Administrator

Administrator

ማርች 8 አለማቀፍ የሴቶች ቀንን ምክንያት በማድረግ በተካሄደው የሴቶች የጎዳና ላይ ሩጫ ‹‹አንዳንድ ያልተገቡ ድርጊቶች ፈፅማችኋል›› በሚል በፖሊስ ቁጥጥር ሥር የዋሉ አስር ከፍተኛ የሰማያዊ ፓርቲ አመራር አባላት ትላንት ፍ/ቤት ቀርበው ፖሊስ አራት ተጨማሪ የምርመራ ቀናት ጠየቀባቸው፡፡
በቁጥጥር ስር የዋሉት 7 ሴቶችና 3 ወንዶች የፓርቲው አባላት በጎዳና ላይ ሩጫ ‹‹አንዷለም ይፈታ፣ ርዕዮት ትፈታ፣ ውሃ ናፈቀን፣ መብራት ናፈቀን›› የሚሉ መፈክሮችን ሲያሰሙ ነበር ተብሏል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ በከፍተኛ የአመራር ቦታ ላይ ያሉና ቋሚ አድራሻ ያላቸው እንደሆኑ በመግለፅ በዋስ እንዲፈቱ ቢጠይቁም ፖሊስ በበኩሉ፤ ወንጀሉ ውስብስብ በመሆኑ አራት ተጨማሪ ቀናት የምርመራ ጊዜ ያስፈልገኛል ሲል አመልክቷል፡፡
ፍ/ቤቱም የተጠርጣሪዎቹን የዋስትና መብት በመከልከል ለትናንትና ቀጠሮ ሰጥቶ ነበር፡፡ ትላንት ፍርድ ቤት የቀረቡት ተጠርጣሪዎች ላይ ፖሊስ ተጨማሪ አራት ቀን ምርመራ ጊዜ ጠይቆ ፍ/ቤቱም ለመጭው ማክሰኞ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

መጽሐፉ ለአቡነ ማትያስና ለጠ/ሚ ኃይለማርያም እንዲደርሳቸው ተደርጓል
ደብዳቤው ለእስራኤሉ ጠ/ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታናሁ እና ለተመድ ተልኳል

       ከተፃፈ ከ2 ሺህ ዓመታት በላይ አስቆጥሯል የተባለውንና ስለ ቅዱስ ኤልያስ መምጣት ምስጢር የሚተነትነውን መጽሐፍ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ተቀብላ ወደተለያዩ ቋንቋዎች በማስተርጎም ምዕመናኖችን እንድታስተምር፣ “ማህበረ ሥላሴ ዘደቂቀ ኤልያስ” ለቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ በጻፈው ደብዳቤ ጠየቀ፡፡
ማህበሩ፤የመጽሐፉን ኮፒዎች ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሣለኝ እና ለብፁዕ አቡነ ማትያስ  ህዝቡን እንዲያስተምሩበት ከሚያሳስብ ደብዳቤ ጋር መላኩን አስታውቋል፡፡
አርቲስት ጀማነሽ ሰለሞን አባል የሆነችበት ማህበረ ሥላሴ፤“ቅድስት ቤተ-ክርስቲያን ለሁለት ሺህ ዘመን ስትጠብቀው የቆየችውን ምስጢራዊ መጽሐፍ በአደራ የመረከብና ለዓለም ሁሉ የማሳወቅ ፅኑ ኃላፊነትን ይመለከታል” በሚል ርዕስ ለፓትርያርኩ፣ በግልባጭ ደግሞ ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እንዲሁም ለእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔትናሁ እና ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት በፃፈው  ደብዳቤ “ማህፈድ ብርህት ዘዲዮስቆሮስ አንበሳ” በሚል ርዕስ በግዕዝ ቋንቋ የተፃፈውን መጽሀፍ፣ የቤተ-ክርስቲያኗ ሊቃውንት ተቀብለው ምእመናኑን ስለ ቅዱስ ኤልያስ እና ትክክለኛይቱ ሰንበት እንዲያስተምሩበት አሳስቧል፡፡
ደብዳቤው ለእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር የተላከው ኢትዮጵያና እስራኤል በመንፈሣዊ አሰራር አንድ ስለሚሆኑበት ሁኔታ ለማመልከት ነው ያሉት የማህበሩ አመራሮች፤ለተባበሩት መንግሥታት የተላከውም መልእክቱ ለዓለም ሁሉ እንዲዳረስ ስለሚፈለግ ነው ብለዋል፡፡
ከ2 ሺህ ዓመታት በፊት እንደተፃፈ የሚነገርለት መጽሐፉ፤ ስለ ቀዳሚት ሰንበት ምንነትና ዘለዓለማዊነት በግልፅ እንደሚያብራራ እንዲሁም የኢትዮጵያና የእስራኤልን አንድነትና ትንሳኤ ምስጢር ተንትኖ እንደሚያስረዳ ተጠቁሟል፡፡
ማህበሩ በላከው መልዕክት፣ ቅዱስ ኤልያስ ከብሄረ ህያዋን ይዞት የመጣውን መጽሀፍ፣ የቤተ-ክርስቲያኒቱ ሊቃውንት እንዲመረምሩት፣ በተለያዩ ቋንቋዎች እንዲተረጎምና እንዲታተም፣ ምዕመናንም እንዲያነቡት የማድረግ ግዴታ ፓትርያርኩ እንዳለባቸው ያሳስባል፡፡ “ይህ ሳይሆን በእንቢተኝነትና በቸልታ ለዘመናት በተስፋ የተጠበቀውን ይህን መጽሀፍ እንዳይቀርብ ቢያደርጉ፣ ከብሄረ ህያዋን የመጣው ቀናኢ ነቢይ ዓለምን ሁሉ እየገሰፀ ባለበት ኃያል፣ ስልጣኑ ፅኑ ፈራጅነቱና ቁጣው የሚፈርድ መሆኑን አረጋግጠን እንነግርዎታለን” ብሏል፡፡ “ለቤተ-ክርስቲያኒቱ ሲኖዶስ እና ካህናት ጥፋትና የመጨረሻው ውድቀት ነው” ሲልም ለመፅሃፉ ትኩረት እንዲሰጥ ማህበሩ  አበክሮ አሳስቧል፡፡
በጉዳዩ ዙሪያ የፓትርያርኩን ጽ/ቤት እና የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጽ/ቤት በስልክ አግኝተን ለማነጋገር ያደረግነው ተደጋጋሚ ሙከራ ሳይሳካ ቀርቷል፡፡


ነገ የሦስት ወር ንቅናቄውን በአዲስ አበባ ይጀምራል

      ከመድረክ ጋር ያለውን ጥምረት አቋርጦ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር የውህደት ድርድር የጀመረው አንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ፓርቲ፤በመጪው ዓመት ምርጫ የሚሳተፈው የምርጫው አስፈፃሚ አካላት ነፃና ገለልተኛ መሆናቸው ከተረጋገጠ ብቻ እንደሆነ  ሊቀመንበሩ ኢ/ር ግዛቸው ሽፈራው ገለፁ፡፡
በ97 ምርጫ ቅንጅት የነበረውን ጥንካሬ ፓርቲያቸው መድገም እንደሚፈልግ የገለፁት ኢ/ር ግዛቸው፤ ህዝቡ ብሶት ላይ ስለሆነ በምርጫው ተቃዋሚዎች በቀላሉ ሊያሸንፉ እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡ ፓርቲያቸው ወደ ምርጫው የሚገባው ግን ለምርጫው ነፃና ፍትሃዊ መሆን አስፈላጊ የሚባሉት ገለልተኛ የምርጫ ቦርድ፣ ሚዲያ እና የፍትህ ተቋማት መኖራቸውን ካረጋገጠ በኋላ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ “ይህ ጥያቄያችን ከተመለሰ በምርጫው በእርግጠኝነት እናሸንፋለን” ብለዋል የፓርቲው መሪ፡፡
ፓርቲያቸው ከመድረክ ጋር ስላለው ግንኙነት የተጠየቁት ኢ/ር ግዛቸው፤ አንድነት ከቢሮ እና ከመግለጫ ፖለቲካ ተላቆ ትግሉን ወደ ህዝብ ለማውረድ  ያደረገው እንቅስቃሴ የመድረክ አመራሮችን እንዳስኮረፈና እገዳው እንደተላለፈ ጠቅሰው “እገዳው ትክክል አይደለም፤ አንሱትና ባቀረብነው የውህደት ጥያቄ መሰረት አብረን እንስራ ብለናቸዋል” ብለዋል፡፡
“መድረክ ከአንድነት የተሻለ ጥንካሬ እንደሌለው ገምግመናል” ያሉት ሊቀመንበሩ፤ ውህደቱን አንፈልግም ቢሉም እንኳን በሚያግባቡን ጉዳዮች ላይ በቅንነት አብረን ልንሰራ እንደምንችል ነግረናቸዋል ብለዋል፡፡
ከእዚህ በኋላ አንድነት በቀጥታ ውህደት ከመፈፀም ውጪ ከየትኛውም ፓርቲ ጋር ግንባርና ቅንጅት የመፍጠር ፍላጎት እንደሌለውም ኢ/ር ግዛቸው ጨምረው ገልፀዋል፡፡
ፓርቲው በነገው እለት “የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት” ሁለተኛ ዙር ንቅናቄ በአዲስ አበባ የሚጀምር ሲሆን  አጀንዳውም መሬት የግል እንዲሆን የሚጠይቅ ነው ተብሏል፡፡ ለ3 ወር ይዘልቃል የተባለውን ይሄን ንቅናቄ በተመለከተ የተጠየቁት ኢ/ር ግዛቸው፤“በአንድነት ፕሮግራም ውስጥ ከመንግሥት ይዞታና ከአንዳንድ ተቋማት ይዞታ በስተቀር መሬት የግል መሆን አለበት በሚል በግልፅ አስቀምጠናል፡፡ ይህን መነሻ አድርገን በመሬት ጉዳይ ላይ ህዝብ ተወያይቶ የራሱን አቋም የሚይዝበት ትልቅ ንቅናቄ አዘጋጅተናል” ሲሉ አስረድተዋል፡፡
 አሁን ያለው የመሬት ፖሊሲ ለኑሮ ውድነቱ መባባስ አስተዋፅኦ አበርክቷል ያሉት ኢ/ር ግዛቸው፤ “የኑሮ ውድነቱ ካለን የመሬት ሃብት ተጠቃሚ ያለመሆናችን ውጤት ስለሆነ፣ ጥያቄያችን የኑሮ ውድነት አጀንዳንም በበቂ ሁኔታ የያዘ ነው” ብለዋል፡፡ መንግስት በበኩሉ፤ መሬት የህዝብና የመንግስት ነው የሚል ፖሊሲ እንደሚያራምድ ይታወቃል፡፡
(ከአንድነት ፓርቲ ሊቀመንበሩ ኢ/ር ግዛቸው ሽፈራው ጋር የተደረገው ቃለምልልስ ሙሉ ቃል በገፅ 5 ላይ ያገኙታል፡፡)


          የ38 አመቱ ኢትዮጵያዊ ዶክተር ፍሰሃ ኡንዱቼ በካናዳ የመሰረተ ልማትና የትራንስፖርት ሚኒስቴር የማኒቶባ ግዛት የአየር ንብረትና የጎርፍ አደጋ ትንበያ ዳይሬክተር ሆነው መመረጣቸውን ዊኒፒንግ ፍሪ ፕሬስ ዘገበ፡፡
የካናዳ የመሰረተ ልማትና የትራንስፖርት ሚኒስትር ስቲቭ አሽተን ዶክተሩን ለመገናኛ ብዙሃን ለማስተዋወቅ በተዘጋጀ ስነስርዓት ላይ ተገኝተው እንደተናገሩት፣ ከተለያዩ አገራት የተውጣጡ በርካታ ባለሙያዎች የተሳተፉበትን ከፍተኛ ውድድር በማሸነፍ ለማኒቶባ ግዛትየአየር ንብረትና የጎርፍ አደጋ ዳይሬክተር ለመሆን የተመረጡት ዶክተር ፍሰሃ፣ ላለፉት 15 አመታት በሃይድሮሎጂና ከጎርፍ አደጋ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች በአሜሪካና በተለያዩ የአውሮፓ አገራት የካበተ የስራ ልምድ አላቸው፡፡
ላለፉት አምስት አመታት የግዛቷ የውሃ ቁጥጥር ስርዓቶች ዕቅድ ከፍተኛ መሃንዲስ ሆነው ያገለገሉት ዶክተር ፍሰሃ፣ ከዚያ ቀደምም ኤኢኮም በተባለ አለማቀፍ የምህንድስና አገልግሎቶች ኩባንያ ውስጥ የውሃ ሃብቶች መሃንዲስ ሆነው ማገልገላቸው ተነግሯል፡፡ ኒዘርላንድ ውስጥ ከሚገኘው ኢንተርናሽናል ሃይድሮሊክ ኢንጂነሪንግ ኢንስቲቲዩት በሲቪል ምህንድስና የሁለተኛ ዲግሪያቸውን የተቀበሉት ዶክትር ፍሰሃ፣ በኖርዌጂያን ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ሳይንስ ኤንድ ቴክኖሎጂ ሌሎች የምርምር ጥናቶችን እንደሰሩ ተጠቁሟል፡፡
ከማኒቶባ ዩኒቨርሲቲ በውሃ ሃብቶች የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ከተቀበሉ በኋላም፣ በተለያዩ ተቋማት ውስጥ ከጎርፍ አደጋ ትንበያና ከአደጋ ቁጥጥር ጋር በተያያዙ ጉዳዮች በውሃ ሃብቶች መሃንዲስነትና በመምህርነት አገልግለዋል፡፡በወቅቱ ከጋዜጠኞች ጥያቄ የቀረበላቸው ዶክትር ፍሰሃ፣ በውሃው ዘርፍ የጀመሩትን ጥናት አጠናክረው ለመቀጠል የሚያስችሏቸውን የጎርፍ አደጋዎች የሚበዙባቸው አካባቢዎችና በጎርፍ አደጋ ትንበያ ላይ ልዩ ትኩረት አድርገው የሚሰሩ ዩኒቨርሲቲዎች ሲያጠኑ እንደቆዩና ማኒቶባ ግዛት ለዚህ ተመራጭ መሆኗን በማረጋገጥ ወደዚያው ለመሄድ መወሰናቸውን ተናግረዋል፡፡
ዶክተር ፍሰሃ ባለትዳርና የሁለት ልጆች አባት ናቸው፡፡
           አምስቱ የአድዋ ተጓዦች ከአዲስ አበባ 260 ኪ.ሜ አካባቢ ወለቲ በተባለች ትንሽ ከተማ የበእምነት ደገፉ እናት የነገሯቸውን አሳዛኝ ነገር አይረሱትም፡፡ በእምነት ደገፉ የ5 ዓመት ህፃን ነው። ይህ ህፃን ሁለቱም ኩላሊቶቹ ደም ስለማያጣሩ ሀኪም ቤት እየተወሰደ ደሙ እየተለወጠ ነው እስካሁን በሕይወት የቆየው፡፡ ሁሉም የትንሷ ከተማ ነዋሪዎች ወደ ከሚሴ ከተማ እየሄዱ ለህፃኑ ደም ለግሰዋል፡፡ አሁን በመንደሯ ለበእምነት ደም ያልሰጠ ሰው የለም፤ ሁሉም ተዳርሷል፡፡ እባካችሁ ወደ አዲስ አበባ ስትመለሱ ልጄ ዘላቂ ህክምና አግኝቶ፣ ህይወቱ ሰንብታ አድጎና ተምሮ ለአገሩ ቁም ነገር የሚሰራ ልጅ አድርጉልኝ ሲሉ ተጓዦቹን ተማፀኑ፡፡ ተጓዦቹም በሰሙት ነገር ልባቸው ክፉኛ ተነካ፡፡ በተለያዩ ሚዲያዎች በእምነት ያለበትን ሁኔታ ለኢትዮጵያ ህዝብ ገልፀው ሁሉም የአቅሙን እንዲረዳ በማስተባበር የህፃኑን ህይወት ለመታደግ ቃል ገቡ፡፡
ህፃኑን መርዳት የምትፈልጉ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የከሚሴ ቅርንጫፍ ሂሳብ ደብተር ቁጥር 10000714572347 ያስገቡለት፡፡ የእናቱ ስም አትክልት እሼቱ ይባላል፡፡

ከፍተኛ ተሰጥኦ እንዳላት የሚነገርላት የኢትዮጵያ ጃዝ አቀንቃኝ የሺ ደምመላሽ በሚያዝያ ወር አጋማሽ ላይ በኒውዮርክ የሙዚቃ ኮንሰርት እንደምታቀርብ ታዲያስ መፅሄት ዘግቧል፡፡
የጃኖ ባንድና የጂጂን ሥራዎች ያሳተመው የኒውዮርኩ ፕሮዱዩሰር ቢል ላስዌል “ፋኖ” የተሰኘ ዘፈኗን ዳግም አዋህዶ እያቀናበረላት ሲሆን የሺ አዲስ አልበም ከላስዌል ጋር የመስራት ዕቅድ እንዳላት ታውቋል፡፡
ድምፃዊቷ የኒውዮርክ ኮንሰርቷን የምታቀርበው ከ “ቅኔ” ባንድ ጋር ነው ተብሏል። በኢትዮጵያ አይዶል ዳኝነቷ የምትታወቀው የሺ፤ ከያሬድ ሙዚቃ ት/ቤት በፍሉትና በተጓዳኝ በፒያኖ አጨዋወት ተመርቃለች፡፡ አርቲስቷ “ቅኔ” የተሰኘ የመጀመርያ አልበሟን የዛሬ ሁለት ዓመት ለጆሮ ማብቃቷ ይታወሳል፡፡   

የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሕግ ት/ቤት የ50ኛ ዓመት ኢዮቤልዩ በዓሉን አስመልክቶ ብሔራዊ የምስለ ችሎት ውድድር እንደሚያካሂድ ገለፀ፡፡ ከመጋቢት 16-18 የሚካሄደው ውድድር፤ በአለም አቀፍ ወንዞች አጠቃቀም ዙሪያ የተዘጋጀ ሲሆን በአገሪቱ ያሉ የሕግ ት/ቤቶች በሙሉ ይሳተፋሉ ተብሏል፡፡ የመጨረሻ የዋንጫ ውድድር መጋቢት 18 ከጠዋቱ 2፡30 ሰዓት የሚከናወን ሲሆን በጉዳዩ ላይ ከፍተኛ ምርምር ያደረጉ ምሁር በአገራችን ድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን አስመልክቶ ስለሚነሱ የህግ ክርክሮች የማጠቃለያ ንግግር እንደሚያደርጉ የህግ ት/ቤቱ ጠቁሟል፡፡

በደሳለኝ ግርማ (ዲዶስ ሳምናስ) የተፃፉ የአጭር ልብወለድ እና የግጥም ስብስቦችን የያዘ መፅሃፍ በዛሬው ዕለት በሐረር ይመረቃል፡፡
በአንድ በኩል “አድናቂው” በሚል ርዕስ የአጭር ልብወለድ ስብስቦች ያካተተው መፅሃፉ፤ በሌላው በኩል “እግዜርና አፍሪካ” በተሰኘ ርዕስ የግጥም ስብስቦችን ይዟል፡፡ በኤች ዋይ ኢንተርናሽናል የህትመት ሥራ ድርጅት የታተመው መፅሃፉ፤ በ40 ብር ከ50 ለገበያ ቀርቧል፡፡

የፈጠራ ስራዎች ፀረ-ፊውዳል ድርሰቶች አይደሉም የሚል ምሁር ከመካከላችን ይኖራል? ታዲያ ፀረ-ፊውዳል ታጋዩና የመሬት ላራሹ መፈክር አንጋቢው ተራማጁ የተማሪዎች ማህበር ይህን ህዝባዊ ደራሲ ሳያጎላው ያለፈው ሆን ብሎ ይሆን ወይስ ረስቶት?

ይህን ጽሑፍ ያዘጋጀሁት ስለ አንጋፋው ደራሲ አቤ ጉበኛ አንዳንድ ሃሳቦችን ለመሰንዘር ነው። ጽሑፉ ከምርምርም በሉት ከጥናት ሥራ ጋር የሚመደብ አይደለም፡፡ ወፍ በረር ወይም ወፍ ዘለል ምልከታ አይባልም፡፡ በአጭሩ እኔ ስለአቤ የተሰማኝን የገለጽሁበት መላምታዊ ስሜት ነው፡፡
አቤን እኔ በሚገባ ወይም በቅርበት አላውቀውም፡፡ የአቸፈር ሰው መሆኑን፣ ዳንግላ መማሩን የተረዳሁት በቅርቡ ነው፡፡ የእኛ ዘመን ምሁራን “የየት አገር ሰው ነህ?” ተባብለው በይፋ አይጠያየቁም ነበር፡፡ በትምህርት ቤት ዘመኔ “ሰይፈ-ነበልባል” የተባለውን ድርሰቱን ያነበብሁ ይመስለኛል፡፡ በእኔ የጉርምስና ዘመን፣ በእኔ አካባቢ ስሙ እንደ ሌሎች ደራሲዎች ጎልቶ ሲነገር አልሰማሁም፡፡ ወይም የግንኙነት አድማሴ ጠባብ ነው ወይም በጆሮዬ ተኝቼበታለሁ፡፡ አሁን ይህን እያልሁ ያለሁት በዚያ በእኔ ዘመን ላይ ቆሜ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ አዎ! እንደ ከበደ ሚካኤል፣ እንደ መንግስቱ ለማ፣ እንደ ፀጋዬ ገ/መድህን፣ ሌላው ቢቀር እንደ መንግስቱ ገዳሙ እንኳ በስሙ አይዘመርለትም ነበር፡፡ የፈጠራ ስራው የወረደ ስለሆነ? ፈፅሞ አይመስለኝም፡፡ ሥራዎቹማ! እሳት ጫሪ፣ አነጋጋሪ፣ የአብዮት ማዕበል ጠሪ ነበሩ፡፡ ፀባዩ ከሰው ስለማይገጥም? ይህ በከፊል እውነት ሊሆን ይችላል፡፡ አቤ እከክልኝ-ልከክልህን የማያውቅ በራሱ የሚተማመን የቀለም ሰው ነበር፡፡ ይህን ሁሉ የሆነ ደራሲ ለምን ደመ መራራ ሆነ? መልሱን እኔም አልሰጣችሁም፤ እናንተም እንድትመልሱልኝ አልፈልግም፡፡
በእነዚያ ዘመናት በአቤ ስም ላይ የተጫኑትን ቋጥኞች ከሥር መሰረታቸው ፈልፍሎ ለማወቅ በእርግጥም ጥልቅ ጥናትና ምርምር ይጠይቃል፡፡ እኔ ግን መላምቴን ጎን-ለጎን ባስሔድ ጆሮውን የሚነፍገኝ እንደማይኖር ተስፋ አለኝ፡፡
1. አቤና የአጼው ዘመን
በዚያን ዘመን የነበሩ ደራሲያን፣ አብዛኛዎቹ በቀኝ እጃቸው ብዕር፣ በግራ እጃቸው ሥልጣን የጨበጡ ናቸው፡፡ በዚህም መሰረት የዘመኑ ሹም የሰራው ብቻ ሳይሆን በሩቁ በማንኪያ የነካው ወጥ ሁሉ ይጣፍጥለታል፡፡ ለምን ቢሉ? ወጡ እንዳይጎረና ዙሪያ ከበው የሚያማስሉለት ብዙ ሌቄዎች ከጎኑ ስላሉ … የዚያ ሁሉ ወጥ አማሳይ እጅ ያረፈበት ወጥ ደግሞ በየትኛውም መመዘኛ ሲታይ ላይጣፍጥ አይችልም፡፡
አቤ በዚያን ዘመን የግሽ-አባይ ጎርፍ ከገጠር አምጥቶ ከቀለጠው ከተማ የዶለው ብቸኛ ፍጡር ይመስለኛል፡፡ በቀኝ እጁም የያዘው ብዕር ብቻ ነው፡፡ ብዕሩም በቅኔ ቤት እንጂ በገነተልዑል ግቢ ውስጥ ገብቶ ያልተሟሸ ነው፡፡ ቃላቱም ቱባ-አገራዊ ሽካራ እንጅ ቤተመንግሥታዊ ለስላሳ አይደለም፤ አስተሳሰቡም ደረቅ-ገጠራዊ እንጅ ከተማዊ-ጮሌ አይመስለኝም፡፡ ገፀ-ባህርያቱም አብዛኛዎቹ ከውጭ አገር የኮረጃቸው ሳይሆን ከአካባቢው በተጨባጭ የፈጠራቸው ናቸው። በፖለቲከኞች ቋንቋ ለመናገር፣ አቤ ለዘመኑ ቢሮክራሲ አጎብዳጅ አልነበረም። (አስር ጊዜ አይመስለኝም… ይመስለኛል… የምለው ያለምክንያት አይደለም፡፡ አንድም ከላይ እንደገለጽሁት ጽሑፉ ጥናታዊ አለመሆኑን ለማረጋገጥ ነው፡፡ ሁለትም ለዚህ መረጃ የሚሆን ማጣቀሻ የፈረንጅ ስም ለመጥራት ስላልፈለግሁ ነው፡፡ ሶስትም አገራዊ ሊቃውንትን በመረጃነት እንዳላቀርብ የቀሰምሁት ዘመናዊ የፈረንጅ ትምህርት የሚስበኝ ወደ ነጭ ምሁራን እንጂ ወደ እራሴ ሊቃውንት አለመሆኑን ለማስገንዘብ ጭምር ነው፡፡)
ወደ ተነሳሁበት ነጥብ ልመለስ፡፡ እና! የአቤ ስም በዘመነ አፄ ለምን ገንኖ አልወጣም? ልብ በሉ፤ አቤ በዚያን ዘመን ግራ እጁ ባዶ ቢሆንም ቀኝ እጁ የሚንቦገቦግ የብዕር ሰይፍ ጨብጧል፡፡ ይህ ሰይፈ-ነበልባል የዘውዱን ህዝባዊ የብዕር ሰው ስም በስርአቱ እንዲታፈን መደረጉ ተገቢም ባይሆን የሚጠበቅ ነው፡፡ ያኔ ሥዩመ እግዚአብሔርን መዳፈር ራሱን ፈጣሪን መድፈር ሆኖ ይቆጠራል፡፡ ይህንን የስዩማንን ድፍረት ቅኔ የቆረጠባት ቤተክርስቲያንም ብትሆን በደግ የምትቀበለው አይመስለኝም፡፡ ቀብታ ያነገሰችውን ንጉሥ ከጉያዋ የወጣ ደብተራ፣ በግራ እጁ ስልጣን ያልጨበጠ ብዕረኛ፣ የቁም-ስቅሉን ሲያበላው ቁጭ ብላ አትመለከተውም፡፡ ያኔ! አቤን አውግዢው፤ ወይም የይቅርታ ደብዳቤ አስጽፊው ብትባል አቤን እንዲጽፍ ሳታስገድደው የምትቀር አይመስለኝም፡፡
ንጉሡና በእሳቸው አካባቢ ያሉት መኳንንትና መሳፍንት አቤን የሚመለከቱት እንደ ኮሚኒዝም በጎሪጥ ነው፡፡ በዘመነ አብዮት ቆምጬ፤ “ኢምፔሪያሊዝምን በጎሪጥ ሶሻሊዝምን እንደ በላይ ዘለቀ አያቸዋለሁ” ብሏል አሉ፡፡ ይህ በዘመኑ ቢሮክራሲ የጎሪጥ የሚታይ ሰው፣ ግራ እጁ ባዶ የሆነ፣ ብዕሩ አርፎ የማይተኛ ተንኳሽ፣ በዐይነ-ቁራኛ የሚታይ ሞገደኛ ብዕረኛ፣ እንኳንስ ስም አሞጋሽ፣ አፍ-አካፋች ጓደኛም አይኖረውም፡፡ እንኳንስ በቀኛቸው ብዕር፣ በግራቸው ሥልጣን የጨበጡት ደራሲያን፣ የእነሱ ቅርበት ያላቸውም ንዑስ ደራሲያንም ቢሆኑ አቤን የሚቀርቡ አይመስለኝም፡፡ ከእሱ ጋር መታየት ከእሱ ጋር መፈረጅ ነው፡፡ ከእሱ ጋር መፈረጅ ደግሞ ከእሱ ጋር ግዞት መውረድ ያስከትላል፡፡ በመሆኑም በዘመኑ አቤን የከበቡት ስም አጥፊዎቹ እንጅ ስም አልሚዎቹ አይደሉም ባይ ነኝ፡፡ በቀረው ተመራማሪው ይሙላበት፡፡  
2. አቤና የተማሪው እንቅስቃሴ
እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ ተማሪዎች እንቅስቃሴ በአገራችን ብቻ ሳይሆን በመላው ተራማጅ ዓለም ህዝቦች ዘንድ አንቱ የተባለ ማህበር ነበር፡፡ ማህበሩ ጥልቅ ተራማጅ ብቻ ሳይሆን የሶሻሊስት ርዕዮት አለም ተከታይ ጭምር ነበር፡፡ እንቅስቃሴውም በአገር ውስጥ የነበረው ተሰሚነት ቀላል አልነበረም፡፡ የዘውዱን ስርዓት ቦርቡሮ የጣለው ይህ እንቅስቃሴ እንደሆነ ይታመናል፡፡ ምንም እንኳ ዋርዳ ወይም ማማት ወፎች ፈልገው ያገኙትን የሾላ ፍሬ (አብዮት መሆኑ ነው) አንድ ጉራሽ ሳይቀምሱት ዛፉ ላይ ወጥተው ሲንጫጩ፣ የቤተ መንግሥት ጫካ ተንተርሶ፣ እረኛ መስሎ የበግ ለምድ ለብሶ፣ ያደፈጠ ዝንጀሮ የሾላውን ፍሬ ቢቀማቸውም፣ የተማሪው እንቅስቃሴ ለዚያን ጊዜው ለውጥ ያበረከተው አስተዋጽኦ እጅግ ከፍተኛ ነበር፡፡
ይህ እንቅስቃሴ በላይን ንጉሡ አንቀው ከቀበሩት ጉድጓድ አውጥቶ የታጋይ ካባ ያለበሰ ማህበር ነው። ደጃዝማች ታከለን ፈርጣጭ ንጉሥ አጋች ብሎ ያሟካሸ ነው፡፡ ከዘመኑም ደራሲያን መካከል መርጦ የተቡ ብዕርተኞች ብሎ የካበና የሾመ ነው፡፡ ለ“አልወለድም” ደራሲ፣ በግራ እጁ ባዶ ሆኖ ሥርዓቱን ቀድሞ ለተፋለመ ህዝባዊ የብዕር ሰው፣ ማህበሩ ለምን ያኔ! የጎላ ዕውቅና አልሰጠውም? በግሌ ይህ ተራማጁ የተማሪዎች እንቅስቃሴ በመጽሔቶቹ ላይ ስለ አቤ የፃፈውን ነገር አላነበብሁም፡፡
አቤ በሩሲያ ሥነ-ጽሑፍ ውስጥ ሥራው በተራማጅነት ተፈርጆ ሰፊ መድረክ ሲሰጠው፣ ተራማጁ የተማሪው ማህበር ለምን ስለአቤ ምንም ሳይል አለፈ? አቤ የተማሪው ማህበር የቆመለተን ዓለማ ሙሉ-በሙሉ ያሟላ ብዕረኛ ነው፡፡ የዘውድን ሥርዓት በብዕሩ በጽናት ተፋልሟል፡፡ ለዚህም ድፍረቱ ተግዞ ታስሯል፡፡ ከዘመኑ ብዕረኞች መካከል እንደ አቤ የዘውድ ስርዓትን በብዕሩ በግልጽ የሞገተ ደራሲ እንኳን ያኔ፣ አሁንም ያለ አይመስለኝም፡፡ ታዲያ፣ ጉዳዩ ይህ ሆኖ ሳለ፣ በዓላማ የተሳሰረውን ህዝባዊ ደራሲ፣ ተራማጁ የተማሪዎች ማህበር ለምን ስሙን ሊያገነው አልቻለም? እውን “አልወለድም”ን ባያነብ ነው? ሠይፈ ነበልባልን አንብቦ ባይገባው ነው? ቢያንስ “አንድ ለእናቱ” ብቻውን የአቤን ስም ማግነን ይሳነዋል? የዳኛቸው ወርቁን ብቸኛ ልብወለድ “አደፍርስ”ን በየጥናት ክበባት ያስነበበን የተማሪ ማህበር፣ ለምን ከአቤ ስራዎች አንዱን እንድንወያይበት አላደረገም? የአቤስ የፈጠራ ስራዎች ፀረ-ፊውዳል ድርሰቶች አይደሉም የሚል ምሁር ከመካከላችን ይኖራል? ታዲያ ፀረ-ፊውዳል ታጋዩና የመሬት ላራሹ መፈክር አንጋቢው ተራማጁ የተማሪዎች ማህበር ይህን ህዝባዊ ደራሲ ሳያጎላው ያለፈው ሆን ብሎ ይሆን ወይስ ረስቶት? መልሱን ባውቀውም አልነግራችሁም፡፡ እናንተም እንድትነግሩኝ አልፈልግም፡፡ ለምን ብትሉ መላምት እንጅ ጥናትና ምርምር አይደለምና፡፡
3. አቤና ደርግ
“ሶሽያሊስት ነኝ” ያለው የደርግ መንግሥት ሶሽያሊስት አመለካከት ላላቸው የጥበብ ሰዎች ወዳጅ አልነበረም፡፡ ማርክስ ለማለት ማርቆስ የሚሉትን የደርግ አባላት ያስተካከሏቸው ደብተራቸውን ወርውረው፣ ትምህርታቸውን ጥለው ለዘመናት የታገሉለት አብዮት በእርግጥ የፈነዳ መስሏቸው አገር ቤት የገቡት፣ የተማሪውን ማህበር ሲያንቀሳቅሱ የኖሩት እውነተኛ ተራማጆ ናቸው፡፡ እነዚህም ወጣት ተራማጆች በወጉ ሳይደራጁ አገር ቤት ገብተው ደርግ እርስ-በእርስ ያጨፋጨፋቸውና የተረፉትን እራሱ አርዶ አስፋልት ላይ ያሰጣቸው ናቸው፡፡ በአጭሩ ኮትኩተው-አሰልጥነው፣ መግበው ያሳደጉት ውሻ የበላቸው የዋህ ታጋዮች ናቸው፡፡
ወደ አቤ ስመጣ፣ ደርግ በአብዮት ስም የተረከባት አገር እነአቤ ቀደም ብለው በህዝባዊ ብዕራቸው ያደነቋት፣ የዘመሩላት፣ የተጋዙላት ኢትዮጵያ ናት፡፡ እጅግ በርካታ ህዝቦች አንድ-አንድ ጡብ እየጨመሩ በገነቡት ቤት ላይ ደርግ የመጨረሻዋን ጡብ እንኳ ሳያሰቀምጥ የቤቱ ባለቤት እኔ ነኝ አለ፡፡ በእርግጥም ደርግ ምንም አይነት ጡብ በዚህ የቤት ሥራ ላይ አላኖረም፡፡ በአንፃሩ ግን ደርግ በዘውድ ሥርዐት ታማኝነቱ፣ በአጣና ደብዳቢነቱ፣ በግድያ ፈፃሚነቱ፣ ሕንፃ ገንቢ የሆኑ ተማሪዎችን፣ ምሁራንን በአጠቃላይ ምስኪን ገበሬዎችን አሳዶ ይገድል፣ ህዝባዊ የፈጠራ ሰዎችን ያስር፣ ከግዞት እንዳይወጡ በር ዘግቶ ይጠብቅ የነበረ ዋርድያ ነው፡፡ ይህ ዋርድያ የአገሪቱን ስልጣን ከተረከበበት ቀን ጀምሮ በአፉ ሶሻሊዝም እየሰበከ፣ በተግባር ሶሽያሊስት አመለካከት የነበራቸውን የጥበብ ሰዎች ከኢምፔሪያሊዝም ጋር ደምሮ የጎሪጥ ያያቸው ጀመር፡፡ እንደ አቤ ባይበረታባቸውም መንግስቱ ለማና ሌሎችም የደርግ ጥላቻ ዒላማ ነበሩ፡፡
የአቤ ድርሰቶች ለደርግ የተዋጡለት አይመስልም። ለስልጣን ወይም ለገንዘብ የማይንበረከከው አቤ፤ ከጊዜ በኋላ ብዕሩን ወደ ደርግ እንደሚያዞርበት ገብቶታል፡፡ ደርግ የጀመረውን ትውልድ የማጥፋት ዘመቻውን አቤ ዐይቶ እንዳላየ፣ ሰምቶ እንዳልሰማ ሆኖ በፀጋ የሚቀበለው አይሆንም። በዚህም መሰረት አቤን ከአካባቢው አርቆታል፡፡ የ“አልዋለድም” ደራሲ ጭራሮ-እንጨት ሆኖ ያቀጣጠለውን የአብዮት እሳት ቀርቦ እንዳይሞቅ አግዶታል፡፡ ምንም ዐይነት አስተዋጽኦ እንዳላደረገ ሆን ብሎ ወደ ጎን ገፍቶታል። ዛሬም እንደ ትላንቱ አቤ ከሁሉም የተገለለ ብቸኛ ደራሲ ሆኗል፡፡ ዛሬም እንደ ትላንቱ በጃንዳርም ሰላዮች የሚጠበቅ የብዕር ሰው ተብሏል፡፡ ከአቤ ጋር ቆሞ መታየት ሳይቀር ቀይ ሽብርን የሚጋብዝ አስፈሪ ጉዳይ ሆኗል፡፡ የእሱን ብዕር ምርኳዝ አድርገው ሥልጣን ላይ የወጡ ደርጎች ለምን የአቤ ስም እንዲቀበር ፈለጉ? በእርግጥም አቤ በወቅቱ የደርግ ስጋት ነበረ? አዎ! ነበረ፡፡ ምንአልባት በወቅቱ የፈለቁት ሕቡዕ ድርጅቶች መልምለውት ይሆን? ጨርሶ አልተጠጉትም፡፡ አቤ ከእነሱ ሁሉ ባላይ አርቆ የሚያስብ ታጋይ ብዕረኛ ነበር፡፡ አሁን አጠገቤ ቢሆን ኖሮ “ማንም ተልካሻ በተጠራበት ስም ታጋይ፣ ተራማጅ፣ አትበለኝ” ብሎ ይገስፀኝ ነበር፡፡ አቤ ያኔ! ወደ አንዱ ጎራ ጠባ ቢልማ ኑሮውና ቀብሩም የውሻ ባልሆነ ነበር፡፡
የተፋለመለትን ህዝብ አምኖ ለህዝብ መብትና ፍትህ እየጮኸ፣ የተጋዘለት ህዝብ ግን ሳይደርስለት ደሙ-ደመ ከልብ ሆኖ ቀረ፡፡
እና! በፈጣሪ ተሰይሞም ሆነ ጠበንጃ አንግቦ ሥልጣን ላይ የወጣ ሹም ሁሉ ለምን አቤን ጠላው? ለምን አሳደደው? ለምን ሊቀበር የማይችለውን ስሙን ለመቅበር ሞከረ? መልሱን እኔም አልነግራችሁም … እናንተም እንድትመልሱልኝ አልፈልግም፡፡ ጥያቄ?

Saturday, 08 March 2014 13:00

የቀልድ - ጥግ

ትርጓሜ
ጉባዔ፡- ጉባዔ ማለት ታዋቂ ሰዎች ለየብቻቸው ሊሠሩት የማይችሉትን ነገር አንድ ላይ ሆነው በቃ ምንም ሊሠራ አይቻልም ብለው ተስማምተው የሚወስኑበት ስብሰባ ነው፡፡
*   *   *
አንድ ታላቅ ባለሥልጣን ጉባዔን ሲገልፁት፤ “ጉባዔ ማለት የአንድ ሰው መደናበር በተሰብሳቢው ቁጥር ሲባዛ የሚገኝ የስብስብ ብዛት ነው!”
*   *   *
የ25ኛ ዓመት የጋብቻ ቀኑን የሚያከብር አንድ ባል በጣም ተደብሮ ያየው ጓደኛው ሊያፅናናው እየሞከረ ሲያባብለው፤ ባልዬው ብስጭቱን ሲገልፅ እንዲህ አለ፡-
“በ5ኛው የጋብቻ በዓላችን ጊዜ ሚስቴን ልገድላት አስቤ ጠበቃዬን ባማክረው “20 ዓመት ያስፈድርብሃል ተው” ብሎኝ ተውኩ፡፡ እስቲ አስበው ወዳጄ! ይሄኔኮ ከእሥር ቤት ወጥቼ ነበር!”
*    *   *
ዳኛ (ለተከሳሹ)፡- “በአራት አመት ጥብቅ እሥራትና ከአገር እንድትባረር ተፈርዶብሃል፡፡ የምትለው ነገር አለህ?”
ተከሳሹ፡- “ጌታዬ ሁለተኛው ውሳኔ መጀመሪያ ይሁንልኝ!”
*   *   *
ዳኛ፡- “ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ከማስተላለፉ በፊት የምታቀርበው ነገር አለ?”
እሥረኛ፡- “ኧረ ምንም የለኝ ጌታዬ! 50 ብር ነበረኝ ጠበቃዬ ወሰደው”
*   *   *
ሴትዮዋ አዋቂ ዘንድ ሄዳ ዕጣ-ፈንታዬን ንገረኝ ትለዋለች፡፡
አዋቂ፡- (መዳፏን እያየላት) አንድ ረዥም ጥቁር ሰውዬ መጥቶ ሲያሳልፍሽ ይታየኛል፡፡”
ሴትዬዋ፡- “ምን ምን ያደርግልኛል ጌታዬ?”
አዋቂ፡- “ስጦታ በስጦታ ያደርግሻል፡፡ ናይት ክለብ ወስዶ አለምሽን ያሳይሻል፡፡ ፍቅር ለዘለዓለም ይኑር! ብለሽ ዋንጫሽን ታነሺለታለሽ”
ሴትዬዋ፡- “ጥቁሩ ሰውዬ ብዙ ገንዘብ አለው ጌታዬ?” አለች ሴትዮዋ ፍንክንክ እያለች፡፡”  
አዋቂ፡- “ምን ነካሽ? ሰውዬውኮ የአንድ ትልቅ ኩባንያ ፕሬዚዳንት ነው፡፡ ከእናት አባቱ 900,000 ብር የሚከራይ አፓርትማ ወርሷል”
ሴትዮዋ፡- “ታድዬ! እንዴት ያለ ፀጋ ፈሰሰልኝ ጌታዬ! አንድ ነገር ብቻ እንድጠይቅዎ ይፍቀዱልኝ ጌታዬ?”
አዋቂ፡- “ጠይቂኝ!”
ሴትዮዋ፡- “ባሌንና ሶስቱን ልጆቼን የት አረጋቸዋለሁ? ምን ይውጣቸዋል?”