
Administrator
በኢትዮጵያና ናይጄሪያ ጨዋታ ሰበብ የወረዳ አፈ-ጉባኤና ወታደሮች ሞቱ
በኢትዮጵያ እና በናይጄሪያ የእግር ኳስ ጨዋታ በጋምቤላ ክልል ኚኝኛግ ወረዳ በደጋፊዎች መካከል በተፈጠረ ግጭት የወረዳው አፈጉባኤ እና ወታደሮች እንደሞቱ ምንጮቻችን ገለፁ።
የደቡብ ሱዳን አዋሳኝ በሆነችው የኚኝኛግ ወረዳ ባለፈው እሁድ ኢትዮጵያና ናይጄሪያ በአዲስ አበባ ስቴዲየም ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ባደረጉት ጨዋታ፣ የናይጄሪያ ብሔራዊ ቡድን በማሸነፉ ደስታቸውን በጭፈራ በመግለጽ ላይ በነበሩ እና በድርጊቱ በተቆጡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ደጋፊዎች መካከል ግጭት ተፈጥሮ የኚኝኛግ ወረዳ አፈጉባኤና ከሁለት በላይ ወታደሮች እንደሞቱ ታውቋል፡፡
ችግሩ እንደተፈጠረ ከፌደራልና ከክልል የተውጣጡ ባለስልጣናት ቦታው ድረስ በመሄድ የማረጋጋት ስራ መሥራታቸውን ምንጮቻችን ጨምረው ገልፀዋል፡፡
የክልሉ ፕሬዝዳንት ሁኔታው ለማየት ወደ ስፍራው የሄዱ ሲሆን ስለ ጉዳዩ ፕሬዝዳንቱን በስልክ ለመጠየቅ ያደረግነው ተደጋጋሚ ሙከራ አልተሳካም፡፡
በኤርትራ የስደተኞች ካምፕ ረብሻ ተቀሰቀሰ የአንድ ሰው ህይወት አልፏል
ትግራይ ክልል የማይአይኒ በተባለ ስፍራ የሚገኝ የኤርትራ ስደተኞች ካምፕ ውስጥ በተቀሰቀሰ ረብሻ የአንድ ሠው ህይወት ከጠፋ በኋላ፣ ተጠያቂ ናቸው የተባሉ ሰዎች እንደታሰሩ ምንጮቻችን አመለከቱ፡፡ ስደተኞች የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን በመቃወም ቢሮዎች የሰባበሩ ሲሆን፣ ወደ ጎንደር የሚወስደውም መንገድ ተዘግቶ ነበር፡፡
የረብሻው ምንጭ፣ ከሊቢያ ወደ ጣሊያን ሲጓዙ ለሞቱ በርካታ ኤርትራውያን የተዘጋጀ የመታሰቢያ ስነ ስርዓት እንደሆነ ምንጮቻችን ጠቅሰው ሻማ በማብራት የተጀመረው የመታሰቢያ ምሽት ወደ ተቃውሞ ረብሻ መቀየሩን አስታውሰዋል፡፡ በካምፑ ውስጥ የተፈጠረው ረብሻ ከቁጥጥር ውጭ ሆኗል በሚል ውሳኔ የፀጥታ ሀይሎች ጣልቃ እንደገቡ ምንጮቹ ጠቅሰው፤ በረብሻውና በግጭቱ የአንድ ሰው ህይወት እንደጠፋ ተናግረዋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን (UNHCR) የህዝብ ግንኙነት ተወካይ አቶ ክሱት ገብረእግዚአብሔር፤ በሜዲትራኒያን ባህር ላምፑዱስ የተባለ ደሴት አቅራቢያ ህይወታቸውን ላጡ ወገኖች የሻማ ማብራት ስነ ስርአት እናደርጋለን በሚል የተጀመረው ፕሮግራም ለምን ወደ አመፅ እንዳመራ አናውቅም ብለዋል፡፡ ስደተኞቹ ወደ ጎንደር የሚወስደውን መንገድ እንደዘጉ አቶ ክሱት ጠቅሰው፣ የመንግስታቱ ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን እና አብረውን የሚሠሩ የሌሎች መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ላይ ተቃውሞ ተቀስቅሶ የቢሮ መስኮቶችና በሮች ተሠባብረዋል ብለዋል፡፡ ካምፕ ውስጥ የነበሩና አማራጭ ያጡ ወገኖች በሊቢያ በኩል ወደ ጣሊያን ለመግባት ሲሞክሩ ሞተዋል የሚል ሃሳብ በስደተኞች በኩል እንደተሰነዘረ አቶ ክሱት ጠቁመዋል፡፡
የመንግስታቱ ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን፣ በህጋዊ መንገድ ስደተኞችን ቢያጓጉዝ ኖሮ የበርካቶች ህይወት አይጠፋም ነበር በማለት በኮሚሽኑ ቢሮዎች ላይ ጥቃት እንደተፈፀሙ ሰምተናል ብለዋል-አቶ ክሱት፡፡ ስደተኞች ወደተለያዩ አገራት የሚጓጓዙት በኮሚሽኑ ፍላጎት ሳይሆን በተቀባይ አገራት በጎ ፈቃድ ነው ያሉት አቶ ክሱት፤ ኮሚሽኑ ለስደተኞች እንግልት ተጠያቂ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡
“የብርሃን ፈለጐች”ን ተከትለን ስንጓዝ “የብርሃን ፈለጐች”ን ስንጀምር
“የብርሃን ፈለጐች” ከቀደሙት ሁለት የደራሲው ሥራዎች (አጥቢያና ቅበላ) በገፁ ብዛት ዳጐስ ብሎ የቀረበ ከመሆኑ አንፃር፣ በበቂ የተለፋበትና የተደከመበት ሥራ እንድንጠብቅ የሚያደርገን ነው፡፡ በተለይም ደራሲው “አጥቢያ” እና “ቅበላ”ን አከታትሎ ለአንባቢ ካደረሰባቸው ከሁለት ዓመታት ያነሰ ጊዜ አንፃር “የብርሃን ፈለጐች” ከአራት ዓመታት በኋላ ሲመጣ፣ ከቀደሙት ሥራዎቹ ከአንባቢ ያገኘውን አስተያየት እንዲሁም የራሱን ስህተትና ክፍተት ሞልቶና አርሞ በተሻለ መገለጥ እንደመጣ መገመት የሚከብድ አልነበረም፡፡ በእርግጥም “የብርሃን ፈለጐች” የፈጠራ ድርሰት የመገምገሚያ መሠረታዊ አላባውያን በሆኑት በታሪክ ፈጠራ፣ በዘይቤ፣ በግጭት፣ በተዓማኒነት፣ በልብ ሰቀላና በአተራረክ ቴክኒክ እንዲሁም በሌሎች መመዘኛዎች የተሳካ ሥራ ለመሥራቱ የያዝኩትን ቅድመ ግምት ያጠናከረልኝ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡
ይሁንና ከላይ የጠቀስኳቸውን መሠረታዊ የመገምገምያ ነጥቦች ተጠቅሜ በ“የብርሃን ፈለጐች” ዙሪያ ቅኝት ከማድረግ ይልቅ ለዛሬ የመጽሐፉን ታሪክ ከዋናው ገፀ-ባህርይ አንፃር ለመፈተሽና በዚሁ ላይ ተመስርቼም የደራሲውን የአፃፃፍ ፈለግ በመመርመር፣ አንዳንድ በወጉ መረዳት የሚገቡንን ነጥቦች ማስቀመጥን መርጫለሁ፡፡
ደራሲ አለማየሁ ገላጋይ ለዚህ መጽሐፉ መግቢያ የሚሆን ነገር አላበጀለትም፡፡ ከዚያ ይልቅ ሃያሲ አብደላ ዕዝራ ከሕትመት በፊት በእጁ የገባውን ረቂቅ ተመልክቶ በተረዳውና በገባው መጠን የሰጠውን አስተያየት በመጀመሪያው ገጽ እና ከእዚያው ውስጥ የተቀነጨበውን ደግሞ በመጽሐፉ የኋላ ሽፋን ላይ እንዲሰፍር አድርጓል፡፡ እርግጥ ነው ደራሲው ሥራው ለአንባቢ ከመድረሱ በፊት ለእንደ አብደላ ዕዝራ ዓይነቱ በኢትዮጵያ የስነ ጽሑፍ ሂስ ታሪክ አንድ ሥፍራ ለሚይዝ ባለሙያ አስተያየት አስቀድሞ ማቅረቡ ለአንባቢ ያለውን አክብሮትና ግምት እንዲሁም በሥራው ላይ ያለውን ትጋት የሚያሳይ ነው፡፡ ይሁንና በመግቢያ መልክ የተሰጠውን አስተያየት ቀንሶ በኋላ የመጽሐፉ ሽፋን ላይ መድገሙ ለምን አስፈላጊ እንደሆነ ግልጽ አልሆነልኝም፡፡
“አንባቢያን መጽሐፉ ከዚያ የላቀም ይሁን ያነሰ ታሪክ በውስጡ አልያዘምና አዲስ ነገርን በመፈለግ አትድከሙ” በማለት ሊያቆም ፈልጐም ከሆነ “blurb” ሆኖ የሰፈረልን ማሳሰቢያ በቂ በሆነን ነበር፡፡ ከዚያ ይልቅ (ግዴታም ባይሆን) ደራሲው በራሱ ብዕር የመግቢያውን ሥፍራ በመሰለው የግሉ እምነትና አስተሳሰብ ቢይዘው ኖሮ፣ ቢያንስ በአንባቢያን ዘንድ ስለመጽሐፉ ልዩ ምልከታና አስተያየት ሊፈጠር የሚችልበት የተሻለ አጋጣሚ በተፈጠረ ነበር እላለሁ፡፡
የዘመን ጉዳይ
“የብርሃን ፈለጐች” የሁለት ዘመን ትውልዶች የሚገለጡበት ልብ - ወለድ ነው፡፡ ይኸን ለማለት ያስገደደኝ በእኛ ሀገር የዘመንም ሆነ ትውልድ ሽግግርና ለውጥ በዓመታት ቀመር የሚሰላ ሳይሆን ዙፋን ላይ በተቀመጠው መንግሥት ምንነትና የአገዛዝ ባህርይ የሚወሰን ሆኖ ስለሚሰማኝ ነው፡፡ የአፄ ኃይለሥላሴ ዘመን ትውልድ ከደርግ፣ የደርጉ ደግሞ ከኢህአዴግ የሚለይበት የየራሱ መገለጫ ባህርይ እንደተሸከመው ማለት ነው፡፡ እርግጥ ነው በመጽሐፉ ውስጥ የምናገኘው ታሪክ የተፈፀመበትን ዘመን ደራሲው እንድንረዳ የሚያደርገን በገፀ ባህርያቱ አለባበስ፣ አኳኋንና አልፎም ንግግር ነው፡፡
“የግንፍሌ ማለዶች” በመጽሐፉ ውስጥ በቅድሚያ የምናገኘው የታሪክ ክፍል ሲሆን ዘመኑን ለመገመት ለሚነሳ አንባቢ ግን የራሱን ፈተና ከፊቱ ማስቀመጡ የሚቀር አልሆነም፡፡ የታሪኩ ዋና ገፀባህርይ የሆነው መክብብ፤ የልጅነት ዕድሜውን ያሳለፈባትን ግንፍሌን ከቤተሰቡ፣ ከጓደኞቹ፣ ከጐረቤቶቹና ከሠፈሩ ሰዎች ጋር ባለው ተራክቦ በሚገባ እንድናያት ደራሲው ማድረጉን ሳንክድ ነገር ግን የዘመን ጥያቄ ሲነሳ በአፄው ዘመነ መንግሥት ለመሆኑ ከግምት እንዳናልፍ የሚያደርጉን ሁለት ጉዳዮች እናገኛለን። የመጀመሪያው “ገዳማይ” የሚለው ዘፈን ተደጋግሞ መምጣት ሲሆን (ዘፈኑ በኋላ በደርግ ዘመን በሙሉቀን የተቀነቀነ ቢሆንም ከዐፄው ዘመን የወረሰው በመሆኑ) እና ሁለተኛው የአባቱ የፀጉር አቆራረጥ ከ“ፕሪስሊ” ጋር መገናኘቱ ነው፡፡ ዘፈኑም ሆነ የኤልቪስ ፕሪስሊ የፀጉር ፋሽን በሀገራችን ሰፊ ተቀባይነት የነበራቸው በ60ዎቹ መጀመሪያ ከመሆኑ ጋር በተገናኘ ግንፍሌን የምንመለከትበት መነጽርም የአፄው ዘመን እንዲሆን ብንወስን እንኳን ሌላ ፈተና ደግሞ መምጣቱ አልቀረም፡፡ ይኸውም ዘፈኑ የሚቀርብልን በመክብብ አባት የትዝታ እንጉርጉሮ በመሆኑ፣ ዘመኑን ወደ ደርግ የሚጐትተው ሲሆን የፀጉር አቆራረጥ ዘይቤውም ቢሆን አባቱ በውስጡ ለዓመታት ከተቆራኘው የሙዚቃ ፍቅር ማምለጥ አለመቻሉን የሚያስረግጥ ማሳያ እንጂ የሚገኝበትን ትውልድ የዘመን ፋሽን የመግለጥ አቅሙ ደካማ ከመሆኑ ላይ ነው፡፡ ምናልባት በዚሁ ዘይቤ ሌላ ገፀ ባህርይ ተስሎልን ቢሆን ወይም ተጨማሪ ገለፃ ከመቼት አንፃር ሰፍሮልን ቢሆን በግንፍሌ የታሪክ ዘመን ላይ ጥያቄ ባልኖረንም ነበር፡፡
ወደሁለተኛውና የመጽሐፉ ሰፊ የታሪክ መሽከርከሪያ ወደሆነችው ሞጆ ስንሻገር፣ የዘመን ጥያቄ በደራሲው በቂ ምላሽ የተሰጠበት ሆኗል። ቢያንስ በሁለት ገፀ ባህርያት አማካይነት ሞጆ የተገለፀችበት ዘመን የአብዮቱ ዓመታት እንደነበሩ ግልጽ ነው፡፡ የናፍቆት አባት ተደጋጋሚ “የአብዮታዊት ኢትዮጵያ” ስብከትና የመምህርቱ ሙና ያለፈ የኢህአፓ ትዝታ ሞጆ በየትኛው ዘመንና ትውልድ ተስላ እንደቀረበችልን በቂ ማሳያ ናቸው፡፡
እዚህ ላይ የዘመን ጉዳይ በፈጠራ ድርሰት ውስጥ ቀዳሚውን ሥፍራ ሊያገኝ የሚገባበትን አስፈላጊነት አጽንኦት ሰጥቼ ማስቀመጤ ምክንያቱ ግልጽ ይመሥለኛል፡፡ ይኸውም ማንኛውም የልብ ወለድ መጽሐፍ ለንባብ ሲበቃ፣ ደራሲው በውል የሚያውቀውን ዘመንና ሥፍራ የሚያሳይ መስታወት በአንባቢው ፊት የማቆሙን ግዴታ ከግምት በመክተት ነው፡፡ ድርሰት የቱንም ያህል የደራሲ የፈጠራ ውጤት ቢሆን ፍፁም ውሸት ተደርጐ የማይወሰደውም ከዚህ በመነሳት ነው፡፡ የፈጠራነቱ ባህርይ ውሸት ቢያደርገውም የሚፈጠሩት ገፀ ባህርያት፣ ጊዜያት (ዘመን)፣ ሥፍራዎች፣ ድርጊቶች … ወዘተ የገሃዱ ዓለም ነፀብራቅ በመሆናቸው ደግሞ “እውነት” ሊሆኑ የሚችሉ አድርገን መቀበላችን አይቀሬ ነውና፡፡
የአፃፃፍ ፈለግ
የዚህ ጽሑፍ ዋነኛ ጉዳይ ወደሆነው በ “የብርሃን ፈለጐች” ውስጥ ወደተስተዋለው የአፃፃፍ ፈለግ ደግሞ እናምራና መጠነኛ ፍተሻ እናድርግ። እንግዲህ አንድ ደራሲ እንደሚገኝበት ዘመንና በዘመኑ እንደነገሰውም አስተሳሰብ፣ የራሱን የአፃፃፍ ፈለግ የመከተል ነፃነት እንደተጠበቀ የመሆኑ ጉዳይ ተሰምሮበት ነገር ግን የማኅበረሰቡን ልማድ፣ ወግ፣ ንቃተ ህሊና፣ መሻትና ፍላጐት ደግሞ ከግምት የከተተ መሆኑ ተመራጭ ያደርገዋል፡፡
እርግጥ ነው ደራሲ ከማኅበረሰቡ የተለየ ዓይንና ማስተዋል የታደለ እንደመሆኑ መጠን የተመለከተውንና የታዘበውን ወይም ያስደነቀውን እውነት በመሰለውና ባመነበት መንገድ የማስቀመጡ ነፃነት ለእሱ የተተወ ነው፡፡ ለምሳሌ በአፃፃፍ ስልቱ (Style) ዙሪያ አንድም በምርጫ ወይም በግላዊነት ላይ ተመስርቶ ድርሰቱን ለመፃፍ ይችላል፡፡ በምርጫ ስንል ለምሳሌ የቀለም ምርጫ የግሉ ነው፡፡ ውበትን ለመግለፅ ቀይ ቀለምን ምርጫው ያደረገ ደራሲ “ለምን?” የሚል ክርክር ሊነሳበት አይችልም፡፡ ከግላዊነትም አንፃር ለምሳሌ ረዥም ወይም አጭር ዐረፍተ ነገርን መርጦ መጠቀሙ፣ ተረትና ምሳሌ ማብዛቱ፣ የዘይቤ ምርጫው ሁሉ ከዚሁ የግላዊነት ነፃነቱ የሚመነጩ ናቸው፡፡
ይህ እውነታ እንደተጠበቀ ሆኖ ደራሲ አለማየሁ በ “የብርሃን ፈለጐች” ውስጥ ገንኖ የወጣበት የአፃፃፍ ፈለግ በዘመናችን በርካታ አለም አቀፍና አንዳንድ ጥቂት የሀገራችን ደራስያን (አዳም ረታ ተጠቃሽ ነው) በሥራዎቻቸው በስፋት የሚጠቀሙበት የ“Postmodernism” የአፃፃፍ ፈለግ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ ከዚህ አንፃር የደራሲውን ሥራ ከመቃኘቴ በፊት ይኼ የአፃፃፍ ፈለግ ዋነኛ አትኩሮቱ ምን እንደሆነ በቀላል ማብራሪያ አንባብያንን ግንዛቤ ማስጨበጥ ያሻል፡፡
የ“Postmodemism” እሳቤ በኪነጥበብ ዘርፍ ለማቆጥቆጥ መነሻ የሆነው በኪነ-ሕንፃ (architecture) ጥበብ ላይ የተነሳው አዲስ አስተሳሰብ እንደነበር ይታመናል፡፡ ይኼ ፈለግ ሁለት መሠረታዊ ደረጃዎችን ተሻግሮ፣ በተለይ በ1950ዎቹና 60ዎቹ ያቆጠቆጠ ሲሆን ከእሱ በፊት ቀዳሚ የነበሩት ሁለት ፈለጐች የመጀመሪያው “Premodernism” ሲሆን በመቀጠል ደግሞ “modernism” በመባል ይታወቃሉ፡፡ በ “Premodernism” ማንኛውም የጥበብ ሰው የአስተሳሰቡ መሠረት አድርጐ በሥራው እንዲያንፀባርቅ የሚጠበቅበት መንገድ ከባህሉና ወጉ ወይም እምነቱ የመነጨ ሊሆን ይገባል የሚል ነበር፡፡ በተለይ ይኼን አስተሳሰብ በማራመድ ተጠቃሽ የሆነችው የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ስትሆን ማንኛውም የፈጠራ ሥራ በባህልና እምነት ተፅዕኖ ሥራ መውደቅ እንዳለበት ቀዳሚ ተከራካሪ ሆና ለዘመናት ዘልቃ ነበር፡፡ ከዚያ በመቀጠል የመጣው የ“modernism” ፈለግ ደግሞ የሰው ልጅ አብርሆ መቃኘት ያለበት አዲስ ነገርን በማሰብና በተፈጥሮ ሳይንስ ሊሆን ይገባል እንጂ በባህልና ህግ እንዲሁም በእምነት መሪዎች አስተሳሰብ ሥር መውደቅ የለበትም የሚል ነው፡፡ የዚህ አስተሳሰብ መሠረቱ የሕይወት ትርጉምም ሆነ እውነት የሚመነጨው ከግለሰቡ አመለካከትና አቋም እንጂ በላዩ ከተጫነበት እምነትና ባህል ሊሆን አይገባም የሚል ነበር፡፡ እናም የዚህ ፈለግ አራማጆች ማንኛውም የፈጠራ ሥራ የቀደመውን ባህልና ወግ እንዲሁም አስተሳሰብ ወደ ጐን አስቀምጦ አዲስና ቀልብን የሚማርክ ነገር በመፍጠር ላይ ያተኮረ ሊሆን ይገባል ባይ ናቸው፡፡
የዚህ ፈለግ ተቃዋሚ ሆነው ብቅ ያሉት ደግሞ በተለይ በስነጽሑፍ ዘርፍ በ1970ዎቹ እ.ኤ.አ ገንነው የወጡት “Postmodernist” ናቸው፡፡ “Postmodernist” በዋነኛነት የሚያራምዱት አስተሳሰብ በቀላል አገላለፅ ሲቀመጥ የ“modernism” አስተሳሰብ የሆነውን አዲስና ማራኪ የፈጠራ ሥራ መከወንን ተቀብለው፣ ነገር ግን መሠረቱ ሊያደርገው የሚገባው የቀደመውን ወይም ነባሩን ባህልና ወግ እንዲሁም እምነት ሊሆን ይገባል የሚል ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የ “Postmodernist” የአፃፃፍ ፈለግ በዋነኛነት ለመመለስ የሚሻው ጥያቄ “የሰው ልጅ ማንነት (ሕልውና) በተፈጥሮ ውስጥ ያለው ሥፍራ ምን እንደሆነ” ፈልጐ ማግኘትን ነው። ለምን ተፈጠርኩ? ማነው የፈጠረኝ? የመፈጠርስ ዓላማ በፈጣሪ ወይስ በየግል የአስተሳሰብ አቋም የሚገለፅና የሚወሰን ነው? ከተፈጠርን በኋላስ በምድራዊ ሕይወታችን ለሚገጥመን ክፉም ሆነ በጐ አጋጣሚ ተጠያቂው የማኅበረሰቡ እምነትና ባህል? አካባቢያችንና ቤተሰባችን? ፈጣሪያችን? ወይስ ማን? የሚሉና መሰል ከውስጣዊ ማንነት ጋር የተያያዙ ጥያቄዎችን መንደርደሪያው ያደርጋል፡፡ ይሁንና የጥያቄዎቹ ምላሽ ሊፈለግ የሚገባው ደግሞ ግለሰቡም ሆነ ማኅበረሰቡ በተቃኘበት እምነት፣ ባህል፣ አስተሳሰብና ወግ ላይ ተመስርቶ ሊሆን እንደሚገባ “Postmodernist” ያሰምሩበታል፡፡
እንግዲህ ወደ “የብርሃን ፈለጐች” ስንመለስ፣ በአመዛኙ ይኸው የማንነት (የሕልውና) ጥያቄን መሠረቱ አድርጐ ከመቆሙ ባሻገር ለጥያቄው ምላሽ የሚያፈላልገው ደግሞ ከማኅበረሰቡ ባህልና ወግ ከዚያም ሲያልፍ በፈጣሪው ላይ ከገነባው እምነት የለሽ የመሆኑ እውነታ ነው፡፡ ለዚህ በቂ ማሳያ የሚሆነን ደራሲው በዋናው ገፀ ባህርይ መክብብ አማካይነት ደጋግሞ የሚያነሳውን የማንነት ጥያቄና ከቤተሰቡ እስከ ማኅበረሰቡ እንዲሁም ባህልና ወጉን አልፎም ፈጣሪውን የሚሞግትበት ስልት ይሆናል፡፡
ደራሲው ከመነሻው እንዲህ ዓይነቱን ጥያቄ የሚያነሳልን በመክብብ መፈንከት ይሆናል፡፡ መክብብ በጓደኛው ጋንጩር ተፈንክቶ በጓደኞቹ ሸክም ወደቤቱ ሲወሰድ ከመፈንከቱ በላይ ጥያቄ ፈጥሮበት ከራሱ ጋር ሙግት የሚያስገጥመውና ግርምት የሚፈጥርበት ከውስጡ የሚፈልቀው ደም ነበር፡፡
“አካላችን ውስጥ እንዳልነበር፣ የእኛ እንዳልሆነ በባዕድነት ዝም ብሎ መንዠቅዠቁ አስረገመኝ” (ገፅ 6)
ደራሲው በዋናው ገፀ ባህርይ ውስጥ ከጅምሩ የፈጠረው በራስ ላይ የሚነሳ የማንነት ጥያቄ፣ በቤተሰቡ ውስጥም የሚንፀባረቀው ብዙም ሳንጓዝ በእናቱ አማካይነት ይሆናል፡፡ የመክብብን እናት ማንነት የዘመን ወካይነቷን መነፅር አጥልቀን እንድናይ የምንጋበዘው በቤታቸዉ በሰፈነው ድባብ አማካኝነት ሲሆን ከግድግዳው መገርጣት፣ ከብርሃን ማጣቱ፣ እንደጐሬ ከመክበዱ … ወዘተ ጋር በተገናኘ ለእሱ ጭንቅ የሚፈጥርበት ክስተት በእናቱ ዘንድ ግን ተቃራኒ ስሜት የያዘና ከዚያ ያለፈ የመለወጥ ምኞትም የሚፈጥር አልሆነም፡፡ ለመክብብ የቤታቸው መገለጫ ከሆኑት “ብርሃን የሚውጡ” ቁሳቁሶችም ሆነ ስሜት ከሚያጨልመው ጣራና ግድግዳዉ መካከል ዓይን ሳቢ የነበረው የሚካኤል ስዕል ቢሆንም እሱም እንክብካቤ ተነፍጐና በጢስ ጠቁሮ በቤቱ መንፈስ የተዋጠ ሆኗል፡፡ ሕይወት ዕጣ-ፈንታው አድርጋ የለገሰችውን ድህነት፣ ቤተሰቡ በፀጋ ተቀብሎ መኖሩ ከልጅነቱ አልዋጥልህ ብሎ ጭንቁን የሚተነፍሰው መክብብ፤ ቢያንስ የእምነት መገለጫ የተደረገውን ስዕል እንኳን የመለወጥ ፍላጐት ከእናቱ ዘንድ ማጣቱ፣ እንደ ኑሮው እምነቱም በወደቀ ቤተሰብ ውስጥ ለመኖሩ ማንፀሪያ አድርጐታል፡፡
“ይሄ ምስል በአዲስ ይቀየር ብትባል እናቴ በጀ የምትል አይመስለኝም” (ገፅ 9) በማለት ድህነት ቤተሰቡ ላይ የፈጠረው የኑሮ ብቻ ሳይሆን የእምነት ዝንጋታ በመክብብ በኩል ሲነገረን፣ ደራሲውን የነበረው ባህል፣ ወግ፣ እምነት ላይ የተመሠረተ አዲስ ለውጥና መሻሻል ናፋቂ ሆኖ እናገኘዋለን። የ“Postmodernism” ፈለግ ይኸው ነው፡፡ የገፀ-ባህሪያቱን አስተሳሰብ፣ ስነ-ልቦና፣ እምነት፣ ምልከታ … ዘልቆ በመፈተሽ ከገሃዱ ዓለም እውነታ ጋር በንፅፅር የማቅረብና በአዲስ መንገድ የማስታረቅ ዓላማን አንግቦ የሚጓዝ፡፡
ደራሲው የማንነትን ጥያቄ ከገፀባህርያቱ ስነልቦና እየፈተሸ ምላሽ ሲያፈላልግ ከምናገኝበት ክስተቶች አንዱ በቤተሰብ ዙሪያ የሚያጠነጥን በተለይም በባልና ሚስት መካከል የሰፈነው ግንኙነት ምን መምስል እንደሚገባው የሚመለከት ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ከእናቱ ይልቅ ወደ አባቱ የሚያደላ ፍቅር የምናይበት ዋናው ገፀ-ባህርይ መክብብ፤ በልጅነቱ የተቀረፀበትን “የወላጆቹ ትዳር በእናቱ የበላይነት መመራት” ከባህሉና ከወጉ ጋር የሚጣላ ብቻ ሳይሆን ፍፃሜው መፈራረስ መሆኑን የሚያሳየን በብዙ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ውጥንቅጥ የተሞላው የጐረቤቶቻቸው ትዳር እንደነበር ሲቀጥል፣ የወላጆቹ መጨረሻ ግን መለያየት እንደጠቀለለው በመተረክ ነበር፡፡ ቤተሰብ የማኅበረሰብ መሠረት እንደሆነና ድህነት የሚፈጥረው ፈተና እንኳን በቀላሉ እንደማይሰብረው ደራሲው ከግንፍሌ ነዋሪዎች ሕይወት እግረ-መንገድ እያነሳልን ካስጓዘን በኋላ ወደ ዋናው ገፀ ባህርይ ወላጆች ሲያደርሰን ግን የዘመኑን የትዳር መንፈስ ከኋለኛው የሚያነፃፅርበት ሰበዝ አድርጐ ይመዘዋል፡፡ እናም በራስ ላይ ለሚነሳ የ“ለምን አገባሁ?” ጥያቄና ለትዳር መፍረስ ምላሽ በማድረግ የሚያስቀምጠው ትዳር፤ በነባሩ የባህልና ወግ ሥርዓት መሠረት ወንዱ የሚገባውን የበላይነት ሥፍራ በቅድሚያ መልሶ ሲያገኝ እንደሆነ በመሞገት ነው፡፡
ደራሲው በዋናው ገፀ-ባህርይ መክብብ በኩል ይህንኑ የትዳር መሠረታዊ ችግር የሚያሳየን ከእናቱ አስተሳሰብ በመነሣት ነው፡፡
“እናቴ አባቴን ከጫካ አጥምዳ፣ የሚበላው እየሰጠች የገራችው የግሏ አውሬ ይመስለኛል” (ገፅ 14) ይላል፡፡
ደራሲው በመክብብ በኩል ከሚያነሳቸዉ የማንነት ጥያቄዎች አንዱ እንግዲህ ከሕልውና መሠረቶች አንዱ የሆነውን የቤተሰብን አወቃቀር እንዲህ የሚፈትሽና ምላሽ የሚያፈላልግ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ የማኅበረሰብ መገለጫው በውስጡ እንደሚገኙ ቤተሰቦች (ትዳር) ጥንካሬና ድክመት የሚወሰን ሲሆን የሀገሩ ባህልም ሆነ እምነት በአወቃቀሩ ከማይደግፈው ከዚያ ቤተሰብ የተገኘው መክብብ ደግሞ በማኅበረሰቡ ውስጥ የሚመለከተውን በወንዱ የበላይነት የሚመራ ትዳር፤ ለወላጆቹ ከመሻቱ የተነሣ የፍቅራቸውን ሰዓት እንኳን የሚመለከተው በቅናት መንፈስ ተሞልቶ ነበር፡፡ ዘወትር የአባቱ በእናቱ ተሸናፊነትና ዝቅ ተደርጐ መመልከት፣ እንዲሁም የአባቱ የማያሰልስ ታዛዥነትና ትዳር የለገሰችውን ሥጋዊ ስሜቱን በነፃነት የማርካት መብት ሳይቀር በልምምጥ ለማግኘት በየምሽቱ መታተርን መታዘቡ፣ ለአባቱ በማዘን ብቻ ሳይሆን በመቆርቆርም እንዲያድግ አድርጐታል። ለዚህ ቀላል ማሳያ የምትሆነን የመክብብ እናት ወደ ሞጆ ለመሄድ ስትነሣ የተፈጠረውን ትዕይንት እንመልከት፡-
“እናቴ ወደ ሞጆ ስትሄድ አባቴ በሎሌነት ዘንቢሏን አዝሎ ይከተላታል፡፡ ዘንቢሉ የተሞላው በጆንያ፣ በከረጢት፣ በማዳበሪያና በስልቻ ነው። በዚህ ትዕይንት ትክክል ያልሆነ ነገር እንዳለ ይሰማኛል፡፡ እናቴ ጥቁር ከፋይ ካፖርት በነጠላ ክንንብ ላይ ደርባለች፡፡ ሦስት ማእዘን ቅርፅ ያላትን ቦርሳ ክንዷ ላይ አንጠልጥላለች፡፡ አባቴ ፕሪስሊውን እንደደፋ ኋላ ኋላዋ ቱስ ቱስ ይላል …
“ትክክል ያልሆነ ነገር እንዳለ ይሰማኛል፡፡ እናቴ የአባቴን ፍፁም ታዛዥነት ለመንደርተኛው የምታስመዘግብበት ትዕይንቷ ነው …” (ገፅ.36)
ከትዳር ትርጉም በላይ ደራሲው በመክብብ አማካኝነት የሚያነሳልን ሌላ የማንነት ጥያቄ ደግሞ አባቱ ምኞቱንና ሕልሙን በእናቱ ፍርሃት ሥር ጥሎ እንዲኖር ያስገደደውን የሙዚቃ ፍቅር ነበር። የዚህ ምኞትና ሕልሙ ማስተንፈሻ የነበረችው ጊታር፣ ከአልጋቸው ሥር ተጠቅልላ ስትወረወር፣ አባቱ በምድር ላይ የተፈጠረበትን ምስጢርና ዓላማ እንኳን ፈልጐ እንዳይደርስበት በሚስቱ ፍርሃት ተሸብቦ በዘበኝነት ለመኖር ምርጫው ማድረጉ፣ ለራሱ አስገራሚ ጥያቄ የሚፈጥርበት ነበር፡፡ ከአልጋ ሥር የተጣለችው የመክብብ አባት ጊታር ወደ ማኅበረሰቡ ሕይወት ወርዳ ስትመነዘር፣ ከእያንዳንዱ ሰው የመፈጠር ምክንያት ጋር የተገናኘ ምኞትና መሻትን እንዲሁም መክሊትን የምትወክል ሆና እናገኛታለን፡፡ መሆን የምናስበውንም ሆነ የምንችለውን እንድንሆን መንገዱን በቅድሚያ የሚሰጠን የምናድግበት ቤተሰብና አልፎም ማኅበረሰብ ቢሆንም በመንገዱ ላይ ለመጓዝ ግን ቤተሰብና ማኅበረሰብ የተመሠረተበትን ባህልና ወግ እንዲሁም እምነት መለስ ብሎ መፈተሽ እንደሚገባ ደራሲው የሚሞግት ይመስላል፡፡ ለዚህም ነው የአባቱን ሕልምና ምኞት ለጊዜውም ቢሆን በእናቱ የሞጆ ጉዞ ባገኙት ነፃነት ላይ መስርቶ ከወደቀበት ለማንሳት መክብብ የሚንደፋደፈው፡፡
ይኼን የአባቱ ሕልምና ምኞት ወኪል የሆነ ጊታር የተጣለው ደግሞ የምድሪቷን ድንጋይና አፈር እንዲሁም ቆሻሻ ሲረግጡ ኖረው ከተጣሉ አሮጌ ጫማዎች ሥር እንደነበር ስንመለከት፣ ደራሲው በእያንዳንዳችን ሕይወት ውስጥ ሊፈጥር የፈለገው ስነ-ልቦናዊ ጥያቄ ምን ያህል ጥልቅ እንደሆነ ለመገመት ያስችለናል፡፡ የመክብብ ልጅነት ለአባቱ አዲስ ማንነት (እንደእናቱ) ለመፍጠር የሚውገረገር ዓይነት ሳይሆን የተደበቀውንና የተሸነፈ የሚመስለውን የቀድሞ ሕልምና ምኞቱን እንደ አዲስ ነፍስ ሲዘራበት ለመመልከት የሚጓጓ ማንነትን የተላበሰ ነው፡፡ ከቆሻሻና ከተጣለ የእግር መሸፈኛ ሥር የአባቱን “ራዕይ” ሲጐትት ግን ስለዚያ የአባቱ ራዕይ የሚያውቀው አልነበረም ወይም ዘንግቶታል። ለአባቱ ደግሞ “ራዕዩ” የፍርሃትና የስጋቱ ምንጭ ነበር፡፡ (ገፅ 39-40)
ያለፈው ትውልድና ዘመን በኑሮ ጥያቄም ይሁን በባህልና እምነት ወግ ተሸንፎ የጣለውን የማንነት ፈለግ የአዲሱ ዘመንና ትውልድ ወኪል ሆኖ የቀረበልን መክብብ፤ በፍለጋው መሰማራት ብቻ ሳይሆን ለራሱ ማንነትም ፈለጉን ተከትሎ በመጓዝ ምላሽ እንዲሰጥ ጥያቄውን አሸክሞ ደራሲው ወደ አዲስ መንደር፣ ማኅበረሰብና ሕይወት ይከተዋል፡፡
መክብብ የማንነቱን ስነ ልቦና የቀረፁት ቤተሰብ፣ ማኅበረሰብና በተለይም አብሮ አደግ ጓደኞቹ በአዲሱ የሞጆ ሕይወቱ እንደ ቀላል የሚረሱና የሚጣሉ እንዳልሆኑ ስንመለከት ከላይ አስቀድመን የጠቀስነውን የ“Postmodernism” የአፃፃፍ ፈለግ ደራሲው በሚገባ እንደተከተለ የሚያስረግጥልን ይሆናል፡፡ ከግንፍሌው የቤተሰቡ የድህነትና የመከራ ሕይወት በመነሣት፣ በሞጆ የምቾትና የደስታ ኑሮ በአክስቱ ቤት የተቀበለው መክብብ የምናይበት ለውጥ የስነ-ልቦና ወይም የአስተሳሰብ ሳይሆን የሥጋ ብቻ ሆኖ ይቀራል፡፡ በ“Postmodernism” የአፃፃፍ ፈለግ አንዱ የደራሲ ትልቁ አቅም ሆኖ የሚቆጠረው በገፀ-ባህርያቱ እምነት፣ ፍልስፍና፣ አስተሳሰብ፣ አቋም … ውስጥ ዘልቆ በመግባት ማሳየት እንጂ ድህነት በሀብት፣ ክህደት በእምነት፣ ጥላቻ በፍቅር … የሚሸነፍበትን ውጫዊ ዓለም መፍጠር አይደለም፡፡ በዚህ ረገድ ደራሲው የተዋጣ ሥራዉን ለአንባቢ ማቅረቡን መመስከር የሚያስችሉ በርካታ ማስረጃዎች ማምጣት ይቻላል፡፡
ለምሳሌ በግንፍሌ ያለፈበት የድህነት ሕይወት መክብብን በሞጆ አልጠበቀውም፡፡ ነገር ግን የተቀማጠለ ኑሮው የማንነት ፍለጋውን የማስረሳት አቅም ደግሞ አላገኘም፡፡ በልጅነቱ ደሀና ድህነትን አስመልክቶ የነበረው አስተሳሰብና ጥያቄን በሞጆም ተሸክሞት ይዞራል፡፡ በልጅነቱ ከአባቱ የወረሰው ድብድብ ያለመፍራት ወኔና ድፍረቱን በግንፍሌ ሜዳ በጋሙዳ ላይ እንዳስመሰከረው፣ በሞጆ ደግሞ በረት ገልባጭ ላይ አሳይቶናል፡፡ የኑሮ ለውጡ በመክብብ ስነ-ልቦና ላይ የፈጠረው ይኼ ነው የሚባል ለውጥ በቀላሉ አናገኝም፡፡ በግንፍሌ የምናውቀው መክብብ፤ ፍቅር የሚፈራና የሚያርበተብተው ነበር፡፡ በግንፍሌዋ ንፁህ ላይ ያሳየን የፍቅር ፍርሃት ሞጆ ሲገባ ደግሞ በናፍቆት ሲደግመው እናያለን፡፡ ለመክብብ የኑሮ ምቾት፣ ትምህርት፣ አዲስ መንደርና ጓደኛ የማንነትን ጥያቄ የሚመልሱ ወይም የሚሽሩ አልሆኑለትም፡፡ ለእሱ ከሕይወት የተቀበለው የመፈጠሩ ምክንያት የተጣለውና የወደቀው የአባቱ ምቾትና ሕልም የተዘረጋበትን ፈለግ ተከትሎ መጓዝ ነው፡፡ የመፈጠሩን ሕልም ለትዳሩ መስዋዕት ያደረገው አባቱ፤ በምላሹ ውርደትን ሲቀበል ተመልክቷል። ፍቅርን በመፍራት የተያዘ ስነ-ልቦና ብናይበት አንደነቅም፡፡ መማር ሰርቶ ገንዘብ ከማግኘት ባለፈ ራዕይን ለመፈፀም እንደማያበቃ አሁንም ከአባቱ ማንነት የተረዳው በመሆኑ፣ በትምህርት የራሱን ማንነት እንደማያገኝ ተስፋ የቆረጠ ስነ-ልቦና ቢላበስ የሚገርም አይሆንም፡፡
ራዕይና መክሊትን ለአባቱ ሰጥቶ ደሀ ያደረገውን አምላክም ሕልውናውን ለመቀበል ሲቸገር ብንመለከት በማን-ፈለግ እየተጓዘ እንደሆነ ለመገመት አያስቸግረንም፡፡ በድህነት ሕይወቱ ከአባቱ የወረሰውን የማንነት ፍለጋ በተሻለ የምቾት ሕይወት ውስጥ ራሱን ሲያገኝ አለመዘንጋቱ እንዲሁ የሚጓዝበትን ፈለግ አመላካች ሆኗል፡፡ ደራሲ አለማየሁ ገላጋይ በ “ብርሃን ፈለጐች” ሥራው እነዚህንና ሌሎች የአንድ ዘመንና ትውልድ አባል የሆነ እንደመክብብ ዓይነቱ ሰው የሚያነሳቸውንና የሚያስጨንቁትን ስነ-ልቦናዊ ጥያቄዎች እስከ አእምሮው ጓዳ አብረነው ገብተን እንድንበረብር አድርጐናልና አድናቆታችንን ልንቸረው ይገባል፡፡
ማጠቃለያ
“የብርሃን ፈለጐች” በዓመቱ ከቀረቡልን የስነ-ጽሑፍ ትሩፋቶች ግንባር ቀደሙ ተደርጐ ቢወሰድ የምስማማበት ዋነኛው ምክንያት በአፃፃፍ ፈለጉ (“Postmodernism”) መሠረታዊውን የማኅበረሰብ ባህል፣ እምነት፣ አስተሳሰብ፣ ወግ ሳይለቅ ነገር ግን የትውልዱን መሻት፣ ሕልምና ፍላጐት ከሥጋዊ ስኬት ባሻገር ወደ ልቦናው ጠልቀን እንድንመለከት የመጋበዙ ጉዳይ ነው፡፡ መክብብ ያለፈው ትውልድና ዘመን ወኪል አድርገን በትዝታ የምናስበው ሳይሆን በዛሬው ትውልድ ስነ-ልቦና ውስጥ የተቀበረውን የማንነት ጥያቄ እንድንፈትሽና መልሱን እንደመረዳታችን መጠን እንድንደርስበት ምሳሌአችን ሆኖ የቆመ ሰባኪ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። በእሱ “የብርሃን ፈለጐች” አብረን ስንጓዝ የምንደርስበት እውነትም ወደራስ ማንነት ከመመለስ በላይ ታላቅ ስኬት አለመኖሩን መረዳት ይሆናል፡፡
እናታቸው አንድ ያልሆነች ልጆች - አንዱ “ቁይልኝ!” አንዱ “አንጉችልኝ”
ከዕለታት አንድ ቀን አለቃ ገብረሃና ታመው ቤታቸው አልጋ ላይ ይውላሉ፡፡ አንዲት በሞጥሟጣነቷ በሰፈሩ የምትታወቅ ሴት ልትጠይቃቸው ትመጣለች፡፡
“አለቃ እንደምን አረፈዱ?”
“ደህና ነኝ - እግዚሃር ይመስገን” አሉ አለቃ፡፡
“ሰውኮ አጥብቆም አልነገረኝ፡፡ ለመሆኑ ምንዎትን ነው ያመመዎ?” አለቻቸው፡፡
አለቃ ላለመለስ ፈልገውም ይሁን፣ ግራ ተጋብተው ዝም ይላሉ፡፡ ሴትዮዋ፤
“አለቃ?”
“አቤት?”
“ምነው ዝም አሉኝ? አይመልሱልኝም እንዴ?”
“የዛሬ ህመም ከሚነገር ባይነገር የተሻለ ነው ብዬ ነው፡፡ ብመልስልሽም የምትፈይጅልኝ ነገር የለም፡፡ ህመሜን ላትታመሚልኝ፤ ይሄን አመመኝ ብልሽ ምን ይጠቅመኛል?”
“ቢሆንም፤ እምንዎ ላይ ነው?”
“እኔም አንቺም ያለን ቦታ ላይ ነው”
“አንገትዎ ላይ?”
“አደለም”
“ብብትዎ ውስጥ?”
“አይደለም”
“ንፍፊትዎ ላይ?”
“ደርሰሻል፣ ግን አደለም”
“አይ እንግዲህ፤ እራስዎ ይንገሩኝ?”
“ታፋዬ ላይ ነው ያመመኝ”
“እንዴት አመመዎት?”
“ብጉንጅ ወጥቶብኝ”
“በሞትኩት አለቃ አሁን እንዴት ሊተኙ ነው?”
“አንቺ እንዳልሽ!”
“እርሶ ደግሞ በቁም ነገር ላይ ቀልድ ይጨምራሉ”
“አይ የኔ ቆንጆ እሱም ተጨምሮ በገባሽና እሺ ባልሺኝ”
“እርሶ ጉደኛ ነዎት እናቴ! በሉ እግዜር ምህረቱን ይላክልዎት!” ብላ ለመሄድ ስትነሳ፤
“እንዳፍሽ ያርግልኝ!” አሏት፡፡
ወጥታ ሄደች፡፡ አለቃን የሚያውቅ የሠፈር ሰው ስትወጣ መንገድ አገኛትና፤
“አለቃን ጠይቀሽ መውጣትሽ ነው?”
“አዎን”
“ምን አሉሽ?”
“ብንጉጅ ታፋዬ ላይ አብጦ ነው አሉ፡፡ እግዚአብሔር ይማርዎት አልኳቸው “እንዳፍሽ ያርግልኝ” አሉኝ፡፡
ሰውዬው ከት ብሎ ስቆ፤
“አዬ ቀልደው ብሻል - እንዳፍሽ ሙጥሙጥ ያርግልኝ ማለታቸውኮ ነው” አላት
ሴትዮዋ ተናዳ ወደ አለቃ ተመለሰችና
“እንዴት እንዲህ ይሰድቡኛል አለቃ” ብላ ጠየቀች፡፡
“ለዚህ ነው የመጣሽ? “አይ እህቴ ልሰድብሽ ብፈልግ ኖሮማ ‘ሞጥሟጣ’ እልሽ ነበር” አሏት፡፡
* * *
ህመም ለህመም ካለመደማመጥ ይሰውረን፡፡ የተነገረንን ሳንረዳ በየዋህነት ከመሄድ ያውጣን፡፡ የሚነገርና የማይነገር ህመም ከማማረጥ ያድነን፡፡ ህመማችንን ተጋግዘን ከማዳን በሽሙጥና በወፍ አፍ ስንሸነጋገል፤ በሽታችን ካንሰር - አከል እንደሚሆን ማስተዋል ይገባናል፡፡
የፖለቲካ በሽታችን የጋራ መተሳሰብ ይፈልጋል፡፡ የኢኮኖሚ ድቀታችን የጋራ መደጋገፍ ይጠይቃል፡፡ ማህበራዊና ባህላዊ አኗኗራችን ለውጥ - ተኮርና አፈር - አቀፍ መሆንን ይሻል፡፡ አያሌ ብሔራዊና ሀገራዊ አጀንዳዎች ስላሉን፤ “አውቀን በድፍረት፣ ሳናውቅ በስህተት” የምናሳየው ቸልተኝነት የሀገራችንን ዕድገት እያዘገየን እንደሆን የመገንዘቢያ ሰዓት ነው!!
የቻይና መንግሥት ብሔራዊ ፍልስፍና ይበጀን ከሆነ ለእኛ እንደሚያመች አድርገን የማንወስድበት ምክንያት የለም፡፡ ሶስቱ ጭብጦቹ ሀ) ህግና ደምቦችን (በሶሺዮ - ኢኮኖሚ ደረጃችን አኳያ) በሚገባ ሥራ ላይ ማዋል፤ ለ) ገንዘብን ለሀገር ጥቅም በሚውልበት አኳያ መጠቀም፤ ሐ) ሁነኛ ባለሙያዎችን በሁነኛ ቦታ አስቀምጦ ማሠራት፤ ናቸው፡፡
በተለይ የሶስተኛው መርህ ትርጉም የሚኖረው፤ ሁነኛ ባለሙያ ማለት ቦታው ከሚፈልገው ያነሰ (Underqualified እንዲሉ) ብቻ ሳይሆን፣ ቦታው ከሚፈልገው በላይ (Overqualified እንዲሉ) መሆን፤ የየራሱ አበሳ አለው፡፡ አንዳንዴ “ቦታው ራሱስ አስፈላጊ ነወይ?” ብሎ መጠየቅም ያባት ነው፡፡
ተቃዋሚ ብለን ከፈረጅናቸው ወገኖች ጋር አብሮ የመሥራት እሳቤ ከሀገር ፋይዳው አንፃር መጤን ይኖርበታል፡፡ የሚሞሉት ክፍተቶች/ቀዳዳዎች በርካታ ናቸው፡፡ የአንድ ወገን ርብርቦሽ ብቻ አይሞላቸውም፡፡ እነዚህን ክፍተቶች ሙሉ በሙሉ ለመገላገልና ፍሬ ለማፍራት የሚጠብቀን መንገድ ቀላል አይደለም፡፡ ፍሬ የራሱ ባህሪ አለው፡፡ ያገራችን ገጣሚ እንዳለው
“ፍሬ በስሎ እሚበላው
…ወይ በራሱ ጊዜ ሲወድቅ፣ ወይ እኛ ስንለቅመው ነው!”
መረጃ ለህዝብ መስጠት መፍትሔ ለማግኘት የሚያስችል አጋዥ መሣሪያ ነው፡፡ መብራት ሲበላሽ ምክንያቱን ለህዝብ መንገር ነው፡፡ ኔት - ዎርክ እምቢ ሲል ምን እንደሚሆን ማንም ለመገመት አያቅተውም፡፡ መግለጽ ነው ችግሩ የደም - ሥሮቹ ይደፋፈናሉ፡፡ ሥራዬ ብሎ አትኩሮ ማየት ይገባል፡፡ ደህና መሥመር የያዙ ጉዞዎች ይወለጋገዳሉ፡፡ ሲከፋም ይበጣጠሱና ወደኋላ ይመልሱናል! የውስጥ ደም - መፍሰስ (Internal - bleeding) እያለ አዲስ ደም - ቅያሬ (New - blood - injection) ሙሉ በሙሉ ይሠራል ብሎ ማሰብ ቢያንስ የዋህነት ነው!
የህዝብ ድጋፍ ወሳኝ መሆኑን ምንጊዜም መዘንጋት አይገባም፡፡ ይሄን ለማየት የኢትዮጵያ ህዝብ ለስፖርተኞቻችን የሚሰጠውን ማበረታታትና ጭንቀት ማስተዋል ነው፡፡ በአንድ ጀንበር ሳይሆን የረዥም ጊዜ ውጣ ውረዱን አስቦ፣ ታግሶ፣ ሆደ - ሰፊ ሆኖ፣ ሌሎች የሚሉትን በጥሞና አድምጦ መሄድ ውጤት ላይ እንደሚያደርስ መገንዘብ ዋና ነገር የፖለቲካውን መድረክና የኳሱን ሜዳ አመሳስሎና አነፃጽሮ መሄድ አገራችንን ለመለወጥ በር ከፋች መንገድ ነው፡፡
ሕግ፣ ዳኛ፣ አራጋቢ፣ ተመልካች፣ አሰልጣኝ…አዳጊና ወራጅ ቀጠና …የፌዴሬሽን ሥርዓት… ልብ ላለ - መሬት ለረገጠ ለውጥ - ማስገንዘቢያዎች ናቸው!
(ለብሔራዊ ቡድናችን ቀናውን ሁሉ እንመኛለን!)
ሀገራዊ በሆነ ጉዳይ ፍፁም አንድነቱን ይሰጠን ዘንድ ዐይናችንን ከፍተን የሀገርን ደግ እንይ! አለበለዚያ፤ “እናታቸው አንድ ያልሆነች ልጆች - አንዱ “ቁይልኝ”፣ አንዱ “አንጉችልኝ” ይሆናል፡፡ ከዚህም ይሠውረን!
በውኃ ላይ የታነፀው ይምርሐነ ክርስቶስ የ“ወርልድ ሞኑመንትስ ፈንድ የ2014 ተመራጭ መካነ ቅርስ” ሆነ
ከዛጒዌ ስመ ጥር ነገሥታት አንዱ በነበሩት በንጉሥ ይምርሐነ ክርስቶስ ዘመነ መንግሥት ከተሠሩት ኪነ ሕንጻዎች አንዱ የኾነው ይምርሐነ ክርስቶስ፤ የወርልድ ሞኑመንትስ ፈንድ የ2014 ተተኳሪ መካነ ቅርስ (2014 World Monuments Watch) ሆኖ ተመረጠ፡፡
ፈንዱ መስከረም 28 ቀን 2006 ዓ.ም. ዋና ጽ/ቤቱ በሚገኝበት በኒው ዮርክ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቀው÷ እ.አ.አ በ2014 ዓለም በትኩረት ሊያውቃቸው፣ ሊጠብቃቸውና ለትውልድ ሊያስተላለፍላቸው ይገባል ካላቸው የ41 አገሮች ባህላዊና ታሪካዊ ቅርሶች መካከል ልዩ የኪነ ሕንጻ ጥበብ የሚታይበት የይምርሐነ ክርስቶስ መካነ ቅርስ አንዱ ኾኖ መመረጡ ተገልጧል፡፡
“ወርልድ ሞኑመንትስ ዎች” በተሰኘው ፕሮግራሙ ለአደጋ የተጋለጡና ዝነኛ የቱሪስት መስሕብ የኾኑ ታሪካዊ ኪነ ሕንፃዎችንና ባህላዊ መካነ ቅርሶችን በማስተዋወቅ፣ የቴክኒክና የገንዘብ ድጋፍ በመለገሥ ዘመን ተሻጋሪ እንዲኾኑ ዓለም አቀፍ ቅስቀሳ የሚያደርገው ወርልድ ሞኑመንትስ ፈንድ፣ በዝርዝሩ ያካተታቸው የተመረጡ ቅርሶች ዓለም አቀፍ ትኩረት እንዲያገኙና በአግባቡ እንዲጠበቁ በዓለም ዙሪያ ያሉ ባለድርሻ አካላት ሁሉ አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ጥሪውን አስተላልፏል፡፡
በዩኔስኮ የተመዘገቡ በርካታ የዓለም ቅርሶች የፈንዱ ተጠቃሚ ሲኾኑ ከእኒህም መካከል ፈንዱ እ.ኤ.አ በ1966 ሲቋቋም የክብካቤና ድጋፍ ሥራውን የጀመረባቸው የቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ መቅደስ እንደሚገኙበት በመግለጫው ተመልክቷል።
የይምርሐነ ክርስቶስ መካነ ቅርስ በዓለም አቀፍ ፈንዱ ተመራጭ እንዲኾን በመጠቆምና ለምርጫው የሚያግዙ መረጃዎችን በማቅረብ ከፍተኛ ሚና መጫወቱን ለአዲስ አድማስ የገለጸው የኢትዮጵያ ታሪካዊ ቅርሶች ክብካቤና ልማት ማኅበር፤ መካነ ቅርሱ የ2014 የወርልድ ሞኑመንትስ ፈንድ ተመራጭ መኾኑ ኪነ ሕንጻውን የበለጠ ለማስተዋወቅና ለማልማት ዕድል ይሰጣል ብሏል፡፡ ቅርሶች ዘላቂ ምጣኔ ሀብታዊና ማኅበራዊ አገልግሎት ያበረክቱ ዘንድ ራእይ የሰነቀው ሀገር በቀል ማኅበሩን ጨምሮ በቅርስ ክብካቤ ዙሪያ የሚሠሩ ባለሞያዎች፣ የሥራ ሓላፊዎችና ድርጅቶች ከሚመለከታቸው የብዙኀን መገናኛና ሌሎች አካላት ጋራ በመተባበር እንንዲንቀሳቀሱም ምቹ ኹኔታ ይፈጥራል ተብሏል፡
ከዘጠኝ መቶ ዓመታት በፊት በሰሜን ወሎ ወግረ ስኂን በሚባል ቦታ ሰፊና ግርማ ሞገስ ባለው የተፈጥሮ ዋሻ ውስጥ በውኃ ላይ እንደታነፀ የሚታመነውና ልዩ የኪነ ሕንፃ ጥበብ የሚታይበት ይምርሐ ክርስቶስ÷ በአገራችን ረጅም ዕድሜ ያስቆጠረውን የቤተ መንግሥት ሕንጻ፣ በድንቅ ጥንታዊ ሥዕሎችና ንድፎች ያሸበረቀ ቤተ መቅደስ አሰናኝቶ የያዘ መካነ ቅርስ ነው፡፡ በተጨማሪም ልዩ ልዩ ተንቀሳቃሽ ቅርሶች፣ ያልፈረሱና ዕድሜ ጠገብ የሰው ዐፅሞች፣ የሀገር በቀል ዕፀዋት ጥቅጥቅ ደንና ማራኪ መልክአ ምድር የሚገኙበት ነው፡፡
ለዓለም ኮከብ አትሌቶች ምርጫ ሶስት ኢትዮጵያውያን ታጭተዋል
ዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር (አይ.ኤ.ኤ.ኤፍ) በሳምንቱ አጋማሽ ላይ ለ2013 የዓለም ኮከብ አትሌቶች ምርጫ በሁለቱም ፆታዎች የሚፎካከሩ እጩዎችን ስም ሲያስታውቅ ከእጩዎቹ መካከል ሶስት የኢትዮጵያውያን አትሌቶች ተካትተዋል፡፡ መሃመድ አማን ፤ ጥሩነሽ ዲባባ እና መሠረት ደፋር ናቸው፡፡ አትሌት መሃመድ አማን በ800 ሜትር የዓለም ሻምፒዮን ከመሆኑም በላይ በርቀቱ የዳይመንድ ሊግ አሸናፊ ለመሆን የበቃ እና በዓመቱ ካደረጋቸው 11 ውድድሮች አስሩን ያሸነፈ ነው፡፡ ዘንድሮ በ5ሺ ሜትር የዓለም ሻምፒዮን ለመሆን የበቃችው አትሌት መሰረት ደፋር በርቀቱ የዳይመንድ ሊግ አሸናፊ እንደሆነች ሲታወቅ በ3ሺ ሜትር እና በ10ሺ ሜትር የዓመቱን ፈጣን ሰዓት በማስመዝገብ ተሳክቶላታል፡፡ አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ በበኩሏ በ10ሺ ሜትር የዓለም ሻምፒዮን ከመሆኗም በላይ በ10 ኪሎሜትር የዓመቱን ፈጣን ሰዓት አስመዝግባለች፡፡
በኮከብ አትሌት ምርጫው በሁለቱም ፆታዎች ለመጨረሻ ምዕራፍ የሚደርሱትን ሶስት እጩ ተፎካካሪዎች ለመለየት በድረገፅ በሚሰጥ የድጋፍ ድምፅ ይሰራል፡፡ የዓለም የአትሌቲክስ ማህበረሰብን በማሳተፍ የሚከናወነው የምርጫ ሂደት ከተጀመረ ሶስት ቀን አልፎታል፡፡ ለሶስቱ የኢትዮጵያ ምርጥ አትሌቶች በዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ድረገፅ (www.iaaf.org) አስፈላጊ የሆነውን ድምፅ በመስጠት ድጋፍ ሊሰጥ ይቻላል፡፡ እድሉ ለሚቀጥሉት ሶስት ሳምንታት ክፍት ሆኖ ይቆያል፡፡ በዓለም ኮከብ አትሌቶች ምርጫ ታሪክ ሶስት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ተሸላሚ ሆነው ያውቃሉ፡፡ እነሱም በ1998 እኤአ የተሸለመው ኃይሌ ገብረስላሴ፤ በ2004 እና በ2005 እኤአ አከታትሎ ያሸነፈው ቀነኒሳ በቀለ እና በ2007 እኤአ ላይ የተመረጠችው መሰረት ደፋር ናቸው፡፡
እንግሊዝኛና አስተርጓሚ
...በጊዜው ያጋጥመን ከነበረው አስቸጋሪ ሁኔታ አንዱ የአስተርጓሚዎች በእንግሊዝኛ ቋንቋ ያለመብሰል ነው፤ ቀደም ብዬ እንዳስረዳሁት ከስንዴ፣ እንክርዳድ እንደማይታጣ ከአስተርጓሚዎችም መካከል አንዳንድ ደካሞች (ሞራለ ቢሶች) ሲኖሩ አብዛኛዎቹ ግን፤ በተማሩት የተጠቀሙበትና ጥሩ ኢትዮጵያዊነታቸውን ያሳወቁበት ስለሆኑ ውለታቸው የሚዘነጋ አይደለም፡፡ በዚህ ላይ ልገልፀው የፈለግሁት ግን በጊዜው እንግሊዝኛ እናውቃለን፣ ብለው በአስተርጓሚነት የተቀጠሩት ብዙዎች ሲሆኑ ባለችሎታ ሆነው የተገኙት ግን ጥቂቶች ነበሩ፡፡ ይሁን እንጂ ለመግደርደርና ዐዋቂ ናቸው ለመባል ያህል ባላቸው ቁንጽል ዕውቀት እንግሊዝኛ እናውቃለን የሚሉና በተለይ ከዚህ እንደሚከተለው፤
…የስ ሰር (YES SIR)፣ ኦል ራይት ሰር (ALL RIGHT SIR)፣ ቬርይ ጉድ ሰር (VERY GOOD SIR) በሚለው አነጋገር ብቻ አዘውትረው በመጠቀም የሚብለጠለጡም ነበሩ፡፡
እነዚህ አስተርጓሚዎች ነን የሚሉት ሰዎች፤ በነዚህ ሦስት ቃላቶች አዘውትረው የሚጠቀሙበት ምክንያት ሁለት ነው ይኸውም አንደኛው በተመልካች ዘንድ እንግሊዝኛ ያለመቻላቸው እንዳይታወቅባቸው ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ እንግሊዞቹ ለሚያቀርቡላቸው የቃል ጥያቄ ወይንም ለሚሰጧቸው ትእዛዝ ተቃዋሚ መልስ የሰጡ እንደሆነ (ኖ ሰር NO SIR) ያሉ እንደሆን ይህን ሊሉ የቻሉበት (የተቃወሙበትን) ምክንያት በእንግሊዝኛ አብራርቶ የማስረዳት ግዴታ ስለሚኖርባቸው፣ ከዚህ ሁሉ ጣጣ ለመራቅ የሚሻለው ነገሩ ቢገባቸውም ባይገባቸውም ጐላ ባለ ድምጽ የስ ሰር፤ ኦል ራይት ሰር ቬርይ ጉድ ሰር” ብሎ ዘወር ማለቱ የሚጠቅም ዘዴ መሆኑን ስላመኑበት ነው፡፡
ይሁን እንጂ ይህን የመሳሰሉት በእንግሊዝኛ ንግግር ደካማ የሆኑት አስተርጓሚዎች ትክክለኛ የሆነውን የሥራ ጉዳይ ስለሚመለከት ሁኔታ እንግሊዝኛውን ወደ አማርኛ ወይንም አማርኛውን ወደ እንግሊዝኛ በሚያስተረጉሙበት ጊዜ ንግግሩ አይሳካላቸው እንጂ “ትንሽ ዕውቀት መርዝ ነው” እንደተባለውና “የታሪክ ማስታወሻ” በተባለው መጽሐፍ በገጽ ፬፻፵ እንደተመለከተው ያልሆነውን ሆኗል ያልተባለውን ተብሏል በማለት፣ እንግሊዞቹንና እንግሊዝኛ የማናውቀውን ለማጋጨት፣ ባንዳንድ ሁኔታዎች ለማወናበድ አስችሏቸዋል፡፡ ከዚህ በስተቀር አማርኛና እንግሊዝኛ ቋንቋ ወዲያና ወዲህ እየሆኑ አንዳንድ አስፈላጊ ጉዳዮች በሚተረጐሙበትም ጊዜ ብዙ የሚያስቁ ሁኔታዎችን አድርሰው እንደነበረ በሚከተለው መስመር እገልጻለሁ፡፡
1ኛ፤ ሰዓት እላፊ (CURFEU) በሐምሌ ወር ፲፱፻፴፫ ዓ.ም አሥራ አንድ ሰዎች በሰዓት እላፊ ተይዘው 2ኛ ፖሊስ ጣቢያ ታስረው ካደሩ በኋላ በጊዜው ለነበረው የኦ.ኢ.ቲ.ኤ ፍርድ ቤት ቀርበው በሚጠየቁበት ጊዜ፣ የፍርድ ቤቱ ዳኛ (እንግሊዛዊው) የተከሰሱበትን የነጋሪት ጋዜጣ አዋጅ ተመልክተው “የተከሰሳችሁት ስለሰዓት እላፊ የወጣውን ዐዋጅ ተላልፋችሁ በመገኘታችሁ ነው፤ ጥፋተኛ ናችሁ አይደላችሁም?” ሲሉ ለተከሳሾቹ ጥያቄ ያቀርባሉ፡፡ አስተርጓሚውም ኬርፊው (CURFEU) የሚለውን የእንግሊዝኛ ቃል “ኩርፊያ” ብሎ በመተርጐም “እናንተ በኩርፊያ ወንጀል ተከሳችኋል፤ ጥፋተኞች ናችሁ አይደላችሁም?” ሲል በማስተርጐሙ፣ በአደባባዩ የነበሩት እንግሊዝኛ ቋንቋ የሚያውቁትና የማያውቁትም (ተከሣሾቹ) ጭምር አደባባዩን በሳቅ ከሞሉት በኋላ፣ ካሥራ አንዱ ተከሳሾች አንደኛው ባነጋገሩ ዝግ ያለው የባላገር ሰው ላስተርጓሚው በሰጠው መልስ “እኛ የታሰርነው በሰዓት እላፊ እንጂ በኩርፊያ አይደለም ደግሞስ ከዚያን በፊት የማንተዋወቅ ሰዎች በምን ተገናኝተን እንኳረፋለን፤” ጣሊያንም የፈጀን እርስዎን በመሰሉ አስተርጓሚዎች አሳሳችነት ነውና ይልቁንስ ነገሩን የጣሩልን” ሲል ስለተናገረ፣ ባደባባዩ ያለውን ሕዝብ ብቻ ሳይሆን እንግሊዛዊውን ዳኛ ጭምር አስቋቸዋል፡፡
2ኛ፤ የ2ኛ ፖሊስ ጣቢያ አዛዥ የሆኑት እንግሊዛዊ መኮንን በሰልፍ አቁመውን “ከሦስት ቀን በኋላ ግርማዊ ጃንሆይ ይገባሉ፤ በጥበቃው በኩል ጥንቃቄ ማድረግ አለባችሁ፤ ስለዚህም ጉዳይ ከበላይ መሥሪያ ቤት ፕሮግራም ይደርሰን ይሆናል፤ ያለበለዚያም በነገው ቀን በአውሮፕላን ወረቀት ስለሚጣል ትክክለኛውን ከዚያ መረዳት ይቻላል” ሲሉ ፀጥታውን ማስከበር አለባችሁ፤ ይህን ባትፈጽሙ አውሮፕላን ቦምብ ይጥልባችኋል ብሎ በማስተርጐሙ ሁላችንም በነገሩ ከተደናገጥንና ጥቂት ካሰብን በኋላ፣ ምንም እንግሊዝኛ ባንችል አስተርጓሚው የተሳሳተ መሆኑ ስለገባን ሁላችንም ስቀንበታል፤ ስህተቱን የተረዱት የጣቢያው አዛዥም ገስፀውታል፡፡
ምንጭ (በብርጋዲየር ጄነራል ሞገስ በየነ
“ጊዜ እና ፖሊስ” በሚል ርዕስ ከተዘጋጀ መጽሐፍ የተቀነጨበ፤ ከ1935-1963)
የሞዴስ መዘዝ
ሞዴስ ወንዶችንም ለሞት ሊያበቃ ለሚችል በሽታ ይዳርጋል
ሴቶች የወር አበባቸውን የሚያዩበት ዕድሜ በአኗኗር ሁኔታ፣ በአመጋገብና በአካባቢያዊ ሁኔታዎች ሊለያይ የሚችል ቢሆንም በአብዛኛው ከ14 ዓመት ዕድሜያቸው ጀምሮ የወር አበባቸውን ያያሉ፡፡
ምቾት ባለበት አኗኗር ውስጥ የሚያድጉ ልጆች፤ ከዚህ ዕድሜ ቀደም ብለው የወር አበባቸውን ሊያዩ ይችላሉ፡፡ ይህ ቀደም ባሉት ዓመታት የነበረው የወር አበባ ማያ የዕድሜ ገደብ ዛሬ ዛሬ እየወረደ መጥቶ ታዳጊ ሴት ህፃናቱ፣ በዘጠኝና በአስር ዓመት ዕድሜያቸው ላይ የወር አበባ ማየታቸው እየተለመደ መጥቷል፡፡ ህፃናቱ የሰውነታቸው ዕድገት ፈጣን እንደመሆኑ ሁሉ የውስጣዊ አካላቸው ዕድገትና ለውጥ እንዲሁ ፈጣን ነው፡፡ እነዚህ ታዳጊ ህፃናት የወር አበባ ምንነትና ሒደቱ በሰውነታቸው ላይ ስለሚያስከትለው ተፈጥሮአዊ ለውጥ ግንዛቤ ባላገኙበት ዕድሜያቸው ላይ ይህ ክስተት ሲገጥማቸው ለከፍተኛ ድንጋጤና የሥነልቡና ጫና መዳረጋቸው የማይቀር ነው፡፡
ችግሩ እንዳይከሰት ቤተሰብ በተለይም እናቶች ለሴት ታዳጊ ልጆቻቸው ስለወር አበባ ምንነትና የወር አበባ በሚመጣ ጊዜ ሊደረጉ ስለሚገባቸው ጥንቃቄዎች እንዲሁም በወር አበባ ወቅት የግል ንጽህናን በአግባቡ መጠበቅ እጅግ አስፈላጊነ መሆኑን በጊዜ ማስተማርና ልጆቻቸውን ማዘጋጀት እንደሚኖርባቸው የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ። ልጆቹ ያላወቁትና ይከሰትብኛል ብለው ያላሰቡት ነገር ሲገጥማቸው ከፍተኛ ድንጋጤና የሥነልቡና ችግር እንደሚደርስባቸውም ባለሙያዎቹ ይገልፃሉ።
ቀደም ባሉት ዘመናት እናቶች የወር አበባቸው በሚመጣበት ጊዜ ከነጠላና አሮጌ ቀሚሶች ቅዳጅ እየቆረጡ በሚያዘጋጇቸው ጨርቆች የወር አበባቸውን እየተቀበሉ ንጽህናቸውን ይጠብቁ ነበር። ጨርቆቹ እየታጠቡ ከአንድ ጊዜ በላይ አገልግሎት እንዲሰጡ ይደረጉ ነበር፡፡ አሁንም ቢሆን በአገራችን በርካታ አካባቢዎች ጥቅም ላይ እየዋለ ነው። ሴቶች የወር አበባቸው በሚመጣበት ወቅት የሚጠቀሙበትና ንጽህናቸውን የሚጠብቁበት መንገድ በአብዛኛው ባህላዊና ተለምዶአዊ ነው፡፡
ዘመናዊነቱ እየተስፋፋ፣ ቴክኖሎጂው እያደገ ሲሄድ ለሴቶች የወር አበባ መቀበያነት የሚያገለግሉና የሴቶቹና ንጽህና የሚጠብቁ ሞዴሶች ተሰርተው ገበያ ላይ መዋል ጀመሩ፡፡ የእነዚህ ምርቶች ገበያ ላይ መዋል ሴቶች በወር አበባ ወቅት የሚሰማቸውን የህመም እና ያለመመቸት ስሜት በእጅጉ ከመቀነሱ ባሻገር፣ ንጽህናቸው በአግባቡ ባልተጠበቁ ጨርቆች ሳቢያ የሚከሰቱ ችግሮችን ለማስቀረት አስችሏል፡፡
በፋብሪካ ደረጃ እየተመረቱ በጥቅም ላይ የሚውሉ ዘመናዊ የወር አበባ መቀበያ ፓዶችም ሆኑ የወር አበባ መቀበያ እራፊ ጨርቆቹ እጅግ አደገኛ የሆኑ ችግሮችን እንደሚያስከትሉ ጥናቶች ጠቁመዋል፡፡ “ጆርናል ኦፍ ኢንፌክሽን ዲዚዝ” ይፋ ባደረገው መረጃ፤ በወር አበባ መቀበያ ሞዴሶች ሳቢያ የሚራቡት አደገኛ ባክቴሪያዎች ከሴቶችም አልፈው ወንዶችን ለህልፈተ ህይወት እየዳረጉ ነው፡፡ በወር አበባ ወቅት በሚፈሰው ደም ውስጥ ጉሉኮስን የመሰሉ ለባክቴሪያ መራባት እጅግ አስፈላጊና ምቹ የሆኑ ነገሮች ይገኛሉ፡፡ እነዚህም በወር አበባ መቀበያ ሞዴስ ውስጥ በመግባት በቀላሉ ለመራባትና ለመሰራጨት ይችላሉ፡፡
ስታፈሎከሰስ የተባሉት እጅግ አደገኛ ችግር ሊያስከትል ለሚችል በሽታ ምክንያት የሚሆኑት ባክቴሪያዎች “ቶክሲክ ሽክ ሲንድረም” የተባለና እስከ ሞት ሊያደርስ የሚችል አደገኛ የፍትወተ አካል ኢንፌክሽን ይፈጥራሉ፡፡ በአብዛኛው ችግሩ የሚከሰተው ረዘም ላለ ጊዜ ጥቅም ላይ በሚውሉ (በወር አበባ ወቅት በሴቷ ብልት ላይ ረዥም ሰዓት በሚቆዩ) ሞዴሶች ወይንም ንጽህናቸው በአግባቡ ባልተጠበቀና በተደጋጋሚ በጥቅም ላይ በሚውሉ የወር አበባ መቀበያ ጨርቆች አማካኝነት መሆኑንም መረጃ አመልክቷል፡፡ ችግሩን እጅግ የከፋ የሚያደርገው ሌላው ጉዳይ፤ ይህ በሞዴሱ ሳቢያ የሚከሰተው አደገኛ በሽታ ለወንዶችም መትረፉ ነው፡፡ የችግሩ ሰለባ ከሆነች ሴት ጋር የግብረ ስጋ ግንኙነት የፈፀሙ ወንዶችም “በቶክሲክ ሾክ ሲንድረም” መጠቃታቸው አይቀሬ ነው፡፡ ችግሩ በወቅቱ ታውቆ ተገቢው ህክምና ካልተደረገለትም ለሞት ሊያደርስ እንደሚችል መረጃው አመልክቷል።
የወር አበባ መቀበያ ሞዴሶች በሴቷ ሰውነት ላይ መቆየት የሚገባቸው ከ3-4 ሰዓታት መሆን ይገባዋል ያለው መረጃው፤ ከዚህ ለበለጠ ጊዜ የሚቆይ ከሆነ ለባክቴሪያ መራቢያ ምቹ ሁኔታዎች ስለሚፈጠሩ ይኸው ስታፍሎኮከስ ኦርስ የተባለው ባክቴሪያ ይራባና ”ቶክሲክ ሾክ ሲንድረም” የተባለውን አደገኛ በሽታ ሊያስከትል እንደሚችል ገልጿል፡፡
ይህ እጅግ አደገኛና በግብረሥጋ ግንኙነት ሳቢያ ከአንዱ ወደ አንዱ የሚተላለፍ በሽታ ከመከሰቱ በፊት ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባና ሴቶች በወር አበባ ወቅት የሚጠቀሙበትን ሞዴስ በንጽህና ሊጠቀሙበት እንደሚገባ “ጆርናል ኦፍ ኢንፌክሽን ዲዚዝ” አሳስቧል።
ኢትዮጵያዊው ምሁር በሩሲያ ፕሮፌሰር ዘነበ ክንፉ
“በህይወት እስካለህ ደግ መስራት ጥሩ ነው”
በሆለታ ተወልደው ያደጉት አቶ ዘነበ ክንፉ ታፈሰ፣ ለትምህርት ወደ ራሽያ የሄዱት የዛሬ 22 ዓመት ገደማ ነው፡፡ ከልጅነታቸው ጀምሮ የፅሁፍ ፍቅር ነበራቸው፡፡ ነፃ የትምህርት እድል አግኝተው ወደ ሩሲያ የሄዱትም ኢንተርናሽናል ጆርናሊዝም
(ዓለም አቀፍ ጋዜጠኝነት) ለመማር ነበር፡፡
ትምህርታቸውን እስከ ዶክትሬት ደረጃ የተማሩት ፕሮፌሰር ዘነበ፤ በራሽያ ዩኒቨርስቲ ውስጥ እያስተማሩ ይገኛሉ፡፡ “ቢዝነስ አፍሪካ” የተሰኘ መፅሄት መስራችና ባለቤትም ናቸው፡፡ ጋዜጠኛ ግሩም ሠይፉ ለ14ኛው የዓለም ኦሎምፒክ ሻምፒዮን ሩሲያ በሄደ ጊዜ በሞስኮ ከተማ አግኝቶ አነጋግሯቸዋል፡፡ ስለሆለታ ትዝታቸው፣ ስለ ፅሁፍ ፍቅራቸው፣ ስለትምህርታቸውና ሙያቸው በስፋት አውግተዋል፡፡ እነሆ፡-
ጋዜጠኝነትን የተማሩት ራሽያ ቢሆንም ለጋዜጣ መፃፍ የጀመሩት ሆለታ እያሉ ነበር ሲባል ሰምቻለሁ…
እውነት ነው፡፡ ገና ታዳጊ ሳለሁ ጀምሮ እፅፍ ነበር፡፡ ስልክ አምባ እና ዜኒት የሚሉ የብዕር ስሞች ነበሩኝ፡፡ በእነዚህ ስሞች ፅሁፎቼን ለተለያዩ ጋዜጦችና የሬድዮ ፕሮግራሞች እልክ ነበር፡፡ ለመጀመርያ ጊዜ ፅሁፍ የወጣልኝ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ነው፡፡ በኋላ ለሬድዮ ፕሮግራሞችና ለ“ሰርቶ አደር” ጋዜጣ ሁሉ መፃፍ ጀመርኩ፡፡ ፅሁፎቼ በማህበራዊ ችግሮች ዙርያ የሚያተኩሩ ነበሩ። አዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ የወጣውን የመጀመሪያ ፅሁፌን አራተኛ ክፍል ሆኜ ነው የፃፍኩት፡፡
ስለ እድገትዎ ይንገሩኝ…
የተወለድኩትና ያደግሁት ከአዲስ አበባ ወጣ ብላ በምትገኘው ሆለታ ከተማ ነው፡፡ በ1968 አካባቢ በከተማዋ ድርቅ ተከሰተ፡፡ የከተማው ነዋሪ ውሃ ፍለጋ አራትና አምስት ኪሎ ሜትር ይጓዝ ነበር፡፡ እኔም ከእናቴ ጋር ሄጄ ይህን ችግር አየሁ፡፡ የፃፍኩት ነገር … ለምንድነው ባለስልጣኖች የውሃ ጉድጓድ የማያስቆፍሩት የሚል ሃሳብ ይዟል፡፡ በጣም አጭር ፅሁፍ ነው፡፡ ግማሽ ገፅም አይሆንም፡፡ “የውሃ እጥረትን ለመፍታት የአካባቢው አስተዳደር መንቀሳቀስ አለበት” በሚል ነው የሚቋጨው፡፡ ፅሁፉን በጋዜጣው አድራሻ በፖስታ ቤት ላክሁት፡፡ ብዙም ሳይቆይ ነበር ጋዜጣው ላይ የወጣው፡፡
ከቤታችን ደጃፍ አንድ ባለሱቅ ነበር፡፡ መሃመድ ነው ስሙ፡፡ ስኳር ለመግዛት ወደሱ ሱቅ ስሄድ “ያንተ ስም ነው እንዴ እዚህ ጋዜጣ ላይ የወጣው?” ብሎ አሳየኝ፡፡ ለማንም እንዳትናገር ብሎ ፅሁፌ ያለበትን የጋዜጣውን ገፅ በ10 ሳንቲም ሸጠልኝ፡፡ አየህ የሆለታ እርሻ ምርምር ኢንስቲትዩት ከቤታችን አቅራቢያ ነበር፡፡ በዚያ አትክልት በሚያፈሉበት ስፍራ የውሃ ጉድጓድ ቆፍረው ውሃ በማውጣት ይጠቀሙ ነበር። እዚያ ግቢ ውስጥ ውሃ አለ፡፡ እናቴ እና የከተማው ህዝብ ግን ረጅም ርቀት እየተጓዙ ውሃ ይቀዱ ነበር። የሚገርምህ ፅሁፉ ወጥቶ ብዙም ሳይቆይ ለሆለታ ከተማ ነዋሪ ውሃ ለማሰራጨት የጉድጓድ ቁፋሮ እንዲሰራ ባለስልጣኖች አዘዙ፡፡ ጉድጓድ ተቆፍሮ ውሃ ከወጣ በኋላ፣ ባንቧ ተሰርቶ ከተማው መሃል ውሃ ተገኘ፡፡ እኔም በዚሁ የውሃ ጉድጓድ፣ ውሃ ሻጭ ሆኜ መስራት ቻልኩ፡፡
ከልጅነትዎ አንስቶ ፀሐፊ የመሆን ፍላጐት ያሳደረብዎ ምንድነው?
እንደነገርኩህ ያኔ ገና አራተኛ ክፍል ብሆንም ብዙ አነብ ነበር፡፡ እቤታችን የተለያዩ ጋዜጦች ይመጣሉ፡፡ ጀርመናውያን ጐረቤቶች ስለነበሩን የእንግሊዝኛ ህትመቶችንም የማንበብ ዕድል ነበረኝ፡፡ የስነፅሁፍ ዝንባሌዬ ከፍተኛ ነበር፡፡ አንድ ጊዜ በአንድ ምሽት ባለ16 ገፅ ደብተር ሙሉ ግጥም ፅፌ ለአማርኛ አስተማሪያችን አሳየኋት፡፡ “ይሄ ግጥም የሚሆን አይደለም” ብላ አሳፈረችኝ። ግጥሙ ስለ ምን እንደሆነ ትዝ አይለኝም፡፡ የሆኖ ሆኖ ግጥሙን ትቼ ጋዜጠኛ ለመሆን አስብ ጀመር። ያኔ በጣም ከምወዳቸው ጋዜጦች አንዱ “ፖሊስ እና ርምጃው” ነበር፡፡ በጣም ቆንጆ ጋዜጣ ነው፡፡ አብዮት የተጀመረበት ጊዜ ስለነበር ብዙ ጋዜጦች እና መፅሄቶች ይወጡ ነበር፡፡ ሆለታ ከተማ ውስጥ የእጩ መኮንኖች ማሰልጠኛ፣ የእርሻ ምርምር ኢንስቲትዩት እና ሌሎችም ተቋማት ነበሩ፡፡ በርካታ የውጭ አገር ዜጎችም ነበሩ፡፡ በዚህ ምክንያት ለመረጃ ቅርብ ነበርን፡፡ አባቴም አልፎ አልፎ ጋዜጦችን፣ መፅሃፍት እና መፅሄቶችን ያመጣልኛል። ሬድዮ እከታተላለሁ። ከተፈጥሮ ተሰጥኦዬ ጋር ይህ ሁሉ ሲጨመር ፀሃፊ ለመሆን ያነሳሳኝ ይመስለኛል፡፡
በወጣትነት ዘመንዎ ሆለታ ምን ትመስል ነበር?
የሆለታ ህዝብ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ነው። ልዩነቱ ሁሉም አይነት ብሄረሰብ የተሰባሰቡባት ከተማ መሆኗ ነው፡፡ ቅድም እንደነገርኩህ ሆለታ የእጩ መኮንኖች ማሰልጠኛ፣ የእርሻ ምርምር ኢንስቲትዩት፤ የመሳሪያ ግምጃ ቤት፤ የሙሉጌታ ቡሊ ቴክኒክ ትምህርት ቤት፤ የሱባ ደን ልማት፣ የወተት ሃብት ልማት… እነዚህ ሁሉ የመንግስት ድርጅቶች ነበሩባት፡፡ በኋላም እነ ሙገር በሆለታ መንገድ ላይ ተሰርተዋል፡፡ በእነዚህ የመንግስት ተቋማት ይሰሩ የነበሩት ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የተሰባሰቡ ናቸው፡፡ ኦሮሞው፣ አማራው፣ ትግሬው… ሁሉም ብሄር ብሄረሰብ ነበር፡፡ አትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆኑ የተለያዩ አገራት የውጭ ዜጎች እንዲሁም በርካታ አፍሪካውያን ነበሩ፡፡
ስራ የጀመርኩት እዚያው ሆለታ ውስጥ ነው፡፡ የመጀመሪያው ስራዬ የተለያዩ ሸቀጦችን መነገድ ነበር፡፡ 9ኛ ክፍል ሆኜ ነው የጀመርኩት። ለወታደሮችም እላላክ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ወደ ውትድርና ገባሁና ለአራት አመታት በአየር ወለድነት ሰለጠንኩ፡፡ በሰሜን እና በሰሜን ምዕራብ ዘምቼ፣ ብዙ ግዳጆችን ፈፅሜአለሁ፡፡ በውትድርና ዘመኔም መፃፉን አልተውኩትም፡፡ የሚገርምህ አንጋፋው ደራሲ በዓሉ ግርማ አለቃዬ ነበር። አስመራ ለሰራዊቱ በሚዘጋጅ “የጀግናው ገድል” የተባለ ጋዜጣ ላይ ፊደል ለቀማ (Proof reading) ስሰራ ማለቴ ነው። ያኔ እንግዲህ 19 አመቴ ነበር፡፡ በሰራዊቱ አባልነቴ ጋዜጣ በማቋቋምና የኪነት ቡድን በመመስረት ፈርቀዳጅ ሚና ተጫውቻለሁ፡፡ የኢትዮጵያ አየር ወለድ በኃይለስላሴ ጊዜ ፈርሶ በደርግ ዘመን በድጋሚ በሁርሶ ተቋቋመ፡፡ ከውትድርና የወጣሁት ወሎ አካባቢ በፓራሹት ስወርድ (ዝናብ ስለነበር) ወድቄ በመጐዳቴ ነው፡፡
ከውትድርና ወጥተው የት ገቡ?
ደቡብ ውስጥ ድርቅ ስለነበር በሻሸመኔ መልሶ ማቋቋም ተቋም ውስጥ ተቀጥሬ መስራት ጀመርኩ። አሁንም መፃፌን አልተውኩም፡፡ ባለኝ ትርፍ ጊዜ ሁሉ እየፃፍኩ በተለያዩ ህትመቶች ላይ ይወጣልኝ ነበር፡፡ በሬድዮም ይነበቡልኛል፡፡ የምፅፋቸው በአብዛኛው ትችቶች ነበሩ፡፡ ለምሳሌ “የባህር ዛፍ አጨዳ እና ሽያጭ” በሚል መሃል ሸዋ አካባቢ የሚካሄደውን የደን ጭፍጨፋ የሚመለከት መጣጥፍ ፅፌ ነበር፡፡ የባህር ዛፍ ጭፍጨፋው አደገኛ ችግሮች እንደሚያመጣ፤ የድርቅም ምክንያት እንደሆነ በመግለፅ የፃፍኩት ፅሁፍ፤ በ“ሰርቶ አደር” ጋዜጣ ላይ እንደታተመልኝ ትዝ ይለኛል፡፡
እንዴት ነው በራሽያ ነፃ የትምህርት እድል ያገኙት?
በሁለተኛ ደረጃ ብሄራዊ መልቀቂያ ፈተና 3.4 አመጣሁ፡፡ ውጭ ሄጄ መማር አለብኝ ብዬ አስብ ነበር፡፡ አሁን እንዴት እንደሆነ ባላውቅም ድሮ ስኮላርሺፕ የሚሰጡ አገራት ምርጫ ይቀርብልሃል። በውድድር ነው፡፡ የሦስት አገራት ምርጫ ተሰጠኝ። ከልጅነቴ ጀምሮ የምመኘውን የጋዜጠኝነት ሙያ ለመማር መረጥኩ፡፡ ለኢንተርናሽናል ጆርናሊዚም ነፃ የትምህርት እድል የነበራቸው አገራት ደግሞ ራሽያ፣ ቻይናና ሃንጋሪ ነበሩ፡፡ ሶስቱንም ሞላሁ፡፡ በመጀመርያ ቻይና ደረሰኝ፡፡ ሳይታሰብ ግን በዚያ አገር ብጥብጥ ተነሳ፡፡ ቻይናን የመረጥኩት ትልቅ አገር ነች በሚል ነበር፡፡ ከዚያ ራሽያ ደረሰኝና ከሌሎች ተማሪዎች ጋር ለፈተና ተቀመጥን፡፡ ፓትሪስ ሉምቡባ ዩኒቨርስቲ ነበር የተመደብነው፡፡ ሰባ ተማሪዎች ተወዳድረን ሁለት ልጆች ፈተናውን በማለፍ እድሉን አገኘን፡፡
ከ22 ዓመታት በፊት ሞስኮ ሲገቡ የአገሪቱ ሁኔታ ምን ይመስል ነበር?
ገና አብዮቱ ባይጀመርም በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የለውጥ ንቅናቄዎች እየተስተዋሉ ነበር፡፡ ፕሮስትሬይካና ግላሽኖስት (ግልፅነትና ተጠያቂነት) …የጎርባቾቭ የተሃድሶ እቅድ ተጀምሯል፡፡ ትርምሱ ታዲያ ለጋዜጠኛ ሰርግና ምላሽ ነበር፡፡ እኛ በወቅቱ ቋንቋ እየተማርን ቢሆንም እዚያው በገዛሁት ካሜራ ግርግሮችን ፎቶ እያነሳሁ እሰበስብ ጀመር፡፡ በኋላም ቪድዮ ካሜራ ገዝቼ በከተማዋ የሚታዩ የለውጥ ንቅናቄዎችን እቀርጽ ነበር፡፡ ይሄን የማደርገው ለሚዲያ ለመዘገብ ሳይሆን የራሴን የጋዜጠኝነት ስሜት ለማርካትና መረጃ መሰብሰብ ስለምወድ ነው፡፡ እንደስራ ልምምድም መሆኑ ነው፡፡ በኋላ ላይ “ሞስኮ ታይምስ” ለተባለ ጋዜጣ ሁላችንም መስራት ጀመርን፡፡ በነፃ ሳይሆን እየተከፈለን፡፡ ሞስኮ ውስጥ በአማርኛ ቋንቋ የሚሰራጭ ሬድዮ ጣቢያ ስለነበር እዚያም እሰራ ነበር፡፡ ዜና ማንበብ፤ ደብዳቤዎችን አንብቦ ምላሽ መስጠት ነበር ስራዬ፡፡ በ“ሞስኮ ታይምስ” ጋዜጣ ላይ ደግሞ በተለያዩ ጉዳዮች ዙርያ እፅፍ ነበር፡፡ የመጀመርያው ፅሁፌ ትዝ ይለኛል፡፡ የአፍሪካ ችግሮች ላይ የሚያተኩር ነበር፡፡ ከዚያም ኢትዮጵያን ማስተዋወቅ ጀመርኩ… ስለ ኢትዮጵያ በዓላትና፤ ስለ ባህል ብዙ ፅፌአለሁ፡፡ አብዛኞቹን በራሽያ ቋንቋ የፃፍኳቸው ቢሆንም በእንግሊዝኛም እየፃፍን ክፍያ እናገኝ ነበር፡፡
የትምህርቱስ ነገር?
ኢንተርናሽናል ጆርናሊዝም ለአምስት አመት ተምሬ በባችለር ዲግሪ ተመርቄአለሁ፡፡ ለዲግሪ ማሟያ የፃፍኩት የጥናት ወረቀት በኢትዮጵያ ፕሬስ አጀማመር እና ህጎች ላይ ያተኮረ ነበር፡፡ በአጠቃላይ የሶሻል ሳይንስ ባለሙያ ነኝ፡፡ ማስትሬቴን በራሽያ ታሪክ፣ ፒኤችዲዬን ደግሞ በዓለም አቀፍ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ ላይ ነው የሠራሁት፡፡ በኢንተርናሽናል ፊልም ሁለተኛ ማስትሬት ዲግሪም አግኝቻለሁ፡፡
መቼ ነው የፕሮፌሰርነት ማዕረግ ያገኙት?
በ2001 እ.ኤ.አ ላይ ነው ሙሉ ፕሮፌሰር የሆንኩት፡፡ በዋናነት የማስተምረው በራሽያ ዩኒቨርሲቲ ነው፡፡ ዓለምአቀፍ ጋዜጠኝነትና በአገራት የውጭ ግንኙነት ፖሊሲዎች ውስጥ እንዴት መስራት እንደሚቻል አስተምራለሁ፡፡ በተለያዩ አገራት እየተጋበዝኩም ሌክቸር እሰጣለሁ፡፡ በአጠቃላይ በ59 የዓለም አገራት ተዟዙሬ ሠርቼአለሁ፡፡ በባንግላዲሽ መገናኛ ብዙሐን ላይ አንድ መጽሐፍ አሳትሜያለሁ፡፡ አምና “የአፍሪካና የአረብ አብዮት” በሚል ርዕስ ሌላ መፅሃፍ ፅፌአለሁ፡፡ ባለፉት 5 ዓመታት በተለያዩ ዓለም አቀፍ ችግሮች ላይ ያተኮሩ፣ ከተለያዩ ምሁራን ጋር በትብብር የተዘጋጁ ከ49 በላይ መጽሐፍትና የጥናት ፅሁፎች ለህትመት በቅተውልኛል፡፡
“ቢዝነስ አፍሪካ” የተባለ መጽሔት እንደሚያሳትሙ ሰምቻለሁ፡፡ ስለዚህ ዓለም አቀፍ መፅሄት ይንገሩኝ…
መጽሔቱ የፖለቲካ ነው፡፡ በሦስት ቋንቋ ነው የምንጽፈው፡፡ በዋናነት የቻይና-አፍሪካንና የራሽያ-አፍሪካን ግንኙነትን ይዳሰሳል፡፡ ከፍተኛ አንባቢ ያለው ድረገጽም አለው፡፡ ለመጽሔቱ ቃለምልልስ የምናደርገው ከትላልቅ ኩባንያ ዳሬክተሮች፣ ሚኒስትሮች፣ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ሃላፊዎች ጋር ነው፡፡ የመጽሔቱ ስርጭት ብዙ ባይሆንም በሞስኮ፣ በኬፕታውንና በሻንጋይ ከተሞች ለገበያ ይቀርባል፡፡ ከተመሠረተ 4 ዓመት ሆኖታል፡፡ እኔ በፕሬዚዳንትነት እየመራሁት ነው። በዓለም ዙሪያ እየከፈልናቸው የሚሰሩልን ከ200 በላይ ጋዜጠኞች አሉን፡፡ በራሽያ፣ በቻይና እና በተለያዩ የአፍሪካ አገራት ለሚገኙ ኩባንያዎች የኢኮኖሚ ትንታኔዎችን እንሠራለን፡፡
በኢትዮጵያ እየተሰሩ ስላሉት የመሠረተ ልማት ግንባታዎች ምን ይላሉ?
ኢትዮጵያ በዓለም በፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ ከሚገኙ አገራት አንዷ መሆኗ እውነት ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ስትመለከተው ግዙፍ የመሠረተ ልማት እንቅስቃሴዎች መኖራቸው ተገቢ ነው፡፡ በቂ ነው ለማለት ግን አልደፍርም፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ብዛት እኮ ከፍተኛ ነው፡፡ እስከ 100 ሚሊዮን መድረሱ አይቀርም፡፡ ከዚህ የህዝብ ብዛት አንጻር በብዙ ነገሮች ገና ነን፡፡ በቂ አይደሉም፡፡
የህይወት ፍልስፍናዎ ምንድነው?
ትልቁ ነገር ደግነት ነው፡፡ የተቸገረውን መርዳት፣ የወደቀውን ማንሳት፣ የሞተውን መቅበር። በህይወት እስካለህ ድረስ ደግ መስራት ጥሩ ነው፡፡ እውቀት ያለው እውቀቱን፣ ገንዘብ ያለው ገንዘቡን፣ ጉልበት ያለው ጉልበቱን ለሌላው ማካፈል አለበት። ኢትዮጵያ ከዓለም ሁሉ የምትለየው በዚህ ነው፡፡
ወደ አገር ቤት የመመለስ ሃሳብ አለዎት?
ከአገር ቤት ከጠፋሁ 5 ዓመት ሆኖኛል፡፡ ጊዜ አልነበረኝም፡፡ በተለያዩ የራሽያ ጐረቤት አገሮች ብዙ ስራዎች ነበሩኝ፡፡ በሞስኮ ስኖር ከአገሬ ውጭ እንደሆንኩ አልቆጥረውም፡፡ ሁልጊዜ ከአገር ቤት እንግዶች ይመጣሉ፡፡ ከኤምባሲው ጋር የኢትዮጵያን ጉዳዮች አብረን ነው የምንሰራው፡፡ ለ12 ዓመታት በሞስኮ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ፕሬዝዳንት በመሆን አገለግያለሁ፡፡ አሁን ደግሞ በሞስኮ ውስጥ የአፍሪካ ማህበረሰብ እየሰራሁ ነው፡፡
ዘመኑ የሴቶች ነው? የአትሌቶች ውጤት ምን ይመሰክራል
እዚሁ አዲስ አድማስ፣ አንድ ፀሐፊ “ዘመኑ የሴቶች ሆኗል” በማለት አስተያየቱን እንዳካፈለን ትዝ ይለኛል። አመት ሳይሞላው አይቀርም። ያኔ በለንደን ኦሎምፒክ ማግስት መሆኑ ነው። በኦሎምፒክ ውድድሩ ከተካፈሉት ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች መካከል፣ የወርቅ ሜዳሊያ በማጥለቅ የታሪክ መዝገብ ውስጥ የሚሰፍር ታላቅ ጀብድ የሠሩት ሦስት አትሌቶች አይደሉ? ሶስቱም ጀግኖች፣ ወጣት ሴት አትሌቶች ናቸው - ጥሩነሽ ዲባባ፣ መሠረት ደፋርና ቲኪ ገላና።
የአዲስ አድማሱ ፀሐፊ ይህንን የሴት አትሌቶች አስደናቂ ገድል ሲያይ ነው፣ ዘመኑ የሴቶች እየሆነ ነው ብሎ የፃፈው። በከፍተኛ ትምህርት፣ በዘመናዊ የሙያ መስኮች፣ በቢዝነስ ሥራም እንዲሁ፣ ሴቶች በየቦታው ብቅ ብቅ ማለት ብቻ ሳይሆን ጎላ ጎላ እያሉ መምጣታቸውንም ታዝቧል። ይሄውና ዘንድሮም፣ ያንን ሃሳብ የሚያጠናክር እንጂ የሚያስቀይር ነገር የተፈጠረ አይመስልም።
በእርግጥ፣ በሞስኮው የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ወንድ አትሌቶችም ጥሩ ውጤት አምጥተዋል። ወንድ አትሌቶች አንድ ወርቅ፣ ሶስት ብር እና አንድ ነሐስ አምጥተዋል። ሴት አትሌቶች ደግሞ ሁለት ወርቅና ሶስት ነሐስ። ተቀራራቢ ውጤት ነው። ብሄራዊ ቡድኑም በጥቅሉ፣ በሞስኮ ቆይታው ሶስት የወርቅ ሶስት የብር እና አራት የነሃስ በድምሩ አስር ሜዳልያዎችን በማግኘት ከአለም 6ኛ ከአፍሪካ 2ኛ በመሆን ሻምፒዮናውን አጠናቋል።
በአዲሱ አመት ዋዜማ በሞሪሽየስ በተካሄደው የአፍሪካ ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ግን፣ ሴት አትሌቶች የሚቀመሱ አልሆኑም። ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከተጎናፀፏቸው 7 የወርቅ ሜዳሊያዎች መካከል፣ 6ቱ በሴት አትሌቶች የተገኙ ናቸው። ይህም ብቻ አይደለም። በውድድሩ ከተገኙት ሰባት የብር እና ስምንት የነሐስ ሜዳሊያዎች መካከል አብዛኞቹ፣ በሴት አትሌቶች ውጤት ናቸው። ለዚያውም፣ ካሁን በፊት በኢትዮጵያውያን አትሌቶች ዘንድ እምብዛም ባልተለመዱት፣ በመቶ ሜትርና በሁለት መቶ ሜትር የሩጫ ውድድሮች የተካፈለች አትሌት፣ ሁለት የብር ሜዳሊያዎችን አጥልቃለች። በአራት መቶ ሜትር የመሰናክል ሩጫ የብር ሜዳሊያ፣ በሌላ የአራት መቶ ሜትር ውድድር ደግሞ የነሐስ ሜዳሊ አግኝተዋል - ኢትዮጵያውያን ወጣት ሴት አትሌቶች። ከ1500 ሜትር በላይ ባሉት ሩጫዎችማ፣ ወርቅ በወርቅ ሆነዋል።
ይሄን ይሄን ስናይ፣ እውነትም ዘመኑ የሴቶች ነው ያሰኛል።
አንዳንዴ ግን ጉዳዮች ሰፋ፣ ነገሮችን ራቅ አድርጎ መቃኘት ያስፈልጋል። ለዚህም ነው፤ ወደ ኋላ መለስ ብዬ የሃምሳ እና የአርባ አመታት የኢትዮጵያ አትሌቶች አለማቀፍ ውጤቶችን ለማነፃፀር የሞከርኩት።
እናስ ምን ተገኘ በሉኝ። ትክክል ነው። የሴት አትሌቶች ውጤት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረና እየገነነ መጥቷል። እስከ 1984 ዓ.ም፣ በኦሎምፒክ አደባባይ ድል ለመጎናፀፍ የቻሉ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሙሉ ወንዶች ናቸው - አምስት ወንድ አትሌቶች። ምሩፅ ይፍጠር፣ ሁለት ወርቅና አንድ ነሐስ፤ አበበ በቂላ ሁለት ወርቅ፣ ማሞ ወልዴ ደግሞ አንድ ወርቅ፣ አንድ ብር እና አንድ ነሐስ ተቀዳጅተዋል። መሀመድ ከድርና እሸቱ ቱራ ደግሞ ነሐስ።
በ1984ቱ የባርሲሎና ኦሎምፒክ ግን፣ የአበበ በቂላ ታሪክ በሴቶች ተደገመ። ደራርቱ ቱሉ፣ የወርቅ ሜዳሊያ በማጥለቅ የመጀመሪያዋ ኢትዮጵያዊ ሴት የኦሎምፒክ ጀግና ለመሆን በቃች። ከአራት አመታት በኋላ ደግሞ፣ የፋጡማ ሮባ ወርቅ እና የጌጤ ዋሚ ነሐስ ተጨመረበት። በሲዲኒው ኦሊምፒክ ደራርቱ ቱሉ የወርቅ ሜዳሊያ ስትደግም፣ ጌጤ ዋሚ የብርና የነሐስ ባለቤት ሆነች። ከዚያ በኋላማ የሚያቆማቸው አልተገኘም። በጥቂት አመታት ውስጥ የሴቶቹ ድል ከወንዶቹ አትሌቶች ጋር ተቀራራቢ ለመሆን ከመቻሉም በላይ፣ ብልጫ ወደ ማሳየት ተሸጋገረ።
በአለም የአትሌቲክስ ሻምፒዮናም ላይ፣ የሴት አትሌቶች ውጤት በአስገራሚ ፍጥነት ተመንጥቋል።
እንዲያም ሆኖ፤ የወንዶቹ ውጤት እዚያው በነበረት አልቀረም። ከሞላ ጎደል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መጥቷል። በየጊዜው ከፍ ዝቅ ማለቱ ባይቀርም፣ በጥቅሉ ሲታይ፣ የኢትዮጵያውያን አትሌቶች ውጤት ባለፉት 30 እና 40 አመታት አድጓል፤ ተመንድጓል። የሴት አትሌቶች የስኬት ፍጥነት ግን አጃኢብ ያሰኛል።
በእርግጥ፣ የሴቶች እንቅስቃሴ በጨመረ ቁጥር፣ መንፈስን የሚያነቃቁ የጀብዱና የስኬት ታሪኮች የመበራከታቸው ያህል፣ በተወሰነ ደረጃ አስደሳች ያልሆኑ ቀሽም ታሪኮች መፈጠራቸውም አልቀረም። የትንቢት መልክተኛዋ ጀማነሽንና “የቢግብራዘርዋ” ቤቲን መጥቀስ ይቻላል። ደግነቱ፣ ወደፊት ሳይረሳ የሚቀጥለው ዘመን የማይሽረው ታሪክ፤ የነጥሩነሽ ዲባባና የነመሰረት ደፋር ታሪክ ነው።