Administrator

Administrator

ጳጳሳት የፓትርያርኩን የማኅበረ ቅዱሳን ደንብ ማሻሻያ ቅድመ ኹኔታ አልተቀበሉትም
‹‹ቅድመ ኹኔታው የማኅበሩን አገልግሎት የሚያቀጭጭና በሒደትም የሚያስቆም ነው›› /ታዛቢዎች/

የማኅበረ ቅዱሳን መተዳደሪያ ደንብ ማሻሻያ ረቂቅን እንደ አንድ አጀንዳ የያዘው የዘንድሮው የሲኖዶሱ የርክበ ካህናት ጉባኤ ከረቂቁ ጋር በተያያዘ በፓትርያርኩና በሊቃነ ጳጳሳቱ መካከል በተፈጠረ ፍጥጫ መጠናቀቁ ተገለጸ፡፡
የፍጥጫው መንሥኤ፣ በቅዱስ ሲኖዶሱ የተሠየመው የማኅበረ ቅዱሳን መተዳደርያ ደንብ አጥኚ ኮሚቴ ያዘጋጀው የማሻሻያ ረቂቅ በዝርዝር ከመታየቱ አስቀድሞ ፓትርያርኩ ለውይይቱ እንደ ቅድመ ኹኔታ ያቀረቧቸው ነጥቦች በአብዛኛው የጉባኤው አባላት የገጠመው ተቃውሞ እንደኾነ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
የቅ/ሲኖዶሱን ስብሰባ በርእሰ ጉባኤነት የሚመሩት ፓትርያርኩ፤ በአጀንዳው ላይ የሚካሔደውን ውይይት ቀጣይነት ይወስናል በሚል ካቀረቧቸው ቅድመ ኹኔታዎች ውስጥ÷ ለአጥኚ ኮሚቴው መመሪያ የሰጡባቸው ‹‹ልዩ ልዩ ድንጋጌዎችና ግዴታዎች›› አንድም ሳይቀነሱ በደንቡ እንዲካተቱና ረቂቁ ሕገ ቤተ ክርስቲያኑ ከጸደቀ በኋላ እንዲታይ የሚሉ እንደሚገኙበት ተመልክቷል፡፡
ፓትርያርኩ በቅድመ ኹኔታ አስቀምጠዋቸዋል በተባሉት ነጥቦች ስምምነት ላይ ከተደረሰ ስብሰባው ሊቀጥል እንደሚችል በመጥቀስ፣ ኃይለ ቃልም ተማኅፅኖም በተቀላቀለበት አኳኋን መጠየቃቸው ተዘግቧል፡፡
ይኹንና የሚበዙት ሊቃነ ጳጳሳት በቀጥታ እንደተቃወሟቸው፣ የተቀሩትም ድጋፍ ከመስጠት እንደተቆጠቡ ታውቋል፡፡ ፍጥጫው ቀጥሎ አቡነ ማትያስ ‹‹አቋሜ ይኽው ነው፤›› በሚል አጀንዳውን መዝጋታቸውን ሲያስታውቁም፣ ‹‹የማኅበረ ቅዱሳን ጉዳይ እንዲህ ተብሎ የሚተው አይደለም፤›› በሚል ከኹሉም ሊቃነ ጳጳሳት ጠንካራ ተቃውሞ እንደገጠማቸው ምንጮች ይገልፃሉ፡፡
የቅ/ሲኖዶሱ መደበኛ ስብሰባ የሚካሔደው ምልዓተ ጉባኤው ከጅምሩ ተስማምቶ ባጸደቃቸው የመነጋገርያ አጀንዳዎች መሠረት እንደኾነ በሊቃነ ጳጳሳቱ ተቃውሞ ተጠቅሷል፡፡
የማኅበሩ የመተዳደርያ ደንብ ማሻሻያ ረቂቅ እንዲቀርብ ከታዘዘበት ከጥቅምት 2005 ዓ.ም. ጀምሮ እየተንከባለለ ለኹለት ዓመታት መዘግየቱን ሊቃነ ጳጳሳቱ አስታውሰው፣ የተጓተተው አጀንዳ ‹‹የማኅበሩን አገልግሎት ያቀጭጫሉ፣ በሒደትም ያስቆማሉ›› በሚል በተተቹት የፓትርያርኩ ቅድመ ኹኔታዎች ሊዘጋ እንደማይችልና ተጨማሪ ጊዜ ሳይወስድ ቅ/ሲኖዶሱ ሊወያይበት እንደሚገባ በአጽንዖት በመናገራቸው፣ ጉዳዩ ሳይቋጭ ለቀጣዩ ቀን በይደር ተላልፏል፡፡
አጀንዳው ሰኞ፣ ግንቦት 18 ቀን 2006 ዓ.ም. ጥዋት መታየት ሲጀምር፣ አጥኚ ኮሚቴው በ37 አንቀጾችና በ34 ገጾች አሻሽሎ ያዘጋጀው የማኅበሩ መተዳደርያ ደንብና የኮሚቴው ቃለ ጉባኤ በንባብ መሰማቱም ታውቋል፡፡ ፓትርያርኩ ‹‹ልዩ ልዩ ድንጋጌዎችና ግዴታዎች›› በሚል ራሱን በቻለ ርእስ በደንቡ እንዲካተት ለአጥኚ ኮሚቴው ጥብቅ መመሪያ የሰጡበት ባለ24 አንቀጽ ሰነድም አብሮ እንዲነበብላቸው መጠየቃቸው የመጀመሪያው ቀን የፍጥጫ መነሻ እንደነበር ታውቋል፡፡
በ24 አንቀጾችና በአምስት ገጾች የተዘረዘሩት የፓትርያርኩ ልዩ ልዩ ድንጋጌዎችና ግዴታዎች÷ በአባላቱ በጎ ፈቃድ ተቋቁሞ ከፍተኛ አስተዋፅኦ በማበርከት ላይ የሚገኘውን ማኅበር፤ ከሕገ ተፈጥሮው ውጭ የሚያደርግ፣ በቅ/ሲኖዶሱ ፈቃድ ከሚመራበት ደንብ በተፃራሪ ተቋማዊ ህልውናውን፣ የአመራር ምርጫውን፣ የአባላት አያያዙንና የሥራ ቦታውን ለውጭ ተጽዕኖ አሳልፎ የሚሰጥና አጣብቂኝ ውስጥ የሚያስገባ፣ በአርኣያነት የሚጠቀሰውን የፋይናንስ አሠራሩን ወደ ኋላ የሚጎትት መኾኑን እንደተረዱ ያብራሩ አንድ የቅ/ሲኖዶሱ አባል፣ ‹‹ቀጣዩ ቀንም የከበደ ነገር ይዞ እንደሚመጣ ግልጽ ነበር፤›› ይላሉ፡፡
በይደር የተያዘው አጀንዳ በቀጣዩ ቀን ማክሰኞ ጥዋት ተጀምሮ ለግማሽ ቀን የቀጠለ ቢኾንም ፓትርያርኩና ሊቃነ ጳጳሳቱ የመተዳደርያ ደንብ ማሻሻያውን በዝርዝር ለመመልከት የሚያስችል ስምምነት ላይ ለመድረስ እንዳልቻሉ ታውቋል፡፡
‹‹ፓትርያርኩ በቅድመ ኹኔታ ያስቀመጧቸውን ነጥቦችና በአጀንዳው ቀጣይነት ላይ የያዙትን አቋም አልቀየሩም፤ ሊቃነ ጳጳሳቱም ባጸደቅነው አጀንዳ መሠረት ቅድሚያ ሰጥተን መነጋገር ያለብን የሠየምነው አጥኚ ኮሚቴ አዘጋጅቶ ባቀረበው ረቂቅ ላይ ነው፤ መካተት ያለበት ነገር ካለም ማኅበሩን በሚያሠራ መልኩ እያገናዘብን በሒደት እናየዋለን እንጂ አጀንዳው በቅድመ ኹኔታ መታሰር የለበትም በሚል ለማስረዳት ጣሩ፤ በመጨረሻም ፓትርያርኩ “እንግዲያውስ ስብሰባውን ለመምራት አልችልም” በማለታቸው የስብሰባው መቋጫ ኾኗል፤›› ይላሉ- ሒደቱን ለአዲስ አድማስ የገለጹ የስብሰባው ምንጮች፡፡
የማኅበሩ ደንብ በመጀመሪያ ረድፍ ከሰፈሩት የቅ/ሲኖዶሱ መነጋገርያ ነጥቦች አንዱ እንደነበር ያስተዋሉ ሌሎች የስብሰባው ተከታታዮች በበኩላቸው፤ አጀንዳው ከቅደም ተከተሉ ወጥቶ እየተገፋ በመጨረሻ መነሣቱ በፓትርያርኩና በሊቃነ ጳጳሳቱ መካከል ይህ ዓይነቱ አለመግባባት ሊነሣ እንደሚችል ጠቋሚ ነበር ብለዋል፡፡  
ተከታታዮቹ አክለውም፣ ፓትርያርኩ ስብሰባውን ለመምራት ፈቃደኛ ባይኾኑም በሕገ ቤተ ክርስቲያኑ በተደነገገው የቅ/ሲኖዶስ ስብሰባ ሥነ ሥርዓት መሠረት፣ ምልዓተ ጉባኤው በማኅበሩ መተዳደርያ ደንብ ማሻሻያዎች ላይ የጀመረውን ውይይት ቀጥሎ ውሳኔ ለማሳለፍ የሚችልባቸው አግባቦች እንደነበሩ ገልጸው፣ ቅ/ሲኖዶሱ በግለጫው የመጨረሻው አጀንዳው ባደረገው የማኅበሩ ደንብ ላይ “ውይይት ተደርጎበታል” ከማለት በስተቀር ስብሰባውን የቋጨበት አኳኋን ያልተለመደና አደናጋሪ ነው ብለዋል፡፡
ማኅበረ ቅዱሳን የዘመኑን ኦርቶዶክሳዊ ትውልድ አደራጅቶ ማንነቱን የሚያውቅበትንና በግብረ ገብ የሚታነፅበትን ትምህርተ ሃይማኖት ከማስተማር ባሻገር፣ የቤተ ክርስቲያኒቱ ተቋማት አገልግሎታቸውን በብቃት የሚወጡበትን ኹለገብ ሞያዊ ድጋፍ የመስጠት ሓላፊነት እንዳለበት በደንብ አጥኚ ኮሚቴው ማሻሻያ ረቂቅ ላይ መስፈሩ ታውቋል፡፡
ይኹንና ‹‹ጥበቃና ጥንቃቄ›› በሚል ፓትርያርኩ እንደ መመሪያ ያቀረቧቸው ድንጋጌዎችና ግዴታዎች እንዲሁም ከልዩ ጽ/ቤታቸው ማኅበሩን አስመልክቶ በየጊዜው የሚወጡ መመሪያዎች የማኅበሩን አገልግሎት የማቀጨጭ፣ በሒደትም አዳክሞ የማስቆም ውጤት ሊኖራቸው እንደሚችል ታዛቢዎች ያስረዳሉ፡፡
የማኅበሩ መተዳደርያ ደንብ ማሻሻያ ረቂቅ፣ ቅ/ሲኖዶሱ የማኅበሩ ደንብ እንዲሻሻል ግንቦት 14 ቀን 2004 ዓ.ም. ባካሔደው ስብሰባ÷ ማኅበሩ ከጊዜው ጋር የሚሔድ፣ አገልግሎቱና አደረጃጀቱ የደረሰበትን ስፋትና ዕድገት የሚመጥን፣ ለቤተ ክርስቲያን ኹለንተናዊ ልማት የሚጠቅም ድርጅታዊ መዋቅር እንደሚያስፈልገው ባሳለፈው ውሳኔ መሠረት አምስት ሊቃነ ጳጳሳት፣ ገለልተኛ የሕግ ባለሞያዎችና የማኅበሩ አባላት በታከሉበት አጥኚ ኮሚቴ የጋራ ጥናት የተዘጋጀ መኾኑ ተመልክቷል፡፡
በግንቦት ወር 1984 ዓ.ም. በበጎ ፈቃድ በተሰበሰቡ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች የተመሠረተው ማኅበሩ፤ እየተመራ ያለው ቅ/ሲኖዶስ በ1994 ዓ.ም. ለሦስተኛ ጊዜ አሻሽሎ በሰጠው መተዳደርያ ደንብ ሲኾን አሁን የተሻሻለው ረቂቅ ተመርምሮ ባለመጽደቁ በነባሩ ደንብ እየተመራ ለመቀጠል እንደሚገደድ ተመልክቷል፡፡

በ800 ሜትር ሳይሸነፍ 15 ወራት አልፈዋል
ዘንድሮ ለዳይመንድ ሊግ ድል ለሃትሪክ ተጠብቋል
አዲስ የዓለም ሪከርድ እንደሚያስመዘግብ ግምት ተሰጥቶታል

አትሌት መሃመድ አማን ባለፉት 15 ወራት በሮጠባቸው የ800 ውድድሮች አልተሸነፈም፡፡ ኢትዮጵያ በዓለም የአትሌቲክስ ስፖርት ላለፉት 30 ዓመታት በረጅም ርቀት ከፍተኛ ስኬት ያስመዘገቡ አትሌቶችን በማፍራት ትታወቅ ነበር፡፡ ባለፉት 5 ዓመታት ግን በ20 ዓመቱ የዓለማችን የመካከለኛ ርቀት ምርጥ ሯጭ  ኮርታለች፡፡ አትሌት መሃመድ የኢትዮጵያን የአትሌቲክስ ዝና በአዲስ ምዕራፍ ቀይሶታል፡፡
ዘንድሮ በዳይመንድ ሊግ ውድድሮች ላይ ምርጥ ብቃት ያሳያሉ ተብለው ከተጠበቁ ምርጥ አትሌቶች አንዱ የሆነው መሃመድ በዚህ የውድድር ዘመን የ800 ሜትር የዓለም ሪከርድን ሊሰብር እንደሚችል በመገመትም ላይ ነው፡፡  በእርግጥም በርቀት አይነቱ  የዓለም ንጉስ ለመባል የሚቀረው ሪከርዱን መስበር ብቻ ነው፡፡ አንዳንድ የአትሌቲክስ ባለሙያዎች አትሌቱ አሁን በያዘው ብቃት ከቀጠለ ዘንድሮ ባይሳካለት እንኳን በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት በዓለም አቀፍ ውድድሮች የሚኖሩት ልምዶች የዓለም ሪከርድን የሚያሻሽልበት ብቃት ላይ እንደሚያደርሱት እየመሰከሩ ናቸው፡፡ ከሁለት ሳምንት በፊት የ2014  የዳይመንድ ሊግ ውድድር በኳታር ዶሃ ሲጀመር አንፀባራቂ ከነበሩ አትሌቶች ዋናው የነበረው አትሌት መሃመድ አማን፤ በወቅቱ በ800 ሜትር ውድድር ሲያሸንፍ ያሳየው አስደናቂ የአጨራረስ ብቃት ከፍተኛ አድናቆት አጉርፎለታል፡፡ እንደውም አንዳንድ ዘገባዎች ‹‹ሱፕር አትሌት›› ብለው አግንነውታል፡፡ ይሁንና አትሌቱ ከ2013 አጋማሽ ጀምሮ በተሳተፈባቸው የ800 ሜትር ውድድሮች ሳይሸነፍ ለመቆየቱ በቂ ምክንያት በማቅረብ የሚከራከሩ አልጠፉም፡፡ በእነዚህ ተከራካሪዎች መሃመድ አማን የሚቀናቀነው የጠፋው በተለይ የርቀቱ ሁለት ምርጥ አትሌቶች ጋር ባለመገናኘቱ ነው የሚል ማስረጃ ይቀርባል፡፡ በ2012 እኤአ ላይ ለንደን ኦሎምፒክ ላይ የዓለምን ሪከርድ ያስመዘገበው የ25 ዓመቱ ኬንያዊው ዴቪድ ሩዲሻ በጉዳት ከውድድር ከራቀ ሁለት ዓመት አልፎታል፡፡ ሌላው ምርጥ አትሌት እና በእድሜው እኩያው የሆነው ደግሞ የቦትስዋናው ኒጄል አሞስ ሲሆን እሱም በጉዳት ከውድድር እንደራቀ ነው፡፡
በዓለም አትሌቲክስ ዘንድሮ በከፍተኛ ጉጉት ከሚጠበቁ ትንቅንቆች ዋንኛው መሃመድ አማን ፤ ኒጄል አሞስ እና ዴቪድ ሩዲሻ የሚገናኙበት የ800 ሜትር  ፍጥጫ እንደሆነ ይገለፃል፡፡ ሶስቱ አትሌቶች በዳይመንድ ሊግ መገናኘታቸው እየተጠበቀ ሲሆን በተለይ ከሳምንት በኋላ በአሜሪካዋ ከተማ ዩጂን፤ የሚደረገው የፕሮፎንታይኔ ክላሲክስ ላይ ከተገናኙ አስገራሚ ፉክክር እንደሚኖራቸው   ተገምቷል፡፡ የ800 ሜትር የዓለም ሪከርድ በዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር በኦፊሴላዊ ደረጃ መመዝገብ የተጀመረው በ1952 እኤአ ነው፡፡ የመጀመርያው ሪከርድ በአሜሪካዊው አትሌት ቴድ ሜሪንዴዝ በ1.51 ደቂቃዎች የተመዘገበ ሲሆን ከዚሁ ሪኮርድ በኋላ 24 ጊዜ ሰዓቱ ሲሻሻል በርካታ እንግሊዛዊያንና አሜካዊያን አስተዋኝኦ ነበራቸው፡፡ ከ2008 ጀምሮ የተመዘገቡ ሦስት ሪኮርዶችን ማስመዝገብ የቻለው ኬንያዊው ዴቪድ ሩዲሻ ሲሆን የወቅቱ ሪከርድ ከ2 ዓመት በፊት በለንደን ኦሎምፒክ  በ1 ደቂቃ ከ41.54 ሰኮንዶች ያስመዘገበው ነው፡፡ አትሌት መሃመድ አማን ዘንድሮ በርቀቱ ሪከርድ ለመስበር  ፍላጐት እንዳለው በይፋ የተናገረው ነገር ባይኖርም የራሱን ምርጥ ሰዓት ወይንም የኢትዮጵያን ሪከርድ ለ7ኛ ጊዜ ለማሻሻል ያስባል፡፡ 800 ሜትርን ከ1.40 ደቂቃ በታች እንደሚገባም ያምናል፡፡

ምርጥ ሰዓቶቹ- በ800 ሜትር 1፡42.37 ቤልጅዬም ብራሰልስ  በ2013 እኤአ የተመዘገበ ሰዓት ሲሆን የኢትዮጵያ ሪከርድ ነው፡፡ በ800 ሜትር የኢትዮጵያ ሪከርድን ለስድስት ጊዜያት አሻሽሏል፡፡ በ1500 ሜትር 3፡43.52 ምርጥ ሰዓት ያስመዘገበ ሲሆን በ1 ማይል ያለው ምርጥ ሰዓት ደግሞ 3፡57.14 ነው፡፡
ወቅታዊ ደረጃው- በኦልአትሌቲትክስ ድረገፅ ዘንድሮ በ800 ሜትር በ1405 ነጥብ የዓለም አንደኛ አትሌት ሲሆን በሁሉም የአትሌቲክስ የውድድር መደቦች በተመሳሳይ ነጥብ ከዓለም 8ኛ ነው፡፡ በዓለም የ800 ሜትር የምንግዜም ፈጣን ሰዓቶች ደረጃ 9ኛ ነው፡፡
ማኔጅመንት እና ስፖንሰር -የትጥቅ ስፖንሰሩ ናይኪ ሲሆን፤ ከ2009 እኤአ ጀምሮ ኤሊት ስፖርትስ ማኔጅመንት ኢንተርናሽናል ESMI በመታቀፍ እየሰራ ነው፡፡
አስደናቂ ድሎቹ- አሁን በጉዳት ላይ የሚገኘው የኬንያው አትሌት ዴቪድ ሩዲሻ የ800 ሜትር የዓለም ሪከርድን ለስድስት ጊዜያት አሻሽሏል፡፡ ግዙፉ አትሌት በሩጫ ዘመኑ ካደረጋቸው 47 ውድድሮች 45ቱን አሸንፏል፡፡ የተሸነፈባቸው ሁለት ውድድሮች የመሃመድ አማን ሁለት አስደናቂ ድሎች ናቸው፡፡ የመጀመርያው በ2011 እኤአ ላይ በጣሊያኗ ከተማ ሬቲ ያሸነፈበት ሲሆን በወቅቱ ዴቪድ ሩዲሻ ለመጀመርያ ጊዜ የተሸነፈው ከ34 ተከታታይ ድሎች በኋላ ነበር፡፡ ሁለተኛው ደግሞ በ2012 እኤአ ላይ በዙሪክ የተካሄደ የዳይመንድ ሊግ ውድድር ሲሆን በዚህ ወሳኝ ትንቅንቅ ለመጀመርያ ጊዜ የዳይመንድ ሊግ ዋንጫን ያሸነፈበት ነበር፡፡

ባርሴሎና ለሊዮኔል ሜሲ ሰሞኑን በሰጠው አዲስ የኮንትራት ውል  ተጨዋቹን የዓለማችን ውዱ  ተከፋይ አድርጎታል፡፡ እስከ 2018 በኑካምፕ ለማቆየት በፈጸመው ስምምነት በየዓመቱ 16.3 ሚሊዮን ፓውንድ ይከፍለዋል፡፡ 20 ሚሊዮን ዩሮ ወይም 27 ሚሊዮን ዶላር ወይም 580 ሚሊዮን ብር  ማለት ነው፡፡ በዓለም ዋንጫ ሰሞን 27 ዓመቱን የሚደፍነው ሜሲ ባለፉት 11 ዓመታት ከባርሴሎና ጋር ለ8ኛ ጊዜ የኮንትራት ውል እና ማራዘሚያዎች መፈራረሙ ነው፡፡
የባርሴሎና የምንግዜም ከፍተኛ አግቢ ሲሆን በ425 ጨዋታዎች 354 ጎሎችን አግብቷል፡፡ 6 የላሊጋ፤ 3 የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ፤ 2 የኮፓ ዴላሬይ እና ሌሎች በድምሩ 21 ዋንጫዎችን አግኝቷል፡፡
በአጠቃላይ ዓመታዊ ገቢ  እስከ 73 ሚሊዮን ዶላር የሚያገኘው  ክርስትያኖ ሮናልዶ ይበልጠዋል፡፡ የሜሲ 65 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡
 ለሊዮኔል ሜሲ እስከ 250 ሚሊዮን ፓውንድ የዝውውር ሂሳብ ይጠራል፡፡

በእግር ኳስ ዓመታዊ ትርፍ 2.8 ቢሊዮን ዶላር የአዲዳስ 1.9 ቢሊዮን ዶላር የናይኪ
አዲዳስና ናይኪ ዓለም ዋንጫው ገና ወራት ሲቀሩት በገበያ ዘመቻቸው ከባድ ትንቅንቅ ውስጥ ገብተዋል፡፡ ሁለቱ ኩባንያዎች በእግር ኳሱ የማልያ ትጥቅ አቅራቢነት ከ5 ቢሊዮን ዶላር በላይ በየዓመቱ ያንቀሳቅሳሉ፡፡ በከፍተኛ የቴክኖሎጂ እገዛ የተመረጡ ታኬታዎችና ማልያዎችን በማቅረብ ፉክክራቸውን ያጧጡፋሉ፡፡
ናይኪ ለዓለም ዋንጫው ያቀረበው ታኬታ የቅርጫት ኳስና የሩጫ ጫማዎች የተሰሩባቸውን ቴክኖሎጂ አጣምሮ የያዘው “ማጂስታ” ነው፡፡ ኢኒዬስታና ማርዮ ጎትዜ በዚህ ታኬታ አሠራር ላይ የሃሳብ ተሳታፊ ነበሩ፡፡ የናይኪ “ማጂስታ” ታኬታ ዋጋ 275 ዶላር ነው፡፡ አዲዳስም “አዲዜሮ ኤፍ50” በሚል ስያሜ በሊዮኔል ሜሲ የሚተዋወቁትን የታኬታ ምርቶች ለዓለም ዋንጫው ይዞ ቀርቧል፡፡ የገበያ ዋጋቸው 270 ዶላር አካባቢ ነው፡፡የዓለም ዋንጫዋን ኳስ “ብራዙካ” ያቀረበውም አዲዳስ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት የዓለማችን ግዙፉ የስፖርት ትጥቅ አምራች ኩባንያ በዓለም ገበያ 17% ድርሻ የያዘውና 25 ቢሊዮን ዶላር ዓመታዊ ገቢ ያስመዘገበው የአሜሪካው ናይኪ ነው፡፡ የጀርመኑ ኩባንያ አዲዳስ በ12% የገበያ ድርሻ እና በ20 ቢሊዮን ዶላር ዓመታዊ ገቢ ይከተለዋል፡፡
አዲዳስ  ከዓለም ዋንጫ ውድድሮች እና በአጠቃላይ በእግር ኳስ ስፖርት የቅርብ አጋር ሆኖ ሲሰራ ከ66 ዓመታት በላይ አስቆጥሯል፡፡ በአንፃሩ ናይኪ ከዓለም ዋንጫ እና ከእግር ኳስ ስፖርት ጋር መንቀሳቀስ ከጀመረ ገና 20 ዓመቱ ነው፡፡
በ20ኛው ዓለም ዋንጫ ላይ ናይኪ የ10 ብሔራዊ ቡድኖችን ትጥቅ ሲያቀርብ የአዲዳስ 9 ናቸው፡፡ ፑማ ለ8 ብሔራዊ ቡድኖች ትጥቅ በማቅረብ 3ኛ ደረጃ አለው፡፡  
የዓለም ኮከብ ተጨዋች ክርስቲያኖ ሮናልዶ የናይኪ ታኬታዎች ዋና አምባሣደር ሲሆን የብራዚልና የፖርቱጋል ብሄራዊ ቡድኖች ሙሉ ትጥቅ ከሚወስዱት ይጠቀሳሉ፡፡  የስፔንና የጀርመን ብሔራዊ ቡድኖች ደግሞ የአዲዳስ ዋና ደንበኞች ሆነው ሲጠቀሱ በፊፋ የዓለም ኮከብ ተጨዋች ተብሎ ለ4 ጊዜያት የተመረጠው ሊዩኔል ሜሲ የአዲዳስ ትጥቆች ዋና አምባሳደር ነው፡፡ ፡፡
በኢንተርኔት የማህበረሰብ ድረገፆች በቀጠለው የሁለቱ ኩባንያዎች ዘመቻ ናይኪ ብልጫ ሲኖረው 36 ሚሊዮን የፌስ ቡክ ወዳጆች፣ እንዲሁም 8.8 ቢሊዮን የትዊተር ተከታታዮች በማስመዝገቡ ነው፡፡ አዲዳስ 17 ሚሊዮን የፌስ ቡክ ወዳጆች እና 9.4 ሚሊዮን የትዊተር ተከታታዮች አሉት፡፡

የዓለማችን የረጅም ርቀት ምርጥ አትሌቶች የሆኑት  ቀነኒሣ በቀለ እና ጥሩነሽ ዲባባ በጐዳና ላይ ሩጫዎች ስኬታማ እየሆኑ ናቸው፡፡  ባለፈው ሳምንት  በእንግሊዝ በተካሄደው የቡፓ ግሬት ማንቸስተር ራን በ10 ኪ.ሜ የጐዳና ላይ ሩጫ በሁለቱም ፆታዎች አሸናፊ ሆነዋል፡፡
አትሌት ቀነኒሣ በቀለ በወንዶች ምድብ ያሸነፈው ርቀቱን በ28.23 ደቂቃዎች በመሸፈን ነበር፡፡ የዓለም ማራቶን ሪኮርድ ባለቤቱን ኬንያዊው ዊልሰን ኪፕሳንግ በ5 ሰኮንዶች በመቅደም አስከትሎት ገብቷል፡፡ ይህ ውጤት  ሁለቱ አትሌቶች ለመጀመርያ  በማራቶን የሚገናኙበትን ሁኔታ አጓጊነት ጨምሮታል፡፡ ዊልሰን ኪንሳንግ በ2013 አጋማሽ ላይ በበርሊን ማራቶን 2 ሰዓት ከ03 ደቂቃ ከ23 ሰከንዶች በሆነ ጊዜ  የዓለም ሪከርድን ያስመዘገበ ነው፡፡ ከወር በፊት ቀነኒሳ የመጀመርያ ማራቶኑን በፓሪስ ሮጦ የቦታውን ሪከርድ አስመዝግቦ ሲያሸንፍ በዚያው ሰሞን ዊልሰን ኪፕሳንግም በለንደን ማራቶን በተመሳሳይ የቦታውን ሪከርድ አስመዝግቦ ማሸነፉ ይታወሳል፡፡ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ በቀጣዩ የውድድር ዘመን ከዊልሰን ኪፕሳንግ ጋር በማራቶን መሮጥ ፍላጎት እንዳለውም የሰጠው፡፡ ከቡፓ ግሬት ማንችስተር ራን በኋላ ቀነኒሳ በሰጠው አስተያየት አሁን ትኩረቱ ወደ ትራክ ውድድሮች መመለስ እንደሆነ ገልፆ፤ በተለይ በ10ሺ ሜትር አንድ ውድድር ማድረግ እንደሚፈልግ አስታውቋል፡፡ በሌላ በኩል በሴቶች ምድብ ደግሞ አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ ርቀቱን በ32 ደቂቃ ከ20 ሰኮንዶች በመሸፈን አሸንፋለች፡፡ ጥሩነሽ  በቡፓ ግሬት ማንችስተር ራን ዘንድሮ ያሸነፈችው ለሁለተኛ ግዜ  ሲሆን አምና ውድድሩን ስታሸንፍ በ30.49 ደቂቃዎች በሆነ ጊዜ የቦታውን ሪከርድ አስመዝግባ ነበር ፡፡
ከወር በፊት በፓሪስ እና ለንደን በተካሄዱ የማራቶን ውድድሮች የመጀመርያ ማራቶናቸውን የሮጡት ቀነኒሳ በቀለ እና ጥሩነሽ ዲባባ አጀማመራቸው ስኬታማ እነደሆነ ያመለከቱ መረጃዎች፤ በሚቀጥሉት ዓመታት በሁለቱም ፆታዎች የተያዙ የዓለም ማራቶን ሪከርዶችን ለመስበር ግንባር ቀደም እጩዎች ስለመሆናቸውም ግምት ሰጥተዋል፡፡ የመጀመርያ ማራቶኑን በፓሪስ የሮጠው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ የቦታውን ሪከርድ ካሸነፈ በኋላ ያሳየው ብቃት በሚቀጥሉት 5 ዓመታት የዓለም ማራቶን ሪከርድን ሊሰብር እንደሚችል ያመለክታል በሚል በርካታ ዘገባዎች አውስተውለታል፡፡ አትሌት ቀነኒሳ የፓሪስ ማራቶንን ሲያሸንፍ ርቀቱን የሸፈነበት 2 ሰአት ከ05 ደቂቃ ከ4 ሰኮንዶች ነበር፡፡ በረጅም ርቀት 5 የዓለም ሻምፒዮና እንዲሁም 3 የኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳልያዎች ያሏት ጥሩነሽ ዲባባ ደግሞ ከወር በፊት በለንደን የመጀመርያ ማራቶን ውድድሯን  በሁለት ሰዓት ከ20 ደቂቃ ከ54 ሰኮንዶች በሆነ ጊዜ በሶስተኛ ደረጃ ጨርሳለች፡፡ ይሄው የጥሩነሽ ሰዓት በማራቶን የመጀመርያ ሩጫ ከተመዘገቡ ፈጣን ሰዓቶች በሶስተኛ ደረጃ ተመዝግቧል፡፡

ሚድሮክ ኢትዮጵያ የአትሌቲክስ ክለብ ይመሠረታል
ሚድሮክ ኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ግሩፕ በሚቀጥለው ዓመት የአትሌቲክስ ስፖርት ክለብ እንደሚመሰርት አስታወቀ፡፡  በሚድሮክ ኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ስር ባሉ ኩባንያዎች መካከል ዘንድሮ ለ11ኛ ጊዜ የተካሄደው ዓመታዊ የስፖርት ውድድር ሰሞኑን ተጠናቅቋል፡፡ በዚሁ ዓመታዊ የስፖርት ውድድር መዝጊያ ስነስርዓት ላይ ንግግር ያደረጉት ዋና ስራ አስፈፃሚው ዶ/ር አረጋ ይርዳው የሚድሮክ ኢትዮጵያ የአትሌቲክስ ክለብ ለመመስረት የተወሰነው በስፖርቱ እድገት ላይ ተገቢውን  ድርሻ ለማበርከት ታቅዶ ነው ብለዋል፡፡ የመቻሬ የእግር ኳስ ክለብ ወደ ብሔራዊ ሊግ ደረጃ ለማድረስ ከፍተኛ ጥረት እንደሚያደርግም ዋና ስራ አስፈፃሚው ተናግረዋል።

       ዛሬ በፖርቱጋል ዋና ከተማ ሊዝበን በሚገኘው  ኢስታድዮ ዳ ሉዝ ስታድዬም ለ59ኛው የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ  ዋንጫ  ሁለቱ የማድሪድ ከተማ ክለቦች ሪያልና አትሌቲኮ ማድሪድ  ይፋጠጣሉ፡፡ በሻምፒዮንስ ሊግ ታሪክ ለፍፃሜ ጨዋታ የአንድ ከተማ ክለቦች ሲገናኙ  ለመጀመርያ ጊዜ  ነው፡፡ የዋንጫ ጨዋታው በ200 አገራት የቀጥታ ቴሌቭዢን ስርጭት ሲኖረው እስከ 1 ቢሊዮን ተመልካች እንደሚያገኝ ተገምቷል፡፡ የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር ዋንጫውን ለሚያሸንፈው ክለብ 10.5 ሚሊዮን ዩሮ እንዲሁም ለሁለተኛው ክለብ ደግሞ 6.5 ሚሊዮን ዩሮ ያበረክታል፡፡ በአጠቃላይ ሁለቱ የማድሪድ ክለቦች እስከ ፍፃሜው በነበራቸው ግስጋሴ ከቴሌቭዥን ስርጭት መብት፤ ከሜዳ ገቢ እና ከተለያዩ ንግዶች በነፍስ ወከፍ እስከ 55 ሚሊዮን ዩሮ ድርሻ ይኖራቸዋል፡፡ በሻምፒዮንስ ሊጉ ከዋንጫው ጨዋታ በፊት በተደረጉት 124 ጨዋታዎች 357 ጎሎች ሲመዘገቡ፤ ኮከብ ግብ አግቢነቱን የሪያል ማድሪዱ ክርስትያኖ ሮናልዶ በ16 ጎሎች እየመራው ነው፡፡
ሁለቱ የማድሪድ ከተማ ክለቦች እርስ በራስ የሚገናኙበት ጨዋታ “ኤል ደርቢ ማድሪሊያኖ” በሚል መጠሪያ ሲታወቅ ከዛሬው የዋንጫ ጨዋታ በፊት  264 ጨዋታዎች ተደርገውበታል፡፡  በ143 ሪያል ማድሪድ ሲያሸንፍ በ64  ጨዋታዎች ያሸነፈው  አትሌቲኮ ማድሪድ ነው፡፡ በ57 ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል፡፡ ኤልደርቢ ማድሪሊያኖ አንድ ክፍል ዘመን ያስቆጠረ የእግር ኳስ ትንቅንቅ ነው፡፡  ባለፉት አስር ዓመታት ይህን ታላቅ ደርቢ ሪያል ማድሪድና ባርሴሎና የሚገናኙበት ኤልክላሲኮ ሸፍኖት  ቆይቷል፡፡
 የዓለም ሃብታሙ ክለብ ሪያል ማድሪድ ዛሬ ዋንጫውን ካነሳ በውድድሩ ታሪክ ለ10ኛ ጊዜ ይሆናል፡፡ ከዚህ ቀደም 13 ጊዜ ለፍፃሜ ቀርቦ 9 ዋንጫዎችን ወስዷል፡፡ የመጨረሻው ድሉ ከ12 ዓመት በፊት ነው፡፡ በአንፃሩ አትሌቲኮ የሚያገኘው ድል በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ  ነው፡፡ ከ40 ዓመት በፊት ብቸኛውን የፍፃሜ ጨዋታ አድርጎ  በባየር ሙኒክ 5ለ0 ተሸንፎ ዋንጫውን አልምጦታል፡፡ ሪያል ማድሪድ ኮፓ ዴ ላሬይን ቢያሸንፍም የውድድር ዘመኑን ውጤታማ ለማለት የግድ የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ ያስፈልገዋል፡፡ ባለፈው ሳምንት   ከ18 ዓመት በኋላ  የላሊጋ ዋንጫን ላገኘው አትሌቲኮ የማድሪድ ከተማ በ200ሺ ደጋፊዎች ተጥለቅልቃ ነበር ፡፡ የአውሮፓን ክብር ደርቦ ካሸነፈ  ደግሞ በከተማዋ የሚኖረው ፌሽታ ሚሊዮኖችን ያሳትፋል ተብሏል፡፡
ሪያል ማድሪድ በአገር ውስጥ ውድድሮች ከ60 በላይ፤ በአውሮፓ ደረጃ ከ11 በላይ ዋንጫዎችን የሰበሰበ ሲሆን አትሌቲኮ  በአገር ውስጥ ውድድሮች 24 በአውሮፓ ደረጃ ደግሞ 5 ዋንጫዎች አሉት፡፡
በስፔን ፕሪሚዬራ ሊጋ ሪያል ማድሪድ  32 ጊዜ ሻምፒዮን ሲሆን አትሌቲኮ ዘንድሮ 10ኛውን የሻምፒዮናነት ክብር አግኝቷል፡፡ በኮፓ ዴላሬይ ሪያል ማድሪድ 19 ዋንጫ ሲወስድ አትሌቲኮ ማድሪድ 10 አለው፡፡ሪያል ማድሪድ ለውድድር ዘመኑ የነበረው በጀት 515 ሚሊዮን ዩሮ ሲሆን በ4 እጥፍ የሚያንሰው የአትሌቲኮ በጀት 120 ሚሊዮን ዩሮ ነው፡፡
ሪያል ማድሪድ ማልያውን ከፍተኛ ስፖንሰርሺፕ ሲያገኝበት አትሌቲኮ ማድሪድ ለ2 የውድድር ዘመን ስፖንሰር አጥቶ የአዘርባጃን መፈክር ላንድ ኦፍ ፋየርን ለጥፎ ቅናሽ ገቢ አለው፡፡
ሪያል ማድሪድ  የተመሰረተው ከ112 ዓመታት በፊት ሲሆን በዘንድሮ አጠቃላይ የተጨዋቾች ስብስቡ በትራንስፈር ማርኬት 505 ሚሊዮን ዩሮ የዋጋ ተመን ሲኖረው  ከተመሰረተ ከ111 ዓመታት የሚሆነው የአትሌቲኮ ማድሪድ የተጨዋቾች ስብስብ ተመኑ 282 ሚሊዮን ዩሮ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን (ሉሲዎቹ) በኢኳቶሪያል ጊኒ አስተናጋጅነት በ2007 ዓ.ም. ለሚከናወነው 9ኛው የአፍሪካ ዋንጫ  ለማለፍ  ጥቋቁሮቹን ንግስቶች ከተባሉት የጋና አቻቸው  በደርሶ መልስ ይፋለማሉ፡፡ የመጀመርያው ጨዋታ ነገ በአዲስ አበባ ስታድዬም የሚደረገው ነው፡፡ ሉሲዎቹ በዚሁ ፍልሚያ በሰፊ የግብ ልዩነት ማሸነፍ ከቻሉ የማለፍ እድላቸውን ያጠናክራሉ፡፡ ሁለት የወዳጅነት ጨዋታዎችን ከካሜሮንና ከናሚቢያ ብሔራዊ ቡድኖች ጋር የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን በሜዳቸው እና ከሜዳ ውጭ አድርገዋል፡፡ በጥሩ ደረጃ አቋማቸውን በመፈተሽም አስተማማኝ ብቃት ላይ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን ከፕሪምየር ሊግ 12 ክለቦች የተወጣጡና 16 አዳዲስ ተጨዋቾች በሚገኙበት ቡድን በአጠቃላይ 37 ተጨዋቾች አሰባስቦ ቢያንስ ለወር ያህል ጠንካራ ዝግጅት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡

የተራ ሞባይሎች ተፈላጊነት እየቀነሰ፤ “የስማርት ፎን” ሽያጭ ባለፈው አመት አንድ ቢሊዮን ያህል የደረሰ ሲሆን፤ የምርጦች ምርጥ ሆነው የገነኑት የአፕል አይፎን እና የሳምሰንግ ጋላክሲ ሞባይሎች ላይ ፉክክሩ አይሏል - በየገበያው እና በየፍርድ ቤቱ።
አፕል እስካሁን፣ ግማሽ ቢሊዮን አይፎኖችን ሸጧል። ቆየት ብሎ ወደ “ስማርትፎን” ገበያ የገባው ሳምሰንግ፣ ምርቶቹን በፍጥነት በማስፋፋት ከ200 ሚሊዮን በላይ ጋላክሲ ሞባይሎችን ለመሸጥ ችሏል።
አፕል ባለፈው መስከረም ወር ለገበያ ያቀረበው አይፎን 5፤ በመጀመሪያዎቹ ሶስት ቀናት 9 ሚሊዮን ያህል ተሽጦለታል። ከጊዜ ወደ ጊዜ ሽያጩ እየጨመረ፣ ባለፉት አስራ ሁለት ወራት ብቻ፤ 160 ሚሊዮን የተለያዩ የአይፎን ሞባይሎችን ለመሸጥ ችሏል። ነገር ግን፤ የሳምሰንግ ጋላክሲ ብርቱ ተፎካካሪ ሆነውበታል።
ከአይፎን በሶስት አመት ዘግይቶ የመጣው የሳምሰንግ ጋላክሲ፤ በፍጥነት እየተሻሻለ ከጋላክሲ ኤስ1 ዘንድሮ ጋላክሲ ኤስ5 ደርሷል። ባለፈው ወር  ለገበያ የቀረበው ጋላክሲ ኤስ5፤ ከአይፎን 5 ያልተናነሰ ገዢ እያገኘ እንደሆነ ተዘግቧል።



በሃይማኖት አክራሪነቱ ምክንያት ተቃውሞ የገጠመውን “የሙስሊም ብራዘርሁድ መንግስት” በመገልበጥ ስልጣን የያዙት ጄ/ል አልሲሲ፣ በግብፅ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ያለ ብዙ ፉክክር በሰፊ ልዩነት ያሸንፋሉ ተብሏል።
በእርግጥ ምርጫው የሚጀመረው  ሰኞ ነው። ነገር ግን፤ በውጭ የሚኖሩ ግብፃዊያን ከወዲሁ ድምፅ ሰጥተው ቆጠራ ተካሂዷል። በዚሁ ቆጠራ፤ ጄ/ል አልሲሲ፣ 94.5% ድምፅ ሲያገኙ፣ ወደ ሶሻሊዝም የሚያዘነብሉ ተቀናቃኛቸው 5.5% ድምፅ ማግኘታቸውን ዎልስትሪት ጆርናል ዘግቧል።
ሰኞ በሚጀመረው የአገር ውስጥ ምርጫም አልሲሲ አብዛኛውን ድምፅ እንደሚያገኙ ከመራጮች የተሰበሰበሰ አስተያየት ይጠቁማል። በእርግጥ፤ በጭራሽ ድምፅ ላለመስጠትና ላለመምረጥ የወሰኑ ግብፃዊያን ብዙ ናቸው። ከፊሎቹ ጄነራሉን በጠላትነት የሚቃወሙ የሙስሊም ብራዘርሁድ ደጋፊዎች ናቸው። ከፊሎቹ ደግሞ፤ የተሻለ አማራጭ የያዘ ደህና ፓርቲና ደህና ፖለቲከኛ በማጣት ከምርጫው ራሳቸውን አግልለዋል። ከእነዚህ ውጭ የሆነው አብዛኛው ግብፃዊ መራጭ፤ ለጊዜው ለአገሪቱ የሚበጃት ጄነራል አልሲሲን የመሰለ ጨከን ያለ መሪ ነው ብለው ያምናሉ።
በሌላ በኩል፤ በመፈንቅለ መንግስት ስልጣን ይዘው ከሰላሳ አመት በላይ ግብፅን የገዟት ሆስኒ ሙባረክ፣ 3 ሚሊዮን ዶላር ገደማ የመንግስት ገንዘብ አጭበርብረዋል በሚል ሰሞኑን የሶስት አመት እስር ተፈርዶባቸዋል። ልጃቸው ደግሞ የአራት አመት እስር። ከዚሁም ጋር የ14 ሚሊዮን ዶላር ቅጣት ተወስኖባቸዋል።