተመልክቻለሁ” አለው፡፡
ልዑልም፤ ምን ስሰራ  እንደቆየሁ ፣ማወቅህ መልካም፡፡ ማንነቴንስ አውቀኸዋል ወይ?” ሲል ደግሞ ጠየቀው፡፡
ባላገሩም፤”አላውቅም” አለው፡፡
ልሑል “ንጉስ ማለት ምን ማለት እንደሆነስ ታውቃለህ ወይ?”
ባለገር፤”አላውቅም፡፡”
ልዑሉ፤ “እንግዲያውስ ና ፈረሴ ላይ ውጣና አብረን ወደ ከተማ እንሂድ፡፡ ንጉስ ማለት ምን ማለት እንደሆነ እዚያ ታውቃለህ” አለው፡፡
ልዑሉ ባላገሩን አፈናጦ ወደ ከተማ ይዞት ሔደ፡፡ በመንገድ ላይም “ንጉስ ማለት የተከበረ፣ በሄደበት ቦታ ሁሉ ህዝብ እጅ የሚነሳው፣ መንገደኛው ሁሉ ቆሞ የሚያሳልፈው ትልቅ ሰው”  አለው፡፡
ከተማ ሲደርሱ፣ ህዝቡ ልዑሉን ሲያይ እየቆመ፣ እጅ እየነሳ አሳለፈው፡፡ ግማሹም አቤቱታውን አሰማ፡፡
ይሄኔ ልዑል ወደ ባላገሩ ዞሮ “አሁን ንጉስ ማን እንደሆነ አወቅህ? ንጉስ ማን ይመስላል?” ሲል ጠየቀው፡፡
ባላገሩም “እንግዲህ፤ ወይ እኔ ወደ አንተ መሆናችን ነዋ” ሲል መለሰ፡፡
“ቡመራንግ” ማለት ይሄ ነው -ለሌላው የወረወሩት ቀስት ተመለሶ ወደ ራስ!
ህዝቦችና መሪዎች ሲጠፋፉ የሚፈጠረው ግራ መጋባት አይጣል ነው! የክልል፣ የቀጠና፣ የወረዳና የቀበሌ መስተዳድር፣ የቢሮና የሚኒስቴር ኃላፊዎች እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ከህዝብ ሲርቁ ከላይ እንደተጠቀሰው ባላገር ማንነታቸው ብቻ ሳይሆን ምንነታቸውም ለህዝብ ግራ የሚገባበት ደረጃ ይደርሳል። ህዝቡ ልቡ ክፍት ነው። ህዝብ የነገሩትን ይሰማል። የተረጎሙለትን፣ እውነት ብሎ ይቀበላል። ያወጁለትን አዋጅ፣ ይበጀኝ ብሎ ያከብራል። የደነገጉለትን ህግ፣ በወጉ ሊተዳደርበት ይነሳል። ያወጡለትን መመሪያ አመራበታለሁ ብሎ ይስማማል። እቅዶች አምረው ሲያያቸው ሰምረው አገኛቸዋለሁ ብሎ ተስፋ ያደርጋል። ችግር የሚፈጠረውና ፀብ የሚመጣው፣ አንድም  በተግባር ሲተረጎሙ በመዛባታቸው፣ አንድም ባወጣቸው ክፍል በራሱ በቃ-አባይት እንደሌሉ ሲካዱ /ሲሻገሩ/ ነው። “Law-maker Law- breaker”   እንዲል ፈረንጅም። ያስቡልኛል ያላቸው መመሪያዎችና ኃላፊዎች “አንተና አንቺ” ብለው ከናቁት፣ ያወጡትን መመሪያዎች በሱው ላይ መጠቀሚያ ካደረጓቸው፣ በግልፅ ወገናዊነት “ሁሉም ህዝቦች እኩል ናቸው። አንዳንዶቹ ግን የበለጠ እኩል ናቸው” ካሉት፣ አዋጅም፣ ህግም፣ መመሪያም እንደ ብዙዎቹ ተግባር-አልባ የፕሮጀክት ጥናቶች ያማሩ ወረቀቶች ሆነው ነው የሚቀሩት።
እቅድ በስራ ላይ መዋሉን ለማየት በሚል “የግምገማ” ስብሰባ፣ ጥንት የሚታወቀው “ድርጅታዊ አሰራር” ከተንፀባረቀ፣ “በእኔ አስተያየት” በሚል የጠግል ካባ ቡድናዊ ስሜት የሚስተጋባ ከሆነ፣ አመራርና ተመሪ መራረቁ የማይቀር አባዜ ይሆናል። ህዝቡን በግማገማ ማረቅ አይቻልም! መሪዎችንና መመሪያዎችን እንጂ! እነሱንም በጄ ካሉ! ግምገማዎችም የእውነት ከሆነ! በአንድ ወቅት ስለ ሂስና ግለ-ሂስ ሲወሳ “ሂስ እያሉ ሌላውን መዘርጠጥ፣ ግለ-ሂስ እያሉ ራስን ማዋረድ አይገባም!” ያሉ እንደነበሩ ያስታውሷል። መታረም፣ መተራረም፣ መቻል፣ መቻቻል የሚችለው ትክክለኛ ሂስ ማቅረብ ሲቻል ነው። እዚህ ጋ ድክመት አለ ተብሎ ሲጠቆም ነው። እሱም ቢሆን በጨዋ ቋንቋ ኢትዮጵያዊ ባህልና ወጉን ሳይለቅ መሆን ይኖርበታል፡፡ ሂስ የሚቀርብበትን ሰው ሳያንጓጥጡ ሃሳቡንና ጉዳዩ ላይ ብቻ በማተኮር በቀጥተኛ በማቅረብ፡፡ ህይወት “መካር- አሳስቶኝ”፣ “ፋርሽ-ባትሉኝ” የምንልበት የዕቃ -ዕቃ ጨዋታ አይደለም። መማማር ያስፈልጋል። ሆኖም ትምህርቱ መታወቅ፣ አስተማሪና ተማሪውም አስቀድሞ መለየት አለበት። ገጣሚው ኦማር ካህያም እንዳለው፤ እኔስ ማነኝሳ ቁጭ ብዬ እምማር “አንተ ማነህ እሱ የምታስተምር፣ ሳንባባል ለመቀጠልና ለመማማርም መቻቻል አለብን። አለበለዚያ አንድ አዋቂ የሀገራችን ፀሐፌ- ተውኔት ባንደኛው ቴያትራቸው ውስጥ እንደፃፉት ይሆናል። አንዱ ገፀ-ባህሪ
“ምነው ተጠፋፋን ጓድ”  ሲል ይጠይቀዋል፡፡ ጓዱም ሲመለስ፤ “የአብዮት ጊዜ አይደለም እንዴ? መጠፋፋት መች ገደደ?!” ነበር ያለው፡፡ ይህን መሰል የፖለቲካ ሰዎች ፈሊጥ ህዝቡ ውስጥ እንዲገባ መደረግ የለበትም፡፡ ሕዝቦች እንዲኖሩ እንጂ እንዲጠፋፉ፣ እንዲቻቻሉ እንጂ፣ እንዲናቆሩ መሆን የለባቸውም፡፡ ቅን ልቦና፣ ፅናትና ለሀገር ማስበ ሲኖር መቻቻል ይቻላል፡፡ መሪዎችና የፖለቲካ ድርጅቶችም ቢሆኑ መቻቻል ይችላሉ። ዋናው፤ “ለብቻዬ ስንጥር ከምሆን ከሀገር ጋር እርፍ ልሁን!” ማለት ብቻ ነው፡፡ አለበለዚያ “ህገ ወጥ አደን” ከሚል ማስታወቂያ በኋላ “አተረማመሰው” ይዘፍናሉ እንደተባለው ይሆንብናል፡፡


በጃፓንም አዲስ የቫይረሱ ዝርያ ተገኝቷል

            ከመደበኛው የኮሮና ቫይረስ ጋር ሲነጻጸር በፍጥነት የመሰራጨት አቅማቸው ከፍተኛ እንደሆነ የተነገረላቸውና በብሪታኒያ እና በደቡብ አፍሪካ የተገኙት አዳዲሶቹ የኮሮና ቫይረስ ዝርያዎች በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ በድምሩ ከ50 በላይ ወደሚሆኑ የአለማችን አገራት መሰራጨታቸውን እንዲሁም በጃፓን ደግሞ አዲስ የቫይረሱ ዝርያ መገኘቱን የአለም የጤና ድርጅት አስታውቋል፡፡
ከአንድ ወር በፊት በብሪታኒያ የተገኘው አዲሱ የኮሮና ቫይረስ ዝርያ ወደ 50 የተለያዩ የአለማችን አገራትና ግዛቶች መዛመቱንና በደቡብ አፍሪካ የተገኘው የኮሮና ቫይረስ ዝርያ ደግሞ ወደ 20 አገራትና ግዛቶች መሰራጨቱን ድርጅቱ ባለፈው ማክሰኞ ባወጣው መረጃ አስታውቋል፡፡
አዳዲሶቹ የኮሮና ቫይረስ ዝርያዎች ከ70 በላይ አገራትና ግዛቶች ተሰራጭተዋል ተብሎ እንደሚገመት የጠቆመው የአለም የጤና ድርጅት፤ ባለፈው ሳምንት በጃፓን በአዲስ የኮሮና ቫይረስ የተጠቁ 4 ብራዚላውያን መንገደኞች መገኘታቸውንና በቀጣይም አዳዲስ የቫይረሱ ዝርያዎች ሊፈጠሩ እንደሚችሉና አለማችን በአዲስ የኮሮና ወረርሽኝ ማዕበል ልትመታ እንደምትችልም ስጋቱን ገልጧል፡፡
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ አሁንም በመላው አለም በፍጥነት መሰራጨቱን እንደቀጠለ የገለጸው ድርጅቱ፤ አለማቀፉ የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር ባለፉት 10 ሳምንታት ብቻ በእጥፍ በማደግ ከቀናት በፊት ከ90 ሚሊዮን ማለፉንና የሟቾች ቁጥርም ወደ 2 ሚሊዮን መጠጋቱን አስታውሷል፡፡
በሌላ የኮሮና ቫይረስ ዜና ደግሞ፣ ከ3 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በቫይረሱ ለተጠቁባት አፍሪካ 300 ሚሊዮን የኮሮና ቫይረስ ክትባቶችን ከአለማቀፉ የክትባት ጥምረት መገኘቱንና ክትባቶቹ በሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ ለተለያዩ አገራት ይከፋፈላል ተብሎ እንደሚጠበቅ የአፍሪካ የበሽታዎች ቁጥጥርና መከላከል ማዕከል እንዳስታወቀ አሶሼትድ ፕሬስ አስነብቧል፡:፡
በአፍሪካ ከሚኖረው አጠቃላይ ህዝብ 60 በመቶውን ወይም 780 ሚሊዮን ሰዎችን ለመከተብ መታቀዱንና ለዚህም 10 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ 1.5 ቢሊዮን ያህል ክትባቶች እንደሚያስፈልጉም ዘገባው አመልክቷል፡፡


 በጋዛ ከአየር ላይ ውሃ መስራት ተችሏል

            የሲንጋፖር ናሽናል ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች፣ ከሰው ልጆች ሰውነት ከሚወጣው ላብ፣ የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጨት የሚያስችል አዲስ የምርምር ውጤት ማግኘታቸውን አስታውቀዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው ተመራማሪዎች ይፋ ያደረጉትን መረጃ ጠቅሶ የአገሪቱ መንግስት ድረገጽ እንደዘገበው፣ አዲሱ የምርምር ውጤት ከሰውነት የሚመነጨውን ላብ በመምጠጥ በአዲስ ዘዴ የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጨት የሚያስችል ነው፡፡
የምርምር ግኝቱ በቤተ ሙከራ ውስጥ ውጤታማ እንደሆነ ቢረጋገጥም፣ በስፋት ስራ ላይ የሚውልበት ጊዜ በግልጽ አለመነገሩን የጠቆመው ዘገባው፣ በአዲሱ መንገድ የሚመነጨው ሃይል ግን አነስተኛ እንደሚሆን መነገሩን አክሎ ገልጧል፡፡
በሌላ ሳይንሳዊ ዘገባ ደግሞ፣ በፍልስጤሟ የጋዛ ግዛት ውስጥ በተጀመረ አንድ ፕሮጀክት በጻሃይ ብርሃን ሃይል በመጠቀም ከአየር ላይ እርጥበትን በቀጥታ በመምጠጥ ጥራቱን የጠበቀ የመጠጥ ውሃ ማምረት መቻሉን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ከሰሞኑ ባወጣው ዘገባ አስነብቧል፡፡
ማይክል ሚሪላሺቪ የተባሉት ሩስያ እስራኤላዊው ቢሊየነር ያቋቋሙት ዋተርጂን የተባለ ኩባንያ፣ በጋዛ ያለውን ስር የሰደደ የመጠጥ ውሃ እጥረት ለመቀነስ በማሰብ የጀመረው ይህ ፕሮጀክት፣ በሳይንሳዊ መንገድ ከአየር ላይ በየዕለቱ እስከ 6 ሺህ ሊትር የሚደርስ የመጠጥ ውሃ ለማምረት የሚያስችል እንደሆነ ዘገባው አመልክቷል፡፡
ኩባንያው በአዲስ መልኩ የመጠጥ ውሃ የሚያመርቱ እያንዳንዳቸው 61 ሺህ ዶላር የሚያወጡ ማሽኖችን ለጋዛ ከተማ በስጦታ መልክ ማበርከቱንና ማህበረሰቡ የውሃ ተጠቃሚ መሆኑንም ዘገባው ጠቁሟል፡፡


 የደቡብ ኮርያ የህዝብ ቁጥር በተጠናቀቀው የፈረንጆች አመት 2020 በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ መቀነስ ማሳየቱና ብሔራዊው የውልደት መጠን ከሞት መጠን በእጅጉ ማነሱ ያሳሰበው የአገሪቱ መንግስት፣ ብዛት ያላቸው ልጆችን ለሚወልዱ የአገሪቱ ዜጎች የገንዘብ ሽልማት እንደሚሰጥ ማስታወቁን አናዶሉ ኤጀንሲ ዘግቧል፡፡
የአገሪቱ መንግስት ዜጎች ከመጪው የፈረንጆች አመት 2022 ጀምሮ በሚወልዱት አንድ ልጅ በየወሩ 275 ዶላር ያህል የማበረታቻ የገንዘብ ሽልማት እንደሚሰጣቸው ማስታወቁን የጠቆመው ዘገባው፣ ለነፍሰጡር እናቶችም የቅድመ ወሊድ ወጪያቸውን ለመሸፈን የሚውል የ1 ሺህ 827 ዶላር ገንዘብ ድጋፍ እንደሚያደርግና በየወሩ የሚሰጠው የገንዘብ ድጋፍ  ከ2025 ጀምሮ ወደ 457 ዶላር እንደሚያድግ ቃል መግባቱንም አክሎ ገልጧል፡፡
መንግስት ወሊድን ለማበረታታት አስቦ ባረቀቀው በአዲስ ፕሮግራሙ፣ ወላጆች ልጃቸው አንድ አመት እስኪሞላው ድረስ ለሶስት ወራት የሚቆይ የስራ ዕረፍት ሲወስዱ እያንዳንዳቸው በየወሩ እስከ 2 ሺህ 741 ዶላር የሚደርስ ደመወዝ እንዲከፈላቸው የሚያደርግ መሆኑም ተነግሯል፡፡
በአገሪቱ ባለፈው አመት የተወለዱት ህጻናት 275 ሺህ 800 መሆናቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ ይህ ቁጥር ከ2019 ጋር ሲነጻጸር በ10 በመቶ ያህል የሚያንስ ሲሆን በ2020 ከዚህ አለም በሞት የተለዩት ዜጎች ቁጥር ግን 307 ሺህ 764 እንደነበርና ይህም የአገሪቱን መንግስት በቀጣይ አገር ተረካቢ ትውልድ ይጠፋል የሚል ከፍተኛ ስጋት ውስጥ እንደጣለው አመልክቷል፡፡
የአገሪቱ መንግስት ከዚህ ቀደም ተግባራዊ ባደረገው የማበረታቻ ፕሮግራም አንድ ህጻን ዕድሜው 7 አመት እስኪሞላው ድረስ በየወሩ 91 ዶላር የማበረታቻ አበል ለቤተሰቡ ሲሰጥ መቆየቱንም ዘገባው አስታውሷል፡፡
በሌላ ወሊድ ተኮር ዜና ደግሞ፣ በአዲሱ የፈረንጆች አመት 2021 የመጀመሪያዋ ዕለት በመላው አለም 372 ሺህ ህጻናት መወለዳቸውንና በዕለቱ 60 ሺህ ያህል ህጻናት የተወለዱባት ህንድ ከአለማችን አገራት ብዙ ህጻናት የተወለዱባት ቀዳሚዋ አገር መሆኗን ተመድ አስታውቋል፡፡ የተባበሩት መንግስታት የህጻናት መርጃ ድርጅት ዩኒሴፍ ከሰሞኑ ባወጣው መረጃ እንዳለው፣ በአዲሱ የፈረንጆች አመት በመላው አለም 140 ሚሊዮን ያህል ህጻናት ይወለዳሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

 በተጠናቀቀው የፈረንጆች አመት 2020 አለማቀፍ የላፕቶፕና ዴስክቶፕ ኮምፒውተሮች ሽያጭ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩንና ለዚህም በምክንያትነት የተጠቀሰው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መሆኑን ፎክስ ኒውስ ዘግቧል፡፡
በአለም ዙሪያ ከኮሮና ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ በቤታቸው ውስጥ ሆነው በኮምፒውተር የሚሰሩ ሰራተኞችና ተማሪዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ከመጨመሩ ጋር በተያያዘ በ2020 በመላው አለም 300 ሚሊዮን ያህል ላፕቶፕና ዴስክቶፕ ኮምፒውተሮች መሸጣቸውን የጠቆመው ዘገባው፣  አመታዊው አለማቀፍ የላፕቶፕና ዴስክቶፕ ኮምፒውተሮች ሽያጭ ካለፈው አመት ጋር ሲነጻጸር በ15 በመቶ ያህል ማደጉንም አመልክቷል፡፡
በመላው አለም ጥቅም ላይ የሚውሉ ላፕቶፖችና ዴስክቶፕ ኮምፒውተሮች አጠቃላይ ቁጥር በቀጣዩ የፈረንጆች አመት 1.77 ቢሊዮን ይደርሳል ተብሎ እንደሚጠበቅ ካናሊስ የተባለው የጥናት ተቋም ባወጣው መረጃ መግለጹንም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡

 (የኬኒ ሮጀርስ የዘፈን ግጥም እንደ አጭር ልብወለድ)


              ሰው ሁሉ “ቦቅቧቃው” ይለዋል። እሱ ግን አንድም ቀን እንኳ አንገቱን ቀና አድርጎ አይደለሁም ብሎ ለማስተባበል ሞክሮ አያውቅም። እናቱ ያወጣችለት ስም ቶሚ ነው። የመንደሩ ሰው ግን “ቦቅቧቃው” በሚል የቅፅል ስም ይጠራዋል። እኔ መቼም የሰፈሩ  ሰው ለቶሚ የሰጠው ግምት ትክክል አለመሆኑ ይታወቀኛል።
አባቱ እስር ቤት ውስጥ ሲሞት እሱ ገና የአስር ዓመት ልጅ ነበር። የወንድሜ ልጅ ነውና ከዚያ ወዲህ በአደራ ቶሚን የማሳድገው እኔ ነኝ። ወንድሜ በአልጋ ጣር ላይ ሳለ፣ ለቶሚ የነገረው ነገር አሁንም ትዝ ይለኛል።
“ልጄ ሆይ፤ የእኔ ኑሮ እነሆ አበቃ፣ የአንተ ግን ገና መጀመሩ ነው። ስለዚህ ቃል ግባልኝ። መከራን መሸሽ ከቻልክ ሽሸው። ማምለጥ እየቻልክ ቆመህ አትጠብቀው፣ አንደኛውን ጉንጭህን ሲመቱህ ሌላኛውን ጉንጭህን ብትሰጥ ደካማ ነህ ማለት አይደለም። በዚህ ዕድሜህ መቼም ይህንን መረዳት አያቅትህም። አየህ ልጄ፤ ሰው ለመሆን የግድ  መታገል፣ የግድ  መጋፈጥ የለብህም፡፡"
ሁሉም ሰው የምትሆነውን ሴት ማፍቀሩ ያለ ነገር ነው። ቶሚም ቤኪን በጣም ያፈቅራታል። በእቅፏ ውስጥ በገባ ጊዜም ወንድ መሆኑን ማረጋገጥ አላስፈለገውም፡፡
አንድ ቀን የጋትሊን መንደር ልጆች ሶስት ሆነው እየተፈራረቁ ቤኪን ይሰድቧታል። ይባስም ብለው ይደበድቧታል - ጠግበዋል።
ቶሚ በሥራ ገበታው ላይ ነበር። ድንገት ድምጽ ሰምቶ ብቅ ብሎ ቢያስተውል የሱዋ ቤኪ ናት። ተደብድባለች፣ ታለቅሳለች። የተቀዳደደ ቀሚሷና የተመሰቃቀለ ሁኔታዋ ሩህሩህ ልቡ ከሚችለው በላይ አሰቃቂ ሆነበት።
ወደ ቤት ተመልሶ ገባ። ድንገት ዞሮ ከእሳቱ ማንደጃ ቦታ ላይ የነበረውን ያባቱን ፎቶግራፍ አየ። አነሳው። እያለቀሰም ተመለከተው። በእንባው ፊቱ እስኪታጠብ ድረስ ሲያስተውለው ከቆየ በኋላ በመጨረሻዋ እስትንፋሱ የመከረው ምክር ዳግም ጆሮው ላይ ደወለበት።
“…አንደኛውን ጉንጭህን ቢመቱህ እንኳ ሌላኛውን ጉንጭህን ብትሰጥ ደካማ ነህ ማለት አይደለም… አየህ ልጄ ሰው ለመሆን የግድ መታገል የለብህም።"
ቶሚ ቆጣ ብሎ ወደ ቡና ቤቱ መጣ። የጋትሊን ልጆችም በማንጓጠጥ ሳቁበት። ከመሃላቸውም አንዱ ተነሳና ወለሉን ማህል ለማህል አቋርጦ ወደሱ መጣ። ቶሚ ከዚያ ቦታ ዘወር እንደ ማለት ቃጥቶት ነበር።
“እዩት ይሄን ቦቅቧቃ ፈርቶ ሲሸሽ ተመልከቱ እንግዲህ…” ለከፋቸውንና ስድባቸውን ቀጠሉ። አላገጡበት።
ይሄኔ ቶሚ ትዕግስቱ ተሟጦ አለቀ። ደረቱን በሀሞተ- ሙሉነት ነፍቶ፣  በሩን በግዙፍ  ሰውነቱ ሞልቶ ቆመ። ማን ወንድ ይለፈው! ይሄኔ አካባቢው ሁሉ ፀጥ እርጭ አለ። ከዝምታው ጥልቀት የተነሳ እስፒል እንኳ ብትወድቅ ትሰማ ነበር። ሃያ ዓመት ሙሉ በችግር እየማቀቀ፣ እየዳኸ ያሳለፈው ሕይወቱ፣ በቡሽ እንደተከደነ ጠርሙስ ልቡ ውስጥ በጥንቃቄ ታሽጓል።
ድንገት ያ የልቡ ማሸጊያ ቡሽ ከመቅፅበት ተፈናጥሮ ተከፈተ። እልሁና ቁጣው እንደ ሻምፓኝ ገነፈለ። መቼ ገባ ሳይባል ተወንጭፎ ጠብ ውስጥ ጥልቅ አለ። ያለ የሌለ ጉልበቱን ሳይቆጥብ ይሰነዝርባቸው ጀመር። እያንዳንዳቸውን በቡጢ ማንጋጭል- ማንጋጭሊያቸውን እያለ እየቦቀሰ ዘረራቸው። አንድም የጋትሊን ልጅ ፊቱ ቆሞ አይታይም። ሁሏም ተራ በተራ ምሷን ቀመሰች።
የመጨረሻውን ልጅ መትቶ ሲጥል፣
“ይሄኛው ለቤኪዬ ማስታወሻ ይሁን; አለና ቡና ቤቱን በኩራት ለቅቆ ወጣ።
ወዲያው እንዲህ ሲል ሰማሁት፣
“አባባ አንተ ያጠፋኸውን ዓይነት ጥፋት እንዳልደግም ቃል አስገብተኸኝ ነበር። እነሆ መከራን የቻልኩትን ያህል ሸሸሁ። ከእንግዲህ እኔን ደካማ ነው ብለህ እንዳታስብ። ቀኜን ሲመቱኝም በፍፁም ግራዬን አልሰጠሁም። እንግዲህ አባባ፣ ሰው ሆኖ አንዳንድ ጊዜ መታገልና መጋፈጥ እንደሚያስፈልግ አሁን እንደገባህ በፅኑ ተስፋ አደርጋለሁ።”

Thursday, 14 January 2021 11:41

የወግ ጥግ

 ንግሥት ዘውዲቱ ደብረ ብርሃን በአንድ ገዳም አንድ  ካህን ሾሙ። ያ ካህን ባሪያ ኖሯል። ስለዚህም ካህናቱ አልወደዱትም። በዚያ ላይ የተለመደውን የካህናቱን ግብር ሳያበላ ቀረና ንግስት ዘንድ ከሰሱት- ካህናቱ ተቆጥተው ማለት ነው። ችሎት ቀረቡ ተካሰው።
ንግሥትም- “አንተ፣ ምን ሆነህ ነው የተለመደ ግብራቸውን ሳታበላቸው የቀረኸው?” አሉና ጠየቁት።
ካህኑም- “ንግሥት ሆይ፤ እኔ ለስንት ጅብ ላበላ ነው?!!" አለና መለሰ
ይሄኔ- ከካህናቱ አንዱ፡-
“እንግዲያውስ ንግሥት ሆይ፤ ይህ ካህን ይነሳልን። ለነገሩ አንድ አህያስ ለስንት ጅቦች ሊሆነን ነው? ይነሳልን!”
ማስታወሻ፡- አህያ ነው ያሉት ባሪያ ነው ለማለትም ነው፤ በዚያ ዘመን ቋንቋ፡፡


Page 7 of 516