Administrator

Administrator

 “ሰው ከተሰማራ እንደ የስሜቱ ከዋለበት ስፍራ አይቀርም ማፍራቱ” ይባላል። ሁለቱ ወንድማማቾች ፍፁም ዘካሪያስ እና ነብዩ ዘካሪያስ፣ ለዚህ አባባል ሁነኛ ምሳሌዎች ናቸው።
 ፍፁም ዘካሪያስ፤ በአዲስ አበባ ከተማ፣ ታህሳስ 26 ቀን 1979 ዓ.ም ተወለደ። ቅድመ መደበኛ ትምህርቱን በስድስት አመቱ፣ በአቃቂ ክፍለ ከተማ ከሚገኘው የሠ/ማ/ጉ የአፀደ ህፃናት ት/ቤት ካጠናቀቀ በኋላ፣ መደበኛ ትምህርቱን በአቃቂ አድቬንቲስት ሚስዮን ት/ቤት  ከአንደኛ እስከ አስረኛ ክፍል ተምሯል። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱንም  በFTS ት/ቤት በከፍተኛ ውጤት አጠናቆል። ከዚያም በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ  በትያትሪካል አርት የትምህርት  ክፍል በመግባት፣ ትምህርቱን መከታተል ጀመረ።
ሆኖም በንግድ ስራ ላይ ባለውጥልቅ ፍላጎትና ጉጉት ምክያንት፣. የዩኒቨርስቲ ትምህርቱን በማቋረጥ በወላጆቹ  የሆቴል ንግድ ሥራ ላይ ተሰማራ። በኋላም ስለ ንግድ ስራ አዳዲስ  ሃሳቦችንና የዘመኑን በቴክኖሎጂ የታገዘ የንግድ ስራ ክህሎት ለመቅሰም በማሰብ ወደ አውሮፓ ተጓዘ፡፡ በኔዘርላንድ፣ ቤልጅየም ፣ ኒውዘርላንድ ፣ ጀርመንና ሌሎች አገራትም በመዘዋወር  ሁኔታዎችን ሲያጠና ቆይቶ፣ የተለያዩ መረጃዎችንና የቢዝነስ ሃሳቦችን በመያዝ ወደ አገሩ ተመለሰ።
ወንድሙ ነብዩ ዘካሪያስም፣ በአዲስ አበባ፣ በ1983 ዓ.ም ጳጉሜ 4 ቀን ተወለደ። የቅድመ መደበኛ ትምህርቱን የአሁኑ አቃቂ ክፍለ ከተማ በሚገኘው የሠ/ማ/ጉ የአፀደ ህፃናት ትምህርቱን አጠናቀቀ። የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በአፄ ቴዎድሮስ ፣ ሌስፔራንስ ት/ቤት፣ ቃሊቲ በሚገኘው ብሔራዊ ትምህርት ቤት ከተከታተለ በኋላ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ሳሪስ በሚገኘው አይጎዳ  (school of Igoda ) ት/ትቤት በ2002 ዓ.ም አጠናቋል፡፡  የከፍተኛ ደረጃ ትምህርቱን ም፣በመቀሌ ዩኒቨርስቲ ማርኬቲንግ ማኔጅመንት በመማር በ2006 ዓ.ም የመጀመሪያ ዲግሪውን ተቀብሏል።ከዚያም  በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ አስተዳደር በንብረት ክፍል ውስጥ ተቀጥሮ ለአጭር ግዜ ካገለገለ በኋላ፣ ከወንድሙ ፍፁም ዘካሪያስ ጋር በመሆን ወደ ንግዱ ዓለም ተቀላቅሏል።
ወደ ንግዱ ዓለም የተሳቡት ገና በልጅነታቸው በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ በሚገኘው በእናታቸው ስም በተሰየመው ሮሚ ሆቴል ንግዱን መለማመዳቸውን ይናገራሉ። ከፍ ሲሉም በግል ብንቀሳቀስ ይሻላል በማለት ላይ ታች ሲሉ ከርመዋል። ከዓመታት በፊት አስቀድመው የዳቦ ቤት ንግዱን ሲያከናውኑ የቆዩት ወንድማማቾች በሃገራችን  ያልተሰራ ምን አለ ብለው ቆም ብለው ማሰብ ጀመሩ ።
 መኪናዎች በድንገት በመንገድ ላይ ሲበላሹ በፍጥነት እርዳታ የሚሰጥ በማይገኝበት በሃገራችን ለአሽከርካሪዎች የሚሆን መላ አልነበረም ቢኖርም ከእንግልት የሚያድንበት አንዳችም ስልት አልነበረም። በባህር ማዶ  አቅንተው የነበሩት ፍፁም እና  ዘካሪያስ ግን  ይህንን እንግልት ለማስቀረት የመንገድ ዳር የመኪና ብልሽት የእርዳታ ሰጪ ድርጅትን ለመፍጠር ተነሱ እናም  ኑሃ የመንገድ ዳር የመኪና  ብልሽት እርዳታ ሰጪ ድርጅትን ፈጠሩ። 1915 ዓ.ም በአሜሪካ ሃገር የተጀመረው ይህ አገልግሎት በሌሎችም ዓለም ሃገራት እንዲሁም በእንዲሁም በእዚው በአህጉራችን አፍሪካም ኬንያ ፣ በደቡብ አፍሪካም ልምዱ ያለ ነው።
 ከ100 ዓመት በሃላ ወደ ሃገራችን አምጥተነዋል። እኛ የፈጠርነው አዲስ ያለውን የመንገድ ፍሰት ችግር ይሄን ችግር ሊቀርፍ የሚችል ምንድነው ብለን ይሄ ነው በውስጣቸን የመጣው ሲልም አክሎ ተናግሮዋል። አንድ ስራ ሲጀመር ከባድ ቢመስልም በሃላ በሂደቱ እየተማሩ ብዙ መለወጥ እንደሚቻል ያምኑ ነበር።
ዘመኑ ቲክኖሎጂ ያደገበት እንደመሆኑ መጠን የመኪና የመኪና መንገድ ዳር ብልሽት  የሚያመጣውን እንግልት ለማስቀረት ይህን ተቋም እውን ለማድረግ በርካታ ትግሎችን አድርገዋል። የፊልድ መካኒኮች በየአቅራቢያው መኖራቸውን የሚገልጡት መስራቾች በአዲስ አበባ በሁሉም ክፍለ ከተሞች አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን መተግበሪያውን ከplay store በማውረድ ወይም በአጭር የመስመር ቁጥራቸው 6516 ላይ በሚጠሩበት ሰዓት መካኒኮቹ ፈጣን አገልግሎት እንደሚሰጡ ተናግረዋል። የክፍያ ሂደቱም በወር 275ብር በ ሶስት ወር 825 በስድስት ወር 1500 ብር እና በአንድ አመት 3,000 ብር ጥቅል እንዳላቸው ከመስራቹ አንዱ የሆነው ነብዩ ዘካሪያስ ተናግሩዋል።
  በስራ አለም ውስጥ ማንኛውም ከባድ ነገር በትዕግስት ካለፉት የሚቻል ነው ብለው ያምናሉ። የመንገድ ፍልሰቱን ሚዛናዊ የሚያደርገው የኑሃ ፕሮጀክት ባሳለፍነው መጋቢት 20/2015 በተመረቀበት እለት አትሌት ሀይሌ ገ/ስላሴን ጨምሮ ታላላቅ እንግዶች ታድመው የወጣቶቹን ጥረት አድንቀዋል። ኢ/ር አሰፋ መዝገቡ በመንገድ ደህንነት ዙሪያ የሰሩ ባለሙያ ሲሆኑ የኑሃ ሰዎችንም በማማከር ሙያዊ እውቀታቸውን አካፍለዋል። ኢንስፔክተሩም አንድ ተሽከርከሪ መንገድ ላይ ቆሞ ረጅም ጊዜ ሲቆይ አደጋ ማስከተሉ የማይቀር መሆኑን ገልጠው አገልግሎቱ እጅግ ጠቀሜታ ያለው መፍትሄ አምጪ ነው ብለዋል።
በሌሎች ሃገራት ኢንሹራንሶች በፕራይም ጥቅላቸው ውስጥ በማካተት ሰዎች አገልግሎቱን የሚያገኙበትን መንገድ እንደሚያመቻቹ የሚገልጠው ነብዩ ይሄንን ካየን በሃላ ወደ እኛ ሃገር በማምጣት እርሱንም አርቅቀን በምን መንገድ መሆን እንዳለበት ከውንድሜ ጋር ተወያይተን ከጨረስን በሃላ መተግበሪያውን ለማበልጠግ ስድስት ወር ገደማ አቆይቶናል ሲል ገልጠዋል።
በዚህ አምስት አመት ውስጥ ከአዲስ አበባ ውጪ ባሉ ከተሞች እና በሌሎች ክልል ከተሞች እንደሚስፋፋ እንዲሁም ደግሞ ከሁለት ወር በሃላ ሌላ ይፋ የሚያደርጉት የስራ ዘርፍ እንዳለ ገልጠዋል።

Saturday, 08 April 2023 19:44

ከሶሻል ሚዲያ በጨረፍታ

በእውቀቱ ስዩም)
ማዳበርያ

 እንደ ድሮው ብዙ  የሰውነት እንቅስቃሴ አላደርግም፤  ሲነሽጠኝ፥ በሁለት ሳምንት አንድ ቀን ዢም ( gym) እሄዳለሁ፤ ወደ አዳራሹ እንደገባሁ  አሰልጣኙ ሳያየኝ ፥ ኮቴየን  “ ሳይለንሰር “ ላይ አድርጌ፥  ወደ ጥግ ሄድኩና የመጨረሻውን ሚጢጢ ዳምቤል አነሳሁ፤  ዳምቤሉ ከማነሱ የተነሳ   ሁለት ራስ ያለው ትልቅ ቢስማር ነው እሚመስለው! ብዙም አልቆየም፤ የሆነ ድርብ ጭቆና የሚያህል መዳፍ   ትከሻዬ ላይ ወደቀ፤  ዞር ስል አሰልጣኙ ነው፤ እኔን ለማሰልጠን ሳይሆን ለማሰቃየት የተመደበ ነው እሚመስለኝ::  
“ብረት ከማንሳትህ በፊት ማሟቂያ ስራ” ሲል አዘዘኝ::
 “ ምን ልስራ?”
ትንሽ ሲያስብ ከቆየ በሁዋላ እንዲህ አለ፥
“ግራ እግርህን  አንስተህ ፥ በማጅራትህ  በኩል አሳልፈህ ተረከዝህን  ሳም! “
እንደጀመርኩ አካባቢ ከጂሙ ሁለት ጊዜ በዊልቼር እየተገፋሁ ወጥቻለሁ::
 ሰባት ፑሽአፕ ሰራሁና ሰባት ደቂቃ ከመስታወቱ ፊትለፊት ቆምኩ፤ እዚህ ጂም መምጣት ከጀመርሁ ወዲህ  ለውጥ አለ፤ አንገቴ ዙርያ ሲክስ ፓክ አውጥቻለሁ፤  ጥቂት ቆይቶ፥  አሰልጣኙ “ ስኳት”  አሰራኝ!  ጂም ሄደህ ለማታውቅ አንባቢ፤  “ስኳት”  ማለት ሽንት ቤት ልትቀመጥ ፈልገህ ቁጢጥ ማለት ከጀመርክ በሁዋላ ሽንት ቤቱ መበላሸቱን አይተህ ሀሳብህን ፥ቀይረህ ከመንገድ ስትመለስ ማለት ነው::
   “ ስኳት ቢቀረብኝስ “ አልኩት የተንሸራተተ ዲስኬን ወደ ቦታው እየመለስኩ::
  “ የግድ አስፈላጊ ነው” አለኝ አሰልጣኙ፤
 “ምን ያደርግልኛል!”
“ እግርህንና መቀመጫህን ያዳብረዋል”
“ እግሬን ከመቀመጫዬ  ነጥሎ እሚያዳብር ስፖርት የለም?”
 “ የለም!“ አለኝ ኮስተር ብሎ፤” ተያያዥ ስለሆኑ አብረው ነው እሚዳብሩት!“
 ስተክዝ እንዲህ ብሎ አጽናናኝ፤
 “ አትጨናነቅ! መቀመጫህን  ወደ ነበረበት ለመመለስ  በሚቀጥለው አመት  ሌላ ስፖርት እንሰራለን”
 እንቅስቃሴን ስጨርስ ገላዬን ታጠብኩ፤ ከዛ ብብቴን ወይባ ታጠንኩ፤ በአስር አመት ወደ ወጣትነቴ የተመለስኩ መሰለኝ! የሸሚዜን ሦስት ቁልፎች ፈታሁና ሩብ ደረቴን ለብርድና ለህብረተሰቡ እይታ አጋለጥኩት፤ ከ”ሮዛ”  የሞዴል  ማሰልጠኛ ለሻይ እረፍት  የወጡ ኮረዶች፤  “He is out of my league” በሚል አይነት እሚያዩኝ መሰለኝ፤  በዚህ ቅርጽ ላይ ትንሽ ዝነጣ ልጨምርበት ብዬ፥ እግሬን  በስታይል ፥ ጎተት አያደረግሁ መራመድ ጀመርኩ፡፡
  ግቢያችን በር ላይ ስደርስ ፥ ዘበኛው በአዘኔታ  ከንፈራቸውን አስጩኸው መጠጡና ፥
  “ሪህ ነው ልጄ?”

Saturday, 08 April 2023 19:43

ፍቅር ለቆሸሸው

 ፍቅር ለቆሸሸው
ተስፋ ለሟሸሸው
ቀን በእድል ደመና
ሳይነጋ ለመሸው
የሳቅን ውብ ኪነት
ሀዘን ላበላሸው...
እንባ ወዴት ወዴት
ወዴት ነው ‘ሚሸሸው?
ልብ ለጠበበው ልብ ለጨነቀው
ሳግ ለተጋለበው፣ እልህ ለታመቀው
ሕይወት ለመረረ፣ ቅስም ለደቀቀው
ከዐይኖች የሚፈልቀው
ፈልቆ የሚርቀው?
እንባ አያሌው ሞኙን፣ ማነው ያታለለው?
ልብህን ሽሽና፣ ነፃ ላውጣህ ያለው
ካይን አርያም ቁልቁል፣ ወዳፈር የጣለው
በመራቅ መፍትሄ...
በመራቅ ስርየት፥ ያለ ያስመሰለው?
ፍቅር ለቆሸሸው
ተስፋ ለሟሸሸው
ቀን በእድል ደመና
ሳይነጋ ለመሸው
የሳቅን ውብ ኪነት
ሀዘን ላበላሸው...
እንባ አያሌው ሞኙ...
ወዴት ነው ‘ሚሸሸው?
(ረድኤት አሰፋ)

Saturday, 08 April 2023 19:37

ሳህሉ ቢጠፋ አብረን በላን

ከእለታት አንድ ቀን አንድ አንበሳ፣ አንድ ነብር፣ አንድ ጅብ እና አንድ አህያ ችግር ገጥመዋቸው ተሰባስበው ሁኔታውን ለመገምገም ይቀመጣሉ፡፡ የውይይታቸው ርዕስ ‹‹አገሩን ለምን ድርቅ መታው? ዝናብ ለምን አቆመ? ምግብስ ለምን እጥረት ገጠመን?›› የሚል ነበር፡፡ በተደጋጋሚ፤ ‹‹እንዲህ እየተሰቃየን እስከ መቼ እንቆያለን? ያለ ምግብስ በባዶ ሆድ እንደምን ይዘለቃል?›› ይሉ ጀመር፡፡
ከመካከላቸው አንዱ አንድ ሀሳብ ሰነዘረ፡፡
‹‹ምናልባት እኮ ከእኛ መሀል ሀጥያት የሰራ ይኖር ይሆናል፡፡ በዚህ ምክንያት እግዚሀር ለቅጣት የፈረደብን ፍርጃ ሊሆን ይችላል፡፡ አይመስላችሁም?›› ሲል ጠየቀ፡፡
‹‹እውነት ነው›› አለ ሌላኛው፡፡ ‹‹ምናልባት ሁላችንም የሰራነውን ሀጥያት ብንናዘዝና እግዚያብሄርን ይቅርታ ብንጠይቅ ይሻላል፡፡›› በሚል ሀሳብ ሁሉም ተስማሙና  አንበሳ ኑዛዜውን ማሰማት ጀመረ፡፡
‹‹ወንድሞቼ በጣም የሚፀፅተኝን አንድ ሀጥያት ፈፅሜያለሁ፡፡ አንድ ጊዜ አንድ ወይፈን መንደር ውስጥ አግኝቼ፣ ወገቡን በክርኔ ሰብሬ አንድም አጥንት ሳላስቀር በልቼዋለሁ፡፡ ለዚህም ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡››
ሌሎቹ እንስሳት ኑዛዜውን ካዳመጡ በኋላ የአንበሳን ሀይለኝነት ስለሚያውቁና ስለሚፈሩ እራሳቸውን በአሉታ ነቀነቁና፤
‹‹የለም አቶ አንበሳ፤ በጭራሽ ጥፋት አልፈፀምክም፡፡ የሰራኸው ስራም ምንም ሀጥያት የለበትም! እግዚሀር እንድትፈፅም የሚፈልገውን ተግባር ነው ያከናወንከው›› አሉት፡፡
ቀጥሎ ነብሩ ተናዘዘ፤
‹‹ወንድሞቼ፤ በጣም አዝናለሁ፤ እጅግ የሚፀፅተኝን አንድ ሀጥያት ሰርቻለሁ፡፡ ይኸውም አንድ ቀን አንድ ሸለቆ ውስጥ አንድ ከከብቶች ተነጥሎ የሚንከራተት ፍየል አግኝቼ፣ ቁጥቋጦ ውስጥ አድፍጬ ቅርጭምጭም አድርጌ በልቼዋለሁ፡፡ ለዚህም እግዚሀርን ይቅርታ እጠይቃለሁ›› አለ፡፡
ሌሎቹ እንስሳት የነብርን የአደን ችሎታ አድንቀው ሲያበቁ፤ ‹‹በጭራሽ ሀጥያት አልፈፀምክም አቶ ነብር፡፡ እንዲያውም ያንን ፍየል ባትበላው ኖሮ እግዚሀር ይቆጣ ነበር›› አሉት፡፡
ቀጥሎ ተራው ያያ ጅቦ ነበር ‹‹እኔ ሀጥያተኛ ነኝ ወንድሞቼ›› ሲል ጀመረ፡፡ ‹‹አንዴ አንዲት ትንሽ መንደር ውስጥ ገብቼ አንዲት ዶሮ አግኝቼ ቅርጥፍጥፍ አድርጌ በልቻታለሁ››
እንስሳቱም፤ ‹‹ይሄ በጭራሽ ሀጥያት አደለም፡፡ እንዲያውም እግዚሀር ደስ የሚለው ሁለት ሦስቱን ብትበላቸው ነበር›› አሉት፡፡
ለመጨረሻ አህያ ኑዛዜዋን አሰማች፡-
‹‹ከእለታት አንድ ቀን ጌታዬ ጭነት ጭኖብኝ እየነዳኝ ሳለ፤ አንድ ጓደኛውን አግኝቶ ቆም ብሎ መጨዋወት ጀመሩ፡፡ እኔ ሆዬ የመንገዱ ዳር ዳር እያልኩ አጎንብሼ እዚያ ያገኘዋትን ትንሽ ሳር ስግጥ ቆየሁ፡፡ ይሄንን ሀጥያት ሰርቻለሁ ወንድሞቼ፡፡ ለዚህም እግዚሀርን ይቅርታ እጠይቃለሁ›› አለች፡፡
ሌሎች እንስሳ አህያን ተመለከቷት። አህያን የሚፈራትም ሆነ የሚያደንቃት ማንም የለም፡፡ ከጥቂት ጊዜ ቆይታ በኋላ ሁሉም እራሳቸውን ነቀነቁና፤
‹‹ይሄ በአለም ላይ ከተሰሩ ሀጥያቶች ሁሉ እጅግ በጣም የከፋው ነው፡፡ በሀገራችን ላይ ለሚደርሰው ስቃይና መከራም ዋናው ምክንያት ያንቺ ሀጥያት ነው፡፡ ቀንደኛዋ ሀጥያተኛም አንቺ ነሽ!›› በሚል ወነጀልዋት፡፡
ስለዚህም አንበሳ፣ ነብርና ጅብ ዘለው አህያይቱ ላይ ሰፈሩባት፡፡ አንድም አጥንት ሳያስቀሩ ተቀራመቷት፡፡ ሚስኪኗ አህያ  በዚህ ሁኔታ ተሰዋች፡፡
***
ለግፍ ከዚህ ወዲያ ምሳሌ የለም፡፡ ሀይለኛ ይፈራል፡፡ ሀይለኛ ይደነቃል ሀይለኛ የሰራው ስራ ሁሉ እንደ ትክክል ይወሰድለታል፡፡ ሀጥያት መፈፀሙም ቢታወቅም እንደ ፅድቅ ስራ ይቆጠርለታል፡፡ ውይይቶች እና ግምገማዎች ሁሉ የሱን ንፅህና፣ የእሱን ብፅእና የሚያረጋግጡ እንዲሆኑ ይደረጋል፡፡ በዚህም ምክንያት ደካሞች የሀይለኞች ሲሳይ እንደሆኑ ይኖራሉ፡፡ ደካሞች ምንም አይነት ቅን አገልገሎት ቢሰጡም፣ ምንም አይነት ሸክም ቢሸከሙም ድካማቸው ሁሉ እንደ ከንቱ ተቆጥሮ እንዲያውም ሀጥያተኛ ነው ተብሎ እርምጃ ይወሰድባቸዋል፡፡ የሰሩትን መልካም ነገር ሁሉ እንደ ሀጥያት ይናዘዛሉ፡፡ ከዚያም ይሰዋሉ፡፡ ከዚህ ወዲያ ጭቦኛ ስርአት የለም፡፡ ከዚህም ወዲያ ግፍ አይኖርም፡፡ በሀገራችን ሀይለኞች ተፈጥረው አይተናል። ሀይለኞች ደካሞች ላይ ግፍ ሲፈፅሙም አይተናል፡፡ እንዲህ ባለው ሁኔታ፤ ዲሞክራሲም፤ ሰላምም፤ እድገትም ሊመጣ እንዳልቻለና እንደማይችልም ተገንዝበናል፡፡ አስገራሚው ነገር፤ ደካሞች ሁሉ ከተሰዉት ደካሞች አለመማራቸው ነው፡፡ ሌላው አስገራሚ ነገር፤ ደግሞ ሀይለኞች ሁሉ ከሌሎች ሀይለኞች ታሪክ አለመማራቸው ነው፡፡
ሀይለኞቹ፤ ‹‹ከዚህም ወዲያ አኩሪ ድል የለም›› ብለው እንዲያስቡ የሚያደርጋቸው፡፡ ምናልባትም የደካሞቹ ከተሰውት አለመማር ሳይሆን አይቀርም። በግፍ የሚገኝ ማናቸውም ነገር የኋላ ኋላ ግፍ መሆኑ መረጋገጡም አይቀርም፡፡ የኋላ ኋላ ማስጠየቁ አይቀርም፡፡ እስከ ዛሬ በታሪክ የታየውም ይኸው ሀቅ ነው፡፡
በአንድ ወቅት በአዲስ አበባ ወህኒ ቤት ታስሮ የነበረ አንድ እብድ፣ ጠዋት መናገር የጀመራትን አንድ አረፍተ ነገር ቀኑን ሙሉ ሲደጋግማት ይውል ነበር፡፡ ሰው የማይረዳለት ስለሚመስለው ይሆናል፡፡ ወይም በሌላም እብደታዊ ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡ ከነዚህ ከሚደጋግማቸውም አባባሎች መካከል፤ ‹‹ሞኝ ያስራል ብልጥ ይማራል›› የሚል ነበረበት፡፡ ግፍ የሚፈራ ሞኝ ነው፡፡ ግፍ የተሰራበት ደግሞ ከተማረ ብልጥ ነው፤ ማለት ነው፡፡ ዋናው ማማሩ ነው፡፡ ግፍ የሚፈፅም ሹም፣ አለቃ፣ የአለቃ ቀኝ እጅ፣ ቡድን፣ ፓርቲ ወይም መንግስት ይዋል ይደር እንጂ የእጁን ያገኛል፡፡ መጨረሻው አያምርም፡፡ ‹‹የሚደርቅ ውሀ ውሻ ይበላል›› እንደሚባለው በትንሽ በትልቁ ማኩረፍ፣ መቆጣት፣ ዘራፍ ማለት፣ ማስፈራራት እና ‹‹እርምጃ እወስዳሁ!›› ማለትን ይደጋግማል፡፡በአንድ አገር ጭቦና እኩይ ተግባር፣ ሙስናና ዘረፋ ከበረከተ ቋንቋ ለቋንቋ መጠፋፋት ግድ ይሆናል፡፡ አንዱ በቀኝ የተናገረው ለሌላው ግራ ይሆናል፡፡ መደማመጥ ይጠፋል፡፡ ባለ አንድ አቅጣጫ መንገድ (one way road) እንዲሉ፣ በዚህ በኩል ብቻ ሂዱ ማለት ይበዛል፡፡ ጉዞ ሁሉ ‹‹የተከለከለ መንገድ›› የሚል ፅሁፍ እና መፈክር ይበረክትበታል፡፡ ህዝብ እራስ አቀፍ (Self-censorship) ስርአትን ያዘወትራል፡፡ አለቃው የሚናገረው ለምንዝሩ ካለመግባቱም ሌላ አለቃ እና አለቃ እንኳ በአንድ ልሳን መነጋገር ይሳናቸዋል፡፡ ‹‹መልካም ጋብቻ ይሁንልህ!›› ቢለው ‹‹እግዜር ነው እንዲህ ያደረገኝ!›› ይላል፤ እንደተባለው የወላይታ ተረት መሆኑ ነው፡፡ አዩ ሌላ ወዮ ሌላ ነውና የተዘበራረቀ አሰራር ይሰፍናል፡፡ አቃጅና ፈፃሚ በተለያየ መንገድ ይሄዳሉ፡፡ ይገኛል የተባለው ውጤት፤ እናፈራለን የተባለውን ፍሬ፣ ወይ ጥሬ ይሆናል ወይ ይረግፋል፡፡ለዚህ ጥፋት ወይም ሀጥያት ደግሞ ባለተራ፤ ‹‹ይሰዋል››፡፡
ከቶውንም ዲሞክራሲያውነት የጎደለው እና ጭቦ የበዛበት ስርአት ካለ ግልደፅነት ዘበት ነገር ነው፡፡ ግልፀኝነት ከሌለ ደግሞ የሚሰራው ከማይሰራው፣ ግፈኛው ከቀናው፣ አምራቹ ከአውዳሚው፤ ሀቀኛውና አዋቂው ከአስመሳዩና ከደንቆሮ የሚለይበት ሚዛን ይጠፋል፡፡ ሚዛን አለ ቢባል እንኳ ይሸቅባል፡፡ አዳዲስ ኮሚሽን፣ ባለስልጣን፣ ኮሚቴ ይበዛል፡፡ ‹‹በኮሚቴ ቢወስን ኖሮ ሙሴ ቀይ ባህርን አያቋርጥም ነበር›› እንደተባለው ቁርጥ ያለ እቅድ፣ ቁርጥ ያለ መመሪያ፣ ዕቅጩነት ያለው ተግባራዊ እንቅስቃሴ ማግኘት ከንቱ ድካም ይሆናል፡፡ መልካም ውጤት ሲጠፋ ተጠያቂ ይፈጠራል፡፡ በአድሎ ይፈረዳል፡፡ ‹‹ፋቂ ቆዳ መፋቅ ቢያቅተው ውሻ ይሰድባል›› እንዲል መፅሀፉ፤ አንደኛው ወገን ላይ ሀጥያቱም፤ ይደፈደፋል፤ ይደመደማል፡፡
የኢ-ዲሞክራሲያዊነት፣ የመልካም-አስተዳደር (good Governance ) እጦት፣ የፖለቲካ ቡድኖች ገዢ ተገዢነት ሹኩቻ፣ ወዘተ አንዱ እና ዋነኛው ምንጫቸው አለመተማመን ነው - ‹‹ከጀርባው ምን ይኖር ይሆን?›› የሚል ስጋት እና ጥንቃቄ። ‹‹ያጎረሰኝ እንዲያንቀኝ ፈልጎ ሊሆን ይችላል!›› የሚል አመለካከት ነው፡፡ ይህንን ሁሉ የጎሽ ሂደት ቀለል አድርገን ስንመለከተው እንግዲህ ወትሮውንም በፖለቲካው ጨዋታ ላይ የተሰለፉ ቡድኖች እና ግለሰቦች ከዋና ተጫዋቾች ይልቅ ተለዋጮች (Bench እንዲሉ መፅሀፈ ካምቦሎጆ) የበዙባቸው መሆኑንና በአለመተማመን  የሚጋዙ መበርከታቸውን እናስተውላለን፡፡ አለቃ አለቃን፣ ባለስልጣን ባለስልጣንን፣ ቡድን ቡድንን፣ ፓርቲ ፓርቲን የሚጠራጠርበት ሁኔታ ካለ ለማናቸውም እንቅስቃሴ ልባዊ አንድነት አይኖርም ማለት ነው፡፡ አብሮ መጋዝ ይቻላል እንጂ በአንድ ልብ ለመጓዝ አይቻልም፡፡ የይስሙላ እንጂ የልብ አንድነት አይኖርም፡፡ ቢቸግር ነው እንጂ ከአንድ ገበታ አይቆርሱም ማለት ነው፡፡ ‹‹ሳህን ቢበዛ አብረን በላን›› ማለት እንግዲህ ይሄው ነው፡፡
መጪው የህማማት ጊዜ ከራሳችን ጋር የምንጋገርበት፤ በጥሞና የምናሳልፍበትና ሃጢያታችንን የምንናዘዝበት ያድርልን። በተለይ ደግሞ ለፖለቲከኞቻችንና መሪዎቻችን።
ቅቱ ጥቅስ
‹‹ዛፍ ላይ ወጥቼ ልግደልህ፣ መሬት ሆኜ?›› ቢባል
‹‹ዛፍ ላይ ወጥተህ›› ብሎ መለሰ፡፡
‹‹ለምን?›› ቢለው፤
‹‹ዛፍ እስክትወጣ በህይወት እቆያለሁ…››
የወላይትኛ ምሳሌያዊ አነጋገር

በአቶ ሺመልስ አብዲሳ ስም በህገወጥ መንገድ በተደራጀ ማህበር ሲሚንቶ ሲያከፋፍሉ ነበር በተባለ ተከሳሾች ላይ የእስራትና የገንዘብ ቅጣት ውሳኔ ተሰጠ፡፡
የኦሮሚያ ክልል ሽገር ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ወንጀል ችሎት ትናንት በዋለው ችሎት በሰጠው ውሳኔ ላይ እንደተገለፀው ተከሳሾች በኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሺመልስ አብዲሳ ስም ሀሰተኛ ሰነድ በመጠቀም በህገ-ወጥነት በተደራጀው ማህበር ከ29 ሚሊዮን ብር በላይ የሚወጣ ሲሚንቶ በማውጣት ለግል ጥቅማቸው አውለዋል። ፍርድ ቤቱ በተከሳሾች ላይ የቀረቡትን ማስረጃዎች ከመረመረ በኃላ በመዝገቡ ከተከሰሱ ተከሳሾች መካከል በስምንቱ ላይ እስከ 20 ዓመት በሚደርስ እስራትና በገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ ወሰኗል፡፡የቅጣት ውሳኔው ከተላለፈባቸው ተከሳሾች መካከል የኦሮሚያ ክልል የደህንነት ባለሙያ አቶ አዲሱ አንጋሳ የሚገኙበት ሲሆን የቀድሞ የኦሮሚያ ክልል የንግድ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ወርቁ ጫላም ከተከሳሾቹ መካከል ይገኙበታል፡፡
ፍርድ ቤቱ የኦሮሚያ ክልል የደህንነት ባለሙያ በነበረው ተከሳሽ አቶ አዲሱ አንጋሳ ላይ የሃያ አመት ፅኑ እስራትና የሁለት መቶ ሺብር የገንዘብ ቅጣት የወሰነባቸው ሲሆን በክልሉ የቀድሞ የንግድ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ወርቁ ጫላ ላይ ደግሞ የአምስት አመት ፅኑ እስራትና 10ሺ ብር የገንዘብ ቅጣት ወስኗል፡፡
ፍርድ ቤቱ በተከሳሾች እጅ ላይ የተገኙ 8ሺ ኩንታል ሲሚንቶ እና ከ565 ሺ ብር በላይ ገንዘብ እንዲወረስ ትዕዛዝ ሰጥቷል።

 አዲስ አበባ ከተማን ለማስተዋወቅ ያለመና ከከተማ አስተዳደሩ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በትብብር የተዘጋጀ የጎዳና ላይ ሩጫ ሊካሄድ ነው፡፡ሚያዝያ 16/2015 ዓ.ም የሚካሄደውና ኤም ጆይስ ኢቨንትስት ማርኬቲንግ ከአሀዱ ግሎባል ኔትወርክ ጋር ያዘጋጀው ይኸው የጎዳ ላይ ሩጫ በርካታ፤ ጉዳዮችን ያካተተ ሲሆን የረመዳንን ፆም ምክንያት በማድረግ የአስር ቀና የአፍጥር ግብዣ፤ ፋሲካን በማስመልከት የምሳ ግብዣ እንዲሁም የጎዳ ላይ ሩጫና የተለያዩ የመዝናኛ ፕሮግራሞች መዘጋጀታቸውን ዛሬ አዘጋጆቹ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል። በመስቀል አደባባይ ተጀምሮ እዚያው መስቀል አደባባይ በሚያበቃው የአምስት ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ከ20ሺ እስከ 30ሺ ሰው ይሳተፍበታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

መተግበሪያው ሙስናንና ህገወጥ አሰራርን ይቀርፋል ተብሏል


ቲዮስ ቴክኒሎጂ ከአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮና ከአሽከርካሪና ተሽከርካሪ ፍቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን ጋር በመተባበር፣ የተሽከርካሪ ቴክኒክ ምርመራን የሚያከናውን አዲስ ቴክኖሎጂ ሥራ ሊጀምር ነው፡፡
ተቋማቱ ለ5 ዓመት በጋራ ሊሰሩ የሚችሉበትን ሥምምነት ባለፈው ማክሰኞ መጋቢት 26 ቀን 2015 ዓ.ም በሳፋየር አዲስ ሆቴል ተፈራርመዋል፡፡
በፊርማ ስነ ሥርዓቱ ላይ የአሽከርካሪና ተሽከርካሪ ፍቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን ዋና ሥራ አሥኪያጅ አቶ ፍሬው ደምሴ፣ የትዮስ ቴክኖሎጂ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ቴዎድሮስ አጥናፉ የተሽከርካሪ ምርመራ ተቋማት ፕሬዚዳንት አቶ ሀይሉ ገረሱና ሌሎችም እንግዶች ተገኝተዋል፡፡የተሽከርካሪ ቴክኒክ ምርመራን ቴክኖሎጂው በውጭና በሀገር ውስጥ ከፍተኛ ባለሙያዎች የበለፀገ ዘመናዊ መተግበሪያ ሲሆን የተሽከርካሪ ቴክኒክ ምርመራ ከሶስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት ጠብቆ ውጤቱን ለማእከላዊ የመረጃ ቋት እንደሚያቀብል የቲዮስ ቴክኖሎጂ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ቴዎድሮሰ አጥናፉ አብራርተው ይህም ሙሰኝነትንና ህገ-ወጥ አሰራርን በእጅጉ ከመቀነስ አኳያ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ብለዋል፡፡
እስከ ዛሬ የነበረውን የቴክኒክ ምርመራ ክፍተት አስመልክተው ማብራሪያ የሰጡት የተሽከርካሪና አሽከርካሪ ፈቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ፍሬው ደምሴ፤ ተሽከርካሪዎች በምርመራ ተቋማት የምርመራ ሂደት ሳያልፉ፣ ህገ ወጥ ቦሎ እየወሰዱ መሆናቸውን አብራርተው፣ ይህም ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱና የተሽከርካሪ ምርመራ ድርጅቶች ሊያገኙ የሚገባቸውን ገቢ በማሳጣት በተቋማቱም በአገር ኢኮኖሚም ላይ አሉታዊ ተፅእኖ ሲፈጥሩ ቆይተዋል ብለዋል፡፡ ኃላፊው አክለውም፤ ደህንነታቸውና ጤንነታቸው ያልተረጋገጡ ተሽከርካሪዎች በስራ ላይ እየዋሉ በህይወትና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጥፋት እየደረሰ መሆኑን ጠቁመው፤ ቲዮስ ቴክኖሎጂ ያበለፀገው አዲስ  መተግበሪያ እነዚህን ሁሉ ተግዳሮቶች ከመቅረፍ አኳያ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው አስታውቀዋል፡፡
‹‹ ቴክኖሎጂውን ያበለፀግነው ትራንስፖርቱን ከማዘመን ፣ ህገ ወጥ አሰራርና ሙስናን ከማስቀረትና በህይወትና በንብረት ላይ የሚደርሰውን ጥፋት ከማስቀረት አኳያ አስበን ነው” ያሉት ደግሞ የቲዮስ ቴክኖሎጂ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ቴዎድሮስ አጥናፉ ሲሆኑ ፤ መተግበሪያው በአዲስ አበባ ከሚገኙ 60 የተሽከርካሪ ምርመራ ተቋማት በ15ቱ ላይ የሙከራ ስራ ተሰርቶበት ውጤታማነቱ ተረጋገረጧል  ብለዋል፡፡
እንደ አዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ መረጃ የአዲስ አበባ (አ.አ)፣ የኢትዮጵያ (ኢቲ) እና የኮር ዲፕሎማቲክ (CD) ሰሌዳ ያላቸው ከ650 ሺህ በላይ ተሽከርካሪዎች በአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ተመዝግበው የሚገኙ ሲሆን፤ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ330 ሺህ በላይ ተሽከርካሪዎች ተመርምረው ቦሎ መውሰዳቸውንና እስከ በጀት ዓመቱ መጨረሻ ተመርምረው ቦሎ የሚወስዱ ተሽከርካሪዎች ቁጥር 450 ሺህ ይደርሳል ተብሎ እንደሚጠበቅ በዕለቱ ተገልፃል፡፡

በየዓመቱ ለዩኒቨርስቲ ተማሪዎች የሚዘጋጀው ባለፈው ኖቨምበር 11 ቀን 2022 በተጀመረው ዓለማቀፍ የሁዋዌ አይሲቲ (ICT) ውድድር ከ1500 በላይ ተማሪዎች መሳተፋቸውንና ስድስት ተማሪዎች  በቻይና ለሚካሄደው የመጨረሻ ዙር ውድድር ማለፋቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡
በኢትዮጵያ ለ7ኛ ጊዜ በተካሄደው የሁዋዌ አይሲቲ ውድድር ከተለያዩ የትምህርት ተቋማት ከ1500 በላይ ተማሪዎች ተመዝግበው በኦንላይን የተሰጠውን የመጀመሪያ ፈተና መውሰዳቸውን ሁዋዌ በላከው መግለጫ  አስታውሷል፡፡
ከእነዚህም መካከል 63 ተማሪዎች ፈተናውን አልፈው ከት/ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በተዘጋጀውና ዲሴምበር 28 ቀን 2022 ዓ.ም በአዲስ አበባ በተካሄደው አገር አቀፍ የአይሲቲ ውድድር ላይ የተሳተፉ ሲሆን 15 ያህሉ ለቀጣዩ ክልላዊ የአይሲቲ ፈተና ማለፋቸውን ኩባንያው አመልክቷል፡፡ እነዚህም 15 ተማሪዎች ማርች 22 ቀን 2023 ዓ.ም በአዲስ አበባ የሁዋዌ ኢትዮጵያ ዋና መ/ቤት የተሰጠውንና ለስድስት ሰዓት የዘለቀውን የአይሲቲ ኦንላይ ፈተና   ወስደዋል።በውጤቱም ከጎንደር ዩኒቨርስቲ፣ ከዋቻሞ ዩኒቨርስቲ፣ ከአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ እንዲሁም ከአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዪኒቨርስቲ 6 ተማሪዎች ፈተናውን አልፈው ወደ መጨረሻ ዙር የሁዋዌ አይሲቲ ውድድር ማለፋቸው ተገልጿል፡፡ እነዚህም ተማሪዎ ዘንድሮ በቻይና በሚካሄደው የመጨረሻው የሁዋዌ አይሲቲ ውድድር ኢትዮጵያን ወክለው ይሳተፋሉ።እ.ኤ.አ ከ2015 ዓ.ም ወዲህ የሁዋዌ አይሲቲ ውድድር ተፅእኖ እያደገ መምጣቱን ያመለከተው ኩባንያው፤ በ2022 የተካሄደው 6ኛው የሁዋዌ አይሲቲ ውድድር ከ85 አገራትና ክልሎች የተውጣጡ 150 ሺ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎችን ማሳተፉን  አስታውሷል፡፡

ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ፤ ከ1ሚ.በላይ ደንበኞች የ07 ኔትወርኩን በመቀላቀላቸውና ምርትና አገልግሎቶችን በመጠቀማቸው ተሸላሚ የሚሆኑበትን የመጀመሪያ የዕጣ ሽልማት መርሃ ግብር በዛሬው ዕለት በኩባንያው ዋና መ/ቤት በይፋ አስጀምሯል፡፡
ለ14 ሳምንታት በሚዘልቀው "ተረክ በጉርሻ" በተሰኘው የሽልማት መርሃ ግብር፤ ደንበኞች የሳፋሪኮም ሲምካርዳቸውን ሲያወጡ፣ የአየር ሰዓት ሲገዙና ጥቅሎችን ሲሞሉ እንዲሁም የዋትሳፕ ጥቅሎችን ሲጠቀሙ ፤ ለባለ ዕድለኝነት ብቁ የሚያደርጋቸውን የዕጣ ቁጥር ያገኛሉ ተብሏል፡፡
ደንበኞች በቀን ውስጥ እስከ 10 የሚደርሱ የዕጣ ቁጥሮችን እንደሚያገኙና ቁጥሮቹም የዕለት፣ የሁለት ሳምንት እንዲሁም የወር ሽልማቶችን ለማሸነፍ በሚወጡ ዕጣዎች ውስጥ የሚካተቱ እንደሚሆኑ ተነግሯል፡፡
የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አንዋር ሱሳ የሽልማት መርሃግብሩን አስመልክቶ ሲናገሩ፤" የዛሬው ሁነት ደንበኞቻችንን ለማመስገን የተዘጋጀ ነው፡፡ በተረክ በጉርሻ መርሃ ግብራችን፣ በቀጣዮቹ 14 ሳምንታት ከ1ሚ.በላይ ለሚሆኑ ደንበኞቻችን ሳፋሪኮምን ሲቀላቀሉ፣ የአየር ሰዓታቸውን ሲሞሉና ጥቅሎችን ሲሞሉ በሚደርሷቸው የዕጣ ቁጥሮች 3 መኪኖች፣7 ባጃጆች፣ 7 ሞተር ሳይክሎች፣ ስልኮች ታብሌቶችና ዕለታዊ የአየር ሰዓትን ሽልማትን ጨምሮ የተለያዩ ሽልማቶችን የምንሸልም ይሆናል፡፡ ቢዝነሳችንን እየገነባን ያለነው ደንበኞችን ታሳቢ ባደረጉ መልኩ ሲሆን፤ እያደግን በመጣን ቁጥር ደግሞ ደንበኞቻችንን ከእኛ ጋር በመዝለቃቸው ዕውቅና ልንሰጣቸው ይገባል፡፡" ብለዋል፡፡
ደንበኞች የአየር ሰዓት ለመሙላት ወይም የድምፅ፣ የፅሁፍ መልዕክት ወይም የዳታ ጥቅሎችን ለመግዛት በሚያወጡት እያንዳንዱ 10 ብር፣ 1የዕጣ ቁጥር የሚደርሳቸው ሲሆን፤ ሲምካርድ በመግዛት ኔትወርኩን የሚቀላቀሉ አዳዲስ ደንበኞች በ24 ሰዓት ውስጥ አየር ሰዓት ከሞሉ 3 የዕጣ ቁጥሮች ያገኛሉ፡፡ 1 ጂቢ የዋትሳፕ ጥቅሎችን ከተጠቀሙ ደግሞ 7 የዕጣ ቁጥሮች ያገኛሉ ተብሏል፡፡
ለሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ደንበኞችም ክፍት የሆነው የሽልማት መርሃግብር፣ እስከ ሰኔ 28 ቀን 2015 ዓ.ም የሚዘልቅ ሲሆን፤ ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ኔትዎርኩን በዘረጋባቸውና ሥራ በጀመረባቸው የኢትዮጵያ ክፍሎች የሚገኙ ከ1 ሚሊዮን በላይ ደንበኞችን ዕድለኞች የሚያደርግ እንደሚሆን ተጠቁሟል፡፡
አሸናፊዎች ከብሔራዊ ሎተሪ ጋር በመተባበር በየሁለት ሳምንቱ በዕጣ ተለይተው የሚሸለሙ ሲሆን፤ የዕጣ አሸናፊ መሆናቸውም በ0700 700 700 ተደውሎ እንደሚነገራቸውም ሳፋሪኮም አስታውቋል፡፡
የቴሌግራም ቻናልችንን በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…
 
• በአንድ ወር 500 ሚ. ብር ለማሰባሰብ ታቅዷል
በምስረታ ላይ የሚገኘው ግዕዝ ባንክ አክሲዮን ማህበር፤ ዳግም የአክሲዮን ሽያጭ መጀመሩን አስታወቀ።
በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ከመላው ኢትዮጵያና ከዳያስፖራው የ500 ሚሊዮን ብር የአክሲዮን ሽያጭ በማሰባሰብና የሚፈለገውን የካፒታል መጠን በማሟላት በፍጥነት ወደ ሥራ ለመግባት ታቅዷል ተብሏል፡፡
የባንኩ አደራጅና አስተባባሪ ኮሚቴ አባላት በዛሬው ዕለት ወጋገን ባንክ አንደኛ ፎቅ ላይ በሚገኘው ቢሮአቸው በሰጡት የጋራ መግለጫ፤ግዕዝ ባንክ ከመጋቢት 2012 ዓ.ም ጀምሮ ለምስረታ ሂደት የሚያበቃውን የአክሲዮን ሽያጭ ማከናወን መጀመሩን አስታውሰዋል፡፡
ለባንኩ ምሥረታ የሚያስፈልገውን የካፒታል መጠን ለማሟላት ጥቂት ሲቀራቸው ግን በአገሪቱ ላይ በተፈጠረው የሰላምና መረጋጋት ችግር ሳቢያ ከእንቅስቃሴያቸው ተግተው መቆየታቸውን ያስረዳሉ፡፡ ፡
በህዳር 2013 ዓ.ም የአክሲዮን ሽያጭ እንደሚያበቃም ለሚዲያዎች አስታውቀው እንደነበር ያስታወሱት የኮሚቴው አባላት፤ ሆኖም በተፈጠረው ድንገተኛ ችግር ሳቢያ ያቀዱትን ሳያሳኩ እስካሁን መዘግየታቸውን ተናግረዋል፡፡
አሁን በአገሪቱ የተፈጠረውን ሰላምና መረጋጋት ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ ዳግም የአክሲዮን ሽያጭ መጀመራቸውን ነው፣ የአደራጅ ኮሚቴው አባላት ያስታወቁት፡፡
በምስረታ ሂደቱ ላይ በመሳተፍ የባንኩ መስራች ለመሆን ፍላጎት ያላቸው ግለሰቦችና ድርጅቶችም፤ ከዛሬ ጀምሮ በመላ አገሪቱ ባሉ ባንኮች በተከፈቱ የዝግና የአገልግሎት ሂሳብ ቁጥሮች፣ የግዕዝ ባንክ አ.ማ የመመስረቻ አክሲዮን ግዢን ከብር 50ሺ ጀምሮ ማከናወን እንደሚችሉ ተገልጿል።
የመሥራች አክሲዮን ሽያጩ ቀድሞ እንደነበረው የአንድ አክሲዮን መጠን 1ሺ ብር ሲሆን፤ መሥራች አባል ለመሆንም 50 አክሲዮኖችንና ከዚያ በላይ መግዛት እንደሚያስፈልግ ታውቋል። የመሥራች አባል ከፍተኛው የአክሲዮን ሽያጭ 100 ሚሊዮን ብር ነው ተብሏል።
ዳያስፖራዎችን በተመለከተ እንደተለመደው፣ አክሲዮኖችን ባሉበት ሆነው፣ በሚኖሩበት አገር የመገበያያ ገንዘብ መግዛት እንደሚችሉ ተጠቁሟል።
የአደራጅና አስተባባሪ ኮሚቴው አባላት፤በአገሪቱ ላይ ተከስቶ በነበረው የሰላም ችግር ምክንያት የአክሲዮን ሽያጫቸውን አቋርጠው በነበረበት ወቅት፣ ደንበኞች ላሳዩት ትዕግስትና ድጋፍ ልባዊ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
የቴሌግራም ቻናልችንን በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…
Page 9 of 646