Administrator

Administrator

      በ2002 ዓ.ም “ጀነራሎቹ” በሚል ርዕስ ለንባብ የበቃው ታሪካዊ መፅሐፍ፤ አዳዲስ አስገራሚ፣ አሳዛኝና ቀልብ የሚስቡ መረጃዎችን በማካተት እንደገና የተዘጋጀ ሲሆን በነገው ዕለት ከቀኑ 7 ሰዓት ጀምሮ በግራንድ ዮርዳኖስ ሆቴል እንደሚመረቅ ደራሲው ሻምበል ኢዮብ እንዳለ ለአዲስ አድማስ አስታወቁ፡፡
በዚህ መፅሀፍ ውሰጥ ደም ያፋሰሰውና ያልተሳካው የግንቦት 8 ቀን 1981 ዓ.ም ወታደራዊ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ እንዲሁም ጀነራል ተፈሪ በንቲን ጨምሮ የ106 የደርግ አባላትን ጉርድ ፎቶግራፎችና በደርግ ውስጥ በነበረው የስልጣን ሽኩቻ በተለያየ ጊዜ የተገደሉ የጦር ጀነራሎች በርካታ ፎቶግራፎች እንደተካተተቱ ተጠቁሟል፡፡  
መፅሀፉ ቀደም ሲል በ302 ገጾች፣143 ፎቶግራፎችን አካትቶ የቀረበ ሲሆን የአሁኑ 351 ፎቶዎችን በማካተት በ496 ገጾች መዘጋጀቱንና ለ6ኛ ጊዜ መታተሙን ፀሐፊው ገልፀዋል፡፡ ከ2004 እስከ 2007 ባሉት ጊዜያት ከአገር ውስጥና ከውጭ አገር መፅሀፉን አንብበው አስተያየት ከላኩ ሰዎች የተገኙ ትክክለኛ መረጃዎች የተካተቱበት ነው የተባለው “ጀነራሎቹ”፤ በ165 ብር ለገበያ መቅረቡም ታውቋል። መጽሐፉ እስካሁን አምስት ጊዜ ታትሞ፣ 22ሺህ ቅጂዎች መሸጣቸውንም ጸሐፊው የላኩት መረጃ ያስረዳል፡፡    

     የልጅ ኢያሱ አባት፣ የእቴጌ መነን አያት፣ የደሴ ከተማ መስራችና የአድዋ ግንባር ቀደም ዘማች በነበሩት በወሎው ገዢ በንጉስ ሚካኤል ህይወትና ስራዎች ላይ የሚያጠነጥነው “ሚካኤል ንጉሰ ወሎ ወትግሬ” የተሰኘው መፅሀፍ ሰሞኑን ለንባብ በቅቷል፡፡ በምስጋና ታደሰ የተዘጋጀው ይኼው የታሪክ መፅሐፍ፤በ19ኛው መቶ ክ/ዘመን መጨረሻና በ20ኛው ክ/ዘመን የነበረውን የወሎ ክ/ሀገርንና የኢትዮጵያ ታሪክን ለማወቅ ለሚሹ በመረጃነት ያገለግላል ተብሏል፡፡  አዘጋጁ ምስጋናው ታደሰ፣ መጽሐፉን በሁለተኛ ዲግሪው የማሟያ ፅሁፍ ላይ ተመስርቶ ማሰናዳቱንና የታሪክ ጥናትና ምርምር ሊያሟሏቸው የሚገቡ መስፈርቶችን ለማሟላት ጥረት ያደረገበት እንደሆነም ተጠቁሟል፡፡ በ220 ገጾች የተቀነበበው መፅሀፉ፤ በ70 ብር ለገበያ መቅረቡም ታውቋል፡፡

      የ2008 ዓ.ም የ“ባላገሩ ምርጥ” የድምፅ ውድድር አሸናፊ አርቲስት ዳዊት ፅጌ፣ በውድድሩ ሂደት ያገዙትንና ከጎኑ የነበሩትን ድርጅቶችና ግለሰቦች የሚያመሰግንበት ልዩ የሙዚቃ ዝግጅት ዛሬ ምሽት ይካሄዳል፡፡ የዝግጅቱ አስተባባሪ እንደሻው የኪነ-ጥበብ ፕሮሞሽን በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ ፕሮግራሙ ዛሬ ምሽት በባታ የባህል ምግብ ቤትና መናፈሻ ፓርክ የሚከናወን ሲሆን ምሽቱ ድምፃዊው በውድድሩ ሂደት የረዱትን ድርጅቶችና ግለሰቦች የሚሸልምበትና ከቅላፄ ባንድ ጋር ልዩ የሙዚቃ ዝግጅት የሚያቀርብበት ይሆናል ተብሏል፡፡   
ድምፃዊ ዳዊት ፅጌ በምሽቱ አዲስ የሙዚቃ ስራውን ያቀርባል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ከእውቁ የፒያኖ ተጫዋች ግርማ ይፍራሸዋ፣ ከአርቲስት ግርማ ነጋሽ፣ ከአርቲስት ባህታ ገ/ህይወትና ከአርቲስት ግርማ በየነ ጋር በጋራ እንደሚያቀነቅንም እንደሻው የኪነ-ጥበብ ፕሮሞሽን አስታውቋል፡፡ ባታ የባህል ምግብ ቤትና መዝናኛ ፓርክ እና ኢምር አድቨርታይዚንግ የፕሮግራሙ አጋር እንደሆኑ ለማወቅ ተችሏል፡፡  

    በሊንኬጅ አርት ሪሶርስ ሴንተር አዘጋጅነት የሚካሄደው 10ኛው የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ፊልም ፌስቲቫል ከነገ በስቲያ በ11 ሰዓት በኦሮሚያ ባህል ማዕከል ይከፈታል፡፡ እስከ ህዳር 6 ቀን 2008 ዓ.ም ድረስ በሚቆየው የፊልም ፌስቲቫል ላይ ከ70 በላይ የአገር ውስጥና የውጭ አገር ፊልሞች ሳምንቱን ሙሉ እንደሚታዩ የተገለፀ ሲሆን ከአሜሪካ ኤምባሲ ጋር በመተባበር ከአሜሪካ በሚመጡ የፊልም ባለሙያዎች የአንድ ቀን ኮንፍረንስ ይካሄዳልም ተብሏል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ከእስራኤል በሚመጡ የፊልም ባለሙያዎች ለፊልም ሞያተኞች የግማሽ ቀን ስልጠና እንደሚሰጥ የተጠቆመ ሲሆን ህዳር 6 ቀን 2008 ዓ.ም ለአሸናፊ የፊልም ባለሙያዎች ሽልማት በማበርከት ፌስቲቫሉ እንደሚዘጋ አዘጋጁ ሊንኬጅ አርት ሪሶርስ ሴንተር በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡

Saturday, 07 November 2015 10:23

“The show must go on” ለእይታ በቃ

    በሪቻርድ ቪያ የተፃፈው “The show must go on” የተሰኘ ድራማ በአርቲስት ፈለቀ የማር ውሃ አበበ “ትርኢቱ ይቀጥላል” በሚል ተተርጉሞና ተዘጋጅቶ ትላንት ምሽት በሃርመኒ ሆቴል ለእይታ በቃ፡፡ የ30 ደቂቃ ርዝማኔ ያለው ይሄው ፋርስ ኮሜዲ ድራማ፤ በኒውዮርክ ዩኒቨርስቲ ማስተማሪያ እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል፡፡
በሶል ፕሮሞሽንና በአቶ ሰለሞን ግዛው ፕሮዲዩስ የተደረገው ድራማው፤ በየ15 ቀኑ አርብ በበደሌ ኮሜዲ ምሽት በሃርመኒ ሆቴል ለተመልካች የሚቀርብ ሲሆን አርቲስት ሱራፌል ተካ፣ ሰለሞን ተስፋዬ፣ መስከረም አበራ፣ ሰለማዊት በዛብህ፣ ብሩክ ትንሼ፣ ዳዊት አለሙና ሄኖክ በሪሁን እንደሚተውኑበት ተርጓሚና አዘጋጁ ለአዲስ አድማስ ገልጿል። ድራማው መታሰቢያነቱ ለብሔራዊ ቴአትር 60ኛ ዓመት መሆኑንም አርቲስቱ ተናግሯል፡፡

   በደንበል ሲቲ ሴንተር አራተኛ ፎቅ ላይ “ቫይን” በሚል ስያሜ ዘመናዊ አደረጃጀት ያላቸው መንትያ ሲኒማ ቤቶች የፊታችን ሐሙስ እንደሚመረቁ ተገለጸ። ጎን ለጎን ያሉት ሁለቱ ሲኒማ ቤቶች፣ አንድ መቶና አንድ መቶ አስር ሰዎችን የማስተናገድ አቅም ያላቸው ሲሆን ሲኒማ ቤቶቹን ዘመኑን በጠበቀ የሲኒማ መሳሪያዎች ለማደራጀት ከዘጠኝ ሚሊዮን ብር በላይ እንደፈጀም ተጠቁሟል፡፡ ከ25 ዓመት በላይ በአሜሪካ በኖሩት ባለሀብት አቶ ይግረማቸው ገብሬ የሚከፈቱት ሲኒማ ቤቶቹ፣ ደረጃቸውን የጠበቁ  መቀመጫዎች የተገጠመላቸውና ቫይን የተሰኘ ዘመናዊ ሬስቶራንትን ያካተቱ ሲሆን በቂና አስተማማኝ የመኪና ማቆሚያ እንደተዘጋጀላቸውም ለማወቅ ተችሏል፡፡

    በወጣት ገጣሚ መስፍን ወንድ ወሰን የተጻፈውና 67 ያህል ግጥሞችን ያካተተው “የኔ ቢጤ ሰማይ” የተሰኘ የግጥም ስብስብ መጽሃፍ ከነገ በስቲያ ሰኞ ጀምሮ በገበያ ላይ ይውላል፡፡
ገጣሚ መስፍን በተለይ ለአዲስ አድማስ እንደገለጸው፣ የመጀመሪያ ስራው የሆነውና 100 ያህል ገጾች ያሉት “የኔ ቢጤ ሰማይ” በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ የሚያጠነጥኑ ግጥሞች ተካትተውበታል፡፡
የመሸጫ ዋጋው 40 ብር የሆነው መጽሃፉ፣ ከመጪው ሰኞ ጀምሮ በአዲስ አበባና  በክልል ከተሞች በሚገኙ የመጽሃፍት መደብሮችና በአዟሪዎች በገበያ ላይ እንደሚውልም ገጣሚው ለዝግጅት ክፍላችን ገልጿል፡፡

   በደራሲና ዳይሬክተር ቢኒያም ጆን ተሰርቶ በቢንያም ጆን ፊልም ፕሮዳክሽን የቀረበው “በቁም ካፈቀርሽኝ” የተሰኘ ፊልም የፊታችን ማክሰኞ ከቀኑ 11፡00 ሰዓት ጀምሮ በአቤል ሲኒማ ይመረቃል፡፡ የ1፡45 ሰዓት ርዝመት ያለው ፊልሙ፤ ፕሮዲዩስ የተደረገው በዮሐንስ መስፍን ሲሆን ቀረፃው የተጠናቀቀው በአዲስ አበባና በሃዋሳ እንደሆነ አዘጋጆቹ ገልፀዋል፡፡ ሰርቶ ለማጠናቀቅ ሰባት ወራትን የፈጀው ፊልሙ፤ አራት ዋና እና መቶ አጃቢ ተዋንያን ተሳትፈውበታል፡፡

Saturday, 07 November 2015 10:18

የግጥም ጥግ

የመንፈስ ዘውድ
ነፍስ የራስዋን ዓለም መርጣ እንደሰየመች
ማንም እንዳይገባ በርዋን ጠረቀመች፣
ከርስዋም ቅዱስና ብዙሃናዊ ዓለም
ሠርገው ለሚገቡ ምንም ሽንቁር የለም፡፡
* * *
ሳትንቀሳቀስም ታያለች ባርምሞ
ታችኛው በርዋ ላይ ሠረገላ ቆሞ፤
ሳትንቀሳቀስም ታያለች ንጉሱን
ከግሮችዋ ምንጣፍ ስር ወድቆ ማጐንበሱን፡፡
* * *
እኔም አውቃታለሁ ከወዲያኛው ሀገር
አንድ ነገር ብቻ መርጣ በቁም ነገር፣
ከዚያ የትኩረትዋን በር፣ የልቧን ጥሞና
እንደቋጥኝ ዓለት ጥርቅም አርጋ ደፍና፡፡
ኤሚሊ ዲክንሰን
ሚክሎልና ፍልስፍና ትርጉም በጁዲት ሙሉጌታ

Saturday, 07 November 2015 10:12

የፀሐፍት ጥግ

(ስለ ፍልስፍና)
• ሙዚቃ ከሁሉም ጥበብና ፍልስፍና በላይ
የላቀ መገለጥ ነው፡፡
ሉድዊግ ቫን ቤትሆቨን
• ትንሽ ፍልስፍና ወደ ኢ-አማኝነት
ይመራል፤ ብዙ ፍልስፍና ግን ወደ
እግዚአብሄር መልሶ ያመጣናል፡፡
ፍራንሲስ ቤከን
• ከጥልቅ ፍልስፍናህ ይልቅ በሰውነትህ
ውስጥ ብዙ ጥበብ አለ፡፡
ፍሬድሪክ ኒቼ
• የእኔ ፍልስፍና፡- ህይወት ከባድ ነው፤
እግዚአብሄር ግን መልካም ነው ይላል፡፡
ሁለቱን ላለማምታታት ሞክር፡፡
አኔ ኤፍ.ቤይለር
• የእኔ ፍልስፍና፡- ሰዎች ስለእኔ የሚሉትና
የሚያስቡት ደንታዬ አይደለም… የሚል
ነው፡፡
አንቶኒ ሆፕኪንስ
• አውሮፓ የተፈጠረችው በታሪክ ሲሆን
አሜሪካ የተፈጠረችው በፍልስፍና ነው፡፡
ማርጋሬት ታቸር
• ፍልስፍና ከመደነቅ ይጀምራል፡፡
ፕሌቶ
• ታሪክ በምሳሌ የሚያስተምር ፍልስፍና
ነው፡፡
Thucydides
• ከተለመደው ሳያፈነግጡ እድገት
የማይቻል ነገር ነው፡፡
ፍራንክ ዛፓ