Saturday, 04 May 2024 09:51

በርበራ የኢትዮጵያን 30% ጭነት እንዲያስተናግድ ታቅዷል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የተባበሩት አረብ  ኤሚሬቶች ንብረት የሆነው “ዲፒ ወርልድ ኩባንያ” የሚያስተዳድረው የበርበራ ወደብ፣ የኢትዮጵያን 30 በመቶ ጭነት እንዲያስተናግድ የሶማሌላንድ ባለሥልጣናት ማቀዳቸው ተነገረ፡፡
በዚህም መሰረት የወደብ አጠቃቀምና የጉምሩክ ሥርዓቶችን የተመለከተ ስምምነት በኢትዮጵያና ሶማሌላንድ መካከል መፈረም እንዳለበት የተገለጸ ሲሆን፤ ስምምነቱ በሚቀጥሉት 60 ቀናት ተጠናቅቆ  ሊፈረም እንደሚችል የሶማሌላንድ የወደቦች አስተዳደር አስታውቋል፡፡
የአስተዳደሩ ዋና ዳይሬክተር ሰኢድ ሃሰን አብዱላሂ በሰጡት ማብራሪያ፤ “ኢትዮጵያ ጎረቤታችን ናት፤ አብረን  ቢዝነስ መሥራት እንፈልጋለን። በአሁኑ ወቅት የወደብ አጠቃቀም ስምምነት እያዘጋጀን ነው። አንዴ ስምምነቱን ከተፈራረምን በኋላ፣ በመጀመሪያው ዓመት ከኢትዮጵያ ጭነት 30 በመቶውን እናስተናግዳለን” ብለዋል።
ከጥቂት ወራት በፊት እ.ኤ.አ. ጥር 1 ቀን 2024 ዓ.ም ኢትዮጵያና ሶማሌላንድ የተፈራረሙት የመግባቢያ ስምምነት በተመሳሳይ ወደ ተግባር የሚገባበት የመጨረሻው ስምምነት በ2 ወራት ገደማ ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅም  የሶማሌላንድ ባለሥልጣናት ጠቁመዋል፡፡
የመግባቢያ ስምምነቱ ከተፈረመ በኋላ ውይይቶች ሲደረጉ መቆየቱን ያመለከቱት  ባለሥልጣናቱ፤ የቴክኒክ ኮሚቴዎች መዋቀራቸውንም ተናግረዋል። የመግባቢያ ስምምነቱ  ከመጨረሻው ሂደት ላይ ደርሶ ወደ ተግባር ከተገባ ኢትዮጵያ በሶማሌላንድ የባህር ዳርቻ ላይ የጦር ሰፈር በሊዝ ኪራይ እንደምታገኝ የተገለጸ ሲሆን፤ ሶማሌላንድ በበኩሏ፣ ለረዥም ጊዜያት ስትፈልገው የነበረውን እንደ አገር ዕውቅና የማግኘት ዕድል እንደሚፈጥርላት ባለሥልጣናቱ አመልክተዋል።
ለንግድ ስራ ሌላ ወደብ መገንባት ሳያስፈልግ፣ የበርበራ ወደብን ኢትዮጵያ እንደምትጠቀምበት የሶማሌላንድ ባለሥልጣናት  መግለጻቸው  የተዘገበ ሲሆን፤ ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ፣ ዲፒ ወርልድ እና ሶማሌላንድ የበርበራ ወደብን በጋራ  ለማልማት ስምምነት መፈጸማቸው ይታወሳል።

Read 736 times