Administrator

Administrator

    ግሪን ኮፊ አግሮ ኢንዱስትሪ፤ የመንግሥት ይዞታ የነበረውን የቴፒ ቡና ተክል ልማት ድርጅት በ1 ቢ. ብር  ጠቅልሎ መግዛቱን አስታወቀ፡፡
ትናንት ረፋድ ላይ በሂልተን ሆቴል በተደረገው የሽ    ያጭ ውል ስምምነት፣ የፕራይቬታይዜሽንና የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ በየነ ገ/መስቀልና የግሪን ኮፊ አግሮ ኢንዱስትሪ ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ አቶ ታደለ አብርሃ ውሉን ተፈራርመዋል፡፡
አቶ ታደለ በተለይ ለአዲስ አድማስ እንደገለጹት፣ ግሪን ኮፊ ከሁለት ዓመት ተኩል በፊት የቴፒ ቡና ተክል ልማት ድርጅትን ድርሻ 51 በመቶ በመያዝ፣ መንግሥት ደግሞ ቀሪውን 49 በመቶ ይዞ በሽርክና ለመሥራት ተስማምተው እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ 12 ሺህ ሄክታር ስፋት ያለውን የእርሻ ልማት፣ በ1 ቢሊዮን ብር እንደገለፁት አቶ ታደለ፤ የፊርማ ሥነ - ሥርዓቱ የተፈፀመው የዋጋውን 35 በመቶ፣ 265 ሚሊዮን ብር ባንክ አስገብተው ሲሆን ቀሪውን 65 በመቶ በ5 ዓመት ውስጥ ከፍለው ለማጠናቀቅ መስማማታቸውንም አስረድተዋል፡፡
12ቱ ሺህ ሄክታር መሬት ባረጁ የቡና ዛፎች የተሸፈነ ስለሆነ፣ ከ8-9 ሄክታሩን የተሻለ ምርት በሚሰጡ አዳዲስ ዝርያዎች መተካቱን ጠቁመው፣ ቀሪውም በየዓመቱ 1000 ያህል ሄክታር በአዲስ ምርታማ ዝርያ ይተካል ብለዋል፡፡ ከእርሻ ልማቱ አጠገብ የጋምቤላ ክልል ይዞታ የሆነውን 3ሺህ ሄክታር መሬት ክልሉን ጠይቀው ስለፈቀደላቸው አዲስ ፕሮጀክት ቀርፀው እንደሚያለሙትም አቶ ታደለ አክለው ገልፀዋል፡፡
ከእርሻው የሚገኘውን የቡና ምርት ኤክስፖርት በማድረግ 20 ሚሊዮን ዶላር እንደሚገኝ የጠቀሱት ባለሀብቱ፤ እርሻው ለማር ምርት አመቺ በመሆኑ በዓለም ተወዳጅ የሆነውን ኮፊ ሀኒ የተባለ የማር ዓይነት በአነስተኛ መሳሪያ እያዘጋጁ ወደ ውጭ ሲልኩ ቆይተዋል፡፡ አሁን በብዛት (50 እና 60 ኮንቴይነር ኮፊ ሀኒ) ወደ ውጭ በመላክ ከ4-5 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት ፋብሪካ እየገነቡ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
የቴፒ ቡና እርሻ ልማት በረከት ይህ ብቻ አይደለም፡፡ የተለያዩ ቅመማ ቅመሞች እያመረቱ ለመላክ አቅደዋል፡፡ ብዙም ባይሆን በኢትዮጵያ ውስጥ ፓልም ኦይል የሚገኘው በቴፒ እርሻ ልማት ብቻ እንደሆነ የጠቀሱት አቶ ታደለ፤ ለሙከራ ከማሌዢያና ኢንዶኔዢያ የተለያየ ዝርያ አምጥተው በ120 ሄክታር መሬት ላይ በመትከል ምርቱ ደርሶ አይተውታል፡፡ በአነስተኛ መሳሪያ እያዘጋጁ በየወሩ አንድ መኪና ዘይት ለተለያዩ ድርጅቶች የሚያቀርቡ ሲሆን፤ ወደ ዘይት ከመለወጡ በፊት ያለውን ድፍድፍ፣ የሳሙና ፋብሪካዎች በጥሩ ዋጋ በሰልፍ እንደሚገዙና በየወሩ አንድ መኪና ድፍድፍ እንደሚሸጡ ተናግረዋል፡፡ የፓልም እርሻውን ወደ 10,000 ሄክታር ለማሳደግ የገንዘብ ድጋፍ የሚያደርግ ኩባንያ ማግኘታቸውን ጠቅሰው፣ የእርሻ መሬት ለማግኘት ከክልሉ ጋር እየተነጋገሩ መሆኑንም አቶ ታደለ ገልፀዋል፡፡
በቴፒ እርሻ ልማት ውስጥ ባሉ 6 እርሻዎች፣ 16ሺ ሰራተኞች ተቀጥረው እንደሚሰሩ ለማወቅ ተችሏል፡፡

Saturday, 08 August 2015 09:38

የዘላለም ጥግ

(ስለ ስኬት)
ውድቀት አማራጭ አይደለም፡፡ ሁሉም ሰው ስኬትን መቀዳጀት አለበት፡፡
አርኖልድ ሽዋዚንገር
ያለ አንተ ይሁንታ ማንም ሰው የበታችነት ስሜት እንዲሰማህ ማድረግ አይችልም፡፡
ኢሊኖር ሩስቬልት
ስኬት የዕድል ጉዳይ ነው፡፡  ያልተሳካለትን ማንኛውንም ሰው ጠይቁ፡፡
ኢርል ዊልሰን
አሸናፊው ሽንፈትን ይፈራል፡፡ የተቀረው ደግሞ ማሸነፍን ይፈራል፡፡
ቢሊ ዣን ኪንግ
ውድቀት በራሱ ከተማርንበት ስኬት ነው፡፡
ማልኮም ፎርብስ
የስኬት ምስጢሩ ሃቀኝነት ነው፡፡
ዣን ጊራውዶክስ
ተፈጥሮአችን ነው፡- የሰው ልጆች ስንባል ስኬትን እንወዳለን፤ ስኬታማ ሰዎች ግን እንጠላለን፡፡
ካሮት ቶፕ
ስኬትን መቀዳጀቴ ብቻ በቂ አይደለም - ሌሎች መውደቅ አለባቸው፡፡
ዴቪድ ሜሪክ
ስኬት ሁሉንም ነገር አይደለም፤ ነገር ግን ሰውን ቀጥ ብሎ እንዲቆም ያደርገዋል፡፡
ሊሊያን ሄልማን
ስኬት ምንም ምስጢር የለውም፡፡ የዝግጅት፣ ተግቶ የመስራትና ከውድቀት የመማር ውጤት ነው፡፡
ኮሊን ፓውል
ህልሞችህን ገንባ፤ ያለበለዚያ ሌሎች ህልማቸውን እንድትገነባላቸው ይቀጥሩሃል፡፡
ፋራህ ግሬይ
ህይወት ራስህን የመፈለግ ጉዳይ አይደለም፤ ራስህን መፍጠር ነው፡፡
ጆርጅ በርናርድ ሾው
ደስታ ሁልጊዜ ክፍት እንደነበር ባላሰብከው በር ያጮልቃል፡፡
ያልታወቀ ሰው

Saturday, 08 August 2015 09:33

የግጥም ጥግ

 ላንቺ
(በ.ሥ)
እንዳገው ጃንጥላ፤ ሰማይ ተሽከርክሮ
እንደ ጎፋ ፈረስ፤ መሬቱ ደንብሮ
ሁሉ ሲያዳልጠኝ
ሁሉ ሲያዳክመኝ
ቀሚስሽን ይዤ፤ መትረፌ ገረመኝ፡፡

ኤልሻዳይ ምኞት
(በ.ሥ)
እንደ ድሮ ቀሚስ፤ መሬት እየጠረግሁ
ኮቴሽን ምድር ላይ፤ ተግቸ እየፈለግሁ
እንደ ጉም
ሳዘግም
እንደ ሰርዶ ስሳብ
ባካል ብታመልጭኝ፤ ደረስኩብሽ ባሳብ
መች ሊያግደኝ በሩ፤ መች ሊገታኝ መስኮት
በዝግ በርሽ ገባሁ፤ ልክ እንደ መለኮት
ላንዲት መስቲካ ሻጭ ህጻን
(በ.ሥ)
በደብተርሽ ምትክ
ትንሽ ሱቅ ታቅፈሽ
ካልፎሂያጅ እግር ስር፤ እንደ ድንቢጥ ከንፈሽ
ጋሼ ግዙኝ ስትይ፤ ኣንጋጠሽ ወደ ላይ
ለጉድ ተጎልቸ፤ ምታረጊውን ሳይ
ራሴስ ይታመም፤ ምላሴን ምን ነካው
ግራዋ ይመስል፤ መረረኝ ማስቲካው፡፡
ኣፈር ጠጠር ለብሶ፤ በዶዘር ተድጦ
መስኩ ከነጎርፉ
ሰማይ ከነዶፉ
ለጌቶች ተሽጦ
ኣተር ነው እያሉ፤ ኣፈር ዘግኖ መፍጨት
ገነት ነው እያሉ፤ መስክ ላይ መፈንጨት
ጠበል ነው እያሉ፤ ተጎርፉ መራጨት
ይህንን ማን ሰጦሽ
ገና በልጅነት፤ ልጅነት ኣምልጦሽ፡፡
በምቢልታ በዋሽንት፤ በከበሮ ታጥሮ
በክራር ተማግሮ
በቆመ ከተማ
እምባሽ ቅኝት የለው፤ ለሰው ኣይሰማ፡
ጠዋት የፎከረ፤ ቀትር ላይ ሲረታ
ዛሬ ዝሎ ሲወድቅ፤ ትናንት የበረታ
ኑሮን ያህል ሸክም፤ ያላንቀልባ ሲያዝል፡፡
ምን ጸጋ ለብሶ ነው፤ ትከሻሽ የማይዝል፡፡

በዳንኤል ተገኝ ተደርሶ በአለምፀሐይ በቀለ ዳይሬክት የተደረገውና በዳኒሮጐ ማስታወቂያና ፊልም ፕሮዳክሽን የቀረበው “የሴም ወርቅ” የተሰኘ ፊልም ባለፈው ሰኞ ምሽት በቀይ ምንጣፍ ሥነስርዓት ተመረቀ፡፡
የ1፡45 ደቂቃ ርዝማኔ ያለውን ፊልም ሰርቶ ለማጠናቀቅ 2 ዓመት ያህል የፈጀ ሲሆን 1.5 ሚ. ብር እንደወጣበት አዘጋጆቹ ጠቁመዋል፡፡ በዚህ ልብ አንጠልጣይ የቤተሰብ የፍቅር ፊልም ላይ አርቲስት ፍቃዱ ተ/ማርያም፣ አምለሰት ሙጬ፣ ዳንኤል ተገኝ፣ ሙሉ ሰለሞን፣ ዝናህብዙ ፀጋዬ እና ሌሎች አንጋፋና ወጣት ተዋንያን ተሳትፈውበታል ተብሏል፡፡
በምረቃ ስነ ስርአቱ ላይ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሩ አቶ አሚን አብዱል ቃድርን ጨምሮ አርቲስት አበበ ተስፋዬ (ፋዘር) እና ሌሎችም ታዋቂ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች የተገኙ ሲሆን ሚኒስትሩ ፊልሙን ከተመለከቱ በኋላ በሰጡት አስተያየት፤“በጣም ደረጃውን የጠበቀ የአገራችንን ገፅታ የሚያሳይ ፊልም ነው” ሲሉ ማድነቃቸውን አዘጋጆቹ ለአዲስ አድማስ ጠቁመዋል፡፡
የፊልሙ 70 ከመቶ ቀረጻ የተካሄደው በባህር ዳር እና ጎንደር ከተሞች ላይ ሲሆን ቀሪው አዲስ አበባ መቀረጹን ለማወቅ ተችሏል፡፡ በፊልሙ ላይ ከዕውቅ ተዋናዮች ባሻገር የዳሽን ቢራ ሰራተኞችን ጨምሮ ከ100 በላይ የሚሆኑ ሰዎች መሳተፋቸውን የጠቆመው የፊልሙ ደራሲና ፕሮዱዩሰር አርቲስት ዳንኤል ተገኝ፤ዳሽን ቢራ ለፊልሙ ከ1.3 ሚሊዮን ብር በላይ ስፖንሰር ማድረጉን ገልጿል፡፡
ዳሽን ቢራ ፊልሙ ለተመልካች እንዲበቃ ላደረገው ድጋፍ፣ታዋቂ አርቲስቶችና የውጭ ሃገር ዜጎች የተሳተፉበት ማስታወቂያ ሰርተው ለፋብሪካው በስጦታ ማበርከታቸውን አርቲስቱ ተናግሯል፡፡ ባለፈው ሰኞ በፊልሙ ምረቃ ላይ የታደሙ አንዳንድ ተመልካቾች፤ፊልሙ የዳሽን ማስታወቂያ ይመስላል የሚል ትችት የሰነዘሩ ሲሆን በብስጭት ፊልሙ ከመጠናቀቁ በፊት ጥለው የወጡ እንደነበሩም ለማወቅ ተችሏል፡፡ አርቲስት ዳንኤል፤ ስፖንሰር አድራጊውን የዳሽን ቢራ ፋብሪካን በፊልሙ ውስጥ ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ ለማስተዋወቅ መሞከሩን አልካደም፡፡ ነገር ግን መላ ፊልሙ የዳሽን ቢራ ማስታወቂያን ይመስላል የሚያሰኝ አይደለም ብሏል፡፡   
 #የሴም ወርቅ” በአዲስ አበባ በሚገኙ ሲኒማ ቤቶች በሙሉ በመታየት ላይ መሆኑን የጠቆሙት አዘጋጆቹ፤በባህር ዳር እና በጎንደር ባለፈው ረቡዕ እና ሐሙስ መመረቁን አክለው ገልጸዋል፡፡  

የደራሲ ኻሊድ ሆሴኒ “A Thousand Splendid Sun” የተሰኘው ልቦለድ በአያልቅበት አደም “ዶስቲ” በሚል ርዕስ ወደ አማርኛ የተተረጐመ ሲሆን በቅርቡ ለንባብ እንደሚበቃ ተርጓሚው ለአዲስ አድማስ ጠቁሟል፡፡
ኻሊድ ሆሴኒ ይበልጥ የሚታወቀው “The Kite Runner” በተሰኘ የበኩር ሥራው ሲሆን አሁን ወደ አማርኛ የተተረጎመው ሁለተኛው ሥራው ነው ተብሏል፡፡ በ361 ገፆች የተቀነበበው “ዶስቲ”፤በ80 ብር ለገበያ እንደሚቀርብ ለማወቅ ተችሏል፡፡

የሰዓሊና ገጣሚ ገብረክርስቶስ ደስታ “መንገድ ስጡኝ ሰፊ” የተሰኘ የግጥም መድበል ላይ በነገው ዕለት ከቀኑ 8 ሰዓት ጀምሮ በብሄራዊ ቤተ መፃህፍትና ቤተ መዛግብት ኤጀንሲ አዳራሽ ውይይት እንደሚካሄድበት ሚዩዚክ ሜይዴይ ኢትዮጵያ አስታወቀ፡፡
ለውይይቱ መነሻ ሃሳብ የሚያቀርቡት ገጣሚና ጋዜጠኛ ባንችአየሁ ዓለሙ ሲሆኑ የጥበብ ወዳጆች በውይይቱ ላይ እንደሚታደሙ ሚዩዚክ ሜይዴይ ጥሪውን አስተላልፏል፡፡
በሌላ በኩል የደራሲ ገዛኸኝ ላቀው “የደቦቃ ጥንስስ” የተሰኘ መፅሀፍ በነገው ዕለት ከጠዋቱ 3 ሰዓት የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች በሚገኙበት በዚያው በብሄራዊ ቤተ መፃህፍትና ቤተ መዛግብት ኤጀንሲ አዳራሽ እንደሚመረቅ የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ገልጿል፡፡  

“ወጣትነት የኪነ ጥበብ፣የማነቃቂያና የፈጠራ ማሳያ ዝግጅት; በሚል መሪ ቃል በዛሬው ዕለት ከቀኑ 10፡30 ጀምሮ በአክሱም ሆቴል የሥነ ፅሁፍ ዝግጅት ይቀርባል።  
በፕሮግራሙ ላይ ግጥሞችና ወጎች እንዲሁም በወጣቶች የተዘጋጁ ወጣቱን የሚያነቃቁ ስራዎች እንደሚቀርቡ ታውቋል፡፡ ፕሮግራሙ የተዘጋጀው ለመጀመሪያ ጊዜ ሲሆን በዋናነትም ወጣቱን ለማስተማርና ለማዝናናት ያለመ ነው ተብሏል፡፡  

Saturday, 08 August 2015 09:20

የፀሐፍት ጥግ

(ስለጨለምተኝነት)
- ወጣት ጨለምተኛን እንደማየት አሳዛኝ
ነገር የለም፡፡
ማርክ ትዌይን
- ለጨለምተኛ ሃውልት ቆሞለት አይቼ
አላውቅም፡፡
ፖል ሃርቬይ
- ጨለምተኛ ማለት እውነትን ያለጊዜው
የሚናገር ሰው ነው፡፡
ሲራኖ ዲ በርግራክ
- ሙሉ በሙሉ ጨለምተኛ ነኝ ብዬ
አላስብም፡፡ ስለዚህ በሁሉም ፊልሞቼ
ውስጥ ተስፋን የምታዩ ይመስለኛል፡፡
ስፓይክ ሊ
- እኔ ራሴን እንደ ተስፈኛም ሆነ
እንደጨለምተኛ አልቆጥርም፡፡
ኒክ ቦስትሮም
- ጨርሶ ጨለምተኛ አይደለሁም፤ ነገር ግን
ተስፈኛም አልባልም፡፡
ናቴ ሎውማን
- ጨለምተኛ አንድም ጦርነት አሸንፎ
አያውቅም፡፡
አይዞንሃወር
- ዓለምን ስመለከት ጨለምተኛ ነኝ፤ ሰዎችን
ስመለከት ግን ተስፈኛ ነኝ፡፡
ካርል ሮጀርስ
- ጨለምተኝነት ወደ ደካማነት፣ ተስፈኝነት
ወደ ጥንካሬ ይመራል፡፡
ዊሊያም ጄምስ
- ተስፈኞችም ጨለምተኞችም
ለህብረተሰባችን የሚያበረክቱት አስተዋፅኦ
አለ፡፡ ተስፈኛ አውሮፕላንን ሲፈጥር፣
ጨለምተኛ ፓራሹትን ይፈጥራል፡፡
ጂ.ቢ.ስተርን
- ተስፈኛ አዲሱ ዓመት መጥባቱን ለማየት
እስከ እኩለ ሌሊት ሲጠብቅ፣ ጨለምተኛ
አሮጌው ዓመት መሰናበቱን ለማረጋገጥ
እስከ እኩለ ሌሊት ይጠብቃል፡፡
ቢል ቫውግን
- ጨለምተኝነቴ የጨለምተኞችን ሀቀኝነት
እስከመጠራጠር ድረስ ይዘልቃል፡፡
ኢድሞንድ ሮስታንድ
- ጨለምተኛ ማለት፤ ዕድል ስታንኳኳ
በኳኳታው ድምፅ የሚያማርር ሰው ነው፡፡
ኦስካር ዋይልድ
- የጨለምተኛነት መሰረቱ ፍርሃት ብቻ
ነው።
ኦስካር ዋይልድ
- ምንጊዜም ቢሆን ከጨለምተኛ ሰው
ላይ ገንዘብ ተበደሩ፤ ይከፍሉኛል ብሎ
አይጠብቅም፡፡
ያልታወቀ ደራሲ

‹‹በመዝባሪ ላይ አልደራደርም፤ እስከ መጨረሻው ከፊት ለፊት ነኝ››

    በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የአድባራቱን ሰፋፊ መሬቶችና የገቢ ማስገኛ ተቋማት እየመዘበሩ ራሳቸውን ያበለጸጉ የአስተዳደር ሓላፊዎች በሕግ እንዲጠየቁ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ መመሪያ ሰጡ፡፡
የአስተዳደር ሓላፊዎቹ የአድባራቱን ሰፋፊ መሬቶችና የንግድ ተቋማት ያለጨረታ ከገበያ ዋጋ በታች ከ15 ዓመት እስከ ዕድሜ ልክ በመዋዋል የቤተ ክርስቲያኒቱን ጥቅሞች አሳልፈው በመስጠት ራሳቸውን አበልጽገዋል- ተብሏል፡፡
ፓትርያርኩ መመሪያውን የሰጡት፣ ላለፉት ስምንት ወራት በሀገረ ስብከቱ አድባራትና አንዳንድ ገዳማት የመሬት፣ የሕንፃና የልዩ ልዩ ገቢ ማስገኛ ተቋማት ኪራይ ተመንን ሲያጣራ የቆየው ኮሚቴ ያዘጋጀው ጥናታዊ ሪፖርት ከጠቅላይ ጽ/ቤቱ የውሳኔ ሐሳብ ጋር ከትላንት በስቲያ ከቀረበላቸው በኋላ ነው፡፡
በፓትርያርኩ መመሪያ የተቋቋመው ኮሚቴው፣ በ51 አድባራት መሬት፣ ሕንፃና ሕንፃ ነክ ጉዳዮች ላይ ባካሔደው ጥናት የተጠቆሙት የመፍትሔ ሐሳቦችና በዋና ሥራ አስኪያጁ በብፁዕ አቡነ ማቴዎስ ሰብሳቢነት የሚመራው የአስተዳደር ጉባኤ የተስማማባቸው የመፍትሔ ሐሳቦች በሙሉ ተፈጻሚ እንዲኾኑ አቡነ ማትያስ ትእዛዝ ሰጥተዋል፡፡
በጥናቱ ሒደት የኮሚቴውን አባላት በጥቅም ለመደለል ከመሞከር ጀምሮ በማስፈራራትና ስም በማጥፋት የማጣራት ሥራውን ለማስተጓጐል ሲጥሩ የነበሩ ሐላፊዎች፣ በመፍትሔው አተገባበር ላይም ዕንቅፋት ሊፈጥሩ ይችላሉ ለሚለው ስጋት ፓትርያርኩ በሰጡት ምላሽ፤ ‹‹ወደ ኋላ ወደ ጎን የለም፤ ወደፊት ነው፤ በቤተ ክርስቲያን ሀብት ምዝበራ ከማንም ጋር አልደራደርም፤ ከጎኔ ኹኑ፤ እስከ መጨረሻው ከፊት ለፊት ነኝ›› ሲሉ በቁርጠኝነት ተናግረዋል፡፡
በጥናታዊ ሪፖርቱ እንደቀረበው፤ የገቢ ማስገኛ የንግድ ተቋማቱ፣ ከአዲስ አበባ የመሬት ገበያ አንጻር ሊታሰብ ከማይችልበት ዝቅተኛው በካሬ ሜትር 0.37 ሳንቲም፣ ከፍተኛው ብር 70 ያለጨረታ ከ15 ዓመት እስከ ዕድሜ ልክ የኪራይ ውል ተፈጽሞባቸዋል፡፡ ይህም ጥቂት ሙሰኛ የደብር ሓላፊዎችና ግለሰብ ነጋዴዎች ሚልየነር እንዲኾኑበት ዕድል በመስጠት ቤተ ክርስቲያኒቱን የበይ ተመልካች እንዳደረጋት ተገልጧል፡፡
የአድባራት አለቆች፣ ጸሐፊዎች፣ ሒሳብ ሹሞችና የሰበካ ጉባኤ አባላት በተገኙበት በተካሔደው ማጣራት ለጥናት ቡድኑ መረጃ በመስጠታቸውና ጥያቄ በማንሣታቸው ከመመሪያ ውጭ ከሓላፊነታቸው የታገዱት፣ የአራዳ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ደብር ዋና ተቆጣጣሪ መጋቤ ጥበብ ወርቁ  አየለና የደብረ ጽጌ ቅዱስ ዑራኤል ቤተ ክርስቲያን ዋና ሒሳብ ሹም ወ/ሮ መና የማነ ብርሃን ሥዩም ወደ ቀድሞ የሓላፊነታቸውና ቦታቸው እንዲመለሱ በአስተዳደር ጉባኤው ተወስኗል፡፡
የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የሕግ አገልግሎት መምሪያ፤ ሙሰኛ ሓላፊዎችን ለሕግ ከማቅረብ በተጨማሪ  የገቢ ማስገኛ ተቋማቱ ለሦስተኛ ወገን እየተላለፉ የተሰጡበትን ውሎች በመሰረዝ የቤተ ክርስቲያኒቱን ጥቅም የሚያስከብርና የሚያስቀድም ወጥ አሠራር እንዲዘረጋ ተወስኗል፤ ተቋማቱም በየአጥቢያው በተናጠል የሚተዳደሩበት አካሔድ ቀርቶ በማዕከል የሚመሩበት ሥርዐት እንደሚበጅ የተጠቆመ ሲኾን፤  ይህንንም የሚያስፈጽም ጽ/ቤትና ፓትርያርኩ የሚሰበስቡት ቦርድ እንደሚቋቋም ታውቋል፡፡
የፓትርያርኩ ልዩ ሀገረ ስብከት በኾነው አዲስ አበባ፣ ጥናቱ ባልሸፈናቸው ሌሎች አድባራትና ገዳማትም እንዲቀጥል አቡነ ማትያስ ያዘዙ ሲኾን በመጪው ዓመት ጥቅምት በሚካሔደው 34ኛው ዓመታዊ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤም በአገር አቀፍ ደረጃ እንዲተገበር በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ እንዲወሰንበት እንደሚያደርጉም አስታውቀዋል፡፡

    አዲስ አመራር እንደሚመረጥ ይጠበቃል

      ሰማያዊ ፓርቲ የመጀመሪያውን ጠቅላላ ጉባኤ ነሐሴ 16 እና 17 የሚያካሂድ ሲሆን በዚህ ጉባኤ አዲስ መራር ይመረጣል ተብሎም ይጠበቃል፡፡ በፓርቲው ህገ ደንብ መሰረት ጠቅላላ ጉባኤ የሚደረገው በየ3 ዓመቱ መሆኑን የጠቀሱት የፓርቲው ብሄራዊ ም/ቤት ሰብሳቢ አቶ ሰይድ ኢብራሂም፤ ጉባኤው በሐምሌ መካሄድ የነበረበት ቢሆንም በአንዳንድ ምክንያቶች ምክር ቤቱ ለ3 ወር የማራዘም ስልጣኑን ተጠቅሞ እስከ ነሐሴ ማራዘሙን ገልፀዋል፡፡ በጉባኤው ላይ የሚሳተፉ አባላት ቁጥርና የጉባኤውን አካሄድ ለመወሰን ብሄራዊ ምክር ቤቱ በነገው እለት ስብሰባ እንደሚያደርግም ሰብሳቢው ተናግረዋል፡፡ ጠቅላላ ጉባኤውን እንዲያሳልጥ የተቋቋመው ኮሚቴምበእለቱ ሪፖርቱን ያቀርባል ብለዋል፡፡ በፓርቲው ህገ ደንብ መሰረት አንድ ፕሬዚዳንት ለሁለት የስልጣን ዘመን ብቻ መመረጥ እንደሚችል የጠቆሙት አቶ ሰይድ፤ በአሁኑ ወቅት ፓርቲውን የሚመሩት ኢ/ር ይልቃል ጌትነት ለሁለተኛ ጊዜ ይወዳደሩ አይወዳደሩ እስካሁን እንዳላሳወቁ ተናግረዋል፡፡