Sunday, 28 April 2024 21:13

የአለማየሁ ገላጋይ ዋና (መሪ) ገፀባህርያት “ጀግና ካልሆንክ ስም እንኳን የለህም”

Written by  ቴዎድሮስ ተ/አረጋይ
Rate this item
(2 votes)

 ከአዘጋጁ
በቅርቡ የደራሲና ሃያሲ አለማየሁ ገላጋይ 56ኛ ዓመት የልደት በዓሉን ምክንያት በማድረግ፣ ለንባብ በበቃው “መልክአ ዓለማየሁ” የተሰኘ መጽሐፍ ውስጥ በርካታ በአለማየሁ ህይወትና የሥነፅሁፍ ሥራዎች ዙሪያ የሚያጠነጥኑ መጣጥፎችና ቅኝቶች ተካትተዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል አንጋፋ ጋዜጠኛና ደራሲ ቴዎድሮስ ተ/አረጋይ ከአለማየሁ ጋር ያደረገው ውብ ቃለምልልስ ይገኝበታል፡፡ ከዚህ ጠለቅና ዘለግ ያለ ኢንተርቪው ውስጥ በአለማየሁ ዋና (መሪ) ገፀባህርያት ላይ አተኩረው  ሁለቱም የተወያዩትን ቆንጥረን ከዚህ በታች አቅርበነዋል፡፡ መፅሐፉ በእጃችሁ ካለ ግን ሙሉውን ቃለመጠይቅ አንብቡት እንዳያመልጣችሁ፡፡ በነገራችን ላይ የተዋጣለት ቃለመጠይቅ በማድረግ ቴዎችሮስ ከቀዳሚዎቹ ተርታ ነው፡፡
***
ቴዎድሮስ፡- ዶስቶቭስኪ በተለየ መልኩ ይመስጥኻል?
ዓለማየሁ፡- በጣም፡፡ “ዶስቶቭስኪያን ኖቭል” የተባለ የአጻጻፍ መንገድ አለ፡፡ የዶስቶቭስኪ የአጻጻፍ ስልት ላይ መሰረት የደረገ ነው፡፡ በዓሉ ግርማ አንድ ገጸባህርይ ሲፈጥር፣ በቅንፍ ውስጥ ፈላጭ ቆራጭ ነው፡፡ እሱ የሚናገረው ርትእ ነው፡፡ እሱ የሚያደርገው ፍጹም ነው፡፡ ግቡ የሁሉም ሰው ግብ ነው፡፡ ያን ግብ ደግሞ በጥንካሬ ያሳካል፣ በሞቱም በመግደሉም፡፡ እንደህ ፍፁም የሆነ ገጸባህርይን ነው ሌሎቹ የሚጽፉት፡፡ የዶስቶቭስኪ ዋና ገጸባህርይ ግን እንደዚህ አይደለም፤ ከንቱ ነው፡፡ ሌሎች ሰዎች ናቸው በክፋትም በጥንካሬም ጎልተው የሚታዩት፡፡ ዋናውን ገፀባህርይ አንዱ ለመጣል ሲገፋው ሌላው ለማቃናት ይመልሰዋል፡፡ ዶስቶቭስኪያዊ ልብወለድ ውስጥ ያለው ቀና ገጸባህርይ አንዳንዴ በሴተኛ አዳሪዎች ተገፍቶ ነው ዋና ግብ ላይ የሚደርሰው፡፡ ሴተኛ አዳሪዋ እኮ ከህይወት ላይ የቀዳችው ስለ ሰው ልጅ ጥሩ ትምህርት አላት፡፡ አንትሮፖሎጂስቱ አያውቅም እኮ፣ አንዳንዴ የእሷን ያህል፡፡ የሰውን ልጅ ከነዝባዝንኬው ታውቀዋለች፡፡ ዶቶቭስኪያዊ ልቦለድ ለእኔ ይስበኛል፡፡ ዋናዎቹ ገጸባህርያት ይናውዛሉ፡፡ ግባቸውን መጨበጥ ያቅታቸዋል፡፡ እንዳውም አንዳንዴ ግብ  የላቸውም፡፡ አንዳንዶቹ ለግባቸው ጀርባቸውን ሰጥተው ነው ከግባቸው ውጭ ሲናውዙ የምታየው፡፡ መናወዝ አለ፡፡ አንድ ቤተሰብ ውስጥ ተቀምጦ በሀሳብ ዓለምን እየገዛ ራሱን ማስተዳደር ያልቻለ ገጸባህርይ፡፡
ቴዎድሮስ፡- ያንተም ገፀባህርያት እንዲሁ ናቸው? “ወሪሳም፣ “ታለ”ም ላይ ዋናዎቹ ገፀባህርያት እንዲሁ ናቸው?
ዓለማየሁ፡- ይመስለኛል፡፡ እንደ የ”ወሪሳ”ው መምህር ዓይነቱ ከርፋፋ ነው፡፡ አስረዝመው ሲያስሩት፣ የሚሞክረው የታሰረበትን ለመበጠስ ሳይሆን ገመዱን ይበልጥ አርዝሞ የሚዘዋወርበትን ለመጨመር ነው፡፡ የተሰጠውን በሙሉ በብዙ ፍርሃት ራሱን ያሰረ ገጸባህርይ ነው፡፡ አንዳንዴ ጭፍን የምትባለው ገጸባህርይ ነፃ እንዲወጣ ታግዘዋለች፡፡ ግን ነጻ ሳይወጣ ነው የሚያበቃው፡፡ ስም እንኳን የለውም፡፡ ጀግና ካልሆንክ ስም እንኳን የለህም፡፡ ብዙ ጀግና ያልሆኑ ሰዎች ከፊታችን ጠፍተዋል፡፡ የምታስታውስበት ታጣለህ፡፡ ታለንም ስትመለከት እንደሱ ነው፡፡ ጠንካራ ሰዎችን ሲደገፍ ታየዋለህ፡፡ እየተውተረተረ ያስቸግራል፡፡ እንደውም ባርነቱን በመፈለግ ከእነዚያ ሰዎች ሸሽቶ እንደገና ጭለማ ቤት ውስጥ ይገባል፡፡ መብራት እንኳን የሌለው፡፡…. ህይወቱ ነው መብራት የሌለው፡፡ ህይወቱ ነው መብራት የማይኖረው፡፡ ምናልባትም ለዶስቶቭስኪያዊ ልቦለዶች ቅርበት ያላቸው ሰዎች ስለምሰራ ይመስለኛል እነዚህ የመጡት፡፡ ሁሉንም ነገር ለማድረግ የተፈጠረ ገጸባህርይ ሲሆን አይስማማኝም፡፡ ጠንካራ ሰዎች ልታይ ትችላለህ፣ ግን እነዚያው ሰዎች ሌላ ደካማ ጎን አላቸው፡፡ የምትመለከትበትን መስኮት መቀየር ነው፡፡ ሁሉም ሰው ከድካም ጋር ነው ጥንካሬውን አደባባይ ላይ ይዞ የሚወጣው፤ ልክ ገላችንን ልብስ እንደምንሸፍነው ሁሉ ጥንካሬ የሚመስል ነገር አድርገን ነው አደባባይ የምንወጣው፤ የሚወረወረው ድንጋይ ቂው ብሎ እንዲመለስ፡፡
ቴዎድሮስ፡- በተመሳሳይ፣ ከ”አጥቢያ” እስከ “ቤባንያ” ባሉ ልብወለድ ድርሰቶችህ ውስጥ ጀግና ወይም አሸናፊ ገፀባህርያትን ከመፍጠር ይልቅ ተረቺና ልፍስፍስ ገጸባህርያት መፍጠር ታዘወትራለህ፡፡ ከ”አጥቢያ”ው ሙሉጌታ እስከ “ቤባንያ”ው መፍትሄ ድረስ ያሉትን መሪ ገጸባህርያት እንደ ክርስቶስ ውግራታቸውን በፀጥታ ለመቀበል እጃቸውን ወደታች እንዲያንከረፍፉ የምታደርጋቸው ለምንድነው?
ዓለማየሁ፡- ቅድም እንዳልኩት፣ ዶስቶቭስኪያን ልብወለዶች ወደ መጻፍ እንደማዘንበሌ መሪዎቹ ገጸባህርዮቼ ሽምድምዶች ናቸው፡፡ ስም የላቸውም፡፡ ጀግኖችም አይደሉም፡፡ የ”ወሪሳ”ው መምህር ተረትና ጥቅስ ላይ የቀረ ገፀባህሪይ ነው- “እንግዲህ ተረት እየቆረጠምኩ እስከ ደመወዝ እቆያለሁ” የሚል፤ ሁሌም ወደ ኋላ የሚጎተት ገጸባህርይ፡፡ እንደ በዓሉ ግርማ ገጸባህርያት አይደለም፡፡ አንዳንዴ በመሞት  ውስጥ ነው የሚያሸንፈው፡፡ “እሱ ልክ ነው” አትለውም፡፡ እንደውም የሚናገረውን ትቃወመዋለህ፡፡ ዶስቶቭስሲኪ የፈጠረው ገፀባህርይ “ኩላሊቴ ታሟል” ይላል ገና ሳይመረመር፡፡ አትቀበለውም የሚናገረውን፡፡ የበዓሉ ገጸባህርይ ግን ሳያገናዝብ  አይናገርም፡፡ ሳያገናዝብ አይነቅፍም፡፡ አበራ ወርቁ የሚናገረው ልክ ነው፡፡ የሚደግፈውም የሚነቅፈውም ነው ልክ፡፡ የዶስቶቭስኪ ገፀባህርያት ግን “ወሪሳ” ላይ እንዳለው ገጸባህርይ ስም የለሾች ናቸው፡፡ ወደፊት የማይራመዱ ናቸው፡፡
ቴዎድሮስ፡- ዋና ገጸባህርይነታቸው ታዲያ ምንድነው? ቅድም በዕውኑ ዓለም “ታሪክ የአሸናፊዎች ነው” እንዳልነው፣ ይኸው ወደልቦለዱ አይመጣም ወይ? የተለመደውም ደግሞ እሱ ነው፡፡
ዓለማየሁ፡- ዶስቶቭስኪ እሱን ነው ገልብጦ የመጣው፡፡ ያ “ደካማ” ያልነው ገጸባህርይ በስንፍናው ውስጥ እያስተማረህ ይሄዳል፡፡ አጠገቡ ደግሞ ትናንሽ ጀግኖች አሉ፡፡ እሱን የሚገዳደሩ፡፡ ገፍትረው ለመጣል የሚሞክሩ፡፡ ደግሞ የሚደግፉትም አሉ፡፡ ከዳንኤል ዴፎ ጀምሮ ዶስቶቭስኪ እስኪፈጠር ድረስ ያሉ ገጸባህርያት አንተ የምትለው ዓይነት ጀግኖች ናቸው፡፡ ተረቶቻቸውም የጀግኖች ውሎዎች ናቸው፡፡ ፈሪ ገጸባህርይ ሆኖ አያውቅም፡፡ በወዲያኛው ወገን ተሰልፎ መሳቂያ ለማድረግ የምትመርጠው ነው፡፡ ዶስቶቭስኪ ግን ፈሪውን ዋና ገፀባህርይ አደረገው፡፡ መመታት የሚፈልገውን፡፡ ከረምቦላ ቤት ተደባድበው አንዱን አንስተው በመስኮት ሲወረውሩት ሲያይ “እስቲ እኔንም ይወርውሩኝ” ብሎ ይገባል፡፡ ግን ደግሞ ማንም ሰው ብሎ የቆጠረው የለም፡፡ ለካ በመስኮት ለመወርወርም መብቃት አለብህ፡፡ “እኔ ነገር ለመፈለግ ስሞክር፣ እንደ ዕቃ ገፋ አድርገውኝ ጨዋታቸውን ይጀምራሉ፣” ይላል፡፡
“እበቀላቸዋለኹ” ማለት ጀመረ፡፡ ዐየህ ትንሽነት? እንዲህ ያለውን ትንሽ ገፀባህርይ አንስቶ ዋና ያደርገዋል፡፡
ቴዎድሮስ፡- እኮ እዚህ ላይ እኮ ነው ጥያቄው፡፡ ዋናው ገፀባህርይ በመልካምነትም ይሁን በክፋት እየመራ ስሜታችንን ይዞ ካልወሰደን፣ ዋናነቱ የቱ ጋ ነው? በምንስ ይገለፃል?
ዓለማየሁ፡- ሽንፈቱ እኮ ማሸነፍንም እያወጀ ነው፡፡ አንተ እያረምከው በሄድክ ቁጥር ዋና ገፀባህርዩ አንተ እንባቢው ትሆናለህ አንዳንዴ፤ ምክንያቱም ስለ ስንፍናው በስንፍናው የሚያወራቸው በሙሉ በአንተ እየታረሙ ነው የሚሄዱት፡፡ አንድ ልቦለድ የግድ በዋናው ገጸባህርይ መመራት የለበትም፡፡ ዶስቶቭስኪ ነው ይህን ያመጣው፡፡ ልክም ነው ደግሞ፡፡ ሌላ ጣዕም አቀመሰን፡፡ ሌላ ጣዕም ተመዘገበ፤ በስነ ጽሁፍ ውስጥ፡፡ በፊት እነ ቼኮቭ ሁሉ አልተቀበሉትም ነበር፡፡ “ዐውቃለሁ ባይነት ያበዛል” አለ ቼኾቭ፡፡ ምክንያቱም ትናንሾች የወደቁ መምህራን ናቸው ገጸባህርያቱ፡፡ ለወንጀል የተነሳሱ፣ ወንጀል የሚሰሩ ናቸው፡፡ በእሮሮ የዳሸቁ ኾነው ይሳሉና ከመዳሸቃቸው ውስጥ ሲወጡ አታይም፡፡ የበለጠ ሲዘፈቁበት ነው የምታያቸው፡፡ ከመዳሻቃቸው የሚያወጣቸው ንዋይ እነሱ ጋ ቢደርስም ዝም ብለው ይበትኑታል፡፡  “ወንጀል እና ቅጣት” ላይ ራስኮልኒኮቭ ሰዎች ከገደለ በኋላ ወርቅ አገኘ አይደለም? መልሶ ግን ያንን ወርቅ መንገድ ላይ ሲያዝረከርከው ነው የታየው፡፡ አልተጠቀመበትም፡፡ መልሶ እዚያው ችግር ውስጥ ሲዘፈቅ ነው የምታየው፡፡ ይኽን ማረም ራሱ አንባቢያኑን ዋና ገጸባህርይ ያደርጋቸዋል፡፡ የሚጎድል ነገር እንደሌለ በዶስቶቭስኪ ስራዎች አይተናል፡፡
ቴዎድሮስ፡- በሥራህም ሆነ በግል ሕይወትህ ማሸነፍን ቁምነገር ታደርጋለህ? ስለ ተሸናፊውስ እንዴት ታስባለህ?


ዓለማየሁ፡- ማሸነፍና መሸነፍ መልኩን እየቀያየረ ነው የሚመጣብህ። ማሸነፍ ምሳህን ከመብላት ይጀምራል። ሳይበላ ውጭ በር ላይ የሚቀር ሰው አለ። እሱን ብዙ ርህራሄ ካላቸው ሰዎች ተምሬያለሁ። ለምሳሌ ከአብደላ ዕዝራ ጋር ምሳ ልንበላ ስንሄድ፣ ለሁለታችን ሦስት ምግብ ነው የምናዘው። አንድ አንድ ወይም ግማሽ ግማሽ ከበላን በኋላ ሌላው በፌስታል ተጠቅልሎ በእነሱ በኩል ለደሀ ይደርሳል። ሙሉ ንፁህ ምግብ ብናዝ አይሰጧቸውም፤ ይሳሳሉ። ነካክተን እንተወዋለን። ማሸነፍህን ማካፈል ነው ይሄ። አሸንፈህ ምሳህን መብላት ችለሃል። ላንተ ሁለት ምግብ ስታዝ ለተሸነፈው ደግሞ አንድ ታዛለህ። ካለህ ሁለት ብታደርገውም፣ አንተን አይጎዳህም። መክፈል ችለሃል እኮ። ፉክክርህና ግድ የሚልህ ነገር በየዘመኑ መልኩን እየቀያየረ ይመጣብሃል፤ ንፁህ መልበስ ራሱ። ራስ ካሳ የጻፉት መጽሐፍ ላይ “ማሸብረቅ ነውር ነው” ይላሉ። ወርቀዘቦ ለብሰህና ተንቆጥቁጠህ መሄድ ደስ ይልሃል? እሱን ነው “ነወር ነው” የሚሉት። ማሸነፍህን አለአግባብ ልትጠቀምበት እንደማይገባ ነው መልእክቱ። ግን ደግሞ ማህበረሰቡ በሙሉ የሚያሸበርቅበት ቀን ከሆነ (ለምሳሌ እንደ ሰርግና በዓል ያለ) “ መጠኑን ሳያልፍ አንተም አሸብርቅ” ይላሉ።  በአዘቦት ቀን አሸብርቀህ መውጣት ማሸነፍህን አለ አግባብ መጠቀም ነው። ማሸነፍና መሸነፍ ሁሌም በሕይወት ውስጥ መልኩን እየለዋወጠ እየተተገበረ የሚሄደ ነው። አሸናፊ ስትሆን ተሸናፊውን ማሰብ አለብህ።
እኔ ጋ ትርፍ ልብስ ካለ፣ ራቁቱን ላለው አካፍላለሁ። እሱ ተሸናፊ ነውና፣ እንዲሁ ይሂድ አልልም። ዞር ብዬ ካየሁት፣ እኔም እኮ ደግሞ ሌላ ጋ ተሸናፊ ነኝ። አንድን ጎረምሳ ጠራሁት። የአእምሮ ሕመምተኛ ነው። ልብስና ጫማ ሰጠሁትና፤ የቀረውን በፌስታል ጠቅልዬ፣ “ይዘህ ሂድ” አልኩት። ወጣቱ አንገፍግፎት “ኧረረረ…. ይዤ  አልሄድም። እንደውም እንግዳ ከሀገር ቤት መጥቶ ቤቱ ጠቧል። የባስ ያጥብብበው እንዴ ቤቱን?” አለ፡፡ ምናለ ጣሪያ ላይ ቢያሳድረው? ለሌላ ሰው ቢወስደው? ወስዶስ ቢሸጠው? “ይህቺን ከለበስኩ ሌላው ትርፍ ነውና ይቅርብኝ” ማለቱ ነው። የእሱን ሕይወት ተመኘሁ። የሚፈልገውን ካገኘ ሌላ ትርፍ መሰብሰቡ አላስፈለገውም።

Read 708 times