Tuesday, 23 April 2024 00:00

ሀርመኒ ሂልስ ት̸ ቤት ዓለም አቀፍ የመጽሐፍ ቀን አከበረ

Written by 
Rate this item
(0 votes)
(በብርሃኑ በላቸው አሰፋ ፣ የ”ክቡር ልጆች” መጽሐፍ ደራሲ)
ዓለም አቀፍ የመጽሐፍ ቀን፤ የንባብ ባህልን ለማዳበር፣ ደራስያንንና አታሚዎችን ለማበረታታት ይከበራል፡፡ እ.ኤ.አ. በ1995 ዓ.ም ነበር ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ የመጽሐፍ ቀን የተከበረው፡፡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት ቀኑን የንባብ ልማድ እንዲዳብርና በተለይም ወጣቱን ትውልድ በማነቃቃት፣ የመረጃ ፍሰቱ በንባብ እንዲጎለብት ለማበረታታት በየዓመቱ ያስበዋል፡፡
በሀገራችንም ሀርመኒ ሂልስ ት̸ ቤት በትላንትናው ዕለት በተለያዩ ዝግጅቶች ቀኑን አክብሯል፡፡ ት̸ ቤቱ ደራሲያን መጽሐፍቶቻቸውን ለተማሪ ወላጆች እንዲያስተዋውቁ በማድረግ፣ የልጆች መጽሐፍ ደራሲያን ለተማሪዎች መጽሐፍ እንዲያነቡ በማድረግና የተማሪዎችና መምህራን መጽሐፍ የማንበብ ስነ ስርዓት በማካሄድ ዓለማቀፍ የመጽሐፍ ቀንን በድምቀት አስቦታል፡፡ በመርሃግብሩ ላይ የልጆች መጽሐፍ ደራሲ እምነቴ ድልነሳን ጨምሮ ሌሎችም ታድመዋል፡፡
የት̸ ቤቱ ዳይሬክተር ሩት መንበረ፣ ተማሪዎች የንባብ ባህላቸውን እንዲያሳድጉ ታስቦ ቀኑን አክብረነዋል ብለዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ኤሌክትሮኒክስ የመጽሐፍ ንባብ ትልቁ ተግዳሮት በመሆኑ ልጆች በፍቅር እንዲያነቡ ምቹ ሁኔታን እየፈጠሩ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
ልጆች እና መጻሕፍት
በቅርቡ የተካሄደ አንድ ጥናት እንዳመለከተው፤ ምንም እንኳን 70 በመቶ ወላጆች ማታ ማታ ለልጆች ጣፋጭ ታሪኮችን ማንበብ አስፈላጊነቱን ቢያምኑም፣ ግማሽ ያህሉ ብቻ ይተገብራሉ፡፡ ከአምስት ቤተሰቦች አንዱ ደግሞ በስራ ብዛት የተነሳ ለልጆች የማንበብ ልማድ የለውም፡፡
ይሁን እና ማምሻውን የሚነበቡ ተረቶች ምን ጥቅም አላቸው ?
በወላጅና በልጅ መካከል ያለውን ግንኙነት ያጠናክራሉ
የልጆችን የማንበብ ክህሎት ያዳብራሉ
የልጆችን የፈጠራ አቅም ያጎለብታሉ
የልጆችን የቃላት ችሎታ ያሳድጋሉ
የልጆችን የስሜት ብስለት ያዳብራሉ
የልጆችን የአእምሮ ጤና ያበለፅጋሉ
ለአካላዊ ጤንነት ምግብና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እንደሚያስፈልግ ሁሉ ለአእምሮ እድገት ደግሞ ንባብ ወሳኝ ሚና አለው፡፡ ከመዋዕለ ህጻናት እስከ አራተኛ ክፍል ልጆች ለማንበብ መሰረታዊ ክህሎትን ይማራሉ፡፡ ከአራተኛ ክፍል ጀምሮ ደግሞ ለመማር ያነባሉ፡፡ የፔዳጎጂ ፅንሰ ሃሳብም ተማሪዎች በራሳቸው እንዲማሩና በቀላሉ እንዲገነዘቡ በማድረግ ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የማንበብ ፍላጎትና ተነሳሽነት ይጠይቃል፡፡
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ የልጆች የንባብ ክሂል ብቃት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ ነው፡፡ የሃገራችን ተማሪዎች የመጀመሪያ እርከን ሲጨርሱ ለምን ማንበብ ያዳግታቸዋል ? የተነበበላቸውን ለምን መረዳት ይቸግራቸዋል ? የሚሉት ጥያቄዎች መልስ ያሻቸዋል፡፡
ልጆች የማንበብ ልማድን እንዲያዳብሩ
በየቀኑ ማንበብ ማለማመድ
የስነ ልቦና ባለሙያዎች እንደሚሉት፤ በየቀኑ ለ20 ደቂቃ ተረት ማታ ማታ የሚነበብላቸው ልጆች፣ የአእምሮ ጤናቸው ከመጠበቁ ባሻገር የፈጠራ አቅማቸው ከፍ ያለ ነው፡፡
ወላጆች መጽሐፍትን በማንበብ አርአያ ሊሆኑ ይገባል
ምቹ የንባብ ከባቢ መፍጠር
ከልጆች ጋር ቤተ መጽሐፍት መጎብኘት
ልጆች የሚፈልጉትን መጽሐፍ እንዲመርጡ እድል መስጠት
ልጆች ደስ የሚላቸውን መጽሐፍ ደጋግመው እንዲያነቡ ማበረታታት ይገኙበታል፡፡
Read 530 times