Administrator

Administrator

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም በነገው ዕለት በካይሮ በሚከናወነው የአዲሱ የግብጽ ፕሬዚዳንት አብደል ፋታህ አል ሲሲ በዓለ ሲመት ላይ እንደሚገኙ አህራም ኦንላይን ዘገበ፡፡ኢትዮጵያና ግብጽ ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ጋር በተያያዘ ግንኙነታቸው መሻከር ከጀመረ አንድ አመት ያህል እንዳለፈው የጠቀሰው ዘገባው፣ ከዚያ ጊዜ ወዲህ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለስልጣናት ካይሮን ሲጎበኙ ይህ የመጀመሪያው እንደሚሆን አስረድቷል፡፡
የቱርኩን የዜና ተቋም አናዶሉ ኒውስ ኤጀንሲን ጠቅሶ አህራም ኦንላይን ከትናንት በስቲያ እንደዘገበው፣ የግብጽ መንግስት ባለፈው ሳምንት በአገሪቱ በተከናወነው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ አሸናፊ በሆኑት አል ሲሲ በዓለ ሲመት ላይ እንዲገኝ፣ ለኢትዮጵያ መንግስት በላከው ግብዣ መሰረት ነው፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም የተመራ የከፍተኛ ባለስልጣናት ልኡክ በበዓሉ ላይ የሚገኘው፡፡
የከፍተኛ ባለስልጣናቱ በበዓለ ሲመቱ ላይ መገኘት፣ በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን እየሻከረ የመጣ ግንኙነት በማሻሻል ረገድ የራሱን ሚና ሊጫወት እንደሚችል እየተነገረ ነው፡፡
የግብጽ የፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ኮሚሽን ባለፈው ማክሰኞ ባወጣው የምርጫ ውጤት መሰረት፣ የቀድሞው የአገሪቱ የጦር ሚኒስትር አል ሲሲ በምርጫው 96 ነጥብ 9 በመቶ ድምጽ በማግኘት የፕሬዚዳንትነት ስልጣኑን በይፋ በሚረከቡበትና በሄሊፖሊስ በሚገኘው ብሄራዊ ቤተመንግስት በሚከናወነው በዓለ ሲመት ላይ የ22 አገራት ከፍተኛ ባለስልጣናት ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የምርጫ ውጤቱ ይፋ መደረጉን ተከትሎ፤ የተመድ ዋና ጸሃፊ ባንኪ ሙን፣ አሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ ሳኡዲ አረቢያ፣ ኢራንና ሩሲያን ጨምሮ የተለያዩ አገራት ለተመራጩ ፕሬዚዳንት የደስታ መልዕክቶቻቸውን ያስተላለፉ ሲሆን፤ የቀድሞው የግብጽ ፕሬዚዳንት ሞሃመድ ሙርሲ ደጋፊ የሆነው ‘ዘ ናሽናል አሊያንስ ቱ ሰፖርት ሊጂቲሜሲ’ የተባለው ቡድን በበኩሉ፣ ባለፈው ረቡዕ በሰጠው መግለጫ፣ ህዝቡ በአል ሲሲ መሾም ላይ ያለውን ተቃውሞ አደባባይ ወጥቶ እንዲገልጽ ይፋዊ ጥሪ አቅርቧል፡፡

የሰንበቴ ማህበራቱ በደብረ ምጥማቅ ሰአሊተ ምህረት ቅድስት ማርያም እና ክርስቶስ ሰምራ ካቴድራል አስተዳደር ላይ ያለንን የመልካም አስተዳደር ቅሬታ ለቅዱስ ፓትርያርኩ እንዳናቀርብ ተከለከልን፤ ለእንግልትም ተዳርገናል አሉ፡፡
በቤተክርስቲያኑ የሚገኙ የሰባት ሰንበቴ ማህበራት ጥምረት ተወካዮች ለአዲስ አድማስ እንደገለፁት፤ ከሌላ ደብር ተቀይረው በመጡ የቤተክርስቲያኒቱ አስተዳደሮች እየተፈፀመብን ነው የሚሉትን በደልና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ለቅዱስ ሲኖዶስና ለፓትርያርኩ ለማቅረብ ከ12 ጊዜ በላይ ቢመላለሱም ጉዳያቸው እልባት አላገኘም፡፡
የማህበሩ አባላትና የደብሩ አጥቢያ ምዕመናን የሚያቀርቡት ጥያቄ በአግባቡ ለፓትርያርኩ አልደረሰም የሚሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ የሰንበቴ ማህበራቱ የመሬት ወረራ እያካሄዱ ነው የሚል የተሳሳተ መረጃ ለፓትርያርኩ መድረሱን ተከትሎ “አስቁሟቸው” የሚል ትእዛዝ መተላለፉን፤ ይህን ትዕዛዝ ተገን በማድረግም ያልተስማሙበትንና የቤተክርስቲያኒቱን ቃለ አዋዲ ያልጠበቀ መመርያ አምጥተው በ3 ቀን ውስጥ ፈርሙ በማለት  የደብሩ ኃላፊዎች እንዳስጨነቋቸው ገልፀዋል፡፡
መመሪያውን በ3 ቀን ውስጥ ፈርሙ የሚለውን ትዕዛዝ በመቃወምም ረቡዕ ግንቦት 27 ቀን 2006 ዓ.ም ለቅዱስ ሲኖዶስ ቅሬታ ለማቅረብ ከ400 በላይ ምዕመናን ወደ ፅ/ቤት ቢያመሩም በደህንነትና በፖሊስ አባላት እንዳይገቡ መከልከላቸውንና የፓትርያርኩ ዋና ፀሐፊ “ከእናንተ መሃል 10 ሰው ብቻ በነገው እለት (ሃሙስ) ጥያቄያችሁን ይዞ ይቅረብ” በሚል እንዳሰናበቷቸው የቅሬታ አቅራቢዎቹ ተወካዮች ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡
በቀጠሮው መሰረት ከትናንት በስቲያ ሃሙስ፣ ለፓትርያርኩ የሚቀርብ የአቤቱታ ደብዳቤ ይዘው ቢሄዱም  የሚያስተናግዳቸው አካል ማጣታቸውን ቅሬታ አቅራቢዎቹ ጠቁመው፣ በተደጋጋሚ የፓትርያርኩ በር ቢዘጋብንም ቤተክርስቲያኒቱን ከጥፋት ለመታደግ አሁንም በድጋሚ ጥያቄያችንን ይዘን እንቀርባለን ብለዋል፡፡

የአየር መንገዶች የአመቱ አጠቃላይ ትርፍ 18 ቢሊዮን ዶላር እንደሚደርስ ይጠበቃል

በትርፋማነታቸው ልቀው የተገኙ ሃምሳ የአለማችን አየር መንገዶችን በመምረጥ ይፋ ያደረገው አለማቀፍ የአየር መንገዶች ማህበር /IATA/ ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በ18ኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ገለፀ፡፡ በአመት ከ228 ሚሊዮን  ዶላር በላይ ትርፍ ያስመዘገበው የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ በምርጥ ትርፋማ አየር መንገዶች ዝርዝር ውስጥ ከመግባቱም በተጨማሪ፤ ከአፍሪካ ቀዳሚነቱን እንደያዘ አያታ አስታውቋል፡፡  በጥቂት አመታት ውስጥ በርካታ አውሮፕላኖችን በመግዛት አገልግሎቱን በፍጥነት እያስፋፋ የሚገኘው የኢትዮጵያ አየር መንገድ፤ በትርፋማነት ብቻ ሳይሆን ብዙ መንገደኞችንና ጭነቶችን በማጓጓዝ ታዋቂነቱን እያሳደገ መጥቷል፡፡ በዚህ አገልግሎቱ በአመት 2.3 ቢሊዮን ዶላር ገቢ በማግኘት ከአለማችን ሃምሳ ምርጥ አየር መንገዶች መካከል የ37ኛነት ደረጃን እንደያዘ አያታ ገልጿል፡፡
በትርፋማነት የአለማችን ቀዳሚ አየር መንገድ ተብሎ የተጠቀሰው የጀርመኑ ሉፍታንዛ ሲሆን፣ በአመት ወደ 42 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ገቢ አግኝቷል፡፡ ታዋቂዎቹ ዩናይትድ እና ዴልታ፣ የተሰኙ የአሜሪካ አየር መንገዶች  በ38 እና በ37.6 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ሁለተኛና ሶስተኛ ሆነዋል፡፡
የአየር መንገዶች ማህበር (አያታ) ዳይሬክተር ቶኒ ቴለር በሰጡት መግለጫ፣ የአለማችን አየር መንገዶች በዚህ አመት በድምሩ 18 ቢሊዮን ዶላር የተጣራ ትርፍ ያገኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል፡፡
በየቀኑ በሚደረጉ 100 ሺህ ያህል በረራዎች 50 ሺህ መዳረሻዎችን ማስተሳሰር የቻለውና መቶኛ አመቱን ያከበረው የአለማችን የአቪየሽን ኢንዱስትሪ፤ በያዝነው የፈረንጆች አመት 3.3 ቢሊዮን መንገደኞችንና 520 ሚሊዮን ኩንታል ጭነት ያጓጉዛል ተብሎ እንደሚጠበቅ የጠቆሙት ቶኒ ቴለር፤ ኢንዱስትሪው በአለም አቀፍ ደረጃ ከ58 ሚሊዮን በላይ የስራ ዕድሎችን እንደፈጠረ ተናግረዋል፡፡

                (ሬሣ ብምንታይ ከበደ? ሃሳቡ ኣብ ልዕሊ ሳብ ኣውዲቑ)

               አንድ የታወቀ ተረት እንዲህ ይላል፡፡ አንድ ድንቅዬ ወጣት የሰራዊት አባል የሆነ ገበሬ፤ ባህር ማዶ ተሰዶ ሳለ፤ አንድ ደብዳቤ ከሚስቱ ተልኮለት ኖሮ ይደርሰዋል፡፡ ሚስትየውን ያስጨነቃት ነገር አለ!! ግቢያቸው ውስጥ ድንች ለመትከል ፈልጋ ኖሮ፤ ምን ማድረግ እንዳለባት ልትጠይቀው ነው፡፡ “በምስራቅ በኩል ልዝራው? በደቡብ በኩል ልዝራው?” የሚል ነው የደብዳቤው ጭብጥ፡፡ “ምንም አድርገሽ ምን፤ ወደ ምሥራቅ ያለውን የቤታችንን ወገን እንዳትቆፍሪው ምክንያቱም ብዙ መሣሪያ የቀበርኩት እዚያ ጋ ነው!” ይላል ወታደር ባሏ! በዚያን ጊዜ በጦርነት ወቅት ደንብ እንደሆነው ሁሉ፣ ደብዳቤ ሁሉ ተቀዶ ተነቦ ነው ለባለቤቱ የሚተላለፈው፡፡ ስለዚህ በሳንሱር ሐላፊው ተነበበ፡፡ ስለጉዳዩ ምንም እውቀት የሌላት ሚስቱ ከጥቂት ቆይታ በኋላ፣ ተቆጥታ የፃፈችለት ደብዳቤ መጣ፡- “ስፍር ቁጥር የሌላቸው ወታደሮች የግቢውን ዙሪያ - ገባውን ሲቆፍሩት አመሹ! እሺ ምን ማድረግ ነው ያለብኝ?” የሚል የንዴት መለስ ደብዳቤ ነው የላከችለት፡፡ ወታደሩም፤ “በቃ ቆፍረው ከጨረሱማ፤ ድንቻችንን መትከል ጀምሪ!” አላት፡፡

                                             * * *

    የምናስበው ጠባብ መሬት (ሁዳድ) ሆና ሳለ፤ እሷኑ ማንም ሊወስድብን እንደሚችል ማመዛዘን ጤና ነው፡፡ ያለችንን ትንሽ ሊወርብን የሚችል ኃይል ሊኖር እንደሚችል ልብ እንበል፡፡ ያም ሆኖ “ሳይደግስ አይጣላም አንዘንጋ፡፡ (Blessing in disguise) በእርግጥ ምንም ዓይነት አገራዊ ጉዳይ ላይ ብንጠመድ፤ ሚስጢራዊነትን፣ ድብቅነትንና ልብ-ለልብ አለመናበብን፣ ካላስወገድን አባዜያችን ብዙ ነው፡፡ ምንም ያህል ዕቅድ ቢኖረን፣ ምንም ያህል ስትራቴጂ ቢኖረን፣ ምንም ዓይነት ልዩ ፕሮግራም ቢኖረን፣ ሚስጢራዊ ካደረግነውና ከህዝብ ካራቅነው ዞሮ ዞሮ “ቡመራንግ” ነው የሚሆነው፡፡ የተኮስነው መልሶ ሲመታን እንደማለት ነው፡፡ በዚህ አንፃር እነሱ ካረሱልሽ አንቺ ምን ቸገረሽ?!” የሚለው ወልዕክት ቀላል አይደለም፡፡ “ባልሽ አቂሞኛል ጅልሽ አቂሞኛል፤ አጋዡ ነኝ እንጂ፣ ጎባኑ አድርጎኛል!” የሚል ዘፈን ያስታውሰናል፡፡ (ጎባኑ እንግዲህ ሚስቱን የወሸመበት ሰው መሆኑ ነው፡፡አገዝኩት እንጂ ምን አጠፋሁ? ነው ነገሩ) ያም ሆኖ፣ ደብዳቤው መቀደዱ ይቅርና፣ የፃፍነው ሁሉ የሚነበብ፣ የምንተነፍሰው ሁሉ በየትንፋሹ መካከል ሊመረመር የሚችል፤ መሆኑን ማስተዋል አሊያም የዜግነት ግዴታም፣ ኃላፊነትም ወይም በሁለቱም፤ የሚያስኬድ ጉዳይ መሆኑን ልብ እንበል፡፡ የሀሳብ፣ የመናገር፣ የመፃፍ ነፃነት ወገናዊነትን አያውቅም፡፡ ዲሞክራሲ ውሉን ይስታልና፡፡ ማናቸውንም ኃላፊነት ስንወጣ፤ እኛ፣ ለእኛ፣ በእኛ መሆን አለበት፡፡

ለእኛነታችን ለምናቀርበው ማስረጃ ከጀርባችን ያለ ሰው አያስፈልገንም፡፡ ለ Ghost-waiter እንዲሉ ፈረንጆች፡፡ መተጋገዝ አንድ ሃገር ነው፡፡ ሙሉ በሙሉ በሌሎች ድጋፍ መኖር ግን ክፉ አባዜ ነው፡፡ የራስ ዕሴት ወይም ማንነት ከናካቴው ይጠፋልና! ይሄን ከልብ ያስተዋለ ሊቅ ነው “ሬሣ ለምን ከበደ? ሀሳቡን ሰው ላይ ስለጣለ” ብሎ የተረተው!!

በሞቷ ብዙዎችን ብታሳዝንም... በሥራዎቿ ብዙዎችን ታፅናናለች
ገጣሚ፣ ደራሲ፣ ድምጻዊት፣ የሙዚቃ ደራሲ፣ ጸሃፌ ተውኔት፣ ተዋናይት፣ የመብት ተሟጋች፣  የመጽሄት አርታኢ፣ የዩኒቨርሲቲ መምህርት፣ የፊልም ዳይሬክተር… ሌላም ሌላም ነበረች
አንተነህ ይግዛው

ባለፈው ረቡዕ አመሻሽ ላይ…
“ማያ ተፈጸመች!...” የሚለው አለምን ያስደነገጠ መርዶ ከወደ አሜሪካ፣ ኖርዝ ካሮሊና ተሰማ፡፡ ይሄን ድንገተኛ መርዶ የሰሙ ብዙዎች፣ በድንጋጤ ክው አሉ፡፡ ያችን ታላቅ ሴት እያሰቡ ልባቸው በሃዘን ተሰበረ፡፡ የአገር መሪዎችና ታዋቂ የአለማችን ግለሰቦች ሳይቀሩ፣ አንዲት ውድ ልጇን ያጣችው አሜሪካ ብቻ ሳትሆን፣ መላው ዓለም ስለመሆኑ አፍ አውጥተው መሰከሩ፡፡
የሲኤንኤኑ ዘጋቢ ቶድ ሊዎፖልድ ግን፣ “መላው ዓለምም ቢሆን፣ በዚያች ክፉ ምሽት አንዲት ልጁን አይደለም ያጣው!... አንዲት ማያን አይደለም የተነጠቀው!... ብዙ ልጁን፣ ብዙ ማያን እንጂ!...” በማለት ነው ክስተቱን የገለጸው፡፡
ሚያዝያ 4 ቀን 1928 ሴንት ሉዊስ ውስጥ የተወለደችው ጥቁር አሜሪካዊቷ ማያ አንጄሎ፣ እርግጥም አንድ ሆና ብዙ ሰው ነበረች፡፡ ገጣሚ፣ ደራሲ፣ የመብት ተሟጋች፣ ድምጻዊት፣ የሙዚቃ ደራሲ፣ ጸሃፌ ተውኔት፣ ተዋናይት፣ የመጽሄት አርታኢ፣ የዩኒቨርሲቲ መምህርት፣ የፊልም ዳይሬክተር… ሌላም ሌላም ብዙ ነገር ነበረች፡፡
በድርብ ድርብርብ የሙያ ጉዞዋ አለማቀፍ ዝናን የተጎናጸፈችው ማያ አንጄሎ፣ ለረጅም ጊዜ ሲሰቃያት በኖረው የልብ ህመም ተሸንፋ፣ በተወለደች በ86 ዓመቷ ባለፈው ረቡዕ ምሽት ኖርዝ ካሮሊና ዊንስተን ሳሌም ውስጥ በሚገኘው መኖሪያ ቤቷ ይህቺን አለም በሞት ተሰናበተች፡፡
ኤምኤልቢ ቤከን አዋርድ የሚባለውን አመታዊ ሽልማት የሚያዘጋጀው የአሜሪካ ድርጅት፣ ከሳምንታት በፊት ወደ ማያ አንድ መልዕክት ልኮ ነበር - “የህይወት ዘመን ተሸላሚ ልናደርግሽ ወስነናልና፣ ሆስተን ውስጥ በምናካሂደው ስነ-ስርዓት ላይ እንድትገኚልን በማክበር ጠርተንሻል!” የሚል፡፡ ማያ ግን፣ የጤንነቷ ነገር አስጊ ስለሆነ፣ በስፍራው እንደማትገኝ ከይቅርታ ጋር ገለጸች፡፡ ሽልማቱ በሌለችበት ማክሰኞ እለት ተሰጥቷት፣ እሷ በነጋታው ረቡዕ ይህቺን አለም ተሰናብታ ወደማይቀርበት ዓለም ተጓዘች፡፡
ባለፉት 50 አመታት የአለማችን የስነ-ጽሁፍ መድረክ ጎልተው ከወጡና አለማቀፍ እውቅናን ማትረፍ ከቻሉ ታላላቅ የአሜሪካ ደራሲያን አንዷ የሆነችው ማያ አንጄሎ፣ ራሷን ከትቢያና ከድቅድቅ ጨለማ ውስጥ በእልህ አስጨራሽ ትግል ፈልፍላ አውጥታ ለአለም የሰጠች ታላቅ ሴት እንደነበረች ብዙዎች ይመሰክሩላታል፡፡
ገና በለጋነቷ አንስቶ የመከራን ጽዋ መጎንጨት የጀመረችው ማያ፤ ወላጆቿ ክደው የጣሏት፣ በሰባት አመት ዕድሜዋ የገዛ እናቷ ፍቅረኛ አስገድዶ የደፈራት አሳረኛ ሴት ነበረች - ልጅነቷን ሳትጨርስ የልጅ እናት የሆነች ጎዳና አዳሪ፡፡ ዘ ጋርዲያን እንደዘገበው ደግሞ፣ ይህቺ ለመከራ የፈጠራት ሴት፣ በአንድ ወቅት ህይወቷን በሴተኛ አዳሪነት የምትገፋ ምስኪን ሴት ነበረች - ‘ነበረች’ ነው ታዲያ!...
በጊዜ ሂደት ግን፣ ማያ ራሷንም ታሪኳንም ቀየረች፡፡ ማያ ለአመታት ለብቻዋ ከኖረችበት ጨለማ ስትወጣ፣ ለብዙዎች የተረፈ ደማቅ ብርሃንን ይዛ ነው፡፡ አድማስ ተሻግሮ ማንጸባረቅ የቀጠለውን ብርሃኗን የለኮሰችው፣ “አይ ኖው ኋይ ዘ ኬጅድ በርድ ሲንግስ” በሚል ርዕስ ለንባብ ባበቃችው ግለ-ታሪኳ ነበር፡፡
እ.ኤ.አ በ1969 የታተመውና በአጻጸፉም ሆነ በሚያነሳቸው ርዕሰ ጉዳዮች በዘመኑ ያልተለመደ እንደነበር የሚነገርለት ይህ ድንቅ ስራዋ ለንባብ መብቃቱን ተከትሎ ብዙዎች መነጋገሪያቸው አድርገውታል፡፡ በአለማቀፍ ደረጃ አንባብያን ተሻምተው ከሚገዟቸውና በገፍ ከሚሸጡ ድንቅ መጽሃፍት ተርታ ለመሰለፍና በሚሊኖች ኮፒ ለመቸብቸብም ጊዜ አልፈጀበትም፡፡ ዘመናት የማይሽሩት ተጠቃሽ ስራዋ ሆኖ ዘለቀ - አንባብያንን እያረካ፣ ለጸሃፍት የንሸጣ ምንጭ እየሆነ፡፡
ማያ በዚህ አላበቃችም፣ የሰላ ብዕሯን ወድራ ተግታ መጻፏን ገፋችበት፤ ‘ዘ ኸርት ኦፍ ኤ ውመን’ እና ‘ጋዘር ቱጌዘር ኢን ማይ ኔም’ን ጨምሮ፣ ከፍተኛ ተነባቢነትን ያገኙ ስምንት የግለ-ታሪክ መጽሃፍትን ለአለም አበረከተች፡፡ ሶስት የወግ መጽሃፍትን እንዲሁም ‘ጀስት ጊቭ ሚ ኤ ኩል ድሪንክ ኦፍ ዎተር ፎሪ ዋን ዲሊ’ን (ለፑልቲዘር ሽልማት የታጨ) እና ‘ኤንድ ስቲል አይ ራይዝ’ን የመሳሰሉ በርካታ ተወዳጅ የስነግጥም መድበሎችንም ለንባብ አበቃች፡፡
በውስጧ የሙዚቃ ተሰጥኦ እንዳለ የተረዳችው ማያ፣ እ.ኤ.አ በ1957 የመጀመሪያ የሙዚቃ አልበሟን ‘ሚስ ካሊፕሶ’ በሚል ርዕስ ለአድማጮቿ ከማቅረብ አልፋ፣ ዳንስ በመማር በተለያዩ የአሜሪካ ግዛቶች እየተዘዋወረች መዝፈኗንና በዳንሰኛነት መስራቷን ገፍታበታለች፡፡ ‘ፕሮጊ ኤንድ ቤስ’ በተሰኘ የኦፔራ ኮንሰርት ላይ በዳንሰኝነት በመሳተፍም አለምን ዞራለች፡፡ በጣሊያንና በእስራኤል ዘመናዊ ዳንስን አስተምራለች፡፡ ሶስት የግራሚ ሽልማቶችን በማሸነፍም፣ የሙዚቃ ጉዞዋን ስኬት በታሪክ መዝገብ ላይ በማይለቅ ማህተም አትማለች፡፡
በብሄራዊ ደረጃ የሚካሄደው ናሽናል ብላክ ቲያትር ፌስቲቫል የመጀመሪያዋ ሊቀመንበር የነበረችው ይህቺ ባለብዙ ሙያ ሴት፣ በኒዮርክ ተሰርቶ ለእይታ በበቃ “ዘ ብላክስ” የተሰኘ ቲያትር ላይ የአንዲትን ንግስት ገጸ-ባህሪ ተላብሳ በመተወን የተውኔቱን አለም ተቀላቅላለች። ‘ካባሬት ፎር ፍሪደም’ በሚለውና ራሷ ጽፋና አዘጋጅታ በተወነችበት ሙዚቃዊ ትያትር ስኬትን የተጎናጸፈችውና የላቀ የትወና ችሎታ ባለቤት መሆኗን ያረጋገጠችው ማያ፣ በቲያትር ዘርፍ ለሚሰጠው ለታዋቂው ቶኒ ሽልማት እስከመታጨት ደርሳለች፡፡
በ1960ዎቹ መጀመሪያዎቹ አመታት ወደ አፍሪካ የመጣችው ማያ፣ በወቅቱ በግብጽ እየታተመ ለንባብ ይበቃ በነበረው ‘ዘ አረብ ኦቭዘርቨር’ መጽሄት አርታኢ ሆና ከመስራቷ በተጨማሪ፣ ወደ ጋና በማምራትም የጋና ዩኒቨርሲቲ አስተዳደር ረዳት በመሆን አገልግላለች፡፡
ከስድስት በላይ ቋንቋዎችን አቀላጥፋ የምትናገረውና ከ30 በላይ የክብር ዶክትሬቶችን ያገኘችው ይህቺ ልበ ብሩህ ሴት፣ ዮኒቨርሲቲ ገብታ ባትማርም ዩኒቨርሲቲ ገብታ አስተምራለች። ዊንስተን ሳሌም ውስጥ የሚገኘው ዌክ ፎሬስት ዩኒቨርሲቲ፣ ማያ ለረጅም አመታት በአሜሪካ ጥናቶች መምህርነት ያገለገለችበት ታላቅ ዩኒቨርሲቲ ነው፡፡
“ማያ አንጄሎ በህይወቷና በአስተምህሮቷ በአለም ዙሪያ በሚገኙ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ያነቃቃች ብሄራዊ ውድ ሃብት ነበረች” በማለት ነበር፣ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚደንት ናታን ኦ ሃች በሞቷ ምሽት በስሜት ተውጦ ማያን የገለጻት፡፡
ለኪነ-ጥበብ የተሰጠችው ማያ፣ ወደ ፊልሙ አለምም ጎራ ብላለች፡፡ እ.ኤ.አ በ1972 ፕሮዲዩስ ያደረገችው ጂዮርጂያ፣ ጂዮርጂያ የተሰኘው ፊልሟ፣ ወጥ ፊልም በመስራት የመጀመሪያዋ አፍሪካ አሜሪካዊት ሴት አድርጓታል፡፡
ማልኮም ኤክስ፣ ማርቲን ሉተር ኪንግ፣ ሮዛ ፓርክስና የመሳሰሉት የመብት ተሟጋቾች የቅርብ ጓደኞቿ የነበሩት ይህቺ ሴት፣ ከእነዚህ ወዳጆቿ ጋር በመቀናጀትም ሆነ በተናጠል በአሜሪካ የመብቶች ትግል ንቅናቄ ውስጥ ደማቅ ተሳትፎ ስታደርግ እንደነበር ታሪኳ ይናገራል፡፡
በዚህ ሳምንት በሞት የተለየችው ማያ፣ በህይወት በነበረችባቸው አመታት በመብት ተሟጋችነትና በዘርፈ ብዙው የሙያ ጉዞዋ ያበረከተችው አስተዋጽኦ እጅግ የላቀና የጎላ ስለመሆኑ ከሰሞኑ ከሊቅ እስከ ደቂቅ አፍ አውጥቶ መመስከሩን ይዟል።
“በዘመናችን እጅግ ደምቀው ከታዩ ታላላቅ ብርሃኖች አንዷ ማያ ናት፡፡ ምርጥ ጸሃፊ፣ ልዩ ጓደኛና ፍጹም እጹብ ድንቅ ሴት ነበረች፡፡ ተሰጥኦዋን በተለያዩ መንገዶች ስትገልጽ ኖራለች፡፡ ከሁሉም በላይ ግን ድንቅ ተራኪ ነበረች - እነዚያ ታላላቅ ታሪኮቿ እውነትን የሚዘክሩ ናቸው፡፡” በማለት ነበር ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ሞቷን እንደሰሙ፣ ለማያ ያላቸውን ስሜት ለሲ ኤን ኤን የገለጹት፡፡
የተዋጣላት ገጣሚ የነበረችው ማያ፣ እ.ኤ.አ በ1993 በተከናወነው የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ቢል ክሊንተን በዓለ ሲመት ላይ በመጋበዝ፣ ‘ኦን ዘ ፐልስ ኦፍ ዘ ሞርኒንግ’ የተሰኘ የግጥም ስራዋን አቅርባለች፡፡ በአሜሪካ ታሪክ መሰል የበዓለ ሲመት ግጥሞችን በማቅረብ ሁለተኛዋ ገጣሚ፣ ለዚህ ክብር በመታጨት ደግሞ የመጀመሪያዋ ጥቁር ሴት ናት፡፡
በሙያዋ ባበረከተችው የላቀ አስተዋጽኦ፣ በርካታ ሽልማቶችን ማግኘት የቻለችው ማያ፣ እ.ኤ.አ በ2000 የአሜሪካ ብሄራዊ የስነጥበብ ሜዳይን ያገኘች ሲሆን፤ እ.ኤ.አ በ2011 ላይ ከፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ እጅ፣ በአገሪቱ ለሲቪል ዜጎች የሚሰጠው ከፍተኛው የክብር ሽልማት የሆነውን የፕሬዚዳንቱን የነጻነት ሜዳይ ተቀብላለች፡፡
ባለፈው ረቡዕ በሞት የተለየችው ማያ በሞቷ ብዙዎችን ብታሳዝንም፣ በስራዎቿ ብዙዎችን ታጽናናለች፡፡ የቀብር ስነስርዓቷ በደማቅ ሁኔታ በመጪው ሳምንት እንደሚከናወን ይጠበቃል። አሜሪካ ውድ ልጇን ወደ መቃብር ለመሸኘት እየተዘጋጀች ባለችበት በዚህ ሰሞን፣ ጎን ለጎንም የውድ ልጇን ጅምርና ለአንባብያን ያልደረሱ ውድ የጽሁፍ ስራዎች በኒውዮርክ የህዝብ ቤተ-መጽሃፍት ማሰባሰቧን ተያይዛዋለች፡፡  

       ኧርነስት ሚለር ሄሚንግዌይ፡ 1899 – 1961 - አሜሪካዊው ደራሲ ሄሚንግዌይ፤ ሙሉ በሙሉ ወደ ሥነፅሁፍ  ከመግባቱ በፊት በጋዜጣ ሪፖርተርነት የሰራ ሲሆን በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት  ለአሜሪካ ቀይ መስቀል በአምቡላንስ ሹፌርነትም አገልግሏል፡፡ ወደ ድርሰቱ ዘልቆ ከገባ በኋላ Men without Women በሚል ርእስ  የአጭር ልብወለድ ሥራዎቹን አሰባስቦ ያሳተመ ሲሆን  በመቀጠልም A Farewell to Arms በሚል ርእስ ረዥም ልብወለዱን አሳትሟል፡፡
በልብወለድ ሥራ የፑልቲዘር ሽልማት ያሸነፈበት The Old Man and the Sea ከአስር  ዓመት በፊት በደራሲና ተርጓሚ መስፍን አለማየሁ ወደ አማርኛ ተመልሶ ለአንባቢያን የደረሰ ሲሆን ብዙዎች ማራኪ ሆኖ መተርጎሙን መስክረውለታል፡፡ በነገራችን ላይ የአገራችን አንባቢያን ለብዙዎቹ የሔሚንግዌይ ሥራዎች በተለይ ለአጭር ልብወለዶቹ  እንግዳ አይደሉም፡፡ ጥቂት የማይባሉ አጭር ልብወለዶቹ ወደ አማርኛ የተተረጎሙ ሲሆን የተወሰኑት በእዚሁ ጋዜጣ ላይ መውጣታቸው ይታወሳል፡፡
በተሲያት በኋላው ሞቃት አየር ሳቢያ  ጠዋት ጠዋት መፃፍ እንደሚያዘወትር የገለፀው ደራሲው፤ በቀን አንድ ገፅ ከሩብ ገደማ ይፅፍ ነበር፡፡ ሥነፅሁፍ በብዛት በማምረት ትጋቱ የሚታወቀው ሄሚንግዌይ፤ መቼ መስራትና  መቼ ማቆም እንዳለበትም ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ እ.ኤ.አ በ1934 ዓ.ም ለጓደኛው ለኤፍ. ስኮት ፊትዝጌራልድ በፃፈው ደብዳቤ “አንድ ገፅ ምርጥ ሥራና ዘጠና አንድ ገፆች  ዝባዝንኬ እፅፋለሁ፡፡ ዝባዝንኬውን ታዲያ የቆሻሻ ቅርጫት ውስጥ ለመጣል እሞክራለሁ” በማለት የአፃፃፍ ልማዱን ጠቁሞታል፡፡ ዝነኛው ደራሲ ሄሚንግዌይ፤ በፑልቲዘር ሽልማት ብቻ ግን አልረካም፡፡ እናም  እ.ኤ.አ በ1954 ዓ.ም የሥነፅሁፍ የኖቤል ሽልማት ለማሸነፍ በቃ፡፡

ትሩማን ካፖቴ፡ 1924-1984 - አሜሪካዊው የረዥም ልብወለድ፣ የፊልም ፅሁፍና የቴአትር ደራሲ የነበረው ካፖቴ፤ እ.ኤ.አ በ1966 ዓ.ም በፃፈው In Cold Blood የተሰኘ ዝነኛ ኢ-ልብወለዱ  ይታወቃል፡፡
ይሄ ሥራው ለአንባቢ በበቃ በዓመቱም ወደ ፊልም ተቀይሮ ለተመልካች ቀርቧል- በተመሳሳይ ርእስ፡፡ እውነተኛ ታሪኮችን በልብወለድ የአፃፃፍ ቴክኒክ በማቅረብ ዝነኝነት ያተረፈው ደራሲው፤ ኒው ጆርናሊዝም የተሰኘ አዲስ የአፃፃፍ ስልትን እንዳስተዋወቀ ይነገርለታል።
ካፖቴ በጀርባው ተንጋሎ በአንድ እጁ ሼሪ የተቀዳበት ብርጭቆ፣ በሌላ እጁ ደግሞ እርሳስ ከያዘ ሊፅፍ ተዘጋጅቷል ማለት ነው፡፡ በ1957 ዓ.ም ለፓሪስ ሪቪው በሰጠው ቃለ-ምልልስ፤ ካልተጋደምኩ በቀር ማሰብ አልችልም ብሏል። “አልጋ ላይ ወይም ሶፋ ላይ ሰውነቴን ዘርግቼ በእጄ ሲጋራና ቡና መያዝ አለብኝ፡፡ እያጨስኩና ፉት እያልኩ ነው ለመፃፍ የምዘጋጀው፡፡” ሲል የአፃፃፍ ልማዱን ገልጿል፡፡ እንደ አብዛኞቹ ፀሃፍት ከአዕምሮው የመጣለትን ሃሳብ በቀጥታ በመተየቢያ ማሽን ላይ መፃፍ እንደማይሆንለት የተናገረው ካፖቴ፤ የመጀመሪያ ረቂቅ ፅሁፉን በእርሳስ እንደሚፅፍ፣ ከዚያም ሙሉውን  እየከለሰ በእርሳስ ከፃፈ በኋላ ወደ ታይፕ እንደሚገባ በቃለ-ምልልሱ ወቅት አስረድቷል፡፡

ፍላነሪ  ኦ’ኮኖር፡ 1925-1964 – በ20ኛው ክ/ዘመን የአሜሪካ ሥነፅሁፍ ውስጥ ጉልህ ሥፍራ ከሚሰጣቸው ምርጥ የአጭር ልብወለድ ደራሲያን መካከል  ትጠቀሳለች፡፡ የመጀመርያ የአጭር ልብወለድ መድበሏ A Good Man is Hard to Find ይሰኛል፡፡ እ.ኤ.አ በ1972 ዓ.ም The Complete Stories በሚል ሥራዋ የናሽናል ቡክ አዋርድስ ተሸላሚ ሆናለች፡፡ ዘ ሃቢት ኦፍ ቢይንግ በተባለው መፅሃፍ ላይ ስለአፃፃፍ ልማዷ ስታስረዳ፤ “በየቀኑ ለሁለት ሰዓታት ብቻ ነው የምፅፈው፤ ምክንያቱም ከዚያ በላይ አቅም የለኝም፤ በእነዚህ ሁለት ሰዓታት ውስጥ ግን ምንም ነገር ከሥራዬ እንዲያናጥበኝ አልፈቅድም” ብላለች፡፡  
ፍራንሲን ፕሮዝ፡  የBlue Angel መፅሃፍ ደራሲና የፔን አሜሪካ ማዕከል ፕሬዚዳንት የነበረችው ፕሮዝ  ለየት ያለ የአፃፃፍ ልማድ አዳብራለች። ምንም ጊዜም ስትፅፍ፤ የባለቤቷን ቀይና ጥቁር ስኩዌር ያለው ፒጃማ ሱሪና ቲ-ሸርት እንደምትለብስ ለዴይሊ ቢስት ተናግራለች፡፡ “በመታደልም ይሁን ባለመታደል ለየት ባለ አፓርትመንት ውስጥ ነው የምንኖረው፡፡ 120 ጫማ ከፍታ ያለው መስኮታችን፤ ፊቱን የሰጠው ለተንጣለለ ባህር ወይም ጥቅጥቅ ደን አይደለም፡፡ ከመስኮቱ በአንድ ጫማ ተኩል ርቀት የጡብ ግድግዳ ተገትሯል፡፡ ስለዚህ ምንም ዓይንንና ቀልብን የሚሰርቅ ነገር የለም፡፡ ልፅፍ ስቀመጥ ትኩረቴ ሳይከፋፈል ልሰራ እንደምችል ይሰማኛል” ብላለች- አሜሪካዊቷ ደራሲ ፍራንሲን ፕሮዝ፡፡

Saturday, 31 May 2014 14:42

6ቱ ላጤዎች

የኔ አይን እዚች ላይ
የዚች አይን እሱ ላይ፤
የሱ አይን እዛች ላይ
የዛች አይን እኔ ላይ፤
አቤት ክፉ እጣ
የሃብታም ቤት ጠኔ፡፡
ሶስቱ ኮረዳዎች
ሶስቱ ኮበሌዎች
ይኸው ስንት ዘመን መለያ ስማችን “ስድስቱ ላጤዎች”
(አንድነት ግርማ)


=========

እኔና እሱ
የኔ አበቃቀል፤
በጌሾና ብቅል፡፡
በጥንስስ መጥቼ፤
እሱኑ ጠጥቼ፤
አለሁት በዋዛ፤
እንዲሁ ስንዛዛ፡፡
ያ…ግን ጐረቤቴ፤
ያለው ፊት ለፊቴ፤
ጥንስሱ በወተት፤
ዕድገቱ በእሸት፡፡
እሱ ማር ወተቱን፤
ብርቱካን ካሮቱን፤
ክትፎና ዱለቱን፡፡
አኗኗሩን አውቆ፤
አካሉን ጠብቆ፤
አምሮበታል ፋፍቶ፤
ቦርጩ ከፊት ገፍቶ፡፡
እኔ ግን መጥጬ፤
ቡቅርን ለጥጬ፤
ጨጓራዬን ልጬ፤
በጌሾ ለፍልፌ፤
በሱ ተለክፌ፤
በጥንስስ መንምኜ፤
እንዲሁ ባክኜ፤
ይኸውና አለሁት፤
እሱን እያየሁት፡፡
በመጨረሻ ግን ጥሎ አይጥለኝ ጌታ፤
ድንገት አሳስቦኝ እንዲያ ወደ ማታ፤
አስታወሰኝና ሰጠኝ መፅናናቱን፤
እኔም እሱም ሞተን ከሳጥን መግባቱን፡፡
(ከአምሳሉ ጌታሁን ደርሰህ)

         በደቡብ ክልል በሰገን አካባቢ ህዝቦች ዞን፣ በኮንሶ ወረዳ በካራት ከተማ የተዘጋጀው የባህል ፌስቲቫል ዛሬ ይከፈታል፡፡ የኮንሶ ወረዳ አስተዳደር ባለፈው አመት ተመሳሳይ የባህል ፌስቲቫል ያዘጋጀ ሲሆን የፌስቲቫሉ አላማ ኢትዮጵያን ከአፍሪካ ቀዳሚ ያደረጋትን በዓለም ቅርስ መዝገብ የተመዘገበውን የኮንሶ ባህላዊ መልክአ ምድር ጨምሮ በወረዳው ያለውን ታሪካዊና ባህላዊ ቅርሶች ወደ ኢኮኖሚ ለመቀየር እንዲሁም የአለም አቀፍ ጐብኚዎችን ትኩረት ለመሳብ እንደሆነ የኮንሶ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ በራቆ በላቸው ተናግረዋል፡፡
ዛሬ በሚከፈተው በዚህ የባህል ፌስቲቫል ላይ የተለያዩ ዝግጅቶች የሚቀርቡ ሲሆን የኮንሶ ዲስትሪክት ሆስፒታል ምረቃ፣ በተለያዩ ባህላዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ሲምፖዚየም፣ የመሰረተ ልማት ጉብኝት፣ የጐዳና ላይ የባህል ትዕይንትና ኮንሶን ለአለም የሚያስተዋውቁ ሌሎች ትርኢቶች ይገኙበታል ተብሏል፡፡ ፌስቲቫሉ ከዛሬ ጀምሮ እስከ ፊታችን ሰኞ የሚካሄድ ሲሆን በርካታ የአገር ውስጥና የውጭ እንግዶች ይታደማሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ላለፉት 40 ዓመታት በማህበረሰብ እድገትና በህፃናት ላይ ትኩረት አድርጐ እየሰራ ሲሰራ የቆየው “ኤስ ኦ ኤስ የህፃናት መንደሮች ኢትዮጵያ”፤ ለአርቲስቶችና ጋዜጠኞች የጉብኝት ፕሮግራሞችን ያዘጋጀ ሲሆን ጉብኝቱ የድርጅቱን 40ኛ ዓመት በዓል በማስመልከት የተዘጋጀ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ ድርጅቱ የሚከተለው የህፃናት አስተዳደግ ፍልስፍና፤ አርቲስቶች፣ ጋዜጠኞችና ታዋቂ ግለሰቦች በጉዳዩ ላይ የበለጠ እንዲሰሩ የሚያነሳሳቸው እንደሚሆን ኤስ ኦ ኤስ የላከው መግለጫ ይጠቁማል፡፡ ግንቦት 29 ከጠዋቱ 2፡30 በዋናው የድርጅቱ ቢሮ በጋዜጣዊ መግለጫ የሚጀመረው ፕሮግራሙ፤ በአዲስ አበባ የሚገኙ ተቋማቱን በማስጐብኘት እንደሚቀጥል ታውቋል፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስነ - ጥበባት ኮሌጅ የማስተርስ ዲግሪ ተማሪዎች ከህንድ ኤምባሲ ጋር በመተባበር፣ በአገራችን የመጀመሪያ የተባለውን የአጫጭር ፊልሞች ፌስቲቫል ያካሂዳሉ፡፡ ፌስቲቫሉ ዛሬና ነገ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስድስት ኪሎ ካምፓስ በሚገኘው የባህል ማዕከል የሚካሄድ ሲሆን አላማውም የአጫጭር ፊልሞችን ጥበብ ለአገራችን ተመልካቾች ለማስተዋወቅና በአገራችን ለሚገኙ የአጫጭር ፊልም ፀሐፊዎች፣ አዘጋጆች፣ ፕሮዱዩሰሮችና ተዋንያን እውቅናና ክብር ለመስጠት እንዲሁም ሙያቸውን ለማበረታታት እንደሆነ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቴአትር ጥበባት ትምህርት ክፍል በላከው መግለጫ አስታውቋል፡