Administrator

Administrator

    “የተባረሩት ሙስና መኖሩን በመጠቆማቸው አይደለም”- ድርጅቱ

   በ“የእለት ደራሽ የእርዳታ ትራንስፖርት ድርጅት ሙስና እየተፈፀመ ነው” በሚል ርዕስ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ በወጣ ዘገባ ምክንያት የድርጅቱ የህግ አገልግሎት ክልል ኃላፊ፤ ከስራ እንዲሰናበቱ መደረጋቸውን የገለፁ ሲሆን የድርጅቱ ስራ አስኪያጅ በበኩላቸው፤ ስንብቱ የሙስና ጥቆማ ከማቅረባቸው ጋር የተያያዘ አይደለም ብለዋል፡፡ የእለት ደራሽ የእርዳታ ትራንስፖርት ድርጅት ህግ አገልግሎት ኃላፊ የሆኑት አቶ ያለው አክሊሉ፤ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ ከድርጅቱ የስነ-ምግባር መኮንን አቶ ሰማህኝ ተፈሪ እና ከመሰረታዊ ሰራተኛ ማህበሩ ም/ሊቀመንበር ጋር በመሆን በተቋማቸው ከፍተኛ ሙስና እየተፈፀመ መሆኑንና የፌደራል የስነ-ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ጉዳዩን በቸልተኝነት እየተመለከተው መሆኑን መግለፃቸው ይታወሳል፡፡ አቶ ያለው አክሊሉ ሰኔ 30 ቀን 2006 በተፃፈ ደብዳቤ ከስራ በቀጥታ እንዲሰናበቱ መደረጉን ጠቁመው፤ ስነ ምግባር መኮንኑ አቶ ሰማኸን ተፈሪ በተፃፈ ደብዳቤ ለአዲስ አድማስ በሰጡት መግለጫ በድርጅቱ ውስጥ ያለው የኢንዱስትሪ ሰላም አንዲናጋና ሽብር እንዲፈጠር ማድረጋቸው ተገልፆ፤ በ3 ቀን ውስጥ አለኝ የሚሉትን የሰውና የሰነድ ማስረጃ ለድርጅቱ እንዲያቀርቡ፤ ይህ ባይሆን እርምጃ ሊወሰድባቸው እንደሚችል የሚያመለክት ደብዳቤ ደርሷቸዋል፡፡

ባለፉት ሁለት አመታት በድርጅቱ ይፈፀማሉ ያልናቸውን የሙሰና ተግባራት ለህይወታችን ሳንሳሳ ለማጋለጥ ከፍተኛ ጥረት አድረገናል የሚሉት አቶ ያለው፤ “የፀረ- ሙስና ኮሚሽን ጥቆማችንን በቸልታ ስለተመለከተው ጉዳዩን ወደ ሚዲያ ማቅረብ አስፈላጊ ነው ብለን በማመን ለአዲስ አድማስ ጋዜጣ ዝርዝር መረጃውን ልንሰጥ ተገድደናል ብለዋል፡፡ ዘገባው በጋዜጣው ከተስተናገደ በኋላ የድርጅቱ ስራ አመራሮች ሠራተኞችን ስብሰባ ጠርተው በዘገባው ላይ ውይይት ማድረጋቸውን የጠቀሱት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ በስብሰባው ላይ የድርጅቱን ስም እንዳጠፋን ተደርጐ በሁለት ቀናት ውስጥ እርምጃ እንደሚወሰድብን ለሠራተኛው ተገልጿል ይላሉ፡፡ ስብሰባው በተካሄደ በሁለተኛው ቀን “የስራ ሪፖርት ሲጠየቁ ስርአት የጐደለው ምላሽ አቅርበዋል” በሚል ምክንያት የስራ ስንብት ደብዳቤ እንዲደርሳቸው መደረጉን አቶ ያለው አስታውቀዋል፡፡ የተሰናበቱበት ምክንያትም ቀደም ሲል ለሠራተኞች ቃል በተገባው መሠረት ሳይሆን ስራ አስኪያጁ “የ5 ወራት የስራ ሪፖርት ይቅረብልኝ” ሲሉ በዘለፋ የታጀበ ያልተገባ ምላሽ ሰጥተሃል፤ በሚል ምክንያት እንደሆነ ያብራሩት አቶ ያለው፤“የተፈፀመብኝን በደል በድርጅቱ የስነምግባር መኮንን በኩል ለፌደራል የስነምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን የምርመራና አቃቤ ህግ ዳይሬክቶሬት ባመለክትም ኮሚሽኑ እስካሁን ምላሽ አልሰጠኝም” ብለዋል፡፡

ቀደም ሲል ለፀረ - ሙስና ኮሚሽን በድርጅቱ ተፈጽመዋል ያልናቸውን 56 አይነት ወንጀሎች በማስረጃ አስደግፈን አቅርበናል ያሉት አቶ ያለው፤ አሁንም ቢሆን ከዚህ ትግል የሚገታኝ የለም ብለዋል፡፡ በጉዳዩ ላይ ያነጋገርናቸው የድርጅቱ ስራ አስኪያጅ አቶ ጀማል መሃመድ በበኩላቸው፤ ግለሰቡ ከስራ እንዲሰናበቱ የተደረገው የ5 ወራት የስራ ሪፖርት በአግባቡ እንዲያቀርቡ ሲጠየቁ፣በዘለፋ የታጀበና ከተጠየቀው ጋር ያልተገናኘ ምላሽ በመስጠታቸው የተወሰደ እርምጃ እንጂ የሙስና ጥቆማ ከማድረጋቸው ጋር የተያያዘ አይደለም ብለዋል፡፡ “ሠራተኛው ስብሰባ ተጠርቶ በዘገባው ላይ ውይይት ተካሂዷል የተባለው፣በወጣው ዘገባ ሠራተኛው ሳይረበሽና ሳይደናገጥ ስራውን እንዲያከናውን መመሪያ ለመስጠት ነው” ሲሉ መልሰዋል - አቶ ጀማል፡፡ የፌደራል የስነ - ምግባርና የፀረ - ሙስና ኮሚሽን የትምህርትና የስልጠና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ፤“አንድ የሙስና ጠቋሚ ከስራው ከተሰናበተ አሊያም ጥቅማ ጥቅሙን ካጣ፣በኮሚሽኑ ይህ የተደረገበት ምክንያት በሚገባ ከተጣራ በኋላ፣ ወደ ስራው እንዲመለስ አሊያም ያጣውን ጥቅማጥቅም መልሶ እንዲያገኝ ይደረጋል” ካሉ በኋላ “እንዲህ ያለ ጥቃት ደርሶብኛል የሚሉ ግለሰቦች በየድርጅቶቹ ካሉ የስነምግባር መኮንኖች ጋር በመሆን ወደ ኮሚሽኑ መጥተው ቢያመለክቱ ይመረጣል” ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ከ612 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ከአላማጣ - መሆኒ - መቀሌ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ሃይል ማስተላለፊያ መስመር ሠርቶ አጠናቀቀ፡፡ በየካቲት 2004 ዓ.ም ስራው የተጀመረው የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመር፤ 141 ኪሎ ሜትር የሚረዝም ሲሆን 230 ኪሎ ቮልት ኤሌክትሪክ ይሸከማል፡፡
ሙሉ ለሙሉ ስራው የተጠናቀቀው ይህ ፕሮጀክት፤ ከተከዜ ሃይል ማመንጫ 300 ሜጋ ዋት፣ ከአሽጐዳ ንፋስ ሃይል ማመንጫ 120 ሜጋ ዋት የሚመነጨውን የኤሌክትሪክ ሃይል ያስተላልፋል፡፡
በአምስት አመቱ እድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድና ትግበራ በአጠቃላይ 10ሺህ ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ ለማመንጨት መታቀዱን የጠቆመው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ኮርፖሬሽን፤ የህዳሴው ግድብ ከ35 በመቶ በላይ፣ የጊቤ 3 ግድብ ከ86 በመቶ በላይ፣ የገናሌ ዳዋ ከ56 በመቶ በላይ ግንባታቸው መጠናቀቁን ገልጿል፡፡

Wednesday, 30 July 2014 07:56

ሌላው ጦርነት

“ሃሎ?! ኮሎኔል ሙሳ ነኝ! ማን ልበል?”
“ሃሎ! ጓድ ኮሎኔል…ይቅርታ! ከሆቴሉ እንግዳ መቀበያ ክፍል ነው!”
“ለምንድነው ከእንቅልፌ የምትቀሰቅሱኝ?! ለራሴ የበላሁት ምሳ አልፈጭ ብሎኝ መከራዬን ያሳየኛል! ከጓድ ሊቀመንበሩ ቢሮ በስተቀር ከየትም ቢደወል እንዳትቀሰቅሱኝ አላልኩም?!”
“ይቅርታ ጓድ ኮሎኔል! አንዲት ባልቴት እዚህ ሆቴሉ በር ላይ ቆመዋል…እናቱ ነኝ ይላሉ!”
“የማን እናት?”
“የእርስዎ መሰለኝ…በጦርነቱ ተፈናቅዬ ከምስራቅ ጦር ግንባር ነው የመጣሁት ይላሉ ጓድ ጌታዬ!”
“ለመሆኑ ማን እባላለሁ አለች?”
“በላይነሽ እባላለሁ ይላሉ ጓድ ኮሎኔል! የእርስዎ ወላጅ እናት ነኝ ይላሉ…”
“ልትሆን ትችላለች…ማነው ያለሁበትን ያሳያት ግን? እኔ እናት አገርና አብዮት እንጂ ሌላ እናት አላውቅም!”
“ምን ልበላቸው ታዲያ ጓድ ኮሎኔል?”
“በቃ አላውቃትም አልኳችሁኮ! እናቴ ብትሆን ባትሆንም ግድ የለኝም! ማነው ግን ያለሁበትን ቦታ ያሳያት? ይሄ የአናርኪስቶች ሴራ መሆን አለበት!”
“ማን እንዳሳያቸው አይታወቅም ጓድ ኮሎኔል!”
“አስር ብር ስጧትና እንደዚህ የሚባል ሰው እዚህ የለም ብላችሁ ሸኟት! ይልቁኑ ያቺን የማታዋን ቆንጅዬ ልጅ የሆቴል ታክሲ ልካችሁ አሁኑኑ አስመጡልኝ! እዚህ ሌላ ጦርነት ውስጥ ነው ያለሁት! ይገባችኋል?”
“ይገባናል ጓድ ኮሎኔል! በደንብ ይገባናል!”
“አልገባ ካላችሁ ደግሞ መጥቼ በሚገባችሁ ቋንቋ አነጋግራችኋለሁ!! አናርኪስት ሁላ! ልክ ነው የማስገባሽ!”
“ይገባናል ጓድ ኮሎኔል! ልጅቷን አሁኑኑ እናስመጣታለን!”
“በጓድ ሊቀመንበርና በአብዮቱ ቀልድ የለም! ይገባችኋል?”
“ይገባናል ጓድ ኮሎኔል! በደንብ ይገባናል!”
(ከደራሲ ሙሉጌታ ጉደታ “ያልተሸነፈው”
የአጭር ልብወለድ መድበል የተወሰደ፡፡
ሰኔ 2006 ዓ.ም)

Wednesday, 30 July 2014 07:54

ብረር ብረር አለኝ

       ናፍቆት ደጋግማ ስትመጣ ደጋግሜ የለም አስባልኩ፡፡ ጋሎይስን ለሦስተኛ ጊዜ ማንበቤ ነው። አንዳንዴ መንገዱ መንገዴ ይመስለኛል፡፡ ሌላ ጊዜ በእልሁ ከእኔ ይልቅ አሰፋ ጢሪሪን ወይም ንዳዴን መስሎ ይታየኛል፡፡
መኝታ ክፍሌ ተዘግቶ ማንበብ ስለሰለቸኝ ወጥቼ ካክስቴ ቤት ሥር የቱሪማንቱሪ ቅጠል አንጥፌ ተቀመጥኩ፡፡ መጽሐፉ የተዘጋጀው ለመኝታ ቤት ውስጥ ይመስላል፡፡ ሌላ ቦታ ለማንበብ አይመችም። በደረት አልጋ ላይ ተንበልብሎ በግራ በኩል መጽሐፉን፣ በቀኝ በኩል መዝገበ ቃላቱን አድርጐ በብዙ ማስታወሻ ወረቀቶች ተከብቦ ሲነበብ የበለጠ ይገባል፡፡ ግን ሰለቸኝ፡፡
ልዑል መውደቂያ ዘወትር ጭር እንዳለች ነው። አሁን ግን አንድ ናዝሬት ሚሽን የሚማር ልጅ ለክረምት ዕረፍት ወላጆቹ ጋ መጥቶ ይረብሻታል። ግራር ላይ ወይም የቱሪማንቱሪ ጫፍ ላይ ወጥቶ የተለያዩ ዘፈኖችን በረጅሙ ይለቅቃል፡፡ አሁንም አለ። የት እንደሆነ ግን ላየው አልቻልኩም፡፡ ዘፈኑ ብቻ እየመጣ ከጆሮዬ ጋር ይላጋል፡፡
“ልቤ ቢቀርበት ምነው
ልቤ ቢቀርበት ምነው
ምኞት እኮ ህልም ነው፡፡”
አባቴ በልጅነቱ ይኼን ልጅ ሳይሆን አይቀርም ስል አሰብኩ፡፡ ዘፈኑን ማስታወስ ከማልፈልገው አባቴ መንጭቄ የምጥልበት ስፈልግ ጋሽ በረደድ ትዝ አሉኝ። አክስቴ ላይ ያላቸው ምኞት ህልም እንደሆነ ከዚህ ዘፈን ሊማሩ ይገባቸዋል፡፡ መኖሪያቸው ከአክስቴ ቤት መደዳ ጫፍ ላይ ነው፡፡ ቤታቸው በእኛ ቤት ላይ ምኞት ያለው ይመስል ከሰልፉ አፈንግጦ በመቆልመም በአንድ ዓይኑ ወደዚህ ይመለከታል፡፡ የጋሽ በረደድ ሚስት አጐንብሰው ወጥተው አጐንብሰው ይገባሉ፡፡ ኅይለኛ ናቸው፡፡ የባላቸው ማጋጣነት ወሬ ሲደርሳቸው፣ ወይም ደስ የማይል አዝማሚያ ባላቸው ላይ ሲመለከቱ ቱግ ይላሉ፡፡ ቱግታቸው ፈር የለቀቀ አይደለም፡፡ የባላቸውን አንቱታን አይዘነጉም፤ ግን ይሳደባሉ፡፡
“አንቱ ሸርሙጣ” ይላሉ በእጃቸው ጭብጥ ጀርባቸውን እየደቁ፡፡ “አንቱ ሸርሙጣ፣ አንቱ ሸርሙጣ፣ አንቱ ሸርሙጣ….”
እኔ ጋሽ በረደድ ላይ እስቃለሁ፡፡ ጋሽ በረደድ አይናደዱም፡፡ ለኔ ምላሽ የሰጡ ሳያስመስሉ፤
“አጤ ቴዎድሮስም የተቸነፉ በሚስታቸው ነው፡፡ ለሚስት መቸነፍ የጀግና ወጉ ነው…ምናምን” ይላሉ፡፡
የልዑል መውደቂያ አባወራዎች ጥቂት ናቸው። ግማሽ ክብ ቅርጽ ላይ በድጋሚ የሚጠመጠምባት ሌላ የቤት መቀነት አለ፡፡ እያንዳንዱ ቤት ፀሐይ እንዳይገባበት ደጃፉ ላይ ቱሪማንቱሪ ዛፍ ተተክሏል፡፡ የጋሽ ጥበቡ ቤት እነዚህ መደዳ ጫፍ ላይ ከጋሽ በረደድ ቤት አጠገብ ይገኛል፡፡ የጋሽ ጥበቡ ሚስት ሲበዛ ተፀያፊ ናቸው፡፡ ጋሽ ጥበቡ ከዓይጥ አደን ሲመለሱ፤
“እዛው፣ እዛው….” እያሉ ያንቋሽሿቸዋል፡፡ የአይጥ ማስገሪያቸውን ማዶ አስጥለው ሳሙናና ውኃ ያመጡላቸዋል፡፡ እየተነጫነጩ ዕቃ ሳያስነኩ እራሳቸው ያስታጥቧቸዋል፡፡ ይህን ስመለከት ምናልባትም ባልና ሚስቱ አብረው ማዕድ ከቆረሱ ብዙ ዓመታቸው ሳይሆን አይቀርም እላለሁ፡፡
“በኑሮ ላይ ተቸግሮ ሰው ሲጐዳ፣
መልኩን ጥሎት ገሸሽ ይላል እንደባዳ”
ልጁን እንደ ጥንብ አንሳ ከተንሿጠጠ እራሱ ጋር ግራሩ ላይ አየሁት፡፡ ሹል አፉን እየከፈተ ሲታይ የሚዘፍን ሳይሆን የሚያንቋርር ይመስላል፡፡
በዚህ መካከል ከየት እንደመጣች ያላየኋት ናፍቆት ፊቴ ተገተረች፡፡ ያለወትሮው እግሯ ንፁህ ሆኖ አየሁት፡፡ በስሱ ቅባት የተባበሰሰ ቢሆንም የሞዶ እንኩሮአማ አቧራ አላንዣበበበትም፡፡ በአየር ላይ ተንሳፋ ካልመጣች በቀር እንዲህ ንፁህ ሊሆን እንደማይችል የታመነ ነው፡፡ የእግሯ ጣቶች በሽብር ዓይንን እንዲያፈገፍግ ያስገድዳሉ፡፡  
(ከደራሲ ዓለማየሁ ገላጋይ
“የብርሃን ፈለጐች” የተቀነጨበ

በገጣሚ ትዕግስት ማሞ የተሰናዳው “የእምነት ወጎች” የተሰኘ የግጥም ስብስብ በሲዲ ተዘጋጅቶ ለገበያ የቀረበ ሲሆን ባለፈው ረቡዕ ምሽት በዋቢ ሸበሌ ሆቴል በድምቀት ተመርቋል፡፡
16 ግጥሞችን ያካተተው የግጥም ሲዲ በተመረቀበት ወቅት የቀድሞ መምህሯ ረዳት ፕ/ር ሙሉጌታ ጀዋሬ፣ ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራና ሌሎች ገጣሚያንም ስራዎቻቸውን አቅርበዋል፡፡ በእለቱ ገጣሚ ትዕግስት ስራዎቿን ያቀረበች ሲሆን የታዳሚያን መግቢያ አንድ ሲዲ ነበር፡፡
በሲዲው ውስጥ ከተካተቱት 16 ግጥሞች መካከል “ትዝታና ፍቅር”፣ “ጋዜጠኛው”፣ “ይድረስ ለወንድሜ”፣ “ይማርሽ”፣ “አድዋ”፣ “ክፈለኝ” እና የሲዲው መጠሪያ የሆነው “የእምነት ወጎች” የሚገኙበት ሲሆን በግጥሞቹ ውስጥ ማህበራዊ ጉዳዮች በምፀትና በትዝብት ተዳስሰዋል፡፡ በ50 ብር እየተሸጠ ያለው የግጥም ሲዲው በአሁኑ ሰዓት ከጎጃም በረንዳ ወደ ዮሃንስ በሚወስደው መንገድ ላይ በሚገኘው “ግሬስ” ህንፃ ላይ እየተከፋፈለ ይገኛል፡፡

Wednesday, 30 July 2014 07:47

የፍቅር ጥግ

የዳቦ ረሃብለ ከማጥፋት ይልቅ የፍቅር ረሃብ  ለማጥፋት የበለጠ ያስቸግራል፡፡
ማዘር ቴሬዛ
(ትውልደ አልባንያ ሮማኒያዊ ካቶሊክ መነኩሲት)
ፍቅርን እንደማጣት አስፈሪ ነገር የለም፡፡ ሞት ከዚህም ይከፋል የሚሉ ዋሽተዋል፡፡
ካውንቲ ኩሌን
(አሜሪካዊ ገጣሚ፣ ደራሲና ፀሃፌ ተውኔት)
ለማፍቀር ፅናት ያላቸው ሰዎች ለስቃይም ፅናት ሊኖራቸው ይገባል፡፡
አንቶኒ ትሮሎፔ
(እንግሊዛዊ ደራሲ)
ፍቅሬ፣ እውነቴን ነው ብላ ስትምልልኝ
እየዋሸችኝ እንደሆነ ባውቅም አምናታለሁ፡፡
ዊሊያም ሼክስፒር
(እንግሊዛዊ ባለቅኔና ፀሃፌ ተውኔት)
ሴት አታፈቅርም፤ አፍቃሪው ወንድ ነው፤ ሴቷ እሷ ተፈቃሪ ናት፡፡
ኦገስት ስትሪንድበርግ
(ስውዲናዊ ድራማ ፀሃፊ)
መድረክ ላይ ከ25ሺ የተለያዩ ሰዎች ፍቅራቸውን ይገልፁልኛል፡፡ የማታማታ ግን ለብቻ ወደ ቤቴ አዘግማለሁ፡፡
ጃስ ጆንሊን
(አሜሪካዊ የሮክ ሙዚቃ አቀንቃኝ)
ብቸኝነት ያለመፈለግ ስሜት በእጅጉ የከፋ ድህነት ነው፡፡
ማዘር ትሬዛ
(ትውልደ - አልባንያ ሮማኒያዊ ካቶሊክ መነኩሴ)
የሴት ምናብ በጣም ፈጣን ነው፡፡ በቅፅበት ከአድናቆት ወደ ፍቅር፣ ከፍቅር ወደ ጋብቻ ይዘላል፡፡
ጄን  አውስተን
(እንግሊዛዊት ደራሲ)
ጋብቻ ድንቅ ተቋም ነው፤ እኔ ግን ወደ ተቋሙ ለመግባት ዝግጁ አይደለሁም፡፡
ማ ዌስት
(አሜሪካዊ ተዋናይና ኮሜዲያን)
ባሎችና ሚስቶች እርስ በርስ የማይግባቡበት ምክንያት ፆታቸው የተለያየ በመሆኑ ነው፡፡
ዶሮቲ ዲክስ
(አሜሪካዊት ጋዜጠኛና ደራሲ)

አቶ ሀይለማርያም ወልዱ በቅርቡ “ህልፈተ አንጃ ወ ክሊክ ዘ ኢህአፓ” የሚል መፅሀፍ ለንባብ አብቅተዋል፡፡ ከመፅሀፉ ጋር በተያያዘ  የኢሕአሠ ቤዝ የነበረውን የኢሮብ ህዝብ አስመልክቶ ከአዲስ አድማስ ጋር ቃለምልልስ አድርገዋል፡፡



ኢህአፓ አለሁ ነው የሚለው፤ አንተ በመጽሐፍህ “ህልፈት አንጃ ወ ክሊክ ዘ ኢሕአፓ” በማለት ሞቷል ትላለህ፡፡
ይህ የብዙዎች ጥያቄ ነው፡፡ አለሁ የሚለው ወገን መኖሩን ማሳየት መቻል አለበት፡፡ እኔ እስከማውቀው ድረስ (ኢትዮጵያ ውስጥ ነው ያለሁት) ኢትዮጵያ ውስጥ ኢህአፓ እንደ ድርጅት የለም ፣አመለካከቱ ራዕዩ አለ፡፡ የኢህአፓ ልጆች የታገሉለት ነገሮች በህገመንግስቱ ተረጋግጧል። አተገባበር ላይ “እንዴት ነው” ብትይኝ ሌላ ነገር ነው፡፡ በዚህ አይን ከታየ ኢህአፓ አለ፡፡ ከዚያ ውጪ ኢትዮጵያ ውስጥ ኢህአፓ እንደ ድርጅት የለም። ሜዳው ኢትዮጵያ ውስጥ ነው፤ ዳያስፖራ አለሁ ማለት የትም አያስኬድም፡፡
የበረሃ ስም እስኪለምዱት አይከብድም?
ምንም አይከብድም ግዴታ ነው፡፡ እኔን፤ ብርሃነመስቀል በዛብህ ነህ አለኝ፡፡ ተቀበልኩት። እሱን ክርስቲያን አካባቢ ሰለሞን፤ ሙስሊሞች አካባቢ ሱሌይማን እንለው ነበር፡፡
ከኢህአፓ ሠራዊት ከኢህአሠ የምታደንቀው የጦር መሪ ማን ነበር?
እኔ ጦርነት ላይ የመሳተፍ ዕድል አልነበረኝም፡፡ ሮባ ጥሩ ተዋጊ ነው ሲሉ ግን እሠማለሁ፡፡ ሠራዊቱ የምሁር ሠራዊት ነበር፡፡ ምሁር ሁለት ልብ ነው፤ ለጦርነት ምቹ አይደለም፡፡ እኔም ያው ነበርኩ፡፡
እስቲ ወልዱ ስለ ራስህ ንገረኝ
ትውልዴ ኢሮብ ነው፡፡ የተወለድኩት አሊቴና ነው፡፡  እስከ አስራ ሁለተኛ ክፍል የተማርኩት አዲግራት ነው፡፡ አዲስ አበባ በቀዳማዊ ሀይለስላሴ ዩኒቨርሲቲ ለሁለት አመት ተምሬያለሁ፡፡ በደርግ ዘመን ወደ ትግል ገባሁ፡፡ የመጀመሪያዎቹ የትግል አመታት ጥሩ አልነበሩም፡፡
ለምን የመጀመሪያዎቹ የትግል አመቶች ጥሩ አልነበሩም?
በአጭር ጊዜ ውስጥ ነው ደርግ እጅ ላይ የወደቅሁት፡፡ የድርጅቴን ስም አጋልጦ ላለመስጠት ራሴን ጀብሀ ነኝ አልኩ፡፡  የታሠርኩት አስመራ ውስጥ ስንበል የሚባል ቦታ ነበር፡፡ የተለመደው የደርግ ምርመራ ከተደረገብኝ በኋላ፣ ጉዳዬ ወደ ጦር ፍርድ ቤት ተላለፈ፡፡ በጦር  ፍርድ ቤት በመታየት ላይ እያለ  ወህኒ ቤት ሆኜ ጥሩ ነገሮችን አግኝቻለሁ።
ምን ጥሩ ነገር አገኙ?
በአጋጣሚ ከአዲስ አበባ የወህኒ ቤት አስተዳዳሪዎች ወደዚያ ሲመጡ የጠየቅሁት የመብት ጥያቄ (ት/ቤትና ላይብረሪ እንዲከፈት) ምላሽ በማግኘቱ፣ በእስረኞቹ ዘንድ ተቀባይነት እንዳገኝ አደረገኝ፡፡ ለእኔ የመጀመሪያ ሹመት ማለት ይቻላል። የእስረኞቹ ፀሐፊ ሆንኩ፡፡ ቋንቋ ተማርኩ፣ ብዙ መፃሕፍት አነበብኩ፡፡
ከመታሰሬ በፊት የነበረኝ የማርክሲዝም ዕውቀት ውሱን ነበር፡፡ ከታሠርኩ በኋላ ማርክሲዝም ሌኒኒዝም፣ ማኦይዝም ከዚያም አልፎ ስለ ፎኮይዝም፤ በደንብ በማንበቤ የቲዮሪ ትጥቅ አገኘሁ፡፡  ስለ ህቡዕ የፖለቲካ ድርጅት አሠራር በተግባር የተማርኩትም ወህኒ ቤት ነው፡፡ ከሁሉም ጋር በነበረኝ ግንኙነት የህዝባዊ ግንባር አይን ውስጥ ገባሁ፡፡ በተማርኩት መሠረትም የቤት ስራ ተሰጥቶኝ በብቃት ተወጥቻለሁ፡፡
የቤት ስራው ምን ነበር?
እስረኞችን ማስፈታት ነበር፡፡ ይሄን ያደረግሁት ከተራ ወታደር እስከ ሃላፊዎች ድረስ በድርጅት እንዲታቀፉ በማድረግ ነው፡፡ ኤርትራዊያኑን በኤርትራ ድርጅት ኢትዮጵያውያኑን በኢትዮጵያ ድርጅት፣ እንዲደራጁ በህዋስ ማዋቀር ነበር፡፡
ማን ነበር የመለመለህ?
አንዲት አዜብ የምትባል ልጅ ናት፡፡ አዲስ አበባ እንደምታውቀኝ ነግራኝ የመለመለችኝ፡፡ በኋላ ላይ ግን እሷን ያሠማራት ሰው አስመራ ውስጥ የታወቀ (ከ1966 እስከ 1983 ድረስ የፌዳይን መሪ የነበረ) ልጅ መሆኑን አወቅሁኝ፡፡ የበረሃ ስሙ ቫይናክ ይባላል፡፡
ቫይናክ በቅርብ በመኪና አደጋ ከሞቱት የኤርትራ ጀነራሎች አንዱ ነው አይደል?  ቫይናክ የተባለው ለምንድን ነው?
አዎ በቅርቡ ነው የሞተው፡፡ ቫይናክ ማለት የመድሃኒት ስም ነው፡፡ የራስ ምታት መድሃኒቶች ካፌኖል፣ ቫይናክ፣ አስፕሪን ናቸው፡፡ ቫይናክ እንግዲህ “አስቸጋሪውን የሚያስታግስ” ለማለት የወጣ ይመስለኛል፡፡
ኢሮብ የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ሠራዊት (የኢህአፓ ወታደራዊ ክንፍ) ይንቀሳቀስበት የነበረ ቦታ ነው፡፡ እስቲ ስለአካባቢውና ስለህዝቡ ንገረኝ…
ስለ ህዝቡ ማንነት የተለያዩ አፈታሪኮች አሉ። በአብዛኛው ተቀባይነት ያገኘው፣ አሁን ያለው የኢሮብ ህዝብ ከደጋ አካባቢ  ከውቅሮ በስደት መጥቶ ነው የሚለው ነው፡፡  በኔ እይታ ግን  እዚያ የቆየ ነው የሚሉትን እጋራለሁ፡፡ ምክንያቱም ቋንቋው ከኩሽ ቋንቋዎች የሚመደበው ሳሆ ነው፡፡ ይህ ቋንቋ ከአፋርኛ ጋር ከቀበሌኛ ልዩነት በስተቀር ይግባባል። በምስራቋ አፍሪካ የህዝቦች እንቅስቃሴ ነበር፡፡ በዚህ ውስጥ ግን የሚንቀሳቀሰው ወገን እምነቱንም ሆነ ቋንቋውን አይለቅም፡፡ እኔ ራሴን እንደሳሆ ነው የምቆጥረው፡፡ በሀይማኖት እስከ አስራ ስምንተኛው ክፍለ ዘመን ድረስ ሶስት ቤተክርስትያኖች ነበሩ፣ ህዝቡም ክርስትናን ተቀብሎ ነበር ይባላል፡፡ ነገር ግን የባህላዊ እምነት ተከታዮች ነበሩ፡፡ በየቦታው መስዋዕት የሚያደርጉባቸው ቦታዎች ነበሩ፡፡ ዝናብ ከጠፋ ላም ወይም  በሬ ስጋውን ትልቅ አምራ መጥቶ ሲወስደው መንፈስ ወሰደው ይህን የሚያሳይ እስከአሁን አሁንም ድረስ ህብረተሰቡ በዘፈኑ ላይ የሚያስገባው ሀረግ አለ፡፡ “አኸዬ ጉማይቶ” (“አሞራው ናና ውሰደው” ማለት ነው፡፡) ከዚያ ዝናብ ይመጣልናል ብለውም ያምናሉ፡፡
ቤተክርስቲያኖች አሉ ይባል እንጂ ቄሶች የሚመጡት ከጉንደጉንደ ነበር፡፡ ጉንዳጉንዲ ደቀ እስጢፋኖስ በመባል በሚታወቅ በ13ኛውና 14ኛው ክፍለዘመን አካባቢ በስራዬ የተጀመረ እንቅስቃሴ ውስጥ የነበሩ መነኮሳቶች የነበሩበት ነው፡፡ እንቅስቃሴው በመሪዎች ተወገዘና ተከታዮቹ ተገደሉ፡፡ ከሠራዬ ታቦታቸውን ይዘው ወደ ሽሬ መጡ፣ ወደ ጐንደር ሄዱ፤ ከዚያ ወደ ጐጃም፣ ወደ ሰሜን ሸዋ መጡ፡፡ ሰሜን ሸዋ ደብረብርሃን ላይ እንዲቃጠሉ ተደረጉ፡፡
ከዚያ ያመለጡት በወሎ አድርገው ትግራይ ገብተው ያረፉት ጉንደጉንደ ላይ ነው፡፡ ከደጋ ወደ ኢሮብ ተሰደደ የሚባለው ህዝብ ከዚህ ታቦት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ኢሮብ የሚለው ቃልም ከዚያ ጋር ይያዛል፡፡
እንዴት?
ቆላ ላይ አንድ እንግዳ ሲመጣ “እንደምን ዋላችሁ” ወይ “አመሻችሁ” ካለ፣ አባወራው አይወጣም። እዛው ሆኖ ግቡ ነው የሚለው፡፡ በሳሆ ኦሮባ ይባላል፡፡ ግቡ ማለት ነው፡፡ እኔ ያገኘሁት መረጃ እንደሚያሳየው፤ ታቦት ይዘው የመጡት ጉንዳጉንዳ እንደደረሱ ሰዎች ያገኙና “እዚህ ቤት” ሲሉ ኢሮባ አሏቸው፡፡ ለቀሩት ተከታዮቻቸው በፃፉት ደብዳቤ፤ “እኛን የተቀበሉን ህዝቦች አግኝተናል፤ ህዝቡም ኢሮብ ይባላል” ብለው ፃፉ የሚል ነው፡፡
ኢሕአሠን  እንዴት ነው የኢሮብ ህዝብ  ኦሮባ ያለው?
አንደኛው ከኢህአፓ መስራቾች አንዱ የሆነው ተስፋዬ ደበሳይ የአካባቢው ተወላጅ ነው፡፡ ተስፋዬን    ጨምሮ ብዙ የአካባቢው ተወላጆች አውሮፓ በተለይ ቫቲካን ነበሩ፡፡ ምክንያቱም ከኢሮብ ጐሳዎች አንዱ የሆነው ቡክናይተአረ የሚባለው  የካቶሊክ እምነት ተከታይ ስለሆነ የትምህርት እድል ይሰጣቸው ነበር።
የኢሕአሠን ትግል  ጐጃም  ለማድረግ ታስቦ ነበር፡፡ ነገር ግን ሱዳን በዚያን ወቅት አስተማማኝ ሀይል አልነበረም፡፡ ባሌም ታስቦ ነበር፡፡ ሶማሌያም አስተማማኝ አልነበረም፡፡ ሌላው ደግሞ አወሮፓ የነበሩ የኢሮብ ተወላጆች የተወሰኑት የኢህአፓ አባል ስለነበሩ ከህዝቡ ተቀባይነት ማግኘት ከባድ አይሆንም በሚል ይመስላል፡፡ ቦታው ለቀይ ባህርም ቅርብ ነው፡፡ አዱሊስ ቅርብ ነው፡፡ አሲምባ ተራራ ጫፍ ላይ የየመን ዋና ከተማ ትታያለች፡፡ ስንቅ ለማጓጓዝም አመቺነቱን በማየት፣ ጂኦግራፊውም ስትራቴጂካዊ ቦታ ላይ ስለሆነ ነው፡፡  
ህዝቡስ?
የኢሮብ ህዝብ አንድን ነገር ቶሎ አይቀበልም። ከተቀበለ ደግሞ ጽኑ ነው፡፡ እንዲቀበል ደግሞ የራሱን ሰው ይፈልጋል፡፡
የኢሮብ ህዝብ ዛሬ ላይ የኢሕአሠን ሠራዊት እንዴት ያስታውሰዋል?
የልጆቻችን ወንድሞች እና ጓደኞች እንደሆናችሁ ሰምተናል፡፡ እንደ ልጆቻችን እንቀበላችኋለን፡፡ ግን ከድታችሁን ለጠላት አጋልጣችሁን እንዳትሄዱ” ነበር ያሏቸው፡፡ አሁን ህዝቡን እንዴት ያዩታል ላልሽኝ፤ ኢሕአሠን በደንብ ነበር የተቀበሉት፡፡ ወደኋላ ግን በኔ እይታ  በጣም አዝነውበት ነበር፡፡
ለምን
ካዘኑባቸው ምክንያቶችም አንዱ፣ አንጃ ተብለው በተገደሉ ሰዎች ምክንያት ነው፡፡ አንጃ በሚል ተይዘው የነበሩትን ሰዎች አስመልክቶ የኢሮብ ህዝብ ሽማግሌ ልኳል፡፡ እነዚህን ልጆች እንዳትገድሉ ብሏል፡፡ በወቅቱ የፖሊት ቢሮ አባል የነበረው ዘርዑ ክህሸንም አይገደሉም ብሎ ቃል ገብቶላቸው ነበር። ግን ተገደሉ፡፡ ጨካኞች ናቸው አሉ፡፡ ሌላው ባልጠበቁት ሁኔታ ሲሸነፍ አዩት፡፡ ሀይል ነበረው ፣መሳሪያ ነበረው፡፡ ሠራዊት ነበረው ግን ተሸነፈ። አላማውን ሲያነሱ ግን እስከአሁን “ያ ሠራዊት” ይላሉ፡፡ ከሁሉም የኢትዮጵያ ክፍል የተውጣጣ በመሆኑ ልዩ ነው፡፡ ስሜቱ የተዘበራረቀ ነው፡፡
መጽሐፍህ ላይ “ገበሬ የሀይል ሚዛን ወደሄደበት ፊቱን ያዞራል” ብለሀል፡፡ የኢሮብ ህዝብን ከዚህ አባባል ጋር በማገናኘት  አስረዳኝ?…
ይህ በሁሉም ገበሬ የሚታይ ነው፡፡  ኢሮብ አንደኛ ገበሬ አልነበረም፡፡ አርብቶ አደር ነበር። የጐሳ ትስስር ነው የነበረው፡፡ የኔ ወገን የሆነው ለኔ ሲል ለኔ ያደላል፤ ወደኋላ ግን ትክክለኛ የገበሬ ጥቅመኝነት አይቼበታለሁ፡፡ ሠራዊቱ አካባቢውን ለቆ ከወጣ በኋላ እኔ እዚያ ቆይቻለሁ፡፡ አጋፍጠው ሊሰጡኝ ባይፈልጉም ስጋት ግን አለባቸው፡፡ ብሄድላቸው ደስታቸው ነው፡፡ የገዛ ዘመዶቼ ከዚያ አካባቢ ብጠፋላቸው ደስ ይላቸው እንደነበር አውቃለሁ፡፡
ስለአባትህ ንገረኝ…
አባቴ በወቅቱ ዘመናዊ ትምህርት ከወሰዱት ውስጥ ነው፡፡
አባትህ ሽፍታ ነበሩ ይባላል ዕውነት ነው?
አዎን
የአካባቢው ዳኛም፣ አስተዳዳሪም፣ ፖሊስም ሁሉንም ነው፡፡ አባቴ በአካባቢው ተወዳጅ ነበር፡፡ በለቅሶም ሆነ በሠርግ ስሙ ይነሳል፡፡ ተስፋዬ ደበሳይ በእረፍት ጊዜው የሚውለው ከአባቴ ጋር ነበር፡፡ ብዙ የህግ እውቀት ከአባቴ እንዳገኘ ነግሮኛል፡፡ የትግል ሜዳ ላይ ከብርሃነመስቀል ጋር ሲያስተዋውቀኝ፣ አባቱ በህይወት ቢኖሩ ከኛ ጋር ይሠለፉ ነበር ብሎታል፡፡
በድንበር ኮሚሽኑ ውሳኔ መሠረት ለኤርትራ እንዲሰጡ የተወሰኑ የኢሮብ አካባቢዎችን አንተ እንዴት ነው የምታያቸው?
አባቴ በሀላፊነት ላይ በነበረ ጊዜ ትልቁ ራስምታቱ እሱ ነበር፡፡ በተለይ አይጋ የውጥረት ቦታ ነው፡፡ በደንብ ሳይካለል የቀረ ቦታ ነው፡፡
ኢሮብ በትግራይ በኩልና ኢሮብ በኤርትራ መሠረታቸው አንድ ነው?
አዎ አንድ ነው፡፡ የሶስት ወንድማማቾች ልጆች ናቸው፣ ኢሮቦች፡፡ ሀሳበላ፣ ቡክናይተአረ  እና ጋዳ ይባላሉ፡፡ ጋዳ በሰሜን በኩል ነው ወደ ኤርትራ የሚጠጋው፤ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ ናቸው። የነሱ ግንኙነት ከኤርትራ ጋር ነው - በጣም ተቀላቅለዋል፡፡ ቋንቋው ትግርኛ እና ሳሆ ነው፡፡ መሀል ያለው ቡክናይታ ካቶሊክ ነው፤ ከነሱ  ወደ ሰሜን ስትሄጂ መነኩሲቶ የሚባል የኤርትራ ቦታ አ። እነሱም ካቶሊኮች ናቸው፡፡ የጋብቻ ግንኙነታቸው ከካቶሊኮቹ ጋር ነው፡፡ ብቻውን የሚቀረው ሃሰበላ ነው፤ ከአጋመ ጋር ይዋሰናል፤ ኦርቶዶክስ ነው፡፡ በዘር የተሳሰሩ ናቸው፤ በኮሚሽኑ ውሳኔ መሠረት፤ ብክናይተአረና ጋዳ ለኤርትራ  ተወስነው ሀሰበላ ነው ለኢትዮጵያ የቀረው፡፡ ቦታዎቹን ሳውቃቸው በኢትዮጵያ ግዛት ስር የነበሩ ናቸው፡፡
የታሪክ ተማሪ ነህ ድንበር ማስመር ላይ ስህተት እንዳለ ነግረኸኛል፡፡ እሰቲ ስለእሱ አብራልኝ …  
ከአድዋ ጦርነት በኋላ በማካለል ላይ የተደረገ ስህተት ነው፡፡ መረብ፣ በላሳ፣ ሙና የሚለው ነው። በካርታው ላይና መሬት ወርዶ ያለው ላይ ማለት ነው፡፡ በጣሊያን ጊዜ ራሱ ቦታው የአርበኞች ቦታ ነበር፡፡ ከኤርትራም ሆነ ከትግራይ በኩል ጣሊያንን የተዋጉ አርበኞች የተሸሸጉት ኢሮብ ነው፡፡ ኢሮብ ኢትዮጵያዊ ነው፡፡
መጽሐፉን ለማዘጋጀት ያነሳሳህ ምንድንነው?
መጽሐፉን ለመፃፍ ካሰብኩ ቆይቻለሁ፡፡ ግን የጽሑፍ ችሎታ የለኝም፡፡ ብዙ መፃሕፍቶች እየወጡ ነው፤ አንብቤያለሁ፡፡ አንድ ሳይነኩዋት የሚያልፉዋት ቦታ አለ፤ ሁሌም ይከነክነኛል፡፡ ይህ ድርጅት በአንድ ወቅት በጣም ገንኖ የወጣ፣ ተቀባይነት ያገኘ ነበር፡፡ የተቀጨው ግን በአጭሩ ነው፡፡  
ለውድቀቱ መፍጠን አስተዋጽኦ ያደረጉት ምንድን ናቸው? ውስጣዊ ችግሩ ወይስ ውጫዊው? የሚለውን ለማሳየት በክፍፍሉ ላይ አተኮርኩ፡፡ የተወሰኑ ዶክመንቶች፣ ግለሰቦችና የራሴን ተመክሮ አካትቼ አስቀመጥኩ፡፡ የቀረውን ሌላው ሊሞላው ይችላል ብዬ ነው፡፡
መጽሐፉ ከዚህ በፊት በሌሎች መፃሕፍቶች ወይም ሰነዶች ላይ ያሉ መረጃዎችን ነው የገለበጠው የሚል አስተያየት ይሰነዘራል፡፡
አዎ ትክክል ነው፡፡ የማውቃቸውም ያነበብኳቸውም  የማምንባቸውም ስለሆኑ ነው የተጠቀምኩባቸው፡፡
ከኢሕአሠ ሸፍተህ ነበር፡፡ ከደርግም ሸፍተሃል ይሄ ነገር እንዴት ነው?
አዎ ሸፈትኩ ድርጅትህን ከድተህ መሳሪያ ይዘህ መጥፋት ከባድ ወንጀል ነበር፡፡ እኔ እርምጃ አልተወሰደብኝም፡፡ የሸፈትኩት እስር ቤት አያለሁ ለሠራዊቱ የነበረኝ ግምትና ስሄድ ያገኘሁት  በጣም የተለያየ ስለነበረ ነው፡፡ መጽሐፌ ላይ የአሊቴናን ካርታ ያስገባሁት ያለምክንያት አይደለም፡፡
አሊቴና በጣም ስትራቴጂክ ናት፣ ሁለት በር አላት፡፡ ያንን ጥሶ የህወሓት ሠራዊት ሲገባ ኢሕአሠ እንዳለቀለት ገባኝ፡፡ ከዛ ደግሞ ማጋለጥ ውስጥ ተገባ፡፡ ተጠርቼ ነበር አልሄድኩም፡፡ ሠራዊት ሆኖ መቀጠል አይችልም፡፡ ለውጥ ያስፈልገዋል ብዬ አሰብኩ፡፡ እና መጀመር አለብኝ ብዬ ከጓደኛዬ ጋር ተመካከርኩና እንገንጠል አልን፡፡ ለውጥ እናድርግ ወይ ለውጥ አድርገው ይቀላቅሉን አልን፡፡ ጓደኛዬ የትጥቅ እና ስንቅ ሃላፊ ነበረ፡፡ የተቀበሩ መሳሪያዎች ያሉበትን ቦታ ያውቃል፤ ችግር እንደማይገጥመን ደምደመን፤ ሄድን፡፡ ከዚያ ብዙ ሽማግሌዎች ተላኩብን በኋላ ግን ሃሳቤን የሚያስቀይር ሚስጥር አገኘንና ለመመለስ ወሰንኩ ፡፡ ህወሓት ለጦርነት እንደተዘጋጀ ሰማን፡፡ በዛ ሰአት ጥሎ መሄድ ስላልታየኝ ተመለስኩና ያገኘሁትን መረጃ ሰጠሁ፡፡ በዚህ ምክንያት ይመስለኛል ያልታሠርኩት፡፡
የመጨረሻዎቹ የኢሕአሠ ቀኖች  በትግል ሜዳ ላይ ምን ይመስሉ ነበር?
በጣም አስቀያሚ፡፡  ጦርነት እየገፋ መጣና ኢሮብ አካባቢ ደረሰ፡፡ ለመውጣት በኤርትራ በኩል  መንገድ መከፈት ነበረበት፡፡  ጀብሀ፤ አይሀ በምትባል ቦታ ብቻ ነው ማለፍ የሚቻለው ብሎ ቢስማማም  አንድ ጋንታ በሌላ መንገድ ለመግባት ስትሞክር ትያዛለች፡፡ ስንደርስ ትጥቅ አስፈትተዋቸው አናስገባም ይሉናል፡፡ ከዚያ መሳሪያቸውን ተረክበን ከሚሊሺያዎቹ ጋር አንድ ኮረብታ ላይ ቁጭ ብለን ሸመዛና በሚባል ሜዳማ ቦታ ላይ የኛ ሠራዊት ይተማል (ለቅሶ)፡፡
አንተ እዚያ ቀረህ?
ለአንድ አመት ኢሮብ ቆየሁ፡፡ መቆየቴ ጥሩ ነበር። ደርግ አዲስ አበባ ውስጥ ያደርግ የነበረውን ሰቆቃ ለማምለጥ የሚመጡትን እየተቀበልን እናሳልፍ ነበር፡፡ ማህተም ያለው ሰነድ እጃችን ላይ ነበር፡፡
በኋላስ አንተ ምን ሆንክ?
እዚ መቆየት ከባድ ነበር፡፡ የቀረሁት ከገበሬዎች ጋር ነው፡፡ ቀድሞ ያነሳነው የገበሬ ባህርይ እየገፋ ሲመጣ፣ መቆየት የሚፈልጉት እዚያው ቀሩ፡፡ ህወሓትን የሚቀላቀሉ፡፡ ተቀላቀሉ እኔ አዲስ አበባ ት/ቤት ገባሁ፡፡
ቀጣዮቹ አመታትስ?
አስተማሪ  ነው የምትሆነው፣ ተብዬ ጐጃም ተመደብኩ፡፡ ጐጃም ሳለሁ እስከ 1983 ድረስ ስለነበሩት ጓዶች እንዴት እንደነበሩ አውቃለሁ፡፡
እንዴት ነበሩ?
ቻግኒ  እና ዳንግላ እነሱን ለመፈለግ ሄጃለሁ።  ግን እኔ የማውቀው የኢሕአሠን አይነት ሆኖ አላየሁትም፡፡ በሽፍትነት ደረጃ እንደነበሩ ነው የሰማሁት፡፡
ከዚያስ
ወደ መጨረሻ አካባቢ (ከሁለት አመት በኋላ) የኢህድን ወሬ እሠማ ስለነበር “እነሱ ይሆኑ እንዴ እውነተኞቹ ኢህአፓዎች?” በሚል ማፈላለግ ጀመርኩ፡፡ 79 እና 80 አካባቢ ከማን ጋር እንደሆነ በትክክል ባላውቅም (ኢህዴን፣ ህወሓት፣ ሻዕቢያ) አዲስ አበባ ውስጥ በትክክል የፖለቲካ እንቅስቃሴ ላይ ነበርኩ፡፡
ደርግ እንዲወድቅ እንቅስቃሴ ከሚያደርጉት ከማናቸውም ጋር በህቡዕ እሠራ ነበር፡፡ ደርግ ሲወድቅ ቀጥታ ያገኘኋቸው ኢህዴኖችን ነው፡፡ ፎረም 84 የሚመራው በነሱ ነበር፡፡  ከአመራሮቹ አንዱ ሆንኩ፡፡ እራሴን እንደ ኢህዴን ቆጠርኩ፡፡ የክልል 14 ፀሐፊ ነበርኩ፡፡
ኢህዴንን ለምን መረጥክ?
አንደኛ ከኢሕአሠ የማውቃቸው ስለነበሩ፡፡ ሲሆን ቀጥሎ ህብረ - ብሔራዊ ስለነበር ነው፡፡
ለምን ከሃላፊነትህ ለቀቅህ?
ኢህዴን ወደ ብአዴን ሲቀየር ወደ የብሔር ድርጅት የሚል ነገር  ሲመጣ ስላልተስማማኝ ነው፡፡ ሌላው ደግሞ ያነበብኳቸው መፃሕፍቶች በዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ላይ ያሳደሩብኝ ተጽእኖዎች ሊያስቀጥለኝ ስላልቻለ! አልቻለም፡፡ በ1989 ዓ.ም በፈቃዴ ለቀቅኩ፡፡

ሌሊት አጎበር ስላለ ትንኟ የንክሻ ሰዓቷን ወደ ቀን አዘዋውራለች
(አቶ ገዛኢ አምባዬ፤ የባዝኦፍ አምራች ኩባንያ መስራችና ዳይሬክተር)
በሙያቸው አካውንታንት የሆኑት አቶ ገዛኢ አምባዬ፤ በ1964 ዓ.ም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ውስጥ ተቀጥረው በሙያቸው መስራት እንደጀመሩ ይናገራሉ፡፡ በውሃና ፍሳሽ፣ በኢትዮጵያ ውሃ ስራዎች ድርጅትና በብረታ ብረት ኮርፖሬሽን በከፍተኛ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ያገለገሉ ሲሆን በ1981 ዓ.ም ወደ ኬኒያ በማምራት የኢምፖርት ኤክስፖርት ስራ ላይ ከመሰማራታቸውም በተጨማሪ ባርና ሬስቶራንት በመክፈት ለረጅም አመታት መስራታቸውን ገልፀዋል፡፡ አንበሳ ባንክና ኢንሹራንስን ከመሰረቱት ሰዎች አንዱ የሆኑት አቶ ገዛኢ፤ ከ10 ዓመት በፊት ከውጭ ተመልሰው በአገራቸው መኖር ሲጀምሩ፣ ወባ በአገሪቱ ላይ እያደረሰ ያለውን ጥፋት መመልከታቸውን ያስታውሳሉ፡፡ ወባ በአፍሪካ እያደረሰ ያለውን ጥፋት በተመለከተ ጥናት ሰርተውም ለአሜሪካው ግዙፍ ኩባንያ IFF በመስጠት ተቀባይነት በማግኘታቸው፣ በለገጣፎ አካባቢ “ባዝኦፍ” የተሰኘ የወባ ትንኝ ማባረሪያ መድኀኒት በማምረት ላይ ይገኛሉ፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፤ በመድኀኒቱና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ከአቶ ገዛኢ አምባዬ ጋር ተከታዩን ቃለ-ምልልስ አድርጋለች፡፡


“ባዝኦፍ” የተባለውን የወባ ማባረሪያ ቅባት እንዴት ሊያመርቱ ተነሱ?
እኔ በ1981 ጀምሮ ወደ ጎረቤት አገር ኬኒያ ሄጄ ነበር፡፡ ከኢትዮጵያ ወይንና አምቦ ውሃ እየወሰድኩ ለኬኒያ፣ ለሩዋንዳ ለኡጋንዳና ብሩንዲ አከፋፍል ነበር። ኬኒያም ውስጥ “ግሪን” የተባለ ባርና ሬስቶራንት ነበረኝ፡፡ እዚያ እየሰራሁ እያለ IFF (International Flavors and Fragrance) የተባለ የአሜሪካኖች ትልቅ ኩባንያ ነበር፡፡ ይህ ኩባንያ ማጣፈጫዎችንና መዓዛማ ዘይቶችን ያመርታል፡፡ እነ ኮካ ኮላ፣ ለነ ፔፕሲና ሌሎችም ትልልቅ ኩባንዎች የሚያከፋፍል ነው፡፡ ከ10 ዓመት በፊት የዚህ ትልቅ ኩባንያ ወኪል ሆኜ ነው ወደ ኢትዮጵያ የመጣሁት። ሁኔታዎችን በማመቻቸት ስመላለስና እዚህ ቢሮ ስከፍት ግን 15 ዓመት ሆኖኛል፡፡ እናም እነሱ ጋር  በነበረኝ ግንኙነት ቸኮሌት፣ ከረሜላና መሰል ጣፋጮችን የሚያመርት ኩባንያ ለራሴ መክፈት አስቤ ስንቀሳቀስ፣ በወቅቱ ወባ በተለይ በአማራና በሌሎች ክልሎች የአገሪቱ ፈተና ሆኖ አየሁት፡፡ መነሻዬ ይሄ ነው፡፡
ከዚያ ምን አደረጉ?
በወቅቱ ወባ ህዝቡን እየፈጀች መሆኑን ከተለያዩ ሚዲያዎች አንብቤ ነው በጣም ያዘንኩት፡፡ ምን ይሻላል ምንስ ቢደረግ ህዝቡን መታደግ ይቻላል በሚል ራሴ በራሴ ትግል ውስጥ ገባሁ፡፡ አንድ ጥናት አጠናሁና “IFF” ላልኩሽ ኩባንያ አቀረብኩኝ፡፡ አፍሪካ የኮስሞቲክስም የሽቶም ችግር እንደሌለባት፣ በአሁኑ ጊዜ ሕዝቧ በወባ እያለቀ ስለመሆኑ፣ አምራች ኃይሉ በወባ ጥቃት እያለቀ እንደሆነ የሚያሳይ ነው ጥናቱ። ጥናቱን ተቀብለው ካዩት በኋላ “ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ፍሎሪዳ” አገሩም ወባማ ስለሆነ ቀድመው አጥንተው ነበር፡፡ ጥናቱን ያጠኑበትን ዋና መነሻ ሲነግሩኝም፤ “The Boston Tea Revolution” በነበረ ጊዜ የአሜሪካ ሰራዊት ያለቀው በወባ ነው፡፡ ያኔ ግን ወባ ነው ተብሎ በሽታው ተለይቶ አልታወቀም ነበር። የሆነ ሆኖ ጥናቱን ተቀበሉት፡፡ ከዚያ “ኢሴንሻል ኦይሉን” እንዲልኩልኝ አደረግሁኝ።
ኦይሉ ከተላከ በኋላ መጀመሪያ ጥናቱን የትኛው የአፍሪካ አገር አደረጉ?
መጀመሪያ ጥናቱ እንዲጠና የወሰንኩት ኬኒያ ነው፡፡ ምክንያቱም ኬኒያ ውስጥ “ኢሲፕ” የተባለ የዓለም ሳይንቲስቶች በሙሉ ስለ “ትሮፒካል ዲዚዝ” ጥናት የሚያደርጉበት ማዕከል ስላለ ነው። ከእነሱ ጋር ስምምነት በማድረግ፣ ከአሜሪካ የተላከው “ኢሴንሻል ኦይል” ከፔትሮሊየም ጄሊ (በተለምዶ ባዝሊን የምንለው) ጋር ተቀላቅሎ ቢሰራ በእርግጥ የወባ ትንኝን ያባርራል ወይ? የሚለውን እንዲያረጋግጡልኝ ነው ያደረግሁት። ብዙ ዶላር ካስከፈሉኝ በኋላ ጥናቱን ሰሩልኝ። ብዙ ዶላር የከፈልኩት ጥናቱ ሰፊ ስለሆነ ነው። አንደኛ የላብራቶሪ ሙከራ ያደርጋሉ፣ ሁለተኛ ወባ በተነሳ ጊዜ ገጠር ገብተው ካምፕ ሰርተው፣ ህዝብን አስተባብረው፣ ደም ምርመራ ያደርጋሉ። ምክንያቱም ጥናቱን የሚያካሂዱት በዓለም የጤና ድርጅት (WHO) መስፈርት መሰረት ስለሆነ ነው። ጥናቱ ወደ ሁለት ዓመት ገደማ ወስዶ፣ በመጨረሻ ምርምሩን አድርገን፣ሰ ቅባቱ “ባዝኦፍ” ከ 8 ሰዓት በላይ የወባ ትንኝ ያባርራል ሲሉ የምስክር ወረቀት ሰጥተውኛል፡፡ ይህ ከሆነ ወደ ስምንት ዓመት ገደማ ይሆነዋል፡፡
መድኀኒቱ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እውቅና አግኝቷል?
በሚገባ! እኔ ሰርተፍኬቱ ከተሰጠኝ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ሳመጣው፣ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ኃላፊዎች በጣም ተደስተው ነበር፡፡ እኔ ባዝኦፍን ወደ ኢትዮጵያ ባስገባሁበት ወቅት ሰዎች የሚጠቀሙት አጎበር በኬሚካል ያልተነከረ ስለነበር ብዙም ውጤታማ አልነበረም፡፡ ስለዚህ ጤና ጥበቃችሁ “ይህ መድኀኒት አማራጭ ስለሚሆነን አገር ውስጥ ያሉ የምርምር ተቋማት ለምን ጥናት አያደርጉበትም? ፓስተር ወይም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቢመራመሩበት ጥሩ ነው” አሉኝ፡፡
ምርምሩ ተካሄደ?
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲዎች እንዲያጠኑት እንደገና ስምምነት አደረግን፡፡ “አክሊሉ ለማ የምርምር ማዕከል” የትሮፒካል ዲዚዝና የወባ ምርምር ማዕከል ነው፡፡ በዚህ መሰረት የላብራቶሪ ሙከራ ተደረገበት። ቆቃ አካባቢ ወባ ተነስቶ ስለነበር ዶክተሮቹ እዚያ ድረስ ሄደው ምርምርና ጥናት አድርገው፣ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ውጤቱ አመርቂ ነው በሚል ማረጋገጫ ሰጡኝ፡፡
ባዝ ኦፍ የሚመረትበት ፋብሪካ የት አካባቢ ይገኛል? በዓመት ምን ያህል ያመርታል?
ፋብሪካው ለገጣፎ ይገኛል፡፡ በጥሩ ሁኔታ እያመረትን ነው፡፡ አንደኛ ለፋርማሲዎች እናከፋፍላለን፤ ዋና የባዝኦፍ ተጠቃሚ ግን መከላከያ ሰራዊታችን ነው፡፡ ሰራዊቱ በፊት ከውጭ እያስመጣ ይጠቀም ነበር፡፡ እኛ ማምረት ከጀመርን በኋላ ከውጭ ማስገባታቸውን አቁመዋል፡፡ የተሻለ ጠቀሜታ አግኝተንበታል በማለት፣ በጀታቸው ውስጥ አስገብተው በየአመቱ ይወስዳሉ፡፡ ፌደራል ፖሊስም እንዲሁ እየወሰደ ነው፡፡ ሌሎች ተቋማትም መውሰድ ጀምረዋል፡፡ መንግስትም ይህንን በማየት ከወርልድ ባንክ ባገኘው ድጋፍ፣ በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በኩል ወደ 103 ሺህ ዶላር ገደማ ድጋፍ አድርጎልናል፡፡ ይህ እርዳታ የተሻለ ምርምርና ጥናት ለማካሄድ እንዲሁም ኤክስፖርት ለማድረግ እንቅስቃሴ የሚውል ነው፡፡
እስካሁን ወደ ውጭ መላክ አልጀመራችሁም?
ጀምረናል፤ ወደ ናይጄሪያ፣ ኡጋንዳ፣ ሱዳን ሱማሌላንድና ሞቃድሾ ልከናል፡፡ሰ በአሁኑ ሰዓት ሌሎች የወባ ችግር ያለባቸው አገሮችም ምርቱን ለመውሰድ ጥያቄ እያቀረቡ ነው፡፡
“ኢሴንሻል ኦይሉ” ከአሜሪካ IFF እያስመጣችሁ ነው የምትጠቀሙት? ሌላስ ማቴሪያል ምንድን ነው የሚያስፈልጋችሁ?
ቤዙ እንዳልኩሽ ባዝሊን ነው፡፡ ባዝሊን ከውጭ ይመጣል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ከአንዳንድ ሳይንቲስቶች ጋር “ኢሴንሻል ኦይሉ”ን እዚሁ ለማምረት በምክክር ላይ ነን፡፡ አገራችን በርካታ ለመድኀኒትነት የሚያገለግሉ ሁሉም አይነት ዕፅዋት ስላላት ምቹ ናት፡፡ መድኀኒቱ ከእፅዋት ነው የሚሰራው፡፡ እነሱ የሰሩት ፎርሙላ ስላለን “ኢሴንሻል ኦይሉ”ን እዚሁ ለማምረት ዶክተሮቹን አጋር አድርገን ፋብሪካውን በማቋቋም ላይ ነን፡፡
ከረሜላና ቸኮሌት የሚያመርት ኩባንያም እንዳለዎት ሰምቻለሁ፡፡ ከባዝኦፍ ማምረቻው ጋር አንድ ላይ ነው ያሉት?
ቅርብ ለቅርብ ነበሩ፡፡ አሁን መለያየት ስላለባቸው እየለየናቸው ነው፡፡ በሁለቱም ኩባንያዎች ውስጥ አንድ የእንግሊዝ ኩባንያ በሽርክና ለመስራት መጥቷል፡፡ አሁን ከፍተኛ እንቅስቃሴ አለ፡፡ “ባዝኦፍን” ስናመርት በዚያውም ሽቶና መሰል መዓዛ ያላቸውን ምርቶችም እዚህ ለማምረት እያስመዘገብን ነው፡፡ አላማችን ከውጭ የሚመጡ የቼኮሌት፣ ከረሜላ፣ የወባ መድኅኒቶችና ሌሎችንም አስቀርተን አገር ውስጥ እንዲመረቱ ማድረግ ነው። እዚህ አምርተንና እሴት ጨምረን ኤክስፖርት ማድረግ ከኢኮኖሚም አኳያ አገሪቱን ይጠቅማታል፡፡
ባዝኦፍ ከስምንት ሰዓት በላይ የወባ ትንኝን እንደሚያባርር ተገልጿል፡፡ የመከላከል አቅሙ በመቶኛ ሲሰላ ምን ያህል ነው?
የዓለም የጤና ድርጅት አንድ መድኀኒት ከ60 እስከ 68 በመቶ መከላከል ከቻለ ውጤታማ ነው ይላል፡፡ ባዝኦፍ ግን 90 በመቶ አመርቂ ነው፡፡ ከስምንት ሰዓት በላይ እስከ 11 ሰዓት ድረስ ይሰራል። እየቆየ ኃይሉ እየደከመ እየደከመ ስለሚሄድ ግን በአማካኝ ከስምንት ሰዓት በላይ ይሰራል፤ በሚል እውቅና ተሰጥቶታል፡፡
አሁን አሁን በወባማ አካባቢ የሚገኙ ነዋሪዎች በኬሚካል የተነከረ አጎበር እየተጠቀሙ ነው፡፡ የባዝኦፍ ተጨማሪ ነው ወይስ እንዴት ነው?
አሁን ጥሩ ጥያቄ አመጣሽ፡፡ ሁሉም የተነከረ አጎበር ስለሚጠቀም፣ ሌሊት ትንኟ የሰዎችን ደም ማግኘት አልቻለችም፡፡ ስለዚህ የምትናከስበትን ሰዓት ቀይራለች፡፡ ለመኖርና እድሜዋን ለማራዘም ንክሻዋን ወደ ቀን አዘዋውራለች፡፡ የአሜሪካ ሳይንቲስቶችም ጥናት የሚያሳየው ይህንኑ ነው። ይህን በተመለከተ ሳይንቲስቶች በ6300 ሰዎች ላይ ጥናት ሲያደርጉ ለመጀመሪያው ቡድን አጎበር ብቻ ሰጡ፣ ለሁለተኛው ደግሞ መከላከያ ቅባቱንም አጎበሩንም ሰጡ፡፡ ውጤቱ ምን ሆነ መሰለሽ? አጎበሩንም መከላከያ ቅባቱንም የተጠቀሙ ሙሉ በሙሉ ከወባ በሽታ ነፃ ሲሆኑ አጎበሩን ብቻ ከተጠቀሙት መካከልብዙዎቹ በቀን እየተነከሱ የወባ ተጠቂ መሆናቸውን ያሳያል፡፡
አሁን ባዝኦፍን ተፈላጊ ያደረገው አንዱም ጉዳይ የወባ ትንኟ የንክሻ ሰዓቷን ወደ ቀን ማዛወሯ ነው፡፡ ቀን ቀን አጎበር ተሸክመሽ አትንቀሳቀሺም፤ ስለዚህ የግድ በወባማ አካባቢና በወባ ነሻ ወቅት ቀንም ባዝኦፍ መቀባት ግድ ነው፡፡
አሁን ክረምት እንደመሆኑ እስከ ህዳር ባለው ጊዜ ወባ በከፍተኛ ሁኔታ የሚቀሰቀስበት ወቅት ነው፡፡ በአሁኑ ሰዓት የምርታችሁ ተፈላጊነት ምን ይመስላል?
እንደነገርኩሽ በቋሚነት የሚወስዱ እንደ መከላከያ ሰራዊት ያሉ ተቋማት አሉ፡፡ ምርቱ በጣም ተፈላጊ ነው፡፡ አሁን ሁለቱም ፋብሪካዎች በ6500 ካ.ሜ ላይ ነው ያሉት፡፡ 15 ሺህ ካሬ ለባዝኦፍ ማስፋፊያ ጠይቀን እየጠበቅን ነው፡፡ ጉዳዩ አንገብጋቢና መንግስትን የሚያግዝ በመሆኑ ማስፋፊያው ሲፈቀድ፣ በስፋትና በጥራት ለማምረት ዝግጁ ሆነናል፡፡ አጋሮቻችን ብሩን ልከዋል፤ የገበያውን አዋጭነት፣ ላለፉት ዓመታት ሁለቱም ኩባንያዎቻችን የነበራቸውን ጉዳዮች መሰል ታሪኮች አስጠንተው ካመኑበት በኋላ ነው ገንዘቡን የላኩት፡፡
በመጨረሻ የሚሉኝ ካለ?
ያው ባዝኦፍ በዚህ መልኩ እየተመረተ ነው፡፡ ለወባ በሽታ በአማራጭነት በመቅረቡ መንግስትም ደስተኛ ነው፡፡ኤክስፖርት እየተደረገ የውጭ ምንዛሬም እያመጣ ነው፡፡ መከላከያው ትልቅ ፋይዳ ያለው ስለሆነ፣ ወደፊት የወባን በሽታ ሙሉ ለሙሉ ለመቅረፍ በምንችልበት አቅም ላይ እንድንደርስ በምርምሩም ሆነ በሁሉም ረገድ በርትተን እንሰራለን፡፡

የ95 ዓመት አባት አርበኛ ናቸው፡፡ ያልዘመቱበት የጦር አውድማ የለም። በዚህ ዕድሜያቸው ከ70 ዓመት በፊት የተደረጉ ጦርነቶችን ከእነ ዓመተምህረታቸው ያስታውሳሉ፡፡
ባለፈው ሳምንት በኢኮኖሚና ንግድ አምድ ላይ ቃለምልልስ የተደረገላቸው “የባላገሩ አስጐብኚ ድርጅት” ባለቤት፣ አባት አርበኞችን ወደ ታላቁ ህዳሴ ግድብ ወስዶ የማስጐብኘት ሃሳብ የመጣላቸው በእኚህ አዛውንት ጥያቄ መሆኑን ገልፀውልናል፡፡
የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛዋ ናፍቆት ዮሴፍ ከእኚህ የዕድሜ ባለፀጋ አባት ጋር ማራኪና አዝናኝ ቃለምልልስ አድርጋለች። እነሆ:-



ስምዎትን ያስተዋውቁኝ አባት…
ሃምሳ አለቃ ደምሴ ፀጋዬ እባላለሁ፡፡ ትውልድና እድገቴ ወሎና ጎንደር ነው፡፡ በአንድ ጎን ደባት ገብርኤል ነኝ፡፡ በሌላ ጎኔ ደግሞ ወሎ ውስጥ የጁ እና ላስታ ነው እድገቴ፡፡ ጠቅለል ስታደርጊው ዘር ሃረጌ ከወሎ እና ከጎንደር ይመዘዛል ማለት ነው፡፡
እስቲ ስለልጅነት ያጫውቱኝ?
እንዴ! የአስተዳደጌ ሁኔታማ ምን ይወራል። የተወለድኩት በ1911 ዓ.ም ታህሳስ 3 ቀን ነው፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምረሽ እድሜዬን ማስላት ትችያለሽ፡፡ ጠላታችን ጣሊያን መጥቶ አባቶቻችን ሲዘምቱ የ18 ዓመት አፍላ ጎረምሳ ነበርኩኝ፤ በ1928 ዓ.ም ማለት ነው፡፡ አባቴ በውጊያው ቆስሎ ነበር ከዘመቻው የተመለሰው፡፡
የት ቦታ አባትዎ እንደቆሰሉ አልነገሩዎትም?
ነግሮኛል! ማይጨው ላይ ነው የተመታው፡፡ የዘመተው ከደጃዝማች አድማሱ ብሩ ጋር መሆኑንም አጫውቶኛል፡፡ ደጃዝማቹ እዚያው በውጊያው ሲሞቱ፣ አባቴ ግን ቆስሎ መጣ፡፡ የማስታውሰው እኔ የ19 ዓመት ወጣት ስለነበርኩ፣ አባቴ ውጊያ ሲሄድ የእርሻውን ስራ እኔ እሸፍን ነበር፡፡ አባቴ ከውጊያ የመጣ ቀንም ሞፈርና ቀንበሬን አነባብሬ እርሻ ወርጄ ማሽላ ስዘራ ነበር የዋልኩት፡፡ እነሱ ሲመጡ ጥይቱ እንደ ማሽላ ቆሎ… ጣ  ጣ   ጣ  ጣ ይላል፡፡ ምንድን ነው ነገሩ ብዬ ስጠይቅ፤ “አባትሽ መጣ” አሉኝ፤ አንቺ ነበር የሚሉኝ፡፡
ለምንድነው አንቺ የሚልዎት?
ምክንያቱ በግልፅ አይገባኝም፡፡ ስገምት ግን ስራመድ ከእግሬ እንደ ሴት ፈጠን እላለሁ፡፡ ለዚያ ይመስለኛል፡፡
ከዚያስ?
ከዚያማ ማሽላውን ዘርቼ ጨርሼ፣ ሞፈርና ቀንበሩን እዚያው ትቼ፣ መዋጆውን ይዤ በሬዎቼን እየነዳሁ ነበር፤ ወደ ቤት ለመግባት፡፡ በኋላ አባትሽ መጣ ሲሉኝ፣ መዋጆውንም በሬውንም ትቼ በሩጫ ወደ ቤት መጣሁ፤ ስደርስ አባቴን አገኘሁት፡፡
በጣም ተጎድተው ነበር?
በጣም እንጂ! ሚያዚያ ወር ላይ ነበር የመጣው፡፡ ከዚያ ግንቦት፣ ሰኔ፣ ሐምሌ እና ነሐሴን አስታመምነው፡፡ ከተሻለው በኋላ አሁንም የጠላት ጦር እያየለ ሲመጣ፣ “አገሬ ተወርራ አልቀመጥም” ብሎ ታላቅ ወንድሙን፣ የመጀመሪያ ልጁን (ታላቄን)፣ እኔን አስከትሎ ከአንድ ቤት አራት ሆነን ዘመትን!! ታች ጋይንት አርብ ገበያ ላይ በተደረገው ጦርነት ህዝብ አለቀ፡፡ ከላይ በአውሮፕላን እንደበደባለን፣ በመሬት ይህ ነው ብዬ በቁጥር የማልጠቅሰው እስከ አፍንጫው የታጠቀ የጣሊያን ወታደር አለ፡፡ ምን አለፋሽ… ምድር ቃጤ ሆነች፡፡ እኔ ነጭ ቃታ ቤልጂግ ይዣለሁ፣ አባቴ ረጅም ለበን የሚባል መሳሪያ ይዟል። አባቴ ጥይት ሲያልቅበት አፈሙዙን ድንጋጥ ሰብሮ መሃል ገባ፡፡ ይህን ነጫጭባ ሁላ አንጀት አንጀቱን ዘክዝኮ ዘክዝኮ ከጣለ በኋላ፣ እሱም ወንድሙም፣ የመጀመሪያ ልጁም እዚያው አለቁ (ሲያወሩኝ ስሜታቸው እየጋለ ነው)
እርስዎም በምን ተዓምር ተረፉ ታዲያ?
እኔ አብሬ መሞት ፈልጌ ነበር፡፡ ሰዎች “አንተ እንኳን ትረፍ” በሚል ወደ ኋላ ጎተቱኝና ከእነሱ ጋር አፈገፈግን፡፡ ከዚያ ተርፌ አምስቱን አመት ጣሊያን ከአገራችን እስኪወጣ ተዋግቼ ይኸው እዚህ ደረስኩኝ፡፡
ኮሪያ ዘምተዋል እንዴ?
እንዴታ! ኮሪያና የኤርትራ ዘመቻ አንድ ቀን ነው የዘመትነው፡፡ በወቅቱ ኤርትራ በፌዴሬሽን ነበር የምትተዳደረው፡፡
ራስ ገዝ ነበረች አይደል?
አዎ! ከዚያ በኋላ ከእኛ ጋር ተቀላቀለች፡፡ ይህ እንግዲህ በ1973 ነው፡፡ ከዚያ በኋላ “ወርቋ ኤርትራ ከእናቷ ኢትዮጵያ ጋር በሰላም ተቀላቀለች” ተባለ። ወታደሮቹና ኤርትራዊያኑ አምስት ቀን ሙሉ አብረውን ሲበሉና ሲጠጡ ቆይተው ጃንሆይ ወደ አዲስ አበባ ሲመለሱ፣ እኛ ወደ ምፅዋ ልንወርድ ስንል መንገድ ላይ ጠብቀው አይጠምዱንም መሰለሽ! አስቢው… ሁለት ሻምበል ጦር ወደፊት ሄዷል፡፡ የመሳሪያ ግምጃ ቤቱንና ጠቅላይ ሰፈሩን ሰዎች ከሁለት ቆርጠው ተኩስ ከፈቱብን፡፡
ከኢትዮጵያ ጋር ተቀላቀለች ከተባለ በኋላ ነው?
ታዲያስ! አብረውን በልተው ጠጥተው… የሻዕቢያ ነገር ተመልከቺ! ከዚያ እኔም በሁለት ጥይት ተመትቼ ወደቅኩኝ፡፡
ተጐድተው ነበር?
ታፋዬን ነው የተመታሁት፡፡ ከዚያ በኋላ የሆነውን የተደረገውን አላውቅም፤ ራሴን ስቼ ነበር፡፡ በኋላ ስነቃ አብረውኝ የነበሩት በመትረየስ ጭንቅላታቸውን ተመትተው እኔ ላይ ወድቀዋል። ሬሳ ሲነሳ እኔ ከእነ ነፍሴ ተገኘሁ፡፡ የሚያውቁኝ ሰዎች “አሞራዋ በነፍስ አለች” ብለው እኔን ጨምሮ ሰባት ቁስለኛ በሄሊኮፕተር ተጭነን፣ አዲስ አበባ ምኒልክ ሆስፒታል ገባን፡፡ ሁለቱ ጓዶቻችን ሆስፒታል እንደደረሱ ሞቱ፡፡ አምስታችን ተረፍን፡፡
ሆስፒታል ምን ያህል ጊዜ ለህክምና ቆያችሁ?
አንድ አመት ከዘጠኝ ወር ያህል ሆስፒታል ቆይተናል፡፡ ከዚያ በየቦታው አንድ አንድ ጋሻ መሬት ተሰጠን፡፡ ለእኔ ጉራጌ ዞን ጨወና ወረዳ፣ አመያ የተባለ ቦታ ደረሰኝ፡፡ ያንን መሬት ስቃበጥበት ኖርኩኝ፡፡
የትዳር ህይወትዎ ምን ይመስላል? ልጆችስ ወልደዋል?
ልጆች ወልደዋል ወይ ነው ያልሽው? ያውም በቁና ሙሉ ነዋ! ትዳር ይዤ መውለድ የጀመርኩት በ1937 ዓ.ም ነው፡፡ 19 ልጆች ወልጃለሁ፡፡
ሁሉም በህይወት አሉ?
19 ልጆች ወልጄ አሳድጌ ነበር፡፡ አምስቱ ሞቱብኝ፡፡ አሁን 14 ልጆች፣ 18 የልጅ ልጆች፣ ብዙ የልጅ ልጅ ልጆች አሉኝ፡፡ ከቅድመ አያትም እስከ ምንጅላትነት ደርሻለሁ፡፡
እንደ እርስዎ አርበኛ የሆነ የሆነ ልጅ አለዎት?
አይይይ…….የለኝም፡፡ ወደፊት አርበኛ ይሆኑ እንደሆነ እንጂ እስካሁን የለኝም፡፡
ሶማሊያ ኢትዮጵያን ስትወርር ዘምተዋል?
እንዴ ምን ነካሽ… በደንብ እንጂ! በኦጋዴን ዘጠነኛ ማካናይዝድ ጦር ውስጥ ነበርኩኝ፡፡ ይህ ሁሉ አልፎ መጨረሻ አካባቢ ጡረታ ልወጣ ስል አዲስ አበባ መጣሁ፡፡ በመከላከያ ሚኒስቴር በደሞዝና መዝገብ ቤት ተቀጥሬ ስሰራ ቆይቻለሁ፡፡ በሂሳብ አስተዳደርና በመዝገብ አያያዝ ባለሙያ ሆኜ ነው የሰራሁት፡፡
ተምረዋል ማለት ነው?
እስከ ስድስተኛ ክፍል ተምሬ ሚኒስትሪ ወስጃለሁ፡፡ በየነ መርዕድ ት/ቤት ነው የተማርኩት። እዚሁ አዲስ አበባ ውስጥ ከዚያ በኋላ በርካታ መስሪያ ቤቶች ሰርቻለሁ… ይገርምሻል!
አሁን በጥንታዊት ኢትዮጵያ አርበኞች ማህበር ውስጥ ተሳትፎም ምንድነው?
በፊት በሌላ ኮሚቴ ውስጥ እሰራ ነበር፡፡ አሁን የመቃብር ኮሚቴ ነኝ፡፡
በጡረታ ደሞዝ ነው የሚተዳደሩት?
ጡረታም አለኝ ግን ብዙ ልጆቼ ከውጭ በየአቅጣጫው ብር ይልካሉ፤ የብር ችግር የለብኝም። ከባለቤቴ ጋር ዘና ብዬ ተደስቼ ነው የምኖረው፡፡
እድሜዎ 95 ዓመት እንደሆነ ነግረውኛል፡፡ ግን ሙሉ ጥርስ፣ ሙሉ ጤና አለዎት፡፡ አመጋገብዎ እንዴት ነው?
የተገኘውን እበላለሁ፤ መጠጥ ድሮም አሁንም በአፌ አይዞርም፤ ውሃ ብቻ ነው የምጠጣው፡፡ ጥሬ ስጋ ድሮ እበላ ነበር፤ አሁን ለጤና ጥሩ አይደለም ስለሚባል ትቻለሁ፡፡
የታላቁን የህዳሴ ግድብ ለመጎብኘት ከፍተኛ ጉጉት እንዳለዎት ሰምቻለሁ…?
ወይ ልጄ ሁሉም በየጊዜው በየትውልዱ ታሪክ ይሰራል፡፡ በእኛ ትውልድ ያለ በቂ መሳሪያ በጦርና በጎራዴ ዘመናዊ መሳሪያ የታጠቀውን ጣሊያንን አሳፍረናል፡፡ አክሱምን፣ ላሊበላን፣ ጎንደርን ገንብተው ያለፉ ትውልዶች አሉ፡፡ ይሄ ትውልድ ደግሞ ለም አፈር አዝሎ ሲጓዝ፣ ሌላ አገር ሲያለማ የነበረውን አባይን ሲገድብ እድሜ ሰጥቶኝ ከደረስኩ እንዴት አልጓጓ? ግድቡን ጠዋት ጎብኝቼ ማታ ብሞት ደስታውን አልችለውም፡፡
ከዚህ በኋላ ስንት ዓመት መኖር ይፈልጋሉ?
እየውልሽማ… እግዚያብሔር ለአብርሃም 500 ዓመት ሲሰጠው፣ ለዚህች አጭር እድሜ ብዬ ቤት አልሰራም ብሎ በድንኳን ኖረ፡፡ እኔ አሁን ወደ 95 ዓመት እየሄድኩ ነው፡፡ ለእኔስ 150 ዓመት ቢሰጠኝ ምን ይለዋል? (ረጅም …..ሳቅ)

ሰሞኑን በእጅጉ ማርኮኝ የተመለከትኩት “Trance” የተሰኘ ፊልም ላይ፣ ዋና ገፀ-ባህሪው ሳይመን ሳያውቀው የገባበት የቁማር ጨዋታ (gambling) የለየለት ሱሰኛ ያደርገውና የዕዳ አረንቋ ውስጥ ይዘፈቃል፡፡ ከቁማር ሱሰኝነቱ ለመላቀቅ የዘየደው መላ ወደ ቴራፒስት ዘንድ መሄድ ነው፡፡ በሂፕኖቴራፒ ከቁማርተኝነቱ ለመፈወስ፡፡ ሂፕኖሲስ የህክምናው (ቴራፒው) ሂደት ሲሆን ባለሙያው ወይም ባለሙያዋ ሂፕኖቲስት ይባላሉ፡፡ ቴራፒውን የወሰደው ሰው ደግሞ “ሂፕኖታይዝድ” ሆኗል ይባላል፡፡
በነገራችሁ ላይ ሂፕኖሲስ ታካሚውን በሰመመን ስሜት ውስጥ በማስገባት፣ ሃሳቡንና ትኩረቱን በአንድ የሆነ ጉዳይ ላይ እንዲያነጣጥር፣ የተወሰኑ ቃላትን ወይም ዓ.ነገሮችን በመደጋገም አሊያም የአዕምሮ ምስል በመፍጠር… የሚሰጥ ህክምና (ቴራፒ) ነው፡፡ ሂፕኖሲስ ያልተፈለገ ባህሪን (ድርጊትን) ለማስወገድ ወይም ለመቆ›ጣጠር በቁጥጥር ሥር ለማዋል ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል፡፡ ከሲጋራ ሱሰኝነት ለመላቀቅ፣ ከእንቅልፍ እጦት (Insomnia) ለመገላገል፣ ከመጠን በላይ የመብላት ፍላጐትን ለማስወገድ …ወዘተ ሊያግዝ እንደሚችል ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡
ወደ ፊልሙ ልመልሳችሁ፡፡ በቁማር ሱሰኝነት ኑሮው የተቃወሰው ሳይመን፤ ኤልዛቤት ላምብ የተባለች ቴራፒስት ዘንድ በመሄድ ችግሩን ተናግሮ ቴራፒውን ይጀምራል፡፡ የቁማር ሱሰኝነቱ ስር የሰደደ በመሆኑ ብዙ ጊዜ እንደሚወስድበት ይገለጽለትና ህክምናውን ይቀጥላል፡፡ በዚህ ሂደትም ከኤልዛቤት ጋር እየተቀራረበ ይመጣል፡፡ የጦፈ የፍቅር ግንኙነትም ይጀምራል፡፡
ቴራፒስቷ ከደንበኞቿ ጋር እንዲህ ያለ ግንኙነት ውስጥ መግባት እንደሌለባት ታውቃለች፡፡ ግን አንዴ ሆነ፡፡ እናም “የፈሰሰ ውሃ አይታፈስም” ብላ ገፋችበት። ከጥቂት ጊዜ በኋላ የሳይመን ፍቅር ወደ ጥርጣሬና ቅናት እየተቀየረ መጣ፡፡ የት ገባሽ፣ የት ወጣሽ ማለት አበዛ፡፡ ፍቅረኛውን የሚያጣት፣ እየመሰለው ይጨነቅ ጀመር፡፡ ቅናቱ እየተባባሰ እንደ እብደት አደረገው፡፡ መላ ህይወቱን እሷ ላይ ጣለ፡፡ ከእሷ ከተለየ የሚሞት ሁሉ መሰለው፡፡ በዚህ የተነሳም ያፈቀራትን ያህል ጠላት፡፡ አንድ ቀን ሬስቶራንት ውስጥ ተቀምጠው ሳለ “ወንድ አየሽ” ብሎ በጥፊ አጠናገራት፡፡ ይሄን ጊዜ ነው ኤልዛቤት ከዚህ ጨዋታ መውጣት እንዳለባት የወሰነችው፡፡ ግን በየት በኩል? ሳይመን አለቅም ብሎ ሙጭጭ አለባት፡፡ ረዥም የይቅርታ ደብዳቤ ፃፈላት። እየደወለ ነዘነዛት፡፡ እያለቀሰ ተማፀናት፡፡ ኤልዛቤት ግን የዚህ መጨረሻ ምን እንደሚሆን አላጣችውም፡፡ ነገርዬው በዚህ ከቀጠለ የማታ ማታ እንደሚገድላት ቅንጣት አልተጠራጠረችም፡፡
ጉዳዩን ለፖሊስ ብታመለክትም ነገሬ ሳይሏት ቀሩ፡፡ ጠበቆች፤ ስሟን ቀይራ አገር ጥላ እንድትወጣ መከሯት፡፡ እሷ ደግሞ ይሄን ለማድረግ ፈቃደኛ አልነበረችም፡፡ ሁለት ጊዜ ተጎጂ መሆንን አልፈቀደችም፡፡ እናም ጉዳዩን በቁጥጥሯ ሥር ለማዋል መረጠች፡፡
ሳይመንን ከቁማር ሱሰኝነት ለመገላገል ወይም ቁማር ለማስረሳት ስትጠቀምበት የቆየችውን ቴራፒ ለዚህ ዓላማ አዋለችው፡፡ “መርሳት የምትፈልገው ቁማሩን ሳይሆን እኔን ነው” በማለት እርሷን እንዲረሳት ተከታታይ ቴራፒ ሰጠችው፡፡ ቀስ በቀስም እሷን እየረሳ መጣ፡፡ እሷን ብቻ ሳይሆን የፍቅር ግንኙነታቸውንም ጭምር ረሳው፡፡ ሁሉ ነገር ከአዕምሮ ትውስታው እልም ብሎ ጠፋ፡፡ የቁማር ሱሱን ሊረሳ ሄዶ ፍቅሩን ረስቶ ተመለሰ፡፡
አንዳንድ በፀብና በቅናት የተሞሉ አደገኛ የፍቅር ግንኙነቶች እንዲህ “ዲሊት” እየተደረጉ ከትውስታ ማህደር ቢጠፉ ብዙ ጥንዶችን ከከፋ ችግር ሊታደጉ ይችላሉ፡፡ በእርግጥ ወደ ፊልሙ መጨረሻ አካባቢ የሳይመን ትውስታ ይመለሳል፡፡ “ለምን እንድረሳ አደረግሽኝ?” ብሎ የቀድሞ ፍቅረኛውን ይጠይቃታል፡፡ ኤልዛቤትም “ትውስታህ በሰረገላ ቁልፍ ተከረቸመ እንጂ ከጥቅም ውጭ አልሆነም” ስትል ትመልስለታለች፡፡
ኤልዛቤት በሂፕኖቴራፒ ክህሎቷ ራሷን ከሞት፣ የቀድሞ ፍቅረኛዋን ደግሞ ከዕድሜ ልክ እስርና ፀፀት ለማትረፍ ችላለች፡፡ ይሄን ፊልም ተመልክቼ ስጨርስ ወደ አዕምሮዬ የመጣው፣ በሃይልና በዱላ የታጀበው የአገራችን የፍቅር ግንኙነት ነው፡፡ በበዛ ቅናት እየተሰቃየ ሚስቱን ለሚደበድብ ባል፤ ይሄ ቴራፒ ግሩም ይመስለኛል፡፡ ፍቅረኛውን ከእነ ትዝታዋ በማስረሳት አዲስ ህይወት እንዲመራ ለማድረግ ይረዳል፡፡
በሂፕኖቴራፒ ሰዎች እንዲረሱ ብቻ ሳይሆን የረሱትንም እንዲያስታውሱ (ትውስታቸው እንዲመለስ) ማድረግ ይቻላል፡፡ ሳይመን ጭንቅላቱ ላይ ጉዳት ከደረሰበት በኋላ ያስቀመጠበት የጠፋበትን የመኪና ቁልፍ በሂፕኖሲስ እንዲያስታውስ አድርጋዋለች - ቴራፒስቷ ኤልዛቤት፡፡ ዓምና ለእይታ የበቃውን “Trance” የተሰኘ ፊልም ፈልጋችሁ ተመልከቱት፡፡ ድንቅ ፊልም ነው!! (በነገራችሁ ላይ እኔ የተረኩት ከሙሉ ፊልሙ እጅግ ጥቂቱን ብቻ ነው)