Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 14 January 2012 10:31

ኢህአዴግ፤ “እኔን የመሰለ ሌላ ማንም የለም!” ይላል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የአገራችን ፓርቲዎች መመሳሰል እንደመንትዮች ነው

“ከ80 ሚሊዮን ህዝብ ውስጥ፤ ብልህነትና ብቃት የያዙ ዜጎች ሊጠፉ አይችሉም” የምንል ከሆነ ደግሞ፤ ዋናው ችግር የነፃነት እጦት ነው ወደሚል መደምደሚያ መሄድ ሊኖርብን ነው። በሌላ አነጋገር፤ ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲ ከሌለ፤ ሰበቡ ሌላ ሊሆን አይችልም - አንድም የህዝቡ ድክመት ነው፤ አልያም የመንግስት አፈና ነው። ወይም ደግሞ የሁለቱ ቅልቅል።

የአገራችን ፓርቲዎች በሃሳብ ይቀራረባሉ ወይስ ይራራቃሉ? በሃሳብ የሚራራቁ ከሆነ፤ “የትኛው ሃሳብ የትኛው ፓርቲ” እንደሆነ ለመለየት ቀላል ይሆንልናል። ግን ቀላል ሆኖ አልተገኘም። ስትሞክሩት፤ ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ታያላችሁ። ለምን? የፓርቲዎቹ ሃሳብ በጣም ተቀራራቢና ተመሳሳይ ነዋ። በአብዛኛው፤ አንዱ የሌላው “ፎቶ ኮፒ” ሊመስለን ይችላል። እስቲ በጨዋታ (በጌም) መልክ እንሞክረው።

ኢትዮጵያ፤ “በህብረቀለም ያሸበረቀና ውብ ታሪክ ያላት አገር ነች” ... ይህን ሃሳብ ወይም ይህን አባባል የምንሰማው ከየትኛው ፓርቲ እንደሆነ ለማወቅ ሞክሩ። ከኢህአዴግ ወይስ ከተቃዋሚ? በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ የተለያዩ ሃሳቦችንና አባባሎችን እየጠቀስኩ ይህንኑን ጥያቄ አቀርብላችኋለሁ። ከጨዋታው ጎን ለጎን የምናነሳው ቁምነገር አለ።  “ከኔ ሌላ ለኢትዮጵያ የሚበጅ ፓርቲ የለም” የሚለውን የኢህአዴግ እምነት እንፈትሻለን። እንዲሁ በደፈናው ሳይሆን፤ ከኢህአዴግ የሚሰነዘሩ መከራከሪያዎችን መጥቀስ ይኖርብናል - የሚሰነዘሩበት ጥያቄዎችንም ጭምር። ለመሆኑ፤ ኢህአዴግ፤ “ከኔ ሌላ የለም” የሚለው ለምንድነው?

በኢህአዴግ የሚቀርቡ ሁለት ምክንያቶች

ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲ የለም። ለሚቀጥሉት አመታትም አይጠናከሩም

በሃሳብ እንራራቃለን፤ የኢህአዴግን ሃሳብ ካልተቀበሉ ዋጋ የላቸውም

ለኢህአዴግ የሚቀርቡ ሁለት ጥያቄዎች

ጠንካታ ተቃዋሚ ፓርቲ የመፍጠር ችሎታ፣ በኢትዮጵያውያን ውስጥ የለም?

የኢህአዴግና የተቃዋሚዎች ሃሳብ በመቀራረቡ ለመለየት አስቸጋሪ መሆኑስ?

በኢህአዴግና በበርካታ ተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል የሚታየው የጥላቻ ስሜት እንደ እሳት የሚንቀለቀል መሆኑን አልክድም። በየጊዜው የሚፈጥሩት ውዝግብና የሚወራወሩት ውንጀላም፤ “አለቅን” ያሰኛል። የሚያጣላቸውና የሚያወዛግባቸው ነገር፤ ምንኛ ትልቅ ጉዳይ ቢሆን ነው? ከፓርቲዎቹ የምታገኙት መልስ ተመሳሳይ ነው። “እኔ መልአክ፤ እሱ ሰይጣን... የኔ ሃሳቦች አገርን የሚያመጥቁ፤ የእሱ ሃሳቦች አገርን የሚቀብሩ...” በሚል መንፈስ የፀባቸውን መንስኤ ይዘረዝራሉ። የጠላትነታችን መንስኤ፤ በሃሳብ እጅግ ስለምንራራቅ ነው ይላሉ - ኢህአዴግም፤ ተቃዋሚዎችም።

ኢህአዴግ፤ ለዚህች አገር፤ “ከኔ ሌላ ማንም የላትም” በማለት የሚከራከረውምኮ፤ “በሃሳብ እንራራቃለን” የሚል ምክንያት ላይ በመመርኮዝ ነው። ጠልቀን ከመግባታችን በፊት፤ በቅድሚያ አንድ ጥያቄ ልታነሱ ትችላላችሁ። ለመሆኑ፤ ኢህአዴግ ለኢትዮጵያ ብቸኛ ተስፋ ነኝ ብሎ ያምናል? “አገሪቱ ከኔ ሌላ ማንም የላትም” ብሎ ያስባል? አዎ፤ በተደጋጋሚ በራሱ በኢህአዴግ አንደበት የተገለፀ ጉዳይ ስለሆነ፤ ምሳሌዎችን መጥቀስ እንችላለን። ኢትዮጵያን ወደ ለውጥ የመምራት “ታሪካዊ ግዴታ ተጥሎብኛል” ብሏል ኢህአዴግ - በ2000 አ.ም ባሳተመው ልዩ የሚሊኔየም እትም። ለረዥም አመታት የመንግስትን ስልጣን ይዞ እንደሚቀጥልም በዚሁ የመፅሄት እትሙ በዝርዝር ገልጿል። ይህም ብቻ አይደለም።

ኢህአዴግ፤ በ2002 አ.ም በተካሄደው ምርጫ፤ ከ99.5 በመቶ በላይ ካሸነፈ በኋላ ባሳተመው መፅሄት፤ ለረዥም አመታት በስልጣን ላይ እንደሚቆይ ከነምክንያቱ  ለማስረዳት ሰፊ ትንታኔ አቅርቧል። ኢህአዴግ፤ “ከኔ ሌላ ተስፋ የላችሁም” ብሎ እንደሚያምን ያን ያህልም አከራካሪ አይደለም። ይልቅ ወደ ምክንያቶቹ እንሻገር። ኢህአዴግ የመጀመሪያውን ምክንያት ሲያቀርብ፤ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ደካማ እንደሆኑና ስልጣን የመያዝ ብቃት እንደሌላቸው ይገልፃል። ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር በሃሳብ እጅግ እራራቃለሁ የሚለው ኢህአዴግ፤ የኔን ሃሳብ ካልተቀበሉ ወደፊትም አይጠናከሩም፤ ስለዚህ ለረዥም አመታት በስልጣን ላይ እቆያለሁ፤ በማለት ሁለተኛውን የመከራከሪያ ምክንያት ያቀርባል።

የኢህአዴግ መከራከሪያ ምክንያቶች አሳማኝ ናቸው? የመጀመሪያው ምክንያት ብዙም አያስኬድም። እንዲያውም ኢህአዴግን ተጠያቂ ሊያደርግ የሚችል ምክንያት ነው። ኢህአዴግ በልበሙሉነት፤ “ተቃዋሚ ፓርቲዎች ደካማ ናቸው” ሲል፤ “ደካማ አይደሉም” የሚል ምላሽ ይዘው የሚመጡ እንደሚኖሩ አያጠራጥርም። ነገር ግን፤ ዋናው ጉዳይ ይህ አይደለም።

በአንድ አገር ስልጡን የነፃነት ስርአት እንዲሰፍን፤ ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲ አስፈላጊ እንደሆነ ብዙ ጊዜ ሰምተናል። ኢህአዴግም ደጋግሞ ተናግሯል። ነገር ግን፤ ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲ ከሰማይ አይወርድም። አንደኛ፤ ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲ ለማቋቋም የሚችሉና ብቃት ያላቸው ዜጎች ያስፈልጋሉ። ይሄ የዜጎች ሃላፊነት ነው። ሁለተኛው ደግሞ የመንግስትና የገዢው ፓርቲ ሃላፊነት ነው፤ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎችን ለማካሄድ የሚያስችል ፤ ለነፃነትና ለህግ የበላይነት ክብር የሚሰጥ የዲሞክራሲ ጅምር መኖር አለበት። የተሟላ ነፃነት ባይሆን እንኳ፤ የነፃነት ጅምር ስርአት ያስፈልጋል። ኢህአዴግ ደግሞ፤ ለፖለቲካ ነፃነትና ለፓርቲ እንቅስቃሴ ሰፊ እድል የሚሰጥ የዲሞክራሲ ጅምር አስፍኛለሁ ይላል።

ታዲያ፤ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ለምን ደካማ ሆኑ? መቼም እርግማን ሊሆን አይችለም። ታዲያ፤ የዜጎች ድክመት ነው?  ከኢህአዴግ መሪዎችና አባላት በስተቀር፤ ጠንካራ ፓርቲ የመመስረት ችሎታና ብቃት ያላቸው ዜጎች በአገራችን ስላልተፈጠሩ ይሆን? የጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲ ጠቀሜታን የመገንዘብ ብልህነት ያላቸው ዜጎች ስላልተገኙ ይሆን? ምላሻችን “አዎ” የሚል ከሆነ፤ ጥፋቱ የዜጎች ይሆናል፤ በአጠቃላይ ህዝቡ እንደ አላዋቂና እንደ ደካማ ወደ መቁጠር እንሄዳለን።

“ከ80 ሚሊዮን ህዝብ ውስጥ፤ ብልህነትና ብቃት የያዙ ዜጎች ሊጠፉ አይችሉም” የምንል ከሆነ ደግሞ፤ ዋናው ችግር የነፃነት እጦት ነው ወደሚል መደምደሚያ መሄድ ሊኖርብን ነው። በሌላ አነጋገር፤ ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲ ከሌለ፤ ሰበቡ ሌላ ሊሆን አይችልም - አንድም የህዝቡ ድክመት ነው፤ አልያም የመንግስት አፈና ነው። ወይም ደግሞ የሁለቱ ቅልቅል።

እና ምን ትላላችሁ? “ተቃዋሚዎች ደካማ ስለሆኑ፤ ለረዥም አመታት በስልጣን ላይ እቆያለሁ” የሚለው የኢህአዴግ መከራከሪያ ያስኬዳል? ሁለተኛውንም መከራከሪያ እንመልከት -  “ከተቃዋሚዎች ጋር በሃሳብ እራራቃለሁ። የኔን ሃሳብ ካልተቀበሉ፤ ደካማ እንደሆኑ ይቀጥላሉ፤ ስለዚህ ለረዥም አመታት የመንግስት ስልጣን በእጄ ይቆያል”። ይሄም መከራከሪያ፤ ብዙ አያራምድም። በብዙ ችግሮች የተከበበ ነው። እንዲያው፤ “ኢህአዴግ ትክክለኛ ሃሳቦችን የያዘ ፓርቲ ነው” ብንል እንኳ፤ የተሻለ ሃሳብ የሚያመጣ ዜጋ እንዴት ይጠፋል? ቢያንስ ቢያንስ ደግሞ፤ ተወዳዳሪና ተፎካካሪ ሃሳቦችን የሚያመነጭ ዜጋ እንዴት አይኖርም? ከዚያ ሁሉ ህዝብ ውስጥ፤ ከኢህአዴግ ውጭ ጥቂት ብልሆች አይፈጠሩም?

መከራከሪያውን የከበቡት ችግሮች እነዚህ ብቻ አይደሉም። ለመሆኑ፤ ኢህአዴግና ተቃዋሚዎች፤ በተደጋጋሚ እንደሚነግሩን፤ “በሃሳብ የተራራቁ ናቸው? ሊራራቁ አይችሉም። የአገራችን ዋና ዋና ፓርቲዎች፤ በማንኛውም አገር እንደሚታዩ ዋና ዋና ፓርቲዎች፤ እርስበርስ ያን ያህልም በሃሳብ እንደማይራራቁ ካሁን በፊት መፃፌን አስታውሳለሁ። ለየት ያሉና በሃሳብ የሚርቁ ጥቃቅን ፓርቲዎች መኖራቸው አይቀርም። ዋና ዋና ፓርቲዎች ግን፤ በየትም አገር ቢሆን፤ በተቀራራቢ ሃሳብ ዙሪያ የሚሽከረከሩ ናቸው። ከአገሪቱ ስልጣኔ ወይም ኋላቀርነት፤ አገሪቱ ውስጥ በሰፊው ከሰፈነው አስተሳሰብና ልማድ ጋር የተያያዘ ነው የፓርቲዎች ሃሳብ።

የአሜሪካ ዋና ዋና ፓርቲዎች፤ በሃሳብ ይቀራረባሉ። ከሌላ አገር ፓርቲ ጋር ሲነፃፀሩ፤ የአሜሪካ ፓርቲዎች፤ ለነፃ ገበያና ለግለሰብ ነፃነት የተሻለ ክብር ይሰጣሉ። አሜሪካ ውስጥ በስፋት የሰፈነውን አስተሳሰብ በማንፀባረቅ ይመሳሰላሉ። “በመጠኑ ወደ ግራ ያዘነበሉ ወደቀኝ ያዘነበሉ” በማለት ዋና ዋናዎቹን ፓርቲዎች መለየት ቢቻልም፤ በሰፊው ሲታዩ ግን እጅግ ተቀራራቢ ናቸው። ከሌላ አገር ፓርቲዎች ጋር ሲነፃፀሩ፤ የአሜሪካ ዋና ዋና ፓረቲዎች፤ ወደ ካፒታሊዝም ያመዝናሉ።

ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ የአፍሪካ ፓርቲዎች ደግሞ፤ ለነፃነት ክብር ባለመስጠት ይመሳሰላሉ። ከ1960ዎቹ ፖለቲካ (ማለትም ከሶሻሊዝምና ከፋሺዝም አስተሳሰብ) ጋር የተቆራኙ ናቸው የአፍሪካ ዋና ዋና ፓርቲዎች። “ይሄኛው ትንሽ ወደ ቀኝ፤ ያኛው ደግሞ ወደ ግራ ያዘነብላሉ” በማለት ለመለየት ካልሞከርን በቀር፤ እግጅ ተመሳሳይ ናቸው - የሶሻሊዝም አልያም የፋሺዝም ግርፍ ናቸው። የአገራችንም እንዲሁ። ለዚህም ነው በሃሳብ ተቃራራቢ ከመሆናቸው የተነሳ፤ አንዱን ከሌላው መለየት ቀላል የማይሆነው። ካላመናችሁ ራሳችሁ ሞክሩት።

አንድ ፓርቲ፤ ስለ ኢትዮጵያ ጥንታዊ ስልጣኔ፤ ምን እንዳለ ልጥቀስላችሁ። የኢትዮጵያ ስልጣኔ፤ “ከአለም ታላላቅ ስልጣኔዎች ውስጥ የሚመደብ እንደነበር ይታወቃል” ብሏል ፓርቲው። የትኛው ፓርቲ ይመስላችኋል? ከኢህአዴግ የሚሌኒየም ትንታኔ የተወሰደ ጥቅስ ነው። ነገር ግን፤ የአንድነት ፓርቲ የፖለቲካ ፕሮግራም ውስጥም፤ በመጀመሪያው አረፍተነገር ተመሳሳይ ሃሳብ አጉልቶ ይነሳል። “አገራችን ኢትዮጵያ፤ ከቀደምት የአለማችን ስልጣኔዎች የሚመደብ ረዥም ታሪክ ያላት...” በማለት ይቀጥላል የአንድነት ፓርቲ ሰነድ።

“አሸብራቂ ባህልና ማንነት ያላቸው ብሄር ብሄረሰቦች የያዘች፤ የተለያዩ ሃይማኖታዊ እምነት ተከታይ ዜጎቿ ተቀላቅለው የሚኖሩባት” በማለት ኢትዮጵያን ለመግለፅ የሚሞክረውስ የትኛው ፓርቲ ነው? ከዚያው ከአንድነት ፓርቲ ፕሮግራም የተገኘ ገለፃ ነው።  ነገር ግን፤ የኢህአዴግ መፅሄትም፤ ኢትዮጵያ፤ በርካታ ብሄር በሄረሶች ባህል እየተወራረሱና እየተቀላቀሉ፤ የሃይማኖት እምነቶችም እየተከባበሩ የሚኖሩባት እንደሆነች በመጥቀስ፤ “በህብረቀለም ያሸበረቀና ውብ ታሪክ ያላት አገር ነች” ሲል ፅፏል።

ጥንታዊው ስልጣኔ ግን አልዘለቀም። አገራችን በጥንታዊ ስልጣኔ የምትታወቅ ቢሆንም፤ ከጊዜ በኋላ “ዘመናዊት ኢትዮጵያ ይበልጥ የምትታወቀው በእርስ በርስ ጦርነቶች... እንደዚሁም ... በድህነት ነው” ... የየትኛው ፓርቲ አባባል ይመስላችኋል?

ስልጣኔዋ እያሽቆለቆለ እንደመጣ የገለፀው ሌላኛው ፓርቲ በበኩሉ፤ “አገራችን በአለም ደረጃ የድህነትና የተመዋችነት ተምሳሌት የምትሆንበት ደረጃ ላይ ደረሰች...” ብሏል። ይሄኛው አባባልስ? (ይሄኛው አባባል የኢህአዴግ ነው። የመጀመሪያው ደግሞ የአንድነት ፓርቲ)

በእርግጥ፤ በጥንታዊ የታሪክ ጉዳዮች ላይ፤ የአገሪቱ ፓርቲዎች ተቀራራቢ ሃሳብ ቢኖራቸው አይገርምም ትሉ ይሆናል። ተቀራራቢነታቸው ግን ያ ብቻ አይደለም። የቅርብ ጊዜ ታሪክ፤ የአፄ ሃይለስላሴና የደርግ ስርአትን በተመለከተ የፓርቲዎቹን ሃሳብ እንመልከት።

ኢትዮጵያ፤ በከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰትና በብሄር ብሄረሰቦች መብት ጥሰት የምትታወቅ አገር እስከመሆን መድረሷን ይጠቅስና፤ “የመንግስትን ስልጣን የጨበጡትም ይሁኑ በተቃዋሚነት የተሰለፉት ወገኖች ይህን ለማስተካከል ያደረጉት ትግልና ሙከራ ፤ ችግሩ መፍትሄ እንዲያገኝ ያደረገው አስተዋፅኦ እምብዛም ነው” ይላል አንደኛው ፓርቲ። ከታሪክ የምንገነዘብ አንድ መሰረታዊ እውነት፤ “የአገራችን ብሄራዊና ሃይማኖታዊ ብዙህነት... ለማስተናገድ የተደረጉ ሙከራዎች ስኬታማ ሳይሆኑ የቀሩበት ሂደት መሆኑን ነው” ይላል ሌላኛው ፓርቲ።

(የመጀመሪያው የአንድነት ፓርቲ አባባል ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ የኢህአዴግ አገላለፅ ነው።)

“ፊውዳላዊ ስርአት፤ ...በመላው ጭቁን ዜጎች ትግል ሊንኮታኮት በቃ፡፡ ነገር ግን ህዝቡ በአግባቡ ያልተደራጀ ስለነበር ስልጣን በቀላሉ ወደ ወታደራዊው ደርግ ተሸጋገረ።... የአገራችን ህዝቦች በደርግ ፀረዴሞክራሲያዊ አገዛዝ ያለአንዳች ልዩነት የተረገጡበት ሁኔታ መኖሩ የሚያከራክር ጉዳይ አይደለም” ይላል አንደኛው ፓርቲ።

“የኢትዮጵያ ህዝብ ባካሄደው ትግል ዘውዳዊው አገዛዝ የተገረሰሰበት ሁኔታ ቢፈጥረም፤ የተፈጠረውን ሁኔታ በመጠቀም ስልጣን የያዙት ወታደራዊ መኮንኖች ለሰብአዊ መብት ጥብቃ፤ ለብሄር ብሄረሰቦች መብት መከበር የተደረገውን ትግል በመደፍጠጥ ህዝቡን ለከፋ ስቃይና አፈና ዳርገውታል” ይላል ሌላኛው ፓርቲ።

(የመጀመሪያው የኢህአዴግ፤ ሁለተኛው ደግሞ የአንድነት ፓርቲ አገላለፅ ነው።)

በእርግጥ፤ ስለአሁኑ ዘመን ሲናገሩ እርስ በርስ ይወጋገዛሉ። ነገር ግን፤ ስለ መብት፤ ስለ ኢኮኖሚ እና ስለ ማህበራዊ ጉዳዮች የዘረዘሯቸውን ሃሳቦች (ፖሊሲዎች) ብጠቅስላችሁ፤ ከተመሳሳይነታቸው የተነሳ አንዱን ከሌላው ለመለየት መቸገራችሁ አይቀርም።

 

 

Read 3060 times Last modified on Saturday, 14 January 2012 10:46