Administrator

Administrator

በመገበያያ ገንዘቧ ዶላር ላይ የታዋቂ መሪዎቿን ምስል የምታወጣው አሜሪካ፣ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ የሴት ምስል ለማውጣት መወሰኗን ዘ ቴሌግራፍ ከትናንት በስቲያ ዘገበ፡፡ የአሜሪካ የገንዘብ ተቋም እንዳስታወቀው፣ በአገሪቱ የ10 ዶላር ኖት ላይ የአንዲትን ታላቅ አሜሪካዊት ሴት ምስል ለማውጣት ውሳኔ ላይ የተደረሰ ቢሆንም፣ በዶላሩ ላይ የምትወጣዋ ሴት ማን ናት የሚለው ግን ገና አልታወቀም፡፡
ከዚህ በፊት በአሜሪካ የ10 ዶላር ኖት ላይ የነበረው ምስል የአሌክሳንደር ሃሚልተን እንደነበር ያስታወሰው ዘገባው፣ የአገሪቱ የትሬዠሪ ጸሃፊ ጃክ ሊው በጉዳዩ ዙሪያ ከህዝብ ጋር ከመከሩና በድረገጽ አማካይነት የሚሰጠውን ጥቆማ ከገመገሙ በኋላ በኖቱ ላይ ምስሏ የሚወጣላትን ሴት እንደሚመርጡ አስታውቋል፡፡
አዲሱ ዶላር ከአምስት አመታት በኋላ በሚከናወነውና የአገሪቱ ሴቶች የመምረጥ መብታቸውን የተጎናጸፉበትን 100ኛ አመት ለመዘከር በሚዘጋጅ ስነስርዓት ላይ ይፋ እንደሚሆንም ይጠበቃል፡፡
በአገሪቱ የመገበያያ ገንዘብ ላይ ምስሏ የሚወጣላትን ሴት በተመለከተ ዘገባው ባስቀመጠው ግምት፣ ሴቶችን ከባርነት በማውጣት ታሪክ የሰራችው ሃሬት ቱብማን፣ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ፍራንክሊን ሩዝቬልት ባለቤት ኤሊኖር ሩዝቬልት፣ የጥቁሮች መብት ተሟጋቿ ሮዛ ፓርክስ፣ ቼሮኬን ለ10 አመታት ያህል ያስተዳደሩት ዊልማ ማኒከርን ጠቅሷል፡፡

አምና የተመዘገበው ዝናብ በ30 አመታት ዝቅተኛው ነው
   ሰሜን ኮርያ ባለፉት መቶ አመታት ገጥሟት በማያውቅና የከፋ የምግብ እጥረቷን በከፍተኛ ሁኔታ በማማባስ ወደ ቀውስ ያስገባታል ተብሎ በተሰጋለት ድርቅ መመታቷን ስካይ ኒውስ ዘገበ፡፡ የአገሪቱን የዜና ወኪል ኬሲኤንኤን ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፤ ህዋንጌና ፓዮንጋን የተባሉትን ዋነኞቹ የሰሜን ኮርያ ሩዝ አብቃይ ግዛቶች ጨምሮ በመላ አገሪቱ የሚገኙ የሩዝ ሰብሎች በዝናብ እጥረት ሳቢያ በቡቃያው አርረዋል፡፡ አገሪቱ በክፍለ ዘመኑ የከፋ ባለችው ድርቅ መመታቷንና በግብርና እንቅስቃሴዋ ላይ ከፍተኛ ጥፋት መድረሱን ያስታወቀች ሲሆን፣ ድርቁ ተመድ ከአምስት አመት ዕድሜ በታች ከሚገኙ ሶስት ህጻናት አንዱ በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ሳቢያ የመቀጨጭ ችግር ተጠቂ እንደሆነ ባረጋገጠባት ሰሜን ኮርያ ላይ የከፋ ጥፋት ያስከትላል ተብሎ እንደሚሰጋ ጠቁሟል፡፡  
ባለፉት 30 አመታት የአገሪቱ ታሪክ ዝቅተኛ የተባለው የዝናብ መጠን ባለፈው አመት መመዝገቡ፣ ለድርቁ መከሰት በምክንያትነት የተጠቀሰ ሲሆን፣ ሩዝ በቂ ውሃ ካላገኘ በአግባቡ ማደግ አለመቻሉና የዝናብ እጥረቱ መቀጠሉ አደጋውን የከፋ እንደሚያደርገው ይጠበቃል ተብሏል፡፡ የአገሪቱ አርሶ አደሮች የውሃ ፓምፖችን በመጠቀም ሰብሎቻቸውን ውሃ እንዲያጠጡና ከጥፋት እንዲታደጉ የሚያበረታታ አገር አቀፍ ዘመቻ መጀመሩም ታውቋል፡፡

  በድረ-ገጾች ላይ የሚጫነው መረጃ መጠን ከሶስት አመታት በፊት ከነበረው በእጥፍ ያህል መጨመሩን ተከትሎ፣ የድረ-ገጾች ፍጥነት በአለማቀፍ ደረጃ መቀነሱንና ድረ-ገጾችን ለመክፈት የሚፈጀው አማካይ ጊዜ መጨመሩን ሲኤን ኤን ዘገበ፡፡
በአሁኑ ወቅት አንድ ድረ-ገጽ ሳይት የሚይዘው አማካይ የመረጃ መጠን 2.1 ሜጋ ባይት ደርሷል ያለው ኤችቲቲፒ፣ ለድረ-ገጾች ፍጥነት መቀነስ በምክንያትነት ከተጠቀሱት መካከል ቪዲዮዎች፣ ስዕሎችና ድህንነትን ለማስጠበቅ በሚል የሚጫኑ ሌሎች መረጃዎች መብዛታቸውና የመረጃ ዝውውሮች መጨናነቃቸው ይገኙበታል፡፡
ስማርት ፎኖችና ታብሌቶች በስፋት ለኢንተርኔት አገልግሎት መዋላቸውም ለድረ-ገጾች ፍጥነት መቀነስ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ዘገባው ጠቁሞ፣ ምንም እንኳን ፍጥነቱ የቀነሰው በሰከንዶች እድሜ ቢሆንም፣ እያንዳንዷ ማይክሮ ሰከንድ ትልቅ ዋጋ በያዘችበት በዚህ የመረጃና የፈጣን የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዘመን ጉዳዩ አሳሳቢ ነው የሚል አስተያየት መሰጠቱን አስታውቋል፡፡
የኢንተርኔት ተጠቃሚነት በአለማቀፍ ደረጃ እያደገ መምጣቱን ተከትሎ የኔትወርክ መጨናነቅ መፈጠሩ፣ የብራውዘሮች አይነትና አቅም መለያየትም ለችግሩ መከሰት በምክንያትነት ተጠቅሰዋል፡፡

- በቀን ከ42 ሺህ በላይ ሰዎች ይሰደዳሉ
- ባለፈው አመት 60 ሚ. ያህል ሰዎች ተሰደዋል፤ ግማሽ ያህሉ ህጻናት ናቸው
- በግጭት ሳቢያ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር በ350 በመቶ አድጓል
- አይስላንድ የአለማችን ሰላማዊ አገር ናት

       ባለፈው የፈረንጆች አመት 2014 ብቻ በዓለማችን የተለያዩ አገራት ለተደረጉ ጦርነቶችና የእርስ በርስ ግጭቶች ከ14 ትሪሊዮን ዶላር በላይ ወጪ መደረጉን ዘ ቴሌግራፍ ዘገበ፡፡
ኢንስቲትዩት ፎር ኢኮኖሚክስ ኤንድ ፒስ የተባለው አለማቀፍ ተቋም ያወጣውን ሪፖርት ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ ባለፈው አመት ለጦርነትና ለእርስ በርስ ግጭት የወጣው አጠቃላይ ወጪ፣ ከዓለማችን አጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት 13 በመቶ እንደሚሆንና የእንግሊዝ፣ የፈረንሳይ፣ የጀርመን፣ የካናዳ፣ የስፔንና የብራዚል ኢኮኖሚ በአንድ ላይ ተደምሮ አይደርስበትም፡፡
አለማችን ግጭትን በ10 በመቶ መቀነስ ከቻለች ለጦርነትና ለእርስ በርስ ግጭት ከሚወጣው ገንዘብ 1.43 ትሪሊዮን  ዶላር ማዳን ትችላለች ብለዋል የኢንስቲትዩቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ ስቲቭ ኪሌላ፡፡ ሰሞኑን ይፋ የተደረገው አለማቀፍ የሰላም ሁኔታ አመልካች ሪፖርት በበኩሉ፣ በ2015 የግጭት መናኸሪያ በመሆንና በአደገኛ ሁኔታ ውስጥ በመገኘት ረገድ የአለማችን ግንባር ቀደም አገር ሶሪያ መሆኗንና ኢራቅና አፍጋኒስታን እንደሚከተሏት አስታውቋል፡፡
በአመቱ የሰላም ሁኔታዋ በከፍተኛ ሁኔታ የቀነሰባት አገር ሊቢያ ናት ያለው ሪፖርቱ፣ የእርስበርስ ግጭት ከተነሳበት ጊዜ አንስቶ 6ሺ ያህል ዜጎች የሞቱባትንና 1 ሚሊዮን ህዝብ የተፈናቀለባትን ዩክሬን በሁለተኛነት አስቀምጧታል፡፡ በአለማችን በግጭቶች ሳቢያ ለህልፈተ ህይወት የሚዳረጉ ሰዎች ቁጥር ባለፉት አራት አመታት ከ350 በመቶ በላይ አድጓል ያለው ሪፖርቱ፣  በ2010 ብቻ 49 ሺህ ሰዎች መሞታቸውንና ይህ ቁጥር በ2014 ወደ 180 ሺህ ከፍ ማለቱን ጠቁሟል፡፡ ይህም ሊሆን የቻለው በ2013 ከሽብርተኝነት ጋር በተያያዘ ለሞት የሚዳረጉ ሰዎች ቁጥር 61 በመቶ በማደጉ ነው ያለው ሪፖርቱ፤ በአመቱ ከሽብርተኝነት ጋር በተያያዘ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 18ሺህ እንደነበርና አብዛኞቹ ሟቾችም በአፍጋኒስታን፣ ኢራቅ፣ ናይጀሪያ፣ ፓኪስታንና ሶሪያ የተገደሉ እንደሆኑ አስታውቋል፡፡
በአንጻሩ ደግሞ ሰላማዊ ሆና በመዝለቅ ቀዳሚዋ አህጉር ናት በተባለችው አውሮፓ የሚገኙት አይስላንድ እና ዴንማርክ የዓለማችን ሰላማዊ አገራት ተብለዋል በሪፖርቱ፡፡ ቢቢሲ በበኩሉ፤ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን መረጃ ጠቅሶ ከትናንት በስቲያ እንደዘገበው፣ በጦርነትና በእርስ በእርስ ግጭት  ሳቢያ የሚሰደዱ ሰዎች ቁጥር ታይቶ በማይታወቅበት ደረጃ ከፍ በማለት በ2014 60 ሚሊዮን ያህል ደርሷል፡፡ በየዕለቱ አገራቸውን ጥለው የሚሰደዱ ዜጎች ቁጥርም 42 ሺህ 500 ደርሷል፡፡
የተመድ የስደተኞች ኮሚሽን ያወጣው ሪፖርት እንደሚለው፣ የስደተኞች ቁጥር በ2013 ከነበረበት በ8.3 ሚሊዮን ያደገ ሲሆን ለስደተተኞች ቁጥር መጨመር ዋነኛ ምክንያት የተደረገውም ተባብሶ የቀጠለው የሶርያ ግጭት እንደሆነ ተረጋግጧል፡፡ ባለፉት አምስት አመታት 15 ያህል ግጭቶች መከሰታቸውን ወይም እንደገና ማገርሸታቸውን የጠቆመው ሪፖርቱ፣ ከእነዚህ መካከልም ስምንቱ በአፍሪካ፣ ሶስቱ ደግሞ በመካከለኛው ምስራቅ አገራት የተከሰቱ እንደሆኑ በመግለጽ፣ በዚህም እስከ 2014 መጨረሻ 59.5 ሚሊዮን ሰዎች ከመኖሪያቸው ተፈናቅለው ለስደት መዳረጋቸውንና ከእነዚህም ግማሽ ያህሉ ህጸናት መሆናቸውን አስታውቋል፡፡
ስደተኞቹ የአንድ ሃገር ህዝብ ቢሆኑ፣ አገሪቷ በአለማችን በህዝብ ቁጥር ብዛት 24ኛ ደረጃ ልትይዝ እንደምትችል አስታውቆ፤ 19.5 ሚሊዮን የሚሆኑ የተለያዩ አገራት ዜጎችም በስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች አስከፊ ኑሮ እንደሚገፉም አክሎ ገልጧል፡፡
በርካታ ዜጎች ከሚሰደዱባቸው የዓለማችን አገራት መካከል ቀዳሚዋ 4 ሚሊዮን ሰዎች የተሰደዱባት ሶርያ ስትሆን. አፍጋኒስታን በ3 ሚሊዮን፣ ሶማሊያ በሁለት ሚሊዮን ይከተላሉ፡፡ በሜዲትራንያን ባህር በኩል ወደተለያዩ የአውሮፓ አገራት የገቡ 1.8 ሚሊዮን ስደተኞች ጥገኝነት ለማግኘት ያቀረቡትን ጥያቄ ምላሽ እየተጠባበቁ እንደሚገኙና፣ ከእነዚህም መካከል ብዙዎቹ በጀርመንና በስዊድን እንደሚገኙም ሪፖርቱ ጠቁሟል፡

Saturday, 20 June 2015 11:11

የፀሐፍት ጥግ

ስለትወና)
ትወና፤ የሌሎችን ሰብዕና የመውሰድና የራስህን ጥቂት ተመክሮ የማከል ጉዳይ ነው።
ዣን ፖል ሳርተር
ተዋናይ ለመሆን ህንፃ መሆን አለብህ፡፡
ፖል ኒውማን
ትወና ስሜታዊነት አይደለም፤ ስሜትን በተሟላ መንገድ መግለፅ መቻል እንጂ፡፡
ቶማስ ሬይድ
ሥነ ጥበብ እጃችን፣ ጭንቅላታችንና ልባችን እንደ አንድ ሆነው የሚጣመሩበት ነው፡፡
ጆን ሩስኪን
ትወና ደስ የሚል ስቃይ ነው፡፡
ዣን ፖል ሳርተር
ትወና ከሞላ ጎደል ከጨዋታ በላይ አይደለም። ሃሳቡም ህይወትን ሰዋዊ ማድረግ ነው፡፡
ጄፍ ጎድልብሊም
የትወና ጥበብ ሰዎች እንዳያስሉ ማድረግንም ይጨምራል፡፡
ራልፍ ሪቻርድሰን
ትወና እወዳለሁ፤ ምክንያቱም ህልም እውን የሚሆንበት፣ ቅዠት ህይወት የሚዘራበትና የሚቻለው ነገር ሁሉ ገደብ የሌለበት በመሆኑ ነው፡፡
ጄሲካ አልባ
ራሴን ለፍቅረኛ እንደምሰጠው ነው ለገፀባህርያቶቼ የምሰጠው፡፡
ቫኔሳ ሬድግሬቭ
ተዋናይ ህይወትን መተርጎም አለበት፤ ያንን ለማድረግ ደግሞ ህይወት የምትሰጠውን ተመክሮ ሁሉ በፀጋ ለመቀበል ፈቃደኛ መሆን ይኖርበታል፡፡
ማርሎን ብራንዶ
ተዋናዮች ከህይወት በላይ መግዘፍ አለባቸው። በዕለት ተዕለት ህይወት ከብዙ ተራና እዚህ ግቡ የማይባሉ ሰዎች ጋር ትገናኛላችሁ፡፡ በመድረክም ላይ ከእነሱ ጋር የምትጋፉበት ምክንያት አይታየኝም፡፡
ኒኖን ዲ ሌንክሎስ
የታላቅ ተዋናይ መሰረታዊ ጉዳይ በትወና ውስጥ ራሱን መውደዱ ነው፡፡
ቻርሊ ቻፕሊን

ከዕለታት አንድ ቀን የዱር አራዊት ንጉሥ “አያ አምበሶ ታሟል እና ሄደን እንጠይቀው” ብለው የዱር አራዊት እመት ጦጢትን ይነግሯታል፡፡
እመት ጦጢትም፤
“እስቲ እናንተ ቀደም ብላችሁ ሂዱ፡፡ እኔ፤ አያ አምበሶ የሚመገበውን ምግብ ለማዘጋጀት የሚጠቅመውን ራሺን ልሸማምት” አለቻቸው፡፡
የዱር አራዊቱ ወደ አያ አምበሶ ሄዱ፡፡ ጦጢት ወደ ኋላ ቀርታ ዝም ብላ የሚሆነውን ታዳምጥ ጀመር፡፡
የዱር አራዊቱ አያ አምበሶ ጋ ደርሰው፣
“አያ አምበሶ ተሻለዎ ወይ?” ይላሉ፡፡
አያ አምበሶም፤
“ኧረ እየባሰብኝ ነው የመጣው፡፡ እርጅናም በጣም እየተጫነኝ ነው፡፡ በዛ ላይ የሚያስታምመኝ አንድም እንስሳ አጠገቤ የለም፡፡ ደግም ምግብ እንደልቤ አልበላም” አለ፡፡
ሁሉም ደንግጠው “ምን ብናደርግ ይሻላል?” ተባባሉና “ምን ዓይነት ምግብ ያምርዎታል?” ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡
አያ አምበሶ፤ “በየቀኑ የሚያምረኝ ሥጋ ዓይነቱ ይለያያል
አንድ ቀን የድኩላ ያምረኛል፡፡
ሌላ ቀን የጎሽ ያምረኛል፡፡
ደሞ ሌላ ቀን የቀጭኔ ሥጋ እንደጉድ ያምረኛል፡፡  
ደሞ አንዳንድ ሰሞን የነብር ሥጋ ያስፈልገኛል፡፡ ይሄን ካላገኘሁ የምድን አልመሰለኝም” አለ፡፡ የዱር አራዊቱ ደግመው ተሰበሰቡና፤
“ጎበዝ ምን እናድርግ?” ተባባሉ፡፡
ሁሉም፤ “ጦጣ መላ አታጣም፡፡ ሄደን እንጠይቃት” አሉ፡፡
ከአያ አምበሶ ጊዜ ቀጠሮ ወሰዱ፡፡ ሀሳባቸውን በደምብ አብስለው እስኪመጡ ተራ ገብተው ሊያስታምሙ ተስማሙ፡፡
ጦጢት እንዳደፈጠች ዛፉዋ ላይ ሆና ትጠብቃለች፡፡ ወደ እሷው ዘንድ ሄዱና፤
“እመት ጦጢት አያ አምበሶ ግራ - የሚያጋባ ጥያቄ አቀረቡልን፡፡ ይኸውም ከየአንዳንዱ እንስሳ በዓይነት በዓይነቱ ምግብ ያምረኛል አሉ፡፡ ይህን እናድርግ ካልን በቀን በቀን አንድ አንድ እንስሳ ይታረድ እንደማለት ነው?” አሏት
እመት ጦጢትም፤
“ይሄ መቼም ዐይናችን እያየ እያንዳንዳችን በየተራ እንሙት ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የሚሻለው አንድ ሆነን፣ በአንድ ድምፅ፣ ፈትልና ቀስም ሆነን፤ ይሄ የማይሆን ምኞት ነው፡፡ የታመመ፣ ወይም ጊዜው የደረሰ እንስሳ ካገኘን እናቀርብልዎታለን፡፡ አለበለዚያ ግን ምንም የምንረዳዎት ነገር የለም፤ እንበል፡፡ ግን አንድ ልብ ይኑረን!” አለች፡፡ የዱር አራዊቱ በጦጣ ሀሳብ ተስማሙ፡፡
እንደተባባሉት ዋና ተናጋሪ መርጠው ለአያ አምበሶ የወሰኑትን ውሳኔ ገለጡ፡፡
አያ አምበሶ፤ በየቀኑ ምን ምን የምግብ ዓይነት መርጠው ይሰጡኝ ይሆን? እያለ በጉጉት ሲጠብቅ የወሰኑትን ሲሰማ፤ ባለበት በድን ሆኖ ቀረ፡፡ በዚያው ህይወቱ አለፈ፡፡
*    *     *
አለቃ ምንዝሩን የሚያጠቃበት፣ ሥርዓቱን ለግል ጥቅሙ ለማዋል የሚሯሯጥበት፣ አልፎ ተርፎም የደጋፊዎቹን ህልውና ሳይቀር የሚያናጋበት ሁኔታ ከፈጠረ ጤና አይኖርም፡፡ ሥርወ - መንግሥቱም የረጋ አይሆንም፡፡ ዛሬ በሚሊዮንና በቢሊዮን ብር የሚቆጠር ፕሮጀክት፣ ህንፃ፣ ፋብሪካ ወዘተ የሚወራበት አገር ነው ያለን፡፡ የህዝቡ ኑሮ ግን ፈቀቅ አላለም፡፡ ምናልባት የህንድ ዓይነት ጥቂቶች ከዝሆን ጥርስ የተሰራ ፎቅ ማማ ላይ ያሉ የናጠጡ ሀብታሞች ከአናት የተቀመጡባት፣ በአንፃሩ ህልቆ መሳፍርት ድሆች የጉስቁልና ህይወት የሚመሩባት አገር እንዳትሆን መስጋታችን አልቀረም፡፡ ማባሪያ የሌለው ምዝበራና ሙስና ጓዳ - ደጁን ሞልቶት፣ በህጋዊ መንገድ ያልተገኘ ብልፅግና ሥር የሰደደበት ሁኔታ እያለ ዕድገት ማምጣት ከባድ ነው፡፡ ሀንቲግተን ዘመናዊነትና ሙስና በሚለው ሀተታው፤ “ሙስና የባለሥልጣናት ጠባይ ሲሆን፤ ከተለመደው ህግ በማፈንገጥ ሥልጣንን ለግል ጥቅም ማዋል ነው … በእርግጥም ሙስና ስኬታማ ፖለቲካዊ ተቋም አለመኖር ምልክት ነው!” ብሏል፡፡
የሲቪል ተቋማት አለመኖር (Civic Society) የዲሞክራሲ መዳከም ምልክት መሆኑን የፖለቲካ ሊቃውንት ይናገራሉ፡፡ ይህን መሰል ተቋማት ብዙ ያስፈልገናል። ለውጥ በመጣ ቁጥር አዳዲስ ሹማምንትን ማየት የተለመደ ነው፡፡ የምናያቸው ሹማምንት ፊት ካየናቸው የተሻሉ እንዲሆኑ እንመኛለን/እንናፍቃለን፡፡ ያንን ካላገኘን “ሣር የምትበላው በቅሎ ሄዳ ልጓም የምትበላው መጣች” የሚለው ተረት ዕውን እንዳይሆን ያሰጋል!! ከዚህ ይሰውረን!

Saturday, 20 June 2015 10:13

‹‹እውነት!?››

‹‹እውነት!?››
አንድ የገዢው ፓርቲ አባል ‹‹ምርጫ በማሸነፉ›› ደስ ተሰኝቶ ሚስቱ ጋ ደወለ አሉ፡፡
‹‹ሄሎ ማሬ!›› ‹አቤት ውዴ! ‹‹ምርጫውን እኮ አሸነፍኩኝ!›› አለ ደስታ ባመጣው ፈገግታ ታጅቦ፡፡ ‹‹እውነት!?›› እሷም ደስታ የሚያደርጋትን አሳጥቷት ባለማመን ጠየቀች፡፡ ጥያቄዋ ግን ባልን አስቆጣው፤ ‹‹እ!? ምን አልሽ አንቺ!›› ‹‹እውነት አሸነፍክልኝ ወይ?› ነው ያልኩት፡፡›› አሁንም ደስታዋ አላባራም፡፡
‹‹አንቺ ሴት ከፀረ ሰላም ኃይሎች ጋር መዋል ጀመርሽ ማለት ነው!?›› ንዴት የሚያደርገውን እያሳጣው፡፡
‹‹ምን እያልክ ነው ውዴ?›› ግራ ቢገባት ጠየቀች፡፡
‹‹እዚህ ጋ ‹እውነት› የሚለውን ቃል ምን አመጣው!? ‹አሸነፍኩ› ማለት፤ ያው አሸነፍኩ ነው! አይገባሽም እንዴ!››
(ከበኃይሉ ገ/እግዚአብሄር ፌስቡክ)

     ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ በወጣው የአዲስ አድማስ ዕትም ላይ በብዙዎች የተዘነጋውንና ከህወሓት 10 መስራቾች አንዱ የነበረውን የታጋይ አብጠው ታከለን ታሪክ ጋዜጣችሁ ለህዝብ ለማስተዋወቅ ያደረገውን ጥረት እናደንቃለን፤ምስጋናችንንም  እናቀርባለን፡፡ምንም እንኳን የአባታችን የትግል ታሪክ ተገቢውን ዕውቅና እንዲያገኝ ለሚመለከታቸው የፓርቲና የመንግስት ባለሥልጣናት ለማስታወስ  ከጎንደር አዲስ አበባ በመጣን ጊዜ የሚያነጋግረን አጥተን ብንከፋም፣ ጉዳያችንን ለማስረዳት የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ (ነፍሳቸውን ይማርና) ባለቤት ወ/ሮ አዜብ መስፍን ቢሮ በሄድንበት ወቅት በታላቅ ክብር፣ ከመቀመጫቸው
ተነስተው በመቀበል  ስላስተናገዱን ልናመሰግናቸው እንወዳለን፡፡ ይሄም ብቻ አይደለም።  ወይዘሮ
አዜብ “ጉዳያችሁ ጉዳዬ ነው” ብለው ታጋይ አብጠውን በተመለከተ የሚቻለው ሁሉ እንዲደረግ የበኩሌን ያለሰለሰ ጥረት አደርጋለሁ በማለት በእጅጉ አበረታተውናልና በድጋሚ ከልብ እናመሰግናለን፡፡ አባታችን አቶ አብጠው ታከለ፤ ከህውሓት የትግል ጥንስስ ጀምሮ ህይወቱ እስካለፈችበት 2000 ዓ.ም ድረስ ከኢህአዴግ የትግል መስመር ያልወጣና በያዘው አቋም የፀና እንደነበርም በዚህ አጋጣሚ እንዲታወቅልን እንፈልጋለን፡፡
ቤተሰቦቻቸው 

ማኅበረ ቅዱሳንን በመወንጀል ‹‹ወጣቶቹን ሰብስባችሁ እሰሩልን›› ያሉ አስተዳዳሪዎች የፖሊስ እና
የደኅንነት አካላትን በተባባሪነት ወቀሱ‹‹ማኅበረ ቅዱሳንን እንደተቋም መወንጀል አትችሉም፤ ፖሊስ የእናንተ ብቻ አይደለም፤ መጀመሪያ ራሳችኹን ፈትሹ›› /ዶ/ር ሺፈራው ተክለ ማርያም
     በሙስና መንሰራፋት፣ በመልካም አስተዳደር እና በፍትሕ ዕጦት ሳቢያ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እየተደረገ ካለው የአገልጋዮች እና የምእመናን መነሣሣት ጋር በተያያዘ የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር የቤተ ክርስቲያኒቱን አካላት ማነጋገር ጀመረ፡፡ ብልሹ የሰው ኃይል አስተዳደር እና የፋይናንስ አሠራር በተከታዩ ዘንድ የሚፈጥረው የተከማቸ ቅሬታ፣ የሃይማኖት ተቋማቱ እምነት እንዲያጡ ምክንያት እየኾነ እንዳለ በሥልጠና ሰነዶቹ የሚገልጸው ሚኒስቴሩ፣ በቅርቡም የወሳኝነትና የተሳትፎ ድርሻ ያላቸው የተለያዩ የቤተ ክርስቲያኒቱ የአስተዳደር እና የአገልግሎት አካላት የሚሳተፉበት ተከታታይ ውይይት እንደሚያካሒድ ተጠቁሟል፡፡በሚኒስቴሩ ጥያቄ፣ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የተመረጡ የአድባራት አስተዳዳሪዎች ከትላንት በስቲያ ከቀትር በኋላ ከሚኒስትሩ ዶ/ር ሺፈራው ተክለ ማርያም እና ከሚኒስትር ዴኤታው አቶ ሙሉጌታ ውለታው ጋር የውይይቱ ቅድመ ዝግጅት ነው የተባለ ምክክር አድርገዋል፡፡በዋና ሥራ አስኪያጁ ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ የተመሩ የኻያ አምስት አድባራት አስተዳዳሪዎች በተካፈሉበት በዚኹ ምክክር፣ ‹‹በማኅበራት ሰላማችንን እያጣን ነው፤ ሰንበቴ ሲከበን እናንተም የላችኹም፤ መንግሥትም የለም፤ አልደገፋችኹንም፤ አልረዳችኹንም›› የሚሉ ክሦች እና አቤቱታዎች ከአንዳንድ አለቆች መቅረቡ ተጠቅሷል፡፡ካለፈው ሚያዝያ ወር መጨረሻ ጀምሮ የሀገረ ስብከቱ ሰንበት ት/ቤቶች ፥ ሙስና እንዲወገድ፣ መልካም አስተዳደርና ፍትሕ እንዲሰፍን፣ እምነትና ሥርዐት እንዲጠበቅ በሰልፎችና በስብሰባዎች
የሚያካሒዱት እንቅስቃሴም ‹‹ማኅበረ ቅዱሳን ልብሱን ለውጦ የመጣበት ነው›› ብለዋል - አስተዳዳሪዎቹ፡፡
የሰንበት ት/ቤት አባላቱ የመለያ ልብሶቻቸውን (ዩኒፎርሞቻቸውን) ለብሰው በመውጣት በሚያደርጓቸው ሰልፎችና ስብሰባዎች መንግሥት የጸጥታ ርምጃ ሳይወስድ በዝምታ መመልከቱን የተናገሩት አስተዳዳሪዎቹ፣ የፖሊስ እና የደኅንነት አካላትን በተባባሪነት በመውቀስ፣ ‹‹ወጣቶቹን እሰሩልን›› ብለው ሲጠይቁ ተሰምተዋል፡፡የቤተ ክርስቲያንን ሀብት ለግላቸው በማካበት ከገቢያቸው በላይ የሚኖሩ አለቆች በሥነ ምግባርና በፀረ ሙስና ኮሚሽን እየተመረመሩ በሀገሪቱ ሕግ እንዲጠየቁ የሰንበት ት/ቤቶቹ የሚጠይቁ ሲኾን
ዋና ሥራ አስኪያጁ እና አንዳንድ አለቆች በአንፃሩ፣ ‹‹ዶልፊን እና ሃይገር የሚያቆሙ ናቸው፤ ቢዝነስ አድርገውታል” በማለት ይከሷቸዋል፡፡በምክክሩ ወቅት ብሶት ነው የሚያስጮኸኝ በማለት በከፍተኛ ድምፅ የተናገሩ አንድ አስተዳዳሪ፣ “ማኅበረ ቅዱሳን አባላቱን የሰንበት ት/ቤት ዩኒፎርም አስለብሶ መውጣት ጀምሯል፤ ሕንፃውን ከየት አምጥቶ ነው ያቆመው?” ሲሉ በሰንበት ት/ቤቶቹ መነሣሣት ማኅበሩን ተጠያቂ አድርገዋል፡፡ “ወጣቱን ዩኒፎርም እያስለበሱ ይልካሉ” ያሉ የሌላ ደብር አስተዳዳሪም፤ “እንዴት አድርገን
መከላከል እንዳለብን አሠልጥኑን እንጂ ስለሰላም ምን ያደርግልናል” በማለት የሚኒስቴሩን
ሓላፊዎች አስደምመዋል ይላሉ የስብሰባው ተሳታፊዎች፡፡ፖሊስ እና የጸጥታ አካላት የሕዝብን ሰላም እና ደኅንነት የሚጠብቁ መኾናቸውን የተናገሩት ሚኒስትሩ ዶ/ር ሺፈራው ተክለ ማርያም፣ ‹‹ፖሊስ ለእናንተ ብቻ ነው እንዴ?›› ሲሉ አለቆቹን ጠይቀዋቸዋል፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን በሲኖዶስ ዕውቅና የተሰጠው ሕጋዊ ማኅበር መኾኑን ሚኒስትሩ ጠቅሰው፣ ችግር ያለባቸው ግለሰቦች ይኖራሉ እንጂ ማኅበር እያችሁ በጅምላ መጥራት የለባችኹም፤ ተቋሙን በጅምላ መፈረጅ ወንጀል ነው፤›› ብለዋል፡፡ ሀገረ ስብከቱን ጨምሮ አስተዳዳሪዎቹ በሚመሯቸው አድባራት መልካም አስተዳደርን በማስፈን ለምእመናንና ለሰንበት ት/ቤቶቹ ወጣቶች ምሳሌ መኾን እንደሚገባቸው የተናገሩት ሚኒስትሩ፣ ‹‹ሰው እሰሩ ያላችኹት ሌላ ችግር ነው የሚፈጥረው፤ የምናስረው ሰው የለም፤ መጀመሪያ ራሳችኹን ፈትሹ›› በሚል ለአለቆቹ የእሰሩልን ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ በሚኒስቴሩ ዕቅድ መሠረት ይካሔዳል የተባለውና በቤተ ክርስቲያኒቱ ከሚታየው የአገልጋዮችና የምእመናን መነሣሣት ጋር የተገጣጠመው ይኸው የቅድመ ውይይት ምክክር፣ በቤተ ክርስቲያኒቱ የአስተዳደር መዋቅር የወሳኝነት እና የተሳትፎ ድርሻ ያላቸውን የማኅበረ ካህናትን፣ የማኅበረ ምእመናንና የሰንበት ት/ቤቶች ተወካዮችን
ሊያካትት እንደሚገባው አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ፡፡በዘመናዊ አሠራር፣ በመልካም አስተዳደር እና በሰላም ጉዳዮች ላይ የሚያተኩረው ዋናው ውይይት፤ በሚቀጥሉት ኹለት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ እንደሚጀመር የሚኒስቴሩ ምንጮች አስታውቀዋል፡፡ የውይይቱን አቅጣጫ ለማመቻቸት በሚል ከትላንት በስቲያ በሀገረ ስብከቱ ሓላፊዎች ከተመሩት የአድባራት አለቆች ጋር ከተካሔደው ምክክር ፍጻሜ በኋላ ‹‹ዘመናዊ አሠራር ዴሞክራሲዊነት እና ብዝኃነት›› በሚል ርእስ በሚኒስቴሩ የተዘጋጀ የመወያያ ሰነድ እንደተሰጣቸውም ንጮቹ ገልጸዋል፡፡