Administrator

Administrator

ፒያሳ አካባቢ የሚገኘውና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዓላትን ከነትውፊታዊ ይዘታቸው በማክበር የሚታወቀው ኤልቤት ሆቴል የ2006 ዓ.ም መጀመርያ ዐውደዓመትን ዋዜማ በባሕላዊ ይዘት እንደሚያከብር አስታወቀ፡፡ ከቀኑ 11 ሰዓት በመጀመር በሚቀርበው ዝግጅት ወጣቶች የባህል ልብስ ለብሰው “አበባየሆሽ” ብለው የሚዘፍኑበት ሲሆን የዘመን አቆጣጠርን አስመልክቶ ማብራሪያ በባለሙያ ይሰጣል፡፡ በዝግጅቱ የባሕል ዘፈኖች፣ ግጥሞችና መጣጥፍ እንደሚቀርቡና የችቦ ማብራት ሥነ ሥርአትም እንደሚኖር ይጠበቃል።

በደራሲ አለማየሁ ገላጋይ የተጻፈው ‘የብርሃን ፈለጎች’ የረጅም ልቦለድ መጽሃፍ ባለፈው ሰኞ ለንባብ በቃ፡፡ ከዚህ በፊት አጥቢያ፣ ቅበላ፣ ስብሃት ገብረ እግዚያብሄር - ህይወትና ክህሎት፣ ኩርቢት፣ የፍልስፍና አጽናፍና ኢህአዴግን እከስሳለሁ የተሰኙ መጽሃፍትን ለአንባብያን ያቀረበው ደራሲው፣ በቅርቡ ለንባብ የበቃውንና በደራሲ ስብሃት ገብረ እግዚያብሄር ዙሪያ የሚያጠነጥነውን ‘መልከዓ ስብሃት’ የተሰኘ መጽሃፍም በአርታኢነት አዘጋጅቷል፡፡
248 ገጾች ያሉትና ለደራሲው ስምንተኛ ስራው የሆነው የብርሃን ፈለጎች የረጅም ልቦለድ መጽሃፍ፣ በተለያዩ የመጽሃፍት መደብሮችና በአዟሪዎች በ45 ብር እየተሸጠ ይገኛል፡፡
ደራሲ አለማየሁ ገላጋይ በአዲስ አድማስና በሌሎች ጋዜጦች እንዲሁም መጽሄቶች ላይ ለረጅም አመታት የተለያዩ ስነጽሁፋዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ጽሁፎችን በማቅረብ ይታወቃል፡፡

በ40 ዎቹ መጨረሻ ዕድሜዋ ላይ የምትገኘው አንጋፋዋ ድምፃዊ ሐመልማል አባተ፤ ሰሞኑን ዘጠነኛ አልበሟን ለጆሮ አብቅታለች፡፡ በአዲሱ አልበሟ ምን አዲስ ነገር ይዛ መጣች? የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ሰላም ገረመው ከሐመልማል አባተ ጋር ተከታዩን ቃለምልልስ አድርጋለች፡፡

ብዙ ጊዜ አልበም የምታወጪው የበአላት ሰሞን ነው፡፡ ይሄ በአጋጣሚ ነው ወይስ ሆን ብለሽ?
አጋጣሚ ነው፡፡ ከዚህ በፊት “አውደ አመት” የሚል ካሴት ለአዲስ አመት አውጥቼ ነበር፡፡ ከዛ በኋላ ሠው ሁልጊዜ ለአዲስ አመት ካሴት የማወጣ ይመስለዋል፡፡ እንደ አጋጣሚ ሆኖ የአሁኑም አልበሜ ሄዶ ሄዶ አዲስ አመት ጋ ደረሠ፡፡ በዚህ ደሞ ደስተኛ ነኝ፡፡
ከኮፒ ራይት ጥሰት ጋር በተገናኘ በቀዳሚነት “ካሴት አላወጣም” ያልሽው አንቺ ነሽ፡፡ ውሳኔሽ አልጐዳሽም?
እርግጥ አንድ ነገር ስትፈልጊ አንድ ነገር ታጫለሽ፡፡ በፊት የሚሠራው ከቨር ነበር፤ ከቨር ይሠራና ይላካል፡፡ በዚህ ጊዜ ሁሉም ሰው አንድ አይነት ጥራት ያለው ስራ አያገኝም፡፡ ምክንያቱም ሁሉም በራሱ ቴፕ ነበር የሚቀዳው፡፡ አንዳንዴ ክፍለ ሀገር ሔጄ የተቀዳውን ድምፄን ስሠማው፣ የህፃን ልጅ ድምፅ የሚመስልበት ጊዜ አለ፡፡ አንዳንድ ቦታ ደግሞ የወንድ ድምፅ ይመስላል፡፡ ያኔ ነው ውሳኔ ላይ የደረስኩት። “ከቨር የሚባል ነገር አይታተምም፤ ካሴቱ በፋብሪካ ነው የሚታተመው” ብዬ ወሠንኩ። ምክንያቱም ሠው የሚከፍለው ገንዘብ እኩል ነው፤ ግን የተለያየ ጥራት ነው የሚያገኘው። አሁን ካሴቱን እራሱ በፋብሪካ አሳትሜ ሁሉም ሠው አንድ አይነት ጥራት ያለው ሥራ እንዲያገኝ እየጣርኩ ነው። ለእኔ ምናልባት ሊጐዳኝ ይችላል፡፡ ቢሆንም ይሔንን ማድረግ የግድ ነው፡፡ በኮፒ ራይት ጥሰት ዙሪያ መንግስት መፍትሔ እንዲሰጠን ብዙ ጊዜ ጠይቀናል፡፡ ለረጅም ጊዜ ጠብቀናል፡፡ ህጉ ተፈፃሚ መሆን ነበረበት፡፡ ነገር ግን የኮፒራይት ጥሰት ፈጽመው የምናሳስራቸው ሠዎች ቶሎ ይፈታሉ፡፡ ይሄ ተገቢ አይደለም፡፡ አሁን ትንሽ ለውጥ እየታየ ነው፡፡ የሚመለከተው ወገን ለጉዳዩ ትኩረት ቢሠጠው እኮ አርቲስቱ ብቻ ሳይሆን ሁሉም ተጠቃሚ ነው፡፡ እኛ ሀብታም ስንሆን መንግስትም ሀብታም ይሆናል፡፡ እና አሁንም ተስፋ አንቆርጥም፡፡
የአሁን ዘመን ድምፃውያን በቴክኖሎጂ ይታገዛሉ። ይሄ ነገር ጥቅሙ ነው ጉዳቱ የሚያመዝነው?
ቴክኖሎጂ ጥቅም እንዳለው ሁሉ ጉዳትም አለው፡፡ የድሮ አሠራር አድካሚ ቢሆንም ደስ ይላል፡፡ ሁሉም ሙዚቀኛ እኩል አጥንቶ፣ እኩል ሠርቶ ቀጥታ ነበር የሚቀዳው፡፡ አንድ ዘፈን ሰርተን ሰርተን ሊያልቅ ሲል ከተሳሳትን፣ እንደገና ሀ ብለን ነበር የምንጀምረው፡፡ ግን ቀጥታ እየሠሙ መቀዳት በጣም ደስ የሚል ነገር አለው። አሁን ደግሞ ቴክኖሎጂው በጣም አግዞናል፡፡ ብሳሳት እዛችው የተሳሳትኩበት ቦታ ብቻ ነው የምንቀዳው። ግን ኦሪጅናሉን የድምፅ ቅላፄ እየወሠደው ነው። እርግጥ እንደ ድምፃዊው ችሎታ ይለያያል፡፡ ለምሳሌ ቴክኖሎጂ እንዳለ ሆኖ በጥንቃቄና በጥራት መስራት ይቻላል፡፡ ይሄ ግን በባለሙያው ብቃት ይወሰናል፡፡ አንዳንዴ የሚዘገንን ነገር እሠማለሁ፡፡ አንዴ ሰምተሽው ሆ ብሎ የሚጠፋ ነገር ይሆናል፡፡ እናም ቴክኖሎጂ ጥቅምም ጉዳትም አለው፡፡
በኮምፒውተር ታግዘው አልበም የሚያወጡ አርቲስቶች በተለይ መድረክ ላይ ያንኑ ድምጽ ለማውጣት ሲቸገሩ ይታያል…
ልክ ነው፤ ድምፅ ላይ በጣም ችግር ያመጣል። ለዚህ ነው በተፈጥሮ ድምፅ መቀዳት ያለብን። አንድ ዘፋኝ ያልሆነ ሠው የድምፅ ልምምድ በማድረግ ዘፋኝ መሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን በእነዚህ የኮምፒውተር ሲስተሞች ታግዞ ከሰራ እንደምናየው ነው፤ መድረክ ላይ ያስቸግራል፡፡
አልበም በማውጣት ረገድ ከአሁኑኑ ከድሮው አሰራር የትኛው ቀና ነው? ለአርቲስቱ ማለቴ ነው…
የመጀመሪያ ካሴቴ የወጣ ጊዜ እኮ እንደ አሜሪካ ሰለብሪቲ ነበር የምንሠራው፡፡ ሁሉም ነገር በአሳታሚው በኩል ነው የሚያልቅልሽ። አሁን ግን በኮፒራይት ጥሰት የተነሳ ነጋዴው ከስራው ወጥቷል፡፡ ያሉትም ቢሆኑም በጣም እየከበዳቸው ነው፡፡ ብዙ ብር ካወጡ በኋላ ስራው ኮፒ ስለሚሆን አይደፍሩትም፡፡ አሁን ትንሽ ለውጥ አለ፡፡ በ2006 ደግሞ የተሻለ ለውጥ ይመጣል ብዬ አስባለሁ፡፡ እስከዛው ግን በግላችን እየሞከርን ነው። አልበም ሲሰራ ብዙ ወጪዎች አሉ፡፡ አልበሙን ካስደመጥን በኋላ ከኮንሠርት እናገኛለን በሚል ነው የምንሰራው፡፡
እስቲ ስለአዲሱ አልበምሽ ንገሪኝ…ወጪውን፣ አሳታሚውንና ስለ ስራዎችሽ ይዘት…
አልበሜ መጠሪያው “ያደላል” የሚል ነው። ስያሜው ብዙ ትርጉም አለው፡፡ አርቲስቱን ቤቱ ቁጭ ብሎ የሚዘርፈውን የሚመለከት ሊሆን ይችላል፡፡ ሰሙ ደግሞ እግዚአብሔር በአምሳሉ ሲፈጥረን ለሠው አድልቷል የሚል ነው፡፡ ወርቁን እንደተፈለገ መተርጐም ይቻላል። በዚህ አልበም ሳይካተቱ የቀሩ ብዙ ትላልቅ ስራዎች አሉ፡፡ ሁሉም ነገር ሊወጣ ስለማይችል ያልተሠሩት ከተሠሩት በላይ አሉ። ለአዲሱ አልበሜ ብዙ ወጪ ነው ያወጣሁት፡፡ በዚህ አጋጣሚ መግለጽ የምፈልገው ካሴቱ ላይ ከተለመደው ውጭ ብዙ ስራዎች መካተታቸውን ነው፡፡ ሌላ ጊዜ የተለመደው ሲዲ ላይ ነበር፡፡ አሁን ግን ካሴቱን “C80” አድርጌ 16 ዘፈኖች ተካተውበታል፡፡ ሲዲው ላይ 14 ዘፈኖች አሉ፡፡ አሁን በአሜሪካ ካሴት ፋሽን ሆኗል፡፡ የእኛ አገር ሲዲ ጥራቱ ብዙም አይደለም፡፡ ስለዚህ ካሴቱን ተመራጭ አድርጌያለሁ፡፡ ሙዚቃውን ሙሉ በሙሉ ያቀናበረው አበጋዝ ነው፡፡ በግጥምና በዜማ አዳዲስ ደራሲዎችን አሳትፌያለሁ:- ምስክር አወል፣ ማስረሻ ተፈራ፣ የእኔው አካሉ፣ ፀጋዬ ስሜ (ጥሩ ጉራጊኛ ሠጥቶኛል) የሸዋ ኦሮሞ ባህላዊ ዘፈንም ሠርቼአለሁ። እስከዛሬ የሀረር ኦሮሞን ባህላዊ ዜማዎች ነበር የምሰራው፡፡ አሳታሚዋ እኔ ነኝ፡፡ ለዚህ ስራ ከ500ሺ ብር በላይ ወጪ አድርጌአለሁ። አከፋፋዩ ደግሞ ትልቅ ስም ያለው ሮማርዮ ሪከርድስ ነው። በጣም ቆንጆ ስራ ነው። አንድን ስራ እኔ ካላመንኩበት አላወጣውም፡፡ ያለዚያ እኮ በየአመቱ ካሴት አወጣ ነበር፡፡
ጳጉሜ 5 ለአዲስ ዓመት ዋዜማ በሚሊኒየም አዳራሽ ትዘፍኛለሽ፡፡ ዝግጅት ምን ይመስላል?
የምንችለውን ያህል እያደረግን ነው። ከአዳዲሶቹ ዘፈኖችም የተወሰኑትን እጫወታለሁ። በአዲስ አመት ያልተደሠተ ሰው አመቱን ሙሉ አይደሠትም ይባላል፡፡
በ2005 ዓ.ም በአገር ደረጃ ምን ለውጥ አስተውለሻል?
ሁሌም መጥፎ ጐን ብቻ ማውራት ጥሩ አይደለም፤ በጐ ጐንም መወራት አለበት። ለምሳሌ ከአሠራር ለውጥ ብንነሳ፣ የውልና ማስረጃ ቢሮ ትልቅ አርአያ ነው፡፡ ልክ እንደ ውጪ አገር ቁጥር እየሰጠ ነው የሚያስተናግደው፡፡ ያለ ወረፋው የሚገባ የለም፡፡ በዚህ ረገድ አቶ ይርጋን በጣም ማመስገን ነው የምፈልገው፡፡ ምክንያቱም ሌላ ቦታ እኛ ቁጭ ብለን ስንጠብቅ፣ ነጮች በቅድምያ ሲስተናገዱ ነው የምናየው። ቅር ያለኝ የቦሌ መንገድ ነው፡፡ እርግጥ ነው የቦሌ መንገድ በጣም አምሮበታል ፤ ነገር ግን ባለ ህንፃዎቹ ፓርኪንግ አለመስራታቸው እንዳለ ሆነ የፓርኪንግ ችግር ተፈጥሯል፡፡ እዚያ አካባቢ መኪና አቁሞ እቃ መግዛት አልተቻለም። ድሮ ቦሌ የሚታወቀው ካፌዎቹ በረንዳ ላይ ሠዎች ቁጭ ብለው ሲዝናኑ ነበር፡፡ አሁን ከሠኞ እስከ አርብ ጭር ብሎ ነው የሚውለው፡፡ ሌላው የመንገዶቹ አሠራሮችና የመብራት ሁኔታ አካል ጉዳተኛን ያማከለ አይደለም፡፡ እነሱም ዜጐች ናቸው፡፡ ይሄን ጉዳይ በተመለከተ ሁለት ቀን በግሌ መንገድ ትራንስፖርት ሄጄ ነበር፡፡ ግን የማናግረው ሰው ማግኘት አልቻልኩም፤ ስብሠባ ናቸው በሚል ምክንያት፡፡ በኪነጥበብ ዘርፍ ግን ምንም ለውጥ የለም፤ አርቲስቱ እየደከመ ነው ያለው፡፡ እኔ ውጪ ሀገር ሠርቼ የመጣሁትን ነው እየበላሁ ያለሁት እንጂ፤ ኪነ ጥበብ ቀዝቅዟል፡፡
በትርፍ ጊዜሽ ምን ትሰርያለሽ?
የቤት ስራ ያስደስተኛል፤ አበስላለሁ። አትክልቶችን እንከባከባለሁ፡፡ የሁለት ልጆች እናት ነኝ፡፡ ትልቋ ልጄ ማክዳ ትባላለች። በዚህ አመት ከአሜሪካ፣ ፖኖን ዩኒቨርስቲ ትመረቃለች፡፡ አሜሪካን አገር ጐበዝ ተማሪዎችን ለማበረታታት የምርቃት ሰርተፍኬታቸውን ፕሬዚዳንቱ ናቸው የሚሰጡት - በኋይት ሀውስ፡፡ የእኔም ልጅ ከክሊንተን፣ ከቡሽ እና ከኦባማ እጅ ወስዳለች። ይሔ ደስ ይላል፡፡ አሁን በአንትሮፖሎጂ ትመረቃለች፡፡ ከዚያ ወደ አገሯ መጥታ የመስራት ፍላጐት አላት፡፡
ሀመልማል ትዳር ትፈራለች እንዴ?
ምን ያስፈራል? እግዚአብሔር ላለለት ሠው በጣም ይመከራል፡፡ ከመጣ ደግሞ ሠርግ መደገስ ይቻላል፡፡ ልጆቼም አንዳንዴ ያሾፉብኛል፤ “እኛ ሚዜ እንሆናለን፤ አንቺ ደግሺ፤ ግን ባል የለም” ይሉኛል፡፡ አሁንም ከመጣ እሰየው ነው፡፡
ምን ዓይነት ሙዚቃዎችን ማድመጥ ትወጃለሽ?
ማናቸውንም የትዝታ ዘፈኖች አደምጣለሁ። ከበፊቶቹ ሙሉቀን ለእኔ ልዩ ነው፤ ከወጣት የጐሳዬን ዘፈኖች እወዳለሁ፡፡ ሁሉም ግን የራሱ የሆነ ጣዕም አለው፡፡
በ2005 ዓ.ም ያስደሰቱሽንና ያስከፉሽን ጉዳዮች ጥቀሺልኝ…
የጥበብ አጋራችን የነበረውን ድምፃዊ እዮብን ማጣታችን አሳዝኖኛል፡፡ የእዮብን መልካምነት ለማወቅ የቀብር ስነስርዓቱን መመልከት በቂ ነው፡፡ እንደ አንጋፋዎቹ ነው በበርካታ ህዝብ የተሸኘው፡፡ ሌላው በመብራት ሃይል ችግር ቤቴ ተቃጥሎ ነበር። ምንም እንኳን ራሱ መብራት ኃይል ቢሠራውም። እንደዚህ አይነት ስህተት እንዳይከሠት መብራት ሀይል ጥንቃቄ ማድረግ አለበት፡፡ ካሴቴ አልቆ ለ2006 አዲስ ዓመት መድረሱ ደግሞ በዓመቱ ካስደሰቱኝ ነገሮች ዋነኛው ነው፡፡
ሞሃ ለስላሳ እንዴት 500ሺህ ብር ስፖንሰር አደረገሽ?
ይሄ ገና ያልተሰራና ያልተጣራ ነገር ነው፤ ስለዚህ በዚህ ጉዳይ ላይ ምንም መናገር አልፈልግም፡፡
ቀጣይ ዕቅድሽ ምንድነው?
በሙዚቃው መገስገስ ነው የምፈልገው፤ከራሴ ስራ አልፌ የሌሎችን ፕሮዲዩስ ማድረግ እፈልጋለሁ። አመል ፕሮዳክሽን የተባለ ድርጅት አቋቁሜያለሁ፤ በዛ በኩል የሌሎችን ስራዎች ለማሳተም እቅድ አለኝ።
ለዋዜማ ኮንሰርት ምን ያህል ተከፈለሽ?
ይሄ የግል ጉዳይ ነው፤ መናገር ይከብዳል፤ ምክንያቱም እኔ እንደሌሎች ያልተከፈለኝን ተከፈለኝ ብዬ አጋንኜ ማውራት አልፈልግም፡፡ ከአዘጋጆቹም ጋር ጉዳዩ በግል እንዲያዝ ተነጋግረናል፡፡ ስለዚህ መናገሩ አስፈላጊ አይደለም፡፡

“...እስከአሁን የማልረሳው አንድ አጋጣሚ አለኝ፡፡ አንዲት እናት በቤትዋ ሳለች ምጥ ጀምሮአታል፡፡ ከዚያም ይበልጥ ስትታመምባቸው እኔ ወዳለሁበት በሲዳማ ዞን ቦና ዙሪያ ወረዳ ባለው የጤና ጣቢያ ያመጡአታል፡፡ እኔም ስመለከታት የማህጸን መተርተር ደርሶባታል፡፡ አጋጥሞኝ ስለማያውቅ እጅግ በጣም ነበር የደነገጥኩት፡፡ በእርግጥ በኦፕራሲዮን ማህጸንዋ ይወጣል። ነገር ግን እሱም እርምጃ ቢወሰድ እና ሕይወቷ ቢተርፍ ማህጸንዋ ሲወጣ ወደፊት ልጅ መውለድ ስለማትችል ባለችበት ሕብረተሰብ አስተሳሰብ የምትገለል ትሆናለች፡፡ ምክንያቱም ልጅ ለወደፊቱ መውለድ ስለማትችል የነበራት ባልም ይፈታታል... ሌላ ባልም አያገባትም፡፡ በህብረተሰቡም ዘንድ ተቀባይነት ስለማይኖራት ዝም ብላ የምትኖር ትሆናለች፡፡ይሄንን ነገር ዛሬ ላይ ሳስበው ይቆጨኛል፡፡ ምክንያቱም እንደአሁኑ እውቀቱ ቢኖረኝ ኖሮ ወደከፍተኛ ሕክምና ጊዜ ሳልፈጅ አስተላልፌ በሴትየዋ ላይ የደረሰው ችግር ሊቃለል ይችል ነበር…”
ከላይ ያነበባችሁት ገጠመኝ ከአንድ የጤና መኮንን የቀረበ ነው፡፡ የጤና መኮንኑን ያገኘነው በሐዋሳ በኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር እና በዞኑ የጤና መምሪያ እንዲሁም በፕላን ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ ትብብር WATCH (women & their child health) የእናቶችና ሕጻናት ጤናን ለማሻሻል በተነደፈው ፕሮጀክት ድጋፍ ስልጠና ሲወስድ ነበር፡፡ በኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር WATCH (women & their child health) የተሰኘው ፕሮጀክት አስተባባሪ የሆኑት አቶ ቢንያም ጌታቸው እንደሚገልጹት ድጋፍ የሚገኘው ከካናዳ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ሲሆን በዋናነት የሚሰራውም የእናቶችን እና ሕጻናትን ሞት መቀነስ ነው፡፡ ስለዚህም ከዚህ ማህበር ጋር በመተባበር የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር Basic emergency obstetric & new born care (መሰረታዊ የሆነ አጣዳፊ የእናቶችና የህጸናትን ሞት መቀነስ) የሚባለውን የስራ እንቅስቃሴ ስልጠና እና ለጤና ጣቢያዎች የአቅም ድጋፍ የማድረግ ስራ እየሰራ ይገኛል፡፡ የWATCH ፕሮጀክት በኢትዮጵያ ውስጥ በሶስት ክልል ውስጥ በሚገኙ 8/ ስምንት ወረዳዎች ተግባሩን እያከናወነ ሲሆን ይኼውም በደቡብ ሲዳማ ዞን፣ በኦሮሚያ ጅማ ዞን፣ በአማራ ክልል በሰሜን ወሎ ዞን ነው፡፡
በካናዳ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር አማካኝነት በተዘረጋው በዚህ ፕሮጀክት ከውጭ በመጡ ባለሙያዎች የኢትዮያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር አባል ለሆኑ ከፍተኛ ሐኪሞች ስልጠና ተሰጥቶ የነበረ ሲሆን እነዚህ የሰለጠኑ ባለሙያዎችም ከተለያዩ ወረዳዎች ለመጡ የጤና ባለሙያዎች መሰረታዊ የሆነ አጣዳፊ የእናቶችና የህጸናትን ሞት በመቀነስ ረገድ ክህሎትን እያስጨበጡ ይገኛሉ ብለዋል የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ ቢንያም ጌታቸው፡፡
በማሰልጠን ተግባር ላይ ከተሰማሩት የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስትና በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ዶ/ር ይፍሩ ብርሀን እንደሚሉት ለእናቶች ሞት ምንክያት የሚሆኑት ነገሮች በሶስት ወይንም በአራት ሊከፈሉ ይችላሉ፡፡
1/ እናቶችና ቤተሰቦቻቸው የጤና አገልግሎት ለማግኘት አለመፈለግ፣
እነዚህ እናቶች የጤና ችግር ሲያጋጥማቸው በአካባቢው አዋላጅ ነርሶች አማካኝነት ለመውለድ መዘጋጀት ወይንም ምንም ክትትል አለማድረግ እንዲሁም የጤና ችግር ሲገጥማቸው በአፋጣኝ ወደ ጤና ተቋም ወይንም ሆስፒታል አለመምጣት ነው፡፡
2/ በሚኖሩበት አካባቢ የህክምና አገልግሎት የሚሰጥ ተቋም አለመኖር ፣
3/ ወደጤና ተቋም ከመጡ በሁዋላ የጤና ባለሙያው የደረሰባቸውን ችግር ለይቶ አለማወቅ፣...ይህ በአሁኑ ወቅት እንደከፍተኛ ችግር የሚቆጠር ነው፡፡ ምክንያቱም ይህ የሚያሳየው የእውቀት ችግር መኖሩን ሲሆን በዚህም ምክንያት ለእናቶቹ በጊዜው አስፈላጊው ሕክምና የማይሰጥ እና ወደከፍተኛ ሕክምና እንዲተላለፉ አለመደረጉን ነው፡፡ አንዳዶች ሕመም ሲጠናባቸው ወደአቅራቢያው ጤና ተቋም ሲሄዱ በዚያ በሚፈጠረው አላስፈላጊ መዘግየት ምክንያት ሕይወታቸው ከአደጋ ላይ ይወድቃል፡፡ አልፎ አልፎም አግባብ ያልሆነ ሕክምና የሚሰጥበት አጋጣሚ ስለሚኖር ይህንን ክፍተት የሚሞላ አሰራር መኖር አለበት፡፡ ስለዚህም እስከአሁን ባየነው የስልጠና ሂደት ሰልጣኞቹ ሲመጡ የነበራቸው የእውቀት ደረጃ እና ሲጨርሱ የሚኖራቸው ደረጃ በጣም ይለያያል ብለዋል ዶ/ር ይፍሩ ብርሀን፡፡
ሌላው አሰልጣኝ ዶ/ር እንዳለ ሲሳይ ይባላሉ፡፡ ዶ/ር እንዳለ በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የማህ ጸንና ጽንስ ሐኪምና አስተማሪ ናቸው።
“...ይህ ሆስፒታል ሪፈራል ሆስፒታል ስለሆነ ከሌሎች የህክምና ተቋማት የተላኩ ታካሚ እናቶችን ያስተናግዳል፡፡ ነገር ግን በአብዛኛው የሚመጡ እናቶችን ለማዳን በጣም ፈታኝ የሚሆን ሲሆን ይህም ወደሆስፒታሉ የሚልኩ የጤና ተቋማት ጊዜን በአግ ባቡ አለመ ጠቀማቸው ነው፡፡ ለባለሙያዎቹ ስልጠና የሚሰጠው በሚሰሩበት ጤና ተቋማት ባላቸው አቅም ሊያክሙ የሚችሉትን እንዲያክሙና ከአቅማቸው በላይ የሆነውን ግን ጊዜ ሳይ ፈጁ ወደከፍተኛ ሕክምና እንዲልኩ የሚያስችል ነው። ምን አይነቱ የጤና ችግር በጤና ጣቢያ ሊታከም ይችላል? የሚለውን የመለየትና አቅምን የማወቅ ክህሎት አብሮ በስል ጠናው ይሰጣል፡፡ በእርግጥ ስልጠናው አዲስ እውቀትን ከመስጠት የሚጀምር ሳይሆን የነበራቸውን እውቀት እንዴት በስራ ላይ እንደሚያውሉት አቅጣጫ የሚያሳይ ነው፡፡ ነገር ግን ሰልጣኞች አንዳንድ ጊዜ በሚሰጣቸው የልምምድ ተግባር አድናቆት ሲያሳዩ ይታያሉ፡፡ ምክንያቱም በተግባር እንዴት እንደሚፈጽሙት አያውቁምና ነው፡፡ አንዲት እናት እነርሱ ወዳሉበት ጤና ተቋም ስትመጣ በምን መንገድ እንደሚረዱዋት ወይንም በፍጥነት ወደከፍተኛ ህክምና ተቋም እንደሚልኩዋት ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ያለውን አሰራር በሚያዩበት ጊዜ እንደ አዲስ ትምህርቱን ሲቀበሉ ይታ ያሉ፡፡ ይህ ማለት ቀደም ብሎ የነበራቸው ልምድ ምን ያህል እንደነበርና አሁን ምን ያህል እውቀት እንዳገኙ የሚያሳይ ስለሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ክፍተት እንደነበረ የሚያ ረጋግጥ ነው፡፡ ልምምድ የሚያደርጉት በሞዴልነት በተሰሩ የሰውነት ክፍሎች ሲሆን ወደሰው ከመቅረባቸው በፊት ተገቢውን ያህል ስራ እንዲሰሩ ይደረጋል። ከዚያም ወደሆ ስፒታሉ በመግባት ከባለሙያዎች ጋር በመሆን ሰዎችን እንዲረዱ ይደረጋል፡፡ በዚ ህም ከቀን ወደቀን የመስራት ፍላጎትና ብቃታቸው እያደገ ሲሄድ ይስተዋላል፡፡ ስለ ዚህ ስል ጠናው የብዙ እናቶችና ሕጻናት ሕይወት እንዲተርፍ ያስችላል የሚል እምነት አለ ብለዋል ዶ/ር እንዳለ ሲሳይ፡፡
ከሲዳማ ዞን ሸበዲኖ ወረዳ የመጣ ክሊኒካል ነርስ ቀደም ሲል በስራው አለም የገጠ መውን ሲያስታውስ፡-
“...እኔ በምሰራበት ጤና ተቋም አንዲት እርጉዝ ሴት ከእግር እስከራስዋ እየተንቀጠቀጠች እራስዋን ስታ በሰዎች ሸክም ትመጣለች፡፡ እርግዝናው ቀኑን የገፋ ነው፡፡ አብረዋት የመጡ ቤተሰቦችዋ እርስ በእርስ አልተስማሙም፡፡ ገሚሱ የቤት ጣጣ ነው ይላል፡፡ ገሚሱ ደግሞ ለጸበሉ ይደረስበታል መጀመሪያ ሐኪም ይያት ይላል፡፡ እኔ ግን እንደዚያ አይነት ነገር አይቼ ስለማላውቅ ግራ ገባኝ፡፡ ነገር ግን ለማንኛውም ብዬ... ግፊትዋን ስለካ ደምዋ በጣም ከፍ ብሎአል፡፡ በጊዜው ለእሱ የሚሆን መድሀኒትም አልነ በረኝም፡፡ ጊዜ ወስጄ...ያለውን ነገር ፈላልጌ እንደምንም ሰጥቼ በስተመጨረሻው እጄ ላይ ሳትሞትብኝ ወደሆስፒታል ይዘው እንዲሄዱ አደረግሁኝ፡፡ ነገር ግን ሆስፒታል ስትደርስ ሁኔታው እጅግ አስቸጋሪ እንደነበር አውቄአለሁ፡፡ አሁን እንደተማርኩት ቢሆን ኖሮ ...ሁኔታው ከእኔ አቅም በላይ ስለሆነ ምንም ጊዜ ሳልፈጅ በአስቸኳይ ወደከፍተኛ ሕክምና እልካት ነበር፡፡ ወደፊት ግን በሰለጠንኩት መሰረት የምችለውን ሕክምና እሰጣለሁ...እኔ የማልችለውን ግን አላስፈላጊ መዘግየትን አስወግጄ ቶሎ ወደ ከፍተኛ ሕክምና እልካለሁ...” ብሎአል፡፡
ደቡበ ሲዳማ ዞን ሐዋሳ ውስጥ ስልጠና ሲወስዱ ከነበሩት መካከል አቶ ሳምሶን ሰንበቶ ከቦና ዙሪያ ወረዳ እንደገለጸው የእናቶችን ጤንነት በተመለከተ በሐዋሳ ሪፈራል ሆስፒታል እየ ሰለጠኑም ተግባሩንም ከቀደምት ሐኪሞች ጋር በመሆን በመስራት ተገቢውን ልምምድ እያደረጉ ነው፡፡ በተለይም የእናቶችንና የህጸናትን ጤንነት በተመለከተ የተሰጠው ስልጠና መሰረታዊና ህብረተሰቡንም ለማገልገል የሚያስችል ነው እንደ አቶ ሳምሶን ሰንበቶ አስተያየት፡፡ እኔ ባለሁበት አካባቢ እናቶችም ሆኑ ጨቅላ ሕጻናቶች ብዙውን ጊዜ የሚሞቱት ከወሊድ ጋር በተያያዘ ሲሆን በዚህ ምክንያት የሚፈጠረውን ክፍተት ለመዝጋት ሙሉ በሙሉ ባይሆንም በተቻለ መጠን የሚያግዝ እውቀትን ጨብጠናል ብዬ አምናለሁ ብሎአል አቶ ሳምሶን ሰንበቶ፡፡
የWATCH ፕሮጀክትን ተግባራዊ በማድረግ ረገድ ከESOG ጋር በትብብር የሚሰራው የፕላን ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ የደቡብ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ገዳምነሽ ደስታ ትባላለች፡፡ ፕላን ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ ከፕላን ካናዳ እና ከሲዳ ያገኘውን ብር Berehan integrated community development organization በመስጠት ይህ ፕሮጀክት በተያዘለት አላማ መሰረት በሲዳማ ዞን በሶስት ወረዳ ላይ በትክክል በመሰራት ላይ መሆኑን ይቆጣጠራል፡፡ የኢትዮያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበርም ቴክኒካል አማካሪ በመሆን በሶስቱ ወረዳዎች ለሚገኙ እና በዞኑ የጤና መምሪያ ክትትል ምርጫው ተካሂዶ ሰልጣኞች ሲላኩ የስልጠናውን ሂደት በማከናወን የድርሻውን ይወጣል፡፡ በተጨማሪም ሰልጣኞቹ ወደሚሰሩበት ጤና ጣቢያ በሚመለሱበት ጊዜ ስራ ላይ የሚያውሉትን የህክምና መገልገያ መሳሪያና መድሀኒትን ግዢ በሚመለከትም ESOG ያማክራል፡፡ ስለዚህም ፕሮጀክቱ በአሁኑ ወቅት የሚሰራው ሁለት ነገር ላይ ሲሆን አንደኛው አቅም ማጎልበት እንዲሁም ሌላው ደግሞ በመንግስት ተዘርግቶ ባለው የጤና ስርአት ውስጥ ያሉ ክፍተቶችን ማሟላት ነው። ስለዚህም እናቶችና ሕጻናት የሚገጥ ማቸውን የጤና ችግር ለማቃለል በትብብር መሰረታዊ ስራ እየተሰራ ያለበት ደረጃ ላይ ነን ብለዋል ከፕላን ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ ገዳምነሽ ደስታ፡፡
ይቀጥላል

“በርናባስ” በ2005 ዓ.ም ማጠናቀቂያ ላይ ለአንባቢያን የቀረበ ረጅም ልቦለድ ታሪክ ነው፡፡ በደራሲ ትዕግሥቱ ተክለማርያም የተዘጋጀው መጽሐፉ፤ በ353 ገፆች የተቀነበበ ሲሆን በኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር እና በብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት የህትመት ተዟዟሪ ፈንድ የታተመ ነው፡፡
ጽናት፤ የመጽሐፉ ማዕከላዊ መልዕክትና ጭብጥ ነው፡፡ ከዋና ገፀ ባሕሪያት የአንዱ ሥም ነው የመጽሐፉ ርዕስ የሆነው፡፡ “የመጽናት ልጅ” የሚል ትርጉም ያለው ይሄ ስያሜ፤ ከመጽሐፍ ቅዱስ የተወሰደ ነው፡፡ እምነቱ፣ ጽናቱና ታማኝነቱ ተረጋግጦለት “የመጽናት ልጅ” የተባለው የመጽሐፍ ቅዱሱ በርናባስ፤ የእርሻ መሬቱን የሸጠበትን ገንዘብ በሙሉ ለሐዋርያት ወስዶ በመስጠቱ ምክንያት ነበር ዮሴፍ የሚለው ቀዳሚ መጠሪያው ተቀይሮ በርናባስ የተባለው፡፡
“በርናባስ” የረጅም ልቦለድ ታሪክም ተመሳሳይ መልዕክት የያዘ ነው፡፡ ጽኑ ሆኖ ያሰቡት ግብ ላይ ለመድረስ ግን የሚታለፈው ችግርና መከራ ጥልቅና ሰፊ መሆኑን ብቻ ሳይሆን፤ ጽናት ምንድነው? መጽናትና አለመጽናትስ በምን ይመዘናል? መጽናት ምን ያስገኛል ምንስ ያሳጣል? በተቃራኒው አለመጽናትስ? የሚሉና የመሳሰሉ ጥያቄዎች እንዲነሱ ይጋብዛል፡፡
የአንድ ዘመን ልጆች በአንዱ መንደር አድገው፣ በአንድ ክፍል ውስጥ ተምረው …ከጊዜ በኋላ አንደኛው ገበሬ፣ ሌላኛው የጐዳና ተዳዳሪ፣ ከፊሎች ሴተኛ አዳሪ፣ የቢሮ ሠራተኛ፣ መምህር፣ ነጋዴ፣ ባለስልጣን….እንዲሆኑና በደረጃ እንዲለያዩ ምክንያቱ ከመጽናት አለመጽናት ጋር ይያያዛል ወይ? በዓላማው፣ በመርሁና በአቋሙ ፀንቶ የቆየውስ ጽናቱ የጉዳቱ ምክንያት ለምን ይሆናል? ዓላማ በሌለበትስ ጽናት ሲታይ ምን ማለት ይቻላል? ልቦለድ መጽሐፉን ያነበበ እነዚህን ጥያቄዎች ሊያነሳ ይገደዳል፡፡
መጽሐፉ ከሁለት አቅጣጫ እየፈሰሱ መጥተው በአንድ ወንዝ እንደሚገናኝ ውሃ አብረው መጓዝ የቻሉ ታሪኮችን አጣምሮ ይዟል፡፡ አንደኛው በልጅነታቸው የፍቅር ቃል ኪዳን የገቡ ሁለት ወጣቶች፤ ከአስር ዓመት በኋላ አንደኛቸው በሌላኛቸው ዘንድ ያኖሩትን አደራ የማግኘት ፍለጋን ያሳያል፡፡ ሌላኛው፤ በ1960ዎቹ ፖለቲካ ምክንያት ከአገር የወጡ ኢትዮጵያዊያን፤ በስደት ላይ እያሉ ተምረው ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያለው ምሁር ከሆኑ በኋላ፤ የማንነት ጥያቄ ሲያታግላቸው ቤተሰባቸውን ፍለጋ ወደ አገር ቤት ቢመጡም መሻታቸው ፈጣን መልስ ሊያገኝ አለመቻሉን የሚጠቁም ነው፡፡
ልቦለዱ የምልሰት ትረካዎቹን ዘመን ሳይጨምር ከ1991 እስከ 1997 ዓ.ም ያለውን ጊዜ የሚያካልል ሲሆን ገፁ ባሕርያቱ በዋነኛነት የሚንቀሳቀሱት በደብረ ማርቆስና በአዲስ አበባ ከተሞች ነው፡፡ የደብረ ማርቆሱ ገፀ ባሕሪያት የልጅነት ታሪክ ብዙ የሚያስደምሙ ጉዳዮችን ይዟል፡፡
በ1980ዎቹ መጀመሪያ ወንዶቹ በረባሶን፣ ሴቶቹ ደግሞ ኮንጐ ጫማን እንደ ብርቅ ያዩ ነበር። በዲጂታል ቁጥሮች የሚሰራም “ዲስኮ” ሰዓት ያለው ልጅ፣ ጓደኞቹን ያስደንቃል፡፡ በከፋይ ጨርቅ የሚሰራው የቻይናዎች የካራቴ ጫማ መጫማት ከፋሽን ተከታይነት በላይም ያስከብራል። ልጆቹ የሽቦ መኪና ሰርተው የሚነዱበት፣ ጭቃ አድበልቡለው ብይ የሚጫወቱበት፣ ተጠራርተው በሸርተቴ ጨዋታ የሚዝናኑበት የተለያዩ ጊዜያት አሏቸው፡፡
ፍሬን፣ ፍሪሲዮንና ነዳጅ መስጫ “ማርሽ ነው”፣ “አይደለም” ብለው በልጅነታቸው በደብረ ማርቆስ ሆነው ከተከራከሩት ጥቂቶቹ በዕውቀት ብቻ ሳይሆን በዕድሜም ጨምረው አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ይገባሉ፡፡ የመጽሐፉ ዋና ገፀ ባሕሪ በርናባስ አንዱ ነው፡፡ የዩኒቨርስቲው ጨዋታና ቀልዳቸው ግን እንደ ትምህርት ተቋሙ ከፍ ያለ ሆኗል፡፡
“ምትኩ ለማቲማቲክስ ልዩና ጥልቅ ፍቅር፣ ረቂቅ ችሎታ አለው፡፡ የሚነገረውን ማንኛውንም ነገር “ማቲማቲካሊ” ነው የሚረዳው፡፡ የሚያስበውም በዚያው በማቲማቲክስ ነው፡፡ ለምሳሌ በዓይን ፍቅር ወድቆላት “ዩቲሊቲ ማክሲማይዘር” ብሎ የሰየማት የአካውንቲንግ የሁለተኛ ዓመት ተማሪ የሆነችው ፍሬሰላም፤ እዚያው ስድስት ኪሎ ዩኒቨርስቲ በር ላይ ታጥፋ መገናኛ ወደሚገኘው ሰፈራቸው ለመሄድ አንዳንዴ የምትይዛትን 64 ቁጥር አውቶብስ ካየ፣ የአውቶብሷን ቁጥር “Two to the power of six” ብሎ ጭንቅላቱ ውስጥ ይመዘግበዋል፡፡”
በቀልድ ፈጣሪነቱ በዩኒቨርስቲው ግቢ ዝነኛ መሆን የቻለው ሸዋፈራሁ ደግሞ “የ R kellyን I Believe I can fly” ዘፈን ወደ አማርኛ ተርጉሞ “አልበር እንዳሞራ ሰው አርጐ ፈጥሮኛል” እንዳለው በሰፊው ተወርቶበታል፡፡ History of Economic Thought ደግሞ “ሥነ ስስታዊ እሳቤ” በሚል ሀገር በቀል ትርጓሜ አስተዋውቋል፡፡”
በደብረ ማርቆስ በአንድ ክፍል ውስጥ ይማሩ ከነበሩት ተማሪዎች ጥቂቶች ለዩኒቨርስቲ በቅተው ወደ ታላቅ ደረጃ የሚያደርሳቸውን መስመር ሲይዙ፣ ከፊሎቹ በተለያዩ ቦታዎች ተበታትነዋል፡፡ ትምህርቱን አቋርጦ ገበሬ የሆነ አለ፡፡ ሌላኛዋ በአዲስ አበባ ከተማ በሴተኛ አዳሪነት ተሰማርታ፣ ደብረ ማርቆስ የሚገኙ ቤተሰቦቿን ትረዳለች፡፡ የልጆቹ ዕጣ ፈንታ፣ ከመጽናትና አለመጽናት ጋር የተያያዘ ነው ወይ? የሚል ጥያቄ እንድናነሳ ይገፋፉናል፡፡
“ሸሌ ተንኮለኛ ካልሆነች ክፉ ወንድ አይገጥማትም” የሚል መደምደሚያ ላይ የደረሰችው ዊንታ የምትባል ገፀ ባሕሪ፤ በችግር ምክንያት ከደብረ ማርቆስ ወደ አዲስ አበባ መጥታ ሴተኛ አዳሪ ለመሆን ያሰበች ጓደኛዋን ለማዳን ብዙ ትለፋለች፡፡ ጥረቷ እንዳልተሳካ ስታይ፤ ጓደኛዋ መልካም እንዲገጥማት ለወንዶች ክፉ እንዳትሆን ትመክራታለች፡፡
ዊንታ በሴተኛ አዳሪነት ሕይወት በኤችአይቪ (ኤድስ) እስከ መያዝ የደረሰ ብዙ ችግርና መከራ ቢገጥማትም አገር፣ ትውልዱንና ሕብረተሰቡን በመታደግ ሥራና ተግባር ላይ እንደተሰማራች የምታስብበት ጊዜም አለ፡፡ በየቤቱ ብዙ ጉድ አለ የምትለው ዊንታ፤ የሚወዳቸው ሚስትና ልጆች ያሉት አባወራ፤ ከቤቱ ያጣውን እኛ ዘንድ ለማግኘት ይመጣል ትልና “በቃ ሰላሙን አግኝቶ ይመለሳል፡፡ ለምን ቢባል፤ ለጊዜያዊ ሰይጣን፣ ለሚያልፍ ስሜት ኑሮውን ይበጠብጣል? እንዲያውም ባይገርምሽ በኛ ምክንያት የስንት ሰው ትዳር ከመፍረስ እንደዳነ?” ትላለች፡፡ እስከዳር ሌላኛዋ የደብረ ማርቆስ ልጅ ናት። በትምህርቷ እስከ ኮሌጅ ዘልቃ በመመረቅ፣ በሙያዋ ተቀጥራ ትሰራለች፡፡ ለወንዶች ያላት አመለካከት፤ ከሴተኛ አዳሪዋ ዊንታ ጋር ሲነፃፀር መቶ በመቶ ፐርሰንት ተቃራኒ ነው፡፡ “የገጠሟትና በቅርበትም የምታውቃቸው ወንዶች ሁሉም ማለት ይቻላል ክፉዎች፣ ራስ ወዳዶች፣ ከጊዜያዊ ደስታ አርቀው ማየት የማይችሉ ወይም የማይፈልጉ፣ ልብ አውልቆች” ብላ ነው የደመደመችው፡፡
እነዚህ ታሪኮች ስለ መጽሐፉ አስተኔ ገፀ ባሕሪያት የተነገሩ ናቸው፡፡ ዋናው ባለታሪኮች በርናባስና እሌኒ ናቸው፡፡ ሁለቱ ወጣቶች በልጅነታቸው የፍቅር ቃል ኪዳን ገብተው ከተለያዩ ከ10 ዓመት በኋላ ሲፈላለጉና ተገናኝተውም በመሟገትና በመካሰስ ቃላቸውን ስለመጠበቃቸውና በጽናት ስለመቆየታቸው በብዙ ገፆች ይተረክላቸዋል፡፡ ደራሲ ትዕግሥቱ ተክለማርያም፤ ስለ ጽናት ምንነት ለማሳየት የሞከሩት የዋናና አስተኔ ገፀ ባሕሪያትን ሕይወት፣ ዓላማና ግብ በንጽጽር በማቅረብ ነው፡፡
የጽናት ምንነት ማሳያ ሆነው የቀረቡት ሌላኛው ባለታሪክ ቤተሰባቸውን ፍለጋ ከባህር ማዶ ወደ አገራቸው የመጡት ምሁርና በዙሪያቸው የሚንቀሳቀሱ ሰዎች ናቸው፡፡ ባለታሪኩ በአንድ ወቅት በጽናት የታገሉለትና ለስደት የዳረጋቸው አመለካከትና አቋም ነበራቸው፡፡ ከስደት ተመልሰው ቤተሰባቸውን ሲያፈላልጉ እና ለአገር ይጠቅማል ባሉት የልማት ሥራ ላይ ሲንቀሳቀሱም ጽናት ይታይባቸዋል፡፡ ያለፈውን ዘመን በሚተቹበት ሃሳብ “ከጥቂት ወራት በኋላ እንዳረጀ ልብስ አውልቀን ልንጥለው በምንችልው ፍልስፍናችን ምክንያት ስንለያይ እንታያለን፡፡
ከዚያም እርስ በእርሳችን መደማመጥ፣ መታገስና መቻቻል እየተሳነን ሄዷል፡፡ ለዚህ ነበር ስንገዳደልና ስንሞት፣ ስንተላለቅ መቆየታችን” እያሉ ያዝናሉ፡፡ ይህ ደግሞ የዛሬ ሀዘናቸውንና የቀድሞ ዘመን ጽናታቸውን እንዴት ማስታረቅ ይቻላል? ማስታረቅ ካልተቻለስ ጽናት ምንድነው? የሚል ጥያቄን ያስነሳል፡፡
ሀንፍሬ የሚባሉት እኚህ ገፀ ባሕሪ ካለፈው ትውልድ በተሻለ በአሁኑ ዘመን ወጣቶች ላይ የተሻለ እምነት ያሳደሩ ይመስላል፡፡ የእውነተኛ ጽናት ማሳያ ምሳሌ ሆነው የቀረቡት በርናባስና እሌኒን የሚያግዙበት አንዱ ምክንያት ይህ ነው ማለት ይቻላል፡፡
ደራሲ ትዕግሥቱ ተክለማርያም፤ በሕብረተሰባችን ውስጥ ያለውን ጽናትና በተቃራኒው ጽናቱን የሚፈታተኑ ብዙ ማሳያና ትርክቶችን አቅርበዋል፡፡ ዋናው ገፀ ባሕሪያት (በርናባስና እሌኒ) ከ10 ዓመት በኋላ ሲገናኙ አንዳቸው ሌላኛቸውን ቃል ኪዳን አፍርሷል በሚል የተፈጠረባቸውን ጥርጣሬ ለማጥራት በምክንያታዊ ክርክር፣ በግልጽ ውይይት፣ በይቅርታና ንስሀ የደረሱበት እውነት ጽናታቸውን አረጋግጦላቸዋል፡፡ የደራሲ ትዕግሥቱ ተክለማርያም እምነትና ተስፋም በዚህ ተንፀባርቋል፡፡ የዛሬ ወጣቶች ለጽናትም ሆነ ለኃላፊነት ተስፋ የሚጣልባቸው ትውልዶች ናቸው ከሚለው በመነሳት መጽሐፋቸውን ያዘጋጁት ይመስላል፡፡

Saturday, 07 September 2013 10:57

ካልዲስ ኮፊ

በ30ሚ ብር የወተት ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ከፈተ
በ200ሺ ብር ጀምሮ 11 ሚሊዮን ብር ደርሷል
አንድም ካፌ ፍራንቻይዝ አልተደረገም
በቅርቡ የታሸገ ወተት ለገበያ ያቀርባል
17 ቅርንጫፎችና 1,200 ሠራተኞች አሉት
ቦሌና ዙሪያውን አራት ቦታ፣ 22 አካባቢ ትራፊክ ጽ/ቤትን ተሻግሮና ሳይሻገሩ፤ መገናኛ፣ በቅሎ ቤት (ላንቻ)፣ ሳር ቤት፣ ሜክሲኮ፣ ሀብተጊዮርጊስ ድልድይ፣ ፊላሚንጐ፣ ጉርድ ሾላ፣ ጥቁር አንበሳ ት/ቤት አካባቢ ኢ.ኢ ኤ፣ ብትሄዱ፣ አንድ የሚያጋጥማችሁ ካፌ አለ - ካልዲስ ኮፊ፡፡
አቤት! ጊዜው እንዴት ይሮጣል! ካልዲስ ኮፊ “ሀ” ብሎ ሥራ የጀመረው የዛሬ 10 ዓመት ነው -በ1995 ዓ.ም፡፡ የመጀመሪያው ካፌ ከኤድናሞል ፊት ለፊት ባለው አደባባይ አጠገብ የተከፈተው ነው፡፡ ይሁን እንጂ፣ በወ/ሮ ፀደይ አሥራትና በካፒቴን ዳንኤል ከተማ ካልዲስ ኮፊ ኃ.የተ.የግማ (ፒ ኤል ሲ) ሆኖ የተቋቋመው በ1998 ዓ.ም ነበር፡፡
አንዳንድ የንግድ ድርጅቶች ለ10 ዓመት ወይም ከዚያም በላይ ባሉበት ይቆያሉ። አንዳንዶቹ ሁለትና ሦስት ሊያደርሱት ይችላሉ፡፡ ጥቂቶች ደግሞ ከዚያም በላይ ሊሄዱ ይችላሉ፡፡ የካልዲስ ግን የሚገርም ሆነብኝ፡፡ በብዙዎቹ የመዲናዋ አካባቢዎች ካልዲስ ካፌን መመልከት የተለመደ ሆኗል።
የስኬቱ ምክንያት ምንድነው በማለት ባለቤቴን ማነጋገር ፈለግሁና ወደ ካልዲስ ካፌ ጽ/ቤት ሄጄ ለምክትል ዋና ሥራ አስኪያጁ ለአቶ ተስፋዬ ደገፉ የመጣሁበትን ምክንያት ነገርኳቸው፡፡
እሳቸውም ምክንያቴን ካዳመጡ በኋላ፣ ባለቤቶቹን ማግኘት እንደማልችል፣ የምፈልገውን መረጃ ከእሳቸው ማግኘት እንደምችል ነግረውኝ አጭር ቀጠሮ ሰጡኝ። በቀጠሮዬ ቀን ስንገናኝ አቶ ተስፋዬን ካልዲስ ስንት ቅርንጫፎች አሉት በማለት ቃለምልልሴን ጀመርኩ፡፡

 

አሁን 17 ቅርንጫፎች አሉን፡፡ በአዲሱ ዓመት የመጀመሪያ ወር 18ኛውን ቅርንጫፋችንን እንከፍታለን፡፡
የት?
ቦሌ መድኃኒዓለም ቤተክርስቲያን አካባቢ፣ በአትሌት ብርሃኔ አደሬ ሕንፃ ላይ ይከፈታል፡፡
የካልዲስ ካፌ የስኬት ምስጢር ምንድነው?
ድርጅታችን በከተማችን ውስጥ በተመሳሳይ ዘርፍ ከተሰማሩ ድርጅቶች በተለየ ሁኔታ እያደገ ያለ ኩባንያ ነው፡፡ ለዕድገቱ ዋናው መሠረት፣ ሠራተኛው ለሥራ ያለው ጠንካራ ዲሲፕሊን፣ የሥራ አመራር አካሉ በወጣቶች የተገነባ መሆን፣ ሁልጊዜ ለለውጥና ለጥራት በጋራ የሚሠራ የሥራ አመራር ጥረትና ውጤት ነው ለዚህ ያበቃን፡፡
ድርጅታችን ካለፉት ሦስት ዓመታት ጀምሮ በፈጣን ዕድገት ላይ ነው የሚገኘው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ለድርጅታችን ግብዓት የሚሆኑትን ወተትና ዕንቁላል የመሳሰሉትን ምርቶችን ለማምረት አንዳንድ ጥረቶች ጀምሯል፡፡ ለዚህም በቅርቡ በሱልልታ ከተማ ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ ኢንቨስትመንት አድርጐ የወተትና የወተት ተዋጽኦ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ አቋቁሞ፣ ለራሱ የሚያስፈልገውን የወተትና የእርጐ ምርት ከተጠቀመ በኋላ፣ የተረፈውን ገበያ ውስጥ በማስገባት ላይ ይገኛል፡፡
ይህ ፋብሪካ ለጊዜው ከ35 በላይ ለሆኑ ሰዎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል፡፡ ወደፊት የወተት ማቀነባበሪያውን ሥራ ከጨረስን በኋላ፣ ለድርጅቱ ግብአት የሚሆኑ ምርቶችን የማምረት ዕቅድ አለው። ያኔ የሠራተኛው ቁጥር ይጨምራል፡፡
በማቀነባበሪያው ምን ምን ታመርታላችሁ?
እስካሁን ድረስ ቅቤ፣ አይብና ፓስቸራይዝድ ወተት ለራሳችን ነው የምናቀርበው፡፡ አሁን ግን ፍላጐቱ (ዲማንዱ) ከፍተኛ ስለሆነ ገበያ ውስጥ በስፋት ለመግባት እቅድ አለን፡፡
ወተቱን ከየት ነው የምታገኙት? የራሳችሁ ላሞች አሏችሁ እንዴ?
እኛ ላሞች የሉንም፡፡ ወተቱን የምናገኘው ከአካባቢው ገበሬ አሰባስበን ነው፡፡
ለካፌዎቻችሁ በቀን ምን ያህል ወተት እንቁላል፣ ስኳር… ትጠቀማላችሁ?
ለትኩስ መጠጦችና ለኬክ ሥራ በቀን በአማካይ ከ1,200 ሊትር በላይ ወተት እንጠቀማለን፡፡ እንቁላል ለፋስት ፉድና ለኬክም ግብአት ስለሆነ በቀን በአማካይ ከ15 ሺህ በላይ እንጠቀማለን። አሁን እንቁላል የምናገኘው ከኤልፎራ ነው፡፡ ወደፊት የወተት ማቀነባበሪያው ሥራ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ፣ የራሳችንን የእንቁላል ምርት ለማቅረብ አቅደናል፡፡ ቦታውም ተዘጋጅቷል፤ የሚቀረን ወደ ሥራ መግባቱ ነው፡፡ ስኳር በቀን ከሦስት ኩንታል በላይ እንጠቀማለን፡፡ ወደፊት የካፌዎቹ ቁጥር ሲጨምር የምንጠቀማቸው ግብአቶችም ይጨምራል፡፡
ካልዲስ ፍራንቻይዝ አድርጐ (ስሙን ሽጦ) ሸጧል፡፡ አንዳንድ ካፌዎች የእሱ አይደሉም ይባላል። ይኼ ምን ያህል እውነት ነው?
ውሸት ነው፡፡ ካልዲስ ኮፊ በአሁኑ ወቅት አንድም ቅርንጫፍ ፍራንቻይዝ አላደረገም፡፡ ማኔጅመንቱም፣ ሀብቱም በራሱ ነው፡፡ ፍራንቻይዝ እንድናደርግ ከአገር ውስጥም ከውጪም ለምሳሌ፣ ከቻይና ከሱዳን፣ ከደቡብ ሱዳን በተደጋጋሚ ጥያቄ ቀርቦልናል፡፡ ድርጅታችን አሁን ባለበት ሁኔታ ራሱን ለማስተዳደር፣ በፋይናንስም ሆነ በማኔጅመንት በቂ አቅም አለው፡፡ ስለዚህ ፍራንቻይዝ የምናደርግበት ምክንያት የለም፡፡
እቅዳችሁ ስንት ካፌ መድረስ ነው? ካልዲስ ዋጋው ውድ ነው የሚሉ ሰዎች አሉ፡፡ በዚህ ሐሳብ ላይ ምን ይላሉ?
የእኛ ዋጋ ውድ አይደለም፡፡ አንዳንድ ማቴሪያሎች ለምሳሌ አይስክሬም ከውጭ ነው የምናስመጣው፡፡ በከተማችን ያሉ አንዳንድ ካፌዎች ማኪያቶና ቡና በ10 ብር ነው የሚሸጡት፡፡ እኛም በ10 ብር ነው የምንሸጠው፡፡ ስለዚህ ውድ ነው የሚባል አይደለም፡፡ ከምንሰጠው አቅርቦት ጋር ሲተያይ ሚዛናዊ (ፌየር) ነው፡፡
ዕቅዳችን በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ 40 ካልዲስ ካፌዎች መክፈት ነው፡፡ ዕቅዳችንን ካሳካን በኋላ ከአዲስ አበባ ከተማ መውጣት ነው ሃሳባችን፡፡ ይህንንም የምናደርገው ወደ ክልል ከተሞች ወጥተን ቅርንጫፍ ካፌዎች ለመክፈትና ለመምራት ጠንካራ የፋይናንሻልና የማኔጅመንት አቅም አለን ወይ? ብለን ጠይቀን ስናምንበት ነው፡፡
ካልዲስ ሲመሠረት ካፒታሉ ምን ያህል ነበር? አሁንስ?
ካልዲስ ሲመሠረት ካፒታሉ 200ሺህ ብር ነበር። አሁን ከ10 ዓመት በኋላ፣ ለእህት ኩባንያዎች (ሱሉልታ ላይ የተገነባው የወተት ማቀነባበሪያ ፋብሪካና ለእንቁላል ማምረቻ) የወጣውን ሳይጨምር ካፒታላችን በአሁኑ ወቅት 11 ሚሊዮን ብር ደርሷል፡፡
በቀረጥና በታክስ በዓመት ምን ያህል ብር ለመንግሥት ታስገባላችሁ?
በታክስ፤ በቀረጥና በመሳሰሉት በዓመት ወደ መንግሥት ካዝና 12 ሚሊዮን ብር ፈሰስ በማድረግ ኢኮኖሚውን እንደግፋለን፡፡
አንድ ካልዲስ ካፌ ለመክፈት ስንት ብር ያስፈጋል?
በከተማው ውስጥ የቤት ኪራይ በጣም ውድ ነው፡፡ እንደዚያም ሆኖ ቢያንስ የ6 ወር ኪራይ መክፈል ግዴታ ነው፡፡ ይህንን ሳይጨምር የካፌዎቻችን ዕቃዎች (ጠረጴዛና ወንበር) ከፍተኛ ጥራት ያላቸውና ከውጭ የሚመጡ ናቸው፡፡ በአጠቃላይ የውስጥ ዕቃዎችን ለማሟላትና አስውቦ (ዲኮር አድርጐ) አንድ ካፌ ለመክፈት ቢያንስ 200ሺህ ብር ይጠይቃል፡፡
ካልዲስ ስንት ሠራተኞች አሉት?
በሁሉም ካፌዎች የሚሠሩ 1,200 ሠራተኞች አሉን፡፡
ሁሉም ካፌዎች አንድ ዓይነት ዕቃ በመግዛት ተመሳሳይ መልክ እንዲኖራቸው ማድረግ ይቻላል። የሰው ልጅ ግን አንድ ዓይነት ባህርይ አይኖረውም። እንዴት ነው ታዲያ ሠራተኞቻችሁ በሁሉም ካፌ ተመሳሳይ መስተንግዶ እንዲሰጡ የምታደርጉት?
በሥልጠና ነው፡፡ የራሳችን የሆነ የሥልጠና ማዕከል አለን፡፡ ሠራተኞቻችንን ቀጥረን ወደ ሥራ ከማሰማራታችን በፊት ወደማሠልጠኛው ገብተው የንድፈ ሐሳብ (የቲዎሪ) ትምህርት እንዲቀስሙና የተግባር ልምምድ እንዲያገኙ እናደርጋለን፡፡ ከዚያ በኋላ፣ ድርጅቱ የራሱ መመዘኛ ስላለው፣ ያንን መለክያ ያለፉትን ብቻ ቀጥሮ ወደሥራ ያስገባቸዋል። ከዚህም በተማሪ በሁሉም ዘርፍ ለተሰማሩ ሠራተኞች በመስተንግዶ፣ በቁጥጥር፣ በምርት ሥራ ላይ የተሰማሩትን በየጊዜው የሥራ ላይ ሥልጠና በመስጠት ክህሎታቸውን እናዳብራለን፡፡ ቁጥጥር በማድረግ፣ ጉድለት ለሚታይባቸው ሠራተኞች ሥልጠና እንሰጣቸዋለን፡፡ ሠራተኞቻችን ተመሳሳይ መስተንግዶ የሚሰጡት ከአንድ የሥልጠና ማዕከል ስለሚወጡ ነው፡፡
ሥልጠናውን የሚሰጠው ማነው?
ሥልጠናው የሚሰጠው በተለያዩ የኦፕሬሽን ክፍሎች ነው፡፡ ከኦፕሬሽን ክፍሉ ሥራዎች አንዱ በየቅርንጫፉ እየተዘዋወረ ቁጥጥር ማድረግ ነው። ቁጥጥር አድርጐ ጉድለት ሲገኝ ወዲያውኑ እንዲታረም ያደርጋል፤ የሠራተኞችንም የሥራ አፈጻጸም ይገመግማል፡፡ ዕድገት የሚያስፈልጋቸው ሠራተኞች ካሉ ዕድገት እንዲያገኙ ያደርጋል፤ ድክመት ያለባቸው ሠራተኞችም ካሉ ሥልጠና አግኝተው ከሌሎች ጋር የተስተካከለ መስተንግዶ እንዲሰጡ ይደረጋል፡፡
ታታሪ ሠራተኛ ያድጋል ብለዋል፡፡ እንዴት ነው የሚያድገው?
በካልዲስ የዕድገት በሩ ክፍት ነው፡፡ ነገር ግን ማንም ዘው ብሎ የሚገባበት አይደለም፡፡ አንድ ሠራተኛ በተመደበበት ስፍራ ብቃት ካለው፣ ድርጅቱ በሚፈልገው መንገድ ኃላፊነቱን የሚወጣ ከሆነ ዕድገት ያኛል፡፡ ለምሳሌ ከመስተንግዶ ላይ ተነስተው የአመራር አባል በመሆን ከፍተኛ ዲፓርትመንቶችን የሚመሩ ሠራተኞች አሉ። እነዚያን ሠራተኞች፣ ምንም ሙያ ሳይኖራቸው ተቀብለን አሠልጥነን በየጊዜው ክትትል በማድረግ ነው ለዚህ ያበቃናቸው፡፡ በሩ ክፍት ነው ስል፣ ብቃት ያለው፣ የድርጅቱ አሠራር ሲስተም የገባቸውና ጥረት የሚያደርጉትን ማለቴ ነው፡፡
ብዙ ጊዜ በትላልቅ ድርጅቶች (በባለ 5 ኮከብ ሆቴሎች ሁሉ) ሠራተኛውና ማኔጅመንቱ አይስማሙም፡፡ ያለመግባባት እየተፈጠረ ፍ/ቤት የሚቆሙበት ጊዜም አለ፡፡ እናንተስ? በማኔጅመንቱና በሠራተኛው መካከል ያለው ግንኙነት (መግባባት) ምን ይመስላል?
እንደሚታወቀው ለአንድ ድርጅት ትልቁና ዋነኛው ሀብት ሠራተኛው ነው፡፡ ቤቱን የቱንም ያህል በውበት ብናንቆጠቁጠው፣ ሠራተኞቹ ጥሩ ካልሆኑ ያ ሁሉ ድካም ሜዳ ላይ ነው የሚቀረው። ይህን ግምት ውስጥ ስለምናስገባ፣ ሠራተኞቻችንን እናሠለጥናለን፣ እናሳድጋቸዋለን፣ ለመሪነት ደረጃም እናበቃቸዋለን፤ ይህም ሠራተኞቹን ያተጋቸዋል። በተጨማሪም ድርጅቱ በዓመት ለሠራተኛው 6 በመቶ የደሞዝ ጭማሪ ያደርጋል፡፡ ይህ ብቻም አይደለም፡፡ የተገኘው ውጤት ይገመገምና ድርጅቱ በማንኛውም ጊዜ የደሞዝ ጭማሪ ሊያደርግ ይችላል፡፡ በዓመቱ መጨረሻም ገቢና ወጪው ተሰልቶ የተገኘው ውጤት ይመዘንና ለሠራተኞች ቦነስ እንሰጣለን፡፡ ድርጅቱ የተገኘውን ትርፍ ብቻውን አይበላም፡፡ ትርፉን ካስገኙለት ሠራተኞች ጋር ይካፈላል፡፡
ሌላው መተማመኛችን በማንኛውም ሰዓት አንድ ሠራተኛ ኃላፊዎች በድለውኛል ካለ ለበላይ አካል ቅሬታውን ለማቅረብ በሩ ክፍት ነው፡፡ ይኼ የምንኮራበት ሲስተማችን ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ሠራተኛ ምክትል ሥራ አስኪያጁ አቶ ተስፋዬ በደለኝ ካለ፣ ከእኔ በላይ ላለ ኃላፊ (አለቃ) ለዋና ሥራ አስኪያጇና ባለቤቷ ድረስ ቀርቦ ቅሬታውን የማቅረብ መብት አለው፡፡ ይኼ ነገር ሠራተኞቻችንን የሚያስደስታቸው ይመስለኛል፡፡
የሆቴልና ቱሪዝም (የካፌዎች) ኢንዱስትሪ እያደገ ነው ያለው፡፡
ካልዲስ ውስጥ ያሉ ሠራተኞች ወደ ሌላ ቦታ ሄደው ለመሥራት ብቁ መሆናቸውን ስለሚያውቁ፣ እኛ ጋ መሥራቱን እንደማሠልጠኛ ተቋም ነው የሚቆጥሩት፡፡ እነዚህ ነገሮች ናቸው እንግዲህ በእኛና በሠራተኞቻችን መካከል ሰላም እንዲኖር የሚያደርጉት፡፡
40 ካፌዎች በአዲስ አበባ ከከፈታችሁ በኋላ ዕቅዳችሁ ምንድነው?
በአዲስ አበባ ከተማ 40 ካፌዎች ከከፈትን በኋላ ወደ አጐራባች ከተሞች እንወጣለን፡፡ ወደ ክልሎች የምንወጣው እዚህ 40 ካፌዎች ስለሞላን ብቻ ሳይሆን ለሥራችን ግብአት የሚሆኑ ነገሮችን 50 በመቶ ራሳችን ማምረት ስንችል ነው፡፡ ከወተት የሚገኝ ብዙ ተዋጽኦ አለ፡፡ ቺዝ፣ ቅቤ፣ ክሬም፣… እነዚህ ለኬክ አስፈላጊ ግብአት ናቸው፡፡ ከዚህ በኋላ ደግሞ ወደ እንቁላል ምርት (ፖልተሪ) እንገባለን፡፡
በመቀጠል ደግሞ አትክልቶችን ማቅረብ እንፈልጋለን፡፡ እነዚህ ሁሉ ከተሟሉና በአዲስ አበባ 40 ካፌ ከሞላን በኋላ ወደ ክልል ለመውጣት ነው ዕቅዳችን፡፡ ፍራንቻይዝ የሚለውንም 40 ከሞላን በኋላ ቆሞ ብለን የምናየው ይሆናል፡፡ በመጨረሻም፤ አንባቢዎች ሥራ አስኪያጁን እንዲተዋወቁ አቶ ተስፋዬ ማናቸው? ትምህርትና የሥራ ልምዳቸውስ በማለት ጠየቅሁ፡፡
አቶ ተስፋዬ ከንግድ ሥራ ኮሌጅ በአካውንቲንግ ዲፕሎማ፣ ከአልፋ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ በአካውንቲንግ የመጀመሪያ ዲግሪ አላቸው፡፡ ለ10 ዓመታት በተለያዩ የመንግሥት ድርጅቶች በኦዲተርነትና በሂሳብ ኃላፊነት ሠርተዋል፡፡
በበደሌ ቢራ ፋብሪካ ለ8 ዓመታት ከአካውንታንት እስከ ፋይናንስ ሥራ አስኪያጅነት፣ በካልዲስ ለሁለት ዓመት በፋይናንስ ኃላፊነትና ለአራት ዓመት ድርጅቱን በምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅነት እየመሩ ነው፡፡
አቶ ተስፋዬ በካልዲስ ካፌ ኃ.የተ.የግል ማህበር ውስጥ ለ6 ዓመት ስለሰሩ በደንብ ያውቁታል፤ በአድናቆት የሚናገሩለትም ነገር አለ፡፡ “አንዱ፣ በትንሽ ካፒታል ጀምሮ ለ1,200 ሠራተኞች የሥራ ዕድል መፍጠሩ ነው፡፡ ሌላው ደግሞ ባለቤቶቹ በቅንነት የሚፈጽሟቸው ተግባራት ናቸው፡፡ አካለ ስንኩላንን፣ በሽተኞችን፤ ካንሰር ሶሳይቲን በገንዘብ ይረዳሉ፡፡
ጐበዝ ተማሪ ሆነው ችሎታው እያላቸው የሚረዳቸው በማጣት መማር የማይችሉትንም ይረዳሉ፡፡ ለምሳሌ አንድ ልጅ ከአምቦ አምጥተው እያስተማሩ ነው፡፡ ልጁ ከ1ኛ ክፍል እስከ 11ኛ ክፍል 1ኛ ነው የሚወጣው፡፡ እነዚህን ነገሮች አደንቅላቸዋለሁ፡፡” ብለዋል፡፡

Saturday, 07 September 2013 10:41

የግል ሐኪምዎ የሆነው ሙዝ!

በስትሮክ የመሞት አደጋን ከ50-60 በመቶ ለመቀነስ ያስችላል
ለስኳር ህመምና ለደም ማነስ ሙዝን መመገብ ይመከራል

በኢትዮጵያ እንደተገኘ የሚነገርለትና በዓለማችን በስፋት እየተመረተ ለምግብነት የሚውለው ሙዝ እጅግ በርካታ ጠቀሜታዎች አሉት፡፡ ሙዝ ከምግብ ይዘቱ በተጨማሪ ለተለያዩ በሽታዎች ፈውስ ሊያስገኙ የሚችሉ ንጥረ ነገሮችንም አካቶ ይዟል። እነዚህ ንጥረነገሮች ለበርካታ በሽታዎች ፈውስ ከመሆናቸውም በላይ፣ በሽታው ከመከሰቱም በፊት ለመከላከል የሚያስችለንን አቅም ያጐናጽፉናል፡፡ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በጠቅላላ ህክምና ክፍል ሐኪም የሆኑት ዶ/ር ታዬ አለማየሁ እንደሚናገሩት፤ ሙዝ በስትሮክ ምክንያት ሊከሰት የሚችለውን ሞት በግማሽ መቀነስ ይችላል፡፡
ሙዝ በውስጡ የካርቦሃይድሬት ንጥረነገሮችን የያዘ በመሆኑ ከፍተኛ ሃይል እንድናገኝ ይረዳናል። ሁለት ሙዝ በልተን በምናገኘው ሃይል ለዘጠና ደቂቃ አድካሚ የጉልበት ሥራዎችን መሥራት እንደምንችል ዶ/ር ታዬ ይናገራሉ፡፡
ብዙዎቻችን ሙዝን ለምግብነት በማዋል ለሰውነታችን ሃይልና ሙቀት ለማግኘት እንደምንችል ከማወቅ የዘለለ ነገር አስበን አናውቅም፡፡ ነገር ግን ሙዝ በውስጡ የያዛቸው ተፈጥሮአዊ የስኳር ወይም የጣፋጭ ምንጭ የሆኑት ግሉኮስ፣ ስክሮስ፣ እና ፍሩክቶስ የተባሉት ንጥረነገራት ከሙዝ የፋይበር (የቃጫነት) ተፈጥሮ ጋር ተዳምረው መጠነሰፊ ጠቀሜታዎችን ይሰጣሉ። ከበርካታ የሙዝ ጠቀሜታዎች መካከል ጥቂቶቹን ከዚህ እንደሚከተለው ለማየት እንሞክራለን፡፡
1. ለአእምሮ እድገት
ሙዝ በውስጡ ከፍተኛ የፖታሺየም ንጥረነገርን ይዟል፡፡ ይህም ንጥረ ነገር የአንጐልን የሥራ ብቃት ለማሻሻል እና ለማሳደግ እንዲሁም ንቁና ጤናማ አዕምሮ እንዲኖረን በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው፡፡
2. ለስትሮክ
በሙዝ ውስጥ ያለው ፖታሺየም፣ የደም ሥርዓትን በማስተካከል ባልታሰበ ሁኔታና በድንገት የሚከሰተውን የስትሮክ ችግር ለመከላከል ያግዛል። ሙዝ በሰው ልጆች የአመጋገብ ሥርዓት ውስጥ ተካቶ ዘወትር ለምግብነት የሚውል ከሆነ፣ በስትሮክ ምክንያት የሚመጣውን ድንገተኛ ሞትና የአካል ጉዳት ከ50-60 በመቶ ለመቀነስ ያስችላል፡፡
3. ለደም ግፊት
ሙዝ በተፈጥሮው በውስጡ የሚይዘው ዝቅተኛ የጨው መጠን በመሆኑ የደም ግፊትን ለማረጋጋት ይረዳል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በውስጡ ያለው ፖታሺየም የደም ግፊትን ለማስተካከልና በግፊት ሳቢያ የሚከሰቱ ከባድ የጤና ችግሮችን ለመከላከል ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው፡፡
4. ለጨጓራ ህመም
አብዛኛዎቻችን ሙዝ ከበድ ያለ ምግብ እንደሆነ በማሰብ፣ ሙዝ የጨጓራ ህመማችንን እንደሚያባብስብን ስንናገር እንደመጣለን፡፡ ይሁን እንጂ ሙዝ ለጨጓራ ችግሮች ሁነኛ መፍትሔ ነው። ሙዝ በባህርይው በጣም ለስላሳ በመሆኑ በጨጓራ ላይ መጨናነቅን የማይፈጥር ሲሆን የጨጓራ አካባቢን በመሸፈን፣ የጨጓራ ውስጥ አሲድን በማስተካከልና በማመጣጠን የጨጓራ ቁስለት እንዳይፈጠር ለማድረግ ያስችላል፡፡
5. ለድብርት
ሙዝ በውስጡ የሚይዘውና ትራይፕቶፋን የተባለው ንጥረ ነገር በሰውነታችን ውስጥ ሴሮቶኒን የባለ ሆርሞን እንዲፈጠር ያደርጋል፡፡
ይህ ሆርሞን አይነተኛ ተግባሩ ሰውነታችንን ከድካምና ከድብርት በማላቀቅ ወደተሻለ ስሜት ውስጥ እንድንገባ ማድረግ ነው፡፡
6. ለሆድ ድርቀት
በሙዝ ውስጥ የሚገኘው ፋይበር ለምግብ መፍጨት ሥርዓታችን ከፍተኛ ጠቀሜታን ይሰጣል፡፡ የምግብ መፍጨት ሥርዓትን የሚያከናውኑት የሰውነታችን ክፍሎች በቂ የውሃ መጠን እንዲኖራቸው በማድረግ ሆድ ድርቀትን ይከላከላል፡፡ አንጀት የተለሳለሰ እንዲሆን በማድረግ ከሰውነታችን መውጣት የሚገባቸው አላስፈላጊ ነገሮች (ቆሻሻዎች) እንዲወገዱ ለማድረግ ይረዳል፡፡
7. ለስኳር ህመም
ሙዝ በውስጡ ከፍተኛ ቫይታሚን B6 የያዘ ነው። ይህም በደም ውስጥ የሚኖረውን ከፍተኛ የስኳር መጠን እንዲቀንስ በማድረግ፣ በሰውነታችን ውስጥ የሚገኘውን የስኳር መጠን ለመቆጣጠር ያስችለናል፡፡ ከስኳር መብዛት ጋር ተያይዞ የሚከሰተውን የጠዋት ህመምንም ያስቀራል፡፡
8. ሙዝና ደም ማነስ
በሙዝ ውስጥ የሚገኘው የብረት ማዕድን ጠቀሜታው በደማችን ውስጥ ከፍተኛ መጠን ያለው የሔሞግሎቢን ምርት እንዲኖር ማድረግ ነው፡፡ ይህም በሔሞግሎቢን እጥረት ሳቢያ የሚከሰተውን የደም ማነስ እንዳይከሰት ያደርጋል፡፡
9. ሙዝ ለስካር
ሙዝ ከወተትና ከማር ጋር ተደባልቆ ለምግብነት ሲውል በከፍተኛ መጠጥ ወይም በስካር ሳቢያ የሚከሰትን ሃንግኦቨር (ያደረ ድምር) በቀላሉ ያስወግዳል፡፡ በመጠጥ ሳቢያ የተጐዳን ሰውነት እንዲነቃቃና ብርታት እንዲያገኝ በማድረግ ረገድም ሙዝ ከፍተኛ ሚናን ይጫወታል፡፡ የሲጋራ እና መሰል ሱሶች ተጠቂ የሆኑ ሰዎች ሱሱን ለማቆም እንዲችሉ ሙዝ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡
10. ለሞቃታማ አየር
በሞቃታማ የአየር ንብረት ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ሙዝን ቢመገቡ ሰውነታቸው ሙቀቱን እንዲቋቋም በማድረግ፣ የተረጋጋና የተስተካከለ የሰውነት ሙቀት እንዲኖረን ያደርገናል፡፡
11. የሙዝ ተጨማሪ ጠቀሜታዎች
በወባ ትንኝ የተነደፈ ሰው ወይንም በማንኛውም ተናካሽ ወይም ተናዳፊ ነፍሳት የተነደፈ (የተነከሰ) ሰው በሙዝ ልጣጭ የውስጠኛው ክፍል የተነደፈበትን (የተነከሰበትን) ቦታ በደንብ በማሸት እብጠቱን መቀነስ ይችላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ንድፍያው (ንክሻው) የፈጠረበትን የማቃጠልና የመለብለብ ስሜት ለማስወገድ ይችላል፡፡ ጫማዎን ከጠረጉና ቆሻሻውን ካስወገዱ በኋላ በሙዝ ልጣጭ ቢወለውሉት ጫማዎ እንደመስታወት ያበራልዎታል።
ፍሪጅዎ መጥፎ ጠረን (ሽታ) ካመጣብዎ አንድ ሁለት ሙዞችን ያስቀምጡበት፡፡ የፍሪጅዎ ጠረን በቅጽበት ይቀየራል፡፡
ሰውነትዎ በድካም ወይም በህመም ከተጐዳና የምግብ ፍላጐት ከሌለዎ አንድ ሙዝ እንደምንም ይመገቡ፡፡ ሰውነትዎ ሲበረታና የምግብ ፍላጐትዎ ሲጨምር ይታወቅዎታል፡፡
በአጠቃላይ ሁላችንም እንደቀላል የምናየውና ብዙም ትኩረት የማንሰጠው ሙዝ ለከፍተኛ የጤና ችግር የሚዳርጉንን በሽታዎች ለመከላከልና ለማስወገድ ይረዳናል፡፡
ታዲያ ይህን የግል ሐኪምዎ የሆነ ፈዋሽ ፍሬ በፍሪጅ ውስጥ ከተው አያበላሹት፡፡ ንፋስ ያለበት ያልታመቀ አየር ለሙዝ የሚስማማ ነውና - በዚያ ያኑሩት፡፡

(የጐንቸ ኤትወኸተታወካኾንም፣ ቢውሪ አንቃታ ባረም፣ አንቃሸታ ቦካኾን አቤተትኾንም)
ከዕለታት አንድ ቀን በአንድ ቤት ውስጥ አንድ አህያና አንድ የቤት ውሻ ይኖሩ ነበረ፡፡
አህያው እግርግም ውስጥ ይታሰራል፡፡ ብዙ መኖ በዙሪያው ይቀመጥለታል፡፡ በጣም ጠግቦ ይበላል። ጌታው ደግ በመሆኑ እንደልቡ እንዲያናፋም ይፈቀድለታል፡፡
የቤት ውሻው ደግሞ ጌታው ከውጪ ሲመጣ በር ድረስ ሄዶ ይቀበለዋል፡፡ ጌታውም ያመጣለትን ቅንጣቢ ሥጋ ይሰጠዋል፡፡
ወደቤት አስገብቶም እጭኑ ላይ አስቀምጦ እያሻሸ እራት ሲበላ እንደገና ጉርሻ ይሰጠዋል፡፡ አህያ ከደጅ ሆኖ ለውሻው የሚደረግለትን እንክብካቤ በማየት በጣም ይቀናል፡፡
አንድ ቀን አህያ፤
“ውሻ ሆይ?” ይላል፡፡
“አቤት” አለ ውሻ፡፡
“እኔ ባንተ ህይወት በጣም እቀናለሁ”
“ለምን?”
“ጌታችን ከበራፉ ጀምሮ እየመገበህ፣ እያሻሸህ፣ አብሮ ገበታ እያቀረበህ፣ አብረህ ቴሌቪዥን እንድታይ እየፈቀደልህ፣ ሳሎን እያሳደረህ እንደሰው ያኖርሃል፡፡ እኔ ግን ብርድ እየፈደፈደኝ አድራለሁ፡፡ ጠዋት ተነስቼ እህል ተጭኜ ወፍጮ ቤት እሄዳለሁ፡፡ ስመለስ ቀርበታ ተጭኜ ወንዝ እላካለሁ፡፡ ከዛ ሸቀጣ ሸቀጥ ተጭኜ ገበያ እሄዳለሁ፡፡ እንዲሁ ስሸከም ውዬ ስሸከም ይመሻል፡፡ የኔን ኑሮ ካንተ ሳወዳድረው ንድድ ይለኛል” አለው በምሬት፡፡
ውሻም፤
“ምን ታደርገዋለህ፡፡ ይሄ የተፈጥሮ ጉዳይ ነው፡፡ ምንም ብናደርግ ልናሻሽለው የምንችለው ጉዳይ አይደለም፡፡”
አህያም፤
“የለም ይሄንን የምንለውጥበት ጊዜ መምጣቱ አይቀርም፡፡ እኔ የማደርገውን ታያለህ” አለ፡፡
ውሻም፤
“ተው አይሆንም፡፡ ይህንኑ ኑሮህን ታበላሸዋለህ፡፡ አርፈህ ብትቀመጥ ይሻላል” አለውና ተለያዩ፡፡
አንድ ቀን አህያ የታሰረበትን ገመድ በጠሰና እየፈነጨ ሳሎን ገባ፡፡ እንደውሻው ጭራውን እየቆላ ጌታው ጭን ላይ ሊቀመጥ ሲሞክር አገሩን አተራመሰው፡፡ ሳህኑ መሬት ላይ ወደቀ፡፡ ጌታው ተፈነገለና ከነወንበሩ ወለሉ ላይ ተንጋለለ!
ይሄኔ የቤቱ አሽከሮች ትላልቅ ቆመጥ ይዘው መጡ፡፡ አህያውን እንዳይሞት እንዳይድን አድርገው እየቀጠቀጡ ከቤቱም፤ ከግቢውም አስወጥተው በሩን ዘጉበት፡፡ አህያ ደም በደም ሆኖ ባቡር መንገድ ላይ ተኝቶ ቀረ፡፡
* * *
ቦታን አለማወቅ እርግማን የመሆኑን ያህል አቅምን አለማወቅ ደግሞ ከመርገምት የከፋ መርገምት ነው፡፡ መንገድ ስላለና እግር ስላለን ብቻ አንሄድበትም፡፡ አቅጣጫውን ማወቅ አለብን፡፡ ወቅትንም መጠበቅ ይጠበቅብናል!
ስለዚህ እንግዲህ፣ ቦታ፣ አቅም፣ መንገድና አቅጣጫን ማወቅ የመጪው ዘመን ትምህርታችን ይሁን።
ያለፈው ዓመት የሰላም፣ የጤናና የብልጽግና ይሆን ዘንድ በአመቱ መግቢያ ተመኝተን ነበር፡፡ ሰላም ነበር ወይ? በልጽገናል ወይ? ጤና ነበርን ወይ? ብለን ሳንጠያየቅ ዘንድሮ ደግሞ የሰላም፣ የጤናና የብልጽግና ጊዜ ልንመኝ 2006 ዓ.ም ደጃፉ ላይ ቆመናል፡፡
በደጉ ጊዜ ሆያ ሆዬ ሲጨፈር፤
ብትሰጠኝ ስጠኝ ባትሰጥ እንዳሻህ
ከጐረቤትህ ከነሱ ጋሻህ” ይባል ነበር፡፡
ዛሬ ጋሻ ቀርቶ ሁዳይም የለምና ዘፈኑ ተቀይሯል፡፡
“እዚያ ማዶ አንድ ሻማ እዚህ ማዶ አንድ ሻማ፤
የኛ መብራት ኃይል ባለመቶ አርማ” በሚል ምፀት ተለወጠ፡፡
“ክፈት በለው በሩን የጌታዬን” ብለናል በቡሄ፡፡ የሀሁ በስድስት ወሩዋ ሙሾ አውሪጅ እቴሜት ጌኔ አምበርብር ደግሞ
“ዋይ ዋይ
ህመም ለህመም ሳንወያይ
አንተ ከመሬት እኛ ከላይ” ያለችውን ገልብጠን “እኛ ከመሬት አንተ ከላይ” ተባብለናል፡፡
ለውጥ በአንድ ጀንበር ይምጣ አይባልም፡፡ “ዓይንህነገ ይበራልሃል” ሲባል፤ ዛሬን እንዴት አድሬ” አለ እንደሚባለው አንሆንም፡፡
ምኞታችንና ጥያቄያችን ብዙ፤ መልሳችን ግን ጥቂት ነው፡፡ ሚዛን ይሸቀባል ወይ? የኑሮ ውድነት የት ደረሰ? ዲሞክራሲያችን ፋፋ ወይ? ፍትሕ አበበ ወይ? ኢኮኖሚው አደገ ወይ? ትምህርት ተስፋፋ ወይ? እስፖርት በለፀገ ወይ? ቤት ኪራይ ቀነሰ ወይ ሙስና ቀነሰ ወይ? ወንጀል መነመነ ወይ? ሹም - ሽር ቀነሰ ወይ? መንገድ በዛልን ወይ? ህንፃዎች በዙ ወይ? መኖሪያ ቤት በዛልን ወይ? ሻጭና ሸማች ተስማምተው ከረሙ ወይ? መልካም አስተዳደር ሰፈነ ወይ? መብራት ይጠፋል ወይ? ውሃ ይደርቃል ወይ? ኔትዎርክ ይበጣጠሳል ወይ? በመጨረሻም ገቢ ጨመረ ወይ? ወጪ ቀነሰ ወይ? ወይስ የተገላቢጦሽ ሆነ?
ጥያቄያችን እጅግ ረዥም መልሳችን በጣም አጭር ነው፡፡
በአጠቃላይ ግን ኑሮ ተመቸን ወይ? ሰፊው ህዝብ “የባሰ አታምጣ” አለ? ወይስ “ነገ በተስፋ የተሞላ ሆነልኝ” አለ፡፡ መቼም፤ ወቅቱ የትራንስፎርሜሽን ነው ብለን ለማጽናናት አንችልም፡፡ አዝመራ እሚደርሰው በሰኔ እኔን የራበኝ አሁን” ይለናላ! በክፉ ዘመን የሰው ሁሉ ስሙ “አበስኩ ገበርኩ ነው” እንዳለው ይሆን?
የዱሮ ዘመን ሊቀመንበር፤ ኤክስፐርቶች ግራፍና ስታቲስቲክስ ደርድረው፤ “ሀገራችን ለመለመች፣ አደገች፣ ዘንድሮ እህል በሽበሽ እንደሚሆን ነው ስታቲስቲክሱ የሚያሳየው” ሲሉ፤ የሀገሪቱ መሪ “የግድግዳውን ስታቲክስ አይተናል፡፡ የመሬቱን ንገሩኝ፡፡
ገበያው ጋ ሄደን እህሉ መኖሩን አሳዩኝ!” አሉ ይባላል፡፡
በልተን ለማደር ችለናል ወይ? እንደማለት ነው፡፡ የኑሮ ውድነትን መባባስ ለማየት አውዳመቶቹን መመርመር ነው፡፡ የጉራጌው ተረት ሁሉንም ይቋጨዋል:-
“ጅቡን የወጋኸው ምኑን ነው? ቢሉት፤ አፉን አለ፡፡ አፉን ከወጋኸውማ አሰፋኸው!”

እነ አቶ መላኩ ፈንታ በስህተት ፍ/ቤት ቀርበው ነበር
ከኦዲት ምርመራ አለመጠናቀቅ ጋር በተያያዘ ክስ ሳይመሰረትባቸው በፀረ ሙስና አቃቤ ህግ ጉዳያቸው እንደገና ወደ ጊዜ ቀጠሮ መዝገብ በተመለሰባቸው የከባድ ሙስና ተጠርጣሪዎች ላይ በድጋሚ የ8 ቀን የምርመራ ጊዜ ተሰጠ፡፡
በትናንትናው እለት ዳኞች ተሟልተው ባለመቅረባቸው ጉዳያቸው በጽ/ቤት በኩል የታየው በእነ አምባው ሰገድ መዝገብ ተካተው የነበሩት አቶ ተክለአብ ዘርአብሩክ፣ በእነ አቶ ገ/ዋህድ ወ/ጊዮርጊስ መዝገብ ተካተው የነበሩት ባለሃብቶቹ አቶ በእግዚአብሔር አለበል እና አቶ ምሕረተአብ አብርሃ እንዲሁም በራሳቸው ስም በተሰየመው መዝገብ ተካተው የነበሩት ፍፁም ገ/መድህን ናቸው፡፡
የኮሚሽኑ መርማሪ ቡድን ቀደም ብሎ በዋለው ችሎት በተሰጠው የ10 ቀን የድጋሚ ምርመራ ጊዜ ውስጥ የኦዲት ስራውን ሲከታተል መቆየቱን በማመልከት፣ አሁንም የኦዲት ስራው ባለመጠናቀቁ ተጨማሪ የ14 ቀን ጊዜ እንዲሰጠው ለፍ/ቤቱ ጥያቄ አቅርቧል፡፡ ፍ/ቤቱም የኦዲት ስራው በምን ያህል ጊዜ እንደሚጠናቀቅ የመርመሪ ቡድኑን የጠየቀ ሲሆን፣ መርማሪ ቡድኑም “በ15 ቀን ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል” የሚል ምላሽ ሰጥቷል፡፡
ፍ/ቤቱም በመርማሪ ቡድኑ ከተጠየቀው የ14 ቀን ቀጠሮ ውስጥ 8 ቀን ብቻ በመፍቀድ መዝገቡን ለመስከረም 3 ቀን 2006 ዓ.ም ቀጥሯል፡፡
በሌላ በኩል በትናንትናው እለት ጠዋት ክስ ተመስርቶባቸው የክሣሳቸውን ዝርዝር ለማዳመጥ ለጥቅምት 11 እና 12 ተቀጥረው የነበሩት አቶ መላኩ ፈንታ እና አቶ ገ/ዋህድ ወ/ጊዮርጊስን ጨምሮ ሌሎች ተከሳሾች በስህተት ፍ/ቤት ያለቀጠሮ የቀረቡ ሲሆን፣ የማረሚያ ቤቱ አጃቢ ፖሊሶችም ቀጠሮ እንዳልነበረ ካረጋገጡ በኋላ ተከሳሾቹን ወደ ማረሚያ ቤት መልሰዋቸዋል፡፡

በቅርቡ ከመኢአድ ሊቀመንበርነታቸው በመልቀቅ በፓርቲው የበላይ ጠባቂነት የቀጠሉት የኢ/ር ኃይሉ ሻውልን የህይወት ታሪክ የያዘ መፅሀፍ ከነገ በስቲያ ለንባብ እንደሚበቃ የመፅሀፉ አዘጋጅ ጋዜጠኛ ፍሬው አበበ ገለፀ፡፡ “ህይወቴና የፖለቲካ እርምጃዬ” በሚል ርዕስ የተዘጋጀው መፅሃፉ፤ የኢ/ር ኃይሉ የህይወት ውጣ ውረድና የፖለቲካ ተሳትፎ ላይ እንደሚያተኩር አዘጋጁ ለአዲስ አድማስ ተናግሯል፡፡
በተለይም ከ97 ምርጫ ጋር በተያያዘ የተፈጠሩ ክስተቶችና ለቅንጅት መፍረስ ምክንያት ነው ያሉትን ጉዳዮች ያሳዩበት መፅሃፍ እንደሆነ የገለፀው አዘጋጁ፤ ከምርጫው ጋር ተያይዞ የቅንጅት አመራሮች መታሰር፣በእርቅ መንፈስ የተጀመረው ሽምግልና እንዴት ወደ ይቅርታ መጠየቅ እንደተቀየረ፣ በእስር ላይ የነበረው የቅንጅት አመራር ክፍፍል ምን መልክ እንደነበረው እና መሰል ጉዳዮችን የሚተነትኑ አዳዲስ መረጃዎች እንደተካተቱበት አብራርቷል፡፡
“በተለይ ኢንጂነር ኃይሉ ሻውል የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ ችግሮች ሁሉ ወደ ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ብቻ ሳይወረውሩ፣ በራሱ በተቃውሞ ጎራው ያሉትንም ችግሮች አንድ በአንድ ነቅሰው በመፅሀፋቸው ለማሳየት መቻላቸው፣ ለአገሪቱ ፖለቲካዊ ችግሮች መፍትሄ ለሚሹ ወገኖች ሁሉ ጥሩ መረጃ የሚሰጥ እንደሚሆን ይታመናል” ብሏል አዘጋጁ፡፡ የመፅሃፉ ሁለተኛ ክፍል በአዲሱ ዓመት ለንባብ እንደሚበቃም ለማወቅ ተችሏል፡፡ የፊታችን ሰኞ በ55 ብር ለገበያ የሚቀርበው የኢንጅነሩ መፅሃፍ፤ በስድስት ክፍሎችና በ175 ገፆች ተቀንብቦ የተዘጋጀ ነው ተብሏል፡፡