Administrator

Administrator

 አንዳንዴ ፈረንጆችን ከእኛ የሚለያቸው ስለ ሰማይ ቤትም ለመቀለድ መቻላቸው ነው፡፡ የሚከተለው ተረት አንድ ምሣሌ ነው፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ጠበቃ ይሞትና ወደ ሰማይ ቤት ይሄዳል፡፡ በገነት በራፍ ላይ ቅዱስ ጴጥሮስ ያገኘዋል፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ የሁሉም ሰው ኃጢያት መዝገብ በእጁ ነውና የጠበቃውን ስም ፈልጎ ያገኘዋል፡፡ ከዚያ የሰራውን ኃጢያት ዝርዝር ያያል፡-
1ኛ. አንድን ከአየር መበከል ጋር ተያይዞ የተከሰሰን ሰው በመከላከል ጥብቅና ቆሟል
2ኛ. ደህና ገንዘብ ይከፈልሃል ስለተባለ ብቻ በግልፅ በነብስ ግድያ የተከሰሰን ነብሰ ገዳይ በመከላከል ጥብቅና ቆሟል፡፡
3ኛ. አብዛኛዎቹን የጥብቅና ደምበኞቹን ከልኩ - በላይ አስከፍሏል፡፡
4ኛ. አንዲትን የዋህ ሴት ለሌሎች ወንጀለኞች ጥፋት ማምለጫ ሰበብ እንድትሆን በመፈለግ፤ እንዲፈረድባት አድርጓል፡፡
ጠበቃው ይህን ክስ በመቃወም ተሟገተ፡፡ ክሶቹን በሙሉ ተቀበለና አንድ መሟገቻ ግን ይዞ ቀረበ፡-
“አንድ የምፅዋት ስጦታ ለነዳያን በህይወቴ አንዴ ሰጥቻለሁ” አለ፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ መዝገቡን አየና፤
“አዎን አዎን ስምህ አለ፡፡ ለአንድ ጎዳና ተዳዳሪ አሥር ሳንቲም ሰጥተሃል! ለአንድ ሊስትሮ ደግሞ አንድ ሳንቲም ሰጥተሃል! ትክክል ነኝ?” ጠበቃው ግራ የተጋባ መልክ እየታየበት፤ “አዎን!” አለ፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ አጠገቡ ወዳለው መልዐክ አየ፡፡
“ይሄን ልጅ አሥራ አንድ ሳንቲሙን ስጠውና ወደ ገሀነም አስገባው!” አለው፡፡
*       *     *
በሰው ላይ ግፍ ማስፈረድ፣ አላግባብ ገንዘብ መዝረፍ፣ የአብዬን እከክ ወደ እምዬ ልክክ ማድረግ፣ የማታ ማታ ማስጠየቁ አይቀሬ ነው፡፡
በርካታ ሌብነት፣ በርካት ግፍ፣ በርካታ የማጭበርበር ተግባር ፈፅመን ስናበቃ፣ ቅንጣቷ ደግነቴ ትመዝገብልኝ ማለት ግብዝነት እንጂ ብልጠት አይሆንም፡፡ ዕድሜያችንን ሙሉ የሰራነው ተንኮል እየታወቀ፣ አንድ ቀን የመፀወትኩትስ? ብሎ መከራከር ዐይናውጣነት ከመሆን በቀር ከፍርድ አያድንም! ዐረቦች “ሌባው በሰረቀው ሳይሆን ሳይሰርቅ በተወውም ይታወቃል” ይላሉ፡፡
የሀገራችን ፖለቲከኞች ነገር ለተፎካካሪ የሚመችና የተጋለጠ ነው፡፡ “ብቅል አስጥታ ነበር፤ እሽ ብትል እንዴት ጥሩ ነበር” ተብሎ ሁሌም የሚታለፍ ፌዝ መሳይ ነው፡፡
የሀገራችን ኢኮኖሚም ጥቂቶች ከዝሆን ጥርስ (Ivory - Power) ላይ ሆነው የሚነጩበት፣ ብዙሃኑ ትቢያ ላይ የሚተኙበት ዓይነት እየሆነ ነው፡፡ ቱርኮች “አንዱ በይ አንዱ የበይ ተመልካች የሆነ ዕለት የዓለም መጨረሻ መጣ ማት ነው” ይላሉ፡፡ እንደዚያም ቢባል አይገርምም፡፡
የመሰረተ - ልማት ሂደቱ ደግ ነው ቢባልም፤ በዙሪያው ያለው ሙስና ቀለም በተቀባ ቆርቆሮ እንደሚሸፈን ቆሻሻ ቦታ ሊሆን አልቻለም፡፡ የሚያስደንቀው ሌቦቹ ቀና ብለው የሚሄዱበት፣ ተመዝባሪዎቹ የሚያቀረቅሩበት ሁኔታ መሆኑ ነው፡፡
የካፒታሊዝምን ነገረ - ሥራ ሳንመረምር ተቀብለን አንድምታዎቹ በፖለቲካችንም፣ በኢኮኖሚያችንም፣ በማህበራዊ ኑሯችንም ሲንፀባረቁ መማረራችን አስገራሚ ነው፡፡ ዲሞክራሲ ልሙጥ በሆነ ህብረተሰብ ውስጥ ፋይዳው ከሲታ ነው፡፡ የሚወዳደር፣ የሚፎካከር፣ የሚከራከር፣ የሚታገል፣ የሚደራደር ህብረተሰብን ግድ ይላል፡፡ “ሞኝ ሸንጎ ተሰብስ አገኘሽ፣ ቁርስ የሌለው ቡና አፈላሽ” አይነት ከሆነ ጉዞው ዘገምተኛ ይሆናል፡፡ ቢያንስ “ምቀኛ አታሳጣኝ” የሚለውን አገርኛ ባህላዊ አነጋገር ማስተዋል ይጠቅማል፡፡
ኃያላን መንግሥታት ዐይን ቢጥሉብን ፍፅምና ያለን ሊመስለን አይገባም፡፡ ሁሉም የየራሱ ገበታ እንዳለው አንርሳ፡፡ ዞሮ ዞሮ ራስን ችሎ እንደመገኘት የመሰለ ነገር የለም! “ተሸፋፍነው ቢተኙ፣ ገልጦ እሚያይ አምላክ አለ” የሚለውን ተረት አንርሳ፡፡ የኢኮኖሚ ችግርን መባባስ መደበቅ አይቻልም፡፡
ምድረ - በዳውን እየማተርን የበረሀ - ገነት (oasis) አየን ብንል ራስን ከማታለል በቀር ሌላም መላ የለው፡፡ ያለን አለን፣ የሌለን የለንም፡፡ የማንኖረውን ኑሮ እየኖርን ነው ብለን ብንኩራራና ብንቦተልክ ኑሯችን አጋልጦ እርቃናችንን ያሳየናል!
ሥራችን የሆነውን ኃላፊነት ሳንወጣ ከሁሉም በላይ ደግሞ፤ ሌላው ላይ መላከክ ሀገራችን በየጊዜው የሚያጋጥማት የፖለቲካ ጨዋታ ነው፡፡ ሁሉ ወቃሽ ሁሉ ከሳሽ ሆነና የየራሱን ግዴታ የሚያይበት ዐይን ጠፋ፡፡ “ሁሉም ፈረስ ላይ ከወጣ፣ ማን መንገድ ይምራ?” እንደሚለው የወላይትኛ ተረት ነው፡፡ የጠያቂው ብዛት የተጠያቂውን ደብዛ ያጠፋዋል! ይህ መፈተሽ ያለበት የፖለቲካ ችግራችን ነው፡፡
“ድመት አይጥ እንዲይዝ ተብሎ ችቦ አይበራለትም” የሚለው የጉራጌ ተረት ሁሉም በየራሱ ሥራ መፈተሽና መጠየቅ እንደሚገባው ነው የሚያሳየን፡፡ ይህንን ልብ እንል ዘንድ ልብ ይስጠን!

በደራሲና ጋዜጠኛ አንተነህ ይግዛው የተጻፈው “ባቡሩ ሲመጣ...” የተሰኘ የአጫጭር ልቦለዶች ስብስብ መጽሐፍ፣ የፊታችን አርብ ከ11፡30 ሰዓት ጀምሮ በኢትዮጵያ ሆቴል በሚከናወን ኪነጥበባዊ ዝግጅት ተመርቆ በገበያ ላይ ይውላል፡፡
የደራሲው ሁለተኛ ስራ የሆነው “ባቡሩ ሲመጣ...”  በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ የሚያጠነጥኑ 14 አጫጭር ልቦለዶችን በ210 ገጾች አካትቶ የያዘ ሲሆን፣ የመሸጫ ዋጋውም ለአገር ውስጥ 60 ብር፣ ለውጭ አገራት ደግሞ 16 ዶላር እንደሆነ ደራሲና ጋዜጠኛ አንተነህ በተለይ ለአዲስ አድማስ ገልጿል፡፡
ጋዜጠኛና ደራሲ አንተነህ ይግዛው፣ የመጀመሪያ ስራው የሆነውን “መልስ አዳኝ” የተሰኘ የአጫጭር ልቦለዶች ስብስብ መጽሃፍ በ2003 ዓ.ም ለንባብ ያበቃ ሲሆን፤ በቅርቡም የወጎች ስብስብ መጽሃፍ ለህትመት እንደሚያበቃና በአንድ ታዋቂ ኢትዮጵያዊ የቢዝነስ ሰው የህይወት ታሪክ ዙሪያ የሚያጠነጥን መጽሐፍ እያዘጋጀ እንደሚገኝም ገልጿል፡፡
አንተነህ ይግዛው፣ ከሁለት አመታት በፊት በፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን በኩል ለአንድ አመት ከአራት ወራት የተላለፈውን “ስውር መንገደኞች” የተሰኘ ተወዳጅ ሳምንታዊ የሬዲዮ ድራማ በደራሲነትና በተዋናይነት ለአድማጭ ማቅረቡም ይታወሳል፡፡

የአቶ ካሣዬ ተክለአረጋይ ቤተሰቦች የተለያየ ቅፅ ኢንሳይክሎፒዲያ፣ የወንጀለኛ መቅጫ፣ የተጠቃለሉ ሕጐች፣ የሕግ መጽሔቶችና ጠቅላላ ዕውቀትን ጨምሮ 60 ያህል መፃሕፍትን ለዕውቀትና ትጋት አሰፋ ጎሳዬ የሕዝብ ቤተ-መፃሕፍት ሰሞኑን አበረከቱ፡፡
የሕግ ባለሙያ የነበሩት አቶ ካሣዬ ተክለአረጋይ በሕይወት ሳሉ ሲጠቀሙባቸው የነበሩ መፃሕፍትን ለቤተመፃሕፍቱ ያበረከቱት ልጃቸው አቶ ሰለሞን ካሣዬ ናቸው፡፡ የአቶ ሰለሞን ካሣዬ ባለቤት ወ/ሮ ምህረት ጌታቸው በወቅቱ እንደተናገሩት፤ “መጻህፍቱን እንድንሰጣቸው  የጠየቁ ግለሰቦች የነበሩ ቢሆንም መፃሕፍቱ የበለጠ ከአንባቢያን ጋር ሊገናኙ የሚችሉት በቤተ-መፃሕፍት ውስጥ ቢቀመጡ ነው በሚል እምነት አበርክተንላችኋል” ብለዋል፡፡

 በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ የሰሉ ሥነ ፅሁፋዊ ሂሶችን በማቅረብ የሚታወቀው ደራሲና ሃያሲ ዓለማየሁ ገላጋይ የጻፈው “ወሪሳ - የውድቀት ፈለጎች” የተሰኘ የረዥም ልብ ወለድ መፅሃፍ ሰሞኑን ለንባብ በቃ፡፡
አዲሱ ልብወለድ ለደራሲው 9ኛ መፅሃፉ ሲሆን በ49 ብር እየተሸጠ መሆኑ ታውቋል፡፡
ዓለማየሁ ከዚህ ቀደም “አጥቢያ”፣ “ቅበላ” እና “የብርሃን ፈለጎች” የተሰኙ ግሩም የረዥም ልብወለድ ስራዎችን ያሳተመ ሲሆን “ኩርቢት” የሚል የአጭር ልቦለድ መድበልም ለአንባቢያን አድርሷል፡፡ በደራሲ ስብሃት ገብረእግዚአብሄር ህይወትና ክህሎት ዙሪያ ያሰናዳው መፅሃፉም የሥነፅሁፍ  ምሁራንን ያነጋገረና ያሟገተ መሆኑ ይታወሳል፡፡ ደራሲው፤ “ፍትህ”፣ “አዲስ ታይምስ” እና“ፋክት” በተሰኙ የህትመት ውጤቶች ላይ ያቀርባቸው በነበሩ ማራኪና ኮርኳሪ መጣጥፎቹ የብዙዎችን ቀልብ ለመሳብ ችሏል፡፡

 አምስት በአማርኛና አንድ በኦሮምኛ ቋንቋ የተፃፉ ስዕላዊ ባለቀለም የህጻናት መፃህፍት ተዘጋጅተው የታተሙ ሲሆን በነገው ዕለት ከቀኑ 8 ሰዓት ጀምሮ ከደንበል ህንፃ ፊት ለፊት፣ ከዴሉክስ ፈርኒቸር ጀርባ በሚገኘው ኢግሉ አይስክሬም ቤት ይመረቃሉ፡፡
የመፃህፍቱን ታሪኮች በመድረስ አዜብ ወርቁ፣ ዳንኤል ወርቁ፣ ሰላማዊት ሙሉጌታና ሲሳይ ተስፋዬ የተሳተፉ ሲሆን የስዕል ስራዎቹን የሰሩት ሰዓሊ ደረጄ ደምሴ፣ አርክቴክት አሃዱ አባይነህና የህፃናት ስዕል ባለሙያው ይስሃቅ ሳህሌ እንደሆኑ የመፃህፍቱ አሳታሚ “ሚዳቆ ፐብሊሺንግ” ለአዲስ አድማስ በላከው ጋዜጣው መግለጫ ጠቁሟል፡፡ የመፃህፍቱ ዋጋ (እያንዳንዱ) 29 ብር ነው ተብሏል፡፡ “ሚዳቆ  ፐብሊሺንግ” ዋነኛ ትኩረቱን በህፃናት መፃህፍት ላይ ያደረገ የህትመት ተቋም እንደሆነ ተገልጿል፡፡

ከሽብርተኝነት ጋር በተያያዘ የእድሜ ልክ እስራት ተፈርዶባቸው በማረሚያ ቤት የሚገኙት የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ የቀድሞ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ አንዷለም አራጌ በማረሚያ ቤት ሆነው ለሁለተኛ ጊዜ የፃፉት “የሀገር ፍቅር ዕዳ” መጽሐፍ ለንባብ በቃ፡፡
አቶ አንዷለም አራጌ ከዚህ ቀደም “ያልተሄደበት መንገድ” የተሰኘ መጽሐፍን ለአንባቢያን ያደረሱ ሲሆን “የሀገር ፍቅር እዳ ከቀሳ ጐንደር እስከ ቃሊቲ አስር ቤት” የተሰኘው አዲሱ መጽሐፋቸው በ32 ምዕራፎች ተከፋፍሎ፣ በ400 ገፆች የቀረበ ነው፡፡ ዋጋው 100 ብር ነው፡፡

በይግረም አሸናፊ የተፃፉ የልብወለድ እና ወጎች ስብስብ የያዘው “ክብሪት” ለገበያ ቀርቦ እየተነበበ ነው፡፡ በ137 ገፆች  20 ታሪኮችን ያካተተው መፅሃፉ፤ በብር 45.62 ለገበያ ቀርቧል፡፡

 “… ከገራገር ህይወቷ ላይ የሚከተላት ምሳሌ የፍስሃዋን በር የሚዘጋ ነገር አታጣም፡፡ በተፈጥሮ ያልሆነ በልጅ ሃሳብም ያልሆነ፣ በሴትነትም ያልሆነ የሚከተላት ጠልና ጥል እጇ ላይ ነጥሮ ይመጣል፤ አነጣጥሮ ይመታታል፡፡ በሩን ወደ ኋላ ዘጋችው። አይኖቿን ጨፍና አመታቱን አሰበች፡፡ ጠባሳዋን ቆጠረች፡፡ …”
(ከመፅሀፉ የተቀነጨበ)
በደራሲ ሊና ካሳሁን የተፃፉ ታሪኮችን ያካተተው “ፍቅር እና አደራ እና ሌሎችም” የተሰኘው መፅሃፍ ሰሞኑን ለአንባቢያን የቀረበ ሲሆን በዛሬው እለት ከቀኑ 9 ሰዓት ጀምሮ ከሬዲዮ ፋና ህንፃ ጀርባ በሚገኘው ወመዘክር አዳራሽ ይመረቃል፡፡
መፅሀፉ 11 ታሪኮችን የያዘ ሲሆን በ162 ገፆች እንደተቀነበበና በ40.50 ለገበያ መቅረቡ ታውቋል። የደራሲዋ ተከታይ ስራም “የእሳት እራት” የሚል ርዕስ ያለው እንደሚሆን ተጠቁሟል፡፡

  በደራሲና ዳይሬክተር ቴዎድሮስ ለገሰ ተፅፎ የተዘጋጀው “ያየ ይፍረደው” የተሰኘ የቤተሰብ ፊልም ባለፈው ማክሰኞ በአቤል ሲኒማ አዳራሽ ተመረቀ። በአልዩ ፊልም ፕሮዳክሽን የቀረበው ፊልሙ፤ የ1፡30 ርዝመት ያለው ሲሆን ፊልሙን ሰርቶ ለማጠናቀቅ 7 ወር እንደፈጀ ለማወቅ ተችሏል፡፡ በፊልሙ ላይ ተዋንያን ቴዎድሮስ ለገሰ፣ አዚዛ አህመድ፣ ህፃን ማርያማዊት ፍፁም፣ ሔኖክ ብርሃኑና ሌሎችም አንጋፋና ወጣት ተዋንያን ተሳትፈውበታል፡፡

 ሀገሬ ሚዲያ ኮሙኒኬሽን፤ የደቡብ ጎንደር የቱሪዝም ማውጫ ዳይሮክተሪ አዘጋጅቶ አሳተመ፡፡ ማውጫው በ10 ወረዳዎችና በሁለት ከተማ አስተዳደሮች ግዛት ውስጥ የሚገኙ ከ100 በላይ ተፈጥሮአዊ፣ ባህላዊ፣ ታሪካዊና መንፈሳዊ መስህቦችን ያካተተ ነው ተብሏል። ከመስህቦቹ ውስጥ 80 በመቶው ከ250 ዓመት በላይ ዕድሜ ያስቆጠረ ሲሆን ከ50 በመቶ የሚበልጡት ደግሞ ከ500 ዓመት በላይ ዕድሜ ያላቸው ታሪካዊ ቅርሶች እንደሆኑ ታውቋል፡፡
ማውጫው ሥፍራዎቹን ለመጎብኘት የሚያስችሉ መረጃዎች እንዲሁም የትራንስፖርትና ሌሎች አገልግሎቶች የሚገኙባቸውን አግባብ በሚጠቁም መልኩ መዘጋጀቱን የጠቆሙት አሳታሚዎቹ፤ ዳይሬክተሪው ከቱሪዝም ልማት ጋር ትስስር ላላቸው አካላት፣ ለቤተ - መፃህፍትና መንግስታዊና መንግስታዊ ላልሆኑ ተቋማት በነፃ እንደሚታደል ገልፀዋል፡፡
ሀገሬ ሚዲያ ኮሙኒኬሽን፤ በቱሪዝምና ባህል ላይ አተኩሮ የሚሰራ ተቋም ሲሆን ከዚህ ቀደም የሰሜን ሸዋ ዞን ቱሪዝም ዳይሮክተሪ፣ የኢትዮጵያ ተፈጥሮና ፓርኮች ማውጫ፣ የኢትዮጵያ ሙዚያም ማውጫና የኢትዮጵያ ፌስቲቫል ማውጫ አዘጋጅቶ ማሳተሙ ይታወቃል፡፡