Administrator

Administrator

በ2007 ‹‹ሱፕርናሽናል ሊግ›› ይጀመራል
በ2007 ወደ የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ የሚያድጉ ሁለት ክለቦችን የሚለየው የብሄራዊ ሊግ ማጠቃለያ ውድድርን የባህር ዳር ስታድዬም እንደሚያስተናግድ ታወቀ፡፡
ስታድዬሙ ውድድሩን እንዲያስተናግድ የተመረጠው ባለው ዓለም አቀፍ የብቃት ደረጃ የተሻለ ፉክክር ይስተናገድበታል በሚል ግምት ሲሆን በየክልሉ የሚገኙ አዳዲስ የስፖርት ማዘውተርያ ስፍራዎችን  መጠቀም አስፈላጊነቱ ስለታመነበት ነው፡፡ የብሄራዊ ሊግ ማጠቃለያ ውድድር 16 ክለቦችን ያሳትፋል፡፡ በ2006 የኢትዮጵያ ብሄራዊ ሊግ 69 ክለቦች በሰባት ምድቦች ተከፍለው ሲፎካከሩ ቆይተዋል፡፡ ከብሄራዊ ሊጉ 7 ምድቦች  አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ የሚያገኙት 14 ክለቦች እና ሁለት ምርጥ ሶስተኛ ቡድኖች  በባህርዳር ስታድዬም ለሚካሄደው የ16 ክለቦች ማጠቃለያ ውድድር የሚያልፉ ይሆናል፡፡ ውድድሩ ተቀራራቢ ነጥብ በያዙ ክለቦች ጠንካራ ፉክክር ሲታይበት ቆይቷል፡፡  
ይህ በእንዲህ እንዳለ በሚቀጥለው የውድድር ዘመን በተለያዩ ዞኖች ተካፋፍሎ በሚደረገው የብሄራዊ ሊግ እና የፕሪሚዬር ሊግ ውድድር መካከል ሱፕር ናሽናል ሊግ የሚባል አዲስ ውድድር ሊካሄድ ታቅዷል፡፡ ሱፕር ናሽናል ሊጉ 16 ክለቦችን በማሳተፍ ዓመቱን ሙሉ በዙር ውድድር ተካሂዶ ወደ የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ የሚያልፉ ሁለት ክለቦች የሚወሰኑበት ይሆናል። ለብሄራዊ ቡድን የሚሆኑ ተጨዋቾችን ለመመልመል ሱፕር ናሽናል  ሊጉ  አመቺ መድረክ መሆኑ አይቀርም። ምክንያቱም  ወደ ፕሪሚዬር ሊግ የሚያልፉ ክለቦችን ከአድካሚ ውድድሮች በኋላ  ከመለየት ከ16 ቡድኖች ምርጡን ማግኘት የሚሻል በመሆኑ ነው

ለ14ኛው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የፊታችን ሰኞ ምዝገባው ሊጀመር ነው፡፡ ከስድስት ወር በኋላ   በአዲስ አበባ በሚካሄደው የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫው  ላይ ተሳታፊዎች 40ሺ  እንደሚሆኑ ይጠበቃል፡፡
የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ አዘጋጆች እንዳስታወቁት ለ14ኛው የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ውድድር ሰኞ እለት በተመረጡ ስምንት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፍ መስርያ ቤቶች ምዝገባው የሚጀመር ሲሆን  ለመጀመርያዎቹ 1ሺ ተመዝጋቢዎች የልምምድ ቲሸርት እንደሚሰጥ ገልፀዋል፡፡
በሌላ በኩል በነገው እለት ከሚደረገው የቀለበት መንገድ የዱላ ቅብብል ጋር ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ያዘጋጃቸው ውድድሮች ብዛት 100 ደርሰዋል፡፡

ለሁለት ዓመት ተኩል የአሜሪካ ኩባንያ ይመራዋል
“መንግሥት ከንግድ ሥርዓት ውስጥ እጁን ማውጣት አለበት” - የኢኮኖሚ ባለሙያ

     በመንግስት የተቋቋመው “አለ በጅምላ” የንግድ ድርጅት፣ ከመገናኛ ወደ ቦሌ በሚወስደው መንገድ ላይ የመጀመሪያውን የጅምላ ንግድ ማዕከል ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ በተገኙበት ባለፈው ሰኞ አስመርቋል፡፡ ከመንግስት የልማት ድርጅቶች አንዱ የሆነውን ይህን የንግድ ማዕከል ለማቋቋም ከሁለት አመት በላይ ጥናት የተደረገ ሲሆን “A.T. Kearney” የተሰኘ የአሜሪካ ኩባንያ ድርጅቱን የማቋቋምና የማደራጀት ሃላፊነት እንደተሰጠው ለማወቅ ተችሏል፡፡ ለሁለት አመት ተኩልም ኩባንያው የስራ አመራሩን ሃላፊነት በኮንትራት የወሰደ ሲሆን ኮንትራቱ ሲጠናቀቅ፣ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ይተኩታል ተብሏል፡፡
“አለ በጅምላ” የንግድ ማዕከል” ደረቅ የምግብ ሸቀጦች፣ የውበትና ንፅህና መጠበቂያዎች እንዲሁም የፅህፈት መሣሪያዎችን በማቅረብ ስራውን የጀመረ ሲሆን ማዕከሉ ማቀዝቀዣዎች ሲሟሉለት አትክልትና ፍራፍሬዎችንም ማቅረብ እንደሚጀምር የንግድ ሚኒስትሩ አቶ ከበደ ጫኔ፤ ገልፀዋል፡፡
የንግድ ማዕከሉ ከግል የጅምላ ንግድ አስመጪዎች ጋር በትብብር እንደሚሠራ የጠቆሙት ሚኒስትሩ፤ በዋጋ ረገድ አሁን ካሉት የግል አስመጪዎች ከ5 እስከ 15 በመቶ ቅናሽ እንደሚኖረው ጠቁመው፤ “አትራፊነታችን እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በተመጣጣኝ ዋጋ ምርቶች ለተጠቃሚው እንዲቀርቡ እናደርጋለን” ብለዋል፡፡
ዘመናዊ የንግድ አሠራርና መረጃን መሠረት ያደረገ አገልግሎት እንደሚሰጥ የተነገረለት የንግድ ድርጅቱ፤ የማይነጥፍ አስተማማኝ አቅርቦት ይኖረዋል ተብሏል፡፡ ዋነኛ ተልዕኮው የግብይት ስርአቱን ማረጋጋት ቢሆንም በየጊዜው የሚፈጠሩ አዳዲስ ምርቶች በኢትዮጵያ ገበያ ድርሻ እንዲኖራቸው ማድረግና በጥናት ላይ የተመሰረቱ ዘመናዊ የንግድ ስርአቶችና አሠራሮችን መፍጠርም የድርጅቱ አላማ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
አቅርቦትን በተመለከተ የተጠየቁት ሚኒስትሩ፤ ከሃገር ውስጥና ከውጭ ፋብሪካዎች በቀጥታ ምርቶችን መቀበልን እንደሚያካትት አስረድተዋል፡፡ በዚህ እድል ለሚጠቀሙ የሃገር ውስጥ ፋብሪካዎች፤ የገበያ ትስስሮሽ በተጠናከረ መልኩ ይፈጠርላቸዋል ያሉት ሚኒስትሩ፤ ኢንተርፕራይዙ በቀጥታ ምርቱን ከፋብሪካዎች መቀበሉ የግብይት ሰንሰለቱን ያሳጥረዋል፤ የግብይት ስርአቱን የሚረብሹ ደላላዎችም ከጨዋታ ውጪ ይሆናሉ ብለዋል፡፡
“ጅንአድ” የመንግስት ንግድ ድርጅትና አዲስ የተቋቋመው “አለ በጅምላ”፤ ተልዕኳቸው አንድ ቢሆንም አዲሱ ኢንተርፕራይዝ በዘመናዊነት ለመስራት መዘጋጀቱ ለየት እንደሚያደርገው የጠቀሱት ሚኒስትሩ፤ ጅንአድ አሁን የተሰጡትን ስኳር፣ ዘይትና የመሳሰሉ ሸቀጦችን በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ ይቀጥላል፤ “አለ በጅምላ” ሲጠናከር ሁለቱ ተቋማት ሊዋሃዱ ይችላሉ ብለዋል፡፡
“አለ”ን የማቋቋም አስፈላጊነትን አስመልክቶ ያብራሩት ሚኒስትሩ፤ በሀገሪቱ የንግድ ስርአት ዙሪያ ለሁለት አመታት ሲደረግ በቆየው ጥናት፤ የግብይት ስርአቱና የሸቀጦች ዋጋ መልክ የሌለው እንደሆነ መረጋገጡን ጠቅሰው፤ ጥናቱን መነሻ በማድረግም በዘመናዊ መልኩ ግብይት መፍጠር እንዲቻል በርካታ አማራጮች መቅረባቸውን ያወሳሉ፡፡ እንደ ዎል ማርት አይነት ድርጅቶች ወደ ሀገሪቱ ገብተው እንዲሠሩ መፍቀድ የሚለውን ጨምሮ፣ የዎል ማርት አይነት ድርጅት ማቋቋም የሚሉ ሃሳቦች ቀርበው እንደነበር የጠቆሙት ሚ/ሩ፤ “መንግስት የዎል ማርት አይነት ስራ ሊሠራ የሚችል ኢንተርፕራይዝ መክፈት የሚለውን ሃሳብ ተቀብሎ እውን አድርጓል” ብለዋል።
ዎል ማርት በቀጥታ ወደ ሃገር ውስጥ ቢገባ ኖሮ፣ በታዳጊ ደረጃ ያለውን የሃገሪቱን ነጋዴ ሊጐዳ እንደሚችልና ከትርፍ የሚገኘው ገንዘብ ወደ ውጭ ፈሰስ እንደሚሆን ያስረዱት ሚኒስትሩ፤ መንግስት የገበያ ጉድለት ባለበት ሁሉ የመግባት ሃላፊነት ስላለበት፣ የግሉን ዘርፍ በማይጐዳና ተወዳዳሪነቱን በማያቀጭጭ መልኩ፣ ይህን ኢንተርፕራይዝ አቋቁሞ ወደ ገበያው መግባት የሚለውን እንደ አማራጭ መውሰዱን ገልፀዋል፡፡
ተጠሪነቱ ለንግድ ሚኒስቴር የሆነው “አለ በጅምላ”፤ የሰው ሃይሉን ለማጠናከር አለማቀፍ ልምድ ያላቸውን ዳያስፖራዎች ጨምሮ ከ150 በላይ በዘርፉ ልምድና እውቀት ያላቸው የስራ አመራርና የግብይት ባለሙያዎችን እንደቀጠረ ለማወቅ ተችሏል፡፡ በሶስት አመት ጊዜ ውስጥም ከፍተኛ የህዝብ ክምችት አለባቸው ተብለው በተለዩ 27 የክልል ከተሞች ውስጥ ወደ 36 የሚደርሱ የማከፋፈያ ማዕከላት እንደሚከፈቱ ተጠቁሟል፡፡
ሰሞኑን መገናኛ አካባቢ ተመርቆ ስራ ከጀመረው የንግድ ማዕከል በተጨማሪ በቅርቡ ቃሊቲና መርካቶ ቢስ መብራት አጠገብ ሁለት ማዕከላት ተከፍተው ስራ ይጀምራሉ ተብሏል፡፡  
በአለማቀፍ የኢኮኖሚ ተቋም ውስጥ በሃላፊነት የሚሰሩ አንድ የኢኮኖሚ ባለሙያ በሰጡት አስተያየት፤ ለዘመናት የሃገሪቱን የጅምላ ንግድ ሲመራ የቆየው ጅንአድ፤ ትርጉም ያለው ተፅዕኖ አለመፍጠሩን ጠቅሰው፤ ያሁኑም ተቋም የተለየ ተፅዕኖ አይፈጥርም ብለዋል፡፡ “መንግስት ከንግድ ስርአት ውስጥ እጁን ማውጣት አለበት” ያሉት ባለሙያው፤ ማዕከሉ በመሰረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች ላይ ብቻ አተኩሮ ለመስራት መፈለጉ የግል ነጋዴዎችን እምብዛም ላይጎዳ ይችላል፤ ነገር ግን መንግስት በሂደት የጅምላ ንግድ ስርአቱን ሙሉ በሙሉ ለሃገር ውስጥና ለውጭ ባለሃብቶች መተው እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡
“በተለይ የሃገር ውስጥ ባለሃብቶች በብዛት ወደ ጅምላ ንግድ ስርአቱ ገብተው ተወዳዳሪነትን መፍጠር እንዲችሉ መንግሥት ማገዝ ይኖርበታል” ሲሉ አሳስበዋል፡፡ እኔም እንደባለሙያ፣ የጅምላ ንግድ ስርአቱ በጥቂቶች መያዙን እረዳለሁ ያሉት አስተያየት ሰጪው፤ “የመንግስት በጅምላ ንግድ ስርአት ውስጥ መግባት በሃገሪቱ የንግድ ተወዳዳሪነት ደካማ መሆኑን ያመለክታል”፤ በማለት ተወዳዳሪነት መፈጠር እንዳለበትና መንግስትም ለዚህ ምቹ መደላድሎችንና የፖሊሲ አማራጮችን መፈተሽ እንደሚገባው ተናግረዋል፡፡ 

Saturday, 31 May 2014 14:07

ሲያጌጡ ይመላለጡ!

ባለረጃጅም ተረከዝ ጫማዎች
በርካታ ሴቶች ረጃጅም ተረከዝ (ሂል) ያላቸውን ጫማዎች ያደርጋሉ፡፡ እነዚህ ጫማዎች መደበኛውን የሰውነት ክብደት ስርጭት በማዛባትና በእግሮች ላይ ጫና በመፍጠር እግር ያሳብጣሉ፡፡ የእግር ጣቶች አጋማሽ ላይ ድድር እባጮች (Knobs) በመፍጠር የእግርን ውበት ያጠፋሉ፡፡ ሰውነት ቅርፅ መዛባትም ያጋልጣሉ እንዲፈጠርም ሰበብ ይሆናሉ፡፡

አስጨናቂ ቀበቶዎች
ሆድን ጥብቅ አድርገው የሚይዙና ቅርፅን አጉልተው የሚያወጡ ቀበቶዎች፣ በፋሽኑ ዓለም እጅግ የተለመዱ ቢሆኑም በጤና ላይ የሚያስከትሉት ችግር ግን በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ የወገብን ዙሪያ ጥብቅ አድርገው የሚይዙ ቀበቶዎች፣ የአተነፋፈስ ስርአት እንዲዛባ በማድረግ፣ በቂ መጠን ያለው ኦክሲጅን ወደ ሳንባችን እንዳይገባ የግዳሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የምግብ መላም ሂደት እንዲስተጓጎልና ምግብ በአንጀታችን ውስጥ በበቂ ሁኔታ እንዳይንሸራሸር ያደርጋሉ፡፡ ይህም በጨጓራችን ላይ መጨናነቅን በመፍጠር፣ የልብ ማቃጠል ስሜትን ያስከትላል፡፡ ጥብቅ አድርጎ የሚይዝ ቀበቶን ማድረጉ ግድ ከሆነብዎ፣ አለፍ አለፍ እያሉ ቀበቶዎን በማላላት፣ ሰውነትዎን ማዝናናት አስፈላጊ መሆኑን አይዘንጉ፡፡


የጡት መያዣ ጣጣ
በሚያምር የጡት መያዣ ተወጥረው፣ ጉች ጉች ያሉ ጡቶችን ማየት ለተመልካቹ አስደሳች  ቢሆንም ያለልክ የሚደረጉ የጡት መያዣዎች ለተጠቃሚዎቹ ጤንነት አደገኛ ነው፡፡ ፋሽን ተከታይ ሴቶች፤ የጡታቸውን መጠን በማሳነስና ጡታቸውን አጥብቀው በመያዝ ለእይታ ማራኪ የሆነ ቅርፅ የሚያወጡ ጡት መያዣዎችን በብዛት ይጠቀማሉ፡፡
አንዳንድ ሴቶች ዕድሜያቸው እየጨመረና የሰውነት ክብደታቸው እየገዘፈ ቢሄድም፣ ልጅ ቢወልዱም የሚጠቀሙባቸውን የጡት መያዣዎች ቁጥር ለመጨመርና ልካቸው የሆኑ የጡት መያዣዎችን ለማድረግ ፍላጐት የላቸውም፡፡ እነዚህ ያለ ልክ የሚደረጉ ጡት መያዣዎች ደግሞ ትክክለኛ የደም ዝውውርን በማዛባት፣ የጡት አካባቢ ህመሞችን ከመፍጠራቸውም በተጨማሪ በአከርካሪ ላይ ጫና በመፍጠርና፣ እጅግ አደገኛ የሆነ የጀርባ ህመም ሊያስከትሉ ይችላሉ፡፡


ፎርጅድ የፀሐይ መነፅሮች
ጥቋቁር የፀሐይ መነፅሮችን መጠቀም በዘመናችን ወጣቶች ዘንድ እጅግ የተለመደ ነው። ኃይለኛ የፀሐይ ብርሃንን ለመከላከል ይረዳሉ እየተባሉ ከየገበያው ላይ በስፋት እየተሸመቱ የሚደረጉ መነፅሮች ሁሉ የፀሃይ ብርሃንን ይከላከላሉ ብሎ ማመኑ ግን ሞኝነት ነው፡፡ ይልቁንም አንዳንድ ጥቋቁር መነፅሮች፣ ጨረሮችን ወደ አይናችን በመሳብ አይናችንን ለከፍተኛ ጉዳት እንደሚያጋልጡ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ እነዚህ መነፅሮች አይንን የሚጎዱ ዩቪ የተባሉ ጨረሮችን ወደ አይናችን በመሳብ፣ ለአይን መቅላትና ብርሃንን የመቋቋም አቅም ለማጣት ችግር ያጋልጡናል፡፡ ሬቲና የተባለው የአይናችን ክፍል ጉዳትና ካታራክትስ የተባለው የአይን በሽታም በዚሁ መነፅር ሳቢያ እንደሚከሰቱ የህክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ ስለዚህም ለፀሐይ ጨረር መከላከያ የምንጠቀምባቸው መነፅሮች በባለሙያ ማረጋገጥ ይመከራል፡፡


ለጠቅላላ እውቀት
በአውሮፕላን በምንጓዝበት ጊዜ 6 በመቶ ያህል ለጭንቅላት ህመም እንጋለጣለን፡፡
ምድርን ለቀን ወደ ሰማይ ስንወጣ፣ ስበት ስለሚቀንስ ሲሆን ጭንቅላታችን ለአደጋ የመጋለጡ ዕድሉም እየጨመረ ይሄዳል፡፡
አንድ ሰው በቀን 70ሺ ሃሳቦችን የማሰብ አቅም አለው፡፡
የጭንቅላታችን 75 በመቶ ያህሉ ውሃ ነው።
ጭንቅላታችን ኦክስጅን ሳያገኝ በህይወት መቆየት የሚችለው ከ4-6 ደቂቃዎች ብቻ ሲሆን፤ የደም እጥረት ሲገጥመው ደግሞ ከ10 ደቂቃ በኋላ በህይወት አይቆይም፡፡
የጤናማ ሰው አንጎል በአማካይ 100 ቢሊዮን ነርቮች አሉት፡፡
ከአንጎል ወደ አንጎል የሚደረገው የነርቭ ምልልስ አማካይ ፍጥነት፣ በሰዓት 274 ኪ.ሜ ነው፡፡    

ውድ እግዚአብሔር -
ባቢ ቢራ ጠጥቶ ሲመጣ አልወድም፡፡ አፉ መጥፎ መጥፎ ይሸታል፡፡ በዚያ ላይ ይጮህብኛል። አንተ ነህ ቢራ የፈጠርከው? ለምን?
ሳሚ - የ6 ዓመት ህፃን
ውድ እግዚአብሔር -
እሁድ እለት ሙሽሮቹ  ቤተክርስትያን ውስጥ ሲሳሳሙ አየኋቸው፡፡ ፈቅደህላቸው ነው?
ሮዝ - የ5 ዓመት ህፃን
ውድ እግዚአብሔር -
ካንተ የተሻለ ለእግዚአብሔርነት የሚሆን ያለ አይመስለኝም፡፡ እንዲህ ያልኩት እግዚአብሔር ስለሆንክ አይደለም፡፡ የእውነቴን ነው፡፡
ቻርልስ - የ7 ዓመት ህፃን  
ውድ እግዚአብሔር -
ዳይኖሰርን ባታጠፋው ኖሮ መኖር አንችልም  ነበር፡፡ ትክክል ነው ያደረግኸው፡፡  
ኤርሚ - የ7 ዓመት ህፃን
ውድ እግዚአብሔር -
በዓለም ላይ ያሉትን ሰዎች በሙሉ መውደድህ በጣም ያስደንቃል፡፡ እኛ ቤት አራት ሰዎች ብቻ ናቸው ያሉት፡፡ ሁሉንም መውደድ ግን አልቻልኩም፡፡
ናኒ - የ8 ዓመት ህፃን
ውድ እግዚአብሔር -
ሌሊት ሌሊት አስፈሪ ህልሞች አያለሁ። ከእነማሚ ጋር ልተኛ ስል አድገሃል ተባልኩ። አስፈሪ ህልሞች ከየት ነው የሚመጡት? ይሄ የሚመለከተው ሰይጣንን ነው አይደል?
ሔኖክ - የ6 ዓመት ህፃን

Saturday, 31 May 2014 13:56

የፖለቲካ ጥግ

ልበሰለ ፖለቲከኛ ስለቀጣዩ ምርጫ ሲያስብ፣ የበሰለ ፖለቲከኛ ስለቀጣዩ ትውልድ ያስባል፡፡
 ጄምስ ፍሪማን ክላርክ-
መጥፎ ባለስልጣናት የሚመረጡት ድምፅ በማይሰጡ መልካም ዜጐች ነው፡፡
 ጆርጅ ዣን ናታን-
ትናንሾቹን ሌቦች አንገታቸውን ለገመድ እየሰጠን፣ትላልቆቹን ሌቦች ለመንግስት ሥልጣን እንሾማቸዋለን፡፡
           ኤዞፕ
ፈጣሪ  ድምፅ እንድንሰጥ ቢፈልግ ኖሮ እጩዎችን ያቀርብልን ነበር፡፡
ጄይ ሌኖ
ፖለቲካ እንደ ጦርነት የሚረብሽ ብቻ ሳይሆን ከጦርነትም የበለጠ አደገኛ ነው፡፡ በጦርነት አንዴ ብቻ ነው የምትገደለው፡፡ በፖለቲካ ግን ብዙ ጊዜ ትገደላለህ፡፡
 ዊንስተን ቸርችል
ፖለቲካ ደም መፋሰስ የሌለበት ጦርነት ሲሆን  ጦርነት ደም መፋሰስ ያለበት ፖለቲካ ነው፡፡
ማኦ ዜዶንግ  
ለአሜሪካ ፕሬዚዳንትነት ሁለት እጩዎች ብቻ በሚቀርቡባት አገር፣ እንዴት ለሚስ አሜሪካ 50 እጩዎች ይቀርባሉ?
 ያልታወቀ ደራሲ

የመንግስት ፕሮጀክቶችና የሃብት ብክነት
መንግስት ቢዝነስ ውስጥ ገብቶ ሲያቦካና ኢኮኖሚው ውስጥ ድርሻው እያበጠ ሲመጣ፤ የዚያኑ ያህል የሃብት ብክነትና ቀውስ መፈጠሩ አይቀርም። ድሃ አገራት ውስጥ የሚፈጠረውን ብክነት ለመቁጠር መሞከር አስቸጋሪ ነው። ከብልፅግና ርቀው በድህነት የሚሰቃዩት ለምን ሆነና? ብዙ ሃብት ስለሚባክን ነው። መንግስት በገነነባቸው ድሃ አገራት ይቅርና፣ በአሜሪካና በአውሮፓ ውስጥም የመንግስት ብክነት ቀላል አይደለም። አንዳንድ ምሳሌዎችን ልጥቀስ-  ከአገራችን የመንግስት ብክነት ጋር እያያዝኩ፡፡ ቀለል ባሉት ብክነቶች እንጀምር፡፡
ጣሊያን እና ኢትዮጵያ
የጣሊያን መንግስት ከተመሳሳይ የአውሮፓ አገራት የሚለይበት ነገር ቢኖር፤ በመኪና ግዢ የሚስተካከለው አለመኖሩ ነው። ተመሳሳይ የሕዝብ ብዛትና የኢኮኖሚ ደረጃ ካላቸው አገራት ጋር ሲነፃፀር፤ የጣሊያን መንግስት በ10 እጥፍ የሚበልጡ መኪኖች እንዳሉት የዘገበው ዘ ኢኮኖሚስት፤ የመኪኖቹ ቁጥር 630ሺ ገደማ እንደሆነ ገልጿል። ከ10 ቢ. ዶላር በላይ ገንዘብ የባከነውና መኪኖች በገፍ የተገዙት በቂ ገንዘብ ስላለ አይደለም። ግን፤ መንግስት ገንዘብ መበደር ይችላል። የጣሊያን መንግስት እዳ፤ ከአመት አመት ሲከማች፣ አሁን 2.8 ትሪሊዮን ዶላር ደርሷል (2800 ቢሊዮን ዶላር!)። የመንግስትን የገንዘብ ብክነት እቀንሳለሁ በማለት ቃል የገቡት አዲሱ የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ለመነሻ ያህል 1500 የመንግስት የቅንጦት መኪኖችን ለመሸጥ ወስነዋል።
የኢትዮጵያ የሃብት ብክነት በጣም በጣም ይለያል። የተገዙ መኪኖች አገልግሎት ሳይሰጡ ይበላሻሉ፤ ሳይጠገኑ ይቆማሉ፡፡ ከትልልቅ የመንግስት ድርጅቶች መካከል አንዱ የሆነው የውሃ ስራዎች ድርጅትን ማየት ይቻላል፡፡ ከአገልግሎት ውጭ የሆኑትን ሳይቆጠሩ 900 ገደማ ትልልቅ የኮንስትራክሽን መኪኖችና ማሽኖች አሉት፡፡ ነገር ግን ግማሾቹ ያለ አገልግሎት ቆመዋል፡፡
አብዛኞቹ ግማሽ አመት ገደማ ጋራዥ ውስጥ የተቀመጡ ናቸው፡፡ እናም የተለያዩ የግንባታ መኪኖችን ይከራያል፡፡ በአመት ለኪራይ ምን ያህል እንደሚያወጣ ታውቃላችሁ? አምና የድርጅቱ ጠቅላላ በጀት 1.8 ቢሊዮን ገደማ ነበር፡፡ ከዚህ ውስጥ አምና ወደ 700 ሚሊዮን ብር የወጣው ለተሽከርካሪዎች ኪራይ ነው፡፡ በእያንዳንዷ ቀን 1.9 ሚ. ብር መሆኑ ነው፡፡
በየቀኑ አንድ ገልባጭ መኪና ለመግዛት የሚያስከፍል ገንዘብ ለኪራይ ይከፍላል፡፡ በመንግስት አማካኝነት ከቻይና ተገዝተው የመጡ በመቶ የሚቆጠሩ “ሃይገር ባሶች” ንም መመልከት ይቻላል፡፡ ብዙዎቹ  በሁለት አመት እድሜ ከአገልግሎት ውጭ ሆነዋል፡፡ በድሃ አገር አቅም የሃብት ብክነቱ ከአውሮፓም ይብሳል፡፡   
ፈረንሳይ እና ተንዳሆ
በፈረንሳይ መንግስት ትዕዛዝ የተሰሩ ባቡሮች፣ ሰሞኑን መወዛገቢያና መሳለቂያ ሆነው ሰንብተዋል። የባቡሮቹ ስራ የተጀመረው ከሶስት አመት በፊት ቢሆንም፤ የጎን ስፋታቸው ከብዙዎቹ የባቡር ፌርማታዎች እንደሚበልጥ የተወራው ሰሞኑን ነው። ዎልስትሪት ጆርናል እንደዘገበው፤ በአገሪቱ ውስጥ ካሉት ከስምንት ሺ በላይ ፌርማታዎች መካከል፣ 1300 ያህሉ አዳዲሶቹን ባቡሮች ማሳለፍ አይችሉም። ሚኒስትሮችና የፓርላማ ፖለቲከኞች፣ የባቡር ድርጅት ባለስልጣናትና ቢሮክራቶች፣ አንዱ በሌላው ላይ ጣት እየቀሰሩ ቢወዛገቡም፣ መሳለቂያ ከመሆን አላመለጡም። ባቡሮቹን ደፍጥጦ ማሳነስ አይቻል ነገር! ፌርማታዎቹን ከጎንና ከጎን እየሸራረፉ ትንሽ ሰፋ ለማድረግ፣ ወደ 70 ሚሊዮን ዶላር ይመደባል ተብሏል - 1.4 ቢሊዮን ብር ገደማ መሆኑ ነው።
በኤልፓ የተገዙ መአት ትራንስፎርመሮች፣ ምን ሆነው እንደተገኙ ታውቁ ይሆናል፡፡ በጣም ያረጁና በየእለቱ የሚበላሹ የሃብት ብክነት ሆነው አረፉት፡፡ በየከተማው የቄራ ድርጅት እንሰራለን ተብሎ ሲሞከርስ ምን ተፈጠረ? የቄራው የጣሪያ ከፍታ፣ ለከብት እርድ እንደማይበቃ የተረጋገጠው ግንባታው ከተጠናቀቀ በኋላ ነው፡፡
የአገሪቱን የስኳር ምርት ከሁለት እጥፍ በላይ ያሳድጋል ተብሎ ከ10 አመት በፊት የተጀመረውን የተንዳሆ እቅድ ብንተወው ይሻላል፡፡ ቢሊዮን ብሮች የፈሰሰበት ፕሮጀክት ምን ያህሉ ለብክነት እንደተዳረገ አስቡት፡፡
አንድ ምሳሌ ብቻ ልጥቀስላችሁ፡፡ ለብዙ አመታት ከተጓተተ በኋላ ለስኳር ፋብሪካው የሚውል የሸንኮራ አገዳ በ5ሺ ሄክታር  መሬት ላይ ተተከለ፡፡ ፋብሪካው ግን ገና ነው፡፡ ምንም ማድረግ አልተቻለም፡፡ ሸንኮራው ባከነ - የ100ሚ ብር ብክነት፡፡
እንግሊዝ፡
የአገሪቱ አቃቤ ሕጎች፣ የወረቀት መዛግብት ከሚሸከሙ፣ በዘመኑ ቴክኖሎጂ እንዲጠቀሙ ተብሎ ነው 4600  ታብሌቶች (ጠፍጣፋ ሚኒኮምፒዩሮች) የተገዙት። ፍርድ ቤት ውስጥ ክርክር ሲያካሂዱም ሆነ ምስክሮችን ሲያፋጥጡ፣ ወረቀቶችንና ፋይሎችን መያዝ አያስፈልጋቸውም - ታብሌት ተሰጥቷቸዋል። አቃቤ ህጎቹ “ጥሩ ሃሳብ ነበር፤ ግን በታብሌቶቹ ክብደት እጃችን ዛለ” የሚል ቅሬታ ማሰማታቸውን የዘገበው ዋየርድ መፅሄት፤ የታብሌቶቹ ክብደት ወደ 2 ኪሎ ግራም ገደማ መሆኑን ገልጿል። እንደ ላባ የቀለሉ ታብሌቶችን ትቶ፣ እንደ ብረት የከበዱ ታብሌቶችን የገዛው ማን ይሆን? ያው የመንግስት ቢሮክራት ነዋ። እና ምን ተሻለ? የታብሌት ማስቀመጫ አትሮንስ በብዛት ለመግዛት ተወሰነ። ይሄ ትንሹ ብክነት ነው።
የእንግሊዝን የጤና ኢንሹራንስና አገልግሎት፣ በዘመናዊ የኢንፎርሜሽንና ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ለማሻሻል አዲስ ፕሮጀክት የተጀመረው በ2007 ነው። ከዚያ ወዲህ ለፕሮጀክቱ ከ15 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ ፈስሷል። ውጤቱስ? የጤና ኢንሹራንስና አገልግሎት ትርምስምሱ ወጣ። ለማስተካከል እንዳይሞከር ደግሞ፤ ቴክኖሎጂው ጊዜው ያለፈበት ሆኖ ተገኘ። እናም፤ ሙሉ ለሙሉ በአዲስ ፕሮጀክት ሊለወጥ ይገባል ተብሏል። 15 ቢ. ዶላር ቀለጠች (300 ቢሊዮን ብር?)
ስኩል ኔት፣ ወረዳ ኔት፣ የዩኒቨርስቲዎች ቪዲዮ ኮንፈረንሲንግ ማዕከላት እየተባለ ስንት ቢሊዮን ብር እንደወጣ ይታወቃል። አንዳንዶቹ ከአስር አመት በላይ አስቆጥረዋል፤ አንዳንዶቹ ደግሞ አምስት አመት። እነዚህ ፕሮጀክቶች ምን አገልግሎት እየሰጡ ይሆን? ስኩል ኔት እና ወረዳ ኔት ለምን አገልግሎት ሊውሉ እንደሚችሉ እየታሰበበት ነው። የዩኒቨርስቲ ቪዲዮ ኮንፈረንሲንግ ማዕከላት፣ በወር አንዴ ለዚያውም ለጥቂት ደቂቃዎች ነው አገልግሎት የሚሰጡት። አንዳንዶቹማ ፣ በአመት አንዴ ከተከፈቱም ድንቅ ነው።
አሜሪካ እና ጀርመን ከአገራችን ጋር
የአሜሪካ መንግስት፣ አገልግሎት የማይሰጡ 50ሺ ቤቶች እንዳሉት የገለፀው ሄሪቴጅ ፋውንዴሽን፣ ለእነዚህ ቤቶች እድሳት በየአመቱ 25 ቢሊዮን ዶላር በጀት ይመደባል ብሏል። (በኢትዮጵያ አቅም፣ ስንት ሺ ቤቶች ናቸው፣ ሳይከራዩ ወይም ለሽያጭ ሳይቀርቡ ለአምስት አመታት ሲበላሹ የቆዩት?)
ለስልጠና፣ ለምግብ ዋስትና፣ ለማቋቋሚያ... ለምናምን እየተባለ በየአመቱ 125 ቢሊዮን ዶላር ገደማ በጀት ይመደባል - በአሜሪካ። አብዛኛው በጀት በከንቱ እንደሚባክን የገለፁት ጥናት እንዲያካሂዱ የተመደቡ የመንግስት ኦዲተሮች ናቸው። ወደ ሩብ ያህል የሚጠጋው በጀት ግን ሙሉ ለሙሉ ያለ አንዳች ውጤት የሚባክን ነው ብለዋል ኦዲተሮቹ - ወደ 30 ቢ. ዶላር በየአመቱ።
በአገራችንም እንዲሁ፣ ለምግብ ዋስትናና ለስልጠና፣ ለጥቃቅንና ለአነስተኛ ተቋማት፣ ለብድርና ለገበያ ትስስር በሚሉ እልፍ ሰበቦች ብዙ ብር ይባክናል፡፡
በየአመቱ ለግብርና ዘርፍ ከሚመደበው የብዙ ቢሊዮን ብር በጀት ውስጥ ገሚሱ፣ “የምግብ ዋስትና” ተብሎ ለሚታወቀው የድጐማና የእርዳታ ፕሮጀክት የሚውል ነው፡፡ 7.5 ሚሊዮን ያህል የገጠር ተረጂዎችንና ተደጓሚዎችን በመደገፍ ራሳቸውን እንዲችሉ አደርጋለሁ የሚለው መንግስት፤ በዚህ አመት ቁጥራቸውን ወደ 2 ሚሊዮን ዝቅ ለማድረግ አቅዶ ነበር - የዛሬ አራት አመት። ነገር ግን የተረጂዎቹና የተደጓሚዎቹ ቁጥር አሁንም ወደ 7 ሚሊዮን ገደማ ነው፡፡
ከእነዚህ በተጨማሪ የውጭ እርዳታ የሚቀበሉ 6.5 ሚሊዮን ሰዎች መኖራቸውን አትዘንጉ፡፡ በድምር 13 ሚሊዮን ተረጂ ማለት ነው፡፡ ጥቃቅንና አነስተኛ የምርት ተቋማትን በስልጠናና በብድር በመደገፍ በየአመቱ ከ15 በመቶ በላይ እንዲያድጉ የወጣው እቅድስ? በአንድ በኩል እቅዱ ሙሉ ለሙሉ…ከዚያም በላይ ተሳክቷል። ከታቀደው በላይ ለብዙ ወጣቶችና ተቋማት ስልጠና ተሰጥቷል - ብዙ ገንዘብ ተመድቦላቸው፡፡ በቢሊዮን ብር የሚቆጠር ብድርም ተከፋፍሏል፡፡ ተሳክቷል፡፡ በሌላ በኩል ግን እቅዱ በጭራሽ አልተሳካም፡፡ እንዲያውም ከሌሎቹ የኢኮኖሚ ዘርፎች ጋር ሲነፃፀር አነስተኛና ጥቃቅን አምራች ተቋማት አመታዊ እድገታቸው፤ ባለፉት ሦስት አመታት እየቀነሰ አምና ወደ 3 በመቶ ወርዷል፡፡ በቢሊዮን ብር የሚቆጠር ሃብት በከንቱ ባከነ አትሉም?
ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ልጅ ገመድ ዝላይ ከሚዘሉ ልጆች ጋር ሊጫወት ከቤቱ ይወጣል፡፡ አባቱ ከፎቅ ሆኖ የስተውለዋል፡፡
አባትየው የሚያየውን ለማመን አልቻለም፡፡
ልጁ ገመዱን የሚያዞሩትን ልጆች፤
“እኔንም ገመድ ዝላይ አጫውቱኝ?” ሲል ጠየቃቸው፡፡
“እሺ ዝለል” አሉት፡፡
ልጁ መዝለል ጀመረ፡፡
ልጆቹም ገመዱን ማዞር ቀጠሉ፡፡
አስገራሚው ነገር ግን ልጁ የሚዘለው ሌላ ቦታ ነው፤ ልጆቹ ገመዱን የሚያዞሩት ሌላ ቦታ ነው፡፡ ልጁ መዝለውን ቀጠለ፡፡
ልጆቹ ይቀልዱበታል፡፡ ይስቁበታል፡፡ እሱ መዝለሉን ቀጥሏል፡፡ አይፎርሽም፡፡ ደስ ብሎታል፡፡
አባትዬው በሁኔታው አዝኖ ከፎቅ ወርዶ መጥቶ ልጁን መዝለሉን አስቆመውና ወደቤት አስገባው፡፡ ልብሱን አስቀይሮ ወደ ሐኪም ቤት ወሰደው፡፡ ሐኪሙም፤
“ምን ችግር ገጠማችሁ፤ ምን ልርዳችሁ?” አለ
አባት ልጁ ሲጫወት ምን ያደርግ እንደነበረ ገለጠለትና “ምናልባት ልጄ አንድ ዓይነት የአዕምሮ ወይም አካላዊ ችግር እንዳይኖርበት ብዬ ነው” ሲል አስረዳ፡፡
ሐኪሙ ለልጁ ብዙ ምርመራ ካደረገለት በኋላ የዓይን ችግር እንዳለበት አረጋገጠና መነፅር አዘዘለት፡፡
ልጁ መነፅር ተገዛለት፡፡ መነፅሩን አድርጐ ወደ ገመድ ዝላይ ጨዋታው ሄደ፡፡
አሁን በትክክል ገመዱ ማህል ገባ፡፡ አዞሩለት፡፡ በትክክል መዝለል ጀመረ፡፡ አንዳንዴ ነው እንጂ አልፎረሸም፡፡ ቀጠለ ዝላዩን!!
*    *    *
ገመዱ በሌለበት የምንዘል አያሌ ነን፡፡ ሐኪም ያላየ ዐይን ያለን በርካታ ነን፡፡ በትክክል እንዳልዘለልን እያዩ፣ እየታዘቡ፤ እየሳቁ፣ እየተሳለቁ የሚያዩንም ብዙ ናቸው፡፡ ገመድ ማዞሩን እንደስራ ቆጥረው ዕድሜ - ልካቸውን ቢሮክራሲው ውስጥ የሚኖሩም የትየለሌ ናቸው፡፡ እንደ መልካም አባት ያለ መልካም መሪ፣ መልካም ኃላፊ፣ መልካም አለቃ የልጁን ችግር ተረድቶ ወደሀኪም ዘንድ ይወስዳል፡፡ ለችግሩ መፍትሔ ይፈጥራል፡፡
የሚስቁ፣ የሚሳለቁትን ሁሉ ኩም ያደርጋቸዋል፡፡ “የሚሠሩትን አያውቁትምና ይቅር በላቸው” ይላቸዋል፡፡
በገመድ ዝላይ መፎረሽ እንግዳ ነገር አይደለም፡፡ ግን የፉረሻውን ቁጥር መቀነስ ይቻላል። ከገመዱ ውጪ መዝለል ከጨዋታው ውጪ ነው ቢባልም፣ ልምዱ ግን ቀላል አደለም ብሎ መከራከርም ይቻላል፡፡ የልጁ የዕይታ ችግር (Sight problem) የሁላችንም ችግር ቢሆንስ ብለን ማሰብ አለብን (myopic or farsighted እንዲል ፈረንጅ - የአፍንጫ ሥር ማየትና አርቆ - ማስተዋል እንደማለት)፡፡ ማመን ነው እንጂ አለማመን ምን ያቅታል፤ ይላል አንድ ፀሐፊ
ዕውነትን መሠረት ካደረግን ውሸትን መናቅ ቀላል ነው፡፡
“ሐሰተኞች ሰዎች ቢምሉ ቢገዘቱ ነገራቸውን በአየር ላይ በሚበሩና ፍለጋቸው በማይገኝ ዎፎች መስለው፡፡ ለመብረራቸው ፍለጋ እንደሌለው፤ ሐሰተኞች ሰዎች ለሚናገሩትም ነገር ሥር መሠረት የለውምና” ይላሉ የአገራችን ፈላስፎች፡፡
በነባራዊነትና በህሊናዊነት አንፃር ከተመለከትን የማይዋሹ ነገሮችን መዋሸት ጅልነት ነው። አንድ አዛውንት “እንዴት ፖለቲከኛ ለመሆን ቻሉ?” ተብለው ቢጠየቁ፤ “የዕውቀት ማነስ ነው ፖለቲከኛ ያደረገኝ!” አሉ፤ አሉ፡፡ “አንተስ የአገራችን ምሁር ያደረገህ ምንድነው?” ብለው አዛውንቱ ቢጠይቁት “ያው መማሬ ይመስለኛል ሌላ ሰበብ አይሰማኝም” አለ ምሁሩ፡፡ አዛውንቱም “አንተን ምሁር ያረገህ ደሞ ምን መሰለህ?...የዕውነት ማነስ!” አገራችን ከእኒህ አዛውንት ዕሳቤ ውጪ አይደለችም፡፡ የዕውነትና የዕውቀት ማነስ ፖለቲከኛም፣ ምሁርም አድርጐናል፡፡ ያወቀ ያውቀዋል። ያለቦታው ገመድ መዝለልም ክህሎት ይሆናል፡፡ በዛሬ ግንቦት ሃያ ማግስት ሆነን፣ “አንጋረ - ፈላስፋ” የሚለው መፅሐፍ የሚለንን ብናስብ ፀጋ ነውና እነሆ:-
“ዕውነትን መናገር፣ በሐሰት ከመማል መራቅ፣ ሰውን ፊትን አብሮቶ መቀበል፣ እንግዶችን አክብሮ መቀበል፣ በጐ ሥራ መሥራት፣ ጐረቤትን ተጠንቅቆ መያዝ፣ Uዕቢትን አለማድረግ፣ ሁልጊዜ ሰውን ማክበር፣ ትህትናን ማዘውተር፣ አንደበትን ክፉ ከመናገር መግታት፣ ቀናውን ነገር መናገር፣ ለሁሉም በቅንነት መመለስ፣ የወንድምን ኃጢያት መሠወር፣ ሽንገላን (ምሎ - መክዳትን) መተው፣ ጉባዔ ፊት ጮክ ብሎ አለመናገር” እነዚህን ቃላቶች ሁሉ ገንዘብ ያደረገ ሰው በዕውነት አዋቂ ነው፣ ዐዋቂ ይባላል”
ትርጓሜውም፤ ባጭሩ፤
“ዕምነትህን አትካድ፡፡ ከጐረቤት ጠንቅ መጠበቅ፡፡ የፖለቲካ አቀባበልና አያያዝን ማወቅ። በፓርላማ ፊት አለመፎከር፡፡ መሬት ላይ ምን እንደሚጠብቀን አናውቅምና፡፡” ይሄ የወቅቱ መልዕክት ይሁነን፡፡
ነብሳቸውን ይማረውና አባ ጳውሎስ ረዥም ፍትሐተ - ፀሎት ያደረጉለት፤ ነብሱን ይማረውና የአድዋው ደራሲ ስብሃት ገ/እግዚአብሔር፤
“ግንቦት ሃያን እንዴት ታየዋለህ?” ሲባል፤
“እንደሰኔ ሃያ” ያለው አይረሳንም፡፡
ድሎቻችንን አንረሳም፡፡ ሌላ ድል ለማስመዝገብ የቀደሙት ድሎች ከትውስታነት ባሻገር አገልግሎት የላቸውም፤ እንደ አድዋ ድል ሁሉ፡፡ ወሳኙ የዛሬ ዝግጁነታችን ነው፡፡ የዛሬ ማንነታችን ነው፡፡ የሚከፈለን ካሣም በወቅቱ ፍሬ ነበረ፡፡ ወደ ሰላማዊ ትግል ስንዘዋወር ምርቱ ለሌላ ዕድገት መስፈንጠሪያ - ድልድይ (Spring Board) ሆኗል፡፡ ስለዚህም ጊዜው ብዙ መናገሪያ ሳይሆን ማድረጊያ ሆኗል ማለት ነው፡፡ መስከረም ሁለትን ከግንቦት ሃያ የሚለየው ይሄ ነው፡፡ ድፋትና ቅናት ነው በያሬድኛ፡፡ ትንሽ ምላስ እና ብዙ እጅ እንደማለት ነው፡፡ ይሄ ለተቃዋሚም፣ ለአልተቃዋሚም፣ ለአዘቦት - ሰውም ዕውነት ነው፡፡
ለዚህ ነው ከምዕተ - አመታት በፊት የነበሩ ፈላስፎቻችን፤ “ድምፅን ከፍ አድርጐ በመጮህ ቤት የሚሠራ ቢሆን፤ አህያ በቀን በቀኑ ሁለት ቤት በሠራ ነበር!” ያሉት፡፡   

አባል ለመሆን፤ በቴሌኮም፣ በባንክና በኤሌክትሪክ ሃይል ኢንዱስትሪው የመንግስትን ድርሻና ቁጥጥር መቀነስ ግዴታ ነው

የኢትዮጵያ መንግስት በቴሌኮምና በባንክ ዘርፎች ላይ ያለውን ከፍተኛ ድርሻና ቁጥጥር በማቆም ዘርፎቹን ለአገር ውስጥና ለውጭ ኢንቨስትመንት እንዲከፍት የሚገደድ ከሆነ በመጪው አመት የአለም የንግድ ድርጅት አባል የመሆን እቅዱን እንደሚያራዝም የንግድ ሚኒስትር አቶ ከበደ ጫኔ ተናገሩ፡፡
ሚኒስትሩ ባለፈው ማክሰኞ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት እንደተናገሩት፣ የአለም የንግድ ድርጅት አባል አገራት የኢትዮጵያ መንግስት የቴሌኮምና የባንክ አገልግሎት  ለአለማቀፍ ውድድር ክፍት የሚያደርግበትን ጊዜ በተመለከተ ተደጋጋሚ ጥያቄዎች እያቀረቡ ነው፡፡
“የአገልግሎት ዘርፉን በተመለከተ በርካታ ጥያቄዎች እየተነሱ ይገኛሉ፡፡ የቴሌኮም፣ የባንክ እና የኤሌክትሪክ ሃይል ኢንዱስትሪዎችን ለግል ባለሃብቶች ክፍት የምናደርግበትን ጊዜ በግልጽ እንድናሳውቅ በተደጋጋሚ እንጠየቃለን” ያሉት ሚኒስትሩ፤ “የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድን ከማጠናቀቃች በፊት፣ የህግ ማሻሻያዎችን በማድረግ የአገልግሎት ዘርፉን ለአገር ውስጥና ለውጭ ኢንቨስትመንት ክፍት እንድናደርግ ጫና እየተደረገብን ይገኛል” ብለዋል፡፡
መንግስት ጉዳዩን በጥንቃቄ እንደሚይዘው ሚኒስትሩ ጠቅሰው፣ ከአለም የንግድ ድርጅት አባልነት ጋር በተያያዘ አስገዳጅ ቅድመ ሁኔታዎች የሚቀርቡ ከሆነ፣ አገሪቱ በ2015 አባል ለመሆን የያዘችውን ዕቅድ ልታራዝም ትችላለች ብለዋል፡፡
ከሁለት አመታት በፊት የጸደቀው የአለም የንግድ ድርጅት አዲስ ህግ፣ የእድገት ደረጃቸው እጅግ አነስተኛ የሆኑ የአለም አገራት የድርጅቱ አባል ለመሆን የሚችሉበትን መስፈርት በመጠኑ ቀለል እንዳደረገ የዘገበው ሮይተርስ፤ ድሃ አገራት የተለያዩ ዘርፎችን ቀስ በቀስ ወደ ግል ኢንቨስትመንት እንዲያዘዋውሩና ደረጃ በደረጃ ለአለማቀፍ ውድድር ክፍት እንዲያደርጉ የሚፈቅድ መሆኑን አስታውሷል፡፡
“የትኞቹ የአገሪቱ ህጎች ከአለም የንግድ ድርጅት ጋር እንደሚጣጣሙና፣ የትኞቹ እንደሚጣረሱ እየገመገምን ነው” ያሉት አቶ ከበደ፤ “እ.ኤ.አ በ2015 የንግድ ድርጅቱ አባል ለመሆን የያዝነው ዕቅድ ሊራዘም ይችላል” ብለዋል፡፡
አሁን ባለበት ሁኔታ አገሪቱን የአለም የንግድ ድርጅት አባል ለማድረግ ኢኮኖሚው አነስተኛ እንደሆነና የበለጠ ማደግ እንደሚገባው የገለጹት ሚኒስትሩ፤ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ የምትገኘው ቻይና፣ የአለም የንግድ ድርጅትን አባል  ለመሆን በርካታ አመታት ወስዶባታል ብለዋል፡፡
በፍጥነት በማደግ ላይ የሚገኘው የአገሪቱ ገበያ በተለይ በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የውጭ አገራት ባለሃብቶችን መሳብ በመቻሉ፣ በርካታ የስዊድን፣ የቻይና እና የቱርክ ባለሃብቶች በዘርፉ ሰፊ ስራ እያከናወኑ እንደሚገኙ የጠቆመው የሮይተርስ ዘገባ፤ የአገሪቱ ህጎች የቴሌኮም እና የባንክ አገልግሎት በመሳሰሉ ፖለቲካዊ ችግር ሊያስከትሉ ይችላሉ ተብለው በሚታሰቡ ዘርፎች የውጭ ኢንቨስትመንትን ያግዳሉ ብሏል፡፡

ካቻምናም ታፍኛለሁ፣ ዘንድሮ ግን በህግ እጠይቃለሁ ብሏል

ተቀማጭነቱን በሳዑዲ አረቢያ ያደረገውና በርካታ የቴሌቪዥን ጣቢያዎችን በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚያሰራጨው የአረብ ሳተላይት ኮሙኒኬሽን ተቋም (አረብሳት) ካለፈው ሳምንት ጀምሮ እየተፈጸመበት ያለው ዓለማቀፍ የሳተላይት ሞገድ አፈና (Jamming) ምንጩ ከኢትዮጵያ መሆኑን እንዳረጋገጠ ገለጸ፡፡
ሳትኒውስ የተባለው የአገሪቱ የዜና ምንጭ ከትናንት በስቲያ እንደዘገበው፣ አረብሳት በሚያስተላልፋቸው በርካታ የቴሌቪዝን ጣቢያዎቹ ላይ መታየት የጀመረውን የስርጭት መስተጓጎል መነሻ ለማወቅ ባደረገው በረቂቅ ቴክኖሎጂ የታገዘ ጥናት፣ ከኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ የሚነሳና ሆን ተብሎ የሚፈጸም የሳተላይት ሞገድ አፈና (Jamming) እየተደረገበት መሆኑን ማረጋገጡን አስታውቋል፡፡ ይህን መሰሉ ህገወጥ ድርጊት መፈፀሙ መሆኑ እጅግ እንዳሳዘነው ያስታወቀው አረብሳት፤ ከኢትዮጵያም ሆነ ከኤርትራ የሚተላለፍ ምንም አይነት ስርጭት ሳይኖረው፣ የሳተላይት ሞገድ አፈና መደረጉ እንቆቅልሽ እንደሆነበት ገልጿል፡፡
የሳተላይት ሞገድ አፈናው፣ ምናልባትም ከሁለቱ አገራት የአንዱ ተቀናቃኝ የሆኑና ከአረብሳት ሳተላይቶች አቅራቢያ በሚገኙ ሳተላይቶች አማካይነት የሚሰራጩ የቴሌቪዝን ጣቢያዎችን ለማፈን የታለመ ሊሆን እንደሚችል ያለውን ግምትም ሰጥቷል፡፡
እየተፈጸመበት ያለውን ህገወጥ ተግባር ለመመከት በብሄራዊና በአለማቀፍ ደረጃ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን የገለጸው አረብሳት፣ ጉዳዩን ለዓለማቀፉ የቴሌኮምኒኬሽን ህብረት እና ለአረብ ሊግ ማሳወቁንም ጠቅሷል፡፡አረብሳት ጉዳዩን በቀጣይ ከመረመረ በኋላ፣ ከአለማቀፍ የህግ  ተቋማትና የአገሪቱ የህግ አካላት ጋር በመቀናጀት ወደ ህግ እንደሚያመራና እየተቃጣበት ባለው የሳተላይት ሞገድ አፈና ለደረሰበትም ሆነ ለሚደርስበት ጉዳት ካሳ እንደሚጠይቅ  ማቀዱን ተናግሯል፡፡ከሁለት አመታት በፊት ከኢትዮጵያ ተመሳሳይ የሳተላይት ሞገድ አፈና እንደተፈጸመበትም አስታውሷል።