Administrator

Administrator

                በዓመቱ መጀመሪያ በመስከረም ወር 2006 ዓ.ም ለ12 ዓመታት የአገሪቱ ፕሬዚዳንት በመሆን ያገለገሉት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ፤ ከስልጣናቸው የወረዱ ሲሆን በቦታቸውም ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ተተክተዋል፡፡ በአምባሳደርነት ዘመናቸው የውጭ አገር ኢንቨስተሮችን ወደ ኢትዮጵያ በማምጣትና አገር ውስጥ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ በማግባባት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከታቸው የሚነገርላቸው ዶ/ር ሙላቱ፤ የፕሬዚዳንትነት ስልጣናቸውን ከተረከቡ በኋላም ሥራቸው በቤተመንግስት አካባቢ የተገደበ አልሆነም፡፡ በተለያዩ አገራት እየዞሩ የውጭ ኢንቨስተሮችን የማግባባት ሥራቸውን ቀጥለውበታል፡፡
በዓመቱ ከተከናወኑ አነጋጋሪ ጉዳዮች መካከል አንድነት ፓርቲ ከሰላማዊ ሰልፍ ጋር በተገናኘ የመብት ጥሰትና መጉላላት ተፈጽሞብኛል በማለት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባንና የከተማዋን ፖሊስ ኮሚሽን በፍ/ቤት መክሰሱ ተጠቃሽ ነው፡፡
ፍ/ቤቱም ጉዳዩን ከመረመረ በኋላ “ክሱ ለክስ የሚያበቃ ምክንያት የለውም፣ አስተዳደራዊ ውሣኔ ያገኝ የሚል ውሣኔ የሰጠ ሲሆን ፓርቲውም በጊዜው ይግባኝ እንደሚጠይቅ ገልፆ ይግባኝ ለመጠየቅ በሂደት ላይ ይገኛል፡፡  
የቀድሞ የአንድነት ፓርቲ ሊቀመንበር ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ፣ እንዲሁም የኢዴፓ መስራችና ሊ/መንበር የነበሩት አቶ ሙሼ ሰሙ ራሳቸውን ከፖለቲካ ፓርቲ ያገለሉት በዚሁ ባሳለፍነው ዓመት ነው፡፡ ዶ/ር ነጋሶ ከጤና ጋር በተያያዘ፣ አቶ ሙሼ ደግሞ “የጥሞና ጊዜ እፈልጋለሁ” በሚል የፓርቲ ፖለቲካ በቃን ብለዋል፡
ሹመትና ህልፈት
የአማራ ክልልን ለ8 ዓመታት በርዕሰ መስተዳደርነት የመሩት አቶ አያሌው ጎበዜ፣ የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳደር የነበሩት አቶ ሽፈራው ሽጉጤ በአምባሳደርነትና በትምህርት ሚኒስትርነት የተመደቡት ባሳለፍነው ዓመት ሲሆን የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር የነበሩት አቶ አለማየሁ አቶምሳ ባደረባቸው ህመም ህክምና ሲከታተሉ ቆይተው ህይወታቸው ማለፉ ይታወሳል፡፡ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የህዝብ ተሳትፎና ንቅናቄ ክላስተር አስተባባሪና የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስትር የነበሩት አቶ ሙክታር ከድርም የክልሉ ፕሬዚዳንት በመሆን የተሾሙ ሲሆን  በሳቸው ቦታ ወ/ሮ አስቴር ማሞ ተተክተዋል፡፡
የሳኡዲ ስደተኞችን ማባረር
የሳኡዲ አረቢያ መንግስት የመኖሪያ ህጋዊ ፍቃድ የላቸውም በሚል ኢትዮጵያዊያንን ጨምሮ የበርካታ ሃገር ዜጎችን ከሃገሩ በኃይል ማስወጣት የጀመረው ባሳለፍነው ዓመት ጥቅምት ወር  መጨረሻ ገደማ ነበር፡፡ የሳኡዲ አረቢያ መንግስት ህገወጥ ስደተኞች ባላቸው ላይ በወሰደው የማባረር እርምጃ ከ150ሺ በላይ ኢትዮጵያውያን ወደ ሃገር ቤት መመለሳቸው የሚታወስ ሲሆን የዓለም አቀፍ ሚዲያዎችን ትኩረት በሳበው በዚህ ክስተት፣ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በሳኡዲ ኤምባሲዎች በር ላይ ሰላማዊ ሰልፍ በማድረግ ተቃውሞአቸውን ገልፀዋል፡፡ በአዲስ አበባ ለተመሳሳይ ዓላማ ሰማያዊ ፓርቲ የጠራው ሰላማዊ ሰልፍ ግን በፖሊስ በመበተኑ ሳይደረግ ቀርቷል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት በየአረብ ሃገራቱ ለስራ የሚጓዙ ዜጎች ጉዳይ አሳስቦኛል በማለት ወደ የትኛውም የአረብ ሃገራት ለጉልበት ስራ የሚደረግን ጉዞ ለ6 ወር ያህል ማገዱ የሚታወስ ሲሆን እገዳው 9ኛ ወሩን ቢይዝም እስካሁን አልተነሳም፡፡
“የረዳት አብራሪው የአውሮፕላን ጠለፋ”
በኢትዮጵያ አየር መንገድ ለ5 ዓመታት በረዳት አብራሪነት ያገለገለው ሃይለመድህን አበራ፤ በጥር ወር አጋማሽ ላይ ከአዲስ አበባ ወደ ጣሊያን ሲበር የነበረውን የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን  ጠልፎ ስዊዘርላንድ ማሳረፉ ከዓመቱ አነጋጋሪና ትኩረት ሳቢ ጉዳዮች አንዱ ነበር፡፡
ረዳት አብራሪው አውሮፕላኑን ለምን እንደጠለፈ እስካሁንም ይሄ ነው የሚባል አሳማኝ ምክንያት አልተገኘለትም፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ጠላፊው ተላልፎ እንዲሰጠው የጠየቀ ቢሆንም አዎንታዊ ምላሽ አላገኘም፡፡ ጠላፊው የስዊዘርላንድን መንግስት ጥገኝነት ጠይቆ እንደተፈቀደለትና አሁን እዚያው በእስር ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡ ፍትህ ሚኒስቴር በበኩሉ፤ በጠላፊው ላይ  ክስ መስርቶ ፍ/ቤት የአቃቤ ህጎችን ምስክርነት በመስማት  ላይ ይገኛል፡፡
መፍትሔ ያልተበጀለት “የሙስሊሞች ጉዳይ”
“ከሁለት ዓመት በፊት የታሰሩት ሙስሊም መሪዎቻችን ይፈቱ፣ ድምፃችን ይሰማ” የሚሉ ንቅናቄዎች እየተካሄዱ ነው ዓመቱ ያለፈው፡፡ ሐምሌ 11 ቀን 2006 ዓ.ም አርብ በታላቁ አንዋር መስጊድ የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ  ተከትሎ ፖሊስ በወሰደው እርምጃ በሰዎች ላይ ድብደባና ጉዳት መድረሱ ይታወሳል፡፡ ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ሰዎች ታስረው የነበረ ሲሆን በነሐሴ ወር መጀመሪያ ላይ በዋስ ተለቀዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል የቀድሞው “አዲስ ጉዳይ” መፅሄት የፎቶግራፍ ባለሙያ አዚዛ አህመድ እና የሰማያዊ ፓርቲ አመራር አባል ወይንሸት ሞላ ይገኙበታል፡፡
የታሰሩት ሙስሊሞች ጉዳይ በፍ/ቤት መታየቱን የቀጠለ ሲሆን ተጠርጣሪዎቹ የመከላከያ ምስክሮቻቸውን በማሰማት ሂደት ላይ እንደሆኑ ይታወቃል፡፡
አዲሱ ማስተር ፕላን የቀሰቀሰው ተቃውሞ
ሌላው የዓመቱ አብይ ክስተት የአዲስ አበባና በኦሮሚያ ልዩ ዞን ስር የሚተዳደሩ ከተሞች የጋራ ማስተር ፕላን የተነሳ የተቀሰቀሰው ተቃውሞና ረብሻ ሲሆን የሰው ህይወትን ጨምሮ በርካታ ጉዳትና ውድመት ደርሷል፡፡
በአገሪቱ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የሚማሩ የኦሮሚያ ተወላጅ ተማሪዎች በሚያዚያ ወር አጋማሽ ላይ ባስነሱት ተቃውሞ ሳቢያ ከፖሊስ ጋር ግጭት መፈጠሩ ይታወሳል፡፡
ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች በአምቦ ከተማ በተፈጠረው ግጭት 30 የሚደርሱ ሰዎች መሞታቸውን ሲዘግቡ፣ የሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን በበኩላቸው፤ በአጠቃላይ የ11 ሰዎች ህይወት ማለፉን ዘግበዋል፡፡
ተቃውሞውን ለማስቆም በፀጥታ ሃይሎች ከተወሰደው እርምጃ ባሻገር ከፍተኛ የመንግስት አመራሮች ውዝግብ ባስነሳው የጋራ ማስተር ፕላን ዙሪያ ከተማሪዎችና ከህብረተሰቡ ጋር ለበርካታ ሳምንታት ውይይት እንዳደረጉም አይዘነጋም፡፡
“አስደንጋጩ” የጋዜጠኞችና ጦማሪያን እስር
መንግስት በሽብርተኝነት ጠርጥሬያቸዋለሁ በማለት  3 ጋዜጠኞችና 6 ጦማሪያን ማሰሩ የዓለም አቀፍ ሚዲያዎችን ትኩረት የሳበ ሌላው የዓመቱ ጉልህ ክስተት ነበር፡፡ አብዛኞቹ ዓለምአቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማትም እስሩን ከመጪው አገራዊ ምርጫ ጋር በማያያዝ የመንግስት ፍርሃት የፈጠረው ጉዳይ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡
በሚያዚያ ወር አጋማሽ ላይ ጋዜጠኛ ተስፋለም ወልደየስ፣ ኤዶም ካሳዬ፣ አስማማው ሃይለጊዮርጊስ እንዲሁም “ዞን 9” በተሰኘ ድረገጽ ፀሐፊነታቸው የሚታወቁት አጥናፉ ብርሃኔ፣ ማህሌት ፋንታሁን፣ ዘላለም ክብረት፣ ናትናኤል ፈለቀ፣ በፈቃዱ ሃይሉና አቤል ዋበላ ተይዘው መታሰራቸው የሚታወስ ነው፡
መንግስት በተጠርጣሪዎቹ ላይ በሽብርተኝነት ከተፈረጁ ድርጅቶችና ተቋማት ጋር በመተሳሰር እንደሚሰሩ ደርሼበታለሁ በሚል ክስ የመሰረተባቸው ሲሆን ጉዳያቸው በፍ/ቤት በመታየት ላይ ይገኛል፡፡
የአቶ አንዳርጋቸው መያዝና የተቃዋሚ አመራሮች እስር
በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት በአሸባሪነት ከተፈረጁት አምስት የፖለቲካ ድርጅቶች አንዱ የሆነው የ“ግንቦት 7” ዋና ፀሐፊ የነበሩት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ፣ በሰኔ ወር መጨረሻ ላይ በየመን መያዝና ለኢትዮጵያ መንግስት ተላልፎ መሰጠት የተጠናቀቀው አመት ያልተጠበቀ ክስተት ነበር፡፡ የእንግሊዝ ዜግነት ያላቸው አቶ አንዳርጋቸው፤ ቀደም ሲል በሌሉበት በተመሰረተባቸው የአሸባሪነት ክስ የሞት ፍርድ እንደተወሰነባቸው ይታወሳል፡፡
እኚህ የግንቦት 7 ከፍተኛ አመራር በኢትዮጵያ መታሰራቸውን ተከትሎ በተለያዩ የአሜሪካና አውሮፓ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በእንግሊዝ ኢምባሲዎች ደጃፍ ላይ በመሰባሰብ ተቃውሞ ማሰማታቸውን ቀጥለዋል - እንግሊዝ ዜግነት ለሰጠችው ሰው ተገቢውን ጥበቃና ከለላ አልሰጠችም በሚል፡፡
አንዳንዶች እንደሚሉት፤ የአቶ አንዳርጋቸው ጦስ ለአገር ውስጥ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችም ተርፏቸዋል፡፡ እሳቸው በታሰሩ ማግስት በሐምሌ ወር መጀመሪያ ላይ የአንድነት ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሃብታሙ አያሌውና የፓርቲው የድርጅት ጉዳይ ም/ኃላፊ አቶ ዳንኤል ሺበሺ፣ የሰማያዊ ፓርቲ ብሄራዊ ም/ቤት ም/ሰብሳቢ አቶ የሽዋስ አሰፋ እንዲሁም የአረና ፓርቲ አመራር አባል አቶ አብርሃ ደስታ በሽብር ተጠርጥረው የታሰሩ ሲሆን ጉዳያቸውም በፍ/ቤት እየታየ ነው፡፡
የግል የሚዲያ ተቋማት ክስ፤ የአሳታሚዎችና ጋዜጠኞች ስደት
መንግስት በ“ፋክት” ፣ “ሎሚ” ፣ “አዲስ ጉዳይ”፣ “እንቁ”፣ “ጃኖ” መፅሄት እና “አፍሮ ታይምስ” ጋዜጣ አሳታሚዎችና ባለቤቶች ላይ የወንጀል ክስ መመስረቱን በቴሌቪዥን የገለፀው  በሐምሌ ወር መጨረሻ ነበር፡፡ ከመግለጫው ጥቂት ሳምንት በኋላ ለፍ/ቤት የቀረበው የአሳታሚዎችና የስራ አስኪያጆቹ ክስ ጠቅለል ብሎ ሲታይ በተለያዩ የህትመት ውጤቶቻቸው በፃፏቸው ፅሁፎች በህገ-መንግስታዊ ስርአቱ ላይ አመፅ ቀስቅሰዋል፣ በሃሰት ወሬ ህዝብን በመንግስት ላይ የሚያነሳሱ ፅሁፎችን አትመዋል የሚል ሲሆን የፍ/ቤት ሂደቱም ቀጥሏል፡፡
የመንግስትን ክስ ተከትሎ ከ “ፋክት” መፅሄት አሳታሚ በስተቀር የሁሉም ተከሳሽ የሚዲያ ተቋማት ባለቤቶች ሃገር ለቀው የወጡ ሲሆን በአጠቃላይ 16 ያህል የግል ፕሬሱ አባላት አገር ለቀው ተሰደዋል፡፡ መንግስት በበኩሉ፤ በጋዜጠኞች ላይ የተመሰረተ ክስ ስለሌለ የተሰደደ አንድም ጋዜጠኛ የለም ብሏል፤ ጋዜጠኞቹ ለተሻለ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ከአገር መውጣታቸውን በመጠቆም፡፡
“ብዙ የተባለለት የደሞዝ ጭማሪ”
ብዙ የተነገረለትና በጉጉት የተጠበቀው የመንግስት ሰራተኞች የደሞዝ ጭማሪም የተደረገው በዚህ ዓመት ሐምሌ ወር ጀምሮ ነው፡፡ ጭማሪው ከፍተኛ ይሆናል በሚል ግምት ከፍተኛ የመነጋገሪ አጀንዳ ሆኖ የቆየው የደሞዝ ጭማሪው ብዙዎች እንደጠበቁት ግን አልሆነም፡፡ ጭማሪው ከ33 እስከ 46 በመቶ ብቻ ነበር፡፡ ጭማሪውን ተከትሎም ነጋዴው በመሰረታዊ ሸቀጦች ዋጋ ላይ ጭማሪ እንዳያደርግ መንግስት ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ሲሰጥ ቆይቷል፤ ማስጠንቀቂያውን የጣሱ “ህገወጥ” ነጋዴዎች ላይም እርምጃ መወሰዱን መንግስት አስታውቋል፡፡
“ዓለምን ያስደነገጠው ኢቦላ”
በምዕራብ አፍሪካ አገራት ተከስቶ ወደሌሎች የአፍሪካ አገራት የተስፋፋው ኢቦላ፤ መላውን ዓለም ድንጋጤ ውስጥ የከተተው በዚሁ ዓመት ላይ መገባደጃ ላይ ሲሆን አሁንም ስጋት እንደሆነ ቀጥሏል፡፡  
ዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት (WHO) ከትላንት በስቲያ ይፋ ባደረገው መረጃ፤ ቫይረሱ በተከሰተባቸው የአፍሪካ አገራት 2ሺ ገደማ ሰዎች ለህልፈት መዳረጋቸውን አስታውቋል፡፡
 ኢትዮጵያም የዚህ ቫይረስ ተጠቂ እንዳትሆን ከወዲሁ ለመከላከል የተለያዩ የቅድመ ጥንቃቄ እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆኑን መንግስት አስታውቋል፡፡ ቦሌ አየር መንገድን ጨምሮ በተለያዩ የድንበር አካባቢዎች ጊዜያዊ የምርመራ ጣቢያዎች የተቋቋሙ ሲሆን በአዲስ አበባም 50 አልጋዎች ያሉት ልዩ ሆስፒታል መዘጋጀቱን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡


ዋዜማውን የት ለማሳለፍ አስበዋል?

በዘንድሮ የአዲስ ዓመት ዋዜማ ከቀድሞ ዓመታት በተለየ በርካታ የሙዚቃ ድግሶች እንደተዘጋጁ ያሰባሰብናቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ጃኪ ጎሲና አንጋፋው ድምፃዊ ቴዎድሮስ ታደሰ ረቡዕ ምሽት በዋዜማው ታዳሚውን በሚሊኒየም አዳራሽ እንደሚያዝናኑ ይጠበቃል፡፡ አንጋፋው ድምፃዊ አለማየሁ እሸቴም በምሽቱ ዝግጅት ላይ የሚያቀነቅን ሲሆን “የተመስገን ልጆች” የባህል ውዝዋዜ ቡድን የኮንሰርቱ አካል እንደሆኑ ታውቋል፡፡ ኮንሰርቱን ለመታደም ቀደም ብለው ትኬት ለሚገዙ 500 ብር፣ በእለቱ በር ላይ በእለቱ ለመግዛት 600 ብር ነው ተብሏል፡፡ የቪአይፒ ትኬት 1500 ብር ሲሆን እራትን ይጨምራል፡፡
ሃርመኒ ሆቴል
ከኤድናሞል ዝቅ ብሎ በሚገኘው ሃርመኒ ኢንተርናሽናል ሆቴልም ለአዲስ ዓመት ዋዜማ ትልቅ የሙዚቃ ድግስ ተዘጋጅቷል፡፡ በዚህ ድግስ ላይ ዋዜማውን የሚያደምቁት የጃኖ ባንድ አባላት ናቸው ተብሏል፡፡ በዚህ ድግስ ላይ ለመታደም ብቻዎን ከሄዱ በሰባት መቶ ብር የፍቅር ወይም የትዳር አጋርዎን ከያዙ ደሞ በ1200 ብር ይዝናናሉ፡፡
ሒልተን ሆቴል
በቅርቡ ስሙን ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ድርጅት ወደ ኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የቀየረው EBC፤ በዋዜማው ዕለት ከሒልተን በቀጥታ የሚያስተላልፈው የመዝናኛ ዝግጅት እንዳለው ታውቋል፡፡ በዋዜማ ዝግጅቱ ላይ እነማዲንጎ አፈወርቅ፣ ሃመልማል አባተ፣ ኤፍሬም ታምሩ፣ ንዋይ ደበበ፣ ማህሌት ገ/ጊዮርጊስ፣ ዘውዱ በቀለ፣ ሃይሉ ፈረጃና ሌሎች በርካታ አንጋፋና ወጣት ድምፃዊያን ይሳተፉበታል ተብሏል፡፡ በዚህ የዋዜማ ፕሮግራም የመግቢያ ክፍያ እንደሌለና እንግዶች በጥሪ ካርድ እንደሚገቡ ታውቋል፡፡  
ካፒታል ሆቴል
ከኡራኤል ወደ 22 በሚወስደው መንገድ ላይ የሚገኘው ካፒታል ሆቴልና ስፓ እንዲሁ ትልቅ የዋዜማ የሙዚቃ ድግስ ያዘጋጀ ሲሆን ምሽቱ በመሃሪ ብራዘርስ ባንድ ይደምቃል ተብሏል፡፡ በዚህ ምሽት አንጋፋው ድምፃዊ አለማየሁ እሸቴ ሥራዎቹን የሚያቀርብ ሲሆን መግቢያ 1300 ብር ነው፡፡
ሳሬም ኢንተርናሽናል ሆቴል
ሰሜን ማዘጋጃ አካባቢ የሚገኘውና በዓመቱ መጀመሪያ ላይ አካባቢ ስራ የጀመረው ባለ አራት ኮከቡ ሳሬም ኢንተርናሽናል ሆቴልም ለአዲሱ ዓመት ዋዜማ የሙዚቃ ድግስ አዘጋጅቷል፡፡ በዚህ ምሽት ገነነ ሃይሌ፣ የባህል ዘፋኙ ግዛቸው እሸቱ፣ ፀጋዬ ስሜ (ሆሴ ባሳ) እና ሌሎችም የትግርኛና ጉራጊኛ ዘፋኞች የበዓል ዋዜማውን አድምቀውት ያመሻሉ፡፡ መግቢያው 380 ብር እንደሆነ ታውቋል፡፡
ጨጨሆ የባህል ምግብ አዳራሽ
በአዲስ አበባ ከኢምፔሪያል አደባባይ ወደ 17 ጤና ጣቢያ በሚወስደው መንገድ የተገነባውና ባለፈው ቅዳሜ የተመረቀው አዲሱ “ጨጨሆ የባህል ምግብ አዳራሽ” ደግሞ የፊታችን ሐሙስ የአዲስ ዓመት ልዩ የሙዚቃና የባህል ዝግጅቶችን እንደሚያቀርብ ታውቋል፡፡

            አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ በአዲሱ ዓመት ሃገራዊ ኃላፊነትን ለመሸከም መዘጋጀቱን ገለፀ፡፡ ፓርቲው ከትናንት በስቲያ ረፋድ ላይ በጽ/ቤቱ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፤ “የገዢውን ፓርቲ ምርጫ መጣ ነፃ ፕሬስ ውጣ” አይነት አካሄድ አጥብቆ እንደሚቃወም አስታውቋል፡፡
እንደነ አንዷለም አራጌ፣ ናትናኤል መኮንን፣ አንዱዓለም አያሌው፣ ሻምበል የሺዋስ፣ ሃብታሙ አያሌው እና ዳንኤል ሺበሺ ያሉ ወጣት የፓርቲው አመራሮች በፖለቲካ አመለካከታቸው ብቻ ወህኒ ተወርውረው የግፍ ፅዋ እየተጋቱ ነው” ያለው ፓርቲው፤  “አፈናና ስደት በአምባገነን መሪዎች አገር የተለመደና የሚታወቅ ቢሆንም አምባገነንነት በኢህአዴግ እንዲያበቃ ቆርጠን እንታገላለን” ብሏል፡፡
ፓርቲው ከ2003 ዓ.ም እስከ 2007 ዓ.ም ያለውን ጊዜ “የኢትዮጵያ ፖለቲካ ትግል እድሳትና ማንሰራራት ዘመን” ብሎ በመሰየም ባለፉት አመታት በከፍተኛ ህዝባዊ ንቅናቄ የኢትዮጵያን ህዝብ ችግሮች አደባባይ እንዳወጣ አስታውቋል፡፡
“የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት” እና “የእሪታ ቀን” በሚል ያካሄዳቸውን እንቅስቃሴዎች በመጥቀስ፡፡
የፓርቲው ሊቀመንበር ኢ/ር ግዛቸው ሽፈራው በመግለጫው ላይ እንደተናገሩት፤ “አፈናና እስራት ቢበዛብንም ትግሉ ከዚህም የባሰና የከፋ ችግር እንደሚያስከትል እያወቅን ስለገባንበት በሰላማዊ ትግላችን እንቀጥላን“ ብለዋል፡፡
ፓርቲው በ2007 “የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነትና ፍትሃዊ ምርጫ “በሚል አመቱን ሙሉ የሚቆይ ንቅናቄ እንደሚያካሂድ ገልፆ፣ በዚሁ ዓመት በሚደረገው ሃገራዊ ምርጫ ላይ የምርጫ ቦርድ፣ የመገናኛ ብዙሃን፣ የፍትህ ስርዓቱና ሌሎች የዴሞክራሲ ተቋማት በህገ-መንግስቱ የተደነገገውን መሰረት በማድረግ ገለልተኝነታቸውን በአንፃራዊ ደረጃ በማረጋገጥ፣ በምርጫው እንደሚሳተፍና የህዝብን የስልጣን ባለቤትት ለህዝብ እንደሚያበስር አመራሮቹ ተናግረዋል፡፡
 የፓርቲውን ስትራቴጂና የአምስት ዓመት እቅድ መሰረት በማድረግ፣ በአብዛኛው የአገሪቱ ክልል ምርጫ ተኮር አደረጃጀት ለመዘርጋት እንቅስቃሴ መጀመሩንም ፓርቲው አስታውቋል፡፡ “መንግስት ለ2007 ዓ.ም ምርጫ ፍጆታ ሲል ለሰራተኛው ደሞዝ ጨመርኩ ቢልም ህዝቡ ጀኑሮ ውድነት የተሰቃየበትና አሁንም እየተሰቃየ ያለበት ዓመት ሆኗል፡፡” ያሉት አመራሮቹ፣ መንግስት ገበያውን በአስቸኳይ በማረጋጋት የህዝቡን ጫና እንዲቀንስ ጠይቀዋል፡፡
 መንግስት የአዲስ አበባን ይዞታ ለማስፋፋት ሲል የሚመለከታቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች ሳያወያይ ባደረገው አከላለል በተነሳ የህዝብ ቁጣ በርካታ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ለሞት፣ ለአካል ጉዳት፣ ለእስራትና ለተያያዥ ጉዳዮች ያጋለጠ በመሆኑ ከምንግዜውም በላይ ዓመቱን መራራ አድርጎት ማለፉን የተናገሩት የአንድነት አመራሮች በ2007 ዓ.ም ይህ ሁሉ ግፍ ተወግዶ ህዝቡ እፎይታ የሚያገኝበት ዓመት እንዲሆን ፓርቲው ከምንጊዜውም በላይ የሃገርን ኃላፊነት ለመሸከም መዘጋጀቱን ገልፀዋል፡፡ፓርቲው ለኢትዮጵያ ህዝብ ባስተላፈው መልእክት፤ በመጪው አገራዊ ምርጫ ከህዝቡ ጋር በመሆን ሰላማዊ ትግሉን በምርጫ ለማሳካት በአራቱም ማዕዘናት የፖለቲካ ፕሮግራሙን እንደሚተገብርና መጪው ዘመን የኢትዮጵያ ህዝብ ነፃነት በእጁ የሚገባበት በመሆኑ ህዝቡ ከትግሉ ከጎኑ እንዲቆም ጥሪውን አቅርቧል፡፡

          ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል የተባለው አለማቀፍ ተቋም እ.ኤ.አ በ2013 በአለም ዙሪያ በሚገኙ 95 አገራት በሰራው ጥናት፣ ባለፈው አመት ከአፍሪካ አህጉር አነስተኛ ሙስና የተሰራባት አገር ኢትዮጵያ እንደሆነች ማስታወቁን የኬንያው ዘ ስታር ጋዜጣ ዘግቧል፡፡ አልጀዚራ በበኩሉ ትናንት ባወጣው ዘገባ፣ በኢትዮጵያ ንጹህ የመጠጥ ውሃ ማግኘት ቅንጦት ነው ብሏል፡፡
የአገራትን ዜጎች አስተያየትና ሌሎች መስፈርቶችን በመጠቀም ባወጣቸው የሙስና መለኪያዎች በ6 በመቶ ነጥብ ያገኘችው ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አገራት አነስተኛ ሙስና ያለባት አገር እንደሆነች የገለጸው ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል፣ ዴንማርክ፣ ፊላንድ፣ ጃፓንና አውስትራሊያም በተመሳሳይ ሁኔታ 1 በመቶ ነጥብ ይዘው በአለማችን አነስተኛ ሙስና ያለባቸው አገሮች መሆናቸውን በጥናቱ ማረጋገጡን ይፋ አድርጓል፡፡
በሙስና መለኪያዎች 84 በመቶ ውጤት ያገኘችው ሴራሊዮን በአለማችን ከፍተኛ ሙስና የሚፈጸምባት አገር እንደሆነች የገለጸው ተቋሙ፣ ላይቤሪያ፣ የመንና ኬንያ እንደሚከተሏት አስታውቋል፡፡
ከአፍሪካ ሁለተኛዋ አነስተኛ ሙስና ያለባት አገር ሩዋንዳ መሆኗን የገለጸው ተቋሙ፣ በምስራቅ አፍሪካ ከሚገኙ አገራት መካከልም ኡጋንዳ፣ ታንዛኒያና ሱዳን በቅደም ተከተል ከሁለተኛ እስከ አራተኛ ደረጃ ይዘው እንደሚገኙ ተናግሯል፡፡
አልጀዚራ በበኩሉ ትናንት ለንባብ ባበቃው ዘገባው በኢትዮጵያ ንጹህ የመጠጥ ውሃ ማግኘት ቅንጦት እንደሆነ ገልጾ፣ ምንም እንኳን 52 በመቶ የአገሪቱ ህዝብ የንጹህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት የተሟላለት ቢሆንም፣ የውሃ መስመር ቤታቸው ድረስ የተዘረጋላቸው የአገሪቱ ዜጎች 10 በመቶ ያህሉ ብቻ እንደሆኑ አስረድቷል፡፡በአገሪቱ የገጠር አካባቢዎች ከሚኖሩት ዜጎች የንጹህ የመጠጥ ውሃ ቧንቧ መስመር የተዘረጋላቸው አንድ በመቶ ያህሉ ብቻ እንደሆኑም ገልጧል፡፡የአገሪቱ መንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማትን ለማስፋፋት ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ ቢሆንም፣ የንጹህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት አሁንም ድረስ በበቂ ሁኔታ አለመሟላቱንና ከፍተና ስራ መስራት እንደሚገባም አስታውቋል፡፡

        ላለፉት ዓመታት የቅጂና ተዛማች መብቶች ጥሰት በፈጠረው ስጋት ተቀዛቅዞ የከረመው የሙዚቃ ኢንዱስትሪ ዘንድሮ የተነቃቃ ይመስላል፡
ታዋቂ ድምፃውያን ለአዲሱ አመት አዳዲስ ነጠላ ዜማቸውንና አልበማቸውን አበርክተዋል፡፡ ይሄም ለሰሞኑ የአውዳመት ድባብ ተጨማሪ ድምቀት ሰጥቶታል፡፡
የአብነት አጎናፍር “አስታራቂ፣ የታምራት ደስታ “ከዛ ሰፈር”፣ የዮሴፍ ገብሬ “መቼ ነው” የሰለሞን ሃይለ “ውህብቶ”፣ የቤተልሔም ዳኛቸው “ሰው በአገሩ” እና የተስፋፅዮን ገ/መስቀል “ጀመረኒ” እንዲሁም የቴዎድሮ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) “ሰባ ደረጃ” ነጠላ ዜማም ለአዲስ ዓመት ከተበረከቱ የሙዚቃ ስራዎች መካከል በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ፡
“ሙዚቃ እንደ በረዶ በቀዘቀዘበት ዘመን ደፍረውና መስዋዕትነት ከፍለው አዲስ ነገር ይዘው ስለመጡ አድናቆት ይገባቸዋል” ብለዋል በአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የስራ ኃላፊ የሆኑና ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ የሙዚቃ ባለሙያ፡፡
በዚህ አመት ለአድማጭ ይበቃሉ ከተባሉት የሙዚቃ አልበሞች መካከል፣ የኤፍሬም ታምሩ አልበም የሚጠቀስ ሊሆን፣ የድምፃዊው ወላጅ እናት በሳምንቱ መጀመሪያ ከዚህ አለም በሞት በመለየታቸው ምክንያት አልበሙ ሳይለቀቅ ቀርቷል፡
የአብነት አጎናፍር “አስታራቂ”
ከሁለት ሳምንት በፊት ገበያ ላይ የዋለው አብነት አጎናፍር “አስታራቂ” አልበም 14 ዘፈኖች የተካተቱበት ሲሆን ካሙዙ ካሳ፣ ሚካኤል ሀይሉና አቤል ጳውሎስ አቀናብረውታል፡፡  ድምፃዊው ሶስተኛ ስራው በሆነው በዚህ አልበም አገራዊ፣ ማህበራዊ እና የፍቅር ጉዳዮችን የዳሰሳ ሲሆን ከአድማጮች በተገኘ አስተያየት፣ ከአብነት ስራዎች ውስጥ ስለአገር የዘፈናቸው “አያውቁንም”፣ “ለማን ብዬ”፣ “አስታራቂ” እና “የኔ ውዳሴ” የተሰኙት ይበልጥ ተወደዋል፡፡ በAB ሙዚቃና ፊልም ፕሮዳክሽን የታተመው “አስታራቂ” አልበም፤ በአርዲ ኢንተርቴይመንት እየተከፋፈለ ሲሆን የአዲሱ ዓመት አንዱ ገጸ በረከት ነው፡፡ አብነት ከአማርኛ ሙዚቃ በተጨማሪ ሱዳንኛ እንደሚጫወት የሚታወቅ ሲሆን ዘንድሮ ደግሞ “አያሌሌ” የተሰኘ የጉራጊኛ ዘፈን አካትቷል፡፡ ድምፃዊው በአብዛኛው ዘፈኖቹ ላይ በግጥምና በዜማ ድርሰት ተሳትፏል፡፡
የታምራት ደስታ “ከዛ ሰፈር”
ለአዲሱ ዓመት በገፀ-በረከትነት ከቀረቡት አልበሞች ውስጥ የታምራት ደስታ አራተኛ ስራ የሆነው “ከዛ ሰፈር” አንዱ ነው፡፡ ባለፈው ሳምንት ለአድማጭ ጆሮ የደረሰው ይሄው አልበም፤ 14 ዘፈኖችን አካትቷል፡፡ ካሙዙ ካሳ፣ ሚካኤል ሃይሉ፣ ሚካኤል መለሰና ኪሩቤል ተስፋዬ በቅንብር የተሳተፉበት ይሄ ስራ፤ በግጥም እና ዜማ ጌትሽ ማሞ አማኑኤል ይልማ፣ መሰለ ጌታሁንና ኢዩኤል ብርሃኔን አሳትፏል፡፡ በናሆም ሪከርድስ አሳታሚና አከፋፋይነት ገበያ ላይ የዋለው የታምራት አልበም፤ በስፋት እየተደመጠ ሲሆን በተለይም “ሊጀማምረኝ ነው” “አዲስ አበባ”፣ “ማማዬ” እና የአልበሙ መጠሪያ የሆነው “ከዚያ ሰፈር” የተሰኙ ዘፈኖች የበለጠ እየተሰሙ እንደሚገኙ ከአድማጮች አስተያየት ለመረዳት ተችሏል፡፡
የቴዲ አፍሮ “ሰባ ደረጃ”
ከበደሌ ጋር አመቱን ሙሉ በሚዘልቅና “ወደ ፍቅር ጉዞ” በተሰኘ የሙዚቃ ኮንሰርት ከአድናቂዎቹ ጋር ለመገናኘት የጀመረው ስራ የተሰናከለበት ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ)፤ ከሁለት ሳምንታት በፊት የለቀቀው “ሰባ ደረጃ” የተሰኘ  ነጠላ ዜማው በስፋት እየተደመጠ ሲሆን ማህበራዊ ድረ - ገፆችን በተለይም ፌስ ቡክን ተቆጣሮጥት ሰንብቷል፡፡ የቴዲ “ሰባ ደረጃ” ፒያሳ፣ ዶሮ ማነቂያ፣ ሰራተኛ ሰፈር፣ አራት ኪሎን፣ ታሪካዊ ክስተቶችንና አለባበሶችን ከፍቅር ጋር እያሰናሰለ ያነሳሳል፡፡ የቴዲ አፍሮ “ሰባ ደረጃ” ነጠላ ዜማ ሙሉ አልበምን የመወከል ያህል ተቀባይነት አግኝቶ በየምሽት ቤቱ፣ በየሆቴሉና በየሬስቶራንቱ በስፋት እየተደመጠ ያለ የአዲስ አመት የበዓል ድምቀት ሆኖ ቀጥሏል፡፡
የሰለሞን ሃይለ “ውህብቶ”
“ቆሪብኪለኩ” (ቆረብኩልሽ) በሚለው የመጀመሪያ አልበሙ በተለይም “ንኢባባ” በተሰኘው ዘፈኑ የሚታወቀው ወጣቱ የትግርይኛ ዘፋኝ ሰለሞን ሃይለም ከሳምንታት በፊት “ውህበቶ” የተሰኘ አልበም ለአድማጭ አቅርቧል፡፡ አልበሙ 12 ዘፈኖችን ያካተተ ሲሆን፣ ስለ ሃገር፣ ስለ ፍቅር ስለማህበራዊ ጉዳዮች ተነስተውበታል፡፡ ሙሉ ግጥምና ዜማው በራሱ በድምፃዊው የተሰራ ሲሆን፣ በቅንብሩ አብዛኛውን ዘፈኖች ተወልደ ገ/መድህን ሲሰራ፣ ሁለት ዘፈኖችን ዮናስ መሃሪ እና ደነቀው ኪሮስ፣ አንዱን ዘፈን ዘመን አለምሰገድ አቀናብረውታል፡፡ በስፋት እየተደመጠም ይገኛል፡፡
የዮሴፍ ገብሬ “መቼ ነው”
ድምፃዊና ጋዜጠኛ ዮሴፍ ገብሬም አዲሱን አመት ምክንያት በማድረግ “መቼ ነው” የተሰኘ አዲስ የሙዚቃ አልበሙን ከ10 ቀናት በፊት በገበያ ላይ አውሏል፡፡ ለዝግጅት 6 አመታትን የፈጀው ይሄው አልበም፤ በአገር፣ በፍቅር፣ በአንድነትና በመተሳሰብ ላይ የሚያተኩር ሲሆን 7 አቀናባሪዎችና የተለያዩ የግጥምና ዜማ ደራሲዎች ተሳትፈውበታል፡፡ “መቼ ነው” የተሰኘው የአልበሙ መጠሪያ፣ “ክፉ አይንካብኝ” ሲል ስለ አገር የዘፈነው፣ “ፍቅር ነው ያገናኘኝ” እንዲሁም ስለአንድነትና መተባበር (በጉራጊኛ) የዘፈናቸው ይበልጥ ተወዳጅ እንደሆኑለት ከአድማጮች ያገኘነው አስተያየት ይጠቁማል፡፡ አልበሙ በተለያዩ የመዝናኛ ስፍራዎች በስፋት እየተደመጠ ይገኛል፡፡  
የቤተልሔም “ሰው በአገሩ”
በ1996 ዓ.ም ለአድማጭ ባቀረበችው “ቅዳሜ ገበያ” የተሰኘ ባህላዊ ዜማዋ የምትታወቀው ድምፃዊት ቤተልሔም ዳኛቸው፣ ሰሞኑን “ሰው በአገሩ” የተሰኘ አዲስ አልበሟን ለአድማጭ አቅርባለች፡፡
ነዋሪነቷ በስዊዘርላንድ የሆነው ድምፃዊት ቤተልሔም ያቀረበችው አዲስ አልበም፤ 13 ባህላዊና ዘመናዊ ሙዚቃዎች የተካተቱበት ነው፡፡ ታዋቂው የሙዚቃ አቀናባሪና የድምፃዊቷ ባለቤት ዳዊት ጥላሁን ባቀናበረው በዚህ አልበም ውስጥ ራሱ ዳዊትና ቤተልሔም ጥላሁን በዜማና ግጥም ደራሲነት ተሳትፈዋል፡፡
የተስፋፅዮን “ጀመረኒ”
በባህላዊ የማሲንቆ አጨዋወቱ አድናቆት የተቸረው ድምጻዊ ተስፋፅዮን ገ/መስቀል ከሰሞኑ “ጀመረኒ” የተሰኘውንና ራሱን በማሲንቆ ያጀበበትን የትግርኛ ሙዚቃዎች ለአድማጭ አብቅቷል፡፡ ከዚህ ቀደም “ቆልዑ ገዛና” የተሰኘ አልበም አውጥቶ ተቀባይነትን ያገኘው ድምፃዊው፤ በ“ጀመረኒ” አልበሙ የሰርግን ጨምሮ በበርካታ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ የሚያጠነጥኑ 13 ሙዚቃዎችን አካትቷል፡፡ አልበሙን ዳአማት መልቲ ሚዲያ አሳትሞ እያከፋፈለው ሲሆን፣ ለአዲሱ ዓመት በተለይ በትግርኛ ዘፈን አድማጮች ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት ማግኘቱንም ለማወቅ ተችሏል፡፡
“አራዳ” ቪሲዲ ኮሌክሽን
በመስፍን ታምሬ ፕሮዲዩሰርነት የታተመውና 14 እውቅ ድምፃዊያን የተሳተፉበት “አራዳ” ባህላዊ እና ዘመናዊ ዘፈኖች በምስል (በቪዲዮ) የቀረቡበት ነው፡፡ የዚህ ቪሲዲ አዘጋጅ “ኢቫንጋዲ ፕሮዳክሽን” ሲሆን “ፒያሳ ዘ አራዳ ኢንተርቴይመንት” አሳትሞ ከትናንት ጀምሮ እያከፋፈለው ይገኛል፡፡ በ“አራዳ” ኮሌክሽን ቪሲዲ ላይ ሸዋንዳኝ ሃይሉ፣ ብዙአየሁ ደምሴ፣ እመቤት ነጋሱሲ (ሰንዳበል)፣ ጃኪ ጎሲ፣ የኦሮምኛ ዘፋኙ አበበ ከፍኔና  ቤተልሄም ዳኛቸውን ጨምሮ 14 ያህል ታዋቂ ድምፃዊያን ተሳትፈውበታል፡፡
“አራዳ” ብቸኛው ለአዲስ ዓመት የተዘጋጀ ቪሲዲ እንደሆነ ታውቋል፡፡

“How Successful People Think” በሚል ርዕስ በዶ/ር ጆን ማክስዌል ተፅፎ፣ በአባተ መንግስቱ የተተረጎመው “የአሸናፊነት መንገዶች” የተሰኘ መፅሀፍ ባለፈው ሳምንት ለአንባቢያን ደርሷል፡፡ መፅሀፉ እንዴት ወደ አሸናፊነትና ስኬት እንደሚደረስና የመድረሻ መንገዱን የሚያመለክቱ ቁልፍ ነጥቦች የተነሱበት ሲሆን በተለይም በትኩረት ስለማሰብ፣ የፈጠራ አስተሳሰብን ስለመግራትና ስልታዊ አስተሳሰብን ስለመቃኘት በስፋት ይተነትናል፡፡ በ11 ርዕስ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደረገው መፅሀፉ፤ በ168 ገፆች የተቀነበበ ሲሆን በ46 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡ በተያያዘ ዜና በዮሐንስ በላይ የተደረሰው “ሃመልማል” የተሰኘ ልብወለድ መፅሀፍ አንባቢያን እጅ ደርሷል፡፡ መቼቱን ደሴና ኮምበልቻ ላይ ያደረገው ድርሰቱ፤ አዝናኝ የፍቅርና የህይወት ታሪክን ነው ተብሏል፡፡ 57 ገፆች ያሉት የዮሐንስ በላይ መፅሀፍ፤ በ25 ብር ገበያ ላይ ውሏል፡፡

የባለቅኔ ፀጋዬ ገ/መድህን ሥራዎችን የሚቃኘውና “ምሥጢረኛው ባለቅኔ” በሚል ርዕስ በደራሲ ሚካኤል ሽፈራው ተዘጋጅቶ በ1996 ዓ.ም ለአንባቢያን ቀርቦ የነበረው መጽሐፍ፤ በ10ኛ ዓመቱ ለሁለተኛ ጊዜ ታተመ፡፡ ደራሲው ለመጽሐፉ ሰፊ የአርትኦት ሥራ ማከናወናቸውንና አዳዲስ መረጃዎችን ማካተታቸውን በመግቢያው ላይ አመልክተዋል፡፡ 365 ገፆች ያሉት መጽሐፉ፤ በ80 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡

ጋዜጠኛ፣ ደራሲና ዓለም አቀፍ የሰላም አምባሳደር በሆነው ወጣት መኮንን ሞገሴ የተዘጋጀው “ከልካይ የሌለው ስጥ” የተሰኘ መፅሀፍ የፊታችን ሰኞ በብሄራዊ ቴአትር ይመረቃል፡፡ መፅሀፉ በዩኒቨርሲቲ ሴት ተማሪዎች የስነ-ልቦና ዝቅጠት ላይ ያተኩራል የተባለ ሲሆን ፀሐፊው በስድስት ወራት የመስክ ቆይታው በአዲስ አበባ፣ ሃዋሳ፣ ዲላ፣ ሐገረ-ማርያም፣ ያቤሎ፣ ኢትዮጵያ ሞያሌ፣ ኬኒያ ሞያሌ እና ኬንያ ጋንቦ ድረስ በመሄድ በጎዳና ተዳዳሪነት፣ በተሸካሚነት እንዲሁም በአስተናጋጅነት እየሰራ የታዘባቸውን የከተበበት እንደሆነ ታውቋል፡፡ በእሁል ሚዲያና ኮሚዩኒኬሽን አስተባባሪነት የሚመረቀው መፅሀፉ፤ የደራሲው ሁለተኛ ስራ ሲሆን ከዚህ ቀደም “የአስተናጋጁ ገፆች ቅፅ 1” የተሰኘ መፅሀፍ ለንባብ ማብቃቱ ታውቋል፡፡

በሰአሊና ደራሲ ገዛኸኝ ዲኖ የተፃፈው “በቃ እንሂድ” የተሰኘ ልብወለድ መፅሀፍ የፊታችን ማክሰኞ በሩሲያ የሳይንስና የባህል አዳራሽ ከቀኑ 10፡00 ሰዓት ጀምሮ ይመረቃል፡፡ 460 ገፅ ያለውና መቼቱን ኢትዮጵያና ፈረንሳይ ላይ ያደረገው መፅሃፉ፤ በአንድ ሰዓሊ ህይወት ላይ ያጠነጥናል፡፡ በምርቃት ስነ-ስርዓቱ እለት ደራሲያንና ሌሎች እንግዶች የሚገኙ ሲሆን በመፅሀፉ ዙሪያ ውይይት ይካሄዳልም ተብሏል፡ መፅሐፉ በ70 ብር ከ85 ሳንቲም ለገበያ ቀርቧል፡ የመፅሃፉ፤ ደራሲ ሰዓሊ ገዛኸኝ ዲኖ ለ19 ዓመታት በፈረንሳይ አገር እንደኖረ ታውቋል፡፡

  •  ከትኬት ሽያጭ ቢያንስ 5 ሚሊዮን ብር እንደተገኘ ተገምቷል *
  • “ኮንሰርት” የሚወዱ “የእጅ አመለኞች” አስቸግረው ነበር

ከወራት በፊት ሊካሄድ ታቅዶ የነበረው “ሬጌ ዳንሶል ኢን ኢትዮጵያ ቁጥር 1” የሙዚቃ ኮንሰርት የተሰረዘው ከቴዲ አፍሮ ኮንሰርት ጋር በመገጣጠሙ እንደነበር አዘጋጁ “አውሮራ ኤቨንት ኦርጋናይዘርስ” መግለጹ ይታወሳል፡፡ የኮንሰርቱ ተጋባዥ ከያኒ ጃማይካዊው ቢዚ ሲግናል ለሸገር ሬዲዮ በሰጠው ቃለምልልስ ደግሞ፤ “ኮንሰርቱ የተሰረዘው በተለያዩ ምክንያቶች በተከሰቱ መዘግየቶች ነው” ብሎ ነበር፡፡ የሆነ ሆኖ “ለሁሉም ጊዜ አለው” እንዲሉ፣ ኮንሰርቱ ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ በሚሊኒየም አዳራሽ በርካታ ታዳሚያን በተገኙበት ተካሂዷል፡፡ የምሽቱ ድባብ ከምሽቱ 2፡00 ላይ የተጀመረው የሙዚቃ ኮንሰርቱ፤ በአገራችን የሬጌ ሙዚቃ አቀንቃኞችና በዲጄ እየተሟሟቀ የዘለቀ ሲሆን ራስ ጃኒ፣ ሲዲኒ ሳልመን፣ ጃሉድ አወል፣ ሃይሌ ሩትስ እና ጆኒ ራጋ ማራኪ ሥራዎቻቸውን አቅርበዋል፡፡

በየመሃሉ በዲጄ ባባ ትንፋሽ እያገኙ መድረኩን ያደመቁት ኢትዮጵያዊ ድምፃዊያን፤ በታዳሚው ዘንድ ከፍተኛ አድናቆትን አግኝተዋል፡፡ መድረኩ በጥሩ ሁኔታ ተዘጋጅቷል፤ የላይትና የድምፁ ቅንብር እንከን የለሽ ነበር፡፡ ኮንሰርቱ ተጀምሮ እስከሚያልቅ አንድም የድምፅ መቆራረጥና መረበሽ አላጋጠመም፡፡ ድምፃዊያኑ ለኮንሰርቱ በቂ ዝግጅት ለማድረጋቸው በመድረክ ያሳዩት ጥንካሬና ብቃት ምስክር ነው፡፡ ራስ ጃኒ የምሽቱ ምርጥ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ጃሉድ “የገጠር ልጅ ነኝ”፣ “አሻበል ያሆ”፣ የእርግብ አሞራ እና ሌሎችንም ስራዎቹን በጥሩ ሁኔታ በመጫወት ታዳሚውን የማረከ ሲሆን ሃይሌ ሩትስ በበኩሉ፤ “ባዶ ነበር”፣ “እርጅና መጣና” በተሰኙ ታዋቂ ዘፈኖቹ ተመልካቹን አዝናንቷል፡፡ ጆኒ ራጋም አነቃቂ ምሽት ለመፍጠር ችሏል፡፡ ጆኒ ራጋና ሃይሌ ሩትስ በጋራ ተቀናጅተው ያቀረቡት ሥራም ልዩ አድናቆት የተቸረው ነበር፡፡ በየመሃሉ ዲጄ ባባ መድረኩን በሙዚቃ እያደመቀ፣ አርቲስቶቹም ትንፋሽ እየሰበሰቡ፣ ታዳሚውም ልቡ እስኪወልቅ እየጨፈረና እየዘለለ ጊዜው ወደ አምስት ሰዓት ነጐደ፡፡

የዕለቱ “ሰርፕራይዝ” መድረኩን በጥሩ ሁኔታ በመምራት የተሳካለት ጋዜጠኛ አንዷለም ተስፋዬ፤ በኮንሰርቱ መጀመሪያ ላይ “ሰርፕራይዝ” እንዳለ በመግለጽ የታዳሚውን ልብ አንጠልጥሎት ነበር፡፡ እናም የመድረኩ መብራት ደብዝዞ፤አይን የማያጨልም ድባብ ተፈጠረ፡፡ ሰፋፊ ኮፍያ ያደረጉ ሰዎች ደንገዝገዝ ባለው ድባብ ውስጥ እየሮጡ ወደ መድረኩ በመግባት ቦታ ቦታቸውን ያዙ፡፡ ታዳሚው ለ“ሰርፕራይዙ” ጓጉቶ ነበር፡፡ የመድረኩ መብራት ፏ ብሎ በራ፡፡ “ሰርፕራይዟ” ዘፋኝ፤ ነጭ ብልጭልጭ ቲ-ሸርትና ነጭ ቁምጣ ለብሳ ብቅ አለች፡፡ ጭብጨባና ፉጨቱ ቀለጠ፡፡ ድምጻዊት ቤቲ ጂ. “ከአንተ አይበልጥም” የሚለው ዘፈኗን በዳንስ ቡድኗ ታጅባ፣ አብራ እየተውረገረገች አስነካችው፡፡ እየዘፈነችና እየጨፈረች ታዳሚውን አስጨፈረችው፡፡ ሁለተኛ ዘፈኗም ቀጠለ፡፡ በጣም ግሩም አቀራረብ ነበር ያሳየችው፡፡ ሥራዋን ጨርሳ ከመድረክ ስትወርድም በህዝቡ አድናቆትና ሆታ ተሸኝታለች፡፡ የታዳሚውን ልብ የነካ ስራ “እኔ የፕሮግራሙ አዘጋጅ ሆኜ እንኳን አላወቅሁም፤ በጣም የተገረምኩበትና የተደነቅሁበት ጉዳይ ነው” ይላል፤የ“አውሮራ ኤቨንትስ ኦርጋናይዘርስ” ዋና ስራ አስኪያጅ ሸዊት ቢተው፡፡ ቤቲ ጂ.፣ ጃሉድ አወል፣ ሃይሌ ሩትስ እና አንድ ፊቱ አዲስ የሆነ አርቲስት ወደ መድረክ ወጡና ማንም ያልጠበቀውን ዘፈን መዝፈን ጀመሩ፡ “ነገን ላያት እጓጓለሁ” በማለት፡፡

ይሄን ጊዜ ታዳሚው መጮህ፣ ማልቀስና ማፏጨት ያዘ፡፡ በድንገተኛው ዘፈን አዳራሹ ተደበላለቀ፡፡ ከአመት በፊት በድንገት ህይወቱ ያለፈውን የሬጌውን አቀንቃኝ ድምፃዊ ኢዮብ መኮንን ለመዘከር ታስቦ የቀረበው ሙዚቃ የመላ ታዳሚውን ልብ የነካ ነበር፡፡ በመሃል “ወይኔ እዮቤ ውውው…” በማለት ጩኸቷን ያቀለጠችው አንዲት ወጣት ታዳሚ፤እንባዋ በጉንጯ እየወረደ ደረቷን መድቃት ጀመረች፡፡ ጓደኞቿ ተረጋጊ እያሉ ቢያፅናኗትም አልቻለችም፡፡ “እዮቤን በጣም ነው የማደንቀው፤ አሟሟቱም በጣም ያሳዝናል” እያለች ማልቀሷን ቀጠለች፡፡ የብዙሃኑ ታዳሚ ጩኸት፤ ፉጨትና ዝላይማ በቃላት ለመግለጽ አዳጋች ነው፡፡ “ነገን ላያት እጓጓለሁ” ቀጠለ፡፡ አርቲስቶቹ በጣም ያምሩ ነበር፤የሙያ አጋራቸውን የዘከሩበት መንገድም አንጀት ይበላል፡፡ “ይህንን ሃሳብ ያፈለቁት ዝግጅቱን ከእኛ ጋር በአጋርነት የሰሩት የሲግማ ኢንተርቴይንመንት የስራ ባልደረባ ብሩክ እና የአውሮራ ማኔጅመንት አባል ዳዊት ናቸው” ይላል ሸዊት፡፡

ያረፈደው የክብር እንግዳ እኩለ ሌሊት አለፈ፡፡ የእለቱ የክብር እንግዳ ብቅ አላለም፡፡ ዲጄ ባባ የመሸጋገሪያውን ሙዚቃ እያጫወተ 7፡45 ሆነ፡፡ የመድረኩ አጋፋሪ አንዷለም ተስፋዬ ብቅ አለ፡፡ “አሁን በጉጉት የምትጠብቁት እንቁ ድምፃዊ ቢዚ ሲግናል ወደ መድረክ ይመጣል” ሲል አዳራሹ በጩኸት ተሞላ፡፡ ከስንት ጥበቃ እና ጉጉት በኋላ ቢዚ ሲግናል ወደ መድረክ ሲመጣ አዳራሹ ይበልጥ ተናጋ፡፡ ዳልቻ ኮት በነጭ ሸሚዝና ጠቆር ባለ ግራጫ ሱሪ ያደረገው ቢዚ ሲግናል፤ ነጭ ፍሬም ያለው ጥቁር መነፅር ፊቱ ላይ ሰክቶ ለታዳሚው ሰላምታ ሰጠ፡፡ የእሱን ዘፈን ለመስማት ዝግጁ መሆን አለመሆናችንን ጠየቀ፤ “Are you feeling good?” (በጥሩ ስሜት ውስጥ ናችሁ እንደማለት) ታዳሚው በፉጨት እና በጭብጨባ ምላሽ ሰጠ፡፡ በዚህ ምሽት ከዚህ ውብ ህዝብ ጋር በመገናኘቱ የተሰማውን ደስታ አርቲስቱ ገለፀ፡፡ በግምት በ20ዎቹ አጋማሽ ዕድሜ ላይ የሚገኘው ቢዚ ሲግናል፤ እንደብዙዎቹ የሬጌ ሙዚቀኞች ፀጉሩ ድሬድ አይደለም፡፡

ምንም እንኳ በዘፋኝነት ይበልጥ የታወቀው “One more night” የተሰኘውን የፊል ኮሊንሰን ቀደምት ስራ ሪሚክስ አድርጎ ከተጫወተ በኋላ ቢሆንም በርካታ የራሱን ስራዎችም አበርክቷል፡፡ ቢዚ ሲግናል ወደ መድረክ የመጣው ታዳሚው በጭፈራ ጉልበቱን ከጨረሰ በኋላ ነበር፡፡ በየመሃሉ “ቢዩቲፉል ሌዲስ” እያለ ኢትዮጵያውያን ሴቶችን በማድነቅ ማቀንቀኑን ቀጠለ፡፡ አጠገቤ የነበሩ በቡድን የታደሙ ሰዎች “በቃ ያቺን ዋን ሞር ናይት ይዝፈናትና እንሂድ” ሲሉ ሰማኋቸው፡፡ እርሱ ግን አውቆም ይሁን ሳያውቅ ዘፈኗን ወደ መጨረሻ ላይ አደረጋት፡፡ ሲግናል እስከ ሌሊቱ 9፡41 ድረስ መድረክ ላይ ነበር፡፡ ታዳሚው ግን ከቢዚ ሲግናል ይልቅ በኢትዮጵያዊያን አርቲስቶች ይበልጥ መደሰቱን ታዝቤአለሁ፡፡ የኮንሰርቱ አንዳንድ እንከኖች በምሽቱ ድራፍትና ሃሺሽ እኩል ሲጠጡ አመሹ ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ሀሺሽ በየደቂቃውና በየቅርብ ርቀቱ ይጨሳል፤ እንደጉድ ይጦዛል፡፡ ለሽታው ባዕድ የሆነ ያጥወለውለዋል፡፡ ያስመለሳቸውም ነበሩ፡፡ አጠገቤ የነበረ አንድ ታዋቂ አርቲስት፣ ሃሺሽ ከሚያጨስ አንድ ወጣት ጋር አንገት ለአንገት ሲተናነቅ አይቻለሁ- “ሌላ ቦታ ሄደህ አጭስ” በሚል፡፡ በርካታ ኪስ አውላቂዎችም (ሌቦች) አሰላለፋቸውን አሳምረው ነበር፡፡

ቦርሳዎች፣ ሞባይል ስልኮች፣ የኪስ ቦርሳዎችና ሌሎች ንብረቶች ለመንታፊዎች ሲሳይ ሆነው አምሽተዋል፡፡ አንድ የውጭ ዜጋ “ዋሌቴን ተሰርቄአለሁ፤ ውስጡ ፓስፖርት አለው፤ እባካችሁ እዚሁ እንዳልቀር ፓስፖርቱን እንኳን መልሱልኝ” የሚል መልዕክት በመድረክ አጋፋሪው አስነግሯል፡፡ ባለረጃጅም ተረከዝ ጫማዎችን የተጫሙ ሴቶች እግራቸውን ሲደክማቸው ጫማቸውንና ቦርሳቸውን መሬት ቁጭ አድርገው ሲጨፍሩ የሌባ ሰለባ ሆነዋል፡፡ አንዲት ወጣት “ሌላው ቢቀር ጫማዬን እንኳን ባገኝ---” በማለት እንባዋ እንደጎርፍ እየፈሰሰ፣በታዳሚው ስር በመሽሎክሎክ ጫማዋን ስትፈልግ አስተውያለሁ፡፡ የ“አውሮራ ኤቨንትስ ኦርጋናይዘርስ” ዋና ሥራ አስኪያጅ ሸዊት ቢተው ስለስርቆቱ ጠይቀነው ሲመልስ፤ “የእኛ ኮንሰርት የመጀመሪያ ከማይመስልባቸውና ከሚለይባቸው ጉዳዮች መካከል በምሽቱ ከካራማራ ፖሊስ ጋር በመተባበር አዳራሽ ውስጥ ሆነው የሰው ንብረት የሰረቁ ሌቦችን ይዘን ሞባይል፣ ቦርሳ፣ ፓስፖርትና ሌሎች ንብረቶችን ለባለቤቶቹ ማስመለሳችን ነው” ብሏል፡፡ ከተሰረቁት እቃዎች አብዛኞቹ ለባለቤቶቹ እንደተመለሱና አንድ ሁለት ሰዎች ብቻ እቃቸውን ማግኘት እንዳልቻሉ ሸዊት ተናግሯል፡፡ ኮንሰርቱን ከ10 እስከ 12ሺህ የሚደርሱ ሰዎች እንደታደሙት ከዚህም ውስጥ 2ሺህ ያህሉ በተጋባዥነት እንደገቡ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ከትኬት ገቢም ቢያንስ 5 ሚሊዮን ብር ገደማ እንደተገኘ ተገምቷል፡፡