Administrator

Administrator

ፎከር - 50 ለመጨረሻ ጊዜ የተመረተው ከ20 ዓመት በፊት ነው

   በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች፤ ከ50 ሰው በላይ እንዳያጓጉዙ የተጣለባቸው ገደብ ሊያሰራቸው እንዳልቻለ ጠቁመው ገደቡ እንዲነሳላቸው ጠየቁ፡፡  
የበረራ አገልግሎት ሰጪዎቹ፤ ከዚህ ቀደም የወንበር ገደቡን ጨምሮ የጋራዥ ቦታና ሌሎች በዘርፉ የሚታዩ ችግሮች ለስራቸው መሰናክል እንደሆኑባቸው ሲገልፁ ቆይተዋል፡፡
የናሽናል ኤርዌይስ ባለቤትና ስራ አስኪያጅ ካፒቴን አበራ ለሚ ለአዲስ አድማስ  እንደተናገሩት፤ በአሁኑ ወቅት ከ79 ሰው በታች የሚጭን አውሮፕላን ገበያ ላይ የለም፡፡ በተለምዶ ፎከር - 50 በሚል የሚጠሩትና 50 ሰዎችን የሚጭኑት አውሮፕላኖች ለመጨረሻ ጊዜ የተመረቱት ከ20 ዓመታት በፊት ነው፡፡
“79 ሰው የሚጭነውን አውሮፕላን ገዝቶ 50 ሰው መጫን ኪሳራ ነው” ያሉት ካፒቴኑ፤ የወንበር ገደቡ ሊያሰራን ስላልቻለ ሊነሳ የሚችልበት መንገድ ቢኖር የግል የአቬሽን ዘርፍን ወደ አንድ ደረጃ ያሳድገዋል ብለዋል፡፡
በቅርቡ ኢትዮጵያ የዓለም ምርጥ የቱሪዝም መዳረሻ ተብላ መመረጧን ያስታወሱት ካፒቴን አበራ፤ በወንበር ገደቡ ምክንያት ወደ ሃገሪቱ በብዛት እየጐረፉ ያሉትን ቱሪስቶች ለማስተናገድ እንዳልቻሉ ተናግረዋል፡፡ ገደቡ እንዲነሳ በተደጋጋሚ ጥያቄ ማቅረባቸውን አስታውሰውም፣ ይነሳል እየተባለ ሶስት ዓመታት ያለ ውጤት ማለፉን ገልፀዋል፡፡
ከወንበር ገደቡ በተጨማሪም በቦታ ችግር የተነሳ፣ የሰው ሃይሉ እያለ አውሮፕላን የሚያሰሩት ደቡብ አፍሪካ ድረስ በመሄድ መሆኑን ጠቁመው፤ ይሄም ነዳጅን ጨምሮ ለተለያዩ ወጪዎች እየዳረጋቸው እንደሆነ ካፒቴኑ ገልፀዋል፡፡
በአቬሽን ዘርፍ ለረዥም ዓመታት ያገለገሉት አቶ ስንታየሁ በቀለ በበኩላቸው፤ በአሁኑ ወቅት በየትኛውም አገር የወንበር ገደብ እንደሌለ ገልፀው፣ የገደቡ መነሳት ለአገሪቱ ኢኮኖሚ እድገት ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ እያደገች ያለች አገር በመሆኗ የኢኮኖሚ እድገቷን ተከትሎ የቱሪስት ፍሰቱም ስለሚጨምር ቱሪስት የማስተናገድ አቅሟን ልትጨምር እንደሚገባ አቶ ስንታየሁ ያስረዳሉ፡፡ ኢትዮጵያ በአቬሽን ኢንዱስትሪው መልካም ስም ከተቀዳጁ አገራት መካከል አንዷ በመሆኗ በዘርፉ የሚታዩ ችግሮችን ፈትቶ፣ የግሉን ዘርፍ በመደገፍ የአቬሽን ዘርፉን ማሳደግ እንደሚቻል ጠቁመዋል፡፡
የወንበር ገደብ መነሳቱ የተሻሉ አውሮፕላኖችን ለማስገባት እድል ስለሚፈጥር ቱሪስቶች ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት እንዲያገኙ ያስችላቸዋል ያሉት አቶ ስንታየሁ፤ ቱሪስቶቹ በትናንሽ /ቻርተር/  አውሮፕላኖች የሚጠየቁት ከፍተኛ ክፍያም እንደሚቀንስላቸው አብራርተዋል፡፡

• ስጋት ከተጋረጠባቸው 14 ሀገራት ውስጥ ተካታለች
• ሴኔጋል፣ ታንዛኒያ፣ ኡጋንዳ፣ሞዛምቢክ በዕዳ ተዘፍቀዋል

      የውጪ ብድር እዳ ኢኮኖሚያቸውን ሊፈታተን ይችላል የሚል ስጋት ከተጋረጠባቸው 14 የአለም
አገራት ኢትዮጵያ አንዷ መሆኗን ዘ ጋርዲያን የአለም ባንክን ሪፖርት ጠቅሶ ዘግቧል፡፡ በአሁን ወቅት ኢትዮጵያ ከፍተኛ የብድር እዳ እንዳለባት የጠቀሰው ሪፖርቱ፤ ከአጠቃላይ አገራዊ ምርቷ 45 በመቶ የሚሆነው ከብድር የተገኘ ገንዘብ እንደሆነ ጠቁሞ፤ በጥቂት ጊዜያት ውስጥ ይህ አኃዝ ወደ 65 በመቶ ሊያሻቅብ እንደሚችል ጠቁሟል፡፡ ከለጋሽ ተቋማትና ሃገራት የሚገኝ ብድር ለአጠቃላይ አገራዊ ምርት ያለው አስተዋጽኦ ከ30 በመቶ በላይ ከሆነ ሀገራት ወደ ከፍተኛ የእዳ ቀውስ እያመሩ መሆኑን እንደሚያመለክት የጠቆመው ሪፖርቱ፤ ኢትዮጵያም በዚህ የአደጋ ቀጠና በከፍተኛ ደረጃ ከገቡ 14 የአለም  ሀገሮች መካከል ተጠቅሣለች።  ከፍተኛ የውጭ እዳ ውስጥ ተዘፍቀዋል የተባሉት 14 ሀገራት ኢትዮጵያን ጨምሮ ቡታን፣ ኬፕ ቨርዲ፣ ዶሚኒካ፣ ጋና፣ ላኦስ፣ ሞሪታኒያ፣ ሞንጐሊያ፣ ሞዛምቢክ፣ ሣሞኣ፣ ሣኦቶሜ ፕሪንቼቤ፣ ሴኔጋል፣ ታንዛኒያ እና ኡጋንዳ ናቸው፡፡ በሌላ በኩል 24 የአለም ሀገሮች የውጭ እዳቸው በሚያሰጋ ደረጃ እየጨመረና ወደ አደጋው ቀጠናም እየተንደረደሩ ነው በሚል ተጠቅሰዋል፡፡
አንዳንድ በአስጊ ደረጃ እዳ ውስጥ ተዘፍቀዋል የተባሉ ሀገራት፣ የተበደሩትን ገንዘብ ለተገቢው
አላማ መጠቀም አለመቻላቸው ለቀውስ እንደዳረጋቸው በሪፖርቱ የተጠቆመ ሲሆን በዚህ ረገድ ጋና ምሣሌነት ተጠቅሳለች፡፡ ሌሎችም አዋጭ የሆነ የብድር አመላለስ ስርአት ባለመከተላቸው የችግሩ ሠለባ እየሆኑ እንደመጡ የጠቆመው ሪፖርቱ፤ እነዚህ ሀገራት ከዚህ እዳ የሚወጡበትን መንገድ ካላጤኑ ከፍተኛ ቀውስ ሊገጥማቸው ይችላል ብሏል፡፡ በአለም አቀፍ ደረጃ የግል ኩባንያዎችና መንግስታት አለም ባንክን ከመሳሰሉ አበዳሪ ተቋማት ከ2009 እ.ኤ.አ ጀምሮ በየአመቱ የሚበደሩት ገንዘብ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ ነው ተብሏል፡፡ በ2013 እ.ኤ.አ የአለም ሀገራት አጠቃላይ የብድር መጠን 11.3 ትሪሊዮን ዶላር ሲሆን በ2014 13.8 እንዲሁም በዘንድሮው አመት 14.7 ትሪሊዮን ዶላር መሆኑን ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡ 

    ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከግንቦቱ ምርጫ በኋላ አባሎቻቸውና ደጋፊዎቻቸው ላይ ግድያ፣ እስራትና እንግልት እየተፈፀመባቸው መሆኑን የገለፁ ሲሆን መድረክ 5 አባሎቹ እንደተገደሉበት ስታውቋል። ሰማያዊ ፓርቲም በአባላቱ ላይ እየተፈፀመ ነው ያለው ግድያ፣ እስርና እንግልት በአስቸኳይ እንዲቆም ሰሞኑን ጠይቋል፡፡ ድረክ በሰጠው በመግለጫ፤ በደቡብና በኦሮሚያ ክልሎች በአባላቱ ላይ የሚፈፀሙት እስራቶችና
ንግልቶች ተጠናክረው እንደቀጠሉ አመልክቷል፡፡ ከምርጫው በኋላ በትግራይ፣ በኦሮሚያ እና ቡብ ክልል ከተገደሉት 4 የመድረክ አባላት በተጨማሪ ሰኔ 27 ቀን በደቡብ ክልል በከፋ ዞን፣ ቢግንቦ ወረዳ፣ በኢዲዩ ካካ የምርጫ ክልል፣ በጎጀብ ምርጫ ጣቢያ የመድረክ ታዛቢ የነበሩት አቶ አስራት ኃይሌ ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች ግድያ እንደተፈፀመባቸው መድረኩ ለአዲስ አድማስ በላከው መግለጫ አመልክቷል፡፡
የሟቹ አስከሬን ከቀብር ቦታ ጋር በተያያዘም ከፍተኛ እንግልት አጋጥሞት እንደነበር የጠቀሰው መድረክ፤  እስከ ሐምሌ 1 ቆይቶ በህብረተሰቡ ትብብር የቀብር ስነ-ስርአቱ ሊፈፀም መቻሉን አስታውቋል፡፡ በተለያዩ የደቡብና የኦሮሚያ ዞኖችና ወረዳዎች በምርጫው የመድረክ ታዛቢ ወኪሎች የነበሩ፣ አባላት እና ደጋፊዎች ከፓርቲው ጎን በመቆማቸው ብቻ የተለያዩ ማህበራዊ አገልግሎቶች እንዳያገኙ ከመደረጉም በላይ ከፓርቲው አባልነት ራሳቸውን እንዲያገሉ ግፊት እየተደረገባቸው ነው ብሏል - መድረክ፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ሰማያዊ ፓርቲ፤ “የወለደውን የረሳ ብሶት የወለደው ስርአት! የዘመቻ እስርና ግድያ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡” በሚል ሰሞኑን በፅ/ቤቱ በሰጠው መግለጫ፤ በግንቦቱ ምርጫ ማግስት በምርጫው በንቃት ይሳተፉ የነበሩ ዜጎች እየታደኑ እየታሰሩ ነው ብሏል፡፡ ፓርቲው፤ ዜጎችን በፖለቲካ አመለከታቸው ሳቢያ ከስራ ማፈናቀል፣ ማሰር፣ ማሸማቀቅና ማንገላታት እንዲቆም አበክሮ ጠይቋል።
“በሰላማዊ መንገድ የሚታገሉ የሰማያዊ፣ የመኢአድ፣ የቀድሞ አንድነት፣ የመድረኩና ሌሎችም የፖለቲካ ፓርቲ አባላት ኢላማ ተደርገው እየተሳደዱና በጅምላ እየታሰሩ እንዲሁም በአሰቃቂ ሁኔታ እየተገደሉ ይገኛሉ” ብሏል - ፓርቲው በመግለጫው፡፡ ከምርጫው ማግስት ጀምሮ በተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ላይ እየደረሰ ነው ያለው ግድያ፣ እስርና እንግልትም በአስቸኳይ እንዲቆም ሰማያዊ ፓርቲ ጠይቋል፡፡  

    አትሌት ሃይሌ ገብረ ስላሴ በኬንያ ሰላምን ለማስፈን ታስቦ በተዘጋጀውና በአጠቃላይ 800 ኪሎ ሜትሮችን በሚሸፍነው የሰላም ጉዞ የተሰኘ የታዋቂ አትሌቶች የእግር ጉዞ ላይ እንደሚሳተፍ ዘ ጋርዲያን ረቡዕ ዘገበ፡፡“የዜጎች መገደልና ከመኖሪያ ቤታቸው መፈናቀል በሁላችንም ልብ ውስጥ ጥልቅ ሃዘን የሚፈጥር ነገር ነው” ሲል ባለፈው ሳምንት ለጉዳዩ የሚሰጠውን ትኩረት ያሳወቀው ሃይሌ፣ በኬንያ ሰላምን ለማስፈን ታስቦ በሚከናወነው የሰላም ጉዞ የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ እንደሚሳተፍ መግለጹንም ዘገባው ገልጧል፡፡ኬንያውያን ሰላምን ጠቀሜታ እንዲገነዘቡና በተለይም በአገሪቱ ሰሜናዊ አካባቢዎች የሚታየውን የጎሳ ግጭት ለመግታት የሚያስችል አገራዊ ንቅናቄ ለመፍጠር ታስቦ የተዘጋጀው ይህ የሰላም ጉዞ፣ በመጪው ነሃሴ ስድስት ቀን የሚጠናቀቅ ሲሆን ሃይሌም በእለቱ በሚደረገው የመጨረሻው ጉዞ እንደሚሳተፍ ይጠበቃል፡፡
የማራቶን የአለም ክብረወሰን ባለቤት የሆነውን አትሌት ፖል ቴርጋት ጨምሮ ታዋቂ ኬንያውያን
አትሌቶች የሚካፈሉበት ይህ የሰላም ጉዞ፣ በሰሜናዊቷ የኬንያ ከተማ ሎድዋር ባለፈው ረቡዕ የተጀመረ ሲሆን፣ ለ24 ተከታታይ ቀናት በየቀኑ 40 ኪሎ ሜትሮችን በመሸፈን በአጠቃላይ 836 ኪሎ ሜትሮችን ይሸፍናል ተብሏል፡፡አትሌቶቹ በጉዞው ከ250 ሺህ ዶላር በላይ ገንዘብ በማሰባሰብ በአገሪቱ ተለያዩ አካባቢዎች ለሚከናወነው የሰላም ማስፈን ፕሮግራም ለመለገስ ማቀዳቸውንም ዘ ጋርዲያን አክሎ ገልጧል፡፡በህገወጥ የሰዎች ዝውውር የተጠረጠሩ 15 ኢትዮጵውያንን በኬንያ ታሰሩበኬንያ በህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ተግባር ላይ ተሰማርተው ሲንቀሳቀሱ ነበር ተብለው የተጠረጠሩ 15 ኢትዮጵውያን ባለፈው ረቡዕ ኢምቡ በተባለችው የኬንያ ከተማ በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋላቸውን ኢንቲቪ ኬንያ ዘገበ፡፡ ተጠርጣሪዎቹ በአገሪቱ መዲና ናይሮቢና በኢምቡ ከተማ አካባቢ በስውር በህገወጥ መንገድ ሰዎችን ሲያዘዋውሩ እንደነበር የጠቆመው ዘገባው፣ ፖሊስ የደረሰውን ጥቆማ መሰረት በማድረግ ባደረገባቸው ክትትል እንደዛቸው ገልጧል፡፡የከተማዋ ፖሊስ የአካባቢው ነዋሪዎች በሰጡት ጥቆማ ተጠርጣሪዎቹን በአንድ የበቆሎ እርሻ ውስጥ ተደብቀው እንዳሉ በቁጥጥር እንዳዋላቸውና ኢትዮጵውያን መሆናቸውን ከመግለጽ ውጭ፣ ስለተጠርጣሪዎቹ ማንነት መረጃ አልሰጠም፡፡

አንዳንድ ተረት አንዴ ተነግሮ የማይበቃውና ሰዎች ተገርተው እስኪበቃቸው የሚተረት ይሆናል፡፡ የሚከተለው ተረት የእዛ ዓይነት ነው፡፡
አንድ ቤት ውስጥ አባት፣ እናትና ህፃን ልጅ ይኖራሉ፡፡
አንድ ቀን ማታ ህፃኑ በምን እንደከፋው አይታወቅም ክፉኛ ያለቅሳል።
አባት - “አንተ ልጅ ምን ሆንኩ ብለህ ነው የምታለቅሰው?” ይሉታል።
ልጅ ለቅሶውን ይቀጥላል፡፡
እናት - “ዝም በል ማሙሽ፡፡ ዝም ካልክ የማረግልህን አታቅም” አሉት በማባባል ቃና፡፡
ልጅ አሁንም ማልቀሱን ይቀጥላል፡፡
አባት ተናደዱና፤
“እንግዲህ ዝም ካላልክ ለጅቡ ነው የምሰጥህ!”
ልጅ አሁንም ያለቅሳል፡፡
እናት ይጨመሩና፤
“ዋ! ይሄንን በር ከፍቼ እወረውርሃለሁ!”
ለካ ቤት ውስጥ ይሄ ሁሉ ሲሆን አያ ጅቦ ውጪ ቆሞ ያዳምጥ ኖሯል።
ከአሁን አሁን ህፃኑን ይጥሉልኛል ብሎ ይጠብቃል፡፡
ቀስ በቀስ ልጁ ፀጥ አለ፡፡ ባልና ሚስት ራታቸውን በሉ፡፡ ልጁን አስተኙና ተቃቅፈው ተኙ፡፡
ጅቡ ቢጠብቅ፣ ቢጠብቅ ምንም የሚጣልለት ልጅ አላገኘም፡፡
በመጨረሻም፤ ወደ በሩ ጠጋ ብሎ፤
“ኧረ የልጁን ነገር ምን ወሰናችሁ?” አለ፡፡
ባለቤቶቹ በራቸውን ቆላልፈው ለጥ ብለዋል፡፡ አያ ጅቦ ጠብቆ ጠብቆ ሊነጋበት ሲል ወደ ጫካው ሄደ፡፡
*   *   *
በማስፈራራት ልጅን ማስተኛት አይቻልም፡፡ ልጁ የተከፋበትን ምክንያት ማወቅ እንጂ ማባበልም ጥቅም አይኖረውም፡፡ በአንፃሩ እንደ አያ ጅቦ የቀቢፀ ተስፋ ምኞት መመኘትም ራስን የባሰ ረሀብ ውስጥ መክተት ነው!
በሀገራችን የተመኘናቸው የነፃነት፣ የዲሞክራሲና የፍትህ ጥያቄዎች በዱላም በካሮትም (Carrot and stick እንዲሉ) እየተሞከሩ ረዥም ዕድሜ አሳልፈዋል፡፡ ዛሬም የጠራ ጐዳና ላይ አልወጡም፡፡ የተኙ ተኝተዋል፡፡ የሚያለቅሱ ያለቅሳሉ፡፡ እንደ አያ ጅቦ ደጅ የቀሩም ይቀራሉ።
“…አሁን የት ይገኛል፣ ቢፈልጉ ዞሮ
መስማት ከማይፈልግ፣ የባሰ ደንቆሮ”
የሚለውን የከበደ ሚካኤልን ግጥም ልብ ማለት ለሀገራችን በጣም ጠቃሚ ነው፡፡
አሁንም የህዝብን ብሶት እናዳምጥ፡፡ ዛሬም ያልተመለሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ ቀና ልቦና ይስጠን፡፡ ሌላው ቀርቶ የዓለም መንግሥታት የሚያደርጉልንን ድጋፍ ለመቀበልም ቀና ልቡና ያስፈልጋል፡፡ መረጃዎችን፣ አገራችንን የሚመለከቱ ጉዳዮችን እናውቅ ዘንድ ቀና ልቡና አለንና በወጉ የማወቅ መብታችን ሊጠበቅ ይገባል፡፡
የደረስንበት እንዳይርቅ፣ ከእጃችን ያለው እንዳይፈለቀቅ ልዩ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብናል፡፡ ዛሬም መደማመጥ፣ መቻቻልና ዛሬም ረብ ያለው የፖለቲካ አቅጣጫና ተጨባጭ የሀገር ጉዳይን ማንሳት ይጠበቅብናል። የአሸነፈም፣ የተሸነፈም ሀገር ለምንላት የጋራ ቤት ምን ዓይነት አስተዋጽኦ እያደረግሁ ነው ብሎ መጠየቅ አለብን፡፡
ማንም ቢሆን ማን ምርቱ ይታወቃል፡፡ መንገዱም ይለያል፡፡ መሸሸግ የማይቻሉ በርካታ ነገሮች መኖራቸውን ህዝብ ያውቃል፡፡ ምክንያቱም ፍሬ ከዛፉ ርቆ አይወድም።

በድቅድቁ የቀለመውን ፅልመት ሃዘን በከረቸመው ከንፈሮችዋ መሃል በማትጐለጐል ነበልባል የነገን ጭላንጭል ተስፋ እያየች ትዕግስት የሚሉት ተሰጥኦ እንደዛር ተከምሮባት ከባዱን ችላ ስለምትወዳቸው መስዋዕትነት የከፈለች በእውነት ጐበዝ ጀግና ነች…”
ከላይ የቀረበው ቅንጭብ የተወሰደው ደራሲ ዝናሽ ኤልያስ (ዲና) ከጻፈችውና “መስዋዕት” የሚል ርዕስ ከሰጠችው ረዥም ልብወለድ ሲሆን መጽሐፉ ሰሞኑን ለገበያ ቀርቧል፡፡ የታሪኩ ጭብጥ በአንዲት ሴት የህይወት ውጣ ውረድ ዙሪያ የሚያጠነጥን ነው ተብሏል፡፡
“መስዋዕት” በእውነተኛ ታሪክ ላይ ተመስርቶ የተፃፈና በ214 ገፆች የተሰናዳ ሲሆን በ60 ብር ለሽያጭ እንደቀረበ ታውቋል፡፡

በዓለማየሁ ማሞ የተፃፈው “የህይወቴ ፈርጦች” የተሰኘ ግለታሪክ ከትላንት በስቲያ በኢትዮጵያ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን አዳራሽ ተመርቆ ለንባብ በቃ፡፡
ደራሲው በመግቢያው ላይ መጽሐፉን የፃፈበትን ምክንያት ሲያስረዳ፤ “ልጅነቴን፤ የትምህርት ቤት ውሎዬን ኋላም መርከበኛ፤ የጤና ባለሙያ፤ ጋዜጠኛና ደራሲ ሳለሁ ወይም እያለሁ የሆኑትን ግን አንኳር የመሰሉኝን ነው የመረጥኳቸው፡፡ ካሰብኩት ቆየሁ። በዚህም ላይ በጨዋታ መሃል የተነሱ ፈርጦችን ወዳጆቼ ስለወደዷቸው በወረቀት ላይ እንዳኖራቸው ገፋፍተውኛል፡፡” ብሏል፡፡
መጽሐፉ በዘጠኝ ምዕራፎች ተከፋፍሎ በ268 ገፆች የተቀነበበ ሲሆን ለአገር ውስጥ በ80ብር፣ ለውጭ በ20 ዶላር ለገበያ ቀርቧል፡፡ ፀሐፊው አለማየሁ ማሞ ነዋሪነቱ  በአሜሪካ ሜሪላንድ ሲሆን ባለፉት 17 ዓመታት ለጠቅላላ ዕውቀት የሚጠቅሙና ይልቁንም ለነፍስ ዕውቀት የሚበጁ በርካታ መፃህፍትን እንዳዘጋጀ ታውቋል፡፡

የዘንድሮ የትምህርት ጊዜ ማብቃትን ምክንያት በማድረግ “ኑ እናንብብ” የተሰኘ የተማሪዎች የክረምት የመፅሃፍ ንባብ፣ የባህልና የኪነ ጥበብ ፌስቲቫል ሐምሌ 11 እና 12 በአዲስ አበባ የስብሰባ ማዕከል እንደሚካሄድ ተገለፀ፡፡
በፌስቲቫሉ ላይ ከ30 በላይ በመፅሀፍ ህትመትና ሥርጭት ላይ የተሰማሩ ድርጅቶችና ከ20 በላይ የአንደኛ ደረጃ ት/ቤቶች ተሳታፊ ይሆናሉ ተብሏል፡፡ በሁለት ቀን ፌስቲቫሉ ላይ አንጋፋና ወጣት ደራስያን፣ አርቲስቶችና ምሁራን ለህፃናትና ወጣቶች መፃህፍት የሚያነቡ ሲሆን የህፃናት ቴአትሮች፣ መዝሙሮች፣ ፊልሞች፣ የፖፔት ትዕይንቶች እንዲሁም የባህልና ታሪክ የማስተዋወቂያ ዝግጅቶች እንደሚቀርቡ ታውቋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የሥነ - ፅሁፍ፣ የስዕልና የተሰጥኦ ውድድሮችም ተዘጋጅተዋል፡፡
የፌስቲቫሉ ዋና ዓላማ ተማሪዎች የንባብ ባህላቸውን እንዲያዳብሩ ግንዛቤ መፍጠር ሲሆን ከተለያዩ የሙያ መስኮች የተጋበዙ ስኬታማ እንግዶችም የህይወት ልምዳቸውንና የንባብ ጠቀሜታን በተመለከተ ተመክሮአቸውን ለተማሪዎች እንዲያጋሩ ማድረግ ነው ተብሏል፡፡
የተማሪዎች የክረምት ፌስቲቫሉን በኢቢኤስ ቴሌቪዥን “የኢትዮጲስ ጊዜ” የተሰኘ የህፃናት ፕሮግራም አዘጋጅ የሆነው አማራጭ ሚዲያና ኢንተርቴይመንት ከአዲስ ምዕራፍ ፕሮሞሽን ጋር በመተባበር እንዳዘጋጁት ለማወቅ ተችሏል፡፡

Saturday, 11 July 2015 12:38

የኪነጥበብ ጥግ

(ስለ ጃዝ ሙዚቃ)
ጃዝ ከሌሎች የሙዚቃ ዘውጎች የተዋሰውን ያህል፣ ለሌሎች የሙዚቃ ዘውጎችም አውሷል፡፡
ኸርቢ ሃንኮክ
የጃዝ ሙዚቃ ገብቶኛል፡፡ አሰራሩንም ተረድቼዋለሁ፡፡ ለዚያም ነው በሁሉም ነገር ላይ የምጠቀምበት፡፡
ቫን ሞሪሰን
 ለውጥ ሁልጊዜ በመከሰት  ላይ ያለ ነገር ነው። የጃዝ ሙዚቃ አንድ ድንቅ ነገር ያ ነው፡፡
ማይናርድ ፈርጉሰን
የጃዝ ሙዚቃ በተፈጥሮው የብዙ የተለያዩ ዓይነት ሙዚቃዎች ጥምረት ነው፡፡
ዴቪድ ሳንቦርን
በቀን ለ3 ሰዓት ያህል ጃዝ አዳምጣለሁ፡፡ ሉዊስ አርምስትሮንግን እወደዋለሁ፡፡
ፊሊፕ ሌቪን
የጃዝ ሙዚቃ እጅግ በርካታ ተዓምረኛ ዝነኞችን ፈጥሯል፡፡
ዊንቶን ማርሳሊስ
ጃዝ ለእኔ ህያው ሙዚቃ ነው፡፡ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ የሰዎችን ስሜት፣ ህልምና ተስፋ ሲገልፅ የኖረ ሙዚቃ ነው፡፡
ዴክስተር ጎርዶን
ጃዝ በጣም ዲሞክራሲያዊ የሙዚቃ ዓይነት ነው፡፡ ከጋራ ተመክሮ ይመነጫል። የየራሳችንን መሳሪያ ይዘን በጋራ ውበትን እንፈጥርበታለን፡፡
ማክስ ሮች
የጃዝ መንፈስ የግልፅነት መንፈስ ነው፡፡
ኸርቢ ሃንኮክ
ጃዝ በሶስት ወይም በአራት ዓመት የምትማረው አሊያም የሙዚቃ ተሰጥኦ ስላለህ ብቻ የምትጫወተው የሙዚቃ ሥልት አይደለም፡፡
ዊንቶን ማርሳሊስ
ጃዝ የመነጨው ከአኗኗር ዘይቤያችን ነው። የአገራችን የጥበብ ዓይነት በመሆኑም ማንነታችንን ለመረዳት ያግዘናል፡፡
ዊንቶን ማርሳሊስ
ጃዝ የግሌ ቋንቋ ነው ማለት እችላለሁ፡፡
ኤሚ ዊኒሃውስ
ጃዝ እንደ ወይን  ጠጅ ነው፡፡ አዲስ ሲሆን ባለሙያዎች፣ ሲቆይ ግን ሁሉም ይፈልገዋል።
ስቲቪ ላሲ

     ምንም የተፈጥሮ ሀብት የሌላቸው እንደ ዱባይ ያሉ አገሮች ሰው ሰራሽ የቱሪስት መስህብ እየሰሩ የጎብኚዎችን ልብ ሲያማልሉ ኢትዮጵያ በተፈጥሮ፣ በሰው ሰራሽና በህዝቦቿ ቱባ ባህል የበለፀገች ብትሆንም አገሪቷም ሆነች ህዝቦቿ ለዘመናት የዚህ ሀብት ተጠቃሚ አለመሆናቸው በርካታ ኢትየጵያውያን የሚቆጩበት ጉዳይ ሆኖ ቆይቷል፡፡
ሰሞኑን ግን እንደ እግር እሳት የሚለበልበውን ቁጭታቸውን የሚያበርድ ዜና ከወደ አውሮፓ ተሰምቷል፡፡ ይኸውም የአውሮፓ ቱሪዝምና ንግድ ም/ቤት ጠቅላላ ጉባኤ ኢትዮጵያን በ2015 የዓለም ምርጥ የቱሪዝም መዳረሻና ተመራጭ የባህላዊ ቱሪዝም መዳረሻ በማለት በሁለት ዘርፎች መምረጡን የባህልና ቱሪዝም ሚ/ር አስታውቋል፡፡
ሚ/ር መስሪያ ቤቱ ሰሞኑን በሰጠው መግለጫ፣ ኢትዮጵያ ከ31 የዓለም አገራት ጋር ተወዳድራ በቀዳሚነት መመረጧና እውቅና ማግኘቷ መንግሥት ለቱሪዝም ኢንዱስትሪ በተለይም ባህላዊ ቱሪዝምን ለማስፋፋት ያለውን ፍላጎትና ቁርጠኝነት ያመለክታል ተብሏል፡፡
መንግሥት በ2006 ዓ.ም የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅትን በአዋጅ አቋቁሞ የቱሪዝም መዳረሻዎችን እንዲያለማና የቱሪዝም ገበያውን እንዲመራ አድርጓል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በዚሁ ዓመት በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ የቱሪዝም ትራንስፎርሜሽን ም/ቤት አቋቁሞ ለዘርፉ ዕድገት እየሠራ መሆኑ ታውቋል፡፡ ጠቅላይ ሚ/ር ኃይለማርያም ደሳለኝ ለጪስ አልባው ኢንዱስትሪ መበልፀግ የሰጡት ትኩረት በአውሮፓ የቱሪዝምና ንግድ ም/ቤት ጠቅላላ ጉባኤ እውቅና ከማግኘቱም በላይ ከ28 አገራት መሪዎች ጋር ተወዳድረው ግንባር ቀደም የቱሪዝም መሪ በመባል እንዲመረጡ አድርጓቸዋል፡፡ ሽልማታቸውንም በመጪው ሳምንት አርብ እንደሚቀበሉ ተገልጿል፡፡
ኢትዮጵያ ቱሪዝምን ለድህነት ቅነሳ፣ ለስራ ፈጠራ፣ ለዜጎች መተዳደሪያ፣ ለሰላም ግንባታና ለዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትና ለአገር ገፅታ ግንባታ፣ … እንዲውል ማድረጓ እንዳስመረጣት መግለጫው አስታውቋል፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፡፡ በርካታ ብሔር/ብሔረሰቦችን አቅፋ መያዟ፣ የአገሪቷ መልክአምድራዊ አቀማመጥ በጣም ውብና አስደናቂ መሆን፣ በተራራማ አቀማመጧ የአፍሪካ ጣሪያ፣ በበርካታ ወንዞችና ድርጅቶቿ የአፍሪካ የውሃ ማማ መባሏ፣ ህዝቦቿ ለዘመናት ያካበቱት የየራሳቸው ድንቅ ባህልና የባህል መገለጫዎች፣ ባለፉት 10 ዓመታት የባህልና የተፈጥሮ መስህቦቿን ሀብት ለዓለም የቱሪስት ገበያ በማስተዋወቅ ከዘርፉ በሚገኝ ሀብት ህዝቦቿን ተጠቃሚ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት ማድረጓ፣ በ2015 ምርጥ የቱሪስት መዳረሻ ለመሆን እንዳበቃት ተነግሯል፡፡  
እስካሁን ድረስ ኢትዮጵያን በሰው ዘር መገኛነት የሚቀድማት የለም.፡፡ ከማንኛውም አገር የበለጠ በርካታ የቅድመ ታሪክና የሰው ዘር መገኛ መካነ ቅርስ ስላላት ጥናትና ምርምር ከሚደረግባቸው አገሮች አንዷና ተመራጭ ናት፡፡ ከ3 ሚሊዮን በላይ ዕድሜ ያስቆጠሩትን የሉሲ  ወይም ድንቅነሽና ሌሎች ቅሪተ አካላት፣ የጎና ጥንታዊ ድንጋይ መካነ ቅርስ ቦታዎች፣ የታችኛው ኦሞ ሸለቆ ታሪካዊ ግብረ ህንፃዎች፣ ሰማይ ጠቀስ ሀውልቶች፣ ዘመናት ያስቆጠሩ የሦስቱ ሃይማኖቶች የታሪክ አሻራዎች (ፍልፍል ቤተክርስቲያናት፣ ጥንታዊ መስጊዶችና ቤተ - እምነቶች) የሃይማኖት አባቶች የመቃብር ቤቶች፣ ለምርጫ ያበቋት ሀብቶቿ ናቸው፡፡
ከዚህም በተጨማሪ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶች ባለቤት መሆኗም ተገልጿል፡፡ በሚዳሰሱ ቅርሶች የአክሱም ሀውልቶች፣ የጎንደር አብያተ መንግስታት፣ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፣ የጢያ ትክል ድንጋይ፣ የሀረሩ ጀጎል ግንብ፣ የኮንሶ መልክአ ምድር፣ የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ፣ የታችኛው አዋሽና የታችኛው ኦሞ ሸለቆዎች በዓለም ቅርስነት የተመዘገቡ ሲሆን፣ ድሬ ሼክ ሁሴን ሆልቃ ሶፍ ኡመር፣ የጌዴኦ ጥምር ግብርና መልክአ ምድር፣ የመልካ ቁንጡሬ ቅድመ ታሪክ መካነ ቅርስና የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በዓለም ቅርስነት መዝገብ ውስጥ ለመካተት ተራ እየጠበቁ ነው፡፡
በማይዳሰሱ ቅርሶች ደግሞ የመስቀል በዓል በዓለም የውክልና መዝገብ (ዎርልድ ሬፕሬዘንታቲቭ ሊስት) የተመዘገበ ሲሆን የሲዳማ ዘመን መለወጫ ጨንበላላ በዓልና የገዳ ስርዓት በዓለም የውክልና መዝገብ እንዲካተቱ በቅርቡ ለዩኔስኮ እንደምትልክ ታውቋል፡፡
12 ጥንታዊ ጽሑፎችና መዛግብት በዓለም ሜሞሪ ዝርዝር ውስጥ የተመዘገቡ ሲሆን በቅርቡም ሁለት ጥንታዊ ጽሑፎች መላኳ ተገልጿል፡፡ በጥብቅ የተፈጥሮ አካባቢዎች ከሽካ፣ ከካፋና ያዩ በተጨማሪ የጣና ሐይቅ አካባቢም ባለፈው ወር ተመዝግቧል፡፡
ከሁሉም በላይ ኢትዮጵያን ምርጥና ተመራጭ የቱሪስት መዳረሻ ሆና እንድትመረጥ ያደረጋት ሰላምና ፀጥታ ማስከበሯና ለቱሪስቶች ደህንነት ምቹ መሆኗ እንደሆነ መግለጫው አመልክቷል፡፡