Administrator

Administrator

ቻይናዊው ሁ ሴንግ አንዲት የሚወዳት ፍቅረኛ አለችው፡ እናም ፍቅሩን ለመግለፅ ብቻ ሳይሆን Surprise ሊያደርጋት (ሊያስደምማት) ያስብና ትንሽ ይቆዝማል - ሃሳብ እያወጣ እያወረደ፡ ብዙዎቹ የመጡለትን ሃሳቦች አናንቆ ጣላቸው - ፍቅረኛውን ለማስደመም ብቃት እንደሌላቸው በመቁጠር፡፡ በአዕምሮው የሃሳብ ጅምናስቲክ ሲሰራ ቆይቶ ግን አንዲት ሃሳብ አንጀቱ ላይ ጠብ አለችለት፡፡ ሃሳቡን ለመተግበርም ሲበዛ ተጣደፈ፡፡ ፍቅረኛውን ሊያስደምምበት በወጠነው ሃሳብ እሱ ራሱ ቀድሞ ተደመመና ቁጭ አለ፡፡ ከድማሜው ሲወጣ ሃሳቡን ወደ ተግባር ለውጦ የማሰቡን በረከት ሊቋደስ ቋመጠ፡፡ በቻይና የቾንኪዊንግ ግዛት ነዋሪ የሆነው ሴንግ፤ ፍቅረኛውን በምን ሰርፕራይዝ እንደሚያደርጋት ለማንም አልተናገረም፡፡ ምስጢር ነው - እሱና እሱ ብቻ የሚያውቁት፡፡ ፍቅረኛውም የምታውቀው ሰርፕራይዝ ከተደረገች በኋላ ይሆናል፡፡ ሁሴንግ በቀጥታ የሄደው እንደ ዲኤች ኤል ያለ ፈጣን መልዕክት አድራሽ ተቋም ጋ ነበር፡፡ እዚያም እንደደረሰ ስለሚያደርሱት እቃ ወይም መልዕክት ምንነት ሳይናገር በካርቶን የታሸገ ስጦታ እፍቅረኛው ቢሮ እንዲወስዱለት ብቻ ተነጋገረና ተስማማ፡፡ የአገልግሎት ክፍያውንም ሳያቅማማ ፈፀመ፡፡

ለፍቅረኛው ሊልክላት ያሰበው ስጦታ አበባ አልነበረም፡፡ ጫማ፣ ወርቅ፣ አልማዝ ወይም ወድ አልባሳትም አይደለም፡፡ ለፍቅረኛው ለመላክ ያሰበው ራሱን ነው፡፡ በዚህ ነው የሚወዳትን ፍቅረኛውን ማዝናናትና ማስደመም ያማረው፡፡ እናም መልዕክቱን የሚያደርሱት የድርጅቱ ሠራተኞች ወደ ቤቱ ከመምጣታቸው አስቀድሞ ራሱን እንደ ስጦታ እቃ በካርቶን ውስጥ አሳሽጐ ጠበቃቸው፡፡ መልዕክት አድራሾቹ “አገር አማን” ብለው በተለመደ ፈጣን የአገልግሎት አሰጣጣቸው፣ በአደራ የተሰጣቸውን እቃ ወደተባሉበት ሥፍራ ለማድረስ ከነፉ - በዘመናዊ ፈጣን አውቶሞቢላቸው፡፡ ሆኖም መሃል ላይ የቴክኒክ ችግር ገጠማቸው፡፡ የአድራሻ ስህተት ተፈጠረ፡፡ ይሄ ስህተት ደግሞ ከሁሉም በላይ ራሱን በካርቶን ውስጥ ላሳሸገው ምስኪኑ ሴንግ ከባድ ፈተና ነበር - የህይወት መስዋዕትነት እስከማስከፈል የሚደርስ፡፡ ሴንግ በካርቶኑ ውስጥ ታሽጐ የሚቆየው ቢበዛ ለ30 ደቂቃ ያህል መስሎት ነበር፡፡

በተፈጠረው የአድራሻ ስህተት ግን ጊዜው ወደ 3 ሰዓታት ተራዘመበት፡፡ ጉድ ፈላ - ሴንግ! ካርቶኑ ውስጥ በአየር እጦት ተሰቃየ፡፡ የማታ ማታ ግን እሽጉ ካርቶን እፍቅረኛው ቢሮ መድረሱ አልቀረም፡፡ ፍቅረኛው ካርቶኑን ለመክፈት ስትጣደፍ፣ የሥራ ባልደረባዋ ደግሞ ሰርፕራይዙን ቀርፃ ለታሪክ ለማስቀመጥ ካሜራዋን ደግና እየተጠባበቀች ነበር፡፡ ካርቶኑ ሲከፈት ግን ሰርፕራይዝ የሚያደርግ ሳይሆን በድንጋጤ ክው የሚያደርግ ነገር ገጠማቸው፡፡ ሁ ሴንግ ካርቶኑ ውስጥ ሩሁን ስቷል፡፡ በአየር እጥረት ታፍኖ፡፡ በስጦታ ሰርፕራይዝ ለመደረግ ቋምጣ የነበረችው ፍቅረኛው፤ ህይወቱን ለማትረፍ ተጣድፋ የድንገተኛ ህክምና ባለሙያዎችን አስጠራች፡፡ የህክምና እርዳታ ካገኘ በኋላ ሴንግ ነፍሱ ተመለሰችለት፡፡

“ጉዞው ያንን ያህል ረዥም ጊዜ ይወስዳል ብዬ አላሰብኩም ነበር” ያለው የዋሁ አፍቃሪ፤ “በእሽጉ ካርቶን ውስጥ ሆኜ አየር የማገኝበት ቀዳዳ ለማበጀት ሞክሬ ነበር፤ ሆኖም ካርቶኑ በጣም ወፍራም ስለሆነ አልቻልኩም፤ ጩኸት እንዳላሰማ የነገሩን ድንገቴነት (Surprise) ማበላሸት አልፈለግሁም” ብሏል፡፡ የመልዕክት አድራሹ ድርጅት ቃል አቀባይ በበኩሉ፤ “ገና ከመጀመርያው ምን እንዳሰበ ቢነግረን ኖሮ እሽጉን አንወስድለትም ነበር፤ እንስሳትን እንኳን ለማጓጓዝ ስንቀበል አየር ማግኘት እንዲችሉ በተለየ መያዣ ውስጥ ነው የምናደርጋቸው” ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል - ለኦሬንጅ ኒውስ፡፡ አይገርምም! ፍቅረኛውን ለማስደመም ሲል ህይወቱን ሊያጣ ለጥቂት እኮ ነው የተረፈው፡፡ ካልጠገቡ አይዘሉ፤ ካልዘለሉ አይሰበሩ የሚለው ሀገራዊ አባባል ለቻይናዊው ሁ ሴንግ አይሰራ ይሆን?!

በእባብ የተነደፈ የኔፓል ተወላጅ እባቡን መልሶ በመንከስ ብድሩን እንደመለስ ሰሞኑን ተዘግቧል፡፡ ሮይተርስ የኔፓል ዕለታዊ ጋዜጣ አናፑርና ፖስትን ጠቅሶ እንደዘገበው፤ ሞሃመድ ሳልሞ ሚያ የተባለውን ግለሰብ ኮብራ እባብ የነደፈው በሩዝ ማሳ ውስጥ ነበር፡፡ ሞሃመድ ግን ዝም አላለም፡፡ የገባበት ገብቶ በመያዝ ነክሶ ገድሎታል - እባቡን፡፡ “በዱላ ልገድለው እችል ነበር፤ ነገር ግን በጥርሴ ነክሼ ገደልኩት፤ ምክንያቱም ተናድጄ ነበር” ብሏል ከአገሪቱ መዲና ከካትማንዱ ደቡብ ምስራቅ 200ኪ.ሜ ላይ በምትገኘው መንደር የሚኖረው የ55 ዓመቱ ሞሃመድ፡፡ በኔፓል “ጐማን” እየተባለ የሚጠራው ይሄ የእባብ ዝርያ “ኮመን ኮብራ” በሚል ስያሜም ይታወቃል ብሏል አናፑርና ፖስት፡፡ በእባቡ የተነደፈው ሞሃመድ ሳልሞ ሚያ፤ በመንደሩ የጤና ጣቢያ ህክምና እየተደረገለት ሲሆን ለህይወቱ እንደማያሰጋው ተገልጿል፡፡

እባቡ በኔፓል በመጥፋት ላይ ካሉ የማያጠቡ እንስሳት ዝርያ ዝርዝር ውስጥ የተካተተ ባለመሆኑ እባቡን ነክሶ የገደለው ግለሰብ ከክስ እንደዳነ የአካባቢው ፖሊስ ባለስልጣን አስታውቋል፡፡ እንዲያ ባይሆን ኖሮማ እባቡን ነክሶ በመግደሉ ፍ/ቤት ይቆማት ነበር ተብሏል፡፡ ይታያችሁ … ሞሃመድ እባቡን ነክሶ የገደለው ለአደን አይደለም - ስለነደፈው እንጂ፡፡ ቢሆንም በመጥፋት ላይ ያሉ እንስሳትን መግደል በኔፖል ያስጠይቃል ብሏል - ሮይተርስ፡፡

በሰማይ ላይ የሚበሩ ክንፍ ያላቸው አውቶሞቢሎች እውን የማድረግ ህልም ከዛሬ 82 ዓመት ገደማ ጀምሮ የተወጠነ የቴክኖሎጂ ትልም ሲሆን እስካሁን ግን እንደ ሳይንሳዊ ፊክሽን (ልቦለድ) ሲቆጠር የቆየ ነበር፡፡ ከዚህ በኋላ ግን በሳይንሳዊ ልቦለድነት የሚጠቅሳቸው ማንም አይኖርም፡፡ ለምን ቢባል? በቅርቡ ለገበያ ሊቀርቡ እንደሆነ እየተነገረ ነዋ! የሚበረው መኪና የመጀመርያ በረራውን ያጠናቀቀ ሲሆን በመጪው አመት Transition በሚል ስያሜ ለሽያጭ ይቀርባል ተብሏል፡፡ አውቶሞቢሉ ሁለት መቀመጫዎች፣ አራት ጐማዎችና የሚታጠፉ ክንፎች እንዳሉት ታውቋል፡፡ የክንፎቹ መታጠፍ አውቶሞቢሉ እንደ መኪናም በመሬት ላይ መሽከርከር እንዲችል ያደርገዋል፡፡ ባለፈው አመት Transition በ1ሺ 400 ጫማ ከፍታ ለ8 ደቂቃዎች እንደበረረ የሚታወቅ ሲሆን የንግድ ጀቶች በ35ሺ ጫማ ከፍታ ነው የሚበሩት፡፡

ገና ካሁኑ Transition የተባለውን በምድር ተሽከርካሪ በሰማይ በራሪ መኪና ለመግዛት 100 ሰዎች 10ሺ ዶላር በቅድሚያ ከፍለዋል፡፡ የአውቶሞቢሉ አምራች ኩባንያ Terrafugia inc. በመጪው ሳምንት አዲሱን በራሪ መኪና በኒውዮርክ ለህዝብ እይታ የሚያቀርብ ሲሆን ከዕይታው በኋላ የገዢው ቁጥር እንደሚጨምር ተገምቷል፡፡ ሆኖም ግን Transition በየመንገዱ ላይ እንደልብ የሚታይ አውቶሞቢልም አይደለም፡፡ ለምን ቢሉ? 279ሺ ዶላር ያወጣል ተብሎ ይገመታል - ባለ ክንፋሙ አውቶሞቢል! ይሄን አውቶሞቢል በምድር ላይ እያሽከረከራችሁ ሳለ በትራፊክ ብትጨናነቁ ምንም ማድረግ አትችሉም፡፡

ምክንያቱም ከመሬት ወደ አየር ለመነሳት ማኮብኮብያ ሜዳ ያስፈልገዋል፡፡ የሚበር መኪና በአሜሪካውያን ምናብ ውስጥ ልዩ ቦታ ነበረው፡፡ ከ1930ዎቹ ዓመታት ጀምሮ የፈጠራ ባለሙያዎች ይሄን አውቶሞቢል ለመስራት ሲታትሩ ቆይተዋል፡፡ የአየር መንገድ ኢንዱስትሪ ተንታኝ የሆነው አሜሪካዊው ሮበርት ማን እንደሚለው፤ የሚበሩ አውቶሞቢሎችን እውን ከማድረግ አንፃር እንደ Terrafugia ኩባንያ እጅግ የቀረበ ማንም የለም፡፡ ኩባንያው ለአውቶሞቢሎቹ ልዩ ጐማዎችንና ለተለመዱት መኪኖች ጥቅም ላይ ከሚውሉ መስተዋቶች ቀለል ያሉትን ለመጠቀም ለመንግሥት ጥያቄ አቅርቦ ተፈቅዶለታል፡፡ የአየር መንገድ ኢንዱስትሪ ተንታኙ ሮበርት ማን እንደተናገሩት፤ ከዛሬ አምስት አመት በፊት በፌደራል አቪዬሽን አድሚኒስትሬሽን ውሳኔ ኩባንያው የተለየ ቀላል የስፖርት ኤርክራፍት ስታንዳርድ በመፍጠር እገዛ ተደርጐለታል፡፡ ስታንዳርዱ የኤሮፕላኑን መጠንና ፍጥነት እንዲሁም የፓይለቶች የፈቃድ መስፈርቶችን የሚወስን ነው፡፡ ኩባንያው እንደሚለው፤ የመኪናው ባለቤት የሚሰጠውን ፈተና ማለፍ ያለበት ሲሆን Transition የተባለውን አውቶሞቢል ለማብረር የ20 ሰዓታት በረራ ማጠናቀቅ የግድ ይላል፡፡

አውቶሞቢሉ በመሬት ላይ በሰዓት 70 ማይል የሚፈተለክ ሲሆን በአየር ላይ 115 ማይል ይበራል፡፡ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በአጠቃላይ የአቪዬሽን ገበያው እያሽቆለቆለ መምጣቱን የሚናገሩት ተንታኙ፤ ለዚህም ምክንያቱ ከፍተኛ የነዳጅ ወጪና በአምራቾቹ ላይ የሚያርፈው የወጪ እዳ ነው ይላሉ፡፡ ሌላው ችግር የበረራ ትምህርት የሚወስዱ ሰዎች ጥቂት መሆናቸው ነው፡፡ “ይሄ ለማምረትም ሆነ ለገበያ ለማቅረብ እርካሽ የሚባል ኤርክራፍት አይደለም” የሚሉት ሮበርት ማን፤ “አዲሱ በራሪ መኪና አንዳንድ ለየት ያሉ ነገሮች አሉት፤ እናም ጥቂት ሽያጮች ያገኛል፡፡ ነገር ግን ጥያቄው ምርቱ ትርፋማ ሊሆን ይችላልን? የሚለው ነው፡፡ ተንታኙ ባለሙያ እንደሚሉት ለዚህ ባለክንፍ አውቶሞቢል የበጠ የገበያ ስፍራ የሚሆነው የአሜሪካ ምዕራባዊ ክፍል ነው፡፡ ለምን ቢሉ? በዚያ አካባቢ ሰዎች ረዥም ርቀት ከማሽከርከር ይልቅ መብረርን የሚመርጡ በመሆናቸው ነው፡፡

Terrafugia በበራሪ መኪናዎች ላይ መስራት ከጀመረ ስድስት ዓመት ገደማ ይሆነዋል - ከ2006 ዓ.ም አንስቶ ማለት ነው፡፡ ባለፈው ዓመት በጋ ላይ ኩባንያው ምርቱን በ2011 ዓ.ም (እ.ኤ.አ) ለማቅረብ የገባውን ቃል ለማዘግየት ተገዶ ነበር - በዲዛይን ተግዳሮቶች እና የመለዋወጫ እቃዎች አቅርቦት ችግር ጋር በተያያዘ ማለት ነው፡፡ በራሪው ተሽከርካሪ በኒውዮርክ ለእይታ ሲቀርብ የደንበኞችንና የኢንቨስተሮችን ዓይን እንደሚስብለት ኩባንያው ተስፋ አድርጓል፡፡ “ራሳችንን ለአውቶሞቲቩ ዓለም እንደ አዋጭ ኩባንያ እያስተዋወቅን ነው” ብለዋል - የኩባንያው ቃል አቀባይ፡፡

ኮሎኔል አወል አብዱራሂም በኢትዮጵያ እግር ኳስ እድገት ላይ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ለማበርከት ባመነጩት ሃሳብ የደደቢት ስፖርት ክለብን በ1989 ዓ.ም መስርተዋል፡፡ ታዳጊ ህፃናትን በማሰልጠን ከ16 ዓመት በፊት የተጀመረው ክለቡ ገና በወጣትነት እድሜው በኢትዮጵያ እግር ኳስ ጉልህ አስተዋፅኦ ማበርከቱ እንደሚያኮራቸው ኮ/ል አወል አብዱራሂም ይናገራሉ፡፡ በሚቀጥሉት አምስት አመታት ውስጥ የአፍሪካ ክለቦች ሻምፒየንስ ሊግ ዋንጫን አሸንፎ በዓለም ክለቦች ዋንጫ ላይ አፍሪካን ለመወከል እንዲበቃም ምኞት አላቸው፡፡ ደደቢት በኢትዮጵያ ክለቦች ከፍተኛ ውድድር የሆነውን ፕሪሚዬር ሊግ መሳተፍ ከጀመረ ዘንድሮ ገና በአራተኛው የውድድር ዘመኑ ላይ ቢሆንም፤ በሊጉ የሻምፒዮናነት ፉክክር ከሚጠቀሱት 3 ክለቦች አንዱ ሆኗል፡፡ ለወቅቱ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን 9 ተጨዋቾች በማስመረጥም ግንባር ቀደሙ ነው፡፡

የደደቢት የስፖርት ክለብ ስለሚገኝበት ወቅታዊ ሁኔታ፤ በወደፊት አቅጣጫዎቹ እና ተያያዥ ጉዳዮች ዙርያ ከክለቡ መስራችና ፕሬዝዳንት ኮሎኔል አወል አብዱራሂም ጋር ስፖርት አድማስ ቃለምምልስ አድርጓል፡፡ - የደደቢት ስፖርት ክለብ የተመሰረተበትን 16ኛ ዓመት ከሳምንት በፊት አክብሯል፡፡ ክለቡ በዚህ ጊዜ ያለፈባቸውን ጉልህ ሂደቶች እና ዛሬ የደረሰበትን ደረጃ እንዴት ይመለከቱታል? የደደቢት የስፖርት ክለብ በወቅታዊ የእግር ኳስ እንቅስቃሴው ጥሩ ደረጃ ላይ ነው፡፡ በተለያዩ የስልጠና ፕሮጀክቶች እና ውድድሮች የሚሳተፉ የክለቡ ቡድኖች የሚያበረታታ ውጤት እያሳዩ ናቸው፡፡ የቡድኖቹን ጥንካሬ እና ውጤታማነት በብዙ መልክ መግለፅ ይቻላል፡፡ በፕሪሚዬር ሊግ ተወዳዳሪ የሆነው ዋናው ቡድን የውድድር ዘመኑ ሲጋመስ በደረጃ ሰንጠረዥ አናት ላይ ሆኖ ነው፡፡ ይህ ውጤት ድንገተኛ ክስተት አይደለም፡፡ ክለቡ በፕሪሚዬር ሊግ በተሰለፈባቸው ባለፉት ሶስት የውድድር ዘመናት ለሻምፒዮናነት ከሚፎካከሩ ሶስት ክለቦች አንዱ ነበር፡፡ ዘንድሮም ይህን ብቃት መቀጠሉ የሚያኮራ ነው፡፡ ክለባችን በአደረጃጀቱ በተለይ በተጨዋቾች ስብስቡ አስፈላጊው ጥራት እንዲኖር ያተኩራል፡፡

እንግዲህ ከ16 አመት በፊት ክለቡ ሲመሰረት የተነሳንበት መሰረታዊ አካሄድ ከ10 አመት በታች የሆኑ ህፃናትን አሰባስቦ በማሰልጠን ነበር፡፡ በታዳጊ እና ወጣት ተጨዋቾች ማሰልጠኛ ፕሮጀክቶች ላይ በትኩረት በመስራት ጥራት ያላቸውን ተጨዋቾች ማፍራት አቅደን ነበር የተነሳነው፡፡ አንድ ክለብን በብቁ የተጨዋቾች ስብስብ እና ጥራት ባለው አደረጃጀት ለማቆም ከስር ተነስቶ በረጅም ጊዜ እቅድ መስራቱ አስፈላጊ ነው፡፡ ከ16 አመት በፊት ክለቡን የጀመርንበት የ U-10 ቡድን በሚያገኘው ስልጠና በአገሪቱ ምርጥ ደረጃ ላይ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ስልጠናችንን ወደ U-15 በማሳደግ ቀጠልን፡፡ በ1992 ዓ.ም የደደቢት እግር ኳስ ክለብ በታዳጊ እና ወጣት ቡድኖቹ በአገር አቀፍ ውድድሮች ጥሩ ተፎካካሪ ሊሆን ከመቻሉም በላይ በስብስቡ ጥራት እንደሞዴል ሊታይ የበቃ ነበር፡፡ የደደቢት U-17 ቡድን በነበረው የስብስብ ጥራት እና የተሟላ የብቃት ደረጃ ለአዲስ አበባ ሞዴል ሆኖ ከመታየቱም በላይ የከተማ መስተዳደሩን ፈቃድ አግኝቶ በአገር አቀፍ ውድድር ተሳታፊ ሊሆን የበቃ ብቸኛው የግል ፕሮጀክት ነበር፡፡ እንግዲህ ከክለቡ ምስረታ በኋላ ለሰባት ዓመታት በታዳጊ እና ወጣት ቡድኖች ሰፊ ስራ በማከናወን ቆይተናል፡፡ ከዚያ በኋላ በተመሰረተው ዋና ቡድን 2000 ዓ.ም ላይ ወደ ብሄራዊ ሊግ ውድድር ገባን፡፡ ክለቡን ከመሰረትን ከ12 ዓመት በኋላ ደግሞ ፕሪሚዬር ሊጉን ለመቀላቀል በቅተናል፡፡ ክለቡ የሚያንቀሳቅሳቸው የታዳጊ እና ወጣት ተጨዋቾች ማሰልጠኛ ፕሮጀክቶች ስኬታማ ናቸው?

ደደቢት ብቁ እና ምርጥ ተጨዋቾችን ከተለያዩ ክለቦች በከፍተኛ ገንዘብ አሰባስቦ የተጠናከረ ክለብ የሚባልም ነገር አለ? የተጨዋቾች ግዢ በአንድ ክለብ አወቃቀር የሚያስፈልግ አሰራር እንደሆነ እናውቃለን፡፡ በተጨዋቾች የዝውውር ገበያ ማንም ክለብ የሚሳተፈው በቡድኑ የተጨዋቾች ስብስብ ያሉ ክፈተቶችን ለመሙላት እና ልምዱን ለማጠናከር ነው፡፡ የደደቢት ስፖርት ክለብ የተጨዋቾች ግዢን እንደ ዋና ፖሊሲው ተንቀሳቅሶ የሚሰራበት አይደለም፡፡ የእግር ኳስ ክለባችንን ለመገንባት የምንከተለው ፖሊሲ ከምስረታችን ጀምሮ በሰራንባቸው የታዳጊ እና ወጣት ተጨዋቾች ማሰልጠኛ ፕሮጀክቶች የማያቋርጥ እድገት ላይ የተመሰረተ መሆኑ መታወቅ ይኖርበታል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በደደቢት የስፖርት ክለብ 150 ስፖርተኞችን ይዘናል፡፡ በU-15 ደረጃ በአርባ ምንጭ እና በመቀሌ በሚገኙ ሁለት የፕሮጀክት ማእከሎች 55 ስፖርተኞች በመያዝ እየሰራን ነው፡፡ ለዋናው ቡድን መጋቢ እንደሚሆን የታመነበት እና በU- 17 ደረጃ የምናንቀሳቅሰው ፕሮጀክት 25 ስፖርተኞችን በማቀፍ እየሰራ የሚገኘው በአዲስ አበባ ነው፡፡

ባለፈው አመት በስራ አጋጣሚ ወደ ጋና ሄጄ ባገኘሁት ሃሳብ ደግሞ የተስፋ ቡድንም መስርተናል፡፡ በU-19 ደረጃ የምናሰለጥንበት ይህ የተስፋ ቡድን ለዋናው የቡድን መዋቅር መሰረት መሆኑን በማመን ያስጀመርነው ነው፡፡ ይህን የተስፋ ቡድን በU- 17 ደረጃ ከምንሰራበት የቢ ቡድን ጋር በማቀናጀት የምናንቀሳቅሰው ነው፡፡ በቢ ቡድን ያሉ ተጨዋቾችን በቀጥታ ወደ ዋናው ቡድን በማሳደግ መስራት ውጤታማ አያደርግም፡፡ ስለዚህም በU-19 የምንሰራበትን የተስፋ ቡድኑን ወደ ዋናው ቡድን ለምናሳድጋቸው ተጨዋቾች እንደመሸጋገርያ የምንጠቅምበት ይሆናል፡፡ በዚህ የተስፋ ቡድን ፕሮጀክት በየዓመቱ ያለማቋረጥ ዋናውን ቡድን የምንገነባበትን ሂደት በጥሩ መሰረት ይዘነዋል፡፡

ለክለቡ መጠናከር የሚያግዙ ወጣት ተጨዋቾች ከማፍራት ባሻገር በአገሪቱ ከፍተኛ የሊግ ውድድር ተሳታፊ በሆኑ ክለቦች ለመጫወት የሚበቁ ተጨዋቾችን በዝውውር ገበያው በማቅረብ ገቢ ለማግኘት ተስፋ ያደረግንበት እንቅስቃሴም ነው፡፡ አርባ ምንጭ ላይ በምንሰራው የU- 17 ፕሮጀክት ደግሞ ከሁለት ዓመት በኋላ ለፕሪሚዬር ሊግ የሚመጥኑ ተጨዋቾችን እንደምናወጣበት በእርግጠኝነት እናገራለሁ፡፡ በአጠቃላይ ከእነዚህ የታዳጊ እና ወጣት ተጨዋቾች ፕሮጀክቶች ወደ ሌሎች ክለቦች ያዘዋወርናቸውን ስፖርተኞች ባይኖሩም ዋና ቡድናችንን በእነዚህ ፕሮጀክቶች መገንባቱ በገሃድ የሚታይ ጥቅም ነው፡፡ ዘንድሮ በፕሪሚዬር ሊግ በሚወዳደረው ዋናው ቡድናችን ላለፉት አራት አመታት በማሰልጠን ያፈራናቸውን 7 ተጨዋቾች አስገብተናል፡፡ ደደቢት የስፖርት ክለብ በአደረጃጀቱ የሚያስፈልጉትን መሰረተ ልማቶች አሟልቷል ?ወይንስ ችግሮች አሉ? እንግዲህ ለዋናው ቡድን የስፖርት ክለቡ የተጨዋቾች ካምፕ አለው፡፡ የትጥቅ አቅርቦቱም የተሟላ ነው፡፡ በመሰረተ ልማት ደረጃ ለደደቢት ክለብ ትልቁ ችግር የራሱን የልምምድ ሜዳ አዘጋጅቶ በተማከለ ሁኔታ አለመንቀሳቀሱ ነው፡፡ ደደቢት የራሱ ሜዳ የለውም ማለት ያሳዝናል፡፡ በፋይናንስ ያለው አቅም ደካማ መሆን ያለበትን የሜዳ ችግር ለመቅረፍ ዋና እንቅፋት ሆኖበታል፡፡ በእርግጥ ክለቡ ከአዲስ አበባ መስተዳደር የልምምድ ሜዳውን የሚያቋቁምበት መሬት አግኝቷል፡፡ የከተማዋ ከንቲባ አቶ ኩማ ደመቅሳ እና የመስተዳደሩ አመራሮች የሰጡን ትብብር ከፍተኛ ምስጋና የሚገባው ነው፡፡ በደደቢት የእግር ኳስ ክለብ ስር እዚህ አዲስ አበባ ላይ የሚሰሩ አራት ቡድኖች አሉ፡፡ በአርባምንጭ ያለው ፕሮጀክታችን የሜዳ ችግር የለበትም፡፡

የአርባ ምንጭ መስተዳድር የክለባችን ፕሮጀክት በመደገፍ በከተማዋ የሚገኝ ስታድዬም ቅድሚያ ተሰጥቶን ለፕሮጀክታችን እንደሜዳ እንድንገለገልበት በመፍቀዱ በዚያ ችግር የለብንም፡፡ በመቀሌ ፕሮጀክትም ከክልሉ መስተዳድር ተመሳሳይ ድጋፍ እያገኘን ነው፡፡ እዚህ አዲስ አበባ ተቀማጭ የሆኑት አራት ቡድኖች ግን መደበኛውን የስልጠና እና የልምምድ ፕሮግራም በአራት የተለያዩ ቦታዎች ተዘበራርቀው እየተገለገሉ ናቸው፡፡ እነዚህ አራት ቡድኖች ለሚሰሩባቸው ሜዳዎች ኪራይ በምንከፍለው ገንዘብም ብዙ ወጭ እያወጣን ነው፡፡ አሁን ዋናው ቡድን የሚሰራውየመድን ክለብን ሜዳ ተከራይቶ ነው ፡፡ በአንድ ልምምድ እስከ 700 ብር እየከፈለ ነው፡፡ የተስፋ ቡድናችን ደግሞ በፌደራል ፖሊስ ሜዳ ይገለገላል፡፡ የሴቶች ቡድኑ በህንፃ ኮሌጅ ሜዳ እየሰራ ነው፡፡ ሌላው የፕሮጀክት ቡድን ደግሞ የሚጠቀመው የቀበሌ ሜዳ ነው፡፡ በእነዚህ አራት የተለያዩ ሜዳዎች አራቱ ቡድኖች ተዘበራርቀው መስራታቸው በሜዳ ክራይና በትራንስፖርት ወጪ የስፖርት ክለቡ እየተቸገረ ነው፡፡ ከገንዘብ ወጪውም ሌላ ብዙ እድገትን የሚያስተጓጉሉ ችግሮች እየገጠሙን ነው፡፡ ዋናው ቡድን ከሚሰራበት የመድን ሜዳ በቀር በሌሎቹ ሜዳዎች የተመቹ አይደሉም፡፡ በፈለግነው ሰዓት እና ፕሮግራም ሜዳዎቹን ስለማንጠቀምም ተሰቃይተናል፡፡ የማይመቹት ሜዳዎች በየቡድኑ የተያዙ ተጨዋቾችን ለጉዳት መዳረጋቸው የሚያስቆጭ ነው፡፡ እናም በደደቢት ክለብ ላይ በመሰረተ ልማት ረገድ አሳሳቢው ችግር የራሳችን ሜዳ ሊኖረን አለመቻሉ ነው፡፡ ይሄን ችግር በቀጣይ ዓመት ለመፍታት ፍላጎት አለን፡፡ የአዲስ አአባ መስተዳደር መሬት በሊዝ ሰጥቶናል፡፡ መሬቱን በሊዝ መግዛት ቢኖርብንም 7.5 ሚሊዮን ብር መክፈል ባለመቻላችን እስካሁን አልተረከብነውም፡፡ እስከ ዓመቱ መጨረሻ ከፍለን ካልተረከብነው ሊወሰድብን ይችላል፡፡

የየፕሮጀክቶቹን እንቅስቃሴ ውጤታማ ለማድረግ፤ በየደረጃው የሚወዳደሩ የክለቡን ቡድኖች ማንቀሳቀሻ በጀት ለመመደብ እንዲሁም ክለቡን በመሰረተ ልማት ለማጠናከር በቂ የፋይናንስ አቅም ያስፈልጋል፡፡ የደደቢት ስፖርት ክለብ የሚተዳደርበት አቅም ምን ደረጃ ላይ ነው? የደደቢት ስፖርት ክለብ በቂ የፋይናንስ አቅም የለውም፡፡ በየፕሮጀክቱ የምናደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ውጤታማነት፤ በዋናው ቡድን የፕሪሚዬር ሊግ ጠንካራ ተፎካካሪነት ፤ እንዲሁም በአፍሪካ ደረጃ ባሳየነው አቅም እና ለብሄራዊ ቡድን ከፍተኛ ብዛት ያለውን የተጨዋቾች አስትዋፅኦን በመመልከት ክለቡ በከፍተኛ ፍጥነት እድገት ላይ እንደሚገኝ ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ ይሁንና እነዚህ አበረታች እንቅስቃሴዎችን በዘላቂነት ለመቀጠል የሚያስፈልገው አስተማማኝ ፋይናንስ ግን የተጠናከረ አይደለም፡፡ ከፈጣኑ የክለባችን እድገት ተያይዞም የፋይናንስ ፍላጐቱ እየጨመረ ይሄዳል፡፡ የደደቢት ስፖርት ክለብ ከ16 አመታት በፊት ከተመሰረተ አንስቶ ዛሬም ድረስ የራሱ ገቢ የለውም፡፡ የክለቡ የፋይናንስ አቅም በአጋርነት አብረውን በሚሰሩት ግለሰቦች እና አጋር ድርጅቶች ድጋፍ የተወሰነ ነው፡፡ ክለቡ ሲመሰረት ከተወሠኑ ደጋፊዎች የምናገኘው ድጋፍ በሺዎች የተወሰነ ነበር፡፡ በየውድድር ዘመኑ ግን ክለቡ እያደገ ከመምጣቱ፤ በአህጉራዊ ውድድሮች ተሳታፊ ከመሆኑ እና በተለያዩ ፕሮጀክቶች በስፋት በመንቀሳቀስ ላይ መገኘቱ ከደጋፊዎቻችን በሚሊዮን የሚገመት መዋእለንዋይ የምንፈልግበት ደረጃ ላይ አድርሶናል፡፡

ባለፉት አራት የውድድር ዘመናት አጋር ድርጅቶች በየጊዜው በሚያደርጉልን መዋጮ በጀታችንን በመሸፈን ስንሰራ ቆይተናል፡፡ በ1999 ዓ.ም ክለቡ 10ኛ ዓመቱን ሲያከብር አንዳንድ ድርጅቶች እና ኩባንያዎች በገንዘብ መዋጮ ለክለቡ ድጋፍ መስጠት ጀምረዋል፡፡ የመጀመርያውን ድጋፍ ያገኘነው ለኢትዮጵያ ስፖርት ማደግ ከፍተኛ ፍላጎት ካላቸው ክቡር ሼህ መሃመድ አላሙዲ ነው፡፡ ከእርሳቸው ከ2001 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 18 ሚሊዮን ብር አግኝተናል፡፡ ከዚያ በኋላ ከመከላከያ ድርጅቶች ጋር የምንሰራበትን ሁኔታ በመፍጠር ስንቀሳቀስ ቆይተናል፡፡ ዛሬ እነዚህ የመከላከያ ድርጅቶች የክለቡ ግንባር ቀደም አጋሮች ናቸው፡፡ በተለይ ባለፉት ሁለት ዓመታት ድርጅቶቹ የክለቡ የፋይናንስ ደጀን ነበሩ ለማለት ይቻላል፡፡ ከመከላከያ ድርጅቶቹ ሲሰጥ የቆየው የበጀት ድጋፍ በስፖንሰርሺፕ ስምምነት አይደለም፡፡ ለክለቡ ባላቸው ተቆርቋሪነት የክለቡ ራዕይ ዘላቂነት እንዲኖረውና ለአገር የሚሆነውን አስተዋፅኦ በማመናቸው የበጀት ድጋፍ እያደረጉልን ይገኛል፡፡ የመከላከያ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝና የመከላከያ ብረታ ብረት ኢንጅነሪኒግ ኮርፖሬሽን ዋናዎቹ የክለቡ አጋሮች ናቸው፡፡ እንግዲህ ክለቡ ለዘንድሮ የውድድር ዘመን የያዘው በጀት 16 ሚሊዮን ብር ነው፡፡ ከዚህ በጀት 80 በመቶው የተሸፈነው በእነዚህ ድርጅቶች ነው፡፡

አሁን የክለቡ አመራሮች የክለቡን የፋይናንስ አቅም ለማጠናከር በሚያስችል አቅጣጫ ለመስራት ወስነናል፡፡ ክለቡ በፋይናንስ አቅም ተዳክሞ ከሚገኝበት የዕድገት አቅጣጫ እንዳይሰናከል አጋሮቻችን የዚህ እቅድ ዋነኛ ሃይል ናቸው፡፡ በዚህ መሰረት በቀጣይ የውድድር ዘመን የደደቢት ስፖርት ክለብን በባለቤትነት የሚያስተዳድር ራሱን የቻለ ኩባንያ ለማቋቋም ወስነናል፡፡ ይህ አቅጣጫ የክለቡን የፋይናንስ አቅም በማጠናከር ለህልውናው ወሳኝ ምእራፍ መሆኑን አምነንበታል፡፡ የመከላከያ ድርጅቶች ከደደቢት ጋር በአጋርነት መስራታቸው ከመከላከያ ክለብ የጥቅም መጋጨትን የሚፈጥር ሁኔታ አይደለም ወይ ? የመከላከያ ክለብ ባለቤትነት የሚኒስትር መስሪያ ቤቱ እና ሠራዊቱ ነው፡፡ ባለኝ መረጃ መሠረት ክለቡ ከሠራዊቱ በሚገኝ መዋጮ እና በሚኒስትር መስሪያ ቤቱ በሚለቀቅ በጀት የሚንቀሳቀስ ነው፡፡ እኔው ራሴ በመከላከያ ሚኒስትር ሰራተኛነት እስከ ባለፈው ዓመት በቆየሁባቸው ዓመታት ለመከላከያ ክለብ በየወሩ ከደሞዜ መዋጮ ሳደርግ ቆይቻለሁ፡፡ በአጠቃላይ የደደቢት እና የመከላከያ ክለቦች ከፋይናንስ ድጋፎች ጋር በተያያዘ የገቡት የጥቅም ግጭት ሆነ ቅራኔ ያለ አይመስለኝም፡፡ የመከላከያ ሚኒስትር እና ሰራዊቱ ለደደቢት ክለብ የሚከፍሉት መዋጮ የለም፡፡

የደደቢት ስፖርት ክለብ አጋሮች የሆኑት የመከላከያ ድርጅቶች እንጂ የመከላከያ ሚኒስትር እና ሰራዊቱ አይደለም፡፡ በእርግጥ ደደቢት በስታድዬም በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ክለቡን ለመደገፍ የሚመጡ የሠራዊቱ አባላት ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ይህ ግን እንደማንኛውም የስፖርት ማህበረሰብ ቡድኑን በማድነቃቸው ብቻ የሚያደርጉት እንጅ የክለቡ ባለድርሻ ሆነው አይደለም፡፡ ክለቡ የገቢ ምንጮቹን ለማስፋት የሚያደርጋቸው ጥረቶች በምን ደረጃ ላይ ናቸው? በአገራችን እግር ኳስ ላይ የተጋረጠ አንዱ ትልቅ ችግር የስፖርት ስፖንሰርሺፕ አሠራር አለመስፋፋቱ ነው፡፡ የማልያ ስፖንሰር ሺፕ እንኳን አግኝቶ የክለብን የገቢ አቅም መጨመር ብዙ የተጠናከረ አይደለም፡፡ ደደቢት በማልያ ስፖንሰርሺፕ በፈርቀዳጅነት ሊታይ የሚገባ ጥረት አድርጓል፡፡ ለሁለት አመት በሚቆይ የውል ስምምነት የደደቢት የማልያ ስፖንሰር የሆነው የሳምሰንግ ኩባንያ ነው፡፡ ስምምነቱ ከጅምሩ ለክለቡ 1 ሚሊዮን 400ሺ ብር ያስገኘ ነው፡፡ በማልያ የስፖንሰርሺፕ ድጋፍ የሳምሰንግ ኩባንያ የሚከፍለን ገንዘብ በ300ሺ እንዲጨምር አቤቱታ አቅርበን ነበር፡፡

በጎ ምላሽ አግኝቶ ከማሊያ ስፖንሰር ሺፕ የምናገኘው ገቢ 1 ሚሊዮን 700ሺ ብር ደርሷል፡፡ የማልያ ስፖንሰርሺፕ ድጋፉን ያገኘነው በኢትዮጵያ የሳምሰንግ ኩባንያ ወኪል ሆኖ በሚሰራው የጋራድ ኩባንያ በኩል ነው፡፡ የስፖንሰርሺፕ ውሉን በፈርቀዳጅነት ስንጀምረው በቂ ጥቅም አግኝተንበት አይደለም፡፡ ከኩባንያው ጋር በዘላቂነት የምንሰራበትን መግባባት ለመፍጠር ብለን የፈፀምነው እንደሆነ መታወቅ አለበት፡፡ በርግጥ በመደበኛው አሠራር የማልያ ስፖንሰሩ ትጥቆቹን በሙሉ ለክለቡ ማቅረብ ነበረበት፡፡ እኛ ጅምር የስፖንሰርሺፕ ድጋፉ ቀጣይነት እንዲኖረው ለማበረታታት ብለን ሙሉውን ትጥቅ በመግዛት በመጠቀም ላይ ነን፡፡ ከሚቀጥለው የውድድር ዘመን ጀምሮ ይህን የማልያ ስፖንሰርሺፕ በአዲስ የውል ስምምነት ለማሻሻል እንፈልጋለን፡፡ የሳምሰንግ ኩባንያ ኃላፊዎችም ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀውልናል፡፡ በተለያዩ መንገዶች ሌሎች አጋር ድርጅቶችን በስፖንሰርሺፕ ድጋፍ በዙሪያችን እንዲሰባሰቡ ብንፈልግም በኢትዮጵያ ስፖርት በጋራ ተጠቃቅሞ የመስራት አካሄድ ባለመጠናከሩ አልተሳካልንም፡፡

በርካታ ኩባንያዎችና ድርጅቶች የስፖንሰርሺፕ ስምምነት ለጋራ ጥቅም ይሆናል የሚል እምነት የላቸውም፡፡ የስፖንሰርሺፕ ድጋፍን ከልመና ጋር የምናያይዝበት ደካማ አስተሳሰብ አለ፡፡ የገቢ ምንጮችን የሚያጠናክሩ የስፖንሰር ሺፕ ድጋፎችን ለማግኘት የአገሪቱ እግር ኳስ ደረጃ አለማደግ እንደ ዋና ምክንያት ሆኖ ይጠቀሳል፡፡ ክለቦች በአህጉራዊ ውድድሮች በየውድድር ጠንካራ ተሳትፎና ውጤት እያገኙ መምጣታቸው የብሔራዊ ቡድኖች በትልልቅ አህጉራዊና ዓለም አቀፍ ውድድሮች በዘላቂ ሁኔታ መሳተፋቸው የስፖንሰሮችን ፍላጎት ሊፈጥር እንደሚችል ግን ተስፋ እያደረግን ነው፡፡ መጭው ጊዜ በስፖንሰርሺፕ ድጋፎች የክለቦችን የገቢ ምንጭን ለማስፋት ተስፋ አስቆራጭ አይደለም፡፡ ደደቢት በፌደሬሽኑ በኩል በሚያጋጥሙ ምቹ ያልሆኑ አሰራሮችን በተደጋጋሚ በመጋፈጥ፤ በመቃወም እና ጠንካራ አቋሞቹን በማንፀባረቅ ይታወቃል፡፡ በኢትዮጵያ የክለቦች ውድድር ፕሮፌሽናል የሊግ ኮሚቴ አለመመስረቱን በተመለከተ ምን አስተያየት ይኖርዎታል? ደደደቢት ብሄራዊ ሊግ መወዳደር ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ከፌደሬሽኑ ምቹ ያልሆኑ አሰራሮች ጋር ፊት ለፊት ሲጋጠም ቆይቷል፡፡ ክለቡ የማያምንበትን አሰራር በመተቸት እና አቋሙን በመግለፅ የሚታገል ነው፡፡

በማንኛውም ሁኔታ ለምናቀርባቸው ጥያቄዎች ምላሽ ባናገኝም ለመመርያ ተገዢ በመሆን አቋማችንን ከመግለፅ ወደኋላ አንልም፡፡ የሊግ ኮሚቴ ፌደሬሽኑን ባቀፈ ኮሚቴ የሚሰራበትን ሁኔታ በጣም የምንቃወመው ነው፡፡ የአንድ አገር ሊግ ውድድር በፕሮፌሽናል መካሄድ ካለበት የኮሚቴ አሰራር አይሆንም ፡፡ የፕሪሚዬር ሊግ ውድድርን ተሳታፊ ክለቦች በባለቤትነት ይዘውት እንደኩባንያ መተዳደር አለበት፡፡ በዚህ አይነት አሰራር አለመወዳደራችን ብዙ ነገር እያሳጣን ነው፡፡ በመጀመርያ ደረጃ የሊግ ውድድሩ ለክለቦች በቂ የገቢ አቅም እየፈጠረ አይደለም፡፡ የክለቦች የሜዳ ገቢ እጅግ አነስተኛ ነው፡፡ በዚያ ላይ ፌደሬሽኑ ተገቢ ያልሆነ ድርሻ ይወስዳል፡፡ ከሜዳ ገቢ የፌደሬሽኑ ድርሻ 32 በመቶ መሆኑይህ በፍፁም ትክክል አይደለም፡፡ በዚህ አይነት ዓመቱን በሙሉ ከሜዳ የምንስበስበው ገቢ የአንድ ተጨዋች ደሞዝ እንኳን የሚሸፍን አይደለም፡፡ ፕሮፌሽናል የሊግ አመራርን በኢትዮጵያ የክለቦች ውድድር መከተል ጊዜ ሊሰጠው አይገባም፡፡ የሊጉ ውድድር አብይ ስፖንሰር በማግኘት ከፍተኛ ገቢ ማምጣት አለበት፡፡ ለተወዳዳሪ ክለቦች በቂ የገቢ ድርሻ የማያስገኝ ውድድር ምንም አይነት እድገት ሊኖረው አይችልም፡፡ በአጠቃላይ ክለቦች የተለያዩ የገቢ ምንጮች ሊፈጥሩ የሚችሉበትን አሰራር ዘርግቶ መስራት ያስፈልጋል፡፡ ከ4 ዓመት በፊት በክለቦች ብቻ የሚመራ ፕሮፌሽናል የሊግ ኮሚቴ ለማቋቋም ክለቦች አቋም ነበራቸው ፡፡ ይህ አቋም እስከዛሬ ለምን ተግባራዊ ማድረግ እንዳልተቻለ አይገባኝም፡፡

አርቲስት ፍቃዱ አያሌው ባጋጠመው የነርቭ ህመም ወደ ታይላንድ ባንኮክ ሄዶ ህይወቱን የሚታደግ ህክምና እንዲያገኝ በህክምና ባለሙያዎች ተወሰነ፡፡ የሰዓሊው ጓደኖችና ወዳጅ ዘመዶች በውጭ አገር በሚያደርገው ህክምና ጥሪ ለማሰባሰብ እያስተባበሩ ናቸው፡፡ ሰዓሊ ፍቃዱ የነርቭ ህመሙ ለመታከም አዲስ አበባ ለሚገኘው የሚዮንግ ሰንግ ሆስፒታል ቆይታ ቢኖረውም ሙሉ ለሙሉ ሊፈወስ አልቻለም፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የስነጥበብ ትምህርት ቤት በማዕረግ የተመረቀው አርቲስት ፍቃዱ አያሌው በዳንዲቦሩ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመምህርነት አገልግሏል፡፡ለሰዓሊው የውጭ ሀገር ህክምና ድጋፍ ለሚያደርጉ ሁለት የሞባይል ስልክ ቁጥሮች 0911742168 እና 0919193132 መጠቀም የሚቻል ሲሆን በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የአካውንት ቁጥር 1000031068 437 መላክ እንደሚቻል አስተባባሪዎቹ ገልፀዋል፡፡

የኢትዮጵያ የዜማ አባት የሚባለው ቅዱስ ያሬድ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች እየተዘከረ ሲሆን አዲስ አበባ የሚገኘው የደብረ ይባቤ ቅዱስ ያሬድ ቤተክርስትያን፤ የዜማ አባቱ የተወለደበትን 1500ኛ የልደት በዓል ነገ ከረፋዱ አራት ሰዓት እንደሚያከብር አስታውቋል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን አዲሱ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ እንደሚገኙ በሚጠበቅበት በዓል፤ “በቅዱስ ያሬድ ታሪክ እና ሥራዎች” ላይ ውይይት ይካሄዳል ተብሏል፡፡

ፒያሳ አካባቢ የሚገኘው ኤልቤት ሆቴል ከዚሁ ልደት ጋር በተያያዘ የቅዱስ ያሬድ ዜማዎች በተባበሩት መንግስታት የባሕል ቅርስ ሆነው መመዝገባቸውን አስመልክቶ ዝግጅት እንደሚያቀርብ አስታወቀ፡፡ ዛሬ ከቀኑ 9 ሰዓት በሚቀርበው ዝግጅት፤የቅዱስ ያሬድ ቤተክርስትያን ዘማሪዎች ያሬዳዊ ዜማ እንደሚያቀርቡ ተገልጿል፡፡

በሻሸመኔ ከተማ ጥበብ አፍቃሪዎች የተቋቋመው ከ “አድማስ ፊት” የኪነጥበብ ማህበር 42ኛ ዝግጅቱን ነገ ከሰዓት በኋላ በከተማዋ ሁለገብ አዳራሽ እንደሚያቀርብ ገለፀ፡፡ በዚህ ጥበባዊ ዝግጅት ላይ አርቲስት ታምሩ ብርሃኑ እና ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ልምዳቸውን ለታዳሚዎች እንደሚያካፍሉ ማህበሩ አስታውቋል፡፡

በጋዜጠኛና ደራሲ በኃይሉ ገብረእግዚአብሔር የተፃፈው “ኑሮና ፖለቲካ” የወጎች መጽሐፍ ሁለተኛ ቅጽ ለንባብ በቃ፡፡ አርባ ወጎችን የያዘው መፅሃፉ፤160 ገፆች ያሉት ሲሆን ለአገር ውስጥ 35 ብር፣ ለውጭ አገራት 15 ዶላር እየተሸጠ ነው፡፡ በርካታ ወጎች የተካተቱበት የመጀመርያው ቅጽ አምና በታሕሳስ ወር መውጣቱ ይታወሳል፡፡

  • ፊያሜታ

አነበብኩት፡፡ ደግሜ አነበብኩት፡፡ መላልሼ አነበብኩት፡፡ ለምን እንደሆነ አላውቅም ያነበብኩትን ነገር ለማመን አቃተኝ፡፡ ሉጫ ፀጉራቸው እርስ በርሱ ተገማምዶ ጀርባቸው ላይ የወደቀ፣ ወዝ የጠገበ ላመነት ያገለደሙ፣ እህል የራቀው አንጀታቸውን በሰንሰለት ሸብ ያደረጉ፣ ፂማቸውን ያንዠረገጉ፣ ከአለም ተነጥለው በራቸውን የዘጉ…እንዲህ ያሉ መናኝ ---- በአሉ ግርማን ማሰብ አቃተኝ፡፡ “አበቃ” ብሎ በዘጋው ጦሰኛ ስራው ሰበብ፣ የእሱም ነገር እንዳበቃ ከተነገረለት፤ ከዚያኛው በአሉ የቀጠለ ሌላ በአሉ አልመጣልህ አለኝ፡፡ ከተቋጨ ደራሲነትና ጋዜጠኝነት የቀጠለውን የበአሉ መናኝነት ማሰብ ተሳነኝ፡፡ ባለፈው ሰኞ ምሽት አንድ ወዳጄ በፌስቡክ የላከልኝ “ጉድ” “በአሉ ግርማ በጣና ደሴት ገዳማት የመናኝ ህይወት እየገፋ ተገኘ” የሚል ነበር፡፡ ይህን “ጉድ” ለማመን ቸግሮኝ ጥቂት እንደተወዛገብኩ፣ ነገርዬው “የሚያዝያ ልግጥ” (April the fool) ሊሆን እንደሚችል ገመትኩ፡፡

ይሄን ጉድ ለላከልኝ ወዳጄ አጭር ምላሽ ላኩለት፡፡ “ወሩን ሙሉ “አፕሪል ዘ ፉል” አለ እንዴ?” በማለት፡፡ የወዳጄ ምላሽ ፈጣንና የበለጠ ግራ አጋቢ ነበር፡፡ “እውነቴን ነው የምልህ…አገር ምድሩ የሚያወራው እኮ ስለዚህ ነው፡፡ በአሉ ግርማ በህይወት ተገኝቷል” አለኝ፡፡ የወዳጄ እርግጠኝነት ችላ ብዬው የነበረውን ከመሸ የመጣ “ወሬ”፣ ከፍፁም ቅጥፈት ቆጥሬ እንዳላልፈው አስገደደኝ፡፡ “ጉድ ሳይሰማ ማክሰኞ አይጠባም” በሚል ሌሎች ወዳጆቼ ስለ ጉዳዩ ያውቁ እንደሆነ በዚያው በፌስቡክ ጥያቄ አቀረብኩ፡፡ “አልሰሜን ግባ በለው” አለኝ አንዱ፣ እስከዛሬ ስለ ጉዳዩ አለመስማቴን በሽሙጥ እየገለፀ፡፡ “ጀለሴ አፕሪል ዘ ፉል ነው” ሌላኛው ቀጠለ፡፡ “እኔ እኮ በ1997 ዓ.ም ነው ይሄን ነገር የሰማሁት” ይህቺኛዋ ሴት ናት፡፡ “እውነት ነው?...እባካችሁ የምታውቁ ንገሩኝ” ባህር ማዶ ያለ አብሮ አደጌ፡፡ የሚያሾፉ፣ የሚደሰቱ፣ የሚገረሙ፣ የሚደነግጡ፣ ተስፋ የሚያደርጉ…እንዲህና እንዲያ ያሉ ምላሾች አገኘሁ፡፡

ማክሰኞ ማለዳ… ሳብሰለስለው ያደረኩትን የበአሉ ጉዳይ በተመለከተ መረጃ ሊኖራቸው ይችላሉ ብዬ የማስባቸውን ሁሉ መጠየቅ ጀመርኩ፡፡ አብዛኞቹ ስለ ነገሩ ከሰሙ ቀናት ማለፋቸውን ነበር የገለፁልኝ፡፡ ይሄም ሆኖ ግን አንዳቸው እንኳን ከ’ወሬ’ነት ያለፈ ተጨባጭ መረጃ አልነበራቸውም፡፡ “ወሬ ይሮጣል” እንዲል በዕውቀቱ ስዩም፣ የበአሉም ጉዳይ በፍጥነት አገር ምድሩን ማዳረስ ያዘ፡፡ እንደዋዛ ከቤቱ ወጥቶ የውሃ ሽታ ሆኖ የቀረው በአሉ ግርማ፣ ‘ተፈፀመ’ ተብሎ ከተነገረለት ከአመታት በኋላ፣ እንደገና መቀጠሉ ተወራ፡፡ ድሮም ሞቱም ሆነ አሟሟቱ እንቆቅልሽ ነበርና፣ ብዙዎች ‘አልሞተም’ የሚለውን ፍፁም ላለማመን ምክንያት አልነበራቸውም፡፡ ተድበስብሶ ያለፈውን የበአሉ ሞትና አሟሟት በተመለከተ እርግጠኛ ሆኖ በሙሉ ልብ የሚናገር ሰው ባልተገኘባት አገር፣ የሰሞኑን ወሬ በግማሽ ልብም ቢሆን ለማመን የፈቀዱ ብዙዎችን ማግኘት ላይገርም ይችላል፡፡ ችግሩ ግን እንደ ‘ሞቱ’ ሁሉ ‘መኖሩ’ንም በእርግጠኝነት መናገር የሚችል ሰው መታጣቱ ነው፡፡ “በአሉ ግርማ በህይወት ተገኘ!” የሚለው ወሬ የሁሉም መነጋገሪያ ሆነ፡፡ “ነገርዬው ‘አፕሪል ዘ ፉል’ ነው፣ እባካችሁ ተወት አድርጉት” በማለት ህዝብን ከውዥንብር ለመታደግ የሞከሩ ቢኖሩም፣ አብዛኛው ሰው ግን ድሮም የበአሉ ነገር ያልተፈታ እንቆቅልሽ ሆኖበት ነበርና “አይሆንምን ተተሽ…” በማለት ጆሮ ነፈጋቸው፡፡ የተለያዩ ማህበራዊ ድረ-ገፆችን በመጠቀም መምጫው የማይታወቀውን ድንገተኛ ወሬ በየአቅጣጫው የሚነዙ በረከቱ፡፡ የፌስቡክ ገፆች ስለ “በአሉ ግርማ” በህይወት መኖር በሚያትቱ ወሬዎች ተጣበቡ፡፡ ወሬውን የሰሙም የተሰማቸውን አስተያየት መሰንዘር ያዙ፡፡ ተስፋ ያደረጉ የደራሲው አድናቂዎች፣ “ምናለ እውነት በሆነና የናፈቅነውን ብዕሩን መልሶ ባነሳልን!!... ምናለ ሌላ ኦሮማይ፣ ሌላ ከአድማስ ባሻገር፣ ሌላ ሀዲስ በፃፈልን” ብለዋል፡፡

የበአሉ ሞት ሳይዋጥለት የኖረ ሌላ አድናቂውም፣ ‘ሊኖር ይችላል’ የሚል ጭለማ ተስፋው ጊዜ ጠብቆ እውን ሊሆን መስሎት ክፉኛ በጉጉት ልቡ ተሰቀለ፡፡ “ልክ ጉዳዩን ስሰማ ምን ትዝ እንዳለኝ ታውቃላችሁ?... ስብሃት ገ/እግዚአብሔር በአንድ ወቅት ስለ በአሉ ሞት የተናገረው!” አለ ይሄው ተስፈኛ የበአሉ አድናቂ፡፡ (ስብሀት በአሉን ደርግ አስገድሎታል ብሎ እንደማያስብ መናገሩን ልብ ይሏል)፡፡ ለሰሞንኛው “ወሬ” ልቡን የሰጠ ሌላ የፌስ ቡክ ደምበኛ ደግሞ፣ ስለ በአሉ መኖር እናውቃለን ያሉትን የፌስ ቡክ አባላት ቅንጣት ታህል አልተጠራጠረም፡፡ “በጣም …እጅግ በጣም ደስ የሚል ዜና ነው!...በአሉ በህይወት መኖሩን ከመስማቴ በላይ፣ የመንጌን ንፁህነት ማረጋገጤ አስደስቶኛል” ይላል የዚህ ሰው አስተያየት፡፡ ወሬው ይሮጣል… ከአፍ ወደ አፍ፣ ከፌስቡክ ወደ ፌስቡክ፣ ከትዊተር ወደ ትዊተር እየተሸጋገረ ይጋልባል፡፡

ይሄኛው ከዚያኛው ተቀብሎ በፍጥነት ለባለተራው እያሻገረ፣ ያልሰማ መስማቱን፣ የሰማ ማሰማቱን ተጋበት፡፡ ወሬው በህዝቡ ዘንድ እየፈጠረ ያለው ውዥንብር ያልጣማቸው አንዳንዶች፣ “ኧረ ደግ አይደለም” ለማለት ቢሞክሩም ሰሚ አልነበራቸውም፡፡ መሰረተ ቢሱ አሉባልታ በደራሲው ቤተሰቦች ላይ የሚፈጥረውን የስነ ልቡና ተጽእኖ ቀድመው በመረዳት “ላልተጨበጠና ለማይታመን ወሬ ጆሮ አንስጥ” ለማለት የሞከሩም ነበሩ፡፡ ይሄም ሆኖ ግን ከእነዚህኞቹ ይልቅ እነዚያኞቹ የወሬው አቀጣጣዮች ነበሩ የተሰሙት፡፡ የጉዳዩን እውነትነት ለማጣራትና እርግጥም በአሉ ግርማ ገዳም ውስጥ እንደሚገኝ ለማረጋገጥ ጊዜ ያጡ ፌስ ቡከኞች፣ የደራሲውን የቀድሞ ጉርድ ፎቶግራፍ በመለጠፍ “ሆድ ማንቦጭቦጭ” ቀጠሉ፡፡ ከፎቶግራፉ ግርጌም እንዲህ ሲሉ ፃፉ- “የማይታመን፣ ግን እውነት የሆነ ነገር” ይህን መረጃ (?) አይተው የማይታመነውን ለማመን የዳዱ ቢኖሩም፣ አንዳንዶች ግን “ሙድ መያዛቸው” አልቀረም፡፡ “በአሉ ግርማ ገዳም ገባ” ላሏቸው ወዳጆቻቸው፣ “ፍሬንዶቼ…ሰውዬው እኮ ኮሚኒስት ነበር!...ወይስ…የኮሚኒዝም ርዕዮተ አለም መጨረሻው ምናኔ ነው ተባለ?” የሚል የሽሙጥ መልስ በመስጠት፡፡ “በአሉ ገዳም ውስጥ ተገኘ” በሚል የተጀመረው የሰሞኑ ወሬ ቀስ በቀስ ዘርዘር እያለ መጣ፡፡ “ነገሩ ወሬ ብቻ አይደለም” የሚል አቋም ያላቸው አንዳንዶች፣ “ወሬ”ን ወደ “ዜና” ለማሳደግ ሞከሩ፡፡

“የትኛው ገዳም” ለሚለው የህዝቡ ጥያቄ፣ “የጣና ደሴቱ ደጋ እስጢፋኖስ” የሚል ምላሽ ሰጡ፡፡ ይሄን ተከትሎ ብዙ ጆሮዎች ወደ ባህርዳር አቅጣጫ ተቀሰሩ፡፡ ብዙም ሳይቆይ ደግሞ ብዙ ጆሮዎች ብቻ ሳይሆኑ ብዙ እግሮች አባይን ተሻግረው ወደ ጣና ገዳማት ሊዘልቁና መናኙን በአሉ ሊያገኙ ወረፋ መያዛቸው ተወራ፡፡ “ይቅርታ “ተዘገበ” ነው የሚባለው አይደል?” “ተወራ” ብሎ ማለፍ፣ የድረ - ገፁን የዘጋቢነት ሚና ለማንኳሰስ መሞከር እንዳይሆን ስለሰጋሁ ነው፡፡ “አምሃሪክ ቲዩብ” የተባለው ድረ - ገፅ በወሬ ደረጃ ይናፈስ የነበረውን ጉዳይ በ”ዜና” ደረጃ አሳድጐ ነው ለአንባቢያን ያደረሰው፡፡ ድረ - ገፁ በዜና አምዱ ስር “በአሉ ግርማ ባህርዳር ውስጥ ተገኘ” በሚል ርዕስ የዘገበው መረጃ፣ ደራሲው አለም በቃኝ ብሎ በመመንኮስ ዳጋ እስጢፋኖስ ገዳም ውስጥ እግዚአብሔርን በማገልገል ላይ እንደሚገኝ “አረጋግጧል”፡፡ ይሄም ብቻ አይደለም፡፡ የበአሉ ግርማን የድርሰት ስራዎች ለሚናፍቁ፣ ባለመሞቱ ተደስተው “ከአሁን በኋላስ ይጽፍ ይሆን?” ብለው ለሚጠይቁ የዋህ አንባበያን ሌላ ተጨማሪ የምስራች እነሆ አለ፡፡

በአሉ ገዳም ከገባ በኋላም ድርሰት መፃፍ አለማቋረጡን ጠቅሶ፣ ከቅርብ አመታት ወዲህ በአንድ ወጣት ደራሲ ስም እየታተሙ ለንባብ የሚበቁትና በመቶ ሺህ ኮፒዎች እየተሸጡ ያሉት መጽሐፍት በሙሉ የበአሉ ግርማ ፈጠራዎች መሆናቸው መረጋገጡን (የፈረደበት “መረጋገጥ”) ይፋ አድርጓል፡፡ ድረ - ገፁ በአሉ ግርማ የፃፋቸውና በወጣቱ ደራሲ ስም ለንባብ የበቁ መሆናቸውን ጠቅሶ የአራት መጽሐፍትን ርዕስ ቢዘረዝርም፣ (ዘገባውን በትኩስነቱ ለህዝብ ለማድረስ ከመነጨ ጉጉት በተፈጠረ ስህተት ይመስላል) ከተዘረዘሩት የመጽሐፍት ርዕሶች መካከል አንደኛው፣ ሌላኛው መጽሐፍ ላይ የሚገኝ ገፀ - ባህሪ ስም ሆኖ ተገኝቷል፡፡ በዚህች ትንሽ ስህተት ምክንያት የድረ ገፁን ዘገባ ዋጋ ማሳጣት ያልፈለጉ አንዳንድ ቅን አንባቢዎች ታዲያ፣ “በዘገባው እንደ መጽሐፍ ርዕስ ሆኖ የተጠቀሰው ስያሜ፣ ወጣቱ ደራሲ በበአሉ ስራዎች ባገኘው ገንዘብ ያቋቋመው “ሆቴል” ስም በመሆኑ እንደ መጽሐፍ ቢቆጠር ችግር የለውም” ብለዋል፡፡ እዚህ ላይ የአንድ ወዳጄን ገጠመኝ ማንሳት ይኖርብኛል፡፡

ወዳጄ ከላይ የተጠቀሰውን ወጣት ደራሲ አላደንቅም ባይ ነው፡፡ መጽሐፍቱንም ደጋግሞ ሲተች አውቀዋለሁ፡፡ ሰሞኑን ታዲያ ይሄው ድረ ገጽ መጽሐፍቱ በበአሉ ግርማ እንደተፃፉ ማረጋገጡን ሲያውጅ በደስታ ሰክሮ “እነዚህ መጽሐፍት የበአሉ ግርማ ናቸው ተባለ እኮ” አለኝ፡፡ ደራሲውን ሲያጣጥል መጽሐፍቱን እያደነቀ መሆኑ አልገባውም፡፡ ለሳምንታት ያህል የዘለቀው ሯጭ ወሬ ውቅያኖስ ተሻግሮ ለመዝለቅ ጊዜ አልፈጀበትም፡፡ አባይን ተሻግሮ የወሬውን እውነትነት ለማረጋገጥ የሞከረ ሰው ስለመኖሩ ሳልሰማ ነበር፣ ወሬው ራሱ ውቅያኖስ ተሻግሮ አሜሪካ መግባቱን ያወቅሁት፡፡ መቀመጫውን በአትላንታ ያደረገውና ዘወትር ቅዳሜ የተለያዩ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን በአማርኛ ቋንቋ የሚያቀርበው “አድማስ ሬዲዮ”፣ ዛሬ ማታ ከደራሲ በአሉ ግርማ ሴት ልጅ ጋር በጉዳዩ ዙሪያ ቃለ ምልልስ ሊያደርግ ቀጠሮ ይዟል፡፡ ወደ አካባቢው በመደወል ነገሩን ለማጣራት የሞከሩ ግለሰቦች አጋጥመውኛል፡፡ ወደ ጣና ደሴቶች አምርቶ የዳጋ እስጢፋኖስን ገዳም የአስተዳደር አካላትና ሌሎች የሚመለከታቸውን በማነጋገር እውነታውን ለማጣራት የሞከረው ወጣቱ ጋዜጠኛና ገጣሚ ደመቀ ከበደ፣ ከትናንት በስቲያ የሙከራውን ውጤት እነሆ ብሏል፡፡ ያነጋገራቸው ሁሉ እርግጠኛ ሆነው የሰጡት ምላሽ እንዲህ የሚል ነው፤ “ከመናኞች መካከል ይህ የምትሉት ሰው የለም” ኦሮማይ (?)

መንግስት ከላያችን ላይ እጁን እንዲያነሳ ማድረግ ነው መፍትሄው - ማርጋሬት ታቸር እንዳደረጉት። የችግሩ ስረመሰረት እንዲነቀልና ትክክለኛው መፍትሄ ተግባራዊ እንዲሆን ፈፅሞ የማንፈልግ ከሆነስ? በ“አንዳች ተአምር” መፍትሄ እንዲመጣ እንጠብቃለና - ለ30 አመት በከንቱ ስንጠብቅ እንደኖርነው።

በኤሌክትሪክ፣ በውሃ እና በስልክ ችግር መማረር ሰልችቷቸው፣ “ኧረ ይሄስ፣ መላም የለው!” ብለው በተስፋ ቢስነት የተቀመጡ ሰዎች ይኖራሉ። ይፈረድባቸዋል? “ተስፋ መቁረጥማ ደካማነት ነው” ብለን እንዳንፈርድባቸው፤ “እናንተስ የትኛውን ተስፋ ይዛችሁ ነው?” በሚል ጥያቄ መልሰው ሊያፋጥጡን ይችላሉ። ይሄውና ስንት አመታችን! ከዛሬ ነገ፣ “ይሻሻላል” እያልን፣ እምነታችንን መንግስት ላይ ጥለን፣ ተዝቆ በማያልቅ ተስፋ ስንጠባበቅ ምን አተረፍን? ምንም! አንዳች ተጨባጭ መፍትሄና ማሻሻያ ሳይሆን፣ ቁጥር ስፍር የሌለው የማሳበቢያና የማመካኛ መዓት ነው ስንሰማ የኖርነው። አሁንም ጭምር። እንዲያም ሆኖ፣ ዛሬም ተስፋቸው ሳይሟጠጥ “አንዳች ተአምር” እንዲፈጠር የሚጠብቁም ሰዎች በጣም ብዙ ናቸው - መንግስትን እንደ አባት ወይም እንደ ሞግዚት እንዲሆንላቸው የሚጠብቁ ብዙ ሰዎች! የብዙ ፖለቲከኞችና የብዙ ምሁራን አስተሳሰብም ተመሳሳይ ነው።

የመንግስት ባለስልጣናትም እንደ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ፤ “በአንዳች ተአምር” መፍትሄ እንዲፈጠር ይጠብቃሉ። በተለይ የዘንድሮ ባለስልጣናት ለዜጎች የሚሰጡት መፅናኛና ተስፋ ምን አይነት እንደሆነ ተመልከቱ። ከአስር አመት በፊት፣ የባለስልጣናት ዋነኛ የማመካኛ ሰበብ የደርግ ስርዓት ነበር - “ካለፈው ስርዓት ሲንከባለልና ሲከማች የመጣ ችግር ነው” የሚል መፅናኛ ንግግር እያስቀደሙ፤ “ትንሽ ታገሱ እንጂ ሁሉም ችግር በአምስት አመቱ የልማት እቅድ መፍትሄ ያገኛል” ብለው የተስፋ ቃል ይመግቡን ነበር። “ግድብ የመገንባት እቅድ… ኔትዎርክ የማስፋፋት እቅድ… ጥልቅ የውሃ ጉድጓዶችን የመቆፈር እቅድ…” እያሉ ሲዘረዝሩት አጃኢብ ሊያሰኝ ይችላል። በእርግጥ፣ አንድም እቅድ ባለስልጣናት እንዳወሩለት በጊዜው አይጠናቀቅም።

ለአመታት ይጓተታል፣ ብዙ ገንዘብ ይባክናል። መንግስት የቢዝነስ ስራ ውስጥ ሲገባ፣ ስራ መጓተቱና ገንዘብ መባከኑ የተለመደ ቢሆንም አብዛኛው ሰው በትእግስት ይጠብቃል። ትእግስቱ እየሳሳ ሲሄድም፣ የመንግስት ባለስልጣናት ተጨማሪ ሰበብና የተስፋ ቃል አያጡም። በድህነት ላይ ያሳብባሉ። “የችግሩ ዋና ምንጭ ድህነታችን ነው። አሁን ግን አይዟችሁ። የተጀመሩት ግድቦች ተገንብተው ይለቁ እንጂ፣ ኔትዎርኮቹ ይስፋፉ እንጂ፣ ጥልቅ ጉድጓዶቹ ተቆፍረው ይጠናቀቁ እንጂ… በቃ ከዚያ በኋላ፣ ሁሉም ነገር በሽበሽ ይሆናል” ብለው ይደሰኩራሉ። ኢትዮጵያ፣ በሞባይል ስልክ ስርጭት ከሌሎቹ የአፍሪካ አገራት፣ ከሶማሊያ ሳይቀር ወደ ኋላ መቅረቷ ሳያንስ፣ የኔትዎርክ ጥራቱም እጅግ አሳፋሪና ትእግስት አስጨራሽ በመሆኑ ብዙ ሰው በየጊዜው ምሬቱን ይገልፃል። ታዲያ፣ የመንግስት ባለስልጣናት ምላሽ አያጡም፤ “የአቅም ችግር ስለሆነ፣ የኔትዎርክ ማስፋፊያው በጥቂት ሳምንታት ተጠናቅቆ ችግሩ ይወገዳል” ብለው ሲነግሩን፣ ብዙዎቻችን እንደአዲስ እንደገና ተስፋ እናደርጋለን። ለበርካታ አመታት የተለያየ ሰበብና እቅድ እየሰማን በጉጉት ስንጠብቅ፣ ተስፋችን እውን ሳይሆን እየቀረ አልጨበጥ ቢለንም፤ በአዲስ ሰበብ የታጀበ የባለስልጣናት ቃል ስንሰማ እንደ አዲስ ተስፋ ያድርብናል።

ከሁለት ከሶስት አመት በፊት ስለኤሌክትሪክ እጥረት ስንማረር ትዝ ይላችኋል? “ችግሩ የመነጨው ከኢኮኖሚ እድገቱ ነው፤ የኤሌክትሪክ ፍጆታ ስለጨመረ ነው” የሚል ሰበብ ያቀርቡ ነበር ባለስልጣናት። እስቲ አስቡት! “በኢኮኖሚ እድገት ሳቢያ ደንበኞቼ ብዙ ሸቀጥ እየሸመቱ አስቸገሩኝ” በሚል ሰበብ በየሰአቱ ሱቁን የሚዘጋና ደንበኞቹን ሳያስተናግድ የሚያሰናብት ነጋዴ አይታችሁ ታውቃላችሁ? መክሰር የማይፈልግ ከሆነ፣ ደንበኞችን አያንገላታም። ገበያው ይድራለት እንጂ፣ ነጋዴ በቂ ሸቀጥ ለደንበኞቹ ማቅረብ አያቅተውም - ለራሱ ትርፍ ሲል። ምን ዋጋ አለው? ትርፍ ለማግኘት ተብሎ ለሚከናወን ስራ ብዙም ክብር የለንም። ለማትረፍ ሳያስብ የሚሰራ ሰው ነው የምንፈልገው - መስዋዕትነትን እንደቅድስና እየቆጠርን። በእርግጥም የመንግስት ባለስልጣናት ትርፍ ለማግኘት አይሰሩም። ደንበኛ ቢበዛላቸውና ገበያ ቢደራላቸው ምንም ትርፍ አያገኙበትም። ከመደበኛው ደሞዝ ያለፈ ወደ ኪሳቸው የሚገባ ሽልማት የለም።

በሌላ በኩልም ባለስልጣናት፣ ደንበኞችን ሳያስተናግዱ ቢመልሱና ቢያጉላሉ አይከስሩም፤ ምንም አይጎድልባቸውም። መደበኛ ደሞዛቸውን ማንም አይከለክላቸውማ። ለዚህም ነው፤ ከነጋዴ በተለየ ሁኔታ፣ የመንግስት ባለስልጣናት “ገበያተኛ በዛብኝ” ብሎ መናገር በቂ ማመካኛ ሆኖ የሚታያቸው። ከማመካኛው ሰበብ ጋርም፣ እንደተለመደው የተስፋ ቃል ያዘንባሉ - “ከእንግዲህ አትጨነቁ! የተከዜና የበለስ ግድብ ስለተጠናቀቀ በአጭር ጊዜ የኤሌክትሪክ መቆራረጥ ተረት ይሆናል” ተብሎ ባለፉት ሁለት አመታት ተደጋግሞ ሲነገረን የስንቶቻችን ስሜት በተስፋ እንደተጥለቀለቀ አስታውሱ። በእርግጥ፤ ከዚያ በፊትም እንዲሁ፤ “ግልገል ጊቤ 1 ስለተጠናቀቀ፣ ስራ ሲጀምር የኤሌክትሪክ እጥረት መፍትሄ ያገኛል” ተብለን ነበር - እንደተጠበቀው አልሆነም እንጂ። የውሃ እጥረትም ላይም ተመሳሳይ ነው። ከሃረር እስከ አዳማ ናዝሬት፣ ከአዲስ አበባ እስከ መቀሌ፣ ከደብረማርቆስ እስከ ነቀምት… በውሃ ምንጭ የማትታማው አርባ ምንጭ ሳትቀር፣ በውሃ እጥረት ያልተሰቃየ ከተማ የለም ማለት ይቻላል። እጥረቱ ስለተባባሰም፣ የመንግስት ባለስልጣናት እንደወትሮው፣ “የንፁህ ውሃ አቅርቦት በእጥፍ አድጎ 90 በመቶ ደርሷል” ብለው ራሳቸውንና ሌላውን ዜጋ ማታለል አስቸጋሪ መሆኑ ገብቷቸዋል።

ለዚህም ነው፤ “የከርሰ ምድር፣ የገፀ ምድር ውሃ… የጉድጓድ ቁፋሮ፣ የመስመር ዝርጋታ፣ የግድብ ጠረጋ… ሲጠናቀቅ ችግሩ መፍትሄ ያገኛል” እያሉ በየጊዜው የተለያየ የተስፋ ቃል የሚመግቡን። ብዙዎቻችንም፣ ተስፋ ቁርስና እራት ሆኖልን ለበርካታ አመታት ጠብቀናል። ግን የመፍትሄ ጠብታ አልተገኘም። የመንግስት ባለስልጣናት ከዚህ ሁሉ አመት በኋላ፣ ሰበብና ማመካኛ ሊያልቅባቸው ይችላል ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው። ትክክለኛና ተጨባጭ መፍትሄ የመፍጠር ችሎታ ባይኖራቸው እንኳ፣ አስገራሚ ሰበቦችንና ማመካኛዎችን የመፈብረክ ልዩ የፈጠራ ችሎታ አላቸው። “የውሃ እጥረት ከመባባሱም በተጨማሪ፣ እየቆየ የሚመጣው ውሃ የተበከለና የቆሸሸ ነው” የሚል አቤቱታ ሲቀርብ፣ የመንግስት ባለስልጣናት ምን አይነት ምላሽ እንደሰጡ ታውቃላችሁ? አሉባልታ ነው ብለው አስተባበሉ። እንዴት አትሉም? “ከግድብ ወይም ከጥልቅ ጉድጉድ ተጣርቶ የሚወጣው ውሃ ንፁህ እንደሆነ በላብራቶሪ የተመሰከረለት ነው። የውሃ ማስተላለፊያ ቧንቧዎች አርጅተው ስለተበሳሱ ነው ቆሻሻ እየገባ ብክለት የሚፈጠረው። ስለዚህ የተበከለ ውሃ ታቀርባላችሁ የሚባለው ወሬ አሉባልታ ነው” … የመንግስት ባለስልጣን እንዲህ “ማብራሪያ” ሲያቀርብ፣ “ማመካኛ ሰበብ የመፍጠር ችሎታው” አያስደንቅም? “የውሃ ምንጩ የብክለት ችግር የለበት፤ የማሰራጫ ባንቧዎቹ ላይ ነው ችግሩ”… ብለው ባለስልጣናት ሲነገሩን፤ “እንደዚያ ከሆነስ ችግር የለውም” ብለን እንድንረካ የሚያደርግ “ተአምራዊ መፍትሄ” የሰጡን ይመስላል።

እስቲ አስቡት፤ የሰፈራችሁ ነጋዴ የተበከለ ዘይት ሲሸጥላችሁ፤ “ከፋብሪካው ሳመጣው ንፁህ ነበር፤ እዚህ ሱቅ ውስጥ ነው ብክለት የተፈጠረው” ብሎ ሊያሳምናችሁ ይሞክራል? “ያምሃል? ወይስ ትቀልዳለህ?” ብላችሁ እንደምትቆጡት ስለሚያውቅ፣ እንዲህ አይነት “ማመካኛ ሰበብ” ለማቅረብ የሚሞክር ነጋዴ አይኖርም። የመንግስት ባለስልጣንን ግን ልንቆጣው አንችልም - አስገራሚ “የማመካኛ ሰበቦችን” እየቀያየረ ሲደሰኩር በዝምታ እንሰማለን። “የሃይል እጥረት የለም። ችግሩ የማከፋፈልና የማሰራጨት ጉዳይ ነው” በማለት ባለስልጣናት ሲናግሩስ አልሰማችሁም? በቃ! “የስርጭት ችግር እንጂ የሃይል እጥረት የለም” ብለው ስለተናገሩ፣ ተአምረኛ መፍትሄ የሰጡን ይመስላሉ። “የድህነትና የእጥረት ችግር ሳይሆን የአስተዳደር ችግር ነው” … ሲባልም አድምጣችኋል። እናስ? አብዛኛው ሰውምኮ፣ በየጊዜው ላለፉት አመታት ሲያማርር የቆየው፣ “የአስተዳደር ችግር” … ብሎ እየጮኸ ነው። ያው እንደተለመደው… ውይይት፣ ግምገማ፣ ቢፒአር፣ ቢኤስሲ፣ ካይዘን፣ የመዋቅር ለውጥ፣ ሹም ሽር… በየጊዜው ይሞከራል፤ እናም ብዙ ዜጎች ተስፋ ያሳድራሉ። ግን የውሸት ተስፋ ነው። የእውነት ተስፋ ቢሆን ኖሮ፣ ውሎ አድሮ እንደጠበቅነው መፍትሄ ሳይመጣ መቅረቱን ስንመለከት… “እንዴት? ለምን?” ብለን ከምር እናስብበት ነበር። ከመነሻውም፣ የባለስልጣናት ቃል ስንሰማ የሚፈጠርብን ተስፋ፣ ስስ የውሸት ተስፋ ስለሆነና ብዙም ስለማናምንበት፣ የህልም ምኞት ሆኖ መቅረቱን ስናይ ብዙም አይገርመንም፣ ብዙም አንቆጣም። በፀጋ እንቀበለዋለን። ለምን በሉ። እኔ ደግሞ በሁለት ምክንያቶች ብዬ እመልሳለሁ። አንደኛው ምክንያት፤ የኤሌክትሪክ፣ የውሃ፣ የስልክና ሌሎች ተመሳሳይ ችግሮች በመንግስት ስር እስከተያዙ ድረስ መፍትሄ የማያገኙ መሆናቸው ነው።

ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ፤ ትክክለኛውን መፍትሄ ለማየትና ለመሞከር የማይፈልግ ሰው መብዛቱ ነው - እነዚያን ስራዎች በሙሉ በቢዝነስ ድርጅቶች እንዲከናወኑ ማድረግ ነው ትክክለኛው መፍትሄ። በ10ሺ ብር ደሞዝ የ30 አመት ችግር መፍታት? የቴሌ ወይም የኤልፓ ስራ አስኪያጆች የወር ደሞዛቸው ስንት ይሆን ብለን አስበን እናውቃለን? ብዙዎቻችን አናስብም። ግን፤ በወር 10ሺ ብር የማይደርስ ደሞዝ የሚከፈለው ሰው፣ የ30 አመታትን ችግር አስወግዶ፣ በየእለቱና በየሰዓቱ፣ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች ያለማቋረጥ ኤሌክትሪክ እንዲያቀርብ እንጠብቃለን። ሰውዬው፣ ኤሌክትሪክ ሳይቋረጥ በትክክል ማቅረብ ከቻለኮ፣ በየፋብሪካውና በየቦታው በከንቱ የሚባክን የስራ ሰዓት አይኖርም፤ እናም በየወሩ በቢሊዮን ብሮች የሚገመት ተጨማሪ ምርት ይፈጠራል። ኤሌክትሪክ ሳይቋረጥ ማቅረብ ማለት ትርጉሙ የዚህን ያህል ትልቅ ነው። ታዲያ ይህንን ትልቅ ስራ ለማከናወን የቻለ ስራ አስኪያጅ ምን ጥቅም ያገኛል? ምንም! እንደወትሮው 10 ሺ ብር የማትደርስ ደሞዝ ብቻ! በቢሊዮን ብር የሚቆጠር ሃብት እንድንፈጥር በር የሚከፍት መፍትሄ ሲያመነጭልን፣ የስራ አስኪያጁ ደሞዝ 1 ሚሊዮን ብር ቢሆንለት ይበዛበታል?

በሌላ አነጋገር፣ ኤሌክትሪክ፣ ስልክ፣ ውሃ የመሳሰሉ አገልግሎቶች በግል የቢዝነስ ድርጅቶች እንዲከናወኑ ማድረግና፣ እንደ አገልግሎታቸው ጥራት ትርፋማ የሚሆኑበት የነፃ ገበያ ስርዓት ማስፋፋት ማለት ነው። ይሄኔ፣ ምን ያህል ኡኡታ እንደሚፈጠር አስቡት። አንድ ሺ ብር ተጨማሪ ሃብትና ትርፍ እንድፈጥር የሚያደርግ ሰው፣ የአንድ ብር ትርፍ ቢወስድ ይበዛበታል? አይበዛበትም። ነገር ግን፣ “ዘረፈን” እየተባለ አገር ሙሉ ሲጮህበት አይታያችሁም? አንድ የግል ድርጅት ወይም አንድ ስራ አስኪያጅ ሚሊዮን ብር ትርፍ ከሚያገኝ፣ እኛ የቢሊዮን ብር ተጨማሪ ሃብት ይቅርብን? ኤሌክትሪኩ እንደወትሮው እየተቆራረጠ እንኑር? በኤሌክትሪክ መቆራረጥ ሳቢያ ስራ እየተስተጓጎለ፣ በየወሩ በቢሊዮን ብር የሚቆጠር ሃብት እንክሰር? በየወሩ በቢሊዮን ብር የሚቆጠር ተጨማሪ ሃብት ለመፍጠር የሚያስችል ከባድ ስራ አለ፤ እስከ ዛሬ ለበርካታ አመታት ተሞክሮ አልተሳካም። ማን ይስራው? በ10ሺ ብር ደሞዝ ብቻ ምንም ጥቅም ላያገኝበት ከባዱን ስራ የሚያከናውንልን ሰው እንፈልጋለን።

ጥቅም ላያገኝበት ለምን ይሰራል? የተለመደው አይነት መልስ ልትሰጡ እንደምትችሉ እገምታለሁ - “ለራሱ ጥቅም ብሎ ሳይሆን፣ ለአገር እድገትና ለህዝብ ጥቅም ብሎ መስራት አለበት” በማለት። “ከራስ ጥቅም በፊት ሌሎች ሰዎችን ለማገልገል ቅድሚያ መስጠት ተገቢ ነው” የሚለው የመስዋዕትነት አስተሳሰብ፣ ጥንታዊና የተለመደ አስተሳሰብ ነው - ከአገራችን ባህል ጋር ለዘመናት የተሳሰረ። በ60ዎቹ ዓ.ም ደግሞ፣ የመስዋዕትነት አስተሳሰብ እንደ አዲስ በሶሻሊስት (ወይም በኮሙኒስት) ተማሪዎች ይበልጥ እየተራገበና እየተስተጋባ የአገሬውን ሰው ሁሉ አዳርሷል። የዘመናችን መሪዎችና አንጋፋ ምሁራን፣ በአብዛኛው የያኔው ተማሪዎችና ግርፎች ናቸው። እናም፤ የአብዛኛው ዜጋ አስተሳሰብና የብዙዎቹ መሪዎች አስተሳሰብ ተመሳሳይ ነው። “ለራሱ ጥቅም በማሰብ ሳይሆን ለህዝብ ጥቅም ቅድሚያ እየሰጠ የሚሰራ ሰው”፤ እንዲሁም “ለራሱ ትርፍ ለማግኘት በማቀድ ሳይሆን፣ የአገርን ልማት እያስቀደመ የሚሰራ ድርጅት” ለማግኘትና ለመፍጠርም፣ መንግስት የቢዝነስ ስራ ውስጥ ጣልቃ እንዲገባ የሚደረገው።

ግን ምን ዋጋ አለው? የመስዋዕትነት አስተሳሰብ፣ በኢትዮጵያም ሆነ በሶቭየት፣ በኩባም ሆነ በእንግሊዝ… ድሮም ሆነ ዛሬ፣ ከውድቀት ያለፈ ውጤት አላስገኘም። በሁለት ተያያዥ ምክንያቶች ሳቢያ ነው፣ ይሄ አስተሳሰብ ስህተትና መጥፎ የሚሆነው። አንደኛ ነገር፤ “በጥረትህ ራስህን ለመጥቀም ሳይሆን ሌሎችን ለማገልገል አስብ” ብለን ሺ አመት “መስዋዕትነትን” ስንሰብክ ብንኖር፤ ተከታይና አማኝ ብናገኝ እንኳ፣ በፈቃደኝነት ይህን አስተሳሰብ ሙሉ ለሙሉ የሚተገብር ሰው ብዙም አናገኝም። በፈቃደኝነት ራሱን ለመስዋዕትነት የሚያቀርብ ሲጠፋ፣ በአዋጅና በጠመንጃ ወደ ማስገደድ እንሄዳለና። በአእምሮ ብቃትና በእውቀት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሰዋል የሚባሉ የአገራችን ሃኪሞች፣ ሁለት ክፍል ቤት ተከራይቶ ለመኖር በማያስችል ደሞዝ “ህዝብ እንዲያገለግሉ” ስንጠብቅባቸው ምን ተፈጠረ? አብዛኞቹ ሃኪሞች “ምን በወጣን!” ብለው ጥለውን ሄደዋል። በመላ ኢትዮጵያ የሚገኙ የህክምና ዶክተሮች ቁጥር ከሁለት ሺ ብዙም አይበልጥም።

አሜሪካ ውስጥ፣ በዋሺንግተን ዲሲና በሜሪላንድ ብቻ የኢትዮጵያውያን ዶክተሮች በቁጥር ግን፣ እዚህ አገር ውስጥ ካሉት ይበልጣል።በሌሎች የአሜሪካ ከተሞች፣ በአውሮፓ እና በአፍሪካ አገራት የሚገኙ፣ እዚሁ አገር ውስጥም የህክምና ሙያቸውን ትተው በሌላ ስራ ላይ የተሰማሩ ኢትዮጵያውያን የህክምና ዶክተሮችን ሳንቆጥር ነው። በአጭሩ፣ “ለአገር ልማት፣ ለህዝብ ጥቅም!” የሚባለው የመስዋዕትነት አስተሳሰብ፣ በተግባር አይሰራም። ልማትና ጥቅም አይገኝበትም። በደርግ ዘመን የአገሪቱ ኢኮኖሚና የዜጎች ኑሮ ከአመት አመት እያሽቆለቆለ፣ በ17 አመታት ውስጥ ድህነት በእጥፍ የጨመረው በሌላ ምክንያት አይደለም - “አገር ትቅደም፤ ህዝብን አስቀድም!” በሚል የመስዋዕትነት አስተሳሰብ ምክንያት ነው። ግን በኢትዮጵያ ብቻ አይደለም። “ከራስህ በፊት አገር ትቅደም” ብለው የፎከሩ የ”አገራዊነት” ወይም የ”ብሄረተኝነት” አቀንቃኞች (እንደ ሞሶሎኒና ሂትለር፣ እንደ ሞቡቱና ኢዲአሚን የመሳሰሉ መሪዎች) የየአገራቸውን ህዝብ ለእልቂትና ለድህነት ዳርገዋል። “ከራስህ በፊት ህዝብ ይቅደም” ብለው የጮሁ የ”ህዝባዊነት” ወይም “የሶሻሊዝም” ሰባኪዎች (እንደ ሌኒንና ስታሊን፣ ሞኦና መንግስቱ የመሳሰሉ መሪዎች)፣ የየአገራቸውን ህዝብ በማደህየት ሚሊዮኖችን ለረሃብ እልቂት ዳርገዋል። ሚሊዮኖችን ረሽነዋል።

ሶሻሊዝምን ወይም ፋሺዝምን የዘመሩ አገራት ሁሉ፣ በየጊዜው በኢኮኖሚ ድቀት ሲፈራርሱ አላየንም እንዴ? የትም አገር፣ በየትኛውም ጊዜ በተግባር የብልፅግና ውጤት አስገኝቶ አያውቅም - የድህነትና የውድቀት ውጤት እንጂ። ታዲያ እንዲህ በየአገሩ ከቅርብ እስከ እስከ ሩቅ፣ በየዘመኑ ከጥንት እስከ ዛሬ በተግባር ተሞክሮ መጥፎነቱ የተረጋገጠ የመስዋዕትነት አስተሳሰብ ላይ ሙጭጭ የምንለው ለምንድነው? ዛሬም እንደ ድሮው፤ “ለራሱ ጥቅም በማሰብ ሳይሆን ለህዝብ ጥቅም አስቦ የሚሰራ ሰው” ችግሮችን ሁሉ ይፈታል ብለን አንዳች ተአምር እንዲፈጠር የምንጠብቀውስ ለምንድነው? እንዲሁ ከልጅነታቸው ጀምሮ ሲሰሙት የነበረና የለመዱት አስተሳሰብ ስለሆነ ብቻ፤ በ”ደመነፍስ” እንደበቀቀን እየደጋገሙ የሚናገሩ ይኖራሉ።

ወይም፤ “አዋቂ” ብለው የሚያከብሩት ሰው ሲናገር ሰምተው፣ እንደ ገደል ማሚቶ መልሰው የሚያስተጋቡ ሰዎችም ሞልተዋል። ብዙ ሰዎች ግን፣ “ከራስ በፊት ለአገር ልማት፣ ለራስ በፊት ለህዝብ ጥቅም!” ብለው መስዋዕትነትን የሚሰብኩት፣ “የቅድስና ዋና ምሶሶ ነው” ብለው ስለሚያምኑበት ነው። በተግባር ለኑሮ የማይበጅ እንደሆነ ቢገባቸውም፣ በተጨባጭ ችግሮችን እንደማይፈታ ቢያረጋግጡም፣ በግላቸው ሁልጊዜ ተግባራዊ ሊያደርጉት ከሞከሩ ህልውናቸውን እንደሚያጠፋባቸው ቢያውቁም… ያንን “የመስዋዕትነት አስተሳሰብ” አሽቀንጥረው ሊጥሉት አይፈልጉም፤ ወይም አይደፍሩም። ለምን? የ”ቅድስና ዋና ምሶሶ ነው” ብለው ያምኑበታላ። ሁልጊዜ ተግባራዊ ሊያደርጉት ባይችሉ እንኳ፣ ቢያንስ ቢያንስ ሊሰብኩለት ይፈልጋሉ። ባይሰብኩለት እንኳ፣ ሊቃወሙት አይፈልጉም። ነገር ግን፣ “መስዋዕትነት ለምን ቅዱስ ይሆናል?”፣ “የመስዋዕትነት አስተሳሰብ ለምን ቅዱስ አስተሳሰብ ይሆናል?” … ለዚህ ጥያቄ አንዳችም አሳማኝ ምላሽ እንደሌለ የምትገልፀው አየን ራንድ፤ የመስዋዕትነት አስተሳሰብ ለዘመናት የሰውን ልጅ ለድህነትና ለረሃብ፣ ለእልቂትና ለባርነት የዳረገ ክፉ አስተሳሰብ ነው ትላለች። ለምን? “ጎረቤቴ፣ የራሱን ህይወት ሳያሻሽል፣ የራሱን ኑሮ እያጎሳቆለ፣ የኔን ህይወት ለማሻሻልና ኑሮዬን ለማሻሻል መስዋዕት ይሁንልኝ” ብሎ ማመን እንዴት ቅዱስ አስተሳሰብ ሊሆን ይችላል? የቀማኛና የ”ጥገኛ ተባይ” አስተሳሰብ ነው። “የራሴን ህይወት ሳላሻሽል ኑሮዬን እያጎሳቆልኩ፣ እንደ ጋማ ከብት ሌሎች ሰዎችን ለማገልገል በመስዋዕትነት መቅረብ አለብኝ” ብሎ ማመንስ እንዴት ቅዱስ አስተሳሰብ ይሆናል? ባርነትንና እንሰሳነትን በፀጋ የሚቀበል አስተሳሰብ ነው።

ይሄ የተጋነነ አገላለፅ እንዳይመስላችሁ። “አገርንና ህዝብን ማስቀደም ያስፈልጋል” እያሉ የሚሰብኩ የመንግስት ባለስልጣናትና ምሁራን፣ ስለ ኢንቨስተሮችና ስለ ቢዝነስ ሰዎች ሲናገሩ ሰምታችሁ አታውቁም? “ወርቅ የምትጥል ዶሮ”፤ “የምትታለብ ላም” እያሉ ነው የሚጠሯቸው። እንስሳነትንና ባርነትን በፈቃደኝነት እንድንቀበል የሚያደርግ አስተሳሰብ ተጠናውቷቸዋላ! አንዱ ሰው ባርያና አገልጋይ ከሆነ፣ በዚህኛው መስዋዕትነት “ተጠቃሚ” የሚሆን ሌላ ሰው መኖሩ አያጠራጥርም - ቀማኛ ተገልጋይና ጥገኛ ተባይ። “ለአገር ልማት፤ ለህዝብ ጥቅም” በሚል መፈክር ብዙዎች ንብረታቸውን ተቀምተዋል - በመንግስት ተወርሶባቸዋል። የአገራችን ሃኪሞች ወደ ውጭ አገራት እንዳይጓዙ የተለያዩ እገዳዎች የሚጣልባቸውስ ለምን ይሆን? “እንዲያገለግሉን ልናስገድዳቸው ስለምንፈልግ ነዋ” ብላችሁ እቅጩን መናገር ባትፈልጉ እንኳ ሌላ ትርጉም የለውም። “መንግስት ያንን ይደጉምልን፣ ይሄንን በነፃ ወይም በቅናሽ ያቅርብልን” ብለን የምንጮኸውስ ለምንድነው? ከሌሎች ሰዎች በታክስ መልክ እየቀማ ለኛ ይስጠን እንደማለትኮ ነው። “በሌሎች ሰዎች ላይ ጥገኛ ሆነን እንድንኖር አመቻችልን” እንደማለት ነው። ታዲያ፤ በሌሎች መስዋዕትነት ላይ የመኖር ምኞትን የሚያንቆለጳጵስ የቀማኛና የጥገኛ ተመፅዋች አስተሳሰብ፤ እንዴት ቅዱስ አስተሳሰብ ይሆናል? ሰውን እንደቀማኛ ወይም እንደ ባርያ፣ እንደ ጥገኛ መዥገር ወይም እንደ አገልጋይ እንሰሳ የሚቆጥር አስተሳሰብ ይዘን፤ እንዴት በፍቅር መኖር ይቻለናል? በጠላትነትና በምቀኝነት፣ በግፈኛነትና በተለማማጭነት እንጂ! የመስዋዕትነት አስተሳሰብ እኩይና ክፉ ከሆነ፤ ቅዱስ የሆነው አስተሳሰብ የትኛው ነው? ራስን የመውደድና የመከባበር አስተሳሰብ ነዋ። “ለሌሎች ሰዎች መስዋዕት አልሆንም፤ ሌሎች ሰዎችም ለኔ መስዋዕት እንዲሆኑልኝ አላደርግም” ብሎ ሰው የመሆን ክብሩን የሚጎናፀፍ፣ ቀማኛና ጥገኛ ተባይ መሆንን የሚጠላ፣ ባርያና አገልጋይ እንሰሳ መሆንን የሚፀየፍ አስተሳሰብ ነው፣ ቅዱስ አስተሳሰብ።

የራሱን ህይወት የሚያፈቅርና በጥረቱ ኑሮውን ለማሻሻል የሚተጋ፤ የሌሎችን ህይወት የሚያከብርና ለኑሯቸው መልካሙን ሁሉ የሚመኝላቸው፤ እርስ በርስ ለመጠቃቀም የሚገበያይ ኩሩ ስብእና የሚፈጠረውም በዚህ መንገድ ነው። በዚህ አስተሳሰብ ላይ በመመስረትም ነው፤ የነፃ ገበያና የቢዝነስ ስራ ቅዱስነትን መገንዘብ የምንችለው። በዚህ አስተሳሰብ አማካኝነትም ነው፤ ለዘመናት የዘለቀው የኤሌክትሪክ፣ የስልክ፣ የውሃ እና ሌሎች ችግግችን መፍታት የምንችለው። ማርጋሬት ታቸርን በአርአያነት መጥቀስ ይቻላል። ከሁለተኛው የአለም ጦርነት በኋላ ወደ ሶሻሊዝም ስታዘግም በቆየችው እንግሊዝ ውስጥ፣ ቀስ በቀስ የቢዝነስ ስራዎች በመንግስት እጅ እንዲገቡ እየተደረገ በዚያው መጠንም የአገሪቱ ኢኮኖሚ እየተንኮታኮተ ገደል አፋፍ ላይ የደረሰው በ1970ዎቹ ገደማ ነው። የኤሌክትሪክ፣ የውሃ፣ የስልክ አገልግሎት ብቻ ሳይሆን በርካታ የኢንዱስትሪ መስኮችም በመንግስት ቁጥጥር ስር እንዲሆኑ በመደረጋቸው በየአመቱ እየተዳከሙ፣ አትራፊነታቸው እየቀነሰ፣ ታክስ መክፈል እያቆሙ፣ በመጨረሻ ያለ መንግስት ድጎማ የማይንቀሳቀሱ አክሳሪ ድርጅቶች ሆነው አረፉት። በየአመቱ ከ4.5 ቢሊዮን ዶላር በላይ ድጎማ ይመደብላቸው ነበር - ከዜጎች በሚሰበሰብ ታክስ። ይህም ብቻ አይደለም። የአገልግሎት ጥራታቸውም ተንኮታኩቷል። የቤት ወይም የቢሮ ስልክ ለማስገባት እንደድሮ በአንድ በሁለት ቀን የሚሳካ መሆኑ ቀረ። ተመዝግቦ ለወራት ያህል ወረፋ መጠበቅ የግድ ሆነ። ኤሌክትሪክም እንደድሮው፣ ቀን ከሌት፣ በጋ ከክረምት መቼም የማይቋረጥ የማይጠፋ አስተማማኝ አገልግሎት መሆኑ ቀረ። በጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ በሚካሄድ ስብሰባ ሳይቀር፣ ሻማ መጠቀም የግድ ሆነ። ይሄኔ ነው፣ ማርጋሬት ታቸር “ይብቃን!” ብለው የተነሱት።

በመስዋዕትነት አስተሳሰብ ላይ የተመሰረተ አጥፊ የሶሻሊዝም ኢኮኖሚን በመቃወም፤ በራስ ጥረት የመበልፀግ ቅዱስነትን የሚያንፀባርቅ የካፒታሊዝም ኢኮኖሚን ለማስፋፋት የተነሱት ማርጋሬት ታቸር፤ ግማሽ የአለም ህዝብ ቢያወግዛቸውም፣ የአገራቸው ምሁራንና ፖለቲከኞች ቢኮንኗቸውም፣ በፍርሃት ሳቢያ ከአቋማቸው ለማፈንገጥ አልፈቀዱም። በመንግስት ተይዘው የነበሩ የውሃ፣ የኤሌክትሪክና የስልክ አገልግሎቶችን ብቻ ሳይሆን ሌሎች ኢንዱስትሪዎችንም ወደ ግል የቢዝነስ ድርጅትነት እንዲተላለፉ አደረጉ - 10 ሚሊዮን ያህል ዜጎች የአክሲዮን ድርሻ ባለቤት እንዲሆኑ በሚያደርግ ዘዴ። ብዙም ሳይቆይ የእንግሊዝ ኢኮኖሚና የዜጎች ኑሮ ማንሰራራት ጀመረ። በድጎማ ይንቀሳቀሱ የነበሩ አክሳሪ ድርጅቶች ትርፋማ በመሆን፣ በአመት ወደ 5 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ታክስ የሚከፍሉ የብልፅግና ድርጅቶች ለመሆን በቁ። በየደቂቃውና በየሰዓቱ ይቆራረጥ የነበረው የስልክ፣ የውሃና፣የኤሌክትሪክ እጥረት መፍትሄ ያገኘው በዚህ መንገድ ነው።