Administrator
“የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የዕድሜ ማራዘምያ ነው”- እናት ፓርቲ
“እጅ መንሻ የሚቀበሉ” ባለስልጣናቱን መንግስት አደብ እንዲያስገዛ ጠይቋል
መንግስት በቅርቡ ተግባራዊ ያደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያው መድሃኒት ሳይሆን የዕድሜ ማራዘምያ ክኒን ነው ያለው እናት ፓርቲ፤ “እጅ መንሻ መቀበል ሥራዬ ብለው የያዙትን ባለስልጣናቱን መንግስት አደብ እንዲያስገዛ አሳስቧል ያስገዛ” ሲል እናት ፓርቲ አሳሰበ። ፓርቲው ባለፈው ሰኞ ነሐሴ 20 ቀን 2016 ዓ.ም. ባወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ፤ አጠቃላይ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ትችቷል።
“በያለፉት ስድስት ዓመታት ኢኮኖሚው ወዴት እንደሚሄድ ፍኖተ ካርታ ባለመቀመጡ ለትንበያ እንኳን እስከሚያስቸግር ድረስ ሲታመስ ቆይቷል፡፡” ያለው ፓርቲው፣ “በቅርበት ለሚከታተል ሰው ግን አንድ ቀን የማይወጣው ማጥ ውስጥ ገብቶ ኢኮኖሚው በዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ጫና ውስጥ እንደሚወድቅ ሳይታለም የተፈታ ነበር፡፡” ብሏል።
“የገንዘብ የመግዛት አቅም መዳከም፣ ለምርት ግብዓት የሆኑት እንደማዳበሪያ፣ ትምሕርትና ጤና መሰል አገልግሎቶች ላይ የሚደረገው ድጎማ መቆም በህብረተሰቡ ላይ መጠነ ሰፊ ጫና እያሳረፈ ነው” የሚለው እናት፤ “ሰሚ በመጥፋቱ የማታ ማታ መንግስት ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት ከነአደገኛ ግዴታዎቹ ብድር ለመውሰድ ተገድዷል” ብሏል።
“እነዚህ ዓለምአቀፍ አበዳሪ ድርጅቶች ለደሃ የሚራራ ልብ የላቸውም። አሁን የአንድ ወታደር፣ የመንግስት ሰራተኛ፣ የአስተማሪ ደመወዝ በግማሽ ወርዷል። 11 ሺህ ብር ይከፈላቸው የነበሩ ሰራተኞች ደመወዛቸው 500 ዶላር ነበር፤” በአሁኑ የዶላር ምንዛሪ ይህ ደመወዝ 100 ዶላር ወይም ከዚያ በታች ሆኗል ብሏል በመግለጫው።
“የሚፈራው ማሕበራዊ ቀውስ ሊታከም ከማይችልበት ደረጃ ከመድረሱ በፊት መንግስት የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራውን እንደገና እንዲያጤነው” መንግስትን ያሳሰበው እናት ፓርቲ፣ “መንግስት፤ የሰራተኛውና ደመወዝተኛው የዛሬ ስድስት ዓመቱ የኑሮ ደረጃን የሚመልሰውን የደመወዝ ጭማሪ በአስቸኳይ እንዲያደርግ” ጥሪውን አቅርቧል።
በናይጄሪያ፣ ኬንያ፣ ሱዳንና ግብጽን ጨምሮ በተለያዩ የዓለማችን አገራት “ዕድገትን ለማነሳሳት” ሲባል የተፈጸሙ የገንዘብ አቅርቦት መጨመርን የመሳሰሉ የማስፋፊያ የገንዘብ ፖሊሲዎች የተተለሙባቸውን የስራ አጥነትን ማስወገድ ዓላማ ሳያሳኩ፣ ከፍተኛ የዋጋ ንረት ማስከተላቸውንም ነው የፓርቲው መግለጫው የጠቀሰው። አያይዞም፣ “መንግስት ራሱ ፈቅዶና ፈርሞ ያመጣው ፖሊሲ የፈጠረውን ምስቅልቅል በነጋዴው ማሕበረሰብ ላይ እያመካኘ፣ ሱቅ ማሸግና እጅ መንሻ መቀበል ‘ስራዬ’ ብለው የያዙትን ባለስልጣናቱን አደብ እንዲያስገዛ” እናት ፓርቲ አሳስቧል፡፡
በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጾታዊ ጥቃቶችን ለመቀነስ የወንጀል ሕጉ መሻሻል እንደሚገባው ተነገረ
በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጾታዊ ጥቃቶችን ለመቀነስ የወንጀል ሕጉን ጨምሮ ሌሎች ተያያዥ ሕጎች መሻሻል እንደሚገባቸው ተነግሯል። የኢትዮጵያ የሕግ ባለሞያ ሴቶች ማሕበር የሕግ አማካሪ ወይዘሪት ሕይወት ሙሴ ከአዲስ አድማስ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ በወንጀል ሕጉ ላይ ያልተጠቀሱ ጾታዊ ጥቃቶች በመኖራቸው ሳቢያ ለወንጀል ድርጊቶቹ ተመጣጣኝ ፍርድ እየተሰጠ አለመሆኑን አመልክተዋል።
ወይዘሪት ሕይወት፤ ማሕበራቸው በወንጀል ሕጉ መሻሻል ያለባቸውን ክፍተቶች በመመርመር፣ የሕግ ለውጥ እንዲደረግ የተለያዩ ስራዎችን አጠናቅቆ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለማስረከብ በዝግጅት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል። አክለውም፤ የወንጀል ሕጉና ተያያዥ ፖሊሲዎች ተፈጻሚነታቸው እንዲጠናከር ማሕበራቸው እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን ያብራሩት የሕግ ባለሙያዋ፣ እነዚሁ ሕጎችና ፖሊሲዎች ተሻሽለው ለሌሎች አስተማሪ ውጤትን እንዲያመጡ የተለያዩ ስራዎች በመሰራት ላይ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
“ተጎጂዎች ወደ ማሕበራችን ከማመልከታቸው በፊትም ሆነ ጥቃቶች እንደደረሱ መረጃዎች ሲመጡ ወይም ተጎጂዎቹ ሲያመለክቱ፣ የማሕበራችን ባለሞያዎች ፖሊስ ጣቢያ ድረስ በመሄድ ድጋፍ ያደርጋሉ። ፍርድ ቤት በመገኘት የጉዳዩን ሂደት ይከታተላሉ። በሕግ አግባብ ውሳኔ መሰጠቱን ከመከታተል ባለፈ፣ ከባለጉዳዮቹ ጋር ጉዳዩ ዳር እስኪደርስ ድረስ የክትትል ስራ እንሰራለን።” ሲሉ ማሕበራቸው ሌሎች ለተጎጂ ሴቶች የሚያደርገውን ድጋፍ ዘርዝረዋል።
ማሕበራቸው የወንጀል ሕጉ ላይ በርካታ ስራዎች መሰራት “ይገባቸዋል” ብሎ እንደሚያምን የጠቆሙት ወይዘሪት ሕይወት፤ “የቤተሰብ ሕጉና (የስራ ሕጉን) ጨምሮ -- ተያያዥ ሕገ መንግስታዊ አንቀጾችን ስንመለከት የሴቶችን መብት ያካተቱ የተዘረዘሩ ነጥቦች አሉ። ይሁንና ተፈጻሚነታቸው እጅግ አናሳ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
የወንጀል ሕጉ አስተማሪ ቅጣት እንዲኖረውና በሕጉ ላይ “ይስተዋላሉ” ያሏቸው ክፍተቶች ተመርምረው እንዲስተካከሉ የኢትዮጵያ የሕግ ባለሞያ ሴቶች ማሕበር ዕንቅስቃሴዎችን በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ነው የገለጹት።
በቅርቡ በማሕበራዊ ሚዲያዎች ላይ የመነጋገሪያ ርዕስ ሆኖ ባሰናበተው በሕጻን ሔቨን ዓወት ላይ የተፈጸመው ጾታዊ ጥቃት ዙሪያ ማሕበራቸው ምን ዓይነት ዕንቅስቃሴ እያደረገ እንደሆነ ከአዲስ አድማስ የተጠየቁት፣ ወይዘሪት ሕይወት፣ ማሕበራቸው ጉዳዩ ሚዲያ ላይ ከመውጣቱ በፊት እንደሚያውቅና በአማራ ክልል፣ የኢትዮጵያ የሕግ ባለሞያ ሴቶች ማሕበር የባሕር ዳር ከተማ ቅርንጫፍ ይከታተለው እንደነበር ጠቅሰዋል። የሕጻን ሔቨንን እናት ከማግኘት ባለፈ፣ ማሕበራቸው የወንጀል ድርጊቱን የፍርድ ሂደት ሲከታተል መቆየቱንም የሕግ ባለሞያዋ አስረድተዋል።
“በተከሳሽ ላይ የተፈረደው የ25 ዓመት ፍርድ ‘ይበቃል’ የሚያስብል አይደለም። ያንሳል። ከዚህ የበለጠ ተጠናክረው መቀጠል ያለባቸው ሂደቶች ይኖራሉ። ባለሞያ በመመደብ፣ ጉዳዩ በሚታይበት ችሎት ተገኝቶ ይግባኝ የሚቀርብበት መንገድ ካለ የማየት ስራዎችን ለመስራት እየሞከርን ነው። በሌላ በኩል የተወሰነው ውሳኔ ተፈጻሚነት እንዲኖረው ማሕበሩ እስከመጨረሻው ይከታተላል” ብለዋል።
በኢትዮጵያ ሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጾታዊ ጥቃቶች መባባስ ምክንያቶች አንዱ የወንጀል ሕጉ ክፍተትና የቅጣቱ አናሳ መሆን “ነው” የሚሉት ወይዘሪት ሕይወት፣ ሕጉ ሲወጣ በነበረበት ወቅት ላይ የተወሰነ በመሆኑ አሁን ላይ የሚወሰኑ ቅጣቶችን ተመጣጣኝነት ጥያቄ ውስጥ ማስገባቱን ተናግረዋል። ለዚህም እንደአብነት የሚጠቅሱት አሲድ በፊትና በሌሎች የሰውነት ክፍሎች ላይ በመድፋት የሚፈጸመውን ጥቃት ሲሆን፣ ለዚህም ጥቃት የሚመጥን ቅጣት በወንጀል ሕጉ ውስጥ ባለመኖሩ ምክንያት ለወንጀል ድርጊቱ መስፋፋት ሰበብ መሆኑን አመልክተዋል።
“ወቅቱን ያማከለ ድንጋጌ መኖር አለበት። ማሕበረሰቡ ተጠያቂነትንና የሃላፊነት ስሜትን ማጎልበት አስፈላጊ ነው። ኢትዮጵያ የተቀበለቻቸው ድንጋጌዎች አሉ። የአቅም ግንባታ ስልጠና ያስፈልጋል።” ሲሉ፣ የማሕበራቸውን የመፍትሔ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።
በሌላ በኩል፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) በሴቶች እና ሕጻናት ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች “አሳስቦኛል” ያለ ሲሆን፣ “ወንጀል ፈጻሚዎች አስተማሪና ተመጣጣኝ ቅጣት ባለመቀጣታቸው እና ወንጀል ሰርቶ ያለመያዝ ልምድ በመበራከቱ” የጥቃቶቹ መስፋፋት መንስዔ መሆናቸውን ጠቁሟል። ጉባዔው ይህንን የጠቆመው ባለፈው ረቡዕ ነሐሴ 21 ቀን 2016 ዓ.ም. ባወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው።
ከዚህም ጋር በተያያዘ ኢሰመጉ “የፌደራል መንግስት ከወንጀል ሕጉ ዓላማና ግብ አንፃር የሴቶችና ሕፃናትን አስገድዶ መድፈር እና ጥቃት የሚመለከተው ክፍል ላይ ተገቢውን ጥናት በማድረግ፣ ሕጉ ለሚፈጸሙት ወንጀሎች ተመጣጣኝና አስተማሪ በሆነ መልኩ እንዲሻሻል ጥረት እንዲያደረግ” ጥሪውን አቅርቧል። በተመሳሳይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ የሴቶቸና ህጻናት መብትን የሚመለከቱ ሕግና ፖሊሲዎች እንዲጸድቁ ተገቢውን ድጋፍ እንዲያደረግም ጉባዔው ጥሪ አድርጓል።
በስልጤ ዞን በደረሰው የጎርፍ አደጋ ከ1ሺ በላይ አባወራዎች ተፈናቅለዋል
”ለተፈናቃዮች በቂ እርዳታ እየቀረበ አይደለም”
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል፣ ስልጤ ዞን በደረሰው የጎርፍ አደጋ ከአንድ ሺህ በላይ አባወራዎች መፈናቀላቸው ተገለጸ። ለተፈናቃዮች እየቀረበ ያለው ዕርዳታ ከብዛታቸው ጋር የሚመጣጠን አለመሆኑም ተጠቁሟል።
የዞኑ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ወይዘሮ ወሲላ አሰፋ፤ የጎርፍ አደጋው የደረሰው በሁለት ወረዳዎች፣ በስምንት ቀበሌዎች ላይ እንደሆነ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል። ችግሩ ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ መፍትሔ ለማምጣት ርብርብ እየተደረገ ነው ያሉት ሃላፊዋ፣ ሰዎቹን ከአደጋ ቀጣና የማውጣትና እንዲጠለሉ የማድረግ ስራ መከናወኑን አመልክተዋል።
ከአንድ ሺህ በላይ አባወራዎች የጎርፉ አደጋ ከደረሰባቸው አካባቢዎች እንዲወጡ የተደረጉ ሲሆን፤ ተፈናቃዮቹ በትምሕርት ቤቶች፣ በአርሶ አደር ማሰልጠኛ ተቋምና ዘመዶቻቸው ዘንድ እንዲጠለሉ መደረጉን ሃላፊዋ ገልፀዋል። ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶች ከክልል ጀምሮ የዞን፣ የወረዳና ሌሎች አካላትን በማስተባበር ለተፈናቃዮቹ እየቀረቡ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
“ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ስራዎች ተጀምረዋል። የችግሩ መነሻ የመኸር ዝናብ መጠን እጅግ በጣም ስለጨመረ ደለል የሚወርድበትን አቅጣጫ ውሃ ሞልቶታል። ጥናት የማጥናትና የሚመለከታቸው ሴክተር መስሪያ ቤቶች ቦታውን እንዲያዩ የማድረግ፣ ቀጣይ የዕቅዳቸው አካል እንዲያደርጉ እየሰራን ነው” ብለዋል፣ ወይዘሮ ወሲላ።
የተፈናቃዮቹ ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሆኑን ሃላፊዋ ያስረዱ ሲሆን፣ “አስፈላጊውን ዕርዳታ ለተፈናቃዮቹ ማቅረብ ያስፈልጋል” ሲሉ ተናግረዋል። አክለውም፣ “ከተፈናቃዮች ብዛት ጋር የምናቀርበው ዕርዳታ በቂ አይደለም፤ የተለያዩ አካላት እንዲያግዙን ጥሪ አቅርበናል።
የባንክ ሀሳብ ተከፍቶ ዕገዛ እንዲሰባሰብ እየተደረገ ነው። ክልሉ ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶችን እያቀረበ እያገዘን ነው” ብለዋል።
ሌሎች መንግስታዊ ያልሆኑ ግብረሰናይ ድርጅቶች ዕርዳታ እያቀረቡ እንደሆነ የተጠየቁት ወይዘሮ ወሲላ ሲመልሱ፣ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ድጋፋቸውን እየለገሱ ነው።
ሌሎችም ሁኔታውን እያዩ ሊለግሱን ይችላሉ” ብለዋል።
በዞኑ በደረሰው የጎርፍ አደጋ በበልግና መኽር የለማ አንድ ሺህ ሄክታር ላይ የነበረ ሰብል በውሃ መጥለቅለቁን የጠቆሙት ሃላፊዋ፤ “ዝናቡ በዚሁ ከቀጠለ ሰብሉ ከጥቅም ውጭ ይሆናል።” ሲሉ ስጋታቸውን ገልፀዋል።
የአዲስ ዓመት ባዛርና ኤክስፖ ተከፈተ
አስመጪዎች እና አምራቾች ከሸማች ሕብረተሰቡ ክፍል እንደሚያገናኝ የታመነበት የአዲስ ዓመት ባዛር እና ኤክስፖ ተመርቆ ተከፍቷል። ባለፈው ሐሙስ ነሐሴ 23 ቀን 2016 ዓ.ም. የተከፈተው ባዛር እና ኤክስፖ እስከ አዲስ ዓመት ዋዜማ እንደሚቆይ ተነግሯል።
በመክፈቻ መርሃ ግብሩ ላይ የባሕል እና ስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ደኤታ ወይዘሮ ነፊሳ አልመሃዲን፣ የባሮክ ኤቨንት ኦርጋናይዘር ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሙሉጌታ ብርሃኑን ጨምሮ ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው ዕንግዶች ተገኝተዋል። ሚኒስትር ደኤታዋ ወይዘሮ ነፊሳ ባደረጉት አጭር ንግግር፤ “ንግግር ለማድረግ ሳይሆን ለሸመታ ነው የመጣሁት” ያሉ ሲሆን፣ የባዛሩ መሪቃል “ስለሰላም” መሆኑን አመልክተው፣ ሚኒስቴር መስሪያ ቤታቸው በሰላም ዙሪያ ከሚሰሩ አካላት ጋር በትብብር ለመንቀሳቀስ ዝግጁ መሆኑን ጠቁመዋል።
በዚህ የአዲስ ዓመት ባዛር እና ኤክስፖ ሸማቹ የሕብረተሰብ ክፍል በዓልን ምክንያት አድርጎ ከሚገጥመው የዋጋ ንረት በተመጣጣኝ እና በቅናሽ ዋጋ ከራሱ ከአምራቹና ከአስመጪው የሚገበያይበት እንደሆነ ተጠቅሷል። የተለያዩ የመዝናኛ፣ የምግብ እና የመጠጥ ፕሮግራሞች እምደሚገኙበት በተነገረለት በዚህ ባዛርና ኤክስፖ፣ ከ2 ሺህ በላይ አስመጪና ሻጮች እንደሚሳተፉበት ተገልጿል።
በባዛርና ኤክስፖው ላይ በቀን ከ7 ሺህ እስከ 10 ሺህ ሸማቾች እንደሚገኙ የተገመተ ሲሆን፣ ዕውቅ የኪነ ጥበብ ባለሞያዎች የሙዚቃ ስራዎቻቸውን ለታዳሚዎች ያቀርባሉ ተብሏል። ኢትዮ ቴሌኮም እና ዳሽን ባንክን ጨምሮ፣ በርካታ ተቋማት ባዛር እና ኤክስፖው አጋር እንደሆኑም ተጠቅሷል።
የፕ/ር እንድሪያስ እሸቴ - ዜና ዕረፍት
ዕውቁ ምሁር ፕ/ር አንድርያስ እሸቴ (ፕ/ር) ባደረባቸው ሕመም በሕክምና ሲረዱ ቆይተው ከትላንት በስቲያ ሐሙስ ነሐሴ 23 ቀን 2016 ዓ.ም. ከዚህ ዓለም በሞተ መለየታቸው ተዘግቧል። እኚሁ ምሁር በአወዛጋቢነታቸው የሚታወቁት ምሁሩ፤ በተለያዩ የአገር ውስጥ እና የውጭ አገር የትምሕርት ተቋማት በመምሕርነት ማገልገላቸው በሰፊው የተወሳላቸው ምሁር ነበሩ።
ፕ/ር አንድርያስ ከአባታቸው ከአቶ እሸቴ ተሰማ እና ወይዘሮ መንበረ ገብረማርያም የካቲት 23 ቀን 1937 ዓ.ም. የተወለዱ ሲሆን፣ ሶስተኛ ዓመታቸውን እስኪደፍኑ ድረስ ከወላጆቻቸው ጋር ቆይተው፣ ከአጎታቸው አቶ ጀማነህ አላብሰው ዘንድ ቀሪ የልጅነት ዕድሜያቸውን አሳልፈዋል። የአጎታቸው የቤተ መጽሐፍት ባለሞያ መሆን በቀሪ የሕይወት ዘመናቸው የሙጥኝ ብለው ለገፉበት ጥልቅ የንባብ ልማዳቸው የራሱን አስተዋጽዖ ማበርከቱን ምሁሩ በአንደበቴቸው የመሰከሩት ዕውነታ ነው። እንዲሁም የታሪክ ተመራማሪው ሪቻርድ ፓንክረስት (ዶ/ር) ቤተሰብ ጥብቅ ወዳጅ መሆናቸውም ምሁራዊ ጎዳናቸውን እንደጠረገላቸው ይጠቀሳል።
ከአንደኛ እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ በዳግማዊ ምኒልክ ትምሕርት ቤት የተማሩት አንድርያስ ገና በልጅነታቸው ባመጡት የላቀ የትምሕርት ውጤት ከቀዳማዊ አጼ ሀይለ ሰላሴ እጅ ሽልማት ተቀብለዋል፡፡
ብሩህ አዕምሮ እና ልዩ የንባብ ፍቅር የነበራቸው ስለነበሩም፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምሕርታቸውን በ16 አመታቸው ሲያጠናቅቁ ባገኙት ነጻ የትምሕርት እድል ወደ አሜሪካን አገር በመሄድ የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል። በዊሊያምስ ኮሌጅ በፍልስፍና የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በ1958 ዓ.ም በማዕረግ ሲያጠናቅቁ፣ ከወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዝዳነት አይዘንሃወር እጅ ዲግሪያቸውን በመቀበል ተመርቀዋል፡፡ ቀጥሎም ለድሕረ ምረቃ ፕሮግራም ወደ የል ዩኒቨርሲቲ የሄዱ ሲሆን፣ በየል ቆይታቸው የኢትዮጵያ ተማሪዎች ማሕበር በሰሜን አሜሪካ ሲመሰረት በማሕበሩ ውስጥ ንቁ ተሳታፊ ነበሩ፡፡አንድርያስ (ፕ/ር) የያኔውን የተማሪዎች ንቅናቄ ሲያወሱ በቁጭት፣ “አገሪቱን ከጠቀምነው ይልቅ የበደልነው ነገር ከፍተኛ ይመስለኛል፤ በፖለቲካ እልቂቶች አገሪቱ የተማረውን ዜጋዋን በማጣቷ እስካሁን ድረስ ተጎድታለች” ይላሉ።
በ1950ዎቹ ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሱ በኋላ፣ በያኔው ቀዳማዊ ሃይለ ስላሴ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በማስተማር ስራ ላይ ተሰማርተው ነበር። እንደገና ወደ አሜሪካ ተመልሰው በመሄድ ከፍተኛ ተቀባይት በነበራቸው ‘የልሂቃን ናቸው’ በተባሉ የትምሕርት ተቋማት አስተምረዋል፡፡ ካስተማሩባቸው ተቋማት ውስጥም ዩሲኤልኤ UCLA (ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ካሊፎርኒያ፣ ሎስ አንጀለስ)፣ በርክሌይ፣ ፔንሲልቫኒያ ዩኒቨርሲቲ፣ ብራውን ዩኒቨርሲቲዎች ይገኙበታል፡፡
በአሜሪካ አገር ቆይታቸው ከሌሎች የኢትዮጵያ የወቅቱ ፖለቲካ ከሚያሳስባቸው ሰዎች ጋር በመመካከር፣ ምሁራዊ እና ፖለቲካዊ ተዋስዖ የሚደረግበት ‘እምቢልታ’ የተሰኘ መጽሔት ላይ ሰርተዋል። የዚህ መጽሔት አንደኛው ባልደረባ የነበሩት ፖለቲከኛው አቶ ያሬድ ጥበቡ በይፋዊ የማሕበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ ስለአንድርያስ እሸቴ (ፕ/ር) እንዲህ ሲሉ ምስክርነታቸውን ሰጥተው ነበር፣
“በእምቢልታ መፅሔት ህትመት ዓመታት ለጥቂት ወራት በቅርብ ለማወቅ የቻልኩት ሰው፤ ጨዋታና ለዛ የነበረው የማይጠገብ ምሁር ነበር። በሃሳብ ሲጋጭም እስከ መጨረሻው መከራከር፣ ካስፈለገም በዚያች በትንሽ ቁመናውም ቢሆን ለመጋተርም የማይመለስ ሰው እንደነበር በአንድ ወቅት ከፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ጋር የነበራቸውን መካረር አይቻለሁ። የፀቡን ያህል ይቅር ብሎም ሲታረቅ ልባዊ እንደነበርም አይቻለሁ”
ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) አገሪቱን ሲቆጣጠር ወደ አገራቸው ተመልሰው በመምጣት፣ በ1980ዎቹ ዓመታት በሕገ መንግስት አርቃቂ ኮሚሽን እና በኢንተር አፍሪካ ግሩፕ ውስጥ ሰርተዋል። ከ1995 እስከ 2003 ዓ.ም. ድረስ ለስምንት ዓመታት ያህል የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዘዳንት ሆነው ሲያገለግሉ ቆይተው፣ ከየካቲት 25 ቀን 2003 ዓ.ም. ጀምሮ ደግሞ ወደ ጠቅላይ ሚስትር ጽህፈት ቤት በመዛወር በሚኒስትር ማዕረግ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አማካሪ ሆነው ተሾመው አገልግለዋል።
ፕ/ር አንድርያስ እሸቴ ከቀድሞ ባለቤታቸው ወይዘሮ እሙዬ አስፋው በትዳር በቆዩባቸው ዓመታት፣ የአንድ ወንድ ልጅ (አሉላ አንድርያስ) አባት ነበሩ።
የሁለ ገቡ ከያኒ ኩራባቸው ደነቀ ድንገተኛ ሞት (1957 - 2016}
ሕልፈተ ሕይወቱ ድንገተኛ መሆኑ ለበርካታ ወዳጆቹ እና አድናቂዎቹ አስደንጋጭ ነበር። የቴአትር እና የፊልም ባለሞያው ኩራባቸው ደነቀ በሚመጡት ዓመታት በርካታ የኪነጥበብ ስራዎችን ለመስራት አቅዶ ሲንቀሳቀስ መክረሙን የሚያውቁ ሁሉ ሐዘናቸው ከባድ ሆኗል።
አርቲስት ኩራባቸው ደነቀ የተወለደው በ1957 ዓ.ም. በሐረር ከተማ፣ ልዩ ስሙ ሸንኮር በሚባለው መንደር ውስጥ ነበር። አርቲስት ኩራባቸው ደነቀ በትወና በመድረክ ቴአትሮች ላይ ከ1982 ዓ.ም. ጀምሮ ከተሳተፈባቸው ስራዎች መካከል፤ በሕፃናትና ወጣቶች ቴአትር ‘የዝናቧ እመቤት’ እና ‘የገንፎ ተራራ’ ቴአትሮች፤ በአገር ፍቅር ቴአትር ‘የጨረቃ ቤት’፣ ‘ዓይነ ሞራ’፣ ‘ንጉሥ ሊር’፣ ‘ፍሬሕይወት’፣ ‘ጥሎሽ’፣ ‘አሉ’፣ ‘ጣውንቶቹ’፣ ‘ከራስ በላይ ራስ’ እና ‘የሸክላ ጌጥ’ ቴአትሮች፤ በአዲስ አበባ ቴአትርና ባሕል አዳራሽ ‘የጫጉላ ሽርሽር’ ቴአትር፤ በራስ ቴአትር ‘ቅርጫው’ ቴአትር ይገኙበታል።
ኩራባቸው ተዋናይ ብቻ ሳይሆን ዳይሬክተርም ጭምር ነበር። ከዳይሬክቲንግ ስራዎቹ፣ ይልቁንም ካዘጋጃቸው የመድረክ ቴአትሮች በአገር ፍቅር ቴአትር ‘ስጦታ’፣ ‘ጥሎሽ’ እና ‘መዳኛ’ ቴአትሮች፤ በአዲስ አበባ ቴአትርና ባሕል አዳራሽ ‘ሶስና’፣ ‘አንድ ክረምት’፣ ‘ጥቁሩ መናኝ’ እና ‘የጫጉላ ሽርሽር’ (ዝግጅቱ በቴአትሩ ተዋንያን ነበር) ቴአትሮች፤ በራስ ቴአትር ‘ትንታግ’ የተሰኘ ቴአትር በማዘጋጀት ተሳትፏል።
በሌላ በኩል፤ ካዘጋጃቸው ሙዚቃዊ ድራማዎች መካከል፣ በተለይ በአንጋፋዋ አርቲስት አስናቀች ወርቁ ህይወት ላይ ተመስርቶ የተፃፈውና ያዘጋጀው ‘አስናቀች ኢትዮጵያ’ የተሰኘው ስራ በጉልሕ ይጠቀሳል። በበርካታ የራዲዮ ድራማዎች ላይ በተለይም፣ ደራሲ ሃይሉ ጸጋዬ በጻፋቸውና በቅዳሜ መዝናኛ ፕሮግራም በተላለፉት በአብዛኛዎቹ ላይ ተሳትፏል።
በእነዚህ የኪነጥበብ ስራዎች ሳይወሰን፤ የቴሌቪዥን ድራማዎች ‘ገመና 1’ እና ‘ገመና 2’፣ እንዲሁም ‘እረኛዬ’ ድራማዎች በርካታ አድናቂዎችን ያፈሩለት ስራዎች ናቸው። አርቲስት ኩራባቸው ደነቀ ከወይዘሮ አስቴር ታደሰ ጋር በ1985 ዓ.ም. በጋብቻ ተጣምሮ፣ ሁለት ወንዶች እና አንዲት ሴት ልጆች አፍርቷል።
ባሳለፍነው ሰኞ ነሐሴ 20 ቀን 2016 ዓ.ም. በድንገት ሕይወቱ ያለፈው አርቲስት ኩራባቸው፣ በነጋታው ማክሰኞ የቀብር ስነስርዓቱ ጓደኞቹ፤ የስራ ባልደረቦቹ እንዲሁም ሌሎች አርቲስቶች፣ ብሎም በርካታ ሕዝብ በተገኘበት በቀጨኔ መድሃኔዓለም ቤተክርስቲያን ተፈፅሟል።
ከ60 በላይ ፊልሞች ላይ የተወነው አርቲስት ህልፈት
በተመሳሳይ በበርካታ ፊልሞች ላይ በመተወን የሚታወቀው አርቲስት ጌታቸው እጅጉ (ባቡጂ)፤ ባለፈው ቅዳሜ ነሐሴ 18 ቀን 2016 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት የተለየ ሲሆን፤ የቀብር ስነ ስርዓቱ ሰኞ ዕለት በቅዱስ ዮሴፍ ቤተክርስቲያ ንተፈጽሟል።
‘ሼፉ 2’፣ ‘ወደልጅነት’፣ ‘ጀማሪሌባ’፣ ‘ዕድሜለሴት’ የተሰኙና ሌሎች ከ60 በላይ ፊልሞች ላይ በመተወን በሙያው ለሀገሪቱ የራሱን አስተዋፅዖ አበርክቷል፡፡
በጥልቅ አንባቢነቱ ስሙ የሚነሳው ጌታቸው፤ መጽሐፍትን ስለመተርጎሙ፣ በብዕር ስም አዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ ስለመጻፉም በተለያዩ ጊዜያት መግለጹ አይዘነጋም፡፡
ኪዩር ሆስፒታል ከ1 ቢ. ብር በላይ በሆነ ወጪ አዲስ የማስፋፊያ ግንባታ ጀመረ
በተፈጥሮና በተለያዩ ምክንያቶች ለአካል ጉዳት ለተጋለጡ፣ የእግር መቆልመም፣ የወገብ መጉበጥና ልዩ ልዩ ችግሮች ላገጠሟቸው ልጆችና የከንፈርና ላንቃ መሰንጠቅ ችግር ለደረሰባቸው ልጆች ከቀላልና ውስብስብ ቀዶ ህክምናዎች ጀምሮ የተለያዩ ህክምናዎችን በነጻ በመስጠት የሚታወቀው ኪዩር ሆስፒታል፤ ሐምሌ 19 የሕዝብ መናፈሻ አጠገብ በሚገኘው የድርጅቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ በማውጣት የሚያካሂደውን የማስፋፊያ ግንባታ በይፋ አስጀመረ።
በዚሁ የማስፋፊያ ግንባታ የማስጀመሪያ ፕሮግራም ላይ የኪዩር ሆስፒታል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ወ/ሮ አደይ አባተ እንደተናገሩት፤ የማስፋፊያ ሕንፃ ግንባታው ተቋሙ ያለበትን የተደራሽነት ችግር በተወሰነ ደረጃ የሚያቃልልና የአገልግሎት አሰጣጡን አቅምና ጥራት ለማሳደግ የሚያስችል ነው ብለዋል።
ሆስፒታሉ በአጠቃላይ ሕክምና ድጋፍ ሊስተካከል የሚችል ችግር ያለባቸውን ሕፃናት፣ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በመቀበል ነፃ የሕክምናና የመድሃኒት አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኝ የተናገሩት ክራ አስፈጻሚዋ፤ የሕክምና ባለሙያዎችን ማሰልጠንና ማብቃት በሆስፒታሉ ከሚከናወኑ ተግባራት መካከል ይጠቀሳሉ ብለዋል።
የአገልግሎቱ ፈላጊዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱና፤ ሆስፒታሉ የሚሰጠው አገልግሎት ከታካሚዎች ቁጥር ጋር የማይጣጣም በመሆኑ ከፍተኛ ችግር አጋጥሞናል ያሉት ስራ አስኪያጇ፤ የአገልግሎት አሰጣጡን ጥራት ለማሳደግና የስልጠና አቅሙን ለመጨመር ይረዳ ዘንድ በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት የሚተገበር ግምቱ ከ10 ሚሊዮን ዶላር የሚልቅ የመሠረተ ልማት ማስፋፊያ ፕሮጀክት ማስጀመሩን ገልጸዋል።
ሆስፒታሉ ባለፉት 15 የአገልግሎት ዓመታት፣ ከ118 ሺ 100 በላይ የሚሆኑ አካል ጉዳተኛ ልጆች፣ ሆስፒታሉ ከሚሠጠው አገልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን፤ ከእነዚህም ውስጥ ከ33 ሺ 800 በላይ ነፃ የቀዶ ህክምና አገልግሎት ከመላ አገሪቱ ለመጡ ልጆች መሰጠቱን ስራ አስኪያጇ ተናግረዋል፡፡
በ2001 ዓ.ም የተከፈተውና አዲስ አበባን ማዕከሉን ያደረገው ኪዩር ኢትዮጵያ የልጆች ሆስፒታል፤ ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ባገኘው ህጋዊ ፍቃድና ከጤና ሚኒስቴር ጋር በገባው የፕሮጀክት ስምምነት መሠረት፣ ለአካል ጉዳተኛ ልጆች ነፃ የህክምና አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኝ ለትርፍ ያልተቋቋመ ግብረ ሰናይ ድርጅት ነው፡፡
ህወሓት የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ያደረገውን ሹምሽር ነቀፈ
- "በጽናት እንታገላለን"
ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) በትናንትናው ዕለት በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የተደረገውን ሹምሽር ነቅፏል። ድርጅቱ ነቀፌታውን ያሰማው ዛሬ ማለዳ የድርጅቱ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ወይዘሮ ፈትለወርቅ ገብረእግዚአብሔር በጻፉት ደብዳቤ ላይ ነው።
በደብዳቤው ላይ ህወሓትን ለማፍረስ ጥረት "ያደርጋሉ" ያላቸው ግለሰቦች በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ውስጥ እንደሚገኙ ጠቁሞ፣ "ይሁንና በውጭም ሆነ በውስጥ ድርጅቱን ለማፍረስ ያደረጉት ጥረት ባለመሳካቱ፣ ድርጅቱ በጊዜያዊው አስተዳደር ውስጥ የተሰጡትን ስልጣኖች ከሕግ እና የተቋም አሰራር ውጪ የመንጠቅ ስራ አጠናክረው ቀጥለዋል" ብሏል። "የሕዝባችንን፣ የድርጅታችንን እና የፖለቲካችንን አንድነት ለመጠበቅ በትዕግስት እና በተቋማዊ አሰራር ስንታገል ቆይተናል" ያለው ህወሓት፤ "ዕለታዊ አዋኪ አጀንዳ በመፍጠር ሃላፊነት ላይ መቆየት የፈለጉ" ሲል የጠራቸው የጊዜያዊ አስተዳደሩ አመራሮች በዞን አመራርነት ደረጃ የሚገኙ የህወሓት አባላትን ከስልጣን ማውረዳቸው ገልጿል።
አያይዞም፣ "ይህ ድርጊት ህወሓትን ከስር መሰረቱ ነቅሎ የመጣል የተቀናጀ ዘመቻ ነው። በአንድ ወገን ብቻ የሚደረግ ሹምሽር ተቀባይነት የለውም" በማለት ነቀፋውን ያቀረበው ድርጅቱ፣ በጊዜያዊ አስተዳደሩ መዳቢነት የተሾሙ አመራሮች በስራ ቦታቸው ላይ ሆነው ስራቸውን መስራት እንደማይችሉ በአጽንዖት አመልክቷል። "በአንድ ወገን እየተደረገ ነው" ያለውን ድርጅቱን የማፍረስ እንቅስቃሴ "በጽናት እንታገላለን" ብሏል።
ህወሓት 14ኛ ጠቅላላ ድርጅታዊ ጉባዔውን ማካሄዱ ተከትሎ፣ ለጋዜጠኞች መግለጫ የሰጡት የድርጅቱ ሊቀ መንበር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል "የራሳችንን አመራር በጊዜያዊ አስተዳደር ውስጥ መመደብ እንችላለን" ሲሉ "ኢትዮጵያ ኢንሳይደር" ላቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተው ነበር። ይሁንና በጊዜያዊ አስተዳደሩ እና ህወሓት መካከል የሚስተዋለው ፍትጊያ እያየለ ቢመጣ፣ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ፖለቲካዊ ልዩነቶች ወደ ግጭት እንደማያመሩ መግለጻቸው ይታወሳል።
ትናንት ከሃላፊነታቸው የተነሱት በጠቅላላ ድርጅታዊ ጉባዔው በፖሊት ቢሮ አባልነት የተመረጡት ወይዘሮ ሊያ ካሳ ሲሆኑ፣ የደቡብ ምስራቅ አስተዳዳሪ ነበሩ። በእርሳቸው ምትክ የእንደርታ ወረዳ አስተዳዳሪ የነበሩት አቶ ፀጋይ ገብረተኽለ መሾማቸውን ፕሬዝዳንት ጌታቸው ትናንት በጻፉት ደብዳቤ ጠቅሰዋል።
ከስፖርተኛ እስከ ቁማርተኛ፡- የድልና ዝና ባህሪያት
1 ከርሞ (ዕድሜን ኖሮ) ማለፍ
የሰው ልጅ ዕድሜ ደረጃዎች አሉት ብሎ ማወጅ አዲስ ግኝት አይደለም፡፡ ዕድሜ በዓለም የኑሮ ቆይታ ውስጥ ሆነው የሚሸመግሉበት/የሚያረጁበት ወይንም የሚያልፉበት ዓመታት ቀመር ነው ብለን ብንወስደውስ? አያስኬድም? በዓለም ላይ የምናየው ሁሉ (ሰው፣ እንስሳት፣ ዛፍ፣ ደንጊያ፣ መሬት፣ ቤት፣ …) በቁጥር የሚተመን የዕድሜ/መክረሚያ ቀምር/ቁጥር አለው፡፡
በሰው ዕድሜ ላይ ለመጻፍ የሞከርኩት ካለ ምክንያት አይደለም፡፡ ወጣቶች በእያንዳንዱ የዕድሜ አጥራቸው ዙሪያ መሥራት ያሉባቸውን ተግባራት እየፈጸሙ እንዲቆዩ፤ ማስተካከል ያለባቸውንም ባሉበት ተጨባጭ ሁኔታ ዝግጁ ሆነው ቀድመው የሚያነጣጥሩበትን ዒላማ ለመጠቆም ነው፡፡ ባለ ዕድሜዎች (ጎልማሶች፣ አረጋውያንና ሽማግሌዎች) ደግሞ እያንዳንዷን የሕይወት ጉዟቸውን በሀሳብ መለስ ብለው እንዲቃኙበትና ለቀሪው መክረሚያቸው እንዲዘጋጁበት በማሰብ ነው፡፡
ማንም ሰው ፍጹም መሆን አይችልም፡፡ በረጅም ዕድሜና በጥሩ ስኬት ተሟልተው የተገኙ ካሉ በጣም ዕድለኛ የሆኑቱ ናቸው፡፡ ምናልባትም፤ ዘመን፣ ዕድሜና ምኞታቸው የተገጣጠሙላቸውና ረጅም የኑሮ ድልና ስኬት ያገኙቱ ደግሞ የተባረኩቱ ናቸው፡፡ በረከት ስጦታ እንጂ በዕድሜ ቆይታ/መክረም እና የሥራ ልፋት የሚያገኙት አይደለም፡፡ በረከት ለሁሉም ዕድሜ የሚቸር ስጦታ ነው፡፡ ዕድሜ በበረከት ምስጢር ውስጥ ተታትቶ (ተሸምኖ) ያለ መክረሚያ (ሕይወት) ነው፡፡
ኖሮ ማለፍ የቢሊዮኖች ዕጣ ፈንታ መሆኑን አውቃለሁ፡፡ ኖራችሁ ብቻ ለማለፍ አትኑሩ፡፡ ላኖረቻችሁ መሬት ምንም ነገር ሳትተዉላት ኑሮን ብቻ ኖራችሁም አትለፉ፡፡ ዛፍ እንኳን ቅርፊትና ቅጠሉን ለመሬት ትቶላት ያልፋል - ሊያዳብራት፡፡ ሲነድም አመዱ ይተርፋታል፡፡ ከመሬት በላይ ስታለፉት የኖራችሁት በስባሽ ሥጋ የሚቀበረው መሬት ውስጥ በመሆኑ፣ ለመሬት ያ ብቻ ይበቃታል ካላችሁ፣ ንፉግ ትሆናላችሁ፡፡ ከላይዋ ስትኖሩ የረገጣችኋት አንሶ፣ ለሁለተኛ ጊዜ መኖሪያ እንድትሆናችሁ ከውስጧ ስትከፈኑባት/ስትቀበሩባት መሬት እንኳን የምታዝንባችሁ ለመሆኑ አልጠራጠርም፡፡ ሁለቱንም ጊዜ ኖራችሁባት እንጂ ምንም ነገር ለመሬት አልተዋችሁላትምና እስቲ እዘኑላት? በላይዋ ላይ አንዲት ትንሽ ነገር እንኳን ተዉላት፡፡ ዕድሜን መቁጠር ይህን ካላከለ ምን ፋይዳ አለው?
የሰው ልጅ የኑሮ ዓይነቱና ሂደቱ ብዙ ነው፡፡ በኑሮ ዘመኑ ምኞቱ በስኬት የተሟላለት፣ ግን ደግሞ ዕድሜን ያልተቸረ ሰው ሊኖር ይችላል፡፡ ያን ዓይነቱን ሰው “በአጭር ባይቀጭ ኖሮ የት በደረሰ” ተብሎ ይወራለታል፡፡ ይቆጩለታል፡፡ “ቢኖር ኖሮ…” ብለው መኖሩን ይመኙለታል፡፡ በአጭር መቀጨት በራሱ አወያይ ሃሳብ ነውና ልዝለለው፡፡
ዕድሜ የተቸረውና ምኞቱ በስኬት የተሟላለት ሰው ደግሞ አለ፡፡ ያንን ዓይነቱን ሰው “በዕድሜው ሙሉ ምኞቱን አሳክቶ የኖረ ሰው ነበር” በመባል ይታወሳል፡፡ እንደሱ በሆንኩኝ የሚል ምኞትን የሚጭርባቸው ሰዎችም ቀላል አይሆኑም፡፡ በዙሪያው ተኮልኩለው ሞቱን/ማለፉን ሳይሆን ኑሮውን ይመኙታል፡፡ ለራሳቸው ዕድሜንና ስኬትን መመኘታቸው መሆኑንም ልብ በሉላቸው፡፡ ሌላው ደግሞ፣ ዕድሜ ተችሮት፣ ምኞቱን ሳያሳካና ማንም እዚህ ግባ ሳይለው ኖሮ ሊያልፍ ይችላል፡፡ ያን ዓይነቱን ሰው ደግሞ “የዕድሜ ጠናዛ” (ዕድሜውን ብቻ በመቁጠር በዓለም ላይ የኖረ) በማለት እንዳልተሳካለትና ቢሠራም የማይሆንለት እንደነበረ በማንሳት ይታወሳል፡፡ እንዲታወስ ካላቸው ቁጭት ሳይሆን፣ አንስቶ ለመጣል (ለወሬ) ሲሉ ያነሱታል (አንስቶ መጣልም ባህል ነው)፡፡ “አይጣል ነው!” ሲባል አልሰማችሁም?
ከጠቀስኳቸው ከሦስቱ ዓይነት ሰዎች የትኛው ይሻላል ብዬ በመጠየቅ ምርጫን አላቀርብላችሁም፡፡ ይህን ዓይነት ጥያቄ “ስድብ” ነው፡፡ ሁሉም ሰው በኑሮ ዘመኑ መታወሻ ነገር ያለው መሆኑን ግን ያዙልኝ፡፡ ወይ በስንፍናው፣ ወይ በክፋቱ፣ ወይ በታታሪነቱ፣ ወይ በመልካም ሥራው፣ በሃብቱ ወይንም በድሕነቱ እንዲታወስ ይሆናል፡፡ ይበልጥ የሚታወሰው ግን የሚታወስ ሥራ የሠራው ነው በማለት፣ ኖሮ ብቻ ያለፈውን ሰው እንዴት ማስታወስ እንደሚቻል እያሰላሰላችሁ አብረን እንዝለቅ፡፡
2. ዕድሜና ስኬት
የሰው ልጅ ዕድሜ ከብዙ ክንዋኔዎች ጋር በቀጥታና በተዘዋዋሪ መንገዶች ይገናኛል፡፡ በዓለም ላይ የሚገኝ አብዛኛው ስኬት (የሃብት፣ የሥራ፣ …) እና ድል (የድርጊት/ውድድር ለምሳሌ፣ ስፖርት) የሚገኘው በወጣትነት ዕድሜ ነው፡፡ ስኬትና ድል ሲጨምር፣ እውቅና እያደገና የግል ዝና እየገነነ ይሄዳል፡፡ የግል ዝና ለአገርም/ለዜጎችም ይተርፋል፡፡ በአንፃሩ፣ ድል ከእድሜና ከተለያዩ አካላዊና ስነ-ልቡናዊ ሁኔታዎች ጋር በቅርብ የተዛመደ በመሆኑ እየቀነሰ መሄዱ አይቀሬ ነው፡፡ በስፖርት (ለምሳሌ፣ ሩጫ፣ እግር ኳስና ቅርጫት ኳስ በመሳሰሉ መስኮች) በግልና በቡድን የተገኙ ድሎችንና ዝናን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ዕድሜ ሲጨምር የውድድር ስፖርትን የመከወን ኃይል/ጉልበት በእጅጉ ይቀንሳል፡፡ በእግር ኳሱም ይሁን በሩጫው በወጣትነት ዕድሜ ተጀምሮ ወደ ጉልምስናው ሲቃረቡ የማቆም ሂደት የሚዘወተረው ተሳትፎው ስኬትን በነበረው ሁኔታ ሊያስቀጥል ስለማይችል ነው፡፡ ሆኖም፣ ዝና በአንድ ወቅት በተከናወነ ሁኔታ ላይ መመስረት በመቻሉ የሚቀጥል ሲሆን፣ ስኬት ግን የዕለት ጥረት ውጤት ነውና ዕድሜ ሲገፋ ይለግማል፡፡ ስኬትን ለማስቀጠል በድል የጨበጡትን ዝናና ወረት (ገንዘብ) በስስት/በዘዴ ሊጠብቁት የሚገባው ለዚያ ነው፡፡
ድልን ዕድሜ የሚጫነው በመሆኑ፣ በዕድሜው መግፋት ምክንያት ድል ያልቀናው ሰው የቀድሞ ዝናውን አያጣውም፡፡ እሱ ያገኘው ድል የራሱ ቢሆንም ከእሱ በኋላ የሚመጣ ወጣት ድሉን ሊጋራውና እንደ አርአያው ሊመለከተውም ይችላል፡፡ ሁሉም በዘመኑ ባለዝናና ባለድል ሆኖ ሊወደስና ሊከበር ይችላል፡፡ ልዩነቱ እያንዳንዱ ባለድል ድሉንና ዝናውን የሚጠብቅበት መንገድ ነው፡፡
ዝና የሰው ልጅ ስስ ብልት ነው - እስከ መጨረሻው በስስት ተንከባክባችሁ ጠብቁኝ ይላል፡፡ አንዱ ከአንዱ በአንጻራዊ ሁኔታ የተሻለ ድል ሊያስመዘግብ ይችል እንደሆነ እንጂ፣ ድል አንዴ ከተመዘገበ ለባለድሉ ቋሚ ዝና ይፈጥረለታል፡፡ አጭርም ሆነ ረዥም ዕድሜ፣ ተከናውኖ የተመዘገበን ዝና አይሽርም፡፡
ድል ለዝና፣ ዝናም ለበለጠ ድል የሚያነሳሱ/የሚያበቁ ናቸውና፤ ድል ሲቀዘቅዝ ዝና በነበረበት ግለት ላይቀጥል ይችላል፡፡ እውቅናው የጨመረለት ሰው ባገኘው እውቅና መኩራራቱም የተለመደ የሰው ባሕርይ ነው፡፡ ባለድል የሆኑ ጥቂት ሰዎች፣ ድልን እያጠነከሩ ካልሄዱ ዝና ሊቀንስ እንደሚችልና እውቅናም እንደሚጋሽብ የማያሰላስሉ ይኖራሉ፡፡ የዕድሜ ባለጸጋ የሆነ ባለዝና የሚኖረው አማራጭ፣ የነበረውን ዝና በሌሎች መልካም ተግባራት ማስጠበቅ ነው፡፡ እንደቀድሞው ያለ ሌላ ተመሳሳይ ድል ማስመዝገብ ላይሆንለት ይችላል፡፡ የዕድሜ ባለጸጎች ላገኛችሁት ዝና መጠንቀቅ ያለባችሁ፣ ዝናችሁ በዕድሜአችሁ አማካኝነት እንዳይበላሽ ነው፡፡ ቅርሳችሁ ስለሆነ ልትጠብቁት ይገባል ለማለት ነው፡፡
አንድ ጊዜ/ወቅት ድልን ከተጎናጸፉ በኋላ፣ ምንጊዜም በዚያ ዝና ብቻ እንዲሞገሱ “ሌላውን መተላለፌን ተውት” በማለት ለሰውም ሆነ ለራሳቸው ክብር የማይጠነቀቁ ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ድሉ ያስገኘላቸው ዝና ቶሎ የሚያሰክራቸውና በፍጥነት ታይተው እንደጤዛ የሚረግፉም በርካታ ናቸው፡፡ አንዴ ባስመዘገቡት ድል እስከ ዕለተ-ሞታቸው ተከብረውና ተወድደው የሚኖሩ ዕድለኞችም አሉ፡፡ እኒህኞቹን በዘላቂነት ሊያስከብራቸው የቻለው ከድል በኋላ ያስመዘገቧቸው መልካም ባህሪያት ጭምር ናቸው፡፡ ድል ከመልካም ተግባርና ባህሪይ ጋር ሲጣመር የዝናን ዘላለማዊ የመሆን ዕድሉን ከፍ ያደርገዋል፡፡ ዕድሜም ክብር ተችሮት ከዝና ጋር አብሮ ይዘልቃል፡፡
ሰው በዕድሜው ምክንያት የበለጠ ድል የመሥራት/የማስመዝገብ አቅሙ እየደከመ ቢመጣም፣ ቀደም ተጎናጽፎት የነበረው ድል ዝናውን ጠብቆ የሚያቆይለት እየመሰለው መኩራራቱን ይቀጥላል፡፡ ድሉ ፈጥሮለት የነበረውን የዝና ሞቅታ ባለበት እንዲቆይ የሚችለውን ከማድረግም አይቆጠብም፡፡ በርካቶች ማበረታቻ እጽ እስከመጠቀም የሚደርሱት ለዚያ ነው፡፡ ያን ጊዜ የውድቀትን ቁልቁለት ይያያዙታል፡፡ ዕድሜ፣ ድልና ዝናም ከንቱ ይሆናሉ፡፡ በዚህ ረገድ ታሪክ ያሳየን ነገር አለ፡፡
የዓለም ምርጥ እግር ኳስ ተጫዋች የነበረውን ማራዶናን የማስታውሰው በቁጭት ነው፡፡ ማራዶና በድንገት ተከስቶ ብርሀኑን ለዓለም ያበራና በቶሎ የጠፋ ኮከብ ይመስለኛል፡፡ ዝናውና (የስፖርት ቤተሰቦች ፍቅርና ሀዘን) በእጽ ሱስ ተለክፎ በኑሮው የተንገዳገደባቸው ዓመታት ከሕሊና የሚጠፉ አይደሉም፡፡ ሮናልዲኒዮን የትኛው ላይ ልመድበው ይሆን? ድንቁ የኳስ ከያኒ ሮናልዲኒዮ (ስሙን በትክክል ጽፌው ይሆን?) ዕድሜ ብቻውን አልተሟገተውም፡፡ ያገኘው ዝና ከቁጥጥር ውጪ አውጥቶት የሚሠራውን አሳጣው ልበል? አሱንም ሳስብ ሀዘን ይሰማኛል፡፡
ከፍተኛ ዝና ላይ የነበረውና፣ “የኳስ ንጉሥ” ተብሎ ተወዳጅነቱን እንደያዘ ተከብሮ በመኖር ለህልፈተ ሥጋ የበቃው፣ የዕድሜ ባለጸጋው የብራዚሉ ፔሌን ማየት ደግሞ በሌላው ጠርዝ የሚገኝ ትልቅ ትምህርት/አርአያነት ነው፡፡
እግር ኳስን እንደ ምሳሌ ወሰድኩኝ እንጂ፣ በሁሉም ድልና ዝና በሚያስገኙ ስፖርቶች (ለምሳሌ፣ አትሌቲክስ፣ የቅርጫት ኳስ) ውስጥ የሚገኙ አያሌ ባለ ድልና ዝናዎች አሁንም አሉ፡፡ ለአብነት ያህል ግን የኳሱ ይበቃል፡፡ በአትሌቲክሱ ዘርፍ ከገባሁኝ፣ በአገራችን ምሳሌ ሊሆኑ የሚችሉ ብዙዎች አሉ፡፡ ዝናን ከዕድሜ ጋር ይዘው በጉዞ ላይ የሚገኙ ወጣቶች፣ ጎልማሶችና አረጋውያን አትሌቶች አሉን፡፡ የኋለኞች/የአሁኖቹ ከፊተኞች መልካም ቢማሩ፣ መልካምን ይሠራሉ፡፡
በጥቅሉ፣ ባለ ድልና ባለዝናው ሁሉ በዕድሜው ምክንያት የለመደውን ሲያጣ የቀድሞውን ድልና ዝና በሃሳብ መመኘቱ የሰው ባሕሪ ነውና ቀድሞ ማሰብ ዋጋ አለው፡፡ አንድ ሥፍራ ላይ ሲደርስ ይበቃኛል ማለት እንደሚገባው ቀድሞ ካላሰበ፣ ወይም በእጁ ላለው ድልና ዝና ካልተጠነቀቀ፣ እንደ ቁማርተኛ ሰው መሆኑም እሙን ነው፡፡ ዕድሜ፣ አንድ ሥፍራ ላይ ሲደርሱ ያገኘሁት በቃኝ ማለትን የግድ ይላል፡፡ ጉልበትን፣ ወቅትን፣ ዕድሜንና ተጽዕኖውን ቀድሞ ማጤን ብልህነት ይመስለኛል፡፡
3. የቁማርተኛ ሰው ባህሪ
የቁማርተኛ ሰው ባህሪ ይገርመኛል፡፡ ድልን/ስኬትን ከቁማርተኛ ሰው ባህሪ ጋር ሳነጻጽር፣ ዕድሜም በውስጡ እንዳለበት እያሰባችሁ ተከተሉኝ፡፡
ቁማርተኛ ሰው ሲቀናው ብዙ ለማግኘት፣ ሳይቀናው ደግሞ እያደር ሊቀናው እንደሚችል እልህ ተያይዞ ቁማር “መጫወቱን” ይቀጥላል፡፡ ሊቀናውም ላይቀናውም ይችላል፡፡ የት ላይ ማቆም እንዳለበት መወሰን ይከብደዋልና ይቀጥላል፡፡ የሚታየው ያጣው (“የተበላው”) ገንዘቡ ነው፡፡
ከእልሁ የሚነቃው ደግሞ በእጁ የነበረው ገንዘብ በሙሉ ሲያልቅና ምንም ማድረግ እንደማይችል ሲረዳ ብቻ ነው፡፡ በጥቅሉ፣ ቀሪ ገንዘብ በእጁ ቢኖር ኖሮ የቀድሞ ገንዘቡን ሁሉ መልሶ ሊያገኝ እንደሚችል ይመኛል እንጂ፣ አልቻልኩም ብሎ ምኞቱንና እልሁን አይገታም፡፡ ምኞት፣ እልህን በውስጡ ቀላቅሎ የያዘ የሰዎች ሁሉ ጉልበት ነው፡፡ እልህ ደግሞ ለጥሩም ሆነ ለመጥፎ ነገር የማድረግ ኃይልን የሚቸር የሰው ድክመት ወይንም ብርታት ነው፡፡ እልህ ብርታት ሲሆን ሰውን ይገነባል፡፡ ድክመት ሲሆን ደግሞ ሰውን ያሳንሳል፡፡ ብርታትና ድክመት በሰው ልጆች የዕድሜ ሂደት ውስጥ የሚከሰቱ ጠባያት ናቸው፡፡
ብልህ ቁማርተኛ ሲበላና (በ ይላላ) ሲበላ (በ ይጥበቅ) ጠባዩና በዚያም ሳቢያ የሚወስናቸው ኤኮኖሚያዊ ውሳኔዎች ይለያያሉ፡፡ ብልህ ቁማርተኛ የሚበላው (በ ይጥበቅ) ቀድሞ የበላውን የተቀናቃኙን ገንዘብ ነው፡፡ ከራሱ የሚሰጠው ጥቂት ነው፡፡ ሊያጣ የሚችለውን ሊያገኝ ከሚችለው አንጻር አስቀድሞ ያሰላል፡፡
ብዙው ቁማርተኛ ከእልሁ የሚነቃው ሁሉንም ገንዘቡን ካጣ በኋላ ሊሆን ይችላል፡፡ ቋሚና ተንቀሳቃሽ ንብረታቸውን በመያዣነት አሲዘው የሚጫወቱ ቁማርተኞች አሉ ይባላል፡፡ ያጡትን ለመመለስ ካላቸው እልህና ምኞት በስተቀር፣ ያሲያዙትን ንብረት በተጨማሪ ሊያጡት እንደሚችሉ በዚያን የጫዎታ ወቅት የደረሱበት የባህሪ ለውጥ አይፈቅድላቸውም፡፡ የሚታያቸው በፊት ያጡት ገንዘብ ሊሆን ይችላል፡፡ ያጡትን መልሰው ማግኘት ሲመኙ፣ የያዙትን ማጣት ሊከተል መቻሉ ግን ሊያልፉት የማይችሉት እውነት ነው፡፡
በርካቶች ከዝና ማማ ላይ ወርደው ተንኮታኩተዋል፡፡ ተጎናጽፎት በነበረው ድል ሳቢያ የተቸረው ዝና እንደነበረ እንዲቆይ የሚመኝ እንዳለ ሁሉ፣ የተበላውን ቁማር ለመመለስ ንብረቱን ሁሉ አስይዞ በእልህ ወደ ኪሳራ የሚንደረደርም አለ፡፡ በእጅ ላይ ባለ ነገር መርካት ትልቅ ችሎታ ነው፡፡ እያንዳንዱ ዕድሜ፣ ድልና ዝና በእጅ ውስጥ የሚገኝ እንቁ ነው፡፡ የዕድሜን፣ የድልንና የዝናን ውኃ ልክ በማወቅ መኖር መልካም ነው፡፡
ይበቃኛል ማለት ከተቻለ፣ በእጅ ያለው ካጡት ይልቅ ይበልጣል፡፡ በቃኝ ማለት መቻል ትልቅ ዕውቀት፣ ሙሉ ሃብት ነው፡፡ ሁሉም ግን አይታደለውም፡፡ ቁማርተኛ ሰው በቃኝ ብሎ ቢያስብ እንኳን የመወሰን ችሎታውና የቁማሩ ባህሪ አይፈቅዱለትም፡፡ ዕድሜም የራሱ ባህሪያት አሉት፡፡ የዕድሜን ቁጥሩን እንጂ ሂደቱንና መጨረሻውን መገመትና መቆጣጠር ከባድ ነው - ጥሩው መጥፎ፣ መጥፎው ደግሞ መልካም ሆኖ ሊደመደም ይችላል፡፡ ዕድሜ አንዳንዴ ምስጢር ነው፡፡
ሰላም ለሁላችን፡፡