Administrator
4ሚ. ህፃናት ልካቸው ባልሆነ ጫማ ይሰቃያሉ
ወላጆች ለልጆች እግር መበላሸት ተጠያቂ ናቸው ተባለ
በቅርቡ የተካሄደ ጥናት፤ በዓለም ላይ 4ሚ. ያህል ህፃናት ልካቸው ያልሆነ በመጫማት እንደሚሰቃዩ ይጠቁማል፡፡ ለዚህ ደግሞ ተጠያቂዎቹ ወላጆች ናቸው ይላል፡፡
የልጆቻቸውን እግሮች ልካቸው ያልሆነ ጠባብ ጫማ ውስጥ እንዲሰቃዩ የሚፈቅዱ ወላጆች፤ ለልጆቻቸው የዘላለም ችግር እያስቀመጡላቸው እንደሆነ ማወቅ አለባቸው ብሏል ጥናቱ፡፡ ጠባሳ፣ እብጠት፣ የጣት ጥፍር ወደ ውስጥ ማደግ… የአጭር ጊዜ ችግሮች ሲሆኑ የረዥም ጊዜ ችግሮች ደግሞ የእግር መንጋደድ ለምሳሌ የጣት መቆልመም እንዲሁም የጉልበትና የቅርጽ መበላሸት እያለ ዝርዝሩ ይቀጥላል፡፡
ወላጆች ለልጆቻቸው ጥርስ ብዙ እንክብካቤ የሚያደርጉትን ያህል ለእግሮቻቸውም ሊያስቡላቸውና ሊጠነቀቁላቸው ይገባል ይላሉ፤ የእግር ጤናና እንክብካቤ ባለሙያዎች፡፡ ለመሆኑ 4ሚ. ህፃናት ለምንድነው ልካቸው ባልሆነ ጫማ የሚሰቃዩት? በቸልተኝነት? በገንዘብ እጥረት? በአመቺነትና ፋሽን በመሆኑ? ሁሉም ሰበብ ይሆናሉ ይላሉ ብለዋል በግላስጐው ካሌዶንያን ዩኒቨርሲቲ፣ በእግር ጤናና እንክብካቤ ዙሪያ ሌክቸር የሰጡት ዶ/ር ጐርዶን ዋት፡፡
የህፃናት እግሮች በዕድሜያቸው የመጀመያዎቹ አራት ዓመታት በፍጥነት የሚያድጉ ቢሆንም የእግራቸው አጥንቶች፣ ጡንቻዎችና መገጣጠምያዎች እንደ አዋቂ እግር ለመጠንከር ግን እስከ 18 ዓመት ድረስ ሊወስድባቸው ይችላል የሚሉት ባለሙያዎቹ፤ የታዳጊዎችም ሆነ የህፃናት እግሮች በቂ ትኩረትና እንክብካቤ እንደሚሹ ያሳስባሉ፡፡ በጥናቱ እንደተጠቆመው፤ ከ10 ወላጆች አንዱ ልጆቹ ለእግራቸው የሚያንሳቸውን ጫማ አሁንም ድረስ እንደሚያደርጉ ሲናገር፣ ገሚሶቹ ወላጆች ደግሞ፤ ልጆቻቸው “ጫማው እግራችንን አሳመመን” ብለው እስኪጨቀጭቋቸው ድረስ አዲስ ጫማ እንደማይገዙላቸው ታውቋል፡፡
የእግር ህክምና ባለሙያዎች እንደሚሉት፤ ብዙ ሰዎች ለልጆቻቸው እግር ጥንቃቄ የማያደርጉት ጠባብ ጫማ መጫማት የሚያስከትለውን ችግር ስለማይረዱት ነው፡፡ ለዚህ ጥናት ቃለ መጠይቅ ከተደረገላቸው ወላጆች ውስጥ 40 በመቶ ብቻ ናቸው የልጆቻቸው ጫማ ልካቸው እንደሆነና ምቾት እንዳለው ለማረጋገጥ የሚተጉት ተብሏል፡፡
ልጆች ጫማ በተገዛላቸው ቁጥር እግራቸው መለካት እንዳለበት የሚያሳስቡት ባለሙያዎቹ፤ ወላጆች ጫማው ላይ የሰፈረውን ቁጥር ብቻ አይተው መግዛት እንደሌለባቸው ይመክራሉ፡፡
የቸኮሌት ነገር!
የደም ግፊትን ይቀንሳል
በኮኮዋ ውስጥ የሚገኙት ፍላቫኖልስ የተባሉት ንጥረ ነገሮች የደም ግፊት የሚቀንሱ መድሃኒቶችን ሥራ እንደሚሰሩ ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡ ፍላቫኖልስ ሰውነታችን ናይትረስ ኦክሳይድ እንዲያመርት በማድረግ ለደም ስሮች መከፈት እገዛ ያደርጋሉ፡፡
የአውስትራሊያ ተመራማሪዎች፤ ኮኮዋ ዘወትር መጠቀም የሰዎችን የደም ግፊት ዝቅ እንደሚያደርግ በጥናታቸው ያረጋገጡ ሲሆን 1 በመቶ ያህሉ ግን ቸኮሌትን ከመጠን በላይ በመመገብ ለሆድ ህመም መጋለጣቸውን በጥናት ወረቀታቸው ላይ አስፍረዋል።
የጉበት ጉዳትን ይከላከላል
ቸኮሌት ለደም ግፊት ያለው ጠቀሜታ የሚመነጨው በውስጡ ካለው ከፍተኛ የፍላቫኖል ይዘት ነው፡፡ በጉበት ቬይኖች ከፍተኛ የደም ግፊት መከሰት ከጉበት ጉዳት ወይም ሥር ከሰደደ የጉበት በሽታ ጋር እንደሚገናኝ ይታመናል፡፡ ቀደም ሲል የተደረገ ጥናት እንደሚጠቁመው፤ ጥቁር ቸኮሌት መብላት በጉበት ውስጥ ያለውን የደም ዝውውር ያሻሽለዋል፡፡ ይኼው የቸኮሌት ዓይነት የጉበት ጉዳትን መከላከል ይችል እንደሆነ ለማረጋገጥ በአሁኑ ወቅት ጥናቶች እየተካሄዱ እንደሆነ ታውቋል፡፡
ለልብ ጤንነት ይጠቅማል
የደም ግፊትን ዝቅ በማድረግ፣ የደም ስሮችን በመክፈትና፣ ብግነትን በመቀነስ ከፍተኛ ሚና የሚጫወተው ቸኮሌት፤ የልባችንን ጤንነት በመጠበቅ ረገድም ጉልህ አስተዋጽኦ ያበረክታል። የልብ በሽታንና ስትሮክንም ይከላከላል፡፡ ከ114ሺ በላይ በሆኑ ሰዎች ላይ በተካሄደው ጥናት፤ ብዙ ቸኮሌት የሚመገቡ ሰዎች እጅግ አነስተኛ ከሚመገቡት ይልቅ በልብ በሽታ የመያዝ ዕድላቸው 37 በመቶ፣ ለስትሮክ የመጋለጥ ዕድላቸው ደግሞ 29 በመቶ እንደቀነሰ ተረጋግጧል፡፡
ሸንቃጣ ያደርጋል
ከ1ሺ በሚበልጡ ሰዎች ላይ በተደረገ ጥናት እንደተረጋገጠው፤ ቸኮሌት መብላት የሚያዘወትሩ ሰዎች ሸንቃጣ የመሆን ዕድላቸው ከፍተኛ ነው፡፡
ለጥናቱ የተመረጡት ሰዎች “በሳምንት ስንት ጊዜ ቸኮሌት ትመገባለህ/ትመገቢያለሽ?” የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው ሲሆን የጥናት ውጤታቸውን በ “አርካይቭስ ኦፍ ኢንተርናል ሜዲሲን” ያሳተሙት ተመራማሪዎች፤ በሳምንት ውስጥ ደጋግመው ቸኮሌት የሚበሉ ሰዎች አልፎ አልፎ ከሚበሉት የበለጠ ሸንቃጣ እንደሆኑ አረጋግጠዋል ፡፡
ብልህና ብሩህ ያደርጋል
በ”ኒው ኢንግላንድ ጆርናል ኦፍ ሜዲሲን” የወጣ አንድ ጥናት፤ ቸኮሌት በብዛት የሚጠቀሙ ህዝቦች ያላት አገር፣ ከሌሎች የበለጠ የኖቤል ሽልማት አሸናፊዎች እንደሚኖራት አመልክቷል፡፡ ቸኮሌት አዘውትሮ መብላት ብልህና ብሩህ ያደርጋል ማለት ነው፡፡ ለዚህም በምሳሌነት የተጠቀሰችው ስዊዘርላንድ ናት፡፡
ስዊዘርላንዶች ቸኮሌት በብዛት በመመገብ የሚታወቁ ሲሆን ብዙ የኖቤል ተሸላሚዎች እንዳሏቸውም ተገልጿል፡፡ የእንግሊዝ ተመራማሪዎች እንደሚሉት፤ በእንግሊዝ የኖቤል ተሸላሚዎችን ለማብዛት እያንዳንዱ ሰው በዓመት 2 ኪ.ግ ቸኮሌት መብላት ይኖርበታል፡፡
ሲጋራ የውበትና የገፅታ፣ የስያሜና የአርማ እገዳ ተጣለበት
ጤናንና ህይወትን ለመታደግ ነው ተብሏል
ሲጋራ ማጨስ ለከፍተኛ የጤና አደጋ፣ ባስ ሲልም ለህልፈት እንደሚዳርግ ማንም ሊክድ አይችልም። እንዲያም ሆኖ ከወደ አየርላንድ የተሰማው አዲስ እገዳ ክፉኛ ያስደነገጠው ከአጫሾች ይልቅ የትምባሆ ኩባንያዎችን ነው። ሰሞኑን አየርላንድ ማንኛውም ሲጋራ ስያሜ፣ የንግድ ምልክትና አርማ እንዳይኖረው የሚያግድ ህግ አውጥታለች፡፡ እገዳው ሲጋራዎች ላይ ብቻ ግን አይደለም፤ የሲጋራ ፓኮዎችም ያለምንም ፅሁፍና ምልክት ለገበያ እንዲቀርቡ ህጉ ያስገድዳል። አዲሱ ህግ የትምባሆ ኩባንያዎችን ቢያስከፋም የአየርላንድ የጤና ሚኒስትር ጄምስ ሬይሊ፤ እገዳው የብዙዎችን ህይወት ለመታደግ ያግዛል ብለዋል፡፡
የምርት ስያሜ፣ የንግድ ምልክትና አርማ ያለው ሲጋራ ለሸማቶች እንዳይቀርብ የሚያግድ ህግ በማጽደቅ አየርላንድ በአውሮፓ የመጀመሪያዋ አገር ናት ተብሏል፡፡
አውስትራሊያ ተመሳሳይ እገዳ በሲጋራ ላይ በመጣል ከዓለም የመጀመሪያዋ አገር ስትሆን ኒውዚላንዶች ደግሞ በረቂቅ ህጉ ላይ እየተከራከሩ እንደሆነ ታውቋል፡፡ እንግሊዝን ጨምሮ ሌሎች የአውሮፓ አገራት እገዳው በህግ የመውጣቱን አስፈላጊነት ገና እያጤኑት ነው ተብሏል፡፡
የአየርላንድ ጤና ሚኒስትር በሰጡት መግለጫ፤ “የህጉ ዓላማ የሲጋራ ፓኮዎች ለሸማቾች ያላቸውን ማራኪነት በመቀነስ፣ በጤና ላይ የሚያደርሱትን አደጋ ማጉላት ነው፡፡ ፓኬቶች ሰዎችን በተለይ ህፃናትን የማሳሳት አቅማቸውን በመቀነስ የማጨስ ጐጂነትን እንዲገነዘቡ እናደርጋለን” ብለዋል፡፡
የትምባሆ ኩባንያዎች ግን እገዳውን አጥብቀው ተቃውመዋል፡፡ የትምባሆ ምርቶችን ስያሜና አርማ አልባ አድርጐ ማቅረብ፣ ሃሰተኛ የሲጃራ ምርቶችን የሚያመርቱ ወንጀለኞችን የሚያግዝና የሚያበረታታ ነው ብለዋል - ኩባንያዎቹ፡፡
ቤንሰን ኤንድ ሄጅስ እና ደንሂል በሚሉ ስያሜዎች የሚታወቁት ሲጋራዎች ባለቤት የሆነው የብሪቲሽ አሜሪካን ቶባኮ (BAT) ቃል አቀባይ እንደተናገሩት፤ የአየርላንድ ካቢኔ ረቂቅ ህጉን ማጽደቁ አሳዝኗቸዋል።
“ምንም ፅሁፍ ያልሰፈረበት ሌጣ ፓኬት፣ ታዳጊዎች ሲጋራ እንዳይጀምሩ ወይም አጫሾች ማጨስ እንዲያቆሙ ስለማድረጉ ተዓማኒ ማስረጃ የለም” ሲል ተሟግቷል ተቋሙ፡፡
በቅርብ ዓመታት ሲጋራ ማጨስ በህብረተሰቡ ላይ የጋረጠውን አደጋ ለመቅረፍ የሚያስችል ውይይት ያደረገችው አየርላንድ፤ እ.ኤ.አ በ2004 ዓ.ም በስራ አካባቢ ሲጋራ ማጨስን ሙሉ በሙሉ የሚያግድ ህግ በማውጣት በዓለም የመጀመርያው አገር ሆናለች፡፡ በሥራ አካባቢ ሲጋራ ማጨስ የሚከለክለው ህግ መሸታ ቤቶችንና ክለቦችንም እንዳካተተ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ እንዲያም ሆኖ ታዲያ የህጉ ተፈፃሚነት 97 በመቶ እንደተሳካ ተገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ ታሪክ
...በዚያም ወራት ደጃች ብሩ፤ ጭልጋ አርባ አምባ ታስሮ ሳለ፣ ሚሽቱ ወይዘሮ የውብዳር ከእልፍኝ አሽከሮቿ አንዱን መልምላ ውሽማ አበጅታ ነበረ፡፡ ይህን ነገር ደጃች ብሩ በሰማ ጊዜ አዘነ፡፡ በበገና እንዲህ ብሎ አለቀሰ፡፡ ...
“መከራን በሰው ላይ እንዲያ ሳቀለው፣
ምንኛ ከባድ ነው እኔ ብይዘው፡፡
መከራ ሲመጣ አይነግርም አዋጅ፣
ሲገሠግሥ አድሮ ቀን ይጥላል እንጅ፡፡
ዘሃው ሰለሰለ ሸማኔው ተቆጣ፣
እስተወዲያው ድረስ መጠቅለያ ታጣ፡፡
የኔታም አይመጡ እኔም አልመለስ፣
ዋ ቢቸና ቀረ እስተወዲያው ድረስ፡፡
ከእልፍኝ ሰው አይግባ ሚሽቴን ሰው አይያት አይሉም አይሉም፣
ፈረሱን ሰው አይጫነው፣ በቅዬን ሰው አይጫነው አይሉም አይሉም፣
ጠጁ ቀጠነብኝ፣ ሥጋው ጎፈየብኝ አይሉም አይሉም፣
ቀን የጣለ ለታ፣ የጨነቀ ለታ፣ ይደረጋል ሁሉም። አለ፡፡
የደጃች ብሩ ግጥም ብዙ ነው፡፡ በሰራው ክፋት ብድሩን ከፈለ፡፡ በዘመኑ ጎጃምን ሲገዛ ያደረገው ክፋት ተጽፎ አያልቅም፡፡ ሚሽቱ ወይዘሮ የውብዳር ቤተክርስቲያን ልትሳለም በምትወጣበት ቀን አስቀድሞ ሰው የገባ እንደሆነ የዱላ በረዶ ይወርድበት ነበር፡፡ በደረቤ በየወረዳው ፲ ፲ (አሥር አሥር) እንስራ ጉንዳን ለምስጥ ማጥፊያ ብሎ ደሃውን አስጨንቆት ነበረ፡፡ ያንን ጊዜ ባላገር ጉንዳን በሣምባ ሥጋ እየተሰለበ በእንስራ ውስጥ እየከተተ ወደ ሶማ አምባ ሲወስድ ጆሮውንና ትክሻውን እየነከሰ አስቸገረው፡፡ የዚህ ጊዜ በለቅሶ ሲአንጎራጉር እንዲህ አለ፡፡
ከመከራው ሁሉ የጉንዳኑ ባሰ፣
የተሸካሚውን ጆሮና ትክሻ እየተናከሰ፡፡ አለ፡፡
ደግሞ የሴት ብልት ጠጉር የበቅሎ ቁርበት ይበጃል ብሎ ፭፻ ጉንዲ ጠጉር በሚዛን አምጡ ብሎ በየወረዳው ጥሎ ደኃውን አስለቀሰው፡፡ በሚዛን ሳይሞላለት ጊዜ የራሱን ጠጉር እየጨመረ ቢሰጥ እምቢ እያለ ወርቅ ተገላገለው፡፡
ያን ጊዜ የሴት ዘመድ የሌለው ተቸግሮ ነበረ፡፡ ደግሞ አፄ ቴዎድሮስ እንዳይሰብረው ብሎ ሶማን ሊያሰራ ፴ ጎበዝ ግንድ ተሸክሞ ሲወጣ፣ ከጠባብ ቦታ ላይ ተጨናንቆ ግንዱ ወንጥሎት ገደል ይዞት ገባና አለቀ፡፡ ይኸን ደጃች ብሩ በሰማ ጊዜ ገበሬ ምንኛ ተዋዳጅ ነው፡፡ አንድነት ወርዶ አለቀ ወይ ብሎ ቀለደ፡፡ አለሚገባ እጁን እግሩን የቆረጠው ሰውም ብዙ ነው፡፡
ይህን ሁሉ ክፋት ክርስቶስ መዝኖ ጊዜው ሲደርስ፣ በአጼ ቴዎድሮስ እጅ አግብቶ ሚሽቱን ለጠብደል ማላገጫ አድርጎ ሲአስለቅሰው ኖረ። የደጃች ብሩን ልቅሶ አጼ ቴዎድሮስ በሰማ ጊዜ ሎሌዎች በድለዋል አሉና ልቅጣዎ ብሎ ላከበት። ደጃች ብሩም ለጊዜው ኀዘን አብርትቶ ነበረና መንግሥትዎን ያሰንብትልኝ፡፡ ቃሉ ደረሰኝ፡፡ ግን የጮሁለት ሰው አለና የዚያን ቁርጥ ሳውቅ ይሁን አለ፡፡
መልክተኛው ከመድረሱ ውሽማዋን መብረቅ ገደለው፡፡ ደጃች ብሩም ክርስቶስ ሰማኝ፡፡ ፍርዱን ፈረደ፡፡ ባላጋራየ ሞተ ብሎ ላከ፡፡ አጼ ቴዎድሮስም ሰምቶ ተደነቀ፡፡ ለካስ ደጃች ብሩ አጥብቀው አዝነዋል፡፡ ክርስቶስም ሰማቸው፤ በኔም ቢአዝኑ ያደርሱብኛል ብሎ ፈተህ አምጣልኝ አለ፡፡
ከታሰረበት ፈትቶ ወደ አጼ ቴዎድሮስ እጅ ሊነሣ ሲኸድ፣ ያው ጋኔኑ ጥንተ ትቢቱ አልለቀው ብሎ ተከናንቦ ሎሚ ታህል ደንግያ በትከሻው ይዞ ሊታረቅ መጣ፡፡ አጼ ቴዎድሮስም ክንንቡንና የድንጋይቱን ማነስ አይቶ ተበሳጭቶ፣ ትቢትዎ አለቀቀዎምሳ ቢለው፣ ክንብንቤን እንደሆነ የጭልጋ በረሃ ጠጉሬን ጨርሶት ባፍር ነው አለ፡፡ አጼ ቴዎድሮስም ከአብራጃው አገር መቅደላ ይቆዩ፡፡ እኔ ልፈታዎ ነበረ፡፡ ነገረ ክርስቶስ ማቆያ በትቢት ምክንያት አመጣብዎ፡፡ ፈቃዱ ሲሆን ይፈታሉ አለው፡፡
ምንጭ - (አለቃ ተክለኢየሱስ፣ የኢትዮጵያ ታሪክ፤ ሐተታ (በሥርግው ገላው (ዶ/ር))
የፍቅር ጥግ
የምወድሽ ስለአንቺነትሽ ብቻ አይደለም። ካንቺ ጋር ስሆን ስለምሆነው እኔነቴም ጭምር ነው፡፡
ሮይ ክሮፍት
መፈቀርን ብቻ አይደለም የምፈልገው፤ መፈቀሬ እንዲነገረኝም እሻለሁ፡፡
ጆርጅ ኤልዮት
ሰዎችን ከፈረጅካቸው ለፍቅር ጊዜ አይኖርህም፡፡
ማዘር ቴሬዛ
አንቺ ለእኔ ጣፋጭ ስቃዬ ነሽ፡፡
ራልፍ ዋልዶ ኤመርሶን
ፍቅር ፈፅሞ ተፈጥሮአዊ ሞቱን ሞቶ አያውቅም፡፡ የሚሞተው ምንጩን ማደስ ስለማናውቅበት ነው፡፡ የሚሞተው በጭፍንነት፣ በስህተትና በክህደት ነው። የሚሞተው በህመምና በቁስል ነው። የሚሞተው በድካም፣ በመጠውለግና በመመረዝ ነው፡፡
አናዩስ ኒን
ቤተሰብ የሚጀምረው ከየት ነው? ጉብሉ ከኮረዳዋ ጋር በፍቅር ሲወድቅ ነው፡፡ ከዚህ የላቀ አማራጭ እስካሁን አልተገኘም፡፡
ሰር ዊንስተን ቸርችል
የተወለድነው ለብቻችን ነው፡፡ የምንኖረው ለብቻችን ነው፡፡ የምንሞተውም ለብቻችንን ነው፡፡ ብቻችንን አይደለንም የሚለውን ማስመሰል መፍጠር የምንችለው በፍቅርና በጓደኝነት አማካኝነት ብቻ ነው፡፡
ኦርሶን ዌልስ
ለእውነተኛ ፍቅር ጊዜም ሆነ ቦታ የለም። የሚከሰተው እንደ አጋጣሚ ነው፡፡ በልብ ምት፣ በአንዲት ብልጭታ፣ በትርታ ቅፅበት ነው፡፡
ሳሬ ዴሴን
ዕባብ ያፍዝ-ያደንግዝ ያደረገባት ወፍ ክንፍ እንዳላት ትረሳለች (የአፈ-ታሪክ ወግ)
“ሉሲ እና ሌሎች አጫጭር ታሪኮች” የሚለው መፅሀፍ ላይ የሚከተለው ታሪክ ይገኛል፡፡
በድሮ ዘመን በጣም ደስተኛ የሆነ ሰው ከሚወዳት ሚስቱና ከአራት ወንዶች ልጆቹ ጋር ይኖር ነበር። የአንጋፋው ልጅ ስም ጥልቅ ዓይን ይባላል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ቆቁ ተባለ፡፡ ሶስተኛው ልጅ ጡንቸኛው የሚል ስም ተሰጠው፡፡ የመጨረሻው ትንሹ ልጅ ህፃን ስለነበር ስም አልተሰጠውም፡፡
አንድ ቀን በማለዳ እናታቸውና ልጆቹ ከመኝታቸው ሲነሱ አባታቸውን ከቤት አጡት፡፡ በሚቀጥለው ምሽትም ሳይመለስ ቀረ፡፡ በማግስቱም የአባታቸው ዱካ ጠፋ፡፡ ልጆቹ ከእናታቸው ጋር ብዙ ተወያዩ፡፡ ወዴት እንደሄደ ማንም የሚያውቅ የለም፡፡
እናታቸው ራሷን በሁለት እጆቿ ደግፋ ለቅሶና ጩኸቷን ለቀቀችው፡፡ ጥልቅ ዓይን “ምናልባት አጎታችንን ሊጠይቅ ሄዶ ይሆናል፡፡” አለ፡፡ “ድግስ ተጠርቶ ወደ ጎረቤት ሄዶ ይሆናል” ሲል ቆቁ የራሱን ግምት ሰጠ፡፡ “ምናልባትም ወደ ተራራ ወጥቶ ነፋስ እየተቀበለ ይሆናል” በማለት ጡንቸኛው የበኩሉን ግምት ተናገረ፡፡
ይሁንና አባታቸው እንደጠፋ ሳምንታት ተቆጠሩ፡፡ አልፎ አልፎ ልጆቹ ወደ ጫካና ወደ ተራራ ሄደው ከፍ ባለ ድምፅ አባታቸውን ይጣራሉ፡፡ መልስ ሳያገኙ ወደቤታቸው ይመለሳሉ፡፡ በሁኔታቸው እየተሰላቹ ስለሄዱ መፈለጉን አቆሙ፡፡
ሕፃን ወንድማቸው ግን እንደነሱ ተስፋ አልቆረጠም፡፡ አንድ ቀን ጧት እናቱ አቅፋው ሳለ፣ ህፃኑ ልጅ “አባቴ የት አለ? አባቴን እፈልጋለሁ፡፡” በማለት ለመጀመሪያ ጊዜ ተናገረ፡፡ ታላቅ ወንድሙ ጥልቅ ዐይን “እውነት ነው፡፡ አባባ የት አለ?” በማለት ሕፃኑን እየተመለከተ እርሱም ጠየቀ፡፡ “አሁኑኑ ተነስተን አጥብቀን ብንፈልገው ይሻላል” ሲል ጡንቸኛው አምርሮ ተናገረ፡፡
መፈለግ ቀጠሉ“ቆይ-ቆይ ከሩቅ ቦታ የለቅሶ ድምጽ ይሰማኛል፡፡ በዚህ በኩል… ጪኸት እየሰማሁ ነው! ተከተሉኝ!” በማለት ቆቁ አስገነዘበ፡፡ እንደ ጩኸቱ ቅርበትና ርቀት ቆቁ በተሰማው አቅጣጫ ተያይዘው ተጓዙ፡፡ በመጨረሻም ወደ አንድ ወንዝ ተቃረቡ፡፡ አባታቸው በወንዙ ዳርቻ በጦሩ ከወጋው አነር ጋር ተፋጦ አዩት፡፡ አነሩ የአባታቸውን እግር አቁስሎታል፡፡ “አባባን ማዳን ይገባናል!” በማለት ጡንቸኛው ጮኸ፡፡ በቅጽበት በጠንካራ ጡንቾቹ አነሩን አነቀው፡፡ የታነቀው አነር አየር አጥቶ ተዝለፍልፎ ወደቀ፡፡
“እጅግ አስፈላጊ በሆነ ሰዓት ደረሳችሁልኝ! ዘነጣጥሎ ይበላኝ ነበር፡፡ በጦር ብወጋውም አስቀድሞ አቁስሎኝ ስለነበር ደከመኝ፡፡ እህል ውሃም ስላልቀመስኩ ድካሜ ተባባሰብኝ፡፡ አመጣጤ የሚታደን ነገር ለማግኘትና ለእናንተ ለማምጣት ነበር” እያለ አባታቸው አስረዳ፡፡ ሁሉም ሰው “ጀግኖች ናቸው፡፡” በማለት አደነቃቸው፡፡
ወንድማማቾቹ ይህንኑ የሕዝብ አድናቆት ሰሙ፡፡ በመካከላቸው ታላቅና ኃይለኛ ጭቅጭቅ ተነሳ፡፡ አባታቸውን በማዳን ማን ዋነኛውን ተግባር (ሥራ) እንደሰራ ለማወቅ ይነታረኩ ጀመር፡፡ ጥልቅ ዐይን “እኔ ዱካውን (ኮቴውን) ባላየው ኖሮ አባታችን የሄደበትን አናውቀውም ነበር” አለ፡፡ ቆቁ በበኩሉ “ዱካው አንድ ቦታ ስንደርስ ጠፍቷል፡፡ እኔ የለቅሶውን ጩኸት ሰምቼ ባልመራችሁ ኖሮ አባታችንን ማግኘት አንችልም ነበር” ሲል ተከራከረ፡፡
“ሁለታችሁም ተሳስታችኋል፡፡ አባታችንን ብናገኘው ምን ዋጋ አለው፡፡ እኔ አነሩን ባልገልለት ኖሮ አባታችን እኮ በአነሩ ይበላ ነበር፡፡ ዋናው ክብር ለእኔ ይገባኛል!” እያለ ጡንቸኛው ደነፋ፡፡ ወደ አባታቸው ሄዱ፡፡ እርሱን በማዳን ረገድ ክብር የሚሰጠው ማን እንደሆነ እንዲነግራቸውም ጠየቁት፡፡
አባታቸውም “ሰማችሁ ልጆቼ እኔን በመታደጋችሁ ባለውለታዬ ናችሁ፡፡ ከሦስታችሁም እኔን አድኖ ለቤት ለማብቃት ትልቁን ክብር የሚያገኝ የለም፡፡ አንዳችሁም ትልቁን ክብር የሚያሰጥ ውለታ አልሰራችሁም፡፡ ለትልቁ ክብር የሚበቃ ሥራ የሰራው ይህ ህፃን ወንድማችሁ ነው፡፡ ክብር ለሕፃኑ ትንሽ ወንድማችሁ ይገባዋል፡፡ ጀግናችሁ ነው” በማለት አባታቸው ነገራቸው፡፡ ትንሹን ሕፃንም ታቀፈው፡፡
* * *
ትክክለኛው ክብርና ምሥጋና ለሚገባው ተገቢውን ክብር እንስጥ፡፡ የሌሎችን ዋጋ ለመውሰድ ጥቅማቸውንም ለመንጠቅ አንሞክር፡፡
በጨው ደንደስ በርበሬ ተወደስን አንመኝ! ዛሬ ሁለ-መናችንን ጠንቅቀን ለማየት ጥልቅ-ዐይን ያስፈልገናል፡፡ የምናየውንና የሚገጥመንን ሁሉ ያላግባብ እንዳንመዝንና የተሳሳተ ምላሽ እንዳንሰጥ ቆቅነት ያስፈልገናል፡፡ ይሄ ሁሉ ኖሮን ግን አቅም ማዳበር ካልቻልን ከንቱ ነው! በመጨረሻም እንደህፃን የዋህ የሆነ ልቡና ያሻናል - የምንፈልገውን ሁሉ በንፅህና ለመጠየቅ! ተስፋ የማይቆርጥ የህፃን መንፈስ ሁልጊዜም ያስፈልገናል፡፡ መሸለም ያለበትና ዘላቂው ተሸላሚ ይሄ ተስፋ የማይቆርጥ የነገ ተስፋ ነው!
ቻይናዎች ሁለት የፊደል ባህሪያትን አገጣጥመው ነው ድቀትን (Crisis)፣ የችግር ጊዜን፤ የሚተረጉሙት። ሁለቱ ባህሪያት ጣጣ (Risk) እና አጋጣሚ (Opportunity) ናቸው፡፡ አንድን ጉዳይ፣ (የችግር ጊዜ) ለማሸነፍ የሚያመጣውን ጣጣ ልንችል፣ ያሉንን አጋጣሚዎች ልንጠቀም ዝግጁ መሆን አለብን እንደማለት ነው፡፡ የሀገራችንን አያሌ ችግሮች እንዲህ ቆርጠን እንፍታቸው ካ›ልንና ዝግጁነት ካላሳየን፣ የውሃ ላይ ኩበት ነው የምንሆነው፡፡ ጣጣውን ችሎ አጋጣሚን ለመጠቀም መነጋገር,፣ መመካከር ፣ አዕምሮን ከአዕምሮ ማወዳደርና መደራጀት ያስፈልጋል፡፡ ዓለም ያለፈቻቸው አምስት ዘመናት አሉ፡፡ አንደኛው “ዓለም እኔን የምትሰማኝን ያህል ናት” ያልንበት ነው፡፡ ሁለተኛው “ዓለም እኔ ነች ብዬ የማስባት ናት” የምንልበት ነው፡፡ ሶስተኛው ዓለም እልቆ መሣፍርት የሌላት ማሽን ናት፡፡ እንዴት እንደምትሠራ እደርስባታለሁ” የምንልበት የሳይንስ ዘመን ነው፡፡ አራተኛው “ዓለም እኔ በፈጠርኳቸው ልዩ ልዩ ምናልባቶች የተሞላች ስትሆን ይምህ የእኔ አመለካከት ያመጣው ነው” የተባለበት ነው፡፡ በመጨረሻም፤ “የእኔ ዓለም ማናቸውም ቀመር (formulation) የማይወስነው መዋቅር ያላት ናት፡፡ እኔ ዓለምን የማያት ከሷ ጋር እንዳለኝ ጅምላ ልምድ ነው። እናም በራሴ ምልክት ስሪቶች (Symbolic constructs) ራሱን ነፃ በማውጣት መንፈስ እየተጫወትኩ፣ እየተንቀሳቀስኩ ነው” የምንልበት ዘመን ነው፡፡ የዓለምን ታሪክ ወደራሳችን ተርጉመን ፋይዳ ሰጥተን ካስተዋልነው፤ ለውጥ የማምጣትና የማሸነፍ ዕድል አለን፡፡
ቴድ ሲልቬይ የተባለ ፀሀፊ ይሄን ይላል “... ለደጋ ፍየሎች መረማመጃ የድንጋይ ደረጃ እንሰራለን። ለእንስሶች ማረፊያ ቤት እንሰራለን፡፡ ሌላው ቀርቶ ለእባብም የሚያስደስተውን የአየር ማረጋጊያ (Air conditioning) እናደርጋለን! ለሰው ልጅ ግን ተገቢውን መጠለያ፣ ለህፃናትም በቂ መኖሪያ ሥፍራ፣ አንሰጥም” ይላል፡፡ ለዜጎቻችን ቢያንስ መሰረታዊውን የቤት ችግር ማስወገድ - በተለይ ይሄ ሁሉ የቤት ሙስና ባለበት አገር - እጅግ ወሳኝ ነው፡፡ አናንቀላፋ፡፡ በግሪክኛ Hypnos - እንቅልፍ ማለት ነው፡፡ Hypnos የሚለው ቃል ሥረ ቃሉ hypnosis ነው፡፡ ይህኛው ግን በመንቃትና በመተኛት መካከል ያለ ሰመመናዊ ስሜት ነው፤ ይለናል ሚካኤል ፓወል፡፡
ሁኔታዎች አጥፊያችን ሆነው ስናገኛቸው በቆቅ ዐይን ማየት እንጂ ሰመመን ውስጥ (Hypnosis) ውስጥ መግባት የለብንም፡፡ መንቃት፣ ጆሮአችንን ማንቃት፣ አቅማችንን ማወቅና መስፈንጠር፤ እመርታ ማሳየት አለብን፡፡ አለበለዚያ እንደ አፈ-ታሪኩ፤ “ዕባብ ያፍዝ ያደንግዝ ያደረገባት ወፍ፤ ክንፍ እንዳላት ትረሳለች” መባል አይቀርልንም፡፡
የስኳር ፕሮጀክቶች ለተቋራጮች የተሰጡት በህገ-ወጥ መንገድ ነው ተባለ
በጥቅምት 2006 ይጠናቀቃል የተባለው የስኳር ፋብሪካ ግንባታ ገና አልተጀመረም
የፋብሪካ ግንባታ በመጓተቱ፤ የ100 ሚሊዮን ብር ሸንኮራ አገዳ ያለ ጥቅም ተወግዷል
የፕሮጀክቶቹ የገንዘብ ወጪ በውል አይታወቅም፤ ያለ ጥናትና ዲዛይን የተጀመሩ ናቸው
መንግስት በመቶ ቢሊዮን ብር ወጪ የስኳር ምርትን 23 ሚሊዮን ኩንታል ለማድረስ የሚያካሂዳቸው ከአስር በላይ አዳዲስና ነባር የስኳር ፕሮጀክቶች ያለ ውጤት ለአመታት የተጓተቱ ሲሆን፤ የመስኖና የፋብሪካ ግንባታዎቹ ለተቋራጭ ድርጅቶች የተሰጡት በህገወጥ መንገድ ያለጨረታ እንደሆነ የፌደራል ኦዲተር ገለፁ፡፡ አስር የስኳር ፋብሪካዎች ግንባታ ህግን ባልተከተለ መልኩ ያለ ጨረታ ሙሉ ለሙሉ ለብረታ ብረት ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን መሰጠቱን ኦዲተሩ ጠቅሶ፤ የፋብሪካዎቿ ግንባታ እንደተጓተተ ገልጿል፡፡ ያለ ጨረታ የመስኖና የአገዳ ልማት ፕሮጀክቶችን ወስደው ስራ ያጓተቱ ተቋራጮች፤ በአዲስ አበባና በየክልሉ የሚገኙ የውሃ ስራ ድርጅቶች እንዲሁም የብረታብረት ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ናቸው፡፡ ፕሮጀክቶቹ የመንግስትን የግዢ መመሪያ ባልተከተለ መልኩ ያለ ጨረታ ለተቋራጮች መሰጠታቸው፣ በታቀደላቸው ጊዜና ወጪ እንዳይጠናቀቁ ያደርጋል ብሏል - የኦዲተሩ የምርመራ ሪፖርት፡፡
ፕሮጀክቶቹ ለተቋራጮቹ የተሰጡበትን አሰራር በተመለከተ ማብራሪያ እንዲሰጡ የተጠየቁት የኮርፖሬሽኑ የስራ ሃላፊዎች፣ በግዢ ክፍሉ በኩል የምናውቀው ነገር የለም የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። የኮርፖሬሽኑን የአምስት አመታት እቅድ አፈጻጸም በተመለከተ የቀረበው መረጃ እንደሚያሳየው፣ በጣና በለስ እና በኦሞ-ኩራዝ ፕሮጀክቶች፣ የ3 ፋብሪካዎች ግንባታ እስከ ጥቅምት 2005 ዓ.ም እንዲጠናቀቅ እቅድ ወጥቶ እንደነበር የገለፀው የፌደራል ኦዲተር፤ እስከ አመቱ መጨረሻ የተከናወነው ስራ ግን ከ45 በመቶ እንደማይበልጥ ገልጿል፡፡ በጥቅምት ወር 2006 ዓ.ም ይጠናቀቃል የተባለው የወልቃይት የስኳር ፋብሪካ ግንባታም፣ ገና ግንባታው ሳይጀመር የእቅዱ ጊዜ ማለፉ ተገልጧል፡፡
በአገዳ ተክል ልማት፣ በመስኖ ስራና በፋብሪካ ግንባታ በኩል ኮርፖሬሽኑ የሚያዘጋጃቸው የስኳር ፕሮጀክት እቅዶች የሰው ሃይልንና የገንዘብ ምንጭን ያላገናዘቡ፣ ተግባሪ አካላትን ያላሳተፉና በበቂ ጥናት ላይ ያልተመሰረቱ መሆናቸውን በምርመራ እንደደረሰበት ኦዲተሩ ገልፆ፤ በዚህም ምክንያት የኮርፖሬሽኑ ዓመታዊ እቅዶች በአመት ከሶስት ጊዜ በላይ ይከለሳሉ ብሏል፡፡ ይህም ፕሮጀክቶቹ እንዲጓተቱ ማድረጉንና መንግስትን ተገቢ ላልሆነ ወጪ እየዳረገው እንደሚገኝ የኦዲተሩ ሪፖርት ገልጿል፡፡ የተንዳሆ ስኳር ፕሮጀክት የፋብሪካ ግንባታ ስራ በታቀደለት ጊዜ መጠናቀቅ ባለመቻሉ ምክንያት፣ በ5ሺህ164 ሄክታር መሬት ላይ የለማ የሸንኮራ አገዳ ምርት ጥቅም ላይ ሳይውል እንዲወገድ መደረጉን ኦዲተሩ ጠቅሶ፤ በዚህም ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ኪሳራ እንደደረሰ አመልክቷል፡፡
ፕሮጀክቶቹ በትክክል ምን ያህል ገንዘብ ወጪ እንደተደረገባቸው በውል ለመለየት አለመቻሉን የገለጸው የኦዲተሩ ሪፖርት፤ ከአገዳ ልማት፣ ከመስኖ ግንባታና ከፋብሪካ ግንባታ ክፍል ጋር የተቀናጀና የተጠናከረ የፕሮጀክት ክትትልና ቁጥጥር አሰራር ባለመኖሩ ምክንያት በየአመቱ ተደጋጋሚ የዕቅድ ክለሳ በማድረግ የዕቅድ አፈጻጸም መጓተትን፣ የወጪ መጨመርን፣ የጊዜ መራዘምንና የሃብት ብክነትን አስከትሏል ብሏል፡፡ ፕሮጀክቶቹ ለአመታት መጓተታቸው፤ የሃብት ብክነትን ከመፍጠር በተጨማሪ በአምስት አመቱ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ላይ የተቀመጠው ግብ እንዳይሳካ ማድረጋቸውን ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡ የአገሪቱ የስኳር ምርት በየአመቱ እንደሚጨምር ታቅዶ የነበረ ቢሆንም፤ ከ2003 ዓ.ም ወዲህ የስኳር ምርት እየቀነሰ እንደነበር ይታወቃል፡፡ በአምስት አመት ውስጥ የስኳር አመታዊ ምርት ከ3 ሚሊዮን ኩንታል ወደ 22 ሚሊዮን ኩንታል እንዲያድግ ታቅዶ እንደነበር የሚታወቅ ሲሆን፤ እስካሁን አራት ሚሊዮን ኩንታል አለመድረሱ ተዘግቧል፡፡
ኢትዮጵያ ግማሽ ሚሊዮን ስደተኞች እያስተናገደች ነው
በየቀኑ 1 ሺ የደቡብ ሱዳን ስደተኞች ወደ ኢትዮጵያ ይገባሉ
አምና ለስደተኞች የምግብ እህል የተገዛው ከኢትዮጵያ ነው
ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ግማሽ ሚሊዮን ስደተኞች እያስተናገደች መሆኑን የገለፀው የዓለም ምግብ ፕሮግራም አብዛኞቹ የሶማሊያ፣ የደቡብ ሱዳንና የኤርትራ ስደተኞች መሆናቸውን አስታወቀ፡፡ ድርጅቱ ያለፈውን ዓመት (2013) የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ሰሞኑን ባቀረበበት ወቅት፤ በየቀኑ 1 ሺ የደቡብ ሱዳን ስደተኞች ወደ ኢትዮጵያ እየገቡ መሆኑን ጠቅሶ ካለፈው ዓመት መስከረም ወር አንስቶ ወደ ኢትዮጵያ የገቡ ስደተኞች 140ሺ እንደደረሱ የድርጅቱ ተጠሪና ዳሬክተር ሚ/ር አብዱ ዴንግ ገልጸዋል፡፡ አብዛኞቹ ስደተኞች ሕፃናት፣ ሴቶችና የሚያጠቡ እናቶች መሆናቸውን ሚ/ር አብዱ ጠቅሰው፣ ለችግሩ ፖለቲካዊ መፍትሔ ካልተፈለገ በስተቀር አሁን ድርጅቱ የቀረው 70 ሚሊዮን ዶላር የሚያገለግለው እስከ መጪው ጥር ወር በመሆኑ፣ በሚቀጥለው ዓመት ለሚያስፈልጋቸው 120 ሚሊዮን ዶላር የዓለም ለጋሾች እጃቸውን እንዲዘረጉላቸው ተማፅነዋል፡፡
ከቀያቸው የተፈናቀሉት የደቡብ ሱዳን ስደተኞች የተጠለሉት በቀላሉ በማይደረስበት የጫካ አካባቢ በመሆኑ፣ በየቀኑ ከጋምቤላ አሶሳ፣ ከአሶሳ ወደ ደቡብ ሱዳን ድንበር እየበረሩ በአውሮፕላንና በጀልባ እየተጠቀሙ 15,000 ሜትሪክ ቶን የምግብ ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልፀዋል፡፡ ድርጅቱ ባለፈው 2013 ዓመት፣ ለስደተኞች 330ሺ ሜትሪክ ቶን የምግብ እህል ከ15 አገሮች መግዛቱን ጠቅሶ፣ 46 ከመቶው ከኢትዮጵያ የተገዛ መሆኑን አመልክቷል፡፡ 120 ቶን እህል ከኢትዮጵያ ገበሬዎችና የህብረት ሥራ ማህበራት ዩኒየን በመግዛቱ፣ 67 ሚሊዮን ዶላር ገበሬዎቹ ኪስ መግባቱንና ኢትዮጵያ ብዛት ያለው የምግብ እህል ከተገዛባቸው አምስት አገሮች አንዷ መሆኗን ጠቁሟል፡፡
የአዲስ አበባ የቁጠባ ቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝ የሰጠው ማስተባበያ
“አዲስ አድማስ” ጋዜጣ የዜጐችን የመኖሪያ ቤት እጥረት ችግር ለመፍታት በመንግስት በኩል እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትንና ውጤታቸውን እንዲሁም የአፈጻጸም ክፍተቶችን አስመልክቶ ለህዝቡ ትክክለኛና ሚዛናዊነቱን የጠበቀ መረጃ በመስጠት ኃላፊነቱን ይወጣል ብለን እናምናለን፡፡ እየተወጣም ነው፡፡ ሆኖም በአዲስ አበባ ቁጠባ ቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝ የሚካሄደውን የ40/60 ቁጠባ ቤቶች ልማት ፕሮግራም አፈፃፀም በተመለከተ በጋዜጣው እትሞች የወጡት መረጃዎች የተሳሳቱ ናቸው፡፡ በተለይም በቅፅ 13 ቁጥር 748 እና 750 ላይ ኢንተርፕራይዙን አስመልክቶ የወጡ ዘገባዎች በትክክለኛ የመረጃ ምንጭ ላይ የተመሰረቱ አይደሉም፡፡ ዘገባዎቹ የተመዝጋቢዎች ቁጥር፣ የሚገነቡት ቤቶች ብዛትና ዓይነት፣ የግንባታ ማነቆዎችን በተመለከተና በመሳሰሉ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩሩ ናቸው፡፡ በርዕሰ ጉዳዮቹ ዙሪያ ዘገባዎች መሰራታቸው ተገቢና ትክክል መሆኑን የምንቀበለው ቢሆንም በዘገባችሁ የቀረቡ አንዳንድ መረጃዎች ትክክለኛ ስላልሆኑ ተከታዩን ማስተካከያ እንድታወጡ እንጠይቃለን፡፡
በቅፅ 13 ቀጥር 750 እትም፤ የ40/60 ቤቶች ግንባታና የተመዝጋቢዎች ፍላጐት አይጣጣምም የሚል ዘገባ ወጥቷል፡፡ የኢንተርፕራይዙ እቅድ ባለ 2 እና ባለ 3 መኝታ ቤት የሚፈልጉ ተመዝጋቢዎችን ማስተናገድ አይችልም ይላል ዘገባው፡፡ ይሄ ፍፁም የተሳሳተና ትክክለኛ ባልሆነ መረጃ ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ ኢንተርፕራይዙ በ9 የግንባታ ሳይቶች የ13,881 ቤቶች ግንባታ እያካሄደ ሲሆን በእያንዳንዱ ሕንፃ ባለ 1፣ በላይ 2 እና ባለ 3 መኝታ ቤቶችን እያመጣጠነ በመገንባት ላይ ነው፡፡
በዚሁ እትም፤ በ40/60 ለሚገነቡ የንግድ ቤቶች አንድም ተመዝጋቢ አልተገኘም ተብሎ ተዘግቧል፡፡ ሆኖም ኢንተርፕራይዙም ሆነ የከተማ አስተዳደሩ የንግድ ቤቶችን የምትፈልጉ ተመዝገቡ ብሎ ያወጣው ማስታወቂያ የለም፡፡ ከነሐሴ 3-17 ቀን 2005 ዓ.ም ድረስ የተካሄደው ምዝገባ ዓላማው የመኖሪያ ቤት ችግር ላለባቸው ዜጐች ቁጠባን መሰረት አድርጐ ቤት ለመገንባት ነው፡፡ የንግድ ቤቶች ምዝገባ ሳይኖር በ40/60 የቤት ልማት ፕሮግራም የንግድ ቤት ተመዝጋቢዎች አልተገኙም የሚል ዘገባ ለመስራት የተፈለገበት ምክንያት ግልፅ አይደለም፡፡
35 በመቶ በባለ 1 መኝታ፣ 25 በመቶ በባለ 2 መኝታና 20 በመቶ ደግሞ በባለ 3 መኝታ ይመዘገባል ተብሎ ቢጠበቅም የተጠበቀው ሳይሆን ቀርቷል በሚል የቀረበውም ዘገባ በመረጃ ላይ የተመሰረተ አይደለም፡፡ መንግስት በ40/60 የቤት ልማት ፕሮግራም፣ ቤት ፈላጊዎችን ሲመዘግብ በባለ 1 መኝታ፣ በባለ 2 መኝታና በባለ 3 መኝታ ላይ ይሄን ያህል በመቶ ዜጐች ይመዘገባሉ ብሎ አቅዶ አልተነሳም፡፡ ሊነሳም አይችልም፡፡ የሚያመለክቱት በአንድ ሕንፃ ላይ የሚኖረውን የቤት ብዛት ምጣኔ እንጂ ከተመዝጋቢው ቁጥር ማነስና መብዛት ጋር የሚያያዝ አይደለም፡፡ መንግስት በአንድ ህንፃ የሚኖረው የማህበረሰብ ስብጥር የተመጣጣነ እንዲሆን ለማድረግ የተከተለው አቅጣጫ መሆኑን ልናስገነዝብ እንወዳለን፡፡
ኢንተርፕራይዙ ከተመዝጋቢዎች ቁጥር ጋር በተያያዘ ምክንያት ወደ ግንባታ የገቡ ቴፖሎጂዎችን እንደሚቀይር ተደርጎ የተዘገበውም ስህተት ነው፡፡ በአሁኑ ሰአት ባለ 12፣ ባለ 9 እና ባለ 7 ፎቅ 13,881 ቤቶችን (219 ብሎኮችን) በመገንባት ላይ ሲሆን በቀጣይነትም ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል፡፡ ከተገለፁት የሕንፃ ከፍታዎች በተጨማሪ በተወሰነ ቦታ በርካታ ሰው ለማስተናገድና ከተማዋን ከፍ ወዳለ ደረጃ የሚያሸጋግሩ ሕንፃዎችን ለመገንባት፣ ኢንተርፕራይዙ በራሱ ተነሳሽነት ባለ 18 እና ባለ 24 ፎቅ ከፍታ ያላቸው ህንፃዎች ዲዛይን አሰርቶ የሚመለከተው አካል እንዲያፀድቀው ልኳል፡፡
በመጨረሻም በሰንጋተራ እየተገነቡ ባሉ ቤቶች የሜትር ስኩየር የስፋት ልዩነት መከሰቱን በተመለከተ የቀረበው ዝርዝር መረጃ፣ ከኢንተርፕራይዙ እውቅና ውጭ የሆነና በትክክለኛ መረጃ ላይ የተመሰረተ አለመሆኑን እንገልፃለን፡፡
ፅንስ በተፈጠረ በሰባተኛው ወር ላይ የሚወለዱ ልጆች የጤናና የአካል እድገት ችግር ያጋጥማቸዋል?
ሁለት የህክምና ባለሙያዎችን ጋብዣለሁ፡፡ አንድ የፅንስና ማህፀን ሃኪም ሌላ ደግሞ የህፃናት ሃኪም ሁለቱም የሚሰሩት በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሲሆን ባነሳሁት ርዕስ ጉዳይ ላይ በዚህ ገፅ (አምድ) ቢታይና ቢነበቡ የእናንተን የአንባብያንን ደረጃ ይመጥኑ ይሆናል ብዬ የገመትኳቸውን ጥያቄዎች ብቻ ለማንሳት ሞክሬአለሁ፡፡
ዶ/ር ሶፋኒት ኃይሌ በአዲስ አበባ ዪኒቨርሲቲ ህክምና ፋክሊቲ የማህፀንና ፅንስ ህክምና ትምህርት ክፍል መምህርት እንዲሁም ሁለተኛ አመት የስፔሻላይዜሽን ትምህርት ፕሮግራም ተማሪ ነች፡፡
ዶ/ር ትንሳኤ አለማዬሁ በጥቁር አንበሳ ሆ/ል በህፃናት የትምህርትና የህክምና ክፍል በመስራት ላይ የሚገኝ ሃኪምና የሶስተኛ አመት የህፃናት ህክምና የስፔሻላይዜሽን ትምህርት ፕሮግራም ተማሪ ነው፡፡
ጥያቄ፡- መደበኛ ከሚባው የእርግዝና ጊዜ (ከዘጠኝ ወራት በፊት)፣ ቀድሞ በሰባተኛው ወር ላይ አንዲት እናት የእርግዝናው ጊዜ በቃኝ፣ ከዚህ በኋላ ጽንሱን ለመሸከም በአካልም በስነ ልቦናም ብቁ አይደለሁም፣ ብትል ማዋለድ ይቻላል?
ዶ/ር ሶፋኒት፡- በመጀመሪያ በሰባተኛው ወርም ሆነ ከዚያ በፊት ባለው ጊዜ ያለ በቂ ምክንያት ፅንስን ማቋረጥ በህግ አይፈቀድም፤ በህክምናው ደግሞ ፅንስ በማህፀን ውስጥ ተገቢውን ጊዜ ባለማቆየቱ የሚገባውን የሳንባ፣ አንጀትና የአእምሮ እድገት አያገኝም ማለት ነው፡፡ በእኛ ሃገር ደግሞ ህፃናትን የምናቆይበት ማሞቂያ ክፍል በበቂ ሁኔታ የተደራጀ ስላልሆነ እክል ሊያጋጥማቸው ይችላል፡፡ ይኽም እስከ ማት ሁሉ ሊደርስ የሚችልበት አጋጣሚ ይኖራል። በእናትም ላይ ድህረ ወሊድ የጤና እክል ሊያጋጥም ይችላል፡፡
ጥያቄ፡- ከሚጠበቀው ጊዜ በፊት የሚወለዱ ልጆች ከጤናና ከአካላዊ እድገት ጋር በተያያዘ የሚያጋጥማቸው ችግር ምንድን ነው?
ዶ/ር ትንሳኤ፡- ከሚጠበቀው ጊዜ በፊት ሲባል ብዙ ጊዜ ከ37ኛው ሳምንት በፊት የሚወለዱ ልጆች ናቸው፡፡ ብዙ ጊዜ ከሚጠበቀው ክብደት በታች ሆነው ይወለዳሉ፡፡ ይኸውም አዲስ የሚወለዱ ልጆች ቢያንስ ክብደታቸው ሁለት ነጥብ አምስት ኪሎ ግራም (2.5ኪሎ ግራም) እና ከዚያ በላይ መሆን ሲገባቸው ከዚህ በታች ይሆናሉ፡፡ ሆኖም ይህ ሁኔታ እድሜአቸው ከሁለት አመትና ሁለት አመት ተኩል በላይ ሲደርሱ በክብደትም በቁመትም ከሌሎች በጊዜአቸው ከተወለዱ ልጆች ጋር ይስተካከላሉ፡፡ ሌላው በተደጋጋሚ የሚያጋጥመን በእነዚህ ቀድመው ከ37ኛው ሳምንት በፊት የሚወለዱ ልጆች ሳንባቸው ሳይጠና ወይም ሳይዳብርና እድገቱን ሳይጨርስ ይወለዳሉ፡፡ ሳንባ ልጅ በእናት ማህፀን ውስጥ እያለ አራት የእድገት ደረጃዎች ይሩታል፡፡ ይሁንና ቀድመው ያለ ጊዜአቸው የሚወለዱ ልጆች ይህን የሳንባ እድገት ሳይጨርሱ ይወለዳሉ፡፡ ይህንም ለማስተካከል የምናደርገው ህክምና ይኖራል፡፡ በተለይ በማሞቂያ ክፍል በሚቆዩበት ጊዜ አይናቸው ላይ፣ አንጀት ላይ የተለያዩ ኢንፌክሽን እደዚሁም በደም ዝውውር ላየ የሚከሰቱ ችግሮች ይኖራሉ፡፡
ጥያቄ፡- ሁሉም ሊከሰቱ የሚችሉት ችግሮች በሙሉ በህክምናው ሊረዳ የሚችል ነው ካደጉ በኋላስ ችግሮቹ ሊያመጡት የሚችሉት ችግር ይኖራል?
ዶ/ር ትንሳኤ፡- የሳንባ አለመዳበር ጋር በተያያዘ እናት ከመውለዷ በፊት የምሰጠው በተለይ ከ48 ሰዓት በፊት የምንሰጠው መድኃኒት አማካኝነት ሊመጡ የሚችሉ ችግሮችን ለመከላከል የሚቻልበት ሁኒታ አለ….
ጥያቄ፡- ከመደበኛው ጊዜ ቀድማ እደምትወልድ ከታወቀ ማለት ነው?
ዶ/ር ትንሳኤ፡- አዎ፣ ያለጊዜዋ ቀድማ እደምትወልድ ከታወቀ፤ ካልታወቀ ደግሞ (ድንገተኛ ከሆነ) ቀጥሎ በሚደረግ ህክምና (ይኸውም ሁሉም የህክምና መሳሪያዎችና አገልግሎቶች በተሟሉበት ሁኔታ) ከ70 እስከ 80 በመቶ የሚወለዱት ልጆች የተስተካከለ እድገት እዲኖራቸው ማገዝ ይቻላል፡፡
ጥያቄ፡- ከፍላጎት ውጭ በሆነ ሁኔታ ደግሞ እናት በተለያዩ አጋጣሚዎች አንዴ ከመደበኛው ጊዜ በፊት ምጥ ቢከሰትባት በቀጣዮቹ እርግዝናዎች ተመሳሳይ ሁኔታ ሊያጋጥማት ይችላል?
ዶ/ር ሶፋኒት፡- አዎ፣ እንዲያውም አንዳንድ ጥኖቶች አንዴ ቀድሞ ምጥ የተከሰተባት እናት በቀጣዩ ጊዜ የማጋጠሙ እድል እስከ 40 በመቶ ሊደርስ ይችላል የሚል መነሻ ያመላክታሉ። ይህ የሚሆንበት ምክንያት ምንድን ነው በመጀመሪያው እርግዝና ቀድሞ ምጥ እንዲከሰት ያደረገው ችግር በተመሳሳይ በሁለተኛውና በቀጣዮችም እርግዝናው ቀድሞ ሊወለድ ይችላል፡፡ ለምሳሌ በታችኛው የመራቢያ ክፍል ላይ ኢንፌክሽን ከነበረ ወይም የተለያዩ የአባላዘር በሽታዎች ተከስተው ከነበረና እነዚህም ችግሮች በአግባብ ካልታከሙ ተከታዮቹ ፅንሶችም ቀድሞ የመወለድ አጋጣሚ ይኖራቸዋል፡፡ ከዚህ ሌላም ከአንድ በላይ ወይም መንታ ልጆችን ያረገዘች እናት ላይ ቀድሞ ምጥ ሊከሰት ይችላል፣ይኽም በተከታዩ እርግዝና በተመሳሳይ ሁኔታ ምጥ ከመደበኛው ጊዜ በፊት እንዲከሰት ያደርጋል፡፡ ስለዚህ ዋናው ነገር አንዴ ምጥ ከ42 ሳምንታት በፊት የተከሰተባት እናት በቀጣዮቹ እርግዝናዎች ተመሳሳይ ክስተት ሊያጋጥም ስለሚችል ቀድሞ መዘጋጀት ይጠይቃል፡፡
ጥያቄ፡- ቀድሞ ያለጊዜው የምጥ ክስተት ከዘር ጋር ይያያዛል ለምሳሌ እናት በሰባተኛው ወር ብትወልድ ልጇም እዲህ ያለ አጋጣሚ ሊኖራት ይችላል?
ዶ/ር ሶፋኒት፡- በዘር የሚተላለፍ ነገር አይደለም ቀድሞ ምጥ የመከሰት ችግር፡፡ ከዚህ ይልቅ በተቃራኒው ዘግይቶ ከ42 ሳምንት በኋላ የሚወልዱ እናቶች ልጆቻቸውም ተመሳሳይ ችግር ሊያጋጥማቸው ይችላል፡፡
ጥያቄ፡- ዘገየ ሲባል ከስንት ወራት ወይም ሳምንታት በላይ ሊዘልቅ ነው ቀደመ ሲባልስ?
ዶ/ር ሶፋኒት፡- ከሚገባው ጊዜ በላይ ዘገየ የምንለው ከ42 ሳምንታት ወይንም 294 ቀናት በላይ ሲሆን ነው፤ ይኽም የሚሰላው እናት የመጨረሻውን የወር አበባ ካየችበት የመጀመሪያው ቀን ጀምሮ ነው፡፡ በዚህ ሂደት ግን ብዙ ጊዜ ስህተት ያጋጥማል፡፡ እናቶች የመጨረሻውን የወር አበባ ክስተት ያለማስታወስ ወይም ልብ ብሎ ያለመመዝገብ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ከዚህ ሌላም የሚዛባ የወር አበባ ክስተት ያላቸው እናቶችና ሆርሞናል የሆኑ (እንክብልና የመርፌ) ወሊድ መቆጣጠሪያ መንገዶችን የሚጠቀሙ እናቶች ላይ እርግዝና በትክክል የተከሰተበትን ቀን ያለመረዳት ሁኔታ ያጋጥማል፡፡ ስለዚህ እርግዝናው ዘግይቷል ወይም ቀድሟል ከሚለው ድምዳሜ መፊት እነዚህን ጉዳዮች ቀድሞ ማጣራት ያስፈልጋል ማለት ነው፡፡
ጥያቄ፡- በአንድና በሌላ ምክንያት እርግዝና ከተከሰተ በሰባተኛው ወር ላይ የወለደች እናት ጡቷ በዚያን ወቅት በቂ የሆነ የወተት ምርት ለልጇ ይሰጣል?
ዶ/ር ሶፋኒት፡- ጡት ወተት ማምረት የሚጀምረው እርግዝናው ልክ ከተከሰተበት ቀን ጀምሮ ነው፡፡ የተለያዩ አካላዊ ዝግጅቶች ያካሂዳል ስለዚህ ልጁ በሰባተኛውም ወር ቢወለድም በቂ የሆነ ወተት ከእናቱ ያገኛል፡፡ ልጁ እንደተወለደ መጥባት ይጀምራል ያ እናት ወተት መስጠቷን ምልክት ሰጭ ነው፡፡ ጡት ሲጠባ ወተቱ ከእናት ወደ ልጅ ሲወርድ ደግሞ መልዕክትከእናት ጡት ወደ መካከለኛ የጭንቅላት ክፍል ያደርሳል፤ ይህ ወተት መመረት እዳለበት የሚጠቁም ምልክት ነው፡፡ ወተት መመረት ይቀጥላል፡፡ ብዛቱም የሚወሰነው በሚጠባው መጠን ነው፤ ብዙ በተጠባ ቁጥር ብዙ ምርት ይኖራል፣ መጥባት ሲቀንስ ይቀንሳል፡፡
አበበ፡- ዶ/ር ሶፋኒት ኃይሌ አመሰግናለሁ
ዶ/ር ሶፋኒት፡- እሺ አመሰግናለሁ