
Administrator
ግብፅ ከኢትዮጵያ የጽሁፍ ማረጋገጫ ጠየቀች
አየር መንገዱ ወደ ቬትናም አዲስ በረራ ጀመረ
ኦቪድ ሪል እስቴት ለገቢዎችና ጉምሩክ ሰራተኞች ቤቶችን ሊገነባ ነው
የፌዴሬሽኑ ምክትል ፕሬዚዳንት አትሌት መሰረት ደፋርን ያካተተ ቡድን ድሬዳዋ ገባ



ሪያል ማድሪድ አሌክሳንደር አርኖልድን አስፈረመ
አምባሳደር መለስ ዓለም አዲስ ሹመት ማግኘታቸውን አስመልክቶ ምን አሉ?
በመዲናዋ 15 ሆቴሎች የኮከብ ደረጃቸውን ተነጠቁ
ለአንጋፋው አርቲስት ኪሮስ ኃ/ሥላሴ ዛሬ የምሥጋናና እውቅና መርሃ ግብር ይካሄዳል
አርቲስት ኪሮስ ኃ/ሥላሴ ከ1975 ጀምሮ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በትያትር ጥበባት በቢኤ ዲግሪ ተመርቆ ሀገር ፍቅር ቴአትር ተመደበ። የወጣትነቱንና ጉልምስና እድሜውን በዚያ አሳለፈ። ሀገር ፍቅር ቴአትር ለኪሮስ ኃ/ሥላሴ መ/ቤቱ ብቻ ሳይሆን ትዳሩም ሕይወቱም ጭምር ነው። ከባለቤቱ አርቲስት ፀዳለ ግርማ ጋር ትዳር የመሰረተውና ልጆች ያገኘው ከሀገር ፍቅር ቴአትር ነው።
ኪሮስ ኃ/ሥላሴ ከመደበኛው ስራ ጡረታ ይውጣ እንጂ ዛሬም ሀሳብና ውሎው፣ ማህበራዊ ሕይወቱ ሀገር ፍቅር ቴአትር ነው። “ሳልሳዊው ባልንጀራ” ፣ “የቬኑሱ ነጋዴ “ ፣ “ናትናኤል ጠቢቡ” ፣ “ጣውንቶቹ “ ፣ “አሉ” ፣ “ባልቻ አባነፍሶ” ን የመሳሰሉ ትያትሮች ላይ በተዋናይነት ተሳትፏል። በርካታ ፊልሞችና የቴሌቪዥን ድራማዎች ላይ ተውኗል። ሀገር ፍቅር ቴአትር እና የአዲስ አበባ ባሕልና ቱሪዝም ቢሮን በተለያዩ ጥበባዊ ሀላፊነቶች መርቷል። በሚሊኒየሙ ጊዜ የአዲስ አበባ ሚሊኒየም ጽ/ቤትን በሊቀመንበርነት መርቷል።
ኪያ ወደ ሀገር ፍቅር ቴአትር የተመደበበት ወቅት አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በትያትር ጥበባት በመጀመሪያ ዲግሪ ማስመረቅና በየጥበብ ቤቶች መመደብ የጀመረበት ወቅት ስለነበረ፣ በወቅቱ በነባሮቹ አንጋፋ የጥበብ ሰዎችና በወጣቶቹ ምሩቃን መካከል የተፈጠረውን መጓተት ለማርገብና ዘመናዊውን እውቀት በልምድ ከካበተው ችሎታ ጋር አቀናጅቶ ለመስራት የኪሮስ ሚና ትልቅ ነው።
በአዲስ አበባ ባሕልና ቱሪዝም ኃላፊነቱ ወቅትም ወጣቶች የተለያዩ የትያትር ክበባትና ኢንተርፕራይዞች ተደራጅተው ተሰጥኦዋቸውን ወደ መድረክ እንዲያመጡ የኪያ አበረታች አቀራረብ ግዙፍ ነው። ከወጣቶች ጋር እንደ ወጣት፣ ከአዛውንቶቹ ጋርም እንደ እነሱ መሆን የሚችል በሁሉም የተወደደና የተመሰገነ ብቁ የጥበብ ሰው ነው። በዚህም “ኪሮስ” የሚለው ስሙ ቀርቶ በወዳጆቹ ዘንድ “ኪያ” መጠሪያ ስሙ ሆኗል።
ተስፋ የኪነጥበብ ኢንተርፕራይዝ እና የኪሮስ ኃ/ሥላሴ ልጆች ሕብረት ፈጥረው በዛሬው ዕለት መጋቢት 27 ቀን 2017 ዓ.ም ከቀኑ 9:30 ሰዓት ጀምሮ በሀገር ፍቅር ቴአትር አዳራሽ ደማቅ የክብርና የምስጋና መርሐ ግብር አዘጋጅተውለታል።
በመርሃ ግብሩም፦
ሙዚቃ (በሀገር ፍቅር ቴአትር እና መሐሪ ብራዘርስ ባንድ) ከታዋቂ ድምጻውያን ጋር፤ በስሙ የተዘጋጀና በታዋቂ ተዋንያን የሚቀርብ አጭር ድራማ፤ በፖሊስ ሰራዊት የማርሽ ባንድ ልዩ ልዩ ጣዕመ ዜማዎች፤ ዶኩመንታሪ (ሕይወቱንና ስራዎቹን የሚዘክር) እና ሌሎች መርሐ ግብሮች ይቀርባሉ።
የአርቲስት ኪሮስ ኃ/ሥላሴ ወዳጆችና አድናቂዎች በሰዓቱና በቦታው ተገኝታችሁ ኪያን በጋራ እንድናመሰግነውና እንድናከብረው፣ ልጆቹ እና ተስፋ የኪነጥበብ ኢንተርፕራይዝ በአክብሮት ጋብዟችኋል፡፡
“ዛፉ ሲወድቅ ዝንጀሮዎቹ ይበተናሉ” - የቻይናዎች አባባል “ቁልቋል የወደቀው ቅርንጫፍ ስላበዛ ነው” - የትግሪኛ ተረት
የተረት - አባት የሆነው ኤዞፕ እንዲህ ይለናል፡፡
ከእለታት አንድ ቀን ተኩላዎች ተመካከሩና መልክተኞች ወደ በጎች ላኩ፡፡
የተኩላዎቹ ልዑካን እበጎች መንደር ደረሱ፡፡ በጎች ተኩሎች መጡብን ብለው ተሸሸጉ፡፡ አድፍጠው ጋጣቸው ውስጥ አድብተው ተቀመጡ፡፡ ተኩሎቹ ግን ረጋ ብለው፣ አደብ ገዝተው፣ “በጎች አትደንግጡ፤ እንደምን ዋላችሁ” አሉ፡፡
“ለድርድር ነው የመጣነው” አሉ ተኩሎቹ፡፡
በጎቹ ቀስ በቀስ ከተደበቁበት ወጡ፡፡
“እኛ በድርድር እምናለን”
“እህስ? ምን እግር ጥሏችሁ መጣችሁ? ምን የድርድር ሃሳብ ይዛችሁ መጣችሁ” አሉ በጎች
“አንድ የቸገረ ነገር ገጥሞን ነበርና ልናዋያችሁ ፈልገን ነው”
“ምንድነው? ከተመካከርን የማይፈታ ምንም ነገር አይኖርም፡፡ ዋናው ተቀራርቦ መነጋገር ነው፤ ንገሩን፡፡”
ተኩሎችም፤
“እግዚአብሄር ይስጥልን፡፡ የቸገረን ነገር ምን መሰላችሁ? ይኸው ከተፈጠርን ጀምሮ ከውሾች ጋር ነጋ- ጠባ እንታገላለን፡፡ የችግራችን መነሻም መድረሻም ውሾች ናቸው፡፡ እርኩስ ውሾች እኛን ባዩ ቁጥር ይጮሃሉ፡፡ ይተነኩሱናል፡፡ ሰፈር ይረበሻል፡፡ ለእኛና ለእናንተ ወዳጅነትና ሰላም ዋናዎቹ እንቅፋቶች ውሾች ናቸው፡፡”
በጎችም፤
“ታዲያ ምን እናድርግ? ምን ዘዴ ብንፈጥር እንቅፋቶቹን ማስወገድ እንችላለን”
ተኩሎችም፤
“እናንተ እሺ ካላችሁማ ዘዴ አይጠፋም ነበር”
“እኮ ዘዴ ካለ ንገሩና?”
“ለጌታችሁ ንገሩ፡፡ ውሾች እንዳልተመቿችሁ ሰላምም እንደነሷችሁ አስረዱ፡፡ ይባረሩልን በሉ”
“ይሄማ ቀላል ነው፡፡ እንነግረዋለን”
በዚህ ተስማሙና ተኩሎቹ ሄዱ፡፡
በጎቹ ውሾቹ እንዲባረሩ ለጌታቸው አመለከቱ፡፡ ጌታቸውም ስንት ዘመን ቤት ደጁን ሲጠብቁ የኖሩትን ውሾች ከቤት አስወጥቶ አባረራቸው፡፡
ከዚያን ቀን በኋላ የዋሆቹ በጎች የዘመናት ጠባቂዎቻቸውን አጡ፡፡ ተንኮለኞቹ ተኩሎች እየተዝናኑ፣ በጎቹን አንድ በአንድ እየለቀሙ፣ በሏቸው፡፡
***
የድርድርን ትርጉም አለማወቅ እርግማን ነው፡፡ ከማን ጋር ነው የምደራደረው? ተደራዳሪዩስ ሊደራደረኝ ያሰበው ምን አስቦ ነው? ጠላቴ እንኳ ቢሆን ድርድሩ ያዋጣኛል ወይ? ከቅርብ ጊዜ ግቤ አንፃር ምን እጠቀማለሁ? ከዘላቄታ ግቤ አንፃርስ ምን እጠቀማለሁ? ትላንትና ምን ዓይነት ግንኙነት ነበረኝ? ዛሬስ? ዛሬን በዛሬው ክስተት መዳኘት እንዴት እችላለሁ? ብሎ ማሰብ የአባት ነው፡፡
በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የአሜሪካው ጄኔራል ማካርተር በፈሊፒንስ የአሜሪካ ጦር አዛዥ ተደርጎ ሲሾም አንድ ረዳት መኮንን አንድ መጽሐፍ ይሰጠዋል፡፡ መጽሐፉ ከዚህ ቀደም የነበሩት አዛዦች የተዋሉባቸውን ጦርነቶች ዝርዝር የያዘ ነው፡፡ ማካርተር “የዚህ መጽሐፍ ስንት ቅጂ አለ?” ብሎ ጠየቀው፡፡ ረዳቱም፤ “ስድስት አለ” አለው፡፡ ጄኔራሉም፤ “መልካም፤ በል ስድስቱንም መጻሕፍት ሰብስበህ አቃጥልልኝ፡፡ እኔ የትላንትና ውሎዎች ባሪያ መሆን አልፈልግም፡፡ ችግር ሲከሰት እዛው ወዲያውኑ መፍትሄ እሰጠዋለሁ፡፡ መጽሐፍቱን በሙሉ አቃጥልና ሁኔታዎች በተከሰቱ ሰዓት እንደ ሁኔታው ግዳጅህን ፈጽም” አለው፡፡ ታሪክ የራሱ ዋጋ ቢኖረውም ይህንን እንደ ተመክሮ መውሰድ ተገቢም ደንብም ነው፡፡ በትላንት ለመመካት ከሆነ ግን የግብዝ አመድ- አፋሽ መሆን ነው!
“ነበርን ማለት ግን ከንቱ ነው፤ ተውነው መጀነኑ በቅቶን
ጉራ መንዛት መዘባነን፣ የሚያዛልቅ ዘዴ ባይሆን” ይለናል ኦቴሎ የሼክስፒሩ፣ በፀጋዬ ገ/መድህን ብዕር ልሳን! ስለታሪክ ስለትላንት ማውራት ሳይሆን ዛሬን ማሸነፍ ነው የፖለቲካ ፋይዳው፡፡ ይሄን ያወቁ ላቁ! ይሄን የናቁ ወደቁ! እንደማለት ነው፡፡
ከ1966 ጀምሮ የተከሰቱ የሀገራችን የፖለቲካ ፓርቲዎች አበሳዎች፣ እከሌ ከእከሌ ሳይባል በትንሹ አስር መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ የተንተራሱ ይመስላሉ፡፡ ከአበሳዎቹ አንደኛው/በትንሽ በትልቁ መከፋፈል፣ ያለመስዋእትነት ድል መመኘት፣ ውሎ አድሮ ጧት የማሉበትን ማታ መካድ፡፡ “ዕምነት ሲታመም ሺ ወረቀት መፈራረም” ነው፡፡ 2ኛው/ለባላንጣቸው ሰርጎ - ገብነት መጋለጥ ነው፡፡ 3ኛው /እርስ በርስ አለመከባበር፣ አለመተሳሰብ፡፡ 4ኛው/ የመስመር ጥራት አለመኖር፤ ርዕዮተ-ዓለማዊ ብስለት ማጣት፡፡ 5ኛው/በትንሽ ድል መወጣጠርና በትንሽ ሽንፈት መፍረክረክ፡፡ 6ኛው/ተጋጣሚን መናቅና ወሬን /አሉባልታን እንደ አቋም መውሰድ፡፡ 7ኛው/ የጊዜን ፋይዳ በትክክል መረዳት፣ ባልፈውስ? አለማለትና የኃይል ሚዛን የማን ነው አለማለት፣ ከተፈፀመም አለመመዘን፣ ይሄ ዓላማ ባይሳካ ምን ሁለተኛ ዘዴ ቀይሻለሁ? ብሎ አለመዘጋጀት፡፡
8ኛው/ ባለፈው ያደረግነው የት አደረሰን? ታሪኩ ተተንትኖ ተገምግሞ ሳያልቅ በነዚያው ተዋንያን ተውኔቱ መቀጠሉ 9ኛው/ እምቢ አላረጅም ማለት ነው፡፡ አዲሱ ያሸንፈኛል አለማለት “the new is invincible የሚለውን መርሳት፤ “ካፈርኩ አይመልሰኝ” ማለት፡፡ 10ኛው/እኔ ባልሆንስ መፍትሄው? ሌላ ቢኖርስ? ከኔ የተሻለ አለ ብሎ ፈጽሞ አለማሰብ!
ከነዚህ ሁሉ ይሰውረን፡፡ እነዚህን ሁሉ ከልብ ከመረመርን ፓርቲዎቹ ሁሉ የቆሙት በአንድ ወይም በሁለት ቡድን ህብለ ሰረሰር (Spinal cord) ዙሪያ ነው፡፡ ይሄ እንግዲህ የሚሆነው
“ከተኳሾቹም - አሉ በልዩ
ማህል - አገዳ የሚለያዩ”
በምንልበት አገር ነው፡፡ ከፖለቲካ ንቃት- ባህሉ (ትምክህቱ፣ ጥበቱ፣ ዕምነቱ፣ የፖለቲካ ጥንቆላው፣ ሟርቱ ወዘተ) ባለበት አገር ልማድን አለመመርመር ጦሱ ብዙ ነው፡፡ አጠቃላይ የፖለቲካ ተመክሮአችን ገና አልተፈተሸም፡፡ “ዳሩ ሲነካ መሀከሉ ዳር ይሆናል” ይላል ያበሻ አባባል፡፡ ዞሮ ዞሮ ግን ግንዱ ሲመታ ቅርንጫፉና ቅጠሉ መርገፉ አይቀሬ ነው፡፡ ቻይናዎቹ “ዛፉ ሲወድቅ ዝንጀሮዎቹ ይበተናሉ” የሚሉን መሰረታዊ ነገር የሚሆነው ለዚህ ነው፡፡ “ቁልቋል የወደቀው ቅርንጫፍ ስላበዛ ነው” የሚለውም የትግሪኛ ተረት አዙረን ስናየው እንደ ቻይናዎቹ ነው፡፡
‘የትዝታዬ ማሕደር’ በቅርቡ ይመረቃል
“ዳግላስ ጴጥሮስ” በሚለው የብዕር ስሙ የሚታወቀውና በርካታ መጣጥፎችን ያስነበበው ደራሲ ጌታቸው በለጠ፤ ‘የትዝታዬ ማሕደር’ በሚል ርዕስ ያዘጋጀውን በሕይወቱ ዙሪያ የሚያጠነጥን መጽሐፍ በመጪው ሳምንት መጋቢት 5 ቀን 2017 ዓ.ም ያስመርቃል፡፡
የጌታቸው በለጠ ግለ-ታሪክ መፅሐፍ በ448 ገፆች የተቀነበበ ሲሆን፤ ከልጅነት እስከ ዕውቀት ያሳለፈውን ሕይወቱን የሚተርክ ነው ተብሏል፡፡ ‘የትዝታዬ ማሕደር’ በ1ሺ ብር ለገበያ የቀረበ ሲሆን፤ በምረቃ ሥነስርዓቱ ላይ ታዋቂ ደራሲያንና የቅርብ ወዳጆቹ ንግግር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል፡፡ ከእነዚህም መካከል ዶ/ር ንጉሴ ተፈራ፣ ደራሲ አበረ አዳሙ፣ ደራሲ ኃይለመለኮት መዋዕል፣ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠና ሌሎችም ይገኙበታል፡፡ ደራሲ ጌታቸው በለጠ፣ የደራሲያን ማህበር ፕሬዚዳንት በመሆን ያገለገለ ሲሆን፤ በማህበራዊና ኪነ ጥበባዊ ሂሶቹም ይታወቃል፡፡