Monday, 22 April 2024 00:00

ጦርነትን የሚንቅ ጀግና እንፍጠር!

Written by 
Rate this item
(4 votes)

አሜሪካ በእርስ በርስ ጦርነቱ ወቅት ያጣችው የሰው ሕይወትና ሀብት የትየለሌ ነው። በዘመኑ የነበረው አብረሃም ሊንከን፣ ለአሜሪካ ዳግም ሀገር መሆን የከፈለው ዋጋና የፈሰሰው የዜጎች ደም ቀላል አይደለም።

የኋላ ኋላ ጦርነቱ አብቅቶ፣ችግር በሰማዩ ላይ ካረበበ በኋላም የመከራው ገፈት ቀማሽ ሕዝቡ ነው። ሠራተኛ ከሥራ ሲቀነስ፣ወታደር ወደቤተሰቡ ሲመለስ፣ብዙ ቤተሰብ ወላጅና ልጆቹን ሲያጣ፣የጨለማው ድባብ፣የሐዘኑ

ምሬት ሀገሪቱን ሲዖል አድርጓት ነበር።
እውነት ነው፤ በጦርነቱ የአንድነት ኀይሉ አሸንፏል። የደቡቡ ወገን የሮበርት ሊ ጦር ተሸንፏል። ዩሊሰስ ግራንት ሲማርክ፣ሮበርት ሊ ከእነ ጦሩ ተማርኳል። ከጦርነቱ በኋላ ደብዛው ጠፍቶ የቆየው ጀኔራል ሸርማን፣

ዐሳውን ለማጥመድ ባሕሩን ብሎ አትላንታን በከባድ ምት ቢመታም፤የአትላንታ ቁስልና ጠባሳ፣መልሶ የአሜሪካ ነው። የገደለው ባልሽ የሞተው ወንድምሽ፣ሐዘንሽ ቅጥ አጣ፣ከቤትሽ አልወጣ ፤ነበር ነገሩ።
እውነት ለመናገር፣ከእርስ በርስ ጦርነት ይልቅ ከሌሎች ሀገራት ጋር የሚደረጉ ጦርነቶች ቀላል ናቸው። ለዚህ ደግሞ ማሳያዋ ራሷ አሜሪካ ናት። ለምሳሌ በዐለም ላይ ካደረገቻቸው ጦርነቶች ይልቅ የበርካታ ሰዎች

ሕይወት ያለፈው በእርስ በርስ ጦርነቱ ነው። በንጽጽር እንይ ከተባለ፣
በኮሪያ ጦርነት -  54,000
በቬትናም -  58,000
በሁለተኛው የዐለም ጦርነት-  400,000
በአንደኛው የዐለም ጦርነት-  117,000
በእርስ በርሱ ጦርነት - 620,000
የዜጎች ሕይወት ጠፍቷል።
ከዚህ በተጨማሪ፣  የደረሰው የኢኮኖሚ ቀውስ ቀላል አይደለም። ይህ ቀውስ የሚለካው ለጦርነቱ በወጣው ወጭና በጦርነቱ በወደሙት ንብረቶች ብቻ ከሆነ ግምታችን የተሳሳተ ነው። በጦርነቱ የሚያልቁት ወጣቶች

ጭንቅላትና አቅም፣ በገንዘብ የማይተመን ተዐምር ሠሪ ሀብት ነው።
ቅድም ካነሳነው የአሜሪካ ጦርነት ጀርባ፣ተገኘ ከሚባለው ድል በስተኋላ፣በርካታ የአሜሪካ እናቶች አልቅሰዋል። ኁልቁ መሳፍርት የሌላቸው  የሠርግ ሳይሆን የልቅሶ ድንኳኖች በየደጁ ተጥለዋል። በዚህ በተጣሉት የልቅሶ

ድንኳኖች ሳቢያ እንባ እንደጎርፍ ያፈሰሱት ጥቂት አይደሉም።
በተለይ በአሜሪካ ታሪክ ለሊንከን አድናቆት ያጎረፈለት አንድ ያልተለመደ ነገር ነበር። ያም አምስት ልጆቿን ላጣችው እናት በራሱ እጅ የማጽናኛ ደብዳቤ መጻፉ ነው። የሚገርም ነው። የአንዲት ታላቅ ሀገር

ፕሬዚደንት እስከመኖሯም ለማትታወቅ አንዲት መናጢ ደኻ እናት፣ ደብዳቤ መጻፉ ጉድ ያስብላል። ይሁን እንጂ በምንም ሁኔታ ላይመለሱ የተቀጠፉትን የሕይወቷን ተስፋዎች አይመልስልትም። ለሊንከን ታላቅ

የፖለቲካ ድል ነው፤ለእናትየው ግን የማይጠገን ስብራት ነው።
ጦርነቱ በድል ተጠናቅቆ ሲያበቃ፣በደማቁ ድል ማግስት ወደ ጎተራ የሚገባ አንድ ኩንታል እህል የለም። የሚለቀመው አጥንት ነው። የሚተርፈው ጸጸት ነው። የዚህ ዐይነት በርካታ ጦርነቶች አልፈዋል። እናቶች ልጆቻቸው

እንደ ችቦ እጅብ ብለው እየዘፈኑ ሄደው፣ላይመለሱ ነድደው ሲቀሩ፣ወገባቸውን አሥረው በእንባ ሲታጠቡ ማየት የሕዝቦች ዕጣ ነው። በነዚያ በነደዱት ወጣቶች ብርሃን ሀገር አትደምቅም፤ከአድማሱ ላይ ጨለማ

አይወገድም። እንደገና ሌላ ወጣት ይገበራል። አንዳንድ ሀገራት የዚህ ዐይነት ጦርነቶች እንዳይደገም፣ዳናቸውም ወደሚቀጥለው ትውልድ እንዳያልፍ፣ ከዚያችው ቀን ጀምረው መስመር ያበጃሉ። ለዚያ ሰቀቀን ሥዕል

ያበጁለታል፤ትዕይንቱ እንዳይደገም መሰመር ያሠምራሉ። አንዳንዶች ግን እንደ መዝሙር ያዜሙታል፤እንደ ውበት ይተርኩታል።
ቁስሉን እንደ ንቅሳት፣ሕመሙን እንደ ምቾት ያቀነቅኑታል።...የወንድ ልጅ እናት ታጠቂ በገመድ፣ልጅሽን አሞራ እንጂ አይቀብረውም ዘመድ፤ እያሉ እናት ወልዳ ለፍሬ ሳይሆን፣ወልዳ ለአሞራ መስጠት እንዳለባት

ይነገራታል። ወይም በሌላ ዜማ፣”መላኩ ተፈራ፣
የእግዜር ታናሽ ወንድም፣የዛሬን ማርልኝ
ዳግም ወንድ አልወልድም” ይባላል።
የጀግና እናት እንባ የሌላት ቋንጣ ሆና እየነደደች ትኖራለች። በአንድ ጦርነት ውስጥ እናት ብቻ ሳትሆን እናት ሀገርም ብዙ የተስፋ ቡቃያዎቿን ታጣለች። ጠመንጃ ይዘው በየፈፋው የወደቁ ልጆቿ መልክ ቢፈተሽ፣ብዙ

ሳይንቲስቶች፣ሺህ መሐንዲሶች፣ተመራማሪዎች፣ወዘተ ይኖራሉ። ይህን ለማየት በዐለማችን ላይ ከተደረጉ ጦርነቶች የተረፉና በኋላ የታላላቅ ግኝቶችና ውጤቶች ባለቤት የሆኑ ሰዎችን ማየት በቂ ነው።እንግዲህ እነዚህ

ትሩፋን ከሞት አፍ ስለወጡ ያንን ሠሩ እንጂ አብረዋቸው ወድቀው የቀሩት ምን ሊሠሩ ይችሉ እንደነበር የሚገምት የለም። ብቻ በድኑ ያምማል።
ታዲያ እነዚያ ሁሉ ወደ ተሰጥዖና ክሎታቸው ሳይደርሱ እሳት በልቶ ዐመድ ያደርጋቸዋል። ወጣቶች በጦርነት ውስጥ ሲማገዱ፣ያልተፈለፈሉ እንቁላሎች ናቸው። ገና ፍሬያቸው ሳይታይ፣ቀናየውን ሳያገኙ ከንቱ ሆነው

ይቀራሉ። ይህ በሰው ልጆች ታሪክ አሳዛኙ ትራጀዲ ነው።
ጦርነት አንዳንዴ ፈጣን ፈውስ፣ወሳኝ መፍትሔ ሊሆን ይችላል። ሰው በገዛ ሀገሩ በነፃነት እንዳይኖር፣ቀንበር ጫንቃው ላይ ሊጭኑበት “አጎንብስልኝ”ሲሉት፣ተቆጥቶ ከሺህ ቀን ባርነት የአንድ ቀን ነፃነት ሲል፣ያኔ “አንዱን

ወንድ እንደሺህ...መመረቅ ግድ ይላል። ሠፈር ተቀምጦ የሚያውደለድል፣ጦር ግንባር ሄዶ ጠላቱን አምሶ ሲያልፍ፣ የጀግና ዘፈን ይዘፈንለታል እንጂ ደረት ተጥሎ አይለቀስም። ጭካኔውም እንደ ርኅራኄ ይታያል።
በጀመርናት ኀያል ሀገር መሪ በትሩማን ገጠመኝ ሰው መግደል፣ ማረፍና ማሳረፍ የሚሆንበትን አጋጣሚ እንይ። ከዕለታት በአንዱ ቀን የ18ኛው ፕሬዚደንት የዩሊሰስ ግራንት ሴቶች ልጆች ትሩማን ቤት ይገኙና ሁሌ

የሚገርማቸውን ጥያቄ ይጠይቋቸዋል።
“ለመሆኑ ሒሮሽማና ናጋሳኪ ላይ ቦምብ ያስጣሉ ቀን እንቅልፍ ወሰደዎት?”
ሲሏቸው፣ መልሳቸው የሚያስደነግጥ ነበር።
“በጣም ኀይለኛ እንቅልፍ ነበር የወሰደኝ” አሉ።
”እንዴት በሰዎች ላይ ያንን ሁሉ እሳት አዝንበው፣ እንቅልፍ ሊወስዳቸው ቻለ?”ብለን መጠየቃችን አይቀርም። ይሁን እንጂ ጉዳዩ ሲፈተሽ፣የጦርነቱ መንሥዔና ዓላማ ሌሎችን ዕረፍት ለመንሳት ኂትለር የጠነሰሰው

ስለነበር፣ሌሎቹ የሚዋጉት ለህዝባቸው ሕልውናና ለሀገራቸው ሉዐላዊነት ስለነበር፣ጦርነቱን በድል ደምድሞ ከዚያ አንገፍጋፊ ስቃይ መውጣት ያስፈልግ ነበር።
ጦርነቱን ያለማሸነፍ ደግሞ የሚያስከትለው ፍዳ እንቅልፍ አይሰጥም። ይሁን እንጂ ጦርነትን ከሚያዝዘው በላይ ጦርነቱ ላይ በቀጥታ የተሳተፈው ወታደር የተለየ ስሜት ሊፈጠርበት ይችላል። በዚያው ጦርነት

የመጀመሪያውን ጄት ያበረረው ምክትል የመቶ አለቃ፣በሕይወቱ ላይ የተፈጠረው ቀውስ ሌላ ነበር። ያ ወጣት መኮንን ቦምቡን ሲጥል፣ የተጣለበት የከተማዋ ነዋሪዎች የጮኹት ጩኸት በእዝነ-ልቡናው

እየተሰማው፣ምስላቸው በዐይነ ሕሊናው እየታየው እንቅልፍ እምቢ አለው። ምንም ዐይነት ሱስ ያልነበረበት ሰው፣ሲጋራ ማጤስ፣መጠጥ መጠጣት ጀመረ። ጦርነት መልኩ ብቻ ሳይሆን ውጤቱም ልዩ ልዩ ነው።

ከጦርነቱ ዳር የሚያጋፍረውና ውስጥ ሆኖ የሚፋለመው የስሜት ድንበራቸው ይለያያል።
በአሜሪካው የእርስ በርስ ጦርነት ከግማሽ ሚሊየን በላይ ሕዝብ አልቆ፣ቁጥር ስፍር የሌለው ውድመት ደርሶ መጨረሻ ላይ የሁለቱ ወገን የጦር አዛዦች ሲገናኙ፣ ስለቀደመውና በሜክሲኮ ጦርነት አብረው በነበሩበት

ጊዜ ስለሠሩት የሼክስፒር ቴአትር ማውራት ጀምረው ነበር። የዚያ ሁሉ ሰው ደም መፍሰስ ከኪሳራና እልቂት ውጭ አንዳች ጥቅም የለውም። በምንም መንገድ ቢሰላ፣በየቱም አቅጣጫ ቢተነተን፣ ከኪሳራ የተለየ

ውጤት ሊያመጣ አይችልም።
የአሜሪካው ልዩነት ግን ያንን ጦርነት፣ “ጠባሳን ያየ በእሳት አይጫወትም” ማለታቸው ነው።
ለሀገራቸው ጥቅም ብለው እስካሁን ሲዋጉ እንኳ፣በገዛ ምድራቸው ሳይሆን በሌሎች ሀገራት ነው። እኛ ግን ዘመናችንን ሁሉ በጦርነት የፈጀን፣ጦርነት መዋጋት ብቻ ሳይሆን፣መፍጠር እንችላለን ብለን

የምንመጻደቅ፣ውርደትን እንደ ክብር የምንቆጥር ነን። ጀግና ብለን የምንዘፍንላቸውና ስማቸውን የምናነሳቸው እንኳ ጦር ሜዳ የዋሉ፣የውጭ ጠላት ብቻ ሳይሆን ወገናቸውን የገደሉትን ነው።
አሳዛኙ ነገር ብዙ ጊዜ ከፈረንጅ ብድር የምንወስደው፣ፋብሪካ ለመገንባት፣እርሻ ለማስፋፋት አይደለም፤ለመገዳደል ነው። የሥልጣን ውርርሳችንም ሁሌም በሚባል ደረጃ በጠመንጃና በኀይል ስለሆነ፣ከጥንት ጀምሮ በአንድ

እጃችን ጠመንጃ፣በሌላኛው ዳቦ ስንለምን እንኖራለን። የተፈጠርነው ለጦርነት እስኪመስል ድረስ ጭር ሲል አንወድድም፤በየትውልዱ የጦርነት እሳቶች ይነድዳሉ፤ወጣቶች እንደችቦ እሳት ውስጥ ገብተው ይነድዳሉ።

ወልዶ፣አሳድጎ ለእሳት መቀለብ ብርቃችን አይደለም። ወንድምን ገድሎ መፎከር እንደ እርም አይቆጠርም። በቀደሙት አባቶቻችን ዘመን እንደሚሰማው፣ልጃገረዷ ወፍጮ ላይ ሆና እህሉን እየሸረከተች፣ግጥም

ስትገጥም፣ዜማ ስታንቆረቁር ወንዱ ፈረሱን ጭኖ ለግድያ ይወጣል። ወይ ይገድላል፤አሊያም ይሞታል። በቅርቡ ዘመን ደግሞ ዘመናዊው ኪነት ጦር ግንባር ድረስ ሄዶ “ወደፊት በሉለት፣ይለይለት”ይላል።
ይህ በራሱ ሀገር ለማዳን ሲሆን ችግር የለበትም፤ምርጫ ሲጠፋ ሀገር መፍረስ አይገባትም። ግን ከጦርነት ሌላ ምርጫ የለም ወይ?...ችግሮችን ለመፍታት ተሞክሮ ካልተሳካ በስተቀር፣እርቅን ገፍተው ካልመጡብን

ለምን እንጋደላለን?...ለምን ገንዘባችን ይባክናል?..ሥራ አጦችን ጦር ሜዳ ወስደን ከምንማግድ፣ለምን ጠመንጃና መድፍ በምንገዛበት ብር ፋብሪካ አናቋቁምም?...እኛ ዕድገት አያስፈልገንም?...ጥሩ

ኑሮ፣ጥሩ ሕይወት አይገባንም?...በሳይንስና ቴክኖሎጂ፣በጥናትና በምርምር ከዐለም ሕዝቦች ጋር እኩል እንዳንራመድ ማን ከለከለን? ገንዘባችንስ ለልማት የሚውለው መቼ ነው?..አንጀታችንን አሥረን መልማት

ሲገባን፣አንጀታችንን አሥረን ከጠገበ ፈረንጅ መሳሪያ በመግዛት ኪሱን የምናሳብጠው እስከ መቼ ነው?
ፕሮፌሰር መስፍን፤ ስለ እኛ ጦርነት ወዳድነት እንዲህ ሲሉ ጽፈው ነበር፤
“...ጦርነትን፥ጀግንነትንና ገዳይነትን እንደ ትልቅ የክብርና የማዕረግ ምንጭ አድርጎ የሚመለከት ሕዝብ ታሪክ፤ በአጠቃላይ የጦርነት ታሪክ ቢሆን የሚያስደንቅ አይደለም። ሌላው ትልቁና አስገራሚው ነገር፣ጦርነቶቹ

በአብዛኛው በውጭ ሰዎች ቁስቆሳ የተደረጉና የተጀመሩ መሆናቸው ነው። በተለይ ቅኝ ገዢዎች በየዐውደ-ውጊያው ያጡትን ድል በተለያዩ ስልቶች በመጠቀም ሊበታትኑን ሞክረዋል።
አንዳንዶቹ እንድንገነጣጠል፣ሌሎቹ እርስ በርስ እንድንዋጋና ሰላም እንድናጣ ሌት ተቀን ሠርተዋል። እኛም ማስተዋል ስላቃቸን ጦር መዝዘን ተላልቀናል። በተለይ በቅርብ ዐመታት የብሔር ብሔረሰቦችን መብት ታክኮ

የመጣው ጥላቻ፣ ከመቼውም ጊዜ ይልቅ ሀገራችንን አደጋ ላይ ጥሏታል። በደርግ ዘመን በሕወሓት የሚመራው ኀይል አምፆ በተደረገው የዐሥራ ሰባት ዐመታት ጦርነት፣ የጠፋው የሰው ሕይወትና የባከነው ሀብት

ለልማት ቢውል ኖሮ ምን ያህል መራመድ እንችል እንደነበር መገመት አያዳግትም።
በወቅቱ ጭቆናን ተቃውሜያለሁ ያለው ደርግ፣ በተራው ጨቋኝ ሆኖ፣ዐማፅያን እግሩ ሥር ሲፈለፈሉ፣ከመደራደር ይልቅ በጠመንጃ ብቻ መፍትሔ ለማምጣት አስቦ የማያቋርጥ ጦርነት ውስጥ ገብቷል።

በቀጣዩ፣ሥልጣን ላይ የወጣው ወያኔ መራሹ መንግሥትም ከደርግ ስላልተማረ፣ወዲያውኑ ኦነግን ከመንግሥት መዋቅር በመንቀል የሴራ ፖለቲካውን ጀምሮ እርሱም በተራው እያሳደደ የሚገድለው አንድ ጠላት አዘጋጀ።

...እናም ተራራና ሜዳው ባሩድ ማሸተቱን፣ደም መጠጣቱን ቀጠለ። በምሥራቅ ኢትዮጵያም በተመሳሳይ ሌላ ተቃዋሚ ተፈጥሮ የተለመደው ደም የመፋሰስ መንገድ ቀጠለ።
በምሥራቅ ኢትዮጵያም በተመሳሳይ ሌላ ተቃዋሚ ተፈጥሮ የተለመደው ደም የመፋሰስ መንገድ ቀጠለ። ከዚያም በኋላ ሀገራችን ከጦርነት አላረፈችም። ከጦርነት የሚገኝ ምንም ትርፍ ያለመኖሩን እያወቅን እንኳ

ከጦርነት አንወጣም። እንደ ኅበረተሰብ እልኸኞችና ዳተኞች ስለሆንን፣ ነገሮችን በይቅርታና በእርቅ መፍታት አይሆንልንም። ስለዚህ በቅርብ ዐመታት እንኳ በሰሜን ኢትዮጵያ ዘግናኝ የሆነ ጦርነት አካሂደናል። ይሁንና

ከጦርነቱ ማግስት የሰበሰብነው ሬሳ እንጂ ሀብት አይደለም። ያፈራነው አካል ጉዳተኝነት፣ጉሥቁልናና ረሀብ እንጂ ጥጋብና ፍስሃ አይደለም።
ወያኔም ሆነ የመንግሥት ሠራዊት ያወደሙትን  ሀብትና ንብረት፣ መልሰን የምንተካው እኛው ራሳችን ነን። ትግራይ ውስጥ ትምህርት ቤቶች መቃጠላቸው ኪሳራው ዞሮ የሚያንኳኳው የኛኑ ቤት ነው። አማራ ክልል

የፈራረሱት ተቋማት፣ የትግራይንም ክልል ይጎዳሉ። እኛ ያፈረስነውን የምንገነባው ራሳችን እንጂ ሌላ ማንም አጥደለም፡፡  ዳቦ ስንለምን የምንለምነው ሁላችንም ነን።
ትናንት፣ከትናንት ወዲያ፣ዛሬም ጦርነት ውስጥ ነን። እረፍት ኖሮን አያውቅም፤ብራችን ለልማት አልዋለም።ቁስላችን አልደረቀም፤እንባችን አልታበሰም፤እልሀችን አልተነፈሰም። ታዲያ ጦርነት ጥቅሙ፣ሞትና ድኽነት

ከሆነ፣ለምን ምክክርና ውይይትን፣ሰላምና ይቅርታን ለምን አንሞክርም?...ምድራችን ከደም ለምን አታርፍም?...ለመሆኑ ሰው ዐይኑ እያየ፣ለኪሳራ ይነግዳል?...ኧረ ይህን ያደፈ ታሪክ፣በቃ የሚል ጎበዝ፣ጦርነትን

የሚንቅ ጀግና እንፍጠር!
ከአዘጋጁ፡-
ደራሲና ሃያሲ ደረጀ በላይነህ፣ ላለፉት በርካታ ዓመታት በዚሁ ጋዜጣ ላይ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ አያሌ መጣጥፎችን አስነብቧል፡፡ በርካታ የሥነጽሁፍ ሥራዎች ላይ ሂሳዊ ትንተና አቅርቧል፡፡ ደረጀ በላይነህ

ገጣሚና አርታኢም ነው፡፡ 12 ያህል መጻሕፍትን አሳትሞ  ለአንባቢያን አድርሷል፡፡

Read 812 times