Sunday, 28 April 2024 21:24

”የመጨረሻው ፈተና” ሰሞኑን ለንባብ በቃ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  የግሪካዊው ደራሲ ኒኮስ ካዛንታኪስ ”The Last Temptation of Christ“ የተሰኘ ልብወለድ መጽሐፍ ”የመጨረሻው ፈተና” በሚል በማይንጌ ወደ አማርኛ ተመልሶ ሰሞኑን ለንባብ በቃ፡፡
ኒኮስ ካዛንታኪስ በ1883 ዓ.ም. (እ.ኤ.አ) በክሪት ከተማ ተወለደ፡፡ ከአቴንስ ዩኒቨርስቲ የሕግ ዲግሪውን ካገኘ በኋላ፣ በታዋቂው ፈላስፋ ሄንሪ በርግሰን ሥር የፍልስፍና ጥናቱን በፓሪስ አካሂዷል፡፡ ሥነ ጽሑፍና አርትን ደግሞ በጀርመንና ጣልያን ተዟዙሮ አጥንቷል፡፡ ስፔን፣ እንግሊዝ፣ ሩስያ፣ ግብፅ፣ እስራኤል፣ ቻይናና ጃፓን ከተጓዘባቸውና ለተወሰኑ ጊዜያት ከቆየባቸው አገራት ውስጥ ይጠቀሳሉ፡፡ በ1945 ዓ.ም. ለአጭር ጊዜ በግሪክ የትምህርት ሚ/ር ሚኒስትር ዲኤታ በመሆን ተሾሟል፡፡ ከ1947-48 ዓ.ም. ድረስ ደግሞ በዩኔስኮ የትርጉም ቢሮን በዳይሬክተርነት መርቷል፡፡ በአጠቃላይ 30 የሚሆኑ ልብ ወለዶችን፣ ቲአትሮችንና የፍልስፍና መጽሐፎችን ጽፏል፡፡ ልብወለድ መጻፍ የጀመረው በአመሻሽ ዕድሜው ቢሆንም፣ ከ65 ዓመቱ ጀምሮ ባሉት ዘጠኝ ተከታታይ ዓመታት ስምንት የልብወለድ መጻሕፍትን ማበርከት ችሏል፡፡ ታዋቂ ከሆኑት ልብወለዶቹ መካከል፣ Zorba the Greek, The Greek Passion እና The Last Temptation of Christ (የመጨረሻው ፈተና) ይገኙበታል፡፡
በተደጋጋሚ ለሥነጽሑፍ የኖቤል ሽልማት የታጨ ቢሆንም፣ በተለይ ደግሞ በ1952 ዓ.ም. በአንድ ድምፅ ብቻ ተበልጦ ሳይሸለም ቀርቷል፡፡ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው በ1957 ዓ.ም. ነው፡፡ የመቃብር ሀውልቱ ላይ እንዲጻፍ አደራ ያለው ቃል፡-
“ምንም አልፈራም፣   I fear nothing
ምንም አልጠብቅም፣ I hope for nothing
ነፃ ነኝ!” የሚል ነበር፡፡ I am free.

Read 826 times