Administrator

Administrator

በአምስተረዳም አንድ ሰው ከሞተና የሚቀብረው ወዳጅ ዘመድ ከሌለው አንድ ገጣሚ ግጥም ይፅፍለትና በቀብር ሥነ-ሥርአቱ ላይ ያነብለታል፡፡
ቦሊቪያ ውስጥ የሚገኘው ትልቁ ወህኒ ቤት ምኑም እስር ቤት አይመስልም ነው የሚባለው፡፡ እስር ቤቱ ራሱን የቻለ ህብረተሰብ የፈጠረ ሲሆን ግቢው ውስጥ ጥበቃዎች የሉም፡፡ ወህኒ ቤቱን የሚጠብቁት ራሳቸው እስረኞቹ ሲሆኑ የራሳቸውን መሪዎች ይመርጣሉ፤ የራሳቸውን ህጎችም ያወጣሉ፡፡ እዚያው ተቀጥረው በመስራት ከሚያገኙት ክፍያም ለእስር ክፍላቸው ኪራይ ይከፍላሉ፡፡ ከቤተሰባቸው ጋር መኖርም ይፈቀድላቸዋል፡፡ እስር ቤቱ ውስጥ፡፡
እ.ኤ.አ ከ1939 እስከ 1989 ባሉት ዓመታት ከስፔን የተለያዩ ሆስፒታሎች 300ሺ ገደማ አዲስ የተወለዱ ጨቅላ ህፃናት ተሰርቀዋል፡፡ ህፃናቱ የተሰረቁት ደግሞ በውጭ ሰዎች ሳይሆን ህገወጥ የህፃናት ዝውውር መረብ በዘረጉ የህክምና ተቋማት ሃኪሞች፣ ነርሶች፣ ቄሶችና መነኮሳት እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ወላጆች ልጆቻቸውን ሲጠይቁም እንደ ሞቱ ይነገራቸው ነበር፡፡
የጃፓኗ ኦኪናዋ ደሴት በምድራችን እጅግ ጤናማ ሥፍራ በሚል ትታወቃለች፡፡ በዚህች ደሴት ከ100 ዓመት በላይ ዕድሜ ያላቸው ከ450 በላይ ሰዎች ይኖራሉ፡፡
የአውሮፓ ፓርላማ ዋና ተርጓሚ የሆነው አዮአኒስ አይኮኖም 32 ቋንቋዎችን አቀላጥፎ እንደሚናገር መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

       ኖህ ዌብስተር የመጀመሪያውን መዝገበ ቃላት ለማዘጋጀት 36 ዓመት ፈጅቶበታል፡
ዳን ብራውን “ዘ ዳ ቪንቺ ኮድ” የተባለውን መፅሃፉን ከመፃፉ በፊት የፖፕ ሙዚቃ አቀንቃኝና የዘፈን ግጥም ደራሲ ነበር፡፡ ሁለተኛው የሙዚቃ አልበሙ “ኤንጅልስ ኤንድ ዴሞንስ” በሚል ስያሜ ነበር የወጣውስ፡፡
ሲድኒ ሼልደን 50ዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ እስኪገባ ድረስ ረዥም ልብወለዶችን መፃፍ አልጀመረም ነበር፡፡ ከዚያ በፊት በነበሩት ጊዜያት “I Dream of Jeannie” እና “The Patty Duke Show” የመሳሰሉ ተወዳጅ የቴሌቭዥን ድራማዎችን ነበር የሚፅፈው፡፡ ቬልይን “The Bachelor and the Bobby Soxer” በተባለች የፊልም ጽሑፉ ኦስካር አሸንፏል- “ምርጥ ኦሪጅናል የፊልም ጽሑፍ” በሚል ዘርፍ፡፡
የ “ሃሪ ፖተር” ደራሲ ጄ.ኬ.ሮውሊንግ መጀመሪያ ላይ ሥራዋን የሚያሳትምላት አጥታ መከራዋን በልታለች፡፡ ብዙዎች ውድቅ እያደረጉባት ተስፋ ከቆረጠች በኋላ ብሉምስበሪ ፕሬስ ሊያሳትምላት ተስማማ፡፡ እሱም ቢሆን ግን አይሸጥ ይሆናል በሚል ፍራቻ 500 ቅጂዎችን ብቻ ነበር ያሳተመላት፡፡ ሴት ፀሐፊ መሆኗ እንዳይታወቅ ሙሉ ስሟን እንዳትጠቀም አድርጓታል፡፡ አሁን ደራሲዋ ቢሊዮነር መሆኗ ይታወቃል፡፡
የታዋቂዋ ደራሲ ዳንኤላ ስቲል ህይወት በአንዳንድ መልኩ የፈጠራ ሥራዎቿን ይመስላል ይባላል፡፡ ደራሲዋ አምስት ጊዜ ጋብቻ የመሰረተች ሲሆን ሳን ፍራንሲስኮ ክሮኒክል እንደዘገበው፤ ሁለተኛ ባሏ ከእሷ ጋር እያለ አስገድዶ በመድፈር የተፈረደበት የባንክ ዘራፊ ነበር፡፡ ሦስተኛ ባሏ ደግሞ የአደንዛዥ ዕፅ ሱሰኛና ቤት ሰርሳሪ ነበር ተብሏል፡፡



        በአዲስ ጉዳይ መጽሔትና በድረ-ገፆች ላይ የተለያዩ መጣጥፎችንና ግጥሞችን በመፃፍ የሚታወቀው አሌክስ አብርሃም ፤“ዶ/ር አሸብርና ሌሎችም ታሪኮች” በሚል ያዘጋጀው የአጫጭር ልብወለዶች መድበል ባለፈው ሳምንት ለገበያ ቀረበ፡፡ ሃያ አምስት አጫጭር ልቦለዶችንና ታሪኮችን የያዘው መድበሉ፤237 ገፆች ያሉት ሲሆን በሊትማን መጽሐፍት አከፋፋይነት በ50.65 ብር እየተሸጠ ነው፡፡  
በሌላ በኩል በብርያን ትሬሲ ተፅፎ በእስክንድርያ ስዩም የተተረጎመው “መቶ የቢዝነስና የአመራር ህጎች” የተሰኘ የንግድ ክህሎት መፅሀፍ እየተሸጠ ነው፡፡ በስምንት ምዕራፎች ተከፋፍሎ በ142 ገፆች የተቀነበበው  መፅሀፉ፤በህይወትና በስኬት ህግጋት፣ በመሪነት፣ በገንዘብና በሽያጭ ህጎች እንዲሁም በንግድ ሥራ ህጎችና መሰል ጉዳዮች ዙሪያ የሚያጠነጥን ሲሆን የተሳካ የንግድ ስራን ለመጀመር፣ ለመምራትና ለማሳደግ የሚረዳ መፅሐፍ ነው ተብሏል፡፡ የእንግሊዝኛው መፅሃፍ በብዙ ሚሊዮን ቅጂዎች እንደተሸጠና የብዙዎችን የቢዝነስና የአመራር ህይወት እንደቀየረ ተጠቁሟል፡፡ ወደ አማርኛ የተተረጎመው መፅሀፉ   በ35.45 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡

በየሺወርቅ ወልዴ የተፃፈው እና በእውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሰረተው “የጠፋው ቤተሰብ” የተሰኘ ልብ ወለድ መፅሐፍ ለንባብ በቃ፡፡ መፅሀፉ በውስጡ ሌሎች አጫጭር ታሪኮችና ግጥሞች የተካተቱበት ሲሆን ለደራሲዋ ሁለተኛ ስራዋ እንደሆነም ታውቋል፡፡  “የጠፋው ቤተሰብና ሌሎችም” መፅሐፍ 122 ገፆች ያሉት ሲሆን በ35 ብር ለገበያ ቀርቧል። ደራሲዋ ከዚህ ቀደም “አትሮኖስ” የተሰኘ የግጥም መፅሀፍ ለንባብ አብቅታለች፡፡ በሌላ በኩል በገጣሚ ውድነህ ግርማ (የአስቴር ልጅ) የተፃፈው “ሽበቴን ለቅማችሁ” የተሰኘ የግጥም መድበል ሰሞኑን በገበያ ላይ ውሏል፡፡ ከ120 በላይ አጫጭር ግጥሞችን የያዘው መጽሐፉ፤በ65 ገፆች የተቀነበበ  ሲሆን በ30 ብር ይሸጣል፡፡ ግጥሞቹ በፍቅር፣ በማህበራዊ ኑሮ፣ በታሪክና ሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ ያጠነጥናሉ፡፡ ወጣቱ ገጣሚ የግጥም መድበሉ የበኩር ስራው እንደሆነ ጠቅሶ ወደፊት ሊያሳትም ያዘጋጃቸው የልብወለድ ስራዎች እንዳሉትም ገልጿል፡፡

አብርሃም ግዛው ኢንተርቴይመንትና ፕሬስ ሥራዎች ከኤሎሄ አርት ፕሬስ ጋር በመተባበር የሚያዘጋጁት “ስንቅ” መፅሔት ዛሬ ከቀኑ በ10 ሰዓት በኦካናዳ ሬስቶራንት እንደሚመረቅ አዘጋጆቹ ገለፁ፡፡ በኪነጥበብ ላይ አተኩሮ በየአሥራ አምስት ቀኑ እየታተመ የሚወጣው መጽሔቱ፤ባለፈው ቅዳሜ የመጀመሪያ ዕትሙን ለንባብ እንዳበቃ ታውቋል፡፡ “ስንቅ” መፅሔት ከወቅታዊ ጉዳዮች ባሻገር ሙዚቃ፣ ግጥሞች፣ ወጎች እና ሌሎች የኪነጥበብ ስራዎችን ያስተናግዳል፡፡  

    ከለርስ ኦፍ ዘ ናይል ዓለም አቀፍ ፊልም ፌስቲቫል ባለፈው ሰኞ በብሄራዊ ቲያትር ለሁለተኛ ጊዜ የተከፈተ ሲሆን በዘንድሮ ፌስቲቫል ‹‹ሌንሶች ለአፍሪካ ህዳሴ›› በሚል መሪ ቃል ከመጋቢት 15- 22 የፊልም ስክሪኒግ እና ወርክሾፖች እንደሚካሄዱ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ብሉ ናይል የፊልምና ቴሌቭዥን አካዳሚ ከኢትዮጵያ የፊልም ሰሪዎች ማህበር ጋር በመተባበር ያዘጋጁት ፌስቲቫል  የአፍሪካ ህብረት 50ኛ ዓመት መሪ ቃልን በማስተጋባት ሲኒማ ህብረተሰቡን በማነጽ፣በማዝናናት፣አፍሪካውያንን በማቀራረብ፣አፍሪካዊ ባህልን በማዳበር እንዲሁም ለትውልድ በማስተላለፍና ዴሞክራሲያዊ ባህልን በማጎልበት ለአፍሪካ ህዳሴ አስተዋፅኦ  እንደሚያበረክት ተገልጿል፡፡
በአሊያንስ ኢትዮ ፍራንሲስ፣ በጣሊያን ካልቸር ኢንስቲትዩት እና በብሄራዊ ሙዚየም በሚደረጉ የተለያዩ ዝግጅቶች 48 የውጪና የሀገር ውስጥ ፊልሞች ለውድድር እንደሚቀርቡ የታወቀ ሲሆን ከ22 አገራት  የተውጣጡ ከ28 በላይ የፊልም ባለሞያዎች ይሳተፉበታል፡፡ ፌስቲቫሉ የፊታችን ማክሰኞ በብሄራዊ ቲያትር በሚካሄድ የመዝጊያ ፕሮግራም ይጠናቀቃል፡፡
ባለፈው ዓመት ‹‹የአፍሪካ ሲኒማ ዘመናዊ ስፍራ›› በሚል መሪ ቃል በተካሄደው የመጀመሪያው የፊልም ፌስቲቫል፤ ከ28 አገራት የተውጣጡ ከ40 በላይ ታዋቂ የፊልም ባለሙያዎች መሳተፋቸው የሚታወስ ሲሆን 56 ምርጥ የአፍሪካ ፊልሞች ተስተናግደውበታል፡፡

በአፍሪካ ቀንድ በአይነቱ የመጀመሪያው ነው ተብሏል
የኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት የአሜሪካ የንግድ ምክርቤት አካል ከሆነው አለማቀፍ የግል ንግድ ተቋማት ማዕከል (CIPE) ጋር በመተባበር ያቋቋመውና በአፍሪካ ቀንድ በአይነቱ የመጀመሪያው እንደሆነ የተነገረለት የንግድ ስራ ስልጠና አካዳሚ ባለፈው ማክሰኞ ተመርቆ ተከፈተ፡፡
የኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ወ/ሮ ሙሉ ሰለሞን በአካዳሚው የምረቃ ስነስርዓት ላይ እንደተናገሩት፣ በአገሪቱ የንግድ ስራ የልህቀት ማዕከል በመሆን እንዲያገለግል ታስቦ በአዲስ አበባ የተገነባው የዚህ የንግድ ስራ ስልጠና አካዳሚ መከፈት፣ በአገሪቱ የግል ዘርፍ ላይ መነቃቃትን የሚፈጥር ነው፡፡
በአገሪቱ ያለው የግሉ ዘርፍ እንቅስቃሴ ከተለምዷዊ አስተሳሰቦችና አሰራሮች መላቀቅና በዘመናዊ የንግድ ስራ ንድፈ ሃሳቦችና አሰራሮች መመራት እንደሚኖርበት የገለጹት ወ/ሮ ሙሉ፣ አካዳሚው ለንግዱ ማህበረሰብ አባላትና ለሚመለከታቸው ድርጅቶች ሰራተኞች ተገቢውን ስልጠና በመስጠት፣ የግሉን ዘርፍ አቅም በማሳደግ ረገድ ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት አስረድተዋል፡፡
ከምክር ቤቱ የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው፣ የስልጠና ማዕከሉ የኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤትንና  የአባል ድርጅቶችን የአመራርና የአስተዳደር ክህሎት የማጠናከርና ተቋማዊ አቅምን የመገንባት አላማ ያለው ነው፡፡ በንግዱ ዘርፍ በተሰማሩ ተቋማት መካከል ያለውን ግንኙነት፣ ትብብርና፣ ጥምረት ለማሳደግም ይሰራል ተብሏል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ከፍተኛ የህግ ባለሙያው ፕሮፌሰር ሞሃመድ ሃቢብ በበኩላቸው፣ መሰል አለማቀፍ ትብብር መፍጠር፣ ወቅቱን የጠበቀ የንግድ ስራ እውቀትን በማሰራጨት ረገድ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ጠቁመው፣ አካዳሚው መቋቋሙ በአገሪቱ ያለውን የግሉን ዘርፍ እንቅስቃሴ እንደሚያነቃቃና እድገቱን እንደሚያፋጥን  ተናግረዋል፡፡
የልህቀት ማዕከሉ መገንባቱና ተገቢውን ስልጠና መስጠቱ፣ የግሉ ዘርፍ በአገሪቱ ልማትና እድገት ላይ የሚጠበቅበትን የመሪነት ሚና እንዲጫወት የሚያስችል መነሳሳት እንደሚፈጥርም አክለው ገልጸዋል፡፡
ባለፈው ማክሰኞ በተከናወነው የአካዳሚው የምረቃ ስነስርዓት ላይ የመንግስት ተወካዮች፣ የተለያዩ አገራት አምባሳደሮች፣ የአለማቀፍ የልማት ድርጅቶች ተወካዮች፣ የኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት አጋሮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል፡፡
የኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት፣ ከ60 አመታት በላይ የአገሪቱን የንግድ ማህበረሰብ ማገዝ የሚያስችሉ ስራዎችን ሲያከናውን መቆየቱ ተነግሯል፡፡

      በኢትዮጵያ የቴሌኮም ፕሮጀክቶች ላይ ላለፉት 12 ዓSqƒ ሲሰራ የቆየው ዜድቲኢ፣ አሁን በመካሄድ ላይ በሚገኘው የቴሌኮም ማስፋፊያ ፕሮጀክት 50 በመቶ ድርሻ መውሰዱ የሚታወቅ ሲሆን፤  በኤሌክትሪክ ሃይል ስርጭት፣ በትምህርት አቅርቦትና በከተማ አስተዳደር ዙሪያ ሶስት የቴክኖሎጂ ውጤቶቸን ለኢትዮጲያ ገበያ አስተዋወቀ፡፡
ፓወር ግሪድ፣ ኢለርኒንግ እና ስማርት ሲቲ በመባል የሚታወቁት እነዚህ ቴክኖሎጂዎች የተሣለጠ የከተማ አኗኗር ለመፍጠር የሚያስችሉና በከተማ አስተዳደር ውስጥ ወሳኝ የሚባሉትን መሰረታዊ መረጃዎች በማጠናቀር አመራራርን ዘመናዊ ለማድረግ የሚያግዙ ናቸው፡፡
የኢትዮጲያ መንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት በተገኙበት ለሀገር ውስጥ ገበያ የተዋወቁት የቴክኖሎጂ ውጤቶች በፍጥነት እያደገች ባለችው ቻይና እና በአለም አቀፍ ደረጃ ተተግብረው ከፍተኛ ስኬት ያስመዘገቡ መሆናቸውን ዜድቲኢ ገልፆ፤ በአለም አቀፍ የቴክኖሎጂ አምራችነት ቀዳሚ ስፍራ ለማግኘት አስችለውኛል ብሏል፡፡
ስማርት ሲቲ የተሰኘው ቴክኖሎጂ የ2013 የአለም አቀፍ የሞባይል ቴክኖሎጂ የሽልማት አሸናፊ እንደሆነና በቤጂንግ ከተማ ተተግብሮ የአለም አቀፍን የፈጠራ ተሸላሚ ለመሆን እንደበቃ ኩባንያው ገልጿል፡፡  ኢለርኒግና ፓወር ግሪድ የተባሉት ቴክኖሎጂዎችም ከቻይና በተጨማሪ በሞሪሺየስ፣ ፓፓዋ ኒው ጊኒ፣ በአሜሪካ፣ በቬንዙዌላ እና በኬኒያ ተሞክረው ውጤታማ መሆናቸው ተነግሯል፡፡
በፍጥነት እያደጉ ባሉባት የኢትዮጵያ ከተሞች ውስጥ እነዚህ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ተተግብረው ውጤታማ እንደሚሆኑ ዜድቲኢ ጠቅሶ፤ የኢትዮጵያ የህዝብ ብዛት በ2020 ወደ 120 ሚሊዮን ይደርሳል ተብሎ እንደሚጠበቅና ከዚህም ውስጥ 60 በመቶ ያህሉ በከተማ ይኖራል ተብሎ እንደሚገመት ገልጿል።

Monday, 31 March 2014 11:07

የጥንቱ አገረሸ

ሁሉን የሚችል ዳስ አንጣሎ፤ ገትሮ
ደልድሎ፤ አሳምሮ
ሊጡ ተቦካና እንጀራው ተጋግሮ
ለብሶ ተከምሮ፤
ጠጁ ተጣለና በጠላ ጉሮሮ
ሊወርድ ተደርድሮ፤
ወጡ በያይነቱ ባዋቂ ተሠርቶ፤
ቁርጡ ተሰናድቶ፤
ሰው ሁሉ ለመብላት፤ ለመጠጣት ጓጉቶ፤
ሲጠብቅ ሰንብቶ፤
አዝማሪው ለዘፈን ቆሞ ተዘጋጅቶ፤
ማሲንቆው ተቀኝቶ፤

ጨዋታ ፈረሰ!
ዳቦ ተቆረሰ!
ሙሽራው ጠፋና ሠርጉ ተበላሸ፤
የተጠራው ሸሸ፤
ጊዜ ከዳውና በጊዜው ላመሸ፤
ዳሱ ተረበሸ፤
የጥንቱ አገረሸ፡፡
(ከፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም
“ዛሬም እንጉርጉሮ” የተሰኘ የግጥም መድበል የተወሰደ)

የአሜሪካ መንግሥት “የአፍሪካ ስኬታማ ወጣት መሪ” በሚል የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢንጅነር ይልቃል ጌትነት መርጦ ለመሸለም ጥሪ ማድረጉን የፓርቲው ልሳን ጋዜጣ ባለፈው ሳምንት ዘግቧል፡፡ በሌላ በኩል ከአሜሪካ ኤምባሲ በኩል የተገኙ መረጃዎች የሰማያዊ ፓርቲ መሪ የተመረጡት የአሜሪካ  ስቴት ዲፓርትመንት  በየዓመቱ ለሚያዘጋጀው የሊደርሺፕ ፕሮግራም እንጂ ለሽልማት አይደለም ይላሉ፡፡  የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አበባየሁ ገበያው የፓርቲውን ሊቀመንበር ኢንጂነር ይልቃልን በጉዳዩና ኤርፖርት ላይ በገጠማቸው ችግር ዙርያ አነጋግራቸዋለች፡፡

ወደ አሜሪካ ለመጓዝ ኤርፖርት ከገቡ በኋላ ችግር እንደገጠመዎት ሰምቻለሁ፡፡ ችግሩ ምን ነበር?
በአሜሪካ መንግስት ተጋብዤ ለሶስት ሳምንት የምቆይበት “ወጣት የአፍሪካ መሪዎች” የሚል ፕሮግራም ነበር፡፡ በሉፍታንዛ ነበረ የምሄደው። በኤርፖርት ውስጥ አስፈላጊውን ሂደት ሁሉ አልፌ የኢሚግሬሽንና ደህንነት ሰዎች ፎቶ ወስደው ፓስፖርቴን ተቀበሉኝና አንደኛው አለቆቹ ጋር ይዞኝ ሄደ፡፡ ለሶስት ሰዓት ያህል አንድ ክፍል ውስጥ አቆዩኝ፡፡ መጨረሻ ላይ ከፓስፖርቴ ውስጥ አንድ ገፅ ነቅለው አውጥተው … “አንድ ገፅ ወጥታለች” ብሎ ቀዶ አመጣልኝ … እቃዬ አውሮፕላኑ ውስጥ ገብቶ ነበር፤ እሱንም አወረዱት፡፡ ባለፈው ሰኞ ነበር አሜሪካ መገኘት የነበረብኝ፤ ለጊዜው ተስተጓጉሏል።
የአሜሪካ መንግስት “የአፍሪካ ስኬታማ ወጣት መሪ” በሚል እንደሸለማችሁ ባለፈው ሳምንት በፓርቲያችሁ ልሳን ላይ ተዘግቧል፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ ዕድሜው አጭር ከመሆኑ አንፃር ሽልማቱ ይገባናል ትላላችሁ?
ኢትዮጵያ ከዓለም የመጨረሻ ድሃ አገር ናት፡፡ አገሪቱን ከድህነት ለማውጣት የልጆቻችንን ዕድሜ የሚጠይቅ ተከታታይ ሥራ እና ትግል የሚያስፈልገው ነው፡፡ ሥራችንን የምትለኪው ግን በአንፃራዊነት ነው፡፡ ለምሳሌ ሰልፍ የሚባል ነገር ለስምንት አመት ኢትዮጵያ ውስጥ የማይታሰብ ነበር፡፡ አሁን ግን ሁሉም ፓርቲዎች ሰልፍና የአደባባይ የፖለቲካ ስራን እንደ ባህል እየያዙትና፤ እየተነቃቁም ናቸው። የሌሎች ፓርቲ አመራሮች “ህዝቡ ፈርቷል፤ ሰልፍ አይወጣም፣ አይተባበረንም” በሚል ዝም ብለው የመግለጫ ስራ ነበር የሚሰሩት፡፡ አሁን  ነገሮች ተለውጠዋል፡፡ አዲሱ ትውልድ በፊት ተከታይ እንጂ የራሱ ሀሳብ ኖሮት የሚሳተፍ አልነበረም። በሰማያዊ ፓርቲ ውስጥ ግን ሌት ተቀን የሚተጉ ሰዎችን ታያለሽ… እስከመታሰርም ደርሰዋል፡፡ ይህም የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡ የሚታየው የተፈጠረው የፖለቲካ መነቃቃትና ግንዛቤ ነው እንጂ የሀገራችንን ችግር ሰማያዊ ፓርቲ ፈትቶ ይጨርሰዋል ወይ ብትይ …. ትውልዱም የሚጨርሰው አይመስለኝም። ብዙ ተከታታይ ስራዎች ይጠይቃል፡፡ ከነበርንበት ጨለማ አንፃር ነው መታየት ያለበት፡፡ ቅንጅት በመፍረሱ ህዝቡ  ተስፋ ቆርጧል፡፡ ኢህአዴግ ጠቅላይ  በመሆኑና አፋኝ አዋጅ በመያዙ ዘላለማዊ ይመስል ነበር፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ ያንን አስቸጋሪ ሁኔታ ወደ ይቻላል በማምጣትና መነቃቃት በመፍጠር የፖለቲካ ድባቡን ቀይሮታል፡፡ ይሄ ደግሞ ረጅም ጊዜንና ትልቅ ስራን የሚጠይቅ ነበር፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ ግን በአጭር ጊዜ ይሄንን ማድረግ ችሏል፡፡ ከዚህ መንፈስ ነው የሚታየው እንጂ እኛ ብዙ ሰራን ብለን አንኩራራም፡፡ ገና ብዙ ስራ ነው የሚቀረን፤ ወደፊትም ብዙ እንሰራለን፡፡
ሰማያዊ ፓርቲ አሁን በዘረዘሩልኝ ምክንያቶች በአሜሪካ መንግስት “የአፍሪካ ስኬታማ ወጣት መሪ” በሚል ሸልሞታል፤ ሽልማቱም ይገባናል እያሉኝ ነው?
አዎ .. በደንብ ተሸልመናል፡፡ ሽልማቱም ይገባናል፡፡ ሽልማቱ ይገባናል ስንል ግን አሜሪካኖች አይደሉም የሚሸልሙንና የሚያወድሱን፡፡ ግን በራሳቸው መመዘኛ እኛን መምረጣቸው መልካም ነገር ነው፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ የሚያድግ ፓርቲ ነው፡፡ በኢትዮጵያ 70 ከመቶ የሚሆነው ህዝብ ወጣት ነው፡፡ ወጣቱን ሊወክል የሚችል ፓርቲ ነው፡፡ አዲስ አስተሳሰብን እንደፈጠረ ሃይል፣ ሽልማትን አስበን አይደለም የምንሰራው፡፡ ከዚህ በላይ ለሃገራችን ብዙ መስራት ይጠበቅብናል፡፡
በየጊዜው የተለያዩ ፖለቲከኞች ለህዝብ የገቡትን ቃል ሳይፈጽሙ ሸርተት ይላሉ፡፡ ህዝቡን ከዚህ ዓይነቱ ጥርጣሬ እንዴት ማውጣት ይቻላል ይላሉ?
ህልም ተፈርቶ ሳይተኛ አይታደርም፡፡ ከዚህ በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ በተደጋጋሚ ውጤት ያልመጣው የግለሰብ ፖለቲካ በመሆኑና ፖለቲካው በሰዎቹ ስብዕና ላይ በመመስረቱ ነበር፡፡ ይሄም ትግሉን ጎድቷል፡፡ ለዚህ መፍትሔው ትግሉን ህዝባዊ ማድረግና በአንድ ሰው ላይ አለመንጠልጠል ነው፡፡ ህዝቡ ፖለቲካውን የራሴ ነው ብሎ መያዝ አለበት፡፡ ግለሰቦች ሲሄዱ ሌሎች ይተካሉ፡፡
ኢትዮጵያ የወላድ መካን አይደለችም፤ ብዙ ልጆች አሏት፡፡ ፖለቲካውን የጋራ ካደረግነው የህዝቡ ስጋት ይቀንሳል፡፡ ፖለቲካ የዜግነት ጉዳይ ነው፤ ሁሉም መሳተፍ አለበት፡፡ ያ በሆነ ጊዜ ራሳቸውን ብቻ ለአገር ጠቃሚ አድርገው የሚያስቡ ሰዎች መመፃደቃቸውን ያቆማሉ፡፡ ያኔ መግነንም አምባገነንነትም ይጠፋል፡፡ ፓርቲውም ህዝባዊነት ይኖረዋል ማለት ነው፡፡ የሰማያዊ ፓርቲ ልጆች የትኛውም ቦታ ላይ ተወዳድረውና ሰርተው መኖር የሚችሉ ናቸው፡፡ በዚህ በአሰልቺና በተጠላ ፖለቲካ ውስጥ የገቡት የአገር ፍቅር ስላላቸው ነው፡፡ የአገር ፍቅር ደግሞ ከየትኛውም ሽልማትና ሞገስ በላይ ነው፡፡   
ከወር በፊት ለፓርቲ ሥራ ወደ አሜሪካና አውሮፓ ተጉዘው ነበር፡፡ የተለያዩ ስብሰባዎችንም ከዳያስፖራው ጋር አድርጋችኋል፡፡ በዚህ ጉዞ ዋና ዓላማችሁ ምን ነበር?
ሁለት ወር ነው የቆየሁት፤ አውሮፓ አስራ አምስት ቀን፣ አሜሪካ 45 ቀን ያህል፡፡ አትላንታ፣ ሳንሆዜ፣ ቦስተን፣ ላስቬጋስ፣ ሎስአንጀለስ፣ ሲያትል… ነበርኩ። የመጀመሪያ ስብሰባዬ ዲሲ ነበር፡፡ የስብሰባው ዓላማ ሰማያዊ ፓርቲ የተመሰረተባቸውን መሰረታዊ አላማዎችና ምሰሶዎችን ማስተዋወቅ ነበር፡፡ እዚህም አብዛኛውን ቅዳሜና እሁድ ምሁራንን ቢሮዋችን ውስጥ እየጋበዝን በፀረ ሽብር ህጉ፣ በመሬት ፖሊሲ፣ በአጠቃላይ በኢኮኖሚ በታሪካችን ዙሪያ በመወያየት ሰማያዊ ፓርቲ ያለውን አቋም ለህዝብ በተደጋጋሚ ይገልጽ፣ ያስተምር ነበር፡፡ የአሜሪካና አውሮፓ ጉዞ ዓላማ፣ በውጭ ያለው ኢትዮጵያዊ ለሰማያዊ ፓርቲ ሀሳቦችና ፕሮግራሞች ድጋፍ እንዲሰጥና የትግል ስልቶቻችንንም ጭምር ለማስተዋወቅ ነበር፡፡
ሰማያዊ ፓርቲ የቅስቀሳ ሀይል እንጂ ድርጅታዊ መዋቅር የለውም፤ የንቅናቄ ፓርቲ ነው፤ የበሰለ ፖለቲካ አያራምድም የሚል ትችት ይሰነዘርባችኋል? እርስዎ ምን ይላሉ?
የሞተን ፖለቲካ ልታነሺ የምትችይው፤ ህዝብ ሲከተልሽና መነቃቃትን መፍጠር የምትችይው የአገሪቱን ችግር በሚገባ መረዳት ሲቻል፣ ለዚያ ችግር መፍትሄ ሊሆን የሚችል ቀጥተኛ ፖሊሲ ሲኖር፣ ፖሊሲውን ለማስፈፀም ደግሞ ብቃት ያለው አመራር ሲኖር ነው ህዝቡ የሚነቃነቀው፡፡ በስልጣን ላይ የተቀመጡ ሰዎች ፖሊሲ አላቸው፤ ሰማያዊ ፓርቲዎች ግን ፖሊሲ የላቸውም ቢባል ለአመለካከት የማይመች ነው የሚሆነው፡፡ በመሰረቱ አንድ ሰው ሊነቃነቅ የሚችለው  የሚያምንበት ነገር ሲኖር ነው። መነቃነቅ ከተፈጠረ እምነት አለ፡፡
ተቃዋሚ ፓርቲዎች በህብረት ለመስራት የትብብርና የውህደት እንቅስቃሴ ላይ ቢሆኑም ሰማያዊ ፓርቲ ለውህደት ዳተኝነት ይታይበታል የሚል ትችት ይሰነዘርበታል…
በኢትዮጵያ የ40 ዓመት የፖለቲካ ፓርቲዎች ታሪክ “ዛሬ ተዋህደው፤ ነገ ፈረሱ” ሲባል ነው የምናውቀው፡፡ ይሄ እንዲቀጥል አንፈልግም፡፡ ስለዚህም የውህደትንና የጥምረትን ነገር በጥንቃቄ መመርመር እንፈልጋለን፡፡ በሆይሆይታ የሚፈጠሩ ጥምረቶችና ውህደቶች ውጤቱ ሲያመጡ አልታየም። ለምሳሌ አንድነት ወደ መድረክ የገባው በጣም ፈጥኖ ስለነበር ራሱን ጎድቷል፡፡ እናም አንድነት ከመድረክ ታገደ ተባለ፡፡ ሰላሳ ሶስት ፓርቲዎች ተቋቁመው ምንም ነገር ሳይፈይዱ ነው የከሰሙት። በቅርቡ ደግሞ “አንድነትና መኢአድ ለውህደት እየተነጋገሩ ነው” ሲባል ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ተቋረጠ ተብሏል፡፡ እኛ ጥናት ሳይደረግ በፍጥነት ሮጠን ወደ ውህደት አንገባም፡፡ ወደ ፖለቲካው ያልገባ አዲሱ ትውልድ አለ፤ ፓርቲዎች አካባቢ ጊዜ ከምናጠፋ እዛ ላይ አተኩረን ህዝብ ውስጥ ብንሰራ ጉልበትም፣ ሀይልም፣ ዕውቀትም ገንዘብም አለ የሚል አቋም ይዘን ነው የምንንቀሳቀሰው፡፡ በመርህ ደረጃ ግን ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ለመስራት ሰማያዊ ፓርቲ ዝግጁ ነው፡፡
የምርጫ ስነ ምግባር ኮዱን አንፈርምም ብላችኋል፡፡ ለምንድነው ለመፈረም ያልፈለጋችሁት?
አንድ ህግ በሀገር ደረጃ ህግ ሆኖ ከወጣ በኋላ መፈረም አለመፈረም አስገዳጅ አይደለም፤ ትክክለኛም አሰራር አይደለም፡፡ ለምሳሌ የማናምንባቸው አዋጆች ሁሉ ወጥተዋል፡፡ የፀረ-ሽብር አዋጅ፣ የመሬት ሊዝ አዋጅ፣ የሲቪክ ማህበራት ማደራጃ፣ የሚዲያና የመረጃ ነፃነት አዋጅ ወጥተዋል፡፡ እነዚህን አዋጆች ሰማያዊ ፓርቲ አፋኝ አዋጆች ናቸው ብሎ ያምናል፡፡ ህግ ሆነው ከወጡ በኋላ ግን ህገመንግስታዊ በሆነ መንገድ እስከ ምንቀይራቸው ድረስ ለአዋጆቹ መገዛት ግዴታችን ነው፡፡ የስነ ምግባር ደንብና አዋጅ በፓርላማ ህግ ሆኖ ፀድቋል፤ ለእሱ ብቻ መፈረም አያስፈልግም። አዋጅ በወጣ ቁጥር እኮ አንፈርምም፡፡ አጀንዳ ሆኖም መቅረብ የለበትም፡፡ ኢህአዴግ ለድርድር እንቅፋት ለመፍጠር ሲፈልግ ያመጣው ነው፡፡