Saturday, 04 May 2024 10:41

ቀዳም ሥዑር- የተሻረች ቅዳሜ

Written by  ባዩልኝ አያሌው
Rate this item
(2 votes)

እነሆ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ክርስቲያኖች ከሰባቱ አጽዋማት አንዱ የሆነውን ታላቁን የዐቢይ ጾም (አርባ ጾም፣ ሁዳዴ ጾም- በልማድ) በታላቅ ጽሞና እና አርምሞ፣ ጸሎት እና ስግደት አጠናቀው ትንሣኤውን ሊያከብሩ ከደጅአፍ ደርሰዋል፤ ከዋዜማው- ከቀዳም ሥዑር።
ዛሬ የዐቢይ ጾም የመጨረሻው ቅዳሜ ቀዳም ሥዑር ነው። ቀዳም ሥዑር ማለታችን “በጎላው መናገር ልማድ ነው” እንዲል መጽሐፍ ጎልቶ የሚጠራውን አስቀድመን እንጂ የዛሬዋ ዕለት በተለያየ ስያሜም ተጠርታለች። “ለምለም ቅዳሜ”፣ “ሰንበት ዐባይ/ ቅዱስ ቅዳሜ” እየተባለች። ቀዳም ሥዑር የሚለውን መነሻ አድርገውም ምዕመናን “ቅዳሜ ሹር”፣“ቅዳም ሹር” እያሉ ዕለቲቱን ሲጠሩ መስማት የተለመደ ነው።
የዐቢይ ጾም የመጨረሻዋ ቅዳሜ ስለምን በእነዚህ ስያሜዎች ተጠራች? ምክንያተ ነገሩ ምንድር ነው? የሚለውን የነገር መጀመሪያ አድርገን፣ ዕለቱ በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንና ምዕመናን ዘንድ እንዴት ባሉ ሥርዓቶች ይታሰባል? ለምን? ለሚሉት ጥያቄዎች ከመጣፍም ከሊቅ አፍም መልስ እያሰስን እንቀጥል።
ቀዳም ሥዑር
“ቀዳም ሥዑር” የቃሉ ትርጉም “የተሻረች ቅዳሜ” ማለት ነው። ዕለቲቱን ቀዳም ሥዑር (የተሻረች ቅዳሜ) ያሰኛትም፣ ከወትሮው በተለየ በጾም የምትታሰብ (የምትጾም) መሆኑ ነው። ለወትሮው ዕለተ ቅዳሜ የጾም ዕለት አይደለችምና አትጾምም። በዚህች ዕለት ግን (በዓመት አንድ ቀን) ኢየሱስ ክርስቶስ አዳምና ልጆቹን ከዲያብሎስ አገዛዝና እስራት ነጻ ለማውጣት የተቀበለውን ጽኑ ሕማምና መከራ፣ እንዲሁም ሦስት መዓልትና ሦስት ሌሊት በከርሠ መቃብር መቆየቱን በማሰብ ትጾማለች። የማትጾም ሰንበትነቷ በዓመት አንድ ቀን ይኸውም በዕለተ ስቅለት ማግስት፣ በትንሣኤ ዋዜማ ይሻራልና ቀዳም ሥዑር ወይም የተሻረች ቅዳሜ ተብላለች። ሥዑር ብሂል የተሻረ።
በዚህች ዕለት የኢየሱስ እናት ድንግል ማርያም፣ ደቀመዛሙርቱ ቅዱሳን ሐዋርያት እና ሁሉን ትተው የተከተሉት ቅዱሳን አንስት ተላልፎ ከተሰጠባት ዕለት አንስተው ብርሃነ ትንሣኤውን እስከሚያዩ ድረስ እህል ውኃን አንዳች አልቀመሱም። በፍጹም ማመን ያመኑበት፣ ያለመጠራጠር የተከተሉት እና ተስፋቸው የሆነ መምህራቸው በከርሠ መቃብር አርፏልና ነገረ ሞቱን በማሰብ፣ በሦስተኛው ቀን ከሙታን መካከል እነሳለሁ ብሎ ያስተማረውን ነገረ ትንሣኤውንም እንዲሁ በመናፈቅ እለቲቱን በጾም አስበዋታል። ክርስቲያኖችም እንዲሁ የቅዱሳን ሐዋርያትን አሠረ ፍኖት ተከትለው ቢቻላቸውስ ከአርብ ጀምረው በማክፈል፣ ያም ባይሆን አርብ ማታን ተመግበው ቅዳሜን በመጾም የጌታን ትንሣኤ ያከብራሉ።
ለምለም ቅዳሜ
የዐቢይ ጾም የመጨረሻዋ ቅዳሜ “ለምለም ቅዳሜ” (ለምለሚቱ ቅዳሜ) ተብላም ትጠራለች። ለምለም ቅዳሜ መሰኘቷም፣ በዚህች ዕለት ካህናቱ የምስራች ማብሰሪያ የሆነውን ለምለም ቄጤማን ለምዕመናን የሚያድሉበት፤ ምዕመናኑም ቄጤማውን እስከ ትንሣኤ ሌሊት ድረስ በራሳቸው ላይ የሚያስሩበት ዕለት በመሆኑ ነው። “ነገርን ከሥሩ” እንዲሉ ምሥጢሩን ከነቁ እንይዝ ዘንድ ስለምን ለምለም ቄጤማ? ብሎ መጠየቅ ብልሀት ነውና፣ ይህንኑ ጠይቀን ጥቂት እንግፋ።
በትንሣኤ ዋዜማ ቅዳሜ ካህናቱ ለምዕመናን የሚያድሉት ለምለም ቄጤማ ስለምንነት ከዘመነ ኖኅ ታሪክ የሚቀዳ ነው። በቅዱሱ መጽሐፍ እንደተጻፈ፣ በኖኅ ዘመን የሆነውንና ሁሉን ያጠፋውን ማየ አይኅ (የጥፋት ውኃ) መጉደሉን አይታ ትነግረው ዘንድ ኖኅ ርግብን በላካት ጊዜ፣ ርግብ ለምለም ቄጤማና የወይራ ቀንበጥን ባፏ ይዛ ተመልሳለች። ኖኅም ቄጤማውና የወይራው ቀንበጥ የጥፋት ውኃው መጉደል ምልክት መሆኑን ተረድቶ፣ በእግዚአብሔር ፈቃድ በመርከቡ ከልሎ ያቆያቸውን ፍጥረታት ይዞ ከመርከቡ ወጥቷል።
ለምለም ቄጤማና የወይራ ቀንበጥ ለጥፋት ውሃ መድረቅ ምስራች መንገርያ፣ ለአዲስ ዘመን ማብሰሪያ እንደሆኑ ሁሉ፣ እነሆ አሁንም በዘመነ ሐዲስ በክርስቶስ ሞት ሞተ ነፍስ ከሰው ልጆች መወገዱን ለማብሰር ለምለም ቄጤማ ምልክት (ተምሳሌት) ሆኗል።
አስቀድመን እንዳልን በዚህች ዕለት ቀሳውስቱና ዲያቆናቱ ቃጭል /ቃለዓዋዲ/ እየመቱ “ገብረ ሰላመ በመስቀሉ፤ ትንሣኤሁ አግሃደ”ን እየዘመሩ፣ ጌታ በመስቀሉ ሰላምን እንደሰጠን እና ትንሣኤውንም እንደገለጠልን በማብሰር ለምለሙን ቄጤማ ለምዕመናን ያድላሉ። ምዕመናኑም ቄጤማውን በራሳቸው ያስራሉ። በዚህም አይሁድ ጌታችንን ለመስቀል ሲያንገላቱት የእሾህ አክሊልን በጭንቅላቱ ላይ ማኖራቸውን ያዘክራሉ።
ሰንበት ዐባይ/ ቅዱስ ቅዳሜ
ይህች ዕለት ቀዳም ሥዑር፣ ለምለም ቅዳሜ እንደተባለች ሁሉ፣ “ሰንበት ዐባይ/ ቅዱስ ቅዳሜ” ተብላም ትጠራለች። ቅዱስ እግዚአብሔር በጥንተ ተፈጥሮ ሀያ ሁለቱን ፍጥረታት የሚታዩትንና የማይታዩትን፣ በእግር የሚሄዱትን፣ በክንፍ የሚበሩትን፣ በባህር የሚቀዝፉትን፣ በመጨረሻም ሰውን በአርአያውና በአምሳሉ የፈጠረው ከዕለተ እሑድ እስከ አርብ ባሉት ስድስት ቀናት ሲሆን፣ በሰባተኛዋ ቀን (በዕለተ ቅዳሜ) ከሥራው ሁሉ አርፏል። ይህም ቅዳሜን ሰንበት ዐባይ (ታላቋ ሰንበት) አስኝቷታል። ይህችም ዕለት ታላቅ ናትና ሰንበት አድርገው ያከብሯት ዘንድ ህዝበ እግዚአብሔር የተባሉ እስራኤላውያን ታዘው ነበር።
በዘመነ ሐዲስም እንዲሁ፣ ኢየሱስ የማዳን ሥራውን ሁሉ ፈጽሞ በሥጋው በመቃብር ሲያርፍ፣ በአካለ ነፍሱ ደግሞ ሲዖልን በርብሮ ባዶዋን አስቀርቷታል። በዚያ ለነበሩት ነፍሳትም የዘለዓለም ዕረፍትን ያወረሰባት ዕለት ሆናለችና፣ ከዕለታት የተለየች፣ አንድም ልዩ ዕለት ለማለት “ቅዱስ ቅዳሜ” ተብላ ተጠርታለች። የፊተኛይቱ ጥንተ ቅዳሜ ፈጣሪ ፍጥረታትን ሁሉ ፈጥሮ ያረፈባት ሰንበት፤ የኋለኛይቱ ደግሞ ጌታችን የማዳን ሥራውን ፈጽሞ በከርሠ መቃብር ያረፈባት ዕለት በመሆኗ የመጀመሪያይቱ ሰንበት “ሰንበት ዐባይ”፣ ከሐዲስ ኪዳኗ “ቅዱስ ቅዳሜ” ጋር በምሥጢር መተሳሰራቸውን ሊቃውንት ያትታሉ።
ስለዕለቲቱ መጠሪያዎች ነገረ ምክንያት ይህንን ካልን፣ ነገራችን ውል ይይዝ ዘንድ ዕለቱ በቅድስት ቤተክርስቲያን እና በምዕመናኑ ዘንድ እንዴት ባሉ ክንውኖች ይታሰባል የሚለውን አንስተን እንቋጭ።
ቅዳሜ ከሌሊቱ አንስቶ ካህናቱና ምዕመናኑ በቅድስት ቤተክርስቲያን ይሰበሰባሉ። የጧቱ ጸሎት ሲፈጸም ካህናቱ “ገብረ ሰላመ በመስቀሉ” (በመስቀሉ ሰላምን አደረገ፤ ሰላምን መሠረተ) የምሥራች እያሉ በቤተክርስቲያን ለተሰበሰበው ምዕመን ሁሉ የምስራች ማብሰሪያ ምልክት የሆነው ለምለም ቄጠማ ይሰጣሉ። ይኸውም ምድር በማየ አይኅ (በጥፋት ውኃ) በጠፋችበት ጊዜ የተላከችው ርግብ የጥፋት ውኃውን መጉደል ያበሰረችው በአፏ ለምለም ቄጤማን ይዛ በመምጣት እንደሆነ ሁሉ፤ ዛሬም ለሐዲስ ኪዳን ክርስቲያኖች የኃጢአት ውኃ ጐደለ፤ የኃጢአት ውኃ ጠፋ፤ አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን የኖረ የሰው ልጅ በደል ተደመሰሰ፤ በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ነጻነት ታወጀ ለማለት ካህናት ለምለም ቄጠማን በመያዝ ለምዕመናን ያበስራሉ። ለምለሙን ቄጤማም ለምዕመናኑ ያድላሉ።
እነሆ ምዕመናንም የምስራች ተምሳሌት የሆነውን ለምለም ቄጠማ እየሰነጠቁ በራሳቸው ላይ ያስሩታል፤ በጣታቸው ቀለበት ያደርጉታል። በዕለቱ ወደ ቤተክርስቲያን ላልመጡት ምዕመናንም ካህናት በየሰበካቸው ልብሰ ተክህኖ ለብሰው፣ መስቀልና ቃጭል ይዘው ቄጠማውን የምሥራች እያሉ ያድላሉ። ልብሰ ተክህኖ የለበሱ ካህናትና ዲያቆናት ቄጤማ ተሸክመው ቃጭል እያቃጨሉ ሲጓዙ መታየታቸውም ዕለተ ትንሣኤውን ለሚናፍቅ ምዕመን ትልቅ ብስራት፣ ነፍስን በሐሴት የሚሞላ የምስራች ነው።
ምንም እንኳን መጽሐፍ እንዳለ፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ የተነሣው እሑድ በመንፈቀ ሌሊት ቢሆንም፣ አዳም ከሲዖል ወጥቶ ወደ ገነት መግባቱ የታወቀው፣ የክርስቶስ ትንሣኤውም የተመረመረው በቀዳም ሥዑር በመሆኑ፣ በዛሬዋ ዕለት የትንሣኤው ብስራት በአፈካህናት ለሕዝበ ክርስቲያን ይነገራል። ቤተክርስቲያንም የኀዘን ዜማዋን እና አልባሷን ለውጣ በድምጸ ጸናጽል እና ከበሮ ትደምቃለች- ትንሣኤውን በታላቅ ብርሃን ታከብር ዘንድ።
መልካም ትንሣኤ!
***
ከአዘጋጁ፡- ባዩልኝ አያሌው በኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ የቋንቋና ሥነጽሑፍ መምህር ሲሆኑ፣ ላለፉት በርካታ ዓመታት በተለያዩ የኪነጥበብ መድረኮች ላይ በሚያቀርቧቸው ግጥሞችና አዲስ አድማስን ጨምሮ በሌሎች የሕትመት ውጤቶች ባስነበቧቸው ሥነጽሑፋዊ ሂሶቻቸው ይታወቃሉ።

Read 484 times