Administrator

Administrator

Saturday, 20 September 2014 10:34

ከባህር ወጥታ ጤዛ ላሰች

(በባር ወጣችም አወናሰችም) - የጉራጌ ተረት

          ከዕለታት አንድ ቀን አንዲት በባልትናባለሙያ ነኝ የሚሉ ወይዘሮ በአንድ ከተማ ይኖሩ ነበረ ይባላል፡፡ አንድ ቀን “ዛሬ የምሠራው ገንፎ ነው፡፡ ጐረቤት ሁሉ ይጠራ” ብለው አዘዙ፡፡ ጐረቤቱ ሁሉ ተጠራና የገንፎው ግብዣ ተጧጧፈ፡፡ የዱሮ ጊዜ የገንፎ አበላል እንደዛሬ በማንኪያ አልነበረም፡፡ ሁሉም እጁን ታጥቦ ክብ ክብ ሠርቶ የሚችለውን ያህል መጉረስ ነው፡፡ ሴትዮዋ ባለሙያነታቸውን ደጋግመው እየተናገሩ እየፎከሩ፤ “ብሉ እንጂ ጐረስ ጐረስ ነው እንጂ!” እያሉ ያበረታታሉ፡፡ በየክቡ እየዞሩ፤ “እህስ እንዴት ነው ገንፎዬ” ይላሉ፡፡

እንደ ዕውነቱ ከሆነ ገንፎው በጣም ቀጥፎ፣ እጅግ ላቁጦ ጣት ላይ የሚጣበቅ ነው፡፡ አንደኛ ጐረቤት “እንዴ ድንቅ ነው፤ የእርሶ ሙያ ምን ይጠረጠራል” አለ ወደ ሁለተኛው ቀርበው “እህስ ገንፎዬ እንዴት ነው?” ሁለተኛ ጐረቤት - “አይ እጅ! እንዲህ ያለ ሙያ ከየትም አይገኝ!” ሴትዮዋ የበለጠ እየተኩራሩ ወደ ሶስተኛው ዞሩ፤ “እህስ ገንፎዬን እንዴት አገኘኸው?” ይሉታል፡፡ እሱም እንደሌሎቹ የድርሻውን ውዳሴ በመስጠት፤ “ገንፎ ከበሉ አይቀር ይሄን ዓይነቱን ነው! እንደው እንዴት አርገው ቢያገነፉት ነው እሜቴ እንዲህ ያማረልዎ?” ይላል፡፡ በመጨረሻ ወደ አንድ ውሸት የማይወድ አንደበተ - ቀና፣ ቁምነገረኛ ሰው ዘንድ መጥተው፤ “እህስ ወዳጄ ገንፎዬ እንዴት ነው?” ሰውዬው ዝም አለ፡፡ “ምነው ዝም አልክ? አልጣፈጠህም እንዴ?” ብለው አጠንክረው ጠየቁት፡፡ ሁሉ ሰው የሰውዬውን መልስ ይጠብቃል፡፡ ሰውዬው ጉሮሮውን አጠራና፤ “ኧረ እሜቴ፤ እንደው መጣፈጡ ቀርቶ እጄን በለቀቀኝ!” አላቸው፡፡

                                            ***

“ዕውነቱን ተናግሮ የመሸበት ማደር” እጅግ ወሳኝ ነው፡፡አገር ያድናል፡፡ ህዝብን ከግርታ ያወጣል፡፡ በአንፃሩ መሸነጋገል ከቶም የአገር ጠር ነው፡፡ በይሉኝታም ይሁን በፍርሀት፣ አውቀን በድፍረትም ይሁን ሳናውቅ በስህተት፤ መሸነጋገልና መወዳደስ፤ “ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ” ነው፡፡ በትክክል ያልሰራነውን ሠርተሃል ተብለን አደባባይ ወጥተን መፎከር ኋላ ደብቁኝ ደብቁኝን ያመጣል፡፡ እንደ እሜቴ ገንፎ ነውና! ለረዥም ዘመን በታዋቂ - ተደናቂነት፣ አሊያም በሥልጣን መከታ፤ ሲሸነግሏቸው እየተኩራሩ የኖሩ አያሌ ናቸው፡፡ “እናቷ መራቂ ልጅቷ አሜን ባይ” እንደሚባለው መሆኑ ነው፡፡ (Yes-men of Athens እንዲሉ ፈረንጆች) ዛሬም ዕውነተኛውን ዲሞክራሲ ከሐሳዊው ዲሞክራሲ መለየት አለብን፡፡ ሀቀኛውን ፍትሕ ከአስመሳዩ ፍትሕ አጥርተን መጓዝ አለብን፡፡

መልካም አስተዳደርን ከብልሹው አስተዳደር ነጥለን ዕቅጩን መናገር አለብን፡፡ በአደባባይ ስለ ፀረ ሙስና እየተናገርን ዙሪያ መለስ የሙስና አረንቋ ውስጥ ተዘፍቀን ከሆነ ጉዱ መለየት አለበት፡፡ በምንንቀሳቀስበት የሥራ ሂደት ውስጥ ሁሉ “የነካነው ሁሉ ወርቅ ይሆናል” ብለን ደርሶ ሚዳስ እንሁን ብንል፣ ውሎ አድሮ የምንጋለጥበት ሰዓት ስለሚመጣ እያንዳንዷን እርምጃችንን በጥንቃቄ ብንመዝን ይሻላል፡፡ ዕውነቱን በትክክል ተናግሮ የወደፊት መንገድን አርሞ መጓዝ እንጂ መገበዝ ወንዝ አያሻግርም፡፡ ኢኮኖሚው እጅግ ያዘቀዘቀው ህዝብ “እንኳን እናቴ ሞታ እንደውም አልቅስ አልቅስ ይለኛል” እያለ መሆኑን እንገንዘብ፡፡ አገር ያለህዝብ ድጋፍ ወደፊት አትራመድም፡፡

ህዝብን አክብሮ፣ ያለ አንዳች ሽንገላ መታደጊያውን ሰዓት እንወቅ፡፡ ህዝብ አብሮ ለመጓዝ ዝግጁነቱን ያሳየበትን ወቅት በትክክል ለይቶ መጠቀም ብልህነት ነው፡፡ ቸገረኝ ሲል እህ ብሎ ማዳመጥ ትክክለኛ የአመራር መርህ ነው፡፡ ኢኮኖሚያዊ ብሶትንም ሆነ ፖለቲካዊ እሮሮን ሰምቶ በአመቸው መንገድ ሁሉ መፍትሔ መስጠት ወቅቱ የሚጠይቀው ጉዳይ ነው፡፡ ወቅቱን ያላወቀ ወይም ያልተገነዘበ አካሄድ “ከባህር ወጥታ ጤዛ ላሰች” እንደተባለው ይሆናል፡፡ አሁንም አሁንም እናስተውል፡፡ 2007 ዓ.ም የማስተዋያ ዓመት ይሁንልን!

            ሸፍተው የነበሩ የዞኑ የፖሊስ ልዩ ሃይል አዛዥና የሚሊሽያ አባላት እጃቸውን ሰጡ

        በጋምቤላ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በጎደሬ ወረዳ፣ በመዠንገር ዞን በተቀሰቀሰውና አሁንም ድረስ በአንዳንድ ቦታዎች በቀጠለው ግጭት እጃቸው እንዳለበት የተጠረጠሩ የክልሉ ባለስልጣናት ያለመከሰስ መብታቸው ተነስቶ በቁጥጥር ስር እየዋሉ ነው፡፡ በአዲስ አመት ዋዜማ የተቀሰቀሰውና ከ40 በላይ ሰዎችን ህይወት የቀጠፈው ግጭት መነሻ ከመሬት ባለቤትነት ጋር የተያያዘ እንደሆነ ለአዲስ አድማስ የገለፁት ምንጮች፤ “ደገኞች መሬታችንን ይልቀቁ” የሚሉ የአካባቢው ተወላጆችና አንዳንድ የክልሉ ባለስልጣናት በመንግስት ተግባራዊ እየተደረገ ያለውን የሰፈራ ፕሮግራም ተገን በማድረግ ነባር ይዞታ ያላቸውን ነዋሪዎች በማፈናቀላቸው ግጭቱ መፈጠሩን ተናግረዋል፡፡

በአካባቢው ተወላጆችና ከሌሎች አካባቢዎች በመጡ ነዋሪዎች መካከል ለረጅም ጊዜ የቆየና በየጊዜው የሚያገረሽ ግጭት እንዳለ የሚታወቅ ሲሆን፣ በቅርቡ የተከሰተው ግጭት ሊቀሰቀስ እንደሚችል የፌደራል መንግስት በደረሰው መረጃ መሰረት፣ በአፈ ጉባኤ ካሳ ተክለብርሀን የተመራ ቡድን ከክልሉ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር በመተባበር በአካባቢው የማረጋጋት ስራ ቢሰራም፣ በዞኑ ያሉ አንዳንድ የፖሊስና የሚሊሺያ አባላት “መሬታችንን ይልቀቁ” የሚለው ሃሳብ እንዲሰርፅ በማድረጋቸው ግጭቱ እንደተፈጠረ ምንጮቻችን ጠቁመዋል፡፡

ግጭቱ ከተፈጠረ በኋላም የዞኑን የፖሊስ ልዩ ሀይል አዛዥ ጨምሮ የፖሊስና የሚሊሽያ አባላት ሸፍተው ጫካ መግባታቸውን የተናገሩት ምንጮች፤ በአሁኑ ወቅት አዛዡና ሌሎች ጥቂት አባላት እጃቸውን ለመንግስት ሃይሎች እንደሰጡ ገልፀዋል፡፡ በአካባቢው የተከሰተው ግጭት ሁነኛ መፍትሔ ካልተበጀለት፣ በአቅራቢያ ወደሚገኙ ሌሎች አካባቢዎች ሊዛመት ይችላል የሚል ከፍተኛ ስጋት መፈጠሩን ያመለከቱት ምንጮቹ፤ ከወራት በፊት ማንነታቸው ያልታወቀ የታጠቁ ሰዎች ዲማ ተብሎ በሚጠራው የክልሉ አካባቢ አስር ሰላማዊ ዜጎችን ገድለው መሰወራቸውን ገልፀዋል፡፡ በአካባቢው የተከሰተው ግጭት ከክልሉ የፀጥታ ሃይሎች ቁጥጥር በላይ በመሆኑ፣ የፌደራል ፖሊስና የመከላከያ ሃይል ጣልቃ ገብቶ የማረጋጋት ስራ እየሰራ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል፡፡

                       በፊልም ባለሙያው ቴዎድሮስ ተሾመና በደራሲ አትንኩት ሙሉጌታ መካከል በተመሰረተው የመብት ይገባኛል ፍትሃብሄር ክርክር፣ ፍ/ቤት በአርቲስት ቴዎድሮስ ተሾመ ላይ የ10 ሚሊዮን ብር እግድ ከትናንት በስቲያ አስተላለፈ፡፡ ከሳሽ ደራሲ አትንኩት ሙሉጌታ፤ ነሐሴ 13 ቀን 2006 ዓ.ም ለፍ/ቤት ባቀረቡት ክስ፤ አርቲስት ቴዎድሮስ ተሾመ ለእይታ ያበቃው “ሦስት ማዕዘን” የተሰኘ ፊልም ጻሪክ በ2000 ዓ.ም ካሳተሙት “ፍቅር ሲበቀል” የተሰኘ የረዥም ልቦለድ መፅሃፍ የተወሰደ ነው የሚል አቤቱታ አሰምተዋል፡፡ “ሦስት ማዕዘን” የተሰኘው ፊልም መፅሃፋቸው ታትሞ ከወጣ ከ5 ዓመት በኋላ ለዕይታ እንደበቃ በክሳቸው የጠቆሙት ከሳሽ፤ አርቲስት ቴዎድሮስ ያለደራሲው ፈቃድ የቦታና ገፀ-ባህርያት ስሞችን በመቀያየር ብቻ የመፅሀፉን መሰረታዊ ጭብጥና የታሪክ ፍሰት በፊልሙ ውስጥ መጠቀሙን አመልክተዋል፡፡ አርቲስት ቴዎድሮስ ፊልሙን በተደጋጋሚ ለተመልካች በማሳየት ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘቱን በክስ ማመልከቻው ላይ የጠቆሙት ደራሲው፤ ተከሳሽ በፈፀሙት ተግባር ከፍተኛ የሞራል ውድቀት እንደደረሰባቸውና ፊልሙ የመፅሃፉ ቀጣይ ህትመት ላይ ተፅዕኖ እንደፈጠረ በመጠቆም የ10 ሚሊዮን ብር ካሳ ጠይቀዋል፡፡

ከሳሽ የመፅሃፉን ጭብጥ፣ መቼትና የተለያዩ ታሪኮች ከ“ሶስት መአዘን” ፊልም ታሪክ ጋር በማመሳከር ለፍ/ቤቱ በማስረጃነት አቅርበዋል፡፡ ጉዳዩን እየመረመረ የሚገኘው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ ባለፈው መስከረም 6 በዋለው ችሎት፤ የክስ ማመልከቻው ለተከሳሽ ደርሶ መልስ እንዲሰጥበትና የከሳሽ ምስክሮች እንዲቀርቡ ለጥቅምት 28 ቀን 2007 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ በተጨማሪም ከሳሽ ጳጉሜ 3 ቀን 2006 ዓ.ም በፃፉት ማመልከቻ የ10 ሚሊዮን ብር ክስ ማቅረባቸውንና ቢፈረድላቸው ፍርዱን የሚያስፈፅሙበት ንብረት እንደማያገኙ በመጥቀስ ተከሳሹ በተለያዩ ባንኮች ካላቸው ገንዘብ ላይ 10 ሚሊዮን ብር እንዲታገድላቸው ማመልከታቸውን ያስታወሰው ፍ/ቤቱ፤ አቶ ቴዎድሮስ ተሾመ በዘመን ባንክ ከሚገኘው የሂሳብ ደብተራቸው 10 ሚሊዮን ብር እስከ ቀጣዩ ቀጠሮ ድረስ ታግዶ እንዲቆይ ትዕዛዝ አስተላልፏል፡ አርቲስት ቴዎድሮስ ፊልሙን በተደጋጋሚ ለተመልካች በማሳየት ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘቱን በክስ ማመልከቻው ላይ የጠቆሙት ደራሲው፤ ተከሳሽ በፈፀሙት ተግባር ከፍተኛ የሞራል ውድቀት እንደደረሰባቸውና ፊልሙ የመፅሃፉ ቀጣይ ህትመት ላይ ተፅዕኖ እንደፈጠረ በመጠቆም የ10 ሚሊዮን ብር ካሳ ጠይቀዋል፡፡

ከሳሽ የመፅሃፉን ጭብጥ፣ መቼትና የተለያዩ ታሪኮች ከ“ሶስት መአዘን” ፊልም ታሪክ ጋር በማመሳከር ለፍ/ቤቱ በማስረጃነት አቅርበዋል፡፡ ጉዳዩን እየመረመረ የሚገኘው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ ባለፈው መስከረም 6 በዋለው ችሎት፤ የክስ ማመልከቻው ለተከሳሽ ደርሶ መልስ እንዲሰጥበትና የከሳሽ ምስክሮች እንዲቀርቡ ለጥቅምት 28 ቀን 2007 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ በተጨማሪም ከሳሽ ጳጉሜ 3 ቀን 2006 ዓ.ም በፃፉት ማመልከቻ የ10 ሚሊዮን ብር ክስ ማቅረባቸውንና ቢፈረድላቸው ፍርዱን የሚያስፈፅሙበት ንብረት እንደማያገኙ በመጥቀስ ተከሳሹ በተለያዩ ባንኮች ካላቸው ገንዘብ ላይ 10 ሚሊዮን ብር እንዲታገድላቸው ማመልከታቸውን ያስታወሰው ፍ/ቤቱ፤ አቶ ቴዎድሮስ ተሾመ በዘመን ባንክ ከሚገኘው የሂሳብ ደብተራቸው 10 ሚሊዮን ብር እስከ ቀጣዩ ቀጠሮ ድረስ ታግዶ እንዲቆይ ትዕዛዝ አስተላልፏል፡፡

   የሪያድ ልዩ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት፤ የሽብር ተግባራትን ለመፈጸም ተንቀሳቅሰዋል በሚል ክስ በተመሰረተባቸው አራት የሳኡዲ አረቢያ ዜጎችና በአንድ ኢትዮጵያዊ ላይ ከአንድ እስከ አምስት አመት የሚደርስ የእስራት ቅጣት መጣሉን አረብ ኒውስ ዘገበ ፡፡ ስሙ ያልተገለጸው ኢትዮጵያዊና አራቱ ግብረ አበሮቹ፣ የቅዱስ ቁርአንን አስተምሮት በሚጥስ መልኩ ከሚንቀሳቀሱ የአገሪቱ ጽንፈኛ ሃይሎች ጋር ግንኙነት በመፍጠር ብጥብጥ ለማስነሳት ሞክረዋል፤ ሌሎችንም ለአመጽ አነሳስተዋል በሚል በቀረበባቸው ክስ፣ ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው፣ ኢትዮጵያዊው የአምስት አመት እስራት ተፈርዶበታል፡፡ የእስር ጊዜውን ጨርሶ ከወጣ በኋላ ወደ አገሩ እንዲመለስ የተፈረደበት ኢትዮጵያዊው፣ ለሃጂና ኡምራ ጸሎት ካልሆነ በቀር፣ ከአሁን በኋላ ወደ አገሪቱ እንዳይገባም ተከልክሏል፡፡

ሁለቱ ግብረ አበሮቹ የአንድ አመት ከስድስት ወራት እስራትና ለሶስት አመታት የሚቆይ የጉዞ ገደብ የተጣለባቸው ሲሆን፣ ቀሪዎቹ ሁለቱ የአንድ አመት እስራትና ለሶስት አመታት የሚቆይ የጉዞ ገደብ ተጥሎባቸዋል፡፡ተከሳሾቹ በ30 ቀናት ውስጥ ይግባኝ ማለት እንደሚችሉ ፍርድ ቤቱ አስታውቋል፡፡ በተከሳሾቹ ላይ የተላለፈው ውሳኔ፣ ባለፉት ወራት ከተላለፉት መሰል ውሳኔዎች ጋር ሲነጻጸር ቀላል የሚባል መሆኑን የጠቆመው ዘገባው፤ ፍርድ ቤቱ በቅርቡ ከ10 በላይ በሆኑ ተጠርጣሪዎች ላይ እስከ እድሜ ልክ የሚደርስ ቅጣት መጣሉን አስታውሷል፡፡

        በአንጋፋው ደራሲ አዳም ረታ የተጻፈው “መረቅ” የተሰኘ የረጅም ልቦለድ መጽሃፍ ሰሞኑን በገበያ ላይ ይውላል፡፡ ለደራሲው ስምንተኛው የሆነው ይሄው መፅሃፍ፤ ከስድስት መቶ በላይ ገጾች ያሉት ሲሆን፣ በቅርቡ በተለያዩ መጽሃፍት መደብሮችና አዟሪዎች ለገበያ እንደሚውል ታውቋል፡፡ ደራሲ አዳም ረታ ከዚህ በፊት “ማህሌት”፣ “ግራጫ ቃጭሎች”፣ “እቴሜቴ ሎሚ ሽታ”፣ “አለንጋ እና ምስር”፣ “ከሰማይ የወረደ ፍርፍር”፣ “ህማማት እና በገና” እና “ይወስዳል መንገድ፣ ያመጣል መንገድ” የተሰኙ ተወዳጅ የአጫጭርና የረጅም ልቦለድ መጽሃፍትን ለንባብ አብቅቷል፡፡ አዳም ከዚህ በተጨማሪም፣ በአይነቱ ለየት ያለና ከ1ሺህ 600 በላይ ገጾች እንደሚኖረው የተነገረለትን፣ “የስንብት ቀለማት” የተሰኘ ረጅም ልቦለዱን እያጠናቀቀ እንደሚገኝ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡ለረጅም አመታት ኑሮውን በባህር ማዶ ያደረገው አዳም ረታ፣ ሰሞኑን ወደ አዲስ አበባ እንደመጣ ለማወቅ ተችሏል፡፡

Saturday, 13 September 2014 15:54

ሳቅ አታ‘ቅም

ሳቅ አታ‘ቅም
“ሳቅ አታ‘ቅም አሉኝ - ሳቅ እንዳስተማሩኝ
ሳላ‘ቅ ብስቅ እንኳን - ከሳቅ ላይቆጥሩልኝ
እንዴት ብዬ ልሳቅ፣ ሳቅስ መች ለምጄ?
በጭጋግ ታፍኜ፣
በጉም ተጀቡኜ፣
በዶፍ ተወልጄ፡፡”
አትበል ወዳጄ፡፡
* * *
በጉም መሃል እንጅ - የወጣችው ፀሐይ
ነፍስን እያሳሳች - ሀሴት የምታሳይ
ብቻዋን ስትቆም - በጠራራው ሰማይ
ንዳድ ሀሳብ ዘርታ - ባሳር ምታጋይ፡፡
ብቻ ሲሆንማ - ሳቅም ጠራራ ነው፤
ጥርስን ያራቆተ - የከንፈርህ ግዳይ፡፡

ቅርብኝ
ኖኅን መሰኘት አምሮህ - ታንኳ ቢጤ ስትገነባ
አምላክ ያዘዘህ ቀርቶ - ወዳጅህ መርከብህ ከገባ
ዓለም የጨው ክምር ሆና - ፍጥረታቷ ሲረግፉ
ድንገት ታንኳህ ላይ ብገኝ - ነፍሴን አርዷት ዶፉ
ርግቧን መሆን አልሻም፤ ከጎንህ እንዳልገኝ
የትም እንደወጣሁ ልቅር፤ ላንተስ ቁራህን ያድርገኝ
(በቅርቡ በደሴ ከተመረቀው የገጣሚ አካል ንጉሴ “ፍላሎት (የነፍስ አሻራዎች)” 2006፤ የግጥም መድበል የተወሰዱ)


=========


ኢዮሀ!
ኢዮሀ!
አበባ ፈነዳ!
ፀሀይ ወጣ ጮራ፡፡
ዝናም
ዘንቦ
አባራ፡፡
ዛፍ
አብቦ
አፈራ፡፡
ክረምት መጣ ሄደ
ዘመን ተወለደ፡፡
ዓለም አዲስ ሆነ፡፡
ለሊት ሲነጋጋ
ጋራው ድንጋይ ከሰል
የተተረከከ ፍም እሳት ደመናው
ፀሐይ ያነደደው፡፡
ዓለም ሞቆ
ደምቆ፡፡
ብርሃን ሲያሸበርቅ
ጤዛው ሲያብረቀርቅ፤
ሕይወት ሲያንሰራራ
ፍጥረት ሲንጠራራ
ዘመን ተለወጠ መስከረም አበራ፡፡
“ኢዮሃ አበባዬ፡፡”
(ከገብረክርስቶስ ደስታ)

 

የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር..መሑሀ

አዲሱ አመት ..2007.. ዓ/ም ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሰላም ፣የጤናና የብልጽግና እንዲሆን ይመኛል፡፡
የዘመን መለወጫን ምክንያት በማድረግ ከእለቱ ጋር የነበረ ገጠመኝ ልናስነብባችሁ ወደድን፡፡ በመሆኑም ተከታዩን እነሆ ለንባብ ፡፡
.....ነገሩ ያጋጠመኝ በ2006 ዓ/ም መግቢያ ጳጉሜ 4/2005 ነው፡፡ እኔ በእድሜዬ ገና ሰላሳው የገባሁ ስሆን እዩኝ እዩኝ የምል .....መሬቱን ሲረግጠው ድንጋዩ ይፈነቀላል የምባል እይነት ነኝ፡፡.. ታድያ ...አለባበሴን አሳምሬ በአዲስ ዘመን ዋዜማ ነበር ወደ ከተማው ብቅ ያልኩት፡፡ እኔ ወንደላጤ ነኝ፡፡ ቤተሰብ እንዳለው ሰው በግ ወይንም ዶሮ ከሚሸጥበት ሳይሆን ያመራሁት ወደ ልብስ ተራው ነበር፡፡ ብዙም ባይሆንም በመጠኑ ደመወዜ እንደልብ የሚያንቀሳቅሰኝ ነበር፡፡ ከአንድ ኃብታም ድርጅት ውስጥ በአስተዳደ ሩም ፣በእቃ ግዢነቱም ፣በጠቅላላ አገልግሎትነቱም ፣ባለጉዳይ በማነጋገሩም ፣ በመወ ሰኑም ፣በማስወሰኑም...ብቻ ሰውየው ሌላ ሰው መቅጠር ስለማይፈልጉ እኔን ብቻ ከላይ ከታች ስለሚያመላልሱ...እኔም ታድያ ደህና አድርጌ ነበር የተጠቀ ምኩበት፡፡ አሁን ግን አንድ ወር ሆኖኛል ስራዬን ከለወጥኩ.....
ወደ ዘመን መለወጫው ገጠመኝ ልመለስና የ2006/መግቢያ የልብስ ገበያ በዋጋው ብዙም የሚታማ አልነበረም፡፡ ታድያ እየዞርኩኝ ጫማ ስመለከት አንዲት ኮረዳ በድንገት ገጠመችኝ፡፡
... ያነሳሁትን ጫማ እጄ ላይ አይታ...እውይ ባባትህ ...ያምራል ...ብትለካውስ? አለችኝ፡፡
...እኔም ቀና ብዬ ስመለከታት የሆነች ቆንጆ ልጅ ናት፡፡ መለስ አድርጌም...ምን ያረጋል ቢያምር... የወደድሽው አንቺ እንጂ ...ስላት...ታድያ እኔ ከወደድኩልህ መች አነሰህ? አንተ ደግሞ ጉረኛ ነህ መሰለኝ...ብላ ከት ብላ ሳቀች፡፡ አ.አ.ይ እኔ እንኩዋን ጉረኛ አይደለሁም፡፡ ግን እውነ..ን ነውኮ ...ሌሎች አያምርም ቢሉኝስ...ዋጋው ደግሞ ውድ ነው አልኩዋት፡፡
...እንገግዲህ...አለችኝና ትታኝ ወጣች፡፡ እኔ ግን አብሮአት ልቤ ሸፈተ፡፡ ጫማውን መግዛቱን ትቼ እሱዋን ተከተልኩዋት፡፡
..እኔ የምልሽ...
- ምንድነው የምትለኝ...
..የአዲስ አበባ ልጅ ነሽ?...
ከት ብላ ሳቀች፡፡ ምነው? አልኩዋት
- እንጃ...ጥያቄህ አስቆኝ ነዋ...መልሱዋ ነበር፡፡
..ምን ያስቃል...ሁኔታሽ...ንግግርሽ...ሁሉ ደስ ብሎኝ ነውኮ...
- ከአዲስ አበባ ውጭ ያለ ሰው እንደእኔ አይናገርም? አለችኝና ወዲያው
በማስከተል ...ዋናው ነገር... ጫማውን ገዛኸው? አለችኝ፡፡
..አንቺ ትተሸኝ ስትሄጂ ተውኩት...
- ለምን?
..እንዳታመልጪኝ... ልከተልሽ ...ብዬ ነዋ...
- በል ...ና እንሂድና መጀመሪያ ጫማውን ግዛና ከዚያ በሁዋላ እናወራለን...አለችኝ፡፡
በዚህ መልክ ነበር የእኔና የሜላት ግንኙነት የተጀመረው፡፡ ከዚያም ለአንድ ሶስት ወር ገደማ ሻይ ቡና እየተባባልን ቆየን፡፡ ሜላት በጣም ጨዋ ልጅ ነች፡፡ የሰው ገንዘብ በፍጹም አትፈልግም፡፡ አንድ ነገር ላድርግልሽ ስላት ፍጹም ፍቃደኛ አይደለችም፡፡ ለምንበላው ምግብ እንኩዋን ቢያንስ ሻይ ቡናውን ካልቻለች አይመቻትም፡፡ በቃ ...ለትዳር ጉዋደኛ የምትሆነኝ ልጅ አገኘሁ...የእንቁጣጣሽ ስጦታዬ ነች ብዬ አሰብኩ፡፡ ለእናት እና አባ.. ሁኔታውን አጫወትኩዋ ቸው፡፡ ቤተሰቤ በሙሉ ተደሰተ፡፡ መቼ ነው ታድያ ሽማግሌ የምንልከው የሚለው ጭቅጭቅ ከቤተሰቤ እያየለ ሲመጣ እስቲ ቆይ... ከእርሱዋ ጋር እኮ ገና አላወራነውም...እኔ የእራሴን ፍላጎትና ግምት ነው የነገርኩዋችሁ...አልኩዋቸው፡፡
...አንድ እሁድ እኔና ሜላት ለምሳ ቀጠሮ ያዝን፡፡ አብረን እየተመገብን እያለን...ላጎርሳት ስሞክር ...አአይ...አለችና ፊቷ ቅጭም አለ፡፡
..ምነው?...የእኔ ጥያቄ ነበር...
- አአይ...እኔ ጉርሻ አልወድም...
..ለምን?
- አባ..ን ስለሚያስታውሰኝ...ሰው ሲያጎርሰኝ አልወድም...
ለካንስ አባትዋ ሞተዋል፡፡ አዘንኩኝ፡፡ እንደገና ሀሳቤን ሰብሰብ አደረግሁና...
..አኔ የምልሽ...
- እህ...
..ለምን... እ.....ስላት... ገና ሀሳቤን ሳልቋጭ...
-ገብቶኛል ልትለው የፈለግኸው ነገር ገ ብ ቶ ኛ ል... አለችኝ፡፡
.. ታድያ ...ምን ችግር አለው?
-ምንም ችግር የለውም፡፡ ነገር ግን እኔ እነግርሀለሁ፡፡ አለችኝ፡፡
የዚያን እለት በዚሁ ተለያየን፡፡ ከዚያ በሁዋላ ስልክ ብደውል ...ቀድሞ ሳገኛት የነበረበት ካፊ..ሪያ እና ምግብ ቤት ብሔድ...ማንም...ምንም መረጃ ሊሰጠኝ አልቻለም፡፡ አጣሁዋት፡፡ግራ ተጋባሁ፡፡ በጣም ፈለግሁ ዋት...አላገኘሁዋትም፡፡ ጉዋደኛዋን ቤተሰብዋን...ማንንም አላውቅም፡፡ ታመምኩ ፡፡ አድራሻ አልሰጠችኝም፡፡ የት ነው የምትሰሪው ስላት በግልዋ እየተዟዟረች እንደም ትሰራ ነው የነገረችኝ፡፡ እንዲሁ ...ስጨነቅ... ስጨነቅ... ግንቦት 15/2006 /አንድ መልእክት ደረሰኝ፡፡ እንዲህ ይላል...
.....በድንገት ገበያ ላይ የገኘሁህ ወድ ጉዋደኛዬ...እንደምን ሰነበትክ፡፡ ድንገት ስለጠፋሁብህ በመጠኑም ቢሆን እንደጎዳሁህ ይሰማኛል፡፡ ስሜትህን እንዳልጎዳ ብዬ እንጂ እኔ ሚስት ለመሆን ቀርቶ ከወንድ ጋር እንኩዋን ለመገናኘት ገና በሕክምና የማስተካክለው የጤና ጉዳይ ስለነበረኝ አልደፍርም ነበር፡፡ በቤተሰብ አባል ተደፍሬ ...በድብቅ ...በህገ ወጥ መንገድ ጽንስ በማቋረጥ ምክንያት ማህጸኔ ተጎድቶ ስለነበር ለሕክምና ወደ ሆስፒታል መግባት ነበረብኝ፡፡ የመጨ ረሻ ምሳ የበላን ማግስት ነበር ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የገ ባሁት፡፡ ያንን የምሳ ቀጠሮ ብመለስም ባልመለስም ብዬ ሆን ብዬ ነበር ያመቻቸሁት፡፡ አሁን ሕክምናዬን ጨርሼ እቤ.. ገብቻለሁ፡፡ ከፈለግህ ጠይቀኝ፡፡ ላለፈው ይቅርታ አድር ግልኝ፡፡ አሁን እግዚአብሔር ይመስገን ጤነኛ ነኝ፡፡..... ይላል ...በመልእክተኛ የመጣው ደብዳቤ፡፡
እጅግ በጣም ነበር ያዘንኩትም ...የተደሰትኩትም፡፡ ታማ ሆስፒታል በነበረችበት ወቅት ከጎኗ ብሁን ኖሮ እወድ ነበር፡፡ ነገር ግን ያንን እድል አልሰጠችኝምና አዘንኩ፡፡ በሌላ በኩል... ከሕመሙዋ ድና በመውጣቷ ደግሞ በጣም ተደሰትኩ፡፡ ለማንኛውም ሁኔታዋን ለማየት በሰ ጠችኝ አድራሻ ከቤትዋ ሄጄ አገኘሁዋት፡፡ ተቃቅፈን ተላቀስን፡፡ ለካንስ እርሱዋም ወድዳኝ ነበር፡፡ ጭራሽ ፍቅሬ በረታ፡፡ በእቅፍዋ ስር እንድሆን...በእቅፌ ስር እንድትሆን ሁለታችንም ወደድን፡፡
እነሆ...በተገናኘን በአንድ አመታችን...ዛሬ መስከረም 3/2007 ዓ/ም ሰርጋችን ነው፡፡
.....ደስ ብሎናል ...ደስ ይበላችሁ....
ይስሐቅ ብርሐኔ/ከአዲስ አበባ/መሳለሚያ

Saturday, 13 September 2014 13:42

አገኘሁ አዳነ - ጣምራ ጠቢብ

         ተወልዶ ያደገው ጎንደር ነው፡፡ በአባቱ የሥራ ጸባይ ምክንት በልጅነቱ አሥመራን፣ አቆርዳትን፣ ተሰኔን ጨምሮ ወደተለያዩ አካባቢዎች ተጉዟል፡፡ እናቱ በልጅ አስተዳደግ በጣም ጥብቅ በመሆናቸው ከቤት እንዲወጣ የሚፈቀድለት ወይ ወደ ትምህርት ቤት፣ ወይ ወደ ቤተክርስቲያን ብቻ ነበር፡፡ ያንን ዘመን ሲያስታውስ በኪነ ቅብ ሥራዎች ያሸበረቀችውን ሎዛ ማርያም ቤተክርስቲያንን ያነሳል፡፡ ዓይኑም ልቡም፣ ቀልቡም በሥዕል ሕብረ ቀለም የተወጋው ያኔ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ከዚያ ሕፃናት አምባ ገባ፡፡ አምባ የፈለግከውን ለመሆን ነገሮች የተመቻቹበት፣ ነፃነት ያለበት አካባቢ እንደነበር ይናገራል፡፡ አጥር ተበጅቶለት ላደገው አገኘሁ ሕፃናት አምባ የተመቸ ሥፍራ ሆነለት፡፡ አንድ ቦታ ላይ በትኩረት መቆየትን፣ ማንበብን፣ ማስተዋልን ቀድሞ ስለሚያውቃቸው በመጣበት መንገድ ቀጠለ፡፡ ለዛሬ ማንነቱ ያ ዘመን እርሾ እንደሆነውም አይጠራጠርም፡፡
ሠዓሊ አገኘሁ አዳነ ከመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት አንስቶ ሥዕልን ይሞክር ነበር፡፡ ዕድለኛም ስለነበር ከልጅነቱ ምርጥ ምርጥ የሚባሉ መምህራን ገጥመውታል፡፡
አገኘሁ ከልጅነቱ ጀምሮ ጠያቂ ባህሪይ እንደነበረው ያስታውሳል፡፡ አራተኛ ክፍል እያለ የሥዕል መምህሩ በውሃ ቀለም ይሥላል፡፡ ከደቂቃዎች በኋላ አገኘሁ ያየውን ማመን አልቻለም፡፡ እጅጉን ተደነቀ፡፡
“የሚገርም ዓይነት፣ ዓይኑ እሳት የሚተፉ ጥቁር ሰውዬ ሳለ፡፡ ‘እንዴት ውሃ ሰው ይሆናል?’ ‘እንዴት ከሰው ዓይን እንደዚህ ዓይነት ኃይል የበዛበት ብርሃን ይረጫል?’ ስል በመደነቅ የጠየኩትን መቼም አልረሳውም፡፡”
የአገኘሁ ውስጣዊ ፍላጎት፣ ተሰጥዖውና ችሎታው እንዳለ ሆኖ ህፃናት አምባ ያንን የሚያለመልም ውሃ፣ አፈር እና ብርሃን እንደሆነው ይጠቅሳል፡፡ አገኘሁ ራሱን ወደ መንፈሳዊ ሰው አስጠግቶ ያስባል፡፡ ከአራት ማዕዘን ግድግዳ ውጪ ያለን ነገር የሚናፍቅ፣ በገሃድ የሚታይ፣ የሚጨበጠው የሚሰለቸው ዓይነት ሰውም ይመስላል፡፡
ሠዓሊነቱን ሳይቀር ወደዚ ቢወስደው ይወዳል፡፡ “ከሚዳሰስ እውነት ነገረ-ተረትን፤ ከዕለት ዜና ተረትን ልወድ እችላለሁ፡፡ ያለቀና የሚያልቅ ነገር ይሰለቸኛል፡፡ አገኘሁ ሠዓሊ ብቻ አይደለም፡፡ ገጣሚም ነው፡፡ “ጨለማን ሰበራ” እና “ለምን?” የተሰኙ ሁለት መድበሎች አሳትሟል፡፡ በባህርይው ማዳመጥ ደስ እንደሚለው የሚናገረው አገኘሁ አለማዊ ሰው ባይሆንም ይመስላል፡፡
“ሰውን ብደግፍ፤ ክርስቶሳዊ ስብዕና ቢሮረኝ እወዳለሁ፡፡ ማለም፣ ከሃሳብ ጋር መጫወት ደስ ይለኛል፡፡” ሠዓሊ አገኘሁ አዳነ ስፔይንን፣ ሆላንድን፣ ፈረንሳይን፣ ጀርመንን ፖርቹጋልን እና ቤልጂየምን ገብኝቷል፡፡ በነበረው ቆይታም ብዙ ነገሮችን ስለመማሩ ይናገራል፡፡
“በራሴ ፍጹምነት ታስሬ እንደነበር ተገንዝቤአለሁ፡፡ ለምለሚቷ ሀገሬ የሚለውን ሳይቀር ቀንሼአለሁ፡፡ ምክንያቱም በሌላው ሀገር ሃሪፍ ነገር ስላለ፡፡” ሠዓሊ አገኘሁ ባለትዳር እና የሦስት ልጆች አባት ነው፡፡ ቤተሰቦቹ ለሁለመናው ብርታቱ እንደሆኑም ይጠቅሳል፡፡
አገኘሁ ከልጅነቱ መምህርነትን ይመኝ ነበር፡፡ እንደፈለገው ግን ፈጥኖ አላገኘውም፡፡ በተለያዩ መሥሪያ ቤቶች ሲሰራ ቆይቶ ቢዘገይም ከመምህርነት ጋር ተገናኝቷል፡፡ ዛሬ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አለ ፈለገ ሰላም የሥነ-ጥበብ እና ዲዛይን ት/ቤት መምህር ነው፡፡ ሠዓሊ አገኘሁ አዳነ ወደፊት ወደ መፈውሰ ጥበብ ወይም ‘Art Therapy’፣ ‘Physical Therapy’፣ ‘Spritual Therapy’ ቢገባ ደስ እንደሚለው፣ ሥዕሉንም ቢሆን ከሰው ልጅ ጋር በቀጥታ እንዲገናኝ ማድረግ ቢችል ደስ ይለዋል፡፡
ምንጭ፡- ነቢይ ግርማ፣ “ጋለሪያ ቶሞካ አገኘሁ አዳነን ያቀርባል” (2007 ዓ.ም) በሚለው መጽሄት ላይ ያሰፈረው፡፡

Saturday, 13 September 2014 13:20

የዛሬ 40 ዓመት፡፡

(መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም)
… መስከረም ሁለትን ሳስብ ብዙ ነገር ወደ አዕምሮዬ ይመጣል፡፡ ደርግ ከንጉሰ ላይ ሥልጣን ከተረከበ በኋላ በየዓመቱ መስከረም ሁለት ትልቅ ክብረበአል ነበር፡፡ ወጣቱ አብዮት የሚባለውን ሲያይ መጀመሪያ አካባቢ ጉጉና ደስተኛ ነበር፡፡ በአሉም በሠራዊቱ የተለያዩ ትርኢቶች ታጅቦ፣ በየአመቱ በአብዮት አደባባይ (መስቀል አደባባይ) በከፍተኛ ድምቀት ይከበር ነበር፡፡ ወታደሩ ከ4-5 ሰአት የሚዘልቅ ትርኢቶችን ያቀርባል፡፡ በታላቁ ቤተ-መንግስትና በብሔራዊ ቤተመንግስትም በእለቱ ጓድ መንግሥቱ ኃለማርያም እና ባለቤታቸው ወ/ሮ ውብአንቺ ቢሻው በተገኙበት ለሁሉም የቤተመንግስቱ ጠባቂዎች ታላቅ ግብዣ ይደረግ ነበር፡፡
መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም ደግሞ ሲታወስ ደርግ አዋጁን ከተናገረ በኋላ፣ ህዝቡ የእርስ በእርስ ግጭት ጠብቆ ነበር፡፡ ከፍተኛ እልቂት ይመጣል ተብሎ ተሠግቶ ነበር፡፡ ታንኮችና መትረየስ የጫኑ ተሽከርካሪዎች ይርመሰመሱ ነበር፡፡ ሰው መተያየት ፈርቷል፣ መኪናዎቹንና ታንኮቹን ቀና ብሎ ማየት ፈርቷል፡፡ ሰው በአጠቃላይ እርስ በእርስ ተፈራርቷል፡፡ ምናልባት ሌሊት አሜሪካን በአውሮፕላን ወረራ ፈጽማ ወይም እስራኤል መጥታ ንጉሱን ይወስዳሉ የሚሉ ሃሳቦች በፍራቻ መሃል ይንሸራሸሩ ነበር፡፡
ክቡር ዘበኛ እና ወታደሩ ሊጋጭ ይችላል የሚል ስጋትም ነበር፡፡ ነገር ግን ክቡር ዘበኛ ምንም የወሰደው እርምጃ የለም፡፡ የመሣሪያ ድምጽ እንኳ በእለቱ ኮሽ አላለም፡፡ መውረዳቸውን አምኖ ተቀብሏል፡፡ ይህ ባይሆን እንኳ መፈንቅለ መንግስት አድራጊው ወገን፣ ክቡር ዘበኛ ካንገራገረ ማጥቃት የሚችል ሠራዊት በቤተ-መንግስቱ በድብቅ ተዘጋጅቶ ነበር፡፡
ንጉሡ ከቤተ-መንግስታቸው በደርጉ ሃይሎች ተከበው፣ በተዘጋጀችለቸው ቮልስዋገን መኪና ውስጥ ገብተው ወደ 4ኛ ክ/ጦር ሲወሰዱ፣ ብዙ ህዝብ በመንገድ ላይ ወጥቶ ይመለከት ነበር፡፡ በእድሜ ጠና ባሉት ሰዎች ላይ የማዘን ስሜት ይስተዋል ነበር፡፡ ወጣቱ ደግሞ “ሌባው! ሌባው! ሌባው!” የሚል ስድብ በፉጨትና በጩኸት እያጀበ ይሰነዝራል፡፡ ወጣቱ በጣም ይሳደብ ነበር፡፡ በተለይ ቮልስዋገኗ መስቀል አደባባይ አካባቢ ስትደርስ የነበረው ፉጨትና ጭብጨባ ልዩ ነበር፡፡
ደርጉ ዋና ዋና የሚባሉትን የመንግስት ስልጣኖች በሚገባ በቁጥጥሩ ስር ከዋለ በኋላ ስለነበር እሣቸውን ከስልጣን ያወረደው መንገዱ ሁሉ የቀና ሆኖለታል፡፡ ጃንሆይም ይህን ስለሚያውቁ በአጋዦቻቸው አማካይነት ሌላ እርምጃ ለመውሰድ አላንገራገሩም፡፡ ዝም ነው ያሉት፡፡ ወደ ቮልስዋገኗ እንዲገቡ ሲጠየቁ አላንገራገሩም፡፡ ለምን በቮልስዋገን ተወሰዱ? ተብሎ ሲታሰብ ደርግ እሣቸው መሆናቸው ሳይታወቅ እንዲሄዱ የተጠቀመበት ቴክኒክ ነበር፡፡ ተራ ሰው እንዲመስሉና ግርግር እንዳይፈጠር ነው፡፡ ነገር ግን ሰው አውቆታል፡፡ በኋላ ዳርና ዳር መትረየስ የጫኑ ጂፖች አጅበዋቸው ሲሄዱ ሰው ከፉጨትና ጭብጨባ፣ ስድብ በቀር አንዲት ጠጠር እንኳ አንስቶ አልወረወረም፡፡ በዚያ ላይ ደህንነቱ በሰው መሃል ተሰግስጓል፡፡ ወታደሩም አንዳንዱ ሲቪል ለብሷል፡፡ ጃንሆይ ከስልጣን ከወረዱ በኋላ በእውነቱ ምስኪናዊ ህይወት ነው ያሳለፉት፡፡ ማንም ጠያቂ የላቸውም ነበር፡፡ የሚቀርባቸውም ሰው አልነበረም፡፡ ብቻቸውን አንድ ቤት ውስጥ ነበር የሚኖሩት፡፡ ንጉሱ ዘወትር ፊታቸውን ወደ ቤተክርስቲያኑ አዙረው ፀሎት ሲፀልዩ ስታይ በጣም ያሳዝኑ ነበር፡፡ ማንም አያናግራቸውም፤ አይጠጋቸውም ነበር፡፡ አንዲት ምግብ የምታበስል ልጅ አለች፤ እሷም ብትሆን በተወሰነ ሰዓት መጥታ ስራዋን ሰርታ ነው የምትሄደው፡፡ አርብ እና አሮብን ጠንቅቀው ይፆሙ ነበር፡፡ ልጅቱም ዘግይታ ነው ምግብ የምትሰራላቸው፡፡ ልጅቱ ልብሱን አዘጋጅታላቸው ትሄዳለች፡፡ ራሳቸው ይለብሳሉ፡፡ በዚህ መልኩ በዚያው በቤተ መንግስቱ በቀን እስረኝነት ከሰው ተገልለው ሲኖሩ ከቆዩ በኋላ ህይወታቸው ማለፉ ተነገረ…
(“ህይወት በመንግስቱ ቤተ-መንግስት” የተሰኙ ተከታታይ መፅሃፎች ደራሲና የቀድሞ ልዩ ሃይል አባል ወ/ር እሸቱ ወንድሙ ለአዲስ አድማስ ከፍተኛ ሪፖርተር አለማየሁ አንበሴ መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም አስመልክቶ ከሰጡት ቃለ ምልልስ የተወሰደ፡፡)

Saturday, 13 September 2014 13:20

የዛሬ 40 ዓመት፡፡

(መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም)
… መስከረም ሁለትን ሳስብ ብዙ ነገር ወደ አዕምሮዬ ይመጣል፡፡ ደርግ ከንጉሰ ላይ ሥልጣን ከተረከበ በኋላ በየዓመቱ መስከረም ሁለት ትልቅ ክብረበአል ነበር፡፡ ወጣቱ አብዮት የሚባለውን ሲያይ መጀመሪያ አካባቢ ጉጉና ደስተኛ ነበር፡፡ በአሉም በሠራዊቱ የተለያዩ ትርኢቶች ታጅቦ፣ በየአመቱ በአብዮት አደባባይ (መስቀል አደባባይ) በከፍተኛ ድምቀት ይከበር ነበር፡፡ ወታደሩ ከ4-5 ሰአት የሚዘልቅ ትርኢቶችን ያቀርባል፡፡ በታላቁ ቤተ-መንግስትና በብሔራዊ ቤተመንግስትም በእለቱ ጓድ መንግሥቱ ኃለማርያም እና ባለቤታቸው ወ/ሮ ውብአንቺ ቢሻው በተገኙበት ለሁሉም የቤተመንግስቱ ጠባቂዎች ታላቅ ግብዣ ይደረግ ነበር፡፡
መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም ደግሞ ሲታወስ ደርግ አዋጁን ከተናገረ በኋላ፣ ህዝቡ የእርስ በእርስ ግጭት ጠብቆ ነበር፡፡ ከፍተኛ እልቂት ይመጣል ተብሎ ተሠግቶ ነበር፡፡ ታንኮችና መትረየስ የጫኑ ተሽከርካሪዎች ይርመሰመሱ ነበር፡፡ ሰው መተያየት ፈርቷል፣ መኪናዎቹንና ታንኮቹን ቀና ብሎ ማየት ፈርቷል፡፡ ሰው በአጠቃላይ እርስ በእርስ ተፈራርቷል፡፡ ምናልባት ሌሊት አሜሪካን በአውሮፕላን ወረራ ፈጽማ ወይም እስራኤል መጥታ ንጉሱን ይወስዳሉ የሚሉ ሃሳቦች በፍራቻ መሃል ይንሸራሸሩ ነበር፡፡
ክቡር ዘበኛ እና ወታደሩ ሊጋጭ ይችላል የሚል ስጋትም ነበር፡፡ ነገር ግን ክቡር ዘበኛ ምንም የወሰደው እርምጃ የለም፡፡ የመሣሪያ ድምጽ እንኳ በእለቱ ኮሽ አላለም፡፡ መውረዳቸውን አምኖ ተቀብሏል፡፡ ይህ ባይሆን እንኳ መፈንቅለ መንግስት አድራጊው ወገን፣ ክቡር ዘበኛ ካንገራገረ ማጥቃት የሚችል ሠራዊት በቤተ-መንግስቱ በድብቅ ተዘጋጅቶ ነበር፡፡
ንጉሡ ከቤተ-መንግስታቸው በደርጉ ሃይሎች ተከበው፣ በተዘጋጀችለቸው ቮልስዋገን መኪና ውስጥ ገብተው ወደ 4ኛ ክ/ጦር ሲወሰዱ፣ ብዙ ህዝብ በመንገድ ላይ ወጥቶ ይመለከት ነበር፡፡ በእድሜ ጠና ባሉት ሰዎች ላይ የማዘን ስሜት ይስተዋል ነበር፡፡ ወጣቱ ደግሞ “ሌባው! ሌባው! ሌባው!” የሚል ስድብ በፉጨትና በጩኸት እያጀበ ይሰነዝራል፡፡ ወጣቱ በጣም ይሳደብ ነበር፡፡ በተለይ ቮልስዋገኗ መስቀል አደባባይ አካባቢ ስትደርስ የነበረው ፉጨትና ጭብጨባ ልዩ ነበር፡፡
ደርጉ ዋና ዋና የሚባሉትን የመንግስት ስልጣኖች በሚገባ በቁጥጥሩ ስር ከዋለ በኋላ ስለነበር እሣቸውን ከስልጣን ያወረደው መንገዱ ሁሉ የቀና ሆኖለታል፡፡ ጃንሆይም ይህን ስለሚያውቁ በአጋዦቻቸው አማካይነት ሌላ እርምጃ ለመውሰድ አላንገራገሩም፡፡ ዝም ነው ያሉት፡፡ ወደ ቮልስዋገኗ እንዲገቡ ሲጠየቁ አላንገራገሩም፡፡ ለምን በቮልስዋገን ተወሰዱ? ተብሎ ሲታሰብ ደርግ እሣቸው መሆናቸው ሳይታወቅ እንዲሄዱ የተጠቀመበት ቴክኒክ ነበር፡፡ ተራ ሰው እንዲመስሉና ግርግር እንዳይፈጠር ነው፡፡ ነገር ግን ሰው አውቆታል፡፡ በኋላ ዳርና ዳር መትረየስ የጫኑ ጂፖች አጅበዋቸው ሲሄዱ ሰው ከፉጨትና ጭብጨባ፣ ስድብ በቀር አንዲት ጠጠር እንኳ አንስቶ አልወረወረም፡፡ በዚያ ላይ ደህንነቱ በሰው መሃል ተሰግስጓል፡፡ ወታደሩም አንዳንዱ ሲቪል ለብሷል፡፡ ጃንሆይ ከስልጣን ከወረዱ በኋላ በእውነቱ ምስኪናዊ ህይወት ነው ያሳለፉት፡፡ ማንም ጠያቂ የላቸውም ነበር፡፡ የሚቀርባቸውም ሰው አልነበረም፡፡ ብቻቸውን አንድ ቤት ውስጥ ነበር የሚኖሩት፡፡ ንጉሱ ዘወትር ፊታቸውን ወደ ቤተክርስቲያኑ አዙረው ፀሎት ሲፀልዩ ስታይ በጣም ያሳዝኑ ነበር፡፡ ማንም አያናግራቸውም፤ አይጠጋቸውም ነበር፡፡ አንዲት ምግብ የምታበስል ልጅ አለች፤ እሷም ብትሆን በተወሰነ ሰዓት መጥታ ስራዋን ሰርታ ነው የምትሄደው፡፡ አርብ እና አሮብን ጠንቅቀው ይፆሙ ነበር፡፡ ልጅቱም ዘግይታ ነው ምግብ የምትሰራላቸው፡፡ ልጅቱ ልብሱን አዘጋጅታላቸው ትሄዳለች፡፡ ራሳቸው ይለብሳሉ፡፡ በዚህ መልኩ በዚያው በቤተ መንግስቱ በቀን እስረኝነት ከሰው ተገልለው ሲኖሩ ከቆዩ በኋላ ህይወታቸው ማለፉ ተነገረ…
(“ህይወት በመንግስቱ ቤተ-መንግስት” የተሰኙ ተከታታይ መፅሃፎች ደራሲና የቀድሞ ልዩ ሃይል አባል ወ/ር እሸቱ ወንድሙ ለአዲስ አድማስ ከፍተኛ ሪፖርተር አለማየሁ አንበሴ መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም አስመልክቶ ከሰጡት ቃለ ምልልስ የተወሰደ፡፡)