
Administrator
አለማቀፉ የጉዲፈቻ ተቋም በሙስናና በማጭበርበር ሕፃናትን ከኢትዮጵያ ወደ አሜሪካ መውሰዱን ኃላፊው አመኑ
ለክልል ባለስልጣንና ለአንድ የስራ ሃላፊ ገንዘብና ውድ ስጦታ ሰጥቻለሁ ብለዋል
ተቀማጭነቱን በአሜሪካ ያደረገው ‘ኢንተርናሽናል አዶፕሽን ጋይድስ’ የተባለ አለማቀፍ የጉዲፈቻ ተቋም የውጭ ፕሮግራም ክፍል ሃላፊ በመሆን ለረጅም አመታት ያገለገሉት አሊያስ ቢቬንስ፣ ተቋሙ በሙስናና በማጭበርበር ኢትዮጵያውያን ህጻናትን በጉዲፈቻ ወደ አሜሪካ ይወስድ እንደነበር በሳውዝ ካሮሊና የፌደራል ፍርድ ቤት ቀርበው ቃላቸውን እንደሰጡ አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘገበ፡፡
የአሜሪካ መንግስት የፍትህ ተቋም ባለፈው ረቡዕ ያወጣውን መግለጫ የጠቀሰው ዘገባው፣ የስራ ሃላፊው እ.ኤ.አ ከ2006 እስከ 2009 በነበሩት አመታት ኢትዮጵያውያን ህጻናትን በህገወጥ መንገድ ወደ አሜሪካ ለመውሰድ ሲሉ ጉዳዩ ለሚመለከታቸው የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናትና የስራ ሃላፊዎች ጉቦ መስጠታቸውን እንዲሁም ለአሜሪካ መንግስት ሐሰተኛ የጉዲፈቻ ሠነድ በማቅረብ የማጭበርብር ድርጊት ሲፈጽሙ እንደቆዩ ማመናቸውን ጠቁሟል።
የ42 አመቷ አሊያንስ ቢቬንስ ከሌሎች አሜሪካውያንና ኢትዮጵያውያን ግብረ አበሮቻቸው ጋር በመመሳጠር ከኢትዮጵያ የወላጅ አልባ ህጻናት ማሳደጊያዎች ጋር ተፈራርመናቸዋል ያሉትን የተጭበረበሩ የጉዲፈቻ ስምምነቶችና ተያያዥ ሃሰተኛ ሰነዶች ለአሜሪካ መንግስት መስጠታቸውን እንዳመኑ የጠቆመው ዘገባው፣ በዚህ መልኩ በህገወጥ መንገድ ወደ አሜሪካ እንዲገቡ ከተደረጉት ኢትዮጵያውያን መካከል የተወሰኑት፣ ከተቋሙ ጋር የጉዲፈቻ ስምምነት አድርገዋል በተባሉት የወላጅ አልባ ህጻናት ማሳደጊያዎች ውስጥ ያልተመዘገቡና ተገቢው እንክብካቤ ያልተደረገላቸው መሆናቸው እንደተረጋገጠም አመልክቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በኢትዮጵያ ጉዳዩ የሚመለከታቸውን የመንግስት ባለስልጣንና የስራ ሃላፊ የድርጊቱ ተሳታፊ እንዲሆኑ በማሳመን እንዲሁም በጥቅማጥቅሞች ደልለው ወደ አሜሪካ በመውሰድ፣ የህጻናቱ የቪዛ ጉዳይ በቀላሉ እንዲያልቅና ጉዲፈቻውን በማጭበርበር ለማሳካት እንዲዲያግዟቸው ማድረጋቸውንም አምነዋል ብሏል- የአሶሼትድ ፕሬስ ዘገባ፡፡ የድርጊቱ ተባባሪ ከሆኑት ኢትዮጵያውያን መካከል በመንግስት ትምህርት ቤት ተቀጥረው የሚሰሩ ግለሰብ እንደሚገኙበት ለሳውዝ ካሮሊና ፍርድ ቤት የተናገሩት ቢቬንስ ፣ ግለሰቡ በአሜሪካ ለሚገኙ የጉዲፈቻ አሳዳጊዎች የህጻናቱን የጤናና ማህበራዊ ሁኔታ የሚገልጽ መረጃ በመስጠት ላደረጉት አስተዋጽኦ ከተቋሙ ገንዘብ እንደተከፈላቸውና ውድ ስጦታዎች እንደተበረከቱላቸው ተናግረዋል፡፡
የክልል የሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ቢሮ ሃላፊ እንደሆኑ የተነገረላቸው ሌላው የድርጊቱ ተባባሪም፣ ስልጣናቸውን በመጠቀም ተቋሙ በአገራት መካከል የሚያከናውናቸው የጉዲፈቻ ስራ ማመልከቻዎች በኢትዮጵያ ተቀባይነት እንዲያገኙና ህገወጥ ተልዕኮውን እንዲያሳካ በማገዛቸው፣ ሙሉ ወጪያቸው ተሸፍኖላቸው የውጪ አገራት ጉዞ ከማድረጋቸውም በላይ ጠቀም ያለ ገንዘብ እንደተሰጣቸውም ሃላፊው ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡
የቢቬንስን ጉዳይ ሲመለከት የቆየው የሳውዝ ካሮሊና ፍርድ ቤት፣ከጥቂት ቀናት በኋላ በተከሳሹ ላይ ተገቢውን ቅጣት ይጥልባቸዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የመካከለኛው ምስራቅ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ከ21 ቢ. ብር በላይ ያንቀሳቅሳሉ
የመካከለኛው ምስራቅ አገራት ኩባንዎች በኢትዮጵያ ከ21 ቢሊዮን ብር በላይ የሚያንቀሳቅሱ የተለያዩ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች እንዳላቸው ወርልድ ቡሊቲን ዘገበ፡፡
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኤጀንሲ ያወጣውን መረጃ በመጥቀስ ዘገባው እንዳለው፣ ኩባንያዎቹ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች 179 ያህል የምርት፣ የግብርና፣ የሪል እስቴትና የማሽነሪ ኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶችን እያንቀሳቀሱ ይገኛሉ፡፡ 80 የሚደርሱ ፕሮጀክቶች የአገሪቱ መንግስት ትኩረት በሰጠው የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ውስጥ እንደሚገኙ ሲታወቅ 35 ያህሉ ደግሞ ለዘርፉ ግብዓት በሚያመነጨው የግብርናው ዘርፍ እንደተካተቱ ዘገባው አመልክቷል፡፡
በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ከተሰማሩት የመካከለኛው ምስራቅ አገራት ቀዳሚውን ስፍራ የምትይዘው ሳኡዲ አረቢያ ስትሆን አገሪቱ በኢትዮጵያ 86 ፕሮጀክቶችን እያከናወነች እንደምትገኝ ዘገባው ጠቁሞ፤ ከመካከለኛው ምስራቅ አገራት በተጨማሪ ሱዳን፣ ግብጽ፣ ደቡብ አፍሪካና ናይጀሪያን የመሳሰሉ የአፍሪካ አገራትም በተለያዩ ኢንቨስትመንቶች ላይ ተሰማርተው እንደሚገኙ አመልክቷል፡፡
የጸጉር ጤና እንክብካቤና ፋሽን በአፍሪካ የቢሊዮኖች ዶላር ቢዝነስ ሆኗል
በደ/አፍሪካ ብቻ አምና ከ20 ቢ. ብር በላይ የሚያወጡ መዋቢያዎች ተሸጠዋል የአህጉሪቱ “የተፈጥሮ ጸጉር” አመታዊ ሽያጭ ከ120 ቢ. ብር በላይ ደርሷል
የጸጉር ጤንነት እንክብካቤና የፋሽን ስራ በአፍሪካ ብዙ ቢሊዮን ዶላሮችን የሚያንቀሳቅስ ትልቅ ንግድ እየሆነ መምጣቱን ሮይተርስ ከትናንት በስቲያ ዘግቧል፡፡ በአህጉሪቷ እየተስፋፋ የመጣው የጸጉር ጤንነት እንክብካቤና የፋሽን ስራ የህንድና የቻይናን ኩባንያዎች ከማሳተፍ ባለፈ በአለማቀፍ ደረጃ ታዋቂ የሆኑትን “ሎሬል” እና “ዩኒሊቨር” የመሳሰሉ የፋሽንና የውበት ኩባንያዎች ወደ አህጉሪቷ እንዲገቡ ማድረጉን ነው ዘገባው የገለጸው፡፡ የአፍሪካ ሴቶች የጸጉራቸውን ጤንነት የመጠበቅና የዘመኑን አለማቀፍ የጸጉር ፋሽን የመከተል ፍላጎታቸው እያደገ መምጣቱን ተከትሎ፣ በአህጉሪቱ የተለያዩ አገሮች በመስኩ የሚሰሩ አገር በቀል ድርጅቶች እየተበራከቱ የመጡ ሲሆን እነ “ኦግሎብ”ን የመሳሰሉ ታዋቂ አለማቀፍ ኩባንያዎችም በአህጉሪቱ በስፋት መንቀሳቀስ ጀምረዋል፡፡
ዩሮ ሞኒተር ኢንተርናሽናል የተባለ አለማቀፍ የገበያ ጥናት ተቋም ያወጣው የጥናት መረጃ እንደሚለው፤ ባለፈው የፈረንጆች አመት በደቡብ አፍሪካ ብቻ 1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ የጸጉር ውበት መጠበቂያና መዋቢያ ሻምፖዎች፣ ሎሽኖችና ማለስለሻዎች ለገበያ ቀርበው ጥቅም ላይ ውለዋል፡፡በናይጀሪያና በካሜሩን የፈሳሽ የጸጉር ቅባቶችና ውበት መጠበቂያዎች ገበያ ከአመት ወደ አመት እያደገ መምጣቱን የጠቆመው ዘገባው፤ በመላ አህጉሪቱ ያለው አመታዊ የተፈጥሮ ጸጉር ሽያጭም 6 ቢሊዮን ዶላር መድረሱን አስታውቋል፡፡
ታዋቂዋ ናይጀሪያዊት ድምጻዊት ሙማ ጊ በቅርቡ ከ56 ሺህ ብር በላይ ወጪ በማድረግ አንድ የተፈጥሮ ጸጉር ከነመዋቢያው እንደገዛች ብዙሃን በይፋ መናገሯን በዋቢነት የጠቀሰው ዘገባው፤ በደቡብ አፍሪካ ብቻ ከ100 በላይ የተለያዩ አይነት የንግድ ምልክቶች ያሏቸው የተፈጥሮ ጸጉር አይነቶች በገበያ ላይ እንደሚገኙና አመታዊ ሽያጩም 600 ሚሊዮን ዶላር መድረሱን አስታውሷል፡፡ በመላ አፍሪካ እያደገ የመጣው የጸጉር ጤንነት እንክብካቤና የፋሽን ስራ በተለያዩ አገራት ለሚገኙ ቁጥራቸው በርካታ የሆነ ሴቶች ከፍተኛ የስራ ዕድል መፍጠሩንና በኢኮኖሚው ውስጥ የራሱን ድርሻ እያበረከተ እንደሚገኝ የጠቆመው ዘገባው፣ በናይጀሪያና በአንዳንድ አገራት የቤት ለቤት አገልግሎት መስጠት የሚያስችል አሰራር መጀመሩን ገልጧል፡፡
የፍቅር ጥግ
ፍቅር እንደ ቫይረስ ነው፤ ማንም ሰው ላይ በማንኛውም ሰዓት ሊከሰት ይችላል፡፡
ማያ አንጄሎ
ወንዶችን ካልወደድሻቸው እላይሽ ላይ ይሰፍሩብሻል፤ የወደድሻቸው ስትመስያቸው ግን ከመቅፅበት ፊታቸውን ያዞሩብሻል፡፡
ቢዮንሴ ኖውሌስ
ፈፅሞ አፍቅራ የማታውቅ ሴት ጨርሶ ኖረች ልትባል አትችልም፡፡
ጆን ጌይ
(እንግሊዛዊ ገጣሚና ፀሃፌ ተውኔት)
ለፍቅር መድሃኒቱ የበለጠ ማፍቀር ብቻ ነው፡፡
ሔነሪ ብሮሜል
ምንጊዜም በፍቅር ውስጥ ጥቂት እብደት አይጠፋም፤ በእብደት ውስጥ ግን ሁልጊዜም ጥቂት ምክንያት ይኖራል፡፡
ዩሪፒደስ
የምናፈቅረው እንከን የለሽ ሰው ፈልገን አይደለም፡፡ እንከን ያለበትን ሰው እንከን አልባ አድርጎ መመልከትን በመለማመድ ነው፡፡
ሳም ኪን
(To Love and Be Loved)
ማፍቀር ከረዥም ህንፃ ላይ እንደ መዝለል ነው። አዕምሮህ የሚያዋጣ ሃሳብ እንዳልሆነ ይነግርሃል፤ ልብህ ግን መብረር እንደምትችል ሹክ ይልሃል፡፡
ማፍቀርና መፈቀር ፀሃይን ከሁለቱም ወገን ማግኘት ነው፡፡
ዴቪድ ፎስተር
ህፃናት ለእግዚአብሔር የፃፏቸው ደብዳቤዎች
ውድ እግዚአብሔር፡-
እንስሳትም ግንኙነታቸው ከአንተ ጋር ነው ወይስ የራሳቸው እግዚአብሔር ሰጥተሃቸዋል?
ናንሲ፤ የ5 ዓመት ህፃን
ውድ እግዚአብሔር፡-
እግዚአብሔር መሆንህን እንዴት አወቅህ?
ሳሚ፤ የ6 ዓመት ህፃን
ውድ እግዚአብሔር፡-
የተለያዩ ሃይማኖቶች መፍጠርህ ደስ ይላል፡፡ አንዳንዴ ግን አይደባለቅብህም?
አርኖልድ፤ የ6 ዓመት ህፃን
ውድ እግዚአብሔር፡-
ህፃናቶች ከየት ነው የሚመጡት? ማሚ ሆድ ውስጥ ማን ነው የሚከታቸው? ከዚያ በፊት አንተ ጋ ነው የሚኖሩት? ሁሉንም መልስልኝ እሺ፡፡ እወድሃለሁ፡፡
ሱዛን፤ የ6 ዓመት ህፃን
ውድ እግዚአብሔር፡-
አዳዲስ እንስሳት መፍጠር የተውከው ለምንድን ነው? እኛ እኮ የድሮ እንስሳት ብቻ ነው ያሉን፡፡
ጆኒ፤ የ5 ዓመት ህፃን
ውድ እግዚአብሔር፡-
ወንድሜ ሁሌ አይጥ ነኝ እያለ ይቀልዳል፡፡ ለምን ጅራት አትሰጠውም?
ጆዲት፤ የ6 ዓመት ህፃን
ውድ እግዚአብሔር፡-
ማታ ማታ ኮከቦቹን በትክክል ስለምትደረድራቸው ታስደስተኛለህ፡፡
ጄፍ፤ የ5 ዓመት ህፃን
ከክትባት በኋላ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ክስተቶች
ክትባቶች በተመጣጣኝ ዋጋ የህፃናትንና እናቶችን ህይወት ከበሽታ ለመከላከል የሚጠቅሙ ወሳኝ የበሽታ መከላከያ ዘርፍ ናቸው። ከክትባቶች ግኝት በኋላ በዓለም አቀፍ ደረጃ በክትባት መከላከል የምንችላቸው በሽታዎች ስርጭትና ስፋት እጅጉን ቀንሷል። ክትባት የሚሰጠው ጤነኛ በሆኑ ሰዎች ላይ በክትባት መከላከል የምንችላቸውን በሽታዎች ለመከላከል ስለሆነ ጥራቱ እና ደህንነቱ መረጋገጥ አለበት፡፡ ክትባት በሚሰጥበት ወቅት ቀላል የሆኑ ክስተቶች ለምሳሌ ትኩሳት፣ መርፌ የተወጋበት ቦታ የማበጥ ምልክቶች ሊታዩ ይችላሉ፡፡ ብዙ ጊዜ ባይሆንም ከፍተኛ የጐንዮሽ ጉዳት እንደ አለርጂ፣ እራስን የመሳት ችግሮችንም ሊያስከትል ይችላል። በመሆኑም ከክትባት በኋላ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ክስተቶችን መጠንና ጉዳት ለመቀነስ በክትባቶች ምክንያት ስለሚመጡት ጉዳቶች መገንዘብና ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ ወሳኝ ሚና አለው፡፡
ከክትባት በኋላ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ክስተቶች ምንድን ናቸው?
ከክትባት በኋላ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ክስተቶች ማለት ማንኛውም ከክትባት በኋላ የሚከሰት የጤና ችግር፣ የሚያሰጋ እና በክትባት ምክንያት እንደተከሰተ የሚታመን ወይም የሚገመት የጤና ችግር ማለት ነው። ይህ ማለት እውነተኛ በክትባት ምክንያት የመጡ የክትባት ችግሮች ወይም በአጋጣሚ በዚያን ወቅት የሚከሰቱ ሌላ የጤና ችግሮች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በዚህም መሰረት ለመከላከልና ለመቆጣጠር እንዲያመቸን ክስተቶቹን በመከፋፈል እናያቸዋለን፡፡
በክትባት ምክንያት የሚከሰቱ የጐንዮሽ ጉዳቶች
የክትባቶች ዋነኛ ጥቅም በሰውነት ውስጥ በሽታ የመከላከል አቅምን ማጐልበት ነው፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ ለሰውነት ባእድ የሆኑ ንጥረ ነገሮች ወደ ሰውነት ስለሚገቡ ሰውነትም በአንፃሩ ለባእድ ነገሩ ምላሽ ወይም መከላከያ ለመስጠት በሚዘጋጅበት ወቅት የተለያዩ ምልክቶች ሊከሰቱ ይችላሉ፡፡ እነዚህ ክስተቶች የክትባት መድኃኒቱ ተፈጥሮአዊ ይዘት፣ ተጨማሪ ንጥረ ነገር እና የክትባት መድኃኒት እንዳይበላሽ ወይም ለረዥም ጊዜ እንዲቆይ የሚያደርጉት ኬሚካሎች የተነሳ የሚመጡ ናቸው። እነዚህም - ትኩሳት፣ እብጠት፣ መርፌ የተወጋበት ቦታ መቅላት፣ መነጫነጭ፣ የምግብ ፍላጐት መቀነስ፣ ህመም እና ሌሎችም ሊከሰቱ ይችላሉ፡፡ እነዚህ የጐንዮሽ ጉዳቶች አብዛኛውን ጊዜ የሚከሰቱት ክትባቱ በተሰጠበት ቀንና በሁለተኛው ቀን ነው፤ አንዳንድ ጊዜ እስከ ጥቂት ቀናት ድረስ ሊቆዩ ይችላሉ፡፡
የፕሮግራም ስህተቶች
የፕሮግራም ስህተት የምንላቸው በክትባት አያያዝ፣ አቀማመጥ፣ ዝግጅትና አሰጣጥ ሂደት ውስጥ የሚከሰቱ ስህተቶችና አደጋዎች ናቸው። በፕሮግራም ስህተት የሚፈጠሩ ክስተቶች በብዛት በአንድ ቦታ ሊከሰት የሚችል ነው። ይህም በተወሰነ ባለሙያ፣ ጤና ተቋም ወይም የክትባት ብልቃጥ ጋር የተያያዘ ሊሆን ይችላል። በፕሮግራም ስህተት ምክንያት ከሚፈጠሩ ክስተቶች መካከል ዋነኛው ብክለት (infection) ንፅህናው ባልተጠበቀ መርፌ ምክንያት የሚከሰት ነው። ይህም መግል የያዘ እብጠት፣ ለደም ብክለት (sepsis), በደም ንክኪ ምክንያት ለሚተላለፉ በሽታዎች (ኤችአይቪ እና የጉበት ቫይረሶች) የሚያጋልጥ ይሆናል፡፡ እነዚህ ስህተቶች በሚከሰቱበት ወቅት በባክቴሪያ ብክለት ምክንያት ከሆነ ምልክቶቹ በሰዓታት ውስጥ የሚታዩ ሲሆኑ እነዚህም ምልክቶች፣ መርፌ የተወጋበት ቦታ ሲነካ የህመም ስሜት፣ ትውከት፣ ተቅማጥና ከፍተኛ የሰውነት ትኩሳት ናቸው፡፡
በአጋጣሚ (ከክትባቱ ውጪ) የሚፈጠሩ ክስተቶች
እነዚህ ክስተቶች በጊዜ አጋጣሚ ከክትባቱ ጋር የሚከሰቱና በስህተት ከክትባት ጋር የሚያያዙ ናቸው። ይህም ማለት ክስተቱ በአጋጣሚ ክትባቱ በተሰጠበት ወቅት ይፈጠር እንጂ በክትባቱ ምክንያት የተከሰተ ስላልሆነ ክትባቱ ባይሰጥም መከሰቱ የማይቀር ነው። በዚህም ምክንያት የተለያዩ ክስተቶች ሞትንም ጨምሮ በክትባት ምክንያት እንደተፈጠረ ተደርጐ ሊወሰድ ይችላል፡፡ ሆኖም ግን ክስተቱ በጊዜ አጋጣሚ የሚፈጠር በመሆኑ ጥልቅ ምርመራ ሊደረግበት ይገባል፡፡
መርፌ በመወጋት ምክንያት የሚፈጠሩ ክስተቶች
የተለያዩ ሰዎች ወይም ግለሰቦች መርፌ ለመወጋት ሲሉም ሆነ ከተወጉ በኋላ በፍርሃት ምክንያት የሚፈጠርባቸው ክስተቶች አሉ፡፡ ከነዚህም መካከል አንዱ እራስን መሳት ነው፡፡ ይህ ክስተት ከክትባት ይዘቱ ጋር የሚገናኝ አይደለም፡፡ ይህም በብዛት የሚከሰተው ከአምስት አመት በላይ በሆኑ ህጻናት ላይ ነው፡፡
ከክትባት በኋላ የሚያጋጥሙ ክስተቶች መከላከያና መቆጣጠሪያ መንገዶች
ሀ. በጤና ባለሙያዎች
ለክትባት መድኃኒቱ አለርጂ ያላቸውን ቀድመው መለየት፣
ለህፃናት ወላጆችና አሳዳጊዎች ስለ ክትባቱ ባህሪ ማስተማርና መምከር እንዲሁም የትኞቹ ምልክቶች ሲከሰቱ ወደ ጤና ተቋም መምጣት እንዳለባቸው ማስገንዘብ፣
በፕሮግራም ስህተት ምክንያት የሚፈጠሩ ክስተቶችን መለየትና ማስተካከያ እርምጃ መውሰድ፣
በክትባት ብልቃጥ ብክለት የተከሰተ ከሆነ ለባክቴሪያ ምርመራ ወደሚመለከታቸው አካላት መላክ፣
የሚበጠበጡ ክትባቶችን በአምራቹ ምርት ብቻ መበጥበጥ እንዲሁም ከተበጠበጡ ከስድስት ሰዓት በኋላ ጥቅም ላይ እንዳይውል ማድረግ፣
ክትባቶች የሚቀመጡበት ማቀዝቀዣ ፍሪጅ ውስጥ ሌላ መድኃኒት አለማስቀመጥ፣
ለክትባት ተብለው የሚዘጋጁ መመሪያዎችን በደንብ መገንዘብና ተግባር ላይ ማዋል፣
ተገቢውን የክትባት ትምህርት እና ክህሎት ስልጠና መውሰድ፣
ከክትባት በኋላ የሚከሰቱ ክስተቶች ሲፈጠሩ ወዲያውኑ ለሚመለከተው ተቆጣጣሪ አካል ሪፖርት ማድረግ እንዲሁም ምርመራ በማድረግ የማስተካከያ እርምጃ መውሰድ፣
ለ. በህፃናት ወላጆችና አሳዳጊዎች
በጤና ባለሙያዎች የሚሰጠውን ምክርና ትምህርት መከታተልና መተግበር፣
ድንገተኛ እና ያልታሰበ ምልክት ሲያዩ በአፋጣኝ ወደ ጤና ተቋም መውሰድ፣
ለህፃናት የሚሰጠውን የክትባት ምንነት፣ የሚከላከለው የበሽታ አይነት፣ ሊያጋጥሙ የሚችሉ የጎንዮሽ ጉዳቶችንና መደረግ ያለበትን ጥንቃቄ ከጤና ባለሙያዎች መጠየቅ፣
ምንጭ፡-
የዓለም ጤና ድርጅት ከክትባት በኋላ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ክስተቶ ቅኝት መመሪያ
ከክትባት በኋላ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ክስተቶች ቅኝት መመሪያ በኢትዮጵያ
WHO-Vaccine Safety Basics Learning Manual
ችግራችን ምንድነው? ከእውነት፣ ከነፃነትና ከህይወት ጋር መጣላታችን!
1.ለ6 ወር የታገደው “ሕገመንግስታዊ መብት”፤ 9 ወር ሞላው - ለአገር ገፅታ ሲባል
- ወደ አረብ አገራት ለስራ መጓዝ ከታገደ ወዲህ ወደ የመን መሰደድ ተባብሷል
- ባለፉት ሶስት ወራት ከ18ሺ በላይ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች የመን ገብተዋል
- አምና በተመሳሳይ ወራት ወደ የመን የተሰደዱት ኢትዮጵያውያን 14ሺ ናቸው
2.በደቡብ ኦሞ በአመት 300 “እርጉም” ሕፃናት ይገደላሉ - ለብሔረሰብ ባህል ሲባል
- በደቡብ ኦሞ ስለ ሐመር ድንቅ ባሕላዊ አኗኗር ምሁራንና ጋዜጠኞች ይነግሩናል
- በባሕላዊ እምነት ሳቢያ የወላድ መካን የሆኑ እናት፤ ባህላችንን እጠላዋለሁ ይላሉ
- የደቡብ ኦሞ ሸለቆ ላይ ያተኮረው የኤንቢሲ የቪዲዮ ዘገባ “የሞት ሸለቆ” ይሰኛል
3.በዋጋ ቁጥጥር የተነሳ የዳቦ ቤቶች ቁጥር እየተመናመነ ነው - ለህዝብ ጥቅም ሲባል
- ለምሳሌ በሙዝ ላይ የተጫነው የዋጋ ቁጥጥር ሲሰረዝ የሙዝ ዋጋ አልጨመረም
- ዳቦ ላይ የዋጋ ተመን ሲታወጅበት፣ የዋጋ ተመን ያልወጣለት አንባሻ ይበራከታል
- የታክሲ እጥረቱንም ተመልከቱ። የዋጋ ተመን በደርግ ጊዜ ለአገሬው አልበጀም
“ለስራ ወደ አረብ አገራት መጓዝ ለ6 ወር ታግዷል” የሚለውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ የሰማን ጊዜ፤ ብዙዎቻችን በግርምት “እኮ እንዴት?” ብለን አልጠየቅንም። እንደዘበት የተነገረንን መግለጫ እንደተራ ጉዳይ አደመጥነው። ይሄውና ዘጠኝ ወር አለፈው። እንግዲህ አስቡት። የሌላ ሰው ኑሮና ንብረት እስካልነካን ድረስ፤ በግል ሕይወታችን ውስጥ ወዲህ ወዲያ ለመንቀሳቀስ፤ መንግስትን የምናስፈቅድበት አንዳችም ምክንያት የለም። ለዚህም ነው፤ በደርግ ዘመን “የመውጫ ቪዛ” በሚል ሲደረግ የነበረው ቁጥጥር ሙሉ ለሙሉ እንዲቀር የተደረገው። በአገር ውስጥ ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስም ሆነ ከአገር ውጭ የመጓዝ መብት፤ “ተፈጥሯዊ የሰው ነፃነት” ነው። ለነገሩማ፤ በሕገመንግስት ውስጥም ከመሰረታዊ ነፃነቶች ተርታ በጥቁርና ነጭ በግልፅ ሰፍሯል።
“ማንኛውም ኢትዮጵያዊ... በፈለገው ጊዜ ከአገር የመውጣት ነፃነት አለው” ይላል - አንቀፅ 32። እንግዲህ፤ ለነፃነት ወይም ለሕገመንግስት ክብር እንሰጣለን የምትሉ ሁሉ ይህንን አስተውሉ።
በፅሁፍ ላይ የሰፈረው አንቀፅ ቀላል አይደለም። መንግስት፤ መሰረታዊ መብቶችን በይፋ ማገድ የሚችለው፤ ለፓርላማ ቀርቦ በሚፀድቅ “የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ” አማካኝነት ብቻ ነው። ለዚያውም ከፓርላማ አባላት መካከል 51 በመቶ ያህሉ ስለደገፉ ብቻ አይፀድቅም፤ ቢያንስ 67 በመቶዎቹ መደገፍ አለባቸው። ለዚያውም ከ6 ወር ላልበለጠ ጊዜ ብቻ ነው እገዳው የሚቆየው። ይህም ብቻ አይደለም። ስርዓት አልበኝነት ካልነገሰ ወይም የውጭ ወረራ ካላጋጠመ በቀር፤ አልያም አደገኛ ወረርሺኝና የተፈጥሮ አደጋ ካልተፈጠረ በቀር፤ መሰረታዊ መብቶችን ለማገድ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማውጣት አይቻልም።
ይሄ ሁሉ የተባለለት መሰረታዊ የሰዎች መብት ነው፤ በአዋጅና በፓርላማ ሳይሆን፤ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ የታገደው። እገዳውን ለማራዘምማ፣ አዋጅ ይቅርና ብጣሽ መግለጫ ማውጣትም አላስፈለገም። ለመሆኑ፤ ተፈጥሯዊውና በሕገመንግስት የሰፈረውን “የመንቀሳቀስ ነፃነት” እንደ ተራ ነገር ያለገደብ ለመጣስ፤ ምን ምን ማመካኛዎች ቀርበዋል? ሁለት ማመካኛዎች ናቸው የቀረቡት። አንደኛ፤ “እናውቅላችኋለን” የሚል። ሁለተኛ ደግሞ፤ “የአገር ገፅታንና ክብርን እናስጠብቃለን” የሚል።
የመጀመሪያውን ማመካኛ እንመልከት። በመቶ ሺ የሚቆጠሩ ወጣት ኢትዮጵያዊያን በየአመቱ የሚሰደዱት፣ “ትክክለኛ መረጃ ስለሌላቸውና የስደትን አደጋ ስለማይገነዘቡ ነው” ሲባል እንሰማለን። ግን፤ ይሄ አባባል ሃሰት ነው። በሃረር በኩል ድንበር ለማቋረጥ ሲጓዙ ከተገኙት 700 ሰዎች መካከል ብዙዎቹ፣ ዘንድሮ ከሳዑዲ አረቢያ የተባረሩ ወጣቶች ናቸው። አደጋውን አያውቁም ልንል ነው?
በእርግጥ፤ የስደት ጉዞው ስንት ቀን እንደሚፈጅ እቅጩን አያውቁ ይሆናል። በጉዞ ላይ የሚገጥማቸው የውሃ ጥም፣ ዝርፊያ፣ እገታ... የቱን ያህል አደገኛ እንደሆነ በቁጥርና በመቶኛ አስልተው ለመግለፅ አይችሉም። ነገር ግን፤ ከሞላ ጎደል ሁሉም ስደተኞች በርካታ ፈተናዎች እንደሚገጥሟቸው ያውቃሉ። እንዲያውም ከሰማኒያ በመቶ በላይ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች፤ ገና ከመነሻው ዋና ዋናዎቹን ፈተናዎች በዝርዝር ጠንቅቀው እንደሚያውቋቸው ዘንድሮ የተካሄደ ሰፊ የጥናት ሪፖርት ይገልፃል። ዩኤንኤችሲአር፣ አይኦሜ እና ሌሎች አለማቀፍ ተቋማት ያቋቋሙት ፅ/ቤት (RMMS) ነው ጥናቱን ያካሄደው። በሰኔ ወር ይፋ የተደረገው የጥናት ሪፖርት ላይ እንደተገለፀው፤ አብዛኞቹ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች በጉዞ ላይና ከዚያ በኋላ የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን በዝርዝር ከማወቅም በተጨማሪ ህይወታቸው ለአደጋ እንደሚዳረግ ይገነዘባሉ።
ስለዚህ፤ “አያውቁም፤ መረጃ የላቸውም” የሚለው ማመካኛ፤ መሰረት የለሽ ውሸት ነው። ደግሞስ፤ የመረጃና የእውቀት ጉድለት ካለባቸው፤ መፍትሄው መረጃ በስፋት ማቅረብና ማሳወቅ እንጂ፤ “አትጓዙም” ብሎ በግድ መከልከልና ነፃነታቸውን መጣስ ምን አመጣው?
ከዚሁ ጋር አብሮ የሚነሳ ሌላ ማመካኛ አለ - በመቶ ሺ የሚቆጠሩ ወጣት ኢትዮጵያዊያን በየአመቱ የሚሰደዱት፣ “በደላሎች ስለሚታለሉ ነው” የሚል። ይሄም፤ መሰረት የለሽ ውሸት ነው። ካልተሰደድክ ብሎ የሚያስገድድ ደላላ የለም። ደግሞም፤ አዲሱን የጥናት ሪፖርት መመልከት ትችላላችሁ። በስደት ወደ የመን ለመጓዝ የወሰኑት በደላሎች አማካኝነት እንደሆነ ከተጠየቁ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች መካከል፤ 98 በመቶ ያህሉ “አይደለም” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል። በደላሎች ውትወታና ማታለያ ለስደት የተነሳሱት ወጣቶች፤ እጅግ ጥቂት ናቸው - ሁለት ከመቶ ብቻ።
እውነታው እንዲህ በግልፅ ቢታወቅም፤ ስለ ስደት በተወራ ቁጥር፣ እንደተለመደው “ስደተኞች መረጃ የላቸውም፤ ተጠያቂዎቹ ደላሎች ናቸው” የሚል ውንጀላ ከየአቅጣጫው እንደሚዥጎደጎድ አያጠራጥርም። ለምን? ለእውነታ ብዙም ክብር የለንም። ለነፃነትም ዋጋ ስለማንሰጥ፤ በመግለጫ ብቻ “የጉዞ እገዳ” እንጥላለን - “እናውቅላችኋለን” ወይም “የአገርን ገፅታ ታበላሻላችሁ” በሚል ማመካኛ።
ነገር ግን፤ በሕጋዊ መንገድ መጓዝ ቢታገድም፣ በዘፈቀደ መሰደድ መች ይቀራል? ባለፉት ሦስት ወራት ውስጥ ከ18ሺ በላይ ኢትዮጵያውያን ወደ የመን ገብተዋል። በዚህ ከቀጠለ፤ በአመት ከ90ሺ በላይ ይሆናል። አደጋውን አስቡት። ከ2000 ዓ.ም ወዲህ፣ ወደ የመን ሲጓዙ ሁለት ሺ ያህል ሰዎች መንገድ ላይ ሞተዋል። በህጋዊ ምዝገባ ወደ አረብ አገራት የሚደረገው ጉዞ ስለታገደ፤ ያለ ቪዛ ወደ የመን የሚሰደዱ ሰዎች ሲበራከቱ በአመት ውስጥ ምን ያህሉ ሊሞቱ እንደሚችሉ አስቡት። በአማካይ ከ40 በላይ የሚሆኑት ኢትዮጵያዊያን በጉዞ ላይ እንደሚሞቱ ልብ ማለት ያስፈልጋል - በአንድ አመት ውስጥ። “አገር” ወይም “የአገር ገፅታ” ለሚባል ጣኦት መስዋእት እያደረግናቸው እንደሆነ አስቡት። በህጋዊ ቪዛ ሲጓዙ ከነበሩት ውስጥ የዚህን ያህል ሰዎች አይሞቱም ነበር።
“እናውቅላችኋለን” ከምንል ይልቅ “አናውቅላችሁም” ብንል ይሻላቸው ነበር። ምክንያቱም፣ በሺ የሚቆጠሩት ወጣቶች ያለ ቪዛ ለመጓዝ የመረጡበትን ምክንያት ሲጠየቁ፤ ህጋዊው ጉዞ በተንዛዛ ቢሮክራሲ ሳቢያ እንቅፋት ስለበዛበት ነው ብለዋል። ዘንድሮ ደግሞ ከነጭራሹ ታግዷል። ምን ይሄ ብቻ! ጭራሽ በድንበር በኩል ከአገር ልትወጡ ስትሞክሩ ተገኝታችኋል ተብለው እዚሁ አገራቸው ውስጥ የሚታሰሩ ወጣቶችን አይተናል። ወንጀላቸው ምንድነው? የትኛውን የወንጀል አንቀፅ ጥሰዋል? ማንን ጎድተዋል? ምንም!
በአጠቃላይ ሲታይ፤ የኛ ችግር፣ የአገራችን ችግር በአጭሩ ሊገለፅ ይችላል - ለእውነታ ዋጋ አንሰጥም። ለነፃነትስ? ለህገመንግስትስ? ለሰው ሕይወትስ? ለሰው ምርጫና ጥረትስ? ለሰብአዊ ክብርስ ዋጋ እንሰጣለን? አንሰጥም። በዚህም ምክንያት፤ “እናውቅላችኋለን” በሚል ወይም “የአገር ገፅታ” በሚሉ ሰበቦች፤ የሰዎች ተፈጥሯዊ ነፃነትና ሕይወት ላይ እንጫወታለን።
“አይ፤ ለእውነታ፣ ለነፃነትና ለሕይወት ክብር እንሰጣለን” የሚሉ ሰዎች እንደሚኖሩ ይገባኛል። “እገዳው ተገቢ ባይሆንም፣ ቢያንስ ቢያንስ በቀጥታ የሰው ሕይወትና ንብረት ላይ ያነጣጠረ የመብት ረገጣ አይደለም” የሚል መከራከሪያም ያቀርቡ ይሆናል። በቀጥታ የሰው ሕይወት ላይ ያነጣጠረ ሲሆንስ ደንታ ይኖረናል?
ኢትዮጵያዊቷ የደቡብ ኦሞ ተወላጅ ቡኮ ባልጉዳ ይመስክሩ።
ሕፃናት ወደ ገደልና ወደ ወንዝ ይወረወራሉ
የ45 ዓመቷ ቡኮ ባልጉዳ የወላድ መካን ናቸው። ልጆቻቸውን በሞት የተነጠቁ እናት። የወለዱትን ህፃናት በአንዳች በሽታ ወይም በአንዳች አደጋ ማጣት ልብን ይሰብራል። በግድያ ሲሆን ግን፣ ለማሰብም ይከብዳል። እንደ ብዙዎቹ የደቡብ ኦሞ ሴቶች፣ ቡኮ ባልጉዳ ልጅ የወለዱ ጊዜ የደስታና የስጋት ስሜት ቢቀላቀልባቸው አይገርምም። የጎሳ መሪዎች መጥተው የህፃኑን አፍ ከፍተው ድዱን ያያሉ። ህፃኑ የመጀመሪያ ጥርሱን በላይኛው ድዱ ካበቀለ፤ ይዘውት ይሄዳሉ - “ሚንጊ” (እርጉም) ነው በሚል። “በጎሳችን ላይ መዓት የሚያመጣ እርጉም!” የተባለው ሕፃን ወደ ገደል፣ ወደ ወንዝ ይወረወራል። ይሄ ባህል ነው። ለዘመናት የዘለቀ ማይሞገት አይነኬ ባህል! “ለጎሳው” እና “ለባህሉ” ሲባል፤ ሰዎች መስዋእት ይሆናሉ።
ቡኮ ባልጉዳ የመጀመሪያ ልጅ ከተገደለባቸው በኋላ እንደገና ወልደዋል። እንደገና “ሚንጊ ነው” በሚል ተገደለ። እንዲህ ሲወልዱና ሲገደልባቸው ነው የኖሩት። በሕይወት ዘመናቸው ስምንት ወንድ ልጆችንና ሰባት ሴት ልጆችን ወልደዋል። 15ቱም ሕፃናት “ሚንጊ ናቸው” ተብለው ተገድለዋል። የወላድ መካን ያደረጋቸውን ባህል እንደሚጠሉት ይናገራሉ - ቡኮ ባልጉዳ። ዴይሊ ሜይል እንዳለው፤ 300ሺ የሕዝብ ቁጥር በያዙት የሃመር እና የባኮ ማሕበረሰብ ውስጥ በየአመቱ 300 ሕፃናት፣ “ሚንጊ ናቸው” ተብለው እንደሚገደሉ ገልፀዋል። ይሄው የሚንጊ ባህል በመላ አገሪቱ የተለመደ ቢሆን ኖሮ፣ በየአመቱ ከመቶ ሺ በላይ ሕፃናት በተገደሉ ነበር።
አሰቃቂ ነው። ግን ስለ አሰቃቂነቱ ሲነገር ሰምተናል? ተፅፎ አንብበናል?
ብዙውን ጊዜ የሚነገረንና የሚፃፍልን፤ ስለ ሐመር ወይም ስለ ደቡብ ኦሞ ድንቅ ባሕል ነው። እንዲያውም ብዙዎቹ ተናጋሪዎችና ፀሃፊዎች፤ በጋራ የተመካከሩና የተስማሙ፤ አልያም የታዘዙ ይመስል፤ ስለ ሚንጊ አይናገሩም፤ አይፅፉም። ግን የትዕዛዝ ወይም የምክክር ጉዳይ አይደለም። ለእውነታ፣ ለነፃነት፣ ለሰው ሕይወት እና ለሰብአዊ ክብር የላቀ ዋጋ ስለማንሰጥ ነው። በየአመቱ 300 ሕፃናት! ባሕልን ወይም ብሔር ብሔረሰብን በማክበር ስም ነው ይሄ ሁሉ የሚደረገው። ለዚያ ለዚያማ፤ በየአመቱ እንደ ቡኮ ባልጉዳ የመሳሰሉ የብሔረሰቡ ተወላጅ የሆኑና ልጆቻቸውን የሚነጠቁ 300 እናቶች እና 300 አባቶችስ? ምሁራን፣ ጋዜጠኞች፣ ፀሐፊዎች ... ለእውነታ፣ ለነፃነት፣ ለሰው ሕይወትና ክብር የማትቆሙ ከሆነ፣ ሥራችሁ ምንድነው? ፓርቲዎችና ፖለቲከኞች ለነፃነትና ለሰው ሕይወት የማትሟገቱ ከሆነ፣ አላማችሁ ምንድነው? እርስበርስ እየተጠላለፋችሁ ስልጣን መያዝ ብቻ!
ከዳቦ ወደ አንባሻ
በ2003 ዓ.ም ከ8 ቢሊዮን ብር በላይ አዳዲስ የገንዘብ ኖቶችን በማሳተም ከፍተኛ የዋጋ ንረት የፈጠረው መንግስት፤ የዋጋ ንረቱን በነጋዴዎች ላይ በማሳበብ የዋጋ ቁጥጥርና የዋጋ ተመን እንዳወጣ ታስታውሳላችሁ። ከመነሻው፤ የገበያ ጠቃሚነቱኮ፣ ሰዎች በፈቃደኝነት የሚያካሂዱት መሆኑ ነው። ለምንድነው መንግስት በሰዎች ንብረት ላይ አዛዥ ናዛዥ የሚሆነው? “ለህዝብ ጥቅም” ሲባል ነዋ። “ለድሃው ጥቅም” ታስቦ ነዋ። ለሰፊው ሕዝብና ለድሃው ሕብረተሰብ ይጠቅማል እስከተባለ ድረስ፤ የሰዎችን ነፃነት መጣስ ይቻላል። አያችሁ? ለነፃነት ያን ያህልም ክብር የለንም። የዋጋ ቁጥጥርና የዋጋ ተመን የታወጀ ጊዜ ተቃውሞ አሰምተናል እንዴ? ብዙዎቻችን ደግፈናል። መንግስት ከጥቂት ወራት በኋላ የዋጋ ተመኑን ለመሰረዝ የወሰነው፣ ኢኮኖሚውን ይብስ እያቃወሰ እንደሆነ በግልፅ መታየት ስለጀመረ ነው። ነገር ግን፤ ሁሉም የዋጋ ተመን አልተሰረዘም - ለምሳሌ የዳቦ።
እንግዲህ አስቡት። የዋጋ ቁጥጥርና ተመን፣ የሰዎችን ነፃነት የሚጋፋ ቢሆንም እንደግፈዋለን - ለነፃነት ዋጋ ስለማንሰጥ። የዋጋ ቁጥጥርና ተመን፣ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴን የሚያበላሽ እንደሆነ በግልፅ ቢታይም እንደግፈዋለን - ለእውነታ ዋጋ ስለማንሰጥ። ቢያንስ ቢያንስ ለእውነታ ክብር ቢኖረንኮ፣ የዋጋ ተመን እንደማያዋጣ ተገንዝበን ተመኑ እንዲሰረዝ ማድረግ እንችል ነበር። እስቲ ይታያችሁ። በመንግስት የገንዘብ ህትመት ሳቢያ የዋጋ ንረት ሲከሰት፣ እንደሌላው ሸቀጥ የስንዴ ወይም የዱቄት ዋጋም ይጨምራል። ዳቦ ጋጋሪው ግን፤ ዋጋ መጨመር አትችልም ተብሏል።
ይሄ ሊያስኬድ አይችልም። መንግስትም ይህንን ያውቃል። እናም፤ ዳቦ ቤቶች በድሮው ዋጋ የስንዴ ዱቄት እንዲያገኙ አደርጋለሁ አለ። አንደኛ ነገር፤ የመንግስት ቢሮክራት፣ “ምን አተርፋለሁ፣ ምን አገኛለሁ” ብሎ፣ በጊዜ ስንዴ ለማቅረብ ይተጋል? ከደሞዙ ውጭ ምንም አያገኝም። በጊዜ ስንዴ ባያቀርብ ኪሳራ አይደርስበትም። የወር ደሞዙ አይቀነስበትም። እናም፤ እንደምታዩት ዳቦ ቤቶች በየጊዜው የስንዴ እጥረት እየገጠማቸው ስራቸው ይስተጓጎላል። ነገር ግን፤ የስንዴ ዱቄት በፍጥነትና በድሮ ዋጋ ለዳቦ ቤቶች ቢቀርብላቸውም እንኳ ብዙም አያስኬድም። ዳቦ እያመረቱ በድሮው የዋጋ ተመን መሸጥ እንዴት ይሆናል? የቤት ኪራይ፣ የማገዶ፣ የትራንስፖርት... ብዙ ነገሮችኮ ዋጋቸው ጨምሯል። ለዚህም ነው፤ በየሰፈሩ ብቅ ብቅ ሲሉ የነበሩት ዳቦ ቤቶች እየተዳከሙና እየተዘጉ፣ ቀስ በቀስ የየከተማው የዳቦ ቤቶች ቁጥር ሲመናመን የምናየው።
በዳቦ ምትክ፤ አሁን አሁን የአንባሻ ጋጋሪዎች ቁጥር እየተበራከተ መጥቷል። አንባሻ ላይ የዋጋ ቁጥጥር አይደረግማ። ግን፣ ውድ ነው። ምክንያቱም እንደዳቦ፣ አንባሻ በብዛት ማምረት አይቻልም። ለነገሩ፤ በብዛት ማምረት ቢቻል እንኳ ዋጋ የለውም። ያኔ፣ አንባሻ ላይም የዋጋ ቁጥጥር ይጀመርና እሱም ይዳከማላ።
የዋጋ ቁጥጥር ለሰዎች ኑሮ እንደማይበጅ በተደጋጋሚ አይተነዋል። የታክሲዎች ቁጥር የተመናመነውና የትራንስፖርት እጥረት የተባባሰው ለምን ሆነና! ለነገሩማ፤ በደርግ ዘመን በስፋት ተግባራዊ የተደረገው የዋጋ ቁጥጥር፣ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ከማቃወስና ድህነትን ከማባባስ ያለፈ ጥቅም አላስገኘም።
እንዲያም ሆኖ፤ የዋጋ ቁጥጥር ላይ ብዙም ቅሬታ የለንም። ለምን? እውነታውን ብናውቀውም፣ ነፃነትን የሚጥስ ቢሆንም፣ ኑሮን የሚረብሽ ቢሆንም፤ ለእውነታ፣ ለነፃነትና ለሕይወት ብዙም ክብር ስለሌለን የዋጋ ቁጥጥርን አንቃወምም።
የሦስቱ ጀነራሎች ዕጣ ፈንታ
በኢትዮጵያ ታሪክ ዘመናዊና መደበኛ ሠራዊት የተመሰረተው በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመን በ1927 ዓ.ም ነው፡፡ ይህ ሠራዊት ከጦር ሜዳ ውሎ ባሻገር ፖለቲካን ጨምሮ ዘርፈ ብዙ በሆኑ የአገሪቱ ጉዳዮች ላይ ወሳኝ ተሳትፎ ነበረው፡፡
የፖለቲካውን ተሳትፎ እንኳን በስሱ ብንመለከተው፣ ከ1966 እስከ 1985 በነበሩት ዓመታት የኢትዮጵያን አምስት ያገር መሪዎች አፍርቷል፡፡ አራቱ በደርግ ዘመን ርዕሰ ብሔሮች ሆነው ሲያገለግሉ፣ አንዱ ደግሞ የኢህአዴግ ፕሬዚዳንት በመሆን አገልግለዋል፡፡
በደርግ ዘመን አገሪቱን የመሩት ጀነራል አማን አንዶም፣ ጀነራል ተፈሪ በንቲ፣ ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያምና ጀነራል ተስፋዬ ገብረኪዳን ናቸው። የኢህአዴጉ ፕሬዚዳንት ደግሞ መቶ አለቃ ግርማ ወልደጊዮርጊስ ናቸው፡፡ ስለ ጦሩ አመሠራረትና ሂደት ከሚመጣው ሳምንት ጀምሮ በዝርዝር እንመለከተዋለን። ለዛሬ ግን የቆምሻ ያህል ስለ ሦስት ጀነራሎች እጣ ፈንታ እንመለከታለን፡፡
ሦስቱ ጀነራሎች ማለትም ጀነራል ሙሉጌታ ቡሊ፣ ጀነራል ከበደ ገብሬ እና ጀነራል መንግስቱ ነዋይ፤ ጦሩ ሲመሰረት በአፍላ ዕድሜያቸው ተመልምለው በመኮንነት ማዕረግ ለመመረቅ ሆለታ ከከተቱት ወጣቶች መሃል ናቸው፡፡ የጣልያን ወረራ አይቀሬነትን የተገነዘቡት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ፤ ከስዊዲን አገር አምስት የጦር መኮንኖች በማስመጣት፣ በ1927 ዓ.ም የሆለታ ገነት ጦር ትምህርት ቤትን አቋቋሙ፡፡ ስልጠናው ሳይጠናቀቅ የፋሽት ኢጣልያ ወረራ በመጀመሩ ሰልጣኞቹ ለግዳጅ ተጠሩ፡፡
ሰልጣኞቹ እንደ አንድ የተደራጀ ጦር ሆነው መዋጋት ስለነበረባቸው በትምህርት ቤቱ ቆይታቸው ባሳዩት የቀለም ትምህርት እና ወታደራዊ ቅልጥፍና፣ የአመራር ክህሎታቸው እየታየ ሹመት ተሰጣቸው። በዚህ የተነሳም ሙሉጌታ ቡሊና ከበደ ገብሬ የሻለቃ ማዕረግ፣ መንግስቱ ነዋይ ደግሞ የመቶ አለቃ ማዕረግ ተሰጣቸው፡፡
ሦስቱም ጀነራሎች ከሌሎቹ የጦር ጓዶቻቸው ጋር በመሆን የፋሽስት ኢጣልያን ወረራ ለመመከት ዝግጁ ሆኑ። ጦሩ የተሰጠው የጦር ግዳጅ ጣርማ በር ላይ በመመሸግ ወራሪውን ኃይል መመከት ነበር፡፡ ሆኖም በታጠቀው የጦር መሳሪያ ብልጫ እና የሠራዊት ብዛት የፋሽስት ኢጣሊያ ጦር በቀላሉ ድል አደረጋቸው። ኢትዮጵያ ለጊዜውም ቢሆን በኢጣልያ ቁጥጥር ስር ዋለች፡፡ በዚህ ጊዜ ጦሩ በአንድ ላይ ሆኖ ትግሉን መቀጠል አልቻለም። ከፊሉ ጥቁር አንበሳ የሚል ድርጅት በመመስረት ትግሉን ለመቀጠል ወደ ምዕራብ ሲያቀና፣ ሌሎች በሄዱበት አካባቢ ካገኙአቸው አርበኞች ጋር ሲቀላቀሉ፣ የተቀሩት ፋሽስት ኢጣልያ የጦሩን አባላት እያደነ መግደል ሲጀምር ወደ ስደት አቀኑ፡፡
ወደ ስደት ካቀኑት መሃል ጀነራል ሙሉጌታ ቡሊ፣ ጀነራል ከበደ ገብሬ እና ጀነራል መንግስቱ ነዋይ ይገኙበታል፡፡ ሦስቱም ጀነራሎች የተሰደዱት ወደ ጅቡቲ ነው፡፡ ጅቡቲ ውስጥ ሦስቱም ከሌሎች ስደተኛ የጦር ጓዶቻቸው ጋር በመሆን ክፉውንም ደጉንም አብረው አሳልፈዋል፡፡ በወቅቱ ከሦስቱም ጋር ጅቡቲ ከነበሩት መሃል በወቅቱ አቶ ኋላ ላይ ጀነራል ወልደሥላሴ በረካና ጀነራል ወልደዮሐንስ ሽታ ይገኙበታል፡፡ ጅቡቲ ውስጥ ካጋጠማቸው አስከፊ የስደት ኑሮ በላይ ያንገበግባቸው የነበረው በፋሽስት ኢጣልያ ለተወረረችው አገራቸው በሞያቸው ማገልገል አለመቻላቸው ነበር፡፡ አረረም መረረም የጅቡቲ የስደት ኑሮዋቸውን በአንፃራዊ ሰላም ለተወሰኑ ዓመታት ሲመሩ ቆይተው፣ ፈረንሳይ በናዚዋ ጀርመን ድል ተመታ ስትያዝ፣ ኢጣልያ የፈረንሳይ ቅኝ ግዛት የሆነችውን ጅቡቲን በአየር ኃይሏ መደብደብ ጀመረች፡፡
በዚህ ወቅት ጅቡቲ ውስጥ መቆየቱ ለአደጋ መጋለጥ መሆኑን የተገነዘቡት ጀነራሎች ወደ ሌላ ቦታ መሄድ እንዳለባቸው ወሰኑ፡፡ በቅርብ ርቀት ወደምትገኘው የእንግሊዝ ቅኝ ግዛት አካል ወደሆነችው በርበራ ማቅናት እንዳለባቸው ተስማሙ፡፡ በጅቡቲ የነበሩት የጦር ጓዶቻቸውን ብቻ ሳይሆን በወደቡ ይኖሩ የነበሩ ሴትና ህፃናት የሚገኙባቸው ኢትዮጵያውያንን በመያዝ ወደተባለው ቦታ በጀልባ ጉዟቸውን ጀመሩ፡፡
ጀልባዋን ከአንድ ህንዳዊ በመከራየት በህንዱ መሪነት ነው ወደ በርበራ ያቀኑት። እንቅስቃሴአቸውን ሁሉ በንቃት ሲከታተል የነበረው የኢጣልያ ስለላ መረብ በአካባቢው ለነበረው ጦሩ ስለጠቆመ፣ ከፍተኛ አደጋ ለማድረስ የሚችለውን ሁሉ አድርጐ አልተሳካለትም፡፡
ስደተኞቹ በርበራ እንደደረሱ እንደነሱው ሁሉ በርበራ ውስጥ በስደት ከሚኖሩ የጦር ጓዶቻቸው ጋር ተገናኙ፡፡ ከስደተኞቹ መሃል ጀነራል አሰፋ አየነ ኋላ ላይ የኢትዮጵያ አየር ኃይል አባት እየተባሉ ይጠሩ የነበሩት ይገኙበታል፡፡
በርበራም ከኢጣልያ ጥቃት አልተረፈችም። በዚህ ጊዜ የእንግሊዝ ጦር በባህር ኃይሉ ጭኖ ወደ የመን ዋና ከተማ ወሰዳቸው፡፡ ኤደን ለትንሽ ጊዜ ከቆዩ በኋላ ኬንያ በመሄድ፣ ከሌሎች ስደተኛ ኢትዮጵያውያን ጋር በመሆን፣ ጠላታችንን መዋጋት እንፈልጋለን በማለት ለእንግሊዞቹ ማመልከቻ ስለፃፉ እንግሊዞች ወደ ኬንያ ላኩአቸው፡፡
ልብሳቸውን አወለቁ፡፡ መሬት ላይ በመተኛት በጅራፍ እንዲገረፉ በቦታው የነበረው እንግሊዛዊ ለበታቾቹ ትዕዛዝ አስተላለፈ፡፡ በዚህ ጊዜ ስደተኞቹ በሙሉ ልብሳቸውን በማውለቅ ከጄነራል ከበደ ጎን ተኙ። በሁኔታው የተናደዱት እንግሊዞች ጫካ እንዲመነጥሩ ያዘዙአቸው ይሄኔ ነበር፡፡ ያ ሁሉ ግፍ ተፈፅሞባቸው፣ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ አገራቸውን ከፋሽሽት ኢጣልያ ነፃ ለማውጣት ሱዳን መግባታቸው ተሰማ፡፡ ስደተኞቹ “ከንጉሠ ነገስታችን ጋር በመሆን አገራችንን ነፃ እንድናወጣ ወደ ሱዳን እንድንሄድ ፈቃድ ይሰጠን” በማለት አመለከቱ፡፡ እንግሊዞች ግን ጆሮ ዳባ ልበስ አሉ። በእንግሊዝ እርዳታ ሱዳን የገቡት ጃንሆይ፤ “ኬንያ ያሉት ስደተኞች ለማቋቁመው ጦር ስለሚስፈልጉኝ ይላኩልኝ” ብለው ስለጠየቁ፣ ኬንያ ያሉት እንግሊዞች ምንም ማድረግ አልቻሉም፡፡ ሆኖም በጀነራል ሙሉጌታ ቡሊና በጄነራል ከበደ ገብሬ ፅናትና ድፍረት የበገኑት እንግሊዞች፤ ሰበቦች በመደርደር ላለመልቀቅ ጣሩ፡፡ በዚህ የተነሳም ሌሎቹ እነሱን ትተን አንሄድም ብለው ስለቆረጡ ሁለቱንም ለመልቀቅ ተገደዱ፡፡
በኬንያ የከፋ ኑሮ ጫካ ሲመነጥሩ በነበሩበት ጉዜ በያዛቸው ወባ የተጎሳቆሉት ስደተኞች፤ ወደ ኡጋንዳ በመኪና ተጭነው ከሄዱ በኋላ በባቡር ወደ ሱዳን ተጓዙ። ሱዳን አገር ላይ ሶባ በተባለ ቦታ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ባቋቋሙት ጊዜያዊ ጦር ትምህርት ቤት በመግባት የተማሩትን የጦር ትምህርት ከለሱ፡፡
ከስልጠናው በኋላ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴን በመከተል አዲስ አበባ ገቡ፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት በጃንሆይ መሪነት እንደ አዲስ ተደራጅቶ ስራውን ሲጀምር፣ ሦስቱ ጄነራሎች በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች በመመደብ አገራቸውን ማገልገል ጀመሩ። ጄነራል ሙሉጌታ ቡሊ የክብር ዘበኛ አዛዥነት ከደረሱ በኋላ በወቅቱ በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ መንግስት ውስጥ በተፈጠረው የፖለቲካ ሽኩቻ ከቦታው ተነስተው የህዝባዊ ኑሮ እድገት ሚኒስትር ሆኑ፡፡ ጄነራል ከበደ የምድር ጦር ዋና አዛዥ ሆኑ፡፡ ጄነራል መንግስቱ ደግሞ ሙሉጌታን በመተካት የክብር ዘበኛ አዛዥ ሆኑ፡፡ ለሚያውቃቸው ሁሉ የሶስቱ ጄነራሎች ጓደኝነት ጥብቅ ነበር፡፡ ጓደኝነታቸው የወንድማማችነት ያህል ስለነበር ባለቤቶቻቸውም ሆኑ ልጆቻቸው ችግር ሲገጥማቸው በቀጥታ በመሄድ ችግራቸውን የሚያካፍሉት ለነሱ ነበር።
1953 ዓ.ም ለኢትዮጵያ ሕዝብ ወሳኝ ዓመት ነበረች። ለሶስቱ ጄነራሎች ደግሞ የበለጠ፡፡ ያ ሁሉ ከልጅነት ጀምሮ በስደትና በነፃነት፣ በኋላም በነበራቸው ጥብቅ ግንኙነት የተፈጠረው ወንድማማችነት ውኃ በላው። ጄነራል መንግስቱ መንግስት ገልባጭ፣ ጄነራል ከበደ ግልበጣውን አክሻፊ፣ ጄነራል ሙሉጌታ ደግሞ ታሳሪ ሆነው አረፉት፡፡ በዚህ የተነሳም ጄነራል መንግስቱ ግልበጣው ሲከሽፍ በስቅላት ሲገደሉ፣ ጄነራል ሙሉጌታ ደግሞ በጥይት ተደብድበው ሞቱ። ለጊዜው ከሞት የተረፉት ጄነራል ከበደ ገብሬ የመጀመሪያው የተባበሩት መንግስታትን ጦር በኮንጎ የመሩ ጥቁር ጄነራል ሆኑ፡፡ በስራቸው የስዊዲን የአየር ላንድና የአንድ ጄነራሎች ገበሩ፡፡ ከዚያም የመከላከያ ሚኒስቴር በመሆን አገራቸውን አገለገሉ፡፡ በ1966 ወታደራዊው መንግስት ታላላቅ ኢትዮጵያውን የሚገኙበት ባለስልጣኖችን በግድያ ሲቀጣ፣ ጄነራል ከበደ ገብሬም በጥይት ተደብድበው ተገደሉ፡፡
ይቺ ትንሽ ታሪክ የኢትዮጵያን ምስቅልቅል ህይወት በጥቂቱም ቢሆን ታመላክታለች፡፡ የሦስቱም ጓደኛሞች ፍፃሜ ግን አይገርምም፡፡ የሳምንት ሰው ይበለን፡፡
ኢህአዴግ “ረዳት መንግስት” ያስፈልገዋል! (ስንቱ ጋ ይሁን?)
ባለስልጣናት ሥልጣን የማይለቁት “የስልጣን ጡር” ስለሚፈሩ ነው
ኢህአዴግ “ረዳት መንግስት” ያስፈልገዋል ስል ሌላ የፖለቲካ ጨዋታ ውስጥ እንዳትገቡ፡፡ ያልተቀኘሁትን ቅኔም ለመፍታት እንዳትሞክሩ፡፡ እኔ ለማለት የፈለግሁት ኢህአዴግ በግራና በቀኝ በልማት ስለተጠመደ፣ ይህችን አገር በቅጡ ለመምራት “ረዳት መንግስት” ያስፈልገዋል ነው፡፡ እመኑኝ፤ በአማካሪ በምናምን ሊወጣው የሚችለው ጉዳይ አይደለም። በ“ረዳት መንግስት” ብቻ እንጂ፡፡ ያውም እኮ ቀና “ረዳት መንግስት” ከተገኘ ነው፡፡
በነገራችሁ ላይ ልማታዊው አውራ ፓርቲ፤ እዚህ ደረጃ ላይ የደረሰው በራሱ ጥፋት ነው (ለመወንጀል ሳይሆን ለመተቸት ያህል ነው!) የመንግስት ሹማምንቱን በፖለቲካ ታማኝነት ብቻ መመልመሉ ነው ለዚህ ያበቃው (የፓርቲ ፍቅር ሌላ ብቃት ሌላ!) እስቲ አስቡት… ኢህአዴግ እተማመንባቸዋለሁ ብሎ ከሾማቸው የፓርቲው ታማኝ አባላት መካከል ስንቶቹ በሙስና ተዘፍቀው ዘብጥያ እንደወረዱ! ልማታዊ ህዝብ ይፈጥራሉ የተባሉ ስንት ሹመኞች የኪራይ ሰብሳቢ ሰራዊት መልምለውና አሰልጥነው ቁጭ እንዳሉ! (“የት ይደርሳል የተባለ ዛፍ ቀበሌ ቆረጠው” አሉ!)
እኔ የምለው… ኢህአዴግ “ታማኝ” ናቸው ብሎ ከሾማቸው በኋላ ሙሰኛ ሆነው ለተገኙት አባላቱ ተጠያቂው ማነው?(እንደ ደንቡማ ኢህአዴግ ነበር!)
ይሄን ሁሉ ያመጣሁት ዝም ብዬ ለወቀሳ ብቻ አይደለም፡፡ ኢህአዴግ “ረዳት መንግስት” ያስፈልገዋል እስከመባል የደረሰው ራሱ የሾማቸው ኃላፊዎች ስራቸውን በቅጡ ስለማይሰሩ እንደሆነ ለማስረገጥም ጭምር ነው፡፡ አንድም በአቅም ማነስ፣ አንድም ደግሞ በልግመት፡፡ (የአቅም ግንባታ መ/ቤት ተዘግቷል እንዴ?)
ይሄውላችሁ…. አንዳንድ ከተጨባጩ እውነታ የተራራቁ ፖለቲከኞች (ኢህአዴግ “ፅንፈኛ ተቃዋሚዎች” የሚላቸው!) በምርጫ ዋዜማ ላይ እንደሚሉት፤ “ኢህአዴግ አብቅቶለታል፤ አንድ ሐሙስ ነው የቀረው!” ምናምን የሚል ነገር አልወጣኝም (ኧረ ወደፊትም አይወጣኝ!) “ረዳት መንግስት” የሚለው ሃሳብ ከተተገበረ እኮ ኢህአዴግ እንኳን ሊያበቃለት አዲስ ጉልበት ነው የሚያገኘው (እንደ ውለታ እንዲቆጠርልኝ ፈልጌ ግን አይደለም!)
በእርግጥ ሃሳቡ ከፀደቀ ብዙ ጥያቄዎች ሊነሱ ይችላሉ፡፡ ጉዳዩን በተመለከተ አዲስ አዋጅ ሁሉ ሊረቀቅ ይችላል፡፡ ለምን መሰላችሁ? “ረዳት መንግስት” የሚለው ትንሽ አወዛጋቢ ሊመስል ይችላል፡፡ ቢሆንም ግን ሌላ ምርጫ የለም። ለነገሩ የመንግስትና የስልጣን ጉዳይ ሁሌም ስለሚያወዛግበን ነው እንጂ ቀላል ነው፡፡ ምን መሰላችሁ…ለሳይንቲስት ረዳት ሳይንቲስት፣ ለሃኪም ረዳት ሃኪም፣ ለዳኛ ረዳት ዳኛ ወዘተ… እንዳለው ሁሉ፣ ለኢህአዴግ መንግስትም “ረዳት መንግስት” እንዲኖረው ማድረግ ብቻ ነው፡፡ (ህግና ደንብ አውጥቶ ማለቴ ነው!) “ረዳት መንግስት” ከየት ይመጣል? እኔ አላውቅም፡፡ እንዴት ይደራጃል? እሱንም አላውቅም፡፡ (እኔ መፍትሔ አፍላቂ ብቻ ነኝ!)
እዚህ ጋ አንባቢ እንዲረዳልኝ የምፈልገው፣ ኢህአዴግ እንደካምቦዲያ መንግስት ከተቃዋሚዎች ጋር ስልጣን ይጋራ እያልኩ አለመሆኔን ነው፡፡ ሥልጣን ማጋራትም ሆነ መጋራት ሃጢያት ሆኖ ግን አይደለም፡፡ (ላወቀበትማ ሥልጣኔ ነበር!) የዚህ ፅሁፌ ዓላማ “የሥልጣን ማኔፌስቶ” ማዘጋጀት ባለመሆኑ ብቻ ነው፡፡ እናም ሲፈልግ ኢህአዴግ ራሱ ሊያደራጀው ወይም ደግሞ እንደ ማኔጅመንት ኩባንያ ከውጭ አገር በቅጥር ሊያስመጣው ይችላል። ዋናው ነገር ግን “ረዳት መንግስት” በአፋጣኝ እንደሚያስፈልገው ማወቁ ላይ ነው፡፡
በነገራችሁ ላይ ይሄ “ረዳት መንግስት” የሚለው ነገር በመንግስት አስተዳደር የዳበረ ልምድ አለን ከሚሉት ከየትኞቹም የዓለም አገራት ያልተቀዳ ኦሪጂናል “አገር በቀል” ሃሳብ ነው፡፡ (ከስንዴ እስከ ጸረ-ሽብር ህግ ከእነሱ ቀድተን እንችለዋለን እንዴ?) እናላችሁ… ኢህአዴግ በል ካለውና እግረ መንገድ ከመንግስት ሥልጣን ጋር እንዲለማመዱ ካሰበ… አቅም ያላቸውን ተቃዋሚዎች “ረዳት መንግስቱ” አድርጎ ሊሾማቸው ይችላል፡፡ ወይም ደግሞ ከአገሬ ተቃዋሚዎች ይልቅ ቻይናን ነው የማምነው የሚል ከሆነም (ማለቱ አይቀርም!) እንደ ኩባንያ ማኔጅመንት በኮንትራት አስመጥቶ በ “ረዳት መንግስትነት” ሊያሰራቸው ይችላል፡፡ ምርጫው የሥልጣኑ ባለቤት ነው፡፡ (የኢህአዴግ ማለቴ ነው!)
ሰሞኑን የወጣው “ብሉምበርግ” የተሰኘ የፋይናንስ መጽሔት፤ በአዲስ አበባ ተቋቁሞ ጫማ ስለሚያመርት የቻይና ኩባንያ ያወጣውን አንድ ዘገባ አነበብኩ፡፡ ኩባንያው አሁን 3ሺ500 ሰራተኞች ያሉት ሲሆን በ8 ዓመት ውስጥ የሰራተኞቹን ቁጥር 50ሺ የማድረስ ዕቅድ እንዳለው ቻይናዊው ባለቤት ለብሉምበርግ ገልጿል፡፡ እኔን ያስገረመኝ ግን የአንድ ኢትዮጵያዊ ጫማ ሰሪና የቻይና አቻው የደሞዝ ልዩነት ነው፡፡ ኢትዮጵያዊው 40 ዶላር (800 ብር ገደማ) ሲያገኝ ቻይናዊው 400 ዶላር (8ሺ ብር ገደማ) ያገኛል ብሏል - መጽሔቱ፡፡ ኢትዮጵያዊ ጫማ ሰሪ በሰዓት ስንት እንደሚከፈለው ታውቃላችሁ? 25 ሳንቲም ገደማ ነው፡፡ ወይም በቀን 2 ዶላር፡፡ በኒውዮርክ የአንድ ስኒ ቡና ዋጋም 2 ዶላር ገደማ ነው፡፡ አበሻ አገር ጉልበት እርካሽ ነው ወይስ ነፃ? (ለጠቅላላ እውቀት እኮ ነው!)
ወደ ጉዳያችን እንመለስ ---ኢህአዴግ ለ“ረዳት መንግስትነት” ቻይናዎችን ከመረጠ ጉዳዩን ከህግ አንፃር መመርመር ሳያስፈልግ አይቀርም፡፡ (ተቃዋሚዎች እቺን ካገኙ እኮ “ለቅኝ ገዢ አገርን አሳልፎ መስጠት” በሚል መንግስትን ሊከሱት ይችላሉ!)
ይሄውላችሁ ---- አንዳንድ ካድሬዎች፤ ደርግና ንጉሱ እንኳን ያለ “ረዳት ገዝተው” የለም ወይ ብለው ሊያሳጡኝ ይሞክሩ ይሆናል፡፡ ግን እኮ ድሮና ዘንድሮ ለየቅል ናቸው፡፡ መቼም 40 ሚ. ህዝብ መምራትና 90 ሚ ህዝብ መምራት አንድ ሊሆን አይችልም፡፡ በዚያ ላይ የድሮ መንግስታት ሚናቸው የአባትነት ብቻ ነበር፡፡ ኢህአዴግ እኮ የአባትነትም፣ የእናትነትም (“የእንጀራ እናት” የሚሉትም አሉ!) የታላቅ ወንድምነትም፣ የመንግስትነትም ሚና ነው የሚጫወተው፡፡ (“ማን አስገደደው?” ለሚሉ መልስ የለኝም!) ከቅርብ ጊዜ ወዲህማ “ሥራ ብዙ” ሆኗል፡፡ በአንድ በኩል ሃዲድና አስፋልት ያነጥፋል (“የመንገድ መንግስት” ሲሉ ሰማሁ ልበል?) በሌላ በኩል ለቤት ፈላጊዎች ኮንዶሚኒየም ገንብቶ ለማስረከብ ደፋ ቀና ይላል፡፡ (በርና መስኮት የለውም ቢባልም!) እዚያ አባይ ማዶ ደግሞ ከግብጽ ጋር ስንት የተባባልንበትን የህዳሴ ግድብ ይገነባል፡፡
ይሄ ሁሉ ሳያንሰው የስኳር ፋብሪካዎችም እሱኑ ነው የሚጠብቁት፡፡ (እሱንስ ለሆላንዶች ሰጥቶ በተገላገለ!) ይሄ ብቻ ግን አይደለም፡፡ መሰረታዊ የንግድ እቃዎች ከውጭ እያስመጣ “አለ በጅምላ” በተባለው መደብር በኩል ያከፋፍላል፡፡ (ነጋዴን አላምንም ብሎ ነው አሉ!) በዚያ ላይ የፖለቲካ ሥራውም ትንፋሽ ያሳጣው ይመስላል፡፡ የምርጫ ቅስቀሳ ምናምን እኮ አይደለም፡፡ በሽብርተኝነት የጠረጠራቸውን ጋዜጠኞች፣ ጦማሪያኖች፣ ፖለቲከኞች… ከያሉበት ሰብስቦ ማሰር…ፍ/ቤት ማቅረብ፣ መክሰስ፣ ማስፈረድ፣ ለዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ነን ባዮች ኮስተር ያለ የአበሻ መልስ መስጠት… ይሄም የመንግስት ሥራ ነው፡፡ ታዲያ … በእሱስ ይፈረዳል? (ቆይ ስንት ቦታ ይሁን?!)
እውነቱን ልንገራችሁ አይደል ----- የፈረንጅ መንግስት ቢሆን ገና ድሮ “በቃኝ” ብሎ ራሱን ከስልጣን ያሰናብት ነበር፡፡ የአበሻ መንግስት ግን “ብረት” ነው፡፡ (አበሻ እጅ አይሰጥም!) በዚያ ላይ ሹመትን የመሰለ ክቡር ስጦታ ጥለን መሄድ ባህላችን አይደለም (የስልጣን ጡር እንፈራለን!) በዚህ መሃል ነው ብዙ ውጥንቅጥ የተፈጠረው፡፡ በዚህ መሃል ነው የውሃ፣ የመብራት፣ የኢንተርኔትና የኔትዎርክ መጥፋትና መቆራረጥ እንዲሁም የትራንስፖርት ችግር መከራችንን ያበሉን፡፡ በዚህ መሃል ነው ብንጮህ ብንጮህ የሚሰማን ያጣነው። (ኢህአዴግ በብዙ የልማት ሥራዎች ተወጥሯላ!) ለዚህ ነው አይፈረድበትም የምለው፡፡ ግን መፍትሔ ያስፈልጋል፡፡ መፍትሔው ደግሞ “ረዳት መንግስት” ነው፡፡
ሰሞኑን ደግሞ ከመንግስት ሠራተኞች ደሞዝ ጭማሪ ጋር ተያይዞ ነጋዴዎች የሸቀጦችን ዋጋ በማናር ኢኮኖሚውን ለግሽበት እንዳይዳርጉት በአንድ ወገን በህገወጥ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ እየወሰደ፣ በሌላ ወገን ሸቀጦችን በየመ/ቤቱ አከፋፍላለሁ ብሏል፡፡(ሰሞኑን በደርግ ዘመን የረሳሁትን የቀበሌ ሃሎ ሃሎ ሰማሁ ልበል!)
ወዳጆቼ… ኢህአዴግ “ረዳት መንግስት” ያስፈልገዋል ብዬ በእርግጠኝነት የምናገረው ዝም ብዬ አይደለም፡፡ ችግሩን ስላየሁለት ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ኢህአዴግ ከሳጥኑ ውጪ (Out of the box እንዲሉ) የሚያስቡ መፍትሔ አፍላቂ አማካሪዎችም መቅጠር ይኖርበታል፡፡ በመንግስት ደሞዝ ሳይሆን ወፈር ባለ ደሞዝ! (የመንግስት ሠራተኞች የደሞዝ ጭማሪ ምነው ሐምሌን ተሻገረ?) እናላችሁ…ለስንት ዓመት የተወዘፈና ሊፈታ ያልቻለ የችግር ተራራ እኮ እንዲህ በቀላሉ አይናድም፡፡ (ደማሚት ሁሉ ይፈልጋል!)
የፖለቲካ ጥግ
ፖለቲከኛ የሚናገረውን ነገር ስለማያምንበት ሌሎች ሲያምኑት ይገርመዋል፡፡
ቻርልስ ደጎል
(የቀድሞ የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት)
ልጅ ሳለሁ ማንም የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሊሆን እንደሚችል ተነግሮን ነበር፡፡ አሁን ማመን ጀምሬአለሁ፡፡
ክላሬንስ ዳሮው
(አሜሪካዊ የህግ ባለሙያ)
ቤት የማስተዳደርን ችግር የምትረዳ ማንኛዋም ሴት አገር የማስተዳደርን ችግር ለመረዳት ቅርብ ናት፡፡
ማርጋሬት ታቸር
(የእንግሊዝ የቀድሞ ጠ/ሚኒስትር)
ትላንት ማታ ጨረቃዋ፣ ክዋክብቱና ፕላኔቶቹ በሙሉ በእኔ ላይ ወድቀዋል፡፡ (ሰማይ ተደፍቶብኛል እንደማለት) ወገኖቼ፤ የምትፀልዩ ከሆነ ለእኔ ፀልዩልኝ፡፡
ሃሪ ኤስ. ትሩማን
(በወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የነበሩት
የፕሬዚዳንት ፍራንክሊን ዲ. ሩስቬልትን ህልፈት አስመልክቶ ለሚዲያ የተናገሩት)
አንተ አንዲቷ ምዕራፍ ነህ፤ እኔ ሙሉው መፅሃፍ ነኝ፡፡
ፍራንሶይስ ሚቴራንድ
(የቀድሞ የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት አማካሪያቸው የተናገሩት)
አንድ አብዮተኛ ልታስሩ ትችላላችሁ፤ አብዮቱን ግን ማሰር አትችሉም፡፡
ቦቢ ሲሌ
(አሜሪካዊ የሲቪል መብቶችተሟጋች)
አንድ ጊዜ አንድ ታላቅ ሰው፤ ጠላቶቻችሁን ውደዱ ብሎ ነበር፡፡ ይሄ መጥፎ ምክር አይደለም፡፡ ጠላቶቻችንን ልንወዳቸው እንችላለን፡፡ ይሄ ማለት ግን አንዋጋቸውም ማለት አይደለም፡፡
ኖርማን ሽዋርዝኮፕፍ
(አሜሪካዊ ጄነራል)