Administrator

Administrator

   አለማችን ከአንድ አመት በላይ አሳር መከራዋን ሲያሳያት የከረመውንና አሁንም በእጅግ ከፍተኛ ፍጥነት በመሰራጨት ላይ የሚገኘውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በወራት ጊዜ በቁጥጥር ስር ማዋል እንደምትችል የገለጸው የአለም የጤና ድርጅት፤ ይህን ማድረግ የሚቻለው ግን አስፈላጊ ሃብቶችን በፍትሃዊነት መከፋፈል ሲቻል ብቻ እንደሆነ አመልክቷል፡፡
የድርጅቱ ዳይሬክተር ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም በሳምንቱ መጀመሪያ በሰጡት መግለጫ፤ ኮሮናን በቀጣዮቹ ወራት በቁጥጥር ስር ለማዋል የሚያስችሉ መሳሪያዎች ቢገኙም የአለማችን አገራት እነዚህን መሳሪያዎች በፍትሃዊነት መከፋፈልና በዘላቂነት መጠቀም ካልቻሉ ግን ቫይረሱን በቁጥጥር ስር ማዋል አይቻልም ማለታቸውን የዘገበው ሮይተርስ፤ የተገኘው መላ ምን እንደሆነ ግን በግልጽ አልተናገሩም ብሏል፡፡
ቫይረሱ አሁንም በመላው አለም በእጅግ ከፍተኛ ፍጥነት በመሰራጨት ላይ እንደሚገኝና በተለይ ከ25 እስከ 59 አመት የዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ሰዎችን እያጠቃ እንደሚገኝ ያልሸሸጉት ዳይሬክተሩ፤ በፍጥነት ለመሰራጨቱ በምክንያትነት ሊጠቀሱ ከሚችሉት ጉዳዮች መካከል የቫይረሱ አዳዲስ ዝርያዎች በብዛት መፈጠራቸው አንዱ ሊሆን እንደሚችልም ገልጸዋል፡፡

  በአለም ዙሪያ ባለፈው የፈረንጆች አመት ብቻ ከ483 በላይ ሰዎች የሞት ቅጣት ውሳኔ ተላልፎባቸው እንደተገደሉና ከእነዚህም ውስጥ 88 በመቶ የሚሆኑት በአምስት አገራት ውስጥ ብቻ የተፈጸሙ እንደሆኑ አለም አቀፉ የሰብአዊ መብቶች ተቋም አምነስቲ ኢንተርናሽናል ከሰሞኑ ባወጣው አመታዊ ሪፖርቱ አስታውቋል፡፡
በአመቱ በርካታ ቁጥር ያላቸውን ሰዎች በሞት ከቀጡ ቀዳሚዎቹ አምስት አገራት ውስጥ አራቱ የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት መሆናቸውን የጠቆመው ሪፖርቱ፤ ኢራን 246፣ ግብጽ 107፣ ኢራቅ 45 የሞት ፍርድ ቅጣቶችን በመፈጸም ከአለማችን አገራት ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ያለውን ደረጃ መያዛቸውንም አመልክቷል፡፡
ግብጽ የሞት ቅጣት ያስተላለፈችባቸው ሰዎች ቁጥር ከአምናው በሶስት እጥፍ ማደጉን የጠቆመው ሪፖርቱ፣ በሳኡዲ አረቢያ በአንጻሩ ቁጥሩ በ85 በመቶ ያህል ከአምናው መቀነስ ማሳየቱንና ይህም ሊሆን የቻለው አገሪቱ ከአደንዛዥ እፅ ጋር በተያያዙ ወንጀሎች ጥፋተኛ የሆኑትን በሞት ፍርድ መቅጣት በማቋረጧ ሰበብ ነው መባሉንም አክሎ ገልጧል፡፡
በአመቱ በመላው አለም የተመዘገበው የሞት ቅጣት ባለፉት አስር አመታት እጅግ ዝቅተኛው ነው ቢባልም፣ ሪፖርቱ ግን በሞት በመቅጣት የሚታወቁትንና መረጃዎቻቸውን አሳልፈው የማይሰጡትን ቻይና፣ ሰሜን ኮርያ፣ ሶርያና ቬትናምን አለማካተቱ ቁጥሩን በእጅጉ ዝቅ እንደሚያደርገውም ተነግሯል፡፡ በአለማችን 108 ያህል አገራት የሞት ፍርድ ቅጣትን ሙሉ ለሙሉ ማቆማቸውንም ሪፖርቱ ይጠቁማል፡፡


  ቻድን ላለፉት 30 አመታት ያስተዳደሩት ፕሬዚዳንት ኢድሪስ ዴቢ ለ6ኛ ጊዜ በተወዳደሩበት ምርጫ 80 በመቶ ድምጽ በማግኘት ማሸነፋቸውን ይፋ ባደረጉበት ባለፈው ማክሰኞ በአማጺ ሃይሎች በደረሰባቸው ጥቃት መገደላቸውን ተከትሎ፣ የተቋቋመው የአገሪቱ የሽግግር ምክር ቤት በሟቹ ፕሬዚዳንት ወንድ ልጅ ጄኔራል መሃመት ኢድሪስ ዴቢ እንደሚመራ ተነግሯል፡፡
በማዕከላዊ አፍሪካዊቷ አገር ቻድ ቀጣይ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እስኪከናወን አገሪቱን የሚያስተዳድረውንና ለ18 ወራት ይቆያል የተባለውን የሽግግር መንግስት ምክር ቤት የሚመሩት  ባለ አራት ኮከብ ጄነራሉ የ37 አመቱ መሃመት ኢድሪስ ዴቢ፣ ከዚህ ቀደም የአገሪቱ ልዩ ሪፐብሊካን ጋርድ መሪ እንደነበሩም ኦል አፍሪካን ኒውስ ዘግቧል፡፡
የምርጫ ውጤቱ ይፋ መደረጉን ተከትሎ በዋና ከተማዋ ኒጃሚና በመንግስትና ውጤቱን በተቃወሙ አማጺያን መካከል ውጊያ መጀመሩን ያስታወሰው ዘገባው፤ ፕሬዝደንት ዴቢ ከአማጺያን ጋር በመዋጋት ላይ የነበሩ ወታደሮችን እየጎበኙ ባሉበት አጋጣሚ በጥይት ተመትተው ህይወታቸው ማለፉንም አክሎ ገልጧል፡፡
የፕሬዚዳንት ዴቢን መገደል ተከትሎ መንግስትና ፓርላማው እንዲበተን የወሰነውና የሽግግር ምክር ቤት ያቋቋመው የአገሪቱ የጦር ሃይል፣ በመላ ቻድ ብሔራዊ ሃዘን ያወጀ ሲሆን፣ ሁሉም ድንበሮች እንዲዘጉ መደረጉንም ዘገባዎች  ያመለክታሉ።

 ከዕለታት አንድ ቀን ባልና ሚስት ጎጆ የሚወጡበት ቤት ለማግኘት በመሯሯጥ ላይ ሳሉና መንደሩን በመዳሰስ ሲዟዟሩ አንድ ደላላ ያገኛሉ።
ደላላው፡- “ምን ዓይነት ቤት ነው የፈለጋችሁት?” አላቸው።
ሚስትየው፡- “ግቢው ለብቻና ሰፋ ያለ፣  ከጎረቤት የማያገናኝ ፣ መብራትና ውሃ ለብቻው ቢሆን እንመርጣለን” አለች።
ደላላው፡- “ችግር የለውም””፤ ሌላ ጊዜ የምትፈልጉት ነገር አለ ወይ?”
ባልየው፡- “የግንብ አጥር አለ?”
ደላላው፡- “ችግር የለውም፤ አሁኑኑ በአንድ አፍታ ይገኝላችኋል”
ሚስትየው፡- “ግን የብረት በር መሆን አለበት”
ደላላው፡- “ችግር የለም፤ ሞልቷል”
ባልየው፡- “ቀለሙንም እኛ እንደፈለግን የምንለዋውጠው መሆን አለበት”
ሚስት፡- “ከዋናው አስፋልት በጣም የማይገባ ፤ አስፋልት ዳር የሆነ አለ?”
ደላላው፡- “በጣም ብዙ አለ፤ የሱ አይነት”
ባልየው፡- “እሺ ታዲያ መቼ ነው የምታሳየን?”
ደላላው፡- “ዛሬም ይቻላል፤ ነገም ከነገ ወዲያም ካልሆነም በሚቀጥለው ሳምንት፤ አንዱን ቀን”
ሚስት፡-”በቃ ነገ እንየዋ”
ደላላው፡- “ቆይ አንጣደፍ፤ እኔ ሲለቀቅ ልደውልላችሁ”
ሚስት፡- (በንዴት) “እንዴ! ያልተለቀቀ ቤት ነው እንዴ ሞልቷል በሽ ነው የምትለን የነበረው፤ ቀጣፊ!”
ደላላው፡- “እሱማ የስራችን ጸባይ ነው እኮ እመቤቴ”
ሚስት፡- (እንደገናበንዴት) “ምን  የስራችሁ ፀባይ፤ የራሳችሁ ጸባይ ነው እንጂ አስቸጋሪው”
ደላላው፡- “ለማንኛውም አይቶ መፍረድ ነው፤ ግቢውን ስታዩት ትወዱኛላችሁ፤ ነገ እናየዋለን”  በዚሁ ተሰነባበቱ።
በነገታው ወደ ግቢውና ወደ ቤቱ ተያይዘው ሄዱ። ሲታይ ቤቱ ኮርኒሱ የተቦዳደሰ፣ አጥሩ የአረብ ጥርስ ይመስል የወላለቀ ሆኖ ተገኘ።
“ባልየው ምነው የኔ ወንድም፤ ያ ሁሉ ስለ ግቢና ስለ ቤቱ ውበት መቀባጠር ለምን አስፈለገ፤ እኔንስ ባለቤቴንስ ለምን አንገላታኸን? ላንተ ያለውን´ኮ ብትዋሽም ባትዋሽም አታጣውም!?  ምንጊዜም እውነትን ተማመን። የውሸቱ መንገድ ጊዜያዊና የማያደርስህ ነው” ብሎ መክሮ አሰናበተው።
*   *   *
መንገዶች ሁሉ ለመጀመሪያ ጊዜ ብትሄዱ ብትሄዱ ሩቅ ይመስላሉ፤ ከአንድ ጊዜ በላይ ከባድ አይሆኑም። አዲስ ነገር ግራ የሚያጋባን ለዚህ ነው። ምናልባትም ለውጥን የማንረዳውም የምንፈራውም ለዚህ ነው። በዚህ ላይ እድሜና ልማት ካልበሰሉ ጣጣና አባዜያቸው አስጊ ነው። አይጣልም የሚባል ነው።
መንገዳችን ሁሉ አለቀ በስለት
ምን ይበላ ይሆን የተገናኘን ለት
አክርማ እንኳን የለኝ ሰፍቼ አልጨርሰው
እንዴት በያገሩ ጅምር ይተዋል ሰው
ያለውን ድምጻዊ ውብሸትን አለመርሳት ነው። የመጀመሪያው ሰሙ ኢኮኖሚያዊ መንገዳችንን ማቃናት ምን ያህል እንዳልቀናን የሚጠቁም ነው።
ሁለተኛው ስንኝ በየአጋጣሚው እየጀመርን ያልጨረስናቸው ጉዳዮች አያሌ መሆናቸውን የሚጠቁመን ነው። ምን ያልጀመርናቸው ጉዳዮች ነበሩ? ዛሬ ያለነው የለውጥ ኩርባ ላይ ነው። ያላሰብነው፣ ገቢር ወነቢር አልነበረም። ያላቋረጥነው ድልድይ፤ ያልሰበርነውም ድልድይ አልነበረም።
አስረጂ...
ዲሞክራሲ ...
ፍትህ...
እኩልነት...
ጥምር መንግስት...
የተራማጆች ህብረትና ውህደት...
እንደ መግባቢያና የውይይት መድረክ (ፎረም)...
የህዝብ ድርጅት ጊዜያዊ ጽ/ቤት...
የጤናና ትምህርት ቢሮዎች...
የአርበኞች ማህበር...
የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ማህበር...
የኢትዮጵያ ስካውት ማህበር...
የኢትዮጵያ ሴቶች ትግል ድርጅት...
የኢትዮጵያ አብዮታዊ ወጣቶች ድርጅት...
ወክማና ወህክማ...
 እነዚህ ሁሉ የኢትዮጵያን ወጣቶች የቀረጹ ናቸው ቢባል የዋህነት አይሆንም፤ የኢትዮጵያ ኮሌጆች ቅድሚያ ውድድርን አንዘነጋም።
የቀድሞ ቀኃስ የአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ፤ አያሌ ወጣት ምሁራንን ያፈራ፣ የአፍሪካ የተከበረና ለአፍሪካ ሀገሮች ስኮላርሽፕ እስከ መስጠት የደረሰ አንጋፋ ዩንቨርሲቲ የነበረ ነው። ምንም እንኳን ዛሬ ከሐምሌት ጋር፡-
“ያለፈ ጥረታችንን ሳስታምመው ትዝ ሲለኝ
ከሞከርነው ነገር ይልቅ ያልሞከርነው ነው የሚቆጨኝ”
ብንልም ከመሞከር ወደ ኋላ አንልም። ከሁሉም ወሳኙና አንገብጋቢው የእውነትን ፍለጋ ጥረታችንን አለማቋረጣችን ነው። አለበለዚያ ለትውልድ የምንሰጠው ትረካ አይኖረንም። ልጆቻችን የሚረከቡንን ይወቁ! እኛም አውቀን እናሳውቃቸው። ቢደክመንም ቢደክማቸውም እንተጋገዝ። ምክንያቱም እውነቱን ሲያውቁ በየነፍሳቸው የራሳቸውን እድል ይወስናሉና።
ዛሬም በልጆቻችን ላይ እንስራ!

የተከበራችሁ የሀገራችን ሕዝቦች፣
ከሦስት ዓመታት በፊት ወደ ለውጥ ጎዳና የገባነው በመንገዱ ላይ ችግሮች አይገጥሙንም በሚል እሳቤ አልነበረም፡፡ ሀገራችን ትከሻ ላይ
የተቆለለውን የበዛ ችግር ከነውስብስብነቱ ተረድተን እንጂ፤ አቅልለን አይተን አልተነሳንም፡፡ ለዘመናት ሲከመር ቆይቶ ወደ ግዙፍ ተራራነት
የተለወጠው ሀገራዊና ቀጠናዊ ችግሮች በቀላሉ መወገድ ቢችሉ ጥሩ ነበር። ነገር ግን ችግሮቹ እንኳን እርስ በእርስ እየተጓተትን ቀርቶ አንድ
ሆነንም በጥቂት ዓመታት ውስጥ ድምጥማጣቸው የሚጠፋ አይደለም፡፡
ይሄንን በሚገባ አውቀን እስከ መጨረሻው ሕቅታ ዋጋ ለመከፈል ቆርጠን ነው የተነሳነው፡፡ ሀገራችን ያሉባት ችግሮች ምንም ያህል እንደ
ምድር አሸዋ ቢበዙ ፈጽሞ ከዜጎቿ አቅም በላይ እንደማይሆኑ ጽኑ እምነት አለን የሚፈቱትም ተነጣጥለን ሳይሆን በአንድነትና በትብብር
እንደሆነ ገና ከጅምሩ አሳውቀናል፡፡ በወቅቱ ያለ ብዙ ፈተና በአንዲት ጀንበር የተለወጠች ሀገር ትኖረናለች ብለው የጠበቁ ሰዎች እንደነበሩ
ግልጽ ነው፡፡ ለውጡ ከአንድ አቅጣጫ ይመጣልም ብለው እንደታዛቢ ዳር ቆመው የሚመለከቱ መኖራቸውም እንዲሁ፡፡
ያኔ የለውጥ ጉዞ በጀመርንበት ወቅት ሁሉም ሰው ከፍ ባለ ሞራልና በፌስታ ተሞልቶ የነበረ ቢሆንም፣ ሁሉም በጀመረበት የመንፈስ ከፍታ
እንደማያጠናቅቅ ግልጽ ነበር። ሀገራችን ለዘመናት ስትናፍቀው የኖረችው የተስፋ አድማስ ላይ ደርሰን ሁላችንም የመንካት አድሉ ይገጥመናል
ብሎ ማሰቡም ሞኝነት ነው፡፡ በየመንገዱ የሚገጥመንን እሾህና ጋሬጣ ሳያቆስለን፣ እባብና ጊንጡ ሳይነድፈን፣ ሀሩርና ቃጠሎው ሳይለበልበን
የምናልማትን የበለጸገች ሀገር መገንባት ብንቸልማ ኖሮ ገና ድሮ በአደረግነው ነበር፡፡
በረሃውን ሳናቋርጥና ባህሩን ሳንሻገር ጉዞው ይጠናቀቃል ብለው ያሰቡ ሰዎች ከመጀመሪያውም ተሞኝተዋል። ከፊታቸው የተዘረጋውን ፈተና
ቀድመው ያላዩ፣ ጉዞው መሐል ላይ ወገባቸው ዝሎ መንቀጥቀጥ ሲጀምር ቢናደዱ፣ መበሳጨት ያለባቸው በሌላ አካል ሳይሆን በተሳሳተ
ግምታቸው ነው፡፡ አሁንም ቢሆን ይበልጥ ወደ ተስፋ ሰገነታችን እየቀረብን በመጣን ቁጥር ፈተናው እንደሚበረታ መረዳት ይኖርብናል፡፡
በሀገራችን በተለያዩ ጊዜያት ያየናቸው ግጭቶች፣ የሰላም ማጣትና የደህንነት ስጋቶች በለውጥ ጉዞአችን በእጅጉ ከፈተኑን ፈተናዎች ጎራ
የሚመደቡ ናቸው፡፡ መንገድ ያስጀመረንን አንድነት ሊደቁሱ፣ እጅ ለእጅ ያስተሳሰረንን ገመድ ሊበጣጥሱ፣ የጋራ ቤታችንን ሊደረማምሱ
የሚቋምጡ ብርቱ ፈተናዎቻች ጉዞ ከመጀመራችን በፊትም ነበሩ፣ አሁንም አሉ፡፡
ምናልባትም መንገዳችን ላይ ልዩ ልዩ ጋሬጣዎችን እየጣሉ ከጉዞአችን ሊያስቀሩን የሚሹ አካላትን ድብቅ ፍላጎት በአግባቡ ተረድተን
በጥንቃቄና በጥበብ ወደ ግባችን መጓዛችንን እንደማናቆም እስካላሳየናቸው ድረስ በቀሪ ምዕራፎቻችንም ላይ ተከትለውን ይመጣሉ።
የጠላቶቻችን ፍላጎት በጉዞአችን መሐል ወድቀን ግባችንን ሳናሳካ እንድንቀር ነው፡፡ በጋራ ቆመን ያጸናነው ቤታችን ፈራርሶ ወደ ትቢያነት
ሲቀየር ማየት ይሻሉ፡፡ እኛ ደግሞ ለዚያ የተመቸን ሆነንላቸዋል፡፡
አንድ ቤት በሦስት ምከንያቶች ሊፈርስ ይቸላል። በግንባታው ወቅት በገጠሙት ችግሮች፣ ከውስጥ ባሉ ሰዎች እና ከውጭ በሚመጡ
ኃይሎች። እነዚህ ሦስቱ አውቀውትም ይሁን ሳያውቁ የሚተባበሩበት ጊዜ አለ። አንዳንድ ጊዜ በዓላማ፣ አንዳንድ ጊዜ በሂደት፣ አንዳንድ
ጊዜም በውጤት ይተባበራሉ። ከውስጥ ያሉት ሰዎች በውስጥ ጉዳያቸው ሲጣሉ፤ ከውጭ ያሉ ኃይሎች ቤቱን አፍርሰው ቤቱ የተገነባበትን ቦታ
ወይም በቤቱ ውስጥ ያለውን ሀብት መዝረፍ ሲፈልጉ፣ ቤቱ እንዲፈርስ ተባብረው ሊሠሩ ይችላሉ።
ቤቱ ሲገነባ ያጋጠሙት ችግሮች ካሉ ደግሞ ነገሩ “በዕንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” ዓይነት ይሆናል።
የተከበራቸሁ ኢትዮጵያውያን፣
ሁላችንም ልንዘነጋው የማይገባን አንድ ሐቅ አለ። ሀገራችን የጋራ ቤታችን ናት፡፡ የሁላችንም ቤቶች በዚያች ትልቅ ቤት ውስጥ የሚገኙ የቤቱ
ከፍሎች ናቸው፡፡ በየከፍሎቻችን ተወሽቀን ያለነው ሁላችንም የጋራ ቤታችንን አጽንጸን በማቆየት ላይ ተመሳሳይ አቅምና አቋም የለንም። ቤትን
ከውጭ የሚመጣ ኃይል ብቻውን አያፈርሰውም። የውስጦቹ ካልተባበሩት በቀር፡፡ የቤቱ ሰዎች የውጭ አፍራሾች በሦስት መንገድ
ዐውቀውም ይሁን ሳያውቁ ሊተባበሯቸው ይችላሉ፡፡ ሆን ብለው፣ ሞኝ ሆነው እና ተኝተው፡፡
ከሚፈርስ ቤት እንጠቀማለን የሚሉ ሞኝ የቤት ሰዎች አሉ፡፤ ከመሥራትና ከመድከም ዋጋ ማግኘት የሚከብዳቸው፤ የቤቱን ፍርስራሽ ሽጠው
ማትረፍ የሚፈልጉ የፍርስራሽ ጌቶች አሉ፡፡ እነዚህ ሆን ብለው ቤቱ እንዲፈረስ ይሠራሉ፡፡ ቤቱ ቶሎ ፈራርሶላቸው ፍራሹን ለመቸብቸብ
ስለሚቸኩሉ፣ ከውጭ ሆነው ቤቱን ከሚነቀንቁት ጋር ተባብረው ያፈርሳሉ፡፡ ሌሎቹ ደግሞ በምግቡም፣ በልብሱም፣ በሳሎኑም በምኝታ
ቤቱም የሚፈጠርባቸውን ቅሬታ የቤት ማፍረሻ ምክንያት የሚያደርጉ የዋሐን ባለቤቶች ናቸው፡፡
‹የላሞች ጠብ በረቱን ለተኩላ፤ የውሾች ጠብ መንደሩን ለጅብ ይሰጠዋል› እንደሚባለው፣ እነዚህ የቤት ልጆች ከውጭ ያሰፈሰፈውን ጠላት
ባለማወቅ የሚያደርጉት ጠብ፣ ከተራ እሰጣገባ አልፎ ሳያስቡት ቤቱን ያፈርሰዋል። አንዴ ከፈረሰ በኋላ ለውስጦቹ ትርፋቸው ቁጭት
ይሆናል። ከመሆኑ በፊት እንጂ ነገሮች ከተበለሻሹ በኋላ መጸጸትና መቆጨቱ ምንም ትርጉም የለውም፡፡ ሦስተኞቹ ደግሞ ተኝተው ቤት
የሚያፈርሱ ናቸው።፡ የቆሸሸውን ማጽዳት፣ የተሰነጠቀውን መጠገን፣ የጎደለውን ማሟላት፤ የጠመመውን ማቅናት ሲገባቸው እእ ምን አገባኝ›
ብለው ይተኛሉ። አጥሩ ሲፈርስ ሳሎን ሲድረስ ይላሉ፤ ሳሎን ሲፈርስ ምኝታ ቤት እስኪደርስ ይጠብቃሉ፤ ምኝታ ቤቱ ሲፈርስ ጓዳ
ተደብቀው በመተኛታቸው የሚተርፉ ይመስላቸዋል። ሁሉም ግን የጊዜ ጉዳይ ይሆናል፡፡
ዛሬ ታላቋ ቤታችን ኢትዮጵያ በዚህ ሁኔታ ላይ ናት፡፡ ሦስቱም ዓይነት ልጆች አሏት፡፡ ከውጭ ጠላቶቿ ጋር ይሁነኝ ብለው በዓላማ ለማፍረስ
የሚሠሩ፤ በዓላማ ባይገጥሙም በውጤት ከውጭ አፍራሾች ጋር የሚሠሩ፤ ቤታቸው ሲቃጠል እያዩ ከመንቃት ይልቅ በሙቀቱ ተከናንበው
የተኙ። ይህ ወቅት ለኢትዮጵያ ከወሳኝ ወቅቶች አንዱ ነው፡፡ በአንድ በኩል ፍትሐዊ፣ ዴሞከራሲያዊና ተአማኒ ምርጫ አድርገን በሕዝብ
ድምጽ የሚጸና መንግሥት ለመመሥረት በሂደት ላይ ነን በሌላ በኩል ደግሞ የሀገራችን ከፍታ አንዱ ማሳያ የሆነውን የሕዳሴውን ግድብ
ሁለተኛውን ዙር ሙሌት ለማከናወን እየተጋን ነው።
ከእነዚህ ጎን ለጎን የኢትዮጵያ ግሥጋሴ ከሚያሠጋቸው የውጭና የውስጥ ጠላቶች ጋር በየአቅጣጫው ግንባር ለግንባር ገጥመናል፡፡ ኢትዮጵያ
እነዚህን ሦስት ፈተናዎች አልፋ ግቦቿን ካሳካች፣ ከዚያ በኋላ ለማንም በቀላሉ እጅ የማትሰጥ የሁላችን መመኪያ ሆና ትወጣለች፡፡ ይህ
እንዳይሳካ ከምንጩ እናደፍርሰው፣ ከእንጎቻው እንሰቅስቀው፣ ከእሸቱ እናጠውልገው› የሚሉ የማሰናከያ ድንጋዮች በየአቅጣጫው
ተነሥተዋል፡፡ ወሳኙ የእነርሱ መነሣት አይደለም፤ የእኛ ምላሽ እንጂ።
ውድ የሀገራችን ሕዝቦች፣
ከለውጡ ጅማሬ አንሥቶ የገዛ ዛፋችንን ከዛፉ በተቆረጠ ጠማማ እንጨት የመቁረጥ አዝማሚያ መኖሩን እየተናገርንም እየታገልንም ነበር።
በተለያየ አቅጣጫ የሚወረወረው ድንጋት በቤታችን ላይ የሚያደርሱትን አደጋ ለመግታት፣ የፖለቲካ አመራሩና የጸጥታ አካሉ መሥዋዕትነት
የተከፈለበት ትግል አካሂዷል። ከጁንታው ጋር የተደረገው ትግል የዚህ አንዱ ማሳያ ነው፡፡ እነዚህ አካላት ዛሬም አልጠፉም፡፡ የተለያዩ
ብሔሮችን ስሞች ይዘው፣ ሲመች በሰላም ሳይመች በጠመንጃ የላኪዎቻቸውን ዓላማ ለማሳካት እየሠሩ ነው፡፡
የእነዚህን ተልዕኮ ያልተረዱ የዋሖች ደግሞ ሀገር እንድትፈርስ ባይፈልጉም ሀገር እንድትፈርስ ግን እየሠሩ ነው። የቤቱ ጥያቄ የሚመለሰው
መጀመሪያ ቤቱ ሲኖር መሆኑን ዘንግተውታል፡፡ ቤት እያፈረሱ ስለ ቤት ለመወያት ይፈልጋሉ፡፡ ‹ቤቴን እጠብቃለሁ፤ ሙሣቴንም እሟገታለሁ›
የሚሉ አባቶች ልጆች መሆናቸውን ረስተውታል። ስለ ላሟ ወተት የሚኖረው ጥያቄ የሚመለሰው መጀመሪያ ላሟ ስትኖር መሆኑን
ረስተውታል። ከእነዚህ ከሁለቱ ጋር ተደምረው ‹ምን አገባኝ የሚሉ ዜጎችም አሉ፡፡ ምድር ቤቱ ሲቃጠል እሳቱ ሰባተኛ ፎቅ ላይ የሚደርስ
የማይመስላቸው፡፡ ወይ ለመገንባት ወይ ለመመከት አንዳች የማያደርጉ፡፡ እሳቱን ከመከላከል ይልቅ በሙቀቱ ተመቻችተው ያንቀላፉት
ጭምር የሀገራችን ችግሮች ናቸው፡፡
አሁን በአለንበት ጊዜ ሦስት ወሳኝ ዓላማዎቻችንን በጽናት ማሳካት ይኖርብናል። በመጀመሪያ አንድ ወር ያህል ጊዜ የቀረውን ምርጫ ውጤታማ
እናድርገው፡፡ በነቂስ ወጥተን ካርድ እንውሰድ። ሁላችንም ይበጀናል ያልነውን እንምረጥ። የፈለግነውን እንዳንመርጥ እንቅፋት የሚሆንብን
የትኛውም አካል እርሱ የኢትዮጵያ ጠላት ነው፡፡ የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን እየተቋቋምን፤ ችግሮችን እያረምን፣ ጉድለቶችን እየሞላን
ምርጫውን ውጤታማ እናድርገው። ይሄንን ምርጫ በድል ተወጣነው የምንለው ሂደቱ የሚጠበቅበትን ደረጃ ለማለፍ ከቻለ ነው፡፡ ለዚህ
ደግሞ መራጩ ሕዝብ፣ ተመራጮች እና የምርጫ ቦርድ ሀገራዊ ኃላፊነታችሁን እንድትወጡ አደራ እንላለን፡፡
ሁለተኛ ከምርጫው ጎን ለጎን ግድባችንን ባቀድነው መንገድና ጊዜ መገንባትና ሁለተኛውን ዙር የውኃ ሙሌት ማከናወን አለብን፡፡
የትኛውንም ዓይነት ጫና ተቋቁመን፤ የውስጥና የውጭ ፈተናዎቻችንን አልፈን እንሞላዋለን፡፡ ኢትዮጵያን መውደዳችንን የምናሳየው
የኢትዮጵያን ጉዞ በማቀላጠፍ እንጂ በማደናቀፍ አይደለም፡፡ በእሳት ላንቃ ውስጥ እያለፍንም ቢሆን ማድረግ ያለብንን ማድረግ አለብን፡፡
በያዝነው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ግድባችንን ሞልተን ኃይል ማምረት እንጀምራለን በየአቅጣጫው የምናየው የወገኖቻችን አሰቃቂ ግድያ፣
ማፈናቀል፣ ቤትና ንብረት ማውደም፣ ነውጥና ሸፍጥ ሁሉ በሀገር ውስጥ ብቻ የተመረተ አይደለም፡፡
አብዛኛው ጥፋት በውጭ ተምርቶ በሀገር ውስጥ የሚገጣጠም ጥፋት ነው፡፡ ግጭቱንና ጥፋቱን ከውጭ አስመጥተው በሀገር ውስጥ
የሚገጣጥሙት የእፉኝት ልጆች ናቸው። በዚህ ዓመት መጀመሪያ የእፉኝቶችን ዋና መፈልፈያ አፍርሰነዋል። ከዚህ በፊት ፈልፍሎ እዚህና
እዚያ የጣላቸው ግልገሎቹ ግን አሁንም ይቀራሉ፡፡ የትኛውንም ዓይነት የብሔርና የአምነት ስም ቢይዙ፤ ከየትኛው የውጭ ኃይል የሚረዱትን
ገንዘብና መሣሪያ ቢጨብጡ ኢትዮጵያን ይፈትኗት ይሆናል እንጂ አያሸንፋፏትም፡።፡
መጀመሪያ በውስጣችን ያሉትን ባለ ሁለት በላዋዎች እናጸዳለን። ቀን ቀን ለኢትዮጵያ የሚሠሩ የሚመስሉ፤ ሌሊት ሌሊት በኢትዮጵያ ላይ
የሚዶልቱ አሉ። እነርሱ ከውጭ ጠላቶቻችን በላይ ዋነኞቹ ጠላቶቻችን ናቸው፡፡ አጥር ላይ ተቀምጠው፣ አሸናፊውን አይተው፣ ከተመቻቸው
ሊገቡ፣ ካልተመቻቸው ሊሸሹ የሚያስቡ መኖራቸውን ዐውቀናል፡፡ ወቅቱ የምርጫ ነውና መምረጥ አለብን፡፡ ወይ እነርሱን እናጸዳለን ወይ
ኢትዮጵያን አሳልፈን እንሰጣለን። የኛ ምርጫ ኢትዮጵያን ሰእነርሱ ስንል መሠዋት ሳይሆን፤ እነርሱን ለኢትዮጵያ ስንል መሠዋት ነው፡፡
በአጠቃላይ ምርጫውን ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ፍትሐዊ ለማድረግ፤ ግድባችንን በታቀደለት መንገድ ገንብተን ሁለተኛውን ዙር የውኃ
ሙሌት ለማከናወን፤ እንዲሁም ኢትዮጵያን ከውስጥና ከውጭ ጠላቶቿ ታድገን ወደሚገባት ደረጃ ለመውሰድ እንድንቸል፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ
በንቃትና በብስለት ከመንግሥት ጎን እንዲቆም ጥሪ እናደርጋለን። ቆም ብለን እናስብ፤ ከሁሉም በፊት ኢትዮጵያን እናስቀድም፡፡ በፌዴራልና
በከልል የምትገኙ የጸጥታ አካላት፣ ተቀናጅታችሁና ተናብባችሁ በመሥራት የኢትዮጵያንና የኢትዮጵያውያን ሰላምና ደኅንነት እንድታስጠብቁ
እናሳስባለን።
የሚደረጉ ማናቸውም የፖለቲካና የመብት እንቅስቃሴዎች ይደገፋሉ፡፡ የትግላችን ውጤቶች ናቸውና፡፡ እነዚህ የመብትና የፖለቲካ
እንቅስቃሴዎች ግን ኢትዮጵያን እንዲያናውጡ አንፈቅድም፡ ፖለቲካዊ ጨዋታውን ከጨዋታ ሜዳ ውጭ ለማድረግ ለሚፈልጉት ኃይሎች፣
ትእግሥታችን ማለቁን በዚሁ ኢጋጣሚ ልንነግራቸው እንፈልጋለን። ሁሌም እንደምንለው፤ በጽናትም እንድምናምንበት፣ ለኢትዮጵያ ፈተና
ብርቋ፣ ድል ማድረግም ሰበር ዜናዋ አይደለም፡፡ ከዚህ በላይ አልፋ ዛሬ ላይ ደርሳለች። ይሄንን አልፋ ነገ ላይ ትገኛለች፡። ኢትዮጵያ ማሸነፏ
ላይቀር እንዳታሸንፍ ሲታገሉ የኖሩትን ትታዘባቸዋለች፤ በታሪከ ሂደትም ትቀጣቸዋለች፡፡ እርሷ ግን ወጥመዱን በጣጥሳ፣ ሰንኮፉን ነቃቅላ፣
አዚሙን አስወግዳ ያሰበችበት ትደርሳለች።
ኢትዮጵያ እስካሁን የቆየችውም ወደፊትም የምትቆየውም፣ በእኛ በመስዕዋት ልጆቿ ደምና አጥንት ነው። ዛሬ እኛ የምንከፍለው ዋጋ፣ ነገና
ከነገወዲያ ሀገራችንን ወደማይቀለበስ የብልጽግና ከፍታ ላይ እንደሚያደርሳት ምንም ጥርጥር የለውም፡፡
የብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት
ሚያዚያ 16፣ 2013 ዓ.ም
አዲስ አበባ

 በአገራችን ለ10ኛ ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዳግም ለ24ኛ ጊዜ የሚከበረው ዓለም አቀፍ የፓርኪንሰን ቀን ከትናንት በስቲያ ተከበረ፡፡ “ትኩረት ለፓርኪንሰን ሕሙማን” በሚል መሪ ቃል በተከበረው በዚህ በዓል ላይ የፓርኪንሰን ህሙማን የሚገጥማቸውን የጤና ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች የሚዳስሱ ልዩ ልዩ ዝግጅቶች ቀርበዋል፡፡
በፕሮግራም ላይ ንግግር ያደረጉት የፓርኪንሰን ህሙማን መርጃ ተቋም መስራች ወ/ሮ ክበረ ከበደ እንደተናገሩት፤ የፓርኪንሰን በሽታ ሊድን የማይችልና በየጊዜው እየተባበሰ የሚሄድ መሆኑን አስታውሰው፤ ህሙማኑ ለከፋ ችግርና የህመም ስቃይ እንዳይዳረጉ ለማድረግ የሚያስችሉ መድሀኒቶች ማግኘት ይኖርባቸዋል፡፡
በአገራችን ግን ህሙማኑ በመድሀኒት እጦት ሳቢያ እጅግ ለከፋ ስቃይና ህመም ሲዳረጉ ማየት የተለመደ ሆኗል ብለዋል፡፡ መንግስትና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ህሙማን መድሀኒት ማግኘት የሚችሉበት ሁኔታ ላይ ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ ይገባል  ሲሉም ተናግረዋል።  
ህብረተሰቡ ለፓርኪንሰን ህሙማን ተገቢውን ጥበቃና እንክብካቤ በማድረግ ህሙማኑ ከሚያጋጥማቸው ማህበራዊ መገለልና ችግር ሊታደጓቸው ይገባል ብለዋል።


     ከዕለታት አንድ ቀን አንድ አዋቂና አንድ አላዋቂ በመንገድ ላይ እየተጓዙ ሳለ አንድ አውራዶሮ አጥር ላይ ሆኖ ሲጮህ ያያሉ፡፡ ይሄኔ አላዋቂው፤
 “ይሄ አውራ ዶሮ እዚህ መሬት ላይ ሲጮህ‘ኮ እመንግስተ - ሰማይም ልክ ይሄንኑ የሚመስል አውራ ዶሮ በዚሁ ሰዓት ይጮሃል” ይላል፡፡
አዋቂው አዋቂ ነውና፤ “እኔ አይመስለኝም” ይላል፡፡
አላዋቂው፤ “ለምን? አስረዳኛ!”
አዋቂው፣ “አየህ እንደ ዶሮ ያለ ልክስክስና ኩሳም ነገር መንግስተ-ሰማይን ያህል ንፁህ ቦታ አይገባም” አለው፡፡
አላዋቂው አላዋቂ ነውና ለምን እሸነፋለሁ ባይ ነው፡፡
 “አይ ዶሮው ሲጮህ አፉን ወደ መንግስተ-ሰማይ፣ ቂጡን ወደ ሲዖል አድርጎ ስለሆነ ምንም ችግር አይኖርም” ይላል፡፡
 አዋቂው፤ አዋቂ ነውና አልለቀቀውም፡፡
#እንደሰማሁት ሲዖል እርጥቡን የሰው ስጋ እንኳን እንደ ጉድ ያነደዋል ነው የሚባለው፡፡ እንዲህ ያለውን የአውራ ዶሮ ላባማ እንዴት አድርጎ ይምረዋል?” ሲል ጠየቀ፡፡ ይሄኔ አላዋቂው፤ ቆጣና ፍጥጥ ብሎ፤ “ዎ!ዎ! እኔ ምን ቸገረኝ ያባቴ ዶሮ አይደለ ቢያንበገብገው?!” አለ፡፡
 * * *
በየግል መድረኩ፤ በየመሸታ ቤቱ፣ በየሻይ ቤቱ፣ በየሬስቶራንቱ ወዘተ… በዕውቀት መከራከር ከቀረ ውሎ አድሯል፡፡ የተማረ የማይከበርበት፣ ያልተማረ ዘራፍ ሲል የሚደመጥበት ሁኔታ እየበረከተ የመጣበት ዘመን ነው፡፡ በመናገርና አውቆ በመናገር መካከል ልዩነቱ ከመከነ ሰንብቷል! አገሩን፤ “እኔ ምን ቸገረኝ ያባቴ ዶሮ አደለች!” ብሎ በምንግዴ የሚያየው ዜጋ በሚያስገርም ሁኔታ እንደ ባክቴሪያ የሚራባበት አየር እየተፈጠረ ነው፡፡ አገርን መሰረት አድርጎ ፖለቲካን፣ ኢኮኖሚን አሊያም ባህልን ማየት የተነወረበት ጊዜ እየመጣ ይመስላል፡፡ አለማወቅና ስግብግብነት ሲቀናጁ ምን ዓይነት አደጋ ላይ እየጣሉን እንደሆነ ማየት ተስኖናል፡፡ ካፒታሊዝም፤ እናት - አይምሬ ነው! የገዛ ወላጁን ሳይበላ የማይተኛ ሥርዓት ነው፡፡ ሼክስፒር እንደሚለው፤
“ያባትክን አሟሟት ሰበብ፣
 ለማወቅ ሲፈላ ደምህ
ወዳጁንም ጠላቱንም፣
 አብሮ መጥረግ ነው በቀልህ??”
ሊባል የሚችል ጣጣ ውስጥ እየገባን እንደሆነ ማስተዋል ደግ ነው፡፡ ካፒታሊዝም፤ “ለሰላምታም ለጭብጨባም ቫት የሚከፈልበት መሆኑን በአክብሮት እንገልፃለን” ሊያሰኘን የሚችል ምስጥም ዐይን - አውጣም ስርዓት መሆኑን አንዘንጋ፡፡ በአሁኑ ሰዓት ዕውቀት የሚያቀጭጭ ክፉ ባህል ጭበጨባ ነው! አደጋም ነው! ባመኑበትም ባላመኑበትም ማጨብጨብ፣ ባወቁትም ባላወቁትም ማጨብጨብ እርግማን ነው፡፡ ምክን (Reason) የማይገዛው ማህበረሰብ፣ ለገደል ቅርብ ነው ይላሉ ጸሀፍት፡፡ “እባካችሁ ክቡር እምክቡራን የተከበሩ፣ አቶ ወይም ወ/ሮ እገሌን ወደ መድረኩ ጋብዙልኝ” ይላል የመድረክ መሪው፡፡ ከዚያ ጭብጨባ ነው፡ ፡ ቸብ! ቸብ! ቸብ! ትንሽ ቆይቶ፤ “እባካችሁ የተከበሩ ክቡር እምክቡራን አቶ ወይም ወይዘሮ እገሌን ወደ ቦታቸው ሸኙልኝ!” አሁንም ቸብ!...ቸብ!...ቸብ!... ይቀጥላል፡፡ የጭብጨባ ባህል! የፓርቲ አባል ያጨበጭባል፡፡ የድርጅት አባል ያጨበጭባል፡፡ የጎሣ አባል ያጨበጭባል፡፡ ጓደኛና ቲፎዞ ያጨበጭባል፡፡ የተማረው ያጨበጭባል! ያልተማረው ያጨበጭባል! አዋቂው ያጨበጭባል! አላዋቂው ያጨበጭባል! ሃይማኖተኛው ያጨበጭባል! ሃይማኖት - አልባው ያጨበጭባል! የኪነ-ጥበቡ ሰው እያጨበጨበ ጭብጨባ ይቀላውጣል!... ከዚህ የጭብጨባ ባህል ማን ይገላግለን ይሆን? ለጭብጨባም የአየር ሰዓት የሚጠየቅበት ወቅት እየመጣ ነው፡፡ ከማቴሪያል ሙስና ወደ ህሊና ሙስና እየተሸጋገርን ይመስላል! የድንቁርና ሙስናና የዕውቅና ሙስና ምን ያህል እንደሚተጋገዙ የምናይበት ጊዜ ሩቅ አይደለም፡፡ ይሄ ሁሉ ሆኖ አውራ - ዶሮው መጮሁን ይቀጥላል፡፡ የውሻና ግመሎቹ ነገር (The dog barks but the caravan goes) አብቅቶ፤ ግመሎቹም ውሻዎቹም አውራ - ዶሮውን እያዳመጡ መከራከር የጀመሩበት ጊዜ ነው፡፡ አውራ ዶሮ የጮኸውን ያህል ክርክሩም ይጮሃል፡፡ ያገራችን ነገረ በተመለደና ባልተለወጠ ነገረ - ሥራ መጯጯህ መሆኑ ያሳዝናል! ልማዳዊ አካሄዳችን አልለወጥ የሚለው ለውጥ ስለሌለ ይሆን? ሁሉ ነገር የልማድ፣ የወግ፣ የወረት (የfashion) ተገዢ የሆነ መምሰሉ ይገርማል፡፡ የእገሌ ራዕይ፣ ራዕይ፣ ራዕይ … እንደጀመርን … እንደጀመርን … (አንዴ ከገባንበት ስሜት ዓይነት ጭምር)… እንዳጋመስን … እንዳጋመስን … ስንጨርስስ? … እንደጨረስን… እንጨርሰዋለን … እንዳይሆን ያሰጋል፡፡ ከዘፈን ወደ መፈክር መሄድ፣ ከዘፈን ወደ ዘፈን ከመሄድ የተሻለ ነው ወይ? የሚለውን ለማረጋገጥ መሞከር ብልህነት ነው፡፡
 የእኛው ፀሐፌ ተውኔት፣ ገጣሚ ፀጋዬ ገ/መድህን የሚለንን መስማት ደግ ነው፡- “አንድ የፍየል ሙክት ቆዳ እያለፋ ስልቻ የሚያወጣና የሚያዜም ሰራተኛ ነበር፡፡ ደግሞ ጆሮ ደግፍ ይዞታል፡፡ እና ቆዳ ሲያለፋ በረገጠ ቁጥር ያመው ነበር፡፡ በዚያ ምክንያት ዘፈኑ ይበላሽበትና ወደ ለቅሶ ይለወጥበታል። ወደ ህመም ይለወጥበታል፡፡ ግን ህመሙን በዘፈኑ ማስታመም እንጂ ከእዚያ እቤት የሚሰማውን ቻቻታ መስማት አይፈልግም፡፡ እዚያማ የሙክቱ ሥጋ ይበላል፡፡ ሰዎች በደስታ ያሳልፋሉ፡፡ እሱ ግን እዚህ ቆዳ እያለፋ ይሰቃያል” ያው ያንዱ ደስታ ላንዱ ዋይታ ነው፡፡ “ህመምን በዘፈን ማስታመም” አንዱ በሽታችን ነው፡፡ ፖለቲካችን የዚህ በሽታ ልክፍት እንዳለበት ልብ ካላልን አንድንም! የሀገራችን ኢኮኖሚ፤ እሱን ተከትሎም የኑሮ ደረጃውን፤ ማመዛዘን ግራ አጋቢ ነው፡፡ በዚህ ፋሲካ ወይም በሌላ ማናቸውም ክብረ በዓል የሰውን አኗኗር ለማሰብ ብንሞክር፤ …ከዓመታት በፊት ዶሮ እንዴትና በምን ዋጋ ይበላ እንደነበር የሚተርክ ሰው ይገኛል፡፡ ዛሬ አይበላም፤ “አይ ኑሮ” ይላል፡፡ ሌላው ዶሮ አርዷል። በግም አርዷል፡፡ “የቅርጫውን ዋጋ አልቻልነውም‘ኮ፤ ይሄ የኑሮ ውድነት ተጫወተብን! አይ ኑሮ!” ይላል፡፡ የመጨረሻው ዶሮም አለው፡፡ በግም አርዷል፡፡ “በሬው ግን ከቄራ ይገዛ ወይስ ተነድቶ ከገጠር ይምጣ? ቀረጡ፣ ማስነጃው ሰማይ ወጣ እኮ!” “አይ ኑሮ!” እያለ ያማርራል፡፡ በዚህ ኢኮኖሚ ጥላ ሥር ፖለቲከኛው የራሱ ቋንቋ ነው ያለው፡፡ የሕግ የበላይነት ተከብሮ ቢሆን  ኖሮ… የፖለቲካ ምህዳሩ ሰፍቶ ቢሆን ኖሮ … በቂ ተቋማት ተዋቅረው ቢሆን  ኖሮ… ሰብዓዊ መብት ቢከበር ኖሮ… ዲሞክራሲ ዕውነት ቢሆን ኖሮ… በቂ ኮንዶምኒየም ተሰርቶ ቢሆን ኖሮ… የፕሬስ ችግር ቢፈታ ኖሮ…”
አይ ኑሮ! አገራችን ከምትችለው በላይ ኑሮና ኗሪ ተሸክማ የምትጓዝ ናት፡፡ ይሄን ሁሉ ኑሮ፣ ድህነትና ሃሳዊ ጥጋብ መፍቻ ቁልፉ፣ የህዳሴው ግድብ ከነዙሪያ ገባ ዲፕሎማሲው ነው… ለማለት ለጤናማ ኢኮኖሚስትም ለጤናማ ሀገራዊ ፖለቲከኛም ያስቸግራል፡፡ አንድ ያላት ጥርስ በዘነዘና ትነቀስ አይሆንም፡፡ ዶሮ ብታልም ጥሬዋንም አይሠራም፡፡ ዘርፈ - ብዙና መረበ - ብዙ መፍትሔ እናገኝ ዘንድ ዘርፈ - ብዙ ልብ ይስጠን፡፡
“ለሰው እንተርፋለን እንኳን ለራሳችን” የሚለው የዱሮ መፈክር፣ ትዝ ይለናል፡፡ ከዚያ በፊት ግን እርስ በርስ በመተሳሰቡ፣ ለወገን ፈጥኖ በመድረሱ፣ወዘተ-- የማንታማ ልንሆን ይገባል፡፡ ሁሌ እንግዳ ተቀባይ ነን እንደምንል ሁሉ፣ ሁሌ ለጋሥ ነን ማለትን እንፈልጋለን፤ ቅንነታችን የተባረከ ይሁን! በተጨባጭና ከልብ እንግዳ ተቀባይ፣ በተጨባጭና ከልብ ያለን የተረፈንና ለሌላ የምንለግስ ልንሆን ይገባል፡ ፡ በመብራቱም፣ በውሃውም፣ በቡናውም፣ በጤፉም፣ በበጉም በከብቱም፣ በዲሞክራሲውም፣በሰለጠነ የፖለቲካ ባህሉም፣በነጻና ፍትሃዊ ምርጫውም ወዘተ-- የዚህ ዕውነታ ዕሙን ሊሆን ይገባል፡፡ አለበለዚያ “ሳይተርፋት አበድራ ሳትቀበል ሞተች” የሚለው ተረት ዕሙን ይሆናል!!  …አንዳንድ ሰዎች ግንኙነታቸውን ጥሩ ወይም መጥፎ የሚያደርገው ሌላው ሰው ይመስላቸዋል። ህይወት ግን እንደዚያ እይደለችም። ለፍቅር ሃይል፤ “ፍቅር የምሰጠው ሌላው ሰው ፍቅር ሲሰጠኝ ብቻ ነው” ማለት አይቻልም፡፡ አንተ ቀድመህ ካልሰጠህ በቀር ምንም ነገር አታገኝም፡፡
ሁሌም  የሰጠኸውን ትቀበላለህ እናም ነገሩ ፈጽሞ  ከሌላው ሰው ጋር አይገናኝም፣ አንተን ብቻ የሚመለከት ነው! ነገሩ አንተ ከምትሰጠውና ከሚሰማህ ስሜት ጋር ብቻ የተገናኘ ነው።
ከማንኛውም ሰው ጋር ያለህን ግንኙነት ለማሻሻል የምትሻ ከሆነ፣ የዚያ ሰው በጎ ነገሮች ላይ አተኩር። የዚያ ሰው የምትወድለት የምታደንቅለትና ምስጋና ሊቸረው ይገባዋል የምትላቸውን ነገሮች ፈልግ። አሉታዊ ነገሮቹ ላይ ከማተኮር ይልቅ ሆን ብለህ የምትወድለትን ነገር ለመፈለግ ብትጥር የማይታመን ተዓምር ይፈጠራል። ምናልባት ላንተ በሌላው ሰው ላይ አንድ የማይታመን ነገር- የፍቅር ኃይል ነው። ምክንያቱም የፍቅር ኃይል አሉታዊነትን ያከሽፋል፤ በግንኙነት ውስጥ ያለውን አሉታዊነት ጨምሮ። አንተ ማድረግ ያለብህ፤ የዚህን ሰው የምትወድለትን ነገሮች በማሰስ፣ የፍቅርን ኃይል ለዓላማህ ማዋል ነው። ያኔ ግንኙነታችሁን በተመለከተ ሁሉም ነገር ይለወጣል።
በፍቅር ኃይል የታደሱ በመቶዎች የሚሰሉ ግንኙነቶች አውቃለሁ። ከሁሉም ግን ሊፈርስ የተቃረበ ትዳሯን በፍቅር ኃይል ማቃናት የቻለች የአንዲት ሴት ታሪክ ጎላ ያለ ስፍራ ይሰጠዋል። ምክንያቱም ይህቺ ሴት ፍቅር መስጠት ያለውን ሃይል ስትረዳ፣ ምንም እንኳ ትዳሯ በችግሮች የታጠረ ቢሆንም ወዲያውኑ የደስታ ስሜት በውስጧ ለመፍጠር ወሰነች። ያኔ ቤታቸው ውስጥ ያረበበው የደመና ድባብ ተገፈፈ። እናትየዋ ከልጆቿ ጋ የነበራት ግንኙነት ተሻሻለ። ከዚያም የጋብቻ ፎቷቸውን አውጥታ ፊት ለፊት አኖረችው- በየቀኑ ለመመልከት፡፡ ይሄን በማድረጓ አንድ አስገራሚ ነገር ተከሰተ። ለባሏ የነበራትን የቀድሞ ፍቅር አስታወሰች። ፍቅር ተመልሶ ሲመጣ ተሰማት። የፍቅር ስሜት በአስደናቂ ሁኔታ በውስጧ እየበረታ መጣ። ባሏን እንደ አዲስ አፈቀረችው። ከፍቅሯ ታላቅነት የተነሳ የባሏ ድብርትና ቁጣ ጥሎት ጠፋ። ጤንነቱ መመለስ ጀመረ። ከቤቷ ብር ብላ ለመጥፋት ትመኝ የነበረችው ወይዘሮ፤ ወደ ትዳሯ ተመልሳ የሚቀናበት ፍቅር ፈጠሩ፡፡
በግንኙነት ውስጥ ፍቅርን መስጠትን በተመለከተ ሰዎችን ስለሚያሳስት አንድ ነገር እናውራ። ይኼ ነገር ብዙዎች ማግኘት የሚገባቸውን ህይወት እንዳያገኙ ከልክሏቸዋል። ነገሩ አሳሳች የሆነው ሰዎች ፍቅር መስጠት የሚለውን ጉዳይ በተሳሳተ መንገድ ስለተረዱት ነው። ለሌሎች ፍቅር መስጠት የሚለው ጉዳይ በጣም ግልጽ እንዲሆንልህ፣ ለሌሎች ፍቅርን አለመስጠት ምን ማለት እንደሆነ መረዳት አለብህ።
ሌላውን ሰው ለመለወጥ መሞከር ፍቅር መስጠት አይደለም! ለሌላው ሰው የሚበጀውን  እኔ አውቅለታለሁ ብሎ ማሰብ ፍቅር መስጠት አይደለም! ራስን ትክክለኛ ፣ ሌላውን ጥፋተኛ  ማድረግ ፍቅር መስጠት አይደለም! ነቀፌታ፣ ወቀሳ፣ ማማረር፣ መነዛነዝና አቃቂር ማውጣት ፍቅር መስጠት አይደለም!
በግንኙነታችን ውስጥ መውሰድ የሚገባንን ጥንቃቄ የሚሳይ አንድ ታሪክ ላካፍልህ። አንዲት የተማረረች ሚስት፣ ልጆቿን ሰብስባ ባሏን ጥላው ከቤት  ትወጣለች። ባል ሆዬ፤ በዚህ ክፉኛ ስሜቱ ተጎዳ፣ ሁሉንም ነገር በሚስቱ ላይ አላከከ። ውሳኔዋንም አልቀበልም ብሎ አሻፈረኝ አለ።
ሃሳቧን ለማስለወጥ ያልፈነቀለው ድንጋይ አልነበረም። እሱ ይሄን ሁሉ ያደረገው ለሚስቱና ለቤተሰቡ ካለው ፍቅር እንደሆነ ሊያስብ ይችላል። ድርጊቱ ግን የፍቅር አልነበረም። ለትዳራቸው መፍረስ ተጠያቂ ያደረገው ሚስቱን ነው። እሱ ትክክለኛ፣ ሚስቱ ግን ጥፋተኛ እንደሆነች ነበር የሚያምነው። ሚስቱ የራሷን ምርጫ ለማድረግ የወሰደችውን ውሳኔ አልተቀበለም። በመጨረሻ ሚስቱ አካባቢ እንዳይደርስ በፖሊስ ቢነገረውም አሻፈረኝ በማለቱ፣ በቁጥጥር ስር ውሎ ወህኒ ወረደ።
ሰውየው የማታ ማታ ፍቅር እየሰጠ እንዳልሆነ ተገነዘበ። ሚስቱ የምትፈልገውን የመምረጥ ነጻነቷን ሲነፍጋት ፍቅር እየሰጠ አልነበረም። በዚህም የተነሳ እሱም ነጻነቱን አጣ። የመሳሳብ ህግ የፍቅር ህግ ነው። እናም ህጉን መተላለፍ አይቻልም። ህጉን ከጣስክ እራስህን ትጥሳለህ። የፍቅር ህግን የምትከተል ከሆነ ሌላው  ያሻውን እንዳይመርጥ መብቱን አትነፍግም፣ ምክንያቱም ይሄ ፍቅር መስጠት አይባልም።  ልብህ ሲሰበር በጉሮሮ ስለት የመላክ ያህል ስቃይ አለው። እንዲያ ሆኖ ግን የማንንም ሰው ያሻውን  የመምረጥ መብት ማክበር አለብህ። ለሌላው የሰጠኸውን አንተም ታገኘዋለህ። የሌላውን ሰው የመምረጥ ነጻነት ስትነፍግ ፣ የራስህን ነጻነት የሚነፍጉ አሉታዊ ነገሮችን ትጠራለህ። የገንዘብ ፍሰትህ ሊቀንስ ይችላል ወይም ጤናህ ይታወካል አሊያም ስራህ ይበላሻል። እነዚህ ሁሉ ደግሞ ነጻነትህን ይጎዱታል። ለስበት ህግ ሌላ ሰው የሚባል ነገር የለም። ለሌሎች የምትሰጠውን ለራስህ እየሰጠህ ነው።
ለሌሎች ሰዎች ፍቅር መስጠት ማለት፣ በላይህ ላይ እንዲረማመዱ ወይ እንዲጫወቱብህ መፍቀድ ማለት አይደለም፤ ይሄም ፍቅር መስጠት አይባልም። ሌላው ሰው እንዲጠቀምብህ ማድረግ ያን ሰው አይጠቅመውም፣ አንተንም በእርግጠኝነት አይጠቅምህም። ፍቅር አስቸጋሪ (ከባድ) ነው፤ እና በህጉ አማካኝነት እንማራለን፣ እናድጋለን፣ ውጤቱንም እናያለን። ስለዚህ ሌላ ሰው እንዲጠቀምብህ ወይ እንዲጫወትብህም መፍቀድ ፍቅር አይደለም።
(“ተዓምራዊው ኃይል” ከሚለው መፅሐፍ የተቀነጨበ፤ 2003 ዓ.ም)በዚህ መጣጥፍ፣ የኢራን ሙዚቃ መሳሪያዎችን ማስተዋወቅ እንፈልጋለን። ካስተዋወቅናችሁ በኋላ በሁለቱ ሀገሮች ፣በኢራን እና በኢትዮጵያ ባህላዊ ሙዚቃ መሳሪያዎች መሀል ብዙ ተመሳሳይነት እንዳለ ለማየት ትችላላችሁ። ይህም በእነዚህ ሁለት ሀገሮች ባህል ቀደምትና ጥንታዊ ታሪክ መሀል ምስስሎሽ መኖሩን አመልካች ነው።
ሲታር
የሲታር የዘር ግንድ ከእስልምና በፊት ጥንታዊ የነበረው ፐርሽያ ውስጥ የነበረው “ታንቡር” የተባለው የሙዚቃ መሳሪያ  ድረስ የሚመዘዝ (የሚያያይዝ) ነው። ሲታር፣ ከቀጭን የእንጆሪ ዛፍ ዝርያ ከሆነ Mulbeer እንጨት የሚሰራ ሲሆን የመሳሪያው አንገት ከአምስት ወይንም ስድስት ጣትን ወደላይ እና ወደታች በማንቀሳቀስ ድምፅ መቃኘት የሚጣልባቸው አንጓዎች (fits) የታነጸ ነው። “ሲታር” የሚለው ቃል በቃል “ባለ ሶስት ጅማት” የሚለውን ትርጉም ይሰጣል። ነገር ግን አሁን ባለው ወቅታዊ ቅርፅ አራት ጅማቶች  (strings)  ያሉትን ቢሆንም፤ ከመነሻው ግን ሶስት ክሮች/ጅማቶች እንደነበሩት ይገመታል
በሶስት የሚገፋፋ ባህሪው እና ጥልቅ ስሜትን በሚያጭር ድምፀቱ በመንፈሳዊያን ዘንድ ሲታር የሚመረጥ የሙዚቃ መሳሪያ ነው።
ታር
ታር ከክር መሳሪያዎች የሚመደብ ሲሆን አሁን ባለበት ቅርፁ ከአስራ ስምንተኛው ምዕተ አመት አጋማሽ ጀምሮ መከሰት እንደጀመረ ይታወቃል። የመሳሪያው ጎድጓዳ ሳህን መሳይ ክብ መሳይ ክፍል ከMulbeer የእንጆሪ ዛፍ ዝርያ ከሆነ እንጨት የሚሰራ ሲሆን፣ የጣት ማሳረፊያው ረጅሙ የአንገቱ ክፍል ከሃያ ስድስት እስከ ሃያ ስምንት ቅንት ለመለወጥ የሚገለግሉ የታት ማሳረፊያ እርከኖች (feets) ያላዉ ሲሆን፣ ሶስት ድርብ ክር ጥንዶች የሚወጠሩበት ነው። የሚያወጣው የድምፅ እርግብግቢት ከአንድ ከግማሽ እስከ ሁለት “ኦክታቭ” ይደርሳል ተብሎ ይገመታል፣ ክሮቹን በትንሽ መደብ መግረፊያ በመምታት መሳሪያውን ሊጫወት ይቻላል።
ሄይ
ሄይ ምናልባት በክር አማካኝነት ከሚቃኙ ሙዚቃ መሳሪየዎች ሁሉ ለሰው ልጆች ቀደምት እንደሆነ ገመታል። በትንፋሽ የሚነፋው የመሳሪያው ዋሽንት መሳይ መቃ አምስት የጣት ማሳረፊያ ቀደዳዎች ከፊት ለፊት ያሉት ሲሆን በአውራ ጣት የሚደፈን አንድ ቀዳዳ ደግሞ በመቃው ጀርባ በኩል ይገኛል። ከፐርሽያ ባህላዊ መሳሪዎች መሀል እንደ መሰረታዊ የሚቆጠረው ሄይ እስከ ሁለት ከግማሽ ኦክታቭ የድምፅ መጠኑ ሊጎላ እንደሚችል ይታሰባል። የመሳሪያው የላይ ክፍል ከተጨዋቹ አፍ ጋር  ከሚገናኘው ሾል ያ ክፍል ጋር በልጠው ጠባብ ክፍተት ላይ ተደግፎ የሚቀመጥ ነው። ድምፅ ውስጡ የመጀመሪያው ትንፋሽ በምላስ አማካንነት ነው። ወደ መሳሪያው ረድፍ ጀርባ ፣ በአፍ ውስጥ መፈጠር ይጀምራል፤ ይህም ለሄይ በከንፈር አማካኝነት ድምፅ ከሚፈጥሩ መሳሪያዎች የተለየ እና ጥርት ያለ ቅላፄ ያለው ያደርገዋል።
ዳፍ
ዳፍ ከበሮ ቅርፅ ያለው መሳሪያ ሲሆን በብዙ የፐርሺያ ጥንታዊ ከብዙ መቶ አመታት ቀደም ብለው በተሰሩ ስዕሎች እና የሳንቲም ቅርፃ ቅርጾች ላይ ተወክሎ የሚታይ ነው። በመጀመሪያ እይታ በንጽጽር ቀላል ቢመስልም፣ ውስብስብ ምቶችን እና የድምጽ ላጼዎችን የመፍጠር አቅም ያለው መሳሪያ ነው። ዳፍ ከመውጫው ሽፋኑ ስር የብረት ቀለበትና  ሚገጠሙለት በመሆኑ በሚሰጠው ድምጽ ላይ እንደ ደወል መሳይ ቅላጼን ይፈጥራል። የከበሮው ውጫዊ ልባስ ከፍየል ቆዳ የሚሰራ ነው።
ካማንቼ
ካማንቼ ደጋን መሳይ የፐርሽያ ባህላዊ ሙዚቃ መሳሪያ ነው። እድሜ ጠገብ ጥንታዊ መሳሪያ ነው። ከጠጣር እንጨት የታነጸ ቀፎ መሳይ አነስተኛ አካል ያለው ሲሆን ቀፎው አፍ በተወጠረ  የሳሳ ሽፋን ሚለብስ ነው። አንገቱ የሲሊንደር ቅርጽ ያለዉ ሲሆን  የተወጠሩ ክሮች አሉት። በተለያዩ “እሾሃማው ማሲንቆ” ተብሎ ይጠራል፣ ለዚያም ምክኒያቱ በታችኛው  በኩል እንደ እሾህ የሾሉ ቀንዶች ብቅ ብቅ ብለው ስለሚታዩ ነው። መሳሪያውን የሚጫወቱት በቁሙ ነው። ከምዕራቢያኑ “ቫዮላ” ተባለውን መሳሪያ በሚጫወቱበት መንገድ በደጋኑ ላይ የተወጠሩት ክሮች በተጫዋቹ አማካኝነት በሚሳቡ ጊዜ ጥልቅ ሆኑ የድምፅ ለውጥን ይፈጥራሉ። የመሳሪያው አራተኛው ክር በሀያኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ እንደተጨመረ ይገመታል፣ በዚያም ሳቢያ የምዕራባዊያኑ ቫዮሊን ወደ ኢራን የመጀመሪያውን ትውውቅ ማድረግ ቻለ።
ሳንቱር
ሳቱር፣ ባለ ሶስት ኦክታቭ በዝርግ የእንጨት መደብ ላይ ሰባ ሁለት ክሮች የሚወጠሩበት፣ በእንጨት መዶሻ በመምታት ድምፅ ሚሰጥ መሳሪያ ነው። የመሳሪያው ሰባ ሁለት ክሮች በሚቃኙ ሚስማሮች ላይ በአራት- አራት መደብ ተከፍለው የሚታሰሩ ናቸው። ለዝቅተኛ ድምፅ ዘጠኝ (ብሮንዝ) እና ለመሀከለኛ ድምጽ ደግሞ ዘጠኝ (በብረት)
ሳንቱር ከልዩ ልዩ አይነት እንጨት (ከዋልና፣ ከሮዝውድ፣ ከቢቲል ፓም...ወዘተ) እንደሚፈለገው የድምጽ ጥራት ሊሰራ ይችላል። የመሳሪያው የፊት ለፊት ክፍል እና የላይኛው ድምጽ ማስተላለፊያ ልጥፎች የተገናኙ ሲሆን አቀማመጣቸው ለሚፈጠረው የመሳሪያው የድምጽ ጥራት አይነተኛሚና የሚጫወት ነው።
ምንም እንኳን ሳንቱር እድሜጠገብ የሙዚቃ መሳሪያ ቢሆንም በጥንታዊ ስዕሎች ላይ እስከ አስራ ዘጠነኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ቀርቦ አያውቅም።
ቶምባክ
ቶምባክ፣ የፅዋ መጠጫ ቅርጽ ያለው ከበሮ ሲሆን፣ ታንጾ ሚሰራው የእንጆሪ ዛፍ ዝርያ ከሆነ እንጨት ነው። ሰፊ ሆነው የአፉ ጫፍ በጠቦት ወይንም በፍየል ቆዳ ተለብጦ ይሸፈናል። ሁለቱንም እጆች መሳሪያውን ለመጫወት አገልግሎት ላይ ይውላሉ። እጁን በከበሮው ላይ በማንከባለል እስከ ጣትን በተለያየ መንገድ በማፋቸት (srapping) የአጨዋወት ዘዴው ነው። ከፍተኛ ብዛት ያላቸው የድምጽ ቃና በለስላሳ እና ሻካራ መልክ  (textures) አጽንኦት
የመውጣት አቅም ስላለው፣ ተጫዋቹ የሚጫወተውን ዜማ በተለያዩ ቀላማት ለማጋጌጥ እና የምትዞረዋን ለመፍጠር ይረዳዋል።
“ቆም” እና “ባክ” ሁለቱ መሰረታዊ የከበሮው አመታት የውክልና ድምጻቸው ናቸው። የከበሮው መሀል ላይ በመሞት ዝግ ያለውን (ቆም) ድምጽ፣ መሳሪያው ወድ እንደ ጥግ ማግኘት ይቻላል።
ታንቡር
ታንቡር፣ ለአብዛኞቹ ባለ ረጅም አንገት እና ባለ ክር እና የሚመቱ ሙዚቃ መሳሪያዎች እንደ ቅድመ አያት ሊቆጠር የሚችል ነው። የመሳሪያው ሆድ እቃ እንቁ መሳይ ቅርጽ ያለው ሲሆን የእንጆሪ ዛፍ ዝርያ ከሆነ እንጨት ይታነጻል። መሳሪያው ባለ ረጅም አንገት እና ባለ አስራ አራት የጣት መጫወቻ አንጓዎች (ፍሬቶፕ) አሉት።
አንዳንድ ዘመናዊ ታንቡሮች ከጎበጡ የእንጆሪ ዛፍ ቅርንጫፎች የሚሰሩ ናቸው። የመሳሪያው የድምጽ ሳንቃ ከሶስት እስከ አራት ሚሊ ሜትር የሚደርስ ውፍረት ያለው ሲሆን እሱም የሚሰራው ከእንጆሪ ዛፍ እንጨት ነው። ሳንቃው ብዛት ያላቸው ቀዳዳዎች ያሉት እና የተሻለ ድምጽ ለመፍጠር የሚረዱት ናቸው።
ታንቡር ለየት ያለ የአጨዋወት ዘዴን የሚከተል መሳሪያ ነው። በቀኝ እጅ ጣቶች ክሮቹን በመግረፍ የሚርገበገብ፣ ሞልቶ የሚፈስ የድምጽ ቅላጼ ያመነጫል። ይሄ የድጽ ቅላጼ “ሾር” ተብሎ የሚጠራ ሲሆን (ቀጥተኛ ትርጉሙ የውሀ ፍሰት እንደ ማለት ነው)

ኬንያውያን አይኤምኤፍ ገንዘብ እንዳያበድራቸው እየጠየቁ ነው

             አለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም አይኤምኤፍ፣ በኮሮና ሳቢያ ክፉኛ ተጎድቶ የነበረው የአለማችን ኢኮኖሚ በተያዘው የፈረንጆች አመት 2021 በተሻለ ሁኔታ ያገግማል ተብሎ እንደሚጠበቅ ከሰሞኑ ባወጣው ሪፖርት ያስታወቀ ሲሆን፣ የአለም ኢኮኖሚ በአመቱ በአማካይ የ6 በመቶ እድገት እንደሚያስመዘግብ አመልክቷል፡፡
ባለፈው አመት ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ የኔጌቲቭ 3.5 በመቶ ማሽቆልቆል አሳይቶ የነበረው የአለማችን ኢኮኖሚ፤ በቀጣዩ የፈረንጆች አመት በማካይ የ4.4 በመቶ እድገት ያስመዘግባል ተብሎ እንደሚጠበቅም ተቋሙ ባወጣው ሪፖርት ትንበያውን አስቀምጧል፡፡
ያደጉት የአለማችን አገራት በዘንድሮው አመት የ5.1 በመቶ አማካይ እድገት ያስመዘግባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የተነበየው ተቋሙ፤ በማደግ ላይ ያሉ አገራት በአንጻሩ የ6.7 በመቶ እድገት ያስመዘግባሉ ተብሎ እንደሚገመት አክሎ ገልጧል፡፡
በተያያዘ ዜና ደግሞ፣ በብድር የምናገኘው ገንዘብ ለድሃው ህዝብ የሚፈይደው አንዳች ነገር የለም፤ ለባለስልጣናት ኪስ መሙያና ለሙስና ሲሳይ መሆን የለበትም ያሉ ኬንያውያን፤አለማቀፉ የገንዘብ ተቋም ለአገራቸው የገንዘብ ብድር እንዳይሰጥ አቤቱታ ለማቅረብ የድጋፍ ፊርማ ማሰባሰብ መጀመራቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ኬንያውያኑ በድረገጽ አማካይነት #ለኬንያ ማበደር ይቁም; በሚል መርህ በጀመሩት ዘመቻ ፊርማ እያሰባሰቡ እንደሚገኙ የጠቆመው ዘገባው፣ ዘመቻው የተጀመረው ተቋሙ ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ ለኢኮኖሚ ማነቃቂያ የሚውል 2.5 ቢሊዮን ዶላር ለኬንያ ለማበደር መወሰኑን ማስታወቁን ተከትሎ እንደሆነ ገልጧል፡፡

Page 10 of 531